“ማይክል ምንም አይነት ህመምን የማስተናገድ አቅም የሌለው ሰው ነው፡፡ ማመን በሚያስቸግር ደረጃ ህመምን ይፈራል፡፡ ህመምን ለማስወገድ ምንም አይነት መድሀኒት ይወስዳል፡፡ ዶክተሮቹም ለዚህ ፍርሐቱ መሳሪያ ሆነውለታል” ብላለች፡፡ ዴቢ ሮው ከማይክል ጃክሰን ጋር የተዋወቀችውም እዛው ሀኪም ቤት ነበር - የማይክልን ቆዳ በሽታ ከሚያክመው ከዶክተር አርኖልድ ክላይን ጋር በምትሰራበት ወቅት፡፡ እዛ ተዋውቀው ተጋቡ፡፡ በጋብቻ ጥምረት ሦስት አመት አብረው ኖሩ፡፡ ከ1996-1999 … የመጀመሪያዎቹን ሁለት ልጆቹን የወለደችለትም ዴቢ ሮው ናት፡፡ በፍርድ ቤት በሰጠችው ምስክርነቷ፡- ማይክል፤ ለቀዶ ጥገና ብቻ የሚወሰድ ማደንዘዣ ለእንቅልፍ ሲል ይወጋ እንደነበር ተናግራለች፡፡
“… ከሞት ይልቅ እንቅልፍ የማጣቱ ነገር በበለጠ ያስጨንቀው ነበር” ትላለች ዴቢ፡፡ “ምክንያቱም ያለ እንቅልፍ በመድረክ ላይ ሙዚቃዎችን ማቅረብ ስለማይችል ነው”
ለቀዶ ጥገና የሚወሰደውን ማደንዘዣ በ1997 (በፈረንጆቹ አቆጣጠር) መጠቀም ከማዘውተሩ በፊት … የሌላ ህመም ማጥፊያ መድሐኒት ሱሰኛ ነበር፡፡ በ1993 የፔፕሲን ማስታወቂያ ለመስራት ቀረፃ በሚያደርግበት ወቅት በተፈጠረ አደጋ፣ የራስ ቅሉ ላይ የቃጠሎ አደጋ ባጋጠመው ጊዜ ህመሙን ለማስወገድ “ዲሜሮል” የተሰኘ ማደንዘዣ ይወስድ ነበር፡፡ የዚህን መድሐኒት ሱስ መላቀቅ ሳይችል በላዩ ላይ “ፕሮፖፎል” የተባለውን ማደንዘዣ ለእንቅልፍ ሲል ደረበበት፡፡ የእነዚህ የህመም ማጥፊያ መድሐኒቶች መደራረብ በ2009 አለምን ላስደነገጠ ሞቱ ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ሚስቱ በምስክርነቷ ፍንጭ ሰጥታለች፡፡ ዴቢ ሮው የከሳሹ ቤተሰቦች (በተለይ የማይክል ጃክሰን እናት ካተሪን) ከቀጠሩዋቸው ጠበቆች የሚቀርቡላትን መስቀለኛ ጥያቄዎች በፍርዱ ቀጣይ ሂደቶች እንደምትመልስ ይጠበቃል፡፡

በደራሲ ግሩም ተበጀ የተዘጋጀ “የዓለማችን ምርጥ የፍቅር ታሪኮች” መፅሃፍ ለንባብ በቃ፡፡ ሃያ አራት የፍቅር ታሪኮችን የያዘው መፅሃፍ፣ በኤች ዋይ ኢንተርናሽናል ፕሪንተርስ የታተመ ሲሆን የሚያከፋፈለው ሊትማን ጂኒራል ትሬዲንግ ነው፡፡ 127 ገፆች ያሉት መፅሀፍ በ35 ብር ይገኛል፡፡
በሌላም በኩል ተርጓሚ ኢፍሬም አበበ የተረጎመው “ጥበብ ፍቅር” ለንባብ በቃ፡፡ “Mars and Venus together forever” ከተሰኘው የጆን ግሬ መፅሀፍ ወደ አማርኛ የተተረጎመው መፅሃፍ፣ ስለ ተቃራኒ ፆታ ግንኙነት ወንዶች እና ሴቶች ስለሚያስቡባቸው የተለያዩ መንገዶች፣ ስለ ወንዶች የማድመጥ ክህሎት፣ወንዶች ከማርስ ሴቶች ከቬኑስ ስለመሆናቸውና ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ተካተውበታል፡፡ 184 ገፆች ያሉት መፅሃፍ በ “ኤች ዋይ ኢንተርናሽናል ፕሪንተርስ” የታተመ ሲሆን ዋጋውም ብር 40.60 ነው፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ በገጣሚ ዘየደ ወልደጻድቅ የተዘጋጁ 120 ግጥሞችና ቅኔዎች የተካተቱበት “የአባይ ዘመን” የግጥም መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ በሀገር ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ግጥሞችን የያዘው መጽሐፍ፣ በ29 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

በፀሐፌ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ የተደረሰው “ላማ ሰበቅታኒ” የረዥም ልቦለድ መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ “Fantasy” የተሰኘውን የአፃፃፍ ስልት ተከትሎ የተጻፈው መጽሐፍ 174 ገፆች ያሉት ሲሆን የታተመው በ”እማይ ፕሪንተርስ” ነው፡፡ የመጽሐፉ ዋጋ 40 ብር ከ50 ሣንቲም ነው፡፡
ደራሲ ውድነህ ክፍሌ “የቼዝ አለም”፣ “ባቢሎን በሳሎን” ፣ “የታፈነ ጩኸት” እና በሌሎችም ተውኔቶቹ የሚታወቅ ሲሆን ከዓለም አቀፍ አዕምሮአዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የ2000 ዓ.ም “ምርጥ የትያትር ደራሲ” ተብሎ መሸለሙም አይዘነጋም፡፡

የመኤኒት ብሄረሰብን የግጭት አፈታት ባህል በመንተራስ በአንዱአለም አባተ የተደረሰው “መኤኒት”ረዥም ልቦለድ መፅሀፍ የዛሬ ሳምንት እንደተመረቀ “አቢሲንያ የስነጥበብና የሞዴሊንግ ማሰልጠኛ ተቋም” አስታወቀ፡፡ መፅሀፉ ከጧቱ 3 ሰዓት አምስት ኪሎ በሚገኘው ብሄራዊ ሙዚየም ሲመረቅ፣ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው መፅሀፉን የተመለከተ ዳሰሳ፣ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራና አቶ ገዛኸኝ ፀጋው ግጥሞች፣ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ እና ደራሲ ደሳለኝ ስዩም ከመፅሃፉ ቅንጭብ እንዳቀረቡ እንዲሁም የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዝዳንት ደራሲና ሃያሲ ጌታቸው በለጠ፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ገብረፃዲቅ ሀጎስ በክብር እንግድነት እንደተገኙ ማወቅ ተችሏል፡፡ ደራሲው አንዷለም አባተ (ያፀደ ልጅ) የማስትሬት ዲግሪ መመረቂያ ፅሁፉን በብሄረሰቡ የግጭት አፈታት ባህል ላይ እንደሰራና የአቢሲንያ ተቋም መምህር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ስምንተኛው የበደሌ ስፔሻል “የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል በህዳር 2006 ዓ.ም እንደሚካሄድ ሊንኬጅ ማስታወቂያ ህትመትና ፕሮሞሽን አስታወቀ፡፡ ከህዳር 16 እስከ ህዳር 23 የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል፣ “አፍሪካዊያን የራሳቸውን ታሪክ እስኪናገሩ የቅኝ አገዛዝ ታሪክ ቅኝ ገዢዎችን ያደምቃል” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን 70 ያህል ዶክመንተሪ፣አጭር፣ፊቸር እና አኒሜሽን ፊልሞች ይቀርቡበታል፡፡ “African panorama” “Cinema Landmarks” “Contemporary Cnema”, “Regional /Ethiopia Focus” እና “Community Focus” የተሰኙ ፊልሞች የሚቀርቡበት ፌስቲቫል፣ ሽልማቶችም ይኖሩታል ተብሏል፡፡

ጥንታዊውና ታሪካዊውን የአቡነ መልከፄዴቅ ገዳም ይበልጥ ለማስተዋወቅና ለቱሪስቶች ለማስጐብኘት እንዲሁም ለመርዳት በአርቲስቶች የተሰራው “እዩና እመኑ” ቪሲዲ ነገ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል አዳራሽ ይመረቃል፡፡
ትዕግስት ግርማ፣ ይገረም ደጀኜ፣ መሰረት መብራቴና ሌሎች ታዋቂ አርቲስቶች የተሳተፉበት ቁጥር አንድ “እዩና እመኑ” ከዚህ በፊት ተመርቆ ለገበያ ከቀረበ በኋላ በተደረገው ገዳሙን የማስተዋወቅ ስራ እስካሁን የ13 አገራት አምባሳደሮች፣ ሀይሌ ገ/ስላሴና የጀርመኑ ፕሬዚዳንት የጐበኙት ሲሆን ዘወትር ቅዳሜ ከ33-40 መኪና ጐብኚዎች ወደ ስፍራው እንደሚጓዙ ተጠቁሟል።
በአቡነ መልከ ፄዴቅ ገዳም እጅግ አስገራሚ ከሆኑት መስህቦች መካከል የሰው ሬሳ ከአመታት በኋላ አለመበስበሱ፣ ያለቀለም መርገጫ በእጣን መዓዛ ብቻ የሚሰራ ማህተም፣ ከ800 ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው ደወል እና ሌሎችም እንደሚገኙበት ይታወቃል፡፡

በአሊ ይመር ተጽፎ የተዘጋጀውን “እንግዳ ነፍስ” ፊቸር ፊልም ሰኞ ምሽት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር እንደሚያስመርቅ ዙምባራ ፊልም ፕሮዳክሽን አስታወቀ፡፡ በፊልሙ ላይ መንትዮችን ጨምሮ 45 ያህል ተዋንያን እንደተሳተፉበት የጠቀሰው ድርጅቱ፣ፊልሙን ሠርቶ ለማጠናቀቅ አንድ ዓመት እንደፈጀ አስታውቋል፡፡
በሌላም በኩል “ጃንኖ” የተሰኘ ፊልም የ95 ደቂቃ ፊልም በአዲስ አበባ መታየት ጀመረ፡፡
በሐዋሳ ተሰርቶ በዚየው ከተማ ሰኔ 26 ተመርቆ የነበረው ፊልም ባለፈው እሁድ በአለም፣ በዋፋ፣ በዮፍታሔ፣ በሴባስቶፖል፣ በኢዮሃ፣ በሆሊሲቲ ሲኒማ ቤቶች ታይቷል፡፡
ፊልሙን ፋሲል አስማማው ጽፎ ፕሮዲዩስ ያደረገው ሲሆን በደረጄ ደመቀ ዳይሬክተርነት ዘነቡ ገሠሠ፣ እንቁሥላሴ ወ/አገኘሁ፣ አልጋነሽ ታሪኩ፣ ናርዶስ አዳነ፣ ተመስገን ታንቱ፣ ይልፋሸዋ መንግስቴ ደረጄ ደመቀና ሌሎችም ተውነውበታል፡፡

Saturday, 24 August 2013 11:00

ወደ እራት

ጀንበሪቱ ወደ ማደሪያዋ አልዘለቀችም፤ ጨርሶ አልመሸም፡፡ በጊዜ እራት ወደሚያገኙበት ቤት እየሄዱ ነው፡፡
አምስት አመት የሞላው የልጅ ልጃቸው መዳፋቸውን በትንሽ እጁ ጨብጦ ይመራቸዋል፡፡
“አቡሽ”
“እ”
“ወደ እማማ ታንጉት ቤት ውሰደኝ”
ወደተባለው ቦታ የሚያደርሰውን መንገድ አግኝተዋል፡፡ በሶስት ብሩ እራት ይበሉበታል፡፡ በተረፈው ጠጅ ይጨልጡበታል፡፡ ይህን ሲያስቡ የታንጉት ቤት ራቃቸው፡፡
“ደህና ውለዋል ወይ?”
ማንነቱን በሚንቀጠቀጥ ድምፁ ለዩት፡፡ እግር አልባው ተመጽዋች ነው፡፡
“ደህና አምሽተሃል?...ውብ ሊቀር?”
“ዘሀርምስጌን…ዝምበላቸውን ጠየቁት?”
“ዝምበላቸው ይሄ የኛው?” በአይነስውርነትና በግብር የሚመስላቸውን ባልንጀራቸውን አስታወሱ፡፡
“ኋላ ሌላ ዝምበላቸው አለ?”
“እኮ እሱ ምን ሆነ?”
“ምን ገጥሞት አንተ?” ጮኹ፡፡
“ጉድጓድ አደናቅፎት ሲወድቅ ጥርብ ድንጋይ አግኝቶ ጭንቅላቱን ተረተረው”
“በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ያለመሪ መንገድ ምን አስከጀለው?”
“አሂሂ…መሪ ሲኖር አይደል”
“ትንሽ ልጁ የት ሄዶ?”
“አልሰሰሜን ግባ በለው…ተኮበለለ አንድ ሰንበት አልፎት”
ውስጣቸው በድንጋጤ ተናጠ፡፡ ድንገት የዝምበላቸው ገጽታ በሃሳባቸው መስኮት ብቅ አለ፡፡ ዧ ብሎ ተኝቶ ከጭንቅላቱ ላይ የፈሰሰው የረጋ ደም ፊቱ ላይ ደለል ሰርቶ እንደዐይኑ ብርሃን የልቡ ተስፋ ጠፍቶ…
“ልጁ የኮበለለ ተማርሮ ነው፡፡ ከፍቶት ነበር…የዘመኑ ልጆች መከፋታቸውን በልባቸው ይሸሽጉታል፡፡ እኛም ቻይና ገራገር መስለው ይታዩንና እንዘናጋለን፤ የቆረጡ ቀን ግን አጋንንት ናቸው፤ አይጨበጡም”
ይህን ካለ በኋላ እየዳኸ ራቀ፡፡ የዳናው ድምጽ ሲጠፋ ፍርሃት ወረራቸው፡፡ ከንፈራቸው መንቀጥቀጥ ጀመረ፡፡
“አቡሽ” ደግመው ጠሩት፡፡
“እ”
መንገዱን እያሳበረ ይመራቸዋል፡፡
የባልንጀራቸው ዝምበላቸው ስዕል ህሊናቸው ውስጥ ገዘፈ፡፡ አወዳደቁ እንደዋርካ በቁሙ ሲገነደስ፣ ምድር ላይ የተተከለ ስል ድንጋይ ከታች ሲቀበለው…
“አያቴ!”
“አቤት አቡዬ”
“ደፍተሬና እስኪብርቶዬ ሊያልቅብኝ ነው”
ሌላ ጊዜ ቢሆን ኖሮ “አንድ ቀን ይገዛልሀል” ብለው ያዘናጉት ነበር፡፡ አሁን ግን ግብራቸውን ለወጡት፡፡ እጃቸው ወደ ኪሳቸው ፈጠነ፡፡
“በል!..ባለአስራስድስት ሉክ ደፍተርና አንድ እርሳስ ገዝተህ ና”
የጠወለገች የሰንሰል ቅጠል የመሰለችውን አሮጌ ብር ተቀብሏቸው ቱር ብሎ ሄደ፡፡
ወዲያው እንግዳ ብቸኝነት ሲሰፍርባቸው ተሰማቸው፡፡ የልጅ ልጃቸው የዘገየ መሰላቸው፤ “የውብ ሊቀር ንግግር ወደ ልቡ ሰርጐ ይሆን?” ብለው አሰቡ፡፡ “አይ ውብ ሊቀር…አሁን ያን የመሰለ ወግ በልጅ ፊት ይነገራል?”
የትንሹ ልጅ ዳና አልተሰማም፡፡
ዝምበላቸው ዳግመኛ ህሊናቸው ውስጠ ተከሰተ፡፡ ክንዶቹ ተሰብረዋል፡፡ ቅልጥሞቹ ተጋግጠዋል፡፡ ያቃስታል፡፡ “ምነው ጌታዬ…ብታሳርፈኝ” የሚለውን ምሬት ይደጋግማል፡፡
“የዘመኑ ልጆች መከፋታቸውን በልባቸው ይሸሽጉታል፤ እኛም ቻይና ገራገር ይመስሉንና እንዘናጋለን”
የእግር አልባው ተመጽዋች ማሳሰቢያ እዝነ ልቡናቸው ውስጥ ነጠረ፡፡ ሥጋት አጥለቀለቃቸው፡፡
“መጥቻለሁ አያቴ”
አላመኑም፡፡
“አቡሽ”
“እ”
“አንተ ነህ”
“እራሴ ነኝ”
“ደፍተሩንና እርሳሱን ገዛህ”
“አዎ አያቴ”
“ተመስገን” አሉ በልባቸው…ለማረጋገጥ የፈለጉ ይመስል መዳፋቸውን ቁልቁል ሰደዱት፡፡ አግድም የታረሰ ጉድባ የመሰለውን ሸካራ ራሱን ሲነኩት ተረጋጉ፡፡
“አቡሽ”
“እ”
“እስኪብርቶ ነበር የጠየቅኸኝ…ለጊዜው በርሳሱ ጣፍበት፡፡ ነገ ከነገወዲያ እስኪብርቶውን እገዛልሃለሁ”
ዝም አለ ልጁ፡፡
“እውነቴንኮ ነው…እርሳሱንም በደህና ምላጭ ተቀረጽኸው ተእስኪብርቶ አንሶ አያንስም”
በዝምታ ይመራቸዋል፡፡ ዝምታው ረበሻቸው፡፡
“አኩርፈህ ነው?...አሁን ይሄ የሚያስኮርፍ ነገር ሆኖ ነው በጊዮርጊስ…ነገ ከነገ ወዲያ’ኮ ደፍተሩንም እስኪርብቶውንም ጨመር አርጌ እገዛልሃለሁ…ብቻ አንተ ጥሩ ልጅ ሁነህ ተገኝ”
በአርምሞ እንደተከረቸመ ቁልቁል ይዟቸው መውረድ ጀመረ፡፡
በኪሳቸው ከቀሩት ብሮች አንዷን መዘዙ፡፡
“ይቺን ያዝና ነገ እስኪብርቶ ትገዛባታለህ…
እስቲ የልብህ ይድረስ”
ተቀበላቸው፡፡
እናም የሚወዱት ጠጅ በጉሮሮአቸው እንደማይወርድ አወቁ፡፡ እንጀራ በሽሮ የሚገዛ ብር ብቻ ቀርቷቸዋል፡፡
“አያቴ”
“አቤት ጌታዬ”
“እዚህ መንገዱ ዳር እኔን እሚያካክሉ ሕፃናት እንጐቻ ይሸጣሉ”
“እውነትህነው?”
“ማርያምን”
ሌላ ጊዜ ቢሆን ኖሮ “ይሄውልህ እንዲህ እያረጉ ነው ወላጆቻቸውን የሚያስተዳድሩ” ይሉት ነበር፡፡ አሁን ግን “ይገዛልህ እንዴ?”
“እሺ”
እጃቸውን ወደ ኪሳቸው ላኩት፡፡
ሁለት ዳቦዎችን ገዝቶ ከተመለሰ በኋላ
“አንዱን ልስጥህ?” አላቸው፡፡
“የለም ላንተ ይሁንህ”
የማላመጥ ድምጽ በጆሮአቸው ሲገባ፣ የዳቦ መዓዛ ባፍንጫቸው ሲሰርግ ጨጓራቸው ይገላበጥ ጀመረ፡፡ ምራቃቸውን በየቅጽበቱ መዋጥ ያዙ፡፡
“አቡሽ”
“እ”
“ጥሩ ልጅ መሆን አለብህ፡፡ ጥሩ ልጅ በምድር ይባረካል፤ ይወልዳል ይከብዳል”
የተለመደው ዝምታ፡፡
“ነፍሳቸውን ይማርና እናትህና አባትህ ደዌ አከታትሎ ሳይፈጃቸው ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡
ሳይታክቱ ይታዘዙኝ ነበር፡፡ ለዚያ ነው ባሁኑ ጊዜ ኑሯቸው በገነት የሆነ”
ዝም፡፡
“ደጋግ ልጆች በምድር ብቻ አይደለም፤ በወዲያኛው አለም በገነት ከመላዕክት ጋር ይኖራሉ፡፡ መላዕክቱ በለስላሳ ክንፎቻቸው አዝለው ገነትን ያስጐበኟቸዋል…እዚያ መራብ የለም፤ መጠማት የለም፡፡ ተራሮች ሁሉ የሚጣፍጡ ዳቦዎች ናቸው፡፡ ወንዞች ማርና ወተት ያፈሳሉ”
ዝም፡፡
“ጥሩ ልጅ የማይሆኑ ልጆች ግን ፈጣሪ ይቀጣቸዋል፡፡ በምድር ላይ ረሀብተኛና ተቅበዝባዥ ይሆናሉ፡፡ አይወልዱም፤ አይከብዱም”
ክርችም፡፡
“አንድ ልጅ አያቱን ከድቶ ከሆነ ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር፣ “በእርጅና ዘመኑ የታወረውን አያትህን ለምን ከዳህ” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ልጁም የሚመልሰው አይኖረውም፡፡
ከዚያማ…ሲዖል መግባት ዕጣ ክፍሉ ይሆናል፡፡ በሲዖል መብላት የለም፣ መጠጣት የለም፣ ትምህርት ቤት የለም…”
“አያቴ!”
“አቤት!”
“ረስቼው?”
“ምኑን?”
“ትምህርት ቤት”
“እ”
“የስፖርት ብር አምጡ ተብለናል”
ሌላ ጊዜ ቢሆን ኖሮ “ደሞ የምን እስፖርት ነው?” ብለው ኩም ያረጉት ነበር፡፡ ዛሬ ግን ሳግ በተቀላቀለበት ድምጽ “ምን ያህል?” ብለው ጠየቁት፡፡
“እንደተገኘው…አምስት፣ አራትም፣ ሶስትም” ሃሳብ ገባቸው፡፡
“ሁለት ይበቃህ ይሆን?”
“እኔንጃ ይበቃኝ ይሆናል”
ከጥቂት እርምጃዎች በኋላ “እማማ ታንጉት ቤት ደርሰናል” አላቸው፡፡
“አልጠፋህም ማለት ነዋ!”
“ምኑ…አያቴ?”
“የማማ ታንጉት ቤት”
“ኧረግ አይጠፋኝም”
“ጐሽ! በል አሁን ወደመጣንበት መልሰኝ!”
ትንሹ ልጅ አመነታና የመንገዱን አቅጣጫ ቀየረ፡፡
(አዲስ አድማስ፤ ሰኔ 15 ቀን 1994 ዓ.ም)

Published in ልብ-ወለድ
Saturday, 24 August 2013 10:58

ቦርጭ አደጋ አለው!

ቦርጫችን ለድንገተኛ የሞት አደጋ ሊያጋልጠን ይችላል
አደጋው በዕድሜ ከገፉ ሰዎች ይልቅ በወጣቶች ላይ ይከፋል
ችቦ አይሞላም ወገቧ
ማር እሸት ነው ቀለቧ፡፡
የምትለዋ የዘፈን ስንኝ ቆየት ባሉት ዓመታት የቆንጆ ቅርፅና የተስተካከለ አቋም ባለቤት የሆነችዋን ኮረዳ ለማወደስ አገልግሎት ላይ የዋለች የዘፈን ስንኝ ነች፡፡ በዘፈኑ የምትወደሰዋ ቆንጆ፣ የተስተካከለ የሰውነት ቅርፅ እንዲኖራት ወይንም ወገቧ ችቦ እንዲሞላ (ቦርጫም) እንዳትሆን ያደረጉት የምትመገበውን ምግብ መምረጥ መቻልዋና ያገኘችውን ሁሉ ወደአፏ ባለማድረግዋ መሆኑንም ዘፈኑ በገደምዳሜ ይገልፅልናል፡፡ የወገቧ ቅጥነት፣ የዳሌዋ ስፋት እያልን የምናደንቃት ኮረዳ ቦርጫም ባለመሆኗ ያተረፈችው ውበቷን ብቻ ሳይሆን ህይወቷንም ጭምር ነው፡፡
የቦርጭ አለመኖር ከሚሰጠው ያማረ ቅርፅና የተስተካከለ ሰውነት በተጨማሪ ጤናማ በመሆን በህይወት የመቆየታችንን እድል ከፍ ለማድረግ እንደሚያስችለን የሚያረጋግጡ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡

ዘ ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦፍ ሜዲስን በቅርቡ ይፋ ያደረገው አንድ መረጃ እንደሚጠቁመው፤ በወገባችን ዙሪያ (በሆዳችን) አካባቢ የሚከማቸው ስብ (ቦርጭ) ለከፍተኛ የጤና ችግር ባስ ሲልም ለሞት ሊዳርገን ይችላል፡፡ ብዙዎቻችን በሆዳችን ዙሪያ የሚታየው ቦርጭ ውበታችንን ወይም የአለባበስ ስታይላችንን በማበላሸቱ ወይንም ያሻንን እንዳንለብስ እንቅፋት በመሆኑ ከመበሳጨት ወይንም ከመማረር በዘለለ ችግሩ በጤናችንና በህይወታችን ላይ ስለሚያስከትለው መዘዝ ስንጨነቅ አንታይም። ቦርጫችንን አንዳንዴም የሃብት መለኪያ አሊያም የኑሮ ምቾት ማሳያ በማድረግ የምንኮራበት ጊዜም ይኖራል፡፡ በእርግጥ ይህ ሁኔታ ዛሬ ዛሬ እምብዛም ተቀባይነትን አጥቷል፡፡ የውፍረት (ቦርጭ) መንስኤ ሰውነት ለሃይል አቅርቦት ከሚፈልገው መጠን በላይ ምግብ መመገብ ሲሆን፤ ምግቡ በስብ መልክ በሰውነታችን ውስጥ ስለሚከማች ለቦርጭ መፈጠር ምክንያት ይሆናል፡፡ የምንመገበው ምግብ ለሰውነታችን የሃይል ምንጭ የሚሆነው በምግብ ስልቀጣ ስርዓት ወደ ጉሉኮስነት በመቀየር ነው፡፡ ሰውነታችን የሚያስፈልገውን ያህል ከተጠቀመ በኋላ ከሚፈልገው በላይ የሆነውን ምግብ በሰውነታችን ውስጥ በስብ መልክ እንዲከማች ያደርጋል። እነዚህ የስብ ክምችቶች በተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች ውስጥ በስጋ ላይ እየተለጠፉ (እየተደረቡ) ይቀመጣሉ፡፡
ሰውነታችን የምግብ እጥረት ሲያጋጥመው ወይንም በቂ ኃይል ሊሰጠን የሚችሉ ምግቦችን ለማግኘት ሳንችል ስንቀር፣ ሰውነታችን እነዚህን የስብ ክምችቶች እያቀለጠ ለሃይል ምንጭነት ይጠቀምባቸዋል፡፡ በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘው የስብ ክምችት መጠን በየጊዜው እየጨመረ ሲመጣ፣ በሆዳችን አካባቢ በመበራከት ቦርጭን ይፈጥራል፡፡ ይህም ለቦርጫማነትና ተያያዥ ለሆኑ የጤና ችግሮቹ እንድንጋለጥ ያደርገናል፡፡
ቦርጫችን ከቁመታችን ተመጣጣኝ ካልሆነና ከተገቢው መጠን እየጨመረ ከሄደ ከፍተኛ የአደጋ ምልክት ውስጥ መሆናችንን አመላካች እንደሆነ ይኸው መረጃ ይፋ አድርጓል፡፡ የቦርጭ ልክንና የስብ መጠን ክምችቶችን ለማወቅ የሚረዱ ሶስት አይነት መንገዶች መኖራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ እነዚህ ዘዴዎች መፍትሄ ለመሻት እንደሚረዱም ጠቁሟል።
የሰውነታችን ክብደት ከቁመታችን ጋር ተመጣጣኝ መሆኑን፣ በከፍተኛ አደጋ ውስጥ መሆን አለመሆናችንን መለኪያ መስፈርቱ BMI (body max index) ያረጋግጥልናል፡፡ ይህ ዘዴ በሆድ አካባቢ የሚገኘውን የስብ ክምችት መጠን ለማወቅም እንደሚረዳን ይኸው መረጃ ይጠቁማል። ሌላው ችግሩን ማወቂያ መንገድ የወገብን ዙሪያ ክብ (ክበባዊ መጠን) ለማወቅ የሚያስችለን ሲሆን በዚህ ዘዴ በሆዳችን አካባቢ የተከማቸውን የስብ መጠን ለማወቅና ችግሩ በጤናችን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለመረዳት ያስችለናል፡፡ ይህንኑ ቦርጭ ሳቢያ የሚፈጠርብን አደጋ ለማወቅ የምችልበት ሌላውና አስተማማኝ ዘዴ የወገባችንን ዙሪያ ልኬት ለዳሌያችን ልኬት በማካፈል የሚገኘው ውጤት ነው። ይህ ውጤት ለሴቶች 0.8፣ ለወንዶች ደግሞ ከ0.9 -1 ድረስ መሆን ይኖርበታል፡፡ ልኬቱ ከዚህ መጠን ከበለጠ በሆዳችን ላይ ከባድ የስብ ክምችት (ቦርጭ) መኖሩን ያመለክተናል። ይህ መንገድ አስተማማኝ ዘዴ በመሆኑ ትክክለኛ ውጤቱን በማሳየት ወደሞታችን የምናደርገው ጉዞ ምን ያህል የቀረበና የራቀ እንደሆነ ለማወቅ እንደሚረዳን መረጃው አመልክቷል፡፡
ቦርጭ በሰውነታችን ውሰጥ ጎጂ የሆኑ የኮሌስትሮል ክምችቶች እንዲኖሩ በማድረግ ለከፍተኛ የደም ግፊትና የልብ በሽታ ችግሮች ሊያጋልጠን ይችላል፡፡ ሰውነታችን በኢንሱሊን እንዳይታዘዝ በማድረግም ለስኳር ህመም ያጋልጠናል፡፡ በአጥንት መገጣጠሚያዎቻችን ላይ ጫና በመፍጠር ለተለያዩ ህመሞች እንድንጋለጥ ያደርገናል፡፡
ለአንጀት፣ ለጡት፣ ለማህፀንና ለፕሮስቴት ካንሰሮች ሊያጋልጠን ይችላል፡፡ ለአተነፋፈስ ችግሮች፣ ለስትሮክና ለሀሞት ጠጠር በሽታም ሊዳርገን ይችላል፡፡
በሆዳችን ውስጥ የተከማቸው ስብ (ቦርጫችን) ያለ ጊዜያችን የመሞት እድላችንን በእጅጉ የሚያፋጥን መሆኑን የጠቆመው መረጃው፤ ችግሩ በእድሜ ከገፉ ሰዎች ይልቅ ወጣቶችን ወደ ሞታቸው እንደሚወስዳቸው ገልጿል፡፡ በቦርጭ ሳቢያ ለሚከሰተው ሞት ዋንኛ ምክንያቱ በደም ውስጥ የሚገኘው የቅባት መጠን መጨመር ሲሆን ይህም ደማችንን በማወፈር ልባችን በደም መርጨት ሂደቱ ላይ ጫና እንዲደርስበት ያደርገዋል፡፡ ይህም የልባችንን ደም የመርጨት አቅም በመፈታተን ለአደጋ እንድንጋለጥ ያደርገናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሆዳችን አካባቢ የተከማቸው ስብ በራሱ የሚያመነጫቸው ኬሚካሎች በተፈጥሮአቸው ስር ሰደው የሚቆዩ በሽታዎችን የማባባስና እንዲነሳሱ የማድረግ ባህሪይ አላቸው፡፡ በአጠቃላይ ቦርጭ ወደ ሞታችን የምናደርገውን ጉዞ በማሳጠር ያለ ጊዜያችን ለህልፈተ ህይወት ሊዳርገን የሚችል መሆኑን በመገንዘብ ቦርጫችንን በመቀነስ (በማጥፋት) ከአካላዊ ውበታችን በላይ ለህይወታችን መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ቦርጫችን ህይወታችንን ሊያስከፍለን አይገባምና!

Published in ዋናው ጤና
Saturday, 24 August 2013 10:56

የቅድመ ካንሰር ምርመራ...

የማህጸን በር ካንሰር ለብዙ ሴቶች ሕይወት ጠንቅ በመሆኑ የክትባቱዋጋ እንዲቀንስ ብቻም ሳይሆን ጥረት በመደረግ ላይ ያለው በነጻ እንዲሰጥም ጭምር ነው፡፡
የማህጸን በር ካንሰር ከማህጸኑ በር አካባቢ ባለው የውስጠኛ ክፍል ይጀምራል፡፡ እዚያ አካባቢ ያሉ ሴሎች ሲፈጠሩ ከነበራቸው ይዘት ወደ ቅድመ ካንሰርነት ተለውጠው በስተመ ጨረሻው ሙሉ ካንሰር ይሆናሉ፡፡ በማህጸን ካንሰር የተያዙ ሴቶች የብልት መድማት ፣ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የወር አበባ መፍሰስ ፣የወር አበባ ከተቀዋረጥ በበሁዋላ በብልት በኩል ደም መፍሰስና ሽታ ያለው ፈሳሽ ከማህጸን መፍሰስ ፣የማህጸን ምርመራ ከተደረገ በሁዋላ መድማትና በወሲባዊ ግንኙነት ወቅት ሕመም መሰማት ይታይባቸዋል ይላል አንድ መረጃ፡፡ የማህጸን በር ካንሰር ገና በጅምር ደረጃ ላይ እያለ ሊደረግ የሚገባውን ህክምና እና በተለይም ክትባት አሁን ያለበትን ደረጃ በሚመለከት ለዚህ አምድ ዶ/ር ካሳሁን ኪሮስ የአዲስ ሕይወት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር እና በአ.አ ዩኒቨርሲት ህክምና ማእከል ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጽንስና ማህጸን ትምህርት አስተማሪ ናቸው፡፡
ጥ/ ካንሰር በሴቶች የመራቢያ አካል በየትኞቹ የሰውነት ክፍሎች ላይ ይከሰታል?
መ/ በሴቶች የመራቢያ አካል አካባቢ የሚነሳ የካንሰር አይነት እራሱን የቻለ ትምህርት ያለውና
ባለሙያ የሚያስፈልገው ሲሆን ስርጭቱም ሰፊ ነው፡፡
መጀመሪያ በውጭ አካል ማለትም ወደማህጸን መግቢያው ላይ፣
በብልት አካባቢ ፣
ከማህጸን በር እና ልጅ ከሚያቅፈው ክፍል ፣
ዘር ማፍለቂያው ወይንም ኦቫሪ ከሚባለውም የሚከሰት የካንሰር አይነት ያጋጥማል፡፡
ጥ/ የማህጸን ጫፍ ..በር .. ካንሰር ማለት ምን ማለት ነው?
መ/ የማህጸን ጫፍ ..በር .. ካንሰር ማለት በተለይም በታዳጊ አገሮች በአብዛኛው የሚከሰት ነው፡፡ የማህጸን ጫፍ ወይንም በር ማለት ልጅ የሚወለድበት ወይንም ደግሞ የታችኛውን እና የላይኛውን የማህጸን አካል የሚያገናኝ ክፍል ነው፡፡ይህ አካል ቅድመ ካንሰር ወይንም ካንሰር በሚባል ደረጃ ሊጎዳ የሚችል ሲሆን ሕመሙ ወደካንሰር ሳይለወጥ በቅድመ ካንሰር ደረጃ እያለ ለማከም እጅግ አስቸጋሪ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ፡፡ ምክንያቱም ሕመሙ ገና ሲጀምር ባለበት ሁኔታ ምንም ምልክት ስለማያሳይ ነው፡፡ ሕመሙ ገና ከመጀመሪያ ደረጃ ላይ እያለ መኖሩ የሚታወቀው ምርመራ በማድረግ ብቻ ነው፡፡ በምርመራው ወቅት በሐኪም የሚታይ ወይንም የሚዳሰስ ነገር ባይኖር እንኩዋን ፈሳሽ ተወስዶ በሚደረገው የላቦራቶሪ ፍተሻ ካልሆነ በስተቀር ሴቶች ምንም ምልክት አያዩም፡፡ነገር ግን ወደካንሰር ከተለወጠ በሁዋላ የራሱ ደረጃ ስላለው በዚያ ከፋፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ ካንሰር ጊዜ ከወሰደ በሁዋላ ከሆነ ሕመም ፣ፈሳሽ ፣ቁስል የመሳሰሉት ነገሮች ስለሚኖሩ ታማሚዋ ልታውቀው ትችላለች፡፡ ቅድመ ካንሰር ባለበት ደረጃ ሕክምናው ከተሰጠ ጭርሱንም ሊድን የሚችል በሽታ ሲሆን ጊዜ ወስዶ ሕመሙ እየተስፋፋ ከመጣ በሁዋላ ከሆነ ግን ማከም ቢቻልም በሽታውን ጭርሱንም ማጥፋት ግን ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ካንሰር ምርመራ የሚባለው ካንሰር የሚከሰትበት ሁኔታን የሚያሳይ ምልክት የሚታይበትና ሙሉ በሙሉ ወደካንሰር በሽታነት ከመለወጡ በፊት ለሕክምና ዝግጁ መሆን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛዋም ሴት ከ25-30አመት እድሜዋ በሁዋላ በየአመቱ ምርመራ ማድረግ እንዳለባት ሁኔታዎች ያስገድዳሉ፡፡ ምናልባትም የምርመራው ውጤት ደህና ከሆነ እድሜያቸው 60 /አመት እስኪሞላ ድረስ በየሶስት አመት ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ እውነታዎች ያረጋግጣሉ፡፡
ጥ / ካንሰርን ለመከላከል የሚያስችለው ክትባት ከምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
መ/ የማህጸን በር ካንሰር የሚመጣው በቫይረስ ነው፡፡ ቫይረሱም ..ሃበቂሮቃ ቅሮቅሽቁቁቄቂሮ ባሽቈበቋ .. ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ ሲሆን በዚህ ስያሜ የተንተቱት የቫይረስ አይነቶች ወደ 120/ ይደርሳሉ፡፡ ከነዚህም ወደ 30/ የሚሆኑት ፊንጢጣና ማህጸን አካባቢቃስ የሚያጠቁ ናቸው፡፡ ከነዚህም ካንሰር የሚያመጡና የማያመጡ ተብለው የሚከፈሉ ሲሆን ካንሰር የሚያመጡት በቁጥር ከ15-17/ ድረስ የተለዩት ናቸው፡፡ ስለዚህ ክትባቱ የተገኘው ለአ ራቱ ሲሆን ካንሰር ከሚያመጡት ውስጥ ለ16/ እና 17/ እንዲሁም ካንሰር ከማያመ ጡት ማለትም እንደኪንታሮት ላሉት ሕመ ሞች ለሚያጋልጡት ለ6/ እና 11/ ለተባሉት ቫይረ ሶች ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የክትባቱን አገልግሎት ስንመለከት በአብዛኛው ካንሰርን ለሚ ያመጡት ለ16 እና 17 ክትባቱ መገኘቱ ከ 75 ኀበላይ የማህጸን በር ካንሰርን ለመከ ላከል የሚያስችል ክትባት አለ ማለት ነው፡፡ በእርግጥ አሁን ባለንበት ደረጃ ካንሰሩን መቶ በመቶ መከላከል ባይቻልም ለሌሎች ዘጠኝ ለሚሆኑ የቫይረስ አይነቶችም ክትባት በመዘ ጋጀት ላይ በመሆኑ ጥሩ ተስፋን የሚሰጥ ነው፡፡ በእርግጥ ካንሰሩን መቶ በመቶ ለመከ ላከል ካንሰር አምጪ ለሆኑት ከ30/በላይ ለሚሆኑት ቫይረሶች ክትባት መዘጋጀት እንዳ ለበት ይታመናል፡፡
ጥ/ የማህጸን በር ካንሰር ክትባት በሀገራችን አገልግሎቱ ምን ይመስላል?
መ/ ከሶስት አመት ወዲህ የማህጸን በር ካንሰር ክትባት በአገራችን እንዲሰጥ ሁኔታዎች የፈቀዱ ሲሆን ነገር ግን ክትባቱ በመሰጠት ላይ ያለው በአንዳንድ የግል የህክምና ተቋማት ነው፡፡ እስከአሁን ድረስ ክትባቱ በኢትዮጵያ በፕሮግራም ደረጃ ሰፋ ብሎ በመንግስት መርሀ ግብር ተካትቶ ለህብረተሰብ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ስለዚህ ችግሩን ለመከላከል የሚያስችል አገልግሎት በመሰጠት ላይ ነው ሊባል የሚችለው ክትባቱ በመንግስት መርሀ ግብር ተካትቶ በእድሜያቸው ከ9-26 አመት ለሚሆኑ ሴቶች ሲሰጥ ነው፡፡ ይህ የእድሜ መመዘኛ ከወሲብ ድርጊት ጋር የሚያያዝበት ሁኔታ አለ፡፡ ሴቶች የማህጸን በር ካንሰርን ክትባት ወሲብ መፈጸም ከመጀመራቸው በፊት ቢወስዱት የሚመረጥ ሲሆን ነገር ግን በብዛት ለካንሰሩ ያልተጋለጡ እስከሆኑ ድረስ ክትባቱን ቢወስዱ እስከ 75ኀ ድረስ ከካንሰሩ እራሳቸውን መከላከል ይችላሉ፡፡
ጥ/ ክትባቱ በግል አስመጪዎችና በግለሰብ ተጠቃሚዎች መወሰኑ ለምንድነው?
መ/ አሁን ባለበት ሁኔታ ክትባቱን እንደልብ ሰዎች እንዲጠቀሙበት ለማድረግ አስቸጋሪ ከሚሆኑት ነገሮች መካከል የክትባቱ ዋጋ ውድ መሆኑ አንዱ ነው፡፡ ክትባቱ በሶስት ጊዜ በወራት ተከፋፍሎ የሚሰጥ ሲሆን ግዢው ለአንድ ሰው እስከአምስት ሺህ ብር ይደር ሳል፡፡ አንድ ሰው ሁለት እና ሶስት ሴት ልጆች ቢኖሩት እስከ አስራ አምስት ሺህ ብር ሊደርስ የሚችል ዋጋ ስለሚያስወጣ አቅምን የሚፈታተን ይሆናል፡፡ ይህንን ክትባት እንደአገልግሎት ለመስጠት የሚቻልበት መርህ በመንግስት ካልተዘረጋ ብዙሀኑ ሊጠ ቀምበት የሚችልበት መንገድ የለም፡፡ ስለዚህም በአለም የጤና ድርጅት በኩል በሚደረግ ንግግር መድሀኒቱ ወደአገር ውስጥ ሲገባ ከአምስት ዶላር በታች እንዲሆንና በተቻለ መጠን እንዲቀንስ የሚቻልበት መንገድ እየተሞከረ ነው፡፡ የማህጸን በር ካንሰር ለብዙ ሴቶች ሕይወት ጠንቅ በመሆኑ የክትባቱዋጋ እንዲቀንስ ብቻም ሳይሆን ጥረት በመደረግ ላይ ያለው በነጻ እንዲሰጥም ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ ክትባቱ ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን መንግስትም የሚያምንበት በመሆኑ አሰራሩ በምን መንገድ ይሁን የሚለውን በቀጣይ መፍትሔ ያገኛል ተብሎ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡
ጥ/ ሴቶች የማህጸን በር ካንሰር እንዳይይዛቸው መከላከል የሚችሉበት መንገድ አለ?
መ/ ሴቶች የማህጸን በር ካንሰር እንዳይይዛቸው ለማድረግ ዋና መከላከያቸው ክትባት መውሰድ ነው፡፡ ክትባቱ ለጊዜው በመንግስት አሰራር በፕሮግራም ታቅፎ በስፋት እና በነጻ እስካልተሰጠ ድረስ ግን እራስን መከላከል ግድ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን፡-
ንጽህናን መጠበቅ፣
በአንድ መወሰን፣
እድሜ ከ25 አመት በላይ ከሆነ በየአመቱ ቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግ፣
እራስን ከአባላዘር በሽታ መከላከል፣
ሲጋራ እና የመሳሰሉትን ሱስ አስያዥ እጾች አለመጠቀም ፣
በወሲባዊ ግንኙነት ጊዜ ኮንዶም መጠቀም...ወዘተ የመሳሰሉት ለቫይረሱ የሚያጋልጡ በመሆናቸው በተቻለ መጠን ጥንቃቄ ማድረግ ይጠቅማል፡፡
በአጠቃላይ ያለው ሁኔታ እጅግ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ የካንሰር አይነቱ ጥንቃቄ ከተደረገና በጊዜው አስፈላጊው ሕክምና ቢደረግ የሚድን ሲሆን ነገር ግን ለሕክምና ወደሆስፒታል የሚመጡት ታማሚዎች ግን ጊዜ ፈጅተው ካንሰሩ ከተሰራጨ በሁዋላ ሰለሚሆን ማዳን አይቻልም፡፡ ስለዚህ እኔ የምመክረው ማንኛዋም ሴት ሌላውን የጤና ምርመራ እንደምታደርገው ሁሉ በማህጸን ካንሰርም እንደዚሁ ቅድመ ካንሰር ምርመራን በማድረግ አስቀድሞ መከላከል ይቻላል ብለዋል ዶ/ር ካሳሁን ኪሮስ የጽንስና ማህጸን ህክምና እስፔሻሊስት፡፡

Published in ላንተና ላንቺ
Page 5 of 17