በሃሰት “ዶክተር ኢንጂነር” ነኝ ሲሉ የቆዩት ሳሙኤል ዘሚካኤል፤ተሸሽገው ከቆዩበት ኬንያ በአዲስ አበባ ፖሊስና በፌደራል ፖሊስ የኢንተርፖል ዲቪዥን በቁጥጥር ስር ውለው ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ ባለፈው ረቡዕ ፍ/ቤት ቀርበው ፖሊስ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸዋል፡፡ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የከባድ ልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ ዲቪዝዮን ምክትል ኮማንደር አበራ ቡሊና ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ግለሰቡ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ወደ ሃገር ቤት እንዲመለስ ከተደረገ በኋላ በ24 ሰዓት ውስጥ ፍ/ቤት ቀርቦ ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተጠይቆበታል፤ ፖሊስም በግለሰቡ ተጭበርብረናል፣ ተታለናል የሚሉ ግለሰቦች ካሉ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በአካል አሊያም በስልክ ቁጥር 0111110111 እንዲያመለክቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ፖሊስ የራሱን የምርመራ ስራ እያከናወነ ነው ያሉት ም/ኮማንደሩ፤ የምርመራ ሂደቱን በተገቢው መንገድ ለመምራት ሲባል ዝርዝር መረጃዎችን ለመስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ ራሳቸውን “ዶክተር ኢንጂነር” እያሉ ሲጠሩ የነበሩት ሳሙኤል ዘሚካኤል፤ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማዕረግ የተመረቁ፣ በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲም እንደተማሩ በመግለፅ፤ በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለመምህራንና ለተማሪዎች የማነቃቂያ ንግግሮች ያደርጉ እንደነበር መዘገቡ ይታወቃል፡፡ ተጠርጣሪው እነዚህ መረጃዎች በተለያዩ ሚዲያዎች መሰራጨታቸውን ተከትሎ ለየትኛውም የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ምላሽ ሳይሰጡ ከሃገር መውጣታቸው የሚታወስ ሲሆን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የኢንተርፖል ዲቪዥን አማካይነት በቁጥጥር ስር ውለው፣ ማክሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2006 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል፡፡

Published in ዜና

   አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ባለፈው የበጀት ዓመት ከብድር ወለድ፣ ከተለያዩ አገልግሎቶች፣ ከኮሚሽንና ከአገልግሎት ክፍያ በጠቅላላው 1.9 ቢሊዮን ብር ገቢ አግኝቶ፣ 816 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ገለፀ፡፡ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብም አምና ከነበረው 13.1 ሚሊዮን ብር ወደ 16.1 ሚሊዮን ብር ከፍ ማለቱ ተጠቁሟል፡፡ ከሐምሌ 2005 እስከ ሰኔ 2006 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ባንኩ ካለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነፃፀር በገቢም ሆነ በትርፍ የ35 በመቶ ጭማሪ ማስመዝገቡን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ባንኩ በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች 35 አዳዲስ ቅርንጫቾችን የከፈተ ሲሆን በአሁን ሰዓት በመላ ሃገሪቱ በጠቅላላው 150 ቅርንጫፎችን በመክፈት ከግል ባንኮች ቀዳሚውን ስፍራ እንደያዘ አስታውቋል፡፡

አዲስ አበባን ጨምሮ በዋና ዋና ከተሞች የባንኩን ደንበኞች የ24 ሰዓት ኤቲኤም አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግም 100 ተጨማሪ ኤቲኤም ማሽኖች አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፤ 400 አዳዲስ የክፍያ መፈፀሚያ ማሽኖችም በሱፐር ማርኬት፣ በሆቴሎች፣ በሲኒማ ቤቶችና በተለያዩ የመዝናኛ ስፍራዎች እንደተተከሉ የባንኩ መግለጫ ጠቁሟል፡፡ ባንኩ በተገባደደው የበጀት ዓመት ለአንድ ሺህ አንድ መቶ ሰላሳ ሁለት (1132) ዜጎች የሥራ እድል የፈጠረ ሲሆን በጠቅላላው የሰራተኞቹን ቁጥር ወደ አራት ሺህ ሰባት መቶ ሰማኒያ ሰባት (4787) ለማድረስ እንደቻለም ታውቋል፡፡

Published in ዜና

           በአሜሪካ ዳላስ አካባቢ ከፍተኛ ተወዳጅነት ካላቸውና የተለያዩ አገር ዜጎች አዘውትረው ከሚመገቧቸው የአመቱ 100 ምርጥ የምግብ አይነቶች ውስጥ፣ ክትፎ አንዱ መሆኑን ዳላስ ኦብዘርቨር ድረገጽ ዘገበ፡፡ ዳላስ ኦብዘርቨር በተለያዩ ሬስቶራንቶች በመዘዋወር የሰራውን ጥናት በመጥቀስ፣ከትናንት በስቲያ በድረ-ገጹ እንዳስነበበው፣ ዳላስ ውስጥ በሚገኘው ሼባ የተሰኘ የኢትዮጵያውያን ሬስቶራንት ውስጥ እየተዘጋጀ የሚቀርበው ክትፎ፣ በአመቱ የዳላስ አካባቢ ተወዳጅ 100 የምግብ አይነቶች ዝርዝር ውስጥ የ50ኛ ደረጃን ይዟል፡፡ ከሁሉም የምግብ አይነቶች በቀዳሚነት የተቀመጠው ኦይስተር ተብሎ የሚጠራው የባህር ውስጥ ምግብ ሲሆን፣ በተከታይነት የተቀመጠው ደግሞ፣ በባህላዊ አሰራር የሚዘጋጀው የቱርኮች ሳንዱች ነው፡፡

ቺክን ሺሽ ከባብ የተባለው ከዶሮ ስጋ የሚሰራ ምግብ በሶስተኛነት ተቀምጧል፡፡ ዝርዝሩ በዳላስ አካባቢ የሚኖሩ የስጋም ሆነ የአትክልት ተመጋቢዎች በአመቱ የበለጠ የተመገቧቸውንና ያዘወተሯቸውን የተለያዩ የዓለም አገራት የምግብ አይነቶች የያዘ ሲሆን፣ በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱት ምግቦች የሚገኙባቸውን ሬስቶራንቶች፣ አሰራራቸውን፣ የተለዩ የሚያደርጓቸውን መገለጫዎች ወዘተ ጠቁሟል፡፡ በዘንድሮው የዳላስ ተወዳጅ የምግብ አይነቶች ዝርዝር ውስጥ ከስጋ፣ ከእንቁላል፣ ከአትክልትና ከመሳሰሉት ምግቦች የተካተቱ ሲሆን፣ የአሳና የፓስታ ምግቦችም ተጠቅሰዋል፡፡ የሳንዱችና የበርገር አይነቶችም ከአመቱ ተወዳጅ ምግቦች ተርታ ተሰልፈዋል፡፡

Published in ዜና

       የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአብራሪዎች የሚሰጠውን ስልጠና ለማሳደግ ሴስና ከተባለው አውሮፕላን አምራች ኩባንያ የገዛቸውን ‘ሴስና 172’ የተሰኙ ሶስት ተጨማሪ የስልጠና አውሮፕላኖች ባለፈው ሳምንት ወደ አገር ውስጥ ማስገባቱን ገለጸ፡፡ አየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ፤ በቅርቡ ዲያመንድ ከተሰኘው የኦስትሪያ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ 12 አውሮፕላኖችን ገዝቶ ማስገባቱን ጠቁሞ፣ ከሰሞኑ ያስገባቸው አዳዲስ አውሮፕላኖችም አራት መቀመጫዎች ያሏቸውና ባለ አንድ ሞተር እንደሆኑና በአሜሪካና በአውሮፓ ከአስር አመታት በፊት የጥራት ማረጋገጫ አግኝተው በተለያዩ አገራት ለስልጠና አገልግሎት በመዋል ላይ እንደሚገኙ ገልጿል፡፡ የአየር መንገዱን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም በመግለጫው ላይ እንዳሉት፣ አየር መንገዱ እ.ኤ.አ በ2025 እደርስበታለሁ ብሎ ባስቀመጠውና በመተግበር ላይ በሚገኘው ስትራቴጂክ እቅድ ውስጥ ለሰው ሃይል ልማት ትኩረት የሰጠ ሲሆን፣ አውሮፕላኖቹም አየር መንገዱ የሚሰጠውን የአብራሪዎች ስልጠና ዘመናዊና ጥራቱን የጠበቀ ለማድረግ የሚያግዙ ናቸው፡፡

በስትራቴጂክ ዕቅዱ የመጨረሻ አመት በአፍሪካ መሪ የሆነ የአቪየሽን ስልጠና ማዕከል ባለቤት የመሆን ግብ አስቀምጦ በመስራት ላይ የሚገኘው አየር መንገዱ፣ አውሮፕላኖቹ በዘርፉ የሚሰጠውን የስልጠና አቅም እንደሚያሳድጉለት ገልጿል፡፡ አየር መንገዱ ከ80 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት በመመደብ አካዳሚውን የማስፋፋት ፕሮጀክት በመተግበር ላይ እንደሚገኝ የጠቆመው መግለጫው፤የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአቪየሽን አካዳሚ በአፍሪካ ትልቁ የአቪየሽን ስልጠና ማዕከል መሆኑና በያዝነው የፈረንጆች አመት፣ በአፍሪካ የአየር መንገድ ማህበር ‘የአመቱ አገልግሎት ሰጪ የአቪየሽን አካዳሚ’ ተብሎ መሰየሙንም አስታውሷል፡፡ የስልጠና አካዳሚው ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ባለፉት አራት አመታት ከፍተኛ እድገት ማሳየቱንና በአሁኑ ሰአትም አመታዊ የመቀበል አቅሙ ከ1ሺህ በላይ መድረሱን ገልጿል፡፡ በዕቅድ አመቱ መጨረሻ ይህን ቁጥር ከ4ሺህ በላይ ለማድረስ ዕቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡

Published in ዜና

    “የተባረሩት ሙስና መኖሩን በመጠቆማቸው አይደለም”- ድርጅቱ

   በ“የእለት ደራሽ የእርዳታ ትራንስፖርት ድርጅት ሙስና እየተፈፀመ ነው” በሚል ርዕስ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በወጣ ዘገባ ምክንያት የድርጅቱ የህግ አገልግሎት ክልል ኃላፊ፤ ከስራ እንዲሰናበቱ መደረጋቸውን የገለፁ ሲሆን የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ በበኩላቸው፤ ስንብቱ የሙስና ጥቆማ ከማቅረባቸው ጋር የተያያዘ አይደለም ብለዋል፡፡ የእለት ደራሽ የእርዳታ ትራንስፖርት ድርጅት ህግ አገልግሎት ኃላፊ የሆኑት አቶ ያለው አክሊሉ፤ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከድርጅቱ የስነ-ምግባር መኮንን አቶ ሰማህኝ ተፈሪ እና ከመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበሩ ም/ሊቀመንበር ጋር በመሆን በተቋማቸው ከፍተኛ ሙስና እየተፈፀመ መሆኑንና የፌደራል የስነ-ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ጉዳዩን በቸልተኝነት እየተመለከተው መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡ አቶ ያለው አክሊሉ ሰኔ 30 ቀን 2006 በተፃፈ ደብዳቤ ከስራ በቀጥታ እንዲሰናበቱ መደረጉን ጠቁመው፤ ስነ ምግባር መኮንኑ አቶ ሰማኸን ተፈሪ በተፃፈ ደብዳቤ ለአዲስ አድማስ በሰጡት መግለጫ በድርጅቱ ውስጥ ያለው የኢንዱስትሪ ሰላም አንዲናጋና ሽብር እንዲፈጠር ማድረጋቸው ተገልፆ፤ በ3 ቀን ውስጥ አለኝ የሚሉትን የሰውና የሰነድ ማስረጃ ለድርጅቱ እንዲያቀርቡ፤ ይህ ባይሆን እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚችል የሚያመለክት ደብዳቤ ደርሷቸዋል፡፡

ባለፉት ሁለት አመታት በድርጅቱ ይፈፀማሉ ያልናቸውን የሙሰና ተግባራት ለህይወታችን ሳንሳሳ ለማጋለጥ ከፍተኛ ጥረት አድረገናል የሚሉት አቶ ያለው፤ “የፀረ- ሙስና ኮሚሽን ጥቆማችንን በቸልታ ስለተመለከተው ጉዳዩን ወደ ሚዲያ ማቅረብ አስፈላጊ ነው ብለን በማመን ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝርዝር መረጃውን ልንሰጥ ተገድደናል ብለዋል፡፡ ዘገባው በጋዜጣው ከተስተናገደ በኋላ የድርጅቱ ስራ አመራሮች ሠራተኞችን ስብሰባ ጠርተው በዘገባው ላይ ውይይት ማድረጋቸውን የጠቀሱት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ በስብሰባው ላይ የድርጅቱን ስም እንዳጠፋን ተደርጐ በሁለት ቀናት ውስጥ እርምጃ እንደሚወሰድብን ለሠራተኛው ተገልጿል ይላሉ፡፡ ስብሰባው በተካሄደ በሁለተኛው ቀን “የስራ ሪፖርት ሲጠየቁ ስርአት የጐደለው ምላሽ አቅርበዋል” በሚል ምክንያት የስራ ስንብት ደብዳቤ እንዲደርሳቸው መደረጉን አቶ ያለው አስታውቀዋል፡፡ የተሰናበቱበት ምክንያትም ቀደም ሲል ለሠራተኞች ቃል በተገባው መሠረት ሳይሆን ስራ አስኪያጁ “የ5 ወራት የስራ ሪፖርት ይቅረብልኝ” ሲሉ በዘለፋ የታጀበ ያልተገባ ምላሽ ሰጥተሃል፤ በሚል ምክንያት እንደሆነ ያብራሩት አቶ ያለው፤“የተፈፀመብኝን በደል በድርጅቱ የስነምግባር መኮንን በኩል ለፌደራል የስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የምርመራና አቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት ባመለክትም ኮሚሽኑ እስካሁን ምላሽ አልሰጠኝም” ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል ለፀረ - ሙስና ኮሚሽን በድርጅቱ ተፈጽመዋል ያልናቸውን 56 አይነት ወንጀሎች በማስረጃ አስደግፈን አቅርበናል ያሉት አቶ ያለው፤ አሁንም ቢሆን ከዚህ ትግል የሚገታኝ የለም ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ጀማል መሃመድ በበኩላቸው፤ ግለሰቡ ከስራ እንዲሰናበቱ የተደረገው የ5 ወራት የስራ ሪፖርት በአግባቡ እንዲያቀርቡ ሲጠየቁ፣በዘለፋ የታጀበና ከተጠየቀው ጋር ያልተገናኘ ምላሽ በመስጠታቸው የተወሰደ እርምጃ እንጂ የሙስና ጥቆማ ከማድረጋቸው ጋር የተያያዘ አይደለም ብለዋል፡፡ “ሠራተኛው ስብሰባ ተጠርቶ በዘገባው ላይ ውይይት ተካሂዷል የተባለው፣በወጣው ዘገባ ሠራተኛው ሳይረበሽና ሳይደናገጥ ስራውን እንዲያከናውን መመሪያ ለመስጠት ነው” ሲሉ መልሰዋል - አቶ ጀማል፡፡ የፌደራል የስነ - ምግባርና የፀረ - ሙስና ኮሚሽን የትምህርትና የስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ፤“አንድ የሙስና ጠቋሚ ከስራው ከተሰናበተ አሊያም ጥቅማ ጥቅሙን ካጣ፣በኮሚሽኑ ይህ የተደረገበት ምክንያት በሚገባ ከተጣራ በኋላ፣ ወደ ስራው እንዲመለስ አሊያም ያጣውን ጥቅማጥቅም መልሶ እንዲያገኝ ይደረጋል” ካሉ በኋላ “እንዲህ ያለ ጥቃት ደርሶብኛል የሚሉ ግለሰቦች በየድርጅቶቹ ካሉ የስነምግባር መኮንኖች ጋር በመሆን ወደ ኮሚሽኑ መጥተው ቢያመለክቱ ይመረጣል” ብለዋል፡፡

Published in ዜና

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ከ612 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከአላማጣ - መሆኒ - መቀሌ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ መስመር ሠርቶ አጠናቀቀ፡፡ በየካቲት 2004 ዓ.ም ስራው የተጀመረው የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር፤ 141 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሲሆን 230 ኪሎ ቮልት ኤሌክትሪክ ይሸከማል፡፡
ሙሉ ለሙሉ ስራው የተጠናቀቀው ይህ ፕሮጀክት፤ ከተከዜ ሃይል ማመንጫ 300 ሜጋ ዋት፣ ከአሽጐዳ ንፋስ ሃይል ማመንጫ 120 ሜጋ ዋት የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ሃይል ያስተላልፋል፡፡
በአምስት አመቱ እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድና ትግበራ በአጠቃላይ 10ሺህ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ለማመንጨት መታቀዱን የጠቆመው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን፤ የህዳሴው ግድብ ከ35 በመቶ በላይ፣ የጊቤ 3 ግድብ ከ86 በመቶ በላይ፣ የገናሌ ዳዋ ከ56 በመቶ በላይ ግንባታቸው መጠናቀቁን ገልጿል፡፡

Published in ዜና
Page 20 of 20