“ነገር የፈለገኝ እሱ ስለሆነ ክስ መስርቻለሁ”

በዛሚ ኤፍ ኤም 90.7 የሬዲዮ ጣቢያ የሚተላለፈው “ኢትዮፒካሊንክ” አዘጋጅ ጋዜጠኛ ግዛቸው እሸቱ በአርቲስት ዳንኤል ተገኝ መደብደቡንና ግራ አይኑ ላይ ባረፈበት ቡጢ ክፉኛ ተጐድቶ ህክምና እየተከታተለ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ገለፀ፡፡ አርቲስት ዳንኤል ተገኝ በበኩሉ፤ ቀድሞ ነገር የፈለገኝ እሱ በመሆኑ ላደረሰብኝ በደልና መጉላላት ክስ መስርቼበታለሁ ብሏል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ከቀኑ 11 ሰዓት ገደማ ገልፍ አዚዝ ህንፃ 4ኛ ፎቅ ላይ ከሚገኘው ቢሮው ወጥቶ መኪናውን ወዳቆመበት ቦታ በመሄድ ላይ እያለ “አንተ የእኔን ህይወት አበላሽተህ በሰላም ትኖራለህ?” የሚል ድምጽ መስማቱንና ወደኋላው መዞሩን የገለፀው ጋዜጠኛው፤ ከመቅጽበት ግራ አይኑን በቡጢ መመታቱን ተናግሯል፡፡ ከዚያም ለፖሊስ ተደውሎ ወደ ካራማራ ፖሊስ መወሰዳቸውን የገለፀው ግዛቸው፤ ለፖሊስ ቃሉን ከሰጠ በኋላ ወደህክምና ማምራቱን ጨምሮ ገልጿል፡፡
“በዚህ ዓመት ታህሳስ ወር ላይ አርቲስቱ ወ/ሮ ቤተልሄም አበበ ከተባሉ ግለሰብ ጋር ፊልም ለመስራት ከተፈራረመ በኋላ ወ/ሮዋ  “ፊልሙንም አልሰራም፤ ገንዘቤንም አልመለሰም” በሚል ክስ መስርተው ጉዳዩ ፍ/ቤት ቀርቦ በሰራነው ዘገባ ቂም ይዞ ደብድቦኛል” ብሏል፤ ጋዜጠኛው፡፡ “ዜናው በተሰራ በሳምንቱ የስራ ባልደረባዬን ዮናስ ሃጐስን ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ውስጥ ለመደብደብ ሙከራ አድርጐ ነበር” ያለው ጋዜጠኛው፤ ይሁን እንጂ ሁኔታዎች አመቺ ስላልሆኑለት ዝቶበት ሄዶ ነበር ብሏል፡፡ “ጉዳዩ በእኔ ብቻ ሳይሆን በሙያውና በድርጅታችን እንዲሁም በመላው ጋዜጠኛ ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው” ያለው ግዛቸው፤ ሃኪሞች ዓይኔ ላይ ለደረሰብኝ ጉዳት የ10 ቀን የህክምና ክትትል እንደሚያስፈልገኝ ነግረውኛል ብሏል፡፡ በካራማራ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ፖሊስ የሆኑትና ጉዳዩን የያዙት ምክትል ሳጂን ዋቅቶላ ቡሊ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ድርጊቱ በተፈፀመበት ዕለት (ነሐሴ 12) አርቲስት ዳንኤል ተገኝ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ ማደሩንና በነጋታው ቦሌ ምድብ ፍ/ቤት ቀርቦ፣ በሶስት ሺህ ብር ዋስ ተፈትቷል፡፡ አርቲስት ዳንኤል ተገኝ በበኩሉ፤ “መጀመሪያ ነገር የፈለገኝ እሱ ነው፤ እንደተያየን “እኔና አንተ ቆይ ለብቻችን እንገናኛለን” አለኝ፤ “ከእኔ ምን ጉዳይ አለህ ስለው?” ጃኬቴን ቀደደብኝ” ብሏል፡፡
“ከዚህ በፊት ምንም ዐይነት ፀብ የለንም፤ ምናልባት  በሰራው ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ በስም ማጥፋት ወንጀል ማዕከላዊ ክስ መስርቼበት ስለነበር ቂም ይዞ ይሆናል” ያለው አርቲስቱ፤ ጠቡ ወ/ሮ ቤተልሄም ከተባሉት ግለሰብ ጋር የሚገናኝ ነገር እንደሌለው ተናግሯል፡፡
አይኑን በቡጢ መቶት እንደሆነ የተጠየቀው አርቲስቱ፤ “በወቅቱ ተያይዘን ስለወደቅን የሆነውን አላስታውስም” ብሏል፡፡ ጋዜጠኛው “በእኔ ላይ ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ጋዜጠኞች ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው” በማለት ለፖሊስ ቃል መስጠቱን ያስታወሰው አርቲስት ዳንኤል፤ “ከጋዜጠኞች ጋር የነበረኝን መልካም ግንኙነት ለማበላሸት ሆን ብሎ የጠነሰሰው ሴራ ነው” ብሏል፡፡
 

Published in ዜና

          ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በህግ ሙያ የተመረቀችውና በአሜሪካ በአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋችነት በመስራት ላይ የምትገኘው፣ ማየትና መስማት የተሳናት ትውልደ ኢትዮጵያዊት የህግ ጠበቃ ሃቤን ግርማ፣ በአካል ጉዳተኞች ላይ መድልኦ ይፈጽማል ስትል ስክሪፕድ የተባለውን ታዋቂ የአሜሪካ የድረገጽ ኩባንያ መክሰሷ ተዘገበ፡፡ ቢዝነስ ኢንሳይደር ድረገጽ ባለፈው ሳምንት እንደዘገበው፤ ዲጂታል መረጃዎችን ለአንባብያን በስፋት በማቅረብ የሚታወቀው ስክሪፕድ የተባለው ኩባንያ፣ የሚከተለው አሰራር ማየት የተሳናቸው አንባቢዎችን ፍላጎት ያላሟላና መድልኦ የሚፈጥር ነው በማለት ነው ሃቤን በኩባንያው ላይ ክስ የመሰረተችው፡፡ የ26 አመቷ ጠበቃ ሃቤን ግርማ፤ ‘ናሽናል ፌደሬሽን ኦፍ ዘ ብላይንድ’ እና ‘ብላይንድ ቬርሞንት ማዘር ሄዲ ቪነስ’ የተባሉትን የአሜሪካ የአይነስውራን መብቶች ተሟጋች ተቋማት በመወከል በስክሪፕድ ላይ በመሰረተችው ክስ፣ ኩባንያው የድረገጽ አገልግሎቶቹ ሆን ብሎ ለአይነስውራን አንባብያን ተደራሽ እንዳይሆኑ በማድረግ፣ የአገሪቱን የአካል ጉዳተኞች ህግ በሚጥስ መልኩ ያልተገባ ድርጊት ፈጽሟል ብላለች፡፡

ስክሪፕድ ከ40 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ያጠናከራቸውን መረጃዎች በድረገጹና በአፕሊኪሽኖቹ አማካይነት ለደንበኞቹ 8 ነጥብ 99 የአሜሪካ ዶላር ወርሃዊ ክፍያ በማስከፈል የሚያሰራጭ ሲሆን በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የሚጽፉ ደንበኞቹን ስራዎች በድረገጽ አማካይነት ታትመው ለንባብ እንዲበቁ በማድረግ፣ በአለማቀፍ ዙሪያ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኝ ኩባንያ መሆኑን ዘገባው ጨምሮ ገልጧል፡፡ስትወለድ ጀምሮ ማየትና መስማት የተሳናት ሃቤን፤ ትምህርቷን የተከታተለችው በአሜሪካ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከሊዊስ ኤንድ ክላርክ ኮሌጅ ተቀብላለች፡፡ ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲም በህግ የሁለተኛ ዲግሪ ይዛለች፡፡ በአሁኑ ወቅትም በበርክሌይ የአካል ጉዳተኝነት መብት ተሟጋች ጠበቃ በመሆን እያገለገለች ትገኛለች፡፡የቢዝነስ ኢንሳይደር ድረገጽ ‘የ2013 እጅግ አስደማሚ 20 ምርጥ የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች’ በሚል ባለፈው አመት ከመረጣቸው ተጠቃሽ ተማሪዎች መካከል ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሃቤን ግርማ አንዷ እንደነበረች ዘገባው አስታውሷል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ
Saturday, 30 August 2014 10:30

ጋዛ - ከእንባ ወደ እልልታ…

           ለሰባት ሳምንታት የማያባራ የሮኬት ድብደባ ሲወርድባት የዘለቀች፣ 490 ያህል ጨቅላዎቿን ጨምሮ 2 ሺህ 142 ዜጎቿን በሞት የተነጠቀች፣ አይሆኑ ሆና የፈራረሰችው ጋዛ፤ ከከረመባት መከራና ስቃይ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን እፎይ አለች፡፡ ባለፈው ማክሰኞ አመሻሽ ላይ፣ ተረኛውን ሮኬት በፍርሃት እየተርበተበቱ የሚጠብቁት የጋዛ ሰዎች፤ ያልጠበቁትን ከወደ ካይሮ ሲደገስ የሰነበተ አንዳች በጎ ነገር አደመጡ፡፡ የፍልስጤሙ ፕሬዚደንት ማሃሙድ አባስ ከወደ ዌስት ባንክ ይፋ ያደረጉት መረጃ፣ እርግጥም ጧት ማታ በሮኬት ድብደባ አሳር መከራዋን ስታይ ለነበረችው የፈራረሰችው ጋዛ ትልቅ የምስራች ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ እስራኤል በፍልስጤም የቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት በጄ ብላ መቀበሏን ማብሰራቸውን፣ ሃማስም የድል ብስራት ዜናውን ለጋዛ ነዋሪዎች በአጭር የጽሁፍ መልዕክት ማድረሱን ተከትሎ፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በጋዛ ጎዳናዎችና በአደባባዮች ወጥተው ደስታቸውን ገለጹ፡፡ ጣቶቻቸውን ከፍ አድርገው በማውጣት የ v ምልክት አሳይተዋል - “ድል ለፍልስጤም ሆነ!” ለማለት፡፡ የሃማሱ ምክትል መሪ ሞሱአ አቡ ማርዙክም ቢሆኑ፣ እስራኤል የቀረበላትን የተኩስ አቁም ስምምነት ሃሳብ መቀበሏ፣ ለሃማስ ትልቅ ድል ነው ብለዋል፡፡ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ቃል አቀባይ ኦፊር ጌንዴልማን በበኩላቸው፤ አገሪቱ በጋዛ ስታደርገው የነበረው ወታደራዊ ዘመቻ በድል መጠናቀቁን ነው የሚናገሩት፡፡

ሃማስ ከዚህ ቀደም በግብጽ ቀርቦለት አሻፈረኝ ያለውን የሰላም ሃሳብ ነው መልሶ የተቀበለው ይላሉ ቃል አቀባዩ፡፡ በግጭቱ 69 ያህል ዜጎቿን ያጣችው እስራኤል የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት ማርክ ሬጌቭ በበኩላቸው፣ ሃማስ ባለፈው ሃምሌ ወር አጋማሽ ላይ የቀረበለትን የሰላም ስምምነት ሃሳብ በወቅቱ ቢቀበል ኖሮ፣ ይሄ ሁሉ ደም መፋሰስ ባልኖረ ነበር በማለት ተጠያቂነቱን ወደ ሃማስ አድርገዋል፡፡ ስምምነቱን እውን ለማድረግ ደፋ ቀና ሲሉ ለቆዩት ለግብጽ፣ ለኳታርና ለአሜሪካ ምስጋና ይግባቸውና፣ አሁን ደም አፋሳሹ የሁለቱ አገራት ግጭት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ጋብ ብሎ የሚቆይበት ሁነኛ የተኩስ አቁም ስምምነት በሁለቱ ሃይሎች መካከል እንዲደረስ አስችለዋል፡፡ የአልጀዚራው ዘጋቢ አንድሪው ሲሞንስ ከጋዛ በላከው ዘገባ እንዳለው፣ በሁለቱ ሃይሎች መካከል የተደረሰው ስምምነት፣ እስራኤል የዘጋቻቸውን የጋዛ መግቢያዎች በአፋጣኝ እንድትከፍትና በሂደትም በጋዛ ሰርጥ አካባቢ የጣለችውን የእንቅስቃሴ ገደብ እንድታነሳ የሚያደርግ ነው፡፡ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል ተጀምሮ የተቋረጠው ውይይትም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚቀጥል ዘግቧል፡፡ሃማስ በቀጣይ በጋዛ ውስጥ የአየር ማረፊያና የባህር ወደብ ማቋቋም ይገባኛል፣ ፍልስጤማውያን እስረኞችም መፈታት ይኖርባቸዋል እያለ ሲሆን እስራኤልም የጋዛን ነዋሪዎች ሙሉ ለሙሉ ትጥቅ ማስፈታት እፈልጋለሁ እያለች ነው፡፡ እንዲህ እና እንዲያ ያሉ ከግራና ቀኝ የሚነሱ ጥያቄዎች፣ በሁለቱ ሃይሎች መካከል ይካሄዳል በተባለው ቀጣይ ውይይት እልባት ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው ጨምሮ ገልጧል፡፡

ስምምነቱ ጋዛን ከግብጽ ጋር የሚያዋስነው 9 ማይል የሚረዝመው የራፋህ ድንበር እንዲከፈት፣ የጋዛ ድንበሮች በፍልስጤም ሃይሎች ቁጥጥር ውስጥ እንዲሆኑና የመልሶ ግንባታ ስራውን የመምራት ሃላፊነቱንም የፍልስጤም መንግስት እንዲወስድ የሚያደርግ ሲሆን፣ እስራኤልም በጋዛ ውስጥ ያላትን የደህንነት እንቅስቃሴ አሁን ካለበት 300 ሜትር ክልል ወደ 100 ሜትር እንድትቀንስ፣ ከአየርና ከምድር የምትሰነዝረውን ወታደራዊ ጥቃት እንድታቆም የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡ በሁለቱ ሃይሎች መካከል የተደረሰው ይህ ስምምነት እንደሚለው፣ የፍልስጤም መንግስት የጋዛን ድንበር ከሃማስ ሃይሎች ተረክቦ የመቆጣጠር ሃላፊነቱን ይወስዳል፤ እስራአልም ከጋዛ ድንበር በሶስት ማይል ርቀት ገድባው የነበረውን የአሳ ማስገር ስራ ወደ ስድስት ማይል ማስፋት ይጠበቅባታል፡፡ ስምምነቱ በጋዛ ሰማይ ላይ የሰላም አየር መንፈስ ለመጀመሩ ማሳያ ነው ቢባልም ታዲያ፣ የማህበረሰብ መሪዎች ግን፣ ህዝቡ ወደቤቱ እንዳይመለስ እየመከሩ ነው ተብሏል፡፡ ጋዛ አሁንም ገና ከስጋት አልወጣችም የሚል አመለካከትም በብዙዎች ዘንድ ይንጸባረቃል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን፤ አገሬን ብላክቤሪ በተባለው ዘመናዊ ስማርት ፎን የሞባይል ቀፎዬ ብቻ በወጉ ማስተዳደር እችላለሁ ማለታቸውን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡ ዴቪድ ካሜሩን ባሉበት ቦታ ሆነው አገሪቱን የማስተዳደር ስራቸውን በሞባይላቸው አማካይነት በአግባቡ ማከናወን እንደሚችሉ መናገራቸውን የገለጸው ዘገባው፤ በየትኛውም የአለም ጫፍ ላይ ብሆን ብላክቤሪ ሞባይሌን ከእጄ ስለማላወጣት፣ በእሷ አማካይነት ከአስተዳደር ጋር በተያያዘ መስራት የሚገባኝን ነገር ሁሉ ሳላጓድል ማከናወን አያቅተኝም ማለታቸውን አስረድቷል፡፡ ብላክቤሪ ስማርት ፎን መረጃን በማስተላለፍ ረገድ ደህንነቱ የተረጋገጠ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ፣ የሞባይል ቀፎው የዴቪድ ካሜሩን ቀዳሚ ምርጫ መሆኑን የጠቆመው ዘ ጋርዲያን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብላክቤሪ የረጅም ጊዜ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጽዋል፡፡ “ካለፉት ጥቂት አመታት አንስቼ፣ የበአል ቀናትን በመሳሰሉ ስራ ላይ በማልገኝባቸው ጊዜያት አገር የማስተዳደር ስራዬን ሳከናውን የቆየሁት በዚህች ዘመናዊ ብላክቤሪ የሞባይል ቀፎዬ ነው” በማለት በግልጽ ተናግረዋል ብሏል ዘገባው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁለት አመታት በፊት በአፕል አይፓዶች ላይ በሚጫኑ አፕሊኬሽኖች በመጠቀም የአገሪቱን የኢኮኖሚ መረጃ ለማወቅ ሙከራ ማድረጋቸውንና በዚህም፣ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት፣ የባንኮችን የብድር አሰጣጥ አሰራር፣ የስራ ዕድሎችን፣ የንብረት ዋጋ ተመኖችን፣ የምርጫ ውጤቶችን የመሳሰሉ መረጃዎችን በፍጥነት ማግኘት እንደቻሉ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም ቴክኖሎጂ ያለውን እገዛ ማጤናቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

“አትሌት የሆንኩት ባለማወቅ ካዳበርኩት አቅም ነው” አትሌት ወርቁ ቢቂላ ወርቁ ቢቂላ በጣም ታዋቂና አይረሴ የሚያሰኙ በርካታ የአትሌቲክስ ገጠመኞች ያሉት ታዋቂ አትሌት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የዘመን ቀመር ከ1976 ጀምሮ እስከ ፈረንጆቹ 2002 ድረስ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች የአገሩን ባንዲራ በድል አውለብልቧል፡፡ ከጀግናው አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገ/ስላሴ ጋር በተለያዩ የአለም የሩጫ ትራኮች ላይ ጥሩ የቡድን ስራ በመስራት ለድል በቅተዋል፡፡ በአርሲ ክ/ሀገር ሰሬ ወረዳ አርብ ገበያ የተወለደው አትሌት ወርቁ ቢቂላ፣ የጐልደን ሊግ አሸናፊም ነበር፡፡ በጐልደን ሊግ ካስመዘገበው ስኬት በኋላ አዲዳስ ኩባንያ ጋር የማስታወቂያ ውል በመፈራረም ለሶስት አመታት ማስታወቂያ ሰርቷል፡፡ በግምት 48 ዓመት እንደሆነው የሚናገረው አትሌት ወርቁ በአሁኑ ሰዓት በዱከም ከተማ ትልቅ ሆቴልና ትልቅ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ት/ቤት ከፍቶ ኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርቷል፡፡

ለህንፃ ግንባታ በዝግጅት ላይ እንደሆነም ተናግሯል፡፡ ከሩጫ አጀማመሩ፣ ከስኬቶቹ፣ ከቢዝነስ ስራውና ከግል ህይወቱ ጋር በተገናኘ ዱከም በሚገኘው ሆቴሉ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ እስኪ ስለአስተዳደግህ አጫውተኝ… እኔ እንግዲህ ገጠር ነው የተወለድኩት፤ የአርሶ አደር ልጅ ነኝ፡፡ እንደማንኛውም የገጠር ልጅ በእርሻ በከብት ጥበቃ ቤተሰቤን እያገለገልኩ፣ ከዚያው ጎን ለጎን ትምህርት እየተማርኩ ነው ያደግሁት፡፡ ያው ገጠር ውስጥ ስትኖሪ በግብርና ህይወት ውስጥ ብዙ ውጣ ውረዶች አሉ፡፡ እነዚያን ውጣ ውረዶች በፅናት ማለፌ አሁን ላለሁበት ህይወት መሰረት ጥሎልኛል፡፡ ብዙ ጊዜ ስለአትሌቶች ሲነሳ አርሲ ትጠቀሳለች፡፡ ብዙዎቹ ሩጫ ለመድን የሚሉት የመኖሪያ ቤታቸውና ት/ቤታቸው ሩቅ በመሆኑ እየሮጡ ስለሚሄዱ ነው፡፡ የአንተ ሯጭነት መነሻው ከዚህ ይለያል? በእርግጥ እኔ የተማርኩበት ት/ቤት ከቤቴ ብዙ አይርቅም ነበር፡፡

ግፋ ቢል በእግር የ20 ደቂቃ መንገድ ነው፡፡ እሷን በሩጫ በአምስት ደቂቃ ፉት ነው የምላት፡፡ ከቤቴ ሲደወል ተነስቼ እንኳን ሮጬ እደርሳለሁ፡፡ ትልቁ እኔን ለሯጭነት ያበቃኝ ጉዳይ ከብት እረኝነት ላይ እያለሁ አንድ አመፀኛ ወይፈን ነበረኝ፡፡ ይህ ወይፈን አውድማ ላይ እህል ሲወቃ በጄ ብሎ አይወቃም፡፡ ጥጋበኛ ነው፡፡ ሳሩ ለምለም ነው፤ እንደልቡ ይበላል፡፡ ውቂያ ውስጥ ግባ ስትይው ይፈረጥጣል፡፡ በዚህን ጊዜ ጭራውን ይዤ አብረን እንሮጣለን፡፡ ይገርምሻል እኛ የምንኖርበት አካባቢ ሜዳማ ነው፤ ያንን ሁሉ ሜዳ ጭራውን ይዤ አብሬው እሮጣለሁ፡፡ ለምን አብረኸው ትሮጣለህ? አሃ! ወይፈኑ ሮጦ ሮጦ ሲደክምና ሲያለከልክ ይዤው እመለስና ወደ ውቂያው እከተዋለሁ፡፡ ይሄን በየጊዜው ስለማደርግ ለካ ሳላውቀው አቅም አዳብሬ ኖሯል፡፡ በሌላ በኩል እህል እነግድ ነበር፡፡ እህል ለመሸመት የምንሄድበት ገበያ የአራት ሰዓት መንገድ ሲሆን ስንመለስ አራት ሰዓት በድምሩ በቀን የስምንት ሰዓት መንገድ እጓዛለሁ ማለት ነው፡፡ በዚህ በዚህ የአካል ብቃቴ እየዳበረ መጣ፡፡ ይህ የሆነው ሳላውቀው ነው፡፡ ስራዬ ብለህ ሩጫ የጀመርከው እንዴትና መቼ ነበር? ሩጫ የጀመርኩት ት/ቤት እያለሁ ነው፡፡ በስፖርት ክፍለ ጊዜ እንሮጣለን፡፡ እንዳልኩሽ እኔ ከዚያ በሬ ጋር ስሮጥ፣ ገበያ በቀን ስምንት ሰዓት ስጓዝ፣ ሳላውቀው ሯጭ ሆኛለሁ፡፡ በማወቅና ባለማወቅ ነው ስፖርት የሚሰራው ብሏል ኃይልሻ (ኃይሌ ገ/ሥላሴ ለማለት ነው) ከዚያ በስፖርት ክፍለ ጊዜ ሩጫ ስንወዳደር ማን ይቻለኝ! 1500 ሜትርና 800 ሜትር አንደኛ፣ ከት/ቤቶች ጋር ስወዳደር አንደኛ፤ በአርሲ ክ/ሃገር በ1500 እና 800 ሜትር አንደኛ እየሆንኩ ማንም ሊደርስብኝ አልቻለም፡፡

በዚያን ጊዜ የሙዚቃ ክፍለጊዜም ነበረን፤ ሙዚቃም ስፖርትም ማርክ ነበረው፡፡ ዘፈን በድምፄ ስለማልችል ማርክ ሊያመልጠኝ ሆነ፡፡ ዋሽንት መፈለግ አለብኝ ብዬ ተነሳሁ፡፡ በሸምበቆ እሰራለሁ፤ እበሳለሁ፣ አልተሳካም፡፡ ብዙ ስቃይ አየሁ፡፡ የዋሽንት አሰራሩ ችግር ለካስ የራሴው ነው፡፡ በኋላ አንድ የብረት ዋሽንት በአንድ ብር ገዛሁ፡፡ ድምፅ ማውጣት ጀመረች፡፡ በእሷ ቀስ በቀስ ስለማመድ ዋሽንት መንፋት ቻልኩ፡፡ የሙዚቃ ማርኬን ማግኘት ቻልኩኝ ማለት ነው፡፡ በሁለቱም መስኮች ተሳትፎዬ አደገ፡፡ ያኔ ወረዳችን ስፌ ወረዳ ይባል ነበር፤ አሁን ጦሳ ወረዳ ተብሎ ተቀይሯል፡፡ ያኔ በወረዳችን መጥተው ሲያወዳድሩ አንደኛ እወጣ ጀመር፡፡ ልጁ በሙዚቃውም በስፖርቱም ጠንካራ ነው በማለት ካምፕ አስገቡኝ፡፡ መቼ ነው ይህ የሆነው? በ1976 ዓ.ም አካባቢ ነው፡፡ ካምፕ ከገባን በኋላ መማር፣ መሰልጠን ጀመርን፡፡ እዚያም ማሸነፍ ሆነ ስራዬ፡፡ መጨረሻ ላይ ፍስሃ የሚባል ሰው “ጐበዝ አትሌት ስለሆንክ ኢንስፔክተር ትዕዛዙ ውብሸት ከሚባል አሰልጣኝ ጋር ላስተውዋቅህ” አለኝ፡፡ በትልቅ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሰው ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም መሬት ሸልመውታል፡፡ በወቅቱ የወጣቶችና ስፖርት ክፍል ኃላፊ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ፈርቼ እምቢ አልኩኝ፡፡ በኋላ ትዕዛዙ ራሱ ተዋወቀኝና “ምን መሆን ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀኝ “እኔ በህይወቴ መሆን የምመኘው ፖሊስ ነው፤ ፖሊሶችን በጣም እወዳለሁ” አልኩት፡፡ ለምን ነበር የምትወዳቸው? ይሄ ጃምቦ የሚመስል ትልቅ ኮፍያቸውን ሲያደርጉ በጣም ደስ ይሉኛል፡፡ እናም በወር 30 ብር ደሞዝ ላግኝ እንጂ ምንም አልፈልግም አልኩኝ፡፡

ለካስ ቤት ኪራይ አለ፣ ምግብ አለ፣ መታመም አለ፤ ያንን 30 ብር ምን ላደርገው ነበር እያልኩ አሁን ሳስብ ያስቀኛል፡፡ በቃ ትዕዛዙ “በቃ በርታ፤ ስፖርትህን አታቋርጥ፤ በደንብ ስራ” አለኝ፡፡ ከዚያስ? ከዚያማ በ1979 የሰራዊቱ የስፖርት በዓል በአዲስ አበባ ይካሄድ ነበር፡፡ ትዕዛዙ ያኔ ተመልምሎ አርሲ ሄዷል፡፡ እኔ ገና ሰሬ ወረዳ ውስጥ ነበርኩኝ፤ እድሜዬም ገና ነበር፤ በዚህ በአገር አቀፍ የስፖርት በዓል ላይ እሱ አርሲን ወክሎ ሄዶ ነበር፡፡ ስድስት ወር ያህል ቀድሞ አዲስ አበባ ገብቷል፡፡ በስፖርቱ ለመሳተፍ ግዳጃቸውን ፈፅመው የተመለሱ አንድ ሺህ ሰራዊት፣ እንደገና ከዚያው አካባቢ የተመለሱ ስድስት መቶ ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ “ከ1600 ሰራዊት የሚበልጥ፣ ከእነሱ ሁሉ አንደኛ የሚወጣ ወርቁ ቢቂላ የሚባል አትሌት አመጣለሁ” አለ፡፡ “እንዲህ የምትለው ከስልጠና ለመሸሽ ነው፤ እሱ ከተሸነፈ አንተ ትባረራለህ” አሉት፡፡ “ግዴላችሁም ልባረር” አለና እኔ ጋ መምጫ ብር አጥቶ፣ ከጓደኞቹ አንድ አንድ ብር ለቃቅሞ በ10 ብር እኔ ጋ መጣ፡፡ ካምፕ መጥቶ “ወርቁን ፈልጉልኝ” አለ፤ ገና እንዳገኘሁት “በል ልብስህን ያዝና ተነሳ” አለኝ፤ “ለምን?” ስለው “ፖሊስ ላደርግህ ነው” አለኝ፡፡ ያኔ ምን እንደተሰማህ ታስታውሳለህ? በደንብ እንጂ! ቀላል አስታውሳለሁ! ማመን አቃተኝ፤ የምይዝ የምጨብጠውን አጣሁ፡፡ ካምፕ ውስጥ መንግስት የሰጠኝን ልብስ በሙሉ ፀጋዬ ለሚባል ጓደኛዬ “ከመጣሁ መጣሁ፣ ካልመጣሁ የት እንደሄደ አላውቅም ብለህ ልብሱን ብቻ አስረክብልኝ” አልኩት፡፡

ተመልሰህ ወደ ካምፕ የመምጣት ሃሳብ ነበረህ እንዴ? አይ… ምናልባት በጤና ምርመራ ወይም ሌሎች መስፈርቶችን ላላሟላና ልመለስ እችላለሁ በሚል ጥርጣሬ ነው፡፡ ከዚያ ወደ አዲስ አበባ መምጫ ብር ከየት ይምጣ! በሌሊት ዶሮ ሲጮህ ተነሳንና እናቴ ቤት ጅማታ ሎዴ ጉዞ ጀመርን፡፡ ምክንያቱም 20 ብር ያስፈልገናል፡፡ መንገዱ አራት ሰዓት ያስኬዳል፤ ገደላገደል አለው፤ አስቸጋሪ መንገድ ነው፡፡ አንዲት ሸራ ጫማ ነበረችኝ፡፡ እሱ ደግሞ መንግስት የሰጠው ቆዳ ጫማ ነበረው፡፡ ያ ፖሊስ ቤት የተሰጠው ጫማ እንዳይቆሽሽና በአስቸጋሪ መንገድ እንዳይቀደድ አወለቀና የእኔን ሸራ ሰጥቼው፣ እኔ በእግሬ ሆኜ ጉዟችንን ቀጠልን፡፡ እሾሁ፣ ድንጋዩ እግሬን እየጋጠኝ፣ አይደረስ የለም ጠዋት አንድ ሰዓት አካባቢ ደረስን፡፡ ብሩን አገኘህ? እህቴ በወቅቱ ቡና ትነግድ ነበር፡፡ ከእሷ ወሰድኩ፡፡ ትንሽ አረፍንና በሁሩታ በኢተያ አድርገን አዲስ አበባ ገባን፡፡ ከዚያ ማሰልጠኛ ገባሁ፤ ጥቂት እንደቆየን ማጣሪያ ውድድር ተባለ፡፡ ኢንስፔክተር ትዕዛዙ እንደነገርኩሽ፣ ቀልጣፋና ተግባቢ በመሆኑ፣ ምልመላ ፖሊሶችም ሆኑ ኃላፊዎቹ ይወዱታል፡፡ ማጣሪያ ሲባል ተጠራጠረኝ፤ ምክንያቱም “እሱ ከተሸነፈ ትባረራለህ” ተብሏል፡፡ ያኔ ፖሊስ ቤት የመግባት እድል ጠባብና ከባድ ነበር፡፡ እኔ ላይ ጥርጣሬ ሲያድርበት ለማጣሪያ የሚወዳደሩትን ጠዋት ከባድ ልምምድ ሰጥቶ አደከማቸው፡፡ ከሰዓት ማጣሪያው ሆነ፡፡ ባለስልጣኑ ሁሉ ወጣ፣ ሰራዊቱ ተደረደረ፣ ሜዳዋ ጠባብ ስለነበረች ለ1500 ሜትር ስምንት ዙር ነው የምትሮጪው፡፡ ሲጀመር ፈትለክ ብዬ ወጣሁና ደርቤ ደርቤ አንደኛ ወጣሁ፡፡ ጭብጨባው ቀለጠ፤ ያኔ ትዕዛዙን “ሼባው” ነው የሚሉት፣ “የሼባው ልጅ አንደኛ” እያሉ ጮሁ፡፡ አሸነፍኩ፡፡ የመጣንበት የትራንስፖርት ታስቦ ተሰጠን፡፡ ደስታ በደስታ ሆንን እልሻለሁ፡፡ አንተ ግን ያን ጊዜ ያሸነፍከው በሙስና ነው ማለት? እንዴት? ምክንያቱም ከሰዓት በኋላ ማጣሪያው እንደሚካሄድ ሲያውቅ ትዕዛዙ ስልጣኑን ተጠቅሞ ተፎካካሪዎችህን በልምምድ ስላደከማቸው ነው ያሸነፍከው (ሳ…ቅ) በእውነት እልሻለሁ፤ በልምምድ ባይደክሙም እምቅ ጉልበት ስለነበረኝ አሸንፋቸው ነበር፡፡ በእርግጠኝነት ነው የምነግርሽ በዚያን ወቅት እንደ ንፋስ ነበር የምበረው፡፡ እሺ ከማጣሪያው በኋላ ምን ሆነ? ከዚያማ ኦሜድላ ስፖርት ገባን፡፡

የጤና ምርመራ አደረግን፡፡ በምርመራው ወቅት ሲያዩኝ “ስፖርተኛ ነህ አይደል?” አሉኝ፤ “አዎ” አልኳቸው፡፡ “በቃ አንተ የሰራዊታችንን ስም ታስጠራለህ፤ ሰራዊታችንን ብቻ ሳይሆን ለአገራችንም ትልቅ ነገር ታደርጋለህ፤ በርታ ውጤት እንጠብቃለን” አሉኝ፡፡ በቃ ፖሊስ ሰራዊት ውስጥ መግባቴን አረጋገጥኩኝ፡፡ በፕሮፌሽናል ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የሮጥክበትን መድረክ እስኪ አስታውሰኝ ከዚያ በፊት ልነግርሽ የምፈልገው ትዕዛዙ ቀድሞ ስድስት ወር ስልጠና ገብቶ ስለነበር ስልጠናውን ጨርሶ ወጣ፤ እኛ ገና ስድስት ወር ይቀረናል፡፡ ስለዚሀ አርሲ ሆኖ በመደወል “አትሌት ወርቁ ቢቂላ ጎበዝ እና ጠቃሚ በመሆኑ ወደ አርሲ እንዲዛወርልን” በማለት ጥያቄ አቀረበ፡፡ ወዲያው ስልጠናው እንደተጠናቀቀ ሃላፊው “ወደ አርሲ ይዛወር” ብለው ፈቀዱ፡፡ የዚያኔ የደርግ ዘመን ጦርነት ስለነበረ ወይ ወደ አንዱ ግንባር ዘምቼ ሞቼና ተረስቼ እቀር ነበር፤ አሊያም አካል ጉዳተኛም ሆኜ ልኖር እችል ነበር፡፡ በትዕዛዙ ምክንያት ወደ አርሲ ሄጄ የፖሊስ አትሌት ሆኜ ቀጠልኩኝ፡፡ የትምህርትህስ ጉዳይ? ትምህርት እስከ 8ኛ ነበር የተማርኩት፡፡ አርሲ ፖሊስ ስገባ ትዕዛዙ የማታ ተማር አለኝ፡፡ እኔ ደግሞ “እንዴት አድርጌ እማራለሁ” አልኩት፤ ምክንያቱም ገና ከፖሊስ ስልጠና ስትወጪ ጥበቃ ነው የምትሰሪው፡፡ “ጥበቃ ሰርቼ፣ ሩጫ ሮጬ እንዴት ትምህርት ማታ እማራለሁ” አልኩት፡፡ “ጥበቃውን ከእኔ ጋር አንድ ሽፍት እናደርግና የአንተንም አደር እየጠበቅሁ እረዳሃለሁ፤ አንተ ብቻ ትምህርትህን ቀጥል” አለኝ፡፡ አሰላ ጭላሎ ት/ቤት እስከ 11ኛ ክፍል ትምህርቴን ተከታተልኩኝ፡፡ አግደው ወልዴ የሚባል የጥበቃ ኃላፊ ነበር “አይዞህ አንተን አሳድገን አንድ ነገር ላይ እናደርስሃለን ይለኝ” ነበር፡፡ ብቻ ድጋፋቸው በጣም አበረታታኝ፡፡ ትዕዛዙ ደግሞ አሰላ ቤተሰብ ስለነበረው ወንድሙ ቤት እንድቀመጥ አድርጐ ከምግብ ጀምሮ በእንክብካቤ ያኖረኝ ጀመር፡፡ ሁሉን ነገር ትቼ ሩጫዬ ላይ አተኮርኩኝ፤ ከዚያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፕሮጀክት ስለነበረ፤ እዛ ገባሁ፡፡ እዚያ በሶስት ወር ሶስት መቶ ብር ይሰጡናል፡፡

የፖሊስ ደሞዝ ደግሞ 137 ብር ነበረ፡፡ በቃ ሃብታም ሆንን፡፡ ሶስት መቶ ብር ብዙ ነው ያን ጊዜ፡፡ እኔ፤ ሃይሌ ገ/ሥላሴና ሌሎች አትሌቶች ከዚህ ፕሮጀክት ነው የወጣነው፡፡ የፖሊስ አትሌቶችም ሆነን በአየር መንገድም ታቅፈን ነበር፡፡ በዚህ መልኩ ስንሰለጥን ከቆየን በኋላ በ1983 ዓ.ም ኢህአዴግ ገባ፡፡ በወቅቱ ስፖርቱም ሁሉም ብትንትኑ ወጣ፡፡ የለውጡ ሂደት ሲረጋጋ የስፖርቱ ሂደት መቀጠል አለበት ብለው ኢህአዴጎች ስፖርቱን መልሰው አቋቋሙት፡፡ ተበትናችሁ በነበረበት ሰዓት ምን እየሰራህ አሳለፍክ? ይገርምሻል፤ ተበትነንም እኔ ስፖርት መስራቴንና ሩጫ መሮጤን አላቆምኩም፡፡ እናቴም በሶና የተለያዩ ምግቦች እየላከችልኝ፣ ትእዛዙ ውብሸትም እየረዳኝ ልምምዴን ቀጥዬ ነበር፡፡ ከለውጡ በኋላ የመጀመሪያ ፕሮፌሽናል ውድድሬን ያደረግሁት ሃዋሳ ላይ ነበር፡፡ ውድድሩ የ21 ኪ.ሜትር (ግማሽ ማራቶን) ነበረ፡፡ በመሰረቱ የእኔ የሩጫ ዘርፍ አጭር ርቀት ነበር፤ 800፣1500 እና 5000 ሜትር ላይ ነው የምሮጠው፡፡ ሃዋሳ ላይ ስሄድ ትእዛዙ “ታሸንፋላችሁ አይዟችሁ” አለንና ተወዳደርን፡፡ ፊሽካ ተነፋ፡፡ እኔ 21 ኪ.ሜትር ርቀት ተወዳድሬ አላውቅም፤ ግን ሸክሽኬ ሸክሽኬ አፈትልኬ ስወጣ፣ ትዕዛዙ ሳይክል ተከራይቶ ይከተለን ነበር፡፡ በምልክት “አይዞህ” አልኩት፡፡ ይገርምሻል ትዕዛዙ ሰው ሲሞት እንኳን አያለቅስም፡፡ በቁም እያለ መርዳት ያለበትን ይረዳል፣ ያስታምማል፤ ያንን አልፎ ከሞተ “ምንም ማድረግ አይቻልም” ባይ ነው፡፡ “አይዞህ አሸንፋለሁ” የሚለውን ምልክት ስሰጠው አለቀሰ፡፡ አንደኛ ወጥቼ አሸነፍኩኝ፡፡ ከዚያ ፖሊስ ኦሜድላ መግባት አለብህ አለ፡፡ አሰላ ፖሊስ ደግሞ አንለቀውም አሉ፡፡ “ከኦሜድላ ሁለት ወታደር እንሰጣችኋለን፤ ወርቁን ስጡን” አሉ፤ ከዚያ በሁለት ፖሊስ ተቀይሬ ኦሜድላ ገባሁ እልሻለሁ፡፡ የኦሜድላ ፖሊስ ቆይታህ ምን ይመስል ነበር? ኦሜድላ ደግሞ ሃይለኛ ሃይለኛ ልጆች ነበሩ፡፡ ያኔ ሃይልሻ (ኃይሌ ገ/ሥላሴ) ብሄራዊ ቡድን ገብቶ ነበር፡፡

“እባክህ ብቻዬን ሆኛለሁ፤ ቶሎ ወደ ብሄራዊ መጥተህ ተረዳድተን እንስራ” ይለኝ ነበር፡፡ ኦሜድላ እያለሁ ብሄራዊ ቡድን እንድገባ ትዕዛዙ በጎን ጥረት ጀመረ፡፡ እሱ ይጥራል፤ እኔ በውጤት እያሸነፍኩ እደግፈዋለሁ፡፡ ከዚያ ኢትዮጵያ ሻምፒዮን ውድድር ተደረገ፡፡ በአምስት ሺህ አንደኛ ወጣሁ፤ በ10 ሺህ ሁለተኛ ወጣሁ፡፡ 10ሺውን አሸንፌያለሁ ስል አንዱ አንገቱ ብቻ ቀድሞኝ ሁለተኛ አልወጣ መሰለሽ፡፡ ተበሳጭቼ ልሞት! እንደ ኃይሌና ፖልቴርጋት አገባብ ማለት ነው? ትክክል፡፡ እንደዚያ አይነት መሸነፍ ነው የተሸነፍኩት፡፡ ገርባ በትቻ የሚባል የአምቦ ውሃ ልጅ ነው ያሸነፈኝ፡፡ ከዚያ ብሄራዊ ቡድን ገባሁ፤ ይህ እንግዲህ በ1984 ዓ.ም መሆኑ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ውጭ አገር የተወዳደርከው የት ነው? ውጤትህስ? ቦስተን የዓለም አገር አቋራጭ (Cross Country) ውድድር ላይ ተሳተፍኩና በጣም የሚያስቅ ውጤት አመጣሁ፡፡ 90ኛ ወጣሁ (በጣም እየሳቀ…) በረዶው እስከ ቅልጥምሽ ይደርሳል፡፡ እኔ በእንደዚህ አይነት አየር ላይ ተወዳድሬም እንዲህ አይነት የአየር ንብረት አይቼም አላውቅም፡፡ ሃይልሻም አልቀናውም፡፡ ወደኔው አካባቢ ነው ውጤቱ፡፡ ያኔጥሩ የነበረው ፊጣ ባይሳ ነው፡፡ ደራርቱም ጥሩ ነበረች፡፡ ሃይሌ ገ/ሥላሴ 100 ሺህ ብር እንደ ሸለመህ ሰምቻለሁ፡፡ ለምን ነበር የሸለመህ? በፈረንጆቹ 1994 አካባቢ ይመስለኛል፡፡ ከሃይልሻ ጋር አብረን ሮጠናል፤ ማናጀራችንም አንድ ነበር፡፡ በወቅቱ በነበረው ውድድር ሃይሌ ሪከርድ መስበር አላሰበም፡፡ እኔ አፌ ላይ መጣብኝና “ሃይልሻ አብሬህ ልሂድና ልወዳደር ሪከርድ እንሰብራከን አልኩት፡፡ ውድድሩ ሆላንድ ሄንግሎ ውስጥ ነበር፡፡

“ያንተ ውድድር ጣሊያን ሮም ውስጥ ነው፤ ሄንግሎ ውስጥ ሆቴልም የለህም አልተያዘልህም” አሉኝ፡፡ “እኔ ምንም አልፈልግም፤ ሆቴል ብቻ ያዙልኝ፤ ገንዘብም ምንም አልፈልግም፤ ግን ሪከርድ እንሰብራለን” አልኩት፡፡ ተሳካ ታዲያ? ሃይሌ ያኔ እንዳሁኑ ፈረንጅ አልሆነም፤ እንግሊዝኛ ትንሽ ትንሽ ይችል ነበር፤ ለማናጀሩ ሃሳቤን ነገረው፤ እኛ እንግሊዝኛ “Yes” እና “No” ብቻ ነበር የምንችለው፤ እርግጥ የሚናገሩት ይገባናል፤ መመለስ ላይ ነው ችግሩ (ሳ…ቅ) ሄድን ተወዳደርን፤ አሪፍ የቡድን ስራ ሰራን፤ ሪከርድ ሰበርን፡፡ ውድድሩ የ10 ሺህ ሜትር ነበር፤ ሃይሌ ሪከርድ ሰበረ፡፡ ብር የለም የተባልኩት ሰውዬ ማናጀሩ ተደስቶ 5ሺህ ዶላር ለቀቀብኝ፡፡ መቶ ሺህ ብር ተሰጠኝ ማለት ነው፡፡ የሚገርምሽ በሶስተኛው ቀን ሮም ላይ ውድድር አለኝ አላልኩሽም፡፡ ሮም ላይ እሱ ሆላንድ ሄንግሎ ያስመዘገበው ሪከርድ ተሰበረበት፤ ተናደድኩ፤ አበድኩ በቃ ምን ልበልሽ … ሪከርዱ ስለተሰበረ ነው? አዎ … እኔ ባለሁበት እንዴት ይሰበራል ብዬ ነዋ! እኔ ሶስተኛ ወጣሁ፤ የእኔ ውጤት በእለቱ በአምስት ሺህ ሜትር ከዓለም አራተኛ ሆኖ ተመዘገበ ሃይሌ በሩጫው አልተሳተፈም፡፡ እዚያው ሆላንድ ቀረ፤ ግን በቴሌቪዥን ውድድሩን ይመለከት ነበር፡፡ በጣም ተደሰተ፤ ሆላንድ ስገባ “ዝነኛ ሆንክ ኮንግራ” አለኝ፡፡ “በቃ ሌላ ጊዜ ሪከርዱን እንሰብራለን” አለኝ “እሺ እንሰብራለን” ተባብለን ወዲያው ስዊዘርላንድ ዙሪክ ላይ ሪከርድ ሰበርን፡፡ ተዓምር ሰራን፡፡ ከዚህ ሁሉ ድል በኋላ ነው ሃይልሽ 100ሺህ ብር የሰጠኝ፡፡ ጎልደን ሊግ ላይም ተወዳድረሃል ሲባል ሰምቻለሁ … በዚሁ በ1994 ዓ.ም ለአትላንታ ኦሎምፒክ ሚኒማ ለማምጣት ልሞክር ብዬ ነበር የገባሁት፡፡ እኔ፤ ዳንኤል ከመን፤ ፖልቱርጋርና ሌሎችም ነበሩ፡፡ እነዚህ ሰዎች ትልቅ ደረጃ ላይ ያሉ ሯጮች ናቸው፤ በ10ሺህ ሜትር ነው፡፡

እኔ ለሚኒማ ነው የሮጥኩት፡፡ ሩጫው ተጀመረ፤ እጅብ ብለን እንሮጣለን፤ የሚመራውን እግር እግር ስከተል ስምንት መቶ ሜትር ላይ ስደርስ ተለይቼው ወጣሁ፡፡ ጎልደን ሊግ ትልቅ ውድድር ነው፤ ወርቅ ከሚያስገኙ ሰባት ውድድሮች አንዱ ጀርመን ስቱትጋርት ውስጥ አንዱን ማርቼሊስ ከሃይሌ ጋር የበላው እስማኤል ኩሪ የተባለ ሯጭም አለ፡፡ ዳንኤል ኮመንን ደረብኩት እና በዚህ ጎልደን ሊግ አንደኛ ወጣሁ፤ ጩኽት ቀጠለ… ምን ልበልሽ… በዚህ ውድድር አሸናፊነትህ የተነሳ በጥሩ ብር ከአዲዳስ ኩባንያም ጋር ለማስታወቂያ መፈራረምህን ሰምቻለሁ እውነት ነው? እውነት ነው፤ ከውድድሩም ከማናጀሬም ጥሩ ገንዘብ አግኝቼያለሁ፡፡ በተጨማሪም ከአዲዳስ ኩባንያ ጋር ለሶስት ዓመት ማስታወቂያ ተፈራርሜ ነበር፡፡ ጫማ ብትይ ልብስ እስካሁን የምለብሰው የአዲዳስን ምርቶች ነው፡፡ ምን ያህል ዶላር ነበር በዓመት የተፈራረምከው? እነሱ ምን ያህል እንክፈልህ አሉኝ፤ 25 ሺህ ዶላር በዓመት አልኳቸው፤ የኩባንያው ኃላፊ “Is it enough?” አለኝ “Yes it is enough” አልኩት በኋላ “It is no not enough” አለኝ “so how much” አልኩት “60 ሺህ ዶላር እንከፍላለን” አለኝ፡፡ “በሶስት ዓመት 180 ሺህ ዶላር ታገኛለህ፤ በዚህ ተስማምተህ ፈርም” አሉኝ፤ ፈረምኩ፡፡

ፈረንጅ አሪፍ ነው፤ ሌላው ቢሆን እኛ ምን አገባን ብለው በ25 ሺህ ያስፈርሙኝ ነበር፡፡ የሩጫ ጫማህን የሰቀልከው መቼ ነው? ማራቶን ፓሪስ ላይ ከሮጥኩ በኋላ 8ኛ ወጣሁ፡፡ በእርግጥ የመጀመሪዬ እንደመሆኑ በዚያው መቀጠል ነበረብኝ ግን ብዙ ዓመት ስለሮጥኩ ከአገር ቤት ጀምሮ ቆይ ትንሽ ልረፍ አልኩኝ፡፡ በቃ በዛው አቆምኩኝ፤ ወቅቱ በፈረንጅ 2002 ዓ.ም አካባቢ ይመስለኛል፡፡ ብዙ አትሌቶች እና ታዋቂ ሰዎች ስኬት ላይ ሲደርሱ ህንፃም ሆቴልም የሚሰሩት በትውልድ አካባቢያቸው ነው፡፡ አንተ ሆቴል የከፈትከው ዱከም ከተማ ነው እንዴት ነው? አንድ ጓደኛ አለኝ ብርሃኔ ሚደቅሳ ይባላል፤ የሆለታ ልጅ ነው፤ ብዙ ነገሮችን የሚያማክረኝ እሱ ነበር፤ ከውድድር ስመለስ ላዝናናህ አየር ቀይር ብሎኝ ዱከም ይዞኝ መጣ፡፡ ድሮም አካባቢውን እወደው ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ ሃሳቤ አዲስ አበባ ውስጥ ክትፎ ቤት ለመክፈት ነበር፡፡ ብርሃኑ ያልኩሽ ጓደኛዬ ለምን እዚህ (ዱከም) ሆቴል አትከፍትም አለኝ፡፡ በል ቶሎ ደላላ ፈልግና ቦታ ይፈለግ አልኩት፤ መጀመሪያ ቤት ሂድና ከባለቤትህ ጋር ተማከር አለኝ፤ ግዴለም አሳውቃታለሁ ትስማማለች አልኩት፡፡ በኋላ አሁን ሆቴሉ ያረፈበትን ቦታ ገዛሁ፡፡ ለካ ያኔ በነፃ ሁሉ ማግኘት እችል ነበር፤ ቦታ እየገዛሁ እየገዛሁ አስፋፋሁ እስኪ ስለቤተሰብህ ንገረኝ? ጥሩ ትዳርና ቤተሰብ አለኝ፡፡ አራት ልጆች አሉኝ፡፡ የመጀመሪያው ልጄ የ17 ዓመት ልጅና የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ አንደኛው ወደ ስምንት አልፏል፤ ሴትም ልጅ አለችኝ፤ የመጨረሻው ህፃን የሁለት ዓመት ነው፤ ልጆቼ ጥሩና ጨዋ ናቸው፡፡

አሁን ጤናህ እንዴት ነው? ጤናዬ ጥሩ ነው፤ ደስተኛ ሆኜ ነው የምኖረው፡፡ ለስፖርት ፍቅር ላላቸው የአቅሜን እደጉማለሁ፡፡ መርዳት ያለብኝን እረዳለሁ፡፡ ቢዝነስ ላይ ነኝ፤ በጣም በጥሩ ሁኔታ ነው የምኖረው፡፡ የእሬቻ በዓል ከደብረዘይት ቀጥሎ አንተ ሆቴል ውስጥ በድምቀት ይከበራል ይባላል፡፡ እውነት ነው? የእሬቻ በዓል ጊዜ መጥተሸ ብታይ ጉድ ነው የምትይው፡፡ አካባቢው በሰው ይሞላል፤ የሙዚቃ ባንድ አለ፤ የከተማው ሰው ይመጣል፤ የአገር ሽማግሌዎች፣ የገዳ ስርዓት መሪዎች ሳይቀሩ ይታደማሉ፡፡ በልዩ ድምቀት ይከበራል፡፡ በቀጣይም የመስቀል በዓል በዋለ በቀጣዩ እሁድ ይካሄዳል፤ በጣም አስደሳች በዓል ነው፡፡ አባ ገዳ ሆነህ ልትሾም ነው ሲባል ሰምቻለሁ ሰምተሽ ይሆናል፡፡ እሱን ከአካባቢው የአገር ሽማግሌዎችና ከስርዓቱ መሪዎች ብትጠይቂ ይሻላል፡፡ አሁን እሱን ለመናገር ጊዜው አይደለም፤ የሚሆነውን አብረን እናየዋለን፡፡ በተረፈ በሁሉ ነገር ደግፎ አይዞህ ብሎ መንገዱን ምቹና ቀና ላደረገልኝ ኢንስፔክተር ትዕዛዙ ውብሸት ታላቅ አክብሮትና ፍቅር አለኝ፤ ዘመኑ ይባረክ እላለሁ፡፡ ሻለቃ ሃይሌ ገ/ሥላሴንም አመሰግናለሁ፤ ሃይልሻ ጠንካራና ምሳሌ የሚሆን ሰው ነው፡፡ በተረፈ ለሁላችንም እድሜና ጤና ይስጠን፡፡ አገራችንን ከክፉ ይጠብቅልን እላለሁ፤ አመሰግናለሁ፡፡

           25% የሚሆኑ ሴቶች በሕይወት ዘመናቸው የወር አበባ ሕመምን ያስተናግዳሉ፡፡ በአስራዎቹ እና ሀያዎች የእድሜ ክልል ውስጥ ካሉ ሴቶች ከ65-95 % የሚሆኑት የወር አበባ ሕመም ሊኖራቸው ይችላል፡ የወር አበባ ሕመም በእነማን ላይ ወይንም በየትኛው የእድሜ ክልል ይከሰታል? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ተፈጥሮአዊ ሁኔታዎችን መፈተሸ ይጠቅማል፡፡ የወር አበባ ሕመም መከሰት ከጠቅላላው እድሜ ጋር ሲፈተሸ ወደ 25 % ወይንም 1/4ኛ የሚሆኑ ሴቶች በሕይወታቸው የወር አበባ ሕመምን ያስተናግዳሉ፡፡ በተለይም በወጣትነት እድሜ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ማለትም በአስራዎቹ እና ሀያዎች የእድሜ ክልል ውስጥ ባሉት ሴቶች ከ65-95% የሚሆኑት የወር አበባ ሕመም ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ጉዳቱንም ስንመለከት ከሕመሙ ውጭ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጫናው አስከፊ ነው፡፡ የወር አበባ ሕመም እንዴት? በምን ምክንያት ይከሰታል? መፍትሔውስ ምንድነው? ለሚለው ዶ/ር ሙሁዲ አብዶ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እና መምህር የሰጡን ማብራሪያ ለንባባ ቀርቦአል፡፡ ጥ/ የወር አበባ ሕመም ማለት ምን ማለት ነው? መ/ የወር አበባ ሕመም ሲባል የወር አበባ ሊመጣ ሁለት ወይንም ሶስት ቀን ሲቀረው ጀምሮ በፍሰቱ ወቅት የሚሰማ ሕመም ነው፡፡ የወር አበባ ሕመም ስሜቱ ስለአለ ብቻ የወር አበባ ሕመም የሚያሰኘው አይደለም፡፡ 

ነገር ግን ሕመሙ የእለት ተእለት ተግባራት ወይንም ትምህርትን እስከማደናቅፍ ሲደርስ በወር አበባ ጊዜ የሚከሰት ሕመም ሊባል ይችላል፡፡ ጥ/ የወር አበባ ህመም ሲባል ደረጃ አለውን? መ/ የወር አበባ ሕመም ደረጃው ሁለት ነው፡፡ (Primary & secondary) ቀዳሚ እና ተከታይ በሚል ሊገለጽ ይችላል፡፡ ቀዳሚ የሚባለው (Primary dysmenorrheal) አብዛኛውን ጊዜ ከማህጸን ጋር ተያያዥነት ያለው በሽታ ወይንም ችግር በሌለበት ሁኔታ የሚከሰት ሲሆን ይህም ችግር የሚገኘው በተለይም በመጀመሪያዎቹ አስሮቹ ወይንም ሀያዎቹ በሚባሉት የእድሜ ክልል ውስጥ ነው፡፡ እንዲሁም መውለድም ሆነ እርግዝና ሞክሮአቸው በማያውቁ እና ገና በትኩስ እድሜ ላይ ባሉ ልጆች ላይ የመጀመሪያው አይነት የወር አበባ ሕመም ይከሰታል፡፡ ብዙውን ጊዜ ለዚህ በምክንያትነት የሚጠቀሰው የማህጸን በር መጥበብ ወይንም መዘጋት ሊሆን ይችላል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው (secondary dysmenorrheal) የሚባለው ከማህጸን ጋር ተያይዞ በሚመጣ ችግር የሚከሰት የወር አበባ ሕመም ነው፡፡ ለምሳሌም... የማህጸን እጢ የሚባለው (ማዮማ) ፣ እንዲሁም የወር አበባ ኡደት ተዛብቶ ወደሌላ የሰውነት ክፍል ሲሄድ፣ የማህጸን ኢንፌክሽን፣ በማህጸን በር ወይንም ግድግዳው ላይ የሚከሰቱ የእጢ የመለጠፍ አይነቶች፣ የመሳሰሉት ሲሆኑ በዚህ ደረጃ ሴቶች የሚታመሙት እድሜያቸው በአብዛኛው በሰላ ሳዎቹና በአርባዎቹ ክልል ሲደርስ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የወር አበባ ሕመም መጀመሪያ ሳይሰማቸው ቆይቶ እነዚህ ችግሮች በመከሰታቸው ምክንያት የሚፈጠር ሕመም ሊሆንም ይችላል፡፡

ጥ/ ሕመሙን ሊያመጡ የሚችሉ ተጨማሪ ምክንያቶች አሉ? መ/ ሕመሙን ሊያመጡ ይችላሉ ከሚባሉት ምክንያቶች መካከል በተለይም በወጣትት እድሜ ክልል ያሉት ሴቶች ለሕመሙም አነስተኛ ግንዛቤ ያለቸው ወይንም ደግሞ በአእምሮአቸው ተጨናቂ ከሆኑ እንዲሁም ለሕመሙ በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸው እና ደረጃውንም ሳይጠብቁ መጨነቅ ሲያበዙ ሕመሙ የሚከሰትበትን እድል ያሰፉታል፡፡ በሁለተኛም ደረጃ ማህጸን በተፈጥሮው በየወሩ የወር አበባ ኡደት ውስጥ የሚሄድባቸው ለውጦች አሉ፡፡ የወር አበባ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ እራሱን ያዘጋጅና ከዚያ በሁዋላ ከኦቩሌሽን ቀጥሎ የወር አበባ ወይንም እርግዝና እንዲከሰት ዝግጅት ያደርጋል፡፡ በዛ ዝግጅት እርግዝና ሳይከሰት ሲቀር ወደመጨረሻዎቹ ሳምንታት የማህጸን ግድግዳ የመድማት ሂደትን ያስተናግዳል፡፡ እነዚያ የመድማት ክስተቶች በአንዴ የሚከ ሰቱ ሳይሆን ወቅታቸውን ጠብቀው በተወሰኑ ጊዜያቶች የንጥረነገሮችን ኡደታቸውን ለማካሄድ የተለያየ መጠን ደርሰው ዝግጅት በሚያደርጉበት ጊዜ የማህጸን የመኮማተር ወይንም ደግሞ ይህ መኮማተር ሕመም እንዲፈጥር ወይንም እንዲያሳይ የሚያደርጉበት ሁኔታ አለ ፡፡ የወር አበባ ተከስቶ ደም በሚፈስበት ጊዜ ያንን የተዘጋጀውን ደም በበቂ ሁኔታ እንዲፈስ የማህጸን በር የሚባለው ክፍት ሆኖ የወር አበባው ቆሻሻ መውጣት ሳይችል ሲቀር በሚፈጠረው ተፈጥሮአዊ ሂደት የማህጸን በር እንዲኮማተር የደም ዝውውሩ እንዲቀንስ ያደርጋሉ፡፡ ይህ የደም ዝውውር በመቆሙ ወይንም ማህጸን በመኮማተሩ ምክንያት ህመም አምጪ የሆኑትን ንጥረ ነገሮች እንዲፈልቁ ያደርጋል፡፡ በዛም ምክንያት ተደጋጋሚ መኮማተር ስለሚያጋጥም ሕመሙ ያጋጥማል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ከማህጸን ችግር ጋር በተያያዘ የሚከሰተው ሕመም ችግሩ ሲወገድ አብሮ የሚወገድ ነው፡፡ ጥ/ በሽታው የሚገለጽበት ሁኔታ ምን ይመስላል? መ/ በሽታው ብዙውን ጊዜ ከእምብርት በታች ወይንም ሽንት መሽኛ እና የሽንት ፊኛ አካባቢ የተለያየ የህመም ስሜት አለው፡፡

ሴቶቹ ሲገልጹት አንዳንድ ጊዜ እጅግ የሚያም ቁርጠት አይነት ሲሆን አንዳንዴ ደግሞ ወደታች የመግፋት ስሜት ያለው ...ነገር ግን ለመግለጽ የሚያስቸግር ሕመም ነው ይሉታል፡፡ ሕመሙ ወደታችኛው የሰውነት ክፍል ማለትም ወደእግር ታፋ ወይንም ጭን አካባቢ ሁሉ የሚደርስ ስሜት አለው፡፡ ሕመሙ ከፍተኛ ደረጃ በሚደርስበት ጊዜ የማቅለሽለሽ ፣የእራስ ምታት፣ ተውከት ፣ድብርት ፣ ቁርጥማት ፣ተቅማጥ ፣ድርቀት በመሳሰሉት ሁሉ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ስለዚህም ይህ የወር አበባ ሕመም በማህጸን አካባቢ ብቻ የሚከሰት ሳይሆን ጠቅላላ ሰውነት ላይም ሊገለጽ የሚችል ነው፡፡ ጥ/ የወር አበባ ሕመም የሚያስከትለው ማህበራዊ ችግር ምንድነው? መ/ የወር አበባ ሕመም በሴትየዋ ከሚከሰተው የሕመም ስሜት እና የአእምሮ ስቃይ በተለየ ማህበራዊ ችግር ያስከትላል፡፡ የተማሪዎችን ሁኔታ ስንመለከት ከ15-20 ኀ የሚሆኑት ተማሪዎች ከትምህርት ቤት በተደጋጋሚ ከሚቀሩባቸው ምክንያቶች ዋነኛው የወር አበባ ሕመም ነው፡፡ በስራ ላይ ያሉ ሴቶች በተደጋጋሚ በተመሳሳይ ጊዜ ከስራ ለመቅረት ፈቃድ የሚጠይቁበት ምክንያት የወር አበባ ሕመም ነው፡፡

ስለዚህም ይህ ሕመም ከሚያ ደርሰው ስቃይ በተጨማሪ በኢኮኖሚያዊው እና ማህበራዊው ችግር ብዙ ሴቶች ሲጎዱ ይታያሉ፡፡ ሕብረተሰቡ ባለው ግንዛቤ ምክንያትም ሴቶቹ ሕመም ሲደርስባቸው አለመ ረዳት እና ከትምህርትም ሆነ ከስራ በሚቀርበት ጊዜ በቂ ምክንያት እና በቂ መረጃ እያቀረቡ ትብብርን ያለማሳየት ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህ ሕመም ከሕክምናውም ባሻገር አእምሮአዊ እረፍት እና መረጋጋትን እንደሚፈልግ ህብረተሰቡ ቢረዳው እና በቂ ግንዛቤ ኖሮት እርዳታ ቢያደርግላቸው ተገቢ ነው፡፡ ጥ/ የወር አበባ ሕመም በጋብቻ እና ልጅ በመውለድ ምክንያት ይቀንሳልን? መ/ አንዲት ሴት ጋብቻ በመፈጸሙዋ ምክንያት ከወንድ ጋር በምታደርገው ግንኙነት ሳቢያ የወር አበባ ሕመም ሊተዋት አይችልም፡፡ ምክንያቱም የወር አበባ ሕመም መንስኤው ከላይ እንደተገለጸው አንድም ከማህጸን ጋር በተያያዘ ችግር ሲሆን በሌላው በኩል ደግሞ ተፈጥሮአዊ በሆነ መልኩ ነው፡፡ ከመውለድ ወይንም ከእርግዝና ጋር በተገናኘ በመጀ መሪያ ደረጃ የሚከሰተው ሕመም ሊወገድ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ በእርግዝናው ወይንም በወሊድ ጊዜ የማህጸን በር በተወሰነ ደረጃ የሚከፈት በመሆኑ ሕመሙ ሊጠፋ ወይንም ደግሞ ሊታገስ ይችላል፡፡ ጥ/ ሕክምናው ምን ይመስላል? መ/ የወር አበባ ሕመም ላላቸው ሴቶች በቅድሚያ የሚሰጠው ሕክምና ማስታገሻ ነው፡፡

የማስታገሻው መድሀኒት ታማሚዎቹን የሚሰማቸውን ሕመም መጠኑን በጣም ሊቀንስላቸው እና ከስቃይ እረፍት እንዲያገኙ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን በማስታገሸ መድሀኒቶች ሕመሙ የማይታገስ ከሆነ በመቀጠል የሚደረገው ሁለት አይነት ሕክምና አለ፡፡ አንደኛው በሕክምና የሚረዳ ሲሆን ሕመሙ በጣም የከፋ ከሆነ ደግሞ ሰርጂካል የሚባል ሕክምና ይሰጣል፡፡ በእርግጥ እንደዚህ ካሉ ሕክምናዎች ደረጃ ሲደረስ ሴትየዋ በቀጣይ ያላትን ዝግጅት መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በወደፊቱ ጊዜዋ እርግዝናን ታስ ባለች ወይንስ ? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ እርግዝና የምትፈልግ ከሆነ በሕመም ማስታገሻው ትእግስት አድርጎ እርግዝናው እንዲከሰት ማድረጉ ለወደፊቱም ሕመሙን የሚያስታግስ ስለሆነ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ እርግዝናን የማታስብ ከሆነ ግን የእር ግዝና መቆጣጠሪያን ጨምሮ የህመም ማስታገሻዎቹን በሐኪም ትእዛዝ መሰረት በመውሰድ ሁኔታውን ማየት ይቻላል፡፡ በመድሀኒቶቹ ወይንም በማስታገሻዎቹ የማይታገስ ከሆነ እና ችግሩ ከማህጸን ችግሮች ጋር የተያያዘ መሆን አለመሆኑን በምርመራ በማረጋገጥ ምክንያቱ የማህጸን በር መዘጋት ከሆነ የማህጸን በርን በህክምና እንዲከፈት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

Published in ላንተና ላንቺ

          ለአመታት ያላቋረጠው የአገራችን የፖለቲካ ድራማ፣ ዛሬም ከአዙሪት የመላቀቅ ምልክት አይታይበትም። ሰሞኑን በስፋት የተሰራጩ ሁለት ወሬዎችን ብቻ እንመልከት። አንደኛው ወሬ፣ በኢህአዴግ ባለስልጣናት ላይ ያተኮረ ነው። ሌላኛው ደግሞ በግል ጋዜጦችና መፅሔቶች ላይ ያነጣጠረ።
በእርግጥ ወሬዎቹ እንደ ትኩስ “ዜና” ቢሰራጩም፣ አዲስ “መረጃ” አይደሉም። ከነጭራሹ የመረጃ ሽራፊ እንኳ የላቸውም። “የግል ጋዜጦችና መፅሔቶች፣ ከተለያዩ የውጭ ሃይሎች ወይም ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የገንዘብ ድጋፍ ያገኛሉ” እየተባለ በመንግስት ሚዲያ ሲነገር ሰምታችሁ አታውቁም? በተደጋጋሚ ተወርቷል። ከሰሞኑም እንደገና ተከልሶ እንደ አዲስ ሲወራ ሰንብቷል። ግን፣ የትኛው ጋዜጣና መፅሔት መቼ፣ ምን ያህል ገንዘብ ከማን እንደተቀበለ በግልፅ አይልተጠቀሰም። ተጠቅሶም አያውቅም። ተጨባጭና ግልፅ መረጃ ይቅርና፣ ጠቋሚ መረጃ እንኳ ለማቅረብ አልተሞከረም። ጭፍን ውንጀላ ብቻ!
ሁሉም የግል ጋዜጦችና መፅሔቶች ከነውር ንፁህ ናቸው ማለቴ አይደለም። አንዳንዶቹ ንፁህ ላይሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን፣ “ነውር ይፈፅማሉ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ልሳን ናቸው” በማለት ያለ አንዳች መረጃ በተደጋጋሚ ወሬ ማሰራጨት ግን፣ ከተራ የስም ማጥፋት ወይም የስም ማጉደፍ ዘመቻ አይለይም። ታዲያ ለምን የመንግስት ሚዲያና የኢህአዴግ ደጋፊዎች ይህን መረጃ አልባ ወሬ ያሰራጫሉ? ያው... ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማሳጣትና ለማብጠልጠል፣ እንዲሁም ዜጎችንና ጋዜጠኞችን ለማስፈራራት እስካገለገለ ድረስ፣ የሃሰት ወሬ ማሰራጨት ችግር የለውም - ለጭፍን የገዢ ፓርቲ ደጋፊዎች።
ሁለተኛው ወሬም እንዲሁ ያለ ምንም ተጨባጭ መረጃ ነው የተሰራጨው - በጭፍን ተቃዋሚዎች። “በርካታ የኢህአዴግ መሪዎችና ባለስልጣናት በአለማቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ተከሰሱ” የሚለው ወሬ እንደካሁን በፊቱ ባለፉት ቀናትም በብዛት ተሰራጭቷል። ወሬው ሲሰራጭ፣ “እስቲ በፍርድ ቤቱ (በአይሲሲ) ድረገፅ ላይ መረጃ ካለ ለማየት እንሞክር” የሚል ሰው አልተገኘም።
በፍርድ ቤቱ አሰራር፣ ከክስ በፊት መደበኛ ምርመራ ይካሄዳል። ከመደበኛ ምርመራ በፊት ደግሞ መነሻ ፍተሻ አለ። በተለያዩ አገራት፣ በርካታ መንግስታትና ባለስልጣናትን እንዲሁም ታጣቂ ድርጅቶችንና እንደ ኢራቅ አሸባሪዎች የመሳሰሉ ቡድኖችን በተመለከተ ምርመራና ፍተሻ እያካሄደ እንደሆነ አይሲስ በድረ ገፁ ይዘረዝራል። ግን፣ በአገራቱ ዝርዝር ውስጥ የኢትዮጵያ ስም አልተጠቀሰም። እና ለምን፣ ወሬው ያለ መረጃ ተሰራጨ? ያው... ገዢውን ፓርቲ ለማጥላላት፣ ለማንቋሸሽ እስካገለገለ ድረስ ችግር የለውም።
በየጎራው የተቧደኑት ጭፍን ፊታውራሪዎችና ቲፎዞዎች፤ በየፊናቸው የሚያሰራጩት የወሬ አይነት ይለያያል። ነገር ግን፣ በባሕሪያቸው በጣም ተመሳሳይ ናቸው። “ተቀናቃኝ ወገንን ለመወንጀል የሚያገለግል እስከሆነ ድረስ፤ ተጨባጭ መረጃ ሳያስፈልግ ማንኛውንም ወሬ ማሰራጨት ይቻላል” በሚለው ሃሳብ ይስማማሉ። ዛሬ የሚያሰራጩት ወሬ፣ ውሎ አድሮ ሃሰት እንደሆነ ቢታወቅ እንኳ፣ ያን ያህልም አያሳስባቸውም። “የሃሰት ወሬ የተሰራጨው ለበጎ አላማ ስለሆነ አያስነውርም” ብለው ያስባሉ። ምን አይነት በጎ አላማ? “ለአገር እድገትና ልማት፣ የአገርን ክብር ለመጠበቅና የአገርን ገፅታ ለማሳመር፣ የድሃውና የሰፊውን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር” ሲባል ነው ወሬው የተሰራጨው በማለት ማመካኛ ያቀርባሉ። “ለብሔር ብሔረሰብና ለባህል በመቆርቆር፣ ለሃይማኖት ቀናኢነትን ለማሳየትና የአምላክን ትዕዛዝ ለማስፈፀም በማሰብ ነው ወሬው የተሰራጨው” በማለትም ራሳቸውን ያሳምናሉ።

በነሱ ቤት፣ ለበጎ አላማ የሃሰት ወሬ ማሰራጨት መደበኛ የሕይወት ዘይቤ ነው።
በአሳዛኙ ነገር ምን መሰላችሁ? የበጎ ነገሮች ሁሉ ምንጭ የሆነውን ነገር እየናዱት ነው - ማለትም እውነትን ዋጋ እያሳጡ የእውነትን ክብር እያረከሱ ናቸው። በፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ ስለ “እውነት” መነጋገር፣ ከንቱ “ቲዎሪ” ሊመስል ይችላል። ስለሚመስልም ነው፣ ከአመት አመት እየተደናበርን ከአዙሪት መውጣት ያቃተን። ዋናውን ቁልፍ ችላ ብለን ከተውነው፣ እንዴት ብለን መንገዳችንና መድረሻችን እናውቃለን። ለ“እውነት” ታላቅ ክብር የማይሰጥ ባህል ውስጥ፣ መቼም ቢሆን በጎ ለውጥ ሊፈጠር አይችልም። ለእውነት ክብር ከሌለን እንዴት ልንግባባ እንችላለን? ተቀናቃኛችን፣ የቱንም ያህል አስተማማኝ መረጃ ቢያቀርብ፣ ከመጤፍ አንቆጥረውም። በተቃራኒው፣ ምንም መረጃ ሳይኖረን ተቀናቃኛችንን የሚያሳጣ ወሬ እናወራለን - በዙሪያችን የተሰባሰቡ ቲፎዞዎች በጭፍን እንደሚያጨበጭቡልንና ወሬውን እንደሚያራግቡልን እርግጠኛ ነን። ለነገሩ፣ ትክክለኛ መረጃ ሰብስበን ብናቀርብን፣ ተቀናቃኛችንና ቲፎዞዎች፣ ለሴኮንድ ያህል የመስማት ፈቃደኛ አይሆኑም። አልቧልታ እየነዙና እየተቀባበሉ ያስተጋባሉ እንጂ።

“መውጪያ የሌለው አዙሪት” ይሉሃል ይሄ ነው። ታዲያ ይሄ በጎ ነው? በየጎራችን “ለበጎ አላማ” በማሰብ የምናሰራጨው አሉባልታ፣ እንደምታዩት የመጨረሻ ግቡ “ፋታ የለሽ መናቆር” እንደሆነ ተመልከቱ።
ለዚህም ነው፤ በአገራችንም ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን ቀን ከሌት እያወራን መወዛገባችን፣ ክረምት ከበጋ እየተናቆርን መጠማመዳችን፣ መሻኮታችንና መጠላለፋችን ሊያስገርመን የማይገባው። በእርግጥ፣ አብዛኞቹ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ስለ ኢትዮጵያ እየተናገሩ የሚወዛገቡትና የሚናቆሩት ለምን እንደሆነ ብትጠይቋቸው፣ መልሳቸው ተመሳሳይ ነው። በየጎራቸው ለአገሪቱ በጎ ለውጥ ለማምጣት እየተጣጣሩ እንደሆነ ይነግሯችኋል። አብዛኞቹ ምሁራንና ዜጎች ስለ አገራቸው እየፃፉ የሚከራከሩት ወይም የሚሰዳደቡትስ? በየፊናቸው “በቀና መንፈስ መልካም ለውጥን ስለምንመኝ ነው” ይሏችኋል። ምን ዋጋ አለው? ለእውነት ክብር ባለመስጠት፣ የ“በጎ” ነገሮች ጠላት ሆነን እናርፈዋለን።
በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ መጠቀስ ከሚገባቸው በጎ አላማዎች መካከል አንዱ፣ “ነፃነት” የሚባለው ነገር ነው - በራስህ አእምሮ የመጠቀም፣ የራስህን ኑሮ የመምራት፣ የራስህን ሕይወት የማጣጣም ነፃነት። በጥንታዊው የግሪክና የሮም የስልጣኔ ዘመናት፤ እንዲሁም በሬነሰንስ እና በኢንላይትመንት ዘመናት፣ የፖለቲካ ነፃነትና ብልፅግና ከሳይንስና ከእውቀት ጋር በጣምራ የተስፋፉት አለምክንያት አይደለም - እነዚህ ሁሉ የሚመነጩት “እውነት”ን ከማክበር ነው። የነፃነት ተቃራኒ ምንድነው ቢባል፣ በቅድሚያ የሚጠቀሱት፣ አፈናና ጭፍን ፕሮፓጋንዳ ናቸው። አሃ፣ ከመነሻው አፈናና ጭፍንነት የሚስፋፋው ለምን ሆነና? ሰዎች፣ “እውነት”ን እንዳያውቁ ወይም “ሃሰትን” እንዲቀበሉ ማድረግ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ለእውነት ከፍተኛ ክብር የሌለው ሰውም ሆነ ፖለቲከኛ፣ ገዢም ፓርቲ ሆነ ተቃዋሚ፣ ለነፃነትም ትልቅ ክብር ሊኖረው አይችልም። እንዲያውም፤ የአቅሙን ያህል አፈናንና ጭፍንነትን የማስፈን ዝንባሌ ይኖረዋል። የትኛውም ወገን ቢያሸንፍ ለውጥ የለውም። ለምሳሌ፣ የሙስሊም ወንድማማቾችና ሆስኒ ሙባረክ፣ የሶሪያ አክራሪዎች እና በሽር አልአሳድ፣ ... የሚጣሉት አንዱ አምባገነን አፋኝ ሌላኛው የነፃነት ታጋይ ስለሆነ አይደለም። የሰዎችን ሃሳብና ንግግር ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር፣ ማለትም ተቀናቃኝ የሌለው አፋኝ ለመሆን ነው። ጉልበት ያለውና ስልጣን የያዘ አፋኝ ፓርቲ፣ ግድያ፣ እስር፣ ወከባ፣ ፕሮፓጋንዳ ይፈፅማል። ለጊዜው ስልጣን ያልያዘና ጉልበት የሌለው ፓርቲ ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ በአልቧልታ የማሸማቀቅ፣ ስም የማጥፋት፣ በጭፍን የመፈረጅ ዘመቻ ያካሂዳል። ማለቂያ የለሹ አዙሪት የዚህ ውጤት ነው።    
በአገራችን ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች በሁለት ጎራ ስለ ኢኮኖሚ እድገትና ስለ ድህነት የሚያካሂዱትን ውዝግብ በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።  “የኢትዮጵያ ዋነኛ መገለጫ... የሞት አፋፍ ላይ መሆኗ ነው” በማለት ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የተናገሩ ጊዜ የተፈጠረውን ውዝግብ ታስታውሱ ይሆናል። ኢትዮጵያ በድህነት ተዳክማ በልመና የምትንገታገትና የሕልውና አደጋ የተጋረጠባት መሆኗን ጠቅሰው፤ “እርዳታ ባይገኝ ስንት ሚሊዮን ሕዝብ ያልቃል? እርዳታ እንደልብ ቢገኝ እንኳ፣ ረሃብተኛው እጅግ ብዙ ሲሆን እርዳታ ማጓጓዝ ራሱ ትልቅ ፈተና ይሆናል። ከጥፋት ለመዳን መሮጥ አለብን። መፍጠን አለብን፤ ሴንስ ኦፍ ኧርጀንሲ ያስፈልጋል” የሚል ሃሳብ ነው የተናገሩት ጠ/ሚ መለስ። ይሄ ለብዙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚዋጥላቸው አልነበረም።
የዜጎች ድህነት እጅግ አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ አገሪቱ የገደል አፋፍ ላይ መድረሷ እውነት ቢሆንም፤ ብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች “እውነት ብለሃል” በማለት ስምምነታቸውን አልገለፁም። “አዎ አገሬው አደጋ ላይ ነው። ግን፣ መልካም ለውጥ ለማምጣት ገዢው ፓርቲ በብቃት አልሰራም። አገሪቱን ለማሳደግ የሃሳብና የተግባር ብቃት የለህም” ብለው መከራከር ይችሉ ነበር። ግን፤ አላደረጉም። እንዲያውም፤ “ምንም አዲስ የተፈጠረ ነገር ሳይኖር መዓት ማውራት ምንድነው? ኢህአዴግ የአገርን ክብር ደፈረ፤ የአገርን ስም አጠፋ...” በማለት ገዢውን ፓርቲ አብጠልጥለውታል።
አሁን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኗል። በገዢው ፓርቲ ዘንድ፣ ስለ ድህነት ማውራት፣ የአገርን ገፅታ እንደማበላሸት እየተቆጠረ መጥቷል። ተቃዋሚዎች ስለ ድህነት ሲያወሩ... ገዢው ፓርቲ “አዎ ትክክል ነው። አገራችን ድሃ ነች። ባለፉት አስር አመታት ኢኮኖሚው ከእጥፍ በላይ ቢያድግም፤ አሁንም እጅግ ድሃ ነን። ለዚህም ነው በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት መቀጠል አለብን የምንለው” ብሎ ማስረዳት ይችላል። ግን አያደርገውም። አገሪቱ እጅጉን የበለፀገች ያስመስላል፤ ስለ ድህነት የሚያወሩትንም “ፀለምተኛ፣ ፅንፈኛ፣ ከሃዲ” በሚል እየፈረጀ ይሳደባል፤ ያስፈራራል።
ተቃዋሚዎችም፤ “አዎ፣ የኢኮኖሚ እድገት እየታየ ነው። ነገር ግን፤ አሁንም ከ13 ሚሊዮን በላይ ተረጂዎች አሉ። በማምረቻ ኢንዱስትሪ መስክ ለውጥ እየታየ አይደለም። በቂ የስራ እድል እየተፈጠረ አይደለም። መንግስት እየገነነና የግል ኢንቨስትመንት ወደ ኋላ እየቀረ ነው። የያዝከው አቅጣጫ አያዛልቅም” ብለው ማስረዳት ይችላሉ። ግን አያደርጉትም። ገዢውን ፓርቲ ለማንቋሸሽ፣ ለመሳደብ፣ በጭፍን ለመፈረጅ ይቸኩላሉ።
እናማ ሁለቱም ጎራዎች፤ ገዢው ፓርም ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በጭፍን ስሜታዊነት ይቀጥላሉ - አንዱ ሌላውን ለማሳጣት።
ግን በጋራ የሚጠሉት ደግሞ አለ - ሚዛናዊ የሆኑ ሰዎችን። እርስ በርስ ለመናቆር ችግር የለባቸውም - ቁንፅል እውነትና ያገጠጠ ሰበብ አለላቸው። ኢህአዴግ የኢኮኖሚ እድገት እየተመዘገበ ነው ሲል እውነት ነው - የአሪቱን ድህነት እየሸፋፈነ። ተቃዋሚዎች፣ ስለ ድህነትና ችግር የሚናገሩት ነገር እውነት ነው - ስለ ኢኮኖሚ እድገት እየዘነጉ። “እንዴት የህዝቡን ድህነት ትክዳለህ?”፣ “እንዴት የኢኮኖሚ እድገቱን ትክዳለህ?” እየተባባሉ ይናቆራሉ።
“ድህነትም አለ፤ የኢኮኖሚ እድገትም አለ” ብሎ እውነት የሚናገር ሲመጣ ለሁለቱም አይጥማቸውም። ኢህአዴግ የመንግስት ስልጣን ስለያዘ፤ ማስፈራራት፣ ማዋከብና ማሰር ይችላል።
 ተቃዋሚዎች ደግሞ፣ ስልጣን እስኪይዙ ድረስ፣ ስም ማጥፋት፣ ማንቋሸሽና መሳደብ ይችላሉ። ጨዋታው በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ፤ የትኛውም ወገን ቢያሸንፍ ብዙም ለውጥ አያመጣም።

Saturday, 23 August 2014 12:01

አስተኳሽ ግጥሞች!

           እያንዳንዷ ግለሰባዊ ድርጊት የማህበረሰቡ ባህል ውጤት ናት፤ ድርጊቷ መጥፎ ወይም ጥሩ ልትሆን ትችላለች፡፡ ግን መጥፎ የምትሆነው ባህሉ “መጥፎ ናት” ብሎ ከፈረጃት ብቻ ነው፡፡ አለዚያ ምንም ያህል አስቀያሚ፣ ምንም ያህል ጎጂ ብትሆን እንኳ የማህበረሰቡ ባህል “ደግ” ብሎ ከሰየማት ደግ ናት፡፡ ለዚህ አባባል ነቃሽ መጥራት ቢያስፈልግ የቀረርቶና ፉከራ ግጥሞች ህያው ምስክሮች ይሆናሉ፡፡ የጽሁፌ ዓላማም “አስተኳሽ” ግጥሞችን በመጠቃቀስ መጠነኛ ትንታኔ መስጠት ነው፡፡
ሰውን መግደል ወንጀል ነው፤ በሀይማኖት መጻህፍትም ሃጢያት ሆኖ ያስጠይቃል፡፡ የቀረርቶና ፉከራ ግጥሞች ግን መግደልን ያበረታታሉ፤ ገዳዩን ያሞካሻሉ፡፡
“ጎበዝ ሰው ግደሉ፤ ሰው መግደል ይበጃል፤
ይዋል ይደር ማለት ጠላት ያደረጃል” በማለት ግድያን ያፋጥናሉ፡፡ ጠላት ተብሎ የተፈረጀው ሰው ከዋለ ካደረ አቅሙ ይፈረጥምና ከባድ ጥቃት ሊያደርስ ይችላል፡፡ ስለሆነም ጠላትን ቀድሞ መግደል ተገቢ መሆኑን ግጥሙ ይነግረናል፡፡
አደብ ገዝቶ የተቀመጠውን ትዕግስተኛም ትዕግስቱን አሟጥጦ ሰው መግደል እንዳለበት፤ ይዋል ይደር ማለትም ተገቢ አለመሆኑን፣ እንዲህ ሲል ይመክራል፡-
“ጎበዝ ቅደም፤ ቅደም! አትቀደም፤
ገላጋይ አያጣም በኋላ ያለ ደም” ሲል ግድያን ያፋፍማል፤ ትዕግስትን ይኮንናል፡፡ “ለመግደል ያብቃህ እንጂ ከገደልህ በኋላ ገላጋይ አታጣም” እያለም መግደልን እንደ ገለባ ቀላል ያደርገዋል፡፡
“አንድ ዓመት ጎዝመው (አርሰው) አንድ ዓመት ካልጎፉ፣
እናትም ትላለች ልጄ መጣ ዞፉ (የእንግዴህ ልጅ)” ይህኛው ግጥም ደግ ሰው ተብሎ የሚጠራ ሁሉ አንድ ዓመት ያህል አርሶ ወይም ነግዶ ከቆየ በኋላ በሁለተኛው ዓመት ካልሸፈተና ሸፍቶም “መጣ፣ መጣ” ካልተባለ ሌላው ቀርቶ እናት እንኳ ልጇን እንደ እንግዴህ ልጅ እንደምታየው፤ ከገደለ፣ ጫካ ገብቶ ሰላማዊውን ህዝብ ካሸበረ ግን ከልቧ እንደምትኮራበት ያስረዳል፡፡
“ዋርካ ሞኙ፣ ሾላ ሞኞ ሳያብብ ያፈራል፤
አንዱን ካልገደሉት መች አንዱ ይፈራል?”
በመሰረቱ ዋርካም ሆነ ሾላ በደማቁ የሚያብቡት ሞኝ ስለሆኑ አይደለም - ተፈጥሮ ሆኖባቸው እንጂ፡፡ በሌላም በኩል የዋርካና የሾላ አለማበብ ሰውን ከመግደል ጋር የሚያገናኛቸው አንድም ምክንያት የለም፡፡ ገጣሚው ቤት እንዲመታለት የተጠቀመበት መላ ነው፡፡ የግጥሙ ዋና መልእክት ግን “አንዱን ካልገደሉት መች አንዱ ይፈራል?” የሚለው ኃይለ ቃል ነው፡፡
አንዱ ሲገደል ያየ ሁሉ “ሰጥ ለጥ” ብሎ እንዲገዛ ሰውን መግደል ተገቢ ነው ብሎ ይሰብካል - ካልገደሉ፣ ካልበደሉ ክብር የሌለ ይመስል፡፡
“በደም ካልነከሩት እንደ እመጫት አልጋ፣
አገሩ አገር አይሆን፤ አልጋውም አይረጋ” የሚለው ግጥም ደግሞ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው፤ “አልገዛም፣ አሻፈረኝ” ያለውን ሁሉ በደም ካልነከሩት፣ ወይም እንደ እመጫት አልጋ በደም ካላጠቡት ስልጣነ መንግስቱ (አልጋው፣ ዙፋኑ) ሊረጋ እንደማይችል የሚያስጠነቅቅና ጭካኔን፣ ነፍሰበላነትን የሚሰብክ ግጥም ነው፡፡
ይህ አይነቱ ግጥም ለአፍሪካውያን መሪዎች ተስማሚ ይመስላል፤ “መብት፣ ዲሞክራሲ” እያለ አንገቱን ቀና ያደረገውን ሁሉ ካልገደሉ፣ ካላሰሩ፣ ካላሰደዱ፣ ካላሸማቀቁ፣ ካላሳቀቁ ዙፋናቸው የሚረጋላቸው ለማይመስላቸው ግብዞች የተገጠመ፡፡ ለዚህ ሳይሆን ይቀራል አፍሪካዊያን መሪዎች ሰብአዊነት በጎደለው መንገድ ዜጎቻቸውን እየጨፈጨፉ ሲገዙና በወጡበት መንገድ ሲወርዱ የኖሩት?
“በሬውን እረደው! ሚስቱንም አግባበት!... ቤቱን አቃጥልና አስቀምጠው በአመድ፣
ሲጨንቀው፣ ሲጠብበው ያረግሃል ዘመድ”
ይህ ደግሞ በጣም የሚገርም ግጥም ነው፡፡ የህልውናው መሰረቶች ከሆኑት አንዱ የሆነውን በሬ አርዶ በልቶበት፣ የህይወቱ ዋልታና ማገር የሆነችውን ሚስቱን አግብቶበት፣ ያችን ምስኪን ጎጆውን አቃጥሎ  በአመድ አስቀምጦት፣ ዘመድ ሲያረገው አስቡት፡፡ ለነገሩ ወድዶ ሳይሆን ሲጨንቀው፣ ሲጠብበው ብሏል፡፡ አዎ ቀን ሲከፋ፣ አማራጭ ሲጠፋ የሚጎፈንን ግፍን፣  እንደ ላቀ ስጦታ መውሰድ ይቻል ይሆናል፤ ይህን እውነት ባለፉት መንግስታት አይተነዋል፡፡ ልጁን ከጉያው ነጥቀው ገድለው “ልጅህን ለመግደል የባከነውን ጥይት ዋጋ ክፈል፣ ከልጅሽ አስከሬን ላይ ቁሚና ዝፈኚ፣ ለሞተ ዘመድህ እንዳታለቅስ፤ ወዘተ” የሚል ዘግናኝ ግፍ ሲፈጸም ተስተውሏል፡፡
በንጉሡ ዘመንም ቢሆን አባቱን ይገድሉና ልጁን ወይም የቅርብ ዘመዱን “መንግስታችን በደረሰብህ ሃዘን ከልብ አዝኗል” በማለት በመከራው ይቀልዱበት ነበር፡፡ ባለ ሃዘኑም አንጀቱ እርር ድብን እያለ “ፀሐዩ ንጉሳችን ለዘለዓለም ይንገሡ!” ሲል በልቡ ሳይሆን በአፉ ይመርቃል፡፡ አስረጅ ንቀስ ብባል ህጋዊውን ወራሴ መንግስት ልጅ ኢያሱ (አባ ጤናን) በተለያዩ ቦታዎች በዘግናኝ ሁኔታ አስረው ሲያሰቃዩ ሲያሰቃዩ ከኖሩ በኋላ ኃይለሥላሴ ገድለው ሃዘን መቀመጣቸው ነው፡፡
ንጉሡ ይህን ያገጠጠ ወንጀል እንደፈፀሙ ወይም እንዳስፈፀሙ እየታወቀ፣ የልጅ ኢያሱ ልጆችና የቅርብ ቤተሰቦች የንጉሡን (ገዳዩን) ደግነት ሳይወዱ በግድ አድንቀዋል “ሲጨንቀው ሲጠብበው ያረግሃል ዘመድ” ማለት ይህ አይደል?
“ልጅ አሳድግ ብዬ፣ ባገር እኖር ብዬ፣
ለባሻ ዳርሁለት ሚስቴን ‹እቴ› ብዬ” ያለው ምስኪን ተገፊ አይነት መሆኑኮ ነው፡፡
“ገዳይ እወዳለሁ መራዥም አልጠላ፣
ሲደክመኝ አርፋለሁ በጎፈሬው ጥላ” ሲሉ ሴቶች የሚያሞካሹበት መንገድም ሌላው የአስተኳሽ ግጥሞች ማሳያ ነው፡፡ ይህ ግጥም “ገዳይ” ወይም “መራዥ” እንጂ አምራች፣ ጥበበኛ፣ የተማረ፣ ደግ፣ ርህሩህ፣ ወይም ለሰው ልጆች መልካም ተግባር የሚያከናውንን አይደለም የሚያወድሰው፤ በዚህ ስሌት ሲታሰብ ቆነጃጅት ለፍቅር የሚመኙት ጎፈሬውን ነቅሶ የትም እያንቦካቦከ ሰላማዊ ሰዎችን እንደ ዱር እንስሳት እያደነ የሚገድለውን እንጂ ሌላውን አይደለም፡፡
ስለዚህ ወንዱ ሁሉ በቆነጃጅት የተመረጠ ይሆን ዘንድ ጎፈሬውን (መላጦችን አይጨምርም) ነቅሶ መንገላወድ አለበት ማለት ነው፤ ቁምጣ ለብሶ፣ ፀጉሩን አሳጥሮ፣ ጥሮ ግሮ የሚኖረውማ ጠያቂ የለውም - በዚህ ግጥም ስሌት ሲታሰብ፡፡
“ገዳይ፣ ገዳይ ያልሽው አባትሽ አይገድል፣ ወንድምሽ አይገድል
አርሶ ያብላሽ እንጂ ሆድሽ እንዳይጎድል” የዚህ ግጥም መልእክት በአጭሩ እንዲህ ሊተነተን ይችላል፡፡ እርሷ “ገዳይ፣ ገዳይ!” ትላለችለች፤ ግን አባቷም ወንድሟም ገዳዮች አይደሉም፡፡ ስለዚህ “ገዳይ” መውደድ የለባትም። ይልቁንም ሆዷ “እንዳይጎድል አርሰው ሊያበሏት ይገባል። እርሻ ደሞ ነውር” ነው፤ የጀግኖች ሳይሆን የፈሪዎችና የጭሮ አዳሪዎች ጊዜ ማሳለፊያ፡፡ ጀግናው፣ አርሶ የሚያበላውና በርካታ በላተኞችን የሚቀልበው ሳይሆን ነፍሰ ገዳዩ ነው፡፡ ስለዚህ ወንድሟም ሆነ አባቷ ገዳዮች እስካልሆኑ ድረስ “ገዳይ” የሚለውን ቃል እንኳ መጠቀም የለባትም፤ የፈሪ ወይ የአራሽ ልጅ ናታ!
“ሰው መግደል እንደግዜር፣ ዱር መግባት እንዳውሬ መቼ ይቸግራል?
ከጓደኛ ጋራ መጫወት ይቀራል”
በዚህ ግጥም መሰረት እንደ እግዚአብሔር ሆኖ ሰውን መግደል፣ ሰውን ገድሎም አለአንዳች ከልካይ ዱር መግባት ይቻላል፤ ግን አንድ ትልቅ ችግር አለ፡፡ እሱም ከጓደኛ ጋር የነበረው ጨዋታ መቅረቱ ነው፡፡ ምክንያቱም ጓደኞች ሁሉ ከነፍሰ ገዳዩ ጋር ዱር አይገቡማ! ይህ በመሰረቱ ፍጹም የሆነ ዕብሪተኛነት ነው፡፡ ከሰው ነፍስ ይልቅ ለጨዋታ ከፍ ያለ ትኩረት የሚሰጥ፡፡
“ምረር ጎበዝ! ምረር እንደ ኮሶ፣ ምረር እንደ ቅል፣
አልመርር ብሎ ነው ዱባ እሚቀቀል”
ይህኛው ግጥም ደሞ የባሰበት ነው፤ ትሁት መሆን፣ ከሰው ጋር መግባባት መቻል፣ በአጠቃላይም ሰላማዊ ኑሮ አስፈላጊ አይደለም እያለ ነው፡፡ ለቤቱም ለጎረቤቱም መራራና ምኑም የማይቀመስ መሆን ሊደርስ ከሚችል ጥቃት ሁሉ መፍትሄ ነው የሚል ይዘት አለው፡፡ ኮሶና ቅል ተቀቅለው የማይበሉት መራራ በመሆናቸው ነው ብሎ ያምናል፡፡ ስለዚህ አመለ ንክ መሆን፣ ህብረተሰቡን ሰላም መንሳት ተገቢ መሆኑን ይሰብካል፡፡
“ገዳይ በየወንዙ፣ በየሸንተረሩ፣
ይፈለግ የለም ወይ የአዳኝ ውሻ ዘሩ”
“በለው በለኝና ላሳጣው መድረሻ፣
ያዘው ሲሉት አይደል የሚናከስ ውሻ!”
የአንደኛው ግጥም ይዘት በአንደኛነቱ የሚታወቅ ወይም የሚመሰገን ውሻ ዘር እንደሚፈለግ ሁሉ የገዳይ ዘርም ያን አይነት ተፈላጊነት አለው የሚል ነው፡፡ ስለዚህም ገዳዩ በወንጀለኛነቱ፣ በነፍሰ ገዳይነቱ ህግን ከመፍራትና ከመስጋት ይልቅ በነውሩ ሲኮራ እናየዋለን - “ገዳይ በየወንዙ፣ በየሸንተረሩ …” እያለ፡፡
ሁለተኛው ግጥም የሚያመለክተው ሎሌነትን ነው፤ ጌታው “በለው!” የሚል ቃል ይውጣው እንጂ ማንኛውንም ወንጀል ከመስራት የማይመለስ፣ በዚህም በጌታው ፊት ሞገስን ማግኘት የሚችልና እንደውሻ ራሱን ዝቅ በማድረጉ የሚኮራ ይመስላል፡፡ አብዛኞቹ የፉከራ ግጥሞችም ገዳይነትን የሚያሞግሱና ሌላውን ሙያ ሁሉ የሚያኮስሱ ናቸው - ምሳሌ እየጠቀስሁ ላስረዳ፡-
“የአሞራው ሲሳይ፣
ሳቅ ሳቅ ይለዋል አምባጓሮ ሲያይ!”
የሚገርም ነገር ነው፤ ፎካሪው አንድ ቀን የጆፌ አሞራ ሲሳይ እንደሚሆን አስቀድሞ ተገንዝቦታል፡፡ ምክንያቱም አምባጓሮ (ጠብ) ሲያይ ከመጨነቅና ሰላምን፣ ዕርቅን ከመሻት ይልቅ በተቃራኒው ወደ ድግስ ቤት የሚሄድ ይመስል ሳቅ ሳቅ ይለዋል! ነገሩ “ጦር ጠማኝ” አይነት መሆኑ ነው፡፡
“ቆላ ተወልዶ፣ ቆላ ያደገ”
እንደ አራስ ነብር ጠብ የለመደ”
ይህኛው ፎካሪ መልክአ ምድሩን ጨምሮ የጠብ ጐሬ አድርጐታል፤ ቆላ ተወልዶ ቆላ በማደጉ ልክ አራስ ነብር ይመስል ጠብ ለምዷል፤ በዚህም ደረቱን ነፍቶ ይኮራበታል፡፡
በመሠረቱ አራስ ነብር ሰውን የምትጠረጠረው ልጇን ሲነኩባት ነው፡፡ ልጇን ከሚነኩባት ሞቷን ትመርጣለች፡፡ ፎካሪው ግን ጠብ ስለለመደ ብቻ በዚህ ከንቱ አመሉ ይኮፈስበታል፡፡
“አባቱ ነበር ቀንበር አንጠልጣይ፣
ልጁ ደረሰ በጩቤ ዘንጣይ”
“አባቱ ነበር ዳዊት ደጋሚ፣
ልጁ ደረሰ በእርሳስ ለቃሚ”
“አባቱ ነበር ከብት አባራሪ፣
ልጁ ደረሰ ቅልጥም ሰባሪ”
ሶስቱም የፉከራ ግጥሞች ተመሳሳይ ይዘት አላቸው፡፡ ፎካሪው ሰውን በጩቤ በመዘንጠል፣ በእርሳስ በማረም፣ ቅልጥም በመስበር ከአባቱ የተሻለ መሆኑን ለማሳየት ተንቦራችቷል፡፡
አባቱ ዳዊት ደጋሚ ከነበረ ልጁም ቢቻል ከአባቱ የተሻለ ጸሎተኛ፣ አለዚያም ቢያንስ መልካም ሥነምግባር ሊኖረው አግባብ ነበር፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው በብልግናው ይፎክርበታል፣ ይመካበታል፡፡
እኒህንና መሰል ግጥሞችን መደርደር ይቻላል፤ ለነገሩ በግጥም ብቻ አይደለም ገዳይ የሚሞካሸው፡፡ አሁን ቀነሰ እንጂ (አንዳንድ አካባቢዎች እንደ ቀጠለ ነው) ገዳይ ብቻ ሳይሆን ሚስቱም የተለየ ክብር ነበራት፡፡ ወንዝ ስትወርድ ቅድሚያ የሚሰጣት፣ በሰርግ፣  በሰንበቴና በዓመት በዓል የእኩዮቿ ሙገሳ የማይለያት ነበረች፡፡ በመሆኑም በባሏ ገዳይነት ትኮፈስበት፣ የገዳይ ሚስት በመሆኗም ራሷን እንደ ዕድለኛ ትቆጥር ነበር፡፡
በአጠቃላይ በሚሰማውና በሚያየው የማህበረሰቡ የ “ግደል” ባህል ውስጥ ያደገ ሰው መሰሉን ቢገድል፣ ቢያብድና ቢወነብድ እንደ ዶን ኪሆቴ ከግዑዝ አካላት ጋር ሳይቀር ቢገጥም  ተጠያቂው ባህሉ እንጂ ከቶ እንዴት እሱ ሊሆን ይችላል? “በል በል” የሚሉት፣ ደሙን የሚያሞቁትና ወደፊት የሚገፈትሩትኮ አስተኳሽ ግጥሞች ናቸው!

Published in ጥበብ

(ካለፈው የቀጠለ)

ባለፈው ሳምንት መጣጥፌ መጨረሻ ላይ በገባሁት ቃል መሰረት፣ የዛሬ ፅሁፌን ሳምንት ያነሳሁትን ጥያቄ በመድገም እጀምራለሁ፡፡ እውነት አስናቀ በፖሊስ ቁጥጥር ስር አልዋለም ማለት ይቻላል እንዴ?...
እኔ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ አስናቀ ዙሪያው ገደል ሆኖበት፣ ወደ መጨረሻ ውድቀቱ የተገፋው በፖሊስ ሀይል ነው፡፡ ክፍል 56 አካባቢ ለሽያጭ ያዘጋጀው ህገ ወጥ የመኪና መለዋወጫ በመጨረሻ ድንገት ከእጁ ብን ብሎ እንዲጠፋ የተደረገው በፖሊስ ጥረት ነው። ትውልድ የማጥፋት አቅም የነበራቸው ወተቶችም ቢሆኑ ፖሊስ በትዕግስትና በማስተዋል በሰራው ጠንካራ ስራ ነው ምንም አይነት ጉዳት ሳያደርሱ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር ሊውሉ የቻሉት፡፡
በመጨረሻስ?...በመጨረሻ ፍሬዘር አስናቀን በቁጥጥር ስር ለማዋል በስፍራው ተገኝቶ ነበር፡፡ ሽጉጡን ፊትለፊት ወድሮ የማንኛውም ወንጀለኛ የመጨረሻ እጣ ፈንታ ምልክት የሆነውን ካቴና ከፍ አድርጎ እያሳየው ባለበት ወቅት ነው ማህሌት ደርሳ የተኮሰችው፡፡
እዚህ ጋ አንባቢያን በመጨረሻ ካሜራው የአስናቀን ፊት በሰንሰለቱ ቀለበት ሾልኮ ያሳየውን ትዕይንት ለአፍታ በአይነ ህሊናቸው መለስ ብለው እንዲቃኙት እጠይቃለሁ፡፡
ይህ ምን ማለት ነው?.....እንዲህ የሆነውስ በምን ምክኒያት ነው?....እነዚህ ጥያቄዎች በበርካታ የኪነ-ጥበብ ስራዎች በተለይም ደግሞ በፊልም፤ በድርሰትና በስዕል ስራዎች በተደጋጋሚ  ጥቅም ላይ ሲውል ስለሚታየው ተምሳሌታዊነት (ሲምቦሊዝም) እንድናስብ ያደርጉናል፡፡
ሲምቦሊዝም ትርጉሙ ብዙ ነው፡፡ በተለያየ መንገድም ጥቅም ላይ ሲውል ሊታይ ይችላል፡፡ እኔ እየጠቀስኩት ባለሁት መንገድ ሲገለፅ ግን መፃኢ እድልንና የመጨረሻ እጣ ፈንታን አመልካች ተደርጎ ሊገለፅ ይችላል፡፡ ብዙ ስራዎችም በዚህ መንገድ ተሰርተው ለዕይታ በቅተዋል፡፡
ለምሳሌ አንድ ገፀ-ባህሪ በጣም አደገኛ የሆነ ማዕበል ወይም ደግሞ አውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ቢታይ ማዕበሉና አውሎ ንፋሱ የዚያ ሰው መጪ ህይወት በከፍተኛ መከራ፣ ውጣ ውረድና ስቃይ የተሞላ እንደሚሆን የሚጠቁሙ ተምሳሌቶች ናቸው፡፡
እዚህ ጋ በአንድ ርዕሱን በማላስታውሰው ፊልም ላይ ዳይሬክተሩ “ካርሎስ ቀበሮው” በመባል የሚታወቀውን አለም አቀፍ ሽብርተኛ፤ ጭካኔና ምህረት የለሽነት ለማመልከት የተጠቀመበትን ቴክኒክ በጥሩ ሲምቦልነት መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ፊልሙ ሲጀምር ካርሎስ አብራው የተኛችውን ቆንጆ ሴት ትቶ በመነሳት መስኮት ዳር ቆሞ ሲጋራ ሲለኩስ ነው የሚያሳየው፡፡ ወዲያው አንዲት ሸረሪት መጋረጃውን ተጠግታ ድሯን እያደራች ቁልቁል ስትወርድ ያያትና፣ ሲጋራ በለኮሰበት ክብሪት ልብልብ አድርጎ ይገላታል፡፡ ታዲያ ሸረሪቷ በእሳት ተለብልባ ስትሞት፣ እሱ ፊት ላይ እርካታና ሞቅ ያለ ፈገግታ ይታያል፡፡
ይሄ ድርጊት ያለምንም ጫጫታና ግርግር የሰውየውን ማንነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ እኛም የሞከርነው ይሄንኑ ነው:: ከላይ የገለፅኩትን ፊልም ያህል የተዋጣ ባይሆንም አስናቀ በመጨረሻ በህግ የተሸነፈ መሆኑን ለማሳየት በማሰብ ነው የህግ የበላይነትና የወንጀለኛ የመጨረሻ ውድቀት ማሳያ በሆነ ሰንሰለት ቀለበት አሾልከን የአስናቀን ፊት ያሳየነው፡፡ በኛ እምነት የህግን አሸናፊነት ለማሳየት ይሄ በቂ ምልክት ይመስለኛል፡፡
የማህሌትና የአስናቀ ፍፃሜ
በዚህ ንዑስ ርዕስ የሚነሳው ሀሳብ በአብዛኛው እላይ ከተነሳው ሀሳብ ጋ ይተሳሰራል፡፡ ማህሌት አስናቀን እንድትገድለው ለምን ተፈለገ ?..ለምንስ በህግ ቁጥጥር ስር ሲውል አላየነውም?.. ደራሲው ደህና መጥቶ መጥቶ እንዴት ብዙ ስትሰቃይ የኖረችውን ማህሌትን ወንጀለኛ ያደርጋል?..ኢትዮጵያዊ እናቶችን ያልሆኑትን እንዲሆኑ አርጎ ማሳየት ነው ወዘተ… የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ናቸው በዚህ ዙሪያ ተደጋግመው የተነሱት፡፡
እዚህ ጋ ሀሳቤን በዝርዝር ለመግለፅ ከመጀመሬ በፊት በድጋሚ አንባቢያን እስከዛሬ ድረስ ካዩአቸው ፊልሞች፤ ቴያትሮችና ድራማዎች መካከል በተለይ ከ“ሰው ለሰው” ድራማ የታሪክ አወቃቀር ጋር የሚመሳሰል አወቃቀር ያላቸው ታሪኮች በምን አይነት አጨራረስ ፍፃሜ እንዳገኙ እንዲያስታውሱ እፈልጋለሁ፡፡
መቼም ሁሌም ባይሆንም በአብዛኛው የእኩይ ገፀ-ባህሪ ፍፃሜ ውድቀትና ሽንፈት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የኔ ጥያቄ የመጨረሻዋን የሽንፈት ፅዋ የሚጋቱት በማን አማካኝነት ነው?..በፖሊስ ነው ወይስ እድሜያቸውን ሙሉ ሊያጠፉት ደፋ ቀና ሲሉና ሲያሰቃዩት በኖሩት በመልካሙ ገፀ-ባህሪ አማካኝነት ነው?..የሚል ነው፡፡
መልሳችሁ በፖሊስ ወይም  በሌላ አካል ሳይሆን ተቃራኒያቸው በሆነው ገፀ-ባህሪ ነው የሚል እንደሚሆን በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል፡፡ ታዲያ ይሄ የሚሆነው ለምንድን ነው?.. የ“ሰው ለሰው” ፍፃሜስ ከዚህ በተቃራኒው ፍሬዘር አስናቀን በቁጥጥር ስር አውሎ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲወስደው የሚያሳይ ቢሆን ኖሮስ የተመልካቹ ምላሽ ምን አይነት ሊሆን ይችል ነበር፡፡ በእርግጠኝነት ከዚህ በጣም እጅግ እጅግ የበዛና መገመት ከሚቻለው በላይ የጠነከረ ብቻ ሳይሆን የከፋ ቅሬታና ተቃውሞ ይነሳ ነበር፡፡
ብዙ ጊዜ የመጥፎ ገፀ-ባህሪውን ውድቀትና የመጨረሻ ቅጣት ከመልካሙ ገፀ-ባህሪ ወይም ደግሞ ገፀ-ባህሪዎች እጅ አውጥቶ ለሌላው ወገን መስጠት እንደ ትልቅ ውድቀት ብቻ ሳይሆን በተመልካቹ የጋለ ስሜት ላይ በጣም የቀዘቀዘ ውሀ እንደ መቸለስም ነው የሚቆጠረው፡፡
አብዛኛዎቹ ፊልሞችና ቴአትሮች መጨረሻ ከላይ የጠቀስነው አይነት የሚሆነውም ሌላ በምንም ሳይሆን በዚሁ ምክኒያት ነው፡፡ ምስኪኑ ገፀ-ባህሪ ብዙ ጊዜ ባላንጣው ከሆነው ገፀ-ባህሪ ብዙ ቁጥር ካላቸው ተከታዮች ጋር እጅግ በጣም እልህ አስጨራሽ የሆነ ትንቅንቅ ገጥሞ ይተርፋል ብሎ ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ተጎድቶ የጠላቱን ተከታዮች ከረፈረፈ በኋላ የዋነኛ ባላንጣውን ህይወት ሲያጠፋ ነው ፊልሞች የሚያልቁት፡፡ ፖሊሶች የሚደርሱትም በአብዛኛው እሱ ጦርነቱን በድል አድራጊነት አሸንፎ ከጨረሰ በኋላ ነው፡፡
እዚህ ጋ አንድ ጥሩ ምሳሌ ለማሳያነት መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት በሀገራችን ተከታታይ ድራማዎች ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስምና ዝና ማትረፍ የቻለ ድራማ “የቀን ቅኝት” በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ በሬዲዮ ተላልፎ ነበር፡፡ ድራማው ከ 250 ክፍሎች በላይ የነበረው ሲሆን በበርካታ ሙያተኞች ዘንድ የላቀ ውጤታማነቱ ተመስክሮለታል፡፡ “የቀን ቅኝት” በሚተላለፍበት ሰአት የከተሞች እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ ይቀዘቅዝ እንደነበር በጥናት ተረጋግጧል። ከሀገራችን አልፎ በተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማትና ዩኒቨርስቲዎች በርካታ ጥናቶች ተሰርተው በመፅሀፍ ታትመው ወጥተዋል፡፡ ስኬቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ሞዴል ሊሆን እንደሚችል ስለታመነበት ሌሎች ታዳጊ አገራትም የባህሪ ለውጥ ለማምጣት በማሰብ የሚያዘጋጇቸውን ድራማዎች በዚህ መሰረት እንዲያዘጋጁ እስከማድረግ የደረሰ ውጤት አስገኝቶአል፡፡
ድራማውን ሰርቶ ያቀረበው ፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር ኢትዮጵያ የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን እንደመታደል ሆኖ እኔም ከድራማው ሶስት ደራሲዎች መሀል አንዱ ነበርኩ፡፡ ታዲያ ከሀገር ውስጥ አልፎ በአለም አቀፍ ደረጃ ይሄን ሁሉ ክብርና አድናቆት ማግኘት የቻለው የ“ቀን ቅኝት” ድራማ፤ በአጨራረሱ ከፍተኛ የሆነ የአድማጮች ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡
ድራማው በአብዛኛው ከ“ሰው ለሰው” ጋ የሚመሳሰል ነው፡፡ ዳምጠው የሚባል እንደ አስናቀ አይነት እኩይ ገፀ-ባህሪም ነበረው፡፡ ድራማው የሚያልቀውም ዳምጠው በፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ህይወቱ ሲያልፍ ነበር፡፡ ይህ አጨራረስ ለማመን የሚከብድ ከፍተኛ የአድማጭ ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡ የተቃውሞው ምክኒያት ደግሞ ይሄን ሁሉ ጥፋት ሲያደርስ የኖረው ዳምጠው እንዴት በአንዴ በሚገላግል ጥይት ይሞታል፡፡ በጣም በሚያሰቃይ ሁኔታ የእጁን አግኝቶና ማቅቆ መሞት ነበረበት የሚል ነበር፡፡
ዳምጠው በጥይት መገደሉ ቀርቶ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሲውል ድራማው አልቆ ቢሆን ኖሮስ?..ሳይሰቃይ በመሞቱ በጣም የተከፋው ተመልካች፣ አንድ ቀን ሊያመልጥ ይችላል ወይም ደግሞ የእስር ጊዜውን ጨርሶ ይፈታል በሚል ስጋትና ተኝቶ ሲቀለብ ሊኖር ነው በሚል ቁጭት የበለጠ ያዝን ነበር፡፡
በነገራችን ላይ ፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር ከዚህ ትምህርት በመውሰድ በቀጣይ የሚሰሩት ተከታታይ ድራማዎች በጠቅላላ አጨራረሳቸው የአድማጩን ስሜት በጠበቀ መልኩ በጥንቃቄ እንዲሰሩ እከመወሰን መድረሱን አስታውሳለሁ፡፡ እንግዲህ እኛም ስለ “ሰው ለሰው” አጨራረስ ስናስብ መጀመሪያ የተፋጠጥነው ከዚህ እውነታ ጋር ነው፡፡ በ“ቀን ቅኝት” አጨራረስ ወቅት የተነሳው ተቃውሞ በ“ሰው ለሰው” እንዲደገምና የተመልካቹ ስሜት እንዲጎዳ አልፈለግንም፡፡
በዚህ የተነሳ የህግ የበላይነትን ለማሳየት አስናቀ ለረጅም ጊዜ በህግ ሀይል ተገፍቶ መቃብር ጫፍ ላይ እንዲደርስ፣ የመጨረሻ እጣ ፈንታውም በካቴናው ምልክትነት እንዲገለፅ በማድረግ ድራማውን በዚህ ሁኔታ ማጠናቀቅ ብቸኛው ምርጫችን ነበር፡፡ በመሆኑም አስናቀ በማህሌት እጅ በተተኮሰ ጥይት ህይወቱን አጥቶና ከህንፃው ላይ ወድቆ ማለቁ በጣም ተገቢ ነበር፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የተነሳው ነጥብ የማህሌት ወንጀለኛ መሆንና ከኢትዮጵያውያን እናቶች ደግነትና ርህራሄ ተቃራኒ የሆነ ድርጊት እንድትፈፅም በማድረግ የእናቶቻችንን ምስል የሚያበላሽ ስህተት ተፈፅሞአል የሚለው ነው፡፡ ማንኛውም ድራማ፤ ፊልምም ሆነ ቴአትር የሚለካውና የሚመዘነው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ባሳየው ታሪክ መሰረት ብቻ ነው፡፡ ታሪኩ ካለቀ ቦኋላ ምን ይከተላል የሚለው የደራሲውም ሆነ የዳይሬክተሩ ራስ ምታት አይደለም፡፡ ቀደም ሲል በምሳሌነት በጠቀስናቸው ፊልሞች ላይ እንደታየው፣ ባላንጣውን ከነተከታዮቹ ረፍርፎ መጨረሱን አይተን ፊልሙ ካለቀ በኋላ የሱ መፃኢ እድል ወንጀለኛ መሆን አለመሆኑ እንደማያስጨንቀን ሁሉ የማህሌትም ጉዳይ ሊያስጨንቀን አይገባም፡፡
እናትነትም ቢሆን በሀገር በድንበር ተከልሎ የሚለይ አይመስለኝም፡፡ እንኳን የሰው ልጅ ቀርቶ እንስሳትም ቢሆኑ ለልጆቻቸው ባላቸው ፍቅር አይታሙም፡፡ እንዲያውም ቤተሰቦቿን አብዝታ የምትወድ ጥሩ እናት፤ የቤተሰቦቿ ህልውና ላይ አደጋ የሚያጋልጥ ችግር ሲገጥማት እራሷን በመሰዋት ሳይቀር ከማጥፋት ወደኋላ የማትል በመሆኗ ነው የምትታወቀው፡፡
ፍሬዘርና የአስናቀ ልጅ የሆነው ልዑል እንዴት አስናቀን ቆመው ያስገድሉታል በሚል ለተነሳ ነጥብ፣ ግድያው ሲፈፀም በስፍራው መገኘታቸውም ቆሞ እንደማስገደል ካልተቆጠረ በቀር ሁለቱም ቆመው አላስገደሉትም፡፡ ጥይት ደግሞ ከሴኮንድ በጣም ባነሰ የማይክሮ ሴኮንድ ነው ጥፋት የሚያደርሰው በሚል ሀሳቡን ያነሱት ሰዎች ደግመው እንዲያስቡበት ጠቁሞ ማለፉን መርጫለሁ፡፡
ልጅ አባቱ ሲገደል በስፍራው ተግኝቶ መመልከቱን በተመለከተም በእርግጥ ነገሩ በጣም ከባድ መሆኑ አይካድም፡፡ ነገር ግን እንደ አስፈላጊነቱ ታሪኩን ተከትሎ አባት ልጁን ወይም ደግሞ ልጅ አባቱን ሲገል ሊታይ የሚችልበት አጋጣሚም እንደሚኖር አለመዘንጋት ያስፈልጋል፡፡
ለዚህ ጥሩ የሆነው ትክክለኛ ማሳያ ዝነኛው `አካፑሉኮ ቤይ` ነው፡፡ የ“አካፑሉኮ” ቤይ ታሪክ የሚያልቀው እኩይ ገፀ- ባህርይ የሆነው ማክስ በጣም በምትወደውና በምትሳሳለት እናቱ በተተኮሰ ጥይት ህይወቱ ሲያልፍ ነው፡፡
የእነሶስና ታሪክ
ይሄ ታሪክ ገና ከጅምሩ በጣም አነጋጋሪ ሊሆን እንደሚችል አውቀንና አምነን ነበር የጀመርነው፡፡ ታሪኩን አስፈላጊ ያደረጉት ሁለት መሰረታዊ ምክኒያቶች ሲሆኑ እነሱም ድራማውን መጠነኛ የኮሜዲ መልክ እንዲኖረው ማድረግና በከፍተኛ ደረጃ ስለ እርቅና ስለ መቻቻል መልዕክት ማስተላለፊያ እንዲሆን ማሰባችን ነው፡፡
በኛ እምነት ሁለቱን ሀሳቦቻችን በሚገባ አሳክተናል፡፡ ሶስና የድራማው ልዩ ቅመም ሆና ተመልካቹን በከፍተኛ ደረጃ ስታስደስት ኖራለች፡፡ ብዙ ሰዎችም በነሱ ታሪክ ስለ ይቅርታና መቻቻል ትልቅ ትምህርት ማግኘታቸውን በተደጋጋሚ ሲገልፁ ተሰምተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሀገራችንን ሁኔታ መለስ ብለን ለመቃኘት ብንሞክር፣ ብዙ ሰዎች ቁጡና ትዕግስት የለሽ ሆነዋል፡፡ በኢትዮጵያውያን ዘንድ “አመሰግናለሁ” ማለትና “ይቅርታ” መጠየቅ አይታወቁም እስኪባል ድረስ በትናንሽ ቅራኔዎች አስፈሪ የሆነ ከባድ የጠላትነት ስሜት ውስጥ በመግባት ተራርቆ መቅረት ዕለት ተለት ክስተት ሆኖአል፡፡    ስለዚህ የ“ሰው ለሰው”ን ታሪክ ስናዋቅር፣ ይሄን አደገኛ የሆነ የጠላትነት ስሜት ብናክም በጥቃቅን ግጭቶች ትላልቅ ጠላትነት ውስጥ ለሚገቡ ወዳጆችም፤ በጣም ከባድና ከይቅርታ በላይ የሚመስል ጉዳይም በይቅርታ ሊታለፍ እንደሚችል ማሳየት በጣም ጥሩ ውጤት ሊያመጣ ይችላል በሚል ነው ታሪካችንን በዚህ መንገድ ያዋቀርነው፡፡
እዚህ ጋ ትልቅ ጥያቄ የተነሳው ሞገስ የልጁን አባትነት አሳልፎ በመስጠቱ ነው፡፡ ልብ አድርጉ! አሳልፎ የሰጠው ስሙን ብቻ ነው፡፡ ታዲያ ለፍቅርና ለሰላም ሲባል ይሄ ቢደረግ ለምን ያስገርማል፡፡
ሞገስ አሳልፎ የሰጠው ስሙን ብቻ ነው፡፡ አባትነት ከስም ባሻገር ብዙ መገለጫዎች አሉት፡፡ አባትነት ፍቅር ነው፡፡ አባትነት ስሜት ነው፡፡ አባትነት መንፈሳዊ ትስስር ማለት ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ ሞገስ ከስሙ ውጪ ሌሎች የአባትነት መገለጫ የሆኑትን ተግባሮች ሁሉ እንዳይፈፅም የሚከለክለው ምንም ምክኒያት የለም። ጉዳዩ ከፍቅርና ከእርቅ በላይ የሶስቱ ትስስር መቼም ቢሆን ሊፈርስ ይችላል ተብሎ በማይታሰብበት መንገድ ነው እልባት ያገኘው፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ በየትኛውም ሰብአዊና ህጋዊ ሚዛን ብንመዝነው፣ ከሱ ይልቅ እናቱ ነች ህፃኑን የማሳገድ መብት የሚኖራት፡፡ በዚህ ላይ ልጅን አሳልፎ በጉዲፈቻ የመስጠት ባህል ያለው ማህበረሰብ ውስጥ ነው የምንኖረው፡፡ በተለያዩ ምክኒያቶች በወላጅ አባቶቻቸው ሳይሆን በአያቶቻቸው ፤ በአሳዳጊዎቻቸውና በሌሎች ስም የሚጠሩ ብዙ ሰዎች በሀገራችን እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሁሉ እውነታዎች ከግምት አስገብተን ስንመዝነው ነው የሞገስን ድርጊት ተገቢ ሆኖ የምናገኘው፡፡
በመጨረሻም ፅሁፌን ከማጠናቀቄ በፊት ይሄን ሁሉ ስል “ሰው ለሰው” ምንም ስህተት የማይገኝለት እንከን አልባ ድራማ ነው ለማለት እየሞከርኩ አለመሆኑን በትልቁ ላሰምርበት እፈልጋለሁ፡፡
በትክክል ከፈተሽነው በጣም ብዙ እንከኖችና ጉድለቶች ሊኖሩበት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የአስናቀ መጨረሻ ላይ ሽጉጥ ይዞ አለመተኮስ፣ የተወሰኑ ገፀ-ባህሪያት ታሪኮች በአግባቡ እልባት ሳያገኙ መቅረት ወዘተ … ከብዙ በጥቂቱ ሊገለፁ ይችላሉ፡፡
እውነቱን ለመናገር እኛ ከብዙ ድክመቶቻችን አንድ ትልቅ እርምጃ ወደፊት ተጉዘናል፡፡ ከኛ በኋላ የሚመጡ ሙያተኞች ሁለት ሶስት ብለው ይበልጥ እንደሚራመዱ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ለተሻለ ስኬት እንዲበቁም ልባዊ ምኞቴን ከበዛ ትህትና ጋር ልገልፅላቸው እወዳለሁ፡፡
አክብረው ያስከበሩንን ውድ ተመልካቾቻችንንም ከታላቅ ምስጋና ጋር ያክብርልን፤ እድሜ፤ጤና፤ሰላምና ፍቅሩን አብዝቶ ይስጥልን እላለሁ፡፡

Published in ጥበብ

በመኩሪያ መሸሻ የተዘጋጀው “ከቤተ መንግስት ደሴ የብላታ    ወ/ማሪያም መዘክር” የሚል መፅሀፍ ሰሞኑን ለንባብ በቃ።
ማመልከቻና ደብዳቤ በአይነቱ ይገለጥበታል የተባለው መፅሀፉ፤ ብላቴን ጌታ ወ/ማሪያም አየለ ከ1912 ዓ.ም እስከ 1925 ድረስ በቁም እጅ ፅሁፋቸው በማስታወሻነት የከተቡት እንደሆነና ስለማዕድን፣ ስለፀጥታ፣ ስለ አውሮፕላን ግዢ፣ ስለ ጋምቤላ ወሰን፣ ስለ ጣና ባህር ልኬትና ግደባ፣ ስለ ጉምሩክ እቃዎችና መሰል ጉዳዮችን የያዘ መሆኑን አዘጋጁ በመፅሀፉ መግቢያ ላይ ገልጸዋል፡፡ 200 ገጾች ያሉት መፅሀፉ፤ በ35.50 ለሽያጭ ቀርቧል፡፡

Page 4 of 20