Saturday, 28 September 2013 14:31

የ‘ቃለ መጠይቅ’ ነገር…

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለብርሀነ መስቀሉ አደረሳችሁ!
ስሙኝማ…ሰሞኑን…አለ አይደል… ‘ስትራቴጂና ዕቅድ በመንደፍ፣ የእኔን ተጠቃሚነት ከፍ በሚያደርግ አካሄድ ቃለ መጠይቅ ለመስጠት ዝግጅት በማድረግ መርሀ ግብር የምነድፍበትና ወደ ትግበራ ልገባ ዝግጅት በማድረግ ያለሁበት ሁኔታ’ ነው ያለው፡፡ (የአንዳንዱ ሰው ትንፋሽ ምስጋን ይግባው!)
እናላችሁ… ለ‘አቅመ ቃለ መጠይቅ’ ተደረሰም፣ አልተደረሰ…ዘንድሮ ዝም ከተባለ ተውጦ መቅረት ይመጣል! ፎቶ ‘ለአቅመ መጽሔት ሽፋን’ የደረሰ ባይሆንም፣ ድምጽ ‘ለአቅመ ኤፍ.ኤም. “ፕሮግራማችሁ ተመችቶኛል” የበቃ ባይሆንም፣ አኮሰታተርና ‘ሲርየስ’ መምሰል ለአቅመ ቴሌቪዥን “አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች” ባይደርስም…ብቅ ተብሎ “እዚህ ነኝ…” ካልተባለ መኖራችን የሚታወቅልን በህዝብ ቆጠራ ወቅት ብቻ ሊሆን ነዋ!
እናላችሁ…ቃለ መጠየቅ ስሰጥ…አለ አይደል…ያው ‘መፈረጅ’ ምናምን ለሁሉም ስለማይቀር ጋዜጠኛ ሆዬ ከሊጥነት አላልፍ ያለው እንጀራ ‘ማብሰያ ምጣድ’ እንዳያደርገኝ…ልጄ ጠንቀቅ ነው። (በቅንፍ የተቀመጠው በሆዴ…ይቅርታ…በውስጤ የማስበውን እንደሆነ ልብ ይባልልኝ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…)
ያው እንደተለመደው “በዛሬው ዝግጅታችን እከሌ እከሌ የሚባል እንግዳ…” ምናምን ይባልና የመጀመሪያው ‘ጥያቄ’ ይከተላል፡፡
ጥ፡– ስምዎንና የመጡበትን ቢነግሩን፡፡
(የምር እኮ… ‘ዘይገርም ዘንድሮ’ የሚያሰኝ ነው። አይደለም ስሙንና የመጣበትን የተወለደ ቀን ጎረቤት የሆነ ጠበል ይጠጣ እንደነበር ለመናገር ጫፍ ከደረሰ በኋላ በድጋሚ “ስምዎንና የመጡበትን…” ምናምን ተብሎ ሲጠየቅ አያስቸግርም! እናማ እንደፈረደብኝ ‘የተጠየኩትን’ እመልሳለሁ፡፡)
ጥ፡– ለመሆኑ ምግብ ላይ እንዴት ነህ? (እንዴት ነው ነገሩ…ስለ አራት ኪሎ ይጠይቀኛል ስል ስለ ራሴ ኪሎ! አሀ…ስለምግብ መጠየቅ ያው ስለ ኪሎ መጠየቅ ነዋ!)
መ፡– ማለት፣ ምግብ ላይ ስትል…
ጥ፡– ማለት…የምግብ ምርጫህ ምንድነው?
(የምግብ ምርጫ! አጅሬ…በራስህ ተነሳሽነት አራድነትን እንደ አርቲፊሻል ጸጉር ራስህ ላይ ቀጥለህ ጎንጉነሀልና ማሞኘትህ ነው! አሀ…በስንት ነገር ፍረጃ በበዛበት በሆዴ ምን አመጣው! ነገርዬውማ የዋዛ ጥያቄ አይደለችም፡፡ “ስፓጌቲ” ካልኩ…“ይሄ ሰውዬ በግራዚያኒ መታሰቢያ ግንባታ ላይ እጁ አለበት እንዴ?” ሊባል ይችላል፡፡ “ፈጢራ” እንዳልል…“እስቲ ግብጽ ኤምባሲ አካባቢ አዘውትሮ ይታይ እንደሆነ ክትትል ይደረግበት” ሊባል ይችላል…“የበቆሎ ገንፎ” እንዳልል “ለናይጄሪያዎች ስለ አሰላለፋችን ምስጢር አሳልፎ እንዳይሰጥ ልምምድ አካባቢ ዝር እንዳይል…” ሊባል ይችላል። ልጄ ዘንድሮ የምንጠጣው የቢራ አይነት እንኳን ‘መፈረጃ’ በሆነበት ዘመን…)
መ፡– እንጀራ በወጥ…
(ልጄ…ምንም እንኳን ‘የጤፍ ተጠቃሚ ቢበዛም’… ማስፈረጅ እስክትጀምር ድረስ “እንጀራ” ማለቱ ይሻላል!)
ጥ፡– አሀ…እንጀራ ለምሳና…
መ፡– የምን ምሳ ቁርሴም፣ ምሳዬም እራቴም እንጀራ በወጥ ነው፡፡
(እፎይ! ጠያቂዬ ለምሳ ሲያስበኝ የሻይ ቁርስ አደረግሁት…)
ጥ፡– በአጠቃላይ አመጋገብህ እንዴት ነው?
(ሰውየው ምን ነካው! ከምግብ ጋር ጥብቅ የሚለው ይርበዋል እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ… ስሙኝማ…የሆነ ጊዜ አንድ አንባቢዬ ጽሁፎቼን ሲያነብ ስለ ምግብ የሚነሱ ነገሮች ቢበዙበት ለአንድ ወዳጄ ምን አለው መሰላችሁ…“ይሄ ሰውዬ… ይርበዋል!” እናላችሁ…ጥያቄዋ አስቸጋሪ ነች፡፡ ልክ ነዋ…“ቁርሴን በዚህ ሰዓት፣ ምሳ በዚህ ሰዓት፣ እራት በዚህ ሰዓት…” ምናምን ካልኩት ምን ሊባል ይችላል መሰላችሁ… “መካከለኛ ገቢ ለመድረስ ስንትና ስንት ዓመት እየቀረን ይሄ ሰውዬ በቀን ሦስቴ ሊበላ የቻለበት ምክንያት ይጣራ…” ምናምን ሊባል ይችላላ!)
መ፡– ያው በቃ ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ የተለየ አመጋገብ የለኝም፡፡
(አሪፍ ጠያቂ ቢሆን “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ያልከውን ብታብራራልኝ…” ምናምን ይለኝ ነበር፡፡)
ጥ፡– በአሁኑ ጊዜ ለሚታየው የሸቀጦች ዋጋ መናር ምን የምትለው ነገር አለ?
(ኧረ! ተባለ እንዴ!… “ምን ነጋዴዎች ላይ የሚጣለው የታክስ መአት…” ምናምን ብል “የሚገዛው ዕቃ ወይም የሚገዛበት ገንዘብ ሳይኖረው መርካቶ የሚመላለሰው እኮ ነገር ቢኖረው ነው…ለቂማ ምናምን ጣል፣ ጣል ሳያደርጉለት አይቀሩም…” ሊባል ይችላል፡፡ “የዋጋ መወደድ የዕድገት ምልክት ነው…” ብዬ ‘ለጊዜው ስሙ የማይታወሰኝ ኤኮኖሚስት የተናገረውን’ ብደግም “አጅሬዋ እኮ እንደ ምስጥ አፈር ስር ነው የምትሳበው…” ሊባል ይችላል፡፡)
መ፡– እንግዲህ ለዋግ መጨመር ምክንያት የሆኑ ነገሮችን በመመርመር…(እያልኩ ቀብጠርጠር አደርግና ጠያቂዬም እኔም ያልኩት ሳይገባን ‘ጥያቄው ይመለሳል’፡፡)
ጥ፡– ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ምን ትላለህ?
(እንዴት ነው ነገሩ! ኧረ’ባክህ ስለ አራት ኪሎ…)
መ፡– ጥያቄው አልገባኝም፡፡
ጥ፡– ማለት የአገራችን ሙዚቃ አድጓል ወይስ ወድቋል ትላለህ፡፡ (ኧረ እንደው የኢትዮጵያ አምላክ ውድ…ተውኩት፡፡)
መ፡– ኮፒራይት ይከበር…
(ጨረስኩ፡፡ ደግሞ… “ከየትም፣ ከየትም የተቆረሰና የተቦደሰ ዜማ አይሉት ‘ለህዝብ የተደረገ ንግግር’… እየለጠፉ ሙዚቃችንን እንኩሮ እያደረጉት ያሉ አንዳንድ…” ምናምን ብዬ “አንዳንድ ጋዜጠኛ ተብዬዎች…” ልባል! ስለሙዚቃ ስናወራ ከዚህ በፊት ያወራናት ነገር ትዝ አለችኝማ…አንድ ወዳጄ የሆነ ዘፋኝ አልበም ባወጣ ቁጥር ምን ይል ነበር መሰላችሁ…“እንትና ለኢትዮጵያ ህዝብ ንግግር አደረገ…” ይል ነበር፡፡)
ጥ፡– ብሔራዊ ቡድናችን ከሠላሳ አንድ ዓመት በኋላ አሁን ያለበት በመድረሱ ምን ይሰማሀል?
(የብሔራዊ ቡድን ነገር ገና ማስፈረጅ ስላልጀመረ ቀላል ነው፡፡)
መ፡– አሪፍ ነው፡፡
ጥ፡– ስለ አገር ውስጥ ቡድኖችስ ምን ታስባለህ?
(ምንም! ልጄ…ስንት ነገር ሲባል እየሰማን…አንዳንዴ ኳስ ጨዋታ እንደ ‘ሌላ አይነት ፍልሚያ’ እየተቆጠረ…ምንም አላስብም! ይልቅ ስለ አራት ኪሎ…)
መ፡– የአገር ውስጥ ውድድር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ (ዓረፍተ ነገሮች አጠር ሲሉ አሪፍ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…)
ጥ፡– እኔ ጨርሻለሁ፣ እርሶ የሚጨምሩት ነገር አለ? (የምጨምረውማ…የሰጠኋቸው መልሶች ለሲቪህ ይጠቅሙሀል? ልክ ነዋ…አንዳንዴ ቃለ መጠይቅ አድራጊዎች…አለ አይደል…ልክ ስኖውደንን የሚያፋጥጡ የኤፍቢአይ ሰዎች አይነት ሲያደርጋቸው ያየኋቸው ይመስለኛላ! ስሙኝማ…መልሱ እነ እሱ ለክተው፣ ቀደው እንደሰፉት ሆኖ ካልተሰጣቸው የሚቆጡ ‘ቃለ መጠይቅ አድራጊዎችን’ ልብ ብላችሁልኛል! ለምን ቢሉ…ሲቪ ይበላሻላ! እነ እንትና…አለ አይደል… “…ያለበት ሁኔታ ነው ያለው…” “ዓለምን እያስደነቀ ያለው ዘርፈ ብዙ ዕድገት…” “ለብዙ ሀገራት ምሳሌ የሆነው ግስጋሴያችን…” ምናምን እያሉ አልፈው ሲሄዱ ‘የበይ ተመልካች ሆኖ መቅረት’ ይመጣላ!
መ፡– የምጨምረው የለኝም፡፡ (ይልቅ አለቃህን ሂደህ “ለምንድነው ደሞዝ የማትጨምርልኝ?” ብትል አይሻልም!)
ሀሳቤን ለውጫለሁ፡፡
ቃለ መጠይቅ ለማድረግ የነደፍኩት ታክቲከና ስትራቴጂ የእኔን ተጠቃሚነት ገምግሞ በመፈተሽ ልማታዊ የሆነ መፍትሄ የማይሰጥ፣ ይልቁንም ያለፈውን ናፋቂነት የሚታይበትና የተባበሩት መንግሥታትን ‘ሚሌኒየም ዴቬሎፕመንት ጎል’ ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ አካሄድ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እኔ ደግሞ በዚህ ከቀጠልኩ የትንፋሽ እጥረት ሊገጥመኝ የሚችልበት ሁኔታ ነው ያለው!
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Published in ባህል
Saturday, 28 September 2013 14:00

“ሲኖዶሱ ስለመስቀሉ

መግለጫ እስኪሰጥ ህዝቡ በትዕግስት ይጠባበቅ”
ስለመስቀሉ ከሰማይ መውረድ በጀመሪያ መረጃው እንዴት ነው የደረሳችሁ?
መስቀሉ ከሰማይ ወረደ ስለሚባለው የሻለ መረጃ የምታገኙት ወረደ ከተባለበት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎችና አገልጋዮች ነው። እኛ ከሰማይ ወረደ ከተባለ ከቀናት በኋላ ነው በስፍራው የተገኘነው፡፡ ስለዚህ እነሱ እንደነገሩን እንጂ አይተናል ሰምተናል ብለን አይደለም መረጃ የምንሰጣችሁ፡፡
እነሱ ግን እንዴት እንደወረደ አይተናል ስላሉ መረጃውን ከእነሱ ነው ያገኘነው፡፡ ከእነሱ የተነገረን እንግዲህ ነሐሴ 23 ለ24 አጥቢያ ሌሊት እንደወረደ ነው፡፡ ነሐሴ 23 የቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ክብረ በአል ነው፡፡ ጽላቷም ከቅዱስ ገብርኤል ጋር በተደራቢነት አለ፡፡ ሌሊት ማህሌት ቆመን ሳለ ከፍተኛ ድምጽ ተሰማ ነው የሚሉን፡፡ ተደናግጠን ስንወጣ ወደ ቤተልሄሙ አካባቢ መስቀሉ ወድቆ የሚንቦገቦግ ብርሃን አየን ነው ያሉት፡፡ ወዲያውኑ ሲነጋ እንዳንነካ ፈርተን ማንሳትም አልቻልንም፤ ነገር ግን በወቅቱ ዝናብ ስለነበር እዚያው ላይ መስቀሉ ሳይነሳ ድንኳን ተከልንበት ነው ያሉን፡፡ የታቦት መጐናፀፊያ ለማልበስም ወደ መስቀሉ ሳንቀርብ፣ ወርውረን አለበስነው ብለውናል፡፡ እኛ ነሐሴ 24 ወዲያውኑ ከሰአት ነበር የሄድነው፡፡ ስንሄድ ከባድ ዝናብ ስለዘነበና ቦታውም በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ መድረስ አልቻንም፤ ተመለስን፡፡ በ25 እንዲሁ ጥረት አድርገን ነበር፡፡ አልተሳካም። ነገር ግን በ27 ከሰዓት በኋላ ሄድን፡፡ መንገዱ እጅግ ፈታኝና በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ምንም ማድረግ ስለማይቻል ነው እንጂ መንገዱ ከአቅሜ በላይ ነበር፤ ነገር ግን ሊቀጳጳሱ ካልመጡ ለማንሳት እንቸገራለን ስላሉ እንደምንም ቦታው ደረስን።
ህዝቡም በጣም ይጐርፍ ነበር፡፡ ፀጥታ አስከባሪዎችም በብዛት ነበሩ፡፡ ወደ 10 ሰአት አካባቢ ደረስን፡፡ የት ነው ያለው አልናቸው። ወደ ድንኳኑ መሩን፡፡ መሬት ላይ ወድቆ ተመለከትነው፡፡
በወቅቱ ከመሬቱ ላይ እንዲነሳ እነሱ ብዙም ፍቃደኞች አልነበሩም፡፡ እዚያው ላይ እያለ ቤተክርስቲያን እንዲሠራለት ነው የፈለጉት፡፡ ነገር ግን ቤተክርስቲያን የሚሰራለት ከሆነም መስቀሉ መሬት ላይ ሆኖ አይደለም የሚቆፈረውና የግድ ወደመቅደሱ መግባት አለበት አልናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ፍቃድ ከሆነ ለወደፊት ሊሠራ ይችላል ብለናቸው ውዳሴ ማርያም ደግመን የሚገባውን ፀሎት ከካህናቱ ጋር አደረስን፡፡ ከዚያም ወደ ድንኳኑ ገብተን መስቀሉን አነሳን። መጀመሪያ እኔ ነበርኩ መስቀሉን ያነሳሁት። ከዚያም ሰባኪያኑ እንዲይዙት አድርገን ቤተክርስቲያኑ አንድ ጊዜ ዞረን፣ ወደ መንበረ ታቦቱ እንዲገባ አደረግን፡፡ እስካሁን እንግዲህ ይህ ነው ያለው ሂደት፡፡
መስቀሉ ሲነሳ ብርሃናማና የሚያቃጥል ነበረ፣ ብዙ ተአምራቶችም ታይተዋል ተብሏል? በእርግጥ እነዚህ ነገሮች ነበሩ?
ያቃጥል ነበር የሚለው እንደው የሚያቃጥል ቢሆን ኖሮ መቼ እናነሳው ነበር፤ አናነሳውም። እኔ እንደዛ መስሎኝም ነበር የሄድኩት እንጂ መነኮሳቱ ማንሳት ይችሉ ነበር፡፡ የሚያቃጥል ነበረ፣ የሚበራ ነበረ ምናልባት ጨለማ ሲሆን ታይቶ ይሆናል እንጂ እኛ ምንም አላየንም፡፡
ወርቃማና የሚያንፀባርቅ ነው የተባለ ነውስ?
እንግዲህ ወደፊት ስለመስቀሉ በስፋት የሚገለጽ ይሆናል፡፡ ሰዎችም በተለያዩ መንገዶች ስለመስቀሉ እየጠየቁን ነው ጉዳዩን ለሲኖዶሱ አቅርበን፣ ሲኖዶሱ የሚሰጠውን መመሪያ ተቀብለን ያለውን ነገር እንገልፃለን፡፡ እንግዲህ አሁን ህዝጀ ምዕመኑ ግማሹ ያለውን ነገር ተቀብሎ ይሄዳል ግማሹ ደግሞ እንዲሁ ለማታለል ነው ይላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ህዝቡ ግራ የተጋባ በመሆኑ የግድ ሀገ ስብከታችን ሰፋ ያለ መግለጫ የሚሠጥበት ይሆናል፡፡ ብዙ የተባለለት ጉዳይ ስለሆነም የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የግድ ያስፈልጋል፡፡ እዚያ ካሉ ሰዎች ጋርም ሰሞኑን እየተነጋገርንበት ነው፡፡
መስቀሉ በቅዱስ ሲኖዶሱ እውቅና ባላገኘበት ሁኔታ ፎቶግራፉን በ10 ብር ለሽያጭ ማቅረብና ገቢ ማሰባሰብ አግባብ ነው?
እንግዲህ ይሄን የመሳሰለውን ጉዳይ ለማስተካከል ከቤተክርስቲያኑ አስተዳደሮች ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ ችግሩ ምን መሰላችሁ? ቤተክህነት እውቅና ሳይሰጠው ቀድሞ ህዝቡ እውቅና ይሰጠዋል፡፡ እኔ ሄጄ በነበረ ጊዜ ስለመስቀሉ አስተያየት ብሰጥ ኖሮ ምን አይነት ትርምስ ይፈጠር እንደነበረ ትገነዘቡታላችሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ የሆነ ሆኖ ለወደፊት በስፋት ትምህርት እንዲሰጥ ጥረት ይደረጋል፡፡ የቋሚ ሲኖዶሱ የሚሰጠው ልዩ መመሪያ ይኖራል፤ ከዚያ በኋላ መግለጫ ይሰጥበት ሲባል በኋላ መረጃ በስፋት ይሰጣል፡፡
ብዙ ጊዜ ተመሳሳይ ተአምራት ታይተዋል ይባላል፡፡ ለእነዚህ ተአምራት እውቅና የሚሰጠው የትኛው አካል ነው?
ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡
ሲኖዶሱ ካልሰጠ ተቀባይነት አይኖረውም?
አዎ አይኖረውም፡፡ ስለዚህ መስቀሉም ቅዱስ ሲኖዶሱ ውሣኔ ካልሰጠ ተቀባይነት የለውም። በመሠረቱ መስቀሉ ያቃጥላል፣ ይፋጃል የሚባለው ሃሰት ነው፤ መስቀል ይፈውሳል እንጂ አያቃጥልም፡፡ እንዲህ ከዚህ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ ለወደፊት በስፋት ትምህርት የሚሰጥበት ሊሆን ይችላል፡፡
በዚህ ላይ ሲኖዶሱ መቼ ነው ውሣኔ የሚያሳልፈው?
እንግዲህ ዛሬ ከሰአት የቤተክርስቲያኗን አስተዳዳሪዎች ጠርተናቸዋል (ይህ ቃለ ምልልስ የተደረገው ማክሰኞ ጠዋት ነው) ቅዱስ ሲኖዶሱ መረጃ ከነሱ ይጠይቃል፤ ከምን ተነስተው እንደዚህ እንዳሉ ከዚያ በኋላ ጉዳዩ በውይይት እስኪታይ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ስለዚህ በዚህን ጊዜ ውሣኔ ይተላለፍበታል ብሎ ለመናገር አሁን አይቻልም፡፡
መስቀሉን ብፁዕነትዎ ሄደው ተመልክተውታል፡፡ ታዲያ ስለመስቀሉ በእርግጠኝነት መናገር እንዴት አይቻልም? ፓትርያርኩም ባሉበት ነው የሚታየው ብላችኋል?
ፓትሪያርኩ እሄዳለሁ አላሉም እስከመጨረሻውም ላይሄዱ ይችላሉ፡፡ አይደለም እሣቸው እኔም ላልሄድ እችል ይሆናል፡፡ ፓትርያሪኩ ውሣኔ የሚያስተላልፉ ከሆነም በየደረጃው ያሉ ፈፃሚዎች ጉዳዩን የሚከታተሉት ይሆናል፡፡ አሁን ላይ ብዙ መናገሩ ለስህተት ይዳርጋል፡፡ እንዳልኳችሁ የቋሚ ሲኖዶሱ ውሣኔ ይጠበቃል፡፡
ቢያንስ በስልጣን ደረጃ እርስዎ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጻጳስ ነዎት፡፡ መስቀል ወርዷል ተብሎ ፎቶግራፉ ለሽያጭ ሲቀርብ ዝም ብሎ መመልከቱ ተገቢ ነው? ገንዘቡስ በምን ሞዴል ነው ገቢ የሚሆነው?
ሞዴልማ አድባራቱ ሁሉ አላቸው፡፡ በቤተክርስቲያናችን መመሪያ መሠረት፣ የአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ወሳኝ አካል ነው፤ ቤተክርስቲያኗን ወክሎ ይከሳል፣ ይከሰሳል ውል ይዋዋላል፣ የልማት ስራ ይሰራል፡፡ ስለዚህ ሰበካ ጉባኤው ሙሉ ስልጣን አላቸው፡፡ ስርቆትና ማጭበርበር ተፈፀመ የሚባል ከሆነ አጣሪ አካል ሄዶ ነው ሪፖርቱ የሚመጣው፡፡ ነገር ግን የትኛውም ቤተክርስቲያን በተቀመጠለት የአሰራር መመሪያ ገንዘብ የመሰብሰብ መብት አለው፡፡ ይሄ መስቀልም ሰበካ ጉባኤው ወስኖ ፎቶግራፉ 10 ብር ወይም 5 ብር እየተሸጠ ለህዝቡ ይሰራጭ ብሎ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ በትክክልም በዚህ መል/መ ገቢው ለቤተክርስቲያኑ ከሆነ ህጋዊ አሠራር ነው፡፡
ወረደ የተባለው መስቀል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የምትጠቀማቸው የመስቀል አይነት አይደለም የሚሉ አስተያየቶችም እየተሠነዘሩ ነው…
እንግዲህ ስለመስቀሉ አሁን ዝርዝር ነገር መናገር አልችልም፡፡ በእርግጥ ከሠማይ ወርዷል? የማን መስቀል ነው? ከየት የመጣ ነው? የሚለው ከቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሣኔ በኋላ እንገልፃለን፡፡ ውሸት ሆኖ ከተገኘም ሠዎቹ ተጠያቂ ሊሆኑበት ይችላል፡፡
እርስዎ መስቀሉን ከተመለከቱት ይሄ የኦርቶዶክስ ነው አይደለም ለማለት እንዴት ከበድዎት?
እንደነገርኳችሁ የአንድ ሠው አስተያየት ተገቢ አይደለም፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሡ መስቀሉን አስቀርቦ ከተመለከተ በኋላ የሚሠጠው ውሣኔ የግድ ነው። ለነገሩ መስቀል መስቀል ነው፤ ይሄ የእገሌ ነው ያ የእኔ ነው የሚባል አይደለም፡፡ እንግዲህ መስቀሉ ላይ የሥነ ስቅለት ምስል አለበት፡፡ ይሄ አሣሣል የኛ የኦርቶዶክሣያውያን አይደለም የሚለውን የሲኖዶሡ ውሣኔ የሚያረጋግጠው ይሆናል፡፡ ሲኖዶሡ ውሣኔ እንሠጣለን እያለ በዋዜማው እኔ ሌላ ነገር ብናገር አግባብ አይሆንም፡፡ ህዝቡንም ያምታታል፡፡
ለህዝቡ የሚያስተላልፉት መመሪያ ካለ?
እንግዲህ ይሄ በኛ ሃገር ብቻ አይደለም የሚፈጠረው፡፡ በግብፅ (ዘይቱና) እመቤታችን ታየች ተብሎ እኔም አይቸዋለሁ፡፡ አሁን በቅርቡ ደግሞ በሩሲያም ሠማይ ላይ ትልቅ መስቀል ተስሎ ታየ ተብሎ በየሚዲያው ሲነገር የሩስያ ቤተክርስቲያን መግለጫ ስትሠጥበት ነበር፡፡ እና ይሄ በኛ ብቻ ሣይሆን በሁሉም ያለ ነውና ህዝቡ እውነታውን ለማወቅ መታገስ አለበት። ሲኖዶሡ መግለጫ ቢሠጥበት እንኳ ሁሉም ህዝብ በእኩል አረዳድ አይረዳውም፡፡ ግማሹ ተአምር ነው ሊል ይችላል፡፡ ሌላው አይደለም ሊል ይችላል። ለማንኛውም ከቅዱስ ሲኖዶሡ ውሣኔ በኋላ በየሚዲያው መግለጫ የሚሠጥበት ይሆናል፡፡ ህዝቡ ሲኖዶሡ ውሣኔ እስኪሠጥበት ድረስ “ይሄ ነው ያ ነው” ሣይል፣ ተረጋግቶ የራሱን ትችትና ውሣኔ ሣይጨምርበት እንዲጠብቅ እንጠይቃለን፡፡
ውሣኔው በቅርቡ በመገናኛ ብዙሃንና በየቤተክርስቲያኑ የሚሠጥ ይሆናል፡፡ እስከዚያው መታገስ ያስፈልጋል፡፡

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 28 September 2013 13:58

የአዳማ ጉዞ ማስታወሻ!

(ካለፈው የቀጠለ)
“አንኳኩ ይከፈትላችኋል”
ከአዳማ ዕድሮች፣ የእንረዳዳ ዕድሮች ማህበር፣ ሰብሳቢ ከአቶ ታምራት አስፋው ጋር መወያየት ላይ ሳለሁ ነበር ባለፈው ጽሑፌን ያቋረጥኩት። የማህበሩ ሰብሳቢ ባለ ሁለት እርከን ፎቅ በገቢ ምንጭነት ለመሥራት እንዳቀደ፤ የተለያዩና ተያያዥ አካላትን በር እንዳንኳኳ ነገረኝ፡፡
በተለይ ከሃይማኖት ድርጅቶች ጋር በጥብቅ ትስስር እንደተግባቡ አወጋኝ፡፡
“ገብርኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ ትልቅ መድረክ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ሰባቱ ወንጌሎች ተጋብዘው ሌሎችም ምዕመናን በተገኙበት ትልቅ ጉባዔ አድርገን፣ ከፍተኛ ድጋፍ ተገኘ” አለኝ። “ምን ብላችሁ ተናግራችሁ ነው?” አልኩት። አቶ ታምራት የሚገርም መልስ ነው የሰጠኝ፡፡ “መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆቻቸውን ስላጡ ህፃናት ምን ይላል? ህብረተሰቡ ምን ሊያደርግላቸው ይገባል? ምንድነው ግዴታው? ይህንን በተመለከተ አባት መምህራንና ካህናት ለምዕመኑ አስተማሩልን፡፡ የደከሙ አረጋውያንን ስለመርዳት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ምዕመናንስ ምን ይጠበቅባቸዋል? አስረዱልን አልን፡፡ ትልቅ ትልቅ ትምህርት ሰጡልን” ምዕመናኑ፤ ምን ያህል ይሆናሉ ብዬ ጠየኩት፡፡ “ከ10ሺ በላይ” አለኝ በኩራት፡፡
አሁን ደግሞ እንደዚሁ ከሙስሊሞቹም ጋር ተግባብተናል፡፡ አንድ መድረክ ሊፈጥሩልን ነው፡፡ ከካቶሊኮች፣ ከፕሮቴስታንቶችም እንደዚያው ብቻ፤ አንኳኩ ይከፈትላችኋል ነው ሚስጥሩ፡፡ ለሥራህ ራስህን መስጠት ነው፡፡ አሳታፊ ዓይነት አሠራር ካለ የማይከፈት በር የለም፡፡
ከዚያ ሠሌዳ ላይ ያሉ ፎቶዎች አሳየኝ። “ምንድናቸው?” አልኩት፡፡ “ባለሀብቶች” አለ ኮራ ብሎ፡፡ “አላማችንን ተረድተው በሙያም፣ በገንዘብም፣ በቁሳቁስም ድጋፍ የሰጡን ናቸው። ከብፁዕ አቡነ ጐርጐሪዮስ የምሥራቅ ሸዋ አገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ጀምረህ፤ የክሊኒክ ባለቤት በል፣ የሆቴል ባለቤት በል፤ የዩኒቨርሲቲ መምህር/ወጣት (ባለቀይ ክራቫት፣ መምህር የበጐ ፈቃድ አገልጋይ) እነዚህ ሁሉ ህፃናትን በነፃ በማከም፣ በየወሩ ለዕድሜ ልክ የገንዘብ መዋጮ በመስጠት፣ አረጋውያንን በመደገፍና ልጆችን በማሳደግ ስኮላርሺፕ በመስጠት ከፍተኛ ትብብር እያሳዩን ነው፡፡ ሌላውን ተወውና፤ ለህፃናት 25ሺ ለአረጋውያን 25ሺ እና በዓመት ግማሽ ሚሊዮን የሰጠን ሰው አለ፡፡ ያበረታታናል ባለሀብቱ፡፡
“ይቺ በር ማንኳኳት በጣም ጥሩ ናት እ”? አልኩት፡፡
“መጽሐፉ ነዋ ያለው! ለምን እንቆጠባለን፡፡ አለዚያ ትዕዛዝ ማፍረስኮ ነው!”
በኦሮሚያ ሴቶች ጉዳይ ጽ/ቤት በኩል ከአምናው ማስ ስፖርት 326,955.55 ብር አግኝተናል” አለኝ፤ አሁንም በሥራ እርካታ፡፡ ሌላ የተደረደሩ ፎቶዎች አየሁና “እነዚህስ?” አልኩት፡፡ “እነዚህ አረጋውያን ናቸው፡፡ የምንረዳቸው ናቸው፡፡ ቀይ መስቀል ወጣቶችን አስተባብረን ግቢያቸው ይፀዳል፡፡ ልብሳቸው ይታጠባል፡፡ ሲታመሙ እናሳክማቸዋለን፡፡ በዓመት በዓል ቀን ሥጋ ቋጥረን በባጃጅ እንልክላቸዋለን፡፡ ጐረቤት እንዲያጐርሳቸው እናስተባብራለን”፡፡
በምን መረጣችኋቸው? አልኩት፡፡ “መመዘኛ አለና! አምስት መስፈርቶች አሉ” ለአሳዳጊዎች ብድርና ቁጠባ አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ ፋይናንሱን በሂሳብ ህግ በባለሙያ ነው የምናስተዳድረው፡፡ ግልጽ አሠራር ነው ያለን፡፡ ካልሆነ ነገ አለመታመን ይመጣና ያ ሁሉ ግርማ ሞገስ ይሟሽሻል፡፡ ዓላማው ሟሸሸ ማለት ነው፡፡ ምስክርነት ካጣን ማህበር የለም ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው እንደድሮ ልጃገረድ የምንጠነቀቀው!!
ቀጥዬ፤ “አሁን እንደእየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ያሉት አብረዋችሁ የሚሠሩ ድርጅቶች ቢለዩዋችሁ እንዴት ትቀጥላላችሁ?” አልኩት፡፡ “በጭራሽ አትጠራጠር፤ ራሳችንን ችለናል። ለወጣቱ መዝናኛ ማዕከል ዘርግተናል፤ የባለሁለት ፎቁ ገቢ አለ፣ ዘመናዊ ቀብር ማስፈፀሚያ አቅደናል፣ ፎቶ ኮፒ ማዕከል ልናቋቁም ነው፤ ምኑ ቅጡ! ዘላቂነታችን አስተማማኝ ነው፡፡
ከታምራት ጋር ሻይ ቡና ብለን ተለያየን፡፡
* * *
ቁጥር 5 የቅዱስ ገብርኤል መረዳጃ ዕድር - “ልጅነቴን ያስታወሰኝ ዕድር”
“ካፒታላችን ህዝባችን ነው!”
- የዕድሩ ሰብሳቢ
ናዝሬት (አዳማ) አገሬ ነውና ከእንረዳዳ ማህበር ቀጥዬ ካራመራ ሆቴል ጀርባ ወደሚገኘው ቁጥር 5 የቅዱስ ገብርኤል መረዳጃ እድር አመራሁ፡፡ የናዝሬት ፀሐይ ማቃጠል ጀምሯል፡፡ የጥንት የጠዋት የአዳማ ልጅ ብሆንም አልማረችኝም፡፡ “ከልጅ ልጅ ቢለዩ ዓመትም አይቆዩ” ነው መሰለኝ የናዝሬት ፀሐይ መርህ!
“ነባር ዕድር ይመስላል” አልኩት፤ ለዕድሩ ሰብሳቢ ለአቶ ክፍሌ፡፡
“ይሄ ዕድር እኔ ከቤተሰብ የወረስኩት ነው” አለኝ መካከለኛ ዕድሜ ላይ ያለ የሚመስለው ጠይሙ፤ አጠር ያለው መሪ - አቶ ክፍሌ፡፡ ፀሐፊውና ፕሮጄክት ሃላፊው፤ የሥራ ባልደረቦቹ አጠገቡ አሉ፡፡ “ዕድራችን፤ በኃይለ ሥላሴ ጊዜ የተቋቋመ ነው፡፡ ደርግ ሲመጣ ቤቶቹን ወረሰ፡፡ ከሚከራዩት ቤቶች ማህል እስካሁንም ያልተመለሱ አሉ” አለ ክፍሌ በቁጭት፡፡ ከአዳማ እጅግ ነባር ዕድሮች ውስጥ ምናልባት አንደኛ ነው በሚባለው ቅፅር ግቢ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ (62 ዓመት ያህል ሆኖታል፤ 1937 ዓ.ም ስለተመሠተ) ክፍሌ ሲናገር በቁጭት ነው፡፡ “ዕድሩ ቤት ተቸግሯል፡፡ ሌላው ይጠቀምበታል፡፡ ዞሮ ዞሮ እስከደርግ ማብቂያ ድረስ የዕድሩ የልማት ሀሳብ ተቀዛቅዞ ቆየ፡፡ ከ417 በላይ አባላት የነበሩት አንጋፋ ዕድር፤ ግማሹ - አገር እየቀየረ፣ ግማሹ እያረጀ፣ ከፊሉ እየሞተ፤ አሁን ወደ 340 ግድም አባላት አሉት፡፡ በዚህ ዘመን እንግዲህ የልማት አቅጣጫዎች ቀርበዋል፡፡ መንግሥትም ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡”
“ዕድሩ እንዴት የልማት አቅጣጫ ያዘ?”
“በድሮ ጊዜ የነበረው ባህላዊ የመረዳዳት መንፈስ ብቻ ሳይሆን፣ ለምን ወደ ልማት አንገባም? አልን። ገባን፡፡ መንግሥት በዚሁ ከተማ 680 ካ.ሜ ቦታ ሰጠን፡፡ ባለ 4 ፎቅ ት/ቤት ሠርተን-ሥራ ጀምሯል፡፡ አቅጣጫው፤ ላይ ወደ መድሐኒዓለም ነው!”
“በምን ገንዘብ ነው የምትንቀሳቀሱት?” አልኩት።
“የህብረተሰቡን መዋጮ በመጠቀም ነው። ይሄ ህ/ሰብ ሁሉን ያሟላል፡፡ በቂ ደሀ አለው፡፡ መካከለኛና ከፍተኛ ሀብታም አለው፡፡ በዕውቀትም ከመጨረሻ ወለል እስከ ላይ ድረስ አለው፡፡ በጋራ ይሠራሉ። ለምሣሌ ምህንድስናውን የያዙልን አባላት አሉን። በጎ-ፈቃደኞች ማለቴ ነው። የሚገርምህ ቦታውን ስንጠይቅ የተጠየቅነውን ጥያቄ ነው ያነሳህልኝ-“በምን ገንዘብ ትሠሩታላችሁ? ካፒታላችሁን አሳዩን?” አሉን፡፡ ካፒታላችን ህዝባችን ነው፣ ነበር ያልናቸው፡፡ ዕውቀት ያለው፣ ገንዘብ ያለው ህዝብ አለን! በሃሳቡ ተስማሙ፡፡ በደስታ ሰጡን። ት/ቤቱ ዛሬ በወር 17ሺ ብር ያስገባል፡፡ በዚህ አላቆምንም። በየጎዳናው ላይ የሚወድቀውን፣ ረዳት ያጣውን፣ ከኑሮ ወለል በታች የወደቀ ድሀ እንርዳ ብለን ተነሳን፡፡ ያን ጊዜ እየሩሣሌም ህፃናትና ማ/ሰብ ልማት ድርጅት እንዲህ ያለ የተቀደሰ ተግባር የሚያካሂዱ ዕድሮችን ያፈላልግ ስለነበር፤ እኛን ያገኘናል፡፡ ሁሉንም ጠይቆን ፕሮጀክታችንንና ዓላማችንን ከተረዳ በኋላ፤ በገንዘብ ሊደግፈን ፈለገ፡፡ ርዳታ ሰጠን፡፡ እኛም በሚገባ ተግባራዊ አደረግን፡፡ ወላጆቻቸውን ላጡ ህፃናት ድጋፍ ሰጠን፡፡ ለአሳዳጊዎቹ የብድርና ቁጠባ አገልግሎት ሰጠን፡፡ አደጉና ራሳቸውን ቻሉበት፡፡ ለህፃናት የት/ቤት ቁሳቁስ ከላጲስ እስከ ዩኒፎርም ልብስ፣ ቦርሳ፣ መደበኛ ልብስ፣ ጫማ ስናደርስ ቆየን፡፡ ይሄ አንደኛው ፌዝ (Phase) ነበር፡፡ ቀጠልን፡፡ በሁለት፣ ሦስት መርሀግብር ተራ (Phase) 200 ህፃናትንም በትምርት አቅርቦት በኩል ምንም ሳይጐልባቸው እንዲማሩ ወላጆቻቸውና አሳዳጊዎቻቸው ራሳቸውን እንዲለውጡና ራሳቸውን እንዲችሉ ብድር ሰጥተን አጠነከርናቸው፡፡ ህፃናት፤ ከህክምና ማዕከል ጋር እየተነጋገርን እንዲታከሙ አድርገናል፡፡
(ሌሎቹ የዕድሩ አባላት የሰጡት አንኳር አንኳር አስተያየት በሚቀጥለው ሣምንት ከደብረ ዘይትና ከአዋሳ ጉዞ ማስታወሻዬ ጋር ይቀርባል!)
(ይቀጥላል)

Published in ባህል

በ የአመቱ መስከረም ወር ላይ የሚከበረው የኢሬቻ በአል በነገው እለት በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ በደማቅ ስነስርአት ይከበራል፡፡ ይህ ክብረ በአል በኦሮሚያ ክልላዊ አስተዳደርም ትኩረት ከተሠጣቸው ህዝባዊ በአላት አንዱ ሆኗል፡፡ የብሄረሰቡ መገለጫ ባህላዊ ስርአት እንደሆነም በስፋት ትምህርት እየተሠጠበት ነው፡፡ በአንድ በኩል ባህላዊ ስርአት ብቻ ስለሆነ ሃይማኖት ሣይለይ ሁሉን ያሣትፋል የሚሉ ወገኖች ሲኖሩ በሌላ በኩል ደግሞ ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው በአል ነው የሚሉ አሉ - ባህላዊ ስርአት ብቻ አለመሆኑን በመግለፅ፡፡
ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው በአል ነው ነገር ግን በሂደት ከሌሎች ዘልማዳዊ ባህሎች ጋር ተቀላቅሎ ይከወናል ከሚሉትና ይህን አካሄድ ለማረምና ለማቃናት ከሚጥሩ የእምነት ተቋማት መካከል “አለማቀፍ የዋቄፈና ሃይማኖት ማህበር” በሚል የሚጠራው ይገኝበታል፡፡ ከተቋቋመ አምስት አመት ገደማ የሞላው ማህበሩ ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው በአል ነው ብሎ ይከራከራል፡፡ የማህበሩ ሊቀመንበር የሆኑት ጉላ ቀነአ ለሚ ኢሬቻ ከዋቄፈና ሃይማኖት አንፃር ያለውን አንድምታ፣ የአከባበር ሂደቱንና ስርአቱን በተመለከተ ማብራሪያ ለዝግጅት ክፍላችን ሠጥተዋል፡፡ በአሉ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚከበርበት የቢሾፍቱ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ጫላ ሶሪ በበኩላቸው ኢሬቻ ከሃይማኖታዊነቱ ይልቅ ባህላዊነቱ ያመዝናል” ከሚለው ሃሣባቸው ተነስተው ስለበአሉ የበኩላቸውን ማብራሪያ ሠጥተውናል፡፡


“የኢሬቻ በአል ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው ነው” - ጉላ ቀነአ ለሚ
የኢሬቻ በአል አሁን ከሚንፀባረቀው የተለየ ነው እያሉን ነው …
ኢሬቻ ማለት ማምለክ እና ማመስገን ማለት ነው፡፡ ይሄን ስላደረግህልኝ፣ ከክረምት ወደ በጋ (ብራ) ስላሸጋገርከኝ አመሠግናለሁ እየተባለ ፈጣሪ የሚመሰገንበት ነው፡፡ ኢሬቻ ሠፊ አገልግሎቶች አሉት፡፡ መነሻውም በጣም የራቀ ነው፡፡ ሠው ማምለክ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የመጣ ነው። መጀመሪያ እንደውም አምልኮ የተጀመረው በኢሬቻ ነው፡፡ በተለይ የኦሮሞን ብሔር ጨምሮ በኩሽቲክ የቋንቋ ክፍል ውስጥ የሚጠቃለሉ ብሄሮች ሃይማኖቶች ከመምጣታቸው በፊት ኢሬቻ (እርጥብ ሣር) ይዘው ነው ፈጣሪያቸውን የሚለማመኑት፡፡ ኢሬቻ በእርጥብ ሣር ይወከላል፡፡
ለጋብቻ ጥያቄ በራሱ (ኢሬቻ) እርጥብ ሣር አገልግል ውስጥ ተጨምሮ ነው የሚላከው፡፡ እንግዲህ እነዚህን ነገሮች በምናይበት ጊዜ ኢሬቻ ሃይማኖታዊ ዳራ ያለው መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ድሮ ሠዎች መልዕክተኛ ሲልኩ እርጥብ ሣር ቆርጠው በመስጠት፣ “አደራህን በፈጣሪ ስም ይህን መልዕክት አድርስልኝ” ብለው ይልኩታል፡፡ እንግዲህ ቃል በቃል ሲገለፅ፤ ኢሬቻ ሣር ወይም የተመረጡ ዛፎች ቅጠል ማለት ነው፡፡
ኢሬቻ በአመት ሁለት ጊዜ ነው የሚደረገው የመጀመሪያው ከነሐሴ መጨረሻ ጀምሮ እስከ ጥቅምት መጨረሻ ይካሄዳል፤ ሁለተኛው ደግሞ በበልግ ወራቶች ግንቦትና ሠኔ ውስጥ የሚደረግ ነው፡፡ ሁለተኛው ግን አሁን እየተረሣና እየተዳከመ ነው ያለው፡፡ ሠዎች መገንዘብ ያለባቸው ኢሬቻ ሃይማኖት አይደለም ነገር ግን ሃይማኖታዊ ክብረ በአል ነው፡፡ ለምሣሌ ጥምቀት ሃይማኖታዊ በአል ነው እንጂ ሃይማኖት አይደለም፡፡ ኢሬቻም እንዲሁ ነው፡፡
እምነቱ ምንድን ነው?
የሃይማኖቱ ስም ዋቄፈና ነው፡፡ የእምነቱ ተከታይ ዋቄፈታ ነው የሚባለው፡፡ ከዋቄፈና ሃይማኖታዊ በአላት አንዱ ኢሬቻ ነው፤ ሌሎችም ብዙ በአላት አሉ፡፡ ሌላው ከዚህ ሃይማኖታዊ በአል ጋር በልማድ አብሮ ተቀላቅሎ የሚከወን ነገር አለ፡፡ ለምሣሌ ቡና ማፍላት፣ ዛፍ ቅቤ መቀባት፣ ስለት ማግባት፣ ሽቶ ውሃ ውስጥ መወርወር የመሣሠሉ አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ልማዶች ናቸው እንጂ የሃይማኖቱ መርሆች የሚያዛቸው አይደሉም፡፡ ቅቤ መቀባት ግን “ሙዳ” ከሚባለው ስርአት ጋር ይያያዛል፡፡ አንድ ንጉስ ሣይቀባ እንደማይነግስ ሁሉ አንድ የማምለኪያ ቦታም ተቀብቶ እውቅና ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ ነገር ግን አሁን እየተደረገ እንዳለው በየጊዜው ሣይሆን አንድ ጊዜ ብቻ ነው ይህ ስርአት ተፈፃሚ የሚሆነው። አንድ ንጉስ በየጊዜው እንደማይቀባ ሁሉ አንድ የተመረጠ የማምለኪያ ስፍራም በየጊዜው ሊቀባ አይገባም፡፡ ቀቢውም ማንኛውም ሠው ሣይሆን የተመረጠ መሆን አለበት፡፡
የኦሮሞ ህዝብ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታይ ነው፡፡ በክርስትናውም በእስልምናውም ሃይማኖት ውስጥ ያሉ አሉ፡፡ እነዚህ እንዴት ነው የዚህ በአል ተሣታፊ የሚሆኑት?
በምሣሌ ልንገርህ፡- እኔ ክርስቲያን አይደለሁም፤ ዋቄፈታ ነኝ፡፡ ነገር ግን የመስቀል ደመራ ስነስርአትና የጥምቀት በአል ላይ እገኛለሁ፡፡ ለኔ ይሄ ባህሌ ነው፡፡ ስለዚህ ክርስቲያን ለሆኑ ኦሮሞዎች፣ ይሄ ሃይማኖታቸውን ሣይለቁ ባህላቸው መሆኑን ተረድተው ተሣታፊ ሊሆኑበት ይችላሉ ማለት ነው። ለእነሡ ባህል ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ባህል ነው እንጂ ሃይማኖታዊ መሠረት የለውም ማለት የለባቸውም፡፡ ኢሬቻ ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው በአል ነው፡፡ የማንኛውም ሃይማኖት ተከታይና ፍላጐቱ ያለው ሁሉ የመሣተፍ መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የእሬቻ በአል ከዋቄፈና ሃይማኖት በአላት አንዱ መሆኑን መካድ የለበትም ወይም አቅጣጫውን እንዲስት መደረግ የለበትም፡፡
የበአሉ አከባበር ምን ይመስላል?
የኦሮሞ ህዝብ በየቦታው ያለና ሠፊ ስለሆነ የበአሉ ትውፊታዊ አከባበር ወጥነት የለውም፡፡ የተለያዩ ክዋኔዎች ይንፀባረቃሉ፡፡ በአከባበርም ይለያያሉ፡፡ መሠረታዊ ስርአቱ ግን እሬቻ (እርጥብ ሣር) ይይዛሉ፣ በእለቱ የሚዘመሩ መዝሙሮች ይኖራሉ ነገር ግን እነዚህ መዝሙሮች በቱለማ፣ በሜሜ እንዲሁም በቦረና የተለያዩ ናቸው፡፡ ዋናው ነገር ግን መዝሙሩን እየዘመሩ ወደ “መልካ” (ወንዝ) ይሄዳሉ፡፡ እዚያም ሲደርሡ “በክረምት ወቅት ያሉትን ተግዳሮቶች አሣልፈህ ለዚህ ላደረስከን በጣም እናመሠግናለን” ይላሉ፡፡ በዚያው ቀንም ግለሠቦች ኢሬቻውን ይዘው የጐደለባቸውን ለፈጣሪያቸው በፀሎት እየነገሩ መለመን ይችላሉ፡፡ መልካው (ወንዙ) ምልክትነቱ ከዚህ በኋላ በጋ ሆኗል፣ ወንዙም ጐድሏል፤ ዘመድ ከዘመድ ወንዝ እየተሻገረ መጠየቅ ይችላል ብሎ የሚገልፅ ነው፡፡ በእለቱ ሽማግሌዎች ሃይማኖታዊ ንግግሮች ያደርጉና በድሮው ባህል እርድ ይኖራል፣ ያ ይበላ ይጠጣና ፈጣሪን በተለያዩ ጨዋታዎች እያመሠገኑ ወደየመጡበት ይመለሣሉ ማለት ነው፡፡
ሃይማኖቱን የሚመሩት እነማን ናቸው?
ምዕመናኑ “ሚሤንሣ” ይባላሉ፡፡ በገልማ (ቤተ-አምልኮ) ውስጥ በዝማሬ አገልግሎት የሚሠጡት ዋዩ ይባላሉ፡፡ አባ ከኩ የሚባሉት ደግሞ ፀሎት አድራሽ ናቸው፡፡ ሉባ የሚባለው የተለያዩ የአስተዳደር አመራር ቦታዎችን የሚያከፋፍል ነው፡፡ ቀጥሎ የሚመጣው ጉላ ነው፡፡ ጉላ ከተጠቀሡት በላይ ሆኖ በማዕከላዊ ደረጃ ሃይማኖቱን የሚመራ ነው፣ ይህ ግለሠብ በሃይማኖቱ ላይ ከ13 አመት በላይ ያገለገለ መሆን ይኖርበታል፡፡ በሌላ በኩል በገዳ ባህላዊ አስተዳደራዊ ስርአት በኩልም የሚመጣ የጐላ ደረጃ አለ፡፡ የመጨረሻው ደረጃ አባ ኬና ይባላል፡፡ አባ ኬና የገዳ ስርአቱንም ሆነ ሃይማኖታዊ ስርአቱን ልቅም አድርጐ የሚያውቅ ሊቅ ነው፡፡
በዚህ የኢሬቻ በአል አያንቱዎች ተሣትፎ ያደርጋሉ፡፡ ከእነሡ ጋርስ ያላችሁ ግንኙነት ምንድን ነው?
እንዲህ አያንቱ የሚባለው በሃይማኖታዊው ስርአት ውስጥ ያለ ነው፡፡ ነገር ግን እኛ የምንቀበለው አንድ አያንቱ ሠዎችን ይሄን አደርግላችኋለሁ ብሎ ገንዘብ የማይቀበልና አስቀድሞ የተጠቀሡትን ልማዳዊ ክዋኔዎች የማይከውን ከሆነ ብቻ ነው። ከነዚህ ሁሉ የፀዳ ከሆነ ትክክለኛ አያንቱ ነው ብለን እንቀበላለን፡፡ ከመርሆው የወጣ እንደሆነ ግን አንቀበለውም፡፡

=============
“የኢሬቻ በአል
ባህላዊነቱ ያመዝናል” - አቶ ጫላ ሶሪ
የባህልና ቱሪዝም ቢሮው ስለ ኢሬቻ የሚሠጠው ትንታኔ ምንድን ነው?
ኢሬቻ ማለት የኦሮሞ ህዝብ የዋቄፈና ስርአት ነው፡፡ ዋቄፈና ማለት ሃይማኖታዊ ማለት ነው። ትልቁ ነገር የዋቄፈና በአል ነው ብንልም በባህል የተሞላ ነው፡፡
እንደ ሌላው ንፁህ ሃይማኖታዊ በአል ነው ማለት አይቻልም፡፡ በአብዛኛው ባህሉ ነው ጐልቶ የሚንፀባረቀው፡፡ “ኢሬቻ” የምትለዋ ቃል የምትወክለው ሣር ወይም አበባ ነው፡፡ ያንን የያዘ ሠው ኢሬቻ የሚሄድ ሠው ነው፡፡ ዋቄፈና ማለት ደግሞ ለአንድ አምላክ ብዙ ሆኖ ምስጋና ማቅረብ ማለት ነው፡፡
የኦሮሞ ህዝብ በአንድነት ተሠብስቦ በፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበት ነው፡ ይህ ሃይማኖታዊ ቢያሠኘው ይችል ይሆናል፡፡
እድምተኞቹ “መሬሆ” የሚለውን የምስጋና መዝሙር በአንድነት እያሠሙ ለአምላካቸው ምስጋና ያቀርቡበታል፡፡ ባህላዊ የምንለው ደግሞ ህዝቡ የፈለገውን የባህል ጭፈራ እየጨፈረ ነው የሚመጣው ወንዱም ሴቱም በልዩ አለባበስ ተውቦ በአሉ ወደሚከበርበት ስፍራ ይሄዳል፡፡ እንደ ኢሬቻ ባህልን በጉልህ የሚያሣይ በአል የለም፡፡ ለዚህ ነው ባህሉ ስለሚያመዝን ሃይማኖታዊነቱ ይሸፈናል፡፡ በኦሮሞ ባህሎች በእጅጉ የተሞላ ነው፡፡
የዋቄፈና ሃይማኖት ተከታዮች የእምነቱን መሠረታዊ መርሆች በጠበቀ መልኩ እየተከበረ አይደለም የሚል ቅሬታ ያነሣሉ?
አንዳንድ ፈሩን የለቀቁ ሠዎች የሚያደርጉት ድርጊት አለ፡፡
እኛም፣ የኦሮሞ ህዝብም፣ አባ ገዳዎችም የሚቃወሙት ድርጊቶች አሉ፡፡ የኦሮሞ ዋቄፈና በአንድ አምላክ ብቻ ነው የሚያምነው፡፡ እግዚአብሔር ተአምር የሠራበት ቦታ ብለው ነው እዚያ የሚሄዱት እንጂ ወንዝ ለማምለክ አይደለም፡፡
የኦሮሞ ህዝብ ሰይጣን አለ ብሎ አያምንም፡፡ ሰው ሲያብድ በአንድ ጣሳ ውሃ የሚለቅ ሰይጣን እንደት ባህር ውስጥ ይተኛል ብሎ ነው የሚጠይቀው ስለዚህ ኦሮሞ በዛፍ እና በወንዝ አያምንም፡፡
እዚያ ቦታ ግን መሰብሰቦያና ፈጣሪን የሚያገኝበት ቦታ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንዶች በስለት ስም ውሃ ውስጥ ሽቶ መወርወራቸው የመሳሰለው ለባህሉም በእምነቱም ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ነው፡፡
በዘንድሮ በአካልም ይህን መሰሉን ድርጊት ለማስቀረት በአባገዳዎ በስፋት ትምህርት ይሰጣል፡፡
በሚዲያዎች ላይ እሬቻ ባህላዊ ነው እንጂ ሃይማኖታዊ አይደለም ብላችሁ መግለፃችሁን የሚስኪኑም አሉ?በዚህ ላይ የእርሶ ምላሽ ምንድን ነው?
አንድ ማንም ያልገነዘበው ነገር አለ፡፡ ባህልና ሃይማኖት የጤፍ ቅዳች ነው፡፡ ሊለያይ የማይቻል ነው፡፡ በማንኛውም ሃይማኖት ውስጥ ባህል ይንፀባረቃል፡፡ በጋብቻ ውስጥ እንኳ ሁለቱም ይንፀባረቃሉ፡፡
የቀለበት ቃልኪዳን ማህበር ከእምነት ጋር ይገናኛው፣ ጭፈራዎቹና ፌሽታዎች ደግሞ ባህል ናቸው ባህል ማለት የማንነት መግለጫ ነው፡፡ ሃይማኖት፣ ታሪክ ቋንቋ ባህል ውስጥ የሚጠቀለሉ ናቸው እንሊ ባህልና ሃይማኖትን ለያይቶ መመልከት ትክክል አይደለም፡፡ በእሬቻ ላይ ደግሞ የበለጠ የሚንፀባረቀው ባህላዊነቱ ነው የኦሮሞ ትልቁ ፀሎት የሚባለው ምረቃ ነው። ምረቃውን ደግሞ ሙስሊምም ክርስቲያንም ይመርቃል፡፡ ስለዚህ እሪቻ ሁሉንም ሃይማኖት የሚያሳትፍ ባህል ነው፡፡
እሬቻ በዓል የሚውልበት ቀን በምንድነው የሚታወቀው?
በእርግጥ አሁን የእሬቻ አቆጣጠር ከመስቀል ደመራ ጋር ይገናኛል፡፡ ድሮ ሌሎች ሃይማኖቶች ማይገቡ ቀኑ ከነሃሴ ጀምሮ ይከበር ነበር ነገር ግን አሁን ከመስቀል ደመረ ማግስት ባለው እሁድ ቀን ነው የሚሆነው፡፡
በመስቀል ደመራ ነው ቀኑ የሚታወቀው ወቅቱ የአበባና የልምላሜ ወቅት ትልቅ ተስፋ የሚታይበት ስለሆነ ለዚህ በቅተናል ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 28 September 2013 13:44

ተራ ዜጋ መሆን አሰኘኝ!

እስር ቤቱን እኔ አልፈጠርኩትም፡፡ ለእስር ቤቱ የንጽህና አያያዝ ምንም ማበርከት የምፈልገው ነገር የለም፡፡ ሌሎቹ የሚደርጉትን አደርጋለሁ፡፡ ሌሎቹ የማያደርጉትን አላደርግም። ሲሰሩ እሰራለሁ፣ ሲፈሩ እፈራለሁ፣ ሲገድሉ እገድላለሁ…ሲዘርፉ እዘርፋለሁ፡፡ ንሰሐ ሲገቡ እገባለሁ፡፡


ተራ ዜጋ መሆን አሰኘኝ፡፡ ተራ፤ ማንንም የማልጐዳ ማንንም የማልጠቅም፡፡ በቀዮች መሀል የምቀላ፣ በጠይሞች መሀል የምጠይም፤ በጥቁሮች መሀል ጠቁሬ የምመሳሰል፡፡ ማስመሰል ሳያስፈልገኝ የምመሳሰል ተራ ዜጋ መሆን አማረኝ፡፡
አማርኛ የምናገር ተራ ዜጋ በአማሮች ሀገር። የአማሮች ሀገር ወደ ትግሬዎች አሊያም ወደ ኦሮሞዎች ስትቀየር እኔም መስዬ የምቀያየር፡፡ ጥርሰ ፍንጭት ወይንም ግንባረ ቦቃ ሆኜ ድሮ የሆንኩትን፣ ድሮ የከረምኩበትን ማንነት ለአሁኑ ለሆንኩበት የማላሳብቅ፡፡ ሌሎቹንም ሆነ እራሴን የማላሳቅቅ፡፡
ሀገር ሰላም ሲሆን ሰላምን የምመስል፣ ጦርነት ሲመጣ የምዘምት፡፡ ከአሸናፊዎች ጋር እምጨፍር፣ ከተሸናፊዎች ጋር አንገቴን የማቀረቅር ተራ ዜጋ ልሁን፡፡ ንጉስ ሲመጣ በንጉሱ የምምል፣ በደርግ ዘመን የመንግስቱን ፎቶ በጭቃ ቤት ግርግዳዬ ላይ የምለጥፍ…በልማታዊው መንግስት ዘመን ልማትን የማፋፍም…ለሁሉም ወቅት የምሆን ዘመናዊ ተራ ዜጋ ልሁን፡፡ ዘመኔ የሚያራምደኝ፡፡ የሚያራምደኝን የማራምድ፡፡ “የምራመደው ወደ የት ነው?” ብዬ ከመጠየቅ የተሰወርኩ ልሁን፡፡ የተሰወርኩለት ይሰውረኝ!
ስሜ ብሔሬን፣ ብሔረሰቡ በሌለበት የማይመሰክር፤ ፀጥ ያለ ስም ለራሴ የማወጣ፤ ሰፈር ስቀይር የሚቀየር ነፃ አመለካከት ያለኝ አድርባይ ያድርገኝ፡፡ በስብሰባ መሀል የሰውን አትኩሮ የማይስብ አስተያየት ከተገደድኩ ብቻ የምሰነዝር… ሌሎች ቢሰነዝሩብኝ እንኳን የማልከላከል፤ ነገር ግን፤ ሰው በተሰበሰበበት ስፍራ ተሰብስቤ ከመገኘት የማልቦዝን ልሁን፡ የምሰበሰበው፤ ለመመሳሰል እንጂ ለመካፈል እንዳይሆን የምጠነቀቅ…የማንም የሃሳብ መራቀቅ እንዳይገባኝ…የማንም አጉል ሀገር ወዳድነት እንዳያገባኝ ሆኜ የተሰራሁ…የእስር ዘመኔን ብቻ በዚህ ሲኦል ውስጥ አጠናቅቄ መሞት የምፈልግ ተራ ዜጋ መሆን አሰኘኝ፡፡ አማረኝ ተራነት፡፡ በተራው ላይ መጀመሪያም መጨረሻም ያልተሰለፍኩ፣ መሪም ተከታይም ያልሆንኩ ስም የለሽ መሆን ናፈቀኝ፡፡
ልታይ ልታይ ባዮቹንስ ማን አያቸው? ልታይ ልታይ ሲሉ ያያቸው መከራ ብቻ ነው፤ በእኔ ዕይታ። ግን፤ “የኔ እይታ” ብሎ ነገር የለም፤ በተራነት ጽንሰ ሃሳብ ውስጥ፡፡ የኔ ሃሳብ የሚያዋጣ ነው፡፡ የሚያዋጣው መደበቅ ነው፡፡ በእስር እያለሁ፤ የእስር ቤቱ ዘበኛ ሆንኩ ወይንም እስረኛን አሰልፎ ነጂ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ ራስን ከመሸወድ ውጭ። በሞት ነፃ ለምትለቀቅበት እስር ቤት በህይወት ላይ የምታደርገው ነገር ምን ይጠቅማል? ተራ ሆኖ መደበቁ ይሻላል፡፡
እስር ቤቱን እኔ አልፈጠርኩትም፡፡ ለእስር ቤቱ የንጽህና አያያዝ ምንም ማበርከት የምፈልገው ነገር የለም፡፡ ሌሎቹ የሚደርጉትን አደርጋለሁ፡፡ ሌሎቹ የማያደርጉትን አላደርግም፡፡ ሲሰሩ እሰራለሁ፣ ሲፈሩ እፈራለሁ፣ ሲገድሉ እገድላለሁ…ሲዘርፉ እዘርፋለሁ፡፡ ንሰሐ ሲገቡ እገባለሁ፡፡ እኔ ተራ ዜጋ ነኝ፡፡ ምንም ልዩ ነገር ከእኔ አትጠብቁ፡፡
“ከሰይጣን እና ከእግዚአብሔር ማንን ታምናለህ?” አትበሉኝ፤ “በቀላሉ ከህዝቡ ጋር እሚያመሳስለኝን” እላችኋለሁ፡፡ ሰይጣን እና እግዜርን ደባልቆ በሚጠቀም ህዝብ መሀል ለነብሳቸው የቆሙትን አበሳ እንዴት እንዴት አድርጐ እንደገነጣጠላቸው ተመልክቻለሁ። እኔ መገነጣጠልም መነጣጠልም አልፈልግም። ከስምንት ቢሊዮን የፉርጐ ቅጥልጥሎች መሀል አንዱ ነኝ። የተለየ ቀለም ፉርጐዬን ቀብቼ ለኢላማ ራሴን አላጋልጥም፡፡ ሌሎቹ የሚያደርጉትን እያደረግሁ፣ ያደረግሁት እንዳይታወቅ በሚያደርግ ድርጊት ውስጥ መደበቅ እፈልጋለሁ፡፡ አስር ልጆች እወልዳለሁ፡፡ ስም እና ታሪክ ከሌላት ሴት፡፡ ስም እና ታሪክ አላት በተባለላት ሀገር ላይ ለአለም የህዝብ ቁጥር መጨመር እንደሁሉም ሰው የተቻለኝን አስተዋጽኦ አደርጋሁ። “የአለም ህዝብ ቁጥር ጨመረ፤ በመጨመሩ ላይ አስተዋጽኦ አታድርግ” ብለው የሚያስተምሩኝን የስነ ተዋልዶ ወሬኞችንም ምክር እጠቀማለሁ፡፡ ከሚስቴ ውጭ በኮንዶም እጠቀማለሁ፡፡ ከሚስቴ ጋር በኮንዶሚኒየም እኖራለሁ፡፡ የእኔ ብቻ የሆነ የተለየ ጥፋት የለም፡፡ ጥፋቱ የሁላችንም ነው፡፡ እኔ እነሱን ነኝ፡፡ ተራ ዜጋ፡፡ ተርታውን የማያዛንፍ፡፡ ከ “ከንዳ እስከ አሳርፍ” ሁሉም ወደ ተኮሱበት አቅጣጫ፣ ለሁሉም በተሰጠው ጠመንጃ ተኩሻለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ተመትቻለሁ፡፡ ማን እንደመታኝ አላውቅም፡፡ ማንን መትቼ እንደገደልኩም አይወቁብኝ፡፡
እናት (ሀገሬን) እና አባቴን የማከብረው በዙሪያዬ ያሉ እስካከበሩ ድረስ ነው፡፡ ሲተዉ እተዋለሁ፡፡ ሲጀምሩ እጀምራለሁ፡፡ ስሜን ከአባቴ እስከ አያቴ ድረስ ብዙሀኑን የሚመስለውን ለራሴ እሰይማለሁ። መንግስት ይቅርና ፈጣሪ ራሱ ከአካል (የፉርጐ) ሰንሰለቶች ውስጥ እኔን መለየት እንዲያቅተው። በስጋ ሳይሆን በነፍስ ከሌሎች ጋር አንድ መሆን አምሮኛል፡፡ እነሱ ከሚሞቱ እኔ ብሞት ይሻለኛል። ከእስር ቅጣቴ ለመገላገል ሳይሆን…እነሱ ከሞቱ እኔ ማንን እመስላለሁ? በማን ውስጥ እደበቃለሁ? ራሴን መከተል ይከብደኛል፡፡ ራሴ (ጭንቅላቴ) ለመሆኑ የቱ ጋ ነው ያለው? እንዲኖር የምፈልገው እነሱ (ብዙሃኖቹ) ትከሻ ላይ ነው፡፡ እኔ ተራ ዜጋ ነኝ። ምንም የማውቀው ጉዳይ የለም፡፡ እውቀትም ጉዳዬም አይደለም፡፡ በጥርጊያ መንገድ እንጂ ባልተረገጠ ጐዳና መጓዝ ያስፈራኛል፡፡ ባልተረገጠ ጐዳና ተጉዤ ምን እንደሚገጥመኝ እንዴት አቃለሁ? የሰው ልጅ ገጥሞት የማያቅ አሁን ካለሁበት እስር ቤት የበለጠ ስቃይ እና መከራ የያዘ ሌላ እስር ቤት ቢገጥመኝስ?...ደግሞም የበለጠ ስቃይ ያለው እስር ቤት አለ፡፡ ስሙንም ሰምቸዋለሁ፡፡
“ነፃነት” ይባላል፡፡ ከተራነት ያፈነገጠ ሰው… ብቻውን በራሱ ውስጥ የሚታጐርበት እስር ቤት ነው፡፡ ከሁሉም የሚሰቀጥጠኝ ግን፤ ባልተረገጠ ጐዳና ስጓዝ… ማንንም የማይመስለውን፣ የማይፈራውን፣ ፈጣሪን የሚወደውን፣ ልባሙን እኔን ማግኘቴ አይቀርም ብዬ ነው፡፡ ባልተረገጠ ጐዳና መጓዝ የምፈራው ለዚህ ነው፡፡ ራሴን ላለማግኘት ነው የምሸሸው፡፡ አሁን ካለሁበት ራስን ማጣት ከሚቻልበት እስር ቤት የጠነከረ ነው ያኛው፡፡ ደካማውን አድክሞ፣ ጠንካራውን አጠንክሮ ይገድላል፡፡ ለመድከም - ለመድከም ምን እዛ ድረስ ወሰደኝ?...እዚሁ ተራዎቹ መሀል ድካሜን ጥንካሬ አድርጌ መቆየት ስችል!
“ነፃነትን” እና “እኔነትን” አልችላቸውም፡፡ የምችለውን አውቀዋለሁ፡፡ የምችለው የምፈልገውን ነው፡፡ የምችለውን ያህል ነው የምፈልገው፡፡
የምፈልገውን ነው ከላይ ያሰብኩት፡፡ ያሰብኩት ተራ ዜጋ መሆን ነው፡፡

Published in ህብረተሰብ

የሰሜን ወሎ ዋና ከተማ ወደሆነችው የወልድያ ከተማ ነሐሴ አጋማሽ ላይ አቀናሁ፡፡ በየዓመቱ ቡሄ በመጣ ቁጥር የልጅነት ትውስታዬ የሆነው የዚያ አካባቢ የተለየ የቡሄ አጨፋፈርና የመስቀል አከባበር በሬዲዮ ወይም በፕሬስ ውጤቶች ላይ ቀርበው አይቼ አላውቅም፡፡ አሁን ከሌላ ከምጠብቅ ለምን ራሴ አላቀርበውም ብዬ የተነሳሁት፡፡ የወልድያ ከተማ ነዋሪ የሆኑትን አቶ አያሌው ገዳሙን እህሳ? አልኳቸው፤ እንዲህ አወጉኝ፡-
“ሆያ ሆዬ የቡሄ ሶለላ አሆ ሰለሌ አስገባኝ በረኛ” የሚባል አለ፡፡ ቡሄ ጨፋሪው እከሌ እከሌ ቤት እንሂድ ብለው ይሰባሰቡና ወደመረጡት ቤት ሲሄዱ
አስገባኝ በረኛ አሃሃ አሆሆ አስገባኝ በረኛ
በጊዜ እንድተኛ አሃሃ አሆሆ አስገባኝ በረኛ
እየተባለ ከበር ላይ ሆኖ ይጨፈራል፡፡ ከቤቱ በር እንደደረሱም
በሕብረት
አሆ ሰለሌ አሆ ሆዬ በል አሆ ሰለሌ አሆ ሆዬ በል
አሆ ሰለሌ አሆ ሆዬ በል አሆ ሰለሌ አሆ ሆዬ በል
አሆ ሰለሌ ጨረቃ ድመቂ አሆ ሰለሌ አሆ ሆዬ በል
አሆ ሰለሌ ኮከብ ተሰለቂ አሆ ሰለሌ አሆ ሆዬ በል
አሆ ሰለሌ ኧረ እማማ እንትና አሆ ሰለሌ አሆ ሆዬ በል
አሆ ሰለሌ የሴቶች አረቂ አሆ ሰለሌ አሆ ሆዬ በል
እያሉ ይጨፍራሉ፡፡ ሌላው ቀበል ያደርግና:- ዜማውን ወደ ሆያ ሆዬ ይቀይረዋል (ዜማውን እንዴት ልፃፈው?)
ሆያ ሆዬ ሆ
የኔማ ጌታ ሆ
የሰጠኝ ብር ሆ
ሁለመናዋ ሆ
የምታምር ሆ
እንዲህ ሲጨፍሩ ከቤት ውስጥ አንድ ሰው ወጥቶ የሚሰጠውን ይሰጣል
በሕብረት
እሆይ ናሃሃ እሆይ ናሃሃ
እንዳባባ እከሌ መስጠትን ማን አውቆ አሆይ እሆይ
አሆይ ናና አሆይ አሆይ ናና
ባላገር ይሞታል በድሪቶ ታንቆ አሆይ
አሆይ ናና አሆይ አሆይናና
አሆይ እንደቸርዮ አሆይ አሆይናና
አሆይ እንደሚዛኑ አሆይ አሆይናና
ሚዛኑ ሚዛኑ ሚዛኑ ዘለቀ አሆይ
አሆይ ናና አሆይ አሆይናና
እንደሰማይ ኮከብ እያብረቀረቀ አሆይ
አሆይ ናና አሆይ አሆይናና
ቸሩ ሆዬ አሆ
ቸሩ ሆዬ አሆ
እንዳንበሳ አሆ
ምድር ብሳ አሆ
እያሉ ወደቀጣዩ ይሄዳሉ፡፡ የሚሄዱበት ቤት ራቅ ያለ እንደሆን :-
ሽቦ ኧረ ዋርዳው ሽቦ ሃሃ ሃሃዋ
ሽቦ ኧረ ዋርዳው ሽቦ ሃሃ ሃሃዋ…
እያለ ከቦታው ሲደርስ
አስገባኝ በረኛ አሆሆ አሃሃ አስገባኝ በረኛ
በጊዜ እንድተኛ አሆሆ አሃሃ አስገባኝ በረኛ…
እያሉ ወደቤቱ ይጠ/oና
በሕብረት
የቡሄ ሰለላ የቡሄ የቡሄ ሰለላ የቡሄ
የቡሄ ሶለካ ከፈረስ አፍንጫ የቡሄ ሰለላ የቡሄ
የቡሄ ሶለካ ይውላል ትንኝ የቡሄ ሰለላ የቡሄ
የቡሄ ሶለካ ኧረ አባባ እከሌ የቡሄ ሰለላ የቡሄ
የቡሄ ሶለካ ጤና ይስጥልኝ የቡሄ ሰለላ የቡሄ
የቡሄ ሶለካ እንኳን ደህና መጡ የቡሄ ሰለላ የቡሄ
የቡሄ ሶለካ ከሄዱበት አገር የቡሄ ሰለላ የቡሄ
የቡሄ ሶለካ ጠላቶችህ ሁላ የቡሄ ሰለላ የቡሄ
የቡሄ ሶለካ ይቅር ብለው ነበር የቡሄ ሰለላ የቡሄ
እየተባለ ይጨፈራል፡፡
ወዲያው የሚሰጥ እየሰጠ፣ ሌላውም ለመስቀል ገንቦ ጠላ፣ ድፎ ዳቦ ወይም ሰላሣ… ሃያ እንጀራ እሰጣለሁ እያለ ቃል እየገባ ይሸኛቸዋል፡፡
ከ16 ኪዳነ ምሕረት ጀምሮ፤ እስከመስቀል ድረስ ይጨፈራል፡፡ ሆያ ሆዬ ሲል የሰነበተው ጐረምሳም፤ ህፃናትም ያገኘውን ሁሉ በየአለቃው ያዥነት ገንዘብ ያጠራቅምና መስቀል አንድ አራት ቀን ሲቀረው በግ ይገዛል፡፡
የመስቀል ዕለት፤ ወላጆች ትንሽ ትልቁ አዛውንቱ መስቀልን ለማክበር ለሊት ደመራ ተደምሮ ባደረበት ቦታ ልክ ከለሊቱ አስር ሰዓት፣ እያንዳንዱ ችቦውን አብርቶ በመያዝ ከቤቱ እንዲህ እያለ በመጀመር፡-

ዳብር ዳብር ዳብር
የጐመን ምንቸት ውጣ
የሥጋ ምንቸት ግባ…እያለ ይወጣል፡፡
የጤና ግዜ፣ የሰላም ጊዜ፣ የደስታ ጊዜ… የማግኘት ጊዜ ያድርግልን እያሉ… ለከርሞ በሰላም የምንደርስ ያድርገን፣ ዳብር ዳብር እያለ… በየቤቱ፣ በየሙሃቻው፣ ሊጥ በተቦካበት ድህነት ውጣ ሀብት ግባ፣ ጐመን ውጣ ሥጋ ግባ… እያለ መስቀል መለኮሻው ላይ ይሰባሰባል፡፡ ከዚያ ደመራውን እየዞረ
እዮሃ መስቀል ነሽ
ሳይሞት ያግኝሽ
እዮሃ እዮሃ
እየተባለ ሶስት ጊዜ ይዞርና ደመራው ይለኮሳል፡፡ አንዲት ከደመራው መሃል የተተከለች ረጅም እንጨት በመጨረሻ ላይ ስትወድቅ ያቺ እንጨት የወደቀችበትን አቅጣጫ ተመልክተው “ዘንድሮ በዚህ አካባቢ አዝመራ ይዟል” ይባላል፡፡ ይህ ከተባለ በኋላ፤ ቡሄ ሲጨፍሩ የነበሩ ወጣቶች በየቡድናቸው የገዟቸውን በጐች ያቀርባሉ፡፡
“አባቶቻችን እንግዲህ በሰጣችሁን ገንዘብ በግ ገዝተን አበርክተናል” ይላሉ፡፡ ሃያ በግ ቀርቦ እንደሆነ አምስቱን ይወስዱና፡- “የተቀረውን ለእናንተ መርቀናል፤ እናንተ አርዳችሁ ብሉ” ይሉና ቡሄ ለጨፈሩት ይሰጧቸዋል - ዕልልታው ይቀልጣል፡፡ ሽማግሌ ተነስቶ ይመረቃል፡፡
“ዓመት አውዳመት ያድርሳችሁ፡፡ (አብሮ ያድርሰን) ከርሞ ይኸን ጊዜ ደግሞ የሌለው አግኝቶ ያለውም ጨምሮ የምንሰጥ እግዚአብሔር ያድርገን” ተብሎ ይመረቃል፡፡ ከዚያ ቡሄ ጨፋሪዎቹ የተመረቀላቸውን በግ ይዘው ይሄዳሉ፡፡ ማለዳ፤ በጉ ሁላ ይታረድና ገንቦ ጠላ፣ አንድ ሙጌራ ሃምሳ እንጀራ ወይ ሰላሳ እንጀራ ለመስቀል ሊሰጥ ቃል ወደገቡት ሰዎች ቤት ገንቦ እየተያዘ ይዞርና፣ በጉ በታረደት ቤት በጋንና በበርሜል ይቀመጣል፡፡ ምግቡ ይሰናዳና ሁሉም ይበላል፤ ይጠጣል፡፡ ይደሰታል፡፡
በነጋታው ተማሪው ወደ ትምህርቱ፣ እረኛው ወደ ኩበቱ፣ ገበሬው ወደ እርሻው ይሄድና፤ ማታ ለመብላት እንደገና ይሰበሰባል፡፡ ይበላል፤ ይጠጣል ይጨፈራል፡፡ ከዚያም የተዘጋጀው ሲያልቅ… “ለከርሞ ያድርሰን” ተባብሎ፣ ተመራርቆ ይበተናል፡፡
የጤና፣ የሰላም፣ የደስታ ጊዜ ያድርግልን! ለከርሞ በሰላም ያድርሰን! ቸር እንሰንብት!

 

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 28 September 2013 13:35

በተጓዝክ ቁጥር ትሰፋለህ…

  • አባቶች የአክሱምን ሃውልት አቁመዋል፤ ልጆች ከሃውልቱ ስር የካርታ ቁማር ይጫወታሉ
  • አባቶች በቀረፁት ድንጋይ ዓለምን ያስደንቃሉ፤ ልጆች የጠጠር መንገድ መደልደል አቅቶአቸው መኪና አይገባም ይላሉ
  • ዝም ያለቺው አድዋ… ደማቋ ሽሬ… የተቆፋፈረችው አዲግራት…

        የዛላምበሳ - አሲምባ - አሊቴና ጉዞዬን ለማካፈል ከጥቂት ሳምንት በፊት በዚሁ ጋዜጣ የጀመርኩትን ወግ አልጨረስኩም፤ ወጌን ከዳር ለማድረስ፣ ለአፍታ ወደ ጎንደር የፋሲል ጉብኝት ጎራ ብዬ ወደ አክሱም እዘልቃለሁ።
የፋሲል ቤተመንግስትን ስጎበኝ የመጀመሪያዬ አይደለም። ነገር ግን ካሁን በፊት ያላስተዋልኩትን አስደናቂ ነገር በአስጎብኛችን አማካኝነት ተመለከትኩ። ከቤተመንግስቶቹ ድንቅ የሚያደርጋቸውና ድንጋዮቹ እርስ በርስ ተነባብረው እንዲህ እስከዛሬ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቆዩ የሚያስችላቸውን ጥንካሬ ለማግኘት የበቁበትን ድንጋይ ማጣበቂያ ያደረጉት ኖራን ነበር። ታዲያ ኖራው ለረጅም ዓመታት በማጣበቂያነቱ ፀንቶ እንደሚቆይ ለማረጋገጥ በዚያው በፋሲል ቅጥር ጊቢ ውስጥ አንድ መለስተኛ ክፍል ያለው ቤት በድንጋይ ተሰርቶ ለዓመታት ከታየ በኋላ አለመፍረሱ ተረጋግጦና ኖራም ለዘመናት ጠንካራ ማጣበቂያ መሆኑ ታምኖበት ነው ታላላቆቹ ቤተመንግስቶች ተራ-በተራ የተገነቡት። አስደናቂ ነው። በዚህ ዘመን እንኳን የአንድን ነገር ዘላቂነትና አዋጪነት ለማወቅ ሙከራ ሳይደረግ፣ ስንቱ ፖሊሲና ስትራቴጂ በላያችን ላይ ተሞከረብን? ከውሃ ማቆር ስትራቴጂ እስከ ትምህርት ፖሊሲ፤ ከንግድ ምዝገባ ህግ እስከ ብዙ ነው ዝርዝሩ፡፡
ያልተደሰትኩባቸው የአክሱም ወጣቶች
ለመጎብኘት እጅግ የጓጓንለት አክሱም ከተማ ደረስን። በእርግጥም ሰማይ ጠቀስ የሆኑ ድንጋዮችን እንዲህ ባይነት ባይነታቸው ደርድሮና በላያቸው ላይ ደግሞ የቅርፅ ጥበብን በማኖር የዓለምን ዓይን ለመሳብ የበቃንበትን ተዓምራዊ ጥበብ ለሰሩ አባቶቻችንና እናቶቻችን የሚኖረን ክብር እጅግ ከፍ ያለ የሚሆነው ድንገት ከሃውልቶቹ ጋር ዓይን ለዓይን ስንገጣጠም ነው። ያን ጊዜ ድንገት ዞር ስንል ውብ የአርክቴክቸር ጥበብ ያረፈባትን የአክስም ፂዮን ቤተክርስቲያን ከጎናችን እንመለከትና እዚህ ቦታ ስለመገኘታችን ምስጋናችንን ዝቅ በማለት እናቀርባለን። ነቢይ ባገሩ ይሉ ዘንድ እኛ እዚያ በመገኘታችን ደስታ የሚያደርገንን አሳጥቶን ስንቅበዘበዝ፣ የአክሱም ወጣቶች ግን በሃውልቶቹና በቤተክርስቲያንዋ መሃል በሚገኝ ሜዳ ላይ በካርታ ቁማር ይጫወታሉ። የእኛን መምጣት ነገሬም ያሉት አይመስልም። ብዙ ከመኖር ተላምደውት፣ ሃውልቱም ያው ድንጋይ ሆኖባቸዋል፤ ጎብኚም ሲጨርስ ወደ መጣበት ይመለሳል።
ከካርታ ተጫዋቾቹ መሃል አንዱ የደደቢት እግር ካስ ቡድንን ማሊያ የለበሰ ወጣት፣ ወደ እኛ መጣና የአካባቢው ወጣቶች ተደራጅተው የማስጎብኘቱን ስራ እያከናወኑ እንደሆነና ለእኛ ጉብኝት የተመደበው ሰው እርሱ እንደሆነ ነገረን። ለጉብኝታችን 250 ብር እንደሚያስከፍለንና ህጋዊ ደረሰኝ እንደሚያቀርብልን ገለፀ። ጉብኝቱ ተጀመረ። የአክሱም ሃውልቶችንና የታሪካዊትዋ አክሱም ፂዮን ቤተክርስቲያንን ካስጎበኘን በኋላ በግምት ከ5 ኪሎ ሜትር በማይበልጥ ርቀት ላይ የሚገኘውን የአፄ ካሌብን ቤተመንግስት ሊያስጎበኘን በመኪናችን ጉዞ ጀመርን። ከመድረሳችን በፊት ግን ቆምን፤ መንገዱ አልተስተካከለም። መኪና አያስኬድም። ከመኪና ውረዱ ተብለን በእግር ጉዞ ጀመርን። ግራና ቀኝ የድንጋይ ክምር እያለ፣ እነዚህ ወጣቶች ይችን መንገድ መስራት አቅቶአቸው ነው? አባቶቻቸው ያንን የአለም ድንቅ ቅርስ ሰርተው ሲያበቁ፣ እነዚህ ልጆች በግማሽ ቀን ሥራ የካሌብን መሄጃ መንገድ ማስተካከል ተስኖአቸው በካርታ ጨዋታ ጊዜያቸውን ያጠፋሉ።
አስደናቂው የአክሱም ሃውልቶችና አካባቢውን ጎብኝተን ለምሳ ወደ ከተማ ሄድን። ምሳ ተበልቶ ካለቀ በኋላ አስጎብኛችን የጎበኘንበትን 250 ብር እንድንከፍል ጠየቀን። የቡድኑ ገንዘብ ያዥ እኔው ነበርኩና ደረሰኝ ስጠኝና ብርህን ልስጥህ ስለው ተቅለሰለሰ። ለካንስ ያችኑ የማህበር ገቢ ወደ ኪሱ ለማድረግ ማሰቡ ነበር። ደግሞ ሙስና በየት በኩል ተከትላን መጣች? የሆነው ሆኖ በአክሱምና አካባቢዋ በወላጆቻችን ጥንታዊ ስልጣኔ በእጅጉ ተደንቀን፣ በእኛው ዘመናዊ ኋላቀርነት ደግሞ ተሸማቀን ጉዟችንን ወደ አድዋ አደረግን።
ዝም ያለቺዋ አድዋ
እምዬ ምኒልክ ዛሬም ያንቱ ፈረስ
የቸኮለ ይመስላል አድዋ ለመድረስ።
ሐውልትዎን ባዩት ምኒልክ ቢነሱ
ልጓሙ አልችል ብሎት ሊሄድ ሲል ፈረሱ!
(ገጣሚ አርቲስት ንጉሡ ረታ፤ ከአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ 1987 ዓ.ም በሞት የተለየን - ነፍስ ይማር ብያለሁ)
የአፍሪካ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ታሪክ የሚወሳባት አድዋ!... የምኒልክና የጣይቱ አድዋ!... ዛሬ ዝም ብላለች። ውብ የተራራ ሰንሰለቶችዋ በውስጣቸው አቅፈውና ቀብረው የያዙትን የጀግንነት ታሪክ በወጉ የሚያከብርላቸው አጥተው ያኮረፉ ይመስል ተኮፍሰው ይታያሉ። አድዋ ስምና ዝናዋ እንደ ተራሮችዋ ግዝፈት ከዳር ዳር ያስተጋባሉ። ከተማዋ ግን ዝም ጭጭ ያለች ሆነችብኝ። ቡና የሚጠጣበት ስፍራ ፍለጋ ከተማዋን አካልለናል። ይህቺ ከተማ የሟች ጠቅላይ ሚኒስትራችንና የጉምቱ ጉምቱ ባለስልጣኖቻችን የትውልድ ስፍራ አይደለችም እንዴ? በሚልም ሃሳብ ተነሳ። “እና ምን ይጠበስ!” ነው የአድዋ መልስ። ወይ ነዶ ይህ ታሪካዊ ቦታ ደቡብ አፍሪካ ወይንም ግብፅ ወይንም ደግሞ ሊቢያ ውስጥ ቢሆን ኖሮ፣ አድዋን ለመርገጥ ዛሬ በሺዎች የሚቆጠር ዶላር በተጠየቀ ነበር። ያም ሆኖ አድዋ አንቀላፍታለች።
ከዚህ ቀደም አንድ ግለሰብ በአድዋ ተራሮች ላይ ከተማዋን ለማስተዋወቅ አንድ የሆነ የጀመረው ፕሮጀክት እንደነበረ ከመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሰምቼ ነበር። እንዲያውም በትልቁ በብረት የተሰራ አድዋ የሚል ፅሁፍ ያለበት ማስታወቂያም ሳልመለከት አልቀረሁም። ዛሬ ግን ያ…ሁሉ በአድዋ የለም። እንግዲህ የማስታወቂያ ባለሙያው መሃመድ ካሳ፤ ባለፈው ዓመት የአድዋን በዓል በብሄራዊ ቴአትር ከህዝብ ጋር ሲያከብር ቃል በገባው መሰረት፣ በ2006 ዓ.ም የአድዋ በዓልን በዚያው በአድዋ ከተማ ውስጥ በማክበር ከተማዋን ከዝምታ እንደሚገላግላት፤ ከአንቀላፋችበትም እንደሚቀሰቅሳት ተስፋ አደርጋለሁ።
ደማቋ ሽሬ
ሽሬ ዕምደስላሴ ለአንድ ቀንና ሌሊት ጥሩ ጊዜ ካሳለፍንባቸውና እጅግ ከማረኩኝ ከተሞች ውስጥ አንዷ ሆናለች። በትግራይ ክልልም ትልቅ ከሚባሉት ከተሞች መሃል በስም እንደምትጠቀስም ሰምቻለሁ። ምሽት ላይ በሽሬ አንድ የምሽት ቤት በትግርኛና በኤርትራ እንደዚሁም ቆየት ባሉ የአማርኛ ሙዚቃዎች የጨፈርነው ጭፈራ እስካሁን በዓይኔ ላይ አለ። ሰሞኑን በቅርቡ በወጣ “ጊዜያችን” የተሰኘ መፅሄት ውስጥ በዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም የቀረበ አንድ ፅሁፍ አንብቤያለሁ። ርዕሱ “በኤርትራ ሙዚቃ ስሜቱ የማይነካ ኢትዮጵያዊ፤ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ስሜቱ የማይረካ ኤርትራዊ ይገኛል?” ይላል። ማህመድ ሰልማን “ፒያሳ ማህሙድ ጋር ጠብቂኝ” በሚል ርዕስ ባሳተመው መፅሃፍ ላይም አንዲት በዚያው አካባቢ የምትገኝ ከተማን ሲገልፃት፣ በኤርትራ ሙዚቃ የምትደንስ ከተማ ብሏል። ፀጉራቸውን ፍሪዝ ያደረጉ፤ ቁመታቸው ዘለግ ያለ፤ አብዛኞቹ ጉርድ ቦዲ ቲሸርት ያደረጉ የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች በፍቅር በያንዳንዱ ሙዚቃ ሳይታክቱ ሲጨፍሩ ተመለከትኩ።
ላፍታ መንፈሴ ወደ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሄደና አንድ ነገር አስታወስኩ። ይህቺ የትግራይ ምድር እኮ ዛሬ እንዲህ በሙዚቃ ደምቃ የምናያት ለዘመናት ወጣቶችዋን በጦርነት ያጣች፤ ርሃብ ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ያጠቃት ክልል ናት። ህዝቦችዋ ስደትን ጠንቅቀው ያውቁታል። እናም ሁሉንም የሚረሱትና ተንፈስ የሚሉት በሙዚቃ ብቻ ነው። ገና ሙዚቃው ዝ..ዝ..ም ብሎ ሲጀምር ሁሉም ፈገግ ብለው በመነሳት ክባቸውን ሰርተው
አንቺ የትግራይ ምድር
የከበሮሽ ድምፅ ከሩቅ ይሰማ… የጦር መሳሪያን ድምፅ አሸንፎ
የስክስታሽ ውበት ይታይ…ደም ሳይደበቀው አኩርፎ
ልጆችሽ ልክ እንደዛሬው …ለጭፈራ ክብ እየሰሩ
የሰላም አየር በመማግ …ሳይሳቀቁ ይኑሩ!
ሁልጊዜም ሳቅ ይሁን ሁሌም ይሁን ፍቅር
እንዲህ ነው የሚያምርብሽ አንቺ የትግራይ ምድር!
የአዲግራት ጋንታ
አዲግራትም በክልሉ ስማቸው ከሚጠቀስ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ አንዷ ናት። እኛ አዲግራትን ስናቋርጥ ከተማዋ ልክ እንደ አዲስ አበባ እዚህና እዚያ ተቆፋፍራ ልማቱን እያሳለጠችው አገኘናት። ድንገት በአንድ መንደር ውስጥ ውስጥ ከ25 በላይ የሆኑ ህፃናት በአንዲት አሮጌ ኳስ ባንድ ላይ ሆነው ሲጫወቱ ስለተመለከትናቸው ለእነዚህ ልጆች ቢያንስ የአንዲት አዲስ ኳስ ስጦታ ስለምን ሳናበረክትላቸው እናልፋለን በማለት በቀና ሃሳብ ተነሳስተን ወደ ልጆቹ አመራን። የቋንቋ ችግር አለብንና አስተርጓሚ ተጠርቶ ስለስጦታው ሃሳብ ተነገራቸው። በዚህ ጊዜ እንዲያ በፍቅር ሲጫወቱ የነበሩ ልጆች ምክኒያቱ ባልገባን ሁኔታ እርስ በርስ ዱላ ቀር ጭቅጭቅ ውስጥ ገቡ። አስተርጓሚያችንን ምን እንደተፈጠረ ጠየቅነው። ለካንስ እነዚህ ልጆች ምንም እንኳን በዚያች አንድ ኳስ በህብረት ቢጫወቱም የተለያየ ሰፈር ነዋሪዎች ናቸው። ስለዚህ ስጦታው እዚህ ሰፈር ከተገዛ ባለቤትነቱ የዚህ ሰፈር ህፃናት ብቻ እንደሚሆን ተተረጎመልን። እና ምን ይሻላል ብለን ብንጠይቅ የ 4 ጋንታ ልጆች ስለሆንን በየጋንታችን እንሰለፍና ስጦታውን አከፋፍሉን አሉን። ወቸው ጉድ! እጅግ ተገረምንና እስቲ በየጋንታችሁ ተሰለፉ አልናቸው።
እውነትም አራት ከፍ ከፍ ያሉ ህፃናት ከመካከል ወጥተው የየራሳቸውን ጋንታ በ4 በመክፈል አሰለፉ። ሁኔታውን ስናይ አስገረሙንና ስጦታውን ጨመር አድርገን ልናከፋፍላቸው ስንል ሌላ ጉርምርምታ ተነሳብን። ደግሞ ምን ተፈጠረ? ብለን ወደ አስተርጓሚያችን አፈጠጥን። እንደ ህፃናቱ ገለፃ ብዙ የጋንታ አባል ያለው በዛ ያለውን ስጦታ፣ አነስተኛ አባል ያለው ጋንታ ደግሞ አነስ ያለ ስጦታ ሊደርሰው እንደሚገባና ክፍፍሉም ይህንኑ መሰረት ያደረገ መሆን እንደሚጠበቅበት ተረዳን። በተባለው ፍትሃዊ ጥያቄ (ብዙሃን ያሸንፋሉ የሚለውን) እኛም አምነንበት እንደየጋንታቸው ስፋት ስጦታውን አከፋፍለን በገንዘብ ኃይል ፍቅራቸውን ያደፈረስንባቸውን የአዲግራት ህፃናት ተሰናብተን ጉዞአችንን ቀጠልን።
የህፃናቱ የፍትህ ጥያቄ ተገቢነት እንደነበረው መኪናችን ውስጥ በድጋሚ ተስማማን። ለብዙሃን ሰፊ ዕድል የማይሰጠው ፖለቲካችን ብቻ ነው እያልን በመቀለድ ከተማዋን በሚያውቅ አንድ ጓደኛችን አማካኝነት ወደ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ፅ/ቤት ዘንድ አመራን። ይህ ድርጅት ከኦርቶዶክስ፣ ከሙስሊምና ከካቶሊክ ዕምነቶች በተወጣጡ የሃይማኖት መሪዎች የተመሰረተ ሲሆን መሰረታዊ ዓላማውም ነዋሪውን ስለ ሰላም፤ ፍቅር፤ አንድነትና ተቻችሎ ስለመኖር ወዘተ ማስተማርና ማሳወቅ ነው። ድርጅቱ ዕምነት ሳይለይ ለተቸገሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ዕርዳታ የሚያደርግ ሲሆን በተለይ በሰላም ዙሪያ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ከሃላፊው እንደሰማነው አስደንቆናል። ዛሬ የሰላምና የመቻቻል እንደዚሁም አብሮ የመኖር ምሳሌ ናት የምንላት ደሴ ከተማ እንዲህ በሃይማኖት ልዩነት ስትናጥ፣ በአዲግራት ከተማ እንዲህ መሰሉ ጠንካራ ድርጅት መኖሩ ሳይቃጠል በቅጠል የሚያሰኝ ነው ብለን፣ አዲግራትን ተሰናበትንና ጉዞአችንን በመቀጠል በዛላምበሳ በኩል አድርገን አዲ ኢሮብ ገባን።
በባለፈው ፅሁፌ ስለ ኢሮብ ማህበረሰብ ብዙ ስላልኩ ዛሬ ደግሜ አልመለስበትም። በማሳረጊያዬ ደግሜ የምለው ግን ጉዞ መልካም ነው። በተጓዝንም ቁጥር እንዲህ ልምድና ተመክሮአችን እየሰፋ ይሄዳል። አገሪቱን ዞረን ሳናያት ስለ ዕድገትዋ ወይም ስለ ኋላ-ቀርነትዋ መነጋገር ይከብዳል። በአራቱም አቅጣጫዎች ብንሄድ ኢትዮጵያችን ሰፊ፣ ህዝቦችዋም ልዩ መሆናቸውን በእርግጥም እንረዳለንና ሰፊ አስተሳሰብን ለማዳበር የጉዞ ልምዳችን ይዳብር ብዬ ብሰናበትስ?...
ከመሰናበታችን በፊት…
ሰሞኑን ሞባይሌ አቃጨለና የአሜሪካ ኮድ በሆነ የስልክ ቁጥር አንድ ሰው እንደደወለልኝ ነገረኝ። የስራ ፀባዬ ሆኖ አልፎ-አልፎ ከውጪ አገራት ስልክ ስለምቀበል ማን ይሆን በማለት ስልኬን በማንሳት አቤት አልኩኝ። ፈላጊዬ ከወዲያኛው ማዶ ሆኖ “አቶ ዳዊት ንጉሡ ረታ?” አለኝ። “አቤት” አልኩኝ ቆፍጠን ብዬ። “ካህሣይ አብርሃ” እባላለሁ። የአሲምባ ፍቅር መፅሃፍ ደራሲ። የአሲምባው አማኑኤል ሲልም አከለልኝ። ባለፈው 15 ቀን ፅሁፌ የአሲንባ ፍቅር የሚለው መፅሃፉን በአስረጂነት የጠቀስኩ ስለነበረ ይህንኑ ፅሁፌን ከመታተሙ በፊት እንዲያነበውና አስተያየቱን እንዲልክልኝ አስቀድሜ መፅሃፉ ላይ ባገኘሁት የኢሜል አድራሻ ልኬለት ነበር። ሆኖም ፅሁፉ በአማርኛ ስለነበረና በእርሱ ኮምፒውተር ላይ አልከፍትለት ስላለ ፅሁፉን ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ አንብቦት እንደደወለልኝ ነገረኝ። እጅግ በጣምም ተደሰትኩ። አቶ ካህሳይ የእኔና የጓደኞቼን የጉዞ ትዝታ ሲያነብ የራሱን የወጣትነት ጊዜ እንዳስታወሰና በድጋሚ በፅሁፉ አማካኝነት የዚያ አካባቢ ሁናቴ በዓይነ ህሊናው እንደተመላለሰበት ገለፀልኝ። በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣም ተገኛኝተን ይበልጡኑ የወጣትነት የአሲንባ ታሪኩን ሊተርክልኝ ቃል-ተገባብተን፣ እስከዚያው ዘመን ባመጣው ኢሜል ግንኙነታችንን እንድናጠናክር ተስማምተን ተለያየን። አቶ ካህሳይ አብርሃ እጅግ ትህትና ያለውና ተግባቢ፣ ለሰው ልጅም ልዩ ክብር ያለው ሰው መሆኑን ከነበረን የስልክ ጨዋታ ለመገመት ችያለሁ። በተጓዝክ ቁጥር ትሰፋለህ ማለት ይሄ አይደለ? መልካም ቅዳሴ!

Published in ህብረተሰብ

     ባለፉት ጥቂት ዓመታት ስለ ሰንደቅ ዓላማና የባንዲራ ቀን፤ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፤ ስለ ብሔር ብሔረሰቦች ትግል፣ መብትና እኩልነት፤ ስለልማት ሥራዎች፤ ስለተለያዩ የበዓል ቀናት … ወዘተ በርካታ ህብረ ዝማሬዎች ተዘጋጅተዋል፡፡
በህብረት የሚቀርቡ ዝማሬዎች ሀዘንን፣ ደስታን፣ ቁጭትን፣ ንዴትን፣ እርካታን፣ ተስፋን … በመግለጽ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ዓመታት ያስቆጠረ ታሪክ እንዳላቸው በ1997 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) የታተመው “Songs of the Ethiopian Revolution” የተሰኘው መጽሐፍ ይጠቁማል፡፡
በየትኛውም የዓለም አገራት ለተካሄዱ የፖለቲካ፣ የነፃነት፣ የመብትና የልማት ትግሎች መፋጠን ሙዚቃ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው የሚለው መጽሐፉ፤ አብነቶችን ይጠቅሳል፡፡ ጥቁር አሜሪካዊያን ለነፃነታቸው ሲታገሉ፣ አፍሪካዊያን ቅኝ ግዛትን ሲቃወሙ፣ ደቡብ አፍሪካዊያን የአፓርታይድ አገዛዝን ሲያወግዙ፣ ወዘተ… ሙዚቃ ትግሎቹን በማገዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ያብራራል፡፡
አታጋይ፣ አነቃቂና አነሳሽ ሕብረ ዝማሬዎች የሶሻሊስት ሥርዓተ ማህበርን በመገንባትና በማስፋፋት ረገድ በሩሲያ፣ በኩባና እንደ ቺሊ ባሉ የላቲን አሜሪካ አገራት ያስገኙት ውጤት ከፍተኛ እንደነበር የሚገልፀው መጽሐፉ፤ የትግል ህብረ ዝማሬዎች ያስገኙት ጠቀሜታ በደንብ የተጠና ባይሆንም በአገራችን ኢትዮጵያም የ1966 ዓ.ም አብዮት እንዲፈነዳ ትልቅ አስተዋጽኦ ካደረጉት ነገሮች አንዱ ተማሪዎች በየአደባባዩ በህብረት ያዜሟቸው መዝሙሮች ናቸው ይላል፡፡
አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ ለኢትዮጵያ ትቅደም ፖሊሲ፤ የንጉሡን ሥርዓት ለማውገዝ፤ 60ሺህ መምህራንና ተማሪዎች ለተሳተፉበት የዕድገት በሕብረት ዘመቻ፤ ለገጠርና ለከተማ መሬት፣ አዋጅ፣ ኤርትራን ለማስገንጠል የሚታገሉትን ለመቃወም፤ የዚያድባሬን ወረራ ለማውገዝ … እና ለመሳሰሉ ጉዳዮች ሕዝቡን ለማነሳሳት በርካታ ሕብረ ዝማሬዎች ተዘጋጅተው እንደነበርም ያመለክታል፡፡
በ118 ገፆች የተሰናዳው መጽሐፉ፤ በ1972 ዓ.ም ነበር ለአንባቢያን የቀረበው፡፡ በመጽሐፉ የተሰባሰቡት የመዝሙርና ዘፈን ግጥሞች፤ በሰባት ምዕራፎች ተከፋፍለው የቀረቡ ሲሆን የአብዮቱን ዘመን ትኩስ ስሜት፣ የዕድገት በሕብረት ዘመቻን፣ የውርስ አዋጆቹን፣ የፀረ-ኢምፔሪያሊዝም ስሜቶችን የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡
ከአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰቡ አታጋይ መዝሙርና የዘፈን ግጥሞችን ብቻ ሳይሆን ግጥሞቹ የተገኙባቸዉ ብሔረሰቦች መገኛ የት እንደሆነና በተለያዩ ዘመናት በሕዝቦቹ ላይ ስለደረሱ የበደልና የጭቆና ታሪኮች በግርጌ ማስታወሻዎች ለመጠቆም ተሞክሯል፡፡
አማርኛን ጨምሮ በአፋርኛ፣ በጉራጊኛ፣ በትግሪኛ፣ በኦሮሚኛ፣ በሶማሊኛ፣ በወላይትኛና በጋምቤላ ቋንቋዎች የቀረቡ አታጋይና አነቃቂ የመዝሙርና ዘፈን ግጥሞች ፀሐፊያንና የሙዚቃው ተጫዋቾችም በመጽሐፉ ተገልፀዋል፡፡ መርዓዊ ስጦት፣ ታምራት አበበ፣ አህመድ መሐመድ አልጁሐሪ፣ አርጋው በዳሶ፣ አብደላ መሐመድ፣ መሐሪ አብርሃ፣ አብዱልቃድር ሐጂ፣ ሲሳይ ተሾመና አያልነህ ሙላቱ ይገኙበታል፡፡
በግጥሞቹ ለማስተላለፍ የተፈለገውን መልዕክት ግልጽ ለማድረግም፤ ከግጥሞቹ ስንኝ ወይም ቃላት በመውሰድ በግርጌ ማስታወሻ ለማብራራት የተሞከረ ሲሆን “ብሔራዊ ስሜት” ለሚለው ግጥም በእንግሊዝኛ በቀረበው ትርጉም ስር፤ ስለ አድዋ ጦርነት፣ አፄ ዮሐንስ በመተማ ከሱዳኖች ጋር ስላደረጉት ጦርነት፤ አፄ ቴዎድሮስ በእንግሊዞች ባለመማረክ ለኢትዮጵያዊያን ስላወረሱት ሌጋሲ፤ ስለ አቡነ ጴጥሮስ ታሪክና ገድል፤ ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይና ግርማሜ ንዋይ ስለሞከሩት መፈንቅለ መንግሥት፤ የጥላሁን ግዛው ማንነት፣ አሟሟትና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች “ፋኖ ተሰማራ” በሚል ያዜሙት ስለነበረው ህብረ ዝማሬ በግርጌ ማስታወሻ ማብራሪያዎች ቀርበዋል፡፡
“Songs of the Ethiopian Revolution” መጽሐፍ በመግቢያው ላይ እንዳመለከተው፤ አታጋይ፣ አነቃቂና አነሳሽ ህብረ ዝማሬዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ ሰፊ ታሪክ እንዳላቸው ሁሉ በአገራችን የተመዘገበውም ታሪክ በዓመታት የሚቆጠር ነው፡፡ ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ፤ ከትግል ዘመን ጀምሮ በበረሀ ይዜሙ የነበሩ ህብረ ዝማሬዎችና በኋላም የተፈጠሩ አዳዲስ ሥራዎች ባለፉት 20 ዓመታት መድረኩን ተቆጣጥረው ዘልቀዋል፡፡
የደርግ ዘመን አታጋይ፣ አነቃቂና አነሳሽ የዘፈንና የመዝሙር ግጥሞች በዶ/ር ዓለም እሸቴ አዘጋጅነት ታትሞ እንደቀረበው ሁሉ፣ በኢሕአዴግ ዘመንም “ሶረኔ” የተሰኘ ልዩ ልዩ የትግል ግጥሞች እና ደብዳቤዎችን ያካተተ መጽሐፍ በ1998 ዓ.ም ወጥቷል፡፡ “ሶረኔ” ሁለተኛ ዕትም መጽሐፍ መግቢያ ላይ እንዲህ የሚል ሀሳብ ሰፍሯል:-
“በመድብሉ የተካተቱት ደብዳቤዎችና ግጥሞች በትጥቅ ትግሉ ጊዜ የነበሩ ታጋዮች የፀሐይ ሃሩር እና የሌት ቁር እየተፈራረቀባቸው አረፍ ባሉበት ቦታ ሁሉ ባገኙት አጋጣሚ የፃፏቸው ናቸው፡፡ በተጨማሪም የኢህአዴን/ብአዴን አባል ያልሆኑ በከተማና በገጠር በኢህአፓ/አህአሰ አባልነት ይታገሉ የነበሩ ሌሎች ሰዎች የፃፏቸውም ግጥሞች ተካተዋል፡፡ አንዳንዶቹም ከደርግ ውድቀት ማግስት የተፃፉ ይገኙበታል፡፡ ያኔ እነዚህ ግጥሞችና ደብዳቤዎች ፅናትንና ተስፋን የመገቧቸው እውነተኛ ጓደኞቻቸው ነበሩ፡፡ ለእኛ የክብር ሰነዶቻችን፣ አደራዎቻችን ናቸው”፡፡
ከጣሊያን ወረራ በፊት በ “ያገር ፍቅር ማህበር ፕሬስ ክፍል” ተዘጋጅተው ይቀርቡ ከነበሩ አታጋይ፣ አነቃቂና አሞጋሽ ህብረ ዜማዎችና ግጥሞች መካከል ጥቂቶቹም በየዘመናቱ እንደ ወቅቱ ሁኔታ እየተዘጋጁ ለሕዝብ ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡
ጣሊያን ተባርሮ ነፃነት በተመለሰ ማግስት “የአዲስ ዘመን መዝሙር ለነፃነት ክብር” በሚል ርዕስ በ1935 ዓ.ም በመጽሐፍ ተዘጋጅቶ የቀረበው የ35 ገጣሚያን ሥራም የዚሁ አካል ነበር፡፡ በደርግና በኢሕአዴግ የአስተዳደር ዘመናት በስፋት ለቀረቡት ህብረ ዝማሬዎች አርአያ የሆኑትም የቀድሞዎቹ እንደሆኑ ይነገራል፡፡
በኢሕአዴግ ዘመን ለህብረ ዝማሬ አቅራቢዎች ዕውቅናና ሽልማት እንደተሰጠው ሁሉ በቀደመው ዘመንም ተመሳሳይ ተግባራት ተፈጽመዋል፡፡ ለማታገል፣ ለማነቃቃትና ለማሞገስ የቀረቡትና እየቀረቡ ያሉት ህብረ ዝማሬዎች ለፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ቀላል እንዳልሆነ የዘርፉ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

 

Published in ጥበብ
Saturday, 28 September 2013 13:30

ከ1983 የመንግስት ለውጥ በኋላ

የምስራቅ ጎጃም ገበሬዎች የገጠሟቸው ፖለቲካዊ ግጥሞች

የአፍሪቃ እና የኢትዮጵያ ጥናቶች ተቋም
ሐምቡርግ ዩኒቨርስቲ፣ ጀርመን
ጭማቄ ጽሑፍ (Abstract)
ይህ የጥናት ወረቀት በኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ ወዲህ የምስራቅ ጎጃም ገበሬዎች የገጠማቸውን፣ ያዜሟቸውንና ያንጎራጎሯቸውን ፖለቲካዊ ግጥሞች ይመለከታል፡፡ የግጥሞቹ ዋነኛ ጭብጥ በወቅታዊ የገጠር አስተዳደርና በገበሬዎች ማህበራዊ ሕይወት ላይ የሚያተኩር ሲሆን በመንግስት ባለስልጣናት፣ በአገር አንድነት ጥያቄና በተለይም ደግሞ በ1989 ዓ.ም በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተካሄደውን የገጠር መሬት ሽግሽግ ፖሊሲ አፈፃፀምና ሽግሽጉ ያስከተለውን ተፅዕኖ ይቃኛል፡፡ በተጨማሪም ባንድ በኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በገጠሩ ማህበረሰብ ዘንድ እየተባባሰ የመጣውን መንግስትን የመጠራጠር፣ የእርስበርስ ጥላቻና ተቃውሞ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የምግብ እጥረት፣ የምርት ማሽቆልቆል፣ ድህነት፣ ስደትና በሰላም አብሮ የመኖር ተስፋ መጨለም ያሳሰባቸው የጎጃም ገበሬዎች ብቸኛ ሀብታቸው በሆነው ዘይቤያዊና ቅኔ ለበስ አማርኛ ቃልግጥም (Amharic oral poetry) ስሜትን የሚኮረኩሩና ልብን የሚነኩ መልዕክቶች እንደሚሰነዝሩ በምሳሌ በተደገፉ ግጥሞች ትንታኔ ያቀርባል፡፡ የገበሬዎቹ ስነልቦናዊ አስተሳሰብ፣ ባህላዊ ዕውቀትና ስለ አካባቢ ያላቸው ጥልቅ ግንዛቤ፣ ስለ ባህላዊ ዳኝነትና አስተዳደር፣ ስለ ልማትና መሬት አያያዝ ወዘተ የሚያቀርቧቸው ሐሳቦች የሚገልፁበት አንዱ መንገድ ለዘመናት ባካበቱት የስነቃል (oral literature) ቅርስ አማካኝነት በመሆኑ፣ በማህበራዊ ሳይንስና በገጠር ልማት ተመራማሪዎች፣ በስነትምህርት፣ በስነሰብእና፣በስነቃል ምሁራን እንዲሁም በመንግስት ፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት በጥንቃቄ መሰብሰብና በጥልቀት መጠናት እንዳለበት ይህ የጥናት ወረቀት ያመለክታል፡፡
እንደ ጋዜጣ፣ መፅሄት፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥን የመሳሰሉትን መገናኛ ብዙን የመጠቀምና ሐሳቡን በፅሁፍ የመግለፅ ዕድል የማያገኘው የገጠሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ሲደሰትም ሆነ ሲከፋ ስሜቱን የሚገልፀው፣ በደል ሲደርስበት ብሶቱንና ቁጭቱን የሚወጣው በዘፈን፣ በቀረርቶ፣ በፉከራ፣ በእንጉርጉሮ፣ በለቅሶ ዜማና በመሳሰሉት ቃላዊ ቅርሶቹ አማካኝነት ነው፡፡ በአብዛኛው የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዘንድ እንደሚስተዋለው ገበሬዎች ቃልግጥምን፣ ዘፈን እንጉርጉሮን፣ ቀረርቶን ፉከራን ወዘተ.በዕለት ተዕለት ህይወታቸው በለዛና በዘይቤ እየቀመሩ ይጠቀሙበታል፡፡ ድንቅ በሆነ የቋንቋ ቅመራ ችሎታቸውም ግጥምን ለጀግና ሙገሳ፣ ለፈሪ ወቀሳ፣ ለኃዘን እንጉርጉሮ፣ ለተበዳይ እሮሮ፣ ለፍቅር መግለጫ፣ ለሀሜት ማሽሟጠጫ፣ ለችሎት ምልልስ፣ ለአቤቱታ ክስ ወዘተ. ለዘመናት ሲገለገሉበት ኖረዋል፡፡ አሁንም ወደፊትም ይገለገሉበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተለይ እንደኛ ባለ በኢኮኖሚ ታዳጊ አገር የገበሬው ህይወት፣ የጤናው ሁኔታ፣ አለባበሱ፣ አኗኗሩ ወዘተ--- እጅግ አሳዛኝና እጅ ወደ አፍ በሆነበት ድህነት፣ ብሶት፣ ፍትህ ማጣት፣ መበደል፣ ቁጭት፣ ወዘተ…የመሳሰሉት ስሜቶችና ችግሮች የሚገለጹበት አንዱ መንገድ በቃል ግጥም ነው፡፡ ከረጅሙ ታሪካችን እንደምንረዳው በተከታታይ ሥልጣን ላይ የወጡ መሪዎች (መንግሥታት) ገበሬውን በግብር፣ በመዋጮ፣ በዘመቻና በልዩ ልዩ የጉልበት ሥራዎች ከማዋከብ በስተቀር የተሻለ ሕይወት እንዲመራ አላስቻሉትም፡፡ ሌላው ቀርቶ በዚያው ኋላቀር በሆነው የእርሻ መሣሪያ እንኳ መሬቱን አርሶ፣ ልጆቹንና በርካታ ቤተሰቡን እንዳይመግብ በየጊዜው የሚወጡት የመሬት ይዞታ ፖሊሲዎችና አዋጆች እንዲሁም የመንግስት ሹማምንት ያደረሱበትንና እያደረሱበት ያሉትን ማኅበራዊ፣ ሰብአዊ፣ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ በደሎች ሁሉንም መዘርዘር ያስቸግራል፡፡ ለምሳሌ እስቲ በዓጼው ዘመነ መንግስት፣ ምስኪኑ ገበሬ ለደረሰበት ሰብአዊ በደል ብሶቱንና እሮሮውን በእንጉርጉሮ እንዴት እንደገለፀው ከሚከተሉት ግጥሞች እንመልከት፡፡
በሬዬን አረደው፣ ከብቴንም ነዳው፣ ምሽቴንም ተኛት
ጐጆዬን አቃጥሎ አስተኛኝ መሬት
ሲጨንቀኝ ሲጠበኝ ዘመድ አረግሁት፡፡
ታገር እኖር ብዬ፣ ልጅ አሳድግ ብዬ
ለጭቃው ዳርሁለት ምሽቴን እቴ ብዬ፡፡
“ምሽቴን ማን ተኝቷት?”
“በሬዬን ማን አርሶት?” አይሉም፣ አይሉም
ቀን የከፋ ለታ ይደረጋል ሁሉም፡፡
ግጥሞቹ ለማን እንደተገጠሙ መገመት አያስቸግርም፡፡ በዘመኑ ጭቃ ሹም፣ ነጭ ለባሽ፣ የጐበዝ አለቃ፣ ምስለኔ፣ አጥቢያ ዳኛ እየተባሉ ይሾሙ ለነበሩትና በገበሬው ወይም በጢሰኛው ላይ ላደረሱት በደልና ለሠሩት ግፍ በግጥም የተሰጠ ምላሽ ነበር፡፡ በቅርቡ በደርግ አገዛዝ ዘመን በተግባር የታዩትና በኃይል ለመከናወን የተሞከሩት የግብርና ልማት ፕሮጀክቶች፣ የመንደር ምሥረታና የሰፈራ ፕሮግራሞች፣ የገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማኅበራት እንቅስቃሴዎች፣ የመሬት ክፍፍል አስተዳደራዊ ዕቅዶችና አፈጻጸሞች፣ ወዘተ ለገጠሩ ኅብረተሰብ ያተረፉለት ጐልቶ የሚታይ ፋይዳ የለም፡፡
የጐጃምን ገበሬዎች ሥነ ባሕርይና አስተሳሰብ ለመረዳት፣ ስለ መሬት ወይም ርስት፣ ስለ እርሻ በሬና የጦር መሣሪያ አስፈላጊነትና እንዲሁም ስለ ሚስት ያላቸውን የጠለቀና ሥር የሰደደ አመለካከት በልዩ ልዩ ዘዴዎች መመርመርና ማጥናት ያስፈልጋል። በመሬት ወይም በአባት ርስት የተነሣ ስንቱ ገበሬ ሞቷል፤ ስንቱ ተጋድሏል ወይም ደም ተቃብቷል፣ ስንቱ ሸፍቷል፣ ስንቱ አገር ጥሎ ተሰዷል፡፡ የመሬት ይዞታ ዋስትና ለገበሬው ከሁሉም የበለጠ ክብሩና ማዕረጉ ነው፡፡ መሬት ለገበሬው ሕይወቱ፣ ጉሮሮው፣ ትዳሩ፣ ሀብቱ ማለት ነው፡፡ መሬቱን፣ ሀብት ንብረቱን፣ ራሱን፣ ቤተሰቡንና ዘመዶቹን ነቅቶ ለመጠበቅና ከጠላት ለመከላከል ደግሞ እንዳቅሙ፣ እንዳካባቢውና እንደዘመኑ ባህላዊ ወይም ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ይይዛል ወይም ይታጠቃል፡፡ ከቻለና ከተፈቀደለት ካላሽንኮቭ፣ ምኒሽር፣ ዲሞትፈር፣ ወይም በልጅግ ይገዛል፡፡ ካልቻለ ደግሞ ጅንፎ ያለው ጠንካራ ሽመል ወይም ዱላ፣ ጦር ወይም አንካሴ፣ ሳንጃ ወይም ጩቤ ይይዛል፡፡ መያዝ ብቻ ሳይሆን በተለይ በቀረርቶና በፉከራ ጊዜ የሚወደውን ዱላ ወይም የጦር መሣሪያ እያሽከረከረ ወንድነቱን፣ ኃይለኛነቱን፣ ገዳይነቱን፣ ጉዛምነቱን፣ እንዲሁም ሀብቱን፣ ባለቤቱን አባቱንና ዘመዶቹን በግጥም እያነሳ ያሞግሳል፡፡ ጠላቱን ያንኳስሳል፡፡ የጐጃም ገበሬዎች እንደሚሉት ቀረርቶ ሲሰሙ እጅግ ይነሸጣሉ፡፡ ቀረርቶውን በተከታታይ ከሰሙ ወይም ራሳቸው ለሚያቅራራው ሰው ግጥም ከሰጡ በኋላ ህሊናቸውን መቆጣጠር ያቅታቸዋል፡፡ ከዚያም፤
ዘራፍ ዘራፍ ዘራፍ
የኮስትር አሽከር የባለ ውሉ
ዓይኑ መነጠር ጠበንጃው ስሉ፡፡
በማለት ዘለው እፉከራ ውስጥ ይገባሉ። እንግዲህ በዚህን እጅግ ስሜታዊና ድራማዊ በሆነው የቀረርቶና ፉከራ ክዋኔ ጊዜ ነው ገበሬው ሆዱንና ልቡን ሲያብሰለስለው የኖረውን ውስጣዊ ብሶት፣ ቅሬታውንና ንዴቱን በሚመስጥ ግጥም የሚገልፀው፡፡ በዚህን ጊዜ ነው በድብቅ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ የቆየው የኮሚቴዎች፣ የቀበሌ አስተዳዳሪዎች፣ የመንግስት ወኪሎች፣ ባካባቢው የተከሰቱ የርስበርስ ግጭቶችና የዘመኑ ዐበይት ችግሮች በሙገሳም ሆነ በትችት መልክ በግጥም የሚወጡትና የሚስተጋቡት። በተለይ በመንግስት አስተዳደራዊ ለውጥ ወቅት የግጥሞቹ ፖለቲካዊ ፋይዳ ጐልቶ ይታያል፡፡ እላይ ወደተነሳንበት የመሬት ጉዳይ እንመለስና እስቲ የሚከተሉት አሥር ግጥሞች የሚያነሷቸውን ጉዳዮች በጥሞና እንመርምር፡፡ ብዙዎቹ የቀረርቶና የፉከራ ግጥሞች ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ የእንጉርጉሮ ወይም የብሶት የሚባሉት ዓይነት ናቸው፡፡ ግጥሞቹ በ1989ዓ.ም በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተደረገው የገጠር መሬት ሽግሽግ ፖሊሲ አፈፃፀምና በተለይ የሽግሽግ ፖሊሲው በገበሬው ሕይወት ላይ ያስከተለውን አሉታዊ ገፅታ ይመለከታሉ፡፡
ወደ ግጥሞቹ እንመለስና የመጀመሪያው ግጥም መሬቱ የተወሰደበት ገበሬ ያቅራራው ነው። ገጣሚው ከመንግስት አገዛዝ፣ ከመሬት ሥሪት፣ ከግብር እና ከመዋጮ ጋር የተያያዙ ሦስት ታሪካዊ እውነታዎችና የመንግስት አገዛዞች ያነፃፅራል። የመጀመሪያው ግጥም በአፄው ዘመነ መንግስት የነበረውን የ “አስራት” ክፍያ እና በደርግ አገዛዝ የነበረውን እህል በግዳጅ የመነጠቅን ወይም “ኮታ”ን “አረፍሁ” ብሎና ተስፋ አድርጎ የነበረው ገበሬ፣ በዘመነ ኢህአዴግ “የኮር አባል” የሚባል ካድሬና ከበፊቶቹ “የባሰ ቀማኛ” መጥቶ መሬቱን በመጫኛ ሰፍሮ እንደወሰደበት ምሬቱን ይገልፃል፡፡
ሁለተኛው ግጥም ደግሞ ይኸው የኮር አባል የሚባለው የኢህአዴግ ባለስልጣን የገጠሩን ህዝብ እንዴት እንዳሰቃየው ገጣሚው ባካባቢው ከሚገኝና “ኮር/ች” ከሚባል እሾኻማ እንጨት ጋር በማነፃፀር በተለዋጭ ዘይቤ ያመሳስለዋል። የኮር አባላት በመሬት ሽግሽጉ ወቅት ገበሬውን በማንገላታት፣ እርስ በርስ በማጋጨትና መሬቱን በመውሰድ፣ለኢህአዴግ መንግስት ታማኝነታቸውን ያስመሰከሩ “የቁርጥ ቀን ልጆች” ናቸው፡፡ እነዚህ የኮር አባላትም ለአገሩ መፍረስ ተጠያቂዎች እንደሆኑ ግጥሞቹ ያመለክታሉ፡፡
አሥራት ቀረ ብዬ አርፌ ስተኛ
ኮር ቀረ ብዬ አርፌ ስተኛ
የኮር አባል መጣ የባሰው ቀማኛ
መሬቴን ወሰደው ሰፍሮ በመጫኛ፡፡

ጣሊያን አልመጣብን ተኩስ አልተተኮሰ
ወይ ወራሪ አልመጣ ችግር አልደረሰ?
በኮር የተነሳ አገሩ ፈረሰ፡፡

ወትሮም ነገረኛ ነበር ተጥንት
ኮር ነው ያስቸገረን ጠማማው እንጨት፡፡

እኔስ አርስ ነበር የገበሬው፣ የገባሩ ልጅ
መሬቴን ቢለኩት ቢወስዱት ነው እንጅ፡፡
ቀጥሎ የቀረቡት ሁለት ረዣዥም ግጥሞች ደግሞ መሬታቸው በኢህአዴግ ካድሬዎች በግድ የተወሰደባቸው የምስራቅ ጎጃም ገበሬዎች የደረሰባቸውን አሳዛኝ ግፍና ኢሰብአዊ በደል ባጠቃላይ ለአገራቸው ለጎጃም ህዝብ በተለይ ደግሞ ባካባቢያቸው ለሚኖሩ የማቻክል፣ የጎዛምን፣ የበረንታ የጥላትግን፣ የእነሴ፣ የጎንቻ፣ የሳር ምድር፣ የአዋበል እና የአነደድ ወረዳዎች ወገኖቻቸው አቤት ይላሉ፣ ጩኸታቸውንና ጥልቅ ኀዘናቸውን ያሰማሉ።
ይታይህ ማቻክል ይሰማህ ጎዛምን
ይታይህ በረንታ ይሰማህ ጥላትግን
እግዚዎ በል እነሴ ጎንቻና ሳር ምድር
እግዚዎ በል አዋበል እግዚዎ በል አነደድ
እንዴት ይወሰዳል መሬታችን በግድ?
ወይ! አገሬ፣ ኧረ! አገሬ ጐጃም
ወሰዱት መሬቴን እርስትና ጉልቴን
የራብ መከልከያ ልብስና ቀለቤን
አያቴ፣ ቅማቴ እስተምንጅላቴ
የወጣሁበትን፣ የገባሁበትን
ገብሬ፣ ቀቅዬ የኖርሁበትን
ወሰዱት መሬቴን ሰፍረው በገመድ
ተእንግዲህ ደካማው ተእንግዲህ አሮጉ
ኧረ! ወዴት ልግባ ኧረ! የት ልሂድ
ገበሬዎቹ ከአያት ቅድማያቶቻቸው የወረሱት የመሬት ይዞታቸው በመነጠቁ የመኖር ህልውናቸው እንዳከተመና እንደሞቱ ያህል ሆኖ ይሰማቸዋል። ከመጀመሪያው ግጥም እንደምንረዳው ላንዱ ገበሬ ያባቱ ባድማ መወሰድ የሞት ያህል ሲሰማው፣ ሌላው የመሬቱ መወሰድ፣ በመሬት እጥረት ምክንያት ወደፊት ሊደርስ የሚችለው የረሃብ አደጋ ያስጨንቀዋል፡፡ ሦስተኛው ገበሬ ደግሞ በኢሕአዴግ ያገዛዝ ዘመን ላይ እሮሮውን ያሰማል። እንደገጣሚው ዋይታ በ “ዘመነ ወያኔ” መሬቱ ስለተወሰደበት “ልጆቼን ምን ላብላቸው”፣ በምን ላሳድጋቸው” እያለ ብሶቱን ያሰማል፡፡ ሌላው ተስፋ የቆረጠ ገበሬ ደግሞ ከነጭራሹ በሮቹም እንደመሬቱ እንይወሰዱበት በስጋት “በሮቼን አምጡልኝ አርጄ ልብላቸው…” በማለት የኢሕአዴግ ካድሬዎችና የቀበሌ ተመራጮች ያደረሱበትን ሰቆቃና በደል ለዘመዶቹ ያዋያል፡፡
አልሞተ መስሎታል እሬሳው አልወጣ
ያባቱን ባድማ ሲካፈሉት በእጣ፡፡
ተዘንድሮው እራብ የከርሞው ይብሳል
መሬቱ ተወስዶ ምኑ ይታረሳል?
ዘመነ ወያኔ ዘመነ ኢሕአዴግ
መሬቴ ተወስዶ ልጅ በምን ላሳድግ
በሮቼን አምጡልኝ አርጄ ልብላቸው
ደሞ እንደ መሬቱ ሳይቆራርጧቸው፡፡
(PROCEEDINGS OF THE XIV INTERNATIONAL CONFERENCE OF ETHIOPIAN STUDIES
November 6-11,2000, Addis Ababa (IN THREE VOLUMES) VOLUME 3 ገፅ 2045- 2064)

Published in ጥበብ

          የግሪኩ አንጋፋ ፈላስፋ አፍላጦን /Plato/ ፍትህ ምን ማለት እንደሆነ በሚተነትንበት ድርሳኑ /The Republic/ ውስጥ ሁለት ዓለማት መኖራቸውን፣ እነርሱም ዓለመ አምሳያ እና ዓለመ ህላዌ መሆናቸውን ይገልፃል። ዓለመ ኅላዌ እውነት፣ ውበት፣ ፍትህ፣ እውቀት መገኛ እንደሆነና ዓለመ አምሳያ ደግሞ የዓለመ ኅላዌ ቅጅ፣ ጥላ፣ ግልባጭና አምሳያ መሆኑን የሚገልፀው ፕሌቶ፤ አንድ ሰው ፈላስፋ፣ ጥበበኛና ደቂቀ መለኮት የሚባለው ሁለቱንም ዓለማት ጠንቅቆ የመረመረ ሲሆን ነው ይላል፡፡
በዚህ ጽሑፍ የምናየው ጥበበኛው/ፈላስፋው ለምን እና እንዴት መሪ መሆን እንዳለበት አፍላጦን የሰውን ነፍስ መዋቅርና የአንድን ሃገር ሰዎች መዋቅር በንጽጽር ያስረዳበትን ነው፡፡ የነፍስን መዋቅር ሲመረምር ሦስት ዓይነት ነፍሳት አሉ ይለናል፡፡ አንደኛው ነፍስ ከወርቅ የተሰራ ነው፤ ሁለተኛው ነፍስ ከብር የተሰራ ነው፤ ሦስተኛው ደግሞ ከብረት የተሰራ ነው፡፡
በኛ ማህበረሰብ ዘንድ ነፍስ ፍጹማዊ የሆነ አንድ ንጹህ ባህሪ ያላት ተደርጋ ስለምትቆጠር፤ የአፍላጦንን “ነፍስ” በእኛ ሃገር የ “ልቦና” እሳቤ እንተካው (ለነገሩ አፍላጦን ስለ ኢትዮጵያ አለማወቁ ነው እንጅ ነፍስ ተናጋሪ፣ አሳቢ እና ህያዊት ናት፤ አንደኛ ሁለተኛ ሦስተኛ ደረጃ የላትም)። ስለዚህ ሦስቱን ዓይነት የአፍላጦንን ነፍስ፤ ሦስት ዓይነት ልቦና እንበላቸው፡፡ አንዳንድ ልቦች ከወርቅ፣ አንዳንዶች ከብር፣ ሌሎች ደግሞ ከብረት/መዳብ የተሰሩ ናቸው እንበል - ሃሳቡን በቀላሉ እንድንጨብጠው፡፡ እነዚህ የተያዩና እርስ በእርስ የሚፎካከሩ ጠባዮች ያሏቸው ልቦናዎች ናቸው፡፡ እስኪ ሦስቱንም አንድ በአንድ እየዘረዘርን እንመልከታቸው፡፡
ሀ/ ብረታዊ/መዳባዊ ልብ፡- ብረታዊ ባህሪ የሚያደላበት ልቦና ታታሪነት፣ መብል፣ መጠጥ፣ መዝናናት፣ ማምረት … ቅብጥብጥ ዓይነት እና ቀለል ያለ ስሜትን የሚወድ ዓይነት ልብ ነው፡፡ ይህ ልብ ዕለታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር፣ ቀለል ያሉ ዘልማዳዊ ስራዎችን የሚያዘወትር፣ የሚታወቁና የተለመዱ ስራዎች ላይ መጠመድ የሚስማማውና ምቾት የሚሰጠው ነው፡፡ እንደ ጉንዳን ታታሪ ልቦና ነው ይህ ልቦና፡፡ ነገር ግን ፍላጎት/ስሜት ብቻ የሚመራው፤ ፍላጎቱን ማሸነፍ የማይችል ነው፤ ቅብጥብጥነት ያጠቃዋል፡፡
ግዮን መዳባዊ ነው፤ ጸባዩን የተረዱት ያርሱበታል፣ አምርተው ቀለባቸውን ይሰፍራሉ፡፡ ከታችና ከምንጩ ሥር ያሉት የሽንኩርት፣ የካሮት መደባቸውን ያጠጣሉ፤ ፍራፍሬ ያመርቱበታል፤ ከብቶቻቸውን ያጠግባሉ፡፡ ታላቁ ነብይ ሙሴ፤ ከግብጽ በተሰደደ ጊዜ የግዮንን ፈለግ መንገድ መሪ አድርጎ ወንዙን ተከትሎ ወደ መነሻው ወደ ምንጩ ነበር የመጣው እናም ውኃ የሚያጠጡ እረኞችን ያገኘው፡፡ በኋላም የነብይነት ጥሪውን እስኪጀምር ድረስ የካህኑ ዮቶር እረኛ ሆኖ የኖረው እዚሁ ነው፡፡ ግዮን እንዲህ ነው፤ እረኝነትንም ያስተምራል፡፡
ለ/ ብራዊ ልብ፡- ይህ ልብ ወኔያም ደፋር ነው፤ ጦረኝነት/ጀብዱ ይወዳል፣ ቁጡ ነው፡፡ እንደ ብር ጠንካራ ነው፣ በራስ መተማመኑ ከፍተኛ ነው፣ አዳዲስ ነገሮችን ይደፍራል፣ ልዩ መሆንን ይመርጣል፣ አሸናፊነት ባህሪው ነው፣ አይንበረከክም፡፡ ሃገር ጠባቂ መሆን፣ ህዝብን ማስከበር፣ ኃያልነትን፣ ግዛት ማስፋትን ይወዳል፡፡ እንደ አንበሳ ብርቱ ነው፡፡ ነገር ግን ኃይለኛነት የሚገዛው፤ ወኔውን መቆጣጠር የማይችል ነው፡፡
ግዮን ብራዊም ነው፤ ጀግንነትና ጀብዱ ባህሪው ነው፡፡ በአምስቱ አመት የአርበኝነት ዘመን ለኢትዮጵያ አርበኞች መሸሸጊያ ዋሻ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ጥላ፣ ጎጆ ሆኗቸዋል፤ ሲደክማቸው ብርታት፣ ሲጨንቃቸው ተስፋ ሆኗቸዋል፡፡ ከበላይ ዘለቀ ከተሰቀለው
ይሻላል ሽፈራው ሶማ የቀረው
የሚለው እንጉርጉሮ የአባይን እና አካባቢውን አርበኝነት፣ አልገዛም ባይነት የሚያስታውሰን ነው። ኃይለኝነቱን በጠባይ መያዝ ላወቀበት ግዮን የኃይል ምንጭ ነው፡፡ በአልገዛም ባይነቱና ባሸናፊነቱ የኢትዮጵያን ተራሮች አቋርጦ የሱዳን በረሃ ሳያመነምነው፣ የግብጽ አሸዋ ሳይመጠው ሁሉንም ድል አድርጎ ሜድትራኒያን ባህር ይቀላቀላል። ኃይለኝነት ባህሪው ነው፡፡ በፍቅር ሲጠጡት ነው ጤና የሚሰጥ እንጅ ክፋት ይዘው ቢጠጡት ጤና ይነሳል፤ እንደ ስካር አናት ላይ ወጥቶ ቋንቋ ይደበላልቃል፡፡
ሐ/ ወርቃማ ልብ፡- ይህ ልብ ተመራማሪ ነው፤ ሁለቱንም ዓይነቶች ልቦናዎች/ባህሪያት አብጠርጥሮ ያውቃቸዋል፡፡ ከሁለቱ ልቦናዎች በተለየ መልኩ ተመራማሪ፣ ጥበበኛ፣ ሚዛናዊ፣ ምክንያታዊ፣ የሰከነ፣ ጭምት፣ አስተዋይ፣ መንፈሰ ጠንካራ ነው፡፡ ይህ ልብ ሁሉንም ነገር በአመክንዮ ይመረምራል፡፡ ከትንሽ እስከ ትልቅ ሃሳቦችን፤ ከመጥፎ እስከ መልካም ምግባሮችን በአመክንዮ በመመርመር ይበይናል፡፡ ያለ አመክንዮ አይንቀሳቀስም፤ ፍላጎቱን የሚቆጣጠር ወኔውን የሚያምቅ ወርቅ የሆነ ልብ ነው፡፡ ልክ እንደ ንቧ ማር ሰርቶ ብቻዬን ልጨርስ ሳይል፤ መርዛም እሾህ አለኝ ብሎ ሁሉንም የማይናደፍ አመዛዛኝ ነው ይህ ልቦና፡፡
ግዮን እንደ ወርቃማ ልብ ፍርድ አዋቂ ነው። ቋንቋውን ለሚችሉትና ለሚሰሙት ሰዎች ጥበብን ያስተምራል፡፡ አፈር ከሞላበት የኢትዮጵያ ምድር ተሸክሞ የአፈር ድርቅ ላመነመናት ግብጽ ልምላሜ ሆኗታል፡፡ በበረሃ ላለችው ምስር ፈውሱዋ ግዮን ነው። ለበረኧኞች፣ ለመናንያን የጥበብ መልእክተኛቸው ግዮን ነው፡፡ የግብጽ ጠቢባን ግዮንን ለመስኖ ለመጠቀም ባላቸው ታታሪነት የሒሳብ እውቀታቸው እንዳደገ፣ ፓይታጎረስ ቴረም የተባለውም የሒሳብ ቀመር በዚሁ ግድም እንደተገኘ ይነገራል፡፡ ግዮን ቀማሪ ጥበበኛ ነው፤ በጣና ሐይቅም ውስጥ አቋርጦ የሚሄድበት የራሱ የጥበብ መንገድ አለው። በውኃ ላይ የሚሄድ ብቸኛው ወንዝ ግዮን ይመስለኛል፡፡ በውኑ ይች ጥበብ ከምድር ናትን? እንዲህ ያለ ጥበብ ምን ይረቅቅ?
ግዮን ምንጩ ሥር ላሉ የሰከላ እና ጊሼ ሰዎች ዛሬም ድረስ ፈውሳቸው ነው፡፡ ስደተኛው ሙሴ የኦሪትን ሀሁ ለቅሞ የተማረው ከግዮን ነው፡፡ ከአዳም ጀምሮ የፍጥረት ምስጢራት አንድምታ ሲተረተርበት የኖረ፤ ቅኔ እንደ ውኃ ሲፈስበት የኖረ ነው የግዮን መንፈስ፡፡ ግዮን ውኃ አይደለም መንፈስ ነው፤ ግዮን ከተገደበ የሚገደበው ውኃም ብቻ አይደለም፤ ውጪ ውጪውን የሚያየው የኢትዮጵያዊያንን ልቦና ጭምር እንጅ፡፡ ግዮን አንድም ሦስትም ነው፡፡ እርጥብነት፣ ብርሃናዊነት እና ግዙፍ አካልነት የአንዱ የግዮን ሦስት ባህሪያት ናቸው፡፡
በአፍላጦን ፍልስፍና አንድ ልብ ፍትህአዊ ነው የሚባለው ወርቃማ ባህሪው ብሪታዊንና ብራዊውን አሸንፎ መቆጣጠር ሲችል ነው፡፡ ወርቃማ ባህሪው ገዥ የሆነለት ልብ ሰላማዊና ስምሙ ነው፤ ውስጣዊ ነውጥ/አለመስማማት የለውም፡፡ ሁለመናው ውብና ጠቢብ ነው፡፡ ብሪታዊው ባህሪ ገናና ሆኖ እራሱን ማስከበር የማይችል፣ ዕለታዊ ጉዳዮች የሚያሽከረክሩት ልቦና እንዳይሆን፤ አሊያም ብራዊው ባህሪ ገናና ሆኖ ጉልበተኛና አውዳሚ እንዳይሆን፤ ወርቃማው ባህሪ የሁሉም የበላይ ሆኖ ፍላጎታቸውንና ስሜታቸውን እያመጣጠነ ማስተዳደርና መምራት አለበት፡፡ እንደህ አይነት ልብ ጎባጣው የቀናለት፣ የተገራ፣ የታረቀ/ስምሙ/ውብ እና ፍትህአዊ ነው፡፡
አፍላጦን ፍትህ የሰፈነባት ሃገር እንዴት ነው ልትኖረን የምትችለው እያለ ሲመራመር ልክ ሦስት ዓይነት ልቦናዎች እንዳሉ ሁሉ፣ ሦስት ዓይነት ሰዎች አሉ ይለናል፡፡ ሁላችንም እኩል አንድ አይነት ችሎታ የለንም ይለናል፡፡ አንዳንዶቻችን ጥሩ ሠራተኞች ነን /appetitic/ አንዳንዶቻችን ጠንካራ ወታደሮችን /auxiliary/ ሌሎቻችን ደግሞ መልካም ተመራማሪዎች ነን /Spirit/። ስለዚህ ፍትህ የሰፈነባትን ሃገር ለማግኘት ልጆቻችንን ይሄን ተረት እንንገራቸው ይላል አፍላጦን፡፡
አንዳንዶች ከወርቅ፣ አንዳንዶች ከብር፣ ሌሎች ደግሞ ከብረት ልብ መሰራታቸውን ለልጆቻችን ተረት እየነገርን እናሳድጋቸው፡፡ ሁሉም የተለያየ ችሎታ እንዳላቸውና አንዳቸው በአንዳቸው ውስጥ ጣልቃ መግባት እንደሌለባቸው፡፡ ወርቃማ ልቦች ለገዢነት፣ ብርማ ልቦች ለጠባቂነት፣ ብረታማ ልቦች ደግሞ ላገልጋይነት መፈጠራቸውን እንንገራቸው፡፡ ይህ ክፍፍል በምንም አይነት ምክንያት ቢሆን ብሔርን፣ ጎጥን፣ መሰረት ማድረግ የለበትም፡፡
ትምህርትም እንደየአቅማቸውና እንደየልቦናቸው ጠባይ እየተመጠነ ይሰጣቸው፡፡ ምርታማነትን፣ ክህሎትን፣ ፍላጎት ማመጣጠንን፣ ገበያ መፍጠርን ወዘተ ለብረታዊ ልቦች እናሰልጥን፡፡ ዜጋንና ጠላትን መለየትን፣ ሃገርን ማስከበርን፣ ትእዛዝ ተቀባይነትን፣ ወኔን መቆጣጠርን ደግሞ ለብራዊ ልቦች እናስተምር። አለማዳላትን፣ ፍትህአዊነትን፣ ግለ ጥቅም አልባነትን፣ ምክንታዊነትን፣ አመራር ሰጭነትን፣ ተመራማሪነትን ደግሞ ለወርቃማ ልቦች ስልጠና መስጠት ይኖርብናል፡፡
ግለሰቡ ውስጣዊ ሰላም እንዲኖረው ስግብግብነቱን በወኔው ማክሸፍክ፤ ኃይለኝነቱን ደግሞ በምክንታዊነት /አመክንዮ/ ማሸነፍና ወርቃማ ልቡ የሁሉም የበላይና ያለ አድሎ ፈራጅ መሆን እንዳለባት ሁሉ አንድ ሃገር ሰላማዊና ፍትህ የሰፈነባት እንድትሆን ጠቢባን፣ እራሳቸውን የገዙ፣ ፈላስፎች ሊያስተዳድሯት ይገባል፡፡ የሰራተኞችና የጠባቂዎች የበላይ መሆን ያለባቸው ጠቢባን ናቸው። ጠቢብ ሰው፤ ልክ እንደ ወርቃማው ልብ ሰራተኞችና ጠባቂዎች የማያውቁትን ሁሉ የሚመራመር ፈላስፋ ስለሆነ፣ ሁለቱንም ያለ አድሎ የሚያስፈልጋቸውን ልክ እንደየ ልቦናቸው ጠባይ ይመግባቸዋል፡፡ እንዲህ ከሆነ ሃገሪቱ ፍትህ የሰፈነባት ትሆናለች፡፡
ግብረ ጉንዳን እንደ አፍላጦን የብረት ነፍሳት ያሉ ናቸው፡፡ ታታሪዎች፣ ለፍቶ አደሮች፣ ሁሌም የሚጎትቱት የሚሸከሙት ነገር አያጡም ጉንዳኖች፤ እናም ታታሪውን፣ አራሹን፣ አምራቹን፣ ሰራተኛውን ኢትዮጵያዊ ልቦና ቀደም ብለን የብረት ልብ ያልነውን ግብረ ጉንዳን ብንለው የሚወክለው ይመስለኛል፡፡ አንበሳ ደግሞ ደፋር፣ ኃይለኛ፣ ጠንካራ ነው እና የብር ልብ ያልነውን ኢትዮጵያዊ አንበሳ ይወክልልን ይመስለኛል፡፡ ንብ ሁሉንም ቀሳሚ፣ ቀማሚ፣ ወለላ ጠማቂ ነው፤ በመድሃኒትነቱ፣ ጥም አርኪነቱ/ጠጅ/፣ ፈዋሽነቱ የተመሰከረለትን ማርን የሚጠበብበት ንብ ነው፡፡ የወርቅ ልብ ያልነውን ኢትዮጵያዊ ንብ፣ በደንብ ይወክልለናል (አደራ የኢህአዴግ ንብ እንዳትሰማን)፡፡
መደምደሚያ፡- /የኢትዮጵያዊ አንድም ሦስትም ልቦና/ የኢትዮጵያዊ ልቡ እንደ ግብረ ጉንዳን ታታሪ፤ እንደ አንበሳ ደፋሪና እንደ ንብ ተመራማሪ ነው፡፡ እርሻን ቀድመው ከጀመሩት የጥንት ስልጡኖች አንዱ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ምግብ አብስሎ መመገብ፤ እንስሳትን ማላመድና ማርባት፤ ልብሱን ከእጽዋት/ጥጥ/ አዘጋጅቶ መልበስ ከጀመሩት ሁሉ ቀዳሚ ነው ኢትዮጵያዊ፡፡ እነዚህን ሁሉ የኑሮ ዘዬዎች በአንክሮ ብንመረምራቸው፣ የኢትዮጵያዊን ህያው ታታሪ ልቦናን ፍንትው አድርገው ያሳዩናል፡፡ በጉልበቱና በክህሎቱ ለዘላለም ምስክርነት የተከላቸው ውቅርና ትክል ድንጋዮች የታታሪነቱ ምስክር ናቸው (አክሱም፤ ላሊበላ፤ ጢያ ወዘተን ያስታውሳሉ)፡፡
ኢትዮጵያዊ ከጥንትም ጀምሮ አሁንም ድረስ ዳር ድንበሩን ማስከበር፤ አልገዛም ባይነት፤ ጀግንነት ባህሉ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊን በዚህ የሚጠረጥረው ማንም የለም፡- ካለም የእጁን ያገኛል፡፡ ዛሬም ድረስ የአካባቢውን ሰላምና የአለምን ደህንነት ለማስከበር ደፋ ቀና ከማለት አልቦዘነም፤ ኢትዮጵያዊ፡፡ ኃይለኝነትና ጀብዱ እንደ ባህሪ ተዋህደውታል፡፡ ጦሩን ሰብቆ ጋሻውን ነጥቆ አፈር ከድሜ ያበላቸው ጠላቶቹ፣ ለኢትዮጵያዊ ደፋር ልቦና ምስክር ናቸው (ግብጾችና ጣልያንን ያስታውሱ)
የፍትህ አዋቂነቱን፣ ተመራማሪነቱን፣ የጽድቅ ፍቅሩን ለማስረገጥ ደግሞ ቤተ አምልኳችን ለዘመናት ሲመሰክሩለት የኖሩት የምርምር፣ የጠቢባን ልቦና የሚያፈልቀውን እውቀት መመርመር ነው፡፡ የባህላዊ ተቋማቱ እንደ ሽምግልና፣ የገዳ ሥርዓት፣ እድር፣ እቁብ፣ የቡና ማህበራቱ፣ የዝክር ማህበራቱ፣ የባህላዊ ትምህርት ቤቶች የኢትዮጵያዊውን ፈላስፋነቱን የሚመሰክሩ ናቸው። መንግስታት በውስጥ ሽኩቻና ጦርነት ወቅት አቅማቸው ተዳክሞ መዋቅራቸው ሲላላ፣ ማህበራዊ አንድነቱን ያለ መንግስት ማስቀጠል የሚችል እንደ ወርቅ የነጠረ፤ እንደ ንብ የተመራመረ ልብ ያለው ህዝብ ነው ኢትዮጵያዊ፡፡
በግዮን መንፈስ የተቃኘን ኢትዮጵያዊን ህዝብ ለመምራት፣ በጊዜያዊነት በመነዳት ሳይሆን እንደ ግዮን ዘመን የማይሽረው ህዝባዊና ሃገራዊ የጉዞ ራዕይ መሰነቅ ግድ ይላል፡፡ የፖለቲካ ታማኝነት ሳይሆን አገር የመምራት ሙያ ባለቤትነት ያስፈልገናል፡፡ በዘመድ በመሰባሰብ ሳይሆን በጥበብ ማበብ ነው አገር የሚመራው፡፡
ከዘመቻ ባሻገር ማሰብ፤ ዛሬን መስሎ ከመታየት መራቅን፡፡ ፍትህን፣ ጥበብን፣ መልካምነትን ስንቅ ማድረግ ግድ ነው የኢትዮጵያ መሪ ለመሆን፡፡ ለአለቃ መታመንን ሳይሆን ለህዝብ ማገልገልን ማስቀደም ይጠይቃል፡፡ ለዛሬ አሸናፊ ሆኖ ለመታየት ሳይሆን የህሊና ፍርድን ለማሸነፍ መስራት፡፡ የግል ጥቅም በረሃ (ሱዳን) ሳያመነምነን፤ የቂም በቀልና የበታችነት አሸዋ (ግብፅ) መጥጦ ሳያደርቀን፤ ሃገራዊነትንና ህዝባዊነትን ታጥቀን ከባህሩ (ሜድትራኒያን) እንደ ግዮን በታላቅነት፣ ባሸናፊነት መቀላቀል ያስፈልገናል፡፡ እንደ ታላቁ ፈላስፋ አፍላጦን ፍልስፍና ከሆነ፣ ይህንን ኢትዮጵያዊ ለማስተዳደር የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ልቦና አብጠርጥሮ የሚያውቅ፣ ጠቢብ ልቦና ባለቤት መሆን ያስፈልጋል፡፡ እንደ ንቧ መድሃኒት የሚሆን ማር መቀመም የሚችል መሪ፤ እንደ ንቧ ሰፈፍ ቅርጹ ያልተዛነፈ/የተስተካከለ የማር እንጀራ/ አይነተኛ የሆነ እንቁላል መጣያ የሚሆን ሰፈፍ መጋገር የሚችል ቀማሪ መሪ፤ እንደ ንቧ ከሁሉም አበባ ጣፋጩን ቀስሞ፣ ከውኃ ጋር አስማምቶ ዱቄቱ ሳይበዛ ማሩ እንዳይደርቅ፤ ውኃውም ሳይበዛ ማሩ እንዳይንቦጫረቅ ውብና ስምሙ የሆነ፣ የተስተካከለ፣ ለሁሉም ጣፋጭ ለሁሉም መድሃኒት የሆነ ማር ማዘጋጀት የሚችል ፈላስፋ/ጠቢብ መሪ ያስፈልጋታል፤ ኢትዮጵያ፡፡ የዚህ ወርቅ ህዝብ መሪ ለመሆን፣ የወርቆች ሁሉ ወርቅ መሆንን ይጠይቃል፡፡ የዚህ ፈላስፋ ህዝብ መሪ ለመሆን፣ የፈላስፎች ፈላስፋ መሆንን ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያዊ በአዲስ ዓመት አዲስ መንፈስ ሰንቆ፣ በዚህ ምድር አንገቱን ቀና አድርጎ መኖር ይገባዋል፡፡ ግዮናዊያን እንቁጣጣሽ!

Published in ጥበብ
Page 1 of 16