ለአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ግንባታ ቃሊቲ ጉምሩክ ግቢ ውስጥ በቁፋሮ ስራ ላይ በነበሩ 7 የቀን ሰራተኞች ላይ ከትናንት በስቲያ የአፈር መደርመስ አደጋ አጋጥሞ የሶስቱ ህይወት ወዲያው ሲያልፍ አራቱ ህይወታቸው ሊተርፍ ችሏል፡፡ ቃሊቲ ወረዳ 6 ጉምሩክ ግቢ ውስጥ ለባቡር ፕሮጀክት የጉድጓድ ቁፋሮ ሲያከናውኑ አፈር ከተደረመሰባቸው 7 ሰራተኞች መካከል የአራቱን ህይወት ያተረፉት የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠሪያ ባለስልጣን የነፍስ አድን ሰራተኞች ሲሆኑ ሶስቱ ህይወታቸው አልፎ አስከሬናቸው እንደወጣ ታውቋል፡፡ በህይወት የተረፉትም በአካባቢው ወደሚገኝ የህክምና ተቋም ተወስደው ህክምና ተደርጎላቸዋል፡፡ ሐሙስ ረፋድ 4፡30 ገደማ በደረሰው በዚህ አደጋ የሞቱት ሰራተኞች እድሜ ከ20 እስከ 23 እንደሆነ የገለፁት የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከያ የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አቶ ንጋቱ ማሞ፤ ከሁለት ወር በፊት በንፋስ ስልክ ክ/ከተማ ባርኔሮ አካባቢ የባርኔሮ ኮንስትራክሽን 3 የቁፋሮ ሰራተኞችም አፈር ተደርምሶ ህይወታቸውን እንዳጡ በማስታወስ ይህን መሰሉ አደጋ እየተደጋገመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ መሰሉ አደጋ በተደጋጋሚ ህይወታቸውን እያጡ ያሉት የቀን ሰራተኞች መሆናቸውን ያመለከቱት አቶ ንጋቱ፤ አሰሪዎች ለሰራተኞቻቸው የደህንነት መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ከሟሟላት በተጨማሪ አስፈላጊ የስራ ላይ ደህንነት አጠባበቅ ስልጠና ሊሰጧቸው እንደሚገባ አሳስበዋል - በሰሞኑ አደጋ ህይወታቸው ያለፈው ወጣቶችም ሆኑ የተረፉት በወቅቱ ምንም አይነት የአደጋ መከላከያ አለማድረጋቸውን በመጥቀስ፡፡

Published in ዜና

        በአንጋፋው ደራሲ አዳም ረታ የተጻፈው “መረቅ” የተሰኘ የረጅም ልቦለድ መጽሃፍ ሰሞኑን በገበያ ላይ ይውላል፡፡ ለደራሲው ስምንተኛው የሆነው ይሄው መፅሃፍ፤ ከስድስት መቶ በላይ ገጾች ያሉት ሲሆን፣ በቅርቡ በተለያዩ መጽሃፍት መደብሮችና አዟሪዎች ለገበያ እንደሚውል ታውቋል፡፡ ደራሲ አዳም ረታ ከዚህ በፊት “ማህሌት”፣ “ግራጫ ቃጭሎች”፣ “እቴሜቴ ሎሚ ሽታ”፣ “አለንጋ እና ምስር”፣ “ከሰማይ የወረደ ፍርፍር”፣ “ህማማት እና በገና” እና “ይወስዳል መንገድ፣ ያመጣል መንገድ” የተሰኙ ተወዳጅ የአጫጭርና የረጅም ልቦለድ መጽሃፍትን ለንባብ አብቅቷል፡፡ አዳም ከዚህ በተጨማሪም፣ በአይነቱ ለየት ያለና ከ1ሺህ 600 በላይ ገጾች እንደሚኖረው የተነገረለትን፣ “የስንብት ቀለማት” የተሰኘ ረጅም ልቦለዱን እያጠናቀቀ እንደሚገኝ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ለረጅም አመታት ኑሮውን በባህር ማዶ ያደረገው አዳም ረታ፣ ሰሞኑን ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Published in ዜና

            የአዲስ አበባ አስተዳደርና ወረዳው በአካባቢያችን የመልሶ ማልማት ስራ የገባልንን ቃል አልጠበቀም የሚሉት በአራዳ ክ/ከተማ የውቤ በረሃ የልማት ተነሺዎች፣ ቅሬታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤትና ለከተማ ልማት ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ማቅረባቸውን ጠቁመው ከባለስልጣናቱ በጐ ምላሽ እንደሚጠብቁ ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ እና የወረዳው ፅ/ቤት ኃላፊዎች ከአንድ አመት በፊት ከቦታቸው ሲነሱ በከተማው መሃል ባሉ የኮንዶሚኒየም ሳይቶች መኖሪያ ቤት ይሠጣችኋል የሚል ቃል እንደገባላቸው የገለፁት ከ217 በላይ የሚሆኑ የአካባቢው አባወራዎች፤ ሃላፊዎች የገቡትን ቃል አጥፈው ቃል ታጥፎ ገላን ሳይት ትሄዳላችሁ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ ባለፈው እሁድ ከአራዳ ክ/ከተማ የስራ ሃላፊዎች ጋር ባደረጉት ስብሰባም ለተነሺዎቹ የተዘጋጀው የገላን ሳይት ነው በሚል ውሳኔው እንደማይቀየር የሚገልፅ ምላሽ ማግኘታቸውን፤ የጠቀሱት የልማት ተነሺዎቹ ኮሚቴ አባላት፤ ጉዳዩን በዝርዝር የሚያስረዳ የቅሬታ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤትና ለከተማ ልማት ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስገብተው ምላሹን እየተጠባበቁ እንዳሚገኙ ገልፀዋል፡፡

Published in ዜና
Saturday, 13 September 2014 15:54

ሳቅ አታ‘ቅም

ሳቅ አታ‘ቅም
“ሳቅ አታ‘ቅም አሉኝ - ሳቅ እንዳስተማሩኝ
ሳላ‘ቅ ብስቅ እንኳን - ከሳቅ ላይቆጥሩልኝ
እንዴት ብዬ ልሳቅ፣ ሳቅስ መች ለምጄ?
በጭጋግ ታፍኜ፣
በጉም ተጀቡኜ፣
በዶፍ ተወልጄ፡፡”
አትበል ወዳጄ፡፡
* * *
በጉም መሃል እንጅ - የወጣችው ፀሐይ
ነፍስን እያሳሳች - ሀሴት የምታሳይ
ብቻዋን ስትቆም - በጠራራው ሰማይ
ንዳድ ሀሳብ ዘርታ - ባሳር ምታጋይ፡፡
ብቻ ሲሆንማ - ሳቅም ጠራራ ነው፤
ጥርስን ያራቆተ - የከንፈርህ ግዳይ፡፡

ቅርብኝ
ኖኅን መሰኘት አምሮህ - ታንኳ ቢጤ ስትገነባ
አምላክ ያዘዘህ ቀርቶ - ወዳጅህ መርከብህ ከገባ
ዓለም የጨው ክምር ሆና - ፍጥረታቷ ሲረግፉ
ድንገት ታንኳህ ላይ ብገኝ - ነፍሴን አርዷት ዶፉ
ርግቧን መሆን አልሻም፤ ከጎንህ እንዳልገኝ
የትም እንደወጣሁ ልቅር፤ ላንተስ ቁራህን ያድርገኝ
(በቅርቡ በደሴ ከተመረቀው የገጣሚ አካል ንጉሴ “ፍላሎት (የነፍስ አሻራዎች)” 2006፤ የግጥም መድበል የተወሰዱ)


=========


ኢዮሀ!
ኢዮሀ!
አበባ ፈነዳ!
ፀሀይ ወጣ ጮራ፡፡
ዝናም
ዘንቦ
አባራ፡፡
ዛፍ
አብቦ
አፈራ፡፡
ክረምት መጣ ሄደ
ዘመን ተወለደ፡፡
ዓለም አዲስ ሆነ፡፡
ለሊት ሲነጋጋ
ጋራው ድንጋይ ከሰል
የተተረከከ ፍም እሳት ደመናው
ፀሐይ ያነደደው፡፡
ዓለም ሞቆ
ደምቆ፡፡
ብርሃን ሲያሸበርቅ
ጤዛው ሲያብረቀርቅ፤
ሕይወት ሲያንሰራራ
ፍጥረት ሲንጠራራ
ዘመን ተለወጠ መስከረም አበራ፡፡
“ኢዮሃ አበባዬ፡፡”
(ከገብረክርስቶስ ደስታ)

 

Published in የግጥም ጥግ

       የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2015 እኤአ ሞሮኮ ላይ ለሚስተናግደው 30ኛው አፍሪካ ዋንጫ የሚያልፍበት ዕድል ተመናመነ፡፡ ባለፈው ሳምንት በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች በዋልያዎቹ ላይ ደረሱት ምክንያት ሆነዋል፡፡ በምድብ 2 የማጣርያ ጨዋታቸውን ከሳምንት በፊት በሜዳቸው የጀመሩት ዋልያዎቹ በደጋፊያቸው ፊት በአልጄርያ 2ለ1 ሲሸነፉ፤ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ደግሞ ከሜዳቸው ውጭ በብላንታዬር ከማላዊ ጋር ተገናኝተው 3ለ2 ተረተዋል፡፡ በሁለቱ ጨዋታዎች 3ቱን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጎሎች በአልጄርያ ላይ ሳላዲን ሰኢድ በፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም ማላዊ ላይ ጌታነህ ከበደ እና ዩሱፍ ሳላህ አስመዝግበዋል፡፡ በሌሎች የምድብ 2 ጨዋታዎች ማሊ በዋና ከተማዋ ባማኮ ላይ በመጀመርያ ጨዋታዋ ማላዊን 2ለ0 አሸንፋ ባለፈው ረቡእ ደግሞ አልጄርስ ላይ በአልጄርያ 1ለ0 ተሸንፋለች፡፡ ከምድብ ማጣርያው ሁለት ዙር ጨዋታዎች በኋላ በምድብ 2 አልጄርያ በ6 ነጥብ እና በ2 የግብ ክፍያ መሪነቱን ይዛለች፡፡ ማሊ በ3 ነጥብ እና በ1 የግብ ክፍያ እንዲሁም፤ ማላዊ በ3 ነጥብ እና በ1 የግብ እዳ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ተከታትለው ይዘዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ያለምንም ነጥብ በሁለት የግብ እዳ መጨረሻ ነው፡፡
በሁለቱ የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ሽንፈት የገጠመው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚያልፍበት እድል መመናመኑ በተለያዩ አቅጣጫዎች አነጋጋሪ እየሆነ መጥቷል፡፡ ዋልያዎቹ በቀሪዎቹ አራት የማጣርያ ግጥሚያዎች ሁሉንም በማሸነፍ ከፍተኛውን ነጥብ መሰብሰብ ካልቻሉ የሞሮኮ ጉዟቸው አይሳካም፡፡ አንዳንድ የስፖርት ቤተሰቦች የአሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ቡድን በቅድመ ዝግጅት የተሻሉ ስራዎች ማከናወኑን ቢያደንቁትም ይህ ሁኔታ በውጤት ሊተረጎም አለመቻሉ ክፉኛ አሳዝኗቸዋል፡፡ በቡድኑ ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች የመጀመርያው ተጠያቂ አሰልጣኙ ሊሆኑ እንደሚገባ የገለፁም በርካቶች ናቸው፡፡ ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ በወር 18 ሺ ዶላር እየተከፈላቸው ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ካላሳለፉ ኪሳራ ነው የሚል ሃሜት በዝቷል፡፡ ጎን ለጎን ብሄራዊ ቡድኑን በወጣት ተጨዋቾች በማጠናከር በተሟላ መሰረት ላይ እንዲገነቡ ለፖርቱጋላዊው በቂ የስራ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸውም እየተነገረ ነው፡፡ በአልጄርያው ሽንፈት ላይ የሜዳው አለመመቸት እና የታኬታ ችግር፤ በማጥቃት እንቅስቃሴዎች ላይ ከአሰልጣኙ መመርያ ውጭ ብዙዎቹ ዋልያዎች ረጅም ኳስ በተደጋጋሚ በመጣል ስኬታማ አለመሆናቸው እና የተገኙትን ከ5 በላይ የማግባት አጋጣሚዎች ያለመጠቀም ሁኔታዎች እንደምክንያት ይቀርባሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከማላዊ ጋር ባደረገው ሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ በተከላካይ መስመሩ ከፍተኛ መረበሽ እና ስህተት እንደነበረበት የብላንታዬር ጋዜጦች ሲዘግቡ፤ በአንፃሩ ኡመድ ኡክሪ በመጀመርያው ግማሽ ከዚያም ሳላዲን ሰኢድ፤ ጌታነህ እና ሌሎች የቡድኑ የማጥቃት ሙከራዎች ዋልያዎቹ ቢያደርጉም አጨራራሱ አልሆነላቸውም ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ስታድዬም በመጀመርያው የማጣርያ ጨዋታ የገጠመውን ሽንፈት ተስፋ አያስቆርጠንም ብለው የነበሩት ፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ በሁለተኛው ግጥሚያ ከስህተቶቻችን ተምረን ነጥብ ለማግኘት እንፈልጋለን ቢሉም አልተሳካላቸውም፡፡
ላለፉት ሶስት አመታት ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር በመጫወት ልምድ ያላቸውን ልጆች ለሁለት ወራት በከፍተኛ ደረጃ ያዘጋጁት አሰልጣኙ ፤ በተጨዋች ምርጫቸው አስራት መገርሳ፤ በሃይሉ አሰፋ እና ዳዊት እስቲፋኖስን ባለማካተታቸው ተተችተዋል፡፡ ታደለ መንገሻ እና ናትናኤል ዘለቀ የመሰሉ ወጣቶች ወደ ቡኑ በመቀላቀል እና በተከላካይ መስመር ቶክ ጀምስ፤ ሳላዲን በርጌቾን በማጣመር መስራታቸው ደግሞ እንደ ጥሩ ለውጥ ተደንቆላቸዋል፡፡ በተለይ በናትናኤል ዘለቀ ላይ ያላቸው እምነት እና ተስፋ በሁለቱም ጨዋታዎች በገሃድ መረጋገጡ ብዙ ስፖርት ቤተሰብን አስደስቷል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋች የሆነው ናትናኤል ዘለቀ ‹‹ አዲሱ ዋልያ›› ተብሎ እየተሞካሸ ሲሆን፤ በተለይ በአልጄርያው ጨዋታ በተሟላ ብቃት የሰጠው አስተዋፅኦ እና የስነልቦና ጥንካሬው የጨዋታው ኮከብ እንደሚያደርገው አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ መስክረውለታል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከወር በኋላ በ3ኛው እና በ4ኛው የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች በአንድ ሳምንት ልዩነት በሜዳው እና ከሜዳው ውጭ የሚገናኘው ከምእራብ አፍሪካዋ ቡድን ማሊ ጋር ይሆናል፡፡ 5ኛውን የምድብ ማጣርያ ጨዋታ ከ2 ወራት በኋላ ከሜዳው ውጭ ከአልጄርያ ጋር ሲገናኝበት በሳምንቱ በማጣርያው የመጨረሻ ስድስተኛ ጨዋታ ማላዊን በአዲስ አበባ ስታድዬም ያስተናግዳል፡፡

      ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚያዘጋጀው 4ኛው ኮካ ኮላ ተከታታይ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በነገው እለት በሚካሄደው የመጨረሻ ዙር ውድድር ይፈፀማል፡፡ በዋናው የአትሌቶች ውድድር በመጀመርያዎቹ ሁለት ዙሮች ባስመዘገቡት ውጤትና ነጥብ መሰረት በሁለቱም ፆታዎች ተቀራራቢ ነጥብ ያስመዘገቡ ከሁለት በላይ አትሌቶች መኖራቸው በፍፃሜው ከፍተኛ ፉክክር እንዲጠበቅ ምክንያት ሆኗል፡፡ በአትሌቶች ደረጃ በሚካሄደው ፉክክር በሴቶች ምድብ አስቀድመው በተካሄዱት ሁለት ውድድሮች 14 ነጥብ በማስመዝገብ የምትመራው አለሚቱ ሃዊ ናት፡፡ ዘውድነሽ ሃይሌ እና ሽቶ ውዳሴ በእኩል 10 ነጥብ ይከተሏታል፡፡ በወንዶች ምድብ ደግሞ ጌታነህ ሞላ፤ ዘውዱ መኮንንና እና ጋዲሳ ብርሃኑ በእኩል 10 ነጥብ ለመጨረሻው እና ለሶስተኛው ዙር ውድድር ነገ ይተናነቃሉ፡፡ በሁለቱም ፆታዎች ከአንድ እስከ ሶስት ደረጃ ለሚያገኙ ተወዳዳሪዎች ለእያንዳንዳቸው 50ሺ ብር፤ 25ሺህ ብርና 1ሺ 500 ብር ሽልማት እንደተዘጋጀ ታውቋል፡፡ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚዘጋጀው ኮካ ኮላ ተከታታይ የጎዳና ላይ ሩጫ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ ሲካሄድ ለየት የሚያደርገው ሶስቱን ዙር ለሚሮጡ የጤና ስፖርተኞች የሚሸለመው ፕሮፌሽናል የመሮጫ ሰዓት እና ኮርፖሬት ቻሌንጅ በሚል ዘርፍ በለቡድን ሯጮች የተዘጋጀው አዲስ የውድድር አይነት እና ሽልማት ነው፡፡ ከዋናው የአትሌቶች ውድድር ጋር በኮካ ኮላ ተከታታይ የጎዳና ላይ ሩጫ ላይ ከ4ሺ በላይ የጤና ስፖርተኞች የተሳተፉ ሲሆን ነገ በሶስቱም ውድድር ለተሳተፉት ለእያንዳንዳቸው ፕሮፌሽናል የመሮጫ ሽልማት ተዘጋጅቷል፡፡ በኮርፖሬት ቻሌንጅ እያንዳንዳቸው 10 ስፖርተኞች በማስመዝገብ በቡድን ለሚወዳደሩት በተዘጋጀው ሽልማት ደግሞ ለአንደኛው ሙሉ የአዲዳስ ትጥቅ፤ ለሁለተኛው የአዲዳስ ሙሉ ትጥቅ ያለጫማ እንዲሁም ለሶስተኛ ደረጃ የሁለት ወር የጂም አገልግሎት ክፍያ እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር..መሑሀ

አዲሱ አመት ..2007.. ዓ/ም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም ፣የጤናና የብልጽግና እንዲሆን ይመኛል፡፡
የዘመን መለወጫን ምክንያት በማድረግ ከእለቱ ጋር የነበረ ገጠመኝ ልናስነብባችሁ ወደድን፡፡ በመሆኑም ተከታዩን እነሆ ለንባብ ፡፡
.....ነገሩ ያጋጠመኝ በ2006 ዓ/ም መግቢያ ጳጉሜ 4/2005 ነው፡፡ እኔ በእድሜዬ ገና ሰላሳው የገባሁ ስሆን እዩኝ እዩኝ የምል .....መሬቱን ሲረግጠው ድንጋዩ ይፈነቀላል የምባል እይነት ነኝ፡፡.. ታድያ ...አለባበሴን አሳምሬ በአዲስ ዘመን ዋዜማ ነበር ወደ ከተማው ብቅ ያልኩት፡፡ እኔ ወንደላጤ ነኝ፡፡ ቤተሰብ እንዳለው ሰው በግ ወይንም ዶሮ ከሚሸጥበት ሳይሆን ያመራሁት ወደ ልብስ ተራው ነበር፡፡ ብዙም ባይሆንም በመጠኑ ደመወዜ እንደልብ የሚያንቀሳቅሰኝ ነበር፡፡ ከአንድ ኃብታም ድርጅት ውስጥ በአስተዳደ ሩም ፣በእቃ ግዢነቱም ፣በጠቅላላ አገልግሎትነቱም ፣ባለጉዳይ በማነጋገሩም ፣ በመወ ሰኑም ፣በማስወሰኑም...ብቻ ሰውየው ሌላ ሰው መቅጠር ስለማይፈልጉ እኔን ብቻ ከላይ ከታች ስለሚያመላልሱ...እኔም ታድያ ደህና አድርጌ ነበር የተጠቀ ምኩበት፡፡ አሁን ግን አንድ ወር ሆኖኛል ስራዬን ከለወጥኩ.....
ወደ ዘመን መለወጫው ገጠመኝ ልመለስና የ2006/መግቢያ የልብስ ገበያ በዋጋው ብዙም የሚታማ አልነበረም፡፡ ታድያ እየዞርኩኝ ጫማ ስመለከት አንዲት ኮረዳ በድንገት ገጠመችኝ፡፡
... ያነሳሁትን ጫማ እጄ ላይ አይታ...እውይ ባባትህ ...ያምራል ...ብትለካውስ? አለችኝ፡፡
...እኔም ቀና ብዬ ስመለከታት የሆነች ቆንጆ ልጅ ናት፡፡ መለስ አድርጌም...ምን ያረጋል ቢያምር... የወደድሽው አንቺ እንጂ ...ስላት...ታድያ እኔ ከወደድኩልህ መች አነሰህ? አንተ ደግሞ ጉረኛ ነህ መሰለኝ...ብላ ከት ብላ ሳቀች፡፡ አ.አ.ይ እኔ እንኩዋን ጉረኛ አይደለሁም፡፡ ግን እውነ..ን ነውኮ ...ሌሎች አያምርም ቢሉኝስ...ዋጋው ደግሞ ውድ ነው አልኩዋት፡፡
...እንገግዲህ...አለችኝና ትታኝ ወጣች፡፡ እኔ ግን አብሮአት ልቤ ሸፈተ፡፡ ጫማውን መግዛቱን ትቼ እሱዋን ተከተልኩዋት፡፡
..እኔ የምልሽ...
- ምንድነው የምትለኝ...
..የአዲስ አበባ ልጅ ነሽ?...
ከት ብላ ሳቀች፡፡ ምነው? አልኩዋት
- እንጃ...ጥያቄህ አስቆኝ ነዋ...መልሱዋ ነበር፡፡
..ምን ያስቃል...ሁኔታሽ...ንግግርሽ...ሁሉ ደስ ብሎኝ ነውኮ...
- ከአዲስ አበባ ውጭ ያለ ሰው እንደእኔ አይናገርም? አለችኝና ወዲያው
በማስከተል ...ዋናው ነገር... ጫማውን ገዛኸው? አለችኝ፡፡
..አንቺ ትተሸኝ ስትሄጂ ተውኩት...
- ለምን?
..እንዳታመልጪኝ... ልከተልሽ ...ብዬ ነዋ...
- በል ...ና እንሂድና መጀመሪያ ጫማውን ግዛና ከዚያ በሁዋላ እናወራለን...አለችኝ፡፡
በዚህ መልክ ነበር የእኔና የሜላት ግንኙነት የተጀመረው፡፡ ከዚያም ለአንድ ሶስት ወር ገደማ ሻይ ቡና እየተባባልን ቆየን፡፡ ሜላት በጣም ጨዋ ልጅ ነች፡፡ የሰው ገንዘብ በፍጹም አትፈልግም፡፡ አንድ ነገር ላድርግልሽ ስላት ፍጹም ፍቃደኛ አይደለችም፡፡ ለምንበላው ምግብ እንኩዋን ቢያንስ ሻይ ቡናውን ካልቻለች አይመቻትም፡፡ በቃ ...ለትዳር ጉዋደኛ የምትሆነኝ ልጅ አገኘሁ...የእንቁጣጣሽ ስጦታዬ ነች ብዬ አሰብኩ፡፡ ለእናት እና አባ.. ሁኔታውን አጫወትኩዋ ቸው፡፡ ቤተሰቤ በሙሉ ተደሰተ፡፡ መቼ ነው ታድያ ሽማግሌ የምንልከው የሚለው ጭቅጭቅ ከቤተሰቤ እያየለ ሲመጣ እስቲ ቆይ... ከእርሱዋ ጋር እኮ ገና አላወራነውም...እኔ የእራሴን ፍላጎትና ግምት ነው የነገርኩዋችሁ...አልኩዋቸው፡፡
...አንድ እሁድ እኔና ሜላት ለምሳ ቀጠሮ ያዝን፡፡ አብረን እየተመገብን እያለን...ላጎርሳት ስሞክር ...አአይ...አለችና ፊቷ ቅጭም አለ፡፡
..ምነው?...የእኔ ጥያቄ ነበር...
- አአይ...እኔ ጉርሻ አልወድም...
..ለምን?
- አባ..ን ስለሚያስታውሰኝ...ሰው ሲያጎርሰኝ አልወድም...
ለካንስ አባትዋ ሞተዋል፡፡ አዘንኩኝ፡፡ እንደገና ሀሳቤን ሰብሰብ አደረግሁና...
..አኔ የምልሽ...
- እህ...
..ለምን... እ.....ስላት... ገና ሀሳቤን ሳልቋጭ...
-ገብቶኛል ልትለው የፈለግኸው ነገር ገ ብ ቶ ኛ ል... አለችኝ፡፡
.. ታድያ ...ምን ችግር አለው?
-ምንም ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን እኔ እነግርሀለሁ፡፡ አለችኝ፡፡
የዚያን እለት በዚሁ ተለያየን፡፡ ከዚያ በሁዋላ ስልክ ብደውል ...ቀድሞ ሳገኛት የነበረበት ካፊ..ሪያ እና ምግብ ቤት ብሔድ...ማንም...ምንም መረጃ ሊሰጠኝ አልቻለም፡፡ አጣሁዋት፡፡ግራ ተጋባሁ፡፡ በጣም ፈለግሁ ዋት...አላገኘሁዋትም፡፡ ጉዋደኛዋን ቤተሰብዋን...ማንንም አላውቅም፡፡ ታመምኩ ፡፡ አድራሻ አልሰጠችኝም፡፡ የት ነው የምትሰሪው ስላት በግልዋ እየተዟዟረች እንደም ትሰራ ነው የነገረችኝ፡፡ እንዲሁ ...ስጨነቅ... ስጨነቅ... ግንቦት 15/2006 /አንድ መልእክት ደረሰኝ፡፡ እንዲህ ይላል...
.....በድንገት ገበያ ላይ የገኘሁህ ወድ ጉዋደኛዬ...እንደምን ሰነበትክ፡፡ ድንገት ስለጠፋሁብህ በመጠኑም ቢሆን እንደጎዳሁህ ይሰማኛል፡፡ ስሜትህን እንዳልጎዳ ብዬ እንጂ እኔ ሚስት ለመሆን ቀርቶ ከወንድ ጋር እንኩዋን ለመገናኘት ገና በሕክምና የማስተካክለው የጤና ጉዳይ ስለነበረኝ አልደፍርም ነበር፡፡ በቤተሰብ አባል ተደፍሬ ...በድብቅ ...በህገ ወጥ መንገድ ጽንስ በማቋረጥ ምክንያት ማህጸኔ ተጎድቶ ስለነበር ለሕክምና ወደ ሆስፒታል መግባት ነበረብኝ፡፡ የመጨ ረሻ ምሳ የበላን ማግስት ነበር ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የገ ባሁት፡፡ ያንን የምሳ ቀጠሮ ብመለስም ባልመለስም ብዬ ሆን ብዬ ነበር ያመቻቸሁት፡፡ አሁን ሕክምናዬን ጨርሼ እቤ.. ገብቻለሁ፡፡ ከፈለግህ ጠይቀኝ፡፡ ላለፈው ይቅርታ አድር ግልኝ፡፡ አሁን እግዚአብሔር ይመስገን ጤነኛ ነኝ፡፡..... ይላል ...በመልእክተኛ የመጣው ደብዳቤ፡፡
እጅግ በጣም ነበር ያዘንኩትም ...የተደሰትኩትም፡፡ ታማ ሆስፒታል በነበረችበት ወቅት ከጎኗ ብሁን ኖሮ እወድ ነበር፡፡ ነገር ግን ያንን እድል አልሰጠችኝምና አዘንኩ፡፡ በሌላ በኩል... ከሕመሙዋ ድና በመውጣቷ ደግሞ በጣም ተደሰትኩ፡፡ ለማንኛውም ሁኔታዋን ለማየት በሰ ጠችኝ አድራሻ ከቤትዋ ሄጄ አገኘሁዋት፡፡ ተቃቅፈን ተላቀስን፡፡ ለካንስ እርሱዋም ወድዳኝ ነበር፡፡ ጭራሽ ፍቅሬ በረታ፡፡ በእቅፍዋ ስር እንድሆን...በእቅፌ ስር እንድትሆን ሁለታችንም ወደድን፡፡
እነሆ...በተገናኘን በአንድ አመታችን...ዛሬ መስከረም 3/2007 ዓ/ም ሰርጋችን ነው፡፡
.....ደስ ብሎናል ...ደስ ይበላችሁ....
ይስሐቅ ብርሐኔ/ከአዲስ አበባ/መሳለሚያ

Published in ላንተና ላንቺ

የሰቆጣ ተወላጁ አቶ ጌጡ ብርሃኑ ወደ ንግድ ስራ የገቡት በ30 ብር ነወ፡፡ ለዓመታት ብዙ ችግርና መከራ አሳልፈዋል፡፡ ዛሬ ከወንድማቸው ጋር 3ሚሊዮን ብር የፈጀ ባለ3 ኮከብ ሆቴል ገንብተዋል፡፡ ሆቴሉ ለሳቸው ብቻ ሳይሆን መብራትና መንገድ፣ ውሃና ስልክ ለሌላት ሰቆጣም እንደተስፋ ነፀብራቅ ነው የታየው፡፡ የሻደይ በዓልን ለማክበር ዘንድሮ ወደ ሰቆጣ የተሻገሩ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ያረፉት ዲጂ በተባለው የእነ አቶ ጌጡ ሆቴል ነበር፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ሰቆጣ ለሥራ በሄደችበት ወቅት አቶ ጌጡን በንግድ ተመክሮዋቸውና በከተማዋ እንቅስቃሴ ዙሪያ አነጋግራቸው ነበር፡፡ እነሆ፡-


ተወልጄ ያደግሁት በሰቆጣ ከተማ ቀበሌ 04 ነው፡፡ የዚህ ከተማ ሰው ከትንሽ ነገር ተነስቶ ነው ትልቅ ደረጃ የሚደርሰው… ለዚህ ደረጃ ከመብቃቴ በፊት ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፌያለሁ፡፡ ይህን ሆቴል የማስተዳድረው ብቻዬን ሳይሆን ከወንድሜ ጋር ነው፡፡
አካባቢው የቱሪስት መስህብ ቢሆንም በቂና ጥራቱን የጠበቀ የሆቴል አገልግሎት የለም…
ቀደም ሲል እንግዶች ወደ ሰቆጣ ሲመጡ ዘመድ ቤት ነበር የሚያድሩት፡፡ ዘመድ የሌለው ደሞ ቤት ተፈልጎ ወይም ትምህርት ቤትና በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ያድር ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ሁሉም የበኩሉን ጥረት በማድረጉ፣ በዓሉ በጥሩ ሁኔታ ተከብሯል፡፡ ችግሩ በከፊል የተቃለለ ይመስለኛል፡፡
ሰቆጣ ወደኋላ የቀረችበት ምክንያት ምንድን ነው?
አካባቢው በጦርነት ውስጥ የነበረ ነው፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት አልነበረውም፡፡ ጥሩ ሆቴሎችም አይታዩም ነበር፡፡ ወደ ኮረም ስንሄድ መቶ ኪሎ ሜትር በእግር ነበር የምንጓዘው፡፡
አሁንም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ችግሩ አልተፋታም፤ ህዝቡ ሁለትና ሶስት ቀን ትራንስፖርት እየጠበቀ ነው የሚሄደው፡፡ በፈለገውና ባሰበው ሰዓት መጓዝ አይችልም፡፡ መኪኖቹም ወደዚህ መምጣት አይፈልጉም፡፡ አስፓልት አስፓልቱን ነው መስራት የሚመርጡት፡፡ መንገዱ በቶሎ መሰራት አለበት፡፡
ሆቴል የተገነባበት ስፍራ በፊት ምን ነበረ?
ሆቴል የቀለስኩበት ስፍራ በረሃ ነበር፤ ሰው አይኖርበትም፤ ከተማ ቢሆንም እኛ እዚህ አንኖርም ነበር፤ ዋሻ ነው የምንውለው፤ ማታ ነበር ልንተኛ የምንመጣው፡፡ ማንም ሰው በቀን መገበያየት ስለማይችል ቀን ቀን ስፍራው ምድረበዳ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ከተማዋ አስራ አንድ ጊዜ በአውሮፕላን ተደብድባለች፡፡ ጎረቤቶቻችን በአውሮፕላን ድብደባው መሞታቸውን አስታውሳለሁ፡፡
እንዲህ ያለ ለውጥ ይመጣል፤ ብሎ ያሰበ አልነበረም፡፡ በእርግጥ ትግል ይካሄድ ነበረ፤ ታጋዮቹ ይታገላሉ፤ እኛ ግን ብዙም ተስፋ አልነበረንም፡፡ ይሄ ሆቴል ተሰርቶ፣ መንገድ ተከፍቶ ሌላው የደረሰበት እንደርሳለን ብዬ አስቤም አልሜም አላውቅም፡፡ ግን ደረስን፤ ያ ወቅት ዘግናኝ ነበር፡፡ ሰው በደቂቃ ውስጥ ወደ ሬሳ የሚቀየርበት ጊዜ ነበር፡፡ አውሮፕላን ከሰማይ ላይ የሚጥለው አምስት ኩንታል ክብደት ያለው ፈንጂ ነው፡፡ አንድ ጊዜ አስታውሳለሁ የ19 ዓመት ወጣት ነበርኩ፡፡ አውሮፕላኑ የጣለው ናፓል የሚባል ፈንጂ ነበር፡፡ ህዝቡን ጨፈጨፉት … ያ ወቅት አልፏል እንጂ ሰቅጣጭ ነበር፡፡
ስለንግድ አጀማመርዎ አጫውቱኝ?
ከበለሳ ሀሙሲት ወጥቼ በባለ ሀያ ሊትር ጀሪካን ናፍጣ ገዛሁ፡፡ በለሳም ገበያቸው ማታ ነበር፡፡ እኔ አላወቅሁም ነበር፤ ለካስ ጀሪካኑ ተቀዶ በማስቲካ አያይዘው ነበር የሸጡልኝ፡፡ ትንሽ እንደተጓዝኩ ማስቲካው ለቀቀና ናፍጣው መፍሰስ ጀመረ፡፡ ይታይሽ ሁለት መቶ ሃምሳ ብር ነው የገዛሁት፡፡ ትክክለኛ ዋጋው ግን 220 ብር ነበር፡፡ ደሞ ብቻዬን አልነበረም፤ ትርፍ የጋራ ብለን ከሌላ ሰው ጋር ገንዘብ አጋጭቼ ነው፡፡ ጀሪካኑ በትከሻዬ ላይ ተሸክሜ የ5 ሰዓት መንገድ ተጉዤ ተከዜ ገባሁ፡፡ ተከዜ ለም አፈር አለ… አፈሩን አድርጌበት፤ በነጭ ላስቲክ ስጓዝ፣ ሰቆጣ ለመድረስ የ4 ሰዓት መንገድ ሲቀረኝ ማፍሰስ ጀመረ፡፡ ሲያልፍ እንዲህ ይወራል እንጂ በሰዓቱ እያለቀስኩ ነበር፤ ልከስር ነው ብዬ ፈርቼ ማለት ነው፡፡ ግን እንደማይደረስ የለም፤ በአራተኛ ቀኔ እየተሳብኩ ደረስኩ፡፡ ያሰብኩትን ሰላሳ ብር ባላተርፍም በዋናው ተሸጠና ከእዳ ተረፍኩ፡፡
በንግድ እንቅስቃሴ ከታጋዮች ጋር የምትገናኙበት ወቅት ነበር?
አዎ፡፡ ስኳር እወሰድላቸው፣ ፓንት እሸጥላቸው ነበር፡፡ ለ2ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ 32 ኩንታል መኮረኒ አምጥቼላቸዋለሁ፡፡ ጉባኤው የተካሄደበት አለውቅ የሚባል ወንዝ አለ፤ እዚያ ድረስ አቅርቤላቸዋለሁ፡፡ ቲሸርት ነበረች የታጋዮች … አሁን ያቺን ቲሸርት የት አየኋት? አርቲስት ጎሳዬ ተስፋዬ ለብሷት! ያቺ ቲሸርት ለዚህ ድርጅት ባለውለታ ናት፡፡ አንድ ፓንትም ነበረች፤ ባለዚፕ፡፡ እስከ 2ሺ ብር ትይዛለች፡፡ እሷን ሁሉ እሸጥላቸው ነበር፡፡ እኛ እራሱ ገንዘባችንን ሽፍታ እንዳይወስድብን ደብቀን የምንይዘው በፓንቱ ውስጥ ነበር፡፡ እነሱ እና እኛ ምንም ልዩነት አልነበረንም፡፡ ለንግድ ስንቀሳቀስ ደብዳቤ ሁሉ አደርስላቸው ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ደግሞ በጋማ ከብት ሸቀጣችንን ይዘን ስንጓዝ፣ ዛምራ የተባለ ቦታ ላይ ጎርፍ ያዘን፡፡ ሶስት ሆነን መሸጋገር ስላልቻልን ቢያልፍለት ብለን አደርን፤ ጠዋት ላይ ጎደለ ብለን ስንገባ አንደኛው ጓደኛችንን እስከ አህያ ጭነቱ ጠርጎ ወሰደው… ልጁን አተረፍነው፤ ሸቀጡ ተበላ፡፡
ግን ዞኑ ለትግሉ እንዳበረከተው አስተዋጽኦ ምንም የልማት ስራ አልተሰራለትም፡፡ አሁን እኮ በየቦታው ወረዳ ውስጥ እንኳን አስፓልት ነጥፏል፡፡ እያንዳንዱ ቤተሰብ ኮሎኔልና ጄነራል ደረጃ የደረሱ ታጋዮች ያሉበት ነው … በየቤተሰቡ በትግሉ የተሰዋ አለ፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊነታችን ለእኛም ተገቢው ሁሉ ሊደረግልን ይገባል፡፡
የሆቴሉ የንግድ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
አሁን ይሄ ሆቴል ተሰርቷል፡፡ ነገር ግን ሰው ካልመጣ፣ ተጠቃሚ ካልተገኘ መዘጋቱ ነው፡፡ ቀድሞ እስከ 3 መቶ ኪሎ ሜትር በእግራችን እየተጓዝን ነበር ንግድ የምናጧጡፋው፡፡ መንገድ ሲሰለቸኝ በ500 ብር ኪዮስክ ከፈትኩ፡፡ ሳሙና፣ ኦሞ… አምጥቼ ደረደርኩ… ደሴ እየተጓዝኩ ሸቀጦችን ማምጣት ጀመርኩ፡፡ ኢህአዴግ ደርግን ጥሎ ሥልጣን ሲይዝ በእግር መሄድ አቆምን፡፡ መኪና ላይ እንደ እቃ ተጭነን፣ ከኮረም ሰቆጣ ለመድረስ አንድ ቀን ነበር የሚፈጅብን - መቶ ኪሎ ሜትር፡፡ ኮረም መኪና ለማግኘት አራትና ሶስት ቀን እንጠብቃለን … ሱቋ እያደገች መጣች፤ ወደ 3ሺ ብር አገኘሁ፡፡ በ1987 ዓ.ም ሱቅ እየሰራሁ ሳለ መንግስት የግንባታ ሥራዎችን ጀመረ፡፡ እኔም የቀበሌ ሽንት ቤቶች … ግንባታ ላይ መሳተፍ ያዝኩ፡፡
ግንባታ ላይ ሰርተው ያውቁ ነበር?
በድፍረት ነው የገባሁት፡፡ ከወንድሜ ጋር ሆነንም የት/ቤቶችን ግንባታ በኮንትራት በመውሰድ መስራት ጀመርን፡፡ ከዚያ ብሩ ተጠራቀመ… ይሄን ሁሉ ስንሰራ የአንድ ቀን መንገድ በጋማ ከብት ተጉዘን ብረትና ሲሚንቶ እየጫንን ነው፡፡ ባህር ዛፍ የምንጭነው በሰው ደንደስ ነበር፡፡ ወደ አራት ት/ቤቶች በዚህ ሁኔታ ነው የሰራነው፡፡ ቢሮዎችን፣ መጋዘኖችንና ኮንደሚኒየሞችንም እንገነባ ጀመርን፡፡
በአንዴ ከበራችሁ በሉኛ?
ገንዘብ አጠራቀምና በ130ሺ ብር ኤኒትሬ ገዛን፡፡ እድገታችን እየጨመረ መጣ፤ ቆየት ብለን አንድ ፒካፕ ላንድ ክሩዘር ጨመርን፤ ኮንስትራክሽን ዘርፍ ደረጃ ስድስት ገባን፡፡ ይሄኔ ዶዘር ከቀረጥ ነፃ አስገባንና ሥራችንን ገፋንበት፡፡ በመቀጠልም ሁለት ገልባጮች፣ ፒካፕ፣ ኤሮትራከር፣ ወደ ሶስት መኪኖች ባለቤት ሆንን፡፡ ከዚያ ቁጭ ብለን ከወንድሜ ጋር በመመካከ፣ ሰቆጣ ምንድነው የሚያስፈልጋት ብለን አጠናን፡፡ ሆቴል መሆኑን ተረድተን፣ ቦታ ጠየቅንና የከተማ አስተዳደሩ መሬት ሰጠን፡፡ ሆቴሉን ገነባን፡፡
እንዴት ነው ቱሪስቶች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል?
እስካሁን ሆቴሎች የላችሁም በሚል ምንም እንቅስቃሴ አልነበረም፡፡ ስብሰባዎች አልተለመዱም፡፡ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እኮ ከ2ሺ በላይ የውጭ አገር ቱሪስቶች በዚህ በኩል ያልፋሉ፡፡ ሆኖም እዚህ ማረፊያ የለም ስለሚባል አይቆሙም፡፡ መስቀለ ክርስቶስ ከሰቆጣ ከተማ በ5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው ያለው፡፡ ያንን ለማስጐብኘት እንኳ ቱሪዝም በቱሪስት ጋይዱ ላይ አላካተተውም፡፡ ይሄ ሁሉ ሆቴል የላቸውም በሚል ነው፡፡ ይሄን ሆቴል ስንጨርስ የቱሪዝም ጋይዱ ላይ ያስገቡልናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ መንገዱ ተሰርቶ አስፓልት ከሆነልን በእርግጠኛነት የመለወጥ ተስፋ አለን፡፡
የሆቴል ግንባታው ምን ያህል ፈጀ?
3 ሚሊዮን ብር ገደማ ጨርሷል፡፡ 47 ደረጃቸውን የጠበቁ የመኝታ ክፍሎች አሉት፡፡ የ20 ዓመት ድካምና ልፋት ውጤት ነው፡፡ ከ30 ብር ተነስተን ባለ 3 ሚሊዮን ብር ካፒታል ሆነናል፡፡
የሆቴሉ ደረጃ ባለስንት ኮከብ ሊባል ይችላል?
ስንጨርስ 3 ኮከብ ይሰጡናል፡፡ ፓርኪንግ አለው፤ ወደ 2 መቶ ሰው የሚይዝ አዳራሽ እየገነባን ነው፡፡ የአካባቢው ችግር ውሃ ነው .. ውሃ ቢኖረን ፕላኑ ላይ የመዋኛ ገንዳ አለው፡፡ የአልጋዎቻችን ኪራይ ከመቶ ሃያ እስከ ሁለት መቶ ሃምሳ ብር ነው ፡፡
የወደፊት ዕቅድዎ ምንድነው?
አሁን ወደ ዱባይ ለመሄድ እየተዘጋጀሁ ነው፤ ለሆቴሉ የሚያስፈልጉ እቃዎች ለመጫን፡፡ ወደፊት በሆቴልና በቱሪዝም ዘርፍ ስራችንን ለማስፋፋት የሌላ አገር ተሞክሮን ማየት እፈልጋለሁ፡፡
ቤተሰብ መስርተዋል?
አገው ቤተሰብ ለመመስረት ችግር የለበትም፤ የስድስት ልጆች አባት ነኝ፡፡ እንግዲህ እድሜዬ ወደ አርባ ሶስት ዓመት እየተጠጋ ነው፡፡ ብዙ ስራዎችን የሰራሁት ከወንድሜ ጋር ነው፡፡ አዲስ የተከፈተው ሆቴላችን DG ይባላል፡፡ ደሳለኝና ጌጡ ለማለት ነው፡፡ አሁን እቅዳችን የተሻለ ሆቴል መስራትና ፋብሪካዎችን መገንባት ነው፡፡

“ለእያንዳንዱ በሽታ መድኀኒት አለው”

        ጂዎፈሪ ቻውሰር የተባለው ፀሐፊ “General Prologue” በተባለው መፅሀፉ አራት የሙስሊም አረብ ስሞችን ይጠቅሳል - ኢብን ኢሳ፣ ራዚ፣ ኢብን ሲና እና ኢብን ረሽድ ናቸው፡፡ እነኚህ ሰዎች በመጽሃፉ ውስጥ የተጠቀሱት ከረዥም ዓመታት በፊት ለዓለም የህክምና ዘርፍ ባበረከቱት ታላቅ አስተዋጽኦ ነው፡፡ ከ8ኛው - 11ኛው ክፍለ ዘመን የአረብ የህክምና ባለሙያዎች ለዛሬው የአውሮፓውያን የሕክምና ጥበብ መሰረት እንደጣሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የሮማውያን ግዛት በ15ኛው ክፍለ ዘመን መገርሰሱን ተከትሎ አውሮፓ በብዙ ዘርፍ የነበሯትን የእውቀት ሀብት አጥታለች፡፡ በተለይም የግሪካውያን ሳይንስና የቦይታስ የሒሳብና ሎጂክ ጥበቦች በኢንሳይክሎፒዲያ ውስጥ ከመስፈር ውጭ ጥቅም ላይ የሚያውላቸው አላገኙም ነበር፡፡ የአውሮፓ የሃይማኖት አዋቂዎች እኒህን ጥበቦች አግኝተው የሚያስፋፉበትና አዲስ ነገር የሚፈጥሩበት እድል አልነበራቸውም፡፡ በዚህም የተነሳ የአውሮፓ አዲሱ አለም ከህክምና ጥበብ ጋር ተፋታ፡፡
በጊዜው የነበረው የቤተክርስቲያን አመለካከት፣ ከአካላዊ ህክምናዎች ይልቅ መንፈሳዊ ፈውሶች ላይ ያተኩራል፡፡ መድኃኒቶችን መውሰድና አካላዊ ንፅህናን መጠበቅ ተቀባይነት ያልነበራቸው ሲሆን በድን ለሚሆን አካል አለመጨነቅ እንደ ፅድቅ ይቆጠር ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት መላ አውሮፓውያን በሽታን መግታትም ሆነ መከላከል እንደማይቻል ያስቡ ነበር፡፡ ይባስ ብሎ በ7ኛው ክፍለ ዘመን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቀዶ ጥገና “የሰዎችን መንፈስ ያበላሻል” በሚል ሙሉ ለሙሉ ከለከለች፡፡ የአውሮፓ የቀዶ ጥገና ሳይንስም በዚሁ አከተመ፡፡ በተመሳሳይ ዘመን በምስራቅ በኩል የእስልምና ስልጣኔ ብቅ አለ፡፡ እስልምና ድንበሩን በማስፋፋት ብዙ ሀገሮችን መቆጣጠር ቻለ፡፡ ከዚህ መስፋፋት ጎን ለጎን በብዙ ዘርፎች እውቀቶች እና ትምህርቶች መዳበር ጀመሩ፡፡ እስልምናና የቁርዓን ቋንቋ የሆነው አረብኛ አለማቀፋዊ እየሆኑ መጡ፡፡ ላቲንና ግሪክ በምዕራቡ ዓለም እንደነገሱት ሁሉ የአረብኛ ቋንቋም የምስራቁን ክፍል በሰፊው ተቆጣጠረው፡፡ አረብኛ የሥነ-ፅሁፍ፣ የሳይንስና የምሁራን አንደበት በመሆን እውቅናን አገኘ፡፡
ከዚህ በኋላ ነበር የግሪኮች የሕክምና ሳይንስ በሙስሊም ምሁራን መጠናት የጀመረው፡፡ በ636 ዓ.ም ፐርሺያ በሙስሊሞች እጅ ስር የወደቀች ሲሆን የአረብ አስተዳዳሪዎች ለፐርሺያው ጁንዲሻፑር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የህክምና ምርምር ድጋፍ ማድረግን ሥራዬ ብለው ያዙት፡፡ ሙስሊም ምሁራኖች በዚህ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከሒፖክራተስ፣ ጋላንና ሌሎች የግሪክ የህክምና ስራዎች ጋር በቅጡ እየተዋወቁ መጡ፡፡ ከዚህም ባሻገር የባዛንታይን፣ ፐርሺያ፣ ህንድና ቻይና የህክምና እውቀቶችንም መፈልፈል ያዙ፡፡ በዚህ ምክንያት ጁንዲሻፑር ዩኒቨርስቲ ለሙስሊሙ ዓለም ለ200 ዓመት የዘለቀ ታላቅ የህክምና ምርምር ማዕከል ለመሆን በቅቷል፡
በ9ኛው ክፍለ ዘመን በስፋት የተከናወነው የአውሮፓውያንን የህክምና እውቀቶች የመተርጎም ስራ፣ ለአረቦች የህክምና ጥበብ ሁነኛ መሰረት ጥሏል፡፡ ከህክምና መፅሃፍት ትርጉም ጎን ለጎን የሆስፒታሎች ግንባታ የተከናወነ ሲሆን የመጀመሪያው ሆስፒታልም በ805 በባግዳድ ነበር የተቋቋመው፡፡ በሁለት አስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥም በመላው የእስልምና ግዛት 34 የሚደርሱ ሌሎች ሆስፒታሎች ተከፈቱ፡፡ ቁጥራቸውም ከዓመት ዓመት እየተበራከተ ሄደ፡፡
ሆስፒታሎች ለበሽተኞች ህክምና ከመስጠት ባሻገር ምርምር የሚካሄድባቸውና የህክምና እውቀቶች የሚስፋፉባቸው ሆኑ፡፡ የህክምና ት/ቤቶችና ቤተ መፃህፍቶችም ጎን ለጎን መቋቋም ጀመሩ፡፡ በ11ኛው ክፍለ ዘመን ላይም ተንቀሳቃሽ ክሊኒኮች ስራ የጀመሩ ሲሆን ፋርማሲዎችም ሊስፋፉ ችለዋል፡፡ ይህም የአረቡን ዓለም የህክምና እድገት እያጠናከረው መጣ፡፡
ነቢዩ መሃመድ (ሰዐወ) “ለእያንዳንዱ በሽታ መድኀኒት አለው” ባሉት መሰረት፣ ሙስሊም የህክምና ተመራማሪዎች፣ እውቀታቸውን ከጥረታቸው ጋር በማጣመር ከፍተኛ የህክምና አብዮት በአረቡ አለም አካሄዱ፡፡ በ9ኛው ክፍለ ዘመን ላይ መድሀኒቶችን የሚያመርትና የሚያሰራጭ መደብር በባግዳድ የተከፈተ ሲሆን የመጀመሪያው የህክምና ስራም አል-ራዚ በተባለ ባለሙያ ተጀመረ፡፡
አል-ራዚ
አል-ራዚ በምዕራባውያን ዘንድ ራሐዚስ በሚል ስም ይታወቃል፡፡ ከቴህራን አቅራቢያ በምትገኘው ራይ የተባለች የፐርሺያ ከተማ ነው የተወለደው፡፡ ወጣትነቱን በሙዚቀኛነት፣ በሒሳብና በኬሚስትሪ ሙያ ካሳለፈ በኋላ ወደ ባግዳድ በመሔድ በ40 ዓመቱ ህክምናን ማጥናት ጀመረ፡፡ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ራይ ከተማ ተመልሶ፣ በሆስፒታል ውስጥ የአመራር ቦታ ተሰጠው፡፡ ከዚያም ባግዳድ ውስጥ በተገነባው አዲስ ሆስፒታል በዳይሬክተርነት ተሾመ፡፡
አል-ራዚ በአረብ ህክምና ውስጥ በፈርቀዳጅነቱ የሚታወቅ ሲሆን 237 መፃህፍቶችንም ጽፏል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በህክምና ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡ በህፃናት በሽታ ህክምና ላይ የጻፈው መጽሃፉ “የህፃናት ህክምና አባት” አሰኝቶታል፡፡ ንፍጥ የሚያበዛ ጉንፋንና መንስኤውን ተመራምሮ ያገኘ የመጀመሪያው ባለሙያ ነው፡፡ የኩላሊት ጠጠር ላይ ያካሄደው ጥናትም እስካሁን ድረስ ይጠቀስለታል፡፡
አል-ራዚ ከባግዳድ ወደ ትውልድ ቀዬው ራይ በመመለስ፣ በተለያዩ ሆስፒታሎች ውስጥ የፈውስ ጥበቦችን አስተምሯል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እውቅናን ያገኘበትን “አል-ኪታብ አል-ማንሱሪ” የተሰኘ መጽሃፍ በ10 ተከታታይ ክፍሎች አቅርቧል፡፡ በዚህ ሥራው የተለያዩ የህክምና ቀመሮችንና ትርጉሞችን እንዲሁም ምግቦችና መድኀኒቶች በሰው ልጅ አካል ውስጥ የሚፈጥሩትን ተፅእኖ አሳይቷል፡፡ በጣም ገናና ስራው ግን “አል-ኪታብ አል-ሀዊ” በሚል በ25 ክፍሎች ያሰናዳው የህክምና ኢንሳይክሎፒዲያ ነው፡፡ አል-ራዚ ህይወቱን ሙሉ ለህክምና የሚሆኑ መረጃዎችን በማሰባሰብ በወቅቱ ለነበረው የህክምና ሙያ ማጠቃለያ መስጠት የቻለ ድንቅ የህክምና ሰው ነው፡፡ ብዙ በሽተኞችን በህክምና ጥበቡ በመፈወስም ስኬት አስመዝግቧል፡፡ ሀኪሞች እንዴት በሽተኞችን በፈጣን ሁኔታ ማከም እንደሚችሉም አሳይቷል፡፡ ከአል-ራዚ ህልፈት በኋላ የተተካው አል-ሁሴይን ኢብን አብደላህ ኢብን ሲና (980-1037) ሲሆን በአውሮፓውያንና በላቲኖች ዘንድ አቪሲና በመባል ይታወቃል፡፡
አቪሲና
አል-ሁሴን ኢብን አብደላ ኢብን ሲና (980-1037) ወይም አቪሲና የተወለደው አሁን ኡዝቤክስታን፣ ቀድሞ ቡካራ በምትባለው ጥንታዊቷ የፐርሺያ ከተማ ነው፡፡ አርስቶትል የግሪካውያን፣ ገተ የጀርመናውያን እንደሆኑት ሁሉ አቪሲናም የአረቦች እንቁ ነው ሊባል ይችላል፡፡ የአቪሲና እውቀት በህክምና ጥበብ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ በፍልስፍና፣ በሳይንስ፣ በሙዚቃ፣ በግጥምና በእደጥበብ እውቀቱም የመጠቀ ነበር፡፡ በመላው አውሮፓ አሁንም ድረስ “የሐኪሞች ልዑል” በሚል ቅጽል ስሙ ይታወቃል፡፡
ከግብር ሰብሳቢ አባቱ የተወለደው አቪሲና፤ በአስር ዓመቱ ሁሉንም የቁርዓን አንቀፅ ሸምድዶ ሀፊዝ ለመሆን ቻለ፡፡ ከዚያም ህግ፣ ሒሳብ፣ ፊዚክስና ፍልስፍና ተማረ፡፡ በ16 ዓመቱ ወደ ሕክምና ጥናት ገባ፡፡ በ18 ዓመቱም የሳማኒድ ልዑል የነበረውን ኑህ ኢብን መንሱርን በማከም ታዋቂ ዶክተር ሊሆን ቻለ፡፡ ይሄም በቡካራ ታዋቂ በነበረው የንጉሳዊያን ቤተ-መጽሐፍት ገብቶ እውቀት እንዲቀስም እድል ከፍቶለታል፡፡ ኢብን ሲና ከዓመት ዓመት በሥራ የተወጠረ ባተሌ ቢሆንም በተገኘው ትርፍ ጊዜ ሁሉ ይጽፍ ነበር፡፡ ከነዚህም ውስጥ በሃይማኖት፣ በፊዚክስ፣ በአስትሮኖሚ፣ በቋንቋና ስነ-ግጥም ዙሪያ የጻፋቸው ይጠቀሱለታል፡፡ “ኪታብ-አል-ሺፋ”(The Book of Healing) የተሰኘውን የህክምና መጽሃፉን ጨምሮ በአጠቃላይ 20 መጻህፍትን ለዓለም አበርክቷል፡፡ እጅግ ታዋቂ ሥራው “ቃኑን ፊ-አል ጢብ” (The Canon of Medicine) የተሰኘው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቃላት የያዘው መጽሃፉ ሲሆን በዚህ መጽሃፍ ውስጥ ያልተካተተ የህክምና ጥበብ የለም ማለት ይቻላል፡፡
በዚህ መጽሃፉ በዋነኝነት ምግብና የአየር ንብረት በሰው ልጅ ጤና ላይ ያላቸውን ተጽእኖ በሰፊው ያብራራ ሲሆን የጡት ካንሰር፣ኪንታሮት፣ ምጥና የመመረዝ ፈውሶችንም ይፋ አድርጓል፡፡ እኒህ ብቻ ግን አይደሉም፡፡ ስለ ማጅራት ገትርና ከእሱ ጋር የሚመሳሰሉ በሽታዎች መለያ ባህሪያት፣ ስለ ኩላሊት በሽታ፣ ስለ ሰውነት በድን መሆንና ስለ ጨጓራ ቁስለት ከእነመንስኤያቸው ትንታኔ ሰጥቷል፡፡ 760 የሚደርሱ የህክምና ዕጽዋትንና መድሃኒቶችንም በመጽሃፉ አስተዋውቋል፡፡
“ቃኑን ፊ-አል ጢብ” (The Canon of Medicine) የተሰኘው መጽሃፉ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በመላው ዓለም የህክምና ማስተማሪያና ማጣቀሻ በመሆንም አገልግሏል፡፡
በ10ኛው ክፍለ ዘመን የአረቦች የምርምር መፅሀፍት በካታሎኒያን ተርጓሚዎች መተርጎምን ተከትሎ አውሮፓውያን የአረቦችን የእውቀት ሀብት መድፈር ጀመሩ፡፡ አረቦች የእነ ሒፖክራተስን የህክምና ጥበቦች አዳብረው የፈጠሯቸው አዳዲስ ግኝቶች ተመልሰው አውሮፓውያን እጅ ገቡ፡፡ በ12ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የኢብን ሲና ስራ የሆነው “አል-ጢብ” (The Canon) ኮፒ እየተደረገ የአውሮፓውያን የህክምና ሥራ ማጣቀሻ ሆነ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የአል-ራዚ የህክምና መፅሀፍ “አል-ኪታ አልሀዊ” የህትመት ፈጠራ እንደተጀመረ ተተርጉሞ ሰፊ ተቀባይነትን ለማግኘት ችሏል፡፡ ዘጠነኛው የአል-ኪታብ “አል-መንሱር” መፅሀፍ (ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍር ድረስ ያሉ በሽታዎችን የያዘ ነው) በቱቢንጂን ዩኒቨርሲቲ እስከ 15ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የህክምና ካሪኩለም ሆኖ አገልግሏል፡፡
አውሮፓውያን ዛሬም ድረስ ለኢብን ሲና እና አል-ራዚን የህክምና ስራዎች ትልቅ ቦታ ይሰጧቸዋል፡፡ የእነኝህ ሁለት ተመራማሪዎች ታሪክና ሥራዎች በፓሪስ የህክምና ዩኒቨርሲቲ ተሰንደው ተቀምጠዋል፡፡
በአውሮፓውያን ላይ ተፅእኖ መፍጠር የቻሉት ኢብን ሲናና አል-ራዚ ብቻ አይደሉም፡፡ ከ400 መፅሃፍት በላይ የተተረጎመላቸው በአይን ህክምና፣ በቀዶ ጥገና፣ በፋርማሲዩቲካል፣ በህጻናት እንክብካቤና ጤና ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ሌሎች አረቦችም አሉ፡፡ እንግዲህ እነኝህ ናቸው የአውሮፓውያንን የህክምና ሳይንስና ዘመናዊውን ጥበብ አድሰው የወለዱት፡፡
ምንጭ (Aramco world, David Tschanz)

 

Published in ዋናው ጤና

የኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ አቀናባሪ የሆነው ሚካኤል ሰይፉ፤ ከሁለት ወር በፊት ‹‹የአራዳ ልጅ›› የተሰኘ የትውውቅ አልበሙን ለውጭ አገር ገበያ አቅርቧል፡፡ አልበሙ በኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ስልት የተሰሩ 4 ሙዚቃዎችን የያዘ ሲሆን በሸክላ ሲዲ እና ዲጂታል ፎርማት እየተሸጠ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ከ10 ዓመታት በላይ የኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ አጨዋወትን በግሉ ሲማርና ሲያጠና መቆየቱን የጠቆመው ሚካኤል፤ የትውውቅ አልበሙ አድናቆት እንዳተረፈለት ገልጿል፡፡ እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ጀርመንና ፈረንሳይን ጨምሮ ከበርካታ አገሮች ዓለም አቀፍ አድማጮችን እንዳፈራ ይናገራል፡፡
የትውውቅ አልበሙ ከወጣ በኋላ እውቅ ዓለምአቀፍ መፅሄቶች ስለሙዚቃ ሥራዎቹ ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ዘግበውለታል፡፡ የ27 ዓመቱ ኢትዮጵያዊው የሙዚቃ አቀናባሪ ሚካኤል ሰይፉ ስለ አዲሱ የትውውቅ አልበሙ፤ ስለኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ፣ ስለአሳታሚው ኩባንያ፤ እንዲሁም ሌሎች ሙያውን የተመለከቱ ጉዳዮችን ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ግሩም ሰይፉ ጋር አውግቷል፡፡

“የአራዳ ልጅ“ ኢፒ በሚል የትውውቅ አልበምህን ለቀሃል፡፡ ኢፒ ምንድነው?
ወደ ሙሉ አልበም የሚያደርስ ስራ ነው፡፡ ራስን እንደማስተዋወቂያ ሥራ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ከዋናው አልበም በፊት ገበያ ውስጥ የሚገባ ቅድመ አልበም ልትለው ትችላለህ፡፡ ይሁንና አንድ ኢፒ አልበም ከሰራህ በኋላ በቀጥታ ወደ ሙሉ አልበም ስራ ትገባለህ ማለት አይደለም፡፡ ሙሉ አልበምህ ለገበያ ሳይቀርብ ሌሎች ተከታታይ ኢፒ አልበሞችን በመስራት ልትቆይም ትችላለህ፡፡ በሌላው ዓለም ይህን አሰራር ትልልቅ የሙዚቃ ቡድኖችና ባንዶች ይጠቀሙበታል፡፡ ከመጀመርያ አልበሞቻቸው በፊት በኢፒ አልበም ራሳቸውን በማስተዋወቅ ወደ ገበያ የገቡ ጥቂት አይደሉም፡፡ በዚህ ዓይነት አልበም ሙዚቀኛው ምናልባት ከሚታወቅበት ስልት ወጣ ያሉ ስራዎችን ሊያቀርብ ይችላል፡፡ በኢፒ አልበም ውስጥ የቀረቡ ስራዎች በሙሉ በዋናው የአልበም ስራ ላይካተቱ ይችላሉ፡፡ ለአንድ ጀማሪ ሙዚቀኛ ኢፒ አልበም ከወጭም አንፃር ተመራጭ ነው፡፡ ሙሉ አልበም አይደለም፤ እንደ ነጠላ ዜማም አይደለም፡፡ እንደመግቢያ ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይ ግን ልዩ የሙዚቃ ሥራ የሚቀርብበት ነው፡፡
የትውውቅ አልበምህን ስላሳተመልህ ኩባንያ ንገረኝ … እንዴት ነው ግንኙነት የፈጠርከው?
የአሳታሚው ኩባንያ መስራች ከሆኑት አንዱ እዚህ አዲስ አበባ አሜሪካን ስኩል ይማር የነበረ ጓደኛዬ ነው፡፡ ዳዊት ኢክላንድ ይባላል፡፡ የት/ቤት ጓደኞች ከነበርንበት ጊዜ ጀምሮ በሙዚቃ ውስጥ ያለኝን ተሳትፎ ያውቃል፡፡ በሊሴ ገብረማርያም ስማር በተለያዩ ፓርቲዎች በዲጄነት በመስራት ብዙ እውቅና ነበረኝ፡፡ እሱም ሙዚቃ አካባቢ ስለማይጠፋ በዚያው ተዋወቅን፡፡ ጓደኝነታችንም ቀጠለ፡፡ ዳዊት አሜሪካ ከሄደ በኋላ በሙዚቃው እንደቀጠልኩበት ሲረዳ “አልበም ለምን አትሰራም?” እያለ አልፎ አልፎ ይጠይቀኝ ነበር፡፡ እሱ ራሱ ሙዚቀኛ ነው፤ የሙዚቃ መሳርያዎችን ይጫወታል፤ ሙዚቃ ያቀናብራል፡፡ በአሜሪካ ከአሳታሚዎች ጋር ይሰራ ስለነበር፣ ለምን ሥራዎችህን አላሳትምልህም እያለ ይጠይቀኝ ነበር፡፡ከዓመት በፊት ለእረፍት ወደ ኢትዮጵያ መጣ፤ ያኔ የሰራኋቸውን ሙዚቃዎች አሰማሁት፡፡ እረፍቱን ጨርሶ ከሄደ በኋላ ላክልኝ አለኝ፡፡ ያን ጊዜ የራሱን አሳታሚ ገና አልመሰረተም ነበር፡፡ የሙዚቃ አሳታሚ ኩባንያ የመመስረት ሃሳቡ የመጣለት የእኔን ቅንብሮች ከሰማ በኋላ ነው፡፡ በእርግጥ ሰዎች የራሱን አሳታሚ ድርጅት እንዲያቋቁም ይመክሩት እንደነበር አጫውቶኛል፡፡ በኋላም ከጓደኞቹ ጋር ተማክሮ “432 R” የተባለ አሳታሚ ኩባንያ በዋሺንግተን ለመመስረት ወሰነ፡፡ የእኔን የሙዚቃ ስራዎች በማሳተም ኩባንያቸው ወደ ገበያው ለመግባት መፈለጉንም አሳወቀኝ፡፡ በዚህ መንገድ የመጀመርያው ኢፒ አልበሜ “የአራዳ ልጅ” ሊሰራ ችሏል፡፡ የአሳታሚው የመጀመርያ ሥራ የሆነው ይሄ አልበም፤ ስኬታማ እንደሆነም ነግሮኛል፡፡ የዳዊት ኩባንያ በዋሺንግተን ዙርያ ከሚሰሩ 10 ትልልቅ አሳታሚዎች አንዱ ተብሎ ተዘግቦለታል፡፡
“የአራዳ ልጅ” አልበም ውስጥ ስለተካተቱት የሙዚቃ ሥራዎችህ ንገረኝ …
“ድሮፕሌቶን” የሚለው አዲስ ነገር ተገኘ ተብሎ የተነገረ ዜና ላይ ተመስርቼ የሰራሁት ቅንብር ነው፡፡ “ዳርክነስ ኢዝ” ደግሞ በአንድ የጃፓን የአኒሜሽን ፊልም ላይ ተመስርቶ የተሰራ ነው፡፡ ብርሃንና ጨለማ የተባሉ ሁለት ወንድማማቾች ነበሩ፡፡ በእነሱ መካከል ባለው ግንኙነት ተነሽጬ ያቀናበርኩት ሥራ ነው፡፡ “ወዳኝ” የሚለው ያሳለፍኩትን የፍቅር ህይወት መነሻ በማድረግ የሰራሁት ነው፡፡“የአራዳ ልጅ” ብዙ ትርጉም ያለው ሙዚቃ ነው፡፡ እኔ ስለ ብልጣብልጥነት ወይም ስለከተሜነት ሳይሆን እውቀት ያለው ወይም የገባው የሚለውን ሃሳብ ለመግለፅ ነው የተጠቀምኩበት፡፡
እንዴት ነው ከኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ጋር የተዋወቅኸው…
ራሴን እያስተማርኩ የሙዚቃ ቅንብር ስሰራ ከ10 ዓመት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ ሙዚቃን እንደሙያ ለመከተል ስወስን ከቤተሰቤ ብዙም ድጋፍ አልነበረኝም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት እንደማንኛውም ወላጅ የተሻለ ነገር ይመኙልኝ ስለነበር ነው፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቅሁ በኋላ የኮሌጅ ትምህርቴን በአሜሪካ ኒውጀርሲ ውስጥ በሚገኝ ኮሌጅ ለመማር ገባሁ፡፡ ሊበራል አርት የሚያስተምር ራማፖ የሚባል ኮሌጅ ነው፡፡ በኮሌጁ የመጀመርያዎቹ ሁለት ዓመታት ቆይታዬ፣ የትኛውን ዘርፍ በዋና ኮርስነት መምረጥ እንዳለብኝ አልወሰንኩም ነበር፡፡ በሊበራል አርት ዘርፍ ብዙ አማራጭ ኮርሶች አሉ፡፡ በመጀመርያ ቢዝነስ፣ ከዚያም ስነፅሁፍ፣ ቀጥሎም ኬምስትሪ ኮርሶች ለመማር ብሞክርም ሁሉንም አልጨረስኳቸውም፡፡ ምናልባትም ውስጤ የሚፈልገው የሙዚቃ ባለሙያነት ስለሆነ ይመስለኛል፡፡ ሶስተኛ ዓመት ላይ ስደርስ፣ የሙዚቃ ትምህርት በቢኤ ዲግሪ ደረጃ እንደሚሰጥ ሰማሁ፡፡ ለመመዝገብ አላመነታሁም፡፡ በኋላ ግን ከሙዚቃ መሳሪያዎች ጋር የተገናኘ ባለመሆኑ ተውኩት፡፡ የአራተኛ ዓመት ተማሪ ሳለሁ ትልቅ ውሳኔ መወሰን ነበረብኝ፡፡ ይሄውም ሁሉን ነገር እርግፍ አድርጌ ትቼ ወደ ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃው መግባት ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም ትምህርቴን አቋርጬ ወደ ኢትዮጵያ ተመለስኩና ከቤተሰብ ጋር ተወያየሁ፡፡ በሙዚቃ መቀጠል እንደምፈልግ ቁርጡን ነገርኳቸው፡፡ ችግሩ እኔ የምፈልገውን ትምህርት የሚያስተምር የሙዚቃ ትምህርት ቤት በአገር ውስጥ አለመኖሩ ነበር፡፡
ምን ዓይነት ት/ቤት ነበር የፈለግኸው?
የእኔ ፍላጎት ፒያኖ፣ ጊታር፣ ሳክስፎን ወይም ሌሎች ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎችን በመማር ከባንዶች ጋር ለመጫወት አልነበረም፡፡ ፍላጎቴ ሙዚቃን በልዩ የቴክኖሎጂ ቅንብር መስራትና መፍጠር ነበር፡፡ እናም ያንን የምማርበት ዕድል እንደሌለ ስገነዘብ፣ ከ3 ዓመት በፊት በመኝታ ቤቴ ውስጥ ራሴን የማሰለጥንበት ስቱዲዮ መሰረትኩ፡፡ በክፍሌ ውስጥ ከዴስክቶፕ ጋር የሚመጣጠን ብቃት ያለው ላፕቶፕ ነበረኝ፡፡ ሎጂክ የተሰኘ የሙዚቃ ሶፍትዌር ፕሮግራም ላይ ነበር የምሰራው፡፡ ለስቱዲዮ ያግዘኛል በሚል አንድ ስምንት ኦክታቭ ኪቦርድ፣ ሚዲ ኮንትሮለርና ሞኒተሮች ነበሩኝ፡፡ በእነዚህ መሳሪዎች የኤሌክትሮኒክ ሙዚቃን በትጋት ማጥናት ጀመርኩ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ የኤሌክትሮኒክ ሙዚቃዎችን መከታተልና ማጥናት የእለት ስራዬ ሆነ፡፡ የማደንቃቸው አርቲስቶች የፈጠሯቸውን ቅንብሮች ለመስራት እየጣርኩ፣ ጎን ለጎንም የራሴን አዳዲስ የሙዚቃ ሃሳቦች ለመፍጠር ብዙ ጣርኩ፡፡ የሚማርኩኝን የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች በመመርመር፣ ለማቀናበር ጥናቴን ገፋሁበት፡፡ ከዚያም ዓለም አቀፍ ሙዚቃዎችንና የኢትዮጵያን በመቀላቀል አንዳንድ ቅንብሮችን መስራት ጀመርኩ፡፡
ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃን የመረጥኩበት ትልቁ ምክንያት፤ በጣም ሰፊ የሆነ የድምፅ ዓለም በመሆኑ ነው፡፡ የፈጠራ አቅሙ የትየለሌ ነው፡፡ ምን አይነት ድምፅ ሊፈጠር ይችላል ብለህ ብታስብ፣ ምንም ማለቂያ የለውም፡፡ በእጅጉ ከቴክኖሎጂ፣ ከአዳዲስ የሙዚቃ ፈጠራዎች፣ ከምርምርና ከስልጣኔ እድገት ጋር የተዋሃደ ዘርፍ ነው፡፡ እነዚህ ወደ ሙዚቃው ስልት ለመማረኬ በምክንያትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
የኢትዮጵያን ባህላዊ ዜማዎች በኮምፒውተር ቅንብር ቆራርጦ፣ ቀጣጥሎና ቀያይጦ መስራት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ስልቱ የሰነፍ ሙዚቀኛ ስራ ነው እየተባለ ይተቻል፡፡ እንደ አቋራጭ ፈጠራ ነው የሚቆጠረው፡፡ አንዳንዶች እንደውም የሙዚቃ ተፈጥሯዊ ሃይልን የሚያደበዝዝ፣ የሙዚቃ መሳሪያዎችን አቅም የሚያዛባ… ጥፋት አድርገው ሲተቹት ይደመጣል፡፡ እውነታው ግን ያ አይደለም፡፡ ባለንበት ዘመን የሙዚቃ ስልቶች በየሰከንዱ እየተለወዋጡ፣ በየሰከንዱ እያደጉ፣ በየሰከንዱ እየተቀየሩ የሚሄዱ ናቸው፡፡ ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃም የዚህ የማያቋርጥ የሙዚቃ ለውጥ ውጤት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ሙዚቃ፣ ከዜማ ይልቅ ትኩረት የሚሰጣቸው ስንኞች ናቸው፡፡
ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ በኤሌክትሮኒክ የሙዚቃ መሳሪያዎችና በኮምፒዩተር ሶፍትዌሮች በመታገዝ የሚቀናበር ስልት ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የሙዚቃ ስልት መሆኑም ልዩ መገለጫው ነው፡፡ ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ በመላው ዓለም እየተስፋፋ የመጣው ከ1960ዎቹ ወዲህ ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን ወጣት ሙዚቀኞች እየተሰራ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ሲገባ ግን ገና 3 እና 4 ዓመታት ቢሆነው ነው፡፡
እንደ ኤሌክትሮኒክ ሙዚቀኛ፣ ከቴክኖሎጂ ጋር ወቅታዊ እውቀትና ቅርርብ ያስፈልጋል፡፡ የወቅቱን የቴክኖሎጂ እድገት በንቃት መከታተል የግድ ነው፡፡ አለበለዚያ ያለንበት የዲጂታል ዘመን ቆሞ አይጠብቅም፤ ጥሎ ይሄዳል፡፡
“የአራዳ ልጅ” የትውውቅ አልበም ከመውጣቱ በፊት ሥራዎችህን ለሰዎች የማስደመጥ ዕድል ነበረህ?
አዎ ነበረኝ፡፡ “ሳውንድ ክላውድ” የተባለ የሙዚቃና የድምፅ ድረገፅ አለ፡፡ በቪድዮ ሳይሆን በድምፅ ብቻ የሚሰራ ነው፡፡ ሙዚቃ እና ድምፅ ይቀርብበታል፡፡ ማንኛውም የዓለም ዜጋ ገብቶ የሚያዳምጠው ነው፡፡ የሙዚቃ መረጃዎችን ታፈላልግበታለህ፡፡ ለምትፈልገው መረጃ ጥቆማዎችና ሃሳቦችን ያቀርብልሃል፡፡ አንተም የሞከርካቸውን የሙዚቃ ቅንብሮች ትጭንበታለህ፡፡ እንደ አርአያ የምትወስደውን ወይም የተሳካለትን ሙዚቀኛ የምታገኝበትና የምትከታተልበት ድረገፅ ነው፡፡
የሰራኋቸውን ሙዚቃዎች “በሳውንድ ክላውድ” ላይ ለመጫን የወሰንኩት ቅንብሮቼ ምን አይነት የአድማጭ ምላሽ ሊያገኙ እንደሚችሉ ለማወቅ በነበረኝ ጉጉት ነው፡፡ ከዓለም የሙዚቃ ማህበረሰብ ጋር የምገናኝበት ድልድይ እንደሆነም ስለማምን ነው፡፡
ማንም ሰው በዚህ ድረገፅ ከተመዘገበ በኋላ፣ እስከ 15 ዘፈኖች (የአንድ ሰዓት ነፃ ኮታ) አለው፡፡ ከዚህ ኮታ በላይ ሲሆን በዓመት የምትከፍለው ነገር ይኖራል፡፡ ሥራዎቼን ከጫንኩ በኋላ ሊንኩን በፌስቡክ ድረገፄ ላይ በማቅረብ ለማስተዋወቅ ሞከርኩ፡፡
ያን ጊዜ ሰው ተደመመ፡፡ የፌስቡክ ጓደኞቼና ዘመድ አዝማዶች ሥራዎቼን እየተቀባበሉ ሰው አደመጠው፡፡ አስተያቶቹ አበረታች ነበሩ፡፡
እስካሁን “ሳውንድ ክላውድ” ድረገፅ ላይ አስራ አምስት ሥራዎቼን የጫንኩ ሲሆን ሁሉም በታተመው ኢፒ አልበም ውስጥ አልተካተቱም፡፡
ኮምፒዩተርን እንደሙዚቃ መሳሪያ መቁጠር ይቻላል?
ኮምፒውተር እንደ ሙዚቃ መሳሪያ የሚለውን ነገር መረዳት የጀመርኩት ገና ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ነው፡፡ ከ10 እና 12 ዓመት በፊት ማለት ነው፡፡ ያን ጊዜም በኮምፒዩተር ላይ ተጭነው ሙዚቃ ለማቀናበርና ለመጫወት የሚያግዙ ሶፍትዌሮች ነበሩ፡፡ በወቅቱ አስታውሳለሁ ‹‹ፍሩቲሉክስ›› የተባለ ሶፍትዌር በ40 ብር ነበር የገዛሁት፡፡ አሁን 12ኛው የሶፍትዌር ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ እሱን ፔንትዬም ዴስክቶፕ ኮምፒውተር ላይ ጫንኩት፡፡
የኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ አሰራር ከተለመደው የሙዚቃ አሰራር ጋር ያለው ልዩነት እንዴት ይገለፃል?
ድምፅ፣ ከማንኛውም ሁኔታ መፍጠር እንደሚቻል መገንዘቤ፣ ትልቅ የፈጠራ አቅምና ሃይል አጎናፅፎኛል፡፡ ድምፅ ፈልስፈህ፣ እሱን በቅንብር የሙዚቃ ዜማ ካደረግኸው የራስህን ሙዚቃ ፈጠርክ እንደማለት ነው፡፡ ድምፅ መነሻ ነው፡፡ ከዚያ በሶፍትዌሩ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ዜማ መፍጠር ነው፡፡ዘመናዊ ሙዚቃ ሁሉ በኮምፒዩተር ድጋፍ የሚሰራ፣ መደበኛ የሙዚቃ መሳሪያዎችን የማይጠቀም ነው በሚል ትችት ሲቀርብ ያስገርመኛል፡፡ ይህ ለእኔ አይገባኝም፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አቀናባሪ ዲጅታል ሲንትሳይዘር ወይም አናሎግ ሲንትሳይዘር የለውም፡፡
አብዛኞቹ ኪቦርድ ነው ያላቸው፡፡ ይህ ማቀናበርያ ከሲንተሳይዘር የሚለየው የድምፅ አቅሙ አነስተኛ በመሆኑ ነው፡፡ እኔ ራሴ ሲንተሳይዘር ወደ ስቱዲዮዬ ያስገባሁት በቅርብ ነው፡፡ ሲንትሳይዘር በአቶሚክ ደረጃ ድምፅን ሰንጥቆ የሚፈጥር መሳርያ ነው፡፡
ከኮምፒዩተር ላይ ኪቦርድ ፒያኖ፤ ጊታርና ዋሽንት የመሳሰሉ መሳሪያዎችን በመሞከር፤ እያወኻድኩ ጥናት አደርግ ነበር፡፡ በደንብ የምችለው መሳሪያ ባይኖርም ኪቦርድ ፒያኖ እሻላለሁ፡፡ ጊታር፣ ትራምፔትና ከበሮ ለመጫወት የምችልበት በቂ ልምድም አዳብሬያለሁ፡፡
ዘመናዊ ሙዚቃ በኮምፒዩተር ድጋፍ የሚሰራ ነው የሚለውን ትችት ለምንድነው የማትቀበለው?
በአጠቃላይ ሙዚቃን በኮምፒዩተር አቀናብሮ መስራት፣ መተቸቱ አግባብ አይደለም ብዬ አምናለሁ፡፡ ዛሬ እኮ እያንዳንዱ ስቱዲዮ የተለያዩ ቅንብሮችን ለማዋሃድ፤ የተቀዱ ድምፆችን ለማሻሻልና ለማሳመር ኮምፒዩተርን የግድ መጠቀም ይኖርበታል፡፡ በትልቁ ዴስክቶፕ ኮምፒዩተር ብቻ አይደለም፤ በላፕቶፕም ሙዚቃ ይሰራል፡፡ አሁን እንደውም የሞባይል ስልኮችም ለሙዚቃ ማቀናበርያነት እያገለገሉ ናቸው፡፡ እናም ኮምፒዩተር የሙዚቃን ፈጠራ የሁሉም ሰው (ዴሞክራታይዝ) አድርጎታል፡፡
ሙዚቃን በኮምፒዩተር ማቀናበር ቀላል ስራ አይደለም፡፡ የሙዚቃ አቀናባሪነት ሙያን፣ ወቅቱን የጠበቀ የኮምፒዩተር አጠቃቀምን፣ ሙዚቃ መሳሪያዎችን መጫወትን፤ የሙዚቃ ፕሮዱዩሰርነት ችሎታን አጣምሮ የያዘ ክህሎት ይጠይቃል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ በኢትዮጵያ እየታወቀ ነው፡፡ እንዴት ነው የሚያዋጣ አቅጣጫ ነው?
ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ አሁን ከዋናው የሙዚቃ ስልት ተርታ ገብቷል፡፡ የሙዚቃ ስልቶችን ወደላቀ ደረጃ እያሳደገ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማ ከሚባሉ ሙዚቀኞች ብዙዎቹ ፈረንሳውያን ናቸው፤ በጣም ታዋቂው ፒዬር ሄነሪ ይባላል፡፡ ካርሄልዝ ስቶክ ሃውሰን የሚባል ጀርመናዊም አለ፡፡ ከአሜሪካ ደግሞ ቤን ኒል እና ጆን ኬጅ ይጠቀሳሉ፡፡ በዘመናዊ ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ስልት እኒህ አርአያዎቼ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርጥ ሙዚቀኞችን የማፍራት አቅም እንዳላት በልበሙሉነት እናገራለሁ፡፡ የድምፅ ጥበቧን ለዓለም ማካፈል ትችላለች ፡፡
ዓለምን አንድ እያደረገ የመጣው ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ነው፡፡ ቴክኖሎጂ ቅርብ ነው፤በየጊዜው እያደገ የሚሄድም ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ በዚህ ዘርፍ ብዙ መስራት የሚችልበት አቅም አለ፡፡ ብዙ ወጣቶች ችሎታ እያላቸው ተስፋ ቆርጠው መኖር የለባቸውም፡፡
ሙዚቃ ትልቅ ሙያ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ ገበያ ያለውና ገቢ የሚፈጥር ነው፡፡ በአሜሪካው ራማፖ ኮሌጅ በነበርኩበት ጊዜ ክረምት ላይ መጥቼ፣ በቅዱስ ያሬድ ዜማ ላይ አንድ ጥናት ሰርቻለሁ፡፡ እንደሚታወቀው አብዛኛው የኢትዮጵያ ዜማ ስልቶች መነሻቸው ከያሬድ ነው፡፡ ግእዝ፣ እዝልና አራራይ የተባሉት ያሬዳዊ ስልተ-ዜማዎች በጣም ልዩ የሆኑ መሰረታዊ ቅንብሮች ናቸው፡፡
ፉከራ፣ ቀረርቶ፣ ሽለላና ሌሎች ኢትዮጵያዊ ዜማዎች ብዙም አልተሰራባቸውም፡፡ ወደፊት እነዚህን ባህላዊ ዜማዎች በተለያዩ ቅንብሮች በመስራት ዘመን እንዲሻገሩና አለም እንዲያደምጣቸው እሻለሁ፡፡
የሚዚቃ ፍልስፍናህ ምንድን ነው?
ሙዚቃ ረቂቅና ጥልቀት ያላት ስሜት ናት፡፡ ድምፅ ምንም አይነት ገደብ የለውም፡፡ በሌላ በኩል ሙዚቃ ለእኔ ምት ነው፡፡ ውስጤን የሚነካ ልዩ ምት ሳቀናብር፣ ለሌሎች የማጋራው ፈጠራ ነው፡፡ የእኔ ሙዚቃ ምስራቃዊ፤ ምዕራባዊ ወይንም ማርሳዊ አይደለም፡፡
ዓለም አቀፋዊ ድምዕ ነው፡፡ እንደ ዓለም አቀፋዊነቱ ሁሉም የሚጋራው ሲሆን ደስ ይለኛል፡፡ ካልተሳካልኝም ብዙ ችግር የለውም፡፡ በሌላ ሙከራ የምመለስበት የማያልቅ ፈጠራ ነው፡፡
የወደፊት ዕቅድህ ምንድነው?
የአጭር ጊዜ ዕቅዴ፣ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ በተመሳሳይ የሙዚቃ ስራ ያሉ ጓደኞችን በማስተባበር፤ በቋሚነት የኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ላይቭ ቅንብሮችን በመደበኛ ሳምንታዊ ፕሮግራም እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ለመስራት ነው፡፡ በጥናት የተደገፉ ዝግጅቶችን ከማቅረብ ጎን ለጎን ዘርፉን እያሳደጉ መቀጠል ነው ዓላማዬ፡፡
(የሚካኤል ሰይፉ ሙዚቃዎችን
www.soundcloud.com/mic-tek ድረገፅ ማድመጥ ይቻላል)

Published in ጥበብ
Page 8 of 14