የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት መፈንቅለ መንግስቱን አውግዘው፣የታሰሩ ባለስልጣናት እንዲፈቱ ጠይቀዋል
   የቡርኪናፋሶ የቤተ-መንግስት ጠባቂዎች ከትናንት በስቲያ ምሽት በመዲናዋ ኡጋዱጉ ባደረጉት መፈንቅለ መንግስት፣በፕሬዚዳንት ሚሼል ካፋንዶ የሚመራውን የአገሪቱን የሽግግር መንግስት በማፍረስ፣ ጄኔራል ጊልበርት ዴንድሬን በፕሬዚዳንትነት መሾማቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የቤተመንግስቱ ጠባቂዎች ባለፈው ረቡዕ በተከናወነ የካቢኔ ስብሰባ ላይ የሽግግር መንግስቱን ፕሬዚዳንት ሚሼል ካፋንዶ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩን አይዛክ ዚዳን በቁጥጥር ስር በማዋል ማሰራቸውንና በነጋታውም መፈንቅለ መንግስቱን ማድረጋቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡የአገሪቱን የቴሌቪዥን ጣቢያ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ጠባቂዎቹ በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር የሰዓት ዕላፊ አዋጅ በማውጣትና የአገሪቱ የየብስና የአየር ክልሎች ሙሉ ለሙሉ እንዲዘጉ በማድረግ ባከናወኑት በተኩስ የታገዘ መፈንቅለ መንግስት፣ የሽግግር መንግስቱን ጊዚያዊ መሪ ፕሬዝዳንት ሚሼል ካፋንዶን ከስልጣን አውርደዋል፡፡
አገሪቱን ለ27 አመታት ያህል የመሩት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬ፤ ባለፈው አመት ባጋጠማቸው የህዝብ ተቃውሞ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ስልጣኑን የተረከበውና በፕሬዝዳንት ሚሼል ካፋንዶ የሚመራው የአገሪቱ የሽግግር መንግስት በመጪው ጥቅምት ወር ይከናወናል ተብሎ በሚጠበቀው የአገሪቱ ምርጫ ለሚያሸንፈው አዲስ መንግስት ስልጣኑን ለማስረከብ አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ መፈንቅለ መንግስቱ ተካሂዶበታል፡፡የሽግግር መንግስቱ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬ ታማኞች እንደሆኑ የሚነገርላቸውን ፖለቲከኞች በመጪው ምርጫ እንዳይሳተፉ መከልከሉንና የፕሬዚዳንቱ ጠባቂ ሃይል እንዲበተን መገፋፋቱን የጠቆመው ዘገባው፣በዚህ የተቆጡ የፕሬዚዳንቱ ጠባቂዎች መፈንቅለ መንግስቱን ማካሄዳቸውን አመልክቷል፡፡ አገሪቱን በቅኝ ግዛት ታስተዳድር የነበረችዋ ፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ፍራንኮይስ ሆላንዴ በበኩላቸው፣ መፈንቅለ መንግስቱን አውግዘው በእስር ላይ የሚገኙት የሽግግር መንግስቱ ፕሬዚዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

    ፍራንሲስ ፉኩያማ፤ የሰው ልጅ ከ‹‹ታሪክ መጨረሻ›› ደርሷል በማለት፤ በታሪክ ላይ ሞት እንደ ፈረደ፤ በተራኪ እና በ‹‹ተረት›› (story) የሞት ፍርድ ያሳለፉ የ21ኛ ክፍለ ዘመን ምሁራን በርካቶች ናቸው፡፡ ይሁንና፤ እንደ ሪቻርድ (Richard Kearney) ያሉ ምሁራን ይህን ፍርድ ይቃወማሉ፡፡ እንደነሱ ሐሳብ፤ ‹‹ተረት ንገረኝ እስኪ?›› የሚል ሰው እስካለ ድረስ፤ ‹‹ከለታት አንድ ቀን….›› ወይም ‹‹በድሮ ጊዜ …›› ብሎ፤ ተረት ወይም ታሪክ ለመናገር የሚጀምር ሰው አይጠፋም፡፡ ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር፤ሁልጊዜም ከህይወቱ የተደራጀ ተረክ ለማውጣት ከመጣጣር አይቦዝንም፡፡ የህልውናው መሠረት ‹‹ተረክ›› ወይም ‹‹ተረት›› መሆኑን በማንሳት ይከራከራሉ፡፡ ስለዚህ፤በምድር ላይ ሰው የሚባል ፍጡር እስካለ ድረስ፤ተራኪ፣ ታሪክ እና ተተራኪ ይኖራል ይላሉ፡፡
ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር፤ ለህይወቱ በታሪክ መልክ የተደራጀ ቅርፅ ለመስጠት ይፈልጋል፡፡ በዚህ አንጻር ካየነው፤ የህይወት ዋናው ግብ መሆን ያለበት፤ መኖር ሳይሆን፤ታሪክ መፍጠር ነው፡፡ ሶቅራጥስ ያልተመረመረ ህይወት ሊኖሩት የሚገባ አይደለም›› እንዳለ፤ ያልተተረከ ህይወት ሊኖሩት የሚገባ አይደለም ማለት ይቻላል፡፡ ‹‹ትረካ ለታሪክ ሲባል›› አይደለም፡፡ መተረክ ህይወትን የመረዳት ጥረት ነው፡፡ ስለዚህ፤ ያልተተረከ ህይወት፤ ያልተኖረ ህይወት ነው፡፡ ግን ህይወትን ‹‹ተረት›› የማድረግ ዕድል የሚያገኙት ጥቂቶች ናቸው፡፡
አንድ የልብወለድ ገፀ ባህርይ፤‹‹መኖርን’ማ አሽከሮቻችን ይሰሩልናል›› ያለው እውነቱን ነው፡፡ ‹‹የመሳፍንት›› ሥራ፤ታሪክን መተረክ ነው፡፡ ህይወትን እንደ ግጥም ወይም ተረት በመመልከት ማጣጣም ነው፡፡ የታደሉት (የመሳፍንቱ) ሥራ፤ ለህይወት አንድ ቅርጽ ሰጥቶ፤ ትረካ መፍጠር ነው፡፡ የህይወት አሽከር መሆን የማይፈልግ ሰው፤ ዋና ሥራው አድርጎ ሊይዘው የሚገባው፤ህይወትን እንደ ተረት ተመልክቶ፤ ታሪክ መቀመርን ነው፡፡ ‹‹መኖርን’ማ የህይወት አሽከሮች ይኖሩልናል፡፡››
ታዲያ የሰው ልጅ፤ ታሪክን መስራት የሚፈልገው፤ የጨረባ ተዝካር ሊባል ከሚችል ዝብርቅርቅ ህይወቱ ውስጥ የሰመረ ወጥ ታሪክ ለማውጣት ብቻ አይደለም፡፡ ይልቅስ፤ግራ የመጋባት ችግርን ለማስወገድም ነው፡፡ የተበታተኑ የህይወት ሁነቶች የሚያሳድሩብንን ተጽዕኖ ለመቋቋም የምንችለው፤ታሪክ በመፍጠር ነው፡፡ ስለዚህ፤ የሰው ልጅ ግራ መጋባትን ለማስወገድ በማሰብ፤ ታሪክ ለመስራት ይጣጣራል፡፡ ታሪክ ለመስራት ይጣጣራል ሲባል፤ የሌለ ነገርን እንደ ልብወለድ ይፈጥራል ማለት አይደለም፡፡ እርግጥ፤ የሰው ልጅ፤ ከምናብ አንቅቶ የሚፈጥረው ታሪክ ይኖራል፡፡ ሆኖም፤ ያ የምናብ ገፀ ባህርይ ሊፈጥር የሚችለው ደራሲ፤ ራሱ የህይወት ገፀ ባህርይ ነው፡፡  
ደራሲው የሚሆነው የሰው ልጅ፤ ተራኪ ብቻ ሳይሆን ተተራኪም ነው፡፡ ተራኪው ቢፈልገውም ባይፈልገውም በአንድ ተረክ ውስጥ ያልፋል፡፡ ይህም ተረክ በገጽታው ሲታይ ዝብርቅርቅ ወይም ድብልቅልቅ ነው፡፡ ሆኖም፤ዝብርቅርቅ ወይም ድብልቅልቅ ሆኖ በሚታየው በማንኛውም ሰው የህይወት መስክ ውስጥ ሥር ለሥር የሚሄድ አንድ ስውር ታሪክ አለ፡፡ የሁነት ጨፌ በለበሰው በዚህ መስክ፤ ስር ለስር የሚፈስ ወጥ ታሪክ አለ፡፡ ዝብርቅርቁን የህይወት ጃኖ ደርቦ የተቀመጠ ድብቅ ታሪክ አለ፡፡
ስለዚህ፤ የሰው ልጅ፤ ዕለታዊ የሕይወት ዝብርቅርቅ የሚፈጥርበትን ግራ መጋባት ለመሸፈን ብቻ ሣይሆን፤ ዝብርቅርቅ የመሰሉ ነገሮች ድር እና ማግ ሆነው የፈጠሩትን ጃኖ ለብሶ የተቀመጠውን፤የተቀናበረ ቅርጽ የያዘ ታሪክ ‹‹ለማንበብ›› በመፈለግ  የተነሳ፤ ታሪክን መተረክ ይፈልጋል፡፡
እንደሚታወቀው፤ ታሪክ መጀመሪያ፣ መካከለኛ እና መጨረሻ አለው፡፡ በጊዜ የተቀነበበ ህላዌአችንም እንዲሁ ነው፡፡ የሰው ምድራዊ ህይወት፤ዘላለማዊ አይደለም፡፡ ሸማኔ እንደሚሰራው ጋቢ፤ በዘመን እጅ የሚቋጭ ቁጢት ያለው ነው፡፡ የህይወት ጉዟችን በውልደት ተወጥኖ በሞት የሚቋጭ ነው፡፡ ህላዌ እና መከሰቻ እንዳለው አንድ ፍጡር፤ የሚወለድበት እና የሚሞትበት ጊዜ አለው፡፡ ይህ ሁኔታ ለሰው ልጅ ለህይወት፤ አንድ ዓይነት የትረካ ቅርጽ ይሰጠዋል፡፡ በጊዜ የተወሰነ ቁመና፣ ቅርጽ እና መዋቅር ይሰጠዋል፡
ጊዜ፤ ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ አለው፡፡ ስለዚህ፤ በጊዜ መስክ ላይ የሚጓዘው የሰው ልጅ፤ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ወይም የትውስታን ማህደር ገልጦ፤ በህይወቱ የሆነው ነገር ሁሉ ለምን እንደሆነ ለመረዳት ይሞክራል፡፡ በሆነ መንገድ ለህይወት ጉዞው ፍቺ ለመስጠት ይሞክራል፡፡ ይህን ሲያደርግ፤አሁን ከትናንት ጋር የሚያያዝበትን ውል ይፈጥራል፡፡
አንድ ሰው ሲሰክር ወይም ድንገት ህሊናውን ሲስት፤ የሚቋረጠው ትረካ ነው፡፡ ወደ ኋላ ሄዶ፤ አሁን ከቆመበት ነጥብ እንዴት እንደ ደረሰ ካላወቀ ግራ ይጋባል፡፡ የህይወት አያያዥ ክር ተበጥሶ ሲያገኘው፤ማንነቱ ይጠፋበታል፡፡ ስለዚህ፤ ህይወት ትርጉም የሚኖራት ‹‹ትረካ›› ስትሆን ነው፡፡ በእርግጥ፤ ህይወት ትረካ ነች፡፡ እንደ ስካር እና ራስን እንደ መሳት ያለ ችግር የገጠማት ህይወት፤ ወደ ኋላ በመሄድ የ‹‹ገፀ-ባህርውን›› አሁን እና ትናንት የሚያያዝ የትረካ ትልም ታጣለች፡፡ ነገን ማማተርም አትችልም፡፡
በህይወት ጎዳና የቆመ ሰው፤ ወደ ኋላ የማየት (memory) ፍላጎት እንደሚኖረው፤ ወደ ፊት የማማተር (projection) መሻትም ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ የእያንዳንዳችን የህይወት ጉዞ፤ የራስን ህይወት በራስ የመተርጎም  ወይም የመተረክ የማያቋርጥ ጥረት የሚደረግበት ጉዞ ነው፡፡ በዚህ ጉዞአችን፤ እኛ የራሳችንን ህይወት ብንተርከውም - ባንተርከውም፤ ለውጥ የለውም፡፡ ታሪኩ የሚሰራው እኛ ህይወታችንን ዘወር ብለን በማየት፤ ለመገምገም ከመቀመጣችን በፊት ነው፡፡ የመገምገም ፍላጎት በእኛ ህሊና ከማደሩ አስቀድሞ ታሪኩ ተጠናቅቋል፡፡
ህይወታችንን ዘወር ብለን ስናይ፤ መግቢያ፣ መካከለኛ እና መጨረሻ ያለው የታሪክ ትልም (ቅደም ተከተሉ ሊለዋወጥ ይችላል) ይታየናል፡፡ የታሪክን ትልም በተከተለ አኳኋን ህይወታችን ተቀናብሯል፡፡ ከልደት እስከ ሞት የተዘረጋው የህይወት ጉዞ ሳይሆን፤ በምዕራፍ በምዕራፍ ሊከፈል የሚችለው የህይወት ትልም፤ እኛ ታሪክ ለመተረክ ከመነሳታችን ወይም ከመቀመጣችን በፊት የተጠናቀቀ ነው፡፡ አንድ ዓይነት የተቀናበረ ሴራ ተሰርቶ ቁጭ ብሏል፡፡ የእኛ ጥረት፤የተበታተኑ የህይወት ሁነቶች እንደ አፈር ሆነው የቀበሩትን የህይወት ታሪክ፤ እንደ አርኪዎሎጂስት ቆፍረን ማውጣት ብቻ ነው፡፡
አንድ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ፤የሥነ ልሳን ዕውቀት ባይኖረውም፤ የሚናገራቸውን ዐረፍተ ነገሮች የቋንቋውን ሰዋሰው የተከተሉ ይሆናሉ፡፡ ንግግሩን በሰዋሰው ዕውቀት ሊተነትነው ባይችልም፤ ንግግሩ ሰዋሰውን የተከተለ ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ፤ እኛ የራሳችንን ህይወት ለመተረክ ዕውቀት ቢኖረንም ባይኖረንም፤ ታሪካችን የህይወትን ሰዋሰውን በተከተለ አግባብ ተቀምሮ ተቀምጧል፡፡ የህይወትን ሰዋሰው የተከተለ ትረካ ለመስራት ከመነሳታችን በፊት፤ ህይወታችን ሰዋሰውን በተከተለ አግባብ ተተርኮ ተጠናቋል፡፡ በሌላ አገላለጽ፤ እኛ የራሳችንን ህይወት ለመተረክ ከመነሳታችን በፊት፤እስከምንገኝበት የህይወት ምዕራፍ ድረስ ያለው ታሪካችን ተሰርቶ ተጠናቋል፡፡ የእኛ ጥረት ይህን ታሪክ ትርጉም በሚሰጥ፣ በሚያስደስት እና በሚያስተምር አኳኋን ለመተረክ መሞከር ነው፡፡
ህይወትን ወደህይወት ታሪክ የመቀየር ጥበብ ወይም ትርክት የመፍጠር ተግባርም (poiesis) በተለያየ መልክ ይፈፀማል፡፡ የህይወት ታሪካችን፤ ለሰው ለመንገር በተመቸ የሆነ ቅርጽ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ከትንሽ ድፍረት ጋር፤ ሆነ ተብሎ እና ታስቦበት በተነደፈ የትረካ መዋቅር ተቀናብሮ ተቀምጧል ለማለት ይቻላል፡፡ እኛ ታሪካችንን ለመተረክ ከመነሳታችን በፊት የህይወት ጉዟችን (ከሞላ ጎደል ሲፃፍ እና ሲተረክ ሊይዝ የሚችለውን) የትረካ ትልም ይዞ ተቀናብሮ ተጠናቋል፡፡ ‹‹ቅድመ ትረካ›› የነበረው ህይወት መልክ፤ ‹‹ድህረ ትረካ›› ከሚታየው የተለየ ሊሆን አይችልምና፡፡ ሆኖም፤ ህይወታችን አንድ ዘውግ ይዞ ተቀናብሮ ሲቀርብ፤ ስውር የነበረ የታሪክ ትልም ወይም የህይወታችን ‹‹ፆታ›› ተለይቶ እና ማንነታችንም ግልፅ ወጥቶ ይታየናል፡፡ የተደላደለ ማንነታችንን የሚነግረንና የሚያፀናልን ትረካ ነው፡፡
ህይወት፤ በጊዜ መስክ ላይ የተበተነች ናት፡፡ ጊዜም በትናንት፣ በዛሬ እና በነገ የተከፋፈለ ነው፡፡ ማንነታችንም በእነዚህ ሦስት የጊዜ መስኮች ከተበተኑ የህይወት ጡቦች የሚገነባ ነው፡፡ እንደ ቅዱስ አውጉስጦስ አመለካከት፤ የህይወታችን ታሪክ መዋቅር የሚገነባው በእያንዳንዳችን የነፍስ በኣት ነው፡፡
የሰው ልጅ ህይወትም የመበታተን እና የመቀናበር ዝንባሌ አላት- (dispersal and integration)፡፡ ቅዱስ አውጉስጦስ የህይወትን የመበታተኑን ዝንባሌ ‹‹distentio animi›› ይለዋል፡፡ ይህም የመበታተን ዝንባሌ ከሰው ልጅ ደካማ ባህርይ የሚነሳ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ይህም የሚገለፀው፤ የሰው ልጅ ህይወት እና ማንነት፤ለየብቻቸው በቆሙ የትናንት፣ የዛሬ እና የነገ ጎተራዎች የተከተተ ነው፡፡ የማንነት አሻራችን በየቅፅበቱ እንደ ጠብታ እየተጠራቀመ፣ የየራሱን ኩሬ እየሰራ ይቀመጣል፡፡ ተራኪ ሲመጣ፤ ኩሬዎቹ ወደ አንድ ሐይቅ ወይም ወንዝ ይለወጣሉ፡፡ ታሪክ ይሰራል፡፡
ታሪክ፤ ጊዜ የሰራውን ግድብ እያፈረሰ፤የተበታተኑ ሁነቶችን በማዋሐድ አንድ ወንዝ ወይም ሐይቅ ይፈጥራል፡፡ ታሪክ ሲመጣ፤ እያንዳንዷ የድርጊት ፍሬ ተለቅማ፤ በህይወት ኬሚስትሪ ተቀምማ፤ አንድ ዓይነት ጣዕም ያለው እና በአንድ ጽዋ የሚሰፈር ማንነትይፈጠራል፡፡ አውጉስጦስ እንደሚለው፤ በሰው ዘንድ አንድ ወጥ ማንነትን የመገንባት ሥነልቦናዊ ጥረት አለ፡፡ ይህ ሥነ ልቦናዊ ዝንባሌ እና ጥረት፤ የተበታተኑ ሁነቶችን በማዋሐድ እና የህይወት ድርጊቶችን እንዲነጣጠሉ ያደረገውን አጥር በማፍረስ፤ አንድ ውህድ ማንነት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
እንደ አውጉስጦስ አመለካከት፤ይህ የመዋሀድ ዝንባሌ፤የጊዜን አጥር እየናደ፤ በእያንዳንዱ የጊዜ አንጓ የተለጠፉ ድርጊቶችን እያራገፈ፤ የተደራጀ እና አንድ ወጥ የሆነ ማንነት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ አውጉስጦስ ይህንን ሥነ ልቦናዊ ጥረት ‹‹Intentio animi›› ይለዋል፡፡
‹‹ከሰው ልጅ ደካማ ባሕርይ የመነጨ ነው›› የሚለው የመበታተን ዝንባሌ እና ከተበታተኑ ሁነቶች ውህደትን የመፍጠር ሥነ ልቦናዊ ዝንባሌ ጦርነት ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ዝንባሌዎች የሚፈጥሩት ጦርነት ውጥረትን ያስከትላል፡፡ ውጥረቱን ለማርገብ ታሪክ መተረክ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ይህ ውጥረት በእያንዳንዱ ሰው በሚፈጠር ‹‹እኔ ማነኝ?›› የሚል ጥያቄ ይገለጣል፡፡ እያንዳንዱ ህይወት በጊዜ የተቀነበበ፤ በምክንያት እና ውጤት ሰንሰለት የተያያዘ፤የትረካ ትልም ወይም ሴራ አለው፡፡ ሆኖም፤ በዚህ የሴራ ጉዞ የመጨረሻውን ውሳኔ የሚያሳልፍ ባለታሪኩ ሳይሆን ‹‹ደራሲ›› ነው፡፡ ደራሲውም እግዚአብሔር ነው፡፡
ሰው ‹‹ትናንትን›› እና ‹‹አሁንን›› በእርግጠኝነት ያውቃል፡፡ ‹‹ነገ›› ግን የእርሱ አይደለም፡፡ የሰው ልጅ፤ ‹‹ነገ››ን በእርግጠኝነት ሊያውቅ አይችልም፡፡ ‹‹ትናንትን›› እና ‹‹አሁንን›› መሠረት በማድረግ ‹‹ነገን›› አሻግሮ ለመመልከት ሊጣጣር ይችላል፡፡ በተወሰነ መጠንም‹‹የነገን›› ምስል አሻግሮ ሊመለከት ይችላል፡፡ ነገር ግን፤‹‹የነገን›› እርግጠኛ ሥዕል ለማየት አይችልም፡፡ ስለዚህ፤ስልጣኑ በታሪክ የመጀመሪያ እና የመካከለኛ ክፍል የተወሰነ ነው፡፡ የመጨረሻውን ክፍል ‹‹ለጀግናው›› መተው ይኖርበታል፡፡ በአውግስጦስ አመለካከት፤ የህይወት ‹‹ገፀ - ባህርይ›› የሆነውን የሰው ልጅ የመጨረሻ የሚያውቀው፤ ባለሙሉ ስልጣን ደራሲው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡
ታሪክ፤ ከሁነቶች ጡብ የሚገነባ ነው፡፡ ሁነቶችም እንደ ድንች ለየብቻቸው የመቀመጥ ፍላጎት አላቸው፡፡ ታሪክ ድንቾቹን ፈጭቶ እና አቡክቶ አንድ ወጥ ታሪክ የመገንባት ፍላጎት አለው፡፡ ስለዚህ በሁለቱ መካከል ፀብ አለ፡፡ በሁለቱ መካከል ያለውን ፀብ አስወግዶ፤ ሁለቱን ባላንጣዎች አሸማግሎ፤ አንድ ወጥ ታሪክ እንዲገነባ የሚያደርገው ሴራ ነው፡፡ ህልውና በባህርይዋ ተተራኪ  (storied) ነች፡፡ ህይወት ሁል ጊዜም ታሪክን አርግዛ የምትኖር ነች፡፡ ህይወት ጥሩ አዋላጅ የምትፈልግ ፅንስ ሴራ ነች፡፡ ህይወት ጥሩ ተራኪ የምትፈልግ በቁል ሴራ ነች፡፡
ታዲያ በእያንዳንዱ ሰው ህሊና ውስጥ ሊነገሩ የሚሹ በርካታ እንጎቻ ታሪኮች አሉ፡፡ ህይወት ያለትረካ እንደተበጣጠሰ ወረቀት ነች፡፡ ስለዚህ የእያንዳንዱ ሰው ዕለታዊ ድርጊት፤ ወደፊት ግልፅ ወጥቶ ሊታይ የሚችል ወይም ሊተረክ የሚገባ የአንድ ወጥ ታሪክ አካል አድርጎ ማንበብ ይቻላል፡፡ እያንዳንዱ የህይወት ታሪክ (Life story)፤ በትረካ ጥበብ ተገልብጦ እና ተመዝግቦ (Imitated)፤የአንድ ህይወት ወጥ ታሪክ (story of a life) ሆኖ የመደራጀት ብርቱ መሻት አለው፡፡
ተራኪነት፤ ከደረቅ እውነታ የማምለጥ ከንቱ ጥረት ወይም ለደረቅ እውነታ ባርያ ሆኖ የመገዛት መጥፎ ዕዳ ሳይሆን፤ ህይወትን የመረዳት ሰዋዊ ፍላጎት ነው፡፡ የሰው ልጅ የህይወት እውነታ ጎልቶ እንዲታይ ማድረጊያ መሣሪያ ነው፡፡ ራይኮየር (Ricoeur) እንደሚለው፤‹‹ህይወት ትኖራለች፡፡ ታሪክ ትነገራለች፡፡›› ሆኖም፤ ህይወት በደንብ እንደትኖር ታሪክ መሆን ይኖርባታል፡፡ ‹‹ኑሮን ለአሽከሮች ተዉላቸው›› ብለው፤ በተረትና በታሪክ የሚያተኩሩ ጀግኖች ናቸው፡፡
የተተረከች ህይወት፤ካልተተረከችው ህይወት፤ በሐብት እና በይዘት ትበልጣለች፡፡ ምነው ቢሉ፤ የተተረከች ህይወት፤ በተራ የህይወት መነፅር ሊታዩ የማይችሉ ነገሮችን ታሳያለች፡፡ የራቀውን ታቀርባለች፡፡ የረቀቀውን ታጎላለች፡፡ በአዲስ የምልከታ አንፃር፤ ህይወትን ለመመልከት የሚያስችል ዕድል ትፈጥራለች፡፡ ስለዚህ፤ የተተረከች ህይወት ካልተተረከችው ህይወት ትበልጣለች፡፡ የትረካ ጥበባዊ ኃይል፤ የሆነውን ብቻ ሣይሆን፤ ሊሆን ያለውን ዓለም አሻግሮ ለማየት የሚያስችል ዕድል ይፈጥራል፡፡ ህይወት ‹‹ቅድመ-ትረካ›› እና ‹‹ድህረ ትረካ›› አንድ አይደለችም፡፡ ከትረካ በፊት የነበረው ዓለም ተለውጦ ልዩ መልክ ይይዛል፡፡ ትረካ፤ህይወትን ለመረዳት የሚያስችል፣መንገድ አመላካች እና መሪ ዕውቀትን ያስጨብጣል፡፡ በዚህም አዲስ ቅርፅ እና ህብር ያለው ዓለም ይፈጠራል፡፡
የዚህ ትረካ ማጠቃለያ የሚሆን አንድ ቃል አለኝ፡፡ ‹‹ልጄ ሆይ፤ ኑሮን ለህይወት ‹አሽከሮች› ተውላቸው፡፡ አንተ ግን፤ ህይወትን እንደ ተረት ለመቀመር ትጋ›› እላለሁ፤ በጠቢቡ ሰለሞን የአነጋገር ለዛ፡፡   

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 19 September 2015 09:30

“አበል” ለዘላለም ትኑር!

    የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ነው። በእድሜ ገፋ ያሉት መምህር እጃቸው ቾክ በቾክ ሆኖ፣ ብላክቦርዱን በተዘበራረቁ መስመሮች፣ ቅርጾች፣ ቁጥሮችና ፊደላት ሞልተው  እያስተማሩ ነው። ተሜ ላይ የተመለከቱት ነገር ግን እንዲቀጥሉ የሚገፋፋ አልነበረም። ተማሪው ፊት ላይ ድብርት ይነበባል። መምህሩ በድንገት ማስረዳታቸውን አቁመው ያልታሰበ ጥያቄ ጠየቁ፤
“ይህንን ትምህርት መማራችሁ ለምን ይጠቅማችኋል?”
ጥያቄው በክፍሉ ውስጥ መነቃቃትን ፈጠረ።
 “ግን ይሄ ሳብጀክት ለምን ይጠቅማል?”
መምህሩ ተማሪውን ማፋጠጥ ይዘዋል።
“ይህንን ሳብጀክት ለምን ትወስዳላችሁ? ህይወታችሁ ላይ ምን ይጨምራል?”
አሳፋሪ ቢሆንም ከ50 የሚበልጠው የክፍሉ ተማሪ፤ የሚወስደው ኮርስ ለምን እንደሚጠቅመው አያውቅም። መምህሩ ንዴት፣ ብስጭት፣ መገረም----እየተነበበባቸው ይዘውት የመጡትን ጓዝ ሸክፈው ወደ መውጫው በር አመሩ። ክፍሉን ሙሉ ለሙሉ ከመልቀቃቸው በፊት ፊታቸውን ወደኛ መለስ አደረጉና . . .     “ቢያንስ ‘ላንተ ደሞዝ እንዲከፈልህ’ አትሉም?” አሉ፤በንዴት ተሞልተው።  ንግግራቸውን ተከትሎ በተሰማው ሳቅና ሁካታ ታጅበውም ከክፍሉ ወጡ።
ይህ የት/ቤት ትውስታ ትዝ ያለኝ አንድ የስልጠና ስብሰባ ላይ ተቀምጬ ነው። አሰልጣኙ ይናገራል፤ግን ከልቡ አይደለም። ሰልጣኙ ቦታ ቦታውን ይዞ አሰልጣኙን ይሰማል፤ ግን አያደምጥም። አሰልጣኙ ሀሳቡን ሰዎች ላይ ለማጋባት ይዳክራል፤ ግን የሚያምንበት አይመስልም። ሰልጣኙ አስተያየት ይሰጣል፤ልቡናው ግን በስልጠናው ላይ አይደለም፡፡
በዚህ ጊዜ ነው ያንን የት/ቤት ጥያቄ ለራሴ የጠየቅሁት፤ “ይህ ስልጠና ለምን ይጠቅማል?” መልሱ ግን ብዙ አልከበደኝም፡፡ የ10ኛ ክፍል መምህሬ እንዳሉት፤ስልጠናው የሚጠቅመው #አበል ለማግኘት ነው!; የዚህኛው የሚለየው  አበሉን የሚያገኙት መምህሩም ተማሪውም መሆናቸው ነው፡፡ ማንም ሰልጣኝ በምክንያትም ሆነ ያለምክንያት ከስልጠናው አይቀርም። ለምን ቢባል----- አበል ይቀርበታላ፡፡
በመሆኑም እያንዳንዱ ሰልጣኝ ባይሰማም ይመጣል። ባይስማማም ይቀመጣል። መጨረሻ ላይ የሚሰጠውን ‘ተስማሚ ነገር’ (አሞሌ) እያሰበ . . . . ባያነብም ይጽፋል።  የአለቆችን ትኩረት እየሻተ . . . ባይገባውም፣ ሳይገባውም ሀሳብ ይሰጣል። በአንደበቱ ደላይነት ብቃቱን ለማሳየት እየጣረ፤ ሹመት እየሻተ፤ ክብር እያሸተተ  . . . የሚያነበው እንደሌለ ቢያውቅም ሪፖርት ይጽፋል።  እንደማይተገበር ቢያውቅም እቅድ ያወጣል። ነገ ‘ይሻር’ ብሎ ድምጽ እንደሚሰጥ ቢረዳም ዛሬ ‘ይተግበር’ ብሎ እጁን ያወጣል። የ’ይገንባም’ የ’ይፍረስም’ ባለታሪክ ይሆናል። ዜማው ቢጎረብጠውም፣ ስንኙ ለነፍሱ ባይደርስም ይዘምራል። በደንብ ገብቶት የሚያቀነቅነው ግን “አበል ለዘላለም ትኑር” የሚለውን ዜማ ነው።
ተጠባባቂ አትሌት ለማጓጓዝ በጀት የሚያንሰው ፌዴሬሽን፣ ከ30 በላይ የስራ ሀላፊዎችን ምግብ፣ መኝታ፣ አበል ችሎ ባህር ማዶ ይልካል። ለዓመታዊ ክብረበአሉ መደገሻ መቶ ሺ ብሮች የሚመድብ ፋብሪካ፣ የሰራተኞች ደሞዝ ጭማሪ ሲጠየቅ ወገቤን ይላል፡፡
የተበላሹ መንገዶችን ጠግኖ ለመንቀሳቀስ ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ በጀት ያልጸደቀለት የሚመለከተው አካል /’የሚመለከተው አካል’ የሚለው አባባል ግን ላለመነካካት እንዴት አሪፍ ነው/ ብዙ ሺህ ብሮች መድቦ በመንገድ አጠቃቀም ዙሪያ ምርጥ የተባለች አውሮፓዊት ሀገር ላይ የልምድ ልውውጥ ያዘጋጃል። ለአዘጋጅ ኮሚቴው፣ አዘጋጅ ኮሚቴው ያዘጋጀውን ለሚቆጣጠረው የቁጥጥር ኮሚቴ፣ እንዲሁም ነገሮች ሁሉ በስርአት መከናወናቸውን ለሚታዘበው የስነስርዓት ኮሚቴ አበል የሚሆን በጀት ከየትም ብሎ ይከፍላል። ብቻ ‘አበል ለዘላለም ትኑር!’
በወጣቶች ጉዳይ ላይ እሰራለሁ የሚል ተቋምም ‘ወጣቱና የንባብ ልምድ’ የሚል አውደጥናት፣ ሦስት አነስተኛ ቤተመፃህፍት በሚገነባ በጀት ሲያዘጋጅ ትታዘባላችሁ፡፡ ለዚህ ሁሉ ማትጊያው አበል ነው፡፡ ታዲያ ትምህርትስ ለምን በአበል አይሆንም?
‹‹አበል›› ለዘላለም ትኑር!

Published in ህብረተሰብ

   ዘላኖች (አርብቶ አደር የሚል መጠሪያ ተሰጥቷቸዋል) በተፈጥሮአዊ የአኗኗር ዘይቤያቸው የተነሳ በአንድ አካባቢ ወይም ቦታ ረግተው አይቀመጡም. . .አይቆዩም፡፡ በየጊዜው ጓዛቸውን ተሸክመውና  በግመል አሸክመው መሄድ ነው-- ...መሄድ...መጓዝ....፡፡ የበረሃውን ሀሩር ሽሽት፤ ምግብና ውሃ፣ ለከብቶቻቸውም መኖ ፍለጋ .....ይሄዳሉ፣ይጓዛሉ፡፡የአዲስ አበባ ቤት ተከራዮችም እንዲሁ ናቸው፡፡ በአንድ ቤት ወይም ሰፈር አይረጉም...አይቆዩም፡፡ በየጊዜው እቃቸውን በአይሱዙና በፒክአፕ ጭነው መሄድ...ነው----መሄድ..መሄድ...ብቻ፡፡ የኑሮ ውድነቱን ሽሽት፤ ዋጋው ጣራ ያልነካ ወይም ከጣራው በላይ ያልዘለለ ቤት ፍለጋ---መጓዝ፡፡
ዘላኖች ቋሚ መንደር ወይም ቀዬ አልባ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ተከራዮችም ሰፈር አልባ ናቸው፡፡ የሥነልቦና ጫና ሰለባም ይሆናሉ፡፡ አንድ ቦታ ተረጋግቶ መኖር እንደማይቻል ማሰቡ የሚፈጥረው የስነልቦና ተፅእኖ፣ በየጊዜው እቃ ማስጫን ማስወረዱ፣ አዲስ ሰፈር የመላመዱ ፈተና፣ በተለይ ደግሞ ወላጆች ልጆቻቸውን በየጊዜው ከአንዱ የሰፈር ትምህርት ቤት ወደ ሌላ ሰፈር ትምህርት ቤት በማዘዋወር የሚያዩት ፍዳ ቀላል አይደለም፡፡
የአዲስ አበባ #ዘላኖች” ፤በአኗኗራቸው ሁኔታ ምክንያት ቤት ጎረቤት፣ እድርና  ማህበር አልባም ጭምር ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ የማህበራዊ ህይወት ወጎች ለተከራይ ቅንጦት ናቸው፡፡
በነገራችን ላይ የቤት ተከራዮች ዋንኛ አመታዊ ጭንቀት፣ኪራይ ይጨምር ይሆን ወይንስ አይጨምር ይሆን የሚለው ሳይሆን ስንት ይጨምር ይሆን የሚለው ነው፡፡ መጨመሩማ አይቀሬ ነው፡፡ እንደውም በነጋ በጠባው ኪራይ አለመጨመር በህግ ያስቀጣል ተብሎ የተደነገገ ነው የሚመስለው፡፡ ቤቱ ምንም ሳይለወጥ በየጊዜው ኪስን የሚያራቁት ኪራይ መቆለል፣ ለአከራዮች ሙዝ የመላጥ ያህል ቀላል ነው፡፡
ቆዳህን የላጡህ ያህል የሚሰማህ ግን አንተ ነህ - ተከራዩ. . . የአዲስ አበባው ዘላን!!
ደግሞ ለምን እንደሁ እንጃ፣ አከራዮች ሲባሉ የቤት ኪራይ መጨመሩን የሚገልፁት ወይ ጠዋት አልያም ማታ ላይ ነው፡፡ ጠዋት ወይም ማታ ላይ በር አንኳኩተው ወይም ስልክ ደውለው ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ይሄን ያህል ጨምሩ፡፡ አለቀ በቃ፡፡ ከቻልክ ትከፍላለህ፤ ካልቻልክ ትወጣለህ፡፡ ጭማሪው ከተሰማ በኋላ ቀኑ አንዴት እንደሚያልፍ ወይም ሌሊቱ እንዴት እንደሚነጋ አስቡት፡፡ ያው በጭንቀት ይዋላል፤በጭንቀት ይነጋል፡፡
ከገቢያችሁ በላይ የሆኑ  የቤት ኪራይና መሰል የኑሮ ጉዳዮች የሚፈጥሯቸው የወጪ ቀዳዳዎች መስፋት እንዴት ናላ እንደሚያዞር ለእናንተ መንገር ለቀባሪው እንደማርዳት ነው፤ ኑሯችሁን ታውቁታላችኋ፡፡
አንዳንድ አከራይ ደሞ አለ፡፡ መጨመሩ ላይቀር ከጭማሪው ጋር የሰበብ መዓት አግተልትሎ የሚመጣ፡፡ ትንሽ እያመመኝ ስለሆነ ለህክምና ብር ያስፈልገኛል ኪራይ ጨምር፤ ጤፍ፣ ምስር፣ ዘይትና በርበሬ ተወዷል ኪራይ ጨምር፤ እንዲህ ስለሆነ ነው ኪራይ ጨምሪ፣ እንዲያ ስለሆነ ነው ኪራይ ጨምሩ....ጨምሩ...ጨምሩ......፡፡ ኤዲያ ምንድነው በተከራይ ጫንቃ ላይ መወዘፍ (ጠብቆም ላልቶም መነበብ ይችላል) እኔ የህክምና ወጪ ደረሰኞቼን ባሳይ፣ የወሩን ኪራይ ይቀንሱልኛል? ጤፍ፣ ምስር፣ ዘይትና በርበሬ የሚጨምረውስ በአከራይ ላይ ብቻ ነው? ግርም እኮ ነው የሚለው፡፡
አንድ አከራይ ነበሩኝ፡፡ ግቢያቸው ተከራይቼ እንደገባሁ ከሰጡኝ ማስጠንቀቂያዎች መካከል መብራት እያበሩ (ቴሌቪዥን እያዩ፣ እያነበቡ ወይም ስራ እየሰሩ--) ማደር፣ ቤት ውስጥ ተጨማሪ ሰው ማስገባት አይደለም እግር የሚያበዙ ሌሎች ሰዎች መመላለስ ከጀመሩ ያለምንም ማስጠንቀቂያ የቤት ኪራይ እንደሚጨምር እወቅ-----የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡ ማስጠንቀቂያውን ሰጥተውኝ፣ ዱሮ ጠዋት ጠዋት በሬዲዮ በምንሰማው የቡናና ሻይ ማስታወቂያ ዜማ ስልት፤
የኢኮኖሚ ዋልታ ኪራይ ኪራይ
የገቢ ምንጫችን ኪራይ ኪራይ ...
የእድገታችን ገንቢ ኪራይ ኪራይ ..... እያሉ በኪራይ ሰብሳቢነታቸው እየተኩራሩ ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡ እኔም ማስጠንቀቂያውን በሚገባ ነበር ተግባር ላይ ያዋልኩት፡፡  ሌሊት ማንበብ ካለብኝ በሞባይል ባትሪዬ፤ ፊልምም ካየሁ በላፕቶፕ፣ ጓደኞቼም ካስፈለጉኝ፣ ሄጄ ቤታቸው ነበር የማገኛቸው፡፡
ሰውየው ኪራይ መጨመራቸው ላይቀር ሰበብ ይፈልጉ ነበርና አንድ ቀን ማታ ከስራ ስገባ ሳሎን ቤታቸው አስጠሩኝ፡፡ አየኸው!?»
ወደ 32 ኢንች ቴሌቪዥናቸው ዞር ስል፣ በቅርቡ የተመረቀ አንድ ትልቅ ህንፃ ማስታወቂያ ይተላለፋል፡፡ እሳቸው ቀጠሉ ማብራሪያቸውን፡-
«አለም አቀፉ የምጣኔ ሀብት ቀውስ በሁሉም ሀገራት ላይ ተፅእኖውን እያሳደረ ነው፡፡ ሰሞኑን ዜናው ሁሉ እሱ ነው፡፡ እውነቱን እኮ ነው፡፡... የኑሮ ወድነቱማ ሀገራችን ከገባ ቆይቷል፡፡ የሰሞኑ ደሞ ባስ ያለ ነው፡፡ አሁን በቀደም ዕለት ለልጆቼ ጫማና ልብስ ልገዛ መርካቶ ሄጄ . . . . . . »
ሰውየው ይሄን ሁሉ ለምን እንደሚነግሩኝ ቢያንስ ለጊዜው አልገባኝም ነበር፡፡ ድክም ብሎኝ ስለነበር ወሬያቸውም ከኑሮው ጋር ተዳምሮ ስልችት ስላለኝ ከልቤ አልነበረም የማዳምጣቸው፡፡ መጨረሻ ላይ ግን ያሉት ነገር የመጀመሪያውን አሰልቺ ልፍለፋቸውን ዳርዳርታ ግልፅ አደረገልኝ፡፡ በል እስኪ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ኪራይ ጨምር፡፡ ከገባሁ ገና 3 ወር እንኳን አልሞላኝም ብዬ ለመከራከር ባስብም የትም እንደማያደርሰኝ ስለገባኝ  እሺ ብዬ ወጣሁ፡፡
አስቡት እስኪ ኪራይ ለመጨመር ከምዕራቡ አለም የኢኮኖሚ ቀውስ እስከ መርካቶ የልጆች ልብስ ገበያ የሚደርስ ኢኮኖሚያዊ ትንታኔን ያዘለ ሰበብ፡፡
ከጨመሩ ዝም ብለው አይጨምሩም፡፡ ተከራይ እንደሁ ከመክፈል አልያም እቃውን ሸክፎ ቤት ፍለጋ ከመሰደድ ውጪ አማራጭ እንደሌለው ያውቁታል፡፡ ሀይ ባይ የለማ፡፡ ማን የሚጠይቃቸው አለ፡፡ ከሚመለከተው አካል የሚጠበቀው የአከራይ ተከራይ መመሪያ እንደሆነ የውሃ ሽታ ሆኗል፡፡ የከተማውን ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ችግር የሚፈታ የተባለለት የቤቶች ልማትም፣ ችግሩን ማቃለል አባይን በጭልፋ ሆኖበታል፡፡ በዚያ ላይ የኮንዶሚኒየም ቤት ገዝቶ አትርፎ መሸጡ የደራ ቢዝነስ ሆኗል፡፡
በአንድ በኩል በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ለህዝብ በእጣ ይከፋፈላሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እነ አጅሬ (የከተማይቱ ሀብታም የቤት ነጋዴዎች) ወደድ ሲል ለመሸጥ አልያም በውድ ለማከራየት በርካታ ቤቶችን ከህዝቡ ላይ ይገዛሉ፡፡
ሰው ስንት አመት ሲጠብቅ የኖረውን ቤት የማግኘት እድል ሲደርሰው እልል ብሎ በመቀበል ፈንታ የሚጠበቅበትን ክፍያ ለማሟላት ጭንቀት በጭንቀት መሆን ከጀመረ ከራረመ፡፡ ኮንዶምንየም ቤት ደርሷቸው ቅድሚያ ክፍያውን ለመክፈል ስንት እናቶችና አባቶች ልመና እንደወጡ፣ እራሱ ኮንዶምንየም ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ ይሄን ማድረግ ባለመፍቀዳቸው ወይም እርዳታ ለምነውም ስላልተሳካላቸው የመጣላቸውን እድል በውክልና ስም ለነጋዴ የሸጡትን ደግሞ ውልና ማስረጃ ይቁጠራቸው፡፡
እነዚህ ሰዎች የመክፈል አቅም አንሷቸው የሸጡትን ቤት ነገ መልሰው በውድ ዋጋ ተከራይተው ለመኖር ይገደዳሉ፡፡ አንዱ ሰፈር ሲወደድባቸው ወደ አንዱ፣ከዚያም ወደ ሌላው እያሉ እንዲሁ እንደ ዘላን ሲንከራተቱ ይኖራሉ፡፡
አንዱ የቤት ችግር ከአንዱ ሰፈር ወደ አንዱ ሰፈር የሚያላጋው አርቲስት፤ #ለምን ልጅ አትወልድም?; ተብሎ ሲጠየቅ፤ “እኔ ሰፈር የሌለው ልጅ መውለድ አልፈልግም” አይደል ያለው፡፡ ሸጎሌ ይረገዛል፣ ኮልፌ ይወለዳል፣ ሳሪስ ያድጋል (ቤተሰቦቹ ኪራዩን መቋቋም ከቻሉ እስከ 2 አመቱ)፣ ከዚያ አሁን ባለው ሁኔታ ጭማሪውን ችሎ አንድ ሰፈር ውስጥ ከሁለት አመት በላይ መቆየት ስለማይቻል ከቤተሰቡ እቃዎች ጋር በአይሱዙ እየተጫነ የዘላን ኑሮውን ይገፋል፡፡ ይሄንን ልጅ ሰፈርህ የት ነው ብሎ መጠየቅ፣ ውጤቱ ልጁን ማወዛገብ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ምን ብሎ ሊመልስ ይችላል?
እንደው ግን ለአዲስ አበባ ተከራይ የዘለቄታ መፍትሄው ምን ይሆን? አብረን የምናየው ይሆናል፡፡ እኔ ግን በቀጣዩ የአዝማሪዎች የቅብብሎሽ ግጥም ልሰናበታችሁ፡-  
ፈረንሳይ ባስጠይቅ ገባች አሉኝ አስኮ
ምን ታርግ ትልቀቅ እንጂ....
የዘንድሮ ኪራይ ያሳቅቃል እኮ
አስኮ ላይ ባስጠይቅ ገባች አሉኝ ገርጂ
መንግስትና አከራይ ለሰው እዘኑ እንጂ
ገርጂ ላይ ባስጠይቅ ሄዳለች አቡዋሬ
እዛ ይቀንሳል የሚል ሰምታ ወሬ
አቡዋሬ ባስጠይቅ ሄደች አሉ ሰሚት
ኮንዶሚኒየም ግቢ ይሻላል ብለዋት
ሰሚት ላይ ባስጠይቅ ሄዳለች ኮተቤ
እንክርቱዋን ሲያስብ ተሰበረ ልቤ
ኮተቤ ባስጠይቅ ገባች አየር ጤና
የገቢዋን እጥፍ ክራይ ከወሰደው ምን ሰላም አለና
አየር ጤና ስደርስ ሄዳለች ሰበታ
ከራቀ ቅናሽ ነው የሚል ወሬ ሰምታ
ሰበታ ባስጠይቅ ሄደች አሉኝ ገላን
መቼም ቋሚ የለው የከተማ ዘላን፡፡

Published in ዋናው ጤና

   ሻወር የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል ሲባል፣ እንዴት የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ በገላ መታጠቢያ ቤቶች ውስጥ የሚገኘው የሻወር ቧንቧ ጭንቅላት (Shower heads) እጅግ አደገኛ ለሆኑ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽኖች በሚያጋልጡ ባክቴሪያዎች የተሞላ በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የአሜሪካ የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
በመተንፈሻ አካላት ላይ ከፍተኛ የጤና ችግር ያስከትላሉ የተባሉት microbacterium በሚል ስያሜ የሚታወቁት ባክቴሪያዎች በተለይም የጋራ መጠቀሚያ በሆኑ መታጠቢያ ቤቶች ባሉ የሻወር ቧንቧ ጭንቅላቶች ውስጥ በስፋት የሚገኙ ሲሆን ቀዝቃዛ ውሃ የሚያወርዱ ሻወሮች ሙቅ ውሃ ከሚያወርዱት በበለጠ በባክቴሪያዎቹ የተሞሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ባክቴሪያዎች ታዲያ ሰዎች ሻወር ለመውሰድ ቧንቧውን ሲከፍቱ፣ በአየር ውስጥ በመሰራጨት በመተንፈሻ አካላቶቻችን ውስጥ ገብተው ለበሽታ ይዳርጉናል፡፡
ለዚህ መፍትሄው ንፅህና ነው ይላሉ - ባለሙያዎቹ፡፡ የሻወር ቧንቧ ጭንቅላቶች ቶሎ ቶሎ መታጠብና በተወሰነ የጊዜ ገደብ መቀየር እንደሚኖርባቸው የሚናገሩት የህክምና ባለሙያዎቹ፤ እንደ ሆስፒታሎች ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ሊቀየሩ እንደሚገባም ይገልፃሉ፡፡ በዓይን የማይታዩት እነዚህ በሽታ አምጪ ባክቴሪያዎች፤ በተለይ ህመምተኞችን፣ ህፃናትንና አቅመ ደካሞችን በይበልጥ ያጠቃሉ፡፡ የህክምና ባለሙያዎቹ፤ ከእነዚህ የጤና ችግሮች ለመጠበቅ ሻወር በምንወስድበት ጊዜ ምን አይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባን ይገልፃሉ፡-
የገላ መታጠቢያ ስፍራና የሻወር ቧንቧ ማውረጃ ጭንቅላቱ ሁልጊዜም ንፅህናው የተጠበቀ መሆን ይኖርበታል፡፡
ሻወር በሚወስዱበት ወቅት በመጀመሪያ የሚወርደውን ውሃ ገላዎ ላይ አያሳርፉ፡፡  ጥቂት ውሃ ከፈሰሰ በኋላ መታጠብ ይጀምሩ፡፡
የሻወር ቧንቧን ጭንቅላት በየጊዜው እያወረዱ፣ በሞቀ ውሃ ሙልጭ አድርገው ይጠቡት፡
አልፎ አልፎ የፈላ ውሃ በቧንቧው ውስጥ እንዲያልፍ ያድርጉ፡፡
በተለይ በተለያዩ በሽታዎች የሚሰቃዩ ሰዎች ገላቸውን በቁም ሻወር ከመታጠብ ይልቅ በገንዳ ቢታጠቡ ይመረጣል፡፡ ባክቴሪያዎቹ በህመም የተጐዳን ሰውነት በይበልጥ ያጠቃሉና!!

Published in ዋናው ጤና

     በልጆች ባህሪያትና የአስተዳደግ ጥበብ ላይ ትኩረት አድርጐ የተዘጋጀውና በወንደሰን ተሾመ መኩሪያ የተፃፈው “የልጆች ባህሪያትና የአስተዳደግ ጥበብ” መጽሐፍ ባሳለፍነው ሳምንት ገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለወላጆች፣ ለአሳዳጊዎች፣ ለመምህራን፣ ለአሰልጣኞች፣ ለአማካሪዎች እንዲሁም በልጆች ዙሪያ ለሚሰሩ ግለሰቦችና ተቋማት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው የተባለው መጽሐፉ፤ በልጆች አስተዳደግ አቀራረቦችና መሰረታዊ ዘይቤዎች፣ በልጆች ስብዕና ቀረፃ መሰረታዊ ክህሎቶች፣ ልጆች በተለያዩ የእድሜ ክልል ስለሚኖራቸው እድገትና የወላጆች ሚና በሚሉና በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ዳሰሳ አድርጓል፡፡
በ13 ምዕራፎች የተከፋፈለውና በ398 ገፆች የተመጠነው መጽሐፉ፤ ለአገር ውስጥ በ120 ብር፣ ለውጭ በ20 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡

     የተለያዩ የዓለም ጠቢባን አባባሎች ተሰባስበው የተጠናቀሩበትና በ44 ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረው “ጠቢባን ምናሉ” መጽሐፍ ገበያ ላይ ውሏል፡፡
ጥቅሶቹ በ1987 ዓ.ም ተሰብስበው የተተረጐሙ ቢሆንም ከ20 ዓመት በኋላ ለህትመት መብቃታቸውን የመጽሐፉ አዘጋጅ አብነት ስሜ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ጠቅሷል፡፡
ቅሶቹና አባባሎቹ የተለያዩ የህይወት ዘርፍና ክህሎት ጭማቂዎች በመሆናቸው ሌሎችን ያስተምራሉ በሚል መጽሐፉን ማዘጋጀቱንም ፀሐፊው ገልጿል፡፡ 22 ገፆች ያሉት መጽሐፉ በ60 ብር ከ70 ሳምንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡


የአንጋፋው ደራሲ የአበራ ለማ አዲስ ስራ የሆነው “ቅንጣት የኔዎቹ ኖቭሌቶች” አዲስ መጽሐፍ ዛሬ ከቀኑ 8፡00 -10፡30 ሰዓት በኢትዮጵያ ቤተ መፃሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ ይመረቃል፡፡ በአግዮስ ህትመትና ጠቅላላ ንግድ ኩባንያ የታተመው መጽሐፉ በምረቃው እለት በታዋቂው ሃያሲ አብደላ ዕዝራ ዳሰሳዊ ግምገማ እንደሚቀርብበትም ለማወቅ ተችሏል፡፡

 “የተያዙና ያልተያዙ ቦታዎች” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው 17ኛው ዙር የስዕል ትርኢት የፊታችን አርብ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እንደሚከፈት ጋለሪያ ቶሞካ አስታወቀ፡፡ የወጣቱ ሰዓሊ ቃልኪዳን ሾቤ ስራዎች የሚቀርቡበት የስዕል ትርኢቱ፤ለቀጣዩ ሁለት ወራት ለተመልካች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም የጋለሪያ ቶሞካ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ነብዩ ግርማ ገልጿል፡፡ ሳርቤት ካናዳ ኤምባሲ ፊት ለፊት በሚገኘው ጋለሪያ ቶሞካ ለእይታ የሚቀርቡት የሰዓሊው ሥራዎች፤ትርኢቱ በተከፈተ በወሩ የስዕል አፍቃሪዎች፣ሰዓሊያንና ተጋባዥ እንግዶች በታደሙበት ውይይት እንደሚደረግባቸውም ተጠቁሟል፡፡

  የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር፤ከመላው አገሪቱ አሰባስቦ በመሰረታዊ የስነ ፅሁፍ ትምህርት ላሰለጠናቸው ሰልጣኞች ዛሬ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ በቤተመዘክር እውቅና እንደሚሰጥ አስታወቀ፡፡ ማህበሩ ዘንድሮ ለሶስተኛ ዙር ከሐምሌ 6 ቀን እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2007 ዓ.ም ለሁለት ወራት  መሰረታዊ የሥነ ፅሁፍ ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ከተቋቋመበት መሰረታዊ አላማዎች አንዱ ተተኪ ፀሀፍትን ማፍራት ሲሆን በየዓመቱ ከመላው አገሪቱ አሰባስቦ ስልጠና መስጠቱም የተነሳበትን አላማ ለማሳካት እንደሆነ ተገልጿል፡፡  

Page 5 of 16