Friday, 11 September 2015 10:21

ሰው ሲያቅድ...

ጳጉሜ ተጋመሰች፡፡
ማክሰኞም ተጋመሰች፡፡
ጋዜጠኛው በረጅሙ ተንፍሶ ሰዓቱን ተመለከተ - 5፡53 ይላል፡፡
“ሜሎዲ ካፌ በረንዳ ላይ እንገናኝ” ብሎ የቀጠረው፣ ታዋቂው ድምጻዊ ኪሩቤል ወርቁ ከግማሽ ሰዓት በላይ ዘግይቷል፡፡ “ቃል” የሚል አዲስ አልበሙን ሊለቅ የተዘጋጀው ድምጻዊ ኪሩቤል፣ ለጋዜጠኛው የገባውን ቃል ሳያፈርስ አልቀረም፡፡ ከአሁን አሁን ይመጣል እያለ፣ አሻግሮ መንገዱን ሲያማትር የቆየው ጋዜጠኛው፣ ተስፋ ወደመቁረጡ ተቃርቧል፡፡
ትናንት ምሽት ለኪሩቤል ደውሎለት ነበር፡፡ አዲሱን አመት በማስመልከት ለህትመት በሚበቃው የጋዜጣው ልዩ ዕትም ላይ ሊሰራው ስላቀደው ነገር አወያይቶት ነበር፡፡ በጋዜጣው ላይ የመልካም ምኞት መግለጫ እና የአዲስ አመት ዕቅዳቸውን እንዲያስተላልፉ ከመረጣቸው ታዋቂ ግለሰቦች አንዱ እንደሆነ ነግሮታል፡፡ ኪሩቤልም ግብዣውን በደስታ ተቀብሎ፣ ሜሎዲ ካፌ እንገናኝ ብሎ ቀጥሮት ነበር - አልመጣም እንጂ፡፡
ጋዜጠኛው ሲያመነታ ቆይቶ፣ ምነው ዘገየህ ሊለው ወደ ኪሩቤል ደወለ፡፡
ኪሩቤል ቁርጡን ነገረው፡፡
“ሶሪ ፍሬንድ!... የአልበሜ ጉዳይ ቢዚ ስላደረገኝ መምጣት አልቻልኩም!... ሌላ ጊዜ ብናደርገውስ?...” አለው፡፡
“ጥ... ጥሩ!...” አለ ጋዜጠኛው ንዴቱን ለመሸሸግ እየሞከረ፡፡
ጋዜጠኛው ተናዷል፡፡ ጋዜጣው ማተሚያ ቤት ሊገባ ሁለት ቀናት ብቻ እንደቀሩትና፣ ጉዳዩ አስቸኳይ እንደሆነ ነግሮት ነበር፡፡ እሱ ግን፣ ቃለ-መጠይቁን ሌላ ጊዜ ብናደርገውስ የሚል የጅል ጥያቄ ጠየቀው፡፡ የአዲስ አመት መልካም ምኞቱን እንዲያስተላልፍና ዕቅዱን እንዲገልጽ የቀረበለትን ግብዣ፣ ለሌላ ጊዜ ቢሆንስ ብሎ ማራዘም ምን ማለት ነው?... ይህቺኛዋ ጳጉሜ ሄዳ፣ ሌላ ጳጉሜ ስትመጣ እንገናኝ ማለት አይደለምን?... አንድ አመት ሙሉ ታገሰኝ ማለት አይደለምን?...
ስልኩን ዘግቶ በንዴት ተነፈሰ፡፡
ከቢሯቸው ክበብ የቡና ዋጋ ሶስት እጥፍ ዋጋ የተቆረጠለትን፣ በይሉኝታ ተጠፍንጎ ያለ ዕቅዱ አዝዞ ፈጥኖ የቀረበለትን፣ የቅንጡዎችን የሜሎዲ ካፌ ቡና በንዴት ጨለጠው፡፡ መረረው፡፡ ውሃ ሊጠይቅ ወደ አስተናጋጇ ዞር ሲል፣ አይኖቹ ጥግ ላይ የተቀመጠ ሰው ላይ አረፉ፡፡ ጥቁር ማኪያቶ በጉማማ ጭስ የሚያወራርደውን ሰው በጥርጣሬ አየው፡፡ የሆነ ቦታ እንደሚያውቀው እርግጠኛ ነው፡፡ የት እንደሚያውቀው ለማስታወስ ሞከረ፡፡
ጋዜጠኛው ተሳካለት፡፡ ሲጋራውን እየማገ አቀርቅሮ ሲያነብ የሚያየው ይህ ሰው ጆኒ ነው፡፡ በአጋጣሚው ተገረመ፡፡ አምና በዚህ ወቅት ተገናኝተው ነበር፡፡ መገናኘታቸው ብቻም አይደለም ጋዜጠኛውን የገረመው፡፡ የተገናኙት ለተመሳሳይ ጉዳይ መሆኑ ጭምር እንጂ፡፡ ጆኒ ታዋቂ ሰዓሊ ነው፡፡ አምና በዚህ ወቅት የአዲስ አመት መልካም ምኞቱን እንዲያስተላልፍና የአዲስ አመት ዕቅዱን እንዲገልጽ ጠይቆት፣ በፈቃደኝነት አጭር ቃለ መጠይቅ አድርገው ነበር፡፡ ቃለመጠይቁም በጋዜጣው የአዲስ አመት ልዩ ዕትም ላይ ለንባብ በቅቶ ነበር፡፡
“ለምን ዘንድሮም አልጠይቀውም?...” ሲል አሰበ ጋዜጠኛው፡፡
ሃሳቡን መላልሶ አጤነው፡፡ ኪሩቤል ቀጠሮውን ስለሰረዘ፣ ሌላ ታዋቂ ሰው ከመጠየቅ ወደ ኋላ ሊል አይገባውም፡፡ ጆኒም ከኪሩቤል ያልተናነሰ ዝነኛ ሰው ነው፡፡ ኪሩቤል ያልመለሰውን ጥያቄ፣ ወደ ጆኒ ሊያዞረው ይችላል፡፡ እርግጥ አምና በዚህ ወቅት፣ መልካም ምኞቱንና የአዲስ አመት እቅዱን ጠይቆት፣ ፈቅዶ በዝርዝር ነግሮት ነበር፡፡ ካልጠፋ ታዋቂ ሰው፣ ዘንድሮም እሱን መጠየቅ አግባብነት ላይኖረው ይችላል፡፡ ቢሆንም ከጊዜው መጣበብ አንጻር፣ ሌላ ታዋቂ ሰው ከሚፈልግ፣ ከፊቱ ያገኘውን ጆኒን ቢጠይቀው ምንም አይደለም፡፡
ጋዜጠኛው ፈራ ተባ እያለ ወደ ጆኒ አመራ፡፡
“አስታወስከኝ?...” እጁን ለሰላምታ እየዘረጋ ጠየቀው፡፡
“ኖ!... አ... አይ ሚን...” ጆኒ እላቂ ሲጋራውን መኮስተሪያው ላይ እየደፈጠጠ፣ ግራ በመጋባት አንጋጦ እያየ መለሰለት፡፡
“አክቹዋሊ ረጅም ጊዜ ሆኖናል!...” ፈገግ እንዳለ ጨበጠው፡፡
“ይ... ይሆናል...” አሁንም ግራ ተጋብቷል ጆኒ፡፡
“መቀመጥ ይቻላል?...” ወደ ባዶው ወንበር ጠቆመ፡፡
“ኦፍኮርስ!...” እንዲቀመጥ ጋበዘው፡፡
“የሚገርም አጋጣሚ ነው!... ምናልባት ካልረሳህ አምና በዚህ ወቅት...” ብሎ ጀመረና የእውቂያቸውን ሰበብ መተረክ ቀጠለ፡፡
“ኢትዝ አሜዚንግ!... በጣም ተለውጠሃል!... ጋዜጠኝነት ተስማምቶሃል ማለት ነው?...” ጆኒ ተገርሞ ጠየቀው፡፡
ሲያወሩ ቆዩ፡፡
“በጣም ይቅርታ ግን!... አጋጣሚውን ለመጠቀም ብዬ ነው... አንድ ሁለት ሶስት አንቀጽ አጠር አድርገህ መልካም ምኞትህንና የአዲስ አመት ዕቅድህን ከነገርከኝ በቂ ነው!...” በስተመጨረሻ ጋዜጠኛው እያግባባ ጠየቀው፡፡
ጆኒ አመነታ፡፡ ባለፈው አመት መናገሩን በማስታወስ፣ የዘንድሮው መደጋገም ይሆናል ሲል አስተባበለ፡፡
ጋዜጠኛው አልተረታም፡፡ ያለፈው አመት አምና ማለፉን ጠቅሶ፣ ለዘንድሮው ደግሞ ቢሰጥ ችግር እንደሌለው ተናገረ፡፡
ጆኒ አሳበበ፡፡ ስለ አዲሱ አመት የሚያወራበት ጥሩ ሙድ ላይ አለመሆኑን አዲስ ሲጋራ እየለኮሰ ገለጸ፡፡
ጋዜጠኛው እንደ ዋዛ የጆኒን ሲጋራ አያት፡፡ ከሲጋራዋ ጭስ ውስጥ አዲስ መላ እየተጥመለመለ ሲወጣ ታየው፡፡ ደስ አለው፡፡
“አሪፍ አይዲያ መጣልኝ!... ስለ አዲሱ አመት ለመናገር ጥሩ ሙድ ላይ ካልሆንክ፣ ለምን ስለ አሮጌው አመት አናወራም?...” አለው በደስታ ተውጦ፡፡
“ማ... ማለት?...” ሰዓሊው ግራ ተጋብቶ መልሶ ጠየቀው፡፡
ጋዜጠኛው ፈጥኖ አልመለሰም፡፡ እንዴትስ ፈጥኖ ሊመልስ ይችላል?... አሪፍ ያለው ድንገተኛ ሃሳቡ፣ ከለኮስከው ሲጋራ ላይ ብልጭ ያለ ነው ብሎ ይንገረው?... አምና በዚህ ሰዓት ስጠይቅህ እኮ፣ በአዲሱ አመት ሲጋራ የማቆም እቅድ እንዳለህ ነግረኸኝ ነበር!?... አልተውክም እንዴ?...” ብሎ ያስቀይመው?... በፍጹም!...
ተለሳልሶ ጠየቀው፡፡
“ለምን ካለፈው አመት እቅድህ ምን ያህሉን እንዳሳካህ ጠይቄህ ጋዜጣችን ላይ አናወጣውም?...”
ጆኒ ከጭሱ ጋር እየተጫወተ ዝም አለ፡፡
“አይሻልም?...” በልመና ድምጽ ጠየቀው፡፡
“አሪፍ ሃሳብ ነበር... ግን... ሰዓት የለኝም...” ታዋቂው ሰዓሊ ሰበብ ፈጠረ፡፡
“አታስብ!... እኔም ከኤዲተሬ ጋር ቀጠሮ ስላለብኝ፣ ብዙ ሰዓት አልፈጅም!...” አለና ምላሹን ሳይጠብቅ መቅረጸ-ድምጹን ከኪሱ አውጥቶ አፉ ስር ለገታት፡፡
ቃለ-መጠይቁ ተጀመረ፡፡
“ታዋቂው ሰዓሊ ዮሃንስ ታዬ... ያለፈው አመት ላንተ እንዴት ነበር?...”
“አ... አሪፍ ነበር!...”
“ለአመቱ ከያዝካቸው እቅዶችህ ምን ያህሉን አሳካህ?...”
“ብዙዎቹን ያሳካሁ ይመስለኛል!... ለመዘርዘር ትንሽ ያስቸግራል...”
“ለምሳሌ ባለፈው አመት በዚህ ወቅት ስጠይቅህ፣ አገር አቀፍ የስእል ኤግዚቢሽን የማዘጋጀት እቅድ እንደነበረህ ገልጸህልኝ ነበር፡፡ ተሳካልህ?...”
“ምን ይሳካል!?... በኤግዚቢሽኑ ላይ የማቀርባቸውን ስዕሎቼን አዘጋጅቼ ጨርሼ፣ አዳራሽ አልፈቅድ ብለውኝ ሳላቀርብ ቀረሁ!... ከእኔ የሚጠበቀውን ሁሉ በእቅዴ መሰረት አከናውኜ ብጨርስም፣ በቢሮክራሲ ሳቢያ እቅዴ ሳይሳካ ቀርቷል!... እውነቴን ነው የምልህ!... ጥበብ በቢሮክራሲ ገመድ እየታነቀች ስትቃትት የምትኖርበት አገር ውስጥ ነው ያለነው!... ያሳዝናል!... እኛ አገር ጠቢብን እና ሚስጥር ኪስን ከጉዳይ የሚጥፋቸው ሰው የለም!...” አለና ከደረት ኪሱ የመዘዛትን ሌላ ሲጋራ ለኮሳት፡፡
ጋዜጠኛው ከሲጋራዋ ውስጥ ሌላ ጥያቄ መዘዘ፡፡
“ሌላው ዕቅድህ ደግሞ፣ በአዲሱ አመት ሲጋራ ማቆም ነበር... እሱስ?...”
“በየት በኩል አቆማለሁ!?... እስኪ አንተን ልጠይቅህ?... ትልቅ ተስፋ ያደረግህበት፣ ሌት ከቀን የደከምክበት፣ ለወራት የለፋህበት ኤግዚቢሽንህ በቢሮክራሲ ሳቢያ ተሰናክሎ ሲቀር፣ ሲጋራ ይቅርና ሱረት አታጨስም?...”
“እሱስ እውነትክን ነው!... ሌላው ደግሞ... ባለፈው አመት ስጠይቅህ... በአዲሱ አመት ከእጮኛህ ጋር ትዳር መስርተህ አዲስ ህይወት የመጀመር እቅድ እንዳለህ ነግረኸኝ ነበር...”
“ማን?... እኔ?...” ሰዓሊው ደንገጥ ብሎ አቋረጠው፡፡
“አ... አዎ!... ት... ትዝ ይልህ እንደሆን... በህዳር አካባቢ ወደ እጮኛህ ቤተሰቦች ሽማግሌ ለመላክና...”
“ኦ!... እሱን ነው እንዴ?... እሱማ ምን ሆነ መሰለህ... እጮኛዬ አንተ ያደረግክልኝን ቃለ-መጠይቅ ከጋዜጣችሁ ላይ አንብባ በነጋታው እሳት ለብሳ እሳት ጎርሳ መጣችና፣ጥንብ እርኩሴን አውጥታ አትሰድበኝ መሰለህ?!...”
“ለ... ለምን?...”
“ካስታወስክ... ቃለ መጠይቁ መጨረሻ ላይ... #ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም አዲስ አመት እመኛለሁ” ብዬ አልነበር?... እሱን አንብባልህ... #እኔ ሜላት ከዘጠና ምናምን ሚሊዮን ህዝብ ጋር ተደባልቄ መላው የምባል ተራ ሰው አይደለሁም!... ስሜን ጠርተህ ሃፒ ኒው ይር ብትለኝ ምን ይጎድልብሃል!?...; ብላ ሰድባኝ በቆምኩበት ጥላኝ ሄደች!... ከዚያች ቀን ጀምሮ አይቻት አላውቅም!...” አለና ሲጋራውን አጥብቆ መጠጣት፡፡
ጋዜጠኛው በሃዘኔታ አናቱን ወዘወዘና ወደ ሌላ ጥያቄ ተሻገረ፡፡
“እሺ ታዋቂው ሰዓሊ ዮሃንስ ታዬ... ሌላው ደግሞ... #አዲሱ አመት ያስቀየምኳቸውን ሰዎች ይቅርታ የምጠይቅበት የይቅርታ አመት ይሆናል” ብለኸኝ ነበር...”
ሰዓሊው ፈገግ ብሎ ጣልቃ ገባ፡፡
“አይደል?...” ሃፍረት ነገር ተሰምቶታል፡፡
“እንዴት ነው ታዲያ?... ምን ያህል ያስቀየምካቸውን ሰዎች ይቅርታ ጠየቅክ?...” ፈገግ ብሎ ጠየቀው፡፡
“በእውነቱ እንደዛ ያልኩት እንኳን፣ ሌሎች ሰዎች ሲሉ ስለሰማሁ ብቻ ነበር!... የምሬን ነው የምልህ!... እኔ በተፈጥሮዬ ሰው ማስቀየም አልወድም፡፡ ያስቀየምኩት ሰው የለም!... ምናልባት ቅድም ትታኝ ሄደች ያልኩህን እጮኛዬን ካገኘኋት፣ ይቅርታ እጠይቃታለሁ፡፡ ዛሬ እዚህ ካፌ የመጣሁት ራሱ፣ ምናልባት ባገኛት ብዬ ነው...” አቀርቅሮ የማኪያቶ ሲኒውን ማሽከርከር ቀጠለ፡፡
ጋዜጠኛው ያለፈውን አመት ቃለመጠይቅ ለማስታወስ እየሞከረ ሌላ ጥያቄ ሰነዘረ፡፡
“ሌላው ደግሞ... በአዲሱ አመት የተቸገሩትን ለመርዳት ዕቅድ አለኝ ብለኸኝ ነበር፡፡ ይሄኛው ዕቅድህስ ተሳካ?...”
ሰዓሊው ረጅም የመደነቅ ሳቅ ሳቀ፡፡
“አቦ እናንተ ጋዜጠኞች ደግሞ!... ለጨዋታ ያህል ያልኩህን ሁሉ ጽፈኸዋል እንዴ?...”
ጋዜጠኛው ለሰዓሊው ጥያቄ የፈገግታ መልስ ሰጠና ወደ ሌላ ጥያቄ ተሻገረ፡፡
“እ... ሌላም ነገር አስታወስኩ... ትዝ ይለኛል... #በአዲሱ አመት ላሊበላ እና አክሱምን የመሳሰሉ የቱሪስት መስህቦችን የመጎብኘት እቅድ አለኝ; ብለህ ነበር፡፡ የትኞቹን የቱሪስት መስህቦች ጎበኘህ?...”
“እውነቱን ለመናገር የተቻለኝን ጥረት ሳደርግ ብቆይም፣ እስካሁን ድረስ የትኛውንም አልጎበኘሁም...”
“ስለዚህ እሱም አልተሳካም ማለት ነው?...” ጋዜጠኛው ተገርሟል፡፡“ለምን አይሳካም?... ይሳካል እንጂ!... ምን ማለትህ ነው?...” ሰዓሊው ተናዷል፡፡
“ማ... ማለቴ... ያው አመቱ አልቋል ብዬ ነው...”
“ምነካህ!?... ዛሬ’ኮ ገና ጳጉሜ ሁለት ነው!... ዛሬ ማታ በአውሮፕላን ተሳፍሬ፣ ነገ ላሊበላን ጎብኝቼ፣ ከነገ ወዲያ ጧት አዲስ አበባ ከተፍ ማለት ያቅተኛል?...”
“ኧ... ኧረ አያቅትህም!... ምናልባት የአውሮፕላን ትኬት ካጣህ ብዬ ነው...” ለማስተባበል ሞከረ፡፡ሰዓሊው በንዴት ጦፎ ሰዓቱን ተመለከተና አስተናጋጇን ፍለጋ በፍጥነት ዞር አለ፡፡“ታዋቂው ሰዓሊ ዮሃንስ ታዬ... በስተመጨረሻም... አዲሱን አመት በማስመልከት ለጋዜጣችን አንባቢያን የምታስተላልፈው መልዕክት ይኖራል?...”“አለኝ እንጂ!... በጣም አለኝ!... #አንዳንድ ግለሰቦች አመት ሊቀየር ሲል ጠብቀው፣ የአዲስ አመት ዕቅዳቸውን በተመለከተ የሚናገሩትን ነገር በሙሉ የምር አድርጋችሁ አትውሰዱት” ስል ለጋዜጣችሁ አንባቢያን መልዕክቴን አስተላልፋለሁ...” አለና ወደ አስተናጋጆቹ ዞሮ ጮክ ብሎ በንዴት ተናገረ፡፡ “ማነሽ አስተናጋጅ?... እቸኩላለሁ አላልኩሽም!?... ቢል አምጪልኛ!?...”

Published in ልብ-ወለድ
Friday, 11 September 2015 10:18

የፀሐፍት ጥግ

  (ስለ ሳንሱር)
ማንኛውንም ዓይነት ሳንሱር አበክሬ እቃወማለሁ፡፡
ዶን ጆንሰን
ባኮሪያ ምንም መንግሥታዊ ሳንሱር የለም፡፡
ቦንግ ጁን-ሆ
ሳንሱር ልክ እንደ ችሮታ ከቤት መጀመር አለበት፡፡ ነገር ግን ከችሮታ በተለየ መልኩ እዚያው ማዎም ይኖርበታል፡፡
ክላሬ ቡዝ ሉሴ
ለዕድገት የመጀመሪያው አስፈላጊ ሁኔታ የሳንሱር መወገድ ነው፡፡
ጆርጅ በርናርድ ሾው
በብዙ የዓለም ክፍሎች ስላለው ሳንሱር እጨነቃለሁ፡፡
ጂማ ዋልስ
ዓለም ዘላለማዊ የሚላቸው መፃህፍት የራሳቸውን ውርደት የሚያጋልጡ ናቸው፡፡
ኦስካር ዋይልድ
ሰውን ዝም ስላሰኘኸው ለወጥከው ማለት አይደለም፡፡
ጆን ሞርሌይ
መፃህፍት ታግደው አይቀሩም ሃሳች ዘብጥያ አይወርዱም፡፡
አልፍሬድ ዊትኔይ ግሪስዎልድ
ምንጊዜም መፃህፍት ሲቃጠሉ ሰዎችም በመጨረሻ መቃጠላቸው አይቀርም፡፡
ሁንሪክ ሄይን
ብዙ ጊዜ ሳንሱር አድራጊው ከመድረሱ በፊት ራሳችንን ሳንሱር እናደርጋለን፡፡
ስፓይክ ሊ-
ማንንም ለማስደሰት ብዬ ራሴን ፈፅሞ ሳንሱር አላደርግም፡፡
ናታሊያ ኪልስ
የሰዎችን ህልም ሳንሱር ማድረግ አትችልም፡፡
ሮቢን ሂችኮክ
ዘፋኙን እንጂ ዘፈኑን መከርቸም አትችልም፡፡
ሃሪ ቤላፎንቴ

Published in ጥበብ

      በዘመን መለወጫ የጊዜ ክፍል ቁጭ ብዬ፤ 2008 ዓ.ምን አሻግሬ እያየሁ፤ ጉርምስና የወጪ እየጋበዘኝ ነው፡፡ የእርሱን ግብዣ እያጣጣምኩ ሳለሁ፤ ሽምግልና ወዲያ ሆኖ ይጠቅሰኛል፡፡ በእነሱ መሐል ተቀምጬ፤ ሣምንት ካስተዋወቅኳችሁ የዜን መነኩሴ ታሪክ ጋር ቀጣይ ወግ ይዣለሁ፡፡
ሣምንት ትረካውን ያቆየሁት፤ መነኩሴው አውሮፕላን አስነስተው፤ በተመረጠ የጠላት ዒላማ ላይ ሃራኬሪ ሰርተው፤ ለሐገራቸው ጃፓን የሚውሉላትን ውለታ እያሰላሰሉ፤ ግዳጃቸውን ይጠባበቁ እንደ ነበር ገልጬ ነበር፡፡ የጃፓኑ ንጉሥ ሂሮሂቶ፤ ሽንፈትን ከመቀበል ይልቅ፤ እንደዋዛ ነገር የሞት ጽዋን ጨልጦ፤ ምድርን መሰናበት ከሚቀለው የጃፓን ህዝብ ፊት ቆሞ ‹‹ተሸንፈናል›› ብሎ ለመናገር የሚያስገድድ ችግር ውስጥ ገብቷል፡፡
ተከታታይ የአውሮፕላን ጥቃት በማድረግ፤ በበቀል ስሜት የተነሳሳ መንፈሷን ማርገብ የተሳናት አሜሪካ፤ ምድር እና ሰማይን ከሚያርድ፤ በአንድ ደቂቃ ከ200 ሺህ በላይ ዜጎችን እንደ ቅጠል የሚያረግፍ የአቶሚክ ቦምብ የጫነ አውሮፕላን ወደ ሂሮሽማ ላከች፡፡ በሂሮሽማ የደረሰባት ድንጋጤ ሳይላቀቃት፤ ናጋሳኪ ላይ አስፈሪው የጦር አውሮፕላን በጃፓን ሰማይ ሥር ማንዣበብ ጀመረ፡፡ ህልቆ መሳፍርት የሌለው የሂሮሽማ እና የናጋሳኪ ከተማ ህዝብ ለሞት እና ለአካል ጉዳት ተዳረገ፡፡ ከዚህ አደጋ ፊት የቆመውና ከጀርመን እና ከጣሊያን ጋር ተሰልፎ የሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ሲዋጋ የቆየው የጃፓን ንጉሥ ከሽንፈት ደጅ ቆሞ፤ ለውሳኔ ተቸግሯል፡፡
በጃፓን ህዝብ ዘንድ እንደ አምላክ የሚታየው ንጉሡ ሂሮሂቶ፤ ፍፁም የሚያንገሸግሽ ነገር ቢሆንበትም፤ እንደ አምላክ የመታየት እና የመከበር ዘልማድ፤ በግብዝነት እንዲወስን እና ከእውነት ጋር እንዲጣላ ሳያደርገው፤ ሐገሩን እና ህዝቡን ከጥፋት ለማዳን ሲል ‹‹እጅ መስጠት አለብን›› አለ፡፡ ስለዚህ፤ ኃያሏን አሜሪካ ተለማምጦ ሰላም ለማውረድ ወሰነ፡፡
ሆኖም፤ በንጉሡ ምክር ቤት መቀመጫ ያላቸው ሦስት የጦር መኮንኖች ‹‹እርቅ ማድረግ አይሞከርም›› ብለው አስቸገሩ፡፡ እንዲያውም፤ ‹‹አሜሪካን ድል ለማድረግ የሚያስችል ይዘን ያቆየነው ምስጢራዊ የጦር ዕቅድ አለን›› እያሉ ንጉሡ እርቅ እንዳያደርግ ወተወቱ፡፡ እንደ ህፃን እያለቀሱ እና ከእግሩ ሥር እየተንደባለሉ፤ ንጉሣቸውን አጥብቀው ለመኑት፡፡
ብልሑ ንጉሥ ሂሮሂቶ አቅሙን አውቆታል፡፡ ስለዚህ የወታደሮቹ ልመና አበሳጨው፡፡ ተቆጣ፡፡ ተቆጥቶም፤ ‹‹እኔ የምፈልገው ከጦር አበሮቹ (እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና አሜሪካ) የቀረበውን የእርቅ ሐሳብ መቀበል ብቻ ነው›› ብሎ እቅጩን ነገራቸው፡፡ እንዳለውም አደረገ፡፡ ታዲያ ንጉሡ ‹‹ጦርነቱ አብቅቷል›› የሚል ድብዳቤ ለኃያላኑ መንግስታት ለመስደድ መወሰኑን የሰማው የጃፓን የመከላከያ ሚኒስትር አናሚ፤መሬት ላይ ወድቆ እተንከባለለ ንጉሡ እርቅ እንዳያደርግ ቢለምነውም፤ የወታደሮቹ ባዶ ጀግንነት ከጥፋት በቀር የሚጠቅም ነገር እንደማያመጣ የተገነዘበው እና በአስተዋይ መንፈስ የተጤነ ታላቅ ውሳኔ ያደረገው ሂሮሂቶ፤ ‹‹የእርቁን ሐሳብ ተቀብያለሁ›› የሚል ደብዳቤ ለጦር አበሮቹ ሐገራት ሰደደ፡፡ ይህ ውሳኔ፤ መሪ የመሆን ሸክምን እና መሪ መሆን የሚጠይቀው የመንፈስ ፅናት ምን እንደሚመስል፤ ለሰው ልጆች ሁሉ የሚያስተምር ታሪካዊ ውሳኔ በመሆን በዓለም የታሪክ መዝገብ ሰፍሯል፡፡
በአንፃሩ፤ ‹‹እርሱ ከሞተ ወዲያ በህይወት መቆየት ምን ይረባኛል›› ብለው ሃራኬሪ ሊያደርጉ ይችሉ የነበሩት የጦር ጀነራሎች፤ንጉሥ ሂሮሂቶ የሰጡትን ምክር ገፋ አድርጎ፤ ‹‹የእርቁን ሐሳብ ተቀብያለሁ›› በማለቱ በእጅጉ ቢያዝኑም፤ በውሳኔው ተቆጥተው ክፉ ለማድረግ አልተነሳሱም፡፡ እርግጥ፤ የንጉሡ ውሳኔ አበሳጭቷቸው፣ በቁጣ እና በቁጭት ስሜት ተገፋፍተው ክፉ ነገር ከማድረግ አይመለሱም የሚል ሥጋት ስለነበር፤የእርቅ ሐሳቡ በተገለፀበት ቀን፤ ንጉሥ ሂሮሂቶ ሌሊቱን አሳቻ ቦታ ተደብቆ ነበር ያደረው፡፡
እንደተገለፀው፤ የጦር ጀነራሎቹ ንጉሠ ነገስታቸውን ለመድፈር ባይሞክሩም፤ ለቁጣቸው ማስታገሻ የሚሆን ነገር የፈለጉ ይመስል፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ሱዙኪን የመኖሪያ ቤት አቃጠሉት፡፡ ሆኖም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ሱዙኪ አስቀድሞ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ጠርጥሮ፤ እርሱም እንደ ንጉሡ ተደብቆ ስለነበር ከጥቃቱ አመለጠ፡፡
ጀግናው ንጉሥ ሂሮሂቶ በማግስቱ ማልዶ ተነሳና፤ እንደ አምላክ በሚያዩት ጃፓናዊያን ፊት ቆሞ፤ እንደ ሞት የሚጠሏትን ቃል ከአንደበቱ እንድትወጣ ፈቀደ፡፡ ‹‹ጦርነቱ አብቅቷል›› አለ፡፡ ይህን ቃል በጃፓን ህዝብ ፊት ቆሞ መናገር፤ የቀለጠ ብረትን ሳይሳሱ ከመጠጣት ሊቆጠር እንደሚችል የማይረዳው የጃፓናውያንን ባህል የማያውቅ ሰው ብቻ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ፤ በዚያ ጊዜ ከታላቅ ጅግንነት ሊቆጠር የሚችለው፤ የገዛ ሽጉጥን ጠጥቶ መገላገል ወይም ሻምላን ከእንብርት ላይ ቀብቅቦ ራስን ማጥፋት አልነበረም፡፡
ሂሮሂቶ፤ ሳንጃ ከሆዱ ሰክቶ በክብር ቢሞት፤ የክብር አክሊል ደፍቶ ምድርን መሰናበት ይችል ነበር፡፡ በሞቱ፤ ውርደትን ከእርሱ ያርቃት ነበር፡፡ ሆኖም፤ በአንድ ጊዜ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ጃፓናውያንን ህይወት የሚቀጥፈው የአቶሚክ ቦምብ ከሰማይ መዝነቡን ሊገታው አይችልም፡፡ ከጃፓናውያን ባህል እና አመለካከት አንፃር ለሂሮሂቶ፤ የሞት ሞት ተደርጎ ሊቆጠር የሚችለው፤ ህዝብን ከመከራ ለመጠበቅ፤  ‹‹ተሸንፈናል›› የሚል ቃል ከአንደበት ማውጣት ነበር፡፡ እናም፤ ንጉሡ አደባባይ ወጥቶ፤ ‹‹ጦርነቱ አብቅቷል›› ባለ ጊዜ፤ እርሱ አሥር ጊዜ ቢሞትም፤ ሐገሩን እና ህዝቡን ከሺህ ሞት አትርፏል፡፡
ሂሮሂቶ ‹‹ጦርነቱ አብቅቷል›› ብሎ ሲያውጅ፤ የጦር ሚኒስትሩ ሃራኬሪ አደረገ፡፡ ዋና ዋና የሚባሉ የጃፓን ጀነራሎችም በተመሳሳይ እራሳቸውን አጠፉ፡፡ ታናካ የሚሉት አንድ ጀነራል፤ አዋጁ ይፋ ከተደረገበት ደቂቃ ጀምሮ፤ ማንም ሰው በንጉሡ ላይ እጁን እንዳያነሳ ቀን እና ሌሊት ሲጠብቅ ቆየ፡፡ ከዚያም፤ ንጉሡ ደህና መሆኑን በዓይኑ አይቶ ለማረጋጥ በማሰብ ወደ እልፍኝ ሄደ፡፡ እልፍኝ ገብቶ የንጉሡን ደህንነት አረጋገጠ፡፡ ከዚያም እጅ ነስቶ በመውጣት፤ ሃራኬሪ አደርጎ ከሞት ጋር ተቃቅፎ ወደቀ፡፡ ሞተ፡፡ ጀነራል ታናካ ሞተ፡፡
ጀነራል ታናካ በተስፋ መቁረጥ እና አጥንት በሚሰብር ውርደት ጫና ውስጥ ቢወድቅም፤ ማስተዋልን አጥቶ፤ ወታደራዊ መሐላውን አፍርሶ ሐገሩን የሚጎዳ ነገር ከመፈፀም የሚያቅብ የመንፈስ ጽናት እንደ ነበረው በተግባር አረጋግጧል፡፡ ሆኖም፤ ከዚያ አሻግሮ የሚወስድ የመንፈስ ኃይል አልነበረውም፡፡ ስለዚህ ‹‹ውርደትን›› በሞት ገንዞ እና ከፍኖ ወደ መቃብር መውረድን መረጠ፡፡
የንጉሡ ታሪክ፤ በዋና ባለታሪካችን ላይ ግርዶሽ ሰርቶ እንደከለላቸው ተረድቻለሁ፡፡ ሆኖም፤ የመነኩሴው ታሪክ ከንጉሡ ታሪክ ጋር የተያያዘ በመሆኑ፤ የንጉሱ ታሪክ መወሳቱ ተገቢ ነው፡፡ ‹‹የዜን መነኩሴ ለመሆን የበቃሁበት አጋጣሚ›› በሚል ታሪካቸውን ያጫወቱን መነኩሴ፤ የመንግስትን የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ጥሪን ተቀብለው፤ ወታደራዊ ሥልጠና ሲወስዱ ቆዩ፡፡ ከዚያም ለአጥፍቶ መጥፋት ተልዕኮ ዝግጅት ሲዘጋጁ ቆይተው፤ ንጉሡ ‹‹ጦርነቱ አብቅቷል›› ብሎ ሲያውጅ፤ የእምነት መሠረታቸውን የሚያነዋውጽ ፈተና ወደቀባቸው፡፡
ህይወትን በፈቃዱ ተሰናብቶ፤ ከሞት ጋር ሲተሻሽ ከከረመ በኋላ፤ በግድ ወደ ህይወት የተመለሰው ያ ወጣት፤ መልሶ ከህይወት ጋር መታረቁ ከበደው፡፡ ሳያመነታ ወደ ሞት ለመሄድ ተዘጋጅቶ የነበረው ልቡ፤ ድንገት ቀኝ ኋላ ዙር ተብሎ ወደ ህይወት ሲመለስ፤ ነፍሱ በሥነ ልቦና ቀውስ ታመሰች፡፡ በንጉሡ ውሳኔ ቀስማቸው የተሰበረ በርካታ ጃፓናውያን ከፎቅ ላይ እየተወረወሩ ሲሞቱ በማየት ሐዘን ልቡን አንጎዳጉዶታል፡፡
በዚህ ዓይነት ድባብ እና የስሜት ሁከት እንደጎበጠ፤ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ከገባበት የሥልጠና ካምፕ ወጥቶ፤ ግብዙን ሆኖ በቶኪዮ ጎዳና መንከራተት ጀመረ፡፡ በጦርነቱ ሳቢያ የሚሄድበት አድራሻ እና ሐዘን ተጋሪ የቅርብ ዘመድ ጭምር ያልነበረው ያ ወጣት፤ አስቸጋሪ ፈተና ላይ ወደቀ፡፡ ከሞት ወዲያ ማዶ ያለው ዓለም ሊቀበለው ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ አካሉ የሚዘዋወርበት እና በፈቃዱ ጥሎት ሊሄድ የነበረው ምድራዊው ህይወት  ፊት ነስቶታል፡፡ አባት እና እናቱን ጨምሮ ብዙ ዘመዶቹ የጥለውት የሄዱት ይህ ምድራዊ ዓለም፤ ዘመድ አልቦ ወና ሆኖበታል፡፡ ህሊና እና መንፈሱ እንዲህ ዓይነት ጨካኝ የህይወት ሐቅ ውስጥ የተቀረቀረበት ያ ወጣት፤ በቶኪዮ ከተማ ለጊዜው እንኳን የሚጠጋበት ታዛ አልነበረውም፡፡ ለሞት የተሰናዳ መንፈሱ፤ ለህይወት ዝግጁ መሆን ተስኖት ተቸግሯል፡፡ በዚህ ጊዜ፤ ያለፈ የህይወት መንገዱን መለስ ብሎ መመርመር ጀመረ፡፡ ምድረ - ህሊናውን የሚያናውጥ፤ ምድረ - መንፈሱን ቁና የሚያደርግ፤ ነፍሱን እንደ ቅማል የሚያፍተለትል፤ ህሊናን እንደ ደረቅ ሎሚ የሚጨምቅ፤ የእውነት ቅጽበት መጣ፡፡ ልብን ማህለቅት የለሽ በሆነ የጥያቄ ወጀብ የሚመታ፤ እንደ ሱናሚ ባለ አስፈሪ ማዕበል የሚንጥ፤ በጥያቄ እሣተ ጎመራ የሚገለባብጥ፤ የእውነት ቅጽበት ወረደ፡፡
ለ12 ዓመታት የተማረው የአስኳላ ትምህርት፤ መንፈሱ እና ሐሳቡ በዛለበት በዚህች ሰዓት ምርኩዝ በመሆን፤ ለአንድ ቀን ዕድሜም ቢሆን ወደፊት ለመጓዝ የሚያስችል የህሊና ስንቅ እንዳልሰጠው ተረዳ፡፡ ለመከራ ጊዜ መደገፊያ የሚሆን ጥበብ እንዳላስታጠቀው አወቀ፡፡ ትምህርቱ ከህይወትም ሆነ ከሞት ጋር ሊያስታርቀው አልቻለም፡፡ ለዓመታት ሲያደክመው ቆይቶ፤ ዛሬ አውላላ ሜዳ ጥሎት ኮበለለ፡፡
ከመሞቱ በፊት የሞተው ወጣት፤ መልሶ ከህይወት ለመታረቅ የሚያስችል ጥበብ ሊሰጠው ያልቻለውን የአስኳላ ትምህርት ረገመ፡፡ በእንዲህ ያለ ስሜት እየተናጠ ማደሪያ ፍለጋ ተነሳ፡፡ ቀኑን ሙሉ በቶኪዮ ጎዳናዎች ሲንከራተት የዋለው ወጣት፤ አመሻሹ ላይ ሌሊቱን የሚያሳልፍበት ጥግ ለማግኘት ሲያስብ፤ በከተማው ዳርቻ ከሚገኝ አንድ ገዳም በቀር ሌላ መጠጊያ አልታየውም፡፡ ስለዚህ ወደዚያ ለመሄድ ወሰነ፡፡
ይህ ሞት እና ህይወት ያደሙበት ወጣት ወደ ገዳሙ ቅጽር ገብቶ፤ የገዳሙን አስተዳዳሪ ወይም መምህር አገኛቸው፡፡ መጀመሪያ እንዳሰበው፤ ማደሪያ እና ቁራሽ እንጀራ መጠየቁን ትቶ፤ ሌላ ጥያቄ አቀረበ፡፡ ‹‹አባቴ ለመማር ፈልጌ መጥቻለሁና እባክዎን ተቀብለው ያስተምሩኝ?›› አላቸው፡፡
በዚህ በእኛ ሐገር፤ አመንኩሱኝ ብሎ ወደ ገዳም የሄደን ሰው፤ አመክሮ ሳይሰጠው ዕለቱን እንደ ማይቀበሉት፤ ትምህርት ፍለጋ ወደ ዜን መምህር የሚሄድ ሰው፤ በቀላሉ ተቀባይነት አያገኝም፡፡ የዜን መምህራን ‹‹ዓለምን ንቄ፤ የእውነት መንገድ ናፍቄ መጣሁ›› ያላቸውን ሰው ሁሉ አይቀበሉም፡፡ እንዲያውም፤ ተማሪው በተግባር እና በመንፈስ በብዙ ይመዘናል፡፡ መነኩሴው እንዲህ በማለት ይቀጥላሉ፤
‹‹ምን ልታደርግ መጣህ?›› አሉኝ የገዳሙ አለቃ፡፡
‹‹የገዳሙ አለቃ የሆኑት መምህር በትውልድ ቅብብሎሽ በየጊዜው እየተሳለ፤ ከእርሳቸው በደረሰ ጥበብ፤ የመንፈስ ይዞታዬን ለመረዳት ሲጣጣሩ፤ እኔ በህሊናዬ የማስበው ሌላ ነበር፡፡ ‹‹አንተ በከንቱ ትለፋለህ፡፡ እኔ እንደሁ ቸግሮኝ እንጂ የአንተን አሮጌ ጥበብ ለመማር ፈልጌ አይደለም፡፡ አስራ ሁለት ዓመት ያባከንኩበት ትምህርት ይኸው ለጅብ ሰጥቶኝ፤ አውላላ ሜዳ ላይ ጥሎኝ ሲሄድ አይቻለሁ›› እያልኩ አስብ ነበር፤ በልቤ፡፡
***
ከብዙ ምርመራ በኋላ፤ በእኔ ችክ ማለትና በቅዱስ የርህራሄ ስሜት የተሸነፉት መምህሬ፤ በጊዜአዊነት ተቀበሉኝ፡፡ የምበላውን ከሰጡኝ በኋላ፤ ነባር ልማድ በመሆኑ፤ ሰፊውን የገዳሙን ግቢ እንዳፀዳ አዘዙኝ፡፡ በምድረ ግቢው ከበቀሉት ትላልቅ ዛፎች ከረገፉ ቅጠሎች በቀር ብዙ ቆሻሻ የማይታይበትን ቅጽረ ግቢ መጥረግ ጀመርኩ፡፡ ከኔ ራቅ ባለ ሥፍራ በዝምታ ተቀምጠው የነበሩት መምህር፤ ጽማዌ የሚንፀባረቅበት ገጽታ እንደተላበሱ የምሰራውን ሥራ ይከታተሉ ነበር፡፡ ግቢውን ጠርጌ እንደጨረስኩ፤
‹‹አባቴ፤ ቆሻሻውን የት ላድርገው?›› ስል ጠየቅኩ፡፡
እርሳቸውም፤ ‹‹በዚህ ምድር ቆሻሻ የሚባል ነገር የለም›› በማለት ተግሳጽ በመሰለ አኳኋን ምላሽ ሰጡኝ፡፡
ደነገፅኩ፡፡ ትምህርት አንድ አልኩ፡፡
የገዳሙ ማህበረሰብ ማለዳ ተነስተው ለተመስጦ ከመቀመጣቸው በፊት፤ ለብ ባለ ውሃ ገላቸውን ይታጠባሉ፡፡ ስለዚህ፤ ‹‹ቅጠሉ የገላ መታጠቢያ ውሃ ለማሞቅ ያገለግለናል፡፡ በዚያ ጆንያ ጠቅጥቀህ ወደ ጓሮ ወስደህ አስቀምጠው›› አሉኝ፡፡
ቅጠሉን በጆንያ መጠቅጠቅ ጀመርኩ፡፡ አያያዜ ያላስደሰታቸው እኒያ የ80 ዓመት አዛውንት፤ ከእኔ በቀለጠፈ አኳኋን ቅጠሉን በጆንያ ሲጠቀጥቁ አይቼ፤ የእኔ የአካል ብቃት ከዚያ አዛውንት በእጅጉ እንደሚያንስ ተመልክቼ አዘንኩ፡፡ የ12 ዓመታት ትምህርቴ፤ በአካል፣ በአዕምሮም ሆነ በመንፈስ ረገድ የሰጠኝ አንዳች ብቃት አለመኖሩን ተገነዘብኩ›› የሚሉት መነኩሴው፤ ትረካቸውን ይቀጥላሉ፡፡ እኔ ግን በዚህ የዘመን መለወጫ ዋዜማ ላይ ሆኜ፤ ስለ ትምህርት ጥያቄ ማንሳት ፈለግኩ - እንደ መደምደሚያ፡፡
መደምደሚያ
መነኩሴው ትምህርት አንድ … ሁለት … እያሉ ብዙ ያስተምሩናል፡፡ እኔ ግን፤ የመንኩሴውን ታሪክ ተከትዬ ለማንሳት የምፈልገው ጥያቄ፤‹‹በሐገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም በሚገኙ የትምህርት ተቋማት የሚሰጠው ትምህርት ህሊናችንን ለሚጎተጉቱ እና መሠረታዊ ለሆኑ የህይወት ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት የሚያግዘን ነውን?›› የሚል ነው፡፡ ለራሴ ይህን ጥያቄ አቅርቤ፤ ከአዕምሮዬ ያገኘሁት ምላሽ፤ ‹‹በፍፁም፤ አይደለም›› የሚል ነው፡፡
እንኳን ጥያቄዎቹን ለመመለስ፤ ለማክረር እንኳን የሚያግዝ ትምህርት አይሰጥም፡፡ ለህይወት ብቁ የሚያደርግ ትምህርት ሳይሆን ለቢሮ እና ለፋብሪካ ሥራዎች ብቻ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚጥር ትምህርት ነው፡፡ ያም ሆኖ፤ በሥራ ረገድ ተመዝኖም ብዙ ጉድለት የማይገኝበት አይደለም፡፡ የዚህ ችግር ሰለባ የሆነው እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለንም፡፡
እውነተኛ መምህር እና እውነተኛ ተማሪ ከዓለም ጠፍተዋል፡፡ ስለ እውነት ሞትን ለመቀበል የሚደፍረው፤ የመጨረሻው እና እውነተኛው መምህር ከዘመናት በፊት ሔምሎክ ጠጥቶ ሞቷል፡፡ እውነተኛው መምህር ከክርስቶስ ልደት በፊት በ399 ዓመተ ዓለም ሞቶ ተቀብሯል፡፡ የመጨረሻው መምህር ሶቅራጥስ (470-399 ቅ.ል.ክ) በአቴና ሲሞት፤ በእግሩ የተተኩት የዘመናችን መምህራን፤ እውነትን ለንግድ ጥቅም ሊሸጡ የሚችሉ፤ እውነት እና ዕውቀት የብሔራዊ (ቡድናዊ) ጥቅም ማዳወሪያ ሲሆኑ ማየት የማይገዳቸው ሆነዋል፡፡
‹‹ዘላለማዊ ከሆነው እና ከማይሞተው የሰው ልጆች መፍለቂያ ይግቡ›› የሚል ኃይለ ቃል ከመግቢያው በር የሚያስነብበው፤ እውነተኛው ት/ቤት (አካዳሚ)፤ያ የመጨረሻው ት/ቤት፤ ዛሬ የሸፋጮች፣ የሸቃጮች እና የአጭበርባሪዎች ደብር ሆኗል፡፡ ታዲያ፤እውነተኛ ትምህርት፣መምህር እና ተማሪ ከየት ይገኛል? አዲሱ ዘመን፤ ለህይወት የሚረባ ትምህርትን በራሳችን ጥረት ለመቅሰም የምንችልበት ዘመን እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡ መልካም ዘመን ለውድ አንባቢያን፡፡   

Published in ጥበብ


    ካለፈው የቀጠለ
የሀገራችን የባሕረ ሐሳብ ሊቃውንት የሚጠቀሙበት የጊዜ ስሌት እንደሚከተለው ነው።
1 ዕለት = 60 ኬክሮስ
1 ኬክሮስ = 60 ካልዒት
1 ካልዒት = 60 ሣልሲት
1 ሣልሲት = 60 ራብዒት
1 ራብዒት = 60 ኀምሲት
1 ኀምሲት = 60 ሳድሲት
በዚህ መሠረት አንድ ዓመት 365 ዕለት እና 15 ኬክሮስ ይባላል። 15 ኬክሮስ ሩብ ዕለት ወይም 6 ሰዓት ነው። በሌላ አገላለፅ 1 ኬክሮስ 24 ሰዓት ስለሆነ 15 ኬክሮስ 360 ደቂቃ ነው። 360 ደቂቃ ደግሞ 6 ሰዓት ነው።
365 ዕለት፣ 5 ሰዓት፣ 48 ደቂቃ እና 46 ሰከንድ የተባለው አንድ ዓመት በባሕረ ሐሳብ የጊዜ ክፍፍል 365 ዕለት፣ 14 ኬክሮስ፣ 30 ካልዒት፣ 11 ሣልሲት እና 30 ራብዒት ይሆናል። የ11 ደቂቃ እና 14 ሰከንድ ጉድለት የተባለው በባሕረ ሐሳብ ቅመራ መሠረት ጉድለቱ 29 ካልዒት፣ 48 ሣልሲት እና 30 ራብዒት ነው የሚሆነው። 5 ሰዓት፣ 48 ደቂቃ እና 46 ሰከንድ ሲጠጋጋ 6 ሰዓት እንደሚሆነው ሁሉ 14 ኬክሮስ፣ 30 ካልዒት፣ 11 ሣልሲት እና 30 ራብዒት ወደ 15 ኬክሮስ ይጠጋጋል።
የዓመቱ ዕለት እና ዝርዝሩ ከላይ እንደተቀመጠው ነው፤ ለልዩ ንጽጽር የተፈለገ ለየት ያለ ቀመር ግን ይታያል። ይኸ ቀመር አንድን ዓመት 365 ዕለት፣ 15 ኬክሮስ እና 6 ካልዒት ያደርገዋል።
በዚህ አካሔድ 15 ኬክሮስ ራሱ ተጠጋግቶ የተገኘ ሆኖ ሳለ እንደገና 6 ካልዒት ተጨምሯል። 6 ካልዒት 2 ደቂቃ እና 24 ሰከንድ ነው። ይህ በየዓመቱ በትርፍ የሚገኘው 6 ካልዒት በ600 ዓመት ውስጥ ተጠራቅሞ አንድ ዕለት ይሆናል። 6 x 600= 3600 ካልዒት= 60 ኬክሮስ= አንድ ዕለት። 2 ደቂቃ እና 24 ሰከንድም በ600 ሲበዛ 24 ሰዓት ወይም አንድ ዕለት ይሰጠናል።
እንግዲህ በየዓመቱ በተጠጋጋ ተረፍ የሆነው 6 ሰዓት በ 4ዓመት ተጠራቅሞ 24 ሰዓት ወይም አንድ ዕለት አስግቶኝ ጳጉሜን በ4 ዓመት አንዴ  6 እንደሚያደርጋት ሁሉ የ6 ካልዒት ትርፍ በእርግጥ ካለ (የአለ ግን አይመስለኝም) በ600 ዓመት አንዴ ጳጉሜ 7 ትሆናለች።
ችግሩ ያለው አንድ ዓመት 365 ዕለት፣ 14 ኬክሮስ፣ 30 ካልዒት፣ 11 ሣልስት፣ እና 30 ራብዒት መሆን ሲገባው 365 ዕለት፣ 15 ኬክሮስ እና 6 ካልዒት መባሉ ላይ ነው። እንኳን ሌላ 6 ካልዒት ጨምረን ይቅርና 15 ኬክሮስ ስንል ራሱ 29 ካልዒት፣ 48 ሣልሲት፣ እና 30 ራብዒት ያለአግባብ ጨምረን ነው። 6 ካልዒት ሲታከልበት አለአግባብ የሚጨመረው 35 ካልዒት፣ 48 ሣልሲት እና 30 ራብዒት ያለ አግባብ ይሆናል። ይኸ አካሔድ በመደበኛው አቆጣጠር በዓመት የ11 ደቂቃ እና የ14 ሰከንድ የሆነው ትርፍ ወደ 13 ደቂቃ እና 38 ሰከንድ ከፍ ያደርገዋል።  በመደበኛው አካሔድ በየዓመቱ ያለአግባብ የተጨመረው የ11 ደቂቃ እና የ14 ሰከንድ (29 ካልዒት፣ 48 ሣልሲት፣ እና 30 ራብዒት) በ600 ዓመት ተጠራቅሞ የሚሆነው 146 ዕለት፣ 7 ሰዓት እና 40 ደቂቃ ነው። በየ4 ዓመቱ አንድ ዕለት ጳጉሜ ላይ እየጨመርን ስለምንሔድ በ600 ዓመት ጭማሪው ዕለት 150 ዕለት ይሆናል። በአግባቡ ሲሰላ ግን በ600 ዓመት መጨመር የነበረብን (7 ሰዓት እና 40 ደቂቃውን ለጊዜው ወደ ጎን አድርገን) 145 ዕለት ብቻ ነው። ይህ ማለት በ600 ዓመት ውስጥ አለአግባብ 5 ዕለት አክለናል። አለአግባብ አልፎ የታከለውን 5 ዕለት እንቀንስ ቢባል ቅናሹን በብዙ አሠራር ማከናወን ይቻላል። እዚህ ግን ጳጉሜን በ600 ዓመት 7 ሊያደርጋት የሚችለውን አሠራር አቀርባለሁ።
በ600 ዓመት ውስጥ 5 ዕለትን መቀነስ ቀላል ነው። ዘዴው በየ100 ዓመቱ አንድ ዕለት ማንሳት ነው። በዚህ ጊዜ ግን በ600 ዓመት ቅናሻችን 6 ዕለት ይሆናል። ይህን ለማስተካከል አንድ ዕለት መልሰን መጨመር አለብን። ያኔ በ600 ዓመት አንዴ ጳጉሜን 7 እናደርጋለን።
የዚህን የመቀነስ አሠራር በሚከተለው ምሳሌ እንመልከት።
ዓ.ም    ዘመኑ    ጳጉሜ የነበረው    ጳጉሜ ሲስተካከል
100    ዮሐንስ    5    4
200    ዮሐንስ    5    4
300    ዮሐንስ    5    4
400    ዮሐንስ    5    4
500    ዮሐንስ    5    4
600    ዮሐንስ    5    4
599    ሉቃስ    6    7
700    ዮሐንስ    5    4
800    ዮሐንስ    5    4
900    ዮሐንስ    5    4
1000    ዮሐንስ    5    4
1100    ዮሐንስ    5    4
1200    ዮሐንስ    5    4
1199    ሉቃስ    6    7

ዓ.ም     ዘመኑ    ጳጉሜ የነበረው    ጳጉሜ ሲስተካከል
1300    ዮሐንስ    5    4
1400    ዮሐንስ    5    4
1500    ዮሐንስ    5    4
1600    ዮሐንስ    5    4
1700    ዮሐንስ    5    4
1800    ዮሐንስ    5    4
1799    ሉቃስ    6    7
1900    ዮሐንስ    5    4
2000    ዮሐንስ    5    4
2100    ዮሐንስ    5    4
2200    ዮሐንስ    5    4
2300
2400    ዮሐንስ    5    4
2399    ሉቃስ    6    7


በምሳሌው እንደተመለከተው፣ በየ100 ዓመቱ በዮሐንስ ዓመት 5 ይሆን የነበረውን ጳጉሜ 4 ስናደርግ በ600 ዓመት ውስጥ 6 ዕለት እንቀንሳለን። ከዚህ ላይ አንድ ዕለት እንደገና እንቀስና በ600 ዓመት አንድ ጊዜ፣ በመደበኛው አካሔድ በሉቃስ ዘመን 6 ይውል የነበረውን ጳጉሜ 7 እናደርገዋለን። ይኸ የጠቅላላውን ቅናሽ ወደ 5 ዕለት ያወርደውና ተገቢው ቦታ ያስቀምጠዋል። የዘመን ቆጠራችን በዚህ ወይም በሌላ አካሔድ ባለመስተካከሉ ምክንያት ባለፉት 2000 ዓመታት 17 ዕለት ትርፍ ተጠራቅሞብናል። እሱ ተቀንሦ ቢሆን ኖሮ በመጪው በ2008 ዓ.ም መስከረም 11 የምንለው ዕለት መስከረም 18 ይሆን ነበር። በምሳሌው እንደተመለከተው፣100 ዓ.ም ጀምሮ እየተገበርነው መጥተን ከሆነ (ቢሆን) በ599 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ፣ በ1199 ለሁለተኛ ጊዜ፣ በ1799 ለሦስተኛ ጊዜ ሆና ለ4ኛ ጊዜ ደግሞ በ2399 ዓ.ም ከ391 ዓመት በኋላ ጳጉሜ 7 ትሆን ነበር።
እንግዲህ ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ በ600 ዓመት ውስጥ ጳጉሜ 7 መሆን የምትችለው ተገቢውን ሌላ ቅናሽ ካደረግን ነው። ከዚያ ውጭ ያለው ግን አሳማኝ አይመስልም።
ማጠቃለያ
በዓለማችን ላይ ካሉት ሁለት ዋና ዋና የዘመን አቆጣጠሮች አንዱ የጨረቃ፣ ሁለተኛው የፀሐይ ነው። ሁለቱም በሰማያዊ አካላት እንቅስቃሴ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ጨረቃን፣ ፀሐይን እና ከዋክብትን የመሳሰሉ ሰማያዊ አካላትን መሠረት አድርጎ ዘመን መቁጠርን የጀመሩት ኢትዮጵያውያን ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ግምት አለ። ይህ ዕውቀት መጀመሪያ ወደ ግብጻውያን ቀጥሎ ደግሞ ወደ ሌሎች ዓለማት እንደተሠራጨ ይገመታል።
አሁን ኢትዮጵያ የምትጠቀመው የዘመን አቆጣጠር ከቀረው ዓለም ሙሉ በሙሉ የተለየ አይደለም። ከሞላ ጎደል ከጁሊያን ዘመን አቆጣጠር ጋር አንድ ነው። ያ መሆኑ ምንም አያሳፍርም። አቆጣጠሩ ግን እንከን አለው። በ400 ዓመት ውስጥ ከሦስት ዕለት በላይ የሆነ ጊዜ ይጨምርብናል።
የግሪጎርያውያን የዘመን አቆጣጠር ከጁሊያን ይለያል። የግሪጎርያውያን ቆጠራ ማለት የተስተካከለው የጁሊያን ቆጠራ ማለት ነው። አቆጣጠራችንን በጁሊያን ማስተካከል ማለት ባህላችንን መልቀቅ አይደለም። እውቀትን እያሻሻሉ መሔድ እንጂ እንደ እምነት ቃል ሙጭጭ ብሎ ማምለክ አደጋ ይኖረዋል። ማስተካከያውን ከጁሊያንም በተሻለ በዑመር ኻያም አካሔድ ልናስተካክለው እንችላለን። ማስተካከሉ ግን የግድ አስፈላጊ አይደለም። ማስተካከያው ምናልባት አስፈላጊ ባይሆን እንጂ ሊቃውንቶቻችን ይኸ አይጠፋቸውም። ይስተካከል ከተባለ እስካሁን ድረስ 10 ዕለት (17 ም ሊሆን ይችላል) ያህል ትርፍ የመጣውን መጀመሪያ መቀነስ። ይኸ በብዙ መልኩ ሊደረግ ይችላል። አንደኛ ልክ አዲስ ዓመት ሲገባ መስከረም 2 ላይ 10 ጨምሮ መስከረም 12 ብሎ መጀመር። ሁለተኛው ዘዴ አስሩን ትርፍ ዕለት ጳጉሜ 5 በሚውልበት ሁለት ዓመት ውስጥ ከነሐሴ 30 ወደ መስከረም 1 መሸጋገር። ወይም ደግሞ ለሚቀጥሉት አርባ ዓመታት ጳጉሜ በሁለት ዓመት 5 ብቻ እንድትሆን ማድረግ። በዚህ ዓይነት አለአግባብ የተጨመረው 10 ዕለት ይነሳል።
የ10 ዕለት ማስተካከያ ከተደረገ በኋላ በ400 ዓመት ውስጥ ለ400 ተካፍለው የዜሮ ቀሪ በማያመጡበት ዓመታት አንድ ወደ ኋላ ሔዶ በሉቃስ ዘመን ውስጥ ጳጉሜ ከ6 ይልቅ በ 5 እንድትቀጥል ማድረግ። ለምሳሌ 2000 ዓ.ም ለ400 ሲካፈል ቀሪው ዜሮ ነው። ከዚያ በፊት ባለው በ1999 ጳጉሜ 6 ትሆናለች። በ2099፣ በ2199 እና በ2299 ላይ ግን ጳጉሜ በ5 እንድትቀር ይደረጋል። በዚህ አካሔድ በ400 ዓመት ውስጥ 3 ዕለት መቀነስ እንችላለን።
ማስተካከያው በዑመር ኻያም ቀመር መሠረት ይደረግ ከተባለም ቀላል ነው። በዚህ የዘመን አቆጣጠር የምናደርገው በ33 ዓመት ውስጥ 8 ዕለት መጨመር ነው። [በጁሊያን አካሔድ ግን 8 ዕለት የሚጨመረው በ32 ዓመት ውስጥ ነው።] የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር ለማስተካከል ከተፈለገ ለጊዜውም ቢሆን ከዑመር ኻያም አቆጣጠር ይልቅ የጁሊያኑን ብንከተል ከቀሪው ዓለምም ጋር ስለሚያስማማን አይከፋም። በዋናነት መረዳት ያለብን ግን የዘመን አቆጣጠራችን በዓለም ላይ የሌለ እና መሳይ የሌለው አይደለም። ሁለተኛ ደግሞ ፍፁም አይደለም። እንከን አለበት። መለወጡ ግን የግድ አስፈላጊ አይደለም። እንዲያውም በኔ አስተያየት መለወጡ አያስፈልግም፤ አደጋም አለው፤ በዚሁ መቀጠል አለብን። የዘመን አቆጣጠር ዕውቀታችንን ግልጽ አድርጎ መወያየት፣ ማሳወቅ እና መመርመር ግን ይኖርብናል። መለኮታዊ ባናደርገው ጥሩ ነው። ዕውቀታችንን እየገለጥን፣ እየመረመርን እና እያሻሻልን ብንጓዝ ኖሮ አሁን የዓለም ጭራ ሆነን አንቀርም ነበር። ያለፈ አልፏል። አሁን ግን መንቃት አለብን። ከስር የሚቀጥል ከሌለ የሊቃውንቶቻችን ጥበብ ኋላ ቢፈለግ አይገኝም። እኔ ለሀገራችን የባሕረ ሐሳብ (የዘመን ቆጠራ) ሊቃውንት ያለኝ አድናቆት ከፍተኛ ነው። እነርሱ ድንቅ ምሁራን ናቸው። ከዓለም ስንት እርምጃ ቀድመን እየተራመድን ሳለን ቀሪው ዓለም በየት በኩል እንደቀደመን ግን አይገባኝም።
ዋቢ መጻሕፍት፡- የዘመን ቆጠራን ጉዳይ በቀላሉ እና በግልጽ ከሚያስረዱ የሀገራችን መጻሕፍት ውስጥ እኔ በቅጡ ያነበብኳቸው የጌታቸው ኃይሌ ባሕረ ሐሳብ (1993 ዓ.ም)፣ የአለቃ ያሬድ ፈንታ ባሕረ ሐሳብ (2004 ዓ.ም) እና የክንፈ ሚካኤል ዳባ መሠረታውያን ቋሚ የዘመን መቁጠሪያዎች (2000 ዓ.ም) ናቸው። ሌሎችም ማለፊያ መጻሕፍት አሉ።

Published in ጥበብ

    ያለፈው ዓመት ጥሩ የሚባሉ ስራዎችን የሰራሁበት ዓመት ነው፡፡ ሁለት ልጓሞቼን (ወርቅ በወርቅና፣ ሄሮሺማን) በቪሲዲ፣በዲቪዲ ለተመልካች ያቀረብኩበት ዓመት ነበር፡፡ የህዳሴውን ዋንጫም ይዘን ኢትዮጵያን የዞርኩበት ዓመት ነው፡፡ ዘመናዊ  ሲኒማ ቤትና የስፖርት ላውንጅ ግንባታም የጀመርኩበት ዓመት ነው፡፡ በብዙ መልኩ ለኔ ስኬታማ ዓመት ነበር፡፡
ቦሌ አካባቢ ያስገነባሁት ሲኒማ ቤት፣በአዲሱ ዓመት ሥራ ይጀምራል፡፡ መደበኛ ስራዎቹ እንደተጠበቁ ሆነው ሌላ አዲስ ፊልም የመስራት እቅድም አለኝ፡፡

Published in ጥበብ

      ያለፈው የስራ ዘመናችን መጠነኛ ነበር፡፡ የስራ እንቅስቃሴዎቹ ደህና ናቸው፡፡ ያለፉት አመታት ላይ አጥልቶ የነበረው የስራዎች መጓተት በዚህኛውም ላይ አጥልቶ ነበረ፡፡ በዚህ ምክንያት እንቅስቃሴያችን መጠነኛ ነበር፡፡
በቀጣይ አመት ግን ብሩህ ተስፋ እናያለን፡፡ በኢህአዴግ ጉባኤ ላይ እንደተገለፀው፤የመልካም አስተዳደር ችግር ተቀርፎ፣ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የማጠናከሪያ ድጋፍ እየተደረገ ይሄዳል የሚል እምነት አለን፡፡ የሪል እስቴት ግዢና ሽያጭ ህግም ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እሱም በሪል እስቴት ላይ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ይኖረው ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ መጪው ጊዜ ብሩህ ነው ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብም ሰላም፣ ጤናና፣ ፍቅር ይብዛለት!

Published in ጥበብ

   አንጋፋዋ ድምፃዊት አስቴር አወቀና ማዲንጎ አፈወርቅ ለአዲስ ዓመት ዋዜማ ዛሬ ምሽት  በጊዮን ሆቴል የሙዚቃ ኮንሰርት ያቀርባሉ፡፡ ከቀኑ 10፡30 ላይ የኮንሰርቱ መግቢያ በሮች እንደሚከፈቱ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡
የዝግጅቱ አስተባባሪ አቶ እዩኤል ልዑልሰገድ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤በኮንሰርቱ ላይ ድንገተኛ (surprise) እንግዳ የሚኖር ሲሆን እንግዳው 2 ወይም 3 ዘፈኖችን ያቀነቅናል፡፡ አስቴር በዋዜማው ኮንሰርት 25 ዘፈኖችን የምታቀርብ ሲሆን ማዲንጎ 8 ወይም 9 ዘፈኖችን እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡
የ2008 አዲስ ዓመትን ለመቀበል ከሌሊቱ 6 ሰዓት ላይ የርችት ተኩስ ሥነስርዓት ይካሄዳል ተብሏል፡፡ የVIP አቀማመጡ ከመድረኩ ፊት ለፊት መደረጉን የገለፁት አዘጋጆቹ፤ቲኬቶቹ ኤሌክትሮኒክ ስለሆኑ ግፍያ አይኖርም ብለዋል፡፡  

 የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ከፖሊስ ኦርኬስትራ የሙዚቃ ባንድ ጋር በመተባበር በነገው ዕለት ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ ልዩ የዓውዳመት የመዝናኛ ፕሮግራም ማዘጋጀቷን አስታውቋል፡፡ በእለቱ አጫጭር ድራማዎችን ጨምሮ ዘመናዊና ባህላዊ ዘፈኖች ከነውዝዋዜያቸው ይቀርባሉ፡፡ ፕሮግራሙን ከቀኑ 8፡00 ሰዓት እስከ 11፡30 በ30 ብር መግቢያ መታደም እንደሚቻል አዘጋጆች ተናግረዋል፡፡

 ባለፈው ሐምሌ 80ኛ ዓመቱን ያከበረው ሀገር ፍቅር ቲያትር፤ለአዲሱ ዓመት በአል በአል የሚሸቱ ፕሮግራሞችን ከቀኑ 8፡30 ጀምሮ እንደሚያቀርብ አስታወቀ፡፡ የቲያትር ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ካሳዬ ገበየሁ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤በበዓሉ ዝግጅት ላይ የቲያትር ቤቱን የ80 ዓመታት ጉዞ የማያሳይ የዳንስ ትርኢት ይቀርባል፡፡ አንጋፋው ድምጻዊ ጌታቸው ጋዲሳን ጨምሮ በርካታ ዕውቅ ሙዚቀኞች ሥራቸውን ለታዳሚው እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል፡፡ የአውድ ዓመት ፕሮግራሙ ከቀኑ 8፡30 እስከ 12፡30 የሚዘልቅ ሲሆን መግቢያው 30 ብር ነው፡፡

     የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር የአዲስ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ ከጳጉሜ 1 ጀምሮ ሲያቀርብ የነበረውን የሙዚቃ ዝግጅት፣ እስከ መስከረም መጨረሻ እንደሚዘልቅበት የታወቀ ሲሆን በአቶ አክሊሉ ዘውዴ ኮንዳክት የተደረጉ ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃዎች ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ ዛሬ በዋዜማው የተለያዩ የሙዚቃ ትርኢቶች ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ 3 ሰዓት ይቀርባሉ፡፡ድምፃዊ አረጋኸኝ ወራሽና ግርማ ተፈራን ጨምሮ የተለያዩ ተጋባዥ ድምፃውያን በፕሮግራሙ ላይ ያቀነቅናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በፕሮፌሰር አበበ አሻግሬ ተፅፎ በሳሙኤል ተስፋዬ የተዘጋጀው አጭር ድራማም የፕሮግራሙ አካል ነው፡፡ የሙዚቃ ትርኢቱን ዛሬ ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ 3 ሰዓት እንዲሁም ነገ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በ40 ብር መታደም ይቻላል ተብሏል፡፡

Page 8 of 16