Administrator

Administrator

እንግሊዛዊቷ ድምፃዊት አዴሌ በጥቂት አመታት ውስጥ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ሽልማቶችን ሁሉ በመሰብሰብ ስኬታማ እንደሆነች ቢዝነስ ኢንሳይደር ገለፀ፡፡ አዴሌ ከ3 ሳምንታት በፊት በ85ኛው የኦስካር ምሽት ላይ ለጀምስ ቦንድ ፊልም በሰራችው ሙዚቃ በምርጥ ኦርጅናል ዜማ ዘርፍ የኦስካር ሽልማት ወስዳለች፡፡ የ24 አመቷ አዴሌ አዲስ አልበም ለመስራት እንደማትቻኮል ወኪሏ ሰሞኑን ያሳወቀ ሲሆን፣ የመስራት ፍላጎት ቢኖራት እንኳን ዘንድሮ ጋብቻ ለመመስረት ማቀዷ ዝግጅቷን ያስተጓጉለዋል የሚሉ ዘገባዎች ወጥተዋል፡፡

አዴሌ በትልልቆቹ የኪነጥበቡ ኢንዱስትሪ ሽልማቶች ተሸላሚ የሆነችበት እድሜ በጣም የሚያስገርም ነው ያለው ዘ ቢዝነስ ኢንሳይደር፣ 9 የግራሚ፤ 4 የአሜሪካን ሚውዚክ አዋርድ፤ 12 የቢልቦርድ ሚውዚክ አዋርድ እና 4 የብሪት አዋርድ ሽልማቶችን በመሰብሰብ ወደር የለሽ ሆናለች፡፡ ‹21› የተሰኘው የአዴሌ ሁለተኛ አልበም በ2011 እና 2012 የዓለምን ገበያ ለመምራት የበቃ ሲሆን በአለም ዙርያ 12.5 ሚሊዮን ቅጂ ተሸጧል፡፡ አዴሌ ‹‹19›› በሚል ርእስ የመጀመርያ አልበሟን በመልቀቅ የዓለም የሙዚቃ ኢንዱስትሪን የተቀላቀለችው ከ4 ዓመታት በፊት ነበር፡፡

የሆሊውድ ፊልም ሰሪዎች፣ የቻይና መንግስት በሚፈፅምባቸው ሳንሱር ቢማረሩም፣ የአገሪቱ ገበያ ተመችቷቸዋል፡፡ በሌላ በኩል በቻይና የተሰሩ ፊልሞች በዓለም አቀፍ ገበያ እንዳልተሳካላቸው ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡ ለሆሊውድ ፊልሞች፣ ትልቋ ገበያቸው አሁንም አሜሪካ ነች፡፡ በመቀጠልም ጃፓን፡፡ ነገር ግን በቻይና የሆሊውድ ፊልሞች ገበያ በየአመቱ በ30% እያደገ መጥቷል፡፡ እናም በ2012 ቻይና ለሆሊውድ ፊልሞች ሦስተኛ ገበያ ሆናላቸው 2.71 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝተውባታል፡፡ በከፍተኛ ወጪ ተሰርተው ከፍተኛ ገቢ ያስገኙ ፊልሞች (ለምሳሌ ስካይ ፎል እና ዘ ዳርክ ናይት ራይዝስ) በቻይና ገበያ ደርቶላቸዋል፡፡

‹ኩንጉፋ ፓንዳ 3› የተባለውን ፊልም፣ ድሪም ዎርክስ ከቻይና ኩባንያ ጋር በመተባበር እንደሚሰራ የጠቀሰው ኒውዮርክ ታይምስ፣ ዋልት ዲዝኒ ደግሞ‹አይረን ማን 3› በከፊል በቻይና ምድር መቅረፁን ገልጿል፡፡ በ2002 እኤአ በቻይና የነበረው የሲኒማ ቤቶቸ ብዛት ከ10 አመታት በኋላ በ10 እጥፍ በማደግ 13ሺ ደርሷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በቻይንኛ ቋንቋ የተሰሩ የቻይና ፊልሞች፣ በአለም ገበያ ያገኙት ተቀባይነት እጅግ የቀዘቀዘ መሆኑን ያመለከተው የሲኤንኤን ዘገባ ነው፡፡ በቻይና ቋንቋ የተሰሩት ፊልሞች በአገር ውስጥ ያላቸው ገበያ የተሟሟቀ ቢሆንም ከአገር ውጭ ግን ብዙም አልተሳካላቸውም፡፡ “ሎስት ኢን ታይላንድ” የተባለ ፊልም በቻይና እስከ 202 ሚሊዮን ዶላር ቢያስገባም፤ በሰሜን አሜሪካ ያስገባው ከ70ሺ ዶላር አይበልጥም፡፡

የሹሩባ ማውጫዎችን የሚያሳይና በአመት ሁለት ጊዜ የሚታተም መፅሔት ማዘጋጀት መጀመሩን “መኪያ ሹሩባ ሥራ” አስታወቀ፡፡ የመፅሔቱ ዋና አዘጋጅ ወይዘሪት መኪያ ሁሴን፣ መፅሄቱ ረዣዥም ፅሁፎች የሌሉት በእንግሊዝኛ ብቻ የሚታተም ነው ብላለች፡፡ Ethiobraids የተሰኘው መፅሔት 64 ገፆች ያሉት ሲሆን በ100 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

በአባይ ጉዳይ ላይ ከተፃፉት አዳዲስ መፃህፍት መካከል አንዱ፤ የኒውዮርክ ከተማ ነዋሪ በሆኑት አቶ ገብረፃድቅ ደገፋ የተዘጋጀ ሲሆን፣ “ናይል ታሪካዊ፣ ሕጋዊና ልማታዊ ገጽታዎች - ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ማስጠንቀቂያ” በሚል ርእስ ተተርጉሟል፡፡ በአቶ ወርቁ ሻረው ተተርጉሞ በ406 ገፆች የቀረበው መፅሐፍ፤ በ60 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

የአምስት ወር ነፍሰጡር የነበረችውን ባለቤቱን ሆዷ ላይ ስድስት ቦታ በጩቤ ወጋግቶ የገደለው ተጠርጣሪ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ፡፡ ባልና ሚስቱ ለአራት ዓመታት በጋብቻ ተሳስረው ሲኖሩ የሁለት ዓመት ልጅ አፍርተዋል፡፡ በምዕራብ ጐጃም ቡሬ ከተማ ውስጥ በተፈፀመው በዚህ ወንጀል ከሟች ሌላ የሟች ወ/ሮ ተናኜ ገረም ወላጅ እናትና አባት በጩቤ የመወጋት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ የቡሬ ወረዳ ፖሊስ ፅ/ቤት መርማሪ የሆኑት ዋና ሳጅና አልማው ደሴ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት ባለፈው ወር መጨረሻ በባልና ሚስት መካከል በተፈፀመ ያለ መግባባት ሚስት ወደ ወላጆቿ ቤት ሄዳ ነበር፡፡

ባል እዚያ ሄዶ ግድያውን መፈፀሙን ተናግረዋል፡፡ ተጠርጣሪው በትዳር አጋሩ ላይ ይህን ወንጀል በፈፀሙ የአካባቢው ህብረተሰብ ቁጣ ተቀስቅሷል፡፡ ተጠርጣሪው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ መካሄዱን የጠቆሙት ዋና ሳጅን አልማው የምርመራ መዝገቡ ለዐቃቤ ሕግ ተላልፎ ክስ መመስረቱንም ጠቁመዋል፡፡ በተጠርጣሪው በጩቤ የተወጉት የሟች ወላጅ እናትና አባት በአሁኑ ወቅት በህክምና ላይ እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በመንፈሳዊ ኮሌጁ ትምህርት ተቋርጧል፤ ተማሪዎቹም ምግብ መመገብ አቁመዋል

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት÷ ለትምህርት ጥራት መሻሻልና ለደቀ መዛሙርቱ መብት መከበር ከመቆም ይልቅ ገንዘብ ለመሰብሰብና የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ቅድሚያ ይሰጣሉ ያሏቸው ሁለት የአስተዳደር ሓላፊዎች ከሥልጣን እንዲወገዱ ያቀረቡት ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ባለማግኘቱ ትምህርት ማቆማቸውንና ምግብ ከመብላት መከልከላቸውን አስታወቁ፡፡ በጥያቄያቸው ያመለከቷቸው በርካታ የኮሌጁ ችግሮች ላለፉት ዐሥራ አራት ዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩ መኾናቸውን የገለጹት ደቀ መዛሙርቱ÷ የመምህራኑ አቅም ማነስና የትምህርት ጥራት መውደቅ፣ የምግብ መበከልና የአስተዳደሩ በጥቅም ትስስርና በሙስና መዘፈቅ ሊታገሡት ከሚችሉት በላይ በመኾኑ ፓትርያሪኩና የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤቱ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጧቸው መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡

ይኹንና ፓትርያሪኩን በአካል አግኝቶ ለማነጋገር አልያም የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ሓላፊዎችን ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረጉት ጥረት ከኮሌጁ ሓላፊዎች ጋራ በጥቅም ተሳስረዋል ያሏቸው አካላት እንደፈጠሩት በሚያምኑት መሰናክል አለመሳካቱን አስታውቀዋል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ከኮሌጁ አስተዳደር ጋራ የገቡበት ውዝግብ ከተቀሰቀሰ ሁለተኛ ሳምንቱን የያዘ ሲኾን ትምህርት መቋረጡም ተዘግቧል፡፡ ለደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ምላሽ እንደሚሰጥ የገለጸው አስተዳደሩ÷ ደቀ መዛሙርቱ ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ ያቋረጡትን ትምህርት እስከ ረቡዕ ቀትር ድረስ በአስቸኳይ እንዲቀጥሉ አሳስቧል፡፡ ደቀ መዛሙርት ወደ ትምህርታቸው የማይመለሱ ከኾነ ደግሞ በዚያው ዕለት ንብረትና መታወቂያ እያስረከቡ ኮሌጁን ለቀው እንዲወጡ አስተዳደሩ አስጠንቅቋል፡፡

‹‹ለሁለት ሰዎች ሲባል ሁለት መቶ ተማሪ አይባረርም፤ ብቃት የሌላቸውና ኮሌጁን እንደ ርስት በዘመድ ይዘው የጥቅም ማግበስበሻ ያደረጉት አካዳሚክ ዲኑና የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪው ከሓላፊነታቸው ይነሡልን፤›› የሚሉት ደቀ መዛሙርቱ በበኩላቸው÷ ችግሮቻቸው በመሠረቱ ደረጃ በደረጃ መፈታት እንደሚገባቸው ቢቀበሉም ወደ ትምህርት ገበታቸው የሚመለሱት ግን የኮሌጁ ምክትል አካዳሚክ ዲንና የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪው ከሓላፊነታቸው ሲነሡ ብቻ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ እንደሚያስረዱት÷ በተጠቀሱት የኮሌጁ አስተዳደር ሓላፊዎች ደረጃ ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ ምእመኑ ‹‹የገንዘብ ምንጭ ብቻ ኾኗል፤ አገልጋይ ጠፍቷል፡፡›› ደቀ መዛሙርቱ÷ ኮሌጁን እንደ ግለሰብ ቤትና እንደ ዘመድ ርስት ይቆጥራሉ በሚሏቸው ጥቂት ሓላፊዎች መካከል አለ የሚሉት የጥቅም ትስስር በትምህርት ጥራትና በመብታቸው ላይ የፈጠረውን ተጽዕኖ የሚገልጹት ‹‹ኮሌጁ የትምህርት ሳይሆን የንግድ ማእከል ኾኗል፤›› በሚል ነው፡፡

ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሰጡ የደቀ መዛሙርቱ መማክርት አባላት እንዳስረዱት÷ የተለያዩ ገባሬ ሠናይ ድርጅቶች ለኮሌጁ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ፤ ከእነርሱም በላይ በዋናነት ሁሉም አህጉረ ስብከት ከጠቅላላ ገቢያቸው አምስት ከመቶ ፈሰስ ያደርጋሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኮሌጁ ሕንጻውን በማከራየትና የመማሪያ ክፍሎቹን ለተለያዩ ኮሌጆች በመፍቀድ ከፍተኛ ገቢ ይሰበስባል፡፡ ይኹንና ደቀ መዛሙርቱ በሜዳ ላይ የሚማሩበት አጋጣሚ አለ፡፡ በየመርሐ ግብሩ ከተዘረጉት ኮርሶች ብዛት ጋራ የሚመጣጠኑ መምህራንን መቅጠር እየተቻለ የመምህራን ምደባው አራትና አምስት ኮርሶችን በሚይዙ ጥቂት መምህራን መካከል የተወሰነ ነው፡፡ የመምህራኑ ዕውቀት ‹‹ሙሉዕ በኩለሄ›› እስካልኾነና መምህራኑ ከተጨማሪ ሓላፊነቶች ጋራ ከሚያጋጥማቸው የዝግጅት ማነስ የተነሣ ምደባው የትምህርት ጥራቱን የሚጎዳው ይኾናል፡፡ ይህም በትምህርት አሰጣጡና በምዘናው ላይ በሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ የተነሣ አቤቱታ የሚያቀርቡ ደቀ መዛሙርትን የሚያሸማቅቁ፣ ከዚህም አልፎ በመማሪያ ክፍሎችና በቤተ መጻሕፍት ውስጥ ሳይቀር የሚደበድቡ መምህራን መኖራቸውን ነው ደቀ መዛሙርቱ ለአዲስ አድማስ የተናገሩት፡፡

በተማሪዎች አቀባበል ወቅት ኮሌጁ የሙሉ ጤንነት ምርመራ እንደሚያደርግላቸው የገለጹት ደቀ መዛሙርቱ በሂደት ግን በካፊቴሪያው ጥንቃቄ የጎደለው የምግብ ዝግጅት የተነሣ ጤንነታቸው የተጎዳና በቂ ሕክምና የማያገኙ ደቀ መዛሙርት ቁጥር ጥቂት እንዳልኾነ ደቀ መዛሙርቱ ለዝግጅት ክፍሉ ገልጸዋል፡፡ በቤተ መጻሕፍት አገልግሎትና በመረጃ ቴክኖሎጂ ረገድ የሚሰጠው አገልግሎትም አንፋውን ኮሌጅ የሚመጠን እንዳልኾነ ነው ደቀ መዛሙርቱ የሚናገሩት፡፡ ‹‹የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከተቀሩት ሁለት የቤተ ክርስቲያኒቱ ኮሌጆች ጋራ ሲነጻጸር አንጋፋ ቢኾንም ዛሬ ከአስተዳደሩ ድክመት የተነሣ የሚገኝበት ደረጃ ከዘመናዊነት የራቀ ነው፤›› ይላሉ ደቀ መዛሙርቱ፡፡ ይህ የኮሌጁ ኹኔታ የሚያሳስባቸውና በጉዳዩ ላይ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ የሚመክሩ መምህራን ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጣቸውና ስለላ እንደሚካሄድባው ተመልክቷል፡፡

በኮሌጁ ሰፍኗል የሚሉትን ሙስናና የአሠራር ብልሽት የሚቃወሙት የአገርንና የሕዝብን ሀብት ከማዳን አንጻርም በመኾኑ መንግሥትም ሊያግዘን ይገባል፤ ‹‹ችግራችንን የማይፈቱልን ከኾነ ችግር ባይፈጥሩብን›› በማለትም በግል እየጠሩ ያስፈራሩናል፤ ይዝቱብናል ያሏቸውን የፖሊስ አባላት ይጠይቃሉ ደቀ መዛሙርቱ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በአድራሻ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የጻፉትን ጥያቄዎቻቸውን ለጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ለሰብአዊ መብት ኮሚሽንና ለፌዴራል ፖሊስ በግልባጭ ማሳወቃቸውን የገለጹ ሲኾን ለጥያቄዎቻቸው በቂ ምላሽ እስኪያስገኙ ድረስ ውርጩን፣ ረኀቡንና እንግልቱን ተቋቁመው ለመቆየት መወሰናቸውን ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ በደቀ መዛሙርቱ ጥያቄዎችና ተቃውሞዎች ላይ የኮሌጁን ሓላፊዎች አስተያየትና ምላሽ ለማግኘት የኮሌጁ ምክትል አካዳሚክ ዲንን በስልክ ለማነጋገር የሞከረን ቢኾንም ዲኑ በአካል ካልቀረባችኹ በስልክ ምላሽ አልሰጥም ብለውናል፡፡ የዝግጅት ክፍሉ በነበረበት የጊዜ እጥረት ዲኑን በአካል አግኝቶ ሊያነጋግራቸው አልቻለም፡፡

ኤርትራ ውስጥ ሰልጥነው በጋምቤላ ክልል ድንበር አቋርጠው ጥቃት ሊፈፅሙ የነበሩ ታጣቂዎች በሰሜንና ደቡብ ሱዳን መንግስታት ትብብር ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፈው መሠጠታቸውን ምንጮቻችን አመለከቱ፡፡ ስልጠና ካገኙበት ከኤርትራ ተነስተው ሰሜን ሱዳንና ደቡብ ሱዳንን አልፈው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ሊያቋርጡ ሲሉ በሶስቱ አገሮች መሀል ባለው የፀጥታ የትብብር ስምምነት መሠረት ለክልሉና ለፌዴራል መንግስት የፀጥታ ሀይሎች ተላልፈው ተሠጥዋል፡፡

ታጣቂዎቹ በሰላም እጃቸውን እንዲሠጡ የቀረበላቸውን ጥያቄ ባለመቀበላቸው በተከፈተ የተኩስ ልውውጥ ህይወታቸውን ያጡ እንዳሉም የጠቆሙት ምንጮቹ በክልሉ በተፈፀሙ የተለያዩ የሽብር ተግባሮች እጁ እንዳለበት የሚጠረጠረውና በአስመራ ለረጅም ጊዜ የኖረው ኦማን ካውንዳን ጨምሮ አስራ አንድ ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ባለፈው አመት በጋምቤላ ክልል የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ላይ ይጓዙ የነበሩ ተማሪዎች ላይ እና በክልሉ በኢንቨስትመንት በተሰማሩ ፓኪስታንያውያን እንዲሁም በክልሉ ፖሊሶች ላይ ጉዳት አድርሷል በሚል በመንግስት ይፈለግ የነበረው አሜሪካዊ ዜግነት ያለው ኡሞድ ኡዶል ወደ ደቡብ ሱዳን ሄዶ እንደነበር ይታወቃል፡፡

አብረውት ከነበሩ ታጣቂዎች የተወሰኑት ተገድለው አብዛኛዎቹ ተይዘው ጉዳያቸው በፍርድ ሲታይ እሱ ተሠውሮ ሲፈለግ ከቆየ በኋላ በቅርቡ በፌደራል መንግስት ፀረ ሽብር ግብረ ሀይልና የፀጥታ አካላት ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ መገደሉንና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ማረጋገጡ ይታወቃል፡፡

ባለፈው ሳምንት የአዲስ አድማስ ጋዜጣ እትም ላይ በአርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ ዙሪያ የቀረበውን አጭር ዜና ስመለከት ብዙ ሃሳቦች መጡብኝ፡፡ በእርግጥ ሠራዊት ፍቅሬ የተወራበት ነገር አሉባልታ እንደሆነ መግለፁ በዜናው ተዘግቧል፡፡ ነገር ግን ሁለት ቅሬታዎች አሉኝ፡፡ አንደኛው ቅሬታዬ በዜና አዘጋገቡ ላይ ነው፡፡ ሁለተኛው ቅሬታዬ ግን በዜና ዘገባው ላይ ሳይሆን፣ በጊዜው በአርቲስቶች ላይ በሚናፈሱ ወሬዎች ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያ ቅሬታዬን ላስቀድም፡፡ በአዲስ አድማስ የቀረበውን አጭር ዜና፣ በሙያ መመዘኛ እንየው ከተባለ ተቃራኒ ገፅታዎች ይስተዋሉበታል፡፡ ብልሃትና ጥንቃቄ የተሞላበት ዘገባ ነው፡፡

“ብልጠትም ያለበት ይመስላል” ብዬ ስሜታዊ ድምዳሜ ላይ መድረስ አልፈልግም፡፡ ጠንቃቃ ዜና መሆኑን ግን ያለ ጥርጥር መናገር ይቻላል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በዜናው አንዳንድ ገፅታዎች ላይ ግልፅ ጉድለቶች አሉበት፡፡ ለምሳሌ ዜናው ብዙ መረጃዎችን የሚሰጥ ይመስላል፡፡ ይህም የጥንቃቄ ውጤት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ነገር ግን ዜናው ከሚሰጠን መረጃ ይልቅ በርካታ መልስ የሌላቸው ጥያቄዎችን የሚፈጥርብን መሆኑ ትልቅ ጉድለት ነው፡፡ ሌላኛው ጉድለት፣ በዜናው ርእስ ላይ ጭምር የሚታይ ነው፡፡

ለዜናው መነሻ የሆነው ወሬ በዜናው ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ አንዲት ሴት፣ አርቲስቱ ሊስመኝና ሊደባብሰኝ ሞክሯል ብላለች የሚል ወሬ ነው መነሻው፡፡ እንግዲህ ከዚህ ልንገነዘብ የምንችለው ወሬው ስለ ወሲብ ትንኮሳ እንጂ ስለ መድፈር ሙከራ አለመሆኑን ነው፡፡ ደግሞም ወሬው አሉባልታ መሆኑንም አርቲስቱ ገልጿል፡፡ በሌላ አነጋገር፤ ወሲባዊ ትንኮሳ እንደፈፀመ ተደርጐ ሲናፈስ የቆው ወሬ አሉባልታ እንደሆነ አርቲስቱ ተናግሯል፡፡ የዜናው ርእስ ግን “የወሲብ ትንኮሳ” የሚል አገላለፅን ሳይሆን፣ “የመድፈር ሙከራ” የሚል ሀረግ ተጠቅሟል፡፡ ይሄ ጉድለት ነው፡፡

Monday, 25 March 2013 11:13

ቺንዋ አቼቤ አረፈ

ከአፍሪካ ታላቅ ደራሲዎች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነው ናይጄርያዊው ቺንዋ አቼቤ በ82 ዓመቱ ትናንት በአሜሪካዋ ማሳቹሴትስ ከተማ በድንገተኛ ህመም ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡ አልበርት ቺኒዋ ሉሞጉ አቼቤ ከልቦለድ ስራዎቹ ባሻገር በገጣሚነትና በሃያሲነቱ የሚታወቅ ፕሮፌሰር ነበር፡፡

በ1960ዎቹ ስላለፈበት የቢያፍራ ጦርነት ትውስታዎችና የህይወት መታሰቢያ ታሪኩን “There Was a Country: A Personal History of Biafra” በሚል ርእስ ለመጨረሻ ጊዜ አምና ለንባብ አብቅቷል፡፡ ታዋቂው የእንግሊዝ አሳታሚ ኩባንያ ፔንጊውንስ ሞቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፣ ደራሲውን “እጅግ ምርጥ ችሎታ ያለው ፀሃፊ እና የአፍሪካ ታላቅ የስነፅሁፍ ሰብእና” ሲል አሞካሽቶታል፡፡ በአገሩ በናይጄርያና በአለማቀፍ ደረጃ በርካታ ሽልማቶችን ያገኘው አቼቤ በልቦለድ ስራዎቹ በአፍሪካዊነት፤ በብሄርተኝነት፤ በፀረ ቅኝ ግዛት ጭብጦች ዙሪያ በመፃፍ ይታወቅ በነበር፡፡

ቺንዋ አቼቤ ስነፅሁፍ በመላው አህጉሪቱ እንዲስፋፋ፣ በተማሪዎች ዘንድ የልቦለድ ባህል እንዲፈጠርና ከፍተኛ የስነፅሁፍ እድገት እንዲቀጣጠል በተጫወተው ፈርቀዳጅ ሚና ጎልቶ ይጠቀሳል፡፡ በአሜሪካ ኮሌጆች ሲያስተምር ቆይቶ እኤአ በ1958 በፃፈው ‹ቲንግስ ፎል አፓርት› በተባለ የልቦለድ መፅሃፉ ከፍተኛ ዓለማቀፍ ዝና አትርፍዋል፡፡ መጽሐፉ በመላው ዓለም በ50 የተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ 12 ሚሊዮን ቅጂዎች ተሽጥዋል፡፡

የልቦለድ መፅሃፉ በበርካታ የአፍሪካ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤ ኮሌጆች እና ዩኒቨርስቲዎች እንደ መማርያ መፅሃፍ ሊያገለግልም በቅቷል፡፡ አቼቤ የናይጄርያ የመንግስታትንና የባለስልጣናትን ድክመት በመተቸት እንዲሁም ሙስናን በይፋ በማጋለጥ፤ እንዲሁም በተለያዩ የህትመት ውጤቶች መጣጥፎችን በማቅረብ ይታወቅ ነበር፡፡ አቼቤ ከ20 በላይ መፅሃፍትን ለንባብ ያበቃ ሲሆን ከፃፋቸው ልቦለዶች መካከል ‹ኖ ሎንገር አት ኢዝ›፤ ‹አሮው ኦፍ ጎድ›፤ ‹ኤማን ኦፍ ዘ ፒፕል›፤ እና ‹አንትሂልስ ኦፍ ሳቫና› የተባሉት ይጠቀሳሉ፡፡