Administrator

Administrator

የድምፃዊ ብስራት ሱራፌል አዲሱ “ማለፊያ” የተሰኘ የሙዚቃ አልበም  የፊታችን ቅዳሜ፣  ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በሸራተን አዲስ  ጋዝላይት እንደሚመረቅ ተገለጸ፡፡

 የግጥምና ዜማ ደራሲ እንዲሁም ፕሮዱዩሰር የሆነው ድምፃዊ ብስራት ሱራፌል፣ በቅርቡ ለአድማጭ ያደረሰው  ሁለተኛ የሙዚቃ አልበሙ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ተወዳጅነትና ተቀባይነት እንዳገኘ ይነገርለታል፡፡

በርካታ የግጥምና ዜማ ሥራዎችን ለሌሎች ድምጻውያን በመሥራትና በመስጠትም  የሚታወቀው ድምጻዊው፤ እስካሁን ከሰጣቸው መካከልም ድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ፣ ሄለን በርሄ፣ ቬሮኒካ አዳነ፣ ሐይማኖት ግርማ  ይጠቀሳሉ፡፡
 

የ“ማለፊያ” አልበም  የምረቃ ሥነስርዓት፤ ታዋቂ ድምጻውያን፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና  ታዋቂ ግለሰቦች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው  የአርቲስቱ አድናቂዎች በተገኙበት ይከናወናል ተብሏል፡፡

ሀበሻ ቪው 4ኛ ዙር የፊልም ፌስቲቫሉን በለንደን ከተማ ሊያካሂድ ነው

ሀበሻ ቪው 4ኛ ዙር የፊልም ፌስቲቫሉን በእንግሊዝ አገር ለንደን ከተማ በቅርቡ ሊያካሂድ ሲሆን፤ የቅድመ መክፈቻ ሥነሥርዓቱን ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽት በሃያት ሪጀንሲ ሆቴል አካሂዷል፡፡

በዘንድሮው የለንደኑ የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል ለዕይታ የተመረጡት  “ጸጸት” እና “ዝምታዬ” የተሰኙት ሁለት የኢትዮጵያ  ፊልሞች ሲሆኑ፤ የፊታችን ጥቅምት 17 እና 18 ቀን 2016 ዓ.ም በለንደኑ ሪትዚይ ሲኒማ ለዕይታ እንደሚቀርቡ  ታውቋል፡፡

በምሽቱ መርሃግብር ታዋቂ የፊልም ፕሮዱዩሰሮች፣ አዘጋጆችና ተዋናዮች እንዲሁም የፊልም ጥበብ ቤተሰቦች ታድመዋል፡፡

የፊልም ፌስቲቫሉ ዓላማ፤ ኦሪጂናል የኢትዮጵያ ፊልሞችንና ተሰጥኦ ያላቸው ፊልም ሰሪዎችን በመላው ዓለም ለማስተዋወቅና ትኩረት እንዲያገኙ ለማድረግ  ነው ተብሏል፡፡

በመርሃግብሩ ላይ  ንግግር ያደረጉት የሀበሻ ቪው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ትዕግስት ከበደ፣ በፌስቲቫሉ የሚሳተፉ ፊልሞች ከሚመረጡባቸው መስፈርቶች መካከል በአገራችን ቋንቋ መሰራታቸውና ኦሪጂናል መሆናቸው ነው ብለዋል፡፡ ድርጅቱ ፊልሞቹን የሚመርጡና የሚገመግሙ ከ20 በላይ ባለሙያዎች እንዳሉትም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ጠቁመዋል፡፡

በምሽቱ ለኢትዮጵያ ፊልም ዕድገትና አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መድረስ አስተዋጽኦ ያደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት፤ የዛሬ 60 ዓመት ለተሰራው “ሂሩት አባቷ ማነው“ የተሰኘው የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ  ፊልም መሥሪያ የገንዘብ ብድር የሰጠው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንዲሁም የዛሬ 30 ዓመት የተሰራውን “ጸጸት” ፊልም ፕሮዱዩስ ያደረጉት የመጀመሪያዋ ፕሮዱዩሰር ወ/ሮ ሩቅያ መሃመድ ምስጋናና ዕውቅና ከመድረኩ ተችሯቸዋል፡፡

ሀበሻ ቪው ለመጀመሪያ ጊዜ በምሽቱ ባከናወነው የሽልማት (Award) መርሃግብር ላይ ለአንድ ጎምቱ የኪነጥበብ ባለሙያና ለሁለት ተቋማት ሽልማቶችን አበርክቷል፡፡

በግለሰብ ደረጃ ከሀበሻ ቪው የመጀመሪያው ሽልማት የተበረከተላቸው ለ60 ዓመት ከኪነጥበብ ያልተለዩትና አያሌ የጥበብ ባለሙያዎችን ያፈሩት ጋሽ ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ሲሆኑ፤ በተቋም ደረጃ ባለቤትነቱ የአትሌት ሃይሌ ገ/ሥላሴ የሆነው ዓለም ሲኒማና የአዲስ አበባ ከተማ ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ናቸው፡፡

ሀበሻ ቪው ያዘጋጀውን  ሽልማት  ለተሸላሚዎች ያበረከቱት የምሽቱ የክብር እንግዳና ጎምቱው የኪነጥበብ ባለሙያ እንዲሁም የመጀመሪያው የግል ቴአትር ቤት (ቀንዲል) ባለቤት የሆኑት ጸሃፌ ተውኔት አያልነህ ሙላት ናቸው፡፡

ሀበሻ ቪው ቴክኖሎጂና መልቲ-ሚዲያ እ.ኤ.አ ከ2015 ጀምሮ በሥራ ላይ የሚገኝ ድርጅት ሲሆን፤ በአፍሪካዊነትና ተያያዥ ርዕሰጉዳዮች ላይ ይዘቶችን በማበልጸግ ይታወቃል፡፡ ድርጅቱ በአሜሪካ ቨርጂኒያ የተመዘገበ የንግድ ምልክት ሆኖ ሲሰራ የቆየ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ ከ2020 ጀምሮ ደግሞ በኢትዮጵያም ተመዝግቦ እየሰራ ይገኛል፡፡

- አንዳነዴ ሰምተን ከሆነ መጋኛ መታው፣መጋኛ ፊቱን አጣመመው ሲባል ሰምተን ሊሆን ይችላል። የዚህን ነገር ሳይንሳዊ ትንታኔ በጥቂቱ ይዤላቹ ቀርቢያለሁ።
-ፊታችን ከጭንቅላታችን በሚነሱ ነርቮች አማካኝነት የእለት ተእለት ተግባራትን ይከውናል። ከጭንቅላታችን የሚነሱ 12 የጭንቅላት ነርቮች (cranial nerves) አሉ። ከነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ነርቮች የፊታችንን እንቅስቃሴ ያዛሉ፣ ይቆጣጠራሉ። ፊታችን ቀስ በቀስ ወይም በድንገት ሊጣመም ይችላል።
-ድንገተኛ የሆነ የፊት መጣመም (bell's palsy) የምንለው በአንድ በኩል የሚገኘውን የፊት ጡንቻዎች መድከም ፣ መስነፍ ወይም መዛል ሲሆን የፊታችንን ቅረፅ የሚቀይር ከአንጎል ከሚነሱት 12 ነረቮች አንዱ የሆነው ሰባተኛው ነርቭ (facial nerve) ብግነት ወይም እብጠት ምክንያት የሚመጣ የነርቭ ህመም ነው።
ይህ ችግር በማንኛውም የእድሜ ክልል ሊከሰት የሚችል ፣ ግማሽ ፊታችን ወይ በቀኝ ወይም በግራ ፊት እነዳይታዘዝ የሚያደርግ ህመም ነው ፣ ይህም ፊታችንን የሚመግቡ ነርቮች (nerve supplies) ከጭንቅላታችን ሲወጡ በሚከሰት ጫና ወይም ጉዳት ሊከሰት ይችላል።
ምክንያቶቹስ ምንድን ናቸው?
-ይህ ነው የሚባል ምክንያት ባይቀመጥም አንዳንድ ኤክስፐርቶች በአንድ በኩል የሚገኘውን የፊታችንን ጡንቻ የሚቆጣጠረው ነርቭ ሲቆጣ ፣ ወይም እብጠት ሲኖረው ነው ብለው አሰቀምጠዋል። ይህም በተለይ በቫይረስ ኢንፌክሽን አማካኝነት ነው ተብሎ ይታሰባል።
እእነዚህ ቫይረሶች ለምሳሌ Herpes simplex virus,herpes zosther, episten barr virus, CMV virus, mumps virus, adeno virus ይጠቀሳሉ።
ተጋላጭ ሰዎችስ እነማን ናቸው?
-ነፍሰጡር እናቶች ፣ የላይኛው የመተነፈሻ አካል ኢንፌክሽን ፣ ስኳር ፣ ደም ግፊት እና ከመጠን በላይ ውፍረት ያለባቸው ሰዎች ፣ ተጋላጭ ናቸው ተብሎ ይታሰባል።
ምልክቶቹስ?
-በአብዛኛው ጊዜ ምልክቶቹ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በተወሰነ መልኩ ይመለሳል ተብሎ ይታሰባል። ሙሉ ለሙሉ ወደ ነበረበት ለመመለስ ሳምምነታት ወይም ወራት ይፈጃል ተብሎ ይታሰባል። የተወሰኑ ሰዎች ላይ ደግሞ እስከ ሂወት ዘመን ሊቆይ ይችላል።
-ድንገተኛ የሆነ በአንድ በኩል ብቻ የፊት መድከም ፣ መስነፍ ፣ የፊት መውደቅ ፣ ጉነጭ በአየር መሙላት መቸገር ፣ መሳቅ ፣ ፈገግ ማለት ፣ እና ሌሎች የፊት እንቅስቃሴዎች ለማድረግ መቸገር ፣ የፊት መደንዘዝ ፣ የአንድ አይን መክደን አለመቻል ፣ የምራቅ መዝረክረክ ፣ ማፏጨት አለመቻል ፣ የአፍ በአንድ በኩል መውረድ ፣ በግነባር መኮሳተር አለመቻል ፣ ከጆሮ ጀርባ አና መንጋጭላ አካባቢ የህመም ስሜት ፣ እራስ ምታት፣ ጣእም ለማጣጣም መቸገር ፣ የእንባ እና የምራቅ መጥን መለወጥ ፣ ሊኖሩ ይችላሉ።
የሚያመጠውስ መዘዝ?
-የፊት ነርቭ በቋሚነት መጎዳት
-የነርቭ ዘንጎች በትክክል አለማደግ
-የአይን መድረቅ ፣ የአይን ኢነፌክሽን ፣ መታወር ድረስ ሊደርስ ይችላል።
ምርመራዎቹስ?
-የጤና ባለሙያው ከታካሚው ታረክ በመውሰድ እና አካላዊ ምርመራ ከተደረገ በዃላ እንደ አስፈላጊነቱ ምን አልባት አጋላጭ ምክንያቶችን ለማወቅ የደም ናሙና ምርመራ (ለምሳሌ የስኳር ፣ የHIV ፣ የኮሌስትሮል ምርመራ) እንዲሁም የጭንቅላት MRI ወይም CT scan ፣ Electromyography ሊያስፈልግ ይችላል።
ህክምናውስ?
-ይህ አይነት ችግር ሲያዩ ሰዎች ወዲያውኑ የጤና ተቋም መታየት ይጠበቅባቸዋል። ይህም ቶሎ ለመዳን በቶሎ መታከም አስፈላጊ ስለሆነ ነው። መድሀኒቶች ለምሳሌ የህመም እና ፀረ ብግነት መድሀኒቶች ለምሳሌ Corticosteroids, ፀረ ቫይረስ (antiviral) መድሀኒቶች ፣ አካላዊ ህክምና (physical theraphy) ፣ የፊት ማሳጅ ፣ ቀዶ ህከምና ተጠቃሽ ናቸው።
-በተለይ የፊዚዮቴራፒ ህክምና እጅግ ጠቃሚ የሆነ የህክምናው አካል ነው። ይህም የተለያዩ የፊት ላይ እንቅሰቃሴዎች ፣ የፊት ጡነቻ ሰፖርቶች የደነዘዙ የፊት ጡንቻዎችን ወደ ነበሩበት ለመመለሰ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ያሳያሉ።
ጤና ይብዛላችሁ
ዶ/ር ኤርሚያስ
Saturday, 14 October 2023 00:00

አጭር ልብወለድ

ሴት እና ወንድ

ድንግል ነው፡፡ በግል ሀሳቦቹም ሆነ በወሲብ ህይወቱ ድንግል ነው፡፡ ከምንም አይነት ሴት ጋር ቀርቦ ምንም አይነት ፍቅር ሰርቶ አያውቅም፡፡ ጠዋት ተነስቶ ወደ ስራው…ምሽት ላይ ተመልሶ አልጋው ውስጥ መሰተር ነው፤ ለጊዜው ህይወት ለምድር ላይ ትዕይንት የመረጠችለት ገጸባህሪ፡፡ ዛሬ ላይ ሰላሳ አምስት አመቱን እያከበረ ነው፡፡ ሰላሳ አምስት የድንግልና ህይወቱን መልሶ መላልሶ በመርገም ላይ ነው ያለው፡፡ የደወለችለት እናቱ ብቻ ናት፡፡ ከቦረና ሆና ስትደውልልለት ግን ለመልካም ምኞት ሳይሆን፣ ምን ያህል እድሜውን ያለ ሴት አንድዶ እንዳወደመው ልታስታውሰው ነው፡፡ ልደቱ መሆኑን የነገራት ከወቀሳው  በኋላ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት ድፍን ምድር ስለሱ የረሳ እንዲመስለው አድርጎታል፡፡ ማንም ሰው የእሱን መፈጠር እንደረሳና ከሱ ጋርም አብሮ መዋልን እንደማይፈልግ ነው የተረዳው፡፡ መልኩ እንደማያምር አምኗል፡፡ አይኖቹ ስሜትን መናገር እንደማይችሉ ጥንቅቅ አድርጎ ከሌሎች ሰዎች በላይ ማስረዳት የሚችለው እሱ ራሱ ነው፡፡ አጠገቡ የሚቆም ሰው እንደ ሰው ቆጥሮት ሲያከብረው አንድም ቀን ሊመለከት አልቻለም፡፡ የፈለገውን ያክል ጮክ ብሎ ቢናገር የሚያደምጠውና አይኑን የሚያሳርፍበት ሰው ቢያስስ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ተመስገን ማለት እንግዲህ ይህ ነው፡፡ በምድር ላይ ሰው መስሎ ተፈጥሮ ሰው የማይቀርበው…የሰው ነፍስ ተሸክሞ ለነፍሱ ሀዘንም ደስታም የሚመጥን ክብርና ትኩረት ያላገኘ፡፡ ራሱን መልከ ጥፉ አድርጎ የሚያስብና ከዚህም በኋላ ማሰብ ቢያቆም ደስተኛ የሚሆን የሚመስለው ባለ ተብከንካኝ ነፍስ ተሸካሚ ፍጥረት ነው፡፡
አንዳንዴም ሰው የሆነ አይመስለውም፡፡ አንዳንዴ ለምን ብሎ ፈጣሪው እንደፈጠረው አይገባውም፡፡ ለማንምና ለምንም ነገር እንዳይረባ ሆኖ መፈጠሩ በራሱ ሳይሆን በፈጣሪው እንዲገረም አድርጎታል፡፡ አንዳንዴ በሰፈሩ ውስጥ የሚያልፉት ውሾች ጋር ቆም ብሎ ሰዎች እንዳያዩት ግራና ቀኙን እያየ ሊያዋራቸው ይሞክራል፡፡ ውሾቹም በማይገባቸው ቃላት ፈገግ ብሎ የሚያወጋቸውን ተመስገንን በመገረም እያዩት መልስ ሳይሰጡት ያልፋሉ፡፡ አንዳንዴ ደግመው ሲያገኙት ከርቀት የሚሸሹትም አይጠፉም፡፡ ሰላሳ አምስት አመት ምድር ላይ ቆይቷል፡፡ ለህይወት ባዶ…ለሀሳብ ባዶ…ለማህበራዊ ህይወት ባዶ…ለፍቅር ባዶ….ለወሲብ ባዶ…ለስሜት ባዶ…ለደስታ ባዶ…ለሀዘን ባዶ የሆኑ ሰላሳ አምስት አመታት ተሸክሞ ምድርን ረጋግጧል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ሌላ አንድ አመት ቢጨምር የሚያብድ እየመሰለው ነው፡፡ ስለዚህ ምርጫ መምረጥ እንዳለበት ማሰብ ጀምሯል፡፡ ወይ አግብቶ መውለድና ህይወቱን አንድ ብሎ መጀመር ….ወይ ደግሞ መሞት፡፡ ዘላለማዊ ፀጥታ ውስጥ መግባት፡፡ ማንም እንዳያየው ማድረግ፡፡ ከዛ…ዝምታ ብቻ፡፡….
ነፃነት ከመኝታ ቤቷ ውስጥ ሆና የከፈተችውን የላፕቶፗን መስኮት በፍፁም ጥበቃ እየተከታተለች ነው፡፡ ከነጋ ማንም የፃፈላት የለም፡፡ ከነጋ ነው ያልኩት…እንደዛ አይደለም ፌስ ቡኳን ከከፈተች ጀምሮ ማንም በመልዕክት ሳጥኗ ውስጥ የሰላምታ ቃላት የሚሆን እንኳን የላከላት የለም፡፡ ለምን እንደሆነ እስካሁን ድረስ ምንም የምታውቀው ነገር የላትም፡፡ እጅግ የምታምር ሴት እንደሆነች ታውቃለች፡፡ ይሄን ለማወቅ ማንም የሚቸገር አልመሰላትም፡፡ የፌስ ቡክ ወዳጆቿ ግን ይሄን ለማየት አልታደሉም፡፡ ዝም ብላ የአንዲት ሎተስ የተባለች አበባ ምስል ነው ፕሮፋይሏ ላይ የለጠፈችው፡፡
ዛሬ ላይ ግን አዲስ ሀሳብ መጥቶላታል፡፡ የምትፈልገውን ወንድ ለማጥመድ እሷ ራሷን የምትረዳባቸውን መንገዶች በጥንቃቄ መቀየስ እንዳለባት አምናለች፡፡ ስለዚህም ምን አይነት ወንድ ነው ይህ ሚድያ እንዲያመጣልኝ የምፈልገው ብላ ማሰብ ጀመረች፡፡
በመጀመሪያ ችግሮቿን የሚረዳላት፡፡ መልኩ ማንኛውንም አይነት ቀለም ተሸክሞ መምጣት ይችላል፡፡ የተማረ፣ ስራውን የሚያከብር፡፡ እንደ ህፃን ልጁ አይቷት የሚንከባከባት፣ ህይወትና ደስታ የራቀው ህይወቷ ውስጥ የድል ችቦውን ይዞ መጥቶ ጨለማዋ ላይ የሚለኩስላት፡፡ ወንድ ትፈልጋለች፡፡ ወንድ የሆነ ወንድ፡፡ ከቃላቱ በላይ የሚያስብ፡፡ ጉልበቱን በቃላት ሳይሆን በተግባር መዝብሮ ማሳየት የሚችል፡፡ ወንድ የሆነ፡፡ ሴትነቷን ብቻ እያየ ክብሯን የሚያፀናላት …ከዛ ደግሞ ነፃነቷን ተቀብሎ በህይወቷ ውስጥ የምትገዛለትና የሚገዛላት ወንድ ነፃነት ፈልጋለች፡፡ የሴትነት ፍላጎቷም ከዚህ አጥር በላይ አይዘልም፡፡
ሆኖም ከወንድ ፊት ቆማ ማውራት አትችልም፡፡ የመንደሩም ሰው የገዛ ቤተሰቧን ጨምሮ የአይነጥላ ድግምት እንደተደረገባት ያወራሉ፡፡ ከውበቷ ብዛት ብዛት ያለው ወንድ በተለያየ መልኩ የትዳር ጥያቄ ለቤተሰቦቿ ቢልኩም ነፃነት ግን ነፃነቷን እንደ መንገድ ላይ  የሽንኩርት ችርቻሮ አስመርጣ የምትሸጥ አይደለችምና የማናቸውንም ጥያቄ ሳትቀበል ቆየች…አሁን ሀያ ስድስት አመቷ ነው፡፡ እወልዳለሁ እከብዳለሁ ካለችው እድሜ ጣራ አለፍ ብላለች፡፡ አሁን ሰዓቷ እንደደረሰ ይገባታል፡፡
ለዛም ነው ከከፈተችው ሶስት ሳምንት የሆናት የፌስ ቡክ አካውንቷን ከፍታ የመጀመሪያውን ተንደርድሮ የመጣውን ወንድ ለማውጋት ያሰፈሰፈችው፡፡ ፍርሀት ከሌለባት እንደልብ ማውራት እንደምትችል አውቃለች፡፡  መወደድ ሳይሆን መውደድ ትፈልጋለች …መታየት ሳይሆን እሷ በፈቀደችው ሰዓትና ቦታ ማየትና ማዳመጥ ትፈልጋለች፡፡ ውበቷ ያመጣባትን የነፃነት እዳ ተደብቃ በዛች የላፕቶፕ መስኮት ውስጥ ማስመለስ ትፈልጋለች፡፡
እየጠበቀች ነው….አንድ ሰው እያየሁሽ ነው እንዲላት …ከዛ ምርጫዎቿ ላይ ልትሰለጥን ዝግጅት ላይ ናት….……
ተመስገን የሆነ ሰው ማናገር ፈልጓል፡፡ ብቻ የሆነ ሰው ብቻ የሆነ ፍጥረት ይሁን….ብቻ ብቸኝነቱን የሚያላቅቅለት ቃላት የተሸከመ ፍጥረት እንዲያናግረው ጉጉት ላይ ነው፡፡ በእርግጥም አሁን ላይ ተቀምጦበት ካለው ካፌ ውስጥ ከሚርመሰመሰው የሰው ዝርያ መካከል አንዱም ቢሆን ወደ እሱ ቀርቦ ምነው ብቻህን ሆንክ የሚለው አካል እንደማያገኝ አውቆታል፡፡ ድንገት ግን አንድ ነገር ትዝ አለው፡፡ ፌስቡክ የተባለ የተባረከ ነገር እንዳለ ትዝ አለው፡፡ በዚህ አለም ውስጥ መተያየት የለም፡፡ ቃላት አሸናፊዎች ናቸው፡፡ አማራጮች ማብቂያ የላቸውም፡፡ ከብዙ ጊዜያት በፊት ከፍቶት የነበረውን አካውንት አስታውሶ ፌስ ቡኩን ከፈተ፡፡ ከዛም በውስጡ መልኮችን ማማረጥ ውስጥ ገባ፡፡ አንድ አገኘ፡፡ ያገኘው አካውንት ግን በፕሮፋይሉ ላይ ምንም አይነት ፎቶ አላስቀመጠም፡፡ ጨለማ ብቻ ነው የሚታየው፡፡ ጨለማ ብቻ ከሆነ ደግሞ ይህ ሰው ሀዘን ላይ ሊሆን ይችላል ብሎ ገመተ፡፡ ወደ ውስጥ ዘልቆ ስለዛ ሰው ማጥናት አልፈለገም …እንደው ብቻ እድሉ ሳያመልጠው….ያ የፎቶ ሳጥን ውስጥ ያለው ጨለማ ከሱ ቀድሞ የመጣ ብርሀን ሳያገኘው በፍጥነት ወጉን መጀመር እንዳለበት ደረሰበትና የመጀመሪያውን ሰላምታ ማቅረብ ጀመረ፡፡
“ሰላም….”
ምላሽ በፍጥነት አላገኘም፡፡ መልዕክቱ ግን እንደታየ ይናገራል፡፡  ጠበቀ ….
“ሰላም…” የሚል ምላሽ ተላከለት፡፡
ምን ብሎ እንደሚመልስ ግራ ገባው፡፡ ብዙ አሰበ፡፡
“መተዋወቅ ይቻላል?” …. ስርዓቱን ጠብቆ እየሄደ እንደሆነ አመነ፡፡ …ጠበቀ….
“ ይቻላል፡፡”  የሚል ምላሽ ቀጠለ፡፡
ማነኝ ብሎ ይተዋወቅ፡፡ ስራ ሲቀጠር ብቻ ነው ስለ ማንነቱ ተጠይቆ የሚያውቀው፡፡ ማንም ስለሱ የህይወት ታሪክ ማወቅ የሚፈልግ የለም፡፡ አልነበረምም፡፡ ስለዚህ እንዴት አድርጎ ስለራሱ ማስረዳት እንደሚችል የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ሆኖም አሁን ግዴታ ራሱ ባመጣው ጥያቄ ውስጥ እስረኛ ሆኖ ከመክረሙ በፊት መልስ መስጠት አለበት፡፡
ቀጠለ…
“ተመስገን እባላለሁ፡፡ ከዚህ በላይ ስለራሴ ማስረዳት የምችል አይመስለኝም፡፡ እንዴት እንደማወራሽም ምናልባት የማውቅ ሰው አይደለሁም፡፡ ምናልባት ይሄን ስልሽ አንቺን ማስጨነቅና እንድትርቂኝ የሚያደርግ ነገር እየፈጸምኩ እንደሆነ አላውቅም፡፡ እንዲሁ ፕሮፋይልሽን ሳየው ሀዘን ውስጥ ያለሽ እንደሆነ ለመጠየቅና ሀዘንሽን ለመጋራት በማሰብ ነው ላወራሽ የመጣሁት፡፡ “
ብዙ ዝምታ፡፡ ድሮም አውቄው ነበር ብሎ አሰበ፡፡ ቃላቱ ለሰው ልጅ እንደማይሆን እንዲሁ ማመን ከጀመረ የቆየ ነፍስ ይዞ እነዚህን ሁሉ ቃላት በመልዕክት ሳጥኑ መላኩ ምን ያህል ደንባራ ፍጥረት እንደሆነ የሚነግረው መሰለው፡፡ ተስፋ ግን መቁረጥ አልፈለገም፡፡ ደግሞ ላከ፡፡
“የምር ሀዘን ላይ ነሽ ያለሽው?”  
አሁንም ምላሽ የለም፡፡ ምላሹም ቢመጣ ፍጥነት የለውም፡፡ ሴቶች ለምን በፍጥነት ማሰብና ማውራት እንደማይችሉ ሲያስብ ግራ ይገባዋል፡፡ እንደገና ደግሞ መለስ ይልና ይሄኔ እንደኔ አይነቱ ስንት አይነት ጣፋጭ ቃላት እየደረደረ ልቧን ማቅለጥ ላይ ነው ይላል፡፡
ድንገት…
“ነፃነት እባላለሁ፡፡”  የሚል መልዕክት ብቅ አለ፡፡ ይሄን ሁላ የተተራመሰ ቃላት ተጠቅሞ መልስ ማግኘቱ ገረመው፡፡ ከሰው ጋር ሳይሆን ከሮቦት ጋር የሚያወራ መሰለው፡፡ የምር ከሰው ጋር ሀሳብ ሊለዋወጥ መሆኑን ተገንዝቦ ራሱን አመቻችቶ ተቀመጠ፡፡ ምንም ያድርግ ምን ያስብ የማያገባው የካፌው ተጠቃሚ ላይ አይኖቹን በኩራት እያጉረጠረጠ ፈገግ ይል ጀመር፡፡
“ነፃነት ስላወኩሽ ደስ ብሎኛል፡፡” አለ…የምሩን ነው፡፡
“እኔም…” ወዲያው ነው መልሱ የመጣው፡፡ መልሱን ተመልክቶ አይኖቹ እንባ አቀረሩ፡፡  ……..
ነፃነት ከተመስገን ጋር በፌስ ቡክ ማውራት ከጀመረች ሁለት ወራት አለፉ፡፡ እንዳየችው ከሆነ ምስኪን ሰው ነው፡፡ የቻለው ድረስ ሳይሰስት እውነተኛ የሚባሉት ሀሳቦቹን ለማስተላለፍ በመሞከር ላይ ነው፡፡ ይህም እንድትንቀው ሳይሆን የባሰ እንድታከብረው አድርጓታል፡፡ ሆኖም ሁለቱም መልካቸው ምን አይነት እንደሆነ የሚያወቁት ነገር የለም፡፡ እንደው በቃላት ብቻ ነፍሶቻቸውን መጓተት ውስጥ ናቸው፡፡
ዛሬ ላይ ግን ከወትሮው ለየት ያለ ስሜት እየተሰማት ነው፤ ከእንቅልፏ የነቃችው፡፡ አለ አይደል…እየናፈቀች ነው የነቃችው፡፡ አይተውት የማያውቁትን ሰው መናፈቅ ምን የሚሉት ነው ብላ አሰበች፡፡  ሆኖም አሁን ከማንም ጋር ማውራት አትፈልግም…የተመስገን ቃላት ከምታውቃቸው ሰዎች በላይ እውነተኛ ናቸው…ቅን ናቸው፡፡ በውስጣቸው ለህይወት የቀረበ ተስፋን ይዘው ነው ወደ ነፍሷ እንደጎርፍ እየፈሰሱ ያሉት፡፡
ፌስ ቡክ ከፈተች፡፡ እንደ ሁልጊዜው አሁንም ተመስገን ኦንላይን ነው፡፡ ፃፈች…
“ተሜ….” አለች፡፡ እንደዚህ ማለት ከጀመረች ቆየች፡፡
“ወዬ…” አለ፡፡ ሁልጊዜ መልዕክቱን እንዳነበበ ነው በፍጥነት የሚፅፈው፡፡ ሁልጊዜ፡፡
“አንድ ነገር ልጠይቅህ? “….ቃላቶቿ ውስጥ አይኖቿን ማየት እንዲችል እያደረገች ነው የምትፅፍለት፡፡ እሱም እያንዳንዱ ነገር ይገባዋል፡፡
“የፈለግሽውን ጠይቂኝ….”
“አሁን ልክ እኔን እንደምታወራኝ የምታዋራቸው ሴቶች አሉ? ካሉስ ስንት ናቸው?”  የእውነትም እስከዛሬ እንደዚህ አይነት ወሬ አውርተው አያውቁም፡፡ ተመስገን የሚያየውን ማመን አቅቶት የሚይዘው የሚጨብጠው ጠፋው፡፡ ጥያቄው ከብዶት አይደለም፡፡ የነፃነት ነፍስ ነው የከበደው፡፡
“አንቺን ብቻ ነው የማናግረው ነፂዬ፡፡ እውነት ነው የምልሽ፡፡ አንቺን ለማውራት ሳስብ ብቻ ነው ፌስ ቡኩን ራሱ የምከፍተው፡፡….እንዴት ዛሬ ይሄን ጠየቅሺኝ?”  
ነፃነት የሚቀጥለውን መልዕክት ከመፃፏ በፊት እጇ ላይ የያዘችው ስልክ አልጋ ላይ አስቀምጣ ትንሽ ተንጎራደደች፡፡ ብዙ አሰበች፡፡ ለማንኛውም በጭንቅላቷ ለሚመጣ ጥያቄ መልስ ሰጠች፡፡ ወደ ስልኳ ተመለሰች፡፡
“እንድንገናኝ አስቤ ነው፡፡ ማለቴ….በአካል፡፡”
ያለወትሮው በመልዕክት ሳጥኑ ውስጥ ፀጥታ ሰፈነ፡፡  
“የምርሽን ነው?” ከብዙ ቆይታ በኋላ፡፡
“የምሬን ነው፡፡”  በፍጥነት መለሰችለት፡፡ ለምን ቆይቶ እንደመለሰላት መጠየቅ አልፈለገችም፡፡ ብቻ እሺ እንዲላት ብቻ ነው የምትፈልገው፡፡ መልስ ሳታገኝ መሸ፡፡ ብዙ ፀጥታ፡፡ ብዙ ትካዜ፡፡ ብዙ ተስፋ መቁረጥ፡፡ ብዙ ፍርሀት፡፡ ብዙ ጥያቄዎች፡፡ ለነዚህ ነገሮች ሁሉ አሳልፎ ሰጣት፡፡ እሱ አይታወቀውም፡፡ እሱ ስለሚሆነው ነገር ምንም እውቀት የለውም፡፡ ነፃነት ግን ተደብቃበት ከነበረው ራስን የመሸሽና ራስን የመጥላት ስሜት አሳዶ ያወጣት  ይህ ሰው፣ ለሷ ሳታስበው የፈጣሪ ስጦታ ከሆነ ቆየ፡፡ አሁን ህይወቷ ውስጥ ማንንም ሳይሆን የምትፈልገው ተመስገንን ብቻ ነው፡፡ ሌላው ነገር በሙሉ እርግማኗ እንደሆነ ነው እየተረዳች ያለችው፡፡ ተመስገንን አግኝታ ፈጣሪዋን ተመስገን ማለት ነው የምትፈልገው፡፡ አለበለዚያ ግን የብቸኝነቷ ጨለማ ውጦ ሊሰለቅጣት እንደሚችል አምናለች፡፡
መሽቶ ነጋ …መልሶ መሸ፡፡ ተመስገን መልስ አልሰጠም፡፡
…..
ተመስገን ካለበት አልጋ ላይ ሆኖ በትካዜ ከፊት ለፊቱ ያስቀመጠው መስታወት ላይ አይኖቹን አትሞ በሀሳብ ገመድ የማያውቀው የስሜቱ ማማ ላይ ለመድረስ ምጥ ላይ ነው፡፡ ነፃነት ፍቅር ውስጥ እንደገባች መጠርጠር አልፈለገም፡፡ ነገር ግን ፍቅር ውስጥ የገባችው ከእሱ ሳይሆን ከቃላቶቹ እንደሆነም ይረዳል፡፡ የትኛውን ተመስገን አሳምኖት ነፃነትን በአካል ማግኘት እንዳለበት ግን ሊያውቅ አልቻለም፡፡ ከራሱ ጋር ሳይታረቅ የነፃነትን አይኖች መመልከት እንደማይችል ጠንቅቆ ይረዳል፡፡ ምን ማድረግ እንዳለበት የሚያዋየው ከራሷ ከነፃነት ውጭ ማንም የለም፡፡
ነፃነት የህይወት ዘመን ጥያቄ መልሱ ናት…ለሱ የገባው ይሄ ነው፡፡
ሆኖም ጊዜያቶች በነጎዱ ቁጥር የተመስገንም ስሜት በነፃነት ላይ መቀዝቀዝ ጀመረ፡፡ ሌሎች ወንዶች ሲያወሩ ሲሰማ ይገረም ነበር፤ አሁን ግን ገባው፡፡ ወንድ ልጅ በልፋት ያገኛትን ሴት ልጅ ነው የሚፈልገው እንጂ በልመና የምትፈልገውን ሴት ሊቀርብ አይፈቅድም የሚለው ሀሳብ ራሱ ላይ ሲከሰት መደንገጥ ጀመረ፡፡ ነፃነት ምንም አይነት ሴት ልትሆን ትችላለች ነገር ግን እሱ ቀድሞ የመገናኘት ፍላጎት ሳይኖረው እሷ ቀድማ ጠየቀችው፡፡ ቀድማው ፈለገችው፡፡ ቀድማው በርቀት ደብቆ ያስቀመጠውን ስሜቱን በራሷ ቃላት ተረከችበት፡፡ ምናልባት ተበሳጭቶባት ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባት የማይለቅ የሚመስለው የወንድ ልጅ ኩራት ከነፍሱ ተጣብቶ አልላቀቅ ብሎትም ሊሆን ይችላል…የትኛው እንደሆነ ሳያውቀው ነፃነትን ናቃት፡፡
……
ነፃነት ለተጨማሪ ሁለት ተከታታይ ወራት ተመስገን ጋ እየፃፈች ፈለገችው፡፡ የምር ፈለገችው፡፡ ሆኖም ተመስገን የለም፡፡ ድንገት ከሌሎቹ ምናንምቴ የወንድ አይነቶች ጋር ተቀላቅሎ ተሰውሮ እንደሆነ ጠርጥራለች፡፡ ሆኖም ይህ የሀሳብ ግኝት ተመስገንን እንድትጠላው ሳይሆን ይባሱኑ እንድትፈልገውና እንድትወደው አደረጋት፡፡ ለምን እንደሆነ የሴትነት እውቀቷ ሊያስረዳት አልቻለም፡፡ የሚሰማትን ስሜት የምታጋራው ሰው የላትም፡፡ ነፃነት ለጊዜው መውደድ ብቻ ነው የምትችለው …መጠበቅ ብቻ፡፡ እንዲህ አድርጎ የሀሳብ ቅርፊቱ ውስጥ የከተታት ደግሞ ተመስገን ነው፡፡
……
ተመስገን የፌስ ቡኩ አለም ተመችቶት ቁጭ አለ፡፡ ከነፃነት ጋር ያደረገው ንግግር ከሌሎች ሴቶች ጋር በነፃነት ማውራት እንዲችል አድርጎታል፡፡ ከመልኩ ይልቅ ቃላቶቹ የውበቱ መገለጫዎች እንደሆኑ አምኖ ያገኛቸውን ሴቶች በሙሉ በሆሄያት ጥበብ ማንዘሩን ተያያዘው፡፡ አምኗል…የትኛዋም አይነት ሴት አይታው ልትወደው እንደማትችል፡፡ ሆኖም ባልገባው መንገድ እነዚህን ሴቶች መበቀል ላይ እንደሆነ አንድ ቀን ተገለፀለት፡፡
ፍቅር የማይገባቸው፣ በቁስ ሱስ ምክንያት ቁሳዊ እብደት ውስጥ ተሰትረው የተከረቸሙ፣ ህይወት የማይገባቸው፣ ሀሳብን ማድመጥ የማይችሉ፣ ቂጣቸውን ማስፋት ውበታቸውንና እድላቸውን እንደማስፋት አድርገው የሚያስቡ፣ ገንዘብ ሲያዩ ነፍስ የሚዘሩ፣ ውሸትን መምጠጥ የሚችል ስፖንጅ ጭንቅላት የተሸከሙ፣ ሀሜት የማይሰለቻቸው፣ እርስ በራሳቸው የማይዋደዱ፣ የሚቀናኑ፣ ተፈጥሮ ቁጥሩ በማይታወቅ ብዛት የረገመቻቸው ፍጥረቶች እንደሆኑ ማመን ከጀመረ ቆየ…ሴት የተባለች ፍጥረት ሁላ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ካለች ፍጥረት ጋር ኖርኩኝ አልኖርኩኝ ጉዳዬ አይደለም ብሎ ደመደመ፡፡ ውበቱንም የዚያው ውሳኔው ውስጥ አገኘው…ወንድነቱን፡፡ እስከዛሬ ሴቶችን የፈራቸው ስለማያውቃቸው እንደሆነ ተገነዘበ፡፡ ስለዚህ ተዋቸው፡፡ ልክ ይሄን ያሰበ ቀንና መወሰኑን የተረዳ ደቂቃ ላይ የተነፈሳት ትንፋሽ…እፎይታው… ለኔ ለፀሀፊው እንኳን ያልተረዳሁት የነፍስ መቅለል ስሜት እንዲሰማው አድርጎታል፡፡
……
ነፃነት ከወንድ ጋር ካወራችም ሆነ ሰላምታ ከተለዋወጠች ዘመናት አለፉ፡፡ ስታስባቸው ራሱ ያንገሸግሻታል…ወንዶችን፡፡ ከአሁን በኋላ ወንዶች ማለት ለነፃነት…
ውሸታሞች፣ ክብር የማይወድላቸው፣ መፈቀር እርግማናቸው የሆነ፣ በፍቅር ህይወት ውስጥ ሀላፊነት መውሰድ የማይፈልጉ ፈሪዎች፣ የመለመን ሱስ የዳጣቸው የሴት ገላ ባሪያዎች፣ ወሲብ አምላካቸው…ዝሙት ድላቸው የሆነባቸው፣ የሴት ልጅን ነፍስ እንደ ካልሲያቸው በፈለጉት ሰዓት የሚለብሱትና የሚጥሉት አድርገው ሁልጊዜ የሚያስቡ፣ ከራሳቸው በላይ ሴትን ልጅ የሚያውቁ የሚመስላቸው፣ ጨካኞች፣ ሀሳባቸው ብቻውን የሚያሳምም፣ ውሸታሞች፣ ውሸታሞች፣ ውሸታሞች፣ ውሸታሞች፣ ውሸታሞች፣ ውሸታሞች፣ ውሸታሞች…..ወንዶች ማለት ለነፃነት አሁን ላይ እንዲህ ይገለፃሉ፡፡
ስለዚህ ወንድ ልጅን ለማፍቀር የሚበቃ የህሊና ክፍተት በጭንቅላቷ ልታገኝ ስላልቻለች፣ አይኖቿን አይኖቿ ሊያዩት ወደማይችሉት ፈጣሪዋ መለሰቻቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆና በድንግልና ወደ ገዳም የሚሰዳትን የመለኮታዊ እውቀት እስክትጠግብ በጭንቅላቷ ተመገበች፡፡ ወንድ ዝር የማይልበት ገዳም ውስጥ ገብታ ራሷን በምታመልከው ፈጣሪዋ እውቀት ውስጥ ማንም እንዳይደርስባት አድርጋ አጠፋችው፡፡
እንግዲህ ይሄው ነው፡፡ አንድ የህይወት ቅፅበት ዘላለምን ሲተውን ማለት ይሄው ነው፡፡ በነፃነትና በተመስገን ውስጥ ያሉት የሴትና የወንድ ትርጓሜዎችና እውቀቶች አሁን ላይ እኛ ጋር አሉ፡፡ ወንድ ማለት…ሴት ማለት…እያልን የምንገልፃቸው ፍጥረቶች ራሳችንን እንደሆነ እስክንረዳ ድረስ ሴት የወንድ ልጅ ፈተናው፣ ወንድ ደግሞ የሴት ልጅ ድክመቷ እየሆኑ ዘላለም ይነጥባል፡፡ ትርጓሜያችን ምንም ያህል እውነቱን እንደሚስት ብንረዳም እርስ በራሳችን ዘወትር እንግዳ ፍጥረቶች ሆነን ምድርን ትተን እንሄዳለን፡፡ እዚህ ድረስ ነው እውቀታችን የመራን…..ወንድ ሴትን ለመረዳት ሴትም ወንድን ለመርዳት የተፈጠርን ፍጥረቶች አድርገን ራሳችንን እየሰራን፡፡

የአእምሮ ጤና ጉዳዮችን ግንዛቤ ለማስጨበጥና የአእምሮ ህመም ያለባቸውን ሰዎች መብት የማስከበር ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው “የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን” በየዓመቱ መስከረም 29 የሚከበር መሆኑ ይታወቃል። የመጀመሪያው የዓለም የአእምሮ ጤና ቀን እ.ኤ.አ. በ1994 “የአእምሮ ጤና አገልግሎትን በአለም አቀፍ ደረጃ ማሻሻል” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል።
የዘንድሮው መሪ ቃል፣ “አእምሮአችን፣ መብታችን” የሚል ሲሆን ፤ ይህም የአእምሮ ጤና ጉዳይ እንደ ሰብአዊ መብት ሊታይ የሚገባ መሆኑን አፅንዖት የሚሰጥ ነው፡፡
የዓለም የአእምሮ ጤና ቀን በአገራችን እየተከበረ  በመሆኑ  ቀኑን አስመልክቶ በየአገሩ እንደሚደረገው መሰረታዊ አለም አቀፍ መሪ ቃሉን አስመልክቶ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ይከናወናል፡፡ ምክንያቱም የዓለም የአእምሮ ጤና ቀንን የማክበር ዋና ዓላማው፤ ስለ አእምሮ ጤና ጉዳዮች ግንዛቤን ለማስፋት፣ መገለልን ለመቀነስና ስለ አእምሮ ሁለንተናዊ ደህንነት ግልጽ ውይይቶች እንዲደረጉ ለማበረታታት ነውና፡፡  በተጨማሪም፣ ግለሰቦችንና ማህበረሰቦችን ስለ አእምሮ ጤንነት፣ በሰዎች ህይወት ላይ ስላለው ተጽእኖ ግንዛቤ ማስጨበጥን እንዲሁም እርዳታና ድጋፍ ለመፈለግ እንዲበረታቱ ለማስተማር ያለመም ነው። ስለዚህም በዚህ ቀን ካለንበት አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ስለ አእምሯዊ ሁኔታችን አንዳንድ ነገሮችን መነጋገሩ የሚጠበቅ ነው፡፡
እንደሚታወቀው አገራችን የረዥም ዓመታት የበለፀገ ባህልና ቅርስ ባለቤት፣ ታሪካዊትና ኩሩ ህዝብ ያላት ሀገር ነች፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ጦርነት፣ ግጭትና መፈናቀልን ጨምሮ ብዘ ፈተናዎችን እየተጋፈጠች ያለች ሀገር ሆናለች፡፡ እነዚህ ተግዳሮቶች በአእምሮ ጤና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ይታመናል።
 የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ፣ 10 በመቶ ያህሉ  የኢትዮጵያ ህዝብ (በየትኛውም የእድሜ ክልል ውስጥ)፣ እንደ ድብርትና ጭንቀት የመሰለ የተለመደ የአእምሮ መታወክ እንደሚያጋጥመው ይጠቁመናል። ይሁን እንጂ በህሙማኑ ላይ በሚደርስ መገለልና በግንዛቤ ማነስ ሳቢያ ብዙ የአእምሮ ህመም ያለባቸው ሰዎች፣ እርዳታ ወደሚያገኙበት የጤና አገልግሎት መስጫ ቦታ ሊሄዱ አይፈልጉም፡፡ የአደገኛ እፅ አጠቃቀምም በአገራችን ትልቅ ችግር ነው። ለምሳሌ ከመላው ህዝባችን ውስጥ አዲስ ነገርን ለማወቅ ጉጉት አለው የሚባለው አምራችና የኢኮኖሚው ኃይል የሆነው ወጣቱ፣ (40.1 ሚሊዮን ያህሉ) ከ15-35 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኝ መንግሥት ይፋ አድርጓል፡፡ ከዚህ ውስጥ 4.4 % የሚሆነው የአደገኛ እፅ ተጠቃሚነትና ተጋላጭነት ችግር እንዳለበት የሰራተኛ ማህበራዊና ሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴር አመልክቷል፡፡ የአደገኛ እፅ ተጠቃሚነትና ሱሰኝነት ችግር፣ ከሌሎች ከባባድና ቀላል የአዕምሮ ችግሮች ጋር የሚወሳሰብ ችግር እንደሆነ  ይታወቃል፡፡ 50 በመቶ የሚሆኑት የአዕምሮ ጤና እክል ተጠቂዎች የአደገኛ እፅ ተጠቃሚነት ተደራቢ ችግር እንደሚኖርባቸውና 50 በመቶ የሚሆኑት የአደገኛ እፅ ተጠቃሚዎች የአዕምሮ እክል ሊኖርባቸው እንደሚችል በርካታ ጥናቶች ይፋ  አድርገዋል፡፡
በአገራችን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር፣ የተለያዩ የአዕምሮ ጤና እክሎች፣ ትራውማና የአደገኛ እፅ ተጠቃሚነት ችግር ወይም የሱስ ህመም በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምሩ የሚችሉ ተጠባቂ ጉዳዮች በማድረግ፣ የሚመለከታቸው አካላት በጉዳዩ ላይ ሰፊ ስራ እንዲሰሩ መቀስቀስ ያስፈልጋል፡፡
በእርግጥ በኢትዮጵያ የአእምሮ ጤናና የአደገኛ ዕፅ አጠቃቀም መቃወስ የህክምና አገልግሎት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ  እያደገ መጥቷል፡፡ ለዚህም መንግስት የሚያስመሰግነውን ሥራ  ሰርቷል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ሀገሪቱ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው የአእምሮ ጤና ህክምና መስጫ፣ ባለሙያዎችና አነስተኛ በጀት ነው ያሏት።
በዚህ የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን፣ የአእምሮ ጤና ሁለንተናዊ ሰብአዊ መብት መሆኑን በማስታወስ ለጉዳዩ የምንሰጠውን ትኩረት እንዲጨምር ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው፤ ገቢው፣ ማህበራዊ ሁኔታውና የኋላ ታሪኩ ምንም ይሁን ምን፣ ጥራት ያለው የአእምሮ ጤና አገልግሎት የማግኘት መብቱ እንዲከበር ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ በመንግስት ደረጃ በጤና ተቋማት በቀጥታ አገልግሎት የሚሰጡ ወይም በከፊል የሚደጎሙ የማህበረሰብ አገልግሎት መስጫዎች በሚኖሩበት ሁኔታ ላይ ብንወያይበት መልካም ነው።
በአገራችን የአእምሮ ጤናና የአደገኛ ዕጽ አጠቃቀም የሱስ ህመም ችግር የህክምና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ሊደረጉ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮችን ልጠቁም፡-
 በአእምሮ ጤናና በአደገኛ ዕፅ አጠቃቀም የሱስ ህመም ችግር የህክምና አገልግሎቶች ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶችን መንግሥት ቢያበረታታ፤
ተጨማሪ የአእምሮ ጤና ባለሙያዎችን በየዘርፉ ማሰልጠን ቢቻል፤
 የአእምሮ ሕመም ባለባቸው ሰዎች ላይ የሚደርሰውን መገለልና መድልዎ በተደራጀ መልኩ በርካታ ባለድርሻ አካላትን እያሳተፉ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በመስራት ለመቀነስ ጥረት ማድረግ፤
 በመንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ የአእምሮ ጤና ጉዳዮችን ልክ እንደ ፆታዊ የመብት ጥያቄዎች ትኩረት የመስጠትን ጉዳይ፣ “የአእምሮ ጤና ዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ነው” የሚለው ሃሳብ፣ ህገ-መንግሥታዊ መብት መሆኑንም ጭምር በመጥቀስ፣ በስፋት የመነጋገሪያ አጀንዳ ብናደርገውና እርዳታ የመፈለግ አስፈላጊነትን ግንዛቤ ብናሳድግ፤ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ በአገራችን የአእምሮ ጤናንና ሁለንተናዊ ደህንነትን በማስተዋወቅ፣ ሁላችንም የየራሳችንን ሚና መጫወት እንችላለን። ሁሉም ሰው ጤናማ ህይወት የመምራት እድል የሚያገኝበት አለም ለመፍጠር በጋራ እንስራ።
አገር ማለት ሰው ነው! ቸር እንሰንብት!
***
ከአዘጋጁ፡- የጽሁፉ አቅራቢ የመቋሚያ የማህበረሰብ ልማት ድርጅት፣ ኤክስኪውቲቭ ዳይሬክተርና ከሱስ የማገገም አማካሪና አሰልጣኝ (Recovery coach) ናቸው፡፡

በቡዲዝም ሃይማኖት የሚተረት አንድ የታወቀ ተረት አለ፡፡
ሰውዬው አስማተኛ ነው፡፡ አስማቱ የሚሰራው ግን ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ተስተካክለው የሚደረደሩበትን ወቅት ጠብቆ ነው፡፡ አስማተኛው የሰማዩ ፍጥረታት የተወሰነ ቦታ ላይ ሲደርሱ ጠብቆ ይመለከትና ድግምቱን ያነበንባል፡፡ ከዚያም ከሰማይ ብዙ ሀብት ይዘንባል፡፡ ወርቅና አልማዝ ይፈስሳል!
አንድ ቀን ልክ ከሰማይ ሊያዘንብ በተቃረበበት ሰዓት ዘራፊ ወንበዴዎች ደርሰው ያዙትና ገንዘብ አምጣ አሉት፡፡ “ገንዘብ የለኝም ደሀ ነኝ፡፡ ግን በአስማት ሀብት ላዘንብላችሁ እችላለሁ!” ብሎ ድግምቱን ደገመ፡፡ ወርቅና አልማዝ ዘነመላቸው፡፡ እየተሻሙ ከረጢታቸው ውስጥ ይከቱ ጀመር፡፡ ይህን እያረጉ ሳሉ ከየት መጡ ሳይባሉ ሌሎች ዘራፊ ወንበዴዎች ድንገት ከበቡዋቸው፡፡፡ “በሉ አደጋ ሳይደርስባችሁ ከረጢቶቹን ሁሉ ቁጭ አድርጉዋቸው!” ሲሉ አስጠነቀቁዋቸው! የመጀመሪያዎቹ ወንበዴዎች አለቃ እንዲህ አለ፡-
“ጎበዝ! እኛንና እናንተን የሚያጣላን ነገር የለም፡፡ ሀብት እንደሆነ የምትፈልጉት እኛም ያገኘነው ከዚህ ሰው ስለሆነ እርሱን ጠይቁት”
የኋለኞቹ ወንበዴዎች ወደ አስማተኛው ሰው ዞረው፤ “በል ለኛም እንደነሱ ወርቅና አልማዝ ስጠን” አሉት፡፡ አስማተኛውም፤ “ሀብት ለማዝነብ የምችለው ፀሀይ ጨረቃና ከዋክብት ተስተካክለው ሰማይ ላይ በሚሰለፉበት በአንዲት በተወሰነች ቅጽበት ነው፡፡ ይቺ ቅጽበት በዓመታት ውስጥ አንዴ ብቻ የምትገኝ ናት፡፡ ስለዚህ ያቺ ቅጽበት እስክትገኝ መጠበቅ አለብኝ” አላቸው፡፡
ወንበዴዎቹ በጣም ተናደዱ፡፡ ከፊተኞቹ ወንበዴዎች ጋርም ኃይለኛ ድብድብ ጀመሩ፡፡ በዚህ መካከል አስማተኛው ሰው የማምለጫ እድል ስላጋጠመው ሹልክ ብሎ ወደ ጫካው ገብቶ ተደብቆ መጨረሻውን ይመለከት ጀመር፡፡
ወንበዴዎቹ እርስ በርስ ተጫረሱና ሁለቱ መሪዎች ብቻ ቀሩ፡፡
አንደኛው መሪ፤ “ይሄን ሰው በድብድብ አልችለውም፡፡ ስለዚህ በአንዳች ዘዴ ብገድለው ይሻላል” ብሎ አሰበና “ስማ ወዳጄ፣ እኔና አንተ መጋደል አይጠቅመንም፡፡ ይልቁንም ተመካክረን በሰላም መኖር እንችላለን” አለው፡፡
ሁለተኛው የወንበዴ መሪ በሀሳቡ ተስማማ፡፡ ግን እሱም በልቡ፤ “በሌላ ዘዴ አጠፋዋለሁ! ከዚያ ሀብቱ በሙሉ የእኔ ይሆናል” ብሎ አስቦ ነው፡፡ ሀብቱን ሁሉ ተሸክመው ወደ አንድ ዋሻ ገቡ፡፡ ገና ውይይት ሲጀምሩ ግን አንደኛው በጣም እንደራበው ገለጠ፡፡ ስለዚህ አንዳቸው ሀብቱን ሲጠብቁ ሌላኛው ተዘዋውሮ ምግብ ፈልጎ ሊያመጣ ተስማሙ፡፡
ምግብ ፈላጊው እንደወጣ ሀብታቸውን ሊጠብቅ ዋሻው ውስጥ የቀረው ጎራዴውን መሳል ጀመረ፡፡ “ቆይ! ምግቡን ይዞ ሲመጣ አንገቱን ቀንጥሼ እጥልለታለሁ!” አለ፡፡
ምግብ ፍለጋ የሄደው ደግሞ ልክ ምግቡን እንዳገኘ፤ “ይሄን ምግብ መርዝ አስነክቼ አጅሬ እበላ ብሎ ሲስገበገብ ያልቅለታል!” አለና ምግቡን መርዞ ይዞ መጣ፡፡ ሆኖም ለማውራት እንኳን ጊዜ ሳይኖረው ባለጎራዴው አንገቱን ቀንጥሶ ጣለው፡፡
ባለጎራዴው ባገኘው ድል ተደስቶ፤ “አለቀልህ! በእቅድ መመራት ጥቅሙ ይሄ ነው! ጠላትን በዘዴ መጨረስ ነው እንጂ ጉልበትን ተማምኖ ጠብ-መግጠም ዋጋ የለውም! እንግዲህ ምግቤን ልከስክስና ሀብቴን ተሸክሜ ወደ አገሬ ልግባ!” ብሎ ያመጣለትን ምግብ በደስታ መብላቱን ተያያዘው፡፡ ዳሩ ግን ምግቡን እንኳ በቅጡ ሳይመገብ ህይወቱ አለፈች፡፡
አስማተኛው ከተደበቀበት ወጥቶ እየሳቀ ሀብቱን ሰብስቦ ይዞ ሄደ፡፡
***
ለሁሉ ነገር ወቅት ወሳኝ  ነው፡፡ ፀሐይ፣ ጨረቃና ኮከብ ተገጣጥመው ደግ ቦታ ላይ ካልተደረደሩ መልካም ነገር አይመጣም፡፡ ያቺ አመቺና የተስተካከለች ቅጽበት ካልተፈጠረች አገር ሀብት አይዘንብላትም፡፡ ሀገር የምትመኘውን ሰላም፣ የምትናፍቀውን ብልጽግና አታመጣም፡፡ ይህንን ለማየት ብልህና መልካም ዕይታ ብቻ ሳይሆን ቀና ልቡና ይፈልጋል፡፡ “ቆይ እንዲህ አድርጌ በዚህ ዘዴ አጠፋዋለሁ” ብሎ መዶለት ሳይሆን ልባዊ ውይይትን ይሻል፡፡ ደባ ሳይሆን ግልጽነት፣ ጠባብ ወገናዊነት ሳይሆን ሆደ-ሰፊ የሆነ ህዝብን አሳታፊነት፣ በርን ዘግቶ እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን ማለት ሳይሆን “እስቲ ሌሎች የሚሉትን ልስማ” ማለትን ይጠይቃል፡፡ የፖለቲካ ቡድኖች፣ የተቀናቃኝ ወገኖች መሪዎች ወይም የአንድ ቡድን ዋና ዋና ኃይሎች እርስ በርስ እስኪጠፋፉለት እንደአስማተኛው ተሸሽጎ ውጤቱን የሚጠባበቅ ማህበረሰብ ሳይሆን፤ “የሁሉም ሀብትና መብት ባለቤት እኔ ራሴ ነኝ!” የሚል ንቁ ተሳትፎ ያለው ህዝብ እንዲኖረን ነው የምንሻው፡፡ “በሬ የቀለበውን ትቶ የቀጠቀጠውን ይልሳል” ይሏልና ብዙ መስዋዕትነት ለከፈለለት፣ ባደባባይም በሚስጥርም ለደማ ለቆሰለለት ወገኑ ሳይቆረቆር ከረገጠውና ከበደለው ጌታ ስር የማይንበረከክ ህብረተሰብ ነው መኖር ያለበት፡፡ ለመብቱ የሚቆምና ለሀገሩ አሳቢ ሀቀኛ ዜጋ መፈጠር ነው የሚኖርበት፡፡ ነገ አርአያነት ያለው መሪ (Role Model) ቢያሻ ለመምረጥም ሆነ ለመመረጥ ዝግጁ የሆነ ዜጋ ማፍራት ነው የሚገባው፡፡
ዛሬ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመደራጀት መብቱን አስከብሮ የሚያከብር ሲቪክ ማኅበረሰብ የመገንባት ሀላፊነት ነው ያለብን፡፡ የፕሬስ ነጻነት የህዝብ የማወቅ መብት መሆኑን ደግመን ደጋግመን ማሳየት ነው ያለብን፡፡ ፕሬስ የህዝብ ዐይንና ጆሮ ነው፡፡ የጉልበተኛን ጉልበት መገደቢያ፣ የሞሳኙን እጅ መሰብሰቢያ ፕሬስ ነው፡፡ ፕሬስ አንደበት ላጡ አንደበት ነው፡፡ አገራዊውን አባባል ተውሰን ብንገልፀው፤ “ፕሬስና ጭስ መውጪያ አያጣም!” ለማለት ይቻላል፡፡  የክፉ ጊዜ የኖህ መርከብ ነው፤ ፕሬስ-ለጥፋት ውሃ ደራሽ!
እንደ ወቅቱ ወረት (ፋሽን) በየአደባባይ ሸንጎው የሚነሱ የዲሞክራሲ መብቶች፣ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህና የልማት መርሆዎች እንደመፈክር ከሚሰግሩበትና ለለጋሽ አገሮች ፍጆታ ብቻ በቃል ከሚነበነቡበት በቀቀናዊ ባህሪ ተላቀው መሬት የያዘ ተግባራዊ ህልውና እንዲኖራቸው ጥረት ሲደረግ ብቻ ነው ከድህነት መላቀቅ የሚቻለው፡፡ ግምገማ ተፈርቶ በፈጣን ልማት ስም የሚሯሯጡበት እቅድና ጥናት፣ የአለቃን ወይ የኃላፊን መሪ-ቃል “እንደ ፍካሬ እየሱስ ትንቢት ካልደጋገምኩ የት-አባቴ እገባለሁ” በሚል ስጋት የሚለፈፍ ባለ ጭምብል ግልጽነት፣ ከቶም የማደግ ምልክት ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በውጥረት ሰዓት የሚሰራው ሥራ ሁሉ፣ ለድቀት ፈውስ (Crisis management) ፍለጋ የሚነደፍ ፖሊሲ ሁሉ፣ እንደ ቀበርቾና እንደ ወገርት ከጓሮ የሚቆረጥ ያገረ-ሰብ መድሀኒት አይሆንም፡፡ እንደ ረጅም ግብ መምቻ አብሪ ጥናት ተደርጎ ሊታሰብም ከቶ አይችልም፡፡
የአዛዥና የታዛዥ፣ የአለቃና የምንዝር ግንኙነት ባለበት ቢሮክራሲያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ሥርዓት ውስጥ “ታላቅየው ሲመቸው ታናሽየው ሳይድህ በእግር ይሄዳል” የሚባለው ተረት ዓይነት ሁኔታ ቢታይ አይገርምም፡፡ ታላቅም ታናሽም ሩቅ ሳይሄዱ “የእኔ እበልጥ” “እኔ እበልጥ”፣ “የእኔ ልሰማ” “እኔ ልሰማ” ሽኩቻና ጠብ ውስጥ እንደሚገቡ የሩቅና የቅርብ የሀገራችን ገዢ መደቦች ሂደት ታሪካዊ ማህተሙን የረገጠበት ጉዳይ ነው፡፡
በሌላ ወገን ደግሞ በሲቪክ ማህበረሰብ ግንባታ ውስጥ ሁሌም አስቸጋሪ የሚሆኑ ሁለት ፊት ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉትን ሰዎች “የአንድ አራሽ ንግግር” የተሰኘው የኦሌ ኤሪክሰን መጽሐፍ እንዲህ ይጠቅሳቸዋል፡-“ክፎች እንኳ ትጋትን ይወዳሉ፡፡ ሌቦች ተግተው ስለሚሰርቁ ደህና ሰዎች ይመስላሉ፡፡ ጎበዝ የሚገኝበትን ቦታ ብታውቅ ደግነት ያለው አይታጣም፡፡ ከጅብ ጋር የሚጮህ ከበግም ጋር ባ ባ የሚለውን ሰው ግን ከሰይጣን በቀር የሚያመሰግነው የለም፡፡ ካንድ ባርኔጣ በታች ብዙ ጊዜ ሁለት ፊቶች ይታያሉ፡፡ ብዙዎች ከዶሮች ጋር እያሽካኩ ከቀበሮ ይመሳጠራሉ፡፡ አያሌ ሰዎች ቅቤ ባፋቸው የማይቀልጥ እየመሰለ የሚጠቅማቸው እንደ ሆነ እሳትን ይተፋሉ፡፡ በርኖሳቸውን እንደ ነፋሱ ይለውጣሉ፡፡ ከጥንቸል ጋር እየሮጡ ከውሾች አብረው የሚያድኑ ሰዎች እስካሁን ይገኛሉ፡፡ ይህ ለዐይን የሚከፋ፣ ለአፍንጫ የሚከረፋ ነው፡፡ ዝባድ ከውሻ፣ እምነትና ቅንነት ከባለጌ አይገኝም፡፡ ገልበጥባጦች በሁሉ ይቆዩናል፡፡ ከመልአክ ጋር መላዕክት፣ ከጋኔን ጋር አጋንነት ናቸው፡፡ ውሃ መስለው በእሳት ላይ ይገነፍላሉ፡፡ ሲበርድ ይረጋሉ፣ እንደ በረዶ ይሆናሉ፡፡ የሚመሩበት መቀንያ የላቸውም፡፡ በጣራ የሚቆም አውራ ዶሮ ምስል ጭራውን ንፋስ ወደሚነፍስበት ያቀናል፡፡ መልካም ቢሆን ክፉ፣ ግድ የላቸውም፡፡ ትርፍ በሚያገኙበት ነገር ያምናሉ፡፡ ሰው በሚያልፍበት ወጥመድን ይጠልሉ፡፡ እንደ ጥቅማቸው መጠን ውሻ ወይም አንበሳ መስለው ይታያሉ፡፡” ሌላው ብርቱ ጉዳይ በአናቱም ይሁን በጀርባው፣ በሸንጎም ይሁን በቡድን የሚወሰኑ ውሳኔዎች፣ አገርን በሚመለከት የሚታቀዱ ታላላቅ እቅዶች፣ ወደ ተግባር ከመመንዘራቸው በፊት የህዝብን የማወቅ መብት የረገጡ አለመሆናቸውን ማስተዋል ነው፡፡ ማንም ይሁን ማን ይዋል ይደር እንጂ በህዝብ ላይ የፈፀመው ጥፋት፣ ያደረሰው ጉዳት ካለ፣ ነገ ታሪካዊ ተጠያቂነት እንደሚኖርበት አሌ አይሉት ሀቅ ነው፡፡ እንደተጠያቂነቱ መጠን ተመጣጣኝ ፍርድ አለ፡፡ ዛሬ በማስመሰልና ባልባለቀ አዕምሮ የሚያጥሩት የመብት አጥር፣ ነገ አጥሩ የፈረሰ ሰዓት ፀሐይም፣ ጨረቃም፣ ከዋክብትም ይገጣጠሙና ላንዱ ሲነጋ ላንዱ መምሸቱ ግድ ይሆናል፡፡ በተለይ ለዘመናት የተደከመለት የመናገርና ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት፣ የምንመኘው ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት፣ የምናቅደው መልካም አስተዳደር፣ እናሰፍነዋለን የምንለው ፍትሐዊነትና እንገላገለዋለን የምንለው የሙስና አባዜ፣ ያለህዝብ ድጋፍና ያለ ህዝባዊ ልቡና መቼም ፍሬ ሊያፈራ እንደማይችል ለአንዲትም ደቂቃ መርሳት አይገባም፡፡ ያ ካልሆነ “አገር ያልኩህ በረሃ፣ ዱባ ያልኩህ ቅል ያላልኩህን ታበቅል?!” የሚያሰኘን ይሆናል፡፡

የሰላም ምኞት ብዙ ጊዜ የማይሳካው፣… የተጣራና የተሟላ ምኞት ስላልሆነ ነው። “ምናለ ወንድማማቾች ባይገዳደሉ” ብለን መመኘት እንችላለን። ግን አይሳካም። ለምን? አራት ምንያቶችን እንመልከት፡፡ አንዳንዴ  የሐሳባችን ብዥታ ነው ችግሩ። አባራሪ ተግባራት፣ ገዳይና ሟች፣ በዳይና ተበዳይ… ያለ ልዩነት “ፀበኞች” ብለን የምንሰይማቸው ከሆነ፣ ሐሳባችን ደፍርሷል።አንዱ ሰውዬ ነውጠኛ፣ ወንድምዬው  ደግሞ ሰላምተኛ ሊሆን ይችላል። ነውጠኛው ሰላምተኛውን ሲገድለው፣… እንዲሁ በደፈናው ነገሩን አድበስብሰን “ወንድማማቾች ተገዳደሉ” ብለን የምናስብ ከሆነ፣ ሐሳባችን ተዝረክርኳል።
የዘረፋ እና የተዘረፉ፣ ማንና ማን እንደሆኑ ለመለየት ደንታ ሳይሰጠን፣ “የተዘራረፉ” እያልን ለማውራት የምንቸኩል ከሆነ፣ ለሰው ህይወትና ንብረት እንዴት ደንታ ይኖረናል?  ሰዎች ባይዘራፉ?” ብለን ብናስብና ብንመኝ፣ ሐሳባችን የተምታታ ነውና ምኞታችን ትርጉም የሌለው ይሆናል።
ጎጂ እና ተጎጂ፣ ነውጠኛና ሰላምተኛ፣ ሥርዓት አልበኛና ሕግ አክባሪ ሰዎችን ለይተን ማስተዋል፣ በትክክል ማረጋገጥና አጣርተን ማሰብ ካልቻልን፣ ምኞታችን ባይሳካ አይገርምም። ስለምን እየተነጋገርንና ምን እየተመኘን እንደሆነ በቅጡ አናውቅም ማለት ነውና። ወይም የማወቅ ፍላጎት የለንም፡፡
ይህም ብቻ አይደለም።
የሰዎችን ባሕርይ በግል ለይቶ ማወቅ በጣም አስፈላጊ የመሆኑን ያህል፣ ለድርጊታቸውም በቂ ትኩረት ካልሰጠን፣ የሰላም ምኞታችን ከንቱ ይቀራል።
ነውጠኛው ሰውዬ፣ ሁልጊዜ የሁሉም ጥፋቶች ተጠያቂ ብናደርገው ደስ ይለን ይሆናል። ማጣራት ሳያስፈልገን፣… “ያ ልማደኛው መሠሪ ነው የሁሉም ነገር  አጥፊ። የነውጠኛው ሥራ ነው!” ብለን መፍረድ እንችላለን።
ሰላምተኛው ሰውዬ በአንዳች ምክንያት ነውጠኛ ተግባር ሊፈጽም ይችላል። “አይ! እሱ እንዲህ አይትት  ጥፋት አይሰራም፡፡ አድርጎት ከሆነም በደል ቢደርስበት ነውና አይፈረድበትም ከመስመር ተሻግሮ ከልክ አልፎ ክፉ ጥፋት ቢፈፀም እንኳ፣ ሰላምተኛ ሰው ስለነበረ ጥፋቱን አንቁጠርበት። ጠላት ደስ አይበለው” ለማለት እንፈልግ ይሆናል።
በዚህ ዐይነት የተጣመመ ሐሳብ ግን የሰላም ምኞት ወደ ሦስተኛው ችግር እንለፍ።… ሁለት ሰላምተኛ ሰዎች ሲጣሉ፣… ወይም ሁለት ነውጠኞች እርስ በርሱ ጸብ ሲፈጥሩ፣… በተመሳሳይ መፍትሔ ውጤታማ ለመሆን ከተመኘን ተሳስተናል። ሰላምተኛ ሰዎች በአንዳች ሰበብ አለመግባባት ሲያጋጥማቸው፣ ሲነጋገሩና ሲመላለሱ፣ በግልፍታና በስጋት ስሜት፣ ወደ ክፉ ንግግርና ወደ ትንቅንቅ ሊያመሩ ይችላሉ። በነገር ሲመላሱና ሲሰናዘሩ፣ ሁለቱም አጥፊ ሁለቱም ተጎጂ ይሆናሉ። ሁለቱም በዳይ፣ ሁለቱም ተበዳይ እየሆኑ የየራሳቸው ጉዳት ገንኖ እየታያቸው የፀብ ስሜት ውስጥ ይዘፈቃሉ።
መፍትሔውስ? በባህሪያቸው ሰላምተኛ የሆኑ ሰዎች በስህተትና በአለመግባባት ወደማይፈልጉት ፀብ እንዳይገቡ፣… ከተቻለ በእርጋታ መነጋገር ወይም ገላጋይ ዐዋቂዎችን ማማከር፣ ካልሆነ ደግሞ ወደህግ ሙያተኞችና ወደ ዳኝነት ሥርዓት መሄድ ይችላሉ፡፡
አንዱ ሌላኛውን የማጥፋት ነውጠኛ ፍላጎት እስከሌለው ድረስ፣ ትክክለኛና ሚዛናዊ ሀሳብ ሊያስማማቸው ይችላል፡፡ ካልሆነም ዳኝነት ያከባብራቸዋል፡፡ ሁለት ነውጠኛ ሰዎች እርስበርስ ለመጠፋፋት ሲዘምቱ፣ በተመሳሳይ የውይይትና የሽምግልና መንገድ ለማስታረቅ መሞከር ውጤታማ ይሆናል ብለን ካሰብን ግን፣ በከንቱ ደከምን።
 አንዱ ሌላውን ለማጥፋት የሚዘምቱ ከሆነ፣ ሌሎች ሰላምተኛ ሰዎችን ከማጥቃት አይመለሱምና ዋና ጥንቃቄያችን እንዴት አደብ ልናስይዛቸውና ልንቆጣጠራቸው እችላለን የሚል መሆን አለበት፡፡
ነውጠኞችን መቆጣጠር የማይችል አገር፣ የነውጠኞች መጫወቻ ይሆናል፡፡ ልዩነቱም እዚህ ላይ ነው፡፡ የቁጥርና የደረጃ ጉዳይ እንጂ፣
“ነውጠኞች በሁሉም አገር በሁሉም ዘመን መኖራቸው አይቀሬ ነው፡፡
ነውጠኞችን መቆጣጠር የቻሉና ያልቻሉ ሰዎች፣ ሰላምተኛ ወይም ነውጠኛ አገር ይኖራቸዋል፡፡
በሌላ አነጋገር፣… “ሰላምተኛ አገርና መንግስት” ማለት… ነውጠኞች የሌሉበት ወይም ነውጠኛ ተግባር የማይፈፀምበት አገር ማለት አይደለም፡፡ ነውጠኛ ተግባርን በአጭር ማስቆም ነውጠኞችን መቆጣጠር የተቻለበት አገር ነው ሰላምተኛ አገር።
ነውጠኛ አገርና መንግስት ማለት የአገሬው ሰዎች ነውጠኞች ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የነውጥ ተግባራትን ማስቆምና ነውጠኞችን መቆጣጠር የሚችል ሥርዓት ያልተገነባበት ወይም የፈረሰበት አገር ማለት ነው- የነውጥ አገር ማለት፡፡
አንድ ሁለት ገናና ነውጠኞችን በማስወገድ ብቻ አገሬው ሰላም አያገኝም፡፡ ተተኪ ነውጠኞች ይነሱበታል፡፡ የነውጥ ተግባራትን የሚከላከል ሀሳብ፣ ጥፋቶችን የሚያስቆም አቅም፣ ነውጠኝነትን መቆጣጠር የሚችል ስርዓት እየገነባ ሲጓዝ ነው የህሊናም የኑሮም ሰላም የሚያገኘው፡፡
እነዚህን ስህተቶች አጥርተን፣ ሐሳባችንን አስተካክለን፣ የፍልስጥኤምንና የእስራኤልን ታሪክ፣ የሐማስ የሽብር ዘመቻና የእስራኤል መንግስት የአጸፋ ወታደራዊ ዘመቻዎችን መመልከት እንችላለን።
ወይስ ገና የራሳችንን መከራ መመርመር፣ የኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ጦርነትና ትርምስን በቅጡ ማስተዋልና ማገናዘብ ሳንችል የሌሎች አገራት ጦርነት ላይ ጥልቅ ትንታኔ ለማቅረብ ብንሞክር አቅማችን ይፈቅዳል? ብንችልስ ያምርብናል?
በእርግጥ፣ ከየትኛውም አገር የሚገኝ የታሪክ ትምህርት ጠቃሚ እንደሆነ አያከራክርም። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ ኢትዮጵያን የሚነካ ጉዳይ መሆኑም አይቀርም።
የዓለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ ሲቃወስ፣ ለኛም ጦሱ ይደርሰናል።
በዚያ ላይ በርካታ የኢትዮጵያ ተወላጆች የጭካኔ ጥቃት ደርሶባቸው፣ በአሳዛኝ ሁኔታ መሞታቸውንና መጎዳታቸውን ሰምተናል። በአጭሩ የእስራኤልና የፍልስጥኤም ጉዳይ እጅግ ቅርባችን ነው።
ቢሆንም ግን… እዚህ ከቤታችን ከደጃችን ብዙ ጦርነትና ብዙ ሞት፣ ብዙ ትርምስና የኑሮ ችግር አለብን።
አገራችንን በቅጡ ሳናገናዝብ  ውጭ አገራትን  ጦርነት መተንተን ይሆንልናል? ቢከብድም ያስፈልጋል። ከሆነ አይቀር ደግሞ በትክክለኛ ሐሳብና በትክክለኛ ሚዛን ነው ፋይዳ የሚኖረው።



የሰላም ምኞት ብዙ ጊዜ የማይሳካው፣… የተጣራና የተሟላ ምኞት ስላልሆነ ነው። “ምናለ ወንድማማቾች ባይገዳደሉ” ብለን መመኘት እንችላለን። ግን አይሳካም። ለምን? አራት ምንያቶችን እንመልከት፡፡ አንዳንዴ  የሐሳባችን ብዥታ ነው ችግሩ። አባራሪ ተግባራት፣ ገዳይና ሟች፣ በዳይና ተበዳይ… ያለ ልዩነት “ፀበኞች” ብለን የምንሰይማቸው ከሆነ፣ ሐሳባችን ደፍርሷል።አንዱ ሰውዬ ነውጠኛ፣ ወንድምዬው  ደግሞ ሰላምተኛ ሊሆን ይችላል። ነውጠኛው ሰላምተኛውን ሲገድለው፣… እንዲሁ በደፈናው ነገሩን አድበስብሰን “ወንድማማቾች ተገዳደሉ” ብለን የምናስብ ከሆነ፣ ሐሳባችን ተዝረክርኳል።
የዘረፋ እና የተዘረፉ፣ ማንና ማን እንደሆኑ ለመለየት ደንታ ሳይሰጠን፣ “የተዘራረፉ” እያልን ለማውራት የምንቸኩል ከሆነ፣ ለሰው ህይወትና ንብረት እንዴት ደንታ ይኖረናል?  ሰዎች ባይዘራፉ?” ብለን ብናስብና ብንመኝ፣ ሐሳባችን የተምታታ ነውና ምኞታችን ትርጉም የሌለው ይሆናል።
ጎጂ እና ተጎጂ፣ ነውጠኛና ሰላምተኛ፣ ሥርዓት አልበኛና ሕግ አክባሪ ሰዎችን ለይተን ማስተዋል፣ በትክክል ማረጋገጥና አጣርተን ማሰብ ካልቻልን፣ ምኞታችን ባይሳካ አይገርምም። ስለምን እየተነጋገርንና ምን እየተመኘን እንደሆነ በቅጡ አናውቅም ማለት ነውና። ወይም የማወቅ ፍላጎት የለንም፡፡
ይህም ብቻ አይደለም።
የሰዎችን ባሕርይ በግል ለይቶ ማወቅ በጣም አስፈላጊ የመሆኑን ያህል፣ ለድርጊታቸውም በቂ ትኩረት ካልሰጠን፣ የሰላም ምኞታችን ከንቱ ይቀራል።
ነውጠኛው ሰውዬ፣ ሁልጊዜ የሁሉም ጥፋቶች ተጠያቂ ብናደርገው ደስ ይለን ይሆናል። ማጣራት ሳያስፈልገን፣… “ያ ልማደኛው መሠሪ ነው የሁሉም ነገር  አጥፊ። የነውጠኛው ሥራ ነው!” ብለን መፍረድ እንችላለን።
ሰላምተኛው ሰውዬ በአንዳች ምክንያት ነውጠኛ ተግባር ሊፈጽም ይችላል። “አይ! እሱ እንዲህ አይትት  ጥፋት አይሰራም፡፡ አድርጎት ከሆነም በደል ቢደርስበት ነውና አይፈረድበትም ከመስመር ተሻግሮ ከልክ አልፎ ክፉ ጥፋት ቢፈፀም እንኳ፣ ሰላምተኛ ሰው ስለነበረ ጥፋቱን አንቁጠርበት። ጠላት ደስ አይበለው” ለማለት እንፈልግ ይሆናል።
በዚህ ዐይነት የተጣመመ ሐሳብ ግን የሰላም ምኞት ወደ ሦስተኛው ችግር እንለፍ።… ሁለት ሰላምተኛ ሰዎች ሲጣሉ፣… ወይም ሁለት ነውጠኞች እርስ በርሱ ጸብ ሲፈጥሩ፣… በተመሳሳይ መፍትሔ ውጤታማ ለመሆን ከተመኘን ተሳስተናል። ሰላምተኛ ሰዎች በአንዳች ሰበብ አለመግባባት ሲያጋጥማቸው፣ ሲነጋገሩና ሲመላለሱ፣ በግልፍታና በስጋት ስሜት፣ ወደ ክፉ ንግግርና ወደ ትንቅንቅ ሊያመሩ ይችላሉ። በነገር ሲመላሱና ሲሰናዘሩ፣ ሁለቱም አጥፊ ሁለቱም ተጎጂ ይሆናሉ። ሁለቱም በዳይ፣ ሁለቱም ተበዳይ እየሆኑ የየራሳቸው ጉዳት ገንኖ እየታያቸው የፀብ ስሜት ውስጥ ይዘፈቃሉ።
መፍትሔውስ? በባህሪያቸው ሰላምተኛ የሆኑ ሰዎች በስህተትና በአለመግባባት ወደማይፈልጉት ፀብ እንዳይገቡ፣… ከተቻለ በእርጋታ መነጋገር ወይም ገላጋይ ዐዋቂዎችን ማማከር፣ ካልሆነ ደግሞ ወደህግ ሙያተኞችና ወደ ዳኝነት ሥርዓት መሄድ ይችላሉ፡፡
አንዱ ሌላኛውን የማጥፋት ነውጠኛ ፍላጎት እስከሌለው ድረስ፣ ትክክለኛና ሚዛናዊ ሀሳብ ሊያስማማቸው ይችላል፡፡ ካልሆነም ዳኝነት ያከባብራቸዋል፡፡ ሁለት ነውጠኛ ሰዎች እርስበርስ ለመጠፋፋት ሲዘምቱ፣ በተመሳሳይ የውይይትና የሽምግልና መንገድ ለማስታረቅ መሞከር ውጤታማ ይሆናል ብለን ካሰብን ግን፣ በከንቱ ደከምን።
 አንዱ ሌላውን ለማጥፋት የሚዘምቱ ከሆነ፣ ሌሎች ሰላምተኛ ሰዎችን ከማጥቃት አይመለሱምና ዋና ጥንቃቄያችን እንዴት አደብ ልናስይዛቸውና ልንቆጣጠራቸው እችላለን የሚል መሆን አለበት፡፡
ነውጠኞችን መቆጣጠር የማይችል አገር፣ የነውጠኞች መጫወቻ ይሆናል፡፡ ልዩነቱም እዚህ ላይ ነው፡፡ የቁጥርና የደረጃ ጉዳይ እንጂ፣
“ነውጠኞች በሁሉም አገር በሁሉም ዘመን መኖራቸው አይቀሬ ነው፡፡
ነውጠኞችን መቆጣጠር የቻሉና ያልቻሉ ሰዎች፣ ሰላምተኛ ወይም ነውጠኛ አገር ይኖራቸዋል፡፡
በሌላ አነጋገር፣… “ሰላምተኛ አገርና መንግስት” ማለት… ነውጠኞች የሌሉበት ወይም ነውጠኛ ተግባር የማይፈፀምበት አገር ማለት አይደለም፡፡ ነውጠኛ ተግባርን በአጭር ማስቆም ነውጠኞችን መቆጣጠር የተቻለበት አገር ነው ሰላምተኛ አገር።
ነውጠኛ አገርና መንግስት ማለት የአገሬው ሰዎች ነውጠኞች ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የነውጥ ተግባራትን ማስቆምና ነውጠኞችን መቆጣጠር የሚችል ሥርዓት ያልተገነባበት ወይም የፈረሰበት አገር ማለት ነው- የነውጥ አገር ማለት፡፡
አንድ ሁለት ገናና ነውጠኞችን በማስወገድ ብቻ አገሬው ሰላም አያገኝም፡፡ ተተኪ ነውጠኞች ይነሱበታል፡፡ የነውጥ ተግባራትን የሚከላከል ሀሳብ፣ ጥፋቶችን የሚያስቆም አቅም፣ ነውጠኝነትን መቆጣጠር የሚችል ስርዓት እየገነባ ሲጓዝ ነው የህሊናም የኑሮም ሰላም የሚያገኘው፡፡
እነዚህን ስህተቶች አጥርተን፣ ሐሳባችንን አስተካክለን፣ የፍልስጥኤምንና የእስራኤልን ታሪክ፣ የሐማስ የሽብር ዘመቻና የእስራኤል መንግስት የአጸፋ ወታደራዊ ዘመቻዎችን መመልከት እንችላለን።
ወይስ ገና የራሳችንን መከራ መመርመር፣ የኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ጦርነትና ትርምስን በቅጡ ማስተዋልና ማገናዘብ ሳንችል የሌሎች አገራት ጦርነት ላይ ጥልቅ ትንታኔ ለማቅረብ ብንሞክር አቅማችን ይፈቅዳል? ብንችልስ ያምርብናል?
በእርግጥ፣ ከየትኛውም አገር የሚገኝ የታሪክ ትምህርት ጠቃሚ እንደሆነ አያከራክርም። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ ኢትዮጵያን የሚነካ ጉዳይ መሆኑም አይቀርም።
የዓለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ ሲቃወስ፣ ለኛም ጦሱ ይደርሰናል።
በዚያ ላይ በርካታ የኢትዮጵያ ተወላጆች የጭካኔ ጥቃት ደርሶባቸው፣ በአሳዛኝ ሁኔታ መሞታቸውንና መጎዳታቸውን ሰምተናል። በአጭሩ የእስራኤልና የፍልስጥኤም ጉዳይ እጅግ ቅርባችን ነው።
ቢሆንም ግን… እዚህ ከቤታችን ከደጃችን ብዙ ጦርነትና ብዙ ሞት፣ ብዙ ትርምስና የኑሮ ችግር አለብን።
አገራችንን በቅጡ ሳናገናዝብ  ውጭ አገራትን  ጦርነት መተንተን ይሆንልናል? ቢከብድም ያስፈልጋል። ከሆነ አይቀር ደግሞ በትክክለኛ ሐሳብና በትክክለኛ ሚዛን ነው ፋይዳ የሚኖረው።



መንግስት የተመድ ባለሥልጣን መግለጫውን እንዲያስተባብሉ ጠይቋል

በኢትዮጵያ አሁንም የዘር ማጥፋትና ተያያዥ አሰቃቂ ወንጀሎች ስጋት በከፍተኛ ሁኔታ መኖሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘር ማጥፋት መከላከል ልዩ አማካሪ ዋይረሙ ንደሪቱ ገለፁ። አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ (ICHREE) ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ የጦር ወንጀሎችና በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች መቀጠላቸውን ሰሞኑን ገልጿል።  መንግስት በበኩሉ የኮሚሽኑን መግለጫ የሀገሪቱን አሁናዊ ሁኔታ ያላገናዘበ፣ መሰረተ-ቢስ ክስ ነው ሲል አጣጥሎታል።
የመንግስታቱ ድርጅት ልዩ አማካሪ፣ አለም አቀፉን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባለሙያዎች ያወጣውን ወቅታዊ ሪፖርት ዋቢ አድርገው ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ፤ በፌደራል መንግስቱ ወታደሮችና በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ታጣቂዎች መካከል የቀጠለ ውጊያ እየተካሄደ በመሆኑ በአገሪቱ አሁንም የዘር ማጥፋትና ተያያዥ አሰቃቂ ወንጀሎች ስጋት በከፍተኛ ሁኔታ አጥልቷል ብለዋል። በትግራይ፣ አማራ፣ አፋርና ኦሮሚያ ክልሎች ስጋቱ በከፍተኛ ሁኔታ መኖሩንና የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመፈጸም አስቻይ ሁኔታዎች እንዳሉም ጠቁመዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ልዩ አማካሪዋ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ አስመልክተው ባለፈው ማክሰኞ ባወጡት መግለጫ፤ “በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ ነገሮችን በተመለከተ እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች፣ እጅጉን የሚረብሹና እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ ማቅረብ የሚፈልጉ ናቸው” ብለዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሙያዎች ቡድን ሰሞኑን ያወጣው ሪፖርት በእጅጉ እንዳሳሰባቸው የገለፁት ልዩ አማካሪዋ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ውስጥ በተጨባጭ እየተባባሱ የሚሄዱ የደህንነት ስጋቶች እና የመብት ጥሰቶች መኖራቸውንና ለእነዚህ ከባድ ወንጀሎች  ሊያጋልጡ  የሚችሉ ሁሉም ሁኔታዎች እየታዩ መሆናቸውን መግለፁን ተናግረዋል። ቀጣይነት ያላቸው ከባድ የመብት ጥሰቶች መጠነ ሰፊ ጥቃቶች፣ አለመረጋጋት እና ተጠያቂነት አለመኖር በአገሪቱ የሚታዩ ተጠባቂ ስጋቶች መሆናቸውንም ጨምረው ገልፀዋል።
በኮሚሽኑ የተጠቀሱትና በአገሪቱ  እየቀጠሉ ያሉት አስጊ ሁኔታዎች በእጅጉ አሳስቦናል ያሉት ልዩ አማካሪዋ፤ ግጭትን ለማስቆም ከአንድ ዓመት በፊት የተደረሰው ስምምነት በአብዛኛው ውጤት እያስገኘ አለመሆኑን ገልፀዋል። አሁንም በአገሪቱ ደም አፍሳሽ ግጭቶች፣ የጭፍጨፋ ክሶች፣ የጦር ወንጀሎችና በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች እየተፈፀሙ መሆናቸውንም አመልክተዋል። በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ እየታዩ ያሉት የመብት ጥሰቶች እንዲቆሙና ለተፈጸሙትም ወንጀሎች ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ ተመሳሳይ ተግባራት እንዳይፈፀሙ ለማድረግ ያግዛል ያሉት ልዩ አማካሪዋ፤ አገሪቱ ከዚህ አንፃር እርምጃ መውሰድ እንደሚኖርባትና በአገሪቱ እየተባባሰ ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚመለከታቸው ወገኖች በሙሉ የሚጠበቅባቸውን ተግባር በመፈጸም በአገሪቱ ሊከሰት የሚችለውን አደገኛ ሁኔታ ለማስቀረት አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ልዩ አማካሪ አሊስ ዋይሪሙን  ያወጡትን መግለጫ ተከትሎ፣ መንግስት ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ፣ ውንጀላው ሃላፊነት የጎደለው በግዴለሽነት የተሰጠና የአገሪቱን አሁናዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው ሲል አጣጥሎታል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚሁ መግለጫው፣ ልዩ አማካሪዋ ለሰጡት መግለጫ ማጣቀሻ ያደረጉትና በኢትዮጵያ ላይ ተንኳሽ አገላለፅ እንዲጠቀሙ መነሻ የሆናቸው የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ኤክስፐርች ቡድን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ያቀረበው ሪፖርት መሆኑን አመልክቶ ሪፖርቱ በተገቢው መንገድ ያልተዘጋጀና ከእውነት የራቀ ነው ሲል ተችቶታል። የተመድ ባለሙያዎች ቡድን በተገቢው መንገድ በቦታዎቹ ላይ በመገኘት ምርመራ ሳያደርግና በርቀት ባገናኛቸውና ተአማኒነት በሌላቸው መረጃዎች ላይ ተንተርሶ ያወጣውን ሃላፊነት የጎደለው ሪፖርት ዋቢ አድርገው የመንግስታቱ ድርጅት ልዩ አማካሪ የሰጡት መግለጫ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም ብሏል። ከአንድ አመት በፊት በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት በአመዛኙ አልተሳካም ማለት ከሚቻልበት ደረጃ ላይ ደርሷል በማለት በልዩ አማካሪዋ የተሰጠው መግለጫ፣ ፍፁም ሀሰት ነው ያለው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት መግለጫ፤ ስምምነቱ በሰሜን ኢትዮጵያ የመሳሪያ ድምጽ እንዳይሰማ አድርጓል ብሏል። የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚሁ መግለጫውም፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ አማካሪዋ የሰጡትንና የተሳሳተ ነው ያለውን መግለጫ እንዲያስተባብሉ ጠይቋል።

•  በሃማስ ጥቃት  የተገደሉ እስራኤላውያን ቁጥር 1300 የደረሰ ሲሆን፤ ከ3ሺ 300 በላይ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡

•  በእስራኤል የአየር ድብደባ የሞቱ ፍልስጤማውያን ቁጥር 1ሺ 500 የደረሰ ሲሆን፤ 5ሺ 600 ሰዎች ቆስለዋል፡፡


•  በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት 27 አሜሪካውያን ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ በሃማስ ከታገቱት ከ150 በላይ ሰዎች ውስጥ አሜሪካውያን ይገኙበታል፡፡

•  የእስራኤል የጦር ም/ቤት ሃማስን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ክፉኛ ዝቷል፡፡


•  “በአጭርና ግልፅ ቋንቋ አሜሪካ የእስራኤል አጋር ናት” - የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር

•  ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ወደ እስራኤል የላከችው አሜሪካ፤ አውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከቧንም ወደ እስራኤል አስጠግታለች፡፡


•  “አሜሪካ በፍልስጤም ህዝብ ላይ በሚደረገው ወረራ እየተሳተፈች ነው” - ሃማስ

•  በጋዛ የምግብ፣ ውሃ፣ መድሃኒትና ነዳጅ አቅርቦት ተቋርጧል፡፡


•  በእስራኤል የአየር ድበደባ 4238ሺ ፍልስጤማውያን ከጋዛ ተፈናቅለዋል - የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ

•  እስራኤል በምድር ውጊያ ለማካሄድ 300ሺ ወታደሮቿን ወደ ጋዛ ድንበር አስጠግታለች፡፡
•  ሃማስ ጥቃቱን ለመመከት ዝግጁ ነኝ ብሏል፡፡

•  “የሃማስ ብቸኛው አጀንዳ እስራኤልን ማጥፋትና አይሁዶችን መግደል ነው” -አንቶኒ ብሊንከን


•  “እያንዳንዱ የሃማስ አባል በሞት ጥላ ሥር ነው” - የእስራኤል ጠ/ ሚኒስትር

•  ሃማስ ጥቃት ከመፈጸሙ ከቀናት በፊት ግብፅ እስራኤልን አስጠንቅቃ ነበር - አሜሪካ


•  እስራኤል 1.1 ሚ.  ፍልስጤማውያን  በ24 ሰዓት ውስጥ ከጋዛ እንዲወጡ አስጠነቀቀች፡፡

•  የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት፣ በእስራኤልና ሃማስ ግጭት ላይ ለመምከር ዛሬ የዝግ ስብሰባ ያደርጋል፡፡

Page 11 of 676