Administrator
ዓለም አቀፍ ደረጃ ውስጥ የተካተተው 24ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ
ከ21 የተለያዩ አገራት ከ500 በላይ እንግዶች ይመጣሉ
ለመጀመሪያ ጊዜ 50 ሺ ተሳታፊዎች መካፈላቸው ልዩ ያደርገዋል
ለዝግጅቱ ስኬት ከ2ሺ በላይ ሰዎች በትጋት ይሰራሉ
11 ሃኪሞችን ጨምሮ ከ200 በላይ የጤና ባለሙያዎች ይሰማራሉ
24ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፤ ዛሬና ነገ በህፃናትና በዋናው የጎዳና ሩጫ በሚካሄዱ ውድድሮች 54 ሺ ተሳታፊዎች እንደሚካፈሉበት ይጠበቃል። የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዳግማዊት አማረ ከስፖርት አድማስ ጋር ባደረገችው ልዩ ቃለምልልስ እንደተናገረችው፤ ዘንድሮ የጎዳናው ሩጫ ዓለም አቀፍ ደረጃ ውስጥ ገብቶ መካሄዱ ልዩና የሚያኮራ ያደርገዋል።
ከ24ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር ተያይዞ ለበጎ አድራጎት በሚከናወነው የገቢ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ በታቀደው መሠረት 3 ሚሊየን ብር መገኘቱን ለስፖርት አድማስ የገለፀችው ዳይሬክተሯ፤ ከውድድሩ በፊት የፈለግነውን የበጎ አድራጎት ገቢ ማሳካታችን አስደስቶናል ብላለች።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩን በድምቀት ለማክበር ማቀዱን የገለጸችው ዳግማዊት፤ ዘንድሮ ከዓለም አቀፍ የጎዳና ሩጫዎች መመደቡ፤ በመሮጫ ጎዳና ልኬት፣ በውድድር አዘገጃጀት ሂደትና ጥረት እንዲሁም በተሳታፊዎች መስተንግዶ የላቀ አፈፃፀም ማስመዝገቡን በመቀጠል ለተሻለ ደረጃ የሚነሳሳበት እንደሚሆን ጠቁማለች።
በዓለም አቀፍ ጎዳና ሩጫዎች ከመደበኛ ወደ የላቀ ደረጃ መሸጋገር
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ የሚያዘጋጀው የ10 ኪ.ሜ. ሩጫ በዓለም አትሌቲክስ ማህበር ዓለም አቀፍ የውድድር ደረጃዎች የተካተተው ከወር በፊት ነበር። World Athletics ለ24ኛ ጊዜ የሚካሄደው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፤ Label Road Race ከተሰጣቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተርታ ዕውቅና ማግኘቱን አስታውቋል።
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር የጎዳና ውድድሮችን በመመዘን በየአመቱ በሚያወጣቸው ደረጃዎች የመሮጫ ኮርስ ልኬት ፣ የውድድር ሰዓት ምዝገባ እና የታዋቂ አትሌቶች ተሳትፎን ከግምት ውስጥ ያስገባል።
ዳይሬክተሯ ዳግማዊት አማረ እንደገለፀችው፤ የዘንድሮውን ሩጫ ልዩ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች የመጀመርያው 50 ሺ ተሳታፊዎች መኖራቸው ነው። ይህም የ10 ኪ ሜ የጎዳና ላይ ሩጫውን በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ተመሣሣይ ውድድሮች ተርታ ያሰልፈዋል። በተጨማሪ የተሳታፊውን ብዛት ምክንያት በማድረግ ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ከዚህ በፊት የተሞከረው በተለያዮ ቦታዎች የመነሻ ማዕበል ተግባራዊ እንደሚሆንም ጠቁማለች።
“ በዓለም አትሌቲክስ ማህበር የጎዳና ሩጫዎች ደረጃ ውስጥ መግባታችን ዓለምአቀፍ እውቅናችንን ያሰፋዋል፤ አትሌቶች ባስመዘገቡት ውጤት ለተሻለ ውድድር የሚታጩበትን እድል ይጨምረዋል።” ስትል ለስፖርት አድማስ የተናገረችው ዳግማዊት፤ “አሁን ከደረስንበት ደረጃ በኋላ ቀጣይ የሚሆነው Elite label road race ምድብ ላይ መድረስ ሲሆን፤ ዋናው መስፈርቱ የሽልማት ገንዘብ ከፍተኛነት በመሆኑ ወደፊት የምናየው ነው” ብላለች
በስፖርት ቱሪዝም የተጠናከረው አቅጣጫ
በዓለም አትሌቲክስ ማህበር የተሰጠው ደረጃ በተለይ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከቱሪዝም ጋር ያለውን ትስስር እንደሚያጠናክረውም ዳግማዊት ታስረዳለች።” በዋና ውድድሩ ላይ የሚሳተፉ የኡጋንዳና የኬንያ አትሌቶችን ጨምሮ ከ21 የተለያዩ አገራት ከ500 በላይ የታላቁ ሩጫ እንግዶች አዲስ አበባ ይገባሉ። ከ250 በላይ ተሣታፊዎች በታላቁ ሩጫ በኩል የመጡ ሲሆን፤ ሁሉንም በኃላፊነት ተቀብለን እናስተናግዳቸዋለን። የሚመጡትን ስፖርተኛ ቱሪስቶችን ውድድሩ ከመካሄዱ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ተቀበለናል። ብዙዎች የማያውቁት ከሩጫው ውድድር ባሻገር ትልቁ ስራችን እኛን ብለው የመጡትን በተሟላ ሁኔታ ማስተናገድ ነው። በመስተንግዷችን የኢትዮጵያን በጎነት የምናሳይበት ስለሆነ የሚያኮራን ነው። ከውድድሩ በፊት ከምናከናውናቸው ተግባራት አንዱና ዋናው ለታላቁ ሩጫ እንግዶች የተመቸ የኢትዮጵያ ቆይታ በመጨረሻው ሳምንት ያለእረፍት መሥራታችን መሆኑ መታወቅ አለበት” ብላለች።
ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እንግዶች በተያዘ ፓኬጅ ቅዳሜ ጠዋት በእንጦጦ ተራራ ላይ ልምምድ ፤ ማታ ላይ የፓስታ ፓርቲ አድርገው ውድድሩን እሁድ ላይ ይሮጣሉ። ብዙዎቹ ከውጭ አገር የሚመጡት እንግዶች፣ ከተለያዩ የአስጎብኚ ድርጅቶች ጋር በመሆን ከውድድሩ ባሻገር በየራሳቸው የጉብኝት ፕሮግራሞች ይንቀሳቀሳሉ።
ዳግማዊት አማረ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀችው፤ ከውጭ አገራት የሚመጡ የታላቁ ሩጫ እንግዶች፣ ከውድድሩ በተያያዘ ኢትዮጵያ ውስጥ በአማካይ እስከ አምስት ቀናት የሚቆዩ ሲሆን፤ ይህም የስፖርት ቱሪዝሙን የሚያቀላጥፍ ይሆናል።
የዓለም ማራቶን ሪከርድ ባለቤት ትገኛለች
“በሴቶች የዓለም ማራቶን ሪከርድን የያዘችው ኬንያዊቷ ሩት ቼፕቲግ ከልዩ የክብር እንግዶች መካከል ትገኝበታለች። ብዙዎቹ የኬንያ አትሌቶች ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ፍቅር አላቸው። ሩትም በታላቁ ሩጫ ለመሳተፍ በነበራት ፍላጎት ወደ ኢትዮጵያ መጥታለች። እሷ ብቻ ሳትሆን ብዙ እንግዶች ከኬንያ በየዓመቱ ይመጣሉ። በነገራችን ላይ እኛ ከኢትዮጵያ ወጥተን እየሰራን በመሆኑ በስፖርት ቱሪዝም የምናደርገውን እንቅስቃሴ የሚያጠናክር ነው። ሩት ቼፕቲግን ለክብር እንግድነት ስንጋብዛት የዓለም ሪከርድ አላስመዘገበችም ነበር። ከጋበዝናት በኋላ የዓለም ሪከርድን መስበሯ በውድድራችን ላይ ስትገኝ ለሁላችንም ልዩ ክብር የሚሰጥ ይሆናል። የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ለኢትዮጵያ በጣም ፍቅር አላቸው። በዓለም አቀፍ ውድድሮች እንደምንፎካከረው አይደለም።” ብላለች ዳግማዊት አማረ።
ለቢሊዮኖች ተደራሽ ይሆናል
ዘንድሮ ኢከር ስፖርት የተባለ ዓለም አቀፍ የብሮድካስት ማሰራጫ ኩባንያ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሰራጨት ፈቃድ አግኝቷል። ዳግማዊት እንደምትገልፀው፤ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን በተመለከተ የሚሰሩ ዜናዎች ፤ መረጃዎች፤ የፎቶና የቪድዮ ምስሎች በኢከር ስፖርት አማካኝነት በዓለም ዙርያ ለ1 ቢሊዮን ተከታዮች የሚደርስ ይሆናል።
ከ2ሺ በላይ ሰዎች በትጋት ይሰራሉ
በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪ ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ አጠቃላይ ዝግጅት፤ የተሳታፊዎች መስተንግዶ፥ የውድድር ሂደትና አፈፃፀም ላይ ከ2 ሺ በላይ ሰዎች በተለያዩ ሃላፊነቶች እንደሚሰሩ ዳይሬክተሯ ዳግማዊት አማረ ተናግራለች። “በመሮጫ ጎዳናው ላይ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰማሩ አሉ። ዘንድሮ በህክምና አገልግሎት ላይ ለሚከናወኑ ተግባራት ልዩ ትኩረት የተሰጠ ሲሆን፤ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሜዲካል ዲያሬክተር በመመደብ ለተሳታፊዎች ደሕንነት ይሰራል። 11 ሀኪሞችን ጨምሮ ከ200 በላይ የጤና ባለሙያዎች በ500 ሜትር ልዩነት በሚቆሙት 20 ጣቢያዎች በተጠንቀቅ ሆነው ለተሳታፊዎች ድጋፍ ይሰጣሉ” ብላለች።
ወደ ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሽግግር - በዜጋ ተኮር ጥበብ
ከተማችን አዲስ አበባ የጀመረችውን የመታደስ ጉዞ አጠናክራ ቀጥላለች፡፡ በአጭር ጊዜ በፍጥነትና በጥራት ከአለም አቻ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ እየሆነች እንዳለ የብዙዎች ምስክርነት ነው፡፡ ከተማዋ በርካታ የተመሰቃቀሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ስታስተናግድ ቆይታለች፡፡ የለውጥ ፍላጎት ጩኸቶች በማህበረሰቡ ሲሰሙም ነበር፡፡ ሆኖም የህብረተሰቡን መሰረታዊ ጥያቄ መነሻ በማድረግ ከተማዋ እምርታዊ በሆነ መልኩ በለውጥ ግስጋሴ ላይ በመሆኗ የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ሌት ተቀን እየተጋች ትገኛለች፡፡
በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ስራ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የዘመናዊነት ከተማ መስፈርትን በሚያሟላ ደረጃ የተዘረጉ መሰረተ ልማቶች እየተጠናቀቁ ህዝቡን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት በተሰጠ አቅጣጫ መሰረት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በክብርት አዳነች አበቤ በጋዜጣዊ መግለጫ በይፋ ያስጀመሩት የሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ጅማሮ፣ አሁን ያለበት ደረጃና በቀጣይ ለነዋሪው የሚሰጠው ጠቀሜታ ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች ገልጸውታል፡፡ በአዲስ አበባ ባለፉት ስርአቶች የከተማ ማደስ ስራዎች በጥቂቱ ተከናውነው ነበር፡፡ የአሁኑ የኮሪደር ልማት ከበፊቶቹ ምን ለየት ያደርገዋል? ለሚለው መሰረታዊ ጥያቂ አቶ ጥላሁን ወርቁ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ፅ/ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ፡- ምን አሉ?
“አዲስ አበባ ከተማ የአለም አቀፍ ተቋማት፤ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ፤ የሃገራችን ርእሰ ከተማ እንዲሁም ለነዋሪዎቿም ደግሞ የሚመጥን አገልግሎት መስጠት ያለባት ከተማ ነች፡፡ እነዚህ ሁሉ ሲደመሩ የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባን ስሟንና ግብሯን የሚመጥን እንዲሆን ያስቻለ ነዉ፡፡
ካለፉት መንግስታት ጀምሮ ጣሊያን በ1928 ኢትዮጵያን ለመውረር ለሁለተኛ ጊዜ በመጣችበት ጊዜ የንጉሱን ክብረ በዓል አስመልክቶ፣ በደርግ ጊዜ የአፍሪካን ህብረት አስመልክቶ፣ በተለያዩ ጊዜ የእድሳት ሙከራዎች ተካሂደዋል፡፡ በወቅቱ እነዚህ ሁነት ተኮር እድሳቶች ነበሩ፡፡ አሁን እየተሰራ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት ሁሉን ያማከለ የከተማ ማደስ፣ የከተማ ማዘመንና የከተማ ማላቅ ስራ ልዩ የሚያደርገው ሁሉ አቀፍና ታቅዶ ለረጅም ጊዜ ከተማን ልናድስበት የሚገባ ሞዴል አድርገን እንደ ሃገር በራሳችን ጥረት ከእቅዱ ጀምሮ የክብር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሃሳብ ሆኖ የመጣ፣ በዘላቂነት ከተማችንን የምናዘምንበት ተግባር ነዉ፡፡
ነዋሪዎች ከሚያገኗቸው ፋይዳዎች ወሳኝ የሆኑ የመሰረተ ልማት ጥቅም ባሻገር በዋናነት የሰው ልጆችን ህይወት መቀየር ነው፡፡ በዚህ ለውጥ የመንግስት ዋናው የትኩረት አጀንዳ ሰው ተኮር መሆን ነው፡፡ በተለይ በዚህ የኮሪደር ልማት ህንፃዎች የሚታደሱት እንዴት ነው፣ በርካታ ሰዎች በልማቱ ምክንያት እየተነሱ ነው እንዴት እየተስተናገዱ ነው የሚለው ዋናዉ ጉዳይ ነዉ፡፡
እንደ አዲስ አበባ የስኬታችንም ሚስጥር ተብሎ የሚታሰበው እነዚህን በጣም በተጎሳቆሉ ለአደጋዎች የተጋለጡ የሰዉን ልጅ የማይመጥኑ የመኖሪያ ቤቶች የነበሩትን ዜጎች አንስቶ ለኑሮ አመቺ በሆኑ ቤቶች ውስጥ እንዲኖሩ ማስቻል ነው፡፡
ክቡር ጠ/ሚሩ ከመጀመሪያዉ ኦረንቴሽን ቀን ጀምሮ “ማንም ዜጋ በዚህ ልማት ምክንያት መጎዳት የለበትም፤አንድም እናት በዚህ ማልቀስ የለባትም” የሚል አቅጣጫ አስቀምጠዋል፤ በማለት ዜጎች ሳይጉላሉ ከነበረባቸው ያልተመቸ የአኗኗር ዘይቤ ተላቀው ወደተሻለ ህይወት መሸጋገራቸውን የሚያብራሩት አቶ ጥላሁን አክለውም፡-
“በሁለተኛዉ ኮሪደር የተነሳው የወንዝ ዳርቻ ልማት ነው፡፡ ይህም በአዲስ አበባ ከተማ ወደ 607 ኪሎ.ሜ ኔትዎርክ የሚሸፍን ነዉ፡፡ ቦታው ባክኖ፤የቆሻሻ መጣያ ሆኖ ለከተማ ማስዋብ ለአረንጓዴ ምንጭ፤ለዓሳ ማስገሪያ ሊሆኑ የሚችሉ ከተማን ማስዋብ የሚለውን አባባል በጣሰ መልኩ ባለፉት ዘመናት ወንዞቻችን በአካባቢዉ ያሉትን ሰዎች መጥፎ ሽታ የሚበክል የነበረበት ነዉ፡፡ ብዙ ሰዎች የሚቸገሩበትና ለህመም መንስዔ የሚሆኑበት ሁኔታ ነበር፡፤
ታዲያ ይሄን ታሪክ ለመቀየር ከእንጦጦ ፒኮክ የሚዘልቀዉ አንደኛዉ የኮሪደሩ አካል ሆኖ የወንዝ ዳርቻዉ እንዲለማ እንዲሁም የቀበናና የግንፍሌ ወንዝም ተይዞ እንዲለማ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በኮሪደር ልማቱ ላይ የወንዞች ዳርቻ ልማት ሲጨመር በአጠቃላይ የከተማችንን ተወዳዳሪነት እንደ ሃገር የጀመርናቸዉን እነዚህን የልማት ዶቶች ያልናቸዉ የፓርኮች ልማት እርስ በእርስ አገናኝቶ የከተማችንን ከፍታ የሚያልቅ ይሆናል፡፡ መንግስታችን ዜጋ ተኮር መርህን ስለሚከተል በመጀመሪያ ዙር ብቻ ከ4300 በላይ በማይመች ሁኔታ ሲኖሩ ለነበሩ ዜጎች ባለሃብቱን አስተባብረን ባስገነባናቸዉ ቤቶች እንዲገቡ አድርገናል፤በዚህም የህይወት ለውጥ አምጥተናል፡፡ በርካታ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የስራ እድል ተፈጥሮላቸዉ በሚሊዮኖች ገንዘብ አግኝተዉበታል፡፡ የከተማችን ኢንዱስትሪዎች ተነቃቅተዋል፤በተለይ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዉ በከፍተኛ ሁኔታ ተነቃቅቷል፡፡ በፍጥነት ልምድ የተወሰደበት ነዉ፤ስለዚህ ስኬት የተመዘገበበት ሰባት ሀያ አራት በሚል የስራ ባህል የተተካበት ለቀጣይ ክልሎች እንደሃገርም ልምድና ባህል አድርገን እንድንቀጥልበት የሚያስችለን ነዉ፡፡ በመጀመሪያው ዙር ከ50 ሺህ በላይ የጊዜያዊና ቋሚ የስራ እድል የተፈጠረበት ተጨማሪ ስኬት ነው፡፡
በተጨማሪም በኮሪደር ልማት ወቅት ከተለያዩ አከባቢዎች የሚነሱ አሉና በተጨባጭ በሚኖሩበት አካባቢ የመሰረቱት ማህበራዊ ህይወት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ሲነሱ ቀድሞ የነበራቸው ማህበራዊ ህይወት ሊናድ ይችላል፣ ይህንን ከማስጠበቅ አንፃር የዜጎች አብሮነትና ማህበራዊ አንድነት መስተጋብርን ከመጠበቅ አንፃር ምን ያህል እየተሰራ ነው ? ለሚለው ጥያቄ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ስራ አስከያጅ ኢንጅነር ወንደሰን ሴታ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት 8 ቦታዎችን ያካተተ ሲሆን፤ ሁለቱ የወንዝ ዳርቻ ቦታዎች ናቸው፡፡ በተጀመረበት ፍጥነት በሰባት ሃያ አራት የስራ ባህል እየተከናወነ ሲሆን፤ አንዳንድ ከልማት ተነሺዎች ጋር የሚሰነዘሩ ሀሳቦች በመሰረታዊነት መመለስ ስለሚገባቸው ኢንጅነር ወንድሙ ኬታ የሚሉት አለ፡- “የሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ከተጀመረ በኋላ ተነሺዎችን በምናስተናግድበት ወቅት ከአንድ አካባቢ የተነሱ ሰዎችን ወደ አንድ አካባቢ እንዲሄዱ አድርገናል፡፡ የነበራቸውም ማህበራዊ መስተጋብር ሳይጠፋ የተሻለ መሰረተ ልማት ወደ ተሟላበት ንጹህና ፅዱ ወደ ሆነ ቦታ ነው እንዲሄዱ የተደረገው፡፡ በዚህ ሂደት በዋናነት ታሳቢ የተደረገው አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞችና የተለያዩ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ካሉ ቅድሚያ በመስጠት ነው፡፡ በድልድሉ ሂደት የተለያየ አድልኦ እንዳይኖር በእጣ የሚስተናገዱበትና የሚደመጡበት ስራ ተሰርቷል፡፡ ይህ በመሆኑ ምክንያት ነው የአዲስ አበባ ነዋሪ በልማቱ ከጎናችን መቆሙን ያሳየን፡፡
ህዝቡ ካሳ ሳይገመትለት መተማመኛ ደብዳቤ ሳይሰጠው የግል አጥሩን አስጠግቷል፣ ቤቱን አፍርሷል ይህ የሆነበት ምክንያት ወደ ህዝብ ቀረብ ብለን ያለውን ችግር ለመረዳት በመጣራችን ነው፤ በቀጣይም በምንሰራቸው ስራዎች ከህዝቡ ጋር አብረን የምንሰራ ይሆናል፡፡
በመጀመሪያ ዙር የነበሩ ክፍተቶችን ትምህርት ወስደን በ2ኛው ዙር የኮሪደር ልማት በመሙላት የገባንበትን በበቂ ዝግጅት በሚባል መልኩ መስራት እንችላለን፡፡” በማለት ገልጸውታል፡፡
በመነሻችን እንደጠቀስነው ይህ የኮሪደር ልማት ቀጣይነት ያለው፣ የበርካታ ዜጎችን ህይወት በመለወጥ ከተማዋን ዘመናዊ ከተባሉ አቻ ከተሞች ተርታ የሚያሰልፍ መሆኑንም በርካቶች ተስማምተውበታል፤መስክረውለታልም፡፡
“ሩብ ዓመቱ ከሕዝብ ጋር ተቀራርበን የሠራንበት፣ የሥራ ባህልን መለወጥ የተቻለበትም ነው“
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈፃፀም ግምገማን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ በሩብ ዓመቱ የተከናወኑ ሥራዎች ወጪ ቆጣቢ፣ ጥራት ያላቸውና ባጠረ ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ትርጉም ያላቸው ሥራዎች መከናወናቸውንም ተናግረዋል፡፡
“ሩብ ዓመቱ ከሕዝብ ጋር ተቀራርበን የሠራንበት፣ የአመራር ቅንጅት የታየበትና የሥራ ባህልን መለወጥ የተቻለበትም ነው“ ብለዋል።
የኮሪደር ልማትና ከተማዋን መልሶ የማደስ ሥራዎቻችን ውጤታማ ሆነዋል ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ በኮሪደር ልማቱ ለኑሮ ከማይመች ጎስቋላ አካባቢ ያነሣናቸው ነዋሪዎቻችንን ለኑሮ ምቹ የሆነ ንፁህ የመኖሪያ ቤትና አካባቢ እንዲያገኙ ማድረግ ችለናል ብለዋል፡፡
የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የፕሮጀክቶች አፈፃፀም የተሻለ እንደነበርም ገልጸዋል፣ ሁሉንም ሥራ በማስተሳሰር መምራትና ለውጤት ማብቃት መቻል አንዱ ጥንካሬ መሆኑን በመጥቀስ፡፡
“ሌብነትና ብልሹ አሠራር ያልተሻገርናቸው የቤት ሥራዎቻችን ቢሆኑም፣ ነዋሪው የሚሰጠውን ጥቆማና አስተያየት መሠረት በማድረግ የተሠሩ ሥራዎች ፍሬ ማፍራት ጀምረዋል” ብለዋል፡፡
አዲስ አበባን ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል ለማድረግና የሀገራችንን ገፅታ ለመገንባት እመርታ የታየበት ሥራ መከናወኑንም ነው የገለጹት፡፡
“አዲስ አበባን የቱሪስት መዳረሻ፣ ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል ለማድረግና የሀገራችንን ገፅታ ለመገንባት የሰራናቸው የኮሪደር ልማትና ከተማዋን መልሶ የማደስ ሥራዎቻችን ውጤታማ ሆነዋል“ ያሉት ከንቲባዋ፤ “ከተማዋ በሩብ ዓመቱ ብቻ 20 የተለያዩ አህጉርና ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶችን በብቃት ማስተናገድ ችላለች” ብለዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ በመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ የተቋማት ተቀናጅቶ መሥራት ለውጥ የታየበት መሆኑን በመጠቆምም፤ በዚህ ዘርፍ አንዱ የሠራውን ሌላው የሚያፈርስበት ሁኔታ ቀርቶ በመናበብ መሰራቱን ገልጸዋል።
የበጎ ፈቃድ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉንና በርካቶች ተጠቃሚ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡ ለአብነትም ሲጠቅሱ፤ ከ2 ሺ 780 በላይ ቤቶች በበጎ ፈቃድ መሰራታቸውንና ሕዝብና ባለሃብቱን በማስተባበር ከ5 ቢሊዮን በላይ ብር ለዚሁ ሥራ መዋሉን ተናግረዋል፡፡
ቤቶችን በማስተዳደር፣ በማስተላለፍ እንዲሁም በመንገድ ግንባታ ጥሩ ሥራ መከናወኑን ያወሱት ከንቲባዋ፤ በተለይም በሩብ ዓመቱ ከ27 ኪሎ ሜትር በላይ በራስ ኃይል የተሠራ ሲሆን፣ ከ221 ኪሎ ሜትር በላይ መንገዶች ጥገና መካሄዱን ጠቁመዋል፡፡
የስማርት ከተማ ግንባታ ሥራዎች ስኬት የተገኘባቸው መሆናቸውን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፤ በመሬት አስተዳደርና ልማት ቢሮ በኅብረት ሥራ ኮሚሽን፣ በሲቪል ምዝገባ እና የዜግነት አገልግሎት መስኮች የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ፍሬ ማፍራት መጀመራቸውን አመልክተዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ የከተማ አስተዳደሩ አመራር የአስተሳሰብና የተግባር አንድነትን ፈጥሮ ሥራዎችን የመራበት፣ የአመራር ዕድገትና መረጋጋት የታየበት መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡
ከሩብ ዓመቱ ውጤታማ ሥራዎች በመነሣትም ችግሮችን በዘላቂነት ለማረም የሚያስችል የአመራር ቁመና ለመፍጠር፣ ግልፅነትን ለመጨመርና ነዋሪውን በማሳተፍ ለመሥራት የሚያስችል አቅጣጫም መቀመጡን አመልክተዋል፡፡
የተቋም ግንባታ፣ የሰው ተኮር ሥራዎችን ማጠናከር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነትን መቀነስ፣ የገቢ አሰባሰብን ማሻሻል፣ የንግድ ሥርዓቱን ማጠናከር፣ ለነዋሪዎቿ የተመቸች ከተማ መገንባት እንዲሁም የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በመጨረስ ወደ አገልግሎት ማስገባት እና የ2ኛ ዙር ኮሪደር ሥራን በጥራትና በፍጥነት ማጠናቀቅ በቀጣይ በልዩ ትኩረት የሚሠሩ ሥራዎች መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አስገንዝበዋል።
በማጠቃለያቸውም፤ “አገልግሎት አሰጣጣችንን ይበልጥ ቀልጣፋና ከሌብነትና ብልሹ አሠራር የፀዳ በማድረግ፣ በትጋትና በታማኝነት በማሳተፍ፣ መሥራታችንን አሁንም አጠናክረን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡
ከ7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በወባ በሽታ ተይዘዋል
የዓለም የጤና ድርጅት በኢትዮጵያ ከ7 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በወባ በሽታ መያዛቸውን ይፋ አድርጓል። ድርጅቱ አያይዞም፣ ካለፉት ሰባት ዓመታት አንጻር፣ የዘንድሮው ዓመት በበሽታው ስርጭትም ሆነ በሞት መጠን እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ተቋሙ በወባ በሽታ ስርጭት ዙሪያ ባወጣው ሰፊ ሪፖርት እንዳመለከተው፣ ከታሕሳስ 22 ቀን 2016 እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2017 ድረስ 1 ሺሕ 157 ዜጎች ሕይወታቸው አልፏል። በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሕብረተሰብ ጤና ተግዳሮት የሆነው የወባ በሽታ፣ 75 በመቶ በሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች ስርጭቱ በእጅጉ እየተስፋፋ እንደሚገኝም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
“በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ከሚኖሩ ዜጎች መካከል፣ 69 በመቶው ያህሉ ለበሽታው ተጋላጭ ሲሆኑ፣ 20 በመቶዎቹ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ለሞት እየተዳረጉ ነው” ብሏል። ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው ይህ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት፤ እ.ኤ.አ. በ2024 ከተመዘገቡት ኬዞች 81 በመቶ እና 89 በመቶ የሚሆነውን የወባ በሽታ ሞት የሚይዙት አራት ክልሎች መሆናቸውን ያመለከተ ሲሆን፤ እነሱም ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ምዕራብና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ናቸው፡፡
ድርጅቱ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በአጋርነት ከመስራትም ባሻገር፣አስፈላጊ ድጋፎችን እየሰጠ እንደሚገኝ በዚሁ ሪፖርቱ ላይ አስታውቋል።
ሀጢያት ሲደጋገም ፅድቅ ይመስላል
አንድ የአይሁዶች ተረት እንዲህ ይላል፡፡
አንድ በጣም ኃይለኛ ውሸታም ነበር - ስመ ጥር ዋሾ እንዲሉ፡፡ የሃይማኖት መጽሀፍ ባያሌው ያነብባል፡፡ አንድ ቀን እንደተለመደው የፀሎት መፅሐፉን ይዞ በተመስጦ እያነበበ ሳለ፣ ከውጪ የብዙ ሰዎች የጩኸት ድምፅ ይሰማል፡፡ ወደ መስኮቱ ሄዶ ሲመለከት የሚጮሁት ትናንሽ የሰፈር ልጆች ናቸው፡፡ “እነዚህ የሰፈር ልጆች ደሞ ሌላ ተንኮል ሊሰሩ ነው! ቆይ እሰራላቸዋለሁ!” ይልና እንዲህ አላቸው፡፡
“ስሙ ልጆች፤ ወደ - ፀሎት ምኩራቡ ሂዱና እዩ፡፡ እዚያ የባህር ሰይጣን ቆሞ ታያላችሁ፡፡ ምን ዓይነት ግዙፍ ሰይጣን መሰላችሁ? 5 እግር፣ 3 ዓይኖችና እንደ ፍየል ዓይነት ጢም ያለው ነው፡፡ ደሞ አረንጓዴ ቀለም ያለው ነው!”
ልጆቹ የተባለውን ጉደኛ ፍጡር ለማየት ጓጉና እየበረሩ ሄዱ፡፡ ውሸታሙም ሰው ወደ መጽሐፉ ተመለሰ፡፡ በነዚህ ደቃቃ ልጆች እንዴት እንደቀለደባቸው እያሰበ በተንዠረገገው ረዥም ጢሙ ውስጥ ሳቀ፤
ጥቂት ቆይቶ ግን መዓት አይሁዶች ወደሱ ደጃፍ እየጮሁ ሲያልፉ ሰማና ወደ መስኮቱ ሄዶ አየ፡፡ አንገቱን ብቅ አድርጎም፤
“ወዴት እየሄዳችሁ ነው?” ብሎ ጠየቀ፡፡
“ወደ ፀሎቱ- ምኩራብ!” አሉና መለሱ፡፡
“እዚያ ምን ፍለጋ ትሄዳላችሁ?”
“አልሰማህም ወዳጄ! አንድ የባህር ሰይጣን ወጥቷል አሉ፡፡ አምስት እግር፣ ሦስት ዐይን፣ የፍየል ጢም ያለው አረንጓዴ ፍጡር ነው!”
ዋሾው አይሁድ የሰራው ዘዴ አገር እንዳታለለ ገብቶት በደስታ እየሳቀ መፅሐፍ ማንበቡን ቀጠለ፡፡ ግን ብዙም ሳያነብ ሌላ ከፍተኛ ጩኸት ሰማ፡፡ ወጥቶ ቢያይ አገር ይተራመሳል፡፡ አንዳች መንጋ ህዝብ ወደ ምኩራቡ ይነጉዳል፡፡
“ሰማችሁ ወይ ጎበዝ? ወዴት ነው፣ ይሄ ሁሉ ህዝብ የሚተምመው?” አለና ጮሆ ጠየቀ፡፡
“ምን ዓይነት የጅል ጥያቄ ነው የምትጠይቀው! ከፀሎት ምኩራቡ ፊት ለፊት የባህር ሰይጣን ቆሞ እየታየ መሆኑን አልሰማህም? አምስት እግር፣ ሦስት ዐይኖች፣ የፍየል ጢምና አረንጓዴ ሰውነት እንዳለው ተረጋግጧል” አለው ከሰዉ አንዱ፡፡ ዋሾው አይሁድ በነገሩ በመገረም ቀና ብሎ ወደ ሰዎቹ አየ፡፡ ከሚጎርፈው ህዝብ መካከል ዋናውን የቤተ-አይሁድ ሰባኪ ቄስ አያቸው፡፡
“ኧረ የፈጣሪ ያለህ! ዋናው የአይሁድ ሃይማኖት አስተማሪም ወደዚያው እየሄዱ ነው ማለት ነው? ዋናው ቄስ አምነውበት ከሄዱማ በእርግጥም አንድ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ እሳት ካለ ጭስ አለ!”
ባርኔጣውን አጠለቀ፣ ካፖርቱን አደረገ፤ ከዘራውን ያዘና እየሮጠ ከመንጋው ጋር ተቀላቀለ፡፡
“ማን ያውቃል? ያ ያልኩት ነገር ዕውነት ሆኖ፣ የባህሩ ሰይጣን’ኮ መጥቶ ቆሞ ይሆናል!” እያለ በሆዱ፤ ጭራሽ ከህዝቡ ቀድሞ ሩጫውን ተያያዘው፡፡
* * *
እራሱ በዋሸው ውሸት ውሎ አድሮ ተተብትቦ መውጫ መሸሻ የሚያጣ ብዙ መሪ፣ ኃላፊ፣ አስተዳዳሪ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተጠሪ ወዘተ ሞልቷል፡፡ በሀሰት የፈጠረው ሰይጣን ድንገት ህዝቡን ያሳምንና ማጣፊያው ያጥረዋል፡፡ ውሸት እንደ እርግዝና በትንሿ ጀምሮ፤ በኋላ የማይሸፈንበት ደረጃ ይደርስና ፍጥጥ ብሎ የመውጣት ባህሪ አለው፡፡ ለማስወረድ እንሞክርም ቢባል የተወሳሰበ ችግር ይፈጠራል፡፡ ወይ አድጎ የማስወረጃው ጊዜ ያልፋል፡፡ ወይ አስወርዳለሁ ሲሉ የመመረዝ፣ አንዳንዴም የሞት አደጋ ሊደርስ ይችላል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ውሸቱ ከርሞ ከርሞ ሲወለድ ፈጣሪውን ጭምር ማስደንገጡ ነው፡፡ ፈጣሪው የገዛ ፈጠራውን እንደ ጣዖት እንዲያመልክ የሚገደድበት ሁኔታ ሲመጣ ግን ጉዳዩ የአገርና የህዝብ ችግር እንደሚሆን ማስተዋል ይገባል፡፡
ለህዝብ የተዋሸ ውሸት ወሎ አድሮ መጋለጡ አይቀርምና ህዝብን ያስቆጣል፡፡ ይህም አላስተማማኝና ያልተረጋጋ ሁኔታን መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ “ዲሞክራሲን አስፋፋለሁ፣ ሰላምን አሰፍናለሁ፤ የህግ የበላይነት ከመሬት በላይ ስለሆነ እሱን ማረጋገጥ ነው ዋናው፣ ’ይህን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈልነው የመሬት ትርፍና ኪራን ለማስላት አይደለም፣‘ ’የህግ የበላይነት በሌለበት ወፈፍ ያደረገው ሁሉ የመሰለውን እየሰራ ጦርነት መለኮሱ ሰላምም መደፍረሱ ፍፁም የማይቀር ነው፣‘ ሉአላዊነትን አስከብራለሁ፣ ልማትን አፋጥናለሁ፣ አቅም እገነባለሁ፣” ማለት፣ ማለት፣ ማለት፡፡…. ተስፋ፣ ተስፋ፣ ተስፋ…. በየዘመኑ በየወቅቱ ተስፋ ማቆር!! ተስፋው አልጨበጥ ካለ ተዓማኒነት ይጠፋል፡፡
ይህን ሁሉ ቃል ገብተን ተዘናግተን ከተገኘን ሁሉንም መስዋዕትነት የህይወትም፣ የማቴሪያልም ዋጋ መጠየቁ ግልጽ ነውና ከተጠባቂነት ወደተጠያቂነት ያሸጋግረናል፡፡
ውለን አድረንም ’ኃይል የሌለው ታጋይ፣ ስንቅ የሌለው ጎራሽ‘ ልንሆን እንደምንችል ይጠቁመናል፡፡ ይህን አውቀን ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሁኑኑ ማሰብ አለብን፡፡ በመሰረቱ መቼም ቢሆን መች፤ ሰላም፤ የመንቀሳቀሻችን መሽከርክሪት የሚሆነውና ለግብም የሚያበቃን በሌሎች አቅጣጫዎች ሁሉ አቅምና ኃይላችን አስተማማኝ መሆኑን ለማረጋገጥ ስንችል መሆኑን በውል መረዳት ተገቢ ነው፡፡
ስለ ሰላም መደረግ ያለበትን ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሁሉ ጥርጊያውን ማስተካከል ተገቢ የመሆኑን ያህል፤ ራሳችንን ለወረራና ለባላንጣ አመቻችተን መስጠትም ፍፁም አደጋ ውስጥ ሊጥለን እንደሚችል በጊዜ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ምነው ቢሉ “ሀይለኛ መትቶ ካልደገመ ይንጠራራል፤ ሰነፍ እንዲደገም ይለመጣል” ይሏልና፡፡
ከህዝቡ ጋር ሆኜ ስለህዝብ እሰራለሁ የሚል ወገን ሁሉ፤ የህዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ ይጠበቅበታል፡፡ የህዝብ የልብ ትርታ፣ የሀገር እስትንፋስ ነውና፣ በተለይም ለስልጣን ያበቃኝ ህዝቡ ነው የሚል፣ ባለስልጣን የመቆየት አቅሙም ያው ህዝቡ መሆኑን መገንዘብ ምርጫው ብቻ ሳይሆን ግዴታውም ነው፡፡ ምንም ዓይነት የውጪ ጫና የሀገር ህልውናን ከማጣት ጋር ሊተካከል አይገባም፡፡ የህዝብንና የሀገርን ህልውና ለመጠበቅ የምንተገብረውን ነገር በተመለከተ ያለመሸፋፈንና ያለማድበስበስ አቋምን ለይቶ መሄድ ኋላ ውዥንብር ውስጥ ከመግባት ያድናል፡፡ አበው “ወይ ታጥቀህ ተዋጋ፣ ወይ ርቀህ ሽሽ” የሚሉት ለዚህ ነው፡፡
የገዛ ውሸቱን እውነት ይሆን እንዴ? ብሎ ከህዝቡ ፊት እንደሮጠው ይሁዳ የገዛ ንግግራችንና ንድፈ - ሀሳባችን ቁራኛና ሰለባ ሆነን ተጠላልፈን መውደቅ የለብንም፡፡ ኋላ ነገር ሲከፋ፤
“…እሸሸግበት ጥግ አጣሁ”
እምፀናበት ልብ አጣሁ”
እንዳንል መጠንቀቅ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ያ ሳይሆን ቀርቶ በተደጋጋሚና አንድ ነገር እንደበቀቀን የምንለፍፍ ከሆነ፤ “ሀጢያት ሲደጋገም ፅድቅ ይመስላል” ማለት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ታዋቂው ያገራችን ገጣሚ ያለውንም አለመርሳት ነው፡-
“ትቻቸዋለሁ ይተውኝ
አልነካቸውም አይንኩኝ
ብለህ ተገልለህ ርቀህ፤
ዕውነት ይተውኛል ብለህ፣ እንዴት ተስፋ ታደርጋለህ?
…የተወጋ በቅቶት ቢተ’ኛ፣ የወጋ መች እንቅልፍ አለው
የጅምሩን ካልጨረሰው፡፡
እና በእኔ ይሁንብህ
እንቅልፍ ነው እሚያስወስድህ”
በሚኒስትሩ ንግግር ሳቢያ ኢትዮጵያ የሱዳንን አምባሳደር ለማብራሪያ ጠራች
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ አለመግባባቶች ካልተፈቱ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ሊፈጠር “ይችላል” በማለት የሰጡትን አስተያየት በመቃወም ኢትዮጵያ የሱዳንን አምባሳደር ባለፈው ረቡዕ ለማብራሪያ መጥራቷ ተነገረ።
ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ የሱፍ በቅርቡ በቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድሮች ፍሬ ሳያፈሩ ከቀሩ፣ አገራቸው ከግብጽ ጎን ልትሰለፍ እንደምትችልና የሦስቱንም የተፋሰስ አገራት የውሃ መብት የሚያረጋግጥ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ የጦርነት አማራጭ ክፍት እንደሆነ ተናግረዋል።
የሚኒስትሩ አስተያየት ያስቆጣው የኢትዮጵያ መንግስት፣ በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር ለሆኑት አል ዛይን ኢብራሂም በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጥሪ ማድረጉን፣ እንዲሁም ሚኒስትሩ የሰጡት አስተያየት ተቀባይነት እንደሌለውና ከሱዳን ጋር ያለው ጠንካራ ግንኙነት በነበረበት እንደሚቀጥል መግለጹ ተዘግቧል፡፡
የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለሱዳን ትሪቡን እንደተናገሩት፣ ምናልባትም ራሳቸው የሱፍ ንግግራቸውን ለማብራራት በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ ይጓዛሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚሁ ምንጮች፣ ኢብራሂም የሹመት ደብዳቤያቸውን በይፋ ለኢትዮጵያው ፕሬዚዳንት አለማቅረባቸውንም ጠቅሰዋል።
ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ህዳር 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው፤ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጠናከረና ስትራቴጂያዊ መሆኑን በመግለጽ፣ አስተያየቶቹን የማሕበራዊ ሚዲያ ወሬ ሲሉ አጣጥለውታል። ቃል አቀባዩ አክለውም፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጉዳይ በውይይት ለመቋጨት ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸው፣ ግድቡ ለታችኛው ተፋሰስ አገራት ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማይፈጥር አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
ግድቡ በሱዳን ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማይፈጥር ባለፉት 13 ዓመታት መታየቱን ያብራሩት ቃል አቀባዩ፣ በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የውጭ አካላት ጣልቃ መግባታቸውን ኢትዮጵያ እንደምትቃወም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
የቢዝነስ አገናኞች በታሰበው ልክ ወደ ካፒታል ገበያው እየተቀላቀሉ አይደለም ተባለ
በካፒታል ገበያ ላይ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ የሚነገርላቸው የቢዝነስ አገናኞች (ብሮከርስ) በታሰበው ልክ በፍጥነት ወደ ካፒታል ገበያው እየተቀላቀሉ አይደለም ተባለ፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ወደ ካፒታል ገበያ መምጣቱ ሌሎች ድርጅቶችንም ሊያነቃቃ እንደሚችል ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የ2024 ካፒታል ገበያ ጉባኤ፣ ከባለፈው ረቡዕ ህዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም. አንስቶ መካሄድ ጀምሯል። በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው ጉባኤው፤ “ዘላቂነት ያለው መንገድን ማበጀት” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት፣ ከአፍሪካና ከዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማት የተወጣጡ አመራሮችና ባለሞያዎች እየተሳተፉበት ይገኛሉ።
የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃና ተህክሉ፣ ጉባኤው ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ሲያከናውናቸው የቆዩ ስራዎችን ይፋ ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሯ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ አውጪዎች ለካፒታል ገበያው በእጅጉ ያስፈልጋሉ፡፡
“በሰዎች የተሳትፎ መጠን ጉባኤው የተሳካ ነበር” ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ “ይህም ጠንክረን እንድንሰራና ተወዳዳሪ የካፒታል ገበያ ለመፍጠር የሚያነሳሳን ነው” ብለዋል፡፡ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን፣ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መስሪያ ቤት መሆኑን በማውሳትም፣ በካፒታል ገበያ አገልግሎት ለሚሰጡ ሁለት ተቋማት ፈቃድ መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
ሁለቱም የኢንቨስትመንት ማማከር አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ሲሆኑ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ሰነደ መዋዕለ ንዋዩን ይፋ ሲያደርግ ድጋፍ የሰጠው “deloitte” የተሰኘው ተቋም መሆኑን ገልጸዋል። ሌሎች ተቋማትም ፈቃድ ለማግኘት ማመልከቻ ማስገባታቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ ሃና ተህክሉ፤ “በቅርብ ቀናት ውስጥ ፍትሕ ሚኒስቴር ይመዘግበዋል ብለን የምንጠብቀው ሰነደ መዋዕለ ንዋይን ለሕዝብ የማቅረብ መመሪያ ሲወጣ፣ ካፒታል ገበያን ወደ ስራ የሚያስገቡ የሕግ ማዕቀፎች ተሟልተዋል ተብሎ ይታሰባል” ብለዋል። ከ100 በላይ ገጾችን ይዟል የተባለው ይህ መመሪያ፣ ባለፈው ረቡዕ ህዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በፍትሕ ሚኒስቴር እንደጸደቀ ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ “ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ ድርጅቶች ቁጥጥር መመሪያ” የጸደቀ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ የሰነደ መዋዕለ ንዋዮች በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ካልተመዘገቡ ወይም በዓዋጁና በመመሪያው ከዚህ ምዝገባ ነጻ ካልተደረጉ በቀር በኢትዮጵያ ውስጥ ለሽያጭ መቅረብ አይችሉም ተብሏል።
ከዚህ ባሻገር፣ ማንኛውም ሰነደ መዋዕለ ነዋዮችን ለሕዝብ ማቅረብ የሚፈልግ ኩባንያ ሰነዶችን ለህዝብ ከማቅረቡ በፊት ዝርዝር መረጃዎችን ያካተተ የደንበኛ ሳቢ መግለጫ ለባለሥልጣኑ ማቅረብና ማጸደቅ እንደሚጠበቅበት ተብራርቷል። ይህንን ከማድረጉ በፊት ማስታወቂያ ማሰራትም ሆነ ከኢንቨስተሮች ጋር ግንኙነት ማድረግ አይችልም፣ በመመሪያው መሰረት።
በቀጣይ ጊዜያት በአነስተኛ የገንዘብ መጠን በርካታ ሕዝብ የሚሳተፍበትና ለአነስተኛ ድርጅቶች አመቺ ሁኔታ በሚፈጥረው ዓዋጅ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ፣ ቡድን ተዋቅሮ እንደሚሰራበትም ዋና ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲ ኤክስቼንጅ ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ሚካኤል ሃብቴ በበኩላቸው፣ የቢዝነስ አገናኞች (ብሮከርስ) በታሰበው ልክ በፍጥነት ወደ ካፒታል ገበያው እየተቀላቀሉ አለመሆኑን ተናግረዋል። ይሁንና የኢትዮ ቴሌኮም ወደ ገበያው መምጣት ሌሎችን ሊያነቃቃ እንደሚችል አመልክተዋል።
“ያለ አገናኞች የካፒታል ገበያው ሊሰራ አይችልም”ያሉት አቶ ሚካኤል፤ አገናኞቹ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች በመዘዋወር የካፒታል ገበያው ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲፈጠር የሚያስችል ስራ ወደፊት እንደሚሰሩ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
በአሙሩ ወረዳ የታሰሩ ከመቶ በላይ ሰዎች ባለፉት 7 ወራት ፍርድ ቤት አልቀረቡም ተባለ
ከሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም አንስቶ በሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ የታሰሩ ከ100 በላይ ሰዎች እስካሁን ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን የታሳሪ ቤተሰቦች ተናገሩ፡፡ በአሙሩ ወረዳ ኦቦራ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩ እነዚህ ሰዎች “ልጆቻችሁ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጋር ተቀላቅለዋል” ተብለው መታሰራቸውን የጀርመን ሬዲዮ ድምጽ (ዶቸ ቨሌ) ያነጋገራቸው የታሳሪ ቤተሰቦች አመልክተዋል፡፡
ለሰባት ወራት ያህል ያለምንም ፍርድ ታስረዋል የተባሉት ሰዎች፣ አብዛኞቹ አርሶ አደሮች መሆናቸው ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ፣ በጉዳዩ ላይ ጥቆማ እንደደረሰው አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የጅማ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ በዳሳ ለሜሳ፣ 130 ሰዎች ከጸጥታ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በአሙሩ ወረዳ ለሰባት ወራት መታሰራቸውንና ክትትል እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
አንጋፋ የሚዲያ ባለሙያዎች ዛሬ በብሔራዊ ቴአትር ይመሰገናሉ
በ1960ዎቹ እና 70ዎቹ አገራቸውን ያገለገሉ 13 የሚደርሱ ቀደምት የሚዲያ ባለሙያዎች በዛሬው ዕለት ጠዋት ከ3 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር በሚከናወን መርሐ- ግብር እንደሚመሰገኑና ዕውቅና እንደሚሰጣቸው ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን አስታውቋል፡፡
በምስጋና እና ዕውቅና መርሃ ግብሩ ላይ ይታደማሉ ተብለው የሚጠበቁት ጋዜጠኞች፡- አቶ አስፋው ኢዶሳ፣ ወይዘሮ አባይነሽ ብሩ፣አቶ ሀዲስ እንግዳ፣ አቶ ዋጋዬ በቀለ፣ወይዘሮ ሚሊየን ተረፈ፣አቶ ሀይሉ ወልደፃድቅ፣አቶ ተሾመ ብርሀኑ ከማል፣ አቶ ተክሉ ታቦር፣ አቶ ይንበርበሩ ምትኬ፣ አቶ ታዬ በላቸው ፣አቶ ግርማይ ገብረፃድቅና አቶ ኢሳያስ ሆርዶፋ ናቸው።
በዝግጅቱ ላይ እንደሚመሰገኑ ከተመረጡ በኋላ ህይወታቸው ያለፈው የሚዲያ ባለሙያ ሙሉጌታ ወልደሚካኤልም በልጆቻቸው ይወከላሉ ተብሏል፡፡
እነዚህ በዛሬው ዕለት ምስጋናና ዕውቅና የሚቸራቸው አንጋፋ የሚዲያ ሰዎች፣ ከዚህ ቀደም ተገቢውን ዕውቅና ሳያገኙ የቀሩና በሌሎች የሽልማት መርሀ ግብሮች ያልተካተቱ መሆናቸው ታውቋል፡፡ በሁሉም ተመስጋኞች የህይወት ታሪክ ላይ በቂ ጥናትና ምርምር መደረጉም ተጠቁሟል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የቀድሞ ጋዜጠኞችን የቆየ ድምፅና ቪድዮ የሚያሳይ አጭር ዘገባ የሚቀርብ ሲሆን፤ በዝግጅቱ ላይ የሙያ ማህበራት፣ የሚዲያ ኃላፊዎች ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህራንና ሌሎች እንግዶች ይታደማሉ ተብሏል፡፡
የመርሀ -ግብሩ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዕዝራ እጅጉ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም የ45 ሰዎችን ታሪክ በሲዲ፣የ20 ሰዎችን ታሪክ ደግሞ በመፅሐፍ ያሳተመ ነው። በተጨማሪም በርካታ የምስጋና መርሀ- ግብሮችን ያዘጋጀ ባለሙያ ነው።
በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ታጣቂዎች የተወገዙበት ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄ
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብና ቄለም ወለጋ፣አርሲ፣ጉጂ ዞኖችና የተለያዩ ወረዳዎች ታጣቂዎች የተወገዙበትና የሰላም ጥሪ የተላለፉባቸው ሰልፎች ባለፈው ሃሙስ መካሄዳቸው ተገለጸ፡፡ ሰልፈኞቹ በመንግሥት ኃይሎችና በአማጺው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካክል የሚካሄደው ግጭት እንዲቆም መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡ ተፋላሚ ኃይሎች ያቋረጡትን የሰላም ድርድር እንዲቀጥሉና የተኩስ አቁም በማድረግ ለሕዝቡ ሰላም እንዲሰጡም ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል።
አንዳንዶች ሰልፉ በመንግሥት አስተባባሪነት እንደተዘጋጀ ሲናገሩ፣ ሌሎች ደግሞ “መንግሥትና ታጣቂው ቡድን ሰላም እንዲያወርዱ ለመጠየቅ በኅብረተሰቡ የተዘጋጀ ነው” ብለዋል። የኦሮሚያ ክልል ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ኃይሉ አዱኛ፤ “መንግሥት ሰልፉን በማስተባበር ውስጥ እጁ የለበትም” ሲሉ ለቪኦኤ ተናግረዋል፡፡