Administrator
በአደንዛዥ ዕጽ አስከፊነት ላይ የሚያተኩር ማስተማሪያ መጽሐፍ ሊዘጋጅ ነው
ላግዛት የበጎ አድራጎት ድርጅት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰራጭ በአደንዛዥ ዕጽ አስከፊነት ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚያግዝ ማስተማሪያ መጽሐፍ ሊያዘጋጅ መሆኑን አስታውቋል። ድርጅቱ ዛሬ መስከረም 10 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ፣ ኢንተርሌግዠሪ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በሐረሪ ክልል “ትውልድን ከአደንዛዥ ዕፅ ሱስ እንታደግ” የሚል ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።
ዶክተር አንዱዓለም አባተ በአማካሪነት የሚሳተፍበት ይህ የበጎ አድራጎት ድርጅት በዚህ ፕሮጅክቱ በሐረሪ ክልል በሚገኙ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ መምህራን እና የተማሪ ወላጆች እንዲሁም ከትምህርት ቤቶች ውጪ የሚገኘውን የህብረተሰብ አካል ስለ አደንዛዥ ዕፅ ሱስ አስከፊነት ግንዛቤ መፍጠር፣ በክልሉ የሚገኙ በሱስ የተጠቁ ዜጎች የሚታከሙበት ክሊኒክ እና ከሱስ ማገገሚያ ማዕከላትን ማቋቋም፤ እንዲሁም ወጣቶች ለአደንዛዥ ዕዕ ሱስ እንዳይጋለጡ የተለያዩ የክህሎት ማዳበሪያ ስልጠናዎችን መስጠት እና የስራ ዕድሎችን ማመቻቸት ለማሳካት ያቀዳቸው ግቦች እንደሆኑ በዚሁ መግለጫ ተገልጿል።
በተጨማሪም ልምድ ባላቸው ባለሞያዎች በመታገዝ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰራጭ በአደንዛዥ ዕጽ አስከፊነት ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚያግዝ ማስተማሪያ መጽሐፍ በድርጅቱ እንደሚዘጋጅ ላግዛት የበጎአድራጎት ድርጅት መስራች ወይዘሮ ጽዮን ዓለማየሁ ተናግረዋል። በቀደሙት ጊዜያት በአደንዛዥ ዕጽ ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተዘጋጁ መጽሐፍት እንደሌሉ ያስታወሱት ወይዘሮ ጽዮን፣ ይህ የሚዘጋጀው መጽሐፍ በጉዳዩ ዙሪያ የተጻፈ ልዩ መጽሐፍ እንደሚሆን አመልክተዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ፣ ትምህርት ቢሮ፣ ሴቶች እና ህጻናት ቢሮ፣ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት፣ ከአደንዛዥ ዕጽ ሱስ የጸዳና አምራች የሆነ ብቁ ዜጋ መፍጠርን ዋና ራዕይ በማድረግ እንደሚሰራ ገልጿል። ለዚህም ስራ ዕውቁ የሐረሪ ሙዚቃ አቀንቃኝ የሆነው የኢህሳን አብዱሰላም ልጅ የሆነውን ዊሳም ኢህሳንን የክብር አምባሳደር በማድረግ ስራ አስጀምሯል።
ላግዛት የበጎ አድራጎት ድርጅት በ2014 ዓ.ም. የተቋቋመ አገር በቀል እና በቦርድ የሚመራ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው፡፡ የስሙ ትርጉም በማሕበረሰቡ ውስጥ ያለውን ዕምቅ ሃይል በመጠቀም፣ ጤነኛ እና ብቁ ትውልድን በማፍራት የኢትዮጵያን የወደፊት እድገት ማገዝ ማለት እንደሆነ በጋዜጣዊ መግለጫው ተገልጿል፡፡
የሚድያ ሰው ጌታቸው ኃይለማርያም ሊዘከር ነው
የዛሬ 30 ዓመት ህይወቱ ያለፈው ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማርያም፣ በሙያ ባልደረቦቹ የማስታወሻ ዝግጅት ሊደረግለት ነው፡፡
የፊታችን እሁድ መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰአት ጀምሮ በወመዘክር አዳራሽ በሚከናወነው በዚህ ዝግጅት፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ባልደረቦቹ ይታደማሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡
የማስታወሻ ዝግጅቱ ሀሳብ አመንጪና አዘጋጅ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ሲሆን፤ በዕለቱም የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ተማሪዎች በመሰናዶው ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡
አንጋፋው ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማርያም፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬድዮ በጠቅላላው ከ24 ዓመታት በላይ ያገለገለ ሲሆን፤ በተለይም በዜና አቀራረብና አንባቢነት ለብዙዎች አርአያ በመሆን ይታወቃል፡፡
በማስታወሻ ዝግጅቱ ላይ፣ ስለ ጌታቸው ምስክርነት የሚሰጡት ጋዜጠኛ ሚሊዮን ተረፈ ፤ ጋዜጠኛ ዋጋዬ በቀለና ጋዜጠኛ ታዬ በላቸው ሲሆኑ፤ በተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን የተዘጋጀ የ20 ደቂቃ የድምጽ ዘጋቢ ሥራም እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የሚድያ ሰው ጌታቸው ኃይለማርያም፣ አሁን በአንጋፋነታቸው እውቅና የተቸራቸውን እንደ ነጋሽ መሀመድ፣ አለምነህ ዋሴ፣ ንግስት ሰልፉና ብርቱካን ሀረገወይንን የመሳሰሉ ባለሙያዎች ለሙያዊ ብቃት እንዲደርሱ በማሰልጠንና ልምዱን በማካፈል የበኩሉን የተወጣ ባለሙያ ነበር፡፡ ዜና ፋይል የተሰኘውን ፎርማት ለመጀመረያ ጊዜ እንዳስተዋወቀና እንደፈጠረ የሚነገርለት ባለሙያው፤ በብስራተ ወንጌል የሬድዮ ጣቢያም አገልግሏል፡፡
ታላቁ የሚድያ ሰው ጌታቸው፣ ከዚህ ቀደም ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ባሳተመው ‹‹መዝገበ አእምሮ የሚድያ ሰዎች ኢንሳይክሎፒዲያ›› ላይ ታሪኩ የተሰነደለት ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ያነበባቸው ዜናዎችና ምስሎቹም ወግ በያዘ መልኩ ለታሪክ እንዲቀመጥለት ተደርጓል፡፡
በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተጻፈው " ጥቁር አዳኝ " የተሰኘው መጽሐፍ ለንባብ በቃ ::
ጉባኤው
መሳፍንት እየተፈራቁ በነገሱበት ዘመን ንጉሥ አሊጋዝም የድርሻቸውን ገዙ፡፡ በዘመናቸው ብዙ እኩይና ሰናይ ክስተቶች ታዩ፡፡ እኔ ትሁት ጸሐፌ ትዕዛዛቸው ከሰማሁትና ካየሁት መካከል የመረጥኩትን ተረክሁ፡፡
በዚያን ዘመን ሀገራችን በድርቅ ተመታች፡፡
የሰማይ ግት ነጠፈ፡፡
መሬት ፍሬ ነፈገች፡፡
ሕይወት ያለፍሬ ያለቅጠል ቆመች፡፡
አልጋዎች ቃሬዛ ሆኑ፡፡
ግርማዊ ጃንሆይም መፍትሄ ፍለጋ ሊቃውንትን በአዋጅ ጠርተው በየእለቱ ጉባኤ ያደርጉ ጀመር፡፡ በዘመኑም ሰዎችን የሚያሰባስባቸው ጉባኤና ቀብር ሆነ፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን የተመረጡ ሊቃውንት የንጉሡን አዳራሽ ሞልተውት ነበር፡፡
ግርማዊ ጃንሆይ የጸሐይ ሽራፊ በመሰለ ዙፋናቸው ላይ ተቀምጠው ተደምጦ በማይጠገብ ድምጻቸው ይናገሩ ጀመር፡፡
“ወገኖቼ ሊቃውንት ጠቢባን… እንደምታዩት በየጊዜው አስፈሪ መአት እየተላከብን ነው፡፡ የዚያ ምክንያት ምንድን ነው? ራብን እንዳይመለስ አድርገን ለማባረር በምን አኳኋን መስራት አለብን? ይሄ የህይወት የህልውና ጉዳይ ነው… እስከአሁን አስራ ሁለት ጊዜ ተሰብስበናል --አስራ ሁለት ጊዜ ሊቃውንት… ዛሬ ግን ጉዳዩ እልባት ማግኘት አለበት፡፡ ይህን ጥያቄ ሳንመልስ ከዚህ አዳራሽ ንቅንቅ ማለት አንችልም፡፡ ሊቃውንት ናችሁ…መላችሁን ወዲህ በሉ፡፡”
ጸጥታ የእያንዳንዱን አንደበት ሸበበው፡፡
“በሉዋ ሊቃውንት…የምን መለጎም ነው?” ከማለታቸው ከፊት ከተኮለኮሉት አንዱ ተነሳ፡፡ ወገቡን ቆልምሞ እጅ ነስቶ ሲያበቃ “ጃንሆይ እኔ….” ብሎ ሊቀጥል ሲል ድምጡ በፍርሃት ደከመበት፡፡
ጃንሆይ ለማበረታታት ራሳቸውን ሲያወዛውዙለት “እህህ” ብሎ ጉሮሮውን አጽድቶ ገባበት፡፡ “እሺ እንግዲህ እኔ ነጋድራስ የትምጌታ ነው ስሜ -- የእናቴና የእናቴ ዘመዶች መሸሻ ብለው ይጠሩኛል፡፡ ወላጅ አባቴ ዋልድባ ተመግባቱ በፊት የፍጻሜ መንግስት ተክለጊዮርጊስ አማካሪ ነበር፡፡ የሱ ታናሽ ወንድም ደሞ…”
የሊቃውንቱ ዝምታ ወደ ጉርምርምታ ተለወጠ…
“እንግዲህ ስለራሴ ይህንን ታልሁ … ወደ ዋናው ሀሳቤ እገባለሁ፡፡ እንግዲህ ከዚህ ቀደም በርስዎና በአባቶቻችን ፈቃድ ለንግድ በተለያዩ አገሮች ተመላልሻለሁ፡፡ ለመሆኑ የት የት ሄደሃል የሚለኝ ካለ የሄድኩባቸው ሀገሮች የሚከተሉት ናቸው፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ሰማይ የሚታከኩ፤ ዓለምን የማረኩ ቢራሚዶች ባሉባት ግብፅ ነበርኩ፡፡ ተዚያም አስከትዬ የነውጠኛው እስክንድር አገር በሆነችው መቄዶንያ ከራርሜ ወደ ፋርስ ተሻገርኩኝ፡፡ ተፋርስ ወደ ኑቢያ ተኑቢያም …”
“ማነህ ነጋድራስ፡-” አሉ ጃንሆይ ትዕግስቸው አልቆ “ነጋድራስ ነው ያልከኝ? አዎ ነጋድራስ… እኛ እዚህ ወርቅ ጊዜያችንን ቆጥበን የምንሰበሰበው ያንተን የዙረት ታሪክ ለማወቅ አይደለም፡፡ እኛን ያስጨነቀን ጉዳይ ራብ ነው፡፡ በራብ ጉዳይ ላይ መላ ካለህ መላህን ወዲህ በል… አለበለዚያ ለአሁኑ ይቅር ብለንሃል፡፡ ወደ ጥግህ ተመለስ--”
“ጃ… ጃንሆይ…” አለ ነጋድራስ የወረዛ ግንባሩን ባይበሉባው እየፈተገ “እንግዲህ መንገዴን ስቼ ንግግሬን እንደባልቴት አስረዝሜ ተሆነ በእውነቱ ግሳጼ የሚገባኝ ግም ሰው ነኝ፡፡ በውነቱ እኒያን ትልልቅ አገሮች መጥቀሴ ለከንቱ ውዳሴ ብዬ አልነበረም፡፡ ዘላንነት እጣ ፈንታ እንጅ ክብር እንዳልሆነ አውቃለሁ… ይህን ስል ጉዳዩን ረስቼ ሳይሆን በእኝህ አገሮች በነበርኩበት ጊዜ የቀሰምኩትን ጥበብ ለማካፈል አስቤ ነው…”
በጃንሆይ ፊት ላይ ወገግታ ታዬ፡፡
“እንዲያ አትለኝም?” አሉ በደስታ በተቃኘ ድምጽ “እንዲህ ያለውን ሊቅ ነው በመብራት ስንፈልግ የቆየነው፤ በል እስቲ የምታውቀውን ንገረን…”
“ጃንሆይ ሺ ዓመት ይንገሱ…” እንደገና ታጥፎ እጅ ነሳ፡፡ “እንግዲህ አስቀድሜ ወንዞቻችን ስለምን አገር አቋርጠው እንደሚነጉዱ እገልጣለሁ፡፡ ለጥቄ እንዴት አድርገን አናሳ ወንዞችን መገደብ እንደምንችል አብራራለሁ፡፡ ያንን አንድ ባንድ ካስረዳሁ በኋላ መስኖ በምን አኳኃን እንደምናበጅና---”
ሌላ ጉርጉምታ ከሊቃውንቱ መጣ፡፡
“ምን ሆናችኋል?” አሉ ጃንሆይ “መሪጌታ ስነ እየሱስ---ምንድርን ነው ነገሩ? ቅር ያለህ ትመስላለህ?”
በገፈጅ የሚያክል አዳፋ ጥምጣም አናታቸው ላይ የደፉት መሪጌታ ስነ እየሱስ ብድግ ብለው እጅ ነሱ፡፡ ከዚያም ጣዝማ ያበጀችው ሽንቁር በመሰለው አንድ ዓይናቸው ጃንሆይን ሽቅብ እየተመለከቱ፤ እኔ እንኳን ቅር ያለኝ የነጋድራስ ነኝ ባዩ የቋንቋ አጠቃቀም ነው” ከማለታቸው
“እንዴት?” ጃንሆይ ተቀበሏቸው፡፡
“እንዴት ማለት ጥሩ ነው፤ ሊቁ አባታችን ጃንሆይ” አሉ መሪጌታ “ ወንድሜ ነጋድራስ አውቆ በድፍረት ይሁን ሳያውቅ በስህተት እንጃ የታፈረውን የተከበረውን ቋንቋችንን ሲዘነጣጥለው ባይ እንባዬ መጣ፣ ሆድ ባሰኝ፣ ቁጭት ልቤን መዘመዘው---አላስችል አለኝ--” እንደማልቀስ ቃጣቸው፡፡
“በመዠመሪያ ጅረት ማለት ሲገባው አናሳ ወንዝ አለን፡፡ ዝም አልነው፡፡ እሱ ግን ይህንን ሳያርም ሌላ ገደፈ፡፡ ቀጥዬ ማለት ሲገባው ለጥቄ ብሎ ተናረ፡፡ በዚህ መች አብቅቶ መስኖ ለመጥለፍ እል ብሎ መስኖ ማበጀት ብሎ አረፈ፡፡ እንግዲህ ይህንን ዝም ብሎ ማለፍ እንደምን ይቻላል?”
ግራ ቀኙን በዓይናቸው ገመገሙት፡፡
ዝምታውን “አበጀህ” በሚል ተረጎሙት፡፡
“ጃንሆይ… አሳምረው እንደሚያውቁት የህዝብ አንድነት መሰረት ቋንቋ ነው፡፡ የሰናኦር ስልጣኔ የፈራረሰችው በቋንቋ ቅይጥ ምህኛት ነው፡፡ የቋንቋ ቅየጣስ ሰዋሰውን ባልባሌ ሁኔታ ከመጠቀም የሚመጣ አይደለምን ? መቼም የቋንቋ ሊቅ ለመሆን የሰዋሰው ጥበብ መማር አለብን እያልኩኝ አይደለም፡፡ አስተዋይ አድማጭ ለሆነ ቢያንስ የጃንሆይን ንግግር ለሁለት ሰዓት ያህል ማድመጥ የተባ አንደበተኛ አያረግም?--- አያረግም ወይ ሊቃውንት?...”
“እስቲ ይሁንልህ” በሚል ምልክት ሊቃውንት ራሳቸውን ወዘወዙ፡፡
“ስለዚህ እንደኔ እንደኔ የቋንቋ ችግር አለብን፡፡ ይሄን የቋንቋ ችግር ታልፈታን እንደ ሰብአ ባቢሎን እንደምንፈታ ጥርጥር የለውም…”
“እህ…እህ….እህ…” አሉና ጃንሆይ ራሳቸውን ናጡ፡፡
“ማነህ?…ነጋድራስ ነጋድራስ ነኝ ነው ያልከኝ… አዎ ነጋድራስ ተቀመጥ እስቲ”
(ለካ ነጋድራስ ያንን ሁሉ በትር የተቀበለው በቁሙ ነው)
“እስቲ መሪጌታም ይቀመጡ… ለነገሩ እኔም በቋንቋችን ውስጥ ያለውን ጉድለት ጉዳይ ሲከነክነኝ ነው የቆየው… መሪጌታ እንዳሉት የቋንቋ ችግር ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፡፡ የቋንቋችን ችግር ከየት የመነጨ ነው? በምንስ አኳኋን ሊታረም ይችላል? ሊቃውንት ከሞሉባት ሀገር ይህን ሳንመልስ ተዚህ አዳራሽ ብንወጣ የሚያፍረው መከረኛው ህዝባችን ነው---በሉዋ ሊቃውንት መሪጌታ ተርስዎ ልጀምር መሰል?”
”ጥሩ እንግዲህ” አሉ መሪጌታ “በእርግጥ በዚህ ጉዳይ ላይ በደንብ ባውጠነጥን ብዙ በተናገርኩ ይሁን እንጅ አሁንም ቢሆን የቋንቋ ችግርን የምንፈታው እንደ ተክለ አልፋ ያሉትን የሰዋሰው መምህራን ከፍልሰት ስንታደግ ነው ባይ ነኝ…”
“ተክለ አልፋ ምን ሆነ?”
“አዬ ጃንሆይ ተሚያስተምርበት ደብር አሳደዱት’ኮ”
“ተክለ አልፋን?”
“እንዴት ያለውን ሊቅ ጃንሆይ?”
“እኮ ለምን?”
“ምን አውቃለሁ ጃንሆይ ምህኛቱማ ዝምታ ነው”
“ነው?” አሉ ጃንሆይ ነገር በገባው ቋንቋ-- “ለነገሩስ የሊቃውንትን የፍልሰት ወሬ ታንድም ሁለት ጊዜ መስማቴን እኔም አልሸሽግም፡፡ ጉዳዩ እንዲህ ስር የሰደደ መሆኑ ግን አሁን ነው የተገለጠልኝ፡፡ መቼም የጅሎች ሁሉ በኩር ታልሆን በቀር በነግ እናቆየዋለን ብዬ አላስብም፡፡ ሊቃውንታችን የሚፈልሱበት ምህኛት ምንድን ነው--? ማነው የሚያፈልሳቸው---? ነገሩን ተሥር መሰረቱ ለማድረቅ ምን ማድረግ ይገባናል---? መልሱልኝ ሊቃውንት--”
“ጃንሆይ” አሉ መሪጌታ “በኛ አገር ጠቢብ መሆን አብሪ ትል መሆን ማለት ነው፡፡ አብሪ ትል ከሌሎች ትሎች የሚለየው ገላው እንደፍም ማብራቱ ነው፡፡ ታዲያ ብላቴኖች በጨለማ ሲያበራ ሲያዩት በገዛ ብርሃኑ ተመርተው ይመጡና አንስተው ይጨፈልቁታል፡፡ ለጠላቶቹ መንገድ ከማሳየት አልፎ የገዛ ብርሃኑ ለምንም አይጠቅመውም፡፡”
“ተክለ አልፋ የተባረረው ንዋየ ቅዱሳት መዝብሮ ነው---ጃንሆይ” አለ አንድ ከግራ ጥግ ተወርውሮ የመጣ ሻካራ ድምጽ፡፡
“ምን?” ጃንሆይ ገነፈሉ፡፡
“ጃንሆይ በደካማው ሥጋዬና በጠልጣላዋ ነፍሴ እምላለሁ፡፡ ተክለ አልፋ የሳር ውስጥ እባብ ነው፡፡ የስነፍጥረትን መጽሐፍ ሸሽጎ ሊወጣ ሲል እኮ ነው ለቅም ያረግነው”
“እኮ ተክለ አልፋ!?”
“ማን ያምናል ጃንሆይ!...”
“ተነአህያው ሞተልሽ!” አሉ ጃንሆይ ተስፋ መቁረጥ በቃኘው ድምጽ “አልቀናል በሉኛ! እንግዲህ ንዋየ ቅዱሳቱ ተዘርፈው ከወጡ ምን ቀረን? እኛስ አለን ወይ?---ህልውናችንን’ኮ ነው የመዘበሩት---እኛስ እንግዲህ ማን ተብለን ልንጠራ ነው? በምን በኩል ኢትዮጵያውያን ነን እንበል? ጎበዝ እዚህ ላይማ ዋዛ የለም..!
“ተቀመጥ መሪጌታ---በሉ ሊቃውንት ይህንን ጉዳይ መልሱልኝ፡፡ ይህንን ሳንፈታ ብንወጣ የአባቶቻችን አጽም እሾህ ሆኖ ይወጋናል…በሉ እንጅ ምሁራን”
እዚህ ላይ እኩሌቶች ሊቃውንት አዛጉ አንጎላጁ፡፡
ይኼኔ ነው ኋላ ከተቀመጡት አረጋውያን ሊቃውንት መካከል አንደኛው የተነሱት፡፡ እኚህ ሊቅ እድሜም ጥበብም የጠገቡ እንደሆኑ ስለተመሰከረላቸው ሲነሱ አይን ሁሉ ወደሳቸው መጣ፡፡
“ግርማዊነትዎ ፍቃድዎ ከሆነ ብናገር…”
“ቀጥሉ” አሉ ጃንሆይ
“የተከበሩት ጃንሆይ--” አሉ የአቡዬ ገብሬን የመሰለ ረዥም ጺማቸውን እየላጉ፡፡ “አያሌ ሀያላን በሀገሬ ላይ ተፈራርቀው ሲነግሱ አይቻለሁ፡፡ በዚህ እፍኝ በማትሞላ እድሜ የብዙዎች አማካሪ የመሆን እድል አጋጥሞኛል፡፡ እኔ እንደታዘብኩት ከድርቅ፣ ከቸነፈር በላይ ይችን አገር ያደቀቃት ጉባኤ ነው፡፡ ጉባኤ ምን አተረፈልን? ተሰብስበን እንወጥናለን፡፡ ወጥነን እንበተናለን፡፡ ስለዚህ ከሁሉ አስቀድሞ የዚህ ጉዳይ ቢታይ ባይ ነኝ…”
ጃንሆይ ለጊዜው ምንም አላሉም፡፡ አርምሟቸው ግን ጊዜ አልፈጀም፡፡ “አዬ ጉድ…” በመዳፋቸው ጭናቸውን እየጠበጠቡ “እንዲህ ልክ ልካችንን ንገሩን እንጅ… ለነገሩስ አገሩ በጠቢባን እንደማይታማ አውቃለሁ፡፡ ግን በእድሜ ያልተፈተነ ጥበብ የገደል ማሚቶ ነው፡፡ ለመናገርማ ብዙዎች ሲናገሩ ቆይተው የለምን? እንዲህ የንስር ዓይን የታደሉ ብስል ሊቅ ግን ተሰውሮብን የነበረውን ጥበብ ገላለጡት፡፡ ልክ ነው ትልቁ የእኛ ራስ ምታት ጉባዔ ነው፡፡ ጉባያችን ለምን ፍሬ አጣ? እንዴት ፍሬ ይኑረው? ይህንን ተነጋግረን ካልፈታን ከዚህ ጉባዔ ንቅንቅ አንልም፡፡ ነቃ በሉ እንጅ ሊቃውንት፡፡”
ተፈጸመ ዝንቱ መጽሐፍ
ጉባኤው ግን ቀጠለ፡፡
ምንጭ፡- (በራሪ ቅጠሎች፤ 1996 ዓ.ም)
አንጋፋው ምሁር እና ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀ መንበር አንጋፋው ምሁር እና ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
የፕሮፌሰሩን ማለፍ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ “[ፕ/ር በየነ] ረዘም ላለ ጊዜ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውንን ስሰማ ከልብ አዝኛለሁ” ብለዋል።
ፕሮፌሰር በየነ ከታኅሣሥ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥታዊው የፖሊሲ ጥናት ኢንስትዩት አምስተኛው ዳይሬክተር ጄነራል ሆነው ሲያገለግሉ ነበር። ፕሮፌሰሩ ይህን ሹመት ያገኙት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ረፋድ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በኢትዮጵያ ገንቢ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ምልክት ነበሩ” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የተወለዱት መጋቢት 2/1942 ዓ.ም. በአሁኑ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን ነው።
ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ በተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኝነት ስማቸው በጉልህ ከሚነሳ ፖለቲከኞች መካከል ናቸው። በሽግግር ወቅት የደቡብ ፓርቲዎችን ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን አስተባብረው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲ ኅብረት የተባለ የፖለቲካ ድርጅት በመመሥረት 17 መቀመጫ ይዘው ነበር።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀ መንበር አንጋፋው ምሁር እና ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
የፕሮፌሰሩን ማለፍ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ “[ፕ/ር በየነ] ረዘም ላለ ጊዜ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውንን ስሰማ ከልብ አዝኛለሁ” ብለዋል።
ፕሮፌሰር በየነ ከታኅሣሥ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥታዊው የፖሊሲ ጥናት ኢንስትዩት አምስተኛው ዳይሬክተር ጄነራል ሆነው ሲያገለግሉ ነበር። ፕሮፌሰሩ ይህን ሹመት ያገኙት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ረፋድ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በኢትዮጵያ ገንቢ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ምልክት ነበሩ” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የተወለዱት መጋቢት 2/1942 ዓ.ም. በአሁኑ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን ነው።
ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ በተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኝነት ስማቸው በጉልህ ከሚነሳ ፖለቲከኞች መካከል ናቸው። በሽግግር ወቅት የደቡብ ፓርቲዎችን ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን አስተባብረው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲ ኅብረት የተባለ የፖለቲካ ድርጅት በመመሥረት 17 መቀመጫ ይዘው ነበር።
የደርግ መንግሥት ወድቆ በኢህአዴግ አስተባባሪነት በተቋቋመው የሽግግር መንግሥት ወቅት ምክትል የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ተሹመው ለሁለት ዓመት አገልግለዋል። በ1992 ዓ.ም. በሁለተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተወዳድው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልም ሆነው ነበር።
በምክር ቤት ቆይታቸው ወቅትም በሕዝቡ ውስጥ ያሉ አሳሳቢ ጉዳዮችን በማንሳት በመሞገት በአንድ ፓርቲ የበላይነት በተያዘው ምክር ቤት የተለየ ድምጽ ሆነው ቆይተዋል።
ፕሮፌሰ በየነ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ ቁጥራቸው የበዛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት ፈጥረው ተጽእኖ እንዲኖራቸው የበኩላቸውን እንዳደረጉ ይነገርላቸዋል።
በዚህም በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ከቅንጅት ጋር ዋነኛ ተፎካካሪ የነበረውን ኅብረት እንዲሁም ከዚያ በኋላ መድረክ የተባሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረትን ካቀወቋሙ ቁልፍ ፖለቲከኞች መካከል ተጠቃሹ ናቸው።
ፕሮፌሰር በየነ በፖለቲከኛነታቸው ይታወቁ እንጂ አንቱ የተባሉ ሥነ ሕይወት (ባዮሎጂ) ሊቅም ናቸው።
በ1965 ዓ.ም. የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ሕይወት አግኝተዋል ከዚያም ወደ አሜሪካ አቅንተው የከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
የማስተርስ ዲግሪያቸውን ከአሜሪካው ዊስኮንሲን ዩኒቨርሲቲ የተቀበሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ ከቱሊን ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በርካታ የድኅረ ምረቃ እና የዶክትሬት ተማሪዎችን አስተምረዋል፣ አማክረዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል ሊቀ መንበር በመሆን የአካዳሚክ እና የምርምራ ሥራቸውን የጀመሩት ፕሮፌሰር በየነ የኢትዮጵያ ባዮሎጂካል ሶሳይቲ መሥራች እና ፕሬዝዳንት ነበሩ።
ፕሮፌሰር በየነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በወባ እና በሌሎች ጥገኛ ተውሳኮች ላይ ያተኮሩ የምርምር ፕሮጀክቶችን መርተዋል።
በተጨማሪም በበርካታ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና አገር አቀፍ የሙያ ማኅበራት ውስጥ አማካሪ ቦርድ እና የኮንፈረንስ አዘጋጅ ኮሚቴዎችን በመምራት አገልግለዋል።
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በሕዝብ ተሳትፎ፣ በአካዳሚክ ውጤታቸው እና በምርምር መሪነት ብዙ ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ ሽልማቶችን እና የወርቅ ሜዳሊያዎችን አሸንፈዋል።
ምሁሩ በየነ ጴጥሮስ በሙያቸው ወደ 120 የሚጠጉ በአቻ የተገመገሙ ሳይንሳዊ የጥናት ጽሁፎችን በጥናታዊ መጽሔቶች ላይ አሳትመዋል።
ልቦለድ መሳዩ ድንገቴ
በ1972 አሥመራ ከተማ በቁም እስረኝነት ዘመኔ ካጋጠሙኝና ፈፅሞ ከማይረሱኝ ኹነቶች መካከል በአንዱ ቀን ያጋጠመኝን ላጫውታችሁ።
ኒያላ ሆቴል አሥመራ ከሚገኙት ታላላቅ ሆቴሎች በቀዳሚነት የሚጠራ ትልቅ ሆቴል ነው። ያን ቀን እዚያ አካባቢ ለምን እንደሔድኩ ትዝ አይለኝም። ብቻ ከእሱ ፊት ለፊት ከሚገኘውና “ባር ዕምባባ” እየተባለ ከሚጠራው ቡና ቤት ጎራ ብዬ ጥግ ላይ ተቀምጬ መሎቲ ቢራ አዘዝኩ። ቢራዬ እስኪመጣም አካባቢዬን ስቃኝ፤ ከእኔ አንድ ጠረጴዛ አልፎ አምስት ሰዎች ከበው እየተሳሳቁ ያወራሉ። የሚያወሩት በአማርኛ ነው።
ጦር ሠፈር አካባቢ፣ ቃኘው ስቴሽን ውስጥ፣ ኮምፕሽታቶ ካሉት እነ ባር ጎንደር አካባቢ ወይም ክበቦች አካባቢ ካልሆነ እንደ “ባር ዕምባባ” ዓይነት ቡና ቤቶች ውስጥ የሚበዛው ትግርኛ ተናጋሪ እንጅ እንዲህ ዓይነት በአማርኛ ተናጋሪዎች የደመቀ ቤት ብዙ ጊዜ አይገጥምም። እና ብቻዬን ብገባም በቅርቤ የእነሱን ሞቅ ያለ የአማርኛ ጨዋታ በመስማቴ የብቸኝነት ስሜቴ ጥሎኝ ሲሸሽ ተሰማኝ።
ቢራዬም ቀርቦልኝ እየተጎነጬሁ አልፎ አልፎ ጆሮዬን ጣል እያደረግኩ ሳዳምጣቸው፤ ከወሬያቸውም፣ ከሁኔታቸውም ወታደሮች መሆናቸውን ተረዳሁ። በዕድሜም ትንሽ በሰል ያሉ ናቸው። ሲኒየር ወታደሮች ወይም መኮንኖች ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ ጠርጥሬአለሁ። የመጀመሪያ ቢራዬን አጣጥሜ ሁለተኛ ቢራዬን ለማዘዝ ብንጠራራም አስተናጋጇ አላይህ ስትለኝ ድምጼን ጎላ አድርጌ፤ “ይቅርታ የኔ እመቤት!” ብዬ ሳጨበጭብ፤ “አንድ! ሁለት! ሶስት!” የተባለ ይመስል የወታደሮቹ ዐይኖች በሙሉ ዞረው እኔ ላይ ተተከሉ። ለአፍታ “በማጨብጨቤ አጥፍቼ ይሆን እንዴ?” የሚል መደናገጥ ቢሰማኝም፤ አስተናጋጇ እየፈገገችና ወደእኔ እየነጠረች ስትመጣ በምልክትም በንግግርም “ጨምሪልኝ!” አልኳት። ልጅቷ ቢራዬን ልታመጣልኝ ስትሄድ ከሰዎቹ አንዱ፤
“የኔ ወንድም... ና እኛ ጋ ተጫወት፤ ለምን ብቻህን አለኝ” ፈገግ እያለ።
ሲፈ’ግ በጥርሱ በስተግራ በኩል የወርቅ ጥርሱ ብልጭ አለች። እሱን ተከትሎ ሌሎችም፤
“ውነቱን ነው ና እኛ ጋ ና!” በሚል ወዳጃዊ ግብዣቸው አጣደፉኝ።
ግብዣቸውን እምቢ የምልበት ምንም ምክንያት የለኝምና፤ ልጅቷ ቢራዬን ከማምጣቷ በፊት ወንበር ተስቦልኝ፤
“ተስፋዬ እባላለሁ” እያልኩ ሁሉንም ጨብጬ መጀመሪያ ከጋበዘኝ ባለወርቅ ጥርሱ ሰውዬ አጠገብ ተቀመጥኩ። ስሙ አሰፋ ነው።
ቢራዬ መጥቶልኝ “ለእንግዳችን ክብር!” ተብሎ ጠርሙሳችንን አጋጭተን፣ የመጀመሪያ ትንፋሼን ተጎንጭቼ፣ ጠርሙሱን ቁጭ ሳደርግ፤ ከአጠገቡ የተቀመጥኩት ባለጥርሰ ወርቁ ሰው፤
“የመሐል አገር ሰው ነህ አይደል?” አለኝ፤ አሁንም እየፈገገና የወርቅ ጥርሱን ብልጭ እያደረገ፤
“አዎ!”
“መሐል አገር የት?”
“ወሎ!”
“እ...ወ...ወሎ? ወሎ የት?!” አጣደፈኝ፤
“እ... ኮምቦልቻ ነው ተወልጄ ያደግኹት!”
“እናትህም አባትህም እዚያው ኮምቦልቻ?” ሲል ከእኔ በስተቀኝ የተቀመጠው፤
“እንዴ አሰፋ! ...ኧረ ትንፋሽ ስጠው ይጠጣበት... አጣደፍኸው እኮ! ያንተ ነገር ወሎዬ ነኝ ካሉህ ማጀታቸው አይደለም አንጀታቸው ሳትገባ አትወጣ... የታወቀ ነው” ሲለው ሌሎቹም በሳቅ አጀቡት። እሱም እየሳቀ፤
“እሺ ጠጣ! ይቅርታ! ...እውነትም አጣደፍኩህ... ተስፋዬ ነው ያልከኝ አይደል ስምህን?” አለኝ።
“አዎ! ልክ ነህ!” አልኩት።
ቢራዬን አንስቶ አቀበለኝ።
ሰዎቹ በጣም ደስ ይላሉ። አሥመራ ወታደሮች ሰብሰብ ብለው ሲበሉም ሆነ ሲጠጡ ከደረሳችሁ “በሞቴ አፈር ስሆን” ተብሎ በግብዣ መወጠር የተለመደ ነው። ከአቅም በላይ ካልሆነባችሁ በስተቀር ግብዣቸውን የማትቀበሉበት አንዳች አቅም አታገኙም። ወታደር የምወደው በዚህ በዚህ ጭምር ሳይሆን ይቀራል? እና ያው አሰፋ ያልኳችሁ ጥርሰ ወርቁ ለአፉ ያህል “እሺ ይቅርታ” ቢልም ዐይኑ በፍጹም ከእኔ ላይ አልተነሳም። ቢራዬን አንስቼ ስጠጣም፣ ብርጭቆውን ሳስቀምጥም ትኩር ብሎ በዐይኑ ያጅበኛል። መሐል ላይ ያለው አንደኛው ጓደኛቸው፤
“አሰፋ! ኧረ ዐይንህን ንቀል የልጁ ቀለም ገፈፈ እኮ” ሲል እኔን ጨምሮ ሁላችንም በሳቅ አጀብነው። እሱም አብሮን ሲስቅ ቆየና፤
“ቆይ... በውነት ግን እናትህም አባትህም እዚያው ኮምቦልቻ ነው ትውልዳቸው?” አለኝ፤
“አይ! አባቴ የሸዋ ሰው ነው” አልኩት።
እውነት ለመናገር ዝርዝር ጥያቄው ብዙም አላስደሰተኝም። በውስጤ ምን ፈልጎ ነው? የምትል ሳሳ ያለች ንጭንጭ አቆጥቁጣለች።
“እናትህስ?” አለኝ ቀጥሎ፤
“እናቴ... እ... በእናቷ ወገን ተሁለደሬ ዋሄሎ ናት” ስል፤
“ዋሄሎ!” ብሎ እንደመደንግጥ አለና ተቁነጠነጠ “...እሺ ...ሀይቅ ...በአባቷስ” አለኝ?
“በአባቷ በኩል ኩታበር ናት!”
“ኩታበር!” ከመቀመጫው ተስፈንጥሮ ብድግ ሲል እንደመደንገጥ ብዬ፤
“እንዴ ሰውዬው ምን ነካው? ያመዋል እንዴ?” አልኩ በሆዴ።
“ኩታበር የማን ልጅ ናት?” አለኝ ፋታ ሳይሰጥ።
ግራ በመጋባት ለአፍታ ትኩር ብዬ አየሁት፤ ቁመቱ ወደ እጥረቱ የሚያደላ መካከለኛ ነው። የውትድርና ሕይወቱ አጠይሞት እንጅ መልኩ ብስል ቀይ የሚባል ዓይነት ነው። ከቅጥነቱ የተነሳ ጉንጮቹ ጎድጉደዋል። ዐይኖቹ ብርሃን እንዳረፈበት ውሀ የሚያብረቀርቁና ትንንሾች ቢሆኑም፤ ከእኔ የሆነ ነገር መስማት መፈለጉ በፈጠረበት ጉጉት ከጉድጓዳቸው ወጥተው ሊዘረገፉ ደርሰዋል። ደግሜ በልቤ “በዕውነት ሰውዬው ምን ፈልጎ ነው? ይሄን ያህል ጠልቆ ዘር ማንዘሬን የሚጠይቀኝ” እያልኩ ነግሬው ልገላገል በሚል፤
“የአሊ አማኑ ልጅ ናት!” ስል ጭንቅላቱን ይዞ ብድግ በማለት፤
“አውቄዋለሁ! ሥጋዬ ነግሮኛል! ወ ን ድ ሜ” እያለ እየጮኸ በላዬ ላይ ተከመረብኝ።
በዚያ ሰዓት በእኔ ቦታ አያኑራችሁ። እንኳን እኔ ጓደኞቹ ሁሉ ግራ ተጋብተዋል። እንደምንም ከኔ ላይ ሊያላቅቁት እየሞከሩ፤
“እስቲ ቆይ አሰፋ ተረጋጋ፣ ልጁንም እኮ ግራ አጋባኸው፣ ምንድነው የሆንከው?” ሲሉት፤
“አሁን ይሄንን ማን ያምናል?! እኔ ገና ሳየው እኮ ነው ያወቅኩት ...ልቤ ነግሮኛል ...ልክ አይዬን ራሱን እኮ ነው የሚመስለው” ሲል፤
“እ!” ብዬ እኔም ብድግ አልኩና፤
“አይዬን? ማነው አይዬ” አልኩት፤
“አሊ አማኑ ጎበዜ!” አለኝ።
አያቴን ቤተሰቡ ሁሉ አይዬ ነው የሚለው። እኛም እናታችን በምትጠራበት “አይዬ” ነው የምንለው። ሳላስበው ዕንባዬ ድንገት ተዘረገፈ። እና እንደምንም፤
“እና አንተ ማነህ?” አልኩት፤
“ይመር ፈለቀ!”
“ይመር ፈለቀ ...አሰፋ ነኝ አላልከኝም እንዴ?” አልኩት ኮስተር እንደማለት ብዬ፤
“እሱ ሌላ ታሪክ ነው! ወታደር ቤት ስገባ ነው የቀየርኩት”
“እና አንተ የየሺ ፈለቀ ወንድም ...የፈለቀ አማኑ ልጅ...!” ብዬ ሳልጨርስ በልቅሶ ተቃቅፈን ቤቱን ትኩስ መርዶ የተረዳበት
ቦታ አስመሰልነው። ከዚህም ከዚያም ሰዎች ተሰበሰቡ። ጉድ ተባለ። የሠራዊቱ አባላት እንኳን እንዲህ ያለ ነገር አግኝተው እንዲያውም እንዲያው ናቸውና “ወንድማማቾች ተገናኙ” ተብሎ ...የደስ ደሱን ከግራ ከቀኝ መሎቲውን በሣጥን በሣጥን ያወርዱት ጀምር፣ ታላቅ ፌሽታም ሆነ።
አሰፋ መሐል ላይ ከደስታው መለስ ሲል፤
“እስቲ ተመልከቱት አንመሳሰልም? ቁርጥ አይዬን አሊ አማኑን እኮ ነው” እያለ ጓደኞቹ የማያውቁትን አሊ አማኑን መምሰሌን ያረጋግጡለት ዘንድ አገጬን ከግራ ቀኝ እያገላበጠ ያሳያቸው ገባ። እውነቱን ነው፤ እሱም ቁመቱ ከማጠሩ በስተቀር የፊት ገጽታው ቁርጥ አያቴን አሊ አማኑን ነው የሚመስለው። ልብ ብሎ ላየንም ስጋ ዘመድ መሆናችን ያስታውቃል።
ከእናቴ ጋር የወንድማማች ልጆች ናቸው፤ እውነተኛ ስሙ ይመር ፈለቀ የሚባልና የጠፋው የእናቴ አጎት የፈለቀ አማኑ ልጅ ሆኖ ተገኘ። ለካስ የአገራችን የወሎ ሰው “የአላህን መኖር እንዴት ታውቃለህ ሲሉት፤ አላሰብኩት ቦታ ሲያውለኝ” አለ የተባለው እንዲህ ያለው ገጥሞት ኖሯልና።
እናም የቁም የፖለቲካ እስረኛ በሆንኩበት ዘመን አሥመራ መሐል፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የሥጋ ዘመድ የሚባል ነገርን በእንዲህ ዓይነት ልቦለድ በሚመስልና በማይታመን አጋጣሚ አገኘሁ። በዚያው ቀንም “ቤተሰብህን ሳታይማ አታድርም” ብሎ ቃኘው ስቴሽን ታንከኛ ሻለቃ ባለጓዝ ሰፈር ይዞኝ ሄደ። ከባለቤቱና ከሁለት ልጆቹም ጋር ተዋውቄ ባላሰብኩት ደስታ ተጥለቀለቅኩ። ባንድ ቀንም “አጎቴ!” በመባል መጠራት ጀመርኩ። በዚህ ምክንያትም እኔ ከቤተሰቦቼ ጋር በየጊዜው በደብዳቤም በስልክም እገናኝ ስለነበር ሁኔታውን ዘርዝሬ ለእናቴ በኤሮግራም ላኩላት። ሞቷል ብሎ ተስፋ የቆረጠው ቤተሰብ ሁሉ ተስፋም አንሠራራ።
አሰፋና (ይመር ፈለቀ) ቤተሰቡ ኤርትራ በሻዕቢያ እጅ ስትወድቅ ከእልቂት ተርፈው አዲስ አበባ ከገቡት የቀድሞ ሠራዊት አባላትና ቤተሰቦች መካከል ነበሩ። ባለቤቱ ልጆቿን ይዛ እዚህ አዲስ አበባ መገናኛ አካባቢ ዘመዶቿ ጋር ስትቀር፤ እሱም ወሎ “ሐይቅ” ሔዶ ከእህቱ የሺ ፈለቀና ከዘመዶቻችን መሐል ኑሮውን ቀጠሎ ከጥቂት አመታት በፊት አለፈ።
(ሁለገቡ የኪነጥበብ ባለሙያ ተስፋዬ ማሞ ሰሞኑን ለንባብ ካበቃው “ከማዕበል ማዶ” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ የተቀነጨበ)
ልቦለድ መሳዩ ድንገቴ
ልቦለድ መሳዩ ድንገቴ
በ1972 አሥመራ ከተማ በቁም እስረኝነት ዘመኔ ካጋጠሙኝና ፈፅሞ ከማይረሱኝ ኹነቶች መካከል በአንዱ ቀን ያጋጠመኝን ላጫውታችሁ።
ኒያላ ሆቴል አሥመራ ከሚገኙት ታላላቅ ሆቴሎች በቀዳሚነት የሚጠራ ትልቅ ሆቴል ነው። ያን ቀን እዚያ አካባቢ ለምን እንደሔድኩ ትዝ አይለኝም። ብቻ ከእሱ ፊት ለፊት ከሚገኘውና “ባር ዕምባባ” እየተባለ ከሚጠራው ቡና ቤት ጎራ ብዬ ጥግ ላይ ተቀምጬ መሎቲ ቢራ አዘዝኩ። ቢራዬ እስኪመጣም አካባቢዬን ስቃኝ፤ ከእኔ አንድ ጠረጴዛ አልፎ አምስት ሰዎች ከበው እየተሳሳቁ ያወራሉ። የሚያወሩት በአማርኛ ነው።
ጦር ሠፈር አካባቢ፣ ቃኘው ስቴሽን ውስጥ፣ ኮምፕሽታቶ ካሉት እነ ባር ጎንደር አካባቢ ወይም ክበቦች አካባቢ ካልሆነ እንደ “ባር ዕምባባ” ዓይነት ቡና ቤቶች ውስጥ የሚበዛው ትግርኛ ተናጋሪ እንጅ እንዲህ ዓይነት በአማርኛ ተናጋሪዎች የደመቀ ቤት ብዙ ጊዜ አይገጥምም። እና ብቻዬን ብገባም በቅርቤ የእነሱን ሞቅ ያለ የአማርኛ ጨዋታ በመስማቴ የብቸኝነት ስሜቴ ጥሎኝ ሲሸሽ ተሰማኝ።
ቢራዬም ቀርቦልኝ እየተጎነጬሁ አልፎ አልፎ ጆሮዬን ጣል እያደረግኩ ሳዳምጣቸው፤ ከወሬያቸውም፣ ከሁኔታቸውም ወታደሮች መሆናቸውን ተረዳሁ። በዕድሜም ትንሽ በሰል ያሉ ናቸው። ሲኒየር ወታደሮች ወይም መኮንኖች ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ ጠርጥሬአለሁ። የመጀመሪያ ቢራዬን አጣጥሜ ሁለተኛ ቢራዬን ለማዘዝ ብንጠራራም አስተናጋጇ አላይህ ስትለኝ ድምጼን ጎላ አድርጌ፤ “ይቅርታ የኔ እመቤት!” ብዬ ሳጨበጭብ፤ “አንድ! ሁለት! ሶስት!” የተባለ ይመስል የወታደሮቹ ዐይኖች በሙሉ ዞረው እኔ ላይ ተተከሉ። ለአፍታ “በማጨብጨቤ አጥፍቼ ይሆን እንዴ?” የሚል መደናገጥ ቢሰማኝም፤ አስተናጋጇ እየፈገገችና ወደእኔ እየነጠረች ስትመጣ በምልክትም በንግግርም “ጨምሪልኝ!” አልኳት። ልጅቷ ቢራዬን ልታመጣልኝ ስትሄድ ከሰዎቹ አንዱ፤
“የኔ ወንድም... ና እኛ ጋ ተጫወት፤ ለምን ብቻህን አለኝ” ፈገግ እያለ።
ሲፈ’ግ በጥርሱ በስተግራ በኩል የወርቅ ጥርሱ ብልጭ አለች። እሱን ተከትሎ ሌሎችም፤
“ውነቱን ነው ና እኛ ጋ ና!” በሚል ወዳጃዊ ግብዣቸው አጣደፉኝ።
ግብዣቸውን እምቢ የምልበት ምንም ምክንያት የለኝምና፤ ልጅቷ ቢራዬን ከማምጣቷ በፊት ወንበር ተስቦልኝ፤
“ተስፋዬ እባላለሁ” እያልኩ ሁሉንም ጨብጬ መጀመሪያ ከጋበዘኝ ባለወርቅ ጥርሱ ሰውዬ አጠገብ ተቀመጥኩ። ስሙ አሰፋ ነው።
ቢራዬ መጥቶልኝ “ለእንግዳችን ክብር!” ተብሎ ጠርሙሳችንን አጋጭተን፣ የመጀመሪያ ትንፋሼን ተጎንጭቼ፣ ጠርሙሱን ቁጭ ሳደርግ፤ ከአጠገቡ የተቀመጥኩት ባለጥርሰ ወርቁ ሰው፤
“የመሐል አገር ሰው ነህ አይደል?” አለኝ፤ አሁንም እየፈገገና የወርቅ ጥርሱን ብልጭ እያደረገ፤
“አዎ!”
“መሐል አገር የት?”
“ወሎ!”
“እ...ወ...ወሎ? ወሎ የት?!” አጣደፈኝ፤
“እ... ኮምቦልቻ ነው ተወልጄ ያደግኹት!”
“እናትህም አባትህም እዚያው ኮምቦልቻ?” ሲል ከእኔ በስተቀኝ የተቀመጠው፤
“እንዴ አሰፋ! ...ኧረ ትንፋሽ ስጠው ይጠጣበት... አጣደፍኸው እኮ! ያንተ ነገር ወሎዬ ነኝ ካሉህ ማጀታቸው አይደለም አንጀታቸው ሳትገባ አትወጣ... የታወቀ ነው” ሲለው ሌሎቹም በሳቅ አጀቡት። እሱም እየሳቀ፤
“እሺ ጠጣ! ይቅርታ! ...እውነትም አጣደፍኩህ... ተስፋዬ ነው ያልከኝ አይደል ስምህን?” አለኝ።
“አዎ! ልክ ነህ!” አልኩት።
ቢራዬን አንስቶ አቀበለኝ።
ሰዎቹ በጣም ደስ ይላሉ። አሥመራ ወታደሮች ሰብሰብ ብለው ሲበሉም ሆነ ሲጠጡ ከደረሳችሁ “በሞቴ አፈር ስሆን” ተብሎ በግብዣ መወጠር የተለመደ ነው። ከአቅም በላይ ካልሆነባችሁ በስተቀር ግብዣቸውን የማትቀበሉበት አንዳች አቅም አታገኙም። ወታደር የምወደው በዚህ በዚህ ጭምር ሳይሆን ይቀራል? እና ያው አሰፋ ያልኳችሁ ጥርሰ ወርቁ ለአፉ ያህል “እሺ ይቅርታ” ቢልም ዐይኑ በፍጹም ከእኔ ላይ አልተነሳም። ቢራዬን አንስቼ ስጠጣም፣ ብርጭቆውን ሳስቀምጥም ትኩር ብሎ በዐይኑ ያጅበኛል። መሐል ላይ ያለው አንደኛው ጓደኛቸው፤
“አሰፋ! ኧረ ዐይንህን ንቀል የልጁ ቀለም ገፈፈ እኮ” ሲል እኔን ጨምሮ ሁላችንም በሳቅ አጀብነው። እሱም አብሮን ሲስቅ ቆየና፤
“ቆይ... በውነት ግን እናትህም አባትህም እዚያው ኮምቦልቻ ነው ትውልዳቸው?” አለኝ፤
“አይ! አባቴ የሸዋ ሰው ነው” አልኩት።
እውነት ለመናገር ዝርዝር ጥያቄው ብዙም አላስደሰተኝም። በውስጤ ምን ፈልጎ ነው? የምትል ሳሳ ያለች ንጭንጭ አቆጥቁጣለች።
“እናትህስ?” አለኝ ቀጥሎ፤
“እናቴ... እ... በእናቷ ወገን ተሁለደሬ ዋሄሎ ናት” ስል፤
“ዋሄሎ!” ብሎ እንደመደንግጥ አለና ተቁነጠነጠ “...እሺ ...ሀይቅ ...በአባቷስ” አለኝ?
“በአባቷ በኩል ኩታበር ናት!”
“ኩታበር!” ከመቀመጫው ተስፈንጥሮ ብድግ ሲል እንደመደንገጥ ብዬ፤
“እንዴ ሰውዬው ምን ነካው? ያመዋል እንዴ?” አልኩ በሆዴ።
“ኩታበር የማን ልጅ ናት?” አለኝ ፋታ ሳይሰጥ።
ግራ በመጋባት ለአፍታ ትኩር ብዬ አየሁት፤ ቁመቱ ወደ እጥረቱ የሚያደላ መካከለኛ ነው። የውትድርና ሕይወቱ አጠይሞት እንጅ መልኩ ብስል ቀይ የሚባል ዓይነት ነው። ከቅጥነቱ የተነሳ ጉንጮቹ ጎድጉደዋል። ዐይኖቹ ብርሃን እንዳረፈበት ውሀ የሚያብረቀርቁና ትንንሾች ቢሆኑም፤ ከእኔ የሆነ ነገር መስማት መፈለጉ በፈጠረበት ጉጉት ከጉድጓዳቸው ወጥተው ሊዘረገፉ ደርሰዋል። ደግሜ በልቤ “በዕውነት ሰውዬው ምን ፈልጎ ነው? ይሄን ያህል ጠልቆ ዘር ማንዘሬን የሚጠይቀኝ” እያልኩ ነግሬው ልገላገል በሚል፤
“የአሊ አማኑ ልጅ ናት!” ስል ጭንቅላቱን ይዞ ብድግ በማለት፤
“አውቄዋለሁ! ሥጋዬ ነግሮኛል! ወ ን ድ ሜ” እያለ እየጮኸ በላዬ ላይ ተከመረብኝ።
በዚያ ሰዓት በእኔ ቦታ አያኑራችሁ። እንኳን እኔ ጓደኞቹ ሁሉ ግራ ተጋብተዋል። እንደምንም ከኔ ላይ ሊያላቅቁት እየሞከሩ፤
“እስቲ ቆይ አሰፋ ተረጋጋ፣ ልጁንም እኮ ግራ አጋባኸው፣ ምንድነው የሆንከው?” ሲሉት፤
“አሁን ይሄንን ማን ያምናል?! እኔ ገና ሳየው እኮ ነው ያወቅኩት ...ልቤ ነግሮኛል ...ልክ አይዬን ራሱን እኮ ነው የሚመስለው” ሲል፤
“እ!” ብዬ እኔም ብድግ አልኩና፤
“አይዬን? ማነው አይዬ” አልኩት፤
“አሊ አማኑ ጎበዜ!” አለኝ።
አያቴን ቤተሰቡ ሁሉ አይዬ ነው የሚለው። እኛም እናታችን በምትጠራበት “አይዬ” ነው የምንለው። ሳላስበው ዕንባዬ ድንገት ተዘረገፈ። እና እንደምንም፤
“እና አንተ ማነህ?” አልኩት፤
“ይመር ፈለቀ!”
“ይመር ፈለቀ ...አሰፋ ነኝ አላልከኝም እንዴ?” አልኩት ኮስተር እንደማለት ብዬ፤
“እሱ ሌላ ታሪክ ነው! ወታደር ቤት ስገባ ነው የቀየርኩት”
“እና አንተ የየሺ ፈለቀ ወንድም ...የፈለቀ አማኑ ልጅ...!” ብዬ ሳልጨርስ በልቅሶ ተቃቅፈን ቤቱን ትኩስ መርዶ የተረዳበት
ቦታ አስመሰልነው። ከዚህም ከዚያም ሰዎች ተሰበሰቡ። ጉድ ተባለ። የሠራዊቱ አባላት እንኳን እንዲህ ያለ ነገር አግኝተው እንዲያውም እንዲያው ናቸውና “ወንድማማቾች ተገናኙ” ተብሎ ...የደስ ደሱን ከግራ ከቀኝ መሎቲውን በሣጥን በሣጥን ያወርዱት ጀምር፣ ታላቅ ፌሽታም ሆነ።
አሰፋ መሐል ላይ ከደስታው መለስ ሲል፤
“እስቲ ተመልከቱት አንመሳሰልም? ቁርጥ አይዬን አሊ አማኑን እኮ ነው” እያለ ጓደኞቹ የማያውቁትን አሊ አማኑን መምሰሌን ያረጋግጡለት ዘንድ አገጬን ከግራ ቀኝ እያገላበጠ ያሳያቸው ገባ። እውነቱን ነው፤ እሱም ቁመቱ ከማጠሩ በስተቀር የፊት ገጽታው ቁርጥ አያቴን አሊ አማኑን ነው የሚመስለው። ልብ ብሎ ላየንም ስጋ ዘመድ መሆናችን ያስታውቃል።
ከእናቴ ጋር የወንድማማች ልጆች ናቸው፤ እውነተኛ ስሙ ይመር ፈለቀ የሚባልና የጠፋው የእናቴ አጎት የፈለቀ አማኑ ልጅ ሆኖ ተገኘ። ለካስ የአገራችን የወሎ ሰው “የአላህን መኖር እንዴት ታውቃለህ ሲሉት፤ አላሰብኩት ቦታ ሲያውለኝ” አለ የተባለው እንዲህ ያለው ገጥሞት ኖሯልና።
እናም የቁም የፖለቲካ እስረኛ በሆንኩበት ዘመን አሥመራ መሐል፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የሥጋ ዘመድ የሚባል ነገርን በእንዲህ ዓይነት ልቦለድ በሚመስልና በማይታመን አጋጣሚ አገኘሁ። በዚያው ቀንም “ቤተሰብህን ሳታይማ አታድርም” ብሎ ቃኘው ስቴሽን ታንከኛ ሻለቃ ባለጓዝ ሰፈር ይዞኝ ሄደ። ከባለቤቱና ከሁለት ልጆቹም ጋር ተዋውቄ ባላሰብኩት ደስታ ተጥለቀለቅኩ። ባንድ ቀንም “አጎቴ!” በመባል መጠራት ጀመርኩ። በዚህ ምክንያትም እኔ ከቤተሰቦቼ ጋር በየጊዜው በደብዳቤም በስልክም እገናኝ ስለነበር ሁኔታውን ዘርዝሬ ለእናቴ በኤሮግራም ላኩላት። ሞቷል ብሎ ተስፋ የቆረጠው ቤተሰብ ሁሉ ተስፋም አንሠራራ።
አሰፋና (ይመር ፈለቀ) ቤተሰቡ ኤርትራ በሻዕቢያ እጅ ስትወድቅ ከእልቂት ተርፈው አዲስ አበባ ከገቡት የቀድሞ ሠራዊት አባላትና ቤተሰቦች መካከል ነበሩ። ባለቤቱ ልጆቿን ይዛ እዚህ አዲስ አበባ መገናኛ አካባቢ ዘመዶቿ ጋር ስትቀር፤ እሱም ወሎ “ሐይቅ” ሔዶ ከእህቱ የሺ ፈለቀና ከዘመዶቻችን መሐል ኑሮውን ቀጠሎ ከጥቂት አመታት በፊት አለፈ።
(ሁለገቡ የኪነጥበብ ባለሙያ ተስፋዬ ማሞ ሰሞኑን ለንባብ ካበቃው “ከማዕበል ማዶ” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ የተቀነጨበ)
ሚስት የራሱ ጉዳይ ስትል፣ ባል ቸል ሲል፣ ቤቱ ለውሻ ይቀራል
በሞንጎሊያ ከተማ ከብዙ አመታት በፊት ተስቦ ገብቶ ብዙ ሺ ህዝብ ፈጀ፡፡ ጤነኞቹ በሽተኞቹን እየጣሉ ሸሹ፡፡ እንዲህም አሉ፡፡
“እጣ ፈንታ እራሱ’ኮ ኗሪውን ከሚሞተው ያበጥረዋል”
ያን ቦታ ለቅቀው ከሄዱት መካከል ታሪቫ የተባለ የ15 ዓመት ልጅ ይገኝበታል፡፡
የታሪቫ ነብስ ስጋውን ለቅቃ ከሞቱት የሬሳ ክምሮች መካከል አቋርጣ ወደ ደቡብ ሄደች፡፡
በመጨረሻም የገሃነም ኃላፊ ዘንድ ደረሰች፡፡ ኃላፊውም በመገረም፤
“ስጋሽ ገና ህይወት አልባ ሳይሆንና እየተነፈስሽ ሳለ ለምን ጥለሽው መጣሽ? ሲል ጠየቃት ነብሲቱን፡፡
የታሪቫ ነብስም፡-
“ጌታዬ ነዋሪዎቹ ሁሉ ስጋዬ እንደሞተ ነው የተገነዘቡት፡፡ ስለዚህ እኔ ለአንተ ታማኝነቴን ለመግለፅ ነው የመጣሁት፡፡“
የገሃነሙ ኃላፊ ከታሪቫ ነብስ በሰማው በጣም ተገረመና፤ “ታሪቫ የአንተ ጊዜ እንዳልደረሰ አረጋግጥልሀለሁ፡፡ ስለዚህ የእኔን ፈጣን ፈረስ ውሰድና በወፎች ግዛት ወዳለው ጌታ ሂድ፡፡ ሆኖም ሳትሄድ በፊት ከዚህ አንድ የፈለግከውን ነገር ይዘህ ለመሄድ እንድትችል የመምረጥ እድል እሰጥሀለሁ፡፡ ግን ተጠንቀቅ! እዚህ ሀብት፣ መልካም እድል፣ ጤና፣ ናፍቆት፣ ሀዘን፣ ለቅሶ፣ ብልህነት፣ ጉጉትና ምስጋና ሁሉ አሉ፡፡ ና ከነዚህ ሁሉ አንዱን ምረጥ፡፡”
“ጌታዬ እኔ የምመርጠው ታሪኮቹንና ተረቶቹን ነው” አለው፡፡ ከዚያም ታሪኮቹንና ተረቶቹን ሁሉ በኮሮጆ አጨቀለትና ፈጣን ፈረሱን ይዞ ፈረጠጠ፡፡ እዚያ ሲደርስ አንድ ቁራ ከስጋ-አካሉ አይኑን ፈልፍሎ አውጥቶ ወስዶት ደረሰ፡፡ በመሆኑም ሥጋ-አካሉ ታወረ፡፡ ታሪቫ ወደሬሳዎቹ ክምችት ተመልሶ ለመሄድ አልደፈረም፡፡ ስለሆነም ያንኑ የጥንቱን የገዛ ስጋውን ለበሰ፡፡
ከዚያን ጊዜ ወዲህ አይነ-ሥውር ሆኖ መኖር ጀመረ፡፡ ያም ሆኖ በመቶ ለሚቆጠሩ አመታት በሞንጎሊያ ምድር በፈረስ ከአልዩ ተራሮች በስተምእራብ፣ ወደ ደቡብ እስከ ጉቢ በረሀ እስከ ሀንቴ ኑራ ድረስ እየተዘዋወረ፣ ተረቶችን እየተናገረ፣ የወደፊቱን እየተነበየ ለጎሳዎች አገራቸውን መልካም ለማድረግ ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ሲያስተምር ኖረ፡፡ እንግዲህ ከዚያ ወዲህ ነው ሞንጎላውያን አንዱ ለሌላው ተረት መንገር የጀመሩት ይባላል፡፡
“እስቲ እንደ ታሪቫ ወደ ደቡብ ልሂድ፡፡ በእውነተኛው ኑሮዬ ውስጥ የረባ መመሪያ ካጣሁ ምናልባት በአፈ- ታሪኮቹ ውስጥ አገኝ ይሆናል” የሚሉት ለዚህ ነው፡፡
* * *
ነዋሪው ህዝብ ስጋህ ሞቷል፡፡ ነብስህንም ለሲኦል አዘጋጃት ከሚልበት ክፉ ጊዜ ይሰውረን፡፡ ጊዜያችን ሳይደርስ ሞተናል ከማለት፣ ጊዜያችን ደርሶም “አለሁ ዘራፍ” ከማለት ይሰውረን፡፡ በባህላችን ውስጥ ያለውን ትልቁ-እሴት የምናይበት አይን እንዳናጣ እንጠንቀቅ፡፡ መልካሙን ነገር ለማየት የግድ ሲኦል ደጃፍ መድረስ የለብንም፡፡ ዛሬ ውሎዬ እንዴት ነበር ብለን እራሳችንን እንጠይቅ፡፡ ዛሬ ግፍ የተሞላ ቀን ውለን ከሆነ፣ ለነገ ራሳችንን ወቅሰን ንስሀ ገብተን እንዘጋጅ፡፡ ታሪኮቻችንና ተረቶቻችን ቅርሶቻችን ናቸው፡፡ ሁሉም መሬት የረገጠ እውነታ ጭማቂዎች ናቸው፡፡ የውሏችን አሻራ ናቸው፡፡ የሚነግሩንን ልብ ማለት ብቻ ሳይሆን መተግበርም ይጠበቅብናል፡፡ የተወሳሰበ ጭንቅላት ውስጥ በቀላሉ መግባት የሚችሉትን ያህል፣ ጭንጫ-ድፍን ልብንም አረስርሰው ሊሰርጉበት ይችላሉ፡፡ የየእለት ውሎአችን ንጥር ውጤቶች በመሆናቸውም፣ እውነቱን ገላጭ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ የህብረተሰቡን ቅርፊቱን ሳይሆን ቡጡን የማሳየት ሀይል አላቸው፡፡ እንደሞንጎሎች የወደፊቱን ለመተንበይና ጎሳዎች አገራቸውን መልካም ለማድረግ ምን መፈፀም እንደሚገባቸው እንናገርባቸዋለን፡፡ እንደሞንጎሎች በእውነተኛው ኑሮ ውስጥ ረብ ያለው መርህ ሲታጣ፣ አፈታሪኮቹ ውስጥ ለማግኘትም ይቻል ይሆናል ማለት አይከፋም፡፡
ለሀገር ህልውናና ለህዝብ ብልፅግና አንዳች ነገር ማገዝ አለብኝ ያለ ሁሉ አስቀድሞ አቅሙን ከልቡናው ጋር ማስታረቅ አለበት፡፡ አለበለዚያ ልብ ወዲህ አቅም ወዲያ ይሆንና ለፍቶ -መና መሆን ይከተላል፡፡ “ክረምት የሚያወጣን ቁርስና ዳገት የሚያወጣን ጉልበት ባለቤቱ ያቀዋል” ይባላል፡፡ በሀገራችን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ መንግስታዊ ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ድርጅታዊ ሃይሎች ሁሉ ቁርሳቸውንና ጉልበታቸው መመርመርና ዳግም ማየት ይገባቸዋል፡፡ የያዙትን ህዝባዊ አቅም አጥርተው ማወቅ አለባቸው፡፡ የህዝብ ድጋፍ ሲባል እውነተኛ የህዝብ ድጋፍ መሆኑንም ልብ ማለት ይኖርባቸዋል፡፡ ከዳር-አገር እስከ ማህል-አገር ያለውን ህዝብ እንደምን ልብ ለልብ አግባባዋለሁ ማለት ይገባቸዋል፡፡ ትላንት የደገፈኝ ዛሬ ሊገፋኝ ይችላል ብለው ማጤን ይኖርባቸዋል፡፡ ትላንት አለህ ያለኝ ዛሬ ሞተሃል ቢለኝስ ብሎ ማውጠንጠን ተገቢ ነው፡፡ ስህተትን፣ ማንነትን፣ የወደፊት ጎዳናን ለማየት ህዝቡስ ምን አለ? ማለት ደግ ነው፡፡ “እረኛ ምን አለ?” እንዲል፡፡
የሀገራችን የፖለቲካ ሰዎችና ቡድኖች ታሪክ በሰፊው እንደሚያስገነዝበው አንዱ ትልቅ እክላቸው መናናቅ ነው፡፡ አንዱ አንዱን ቁልቁል ማየት! ሽማግሌ መሞቱን፣ ልጅ ማደጉን መዘንጋት! እኔ እዚህ እደርሳለሁ፣ ይሄንን አደርጋለሁ ከማለት ይልቅ እነገሌ የትም አይደርሱም ማለት! ትልቅ የማይመስል ግን እጅግ ግዙፍ እክል ነበር፤ ነውም፡፡ አንድ ደራሲ እንዳለው፤ “ልብ ብጉንጅ ካበቀለ መፍረጥ እንጂ ደግ መሆን አይሆንለትም፡፡” ደግ ማሰብ ደግ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ስለ መቻቻል ሲባል፣ ስለ ሰላም ሲባል፣ ስለ ዲሞክራሲ ሲባል፣ ደም ላለመፋሰስ ሲባል ደግ መሆን ያስፈልጋል፡፡ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ብልጭታን የማያደንቅ ልብ ሊኖር ያሻል፡፡ ቀና አስተሳሰብን ማጎልበት ያስፈልጋል፡፡ በመናናቅ፣ አንዱ አንዱን በማኮሰስ ቤት ማፍረስ እንጂ መገንባት ዘበት ነው፡፡ ወላይታዎች “ሚስት የራሱ ጉዳይ ስትል፣ ባል ቸል ሲል፣ ቤቱ ለውሻ ይቀራል፡፡” የሚሉት ለዚህ ነው፡፡ አገር ቤት መሆኗን አንርሳ፡፡
የጃፓን ትዝታዎቼ
በ1984 ዓ.ም አስራ አንድ ወራት ያህል ለሚፈጅ ስልጠና ጃፓን ሀገር ሄጄ ነበር፡፡ በጃፓን ሀገር ቆይታዬ ከማይረሱኝ ትዝታዎቼ መሀከል የተወሰኑትን እነሆ፡፡
ስልጣኔ፡ ሁላችንም እንደምናውቀው ጃፓን፣ የስልጣኔ ማማ ላይ ከደረሱ ጥቂት የአለማችን ሀገሮች አንዷ ናት፡፡ ካስደነቁኝ ነገሮች መሀከል ለማሳያነት ሁለቱን እዚህ ላይ እጠቅሳለሁ፡፡
ትራንስፖርት፡ ከትራንስፖርት ሥርዓታቸው ውስጥ የማነሳው የባቡር ትራንስፖርትን ነው፡፡ የባቡር ትራንስፖርት ሥርዓታቸው እጅግ በጣም የተደራጀና የተሳለጠ ነው፡፡ እኔ የተማርኩት የጃፓን ሁለተኛ ከተማ በሆነችው ኦሳካ ነው፡፡ ጧት ከምኖርበት አፓርታማ በብስክሌት ባቡር ጣቢያ ድረስ እሄዳለሁ፥ ብስክሌቴን እዚያው ባቡር ጣቢያ ውስጥ በሚገኝ የብስክሌት ማቆሚያ ቦታ አቆማትና በባቡር ት/ቤቴ ወደሚገኝበት ኪዮቶ ከተማ እሄዳለሁ፡፡ ብስክሌት በማቆምበት ቦታ ምንም ጠባቂ የለውም፥ በመሆኑም የህዝቡን የታማኝነት ባህል ልብ እንበል፡፡ ባቡር የምይዝበት ሰአት የተወሰነ ነው፡፡ ከዚያ ባቡሩ ምን ያህል ሰአት እንደሚያከብር ለማወቅ አሰብኩኝና ማጥናት ጀመርኩኝ፡፡ በወቅቱ የነበረችኝ ሰአት በጣም ትክክለኛ(very accurate) ነበረች፡፡ ከዚያ አንድ ቀን በስንት ሰአት እኔ ባቡር የምይዝበት ጣቢያ እንደደረሰ መዘገብኩ፥ የመዘገብኩት ሰአቱን፥ ደቂቃውንና ሰከንዱን ነበር፡፡ በመቀጠልም በተከታታይ ቀናት ባቡሩ በጣቢያው ስንት ሰአት እንደደረሰ መዝግቤ መጀመሪያ ከመዘገብኩት ጋር ሳወዳድረው የጥቂት ሰኮንዶች ልዩነት እንኳን አላገኘሁበትም፡፡ ባቡሩ ደግሞ በየ20 ደቂቃው ይመጣል፡፡ በመሆኑም የባቡር አገልግሎት የጊዜ አጠባበቃቸው(time accuracy) በጥቂት ሰኮንዶች የሚለካ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ይህ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ውጤታማነታቸውን ከሀገራችን ሁኔታ ጋር አወዳድሬ ስላየሁት ነው መሰለኝ እጅግ በጣም አደነቅሁት፡፡ ጃፓን ለሚኖር ግለሰብ ለቅንጦት ካልሆነ በስተቀር የግል መኪና መጠቀም አስፈላጊነቱ ብዙም አልታየኝም ያስባለኝን አገልግሎት ነው ያየሁት። ከሀብታቸው፥ ከከተማቸው ዘመናዊነትና ከቁሳዊ ብልፅግናቸው የበለጠ የገረመኝ ለስራ ያላቸው አክብሮትና ለጊዜ የሚሰጡት ዋጋ በጣም ከፍተኛ መሆኑ ነው፡፡ ለነኚህ ሁለት ትልልቅ እሴቶች ያላቸው አክብሮት በባቡር ትራንስፖርት ሥርዓታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ባየኋቸው የስራ ቦታዎች ሁሉ የታዘብኩት ነገር ነው፡፡ የጃፓን ህዝብ የስራ ክቡርነትና የጊዜን ጠቀሜታ በሚገባ ተገንዝቦ እነኚህን እሴቶች ተግባራዊ በማድረጉ፣ በኢኮኖሚ በልፅጎ አሁን የደረሰበት ደረጃ ደርሷል፡፡ እኛስ? እኛም የስራ ክቡርነትና የጊዜን ጥቅም በሚገባ ተረድተን ተግባራዊ ማድረግ ስንጀምር ማደግ አንጀምራለን፡፡ መቼ? ለሚለው ጥያቄ መልሱን ለናንተ ትቼዋለሁ፡፡
የደን ሽፋን፡ የጃፓን የቆዳ ስፋት የኢትዮጵያን ሲሶ ያህል ቢሆን ነው፡፡ ከዚህ የቆዳ ስፋት ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ሰው ሊኖርበት የማይችል ጋራና ተራራ ነው፡፡ በመሆኑም ሰው ሊኖር የሚችልበት መሬት ከቆዳ ስፋቷ 30 በመቶ ላይ ብቻ ነው፡፡ ቶኪዮና ኦሳካን ጨምሮ ትላልቅ ከተሞቿ በአብዛኛው በባህር አጠገብ(Coastal area) የተቆረቆሩ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የህዝብ ብዛቷ ወደ 127 ሚሊዮን ይጠጋል፡፡ የደን ሽፋኗ እኔ በሄድኩበት ወቅት 66% አካባቢ ነበር፡፡ ይህም ማለት ሰው ሊሰፍርበት የማይችለው ጋራና ተራራዎቿ ቢያንስ ከሰማኒያ በመቶ በላይ ሊባል በሚችል ደረጃ በደን የተሸፈነ ነው፡፡ ይህ እውነታ ደግሞ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ በባቡር ሲኬድ በግልፅ የሚታይ ነገር ነው፡፡
የጃፓን ከተሞች ፅዱና የተዋቡ ናቸው፡፡ ፓርኮች በብዛት አሉዋቸው፡፡ ከከተማ በባቡር ወይም በመኪና ሲወጣ የሚታየው በአብዛኛው የሩዝ እርሻ ወይም እርሻ ከሌለ የተፈጥሮ ደን ነው፡፡ ከከተማቸው ባልተናነሰ የገጠሩ አካባቢ ልምላሜ እጅግ በጣም ይማርካል፤ ያስቀናል፡፡ አሁን ያለው የደን ሽፋናቸው ቢያንስ ቢያንስ ከዛሬ ሰላሳ ሁለት ዓመት በፊት ከነበረው 66% እንደማያንስ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የጃፓን መንግስት በፖሊሲው የደን ሽፋኑን በመጠበቁ ብቻ ሳይሆን፣ ህዝቡም ከተፈጥሮ ጋር ተከባብሮ፤ ተጠባብቆና ተዋዶ የመኖር የረዥም ጊዜ ባህል ያለው በመሆኑ ነው፡፡ (በኛም ሀገር የተፈጥሮ ደንን መጠበቅ ባህላቸው የሆኑ ብሄረሰቦች እንዳሉ ይታወቃል፡፡)
ይህ የጃፓን ህዝብ አመለካከት ከሚከተሉት ፍልስፍናና እምነት ጋርም በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ ከተማን ከመገንባት ባሻገር ከተፈጥሮ ጋር ተከባብሮና ተደጋግፎ በመኖር ደኖችን መጠበቅ የስልጣኔ አንዱና ዋናው ምልክት መሆኑን በተግባር ያስመሰከረች ሀገር ናት፥ ጃፓን፡፡ በዚህም ጉዳይ ላይ እኛስ? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በኔ ግምት መልሱ የሚታዩ ጅምሮች አሉ፥ ይሁን እንጂ ብዙ መንገድ ይቀረናል።
የቤተሰብ ስም (Family name)፡ ጃፓን በወሰድኩት ትምህርት ላይ ከ8 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጣን 8 ተማሪዎች ነበርን፡፡ ፕሮግራሙ አስር ተማሪዎች እንዲኖሩት የታቀደ ቢሆንም፥ ከኮንጎ ኪንሻሳ መምጣት የነበረበት ልጅ ሀገሪቱ በእርስ በርስ ጦርነት ላይ ስለነበረች ባለመምጣቱ፥ የዚምባብዌው ልጅ ደግሞ ጃፓን ድረስ መጥቶ ትምህርት ከመጀመራችን በፊት ሙሉ የጤና ምርመራ በተደረገልን ወቅት ከባድ የጤና እክል ስለታየበት ወደሀገሩ እንዲመለስ በመደረጉ ስምንት ተማሪዎች ብቻ ነበርን በስልጠናው ላይ የተሳተፍነው፡፡ የተሳተፍነው ከኢትዮጵያ፥ ኬንያ፥ ታንዛኒያ፥ ሱዳን፥ ማላዊ፥ ዛምቢያ፥ ጋናና ሴኔጋል የተውጣጣን የአፍሪካ ልጆች ነበርን። የእኔና የሱዳኑ ልጅ የቆዳ ቀለማችን፥ የፀጉራችን የከርዳዳነት ደረጃ፥ የአፍንጫና የከንፈራችን ቅርፅ በጣም ተመሳሳይነት ስላለው “መንትዮቹ”፥ “the twins” እያሉን ይጠሩን እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ ወደ ፍሬ ነገሩ ልመለስ፡፡ አንድ ቀን ምሳ በልተን የትምህርት ሰአት እስኪደርስ በመጫወት ላይ እያለን፣ በጨዋታ መሀከል ታንዛኒያዊው ጓደኛዬ፤ “What is your Family name?” “የቤተሰብ ስምህ ማነው?” አለኝ፡፡ እኔም፤ “እኛ ፋሚሊ ኔም የሚባል ነገር የለንም” አልኩት፡፡ ታንዛኒያዊው፤ “እንዴት? ምን ማለትህ ነው?” አለኝ፡፡ እኔም፤ “አንተስ ምን ማለትህ ነው? አልገባኝም” አልኩት፡፡ የሁለታችን ንግግር በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እያለ የቀሩት ስድስቱም ጓደኞቻችን እሱን ደግፈው፤ “እንዴ ምን ማለትህ ነው? እንዴት ፋሚሊ ኔም የለንም ትላለህ?” ብለው አፋጠጡኝ፡፡ ክርክራችን ሰባት ለአንድ ሆነ ማለት ነው፡፡ ወዲያው በውስጤ እንዴት የኔ አመለካከት ከነሱ ተለየ? እኔ ምን ከነሱ የተለየ ያለኝ ወይም የሌለኝ ነገር ኖሮ ነው ሀሳቤ ከሰባቱም ሊለይ የቻለው? ብዬ አሰላሰልኩ፥ ወዲያው ትዝ ሲለኝ ልዩነታችን ገባኝ፡፡ “Famiy name” የሚባለው አጠራር የአፍሪካውያን ባህል ሳይሆን፤ የፈረንጆቹ፥ ማለትም የቅኝ ገዢዎቹ ባህል ነው፡፡ ደግሞም የሁሉም ጓደኞቼ ሀገራት በቅኝ የተገዙ ናቸው፡፡ የኔ ሀገር ግን አልተገዛችም፡፡ ይህ ነው የልዩነታችን መሰረት፡፡ ከዚያ ወኔ ተሰማኝ፡፡ በጣም ጥሩ መከራከሪያና ማሳመኛ ነጥብ አገኘሁ ብዬ አሰብኩ፡፡ ይሄኔ ፍርጥም ብዬ በልበ ሙሉነት፤ “ስሙ ይሄ “Family name” የምትሉት ነገር መሰረቱ ወይም ምንጩ የአፍሪካ ባህል ቢሆን ኖሮና እኔ ባላውቀውና ባህሌ ባይሆንም እንኳን ትልቅ ክብር ይኖረኝ ነበር፥ ነገር ግን የባህል መሰረቱ የፈረንጆቹ ወይም የቅኝ ገዢዎቹ ስለሆነ ብዙ ቦታ አልሰጠውም፥ ምክንያቱም በቅኝ ገዢዎቻችሁ የተጫነባችሁ ነገር ስለሆነ ነው” አልኳቸው፡፡ ቀጠሉናም፤ “ፋሚሊ ኔም ከሌለህ ማንነትህ እንዴት ነው የሚታወቀው?” አሉኝ፡፡ እኔም፤ “ማንነቴ የሚታወቀው በራሴ ስም፥ በአባቴ ስም፥ በአያቴ ስም፥ በእናቴ ስም፥ በተወለድኩበት አካባቢ ወዘተ” ብዬ መለስኩላቸው፡፡ በጣም የገረመኝ ነገር ይህ አባባሌ ሊገባቸው አለመቻሉ ነው፡፡ እዚህ ላይ አንባቢ ልብ ሊለው የሚገባውና የሚያሳዝነው ነገር፣ ሁሉም ጓደኞቼ ፋሚሊ ኔም የሚለውን ስያሜ ልክ እንደራሳቸው ባህልና ቅርስ አድርገው ከማየታቸው የተነሳ እኔ የምላቸው ነገር ፍፁም ሊገባቸው አለመቻሉ ነው፡፡ ይገርማል! ያሳዝናል! እነኚህ አፍሪካዊ ጓደኞቼ የነጩ ባህል በደምስራቸው ውስጥ ገብቶ ከደማቸው ጋር የተዋሀደ መሆኑን በመረዳቴ ሀዘን ተሰማኝ፡፡ በመጨረሻም ብዙ ተከራክረን መስማማት ባለመቻላችን፣ ላለመስማማት ተስማምተን፥ እኔም እነሱም የምናምንበትንና የምናውቀውን ይዘን ወደ ሌላ ጨዋታ ውስጥ ገባን፡፡
ስንቅ፡ ጃፓን በሄድኩበት ወቅት እናቴ ለስንቅ ይሆንሀል ብላኝ በትልቅ አገልግል እኔ ነኝ ያለ ጩኮ አዘጋጅታ ይዤ መሄዴን አስታውሳለሁ፡፡ እናቴ በሴት ልጅ ሙያ እንከን የማይወጣላት ነበረች፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለእናቴ የሚገባትን ዋጋ፥ “credit”፤ ለመስጠት በሚል ስሜት አንድ ነገር አንስቼ ልለፍ፡፡ ከዛሬ 50 አመት በፊት በ1960ዎቹ አጋማሽ አካባቢ እናቴ የምትጥለው ፊልተር ጠጅ በጣም ምርጥና ተወዳጅ ስለነበረ፥ አንድ ሊትር ፊልተር ጠጅ በአንድ ሙሉ ውስኪ የአባቴ ጓደኞችና ዘመዶች እንደተቀያየሩ አስታውሳለሁ፡፡
ከዚያ ዕቃዬን ሸክፌ(pack አድርጌ) ጉዞ ወደ ጃፓን ሆነ፡፡ በአንድ ትልቅ አገልግል በደምብ የታጨቀ ጩኮ ምን ያህል እንደሚከብድ ይታያችሁ፡፡ በኤርፖርቶች ለዕቃ ማመላለሻ የሚያገለግሉ ጋሪዎች ባይኖሩ ጩኮው ወገቤን ይፈትነው ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ በሙምባይና በሆንግኮንግ አድርጌ ቶኪዮ ደረስኩ፡፡ በቶኪዮ ደረጃ ያለ ዘመናዊ ከተማ ሳይ በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር፡፡ የቶኪዮ ኤርፖርት ከመሀል ከተማው በግምት ሰባ ኪሎሜትር የሚርቅ ሲሆን፥ በኤርፖርቱ የደረስኩት ከቀኑ አስራ አንድ ሰአት ላይ ነበር። የኤርፖርት ውስጥ ፍተሻ ጨርሰን ቶኪዮ ከተማ መሀል ስንደርስ መሽቶ ነበርና ከተማዋ በተለያዩ ውብ መብራቶች የተንቆጠቆጠች ሆነችብኝ። በዚያ ምሽትና በወጣትነት አእምሮዬ ያየሁዋት የቶኪዮ ከተማ ምስል እስከዛሬ ከአእምሮዬ አልጠፋም፡፡ ያ የቶኪዮ ምስል በድሮ ዘመን የጎጃም ነጋዴ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ከሀገሩ ተነስቶ እንጦጦ ጫፍ ደርሶ አዲሳባን ሲያያት፤ “እንጦጦ ላይ ሆኜ አዲስን ሳያት ባለፈርጦች ሰማይ መስላ አገኘኋት” ብሎ የገጠመውን ሲያስታውሰኝ ይኖራል።
በመቀጠል ኤርፖርት ውስጥ የመግቢያ ቪዛችንና የያዝነው ዕቃ ሲፈተሽ ፈታሾቹ አገልግሉን ሲያዩ ግራ ገባቸው። ከዚያ ክፈተው አሉኝ፥ ከፈትኩት፥ ጩኮውን ሲያዩ ይበልጥ ግራ ገባቸው፥ ግራ ከመጋባት አልፈው አንድ እኔ ነኝ ያለ ሀሺሽ አስተላላፊ(drug trafficker) የያዙ መስሎዋቸው በጥርጣሬ አይን አዩኝ። “ይሄ ምንድነው?” አሉኝ። “የሀገራችን ባህላዊ ምግብ ነው” አልኳቸው። እነሱ ግን አላመኑኝም። ከዚያ ለምርመራ ለሌላ ሰው አስተላልፈው ሰጡኝና፣ እነሱ የፍተሻ ስራቸውን ቀጠሉ። ወደ ከተማው መግባቴ ቀርቶ ወደ ማረፊያ ሊወስዱኝ ነው ብዬ ፈራሁ፥ አንድ ክፍል ውስጥ አስገብቶ ጩኮውን በአንክሮ ተመለከተው፥ አሸተተው። ከዚያ ፈታሾቹ የጠየቁኝን “ይሄ ምንድነው” የሚለውን ጥያቄ በድጋሚ ጠየቀኝ። እኔም ፍርጥም ብዬ ያለፍርሀት “የሀገራችን የባህል ምግብ ነው” አልኩት። ያልፈራሁት የያዝኩትን ነገር ምንነት ሲረዱ በነፃ እንደሚለቁኝ ስለማውቅ ሲሆን፥ ፈራሁ ብዬ ከላይ የገለፅኩት ደግሞ ምንነቱን እስኪያውቁ ድረስ ሊያጉላሉኝ ይችላሉ ብዬ ነው። የያዝኩት ሀሺሽ-ነክ ነገር ቢሆን ኖሮ “ምን ያለበት ዝላይ አይችልም” እንደሚባለው ሊነቃብኝ ይችል እንደነበር ገመትኩ። “ከምንድነው የሚሰራው?” አለኝ። “ከገብስና ከቂቤ ነው የሚሰራው” አልኩት። “እስቲ ቅመሰው” አለኝ። እኔም በማንኪያ ቀመስኩት። ግራ የመጋባት ነገር ግማሽ ልብ እንዲሆን አስገደደው። በሙሉ ልብ እንዳያምነኝ ጥርጣሬ አእምሮውን ሰቅዞ ያዘው። ከዚያ ንፁህ ቢላ ይዞ መጥቶ ጩኮውን ከሁለት ቦታ ከፍሎ ከውስጡ በማንኪያ ቆንጥሮ በማውጣት እንደገና ቅመሰው አለኝ። እኔም በትዕዛዙ መሰረት ቀመስኩት። ከላይ ያለውና ከውስጥ ያወጣው የተለያየ ቢሆን ኖሮ፣ በዝርዝር እስኪጣራ ድረስ ችግር ይፈጠርብኝ እንደነበረ ተረዳሁ። በመቀጠልም ከአለቃው ጋር ረዘም ላለ ጊዜ በስልክ ከተነጋገረ በኋላ አገልግሉን መልሶ በማሰር ሰጠኝና አሰናበተኝ። እኔም ዕቃዬን ይዤ የሚቀጥለውን ፍተሻ ከጨረስኩ በኋላ በኤርፖርቱ መግቢያ ላይ ሙሉ ስሜን በሰፊ ወረቀት ላይ ፅፎ ከሚጠብቀኝ ሰውዬ ጋር ተገናኝቼ፣ ቶኪዮ በሚገኘው የአለም አቀፍ ሰልጣኝ ተማሪዎች ወደሚያርፉበት ማዕከል ወሰደኝ።
ብርሀኔ ዳምጠው፡
አቶ ብርሀኔ ዳምጠው በኦሳካ ኮቤ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ነው። በ1967 ዓ.ም አካባቢ ጃፓን ለአጭር ጊዜ ስልጠና ሄዶ እዚያው የቀረ ሀበሻ ነው። ሙያው ከመኪና ጥገና ጋር የተገናኘ የቴክኒክ ሙያ በመሆኑ የሚሰራው ከሙያው ጋር በተገናኘ መስክ እንደሆነ አጫውቶኛል።
አቶ ብርሀኔ የሀገሩ ሰው ይናፍቀዋል። እኔ ጃፓን በሄድኩበት ጊዜ አንድ ኢትዮጵያዊ በኦሳካ ኢንተርናሽናል የስልጠና ማዕከል መኖሩን ሰምቶ በማሰልጠኛው የማዞሪያ ስልክ ደውሎ በስልክ ተገናኘን። ከዚያም በአካል በተገናኘንበት ወቅት ስንጨዋወት አልፎ አልፎ ወደማሰልጠኛው ስልክ ይደውልና ኢትዮጵያዊ ሰልጣኝ መኖሩን ካጣራ በኋላ፣ ካለ ደውሎለት በስልክ ያገኘዋል። ከዚያም በአካል አግኝቶት ስለሀገር ቤትም ሆነ ስለተለያዩ ነገሮች ይጫወታሉ። እንደገመትኩት አቶ ብርሀኔ ጃፓን ለስልጠና በሄደበት ዘመን እንኳን ኢትዮጵያዊ ይቅርና ማንኛውንም ጥቁር ሰው በጃፓን ሀገር ውስጥ ማየት ብርቅ ነበር። የዚህን አባባል እውነትነት እኔ በ1984 ዓ.ም. ጃፓን በሄድኩበት ዘመን በአንዳንድ አካባቢዎች እኔንና አፍሪካዊ ጓደኞቼን ሲያዩን እንደብርቅ ያዩን የነበሩ ሰዎች የመኖራቸው ሀቅ ምስክር መሆን ይችላል።
ከላይ በጠቀስኩት ምክንያት ከአቶ ብርሀኔ ጋር ብዙ ጊዜ በአካል ተገናኝተን ተጫውተናል፥ ቤቱም ጋብዞኛል፥ በአፓርታማ ውስጥ ነው የሚኖረው፥ ፓርኮችና የተለያዩ ቦታዎች አስጎብኝቶኛል። አንድ ቀን እሱ በሚኖርባት ኮቤ በምትባል፥ በኦሳካ ከተማ አጠገብ የምትገኝ የወደብ ከተማ ውስጥ ያለ አንድ ጃፓናዊ የሬስቶራንት ባለቤት ጓደኛው ጋ ወስዶ የጋበዘኝ ሾርባ የሚመስል የጃፓን ምግብ እስካሁን አይረሳኝም። ሾርባው ውስጥ ያለው ስጋ ከባህር ውስጥ የሚገኝ የአሳ ዝርያ መሆኑን ነው የነገሩኝ፥ እውነቱን ግን እግዜር ይወቀው፥ ምክንያቱም ቅርፁ የእባብ ስለሚመስል ነው። ስጋው በጣም ለስላሳ ነበር፥ እኔ በምግብ ላይ ብዙ ወግ አጥባቂ ስላልሆንኩ የቀረበልኝ ምግብ በጣም ጣፍጦኝ ነበር የተመገብኩት።
ታዲያ እንደወትሮው አንድ ቀን የሆነ ቦታ ተገናኝተን ሻይ ቡና እየተባባልን እያለ አንድ ፍፁም ያልጠበቅሁት ነገር ተፈጠረ። በጨዋታ ድባብ ውስጥ የነበረው የአቶ ብርሀኔ ፊት ቀስ በቀስ ተለውጦ በሀሳብ ባህር ውስጥ ሲሰምጥ ታየኝ። “አቶ ብርሀኔ ምን ሆንክ? ደህና አይደለህም እንዴ?” አልኩት። እሱም ምንም መልስ ሳይሰጠኝ አንገቱን ደፋ ከአደረገ በኋላ ቀና ብሎ ምንም ሳልጠብቀው እንባ በግራና በቀኝ ጉንጮቹ እየወረዱ ስቅስቅ ብሎ ማልቀስ ጀመረ። እየሆነ ያለው ነገር ፍፁም ሊገባኝ አልቻለም። ግራ ገባኝ። “አቶ ብርሀኔ ምን ሆንክ? ለምንድነው የምታለቅሰው?” አልኩት፤በድጋሚ።
አቶ ብርሀኔ ገዘፍ ያለ መልከመልካም ጠይም ሰው ነው። ከኔ በግምት አስር አመት ይበልጠኛል። በዚህ ላይ ስልጠናውን ከጨረሰ በኋላ በታወቀ የጃፓን የመኪና አምራች ኩባንያ ውስጥ ሲሰራ ቆይቶ ከሙያው ጋር የተገናኘ የግል ስራ እንደሚሰራ አጫውቶኛል። ስራው መኪኖችን ወደ ጎረቤት የእስያ ሀገራት መሸጥ ነበር። በጣም ጥሩ ገቢ ያለው ሰው መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነገር ነው። ታዲያ ከአፍሪካ የሄደ እንደኔ አይነቱ ቺስታ እንዴት ብዬ፣ ይህ ሰው ስቅስቅ ብሎ ያለቅሳል ብዬ ልገምት? አቶ ብርሀኔ ለቅሶው ቀለል ሲለው የሚከተለውን አጫወተኝ። “እኔ እዚህ ጃፓን ላለፈው 17 አመታት ኖሬያለሁ፥ በዚህ ዘመን ውስጥ ትምህርቴን ጨርሼ በታወቀ ኩባንያ ውስጥ ጥሩ ስራ ነበረኝ፥ ከዚያ የራሴን የግል ስራ ጀምሬ ጥሩ ገቢ ማግኘት ችያለሁ፥ ምንም የኢኮኖሚ ችግር የለብኝም፥ ከራሴ አልፌ ለሰው የምተርፍ ነኝ። ነገር ግን ይሄን ያህል ዘመን እዚህ ሀገር ውስጥ ስኖር ጃፓንን እንደራሴ ሀገር አላያትም፥ የትም ቦታ ስሄድ የሚያጋጥመኝ ሰው እንደ አዲስ የሀገሩ ሰው ነው የሚያየኝ ወይም የሚቀበለኝ፤ ይህ ሁኔታ የባይተዋርነት ስሜት እንዲያድርብኝ አደረገኝ፥ ለዚህ ነው ሆድ ብሶኝ ያለቀስኩት” አለኝ።
አቶ ብርሀኔ ሀበሻና ሌሎች ጥቁሮች በብዛት በሚገኙበት በምዕራባውያን ሀገሮች፥ ለምሳሌ አሜሪካና እንግሊዝ፥ ውስጥ የሚኖር ቢሆን ኖሮ፣ ይህ የባይተዋርነት ስሜት አይሰማውም ነበር። አቶ ብርሀኔን ሆድ አስብሶት እስከማልቀስ ያደረሰው የስነ ልቦና ችግር እንደሆነ ገባኝ። አቶ ብርሀኔ ለሀገሪቱ በፈረንጆቹ አባባል “belongingness” አልነበረውም ማለት ነው። ይህ ተሞክሮ በዚያ የወጣትነት እድሜዬ አንድ ትልቅ ትምህርት አስተምሮኝ አለፈ፥ ሀብትና ገንዘብ ብቻ ለሰው ልጅ ምንም ነገር እንደማይፈይዱ። የታወቀው የማኔጅመንት ምሁር አብርሀም ማስሎው፤ “Hierarchy of needs” ብሎ ካስቀመጣቸው መሀከል አቶ ብርሀኔ በተሰማው የባይተዋርነት ስሜት ምክንያት የተሟላ “safety” (ደህንነት) እና “love” (ፍቅር) ስላልነበረው ሆድ አስብሶት ተንሰቅስቆ እንዲያለቅስ አደረገው።
ምግብ፡ የጃፓን ምግብ በአብዛኛው አትክልት፥ ቅጠላቅጠልና የባህር ምግቦች ናቸው። የራሳቸው የምግብ ማጣፈጫ(sauce) አላቸው። አንዳንድ የምግብ ማጣፈጫዎቻቸው ጣዕም ለየት ስለሚሉ በአማርኛ ቃላት ላገኝላቸው ባለመቻሌ ጣዕሙ ምን አይነት እንደሆነ ለሰው ለመግለፅ በወቅቱ አስቸግሮኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። በሂደት ግን ምግባቸውን ለምጄ በጣም ወድጄው አረፍኩት። ሀገር ቤት ከተመለስኩ በኋላ የጃፓን አሉምኒ አሶሲዬሽን ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ስለነበርኩ (በአንድ ወቅት የአሶሲዬሽኑ ፕሬዚደንት ሆኜ አገልግያለሁ)፣ አልፎ አልፎ እዚህ ያለው የጃፓን ኤምባሲ ግብዣ ይጠራን ነበርና፣ እንደሱሺ አይነቱን የጃፓን ምግብ በኤምባሲው ውስጥ በሚጋብዙን ወቅት በጣም በፍቅር ነበር እበላ የነበረው። (ሱሺ ባህር ውስጥ በሚገኝ ቅጠል መሰል አልጌ የተጠቀለለ አሳና ሩዝ ያለበት የጃፓን ምግብ ነው። አረንጓዴው አልጌ “Spirulina” የሚባለውና የምግብ ይዘቱ በጣም ከፍተኛ የሆነ ምግብ ነው፥ የምግብ ይዘቱ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ውጪ ሀገር በታብሌት መልክ በየሱፐርማርኬቶቹ ይሸጣል፥ እኔ አላጋጠመኝም እንጂ በኛ ሀገርም ሊገኝ ይችላል)።
ምግባቸው ጨው፥ ስኳርና የከብት ቅባት(ቅቤና ጮማ) ስለሌለበት ለጤና በጣም ተስማሚ መሆኑን እመሰክራለሁ። የጃፓን ህዝብ በአለም ላይ ረዥም ዕድሜ ከሚኖሩ ህዝቦች መሀከል በአንደኝነት የሚጠቀስ የመሆኑ ሚስጥር በዋናነት በሚበሉት ምግብ እንደሆነ የተረጋገጠ ነገር ነው። ከምግብ ጋር የተያያዘ ሌላ ነገር ላንሳ። ከጓደኞቼ ጋር አንድ ቀን ምሳ እየበላን በነበረበት ወቅት አንዱ ጓደኛዬ ትኩር ብሎ አየኝ። አበላሌ ከሌሎቹ የተለየ አልነበረም፥ ገበታ አስደንጋጭ የምባል አይነት ሰውም አይደለሁም፤ ኖርማል አበላል ነበር የምበላው፥ እየበላን የነበረውም የተለመደ ምግብ ነው፡፡ ጓደኛዬ፤ “እዚህ አሁን እንዲህ እንደልብህ እየበላህ ሆድህን አስፍተህ ሀገርህ ስትመለስ ምን ትበላ ይሆን?” አለኝ። ምናልባት ሌላ ሰው እንዲህ ቢባል ቢያንስ ሊናደድ ወይም ሊጣላ ይችል ነበር። የኛ ሰው ውጪ ሀገር ሲሄድ የዚህ አይነት ነገር እንደሚያጋጥመው ጠንቅቄ አውቃለሁ፥ በተለይ እኔ ጃፓን የሄድኩበት ዘመን ከ1977ቱ ረሀብ 7 አመት ብቻ ስለሚራራቅና በወቅቱ የነበረው የሀገራችን ረሀብ ትዝታ ትኩስ ስለነበረ የዚህ አይነት ነገር ቢያጋጥም አይገርምም። በመሆኑም ጥያቄው ብዙ አልገረመኝም፥ ወይም አልተናደድኩም። እኔም በምላሼ፤ “ኢትዮጵያ ተራበች ሲባልኮ ሁሉ ቦታ ረሀብ አለ ማለት አይደለም፤ ረሀብ የነበረው በሰሜኑ ክፍል ነበር” አልኩት። እሱም(ሌሎቹም አብረው) “ሰሜኑም ይሁን ደቡቡ እኛ የምናውቀው ኢትዮጵያ ረሀብተኛና ችጋራም መሆንዋን ነው” ብለው ረሀብተኛነታችንን ለመሸፋፈን የፈለግሁ አስመሰሉኝ፡፡ ኢትዮጵያ ተራበች ሲባል ህዝቡ በሙሉ በጠኔ ያለቀ አስመስሎ የማቅረብ አባዜ አለባቸው፤ የምዕራብ ዘመም አመለካከት ያለባቸው የውጪ ዜጎች። በሌላ ጊዜ ደግሞ ታንዛኒያዊው ጓደኛዬ፤ “እኔ ሁልጊዜ ግርም የሚለኝ ሆዳችሁን መሙላት ሳትችሉ ኢትዮጵያ አየር መንገድን የመሰለ ኩባንያ እንዴት መመስረት እንደቻላችሁ ነው!” አለኝ። የዚህ አይነት ክብረ-ነክ ጥያቄዎች በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ያጋጥማሉ፥ ኢትዮጵያዊ ከሆንክ።
መቻያ ትዕግስቱን ካልሰጠህ አስቸጋሪ ነው። ትልቁ ቁምነገር በምትጠየቀው እነኚህን መሰል ጥያቄዎች ምክንያት የሚሰማህ ስሜትና የምትመልሰው መልስ ነው። የሚሰማህ ስሜትና የምትመልሰው መልስ አይነት ያንተን የውስጥ ጥንካሬ መለኪያ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ ቪክቶር ፍራንኬል የተባሉ ታላቅ ሰው ያሉትን አስታወሰኝ፤ “You cannot control what happens to you in your life; but you can always control what you will feel and do about what happens to you.” “በህይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙ ነገሮችን መቆጣጠር አትችልም፥ ነገር ግን በአንተ ላይ በሚያጋጥሙ ነገሮች ምክንያት የሚሰማህን ስሜትና የምትወስደውን ርምጃ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ትችላለህ።” ይህን አባባል እንደ አንድ የህይወታችን መመሪያ ወስደን ብንተገብረው ይጠቅመናል።
(ይቀጥላል)
በካፋ ማሽቃሮ (መስቀል) በድምቀት ይከበራል
የማሽቃሬ ባሮ (የመስቀል በዓል) በካፋ ዞን በአደባባይ ከሚከበሩ ደማቅ በዓላት መካከል ዋንኛው ነው፤ የበዓሉ ተሳታፊዎች ደግሞ ከማንኛውም የሐይማኖት ተቋማት የተውጣጡ ታዳሚዎች ሲሆኑ፣ በዕድሜ ያልተገደበ፣ በጾታ ያልተወሰነ እና ሁሉን የሚያሳትፍ በዓል እንደሆነ ይታወቃል።
በዓሉን በአደባባይ ማክበር የተጀመረው ከዛሬ 150 ዓመታት በፊት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፤ የበዓሉ ዋና ዓላማ ጭጋጋማው ወር መገባደዱን፣ ጭፍና በፍካት መተካቱን፣ ዝናብ በጸዳልና ፍካት መወረሱን እና የእርሻ ወቅት መጠናቀቁን አስመልክቶ ከንጉሡ ምርቃትን ለመቀበል የመሰባሰቢያ በዓል ነው፡፡ በዓሉ፣ ከካፋ ዞን፣ ከክልሉ እና ከሌሎች የአገራችን አካባቢዎች በመጡ ታዳሚዎች በቦንጋ ከተማ በሚገኝ ቦንጌ ሻንቤቶ በተባለ ስፍራ ይከበራል።
ዘንድሮም በዓሉ የሚከበረው በመስከረም 12 እና 13 ሲሆን፣ የተለያዩ የካፋ ሕዝቦች ታሪክ፣ የጥንት የጦርነት ይትባሃል፣ ትውፊት፣ ሙዚቃ፣ ጥንታዊ የፖለቲካዊ አስተዳደር፣ አንትሮፖሎጂ፣ የእርቅ ሥነ-ሥርዐት፣ እርሻ፣ የአዝመራ ቀመር፣ ባሕል፣ አመጋገብ፣ ባሕላዊ መጠጦች እና ሌሎች የካፋ ሕዝቦች መገለጫዎች ይዘከራሉ፤ ለአገራችን ሠላም፣ ለከብቱ ጤና፣ ለቀዬውና ለሰብሉ ማማር እና ለመልካም ዕድል ምርቃት ይያዛል።
የካፋ ሕዝብ በደቡብ ምዕራብ ክልል ከሚገኙ ሕዝቦች መካከል አንዱ ሲሆን፣ የመናገሻ ከተማዋ የቦንጋ ከተማ ከአዲስ አበባ በ460 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል፤ የካፋ ዞን የአረቢካ ቡና መገኛ መሆኑን የታሪክ አሳሾች፣ ተመራማሪዎች፣ ተጓዦች እና ሌሎች ግለሰቦች እማኝ ሆነዋል፤ ከ7ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ቡና የእለት ፍጆታ፣ አነቃቂ እና ፍቱን መድኀኒት ሆኖ ሲያገለግል ኖሯል፤ አገራችን ኢትዮጵያ ለሰው ልጆች ካበረከተቻቸው ገጸ-በረከቶች መካከል የካፋ ቡና አንዱ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ፤ የካፋ ዞን በጫካ ማር፣ በግዙፍ በግ፣ በዝባድ፣ በሻይና ቅመማ ቅመም፣ በእንሰት ምርትና በተለያዩ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች የታወቀ ነው፡፡