Administrator

Administrator

በ2023ቱ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ10,000 ሜትር ፍፃሜ ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ለሀገራችን የመጀመሪያ ሜዳልያ ተከታትለው በመግባት ማስመዝገብ ችለዋል።

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ ውድድሩን በበላይነት ስታጠናቅቅ ለተሰንበት ግደይ ሁለተኛ እጅጋየሁ ታዬ  ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል።

አዳዲስ ቴክሎጂዎችን ቀድሞ በማስተዋወቅና “ምንጊዜም አንድ እርምጃ ቀዳሚ” በሚለው መሪ ቃሉ የሚታወቀው ዳሽን ባንክ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ለውጪ ተጓዦች የሚያገለግል ዓለም አቀፍ ቨርቹዋል የመገበያያ ካርድ ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር አስተዋወቀ።
ካርዱ እስከዛሬ ከተለመደውና በስም ከሚታተመው የፕላስቲክ ካርድ የተለየና በሰማያዊ መደብ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በተለይ ወደ ውጪ ሀገር የሚጓዙ ደንበኞች እንደ ልባቸው የሚገበያዩበት ሲሆን፤ በአገር ውስጥም ሆነው ዶላር ወደ ኢትዮጵያ ብር መመንዘር፣ መገበያየት፣ ያላቸውን ትራንዛክሽን ማወቅና ሁሉን ማድረግ ያስቻላቸው ተብሏል። ካርዱ አንዴ ለደንበኞች ከተሰጠ በኋላ የምስጢር ቁጥሮቹን ለመቀየር ወይም ቢሰረቅ ወዲያው አገልግሎት እንዲያቆም ለማድረግና ሌሎችም የደህንነት መጠበቂያዎች የተሰሩለት ስለመሆኑ በካርዱ ማስተዋወቂያ  ሥነ-ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የዳሽን ባንክ ዋና ሥራ አስፈፀሚ አቶ አስፋው አለሙ ተናግረዋል።
ደንበኞች ካርዱን አንዴ ካገኙ በኋላ የሞሉት ገንዘብ ቢያልቅ ካርዱን መቀየር ሳያስፈልጋቸው እንደገና መሙላት እንደሚችሉ የገለፁት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ በአጠቃላይ ይህ ካርድ ከባቢያዊ ሁኔታን ያገናዘበና ሁኔታዎችን ቀላልና ምቹ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ይህንን ካርድ ለማግኘት ወደ ውጪ ተጓዥ መሆን፣ የዳሽን ባንክ አካውንት ያለው መሆን፣ የጉዞ ቪዛ ፓስፖርትና አውሮፕላን ትኬት ይዞ መቅረብ የሚያስፈልግ ሲሆን፤ በዚህ ካርድ በኢ-ኮሜርስ  (በበይነ መረብ) ከአማዞንና ከሌሎችም የኦንላይ የመገበያያ መድረኮች ግብይት መፈፀም  የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል።
የማስተር ካርድ ፔይመንት ጌትዌይ ካርድን ነጋዴዎች መጠቀም ካስፈለጋቸው፣ ህጋዊ ዌብሳይት (ድረ-ገጽ)፣ ሞባይል መተግበሪያ፣ የነጋዴው ድርጅት በህጋዊ መንገድ የሚሰራ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ የኢንሳ  ሰርትፍኬትና ዳሽን ባንክና ነጋዴው የሚግባቡበት የመብት ግዴታ የውል ስምምነት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተገልጿል።
በማስተዋወቂያ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የማስተር ካርድ የምስራቅ አፍሪካ የኢትዮጵያ ተጠሪ ሽህርያር አሊ ባደረጉት ንግግር እንዳብራሩት፤ ማስተር ካርድ ከዳሽን ባንክ ጋር ያደረገው ጥምረት በኢትዮጵያ እንደ አለም አቀፍ ካርድ ያሉ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ማህበረሰቡ ይበልጥ የዲጅታል አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከፍተኛ ሚና እንደሚያበረክት ተናግረዋል።
በዳሽን ባንክ የቅድመ ክፍያ ማስተር ካርድ ደንበኞች ከኤቲኤምና ከፖስት ማሽን በተጨማሪ በኢ-ኮሜርስ ክፍያ መክፈል ይችላሉ ተብሏል።
ዳሽን ባንክና ማስተር ካርድ ከካርዱ በተጨማሪ የንግድ ተቋማት ክፍያቸውን በበይነ መረብ ከየትኛውም የዓለም ክፍል መቀበል የሚያስችል የማስተር ካርድ ክፍያ መቀበያ ማስተር ካርድ ጌትዌይ ሲስተም ያለው ሲሆን በአጠቃላይ ካርዱ ሶስት አይነት አገልግሎቶችን በአንድ ላይ የያዘ ዘመናዊና የተለያየ አማራጭ ያለው ስለመሆኑ ተብራርቷል።
ዳሽን ባንክ በዚህ የማስተር ካርድ ፕሮጀክትና በቴክኒክ ስራ ላይ ለተሳተፉ ሰራተኞቹ እውቅናና ሽልማት አበርክቷል። ማስተር ካርድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ210 አገራት ውስጥ ክፍያ የሚፈጸምና ከ1.9 ቢሊዮን በላይ ደንበኞችን ያፈራ መሆኑ ተገልጿል።

Saturday, 19 August 2023 20:22

ኢትዮጵያ አሸነፈች‼️

በቡዳፔስት የአለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች የፍፃሜ ውድድር የወርቅ፣ የብር እና የነሃስ ሜዳሊያዎች አገኘች።
ጉዳፍ - ወርቅ
ለተሰንበት - ብር
እጅጋየሁ - ነሃስ

የሃንጋሪዋ መዲና ቡዳፔስት የምታስተናግደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ይጀመራል። ከ201 አገራት የተውጣጡ ከ2100 በላይ አትሌቶች የሚሳተፋበት ሻምፒዮናው በዝግጅት ጥራትና በስፖርት መሰረት ልማቶቹ የላቀ ደረጃ ተሰጥቶታል። ሻምፒዮናው የሚካሄድበት National Athletics center ብሄራዊ የአትሌቲክስ ማዕከል በ75ሺ ስኩ.ሜ ላይ ያረፈ ዘመናዊ ስታድየም ነው። በዳኑቤ ወንዝ ዳርቻ ላይ የተገነባው ስታድዬሙ በሻምፒዮናው ወቅት ከ36ሺ በላይ ተመልካች የሚያስተናግድ ይሆናል። ከሻምፒዮናው በኋላ ደግሞ 15ሺ ተመልካች ብቻ የሚይዝ የአትሌቲክ ስታድዬም ሆኖ እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡ ስታድዬሙን ለመገንባት ከ9600 ቶን በላይ ብረት ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፤ ዙርያውን 62 ሺ ስኩዌር ሜትር በአረንጓዴ ፓርክ የተሸፈነ ነው። በሁለት የሐንጋሪ ኩባንያዎች ጥምረት የተገነባው ይህ የስፖርትና መዝናኛ ፓርክ ከ658 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ወጭ የተደረገበት ሲሆን ዲዛይኑን የሰራው ናፑር አርክቴክት የተባለ ኩባንያ የተከፈለው 14 ሚሊዮን ዮሮ ነው፡፡
አትሌቲክስ በሃንጋሪ ከ125 ዓመታት በላይ ታሪክ እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ። በምስራቅ አውሮፓ በስፖርት ቱሪዝም እየገነነች የመጣችው ሃንጋሪ የዓለም አትሌቲክ ሻምፒዮናን ለማዘጋጀት የስታዲየሙን ግንባታ ሳይጨምር ከ130 ሚሊዮን ዮሮ በላይ ወጭ አድርጋለች። የሻምፒዮናው አዘጋጅ ኮሚቴ ከመንግስት ከ53 ሚሊዮን ዮሮ በላይ የበጀት ድጋፍ ማግኘቱን የሐንጋሪ ቱዴይ ዘገባ አውስቷል። የሻምፒዮናው መሥተንግዶ ለሃንጋሪ ኢኮኖሚ ከ158 ሚሊዮን ዮሮ በላይ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ የጠቀሰው ሃንጋሪ ቱዴይ ከትኬት ሽያጭ 5.3 ሚሊዮን ዮሮ፤ ከስፖንሰሮች ከ100 ሚሊዮን ዮሮ በላይ እንዲሁም ከእንግዶች ወጭ ከ22 ሚሊዮን ዮሮ በላይ ገቢ እንደሚጠበቅ አስታውቋል። የዓለም ሻምፒዮና በቡዳፔስት ሲካሄድ በልዩ ስኬት ከሚጠቀሱት ሁኔታዎች ዋንኛው  ከ300ሺ በላይ የስታዲየም መግቢያ ትኬቶች መሸጣቸው ነው። እነዚህን ትኬቶች ከ125 አገራት የተውጣጡ ስፖርት አፍቃሪዎች መሸመታቸውንን ዘ ሃንጋሪ ቱዴይ አስታውቋል፡፡ ዓለም ሻምፒዮናው በሚካሄድባቸው ሁለት ሳምንታት በድምሩ ከ50 ሺ በላይ የውጭ እንግዶች በቡዳፔስት እንደሚስተናገዱም ተጠብቋል፡፡ ከ3ሺ በላይ የሚሆኑት ከመላው ዓለም የተውጣጡ ሚዲያዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ሻምፒዮናው በዓለም ዙርያ ከ3ቢሊየን በላይ ህዝብን ትኩረት እንደሚስብና ከ1 ቢሊዮን በላይ የቲቪ ተመልካች እንደሚኖረው ተገምቷል፡፡ ሐንጋሪ ከዚህ የዓለም ሻምፒዮና በፊት 4 ጊዜ  በ1916፣ በ1920፣ 1936ና በ1944 ላይ ታላቁን የስፖርት መድረክ ለማስተናገድ አመልክታ አልተሳካላትም ነበር፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ የስፖርት ባለድርሻ አካላት በ2024 እኤአ ላይ ኦሎምፒክን የማስተናገድ ሃሳብ የነበራቸው ቢሆንም መንግት ሃሳቡን ውድቅ እንዳደረገባቸውም ተወስቷል። በመጨረሻም በ2023 እኤአ 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናውን የማስተናገድ እድል ስታገኝ በምስራቅ አውሮፓ የመጀመርያዋ አገር በመሆን አዲስ ታሪክ ሰርታለች፡፡
ለዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች በመመቸት ከዓለማችን የስፖርት ከተሞች በ10ኛ ደረጃ የተጠቀሰችው ቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮናውን ከ50 በላይ የስፖርትና ተያያዥ መሠረተልማቶች ያዘጋጀች ሲሆን ሻምፒዮናው የሚካሄድበት ብሄራዊ የስፖርት ማዕከሉን ጨምሮ የአየር ማረፊያ፤ ሆቴሎች፤ የልምምድ ማዕከሎችና ሌሎችም ናቸው፡፡ ቡዳፔስት ከ149 ዓመታት በላይ እድሜ ያላትና ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖርባት የምስራቅ አውሮፓ ውብ ከተማ ናት፡፡ ከተማዋ በስነህንፃ ውበት የደመቀች ስትሆንም ይህ ታሪካዊ ገፅታዋ በዓመት ከ30 ሚሊየን በላይ ቱሪስት የሚጎበኛት አድርጓታል። በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ከ100 በላይ ፍልውሃዎችና ከ200 በላይ ዋሻዎች ልዩ  የቱሪስት መዳረሻዎቿ ናቸው። ከከተማዋ ውብ የተፈጥሮ ፀጋዎች ዋንኛው በአውሮፓ በግዝፈቱ ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጠውና ታላላቆቹን የቪዬናና የቤልግሬድ ከተሞችን የሚያቋርጠውና በ10 አገራት የሚፈሰው  የዳኑቤ ወንዝ ነው፡፡ በዳኑቤ ወንዝ ላይ የተገነቡት ስምንት ግዙፍ ድልድዮችም በቱሪስቶች ተወዳጅነትን ያተረፋ ናቸው።
13 ሜዳልያዎች (4 የወርቅ 5 የብርና 4 የነሐስ) አትሌቲክስ ዊክሊ
ታዋቂው የአትሌቲክስ ሚዲያ አትሌቲክ ዊክሊ ከዓለም ሻምፒዮናው ጋር አያይዞ ባለፈው ሰሞን  ልዩ እትም አሰራጭቷል። የሚዲያ ተቋሙ በልዮ እትሙ ሻምፒዮናውን አስመልክቶ በተለይ በሩጫ ውድድሮች ላይ በማተኮር ታሪካዊና ወቅታዊ ውጤቶችን በመንተራስ ልዩ ትንታኔና የሜዳልያ ትንበያዎችን በየሩጫ መደቡ አቅርቧል፡፡ በሻምፒዮናው ከሚሳተፉ ከ2000 በላይ አትሌቶች መካከልም የኖርዌዩ ጃኮብ ኢንግሬብስተን፤ የኬንያዋ ፌዝ ኪፕዮጎን፤ የሆላንዷ ሲፋን ሃሰንና የኢትዮጵያዋን ጉዳፍ ፀጋይ የሻምፒዮናው አንፀባራቂ ክዋክብት አበይት እንደሚሆኑ አመልክቷል፡፡
በአትሌቲክ ዊክሊ ትንታኔና የሜዳልያ ትንበያ መሰረት ለኢትዮጵያ የተገመተው በድምሩ 13 ሜዳልያዎች (4 የወርቅ፤ 5 የብርና 4 የነሐስ)  ናቸው፡፡  በAthletics Weekly ትንበያ መሠረት 4 የወርቅ ሜዳሊያዎን ለኢትዮጵያ እንደሚያስመዘግቡ የተገመተላቸው ጉዳፍ ፀጋይ በሴቶች 5ሺ ሜትር፤ ለሜቻ ግርማ በወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል እንዲሁም ታምራት ቶላና ያለምዘርፍ የኋላው በሁለቱም ፆታዎች የማራቶን ውድድር ነው።  5 የብር ሜዳልያዎችን ለኢትዮጵያ እንደሚወስዱ የተነበየላቸው በሴቶች 1500 ሜትር ብርቄ ሃየሎም፤ በወንዶች 5000 ሜትር ዮሚፍ ቀጀልቻ፤  በወንዶች 10ሺ ሜትር  በሪሁ አረጋዊ፤  በሴቶች 10ሺ ሜትር ጉዳፍ ፀጋይና በሴቶች 3ሺ መሰናክል ሲምቦ አለማየሁ ናቸው፡፡ 4 የነሐስ ሜዳልያዎችን ይወስዳሉ ያላቸው ደግሞ በሴቶች 1500 ሜትር ሂሩት መሸሻ፤ በወንዶች 10ሺ ሜትር  ሰለሞን ባረጋ፤ በሴቶች 10ሺ ሜትር  ለተሰንበት ግደይና በሴቶች ማራቶን ጎይተቶም ገብረስላሴ ናቸው፡፡
በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የአትሌቲክስ ዊክሊ ትንበያ ከተሳካ በኢትዮጵያ የዓለም ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪክ ትልቁ ውጤት ሆኖ ሊመዘገብ ይችላል። AW አትሌቲክስ ዊክሊ በዩናይትድ ኪንግደም የተመሰረተ ሲሆን በድረ-ገጽ፣ በመጽሔትና በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራ  ነው።በትራክና የሜዳ ስፖርቶች፣ በአገር አቋራጭ፣ በጎዳና ላይ ሩጫ፤ በተራራ ሩጫና በሌሎች የስፖርት ክንውኖች ዙርያ ይንቀሳቀሳል።ምርጥ ዜናዎችን ፣ አስተያየቶችን፣ ትንታኔዎች፤ ታሪካዊ ዘገባዎችን ያቀርባል። AW ከ80 ዓመታት በላይ እድሜ ያለው ሲሆን ለሩጫና የአትሌቲክስ ስፖርት አድናቂዎች ቁጥር 1 ምርጫ ነው።


ባቢሎንን ከወደቀችበት አንስቼ ሕይወት ዘርቼባታለሁ።የፈራረሰውን ጠራርጌ ገንብቻታለሁ። ግርማዊነቷን እንደገና
አጎናጽፌያታለሁ።አቻ የለሽ ገናና ዝናዋን አድሼላታለሁ…
ይላል ናቡከደነፆር።ኩራቱ ናት - መናገሻይቱ ከተማ ታላቂቱ ባቢሎን።


  ናቡከደነፆር፣ ከቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ወጥቶ ታላቂቱን ከተማ ይቃኛል። በሕንጻዎቿ ከፍታ ይደነቃል። ሌላው ይቅር። በከተማዋ ዙሪያ የተሰሩት ግንቦችና በሮች ያስገርማሉ።
በዚያ ዘመን፣ የግንብ አጥር የሌለው ከተማ በሰላም ማደር አይችልም። የወራሪዎች መጫወቻ ይሆናል። የፍርስራሽ ክምር ያደርጉታል። እስከ ወዲያኛው ከታሪክ መዝገብ ይሰረዛል። ባቢሎን ግን የታሪክ ባለጸጋ ናት። ማንም የማይደፍራቸው ግንቦች ተሰርተውላታል።
በከተማዋ ዙሪያ 80 ሜትር ስፋት ያለው “የመከላከያ ቦይ” ተቆፍሯል። በውኃ ተሞልቷል። ታጣፊ የመሻገሪያ ድልድዮች ተሰርተውለታል። ድልድዮቹን አጣጥፎ ማንሳት ይቻላል። መከላከያውን ቦይ ተሻግሮ የሚመጣ ወራሪ፣ ከፊት ለፊት የኮርቻ ግንብ ይጠብቀዋል።
የመጀመሪያው ግንብ “ካር-ኡ” ይባላል።
ሰፊውን ቦይ እያካለለ በከተማዋ ዙሪያ የተሰራው ኮርቻ ግንብ፣ የ2.3 ሜትር ውፍረትና የ7 ሜትር ቁመት አለው። ከላይ በሁለት ሜትር ቁመት የጥበቃ ዘቦች ምሽግ ተጨምሮበታል። 225 ማማዎች ከፍ ብለው ተሰርተውለታል። ጠላት ይህንን ጥሶ ቢገባ… ከሀያ እርምጃ በላይ አልፎ አይራመድም። ትልቁ የዳርቻ ግንብ ይጠብቀዋል።
ሁለተኛው ግንብ፣ “ዱር-ኡ” ይባላል።
በከተማዋ ዳር በዙሪያዋ የተገነባው ዋና ግንብ ውፍረቱ 6.5 ሜትር ነው። ቁመቱ 14 ሜትር። የምሽግ ቆጥ ሲጨመርበት 16 ሜትር ይሆናል። ከ300 የሚበልጡ ረዣዥምና ትላልቅ ማማዎች አሉት። ይህም ብቻ አይደለም። ከአጠገቡ ሌላ ግንብ አለ።
ሦስተኛው ግንብ፤ “ሳል-ኡ” የሚሉት ነው። በ3.7 ሜትር ውፍረት በጡብ የተሰራው ግንብ፣ ከነ ቆጡ 10 ሜትር ቁመት አለው። እንደ ሰንሰለት ለከተማዋ ዐጥር ሆኖ ይጠብቃታል።
ናቡከደነፆር፣ ተጨማሪ አራተኛ ግንብ በጠንካራ ሸክላዎች ዙሪያውን ደርቦበታል - በ3 ሜትር ውፍረት፣ በ7 ሜትር ቁመት።
በከተማይቱ ዙሪያ በአራት ጥምጥም የተሰሩት ግንቦች፣ እያንዳንዳቸው ከ7.5 ኪሎ ሜትር በላይ ይረዝማሉ።
ይህም ብቻ አይደለም። ንጉሥ ናቡከደነፆር ከተማይቱን በእጥፍ አስፋፍቶ፣ አዳዲስ ድርብርብ ግንቦችን ሰርቷል። የከተማ ዳር ግንቦች ይሏቸዋል።
እንደተለመደው በውኃ የተሞላ የመከላከያ ቦይ በዙሪያው አለ - በ80 ሜትር ስፋት።
ቀጥሎም ደንዳና የዳርቻ ግንብ አለ። “ዳሩ ዳኑ” ይሉታል። ደንዳናነቱ ውፍረቱና ውኃ የማይበግረው መሆኑ ነው። በእሳት ተጠብሶ የተዘጋጀ ሸክላ ተደርቦበት በ11 ሜትር ውፍረት የተሰራው ግንብ፣ 13 ሜትር ቁመት አለው። ርዝመቱ 7.5 ኪሎ ሜትር ነው።
ከዚሁ አጠገብ ሌላ ግንብ ጨመረበት። በ7 ሜትር ውፍረት የተሰራው ግንብ  ከነ ቆጡ በ15 ሜትር ቁመት አለው። ይሄኛውም 7.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው።
የባቢሎን የመከላከያ ግንቦች፣ ከ1400 በሚበልጡ ረዣዥም የጥበቃ ማማዎች ተጠናክረው የተሰሩ ናቸው። ናቡከደነፆር በዚህ ሁሉ ግንባታ እጅግ ቢኮራ አይገርምም። በእርግጥ፣ ከሱ በፊትም ባቢሎን ለበርካታ ሺ ዓመታት የዘለቀች ትልቅ ባለታሪክ ከተማ ናት። ቢሆንም ግን፣ ነቡከደነፆር በብዙ ዕጥፍ አሳድጓታል።
ከናቡከደነፆር በፊት… የባቢሎን ከተማ ግንቦች በአጠቃላይ 2 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ያህል ነበረ።
በናቡከደነፆር ዘመን… 7.5 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ደርሷል። (የሕዳሴ ግድብ 75 በመቶ ያህል ማለት ነው።)
የመጠን ጉዳይ ብቻ አይደለም። የግንባታ ጥራቱም በብዙ ዕጥፍ አድጓል።
ከናቡከደነፆር በፊት… አብዛኛው ግንባታ “በጡብ” ነበር። በፀሓይ የደረቀ የጭቃ ጡብ ማለት ነው። በእሳት የተጠበሰ ጠንካራ ሸክላ እንደ ልብ አይገኝም ነበር። ከግንባታው 15 በመቶ ያህል ብቻ ነው በሸክላ የተሰራው።
በናቡከደነፆር ዘመን ግን፣ የከተማዋ የመከላከያ ግንባታ ከሦስት ዕጥፍ በላይ አድርጓል። አብዛኛው ግባንታ ደግሞ በሸክላ ሆኗል (65 በመቶ ያህል)።
በሌላ አነጋገር፣ ከናቡከደነፆር በፊት ለከተማዋ ግንቦች 22 ሚሊዮን ሸክላዎችን ተጠቅመዋል።
በናቡከደነፆር ዘመን ግን ከ380 ሚሊዮን በላይ ሸክላዎች በከተማዋ ዙሪያ ዐጥር ግንብ ለመስራት ውለዋል። ልዩነቱ ከ15 ዕጥፍ ያልፋል። ባቢሎን ቀድሞውንም ተአምረኛ ከተማ ናት። በናቡከደነፆር ዘመን ደግሞ፣ የራሷን የቀድሞ ታሪክ “የሚያስንቅ” አዲስ ተአምር አይታለች።
ይሄስ መታበይ አይደለም?
በእርግጥ፣ የቀድሞ ገናና ታሪኮችን ማናናቅ ይቅርና፣ ቸል ማለትም እንደ ትልቅ ኀጢአት ነበር የሚቆጥሩት። የባቢሎን ንጉሦች የራሳቸውን የግንባታ ገድል ለታሪክ ሲያስመዘግቡ፣ የቀድሞ ግንባታዎችን ሳይጠቅሱ አያልፉም።
ናቡከደነፆርም በአባቱ ዘመን የተሰሩ ግንቦችን በክብር አንድ በአንድ እየዘረዘረ ገልጿል።
የራሱንም ግንባታ ጽፏል።
ምናለፋችሁ! ባቢሎን የዓለማችን ገናና ከተማ ሆናለች። ከአጠገቧ የሚደርስ ሌላ ተፎካካሪ አልነበረም። በጉልበት የሚያንበረክካት ሌላ ኃያል አገር የለም። ያን ሁሉ አስተማማኝ ግንብ ጥሶ የሚገባ ከየት ይመጣል?
ቀን ከሌሊት ክረምት ከበጋ ባቢሎን የሰላም ምድር ናት።  
በከተማዋ መሐል የኤፍራጥስ ወንዝ ዓመቱን ሙሉ በእርጋታ ይጓዛል። ሲያምረውም እየጋለበ ይጎርፋል። በታሪክ የተነገረላቸው ግዙፍ ግንባታዎች የሚገኙትም ከወንዙ በስተቀኝ በኩል ነው። በወንዙ ዳርቻ ከተገነቡት ወፋፍራም ግንቦች አጠገብ፣ ሁለት ትልልቅ ቤተ መንግሥቶች ተሰርተዋል።
አንደኛው ቤተ መንግሥት የእረፍት ጊዜን ዘና ብሎ ለማሳለፍ የሚያመች ነው። የአትክልት ስፍራዎች፣ መናፈሻዎችና ሰው ሰራሽ ፏፏቴዎች ተሟልተውለታል።
ሁለተኛ ቤተ መንግሥት ትልቅ ነው። 600 አዳራሾችና ክፍሎች እንደነበሩት በተመራማሪዎች ቁፋሮ ተረጋግጧል። መደበኛ የንጉሡ መኖሪያዎችንና የመንግሥት ቢሮችን ያካትታል።
ትልቁ ቤተ መንግሥት ሸክላ የተነጠፈላቸው ግቢዎች (የደጀ ሰላም ቦታዎች) አሉት። ከመሐል የሚገኘው ደጀ ሰላም ከሌሎቹ ሰፋ ይላል። 60 ሜትር በ50 ሜትር ነው። የንጉሡ ደጀ ሰላም ነው። እዚህ ከደረስን…  
የዙፋን አዳራሽ ፊት ለፊት ይታየናል። ከንጉሡ ዋና ቢሮ ደጅ ላይ ቆመናል ማለት ነው።
በጌጠኛ ሸክላዎች የተገነባው አዳራሽ ትልቅ ነው። በጥበብ የተዛነቁት ጌጠኛ ሸክላዎች በኅብረ ቀለማት እንደ “ሴራሚክ” ያብረቀርቃሉ።
የዙፋን አዳራሹ ሦስት በሮች አሉት። ግራና ቀኝ በሮቹ 3.8 ሜትር ስፋት አላቸው። ከመሐል ደግሞ ዋናው በር፣ በ5.8 ሜትር ስፋት የተሰራ ነው - ቁመቱ ከዐሥር ሜትር ይረዝማል።
የአዳራሹ  ስፋት 52 ሜትር በ17.5 ሜትር ነው። ከ900 ካሬ ሜትር ይበልጣል።
የግድግዳዎቹ ውፍረት ሲጨመርበት 1500 ካሬ ሜትር ይሞላል።
ከጎን በኩል የግድግዳው ውፍረት 2.8 ሜትር ነው። በሌላኛው ጎኑም እንደዚያው።
የፊትና የኋላ ግድግዳዎቹ ደግሞ እያንዳንዳቸው በ6 ሜትር ውፍረት የተገነቡ ናቸው።      
እንግዲህ ናቡከደነፆር እንደ አዲስ የገነባቸው የቤተ መንግሥት ሕንጻዎችና ማማዎች ላይ ሆኖ ነው ከተማይቱን የሚቃኛት። ከአጠገቡ ሰፋፊ የክብረ በዓል መንገዶችና  ትላልቅ ቤተ መቅደሶች አሉ። የከተማዋ ትልቁ የመግቢያ በር ከበስተግራ በኩል ይታየዋል።
ኢሽታር በር ይባላል። ራሱን የቻለ ሕንጻ ነው ቢባል ይሻላል። የግንቡ ቁመት አራት ፎቅ ያክላል። ውፍረቱ 50 ሜትር ነው። ስፋቱ ከ50 ሜትር ይበልጣል። አሰራሩ እንደ ቤተ መንግሥት ነው። ሸክላዎቹ እንደ ሴራሚክ በጌጠኛ ቀለማት ያብለጨልጫሉ።
ዛሬ በጀርመን በርሊን ሙዚዬም ውስጥ አምሳያውን ገንብተው ለጎብኚዎች ያሳያሉ። በሺ የሚቆጠሩ ጌጠኛ ሸክላዎች ከቦታው በቁፋሮ እንደተገኙና በድብቅ ወደ ጀርመን እንደተጓጓዙ ታሪክ ጸሐፊዎች ይገልጻሉ።
ናቡከደነፆር ግን የከተማዋን ሕንጻዎች የሚቃኘው እንደ ጎብኚ አይደለም። አዝመራውን በኩራት የሚመለከት ነው የሚመስለው።
በስተቀኝ በኩል ደግሞ፣ “ዝነኛው ግንብ” አለ። “የባቢሎን ግንብ” ሲሉ አልሰማችሁም? የባቢሎን ደብር ልትሉትም ትችላላችሁ። ወይም ደብረ ባቢሎን።  
ደብረ-ባቢሎን።
ከ2600 ዓመታት በፊት፣ በናቡከደነፆር ዘመን በከተማዋ ዕንብርት ተሰርቶ የተጠናቀቀው ደብር ‘ፒራሚድ’ የመሰለ ቅርጽ አለው።
ስፋቱ ከኳስ ሜዳ ይበልጣል።
91 ሜትር በ91 ሜትር ነው። ቁመቱም 91 ሜትር።
ከ30 ሚሊዮን በላይ ሸክላዎችን ፈጅቷል።
በእርግጥ፣ እዚህም ላይ ናቡከደነፆር ነባር ጅምሮችን ሳይጠቅስ አላለፈም። ደብረ ባቢሎን ከሱ በፊትም ተሰርቷል። ነገር ግን አርጅቶና ፈራርሶ ነበር። የናቡከደነፆር አባት እንደ አዲስ ግንባታውን እንዳስጀመረ፣ ግንባታውንም 15 ሜትር ቁመት ላይ እንዳደረሰው በታሪክ ተመዝቧል። ናቡከደነፆርም ይህን መስክሯል። ከዚያም የግንባታውን ጥራት አሻሽሎ ቁመቱንም 91 ሜትር አድርሶ አጠናቅቆታል። ከ20 ፎቅ በላይ ይሆናል። ከአናቱ ላይም ትልቅ ቤተ መቅደስ ተሰርቶለታል (በአብረቅራቂ ሰማያዊ ሸክላዎች)።
በእቶን እሳት ተጠብሰው በጥራት የተዘጋጁ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የናቡከደነፆር ዘመን ሸክላዎች፣ እስከ ዛሬ ድረስ በምድረ ኢራቅ ለቪላ ቤት ግንባታ ተመራጭ መሆናቸውን አስቡት።
አዎ፣ ንጉሥ ናቡከደነፆር በብዙ ጦርነት ትልልቅ ነገሥታትን አሸንፎ ጥሏል። ሰፋፊ ግዛቶችን በወረራ አስገብሯል። እውነት ነው። ይበልጥ የሚኮራው ግን በባቢሎን ግንባታ ነው። በጦርነት ካገኛቸው ድሎች ሁሉ ትበልጣለች።
ሰፋፊ መንገዶቿ፣ የውኃ መተላለፊያ አውታሮቿ፣ የመስኖ እርሻዎቿ… ድንቅ ናቸው።
በባቢሎን  ግንባታዎች ላይ ሰፊ ጥናት ማካሄዱና መጽሐፍ ያሳተሙ ተመራማሪዎች ብዙ ናቸው። ዛሬ ዋናው ተጠቃሽ መጽሐፍ Olof pedersen, “Babylon-The great city” በሚል ርዕስ ያሳሙት መጽሐፍ ነው።

“--ቢሆንም የዮሃንስ ተፈራ አጻጻፍ መንፈሱ በሕይወት ታሪክ ላይ ስለተመሰረተ፣ እንደ ሕዋስ
ቆዳን ዘልቆ ይገባል። ሌላው ጠንካራ ጎን የደራሲው የጽሁፍ ጥንቅር በግብዝነት ስላልተመሰረተ፣
ከታችኛው ማህበረሰብ ተናንሶ መብላት መጠጣቱ የምርም ‘ጥበበኛና ከንቲባ ከሕዝቡ ጋር ነው
መኖር ያለበት።’ የሚለውን ተለምዷዊ ብሂል ማሟላቱ መልካም ነው።--”

ጥንካሬ፦
ጠንካራው ጎኑ ስራው ብቸኛና አንጡራ የሚባል ነው። ስለ አሰብ የዚህ አይነት መጽሐፍ ተጽፎ አያውቅም። በልብወለድ ተደርጎ “ሄላ” የሚል መጽሐፍ አስታውሳለሁ። በኢ-ልብወለድ ግን ይህ መጽሐፍ ብቸኛው ነው። የዶ/ር  ያእቆብ ኃ/ ማርያም  “አሰብ የማናት” የሚለውም ቢሆን፣ የፖለቲካ ትንታኔ እንጂ እንዲህ ሰነድና ዋቢ መጻህፍት አልቦ ከሆነ፣ የህይወት ነጸብራቅ ላይ የተመሰረተ የእውቀት ብልጭታ አይደለም። የጽሁፍ ስራውን አድካሚ፥ መጽሐፉንም ወሳኝ የሚያደርገውም ይህ ነው።
የአሰብ ነዋሪዎችን ሕይወትና ውጣ ውረድ፥ የገቢ ምንጫቸውንና ባህሪያቸውን ለመሳል የተከፈለው ዋጋ፣ ከ400 ገጾች በላይ ያሉትን ኪታብ አል-አሰብ መስጠቱ ጥኡም ነው። የደራሲው ግልጽነትና አይኑን በRomanticism መነጽር ጋርዶ፣ ስለሌላው ጾታዊ ንሸጣው አልደበቀም። አንገቱ እስኪበጠስ እንደኔም ባያይ በአፋር ሴቶች መልክ መማረኩን አምኗል። Realism technic ተጠቅሞ መጻፉ ያስመሰግነዋል። ለምን? አኗኗራችን ንፍጥ ይበዛዋል።
ከአወቃቀር አኳያ ዘርፈ ብዙ (multi layered) ነው። ባህላዊ ዘውግም ማህበረሰባዊ ጠባይም አስተያይቶ ነው የጻፈው። ስለ ወደብ ጥቅሞች ይህ ትውልድ እንዲያውቅ የለፋበት ሂደት መልካም ነው። በርግጥ እዚህ ጋ ባለ ዳሰሳ፣ የ“አረናው” አስራት አብርሃም ባሳተመው፣ “ከሀገር በስተጀርባ” በሚለው፣ ህወሓትን በሚወግርበት መጽሐፉ፣ በአጭርና በእጭቅ ትንታኔ ገልጿል። ቢሆንም የዮሐሃንስ ተፈራ አጻጻፍ መንፈሱ በሕይወት ታሪክ ላይ ስለተመሰረተ፣ እንደ ሕዋስ ቆዳን ዘልቆ ይገባል። ሌላው ጠንካራ ጎን የደራሲው የጽሁፍ ጥንቅር በግብዝነት ስላልተመሰረተ፣ ከታችኛው ማህበረሰብ ተናንሶ መብላት መጠጣቱ የምርም ‘ጥበበኛና ከንቲባ ከሕዝቡ ጋር ነው መኖር ያለበት።’ የሚለውን ተለምዷዊ ብሂል ማሟላቱ መልካም ነው። ጠንካራ ግለሰቦች እንደ ኮማንደር ዘለቀ ቦጋለ፣ ጥናታዊ ፊልም ቢሰራባቸውና፣ በስማቸው መንገድ ብሎም የግንባታና የሀገርን መውደጃ ዝግጅቶች ላይ በስማቸው Conference Paper ቢቀርብ ጥሩ ነበር-ይህም የመጽሐፉ ትሩፋት ነው።
ድክመት፦
አንዳንድ ቦታ ላይ የሀሳብ ወጥነት ጉድለት ይታያል። ‘ስለምን የሀሳብ ወጥነት ጎደለው?’ ሊባል ይችላል። ይህም የሚከሰተው የጽሁፍ አባዜው እንደ ዛር ሲሰፍር ከሚመጣው የሃሳብ ግትልትል ናዳ ለማምለጥና ድምጹንና ምስሉን ከመፍራት ነው፡፡ ጽሁፉ ከውስጥ በግፊት መውጣት ሲጀምር፣ ምስሉና ድምጹ ከውጪ ኩልል እያለ ይመጣል፣ ይሄኔ ሰዎች ከውጪ የሚሰሙትን ድምጽ መበርገግ ይጀምራሉ። በዚህም የተነሳ በሰላሙ ጊዜ ሲታሰቡ የነበሩ ሀሳቦችን ማስገባት ይመጣል-(አላበድኩም ለማለት)። እንግዲህ ዛሩ ደግሞ ነጭናጫ ነገር ስለሆነ ትእግስት የለውም፤ ተቀይሞ እብስ ሲል ጸሃፊው በአእምሮው Mechanical ትግል ይጀምራል። ይሄኔ ቅልቅሉ ብቅ ይላል። የእርግጠኝነት ስሜት መጉደል፥ የእርማት ችግርና የዋቢ መጻሕፍት አሰዳደር መጽሐፉ ለአራተኛ ዙር ከታተመ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
መጽሐፉ ባያልቅም እኛ ስንጨርስ፦
እንግዲህ- የድንቁርና ማሰሪያው ንባብ ነውና፤ መጽሐፉ ይነበብ ዘንድ የጥበብና የታሪክ ስንክሳር ያስገድዳል።

ሁለት መንገደኞች ራቅ ወዳለ አገር ለመሄድ ጉዞ ጀምረዋል፡፡ ሁለቱም የተለያየ ጠባይ ያላቸው ናቸው፡፡
አንደኛው፤ በህይወቴ ሙሉ ዕውነት ፈፅሞ ተናግሮ የማያውቅ ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ዕድሜውን በሙሉ ውሸት የሚባል ነገር ፈፅሞ ተናግሮ የማያውቅ ነው፡፡
ሁለቱ መንገደኞች ብዙ ከተጓዙ በኋላ፣ ወደ ዝንጀሮዎች አገር ይደርሳሉ፡፡ የዝንጀሮዎቹ ንጉስ መንገደኞች መምጣታቸውን ይሰማና፣ ወደ ዙፋኑ እንዲቀርቡ ያዛል፡፡ ግርማ - ሞገሱንና ታላቅነቱን ይረዱ ዘንድ ዙፋኑ ላይ በክብር ይቀመጥና፣ ሌሎቹን ባለሟሎቹንና የበታች ሹማምንቱን በግራና በቀኝ እንዲኮለኮሉ ያደርጋል፡፡ ከግራ ከቀኙ የተደረደሩት ዝንጀሮዎች ረዥም መስመር ሰርተዋል።
መንገደኞቹ ዙፋኑ ፊት ቀርበው ለጥ ብለው እጅ ሲነሱ፤ የዝንጀሮዎቹ ንጉስ፤
“ረዥም መንገድ ላይ እንዳላችሁ ሰማሁ፤ ዕውነት ነው?” አሉ፡፡
ዕውነት የሚናገረው ሰውዬ፤
“አዎን ንጉሥ ሆይ፤ ገና ሁለት ቀንና ሌሊት ተጉዘን ነው ወደ አሰብንበት አገር የምንደርሰው” አለና መለሰ፡፡
“ለምን ጉዳይ ነው የምትሄዱት?”
“የምንሄድበት አገር ያሉት ሰዎች እጅግ የሰለጠኑ ናቸው ይባላል፡፡ እኛ ገና አላየናቸውም። ከነሱ ትምህርት በመውሰድ ያገኘነውን አዲስ ነገር፣ ወደ አገራችን አምጥተን እኛም እንደነሱ ለመሰልጠን አስበናል” አለ፡፡
ንጉሱም፤ “መልካም፡፡ ሃሳባችሁ የተቀደሰ ነው፡፡ ጥሩ ነገር እንዲገጥማችሁ እመኛለሁ፡፡ አሁን ያስጠራሁዋችሁ ስለ እኔና ስለ ባለሟሎቼ ምን እንደምታስቡ እንድትነግሩኝ ነው”
ይሄኔ ውሸት የመናገር ጠባይ ያለው መንገደኛ፤
“ንጉሥ ሆይ፤ ማንም እርስዎን ያየ ሰው እጅግ የተከበሩና ኃያል ንጉስ መሆንዎን አይስተውም።”
“ባለሟሎቼንና ሹማምንቴንስ እንዴት ታያቸዋለህ?”
“እነሱማ አንዳቸውም ከእርሶ ጋር አይተካከሉም፡፡ እርሶ እዚያ አናት ላይ፤ እነሱ ደግሞ እዚህ ታች እግርጌ ናቸው፡፡ የጌታቸውን ክብርና አዋቂነት ይፈራሉ”
የዝንጀሮዎቹ ንጉስ በጣም ተደሰተ፡፡ መደሰቱ እስከሚታወቅበት ድረስ እየተቅበጠበጠ በባለሟሎቹ ፊት ወዲያ ወዲህ ሲል ቆይቶ፤
“እንዳንተ፤ ሁሉ ሰው ዕውነቱን ቢያውቅ የት በደረስን፡፡ እንዳንተ ያሉ ሰዎች ይህቺን ዓለም ቢሞሉዋት የእኛ ሀገር ብቻ ሳትሆን፣ ጎረቤቶቻችንና ከዚያም የራቁት ሀገሮች የት በደረሱ፡፡ በል እንካ ይህን የከበረ ስጦታ ውሰድ፡፡ ስለተናገርከው እውነት ማስታወሻ ይሁንህ” አለና ስጦታውን አበረከተለት፡፡
ይህንን ያስተዋለው ሁለተኛው መንገደኛ በሆዱ እንዲህ አሰበ፡-
“ጌታው፤ አንተስ ስለእኔና ስለባለሟሎቼ ያለህ አስተያየት ምንድን ነው? እንዴት አገኘኸን?” ዕውነት ተናጋሪው መንገደኛም፤
“ንጉስ ሆይ እርሶ ግሩም ነዎት፡፡ ባለሟሎዎችም ግሩም ናቸው፡፡ በምንም አትተናነሱም፡፡ በምንም አትበላለጡም፡፡ ሁላችሁም አንድ አይነት ናችሁ” አለ፡፡
የዝንጀሮዎች ንጉስ ቱግ አለ፤  ተቆጣ፡፡ እጅግ ከመናደዱም የተነሳ፤
“በዝንጀሮዎቹ ጥፍር እየተቧጠጠ እየተሰቃየ እንዲሞት!” ሲል ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
***
ንጉሶች፣ መሪዎችና አለቆች ሁሌም ከሌሎች ባለሟሎችና አጋሮቻቸው እንዲሁም የሥራ ባልደረቦቻቸው እኩል ናችሁ እንዲባሉ አይፈልጉም፡፡ የተለዩ መሆናቸውን፣ የተሻሉ መሆናቸውን፣ ከሁሉ በላይ መሆናቸውን የሚነግራቸውን አማካሪ ነው የሚወዱት፡፡ በጊዜና በታሪክ አጋጣሚ እንጂ እነሱም እንደማናቸውም ባለሟል እንደነበሩ፤ ይዘነጋል፡፡ አንገረ ፈላስፋ፤ “ሸክላ ሲሰበር ገል ይሆናል፤ መኳንንትም ሲሻሩ ያው እንደማንኛውም ሰው ይሆናሉ” የሚለውን ይረሱታል፡፡ እንደ ዕውነቱ ከሆነ ሲሾሙና ሥልጣን ሲይዙ ራሳቸውን ከጥንት ወዳጆቻቸው የተለየ ፍጡር አድርገው ባያዩ፤ ከሥልጣን ሲወርዱ የተዋረዱ አድርገው ራሳቸውን ከህዝብ እንዳይሸሽ በጠቀማቸው ነበር። በእርግጥም፤ ራሳቸውን የተለየ ፍጡር አድርገው ማየት፤ የተለየ እንክብካቤ፤ የተለየ ጥቅም፣ የተለየ ከበሬታ ወደመፈለግ እንዲያመሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፣ በአንደኛው ቴያትሩ ውስጥ “የዘመኑ ተራማጅ፤ ሥልጣን በሸተተው ማግሥት አካሄዱ፣ አረማመዱ ሁሉ እንደ ድመት ኮርማ ይሆናል” ይላል፡፡ በመሰረቱ ማናቸውም ሥልጣን ላይ የሚቀመጥ ሰው የዚያ ወንበር ተሸካሚ፣ የዚያ ኃላፊነት አገልጋይ እንጂ በዚህ ሥልጣን ተገልጋይና የግል ጥቅሙን አሳዳጅ፣ የግል ወገናዊነቱን ተግባሪ ሊሆን አይደለም፡፡ ራስን ልዩ አድርጎ ማስቀመጥ ተነጥሎ መታየትን ብቻ ሳይሆን ዒላማ መሆንን ያስከትላል ይሏልና፤ በዚህም ረገድ ቢሆን አደገኛ ነው፡፡ ዛሬ ያልነውን ነገ መሻር ተዓማኒነትን ያሳጣል፡፡ በምንም ረገድ፤ በምንም ዘዴ ተጠቅመን እናስተባብለው ታዳሚው በልቡ ፅላት እንደሚፅፈው አለመርሳት ነው፡፡ ታዳሚ ጆሮ የገባ ነገር በዋዛ አይፋቅም፡፡ ይህን ምንጊዜም ማስተዋል ይበጃል፡፡ አንዴ ተዓማኒነትን ካልጣን መልሰን ማግኘት ዘበት ነው፡፡ አንድ ሁለት  ግለሰቦችን ቡድኖችን ማታለል ይቻል ይሆናል፤ ህብረተሰብን ግን ማታለል አይቻልም። ይህን እንደዋና መመሪያ ከመያዝ ዋና ነገር ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የምንመራውን ህዝብ ምንም ያህል መልካም ፖሊሲ ብንቀርፅለት፤ ጊዜና ቦታ ለይተን፤ መጠንና ልክ አውቀን፤ ባህል ልምዱን አጣጥመን፤ ካላቀረብንለት ከየትም ከየትም ከምእራብም ከምስራቅም ያሰባሰብነው መመሪያና ደንብ እንዲሁም መተዳደሪያ፤ ባንድ ጊዜ እናስውጥ ብለውን ተርፎ የሚፈሰው፣ ሳይጨበጥ የሚሰበረው፣ ለአደጋ የሚያጋልጠው ይበዛና ካሰብነው ቦታ እንዳንደርስ እንሆናለን። ይኼ በየዘመኑ ደጋግመን አይተናል፡፡ በአንፃሩ ስለተጠነሰሰ ብቻ የማይጠመቅ ብዙ ጠላ አለ፡፡ ስለተወራ ብቻ የልብ የማያደርስ ብዙ ደጋግ እቅድ አለ፡፡ ከወረቀት የማያልፍ አያሌ ህግና ደንብ አይተናል፡፡ የማስፈራሪያ ያክል የሚጮህበት አያሌ መሬት ያላረፈ መፈክር ታዝበናል፡፡ (የቀድሞ መሪ አብዮቱ በፈነዳው በስምንተኛ አመቱ “የምንለውን ብለናል፤ የምናደርገውን እንጀምር” ማለታቸውን ልብ ይለዋል፡፡) ለፖለቲካዊ ልዩነቶች ሁሉ ወታደራዊ እርምጃዎችን እንደብቸኛ መፍትሄ መውሰድ ለአገርም ለመንግስትም ለህዝብም አይበጅም፡፡ ጦርነት ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል ማሻገር አይመከርም ዘላቂ መፍትሄም አያመጣም፡፡
“ሁሉንም እንቁላልህን አንድ ቅርጫት ውስጥ አስቀምጥ” የተባለውን ያህል፤  “ገና ሳይፈለፈሉ ጫጩቶችህን መቁጠር አትጀምር” እንደሚባል አለመርሳት ታላቅ ነገር ነው፡፡ ሁሉንም አባልህን በአንድ አሸንዳ እንዲፈሱ አታድርግ፡፡ የሃሳብ ልዩነትህን ውደድ፤ አስተናግድ፡፡ ሁሉንም ወዳጆችህን ለአንድ ጉዳይ አታውል፡፡ ሁሉንም ተከታይህን የአንድ ሀሳብ ቁራኛ አታድርግ ማለትም ያስኬዳል፡፡

የጋሞ  ህዝብ ጥያቄ በክላስተር የመደራጀት አይደለም ያለው የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋዴፓ)፤ህዝቡ ለረዥም ጊዜ ሲጠይቅ የቆየው ራሱን በራሱ የማስተዳደርና በክልል የመደራጀት ህገመንግስታዊ መብቱ እንዲከበርለት ነው ብሏል፡፡

የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮች፣ ዛሬ ከሰዓት በኋላ 8 ሰዓት ላይ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ጽ/ቤት አዳራሽ ውስጥ፣ በአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች አደረጃጀት ዙሪያ መንግሥት እያደረገ ካለው እንቅስቃሴ ጋር በተገናኙ ጉዳዮች ላይ  ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
አዲሱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመሰረቱት የጌዲኦ፣ የወላይታ፣ የጋሞ፣ ጎፋ፣ የኮንሶ፣ የደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የደራሼ፣ የባስኬቶ እና የአሌ ልዩ ወረዳዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የጋሞ ዞን በክላስተር የክልል አደረጃጀት ውስጥ መካተቱን እንደማይቀበለው ይገልጻል፡፡ የጋሞ ህዝብ ጥያቄ በክላስተር ልደራጅ የሚል አይደለም  ያለው ፓርቲው፤ ህዝቡ ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ-መንግሥታዊ መብቱ እንዲከበርለት ነው የጠየቀው ብሏል፡፡

”የጋሞ ዞን ህዝብ ጥያቄ  ከማዕከልነት ጋር የተያያዘ ወይም የከተማ አመዳደብ ኢ-ፍትሃዊነት ጉዳይ አይደለም“ ያሉት የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ቡንካሾ ሀንጌ፤የህዝቡ ጥያቄ የክልልነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ ነው ብለዋል፤ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ በሰጡት ማብራሪያ፡፡

“የጋሞን ህዝብ በክላስተር መደራጀት ይጎዳዋል የምንለው ያለምክንያት አይደለም” የሚሉት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው፤ “የጋሞ ህዝብ በፊት አዋሳ መጥቶ ነበር አገልግሎቶችን የሚያገኘው፤ በአዲሱ አደረጃጀት ግን አገልግሎት ለማግኘት ዲላ ድረስ መምጣት አለበት፤በዚያ ላይ ከአንድ ማዕከል አገልግሎቶችን ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡“ ሲሉ አስረድተዋል፡፡  


“በክላስተር መደራጀትን የተቃወምነው አርባምንጭ በአዲሱ የክልል አደረጃጀት ዋና  መቀመጫ ሳትሆን በመቅረቷ  ነው  ብለው የሚያወሩ አንዳንድ ወገኖች አሉ፤ ይሄ ግን ሃሰት ነው፡፡” ያሉት የፓርቲው የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ኤልያስ ዛለ በበኩላቸው፤ ህዝቡ ያቀረበው የማዕከልነት ጥያቄ ሳይሆን፣ “ክልላችን ጋሞ፣ ማዕከላችን አርባምንጭ” የሚል ነው ብለዋል፡፡  


ፓርቲያቸውም ሆነ የጋሞ ህዝብ የማዕከልነትን ጥያቄ  እንዳላነሱ የገለጹት  የፓርቲው ም/ፕሬዚዳንት አቶ ዳሮት ጉምአ ጉጌ፤ “በክላስተር አደረጃጀት ማዕከል የሚባል ነገር ያለ አይመስልም፤ እኛ የጠየቅነው  የጋሞ ክልላዊ መንግሥትን የመመሥረት ህገ-መንግስታዊ መብታችንን ነው፤ ማዕከሉንም አርባምንጭ ማድረግ፡፡” ሲሉ በመግለጫው ላይ ተናግረዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ፤ “የጋሞ ሕዝብ በክልል የመደራጀትና ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ-መንግሥታዊ መብቱ ይከበር፤ሕዝቡ ያቀረበው ህጋዊ ጥያቄም ሕገ-መንግሥታዊ መልስ ይሰጠው!” በሚል መሪ ቃል፣ ጋዴፖ  ባለ 7 ገጽ የአቋም መግለጫ በዛሬው ዕለት አውጥቷል፡፡

”የጋሞ ሕዝብ ከላይ እስከ ታች ባሉት መንግሥታዊ መዋቅሮቹና ምክር ቤቶቹ አጽድቆ ያቀረበው የጋሞ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልልነት ጥያቄ ሕገ-መንግሥታዊ ምላሽ ባላገኘበት ሁኔታ፣ በብልጽግና ካድሬዎች የሸፍጥ አሠራር የመጣን ክላስተር የክልል አደረጃጀት” እንደማይቀበለው በመግለጫው የጠቆመው  ጋዴፓ፤“መንግሥት ይህን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ የማሻሻያ እርምጃ እንዲወስድ” በአጽንኦት ጠይቋል፡፡

“መንግሥት የጋሞን ሕዝብ ክልላዊና ሀገራዊ መብት፣ ጥቅምና ክብር በሕገ-መንግሥታዊ መንገድ ያላከበረውን የአዲሱን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምሥረታ ሒደት ከማጣደፍ እንዲቆጠብ” ያሳሰበው ፓርቲው፤ “ይልቁንም የጋሞ ሕዝብን በጉዳዩ ዙሪያ ከላይ እስከ ታች የሚያወያይበትን አካታችና አሳታፊ መድረኮች በአስቸኳይ እንዲፈጥር“ በዚሁ መግለጫው ጠይቋል፡፡

አዲሱን አደረጃጀት  በመቃወም  ለነሐሴ  4 ቀን 2015 ዓ.ም በዞኑ  ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቶ እንደነበር ያስታወሰው ጋዴፓ፤ ነገር ግን የዞኑ አስተዳደር ወታደራዊ ሃይል በማሰማራት፣ ለሰልፍ ከወጡት  400 ያህሉን ማሰሩን ጠቁሞ፣  የጋሞ ሕዝብ ኃሳቡን በነፃነት የመግለጽ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱን የረገጡት የጋሞ ዞን አስተዳደርና የጋሞ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ፣ በሕግ እንዲጠየቁና፣ ይህም መተግበሩን መንግስት ለሕዝብ እንዲገልጽ አሳስቧል፡፡

•  “ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር፣ አገሪቱ በዓመት 1.2 ቢ. ዶላር
 የውጭ ምንዛሪ ታገኝበታለች”

•  “ቀንጢቻ ማይኒንግ”፣ ለሰባቦሩ ወረዳ አስተዳደር የ2 ሚ. ብር ድጋፍ አድርጓል

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን፣ ደርሚ ወረዳ፣ ቀንጢቻ አካባቢ የሚገኘውና የሊትየም ማዕድን ለማምረት የተቋቋመው ቀንጢቻ ማይኒንግ ኃ.የተ.የግ.ማህበር፤ በመጪው መስከረም ወር ሥራ እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው በዛሬው ዕለት የድርጅቱ አመራሮችና ባለአክሲዮኖች፣ የፕሮጀክቱን ሂደትና የደረሰበትን ደረጃ እንዲሁም 150 ሚሊዮን ብር የወጣበት የሊትየም ማዕድን ማውጫ ወደ ኢትዮጵያ እያስገባ መሆኑን በተመለከተ በሸራተን አዲስ ሆቴል፣ ለባለድርሻ አካላትና ለጋዜጠኞች ማብራሪያ በሰጡበት መርሃግብር ላይ ነው፡፡ባለፈው ሳምንት፣በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው ነው የተባለ የሊትየም ማዕድን ማውጫ ማሽነሪ፣ በቀጣይ ሳምንታት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገባ፣ የቀንጢቻ ማይኒንግ ኃ.የተ.የግ.ማህበር መሥራችና  ከፍተኛው የአክሲዮን ባለድርሻ የሆኑት ሀጂ አሊ ሁሴን፣ ከሳኡዲ አረቢያ በስካይፒ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ማስታወቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የቀንጢቻ ማይኒንግ መሥራችና በኢትዮጵያ የአፍሪካ ማይኒንግና ኢንጂነሪንግ ተወካይ የሆኑት ሀጂ አሊ ሁሴን በዛሬው የሸራተን አዲስ መርሃ ግብር ላይ በሰጡት ማብራሪያ፣ ከፍተኛ መዋዕለንዋይ የፈሰሰበት ይኸው የሊትየም ማሽን፣ ከደቡብ አፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመርከብ የተጫነ ሲሆን፤ በመጪው መስከረም ወር ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባና ድርጅቱም ሥራ እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡

ሁለት ተጨማሪ አቅም ያላቸው የሊትየም ማውጫ ማሽነሪዎች ከ2023 የፈረንጆች ዓመት ማገባደጃ በፊት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያስገቡ የገለጹት ሀጂ አሊ ሁሴን፤ይህም በጠቅላላው በሰዓት 270 ቶን ሊትየም የማምረት አቅም እንደሚሰጣቸውና በዓለም ላይ በጣት ከሚቆጠሩ ጥቂት የሊትየም አምራች አገራት ጎራ እንደሚያሰልፋቸው ጠቁመዋል፡፡

ቀንጢቻ ማይኒንግ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባና የሊትየም ማዕድን ከሀገራችን ከርሰ ምድር ወጥቶ ለዓለም ገበያ ሲቀርብ፣ ኢትዮጵያ በዓመት 1.2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ታገኝበታለች ያሉት የድርጅቱ መሥራች፤ ከዚህም ባሻገር  ለ500 ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርላቸውና  መንግሥትም ከፍተኛ የታክስ ገቢ እንደሚያገኝበት አክለው ገልጸዋል፡፡

ቀንጢቻ ማይኒንግ ኃ.የተ.የግ.ማህበር፣ በአጠቃላይ በ80 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ወደ ሥራ መግባቱን ያስታወቁት የድርጅቱ መሥራች፤ በዓለም ላይ አሉ የተባሉ የማዕድን ፍለጋ ባለሙያዎችን አሰማርተው ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት እየተዘጋጁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

“በቀጣይነትም ሊትየም፣ የባትሪ ምርት ዋነኛ ግብአት በመሆኑ፣ ማዕድናችንን እየላክን የበዪ ተመልካች እንዳንሆን፣ የሊትየም ባትሪ ፋብሪካ ለመክፈትም፣ ጥናቱን አጠናቅቀን በዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡” ብለዋል፤ሀጂ አሊ ሁሴን፡፡

በዛሬው መርሃግብር ላይ የቀንጢቻ ማይኒንግ ፕሮጀክቶችን አጠቃላይ ሂደት የሚያሣይ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን ለዕይታ የቀረበ ሲሆን፤ ኤግዚቢሽኑ በባለድርሻ አካላትና በክብር እንግዶች  ተጎብኝቷል፡፡

በሌላ በኩል፣ ቀንጢቻ ማይኒንግ ፈቃድ ወስዶ ፕሮጀክቱን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦና ድጋፍ ያደረጉ አካላት የዕውቅና ሽልማት በድርጅቱ የተበረከተላቸው ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ የፌደራል ማዕድን ሚኒስቴር፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት፣ የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የቆንጢቻ ቀበሌ ይገኙበታል፡፡

ከዕውቅና ሽልማቱ በተጨማሪ፣ ቀንጢቻ ማይኒንግ ኃ.የተ.የግ.ማህበር፣ ለሰባቦሩ ወረዳ አስተዳደር የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

ቀንጢቻ ማይኒንግ ኃ.የተ.የግ.ማህበር ባዘጋጀው በዛሬው  የፕሮጀክት ሂደት ማብራሪያ መርሃግብር ላይ ባለድርሻ አካላት፣ አምባሳደሮች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የባንክ ተወካዮች፣ አባ ገዳዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ጋዜጠኞች ተገኝተዋል፡፡


“…ከመሰላሉ ማውረድ አለባቸው የሚላቸውን ሰዎች ዝንተ አለማቸውን ስማቸውን እንደ ተራራ ሲቆለል የኖረ ነው” የሚል የፅሁፍ መግቢያ ያደረገውን… የፅሁፉም ርእስ … “ደራሲ ብሎ ጠቢብ አይታየኝም” … የሚል ነበር፡፡ በእኔ በኩል ፀሃፊ ከመግቢያውም መስተካከል አለበት እላለሁ፡፡ ለዚህም የማነሳው ሃሳብ እነዚህ ሰዎች… ወደ መሰላሉ እንዴት ወጡ? ማን አወጣቸው? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። በመጀጨመሪያ ደረጃ ሰዎቹን ወደ መሰላሉ ያወጣቸው ስራቸው በማስከተለም ህብረተሰቡ ነው፡፡ ህብረተሰቡ ወደ ላይ ለመውጣቱም ሆነ ወደ ታች ለመውረድ ከፍተኛውን አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ ስለሆነም ማህበረሰቡ ወደ መሰላሉ ማውጣት ብቻ ሳይሆን እንድትመላለስ የሚያደርግህ ዝም ብሎ አይደለም፡፡ ይህም ሲባል ጠቃሚ የሆነ ምርምር በህክምና፣ በእርሻ፣ በሳይንስ፣ በፍልስፍና እንዲሁም በስነ ፅሁፍ በድርሰት… በግጥም… በቅኔ… ህይወትን መምራት የምትችልበትን ቀመር  በመቀመር ህብረተሰቡ… አንድ … ሁለት… እርምጃ ቀድመህ ስትገኝ ህብረተሰቡ እራሱ እዛ መሰላል ላይ ያስቀምጥሀል፡፡ ምክንያቱም ሁሌም ማህበረሰቡ ለህይወቱ ተሞክሮውን፣ መፍትሄ፣ ብሎም ብርሃንን አግኝቶበታል፡፡
ኤፍራጠስ፤ አንተ እንዳልከው ላንተ ማዳም ሲጁ ወከር ትበልጥብሃለች …. ይሁን ስራዋ ለውጫዊ ውበት ይጠቅማልና… ለውስጣዊ ውበትህስ ማንን? ወይስ ለውስጣዊ ውበት አትጨነቅም? አለኝ ካልክስ ከየት አመጣኸው?... እንደው ለማለት ያህል ማህበረሰቡም የራሱ የሆነ ውስጣዊ ውበት አለው፡፡ በእኔ እምነት ስነፅሁፍ ድርሰት፣ ግጥም፣ ቅኔ ብሎም ፍልስፍና አለ ሊባል የማይችል ውስጣዊ ውበት ወይም ንቃተ ህሊና ፍላጎትን እና ጉጉትን እያንዳንዱ ግለሰብ ውስጥ ይፈጥራሉ፡፡ ይህ ደግሞ ምን አይነት እንደሆነ ከጊዜ በፊት ለማስረዳት ጊዜ መፍጀት ይመስለኛል፡፡
እዚህ ላይ እኔ ከነዚህ ሰዎች አልተጠቀምኩም ማለት ሌላ ነገር ነው፡፡ አይጠቅሙም ማለት ግን ትንሽ አስገዳጅነት ባህሪ አለው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የተጠቀሙትን መንካት፣ የናንተን አፍሩስና በእኔ አይነት ገንቡ እንደ ማለት ነው። … እኔ በበኩሌ የዚህ አይነቱን አቀራረብ አልጣመኝም፡፡ እስቲ ሳነብ ያገኘሁትን ላካፍልህ።
“የሰው ልጅ ጌጡ ጥበብ ነው እና ለጠቢባን እውቀትን ያበዙ ዘንድ መናገር ተገቢ ነው፡፡”
ጠቢብ እንዲህ አለ፡- “በጭለማ ማየት እችላለሁ…” የጠቢቡን አባባል ያልተረዳ ሰነፍ ደግሞ ጠየቀ፡-
“በጨለማ ማየት ከቻልክ ታዲያ ለምን መብራት ይዘህ ትሄዳለህ?” ጠቢቡ ከሰነፍ የሚጠብቀው ጥያቄ ነውና ሳይደነቅ መለሰለት፡- “እንደ አንተ አይነት በጨለማ ማየት የማይችል መጥቶ እንዳይገጨኝ ነው” አለው፡፡ ጠቢብ መሆን ባይቻል፣ የጠቢብን ብርሃን ማየት ይቻላል፡፡ ስለሆነም ብርሃኑን በመጠቀም ለህይወት የሚጠቅመውን (የሚበጀውን) ማየት የተመረጠ ይሆናል ብዬ ነው፡፡
እብደት ማለት ምን ማለት ነው? ለእኔ እብደት ማለት … አንድ ሰው ካለው ማህበረሰብ ወጣ ያለ አስተሳሰብ ሲኖረው ነው… ሰዎች ያ ሃሳብ ከራሳቸው በላይ በሆነ ጊዜ አበድን ይላሉ… ግን ያበደው ማን ይሆን? ኤፍራጠስ፤ በፅሁፍህ ላይ “ግማሹ አብዶ ነው የሚሞተው” ብለሀል። ለዚያም የጠቀስከው አማኑኤል ካንትን ነው። ምን አልባት ‘አማኑኤል’ እንደ ‘ባህሉ’ ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡ ባህሉን የቱንም ያህል በጥበብ ቢበስል፣ በዚሁ ምክንያት የሚደርስበትን አደጋ ፍራቻ ጥበብን በእብደት መጋረጃ ሸፍኖት ነበር። ለዚሁም ምሳሌ፡-
አንድ ቀን ባህልን ከንጉስ መቀመጫ ተቀምጦ ተገኘ፡፡ በዚህ ምክንያት ወታደሮቹም ቆዳው እስኪላጥ ሲገርፉት… ጩኸቱን የሰማው ንጉስ፣ መጣና ወታደሮቹን “እናንተ እብዶች፣ ባህሉን እብድ መሆኑን አታውቁም” አላቸው፡፡
ባህልሉን “ንጉስ ሆይ ወታደሮችህን ተዋቸው፤ እኔን ያስለቀሰኝ ሌላ ነው” አለ፡፡ በዚህ ንግግር የተደነቀው ንጉስ ምን ለማለት እንደፈለገ ጠየቀው… ባህሉንም አለው፡-     “እኔ አንድ ቀን ለተቀመጥኩበት ይሄን ያህል ከሆንኩኝ፣ አንተማ ለሀያ አመታት የተቀመጥከው… ያንተ ስቃይና መከራ ትዝ ብሎኝ ነው” አለው፡፡ ንጉስ ለአመታት ያላየውን እውነት እብዱ ባህሉን አሳየው፡፡ ንጉስም አለ “ከእብደት፤ ሚስጥር የእውነት ምንጭ ይገኛል፡፡”
ሌላው የጠቢባኑን የግል ሰብእና ከሚሰጡን እውቀት፣ ጥበብ፣ ብርሃን ጋር በመደባለቅ ማየት አግባብ አይመስለኝም፡፡ ለዚሁም አንድ ሻማ ሲበራ መጠቀም ያለብህ፣ ሻማው የሚሰጠውን ብርሃን በመንተራስ ሌላ ጥበብ… ምርምር… ሌላ እውቀትን ለህብረተሰቡ ሊሰጡና መሰላል ሊያወጡ የሚችሉ የህይወት ቀመሮችን በመቀመር ነው፡፡ አለዚያ ግን ይሄኛው ጥቁር ሻማ… ያኛው ነጭ… ቀይ… እያልን ጊዜያችንን ስናባክን ብርሃኑን በአግባቡ ሳንጠቀም ያልፈናል። ስለሆነም ከውስጣቸው የሚፈሰውን ከኔና ካንተ ውስጥ የሌለውን እውቀት፣ ብርሃን፣ … ጥበብ … መቅሰም ይጠቅማል ባይ ነኝ። ስብሃት ስካር ሲነጋ ይለቃችኋል፣ የኔና ያንተ ደደብነት ግን ዝንታለም አይለቀንም፡፡
ስለዚህ እኔ በበኩሌ ከዚህ አይነቱ ሀጥያት ይሰውረኝ ብያለሁ፡፡ ለምን ቢሉ አለማወቅን የመሰለ ሀጥያት የለምና… ለእኔ፡፡
ሌላው አንድ የጠየከው ጥያቄ ነበር። ዳኛቸው ወርቁ፣ በአሉ ግርማ፣ አቤ ጉበኛ… ብለህ ጠርተህ “ለዚህ ህዝብ አንድ ቀን እንጀራ አብስለውለታል?” ብለህ ጠይቀህ ነበር፡፡ አንዱና ዋናው ችግር ይህ ነው፡፡ ለምንድን ነው ህይወታችን በሌላ ሰው ላይ የሚመሰረተው ወይም እንጀራችንን ሰው እንዲጋግርልን የምንፈልገው? ማን ነው የራሱን ትቶ የሰው እንጀራ የሚጋግረው? የቱ ነው የጠቀስከው ሰው፣ ለሰው ብሎ የሚሰራ? ዶክተር? ነርስ? … መሃንዲስ ነው ድልድይ ለሰው የሚሰራ? እኔ የሚመስለኝ… ምን አልባት ይሻገርበት ስለፈለገ… አለዚያ ደግሞ ወደ ቀጣዩ ሌላ እንጀራ እንደሚያሻግረው አስቦ ለራሱ ሲል ነው የሚሰራው፡፡ እዚህ ላይ አንድ የሰማሁት የፈረንሳዮች አባባል ልጥቀስ “ሁሉም ለራሱ፣ እግዜር ለሁሉም”
ስለዚህ ሁልጊዜ ምን ምን ሰራሁ? እኔ ማን ነኝ? ለሀገሬስ በምን መልኩ አስተዋፅኦ አደረኩ ብሎ እራስን መጠየቅ በራሱ እውቀት (ብርሃን) የሚያመጣውን የመጀመሪያ ደረጃ መድስ ማለት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ የምትመከረው ወይም የምትለመነው የማይጠቅምህን ሁልጊዜ መተው ነው፡፡ ለምሳሌ ሬዲዮንን ስለጋሽ ስብሃት ማውራት ሲጀምር መዝጋት ወይም መስመርን መለወጥ እንዲሁም በETV  ሲመጡህ አሁን አሁን በጣም ተመስገን ነው ወዲያው … TV Africa … መለወጥ የተሻለ ዘዴ በመሆኑም፣ ይህን በመጠቀም የሚያደናቁርህን መሸወድ ትችላለህ፡፡ ስለዚህ ላንተ ያልተፃፈውን አለማንበብ ለምን ቢባል አይጠቅምህም እና… ጊዜና ወቅቱ ሲደርስ ላንተ የሚሆን… ሲፃፍ ማንበብን… ትመከራለህ፡፡ ለዛሬ መፅሀፍ ሳነብ ባገኘሁት ጥቅስ ልሰናበትህ።
“If your mind is not open, keep your mouth shut too” “Let’s hear what you have to say"
“እኔም ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልት እንዲሁም ጥበብ ከስንፍና እንደሚበልጥ አየሁ”
መክ፡13
“የሰው ልጆች ደስታ እና ጥበብ የሚከማቹት በመፅሃፍ ውስጥ ነው…
… ምንጊዜም እያንፀባረቁ ፍሬዎቻቸውም በማሰራጨት ለዘመናት አያሌ ሃሰሳቦችን እና ተግባሮችን ያመነጫሉ፡፡
(ምንጭ፡- አድማስ ሃምሌ 5 ቀን 1995)

Page 6 of 665