Administrator
“የንጉሱ ገመና” ለንባብ በቃ
በጋዜጠኛ ግርማ ለማ የተፃፈውና በቀዳማዊ ሀ/ስላሴ የቤት ውስጥ ውሎ፣ ቤተሰባዊ ህይወትና የጓዳ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነው “የንጉሱ ገመና” ለንባብ በቅቷል፡፡
መፅሀፉ እስከ ዛሬ በንጉሱ ዙሪያ ከተፃፉት መፅሀፎች የሚለየው በቤት ውስጥ ውሏቸውና ገመናቸው ላይ የሚያተኩር በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡ 170 ገፆች ያሉት መፅሀፉ፤ በአርጋኖ የህትመት ኢንዱስትሪ ታትሞ በጃፋር መፅሀፍ መደብር እየተከፋፈለ ሲሆን በ49 ብር ከ75 ሳንቲም ለገበያ መቅረቡም ታውቋል፡፡
“የአዕምሮ አስተዳደር ሞዴል” እና “ፍቅር ምንድነው?” ለንባብ በቁ
ነዋሪነታቸውን በለንደን ባደረጉት ኢንጂነር ወንድሙ ነጋሽ የተፃፉት “የአዕምሮ አስተዳደር ሞዴል” እና “ፍቅር ምንድን ነው?” የተሰኙ መፅሀፎች ለንባብ በቁ፡፡ እነዚህ መፅሀፎች ተከታታይ ክፍል እንደሚኖራቸው የተገለፀ ሲሆን በመጀመሪያው እትም ሰላም፣ ደስታና ፍቅር ስለማግኘት፣ በአላማ ስለመፅናት፣ ስሜትን ስለመቆጣጠር እና በራስ ስለመተማመን በስፋት መተንተኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በ49 እና በ59 ብር ለገበያ የቀረቡት መፃህፍቱ ቀጣይ ክፍላቸው ለህትመት በዝግጅት ላይ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ፀሀፊው ኢ/ር ወንድሙ ነጋሽ ላለፉት 15 ዓመታት በእንግሊዝ የጦር መርከቦችን ከአደጋ የመከላከል ሲስተም መሃንዲስ በመሆን ከመስራታቸው በተጨማሪ በስነ-አዕምሮና በስነ-ልቦና ላይ የተመሰረቱ ተከታታይነት ያላቸው ጥናታዊ መፅሀፍትን በመፃፍ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የመፃህፍቱ ተከታይ ክፍሎች ስለ ጣፋጭ ፍቅር፣ ስለ መልካም ግንኙነት፣ ስለ ስኬታማ ትዳር ስለ ስነ-አዕምሮና ስነ-ልቦና በሳል ግንዛቤ ያስጨብጣሉ ተብሏል።
“ስንክርተነ” የተባለ
የጉራጊኛ የግጥም መፅሀፍ ነገ-ይመረቃል
የቤተ ጉራጌ ባህል ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ በሆኑት በአቶ ተስፋዬ ጐይቴ የተፃፈው “ስንክርተነ” የተባለ የግጥም መፅሀፍ ነገ በደሳለኝ ሆቴል ይመረቃል። 135 ግጥሞችን ያካተተውና በ140 ገፆች ላይ የተመጠነው መፅሀፉ፤ በጉራጊኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ሲሆን አብዛኞቹ ግጥሞች የጉራጌን ባህል፣ ወግና ትውፊት ያስቃኛሉ ተብሏል፡፡ ትልቁን የነፃነት ታጋይ የኔልሰን ማንዴላን ህይወት የተመለከተ ረጅም ግጥም እንደተካተተበትም አቶ ተስፋዬ ጐይቴ ገልፀዋል፡፡
በ33 ብር ለገበያ የቀረበው መፅሀፉ፤ በሴትኛ አዳሪነት ህይወት እና በሌሎችም ማህበራዊ ህይወት ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን ፀሀፊው ከዚህ በፊት “የኬርጋት” እና “ጉራጌንዶ” የተሰኙ የግጥም መፃህፍትን በጉራጊኛ ቋንቋ ፅፈው ለንባብ አብቅተዋል።
ሶስተኛውና “ስንክርተነ” የተሰኘው የግጥም መፅሀፍ ነገ ጠዋት ከ2፡30 ጀምሮ ባለስልጣናት፣ የባህልና ቱሪዝም ሀላፊዎች፣ ጋዜጠኞችና ጥሪ የተደረገላቸው ሌሎች እንግዶች በተገኙበት በድምቀት ይመረቃል ተብሏል፡፡
“ፍለጋው” መፅሀፍ ለአንባቢያን ደረሰ
ነዋሪነታቸውን በለንደን ባደረጉት ኢንጂነር ወንድሙ ነጋሽ የተፃፉት “የአዕምሮ አስተዳደር ሞዴል” እና “ፍቅር ምንድን ነው?” የተሰኙ መፅሀፎች ለንባብ በቁ፡፡ እነዚህ መፅሀፎች ተከታታይ ክፍል እንደሚኖራቸው የተገለፀ ሲሆን በመጀመሪያው እትም ሰላም፣ ደስታና ፍቅር ስለማግኘት፣ በአላማ ስለመፅናት፣ ስሜትን ስለመቆጣጠር እና በራስ ስለመተማመን በስፋት መተንተኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በ49 እና በ59 ብር ለገበያ የቀረቡት መፃህፍቱ ቀጣይ ክፍላቸው ለህትመት በዝግጅት ላይ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ፀሀፊው ኢ/ር ወንድሙ ነጋሽ ላለፉት 15 ዓመታት በእንግሊዝ የጦር መርከቦችን ከአደጋ የመከላከል ሲስተም መሃንዲስ በመሆን ከመስራታቸው በተጨማሪ በስነ-አዕምሮና በስነ-ልቦና ላይ የተመሰረቱ ተከታታይነት ያላቸው ጥናታዊ መፅሀፍትን በመፃፍ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የመፃህፍቱ ተከታይ ክፍሎች ስለ ጣፋጭ ፍቅር፣ ስለ መልካም ግንኙነት፣ ስለ ስኬታማ ትዳር ስለ ስነ-አዕምሮና ስነ-ልቦና በሳል ግንዛቤ ያስጨብጣሉ ተብሏል።
ማህቶተ ጥበብ ዘልሳነ ግዕዝ ለንባብ በቃ
በመምህርት ኑሀሚን ዋቅጅራ ተፅፎ በኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርቲያን ማህበረ ቅዱሳን አሳታሚነት የተዘጋጀው “ማህቶተ-ጥበብ ዘልሳነ” ግዕዝ መፅሀፍ ለንባብ በቅቷል፡፡ 292 ገፆች ያሉት መፅሐፍ እየጠፋና እየተረሳ የመጣውን የግዕዝ ቋንቋ ለመታደግ ጥረት የተደረገበት ሲሆን በ20 ምዕራፎች ተከፋፍሏል፡፡
መፅሐፉ ስለ ግዕዝ ቋንቋ አመጣጥና ቀዳማዊነት፣ ስለ ግዕዝ ምንነት፣ ስለ ግዕዝ ፊደላትና ስለ በርካታ ጉዳዮች ቅኝት ያደርጋል፡፡ መፅሀፉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ማህበረ ቅዱሳን ታርሞና ተስተካክሎ የተፈቀደ ሲሆን መታሰቢያነቱ ለፀሀፊዋ የግዕዝ አስተማሪ የቅኔ መምህር እና ጥበብ ፕሮፌሰር መጋቤ ምስጢራት ጌዲዮን መኮንን የተደረገ ሲሆን በ50 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ፀሀፊዋ ከዚህ ቀደም ለአቡነ ጐርጐ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች የሚያገለግሉ ከአንደኛ እስከ አራተኛ፣ ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ እንዲሁም ከዘጠነኛ እስከ አስረኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች የሚረዱ መፅሀፍቶችን አዘጋጅታለች፡፡
ማህቶተ-ጥበብ ዘልሳነ መፅሀፍ ባለፈው ሳምንት በአማኑኤል ቤተ-ክርስቲያን ተመርቋል፡፡
አብረን ያደርን ቀን
ሰው እንዴት ተታሏል…
ምስራቅ ምትገኝ
ከምዕራብ በስተቀኝ
ሰማይ ላይ ነዉ ብሎ
ጀንበርን ሰቅሏታል አድማስ ላይ ጠቅሎ፤
ግን እንዲህ አይርቁም አይደሉም ሰማይ ላይ
ምስራቅም በከንፈር በጥርስ አምሳል ፀሀይ
እኔ ቤት አድረዋል ጠባብ መደቤ ላይ፡፡
* * *
አዝናለሁ ያዳም ዘር
ብርሃን ካልቀላወጥክ በጉበኔ ተገን
አ-ታ-ያ-ት-ም ነገን !!
ፍርቱና
ስንገናኝ…
ያርባ ቀን እድሌ ያርባ ቀን እድሉ
በቀለበት ታስረው ሰማንያ ተባሉ፤
ስንለያይ…
ሰማንያዉ ተቀዶ
ለሁለት ተጎርዶ
እኔ አርባዬን ይዤ ዳግም እናቴ ጋ
እሱ አርባዉን ይዞ ሌላ አርባ ፍለጋ፡፡
አበባ የሽጥላ
ድንበር አልባው የአፋር ማህበረሰብ
በኤርትራውያን ታጣቂዎች የተጠለፉትን ጀርመናውያን ያስመለሱ የአፋር ሽማግሌዎች ምን ይላሉ?
ከሁለት አመት በፊት ነው ድርጊቱ የተፈፀመው። በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች አንዱ ወደ ሆነው ኢርታአሌ ይጓዙ የነበሩ ጀርመናውያን ቱሪስቶች ከኤርትራ ድንበር አቋርጠው በመጡ ታጣቂዎች ሲጠለፉ ሁለት ኢትዮጵያውያን ተገደሉ፡፡ ከመካከላቸው ማምለጥ የቻለው አንድ ኢትዮጵያዊ፣ በአቅራቢያ ወደ ምትገኘው የአፍዴራ ቀበሌ ኩሩርዋድ መንደር በመምጣት የተፈጠረውን ሁኔታ ለአካባቢው ነዋሪዎች ተናገረ፡፡ የመንደሯ ሽማግሌዎችም በኤርትራ ከሚገኙ የአፋር ባላባቶች ጋር በመደራደር፣ ጀርመናውያኑ በህይወት እንዲመለሱ አደረጉ፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኘው የጀርመን ኤምባሲም ባለፈው ሳምንት የመንደሯ ሽማግሌዎች ጀርመናውያኑን በማስመለስ ላደረጉት ውለታ ምስጋና ያቀረበ ሲሆን ከትግራይ ደጋማ አካባቢዎች በመነሳት በአለት ውስጥ ለውስጥ ይሄድ የነበረን የዝናብ ውሀ አቅጣጫ በማስቀየር፣ ለህብረተሰቡ ጥቅም እንዲሰጥ ያሰራውን ፕሮጀክት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ኢዝሎር ሲሩስ በተገኙበት አስረክቧል፡፡
በኤርትራ ታጣቂዎች ተወስደው የነበሩትን ጀርመናውያን በማስመለስ ትልቅ ሚና የተጫወቱት ጊልሳ ያኢድ እና ሳልህ ኡስማን ሁኔታውን አስመልክቶ የተናገሩትን እንደሚከተለው በአጭሩ አቅርበነዋል፡፡
ቱሪስቶች ኢርታአሌን ለማየት ሲሄዱ ከአፍዴራ የሚያጅቧቸው ሁለት ሚሊሺያዎች እና አንደ መንገድ መሪ ይመደባል፡፡ ከኤርትራ የመጡት ሽፍቶች ሁለቱን ጀርመናውያን ጠልፈው ሲወስዱ ሁለት ኢትዮጵያውያንን ገድለው ነው፡፡ አንዱ ኢትዮጵያዊ ስላመለጠ ሁኔታውን መጥቶ ነገረን። በአፋር ባህል እኛን ብሎ የመጣ ሰው፣ እኛ መሬት ላይ መግደል ወይም ሲገደል ማየት ትልቅ ነውር ነው፡፡ ቱሪስቶቹ ምንም አይነት መሳሪያ አልያዙም። የውሀ ጥማቸውን ለመቁረጥ የላስቲክ ውሀ ብቻ ነበር የያዙት፡፡ ድርጊቱን እንደ ሰማን የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ሀይል፣ ፖሊስ እንዲሁም ሴቶች እና ህፃናት ሳይቀሩ ወደ ስፍራው ሶስት ቀን ተጉዘን ደረስን፡፡ ቦታው ከፍተኛ የውሀ እጥረት ያለበት ስለሆነ ግመሎቻችንን ውሀ ጭነን ነበር የሄድነው። ሴቶቹ እና ህፃናቱ ምግብና ውሀ ለማቅረብ ነው ተከትለውን የመጡት፡፡ የሄድነው እጅግ ተቆጥተን ነበር፡፡ ብንሞትም እንሙት እንጂ እኛን ብለው የመጡ የውጪ ሰዎችን አፍነው መውሰዳቸውና ሚሊሺያዎቹንም መግደላቸው እጅግ አስቆጭቶናል። አርታአሌን በቁጥጥር ስር ካዋልን በኋላ የተወሰኑት የተገደሉትን ሰዎች አስከሬን ጭነው ወደ አፍዴራ ሲመለሱ፣ እኛ በባህላዊው የአፋር የመረጃ መቀባበያ ዘዴ “ዳጉ” መሰረት መረጃ ማሰባሰብ ጀመርን፡፡ በኤርትራም ሆነ በኢትዮጵያ የሚኖረው አፋር በጎሳ የተሳሰረ ነው፡፡ ማንም የታጠቀ ሀይል ይሁን ሽፍታ ከጎሳው ባላባቶች ትእዛዝ አይወጣም፡፡ አስራ ሁለቱ የባላባት ልጆች ተሰባስበው መከሩ፡፡ ከአገር ውጪ ያሉ የባላባት ልጆችም የታገቱትን ሰዎች እንዲያስለቅቁ ጥሪ ቀርቦ መላላኩ ተጀመረ፡፡ ኤርትራ ለሚገኙት ባላባቶች ሰዎቻችን ለምን ተገደሉ? ተጠልፈው የተወሰዱት በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንዲነግሩንና አሳልፈው እንዲሰጡን ጠየቅናቸው፡፡ ባላባቶቹም በጥያቄያችን መሰረት የተጠለፉት ሰዎች እንዲመለሱ ተነጋገሩ። የባላባት ትእዛዝ የማያከብር ማንኛውም አፋር፣ የአፋር ዘር ያለበት ቦታ ላይ መኖር አይችልም። ታጣቂዎቹም ቢሆኑ የባላባቶችን ትእዛዝ ከጣሱ ማረፊያ ስለማይኖራቸው፣ የጠለፏቸውን ሰዎች ለመመለስ በተደረገው ድርድር ተስማሙ፡፡ የመንግስት አካላት በህገ መንግስት ላይ የሰፈሩ ድንጋጌዎችን እንደሚያከብሩ ሁሉ ሽፍቶችም ቢሆኑ የጎሳ ስርአቱንና ውሳኔውን ያከብራሉ፡፡ እኛም ድንበሩን ተሻግረን የተጠለፉትን ሰዎች ለመረከብ ኤርትራ ገባን፡፡ በኤርትራ ከሚኖሩ የአፋር ጎሳዎች አንዱ የሆነው የዳሂሜና ጎሳ ልጅ ሰዎቹን ይዞልን መጣ፡፡ እኛም ለሁለቱ አንዳንድ ግመል ሰጥተን፣ ውሀ የጫነችላቸውን አንድ ግመል አስከትለን ወደ መንደራችን ስንወስዳቸው፣ አጠገባቸው የነበሩት ሰዎች በጭካኔ ተገድለው፣ እነሱ በህይወት መመለሳቸው ደስታና ግራ መጋባት ውስጥ ከተታቸው፡፡ ደስታቸው ግን ወሰን አልነበረው፡፡
በኤርትራ ያሉ ታጣቂዎች እኛ ከቱሪስቶቹ በምናገኘው ጥቅም ደስተኞች ባለመሆናቸው በጣም እናዝናለን፡፡ እኛ ግን ማንም ቢሆን በኛ መሬት እንግዳ ሆኖ እስከመጣ ድረስ የደህንነቱን ጉዳይ በሀላፊነት መውሰድ ባህላዊ ግዴታችን ነው። ፈረንጆቹ እሳቱን ለመጎብኘት ሲመጡ የግመል ኪራይ፣የአጃቢ፣ የመንገድ መሪ --- እየተባለ ስለሚከፈለን ብዙ ጥቅሞችን እናገኛለን፡፡ ከዛን ቀን በኋላም ለቱሪስቶቹ የበለጠ ጥበቃ ማድረግ ጀመርን። አሁን በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ ከአስር በላይ የጎብኚ ቡድን ይሄዳል፡፡ ሁሉም በሰላም ደርሶ እየተመለሰ ነው። ከሁለት አመት በፊት ጠለፋውን የፈፀሙት ሰዎች ስላልተያዙም ልዩ የፀጥታ ሀይል እስከአሁን ጠለፋው የተደረገበት ቦታ ላይ ይገኛል፡፡
ኢህአዴግ ሰልፍ የማይጠራን እኮ ኑሮአችንን ሰልፍ ስላደረገው ነው!
የታክሲ---የዳቦ---የውሃ---የግብር---የቦሎ---ረዣዥም ሠልፎች----
- የማሌዢያው አውሮፕላን ኢትዮጵያ ውስጥ አልወደቀም ተባለ!
- “መሬት የግል ይሁን” የዘመኑ “መሬት ላራሹ” ነው እንዴ?
እኔ የምላችሁ … “አንድነት” ፓርቲ ባለፈው ሳምንት “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” የተሰኘውን ቁጥር 2 ንቅናቄ መጀመሩን ሰምታችሁልኛል?! አይዟችሁ … ብትሰሙም ችግር የለውም፡፡ ይሄኛው “ሽብር” ምናምን የሚል ነገር የለውም (“መሬት የግል ይሁን” ማለት ሽብር ነው እንዴ?) እናላችሁ … የአሁኑ አጀንዳዬ መሬት ነው ብሏል፤ ፓርቲው፡፡ አዎ! መሬት የግል ይሁን እያለ ነው- አንድነት፡፡ (ማን ነበር “ድርሻዬን” እያለ ያቀነቀነው?) እንደምታውቁት … ባለፈው ዓመት ፓርቲው ያደረገው ንቅናቄ፣ ለእኔ ቢጤ “አንድ ለእናቱ” ትንሽ ያስቦካ ነበር፡፡ በሚሊዮኖች ድምፅ “የፀረ-ሽብር አዋጁን አሰርዛለሁ” አይደል ያለው፤ አንድነት፡፡ ኢህአዴግ ያኔ በልቡ “On my dead body!” (ሞቻታለኋ!) ያለ አይመስላችሁም?
እውነት ግን ፓርቲው 1ሚ. ፊርማ አሰባስቧል ማለት ነው? ለነገሩ አንድነት ፓርቲ 1ሚ. ደጋፊ ያጣል ማለት ዘበት ነው፡፡ ፓርቲው ምንም አልተንቀሳቀሰም ቢባል እንኳ ኢህአዴግ አለለት! ከምሬ እኮ ነው … አውራው ፓርቲ በየሰበቡ የሚያስቀይማቸው ሰዎች፤ አንድም ባህርማዶ አሊያም እንደ አንድነት ያሉ ተቃዋሚዎችን መቀላቀላቸው አይቀርም (ጠላት በማብዛት ኢህአዴግ አቻ የለውም!) እኔ የምላችሁ … የኢህአዴግ አባላት ቁጥር ስንት ሆነ? ወይስ እንደ ኢኮኖሚ ዕድገቱ አሁንም እየገሰገሰ ነው፡፡ በነገራችሁ ላይ … ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ የምትሰለፍበት ጊዜ ትንሽ ቀረብ ሳይል አይቀርም (30 እና 40 ዓመት አይፈጅም ማለቴ ነው!) አንድ ወዳጄ ደስ ይለዋል ብዬ ይሄን የምስራች ብነግረው ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ? “እሰይ፤ ኢህአዴግ ተጨማሪ 30 እና 40 ዓመት ስልጣን አያስፈልገውም!” ብሎኝ ቁጭ አለ! እውነቱን ልንገራችሁ አይደል … ስለ ስልጣን ቀን ተሌት የሚያስበው ሥልጣን ላይ የተቀመጠ ብቻ ነበር የሚመስለኝ፡፡ ለካስ እንደ እኔ ወዳጅ ያለውም ስለ ስልጣን ያስባል፡፡ (“ወንበሩ እንደሆነ አንድ ነው” ያሉት የቀድሞው መሪ ትዝ አሉኝ!)
ወደ አንድነት “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” ንቅናቄ ቁጥር 2 ልመልሳችሁ፡፡ እንዳልኳችሁ … የአሁኗ ጥያቄ ወይም ንቅናቄ በመሬት ዙሪያ የምታጠነጥን ናት፡፡ በሌላ አነጋገር “የየግላችን መሬት ይሰጠን!” የምትል ቀጭን ጥያቄ፣ ወይም ትግል ናት፡፡ (የዘመኑ “መሬት ላራሹ”!) በእርግጥ “መሬት የግል ይሁን” የሚለው ጥያቄ፣ የኒዮሊበራሊዝም ጠረን እንዳለው ከሩቅ ያስታውቃል፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት መፈልፈያም ሳይሆን አይቀርም (በግምት ነው!) እናም ለኢህአዴግ አይመቸው ይሆናል (ሁሌ አይደላም አሉ!) ሌላው መካድ የሌለብን ግን ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ የገበሬ .. የጭቁን ህዝብ .. የአርሶአደር-- ፓርቲ ነው፤ ከስር መሰረቱ ማለቴ ነው፡፡ (አሁንማ ኪራይ ሰብሳቢዎች ተደባለቁበት!) እናላችሁ … ኢህአዴግ መሬት የግል እንዳይሆን የሚፈልገው አንዳንዶች እንደሚሉት፤ የጥንት የጠዋቱ የአልባንያ ፅንፈኛ ኮሙኒዝም ትዝ ብሎት ሳይሆን ቆሜለታለሁ ለሚለው አርሶ አደር አስቦ ነው። “መሬት የመንግሥት ይሁን ያልኩት ገበሬው እንዳይሸጠው ብዬ ነው” ይላል-ኢህአዴግ (ገበሬ “ዱርዬ” መሰለው እንዴ?) አንድነት ፓርቲ ይሄኔ ምን ይላል መሰላችሁ? (“ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ናት ይሏታል!”) “መሬት በመንግሥት እጅ ይሁን ያልኩት ገበሬው ስለሚሸጠው ነው ይበል እንጂ አሁን እሱ እራሱ ለውጭ ባለሃብቶች እየቸበቸበው ነው” ሲል ይተቻል አንድነት - አውራ ፓርቲውን፡፡
እዚህ ጋ ግን አንድነት ያላስተዋለው ጉዳይ ያለ ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ መጀመርያውኑም ገበሬውን መሬት ከመሸጥ ለመከላከል ሞከረ እንጂ እኔ ራሴ “መሬት አልሸጥም! ሃራም ነው!” አላለም እኮ! በነገራችሁ ላይ በአሁኑ የአንድነት የመሬት ጥያቄ ወይም ንቅናቄ ላይ አንዳንድ ኢህአዴጎች ቢሳተፉ እንዳይገርማችሁ፡፡ (የመሬት ሱስ እንደሃሺሽ ነው!) ለምን መሰላችሁ? ነገርዬዋ እኮ የድርሻ ጥያቄ ናት! ስንቱ የኢህአዴግ ሹማምንት በ“መሬት ወረራ” ዘብጥያ መውረዱንም እንዳትዘነጉብኝ፡፡ (የባለሥልጣናት ሃብት በኢንተርኔት ሊለቀቅ ነው የተባለው እውነት ይሆን?) እናላችሁ ---- “ሲሶም ብትሆንም የግሉን መሬት ቢያገኝ የሚጠላ የለም፡፡” ይላሉ የኒዮሊበራል ተንታኞች አሉ፡፡ (የመንግሥትም ሆኖ እኮ አልማሩትም!) እኔ የምለው--- መሬት “የመንግሥትና የህዝብ ነው” የተባለው ተቀየረ እንዴ? (መንግሥት ሳይጠቀልለው አልቀረም!) እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ ---- የ60ዎቹ ተማሪዎች የ“መሬት ላራሹ” ጥያቄ ሲያነሱ “መሬት የህዝብና የመንግሥት ይሁን” ማለታቸው ነበር እንዴ? (ታዲያ ኢህአዴግ ከየት አመጣው?)
ይሄን ሁሉ ስለፈልፍ መሬት አቅሌን አስቶኝ እንዳይመስላችሁ፡፡ የነገው የአንድነት ንቅናቄ ላይ ይገኛል ብላችሁም እንዳትጠብቁ፡፡ ወዳጆቼ፤ እኔ ሰፊ የጋዜጣ አምድ እንጂ ሰፊ መሬት ፈላጊ አይደለሁም (መሬት ላይ ይፃፋል እንዴ?) እናላችሁ … የመሬት ጉዳይ ሆኖብኝ ዝም ብዬ ብለፈልፍም ላነሳ የፈለግሁት ጉዳይ ግን ሌላ ነበር (“ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” አሉ!)
ምን መሰላችሁ የፈለግሁት? ተማፅዕኖ ነዉ - ለተቃዋሚ ፓርቲዎች በሙሉ!! (ተማፅኖቱን ያለማንገራገር ይቀበሉ ዘንድ እማፀናቸዋለሁ!) እናላችሁ----የፈለገ አፈናና ወከባ ቢደርስባቸው፣ የፈለገ ቢታሰሩና መብታቸው ቢጣስ … ሌላ መንገድ ይፈልጉ እንጂ የተቃውሞ ሰልፍ እንዳይጠሩን (የድጋፍም ቢሆን ማለቴ ነው!) በክፋት እኮ አይደለም!! ችግር ስላለ ነው፡፡ በነገራችሁ ላይ አንድነት ፓርቲ በዚህ በሁለተኛ ንቅናቄው፣ ህዝባዊ ስብሰባ እንጂ ሰልፍ ባለመጥራቱ በግሌም እንደ ህዝብም አድንቄዋለሁ (“የልብ አውቃ” አሉ!) “መንግሥት ስብሰባውን ለማደናቀፍ ከሞከረ ግን ወደ ሰላማዊ ሰልፍ እቀይረዋለሁ” ማለቱን ግን አልወደድኩለትም፡፡ እናም ሌላ አማራጭ ቢያስብ ደስ ይለኛል፡፡
ከምሬ ነው----“የእድገት ምስቅልቅሉ” እስኪያልፍልን ድረስ… የተቃውሞ ሰልፍ (የድጋፍም ቢሆን!) እንዳትጠሩን--- አደራ እላችኋለሁ! መቼም እስካሁንም ምክንያቴ ይገባችኋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ይኸውላችሁ … ሰልፍ አትጥሩን የምለው በሌላ ሳይሆን ኑሮአችን ራሱ ሰልፍ ስለሆነብን ነው፡፡ ለታክሲ መሰለፍ ከጀመርን ስንት ዓመት ሆነን? (ያውም ጠዋት ማታ!) የዳቦ ሰልፍስ? ብጫ ጀሪካል እየያዙ በየሰፈሩ ለውሃ መሰለፉስ? (“የቦቴ ውሃ” የተባለው እንደ ኔትዎርኩ ጠፋ እንዴ?) የመብራት ቅድመ ክፍያ ካርድም የሚገዛው በብር ብቻ አይደለም - በሰልፍም ነው!! በነገራችሁ ላይ ---- ኢህአዴግ ስራውን ስለሚያውቅ ሰልፍ መጥራት ትቷል! እንዴ ----- ኑሮአችንን ሰልፍ አድርጎታል እኮ!! ባይገርማችሁ----የመጪው ዓመት ምርጫ ካሁኑ ስጋት ሆኖብኛል (ምርጫም እኮ በሰልፍ ነው!)
እኔ የምለው … እንዲህ መሰለፋችን ካልቀረ ግን ለምን ይሄን የሰልፍ ገድላችንን ጊነስ ቡክ ላይ አናስመዘግበውም?! (ፈረንጅ እኮ እንግዳ ነገር ይወዳል!) እርግጠኛ ነኝ ---- ለተከታታይ ዓመታት እንደኛ የተሰለፈ የዓለም ህዝብ የለም፡፡ እናም ከዓለም አንደኝነቱን የሚቀናቀነን አይኖርም፡፡ (ይሄን ለማስመዝገብም ወረፋ አለው እንዴ!!)
የሰሞኗን ምርጥ ኩምክና ነግሬአችሁ ልሰናበት፡፡ ይሄ የገባበት ያልታወቀው 200 ተሳፋሪዎችን የያዘ የማሌዢያ አውሮፕላን ነው የቀልዱ ምንጭ፡፡ እናላችሁ … “አውሮፕላኑ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ አልወደቀም!” እየተባለ በእርግጠኝነት ሲወራ ነው የሰነበተው፡፡ “እንዴት ተረጋገጠ?” አትሉም
“ወደ አውሮፕላን ተሳፋሪዎቹ ሞባይል ሲደወል ይጠራል!”
አያችሁልኝ ---- ኢትዮጵያ ውስጥ ቢወድቅ ኖሮ አይጠራም ነበር ለማለት እኮ ነው!! (አይ ቴሌና ኔትወርክ!)
አንድ የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን “ቴሌ በዝባዥ ነው!” መባሉ ቆጭቷቸው ነው መሰለኝ “ቴሌ አትራፊ እንጂ በዝባዥ አይደለም!” የሚል ማስተባበያ እንደሰጡ ሰማሁ፡፡ ግን “አገልግሎት ሳይሰጥ ገንዘብ የሚወስድ ምን ይባላል?” (አትራፊ ሊሆን አይችልም!)
“የመሬት ጥያቄ ነው የኑሮ ውድነት ያመጣው”
በማርች 8 የጎዳና ላይ ሩጫ የታሰሩ 10 የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ቀጠሮ ተጠየቀባቸው
ማርች 8 አለማቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ በተካሄደው የሴቶች የጎዳና ላይ ሩጫ ‹‹አንዳንድ ያልተገቡ ድርጊቶች ፈፅማችኋል›› በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉ አስር ከፍተኛ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባላት ትላንት ፍ/ቤት ቀርበው ፖሊስ አራት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ጠየቀባቸው፡፡
በቁጥጥር ስር የዋሉት 7 ሴቶችና 3 ወንዶች የፓርቲው አባላት በጎዳና ላይ ሩጫ ‹‹አንዷለም ይፈታ፣ ርዕዮት ትፈታ፣ ውሃ ናፈቀን፣ መብራት ናፈቀን›› የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ ነበር ተብሏል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በከፍተኛ የአመራር ቦታ ላይ ያሉና ቋሚ አድራሻ ያላቸው እንደሆኑ በመግለፅ በዋስ እንዲፈቱ ቢጠይቁም ፖሊስ በበኩሉ፤ ወንጀሉ ውስብስብ በመሆኑ አራት ተጨማሪ ቀናት የምርመራ ጊዜ ያስፈልገኛል ሲል አመልክቷል፡፡
ፍ/ቤቱም የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና መብት በመከልከል ለትናንትና ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡ ትላንት ፍርድ ቤት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች ላይ ፖሊስ ተጨማሪ አራት ቀን ምርመራ ጊዜ ጠይቆ ፍ/ቤቱም ለመጭው ማክሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡