Administrator

Administrator

ኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ለአራት የልብ ሕሙማን ሕጻናት የነጻ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጿል። ይህንን የገለጸው ዛሬ ጳጉሜ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ባዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ ነው።


ሆስፒታሉ የተመሰረተበትን አንደኛ ዓመትና መጪውን አዲስ ዓመት በማስመልከት፣ ለአራት የልብ ሕሙማን ሕፃናት በነፃ ሕክምና እያከናወነ መሆኑን አስታወቋል። "ሕፃናትን በልብ ሕመም ከመሞት ተባብረን እንታደጋቸው" በሚል መሪ ቃል፣ ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ ለ32 ሕፃናት የተሳካ የልብ ቀዶ ሕክምና በነፃ ማከናወኑን የኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ባለቤትና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃን ተድላ በመርሃ ግብሩ ላይ ተናግረዋል።


ሆስፒታሉ 300 ሕፃናትን ለማከም አቅዶ፣ ከእነዚህ ውስጥ የ32 ሕጻናትን ያከናወነ ሲሆን፣ ይህም ነፃ የልብ ቀዶ ሕክምና በገንዘብ ሲሰላ፣ 26 ሚሊዮን ብር እንደሚገመት አቶ ብርሃን አመልክተዋል። ባለፈው አንድ ዓመት ሆስፒታሉ ብቻውን በመሆን ማሕበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን የጠቀሱት አቶ ብርሃን፣ በአሁኑ ወቅት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከ16 ሺህ በላይ የልብ ሕሙማን ሕፃናት ወረፋ ይዘው እየተጠባበቁ መሆናቸውን አስረድተዋል። በተጨማሪም፣ አንዳንዶች ወረፋ ላይ እያሉ ሕክምና ሳያገኙ እየሞቱ ስለሆነ፣ ተቋማትና ግለሰቦች ድጋፍ በማድረግ ሕጻናቱን ከሞት እንዲታደጓቸው ጥሪ አቅርበዋል።


"አንድን ሕፃን በቡድን ለአስር ማሳከም ይቻላል። በመተባበርና በመተጋገዝ ለውጥ ማምጣት ይቻላል” ብለዋል፣ አቶ ብርሃን ንግግራቸው ሲቋጩ።



የዕለቱ የክብር ዕንግዳ እና የኢትዮጵያ የልብ ማሕበር ፕሬዝዳንት አቶ እንዳለ ገብሬ ባደረጉት ንግግር፣ ከ11 ወራት በፊት ማሕበራቸው ከኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ጋር በመነጋገር እና የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ለልብ ቀዶ ጥገና እየጠበቁ ከሚገኙት ታካሚዎች መካከል በጎፈቃደኞችን በማስተባበር በዓመት 3 መቶ ሕጻናትን በኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ለማሳከም እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። አያይዘውም፣ ማሕበራቸው በተለያዩ የመንግስት ሆስፒታሎች፣ ይልቁንም በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተመዝግበው ወረፋ እየጠበቁ ከሚገኙ 16 ሺሕ ያህል ታካሚዎች መካከል፣ ባቋቋመው እና ሰባት አባላት ባሉት የሕክምና ባለሞያዎች ኮሚቴ እየመረጠ እንደሚልክ አቶ እንዳለ ተናግረዋል።


እስከ ዛሬ ድረስ 20 ያህል ታካሚዎች በኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ነጻ የሕክምና አገልግሎት እየተሰጣቸው “ይገኛል” ያሉ ሲሆን፣ የሆስፒታሉን ባለቤት እና መላ የሕክምና ባለሞያዎችን በማሕበሩ እና ታካሚዎች ስም ምስጋናቸውን በማቅረብ፣ ይህን የበጎአድራጎት ስራ ሌሎችም እንዲቀላሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የነፃ ሕክምና ተጠቃሚ የሆኑ ሕፃናትና ቤተሰቦቻቸው በተደረገላቸው የሕክምና ድጋፍ የታካሚዎቹ ጤና መመለሱን በመመስከር ለኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ምስጋና አቅርበዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ከተገኙ ዕንግዶች መካከል፣ አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ ሕክምና ተደርጎላቸው የተፈወሱ ልጆች የነገ አገር ተረካቢ መሆናቸውን አስታውሷል። አያይዞም፣ በአቶ ብርሃን ተድላ የተመሰረተው ኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ባከናወነው ሰብዓዊ ተግባር ያለውን ምስጋና ገልጿል።


በዚህ መርሐግብር ላይ ተጋብዘው ከተገኙት ዕንግዶች መካከል፣ የሆስፒታሉን ጥረት ለማገዝና አጋርነታቸውን ለማሳየት ባለሃብቶቹ አቶ ገበያው ታከለ 200 ሺህ ብር፣ አቶ ጌቱ ገለቴ 500 ሺህ ብር ለግሰዋል። አቶ ብርሃን ተድላ ለተደረገው የገንዘብ ድጋፍ በልብ ሕሙማኑ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

አድማስ ዩኒቨርስቲ 16ኛውን ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባዔውን በዛሬው ዕለት ጳጉሜ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. የተለያዩ የዩኒቨርስቲው አመራሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ፣ ኢንተርሌግዠሪ ሆቴል አካሄዷል። ዩኒቨርሲቲው ለዘንድሮው ጉባዔ የመረጠው የጥናትና ምርምር ርዕስ “የከፍተኛ ትምሕርት ጥራት፣ ጥናትና ምርምር፣ እንዲሁም የማሕበረሰብ አገልግሎት በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ” የሚል እንደነበር ተገልጿል።


ለአንድ አገር በወሳኝነት የሚጠቀሰውን የትምሕርት ጥራትና ከዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኮ አንዱና ዋነኛ የሆነውን የማሕበረሰብ አገልግሎት ምን እንደሚመስል፣ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ቀንድን የሚዳስስ የጥናትና ምርምር ወረቀት በጉባኤው ላይ ቀርቧል።


የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ሞላ ጸጋ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ዩኒቨርስቲያቸው ባለፉት 14 ዓመታት የትምሕርት ጥራትን ማዕከል ያደረገና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ጉባዔዎችን ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውሰው፣ በዚህም ረገድ ሃላፊነታቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

 
በዘንድሮውም የጥናትና ምርምር ጉባኤ በተመረጠው ርዕስ ዙሪያ፣ ምሁራን የጥናትና ምርምር ስራቸውን እንዲያቀርቡ በመጋበዝና ከቀረቡት ውስጥ የተሻለ ይዘት ያላቸውን በማወዳደር በዛሬው ዕለት ለጉባዔው ማቅረባቸውን የገለጹት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት፣ በዚህም ዘርፍ እየታየ ያለውን ክፍተት ለመሙላት መፍትሔ ጠቋሚ የሆኑ የጥናትና ምርምር ውጤቶች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

 
ከትምሕርት ሚኒስቴር፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ከባለድርሻ አካላት የተወከሉ ሃላፊዎች በዚህ ጉባኤ ላይ ተገኝተዋል።


አድማስ ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ባሉ ካምፓሶቹ ከ20 ዓመታት በላይ በርካታ ዜጎችን በተለያዩ የትምሕርት ዘርፎች በማስተማር፣ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎችን ባለሞያ ማድረጉ ሲነገር፣ በዚህ በአገሪቱ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል ዕጥረት በመሸፈን የበኩሉን አስተዋጽዖ እያደረገ ያለ ተቋም “ነው” ተብሏል፡፡

“ሁሉ ማርኬት” የተሰኘ፣ ዕቃ ለመሸጥ እና ለመግዛት የሚያስችል መተግበሪያ ይፋ መደረጉ ተገልጿል። ዛሬ ጳጉሜ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. በኤግዚቢሽን ማዕከል ኢንፊኒቲ ቴክኖሎጂ፣ ታሜሶል ኮሙኒኬሽንና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በ“ሲቢኢ ብር ፕላስ” ባዛር የሚሳተፉ ዲጂታል ነጋዴዎችን በመተግበሪያው ተጠቃሚ ስለማድረጉ ተመልክቷል።

የኢንፊኒቲ ቴክኖሎጂ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ልዑል መኮንን እንደተናገሩት፣ የመትግበሪያው ተጠቃሚዎች ከ10 ሺህ በላይ ከሚሆኑ ነጋዴዎች በዋጋ ጥራት እና ዓይነት አማርጠው ለመግዛት “ያስችላቸዋል” ብለዋል። አክለውም፣ ድርጅታቸው ከታሜሶል ኮሙኒኬሽን፣ አሰንቲክ እና ሲቢኢ ብር ጋር በመተባበር፣ “በዓይነቱ ለየት ያለ ሁሉማርኬት ቪሌጅ የተሰኘ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዲጂታል ነጋዴዎችን በአንድ ቦታ በአካል ከ500 ሺህ በላይ ደንበኞች ጋር ማገናኘት የሚያስችለውን መንገድ በኤግዚቢሽን ማዕከል ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በነጻ አዘጋጅቷል” ሲሉ አስታውቀዋል።

ይህም ዕድል ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት አቶ ልዕል ገልጸው፣ ከ50 በላይ ለሚሆኑ የተመረጡ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ጠቅሰዋል። በዚህም ምክንያት ከ150 በላይ የስራ ዕድል መፈጠሩን ነው ያስረዱት።

“ሁሉማርኬት” በተሰኘው ኤግዚቢሽን ማዕከል ውስጥ በተቋቋመው መንደር የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ እና የሽያጭ መጠናቸው እንዲያሳድጉ መደረጉን አቶ ልዑል ያብራሩ ሲሆን፣ የዲጂታል ግብይትን በማበረታታት ሽያጫቸው እንዲፋጠን “ተደርጓል” ብለዋል።
“የሁሉማርኬት ዓላማ የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት የሆኑትን የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን በዲጂታል መተግበሪያ የስራ ትስስር በመፍጠር ውጤታማ ማድረግ ነው” በማለት፣ አቶ ልዑል ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ኢንፊኒቲ ቴክኖሎጂ “ሁሉግራም” የተሰኘ በአገራችን የመጀመሪያ የሆነውን የሶሻል ሚዲያ የመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያ ለተጠቃሚዎች ማስተዋወቁ ተወስቷል።

  የዛሬ ትጋት ለነገ ትሩፋት ይሆናል ተብሏል። እውነት ነው። የትናንት ትጋት ለዛሬ በረከት ሲሆን እያየን አይደል? አዲስ አበባ እያማረባት ነው። በሚያስመሰግን ጥረት፣ የሚያስከብር ውበት፣ የሚያኮራ ውጤት ተገኝቷል።
አምረው የተሠሩ የከተማዋ አካባቢዎችን የሚጎበኙ የከተማዋ ነዋሪዎችን መመልከት ይቻላል። በተዋቡ መንገዶቿ ላይ ከሕፃን እስከ ዐዋቂ፣ ወላጆችና ልጆች፣ እንዲሁም ወጣቶች ዘና ብለው ይንሸራሸራሉ፣ መንፈሳቸውን ያድሳሉ። ያልነበረ አዲስ ዕድል፣ ያልነበረ አዲስ ልምድ ነው - በኮሪደር ልማት የተፈጠረዉ፡፡   
የአፍሪካ የከተሞች ፎረም” ሰሞኑን በአዲስ አበባ እየተካሄደ መሆኑስ? አዲስ አበባ “ኮራ” ብላ ማስተናገድ ትችላለች። ከመላ አፍሪካ የተሰባሰቡ 490 ከንቲባዎች፣ እንዲሁም ከዓለም ዙሪያ የመጡ የተቋማት መሪዎችና ባለሙያዎች የከተማዋን ውበትና ማራኪ ጎዳናዎቿን አይተዋል። በዐድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ውስጥ ታድመዋል። አዲስ አበባ ኮርታለች።  Adanech Abiebie Fans Club... - Adanech Abiebie Fans Club
በእርግጥም የሙዚየሙ ግንባታና የኮሪደር ልማቱ የሚያኮሩ ሥራዎች ናቸው። ያስመሰግናሉም።
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ለመልካም ውጤት እንዲበቃ የተጉ ሰዎች ምስጋና ይገባቸዋል በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ ለከንቲባ አዳነች አቤቤና ለሌሎች የአዲስ አበባ ከተማ  አስተዳደር ኀላፊዎች፣ ለተቋማትና ለሙያተኞች ሽልማት ሰጥተዋል።
ህዝብን በማስተባበር በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገር መለወጥ በኮሪደር ልማት ስኬቶች መማር እንደሚቻልም ተናግረዋል።  በየትኛውም የልማት ሥራ ህዝብን ማስተባበር፣ ማክበርና ማገልገል እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ ሲገልጹ፣ ዐቅማችን ህዝባችን ነው ብለዋል። በሐሳብም በገንዘብም የልማቱ ምንጮች ኢትዮጵያውያን እንደሆኑም ተናግረዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኮሪደር ልማትን ሐሳብ በማመንጨታቸው እንዲሁም የአመራርና የክትትል ድጋፍ በመስጠታቸው ሥራው ለውጤት መብቃቱን በመግለጽ አመስግነዋል። በሶስት በአራት ወር ውስጥ  የተከናወነው ሥራ፣ የከተማችንን ገጽታ የቀየረ፣ አዲስ የሥራ ባህልን ያዳበረና ለከተማችን ነዋሪዎች ምቹ መኖሪያ እንደትሆን ያደረገ ድንቅ ሥራ ነው ብለዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበላቸውን ምስጋና በአክብሮት በመቀበል፣ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በአጭር ወራት ውስጥ እንዲጠናቀቅ በትጋት ለሠሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኀላፊዎች፣ ለኮንትራክተሮች፣ ለሙያተኞችና ለከተማዋ ነዋሪዎች ሁሉ የተሰጠ ምስጋና ነው ብለዋል - ከንቲባዋ።ውብ፣ ፅዱ፣ ምቹ አዲስ አበባ! - Adanech Abiebie Fans Club | Facebook
ግን ምስጋና ብቻ እንዳልሆነም ሳይጠቅሱ አላለፉም። ለሕዝባችን ይበልጥ እንድንሠራና የላቀ ውጤት እንድናስመዘግብ ተጨማሪ የመንፈስ ብርታት ይሆነናል ብለዋል።
ለትናንት ምስጋና፣ ለነገ አደራ - የመሻገር ምዕራፎች
ሐሳብ በተግባር ወደ ውጤት ሲሸጋገር፣ ማመስገንና ማክበር ተገቢ ነው። ትናንት ሐሳብ ብቻ ነበር። ዛሬ በእውን የሚታይ በረከት፣ የሚጨበጥ ፍሬ ሆኗል። ነገር ግን መነሻ እንጂ ማብቂያ አይደለም። መማሪያና ማሳያ ነው። ገና ብዙ ይቀራል።
አዲስ አበባ ይበልጥ እያበበችና እየበለጸገች መቀጠል አለባት። የእስከዛሬው ሥራ የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው።  ወደ ሁለተኛ ምዕራፍ ሥራ ነው የተሸጋገረው።
ሁለተኛው ምዕራፍ ከመጀመሪያው መብለጥ ይኖርበታል የአዲሱ ዓመት ሥራ ከዘንድሮው የላቀና የተሻለ መሆን አለበት ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
መሻገር ሲባል፣ ከሐሳብ ወደ ተግባርና ወደ ውጤት መድረስ ነው። እንኳን ለዚህ አደረሳችሁ፣… እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ ይባል የለ! በሚያስመሰግን ትጋት፣ ለስኬት በቅተዋል። ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። ግን ተጨማሪ ኀላፊነትም “መጥቶባቸዋል”።
መሻገር ሲባል፣ ከመጀመሪያው ሥራ ከፍ ወዳለ ዓላማና ዕቅድ መሸጋገር፣ ከዘንድሮው ውጤት በመነሣት ላቅ ያለ የሥራ አደራ መቀበል፣ ከባድ ኀላፊነት መሸከም ነው። አዲሱ ዘመን መልካም የሥራና የብልጽግና ዓመት ይሁንላችሁ ይባል የለ! ወደ ላቀ ከፍታ የምትሸጋገሩበት የትጋት ዓመት ይሁንላችሁ እንደማለት ነው።
በአንድ ጎኑ፣ ለትናንት ጥረት ለተገኘው ውጤት ምስጋናና ምረቃ ነው።
በአንድ ጎኑ ደግሞ፣ ተጨማሪ ከባድ ዓላማና የኀላፊነት አደራ ነው።
ታዲያ፣ ጳጉሜ 1 “የመሻገር ቀን” ተብሎ መሰየሙ መልካም አይደለም?  
በእርግጥ፣ ወደ ከፍታ የመሻገር አደራ ቀላል “ሸክም” አይደለም። ከባድ ነው። ሥራ መውደድንና በብርቱ መትጋትን ይጠይቃል። ይህን የሚያጸና የሥራ ባህል እያዳበሩ፣ ለዚህ የሚመጥን አወቃቀርን እየገነቡ አሠራርን እያሻሻሉ መጓዝን ይጠይቃል። እንዴት?
በኮሪደር ልማት አማካኝነት እየተስፋፋና እየለመደ የመጣው “ቀን ከሌት የመሥራት ባህል” አንድ ጥሩ ምሳሌ ነው። የአዲስ አበባ መስተዳድር አስራ አንድ መስሪያ ቤቶች ላይ የአሠራር ማሻሻያ (ሪፎርም) እንደተከናወነ በዓመታዊ ሪፖርት ላይ መገለጹም ይታወሳል። ዘንድሮም ይቀጥላል ተብሏል ።
ውጤታማ፣ ቀልጣፋ፣ የጸዳ አገልግሎትንና አሠራርን እያስፋፉ እያሻሻሉ መጓዝ ያስፈልጋል። ጳጉሜ 2 “የሪፎርም ቀን” ተብሎ ተሠይሞ የለ!
የዛሬ ትጋት የነገ በረከት
አሠራርን ማሻሻል አስተሳሰብንም ማሻሻል ያካትታል። “አይቻልም” የሚል መንፈስን ማሸነፍ፣ እንዲሁም ለሥልጣን ያለንን አስተሳሰብ መለወጥ ይኖርብናል።
የኮሪደር ልማት ሲታቀድና ሲጀመር የነበረንን ስሜት አስታውሱ። የቁፋሮው ብዛት ለውጤት ይደርስ ይሆን የሚል ስጋት ያደረብን ሰዎች ጥቂት አይደለንም። አይፈረድብንም። ሥራ ሲጀመርና ሲቆፈር እንጂ ሲጠናቀቅና ሲመረቅ ማየት ብዙም አልለመድንም። ብርቅ እየሆነብን ሥጋት ያድርብናል።
ሲፈርስና ሲነቀል፣ ሲታጠርና ሲቆሽሽ እንጂ፣ ተተክሎና ተገንብቶ፣ በብርሀን ደምቆና ልምላሜ ለብሶ፣ አምሮና ተውቦ የማየት ልምድ ብዙ ስለሌለን፣ “አይቻልም” የሚል ስሜት ቢያጠላብን አይገርምም።
ደግነቱ፣ ትናንት ያየነው የቁፋሮ ትጋት ዛሬ ከተማዋን የሚያስውብ ድምቀት ሆኖልናል። አምረው በተሰሩ የአዲስ አበባ ሸጋ ጎዳናዎችና መናፈሻዎች ላይ ከማምሻው ጎራ እያልን መንፈሳችንን እናድሳለን። ጥቅሙ ግን ከዚህም ይበልጣል። አስተሳስብን የሚያስተካክል መነሻ ይሆንልናል።
ሐሳብን በተግባር አይተናልና፣ “አይቻልም” ከሚለው ደካማ አስተሳሰብ የሚያላቅቅ አርአያ አግኝተናልና፣ ለላቀ ውጤት፣ ከፍ ላለ ዓላማ፣ ለተጨማሪ ትጋት ያነሣሣናል። የትናንት ትጋት ዛሬ የሚጨበጥ ፍሬ ሲሆን ተመልክተናል። የዛሬ ትጋት የነገ በረከትና ትሩፋት እንደሚሆንልን ምን ያጠራጥራል።
ጳጉሜ 5 “የነገ ቀን” ተብሎ የተሰየመው አለምክንያት አይደለም።የኛዋ ከተማ፣ የኛዋ መዲና፣... - Adanech Abiebie Fans አዳነች አቤቤ አድናቂዎች | Facebook
ሥልጣን የሥራ ኀላፊነት ወይም “ሸክም” መሆን አለበት  
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኀላፊዎች እንደ ዘንድሮ ዐይነት የሥራ ብዛት ካሁን በፊት ገጥሟቸው ይሆን ብለን እንጠይቅ። ሥልጣን፣ ከባድ የኀላፊነት “ሸክም” የሚሆንባቸው አይመስላችሁም? በእርግጥ፣ መልካም ዓላማ ለያዘና ሥራን ለወደደ ሰው፣ “ሸክም” ሳይሆን ክቡር የሥራ ባህል ሆኖ ነው የሚታየው።     
ችግሮችን በስንፍና የማስተባበል ሳይሆን በጥረት እየፈቱ የመሻገር፣ ከዚያም ወደ ተሻለ ከፍታ፣ ለላቀ ውጤት እየተረባረቡ ወደ ላቀ ከፍታ የመሸጋገር ኀላፊነት ነው - ሥልጣን።
ሥልጣን በስንፍና የሚያሰፈስፉበት፣ በስግብግብነት የሚሻሙበት ነገር መሆኑ የሚቀረው በዚህ ዘዴ ሳይሆን አይቀርም። ለትልቅ የአስተሳሰብ ሽግግር ጥሩ ዕድል የሚከፍትልን አይመስላችሁም?
በእርግጥ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናል ማለት አይደለም። የኮሪደር ልማትም እንዲያ በዋዛ የተካሄደና እንደ ዘበት የተገኘ ውጤት አይደለም። ብዙ ፈተናዎች ነበሩበት።
ችግሮችን እየፈቱ፣ ጉዳቶችን እየቀነሱ መሻገር - በሰው ተኮር ዘዴ
የኮሪደር ልማት አየር ላይ አልተካሄደም። ከተማዋ ውስጥ መሬት ላይ ነው የተከናወነው። እናም፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ ከነባር የመኖሪያና የሥራ ቦታ የሚፈናቀሉ ለጉዳት የሚጋለጡ ሰዎች መኖራቸው አይካድም። ችግርን ማድበስበስ ሳይሆን በግልጽ ተጋፍጦ፣ ዕዳውን የመቻልና መፍትሔ የመፍጠር ኀላፊነትን ለመሸከም ፈቃደኛ መሆን ያስፈልጋል።
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት፣ ይህን የስህተትና ስንፍና መንገድ ለመቀየር ትልቅ ጥረት ተደርጎበታል። “ሰው ተኮር” የተሰኘው ዘዴ ይህንንም ይጨምራል ማለት ይቻላል። ራሱን የቻለ “የአስተሳሰብ ሽግግር ነው” ቢባልም አልተጋነነም።
ጉዳቶችን እየቀነሱና ችግሮችን እየፈቱ፣ ግንባታዎችን እያከናወኑ በፍጥነት ማጠናቀቅ ይቻላል። በእርግጥ ሁለቱንም ኀላፊነቶች ለመወጣት ፣ በተለመደው የአሠራር ልማድ አይቻልም። ቀን ብቻ ሳይሆን ሌሊትም መሥራት ያስፈልጋል። በፀሐይ ብርሀን ብቻ ሳይሆን፣ ማታም በአምፖል ከተሠራ፣… ለጉዳት ለሚጋለጡ ነዋሪዎች አጥጋቢ መፍትሔ መፍጠር ይቻላል። የልማት ግንባታዎችንም በፍጥነት ማካሄድ እንደሚቻል በኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ታይቷል።
በእርግጥ፣ ምንም ጉዳት አልደረሰም፤ የተቸገረ ሰው የለም ማለት አይደለም። የተቸገሩ መኖራቸው እውነት ነው። ነገር ግን፣ ቀደም ሲል ከነበሩ አሠራሮች እጅግ የተሻሉ የመፍትሔ አማራጮችን ለመስጠት ተችሏል። ዐቅም በፈቀደ መጠን ሁሉ ጉዳቶችን ለመቀነስ ብዙ ጥረት ተደርጓል። ይሄ ትልቅ ቁምነገር ነው።የብርሀን ዘመን ላይ ነን!... - Adanech Abiebie Fans አዳነች አቤቤ አድናቂዎች | Facebook


ከዚህ ጎን ለጎን፣ ትንሽም ይሁን ትልቅ ችግር ሲያጋጥም፣ በመንገድ ግንባታ ምክንያት የተፈጠረ የትራፊክ ችግርም ቢሆን በቸልታ እንደማይታለፉ በኮሪደር ልማት ላይ አይተናል። የመንግሥት ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ይቅርታ ጠይቀዋል። ነዋሪዎች የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በመገንዘብ ላሳዩት ትብብርና ለሰጡት ድጋፍም ምስጋናቸውን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ እና ከንቲባ አዳነች አበቤ ሁሉም የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ሲመረቁ፣ ለነዋሪዎች ድጋፍ ምስጋናቸውን ሳያቀርቡ ያለፉበት ጊዜ የለም።
የሉዓላዊነትና የኅብር ቀኖች - ለሕዳሴ ግድብም ለአዲስ አበባ ስኬትም።  
ከንቲባዋ፣ የነዋሪዎችን ትብብር በማድነቅና የኅብረትን አስፈላጊነት በመግለጽ፣ “አሁንም እጅ ለእጅ ተያይዘን የማንቀይረው እና የማንለውጠው ሁኔታ አይኖርም” በማለት ለሕዝብ ቃል ገብተዋል። በሕዳሴ ግድብ ላይ እንደታየው ነው በኮሪደር ልማት የሚደገመው። ኢትዮጵያውያን በኅብር ለአገራቸው ብልጽግና ከተባበሩ፣ የማይሳካ ነገር አይኖርም።
ጳጉሜ 3 የሉዓላዊነት ቀን፣ ጳጉሜ 4 ደግሞ የኅብር ቀን ተብለው ተሰይመዋል። 


        ነብሱን ይማረውና ሟቹ ገጣሚውና የሥነ-ጽሁፍ ሰው እንዲሁም የሰላው ሐያሲ አቶ ደበበ ሠይፉ ከማስተማሪያ ክፍለ-ጊዜዎቹ በአንደኛው የሚከተለውን ሙከራ ሰርቶ ነበር።
አንዲት ወፍራም ልጅ ከተማሪዎቹ መካከል ይመርጥና ወደ ሰሌዳው እንድትመጣ ይጠይቃታል። የተባለችውን ትፈጽማለች። ልጅቷ ከተማሪዎቹ ፊት እንድትቆም ያደርግና ሲያበቃ “እስቲ ይህችን ልጅ አሞግሷት” ይልና ይጠይቃል። ጥቂት ተማሪዎች እጃቸውን እያወጡ ማሞገስ ጀመሩ።
“የእኔ ድምቡሽቡሽ!” አለ አንደኛው። “የእኔ ትምቡኬ!” አለ ሁለተኛው።
“የእኔ ደልካካ!” ቀጠለ ሌላው። “የእኔ ሞንዳላ”።
“የእኔ ዱብዬ!” ወዘተ…
ተማሪዎቹ ማሞገሳቸውን ቀጠሉና ዘጠኝ ያህል ማሞገሻ ቃላት ተገኙ። ከዚያ ሙገሳው ቆመ። አቶ ደበበም በሉ እስቲ አሁን ደግሞ ስደቧት አለ። ከሞላ ጎደል የክፍሉ ተማሪ በሙሉ እጁን በሚገርም ፍጥነትና ልበ-ሙሉነት አወጣ። የስድቡ ሥነ-ስርዓት ቀጠለ።
የመጀመሪያው- “ጉርድ በርሜል!” አለ። ሁለተኛው “ግንዲሳ!” አለ። “ድብ!” አለ ሦስተኛው። “ድብዳብ!”፣ “የተነፈሰች ጎማ!”፣ “ግንድ እግር!”፣ “ግማሽ ተራራ!”፣ “ዝፍዝፍ!”፣”ድልብ!”፣ “መሲና”፣ “የጋራ ጉማጅ!”፣ “ቦክሰኛ!”፣ “ተንቀሳቃሽ ቤት!”፣ “የእኔ ሸበላ!” ወዘተ አሥራ አንድ ቃል ተገኘ።
ቀጥሉ ስደቧት አለ፡-
“ቀጫጫ!”፣ “የቆመች ፓስታ!”፣ “ወባ!”፣ “ሲምቢሮ!”፣ “ቋንጣ!”፣ “ሎሊ-ፖፕ እግር!”፣ “ደረቁቻ!”፣ “በልታ እማታስመሰግን!”፣ “ከሲታ!”፣ “ያለቀች መጥረጊያ!”፣ “ሣር!”፣ “ቆረቆንዳ!”፣ “ጎድናም!”፣ “የቆመች አፅም!”፣ “ጥላቢስ!”፣ “ስፒል!”፣ “ሹካ!”፣ “ሹል-ቴክስ!”፣ “ቀስት!”፣ “ጅማት!”፣ “ጣረ-ሞት!”፣ “ሳሙና ላይ የተሰካች ሰንደል!”፣ “ጠሟጋ!”፣… ወዘተ ባንድ ጊዜ ስድቡ ተዥጎደጎደ። ሰሌዳው ሞላ። “በቃ! በቃ!” አለ መምህሩ ጆሮውን በመዳፎቹ ውስጥ ቀብሮ።
ከዚህ በኋላ መምህሩ “ይሄውላችሁ ልጆች ማህበረሰባችን ይሄን ይመስላል።” የስድብ ቃላት ሞልተውናል። የማሞገሻ ቃላት ግን እንዳያችሁት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው።
***
በየኑሯችን ውስጥም ሆነ በየስብሰባው የምናየው የዚህን ባህል አባዜ ነው። “ንጉስ ሳይ፣ ክሰስ ክሰስ ይለኛል” የሚለውም ተረት ሥረ-መሰረቱ ይኸው አባዜ ነው። ስድብ፣ ግዝት፣ ተቃውሞ፣ ማንቋሸሽ፣ እርግማን በህዝብም፣ በመንግሥትም፣ በድርጅቶችም አንደበት ነጋ ጠባ ይመላለሳሉ። ለምስጋናና ለመልካም ስም ሙገሳ መስጠት (Merit) እንደ ታላቅ ኪሳራ ተቆጥረዋል። በየስብሰባው፣ በየግምገማው፣ በየመድረኩ የሚታየው በዚሁ ሌላውን በማንኳሰስና ድክመቱን በማጋነን አባዜ ራስን ትልቅ የማድረግና አንቱ የማለት ፈሊጥ ነው። ውስብስብ የባህል ሳንካ ነው። ትላንትም ነበር። ዛሬም አለ። የወደፊቱ ሊታሰብበት የሚገባ ነው።
የፖለቲካ ድርጅቶች እርስ በርስ ደግ ስራዎቻቸውን ለማየት ጭንቃቸው ነው። ከግለሰብ እስከ ማህበረሰብ ይህ ጣጣ አለ። ከላይ በመምህሩ ሙከራ እንዳየነው ስድብን እንደ ክላሸንኮቭ ጥይት ማከታተል፣ ምስጋናን እንደቦኩ ፀበል በጸሎት ጠብታ በጠብታ መጠበቅ፣ ባህላችን ከሆነ ውሎ አድሯል። ወደላይ የሚወጣን ሰው እግሩን ከመጎተት ጀምሮ ኃጢያቱን በማብዛት የእርግማን መአት ማውረድ፣ የተሻለ የሰራንና አዲስ መንገድ የቀየሰን አሊያም ታላቅ እመርታ ያሳየን ሁሉ ሰንክሎ ለመጣል ሸሚዝን መጠቅለልና ቀበቶን ማጥበቅ በደምና በአጥንት የተወረሰ ልማድ ሆኗል። ይህ ባህል በየቢሮው፣ በየቴያትር ቤቱ፣ በየት/ቤቱ፣ በየስፖርት ሜዳው የሚታይ ነው። የየቢሮው ኃላፊዎችና የየተቋሙ መሪዎች የተሰራውን ደግ  ስራ አሞግሰው ሞራል ከማጎልበትና የሥራውን እድገት ለማሳየት ከመጣር ይልቅ ያልተሰራውን ጠቅሰው ሁሉን አፈር-ድሜ አስግጠው “አትረቡም፤ እናንተን ከምመራ ሞቼ ባረፍኩ” ዓይነት “ግምገማ” ያካሂዳሉ። ማመስገን ካለባቸው ሰው በሌለበት፣ መራገም ካለባቸው ደግሞ ህዝብ በተሰበሰበበት ሆኗል ፈሊጣቸው። ማናቸውም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚም ሆነ የማህበራዊ መዋቅርና መደላድል መሰረቱ ጠብቆ፣ ልስኑ አምሮ ብሩህ የእድገት አቅጣጫ ለመያዝ ገና በመፍረምረም ላይ ባለበት አገር ብቅ ያለውን ደግ ነገር ሁሉ እየኮረኮምን ዘላቂ እድገት እናመጣለን ብሎ ማሰብ “ከአባ ቁፋሮ እሸት ተቀጥፎለት” እንደሚባለው ተረት ዓይነት ነው። ምንም ይሁን ምን በሀገራችን የሚታየውን አጠቃላይ ሁኔታ ደግ ደጉን ለማየት ዓይን ሊኖረን ይገባል። የምርጫ እንቅስቃሴ ጥሩ ሆኖ ያለንቀትና ያለዛቻ ቢሆን ደግ ነገር ነው። ድርጅቶች አመራሮቻቸውን በዲሞክራሲያዊ መንገድ መምረጥና መሻራቸው ያለ ዘለፋ ሲሆን ደግ ነገር ነው።
እርግጥ ሳንካና እኩይ ተግባሩ በበዛና በተወሳሰበ ቁጥር በመሀል ብቅ ጥልቅ የሚሉ እውነቶችንና ሐቀኛ ስራዎችን አንጥሮ አውጥቶ ማመስገን ይከብድ ይሆናል። ልፋት መጠየቁ አይቀርም። የባህል የልማድ ማህተም አለበትና። ያም ሆኖ ግን፣ ወደድንም ጠላንም ጥቃቅኖቹን በጎ ነገሮች በመልቀምና እንደ ችግኝ በማፍላት ነው ወደ ትላልቅ ዛፎች ልንቀይራቸው የምንችለው። የተከፈተውን በር ከማንኳኳት ገርበብ ያለውን ማስከፈት ይሻላል። ደሞ የተዘጋውን በር ለማስከፈት በጥሞና ማንኳኳት ከዚያ ይቀጥላል። እንጂ በጽንፈኝነት ኮረብታ ለኮረብታ ቆሞ ክፉ ክፉውን መደርደር ለፖለቲካ ፓርቲዎችም፣ ለመንግሥትም፣ ለህዝብም የሚበጅ ልማድ አይደለም። ለመጪው አዲስ ዓመት ብዙ ደግ ነገር ለማግኘት ዓይንንም ልቡናንም መክፈት ይፈልጋል። ከሁሉም በላይ ግን ቀና መሆንን ይጠይቃል። እስከ ዛሬ  በክፉ መንገድ ሞክረነው ያጣነውን እስቲ ዛሬ ደግሞ በደግ መንገድም እንሞክረው። ደግ ደጉን ያሳየን!!
አዲሱን ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የጤና፣ የብልፅግና ያድርግልን!!
አዲሱን ዓመት እርስ በርስ የምንተሳሰብበትና ለአገር የምናስብበት ያድርግልን!!
አዲሱን ዓመት ተነጋግረን-ተወያይተን  የምንግባባበት ያድርግልን!!
አዲሱን ዓመት እርስ በርስ የምንከባበርበት ያድርግልን!!
መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን!!

        • ጦርነት እንዳይፈነዳ ስጋት እንዳለው ገልጧል


        የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አቃፊና አሳታፊ ባለመሆኑ፣ ሕዝባዊ ቅቡልነት እንዳነሰው ዓረና ትግራይ ለሉዓላዊነት እና ዴሞክራሲ ገልጿል። ፓርቲው ባለፈው  ረቡዕ ነሐሴ 29 ቀን 2016 ዓ.ም  ባወጣው መግለጫ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የህወሓት የበላይነት የነገሰበት መሆኑንም አስታውቋል።
በክልላዊና አገር አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ባተኮረው በዚህ መግለጫው፤ በትግራይ ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በኋላ የተኩስ ድምጽ መቆሙ በአዎንታዊነት የሚወሰድ መሆኑን አመልክቷል። አያይዞም፣ ስምምነቱ በአግባቡ ባይፈጸምም፣ ተኩስ በመቆሙ ብቻ የክልሉ ሕዝብ በተስፋ እየኖረ መቆየቱን አትቷል።
ሆኖም ግን የህወሓት  አመራሮች ለሁለት ተከፍለው፣ አንደኛው ወገን ከኤርትራ መንግስት ጋር “ግንኙነት ፈጥሯል” ሲል የጠቀሰው ዓረና፤ ሌላኛው ደግሞ “ከፌደራል መንግስት ጋር በመሰለፍ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊያመራ የሚችል እንቅስቃሴ እያደረገ ነው” በማለት አብራርቷል። አክሎም፣ “ይህ ለትግራይ ሕዝብ ጥቅም ሳይሆን ለራሳቸው የስልጣን ጥቅም ሲሉ የሚያደርጉት ነው። ተቀባይነትም የለውም።” ብሏል፣ ፓርቲው በመግለጫው።
ለፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ አምዶም ገብረስላሴ፤ “ከኤርትራ መንግስት ጋር የሚሰራ ቡድን ‘አለ’ ያላችሁት ከምን ተነስታችሁ ነው?” በሚል ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ  ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ራሱ ይህንን ጉዳይ ገልጾታል። ሁለተኛ፣ የፌደራል መንግስት ከወራት በፊት ለፖለቲካ ፓርቲዎች ማብራሪያ ሰጥቶ ነበር። በዚያን ጊዜ አንደኛውን ቡድን በስም ሳይጠቅስ፣ ከኤርትራ መንግስት ጋር ግንኙነት እንዳለው መረጃ አጋርቶ ነበር። እኛ ከዲፕሎማቶች፣ ከተለያዩ አካላት መረጃ አጣርተን ነው ያረጋገጥነው። ይህ ግንኙነት በተደጋጋሚና በግልጽ እየተፈጸመ ነው። ‘ሕገ ወጥ’ በተባለው የህወሓት ጉባዔም ላይ በተወሰነ መልኩ ተነስቶ ነበር። ይህ ጉዳይ መልሶ ወደ ጦርነት የሚያስገባ ስለሆነ፣ እንቅስቃሴው መቆም እንዳለበትና  ተቀባይነት እንደሌለው ነው ያስገነዘብነው።” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
“ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጠንካራ አይደለም” ያሉት  አቶ አምዶም፤ “አስተዳደሩ አቃፊና አሳታፊ ባለመሆኑ፣ ሕዝባዊ ቅቡልነት አንሶታል” ብለዋል። “ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ፣ ጠንካራ መዋቅር መዘርጋት ባለመቻሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በአግባቡ እየሰራ አይደለም” ሲሉም ሊቀመንበሩ አስረድተዋል።
 የህወሓት የበላይነት የነገሰበት ጊዜያዊ አስተዳደር መሆኑን በመጥቀስም፣ “ከ90 በመቶ በላይ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ናቸው አስተዳደሩን የተቆጣጠሩት” ብለዋል።
ትግራይ ክልል ውስጥ በሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች፣ ምሁራንና ሌሎችም ከሲቪክ ማሕበራት የተውጣጣ ጠንካራ የሆነ እስከ ቀበሌ ድረስ መዋቅር መዘርጋት የሚችል ጊዜያዊ መንግስት ዳግም መዋቀር እንደሚኖርበት አቶ አምዶም ጥሪ አቅርበዋል። በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አሳታፊና አቃፊ መሆን እንደሚገባው አውስተው፣ “ሁለቱም ቡድኖች ወደ አካባቢያዊነት እንቅስቃሴ ማዘንበላቸው የትግራይን ሕዝብ አንድነት የሚጎዳ ነው። ትልቅ ስሕተት ነው” ሲሉ ተችተዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ “የተፈጠረው ልዩነት ያለ ግጭት እንዲፈታ እንሰራለን” በማለት መናገራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ይህን ያሉት ከትላንት በስቲያ ሐሙስ  በማይጨው ከተማ ህዝባዊ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው። አቶ ጌታቸው የሚመሩትና ጄነራል ጻድቃን ገብረ ትንሳኤ ያሉበት የከፍተኛ አመራሮች ቡድን ከሰሞኑ በትግራይ ክልል እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፤ ከቀናት በፊትም በዓዲግራት ተመሳሳይ ውይይት አድርጎ እንደነበር ተነግሯል። አመራሮቹ ወደ ማይጨው ባደረጉት ጉዞ በየመንገዱ የከተማው ሕዝብ እየወጣ እንደተቀበላቸው የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው ልዩነት ሕዝቡን እንደሚከፋፍል፣ ይህም በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት ከከተማዋ ነዋሪዎች ጥያቄ ቀርቧል። በተጨማሪም፣ በአመራሮች መካከል የተፈጠረው ‘እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል’ ዓይነት አካሄድ እንዲቆምም ጥሪ ተስተጋብቷል።
አቶ ጌታቸው ረዳ፤ የህወሓት ሕጋዊነትን ለሕዝብ በሚመጥንና የፕሪቶሪያን የሰላም ውል በሚያስከብር መልኩ ለመመለስ እንደሚሰሩ ገልፀዋል። እርሳቸው በሚመሩትና በደብረፀዮን ገብረሚካዔል (ዶ/ር) መካከል በሚመራው የህወሓት ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ልዩነት ያለግጭት እንዲፈታ እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።
“ከዚህ ውጭ የፕሪቶሪያን የሰላም ውል ለማፍረስ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ጦርነትን መጥራት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። በተጨማሪም፣ “የተፈጠረው ልዩነት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ከማድረግ ጎን ለጎን ተፈናቃዮች በአጭር ጊዜ ወደ ቀድሞ የመኖሪያ አካባቢያቸው እንዲመለሱ እናደርጋለን “ በማለት አክለዋል።

 የውጭ ምንዛሪ ዋጋ መናርና እንደልብ አለመገኘት የታሪፍ ማሻሻያውን ለማድረግ ገፊ ምክንያት ነው ተብሏል።


          አዲሱ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ ከመስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገልጿል። የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሽፈራው ተሊላ (ኢ/ር) ባለፈው ረቡዕ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ነሃሴ  ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ከ50 ኪሎ ዋት እስከ 200 ኪሎ ዋት ድረስ የሚጠቀሙ ደንበኞች ድጎማ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው ሲያብራሩ፣ 50 ኪሎ ዋት የሚጠቀሙ ደንበኞች የማሻሻያ ታሪፉን 75 በመቶ፣ ከ50 እስከ 100 ኪሎ ዋት የሚጠቀሙ ደንበኞች 40 በመቶ እንዲሁም ከ100 እስከ 200 ኪሎ ዋት ደግሞ 4 በመቶ ድጎማ እንደሚደረግላቸው ጠቅሰዋል። በማያያዝም፣ “በወር ውስጥ ከ0 እስከ 50 ኪሎዋት በሰዓት የሚጠቀሙ ደንበኞች ድጎማ ሳይደረግላቸው በትክክለኛው የታሪፍ ቀመር ቢሰላ 6 ነጥብ 01 በኪሎ ዋት መክፈል ቢኖርባቸውም፣ ድጎማ በመደረጉ ወደ 0 ነጥብ 98 ዝቅ ብሏል ወይም 84 በመቶ ድጎማ ተደርጎላቸዋል” ብለዋል።
በተጨሪም፤ ከ51 እስከ 100 ኪሎዋት ተጠቃሚ ለሆኑ ደንበኞች 61 በመቶ ድጎማ ተደርጎላቸው፣ ከ6 ነጥብ 01 ወደ 2 ነጥብ 34 ዝቅ እንዲል መደረጉን መ/ቤቱ አስታውቋል ፡፡ ከ101 እስከ 200 ኪሎዋት ለሚጠቀሙ ደግሞ፣ 35 በመቶ ድጎማ በማድረግ፣ ከ6 ነጥብ 01 ወደ 3 ነጥብ 91 የታሪፍ ዋጋ ተቀንሷል በማለት በመግለጫው ላይ አትቷል።
ይህ የተደረገው የታሪፍ ማሻሻያው -- ማለትም የተጨመረው 6 ብር -- የሚከፈለው በአንድ ጊዜ ሳይሆን ከመስከረም ጀምሮ በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ሽፈራው ተሊላ አመላክተዋል። በተጨማሪም፣ 50 ኪሎዋት የሚጠቀሙ ደንበኞች አሁን የሚከፍሉት 27 ሳንቲም እንደሆነ አንስተው፣ ነገር ግን ከመስከረም ጀምሮ የሚከፍሉት 35 ሳንቲም ይሆናል ሲሉ ዋና ስራ አስፈፃሚው አስረድተዋል።
የታሪፍ ማሻሻያው ጥናት ለአንድ ዓመት በሶስተኛ ወገን ባለሞያዎች ቡድን፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተውጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች መጠናቱን፣ ለነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ቀርቦ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደጸደቀ ተነግሯል።
የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ታሪፍ ጋር ሲነጻጸር በጣም ርካሽና  በጣም ዝቅተኛ ነው ሲል የሚያብራራው የታሪፍ ማሻሻያው ሰነድ፤ ለአብነት ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮን፣ ቶጎ፣ ቤኒን፣ ጋቦን፣ ኬኒያና ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ሲነጻጸሩ ለዜጎቻቸው “ውድ” ሊባል በሚችል ዋጋ የኤሌክትሪክ ሃይል እያቀረቡ እንደሚገኙ ያመለክታል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግብዓቶች መግዣ ዋጋ መሻቀብና የውጭ ምንዛሪ መናር፣ ብሎም እንደልብ አለመገኘት የታሪፍ ማሻሻያ ለማድረግ  እንደገፊ ምክንያት ተደርጎ በሰነዱ ላይ ተነስቷል።
የታሪፍ ማሻሻያውን በማስመልከት  ማብራሪያ የሰጡት በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ማሕበር፣ ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ተመራማሪ አቡሌ መሐሪ (ዶ/ር)፤ ማሻሻያው ጊዜውን የጠበቀ እንዳልሆነና ዝቅተኛ ገቢ በሚያገኙ የሕብረተሰቡ ክፍሎች ላይ ተጽዕኖውን እንደሚያሳርፍ ተናግረዋል። አያይዘውም፣ ከምንዛሪ ስርዓቱ ለውጥ እና ከምርታማነት ባሻገር፣ ይኸው ማሻሻያ የራሱን ጫና ይፈጥራል ብለዋል።
መንግስትን የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲያደርግ የሚያስገድድ ምክንያት አለ ለማለት እንደማያስደፍር የገለፁት ባለሙያው፤ “በአንድ ጊዜ ሁሉንም ነገር ለውጠን አንዘልቀውም። የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ስራዎች ቅድሚያ እየተሰጠ በሂደት ነው ይህን ጭማሪ ልንቋቋመው የምንችለው። በማሕበረሰቡ ላይ ተደራራቢ ጫና ስለሚፈጥር፣ የታሪፍ ማሻሻያው ተግባራዊ የሚደረግበት ጊዜ ሊታሰብበት ይገባል።” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

በሶዶ ሁለት ወረዳዎች የታገቱ ገበሬዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ነዋሪዎችን ለማስለቀቅ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ መከፈሉ ተገልጿል፡፡


         ላለፉት አምስት ዓመታት ከጉራጌ ዞን አስተዳደራዊ መዋቅር የወጣና በታጣቂዎች የተያዘ አንድ አካባቢ እንዳለ ተነግሯል። ይህ የተነገረው ከትላንት በስቲያ  ሐሙስ ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም፣  ጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ (ጎጎት) አዲስ አበባ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ለጋዜጠኞች በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጀማል ሳኒ በንባብ ባቀረቡት መግለጫ፤ በምስራቅ መስቃን ወረዳ፣ ኢንሴኖ ዙሪያ ያለው የጸጥታ ችግር ከ5 ዓመታት በላይ መፍትሔ ሳያገኝ፣ አሁንም በአሰቃቂ ሁኔታ የንፁሃን ህይወት እየተቀጠፈ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡  በአካባቢው የተፈጠረው የጸጥታ ችግር መነሻው “የ11/9 ቀበሌዎች ጥያቄ” የተሰኘው በምስራቅ መስቃን እና ማረቆ ወረዳዎች መካከል የተነሳው የ’ይገባኛል’ ጥያቄ እንደሆነ መግለጫው አትቶ፣ “መንግስት ይህንን ጥያቄ በአገራችን በሌሎች አካባቢዎች መሰል የ’ይገባኛል’ ጥያቄዎች በተፈቱበት ሕዝበ ውሳኔ እና ውይይት ከመፍታት ይልቅ በየጊዜው ፖለቲካዊ ፍጆታ በተጫነው ዕርቅ በማተኮሩ ችግሩ እየተባባሰ ሄዷል።” ሲል ትችቱን ሰንዝሯል፡፡
በኢንሴኖ ከመጋቢት 21 እስከ ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ሕጻናትን ጨምሮ 32 ወንዶችና 12 ሴቶች፣ በጠቅላላው 44 ሰዎች መገደላቸውን ፓርቲው በመግለጫው ጠቅሷል። በተጨማሪም  ከ6 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውንና 36 ሰዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ አስረድቷል፡፡
በጉራጌ ዞን የጸጥታ ችግር የተፈጠረበት “ቆስየ” የተሰኘው ሌላኛው አካባቢ መሆኑን ጎጎት አስታውቆ፣ “አካባቢው ሙሉ ለሙሉ መንግስታዊ መዋቅር ፈርሶ በጎበዝ አለቆች እጅ የገባ ነው።” ብሏል። አያይዞም፣ አካባቢው የጉራጌ ዞን አካል ቢሆንም፣ ላለፉት 5 ዓመታት ከዞኑ ቁጥጥር ውጪ በሌሎች አካላት ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ ፓርቲው በመግለጫው አመልክቷል፡፡
ይህንንም ተከትሎ በአካባቢው ነዋሪ የነበሩ የጉራጌ ተወላጆች “ከአካባቢው እንዲሰደዱ ተደርገዋል” ያለው ጎጎት፤ “በአካባቢው ሌሎች እንዲሰፍሩበት እየተደረገ ይገኛል።” ሲል ነው የጠቆመው፡፡ በዚህም የተነሳ መንግስታዊ አገልግሎት በመቋረጡ የአካባቢው ነዋሪ ለከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መጋለጡን፣ እንዲሁም ነባር የገበያ ቀኖች ሳይቀሩ መቋረጣቸውን ጠቅሷል።
ፓርቲው በዚሁ አካባቢ ግብር የሚሰበሰበው ይኸው ታጣቂ ሃይል መሆኑን በመግለጫው ቢያመላክትም፣ የታጣቂውን ሃይል ማንነት በይፋ አልገለጸም። ይሁንና ይኸው ታጣቂ ሃይል ቆስየ አካባቢ “የጉራጌ ዞን ሳይሆን የሃዲያ ዞን ነው” የሚል ሃሳብ እንዳለው፣ የጎጎት የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጀማል ሳኒ ተናግረዋል።
በተጨማሪም፣ ዳርጌ አካባቢ ከዞኑ የፀጥታ ሃይል አቅም ውጪ በመሆኑ ምክንያት የመከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው እንዲገባ መደረጉን በዚሁ መግለጫ ሲነገር፣ በአካባቢው መደበኛ የእርሻና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ደረጃ መታወካቸው ተብራርቷል። በሶዶ ሁለት ወረዳዎች የሃይማኖት አባቶችና ገዳማትን ሳይቀር ኢላማ እንዳደረገ የተነገረለት የዕገታ ተግባር በታጣቂ ሃይሎች “ይፈጸማል” ተብሏል።
ታጋቾችን ለማስለቀቅ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ብር እንደሚጠየቅ አስታውቆ፣ ከ16 በላይ የታገቱ ገበሬዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ነዋሪዎችን ለማስለቀቂያ በድምሩ ከ2 ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሺህ ብር በላይ ተከፍሏል  ብሏል፣ ፓርቲው በመግለጫው፡፡ በተጨማሪም  ከጥቅምት 2015 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ 10 ሰዎች በታጣቂዎች ተገድለው፤ ከ23 በላይ የሚሆኑ  ሰዎች ደግሞ ድብደባ ተፈጽሞባቸው፣ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቋል።
በምስራቅ መስቃን እና ማረቆ አካባቢዎች የሚፈጠረው የጸጥታ ችግር ውስጥ የመንግስት አመራሮች እጅ “አለበት” የሚል ስሞታ ከነዋሪዎች እንደሚሰማ በመጥቀስ፣ ጎጎት ይህንን ስሞታ እንዴት እንደሚመለከተው ከአዲስ አድማስ ለቀረበለት ጥያቄ፣ የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጀማል ሲመልሱ፤ “እየታሰሩና እየተፈቱ ያሉት በታችኛው መዋቅር ላይ ያሉ አመራሮች ናቸው። ችግሩ ከዚያም የዘለቀ ሊሆን እንደሚችል የራሳችን ግንዛቤዎች አሉን። ምናልባት እስከ ክልሉ ከፍተኛ አመራሮችም ድረስ ሊፈተሹ ይገባል። ክልሉ እነዚህን ፈትሾ ከጥቃቶችና ከሴራዎች ጀርባ ያለው ማን እንደሆነ በቅጡ ለይቶ ለሕዝብ ማሳወቅና ተገቢውን ዕርምጃ መውሰድ አለበት ብለን እናስባለን።” ብለዋል፡፡
ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተመሰረተ ጀምሮ፣ ተከታታይነት ባለው ግጭት አካባቢው እየታመሰ ይገኛል ያለው ፓርቲው፤ በምስራቅ መስቃን እና ማረቆ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው የ”11/9” ቀበሌዎች ጉዳይ በሕዝበ ውሳኔ መፍትሔ እንዲያገኝ በማድረግ፣ ሕዝቡ በመረጠው ወረዳ እንዲተዳደር እንዲደረግ ጥሪ ማቅረቡን ጠቁሟል፡፡
ፓርቲው በመግለጫው፣ በቆስየ አካባቢ የተፈጠረው “ወረራ” በአስቸኳይ እንዲቆም፣ መንግስት በወራሪዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድና የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ፣ እንዲሁም በአካባቢው የጉራጌ ዞን መንግስታዊ ተቋማት መደበኛ ስራቸውን እንዲጀምሩም ጠይቋል።
በሶዶ ወረዳዎች፣ ማለትም በሪፌንሶ፣ አማውቴ፣ ጢያ፣ በዱግዳ ቀላ እና ሌሎች አካባቢዎች ላይ የሚፈፀመው ዝርፊያ፣ ዕገታ እና አግቶ ገንዘብ መቀበል ተግባራትን ለማስቆም ተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊት ስምሪት እንዲደረግ ጎጎት  ጥሪ አስተላልፏል።
“ሕግ ይከበር፣ ሕዝብ ከጥቃት ይጠበቅ” በሚል መንግሥት ሃላፊነቱን እንዲወጣ በመቀስቀስ፣ የዜግነት ግዴታቸውን በመወጣታቸው ምክንያት የታሰሩ የጉራጌ የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱም ፓርቲው በመግለጫው ጥያቄ አቅርቧል።


ከማዕበል ማዶ!
የተረሳ የሚያስታውስ፤ የተከደነ የሚገልጥ፤
በየሀብከ ብርሃኔ ጥላሁን
➾ የመጽሐፉ ርዕስ:- ከማዕበል ማዶ … ገፀ ብዙ ስብዕና
➾ የመጽሐፉ አዘጋጅ፦ ደራሲ ተስፋዬ ማሞ
➾ የመጽሐፉ ይዘት:- የደራሲው ግለ ማስታወሻ
➾ የመጽሐፉ የገጽ ብዛት:- 364
➾ የመጽሐፉ የምዕራፍ ብዛት:- ስምንት
➾ የሕትመት ዓመት:- ፩ኛ ዕትም ነሐሴ 2016 ዓ.ም
➾ የመጽሐፉ የሽፋን ዋጋ፦ 450 ብር
እንደ መግቢያ
የታሪኩና የጽሑፉ ባለቤት ደራሲ ተስፋዬ ማሞ ወንድማገኝ ሁለገብ የጥበብ ሰው ነው፡፡ ደራሲ ነው- ዕፀ በለስንና የጨረቃ ጥሪን አስነብቦናል፡፡ የፊልም ደራሲ፣ ዳይሬክተርና ተዋናይ ነው- የፍቅር መጨረሻ እና የሬዲዮና የቴሌቪዥን ድራማዎችን አሳይቶናል፤ አስደምጦናል፡፡ የማስታወቂያ ባለሙያ ነው- በዘመናችን ተወዳጅ የሆኑ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎችን ሰርቶ አሳይቶናል፡፡ አዘጋጅ ነው፤ በሸገር ኤፍ ኤም የጥበብ መንገድ ብዙ የጥበብ ፍሬዎችን አስደምጦናል፡፡ ይህ ገለጻዬ ያንስበት ይሆናል እንጅ ‹‹አይይ በዛበት!›› ተብሎ የሚያሽኮረምም አይደለም፡፡ ይህንንም ለመረዳት ከማዕበል ማዶ… ገፀ-ብዙ መልኮቹን አንብቦ መጨረስ ብቻ በቂ ነው፡፡
ይህ ግለ ማስታወሻ (Memoir) ፀሐፊው በዘመኑ ከሚያስታውሳቸው የሕይወት ገጠመኞች ውስጥ መርጦ፣ የግድ መቆጠብ ስላለበት ከየዘርፉ መጥኖ ለአንባቢ ያቀረበበት ገፀ-ብዙ መልኮች ስብስብ ነው፡፡ ጸሐፊው ዋና ትኩረቱን በአንድ የእብድ ቀን ውሎ ገጠመኙ ጀምሮ ወዲያ ወዲህ እያላጋ በትውስታው ቅርርብ ስሜትና ምልከታ ላይ አተኩሮ የጻፈው ነው፡፡ እውነትን በልብወለዳዊ አተራረክ እየነዳ እንደስሜቱ ሲፈልግ በቃላት ምልልስ እያጫወተን፣ ሲፈልግ ባልነበርንበት ጊዜና ቦታ እየወሰደ በምስል ከሳች ቃላት ፍንዳታ እያስደነገጠን የጻፈው ነው፡፡
የተረሳ የሚያስታውስ፤ የተከደነ የሚገልጥ፤
ግለ ማስታወሻው መደበኛ የአጻጻፍ ሥልትን እየተከተለ፤ መረጃ እየሰጠ ለሚጠራጠሩ ማስረጃ እያቀረበ፤ እውነትነት የሞላው፤ የጸሐፊውን የሕይወት ማስታወሻ ከብዙ በጥቂቱ፣ ከረዥሙ በአጭሩ እየጨለፈ የሚያቀርብ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሆኖ ትናንቱን በማሳየት፣ በማስታወስ አስታውሶም የትናንት ራሱን ከዛሬ ማንነቱና ብስለቱ ጋር እያወዳደረ በመታዘብ፣ መኄስ ያለበትን የራሱ የሆኑ አሉታዊም አዎንታዊም ትችትና አድናቆቶችን አካቶ፤  ከስሜት ይልቅ እውነቱን፣ በማስረጃና በመረጃ እየተረተረ አሳይቶናል፡፡
በዚያ ትውልድ ውስጥ የቀለጡ ሻማዎች ብዙ ናቸው። ለምስክርነት ያልበቁ፤  "በዚያ ትውልድ ውስጥ ያመለጥናችሁ አልፋና ኦሜጋ እኛ ነን።" እያሉ በመመጻደቅ  ሲያደነቁሩን፤ ማዕከላዊ እውነቱን የገለጠልን የዚያ ትውልድ በጎ ምስክር አላየንም። ይህ ከማዕበል ማዶ ማስታወሻ ግን በማዕበል ቀዛፊው ሕይወት ውስጥ የዚያን ትውልድ ስህተቶችን፣ የጣና በለስ ፕሮጀክትን፣ የኤርትራን ጉዳይ፣ እውነታዊ ተጋድሎዎችን... ሁሉ በማዕበሉ ላይ የሕይወት መርከቡን እየቀዘፈ የሚነገር እውነት ገልጦልናል።
ይህን ግለ ማስታወሻ ስናነብ ከድርጊቱ ይልቅ ለድርጊቱ ያለውን ምልከታ፣ ከሕይወቱ ምዕራፍ ውስጥ ሊያስተምሩ የሚችሉትን መጥኖ መምረጡ እና በጊዜ ቅደም ተከተል አለመመራቱን እናስተውላለን። ምሁራን ‹‹በጣም ግላዊ ነገሮች በጣም ዓለም አቀፋዊ ናቸው፡፡" እንደሚሉት በጣም ግላዊ የሚባሉ የሚያሽኮረምሙ ኹነቶችን ያለስስትና ይሉኝታ ማካተቱ ከአጓጊነቱ ባሻገር ልብ ያሞቃል፡፡  
ግለ ታሪካቸውን መጻፍ ያለባቸው ሰዎች በሕይወታቸው ትልቅ ስኬት ያሳኩ ሰዎች መሆን እንዳለባቸው ስለግለ ታሪክ የጻፉ ምሁራን ሁሉ ይስማሙበታል፡፡ በዚህም ተስፋዬ ማሞ ግለ-ማስታወሻውን መጻፉ ‹ዘገየህ› ያስብለው እንደኾነ እንጅ አያንሰውም፡፡ ምክንያቱም ቢያንስ በልብወለድ ድርሰቱ፣ በፊልም ስራው፣ በማስታወቂያ ስራው፣ በመድረክ አጋፋሪነቱ ስኬታማ ሰው ነውና፡፡
በመጽሐፉ ከሌሎች ሰዎች ጋር የነበረውን ግንኙነት እንደ ገባር ተጠቅሞ ማስታወሻውን ስለሚያፈሰው፤ ተስፋዬ ራሱን ብቻ ሳይሆን እንደነ ምንተስኖት ያሉትን ሰዎች ታሪክ ጭምር በማቅመስ ስለሚተርክ ሰዎችን የማወቅ ፍላጎታችንን ይጨምረዋል፡፡ በዚህ አንድ መጽሐፍ ውስጥ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ታሪክ በትናንሽ ቅጽ ያስነብበናል፡፡
ማዕበሉ ወደላይ እና ወደታች (Up and Down) ብቻ ሳይሆን፤ ወዲህና ወዲያ፣ (Zigzag) ግራና ቀኝ (Left and Right) እና ወደኋላ ወደፊት (Back and Forth) ንውፅውፅታ የበዛበት የተረሳ የሚያስታውስ፤ የተከደነ የሚገልጥ ገፀ-ብዙ መልኮችን የሚያሳይ ማዕበል ነው። በዚህ ግለ ማስታወሻ ውስጥ የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ “በግል ሕይወቴ ከደረሰውና ካጋጠመኝ አንድፍታ ላውጋችሁ”  ከተሰኘው መጽሐፍ ላይ ዲያቆን ብርሃኑ አድማሱ ከጻፈው ቀዳሚ ቃል የፕሮፌሰሩን መጻሕፍ ከዳሰሰበት ሦስት አዕማድ ማለትም መራጭነት፣ አጓጊነት እና ሥዕላዊነት አንጻር የቃላቱን ማብራሪያ ወስጄ ከማዕበል ማዶን በመረዳቴ ልክ ለማሳየት እሞክራሁ፡፡
1.መራጭነት (Selectivity)
Selectivity is the quality of carefully choosing someone or something as the best or most suitable. መራጭነት ለመልክአ ነገሩ በጥራትም፣ በክብደትም ተስማሚ የኾነው ታሪክ መምረጥ ነው፡፡
‹‹ኤድዋርድ ቦለስ (Edward Bolles) የተባለ የሥነ ልቦናና የማስታወስ ክህሎት ማዳበር ባለሙያ ስለትውስታ እንዲህ ይላል፡፡ “We remember what we understand; we understand only what we pay attention to; we pay attention to what we want.” የተረዳነውን ነው የምናስታውሰው፤ ትኩረት የሰጠነውን ነው የምንረዳው፤ ትኩረት የምንሰጠው ደግሞ የምንፈልገውን ነው፡፡ በኤድዋርድ አመክንዮ ስንንተራስ የሰው ልጅ የሚመዘነው በሚያተኩርበት ቁም ነገር ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ሰው የትኳሬው ውጤት ነው፡፡ ትኳሬያችን ያለንበት ዛሬን ያነብራል፡፡ እኛ ማለት የትኩረታችን፣ የማስታወሳችን እና የመረዳታችን አቅምና ፍላጎት ውጤት ነን፡፡››
ጋሽ ተስፋዬ በሕይወት ዘመኑ ብዙ የሚያስታውሳቸው፤ ብዙ የተከዘባቸው  እና የፈነጠዘባቸው፤ መልካምም መጥፎም አጋጣሚዎች አሉት፡፡ ሁሉንም ግን እንዳልጻፈልን የተጻፈው ታሪኩ ይነግረናል፡፡ በማስተወሻው ውስጥ የመምረጥ ችሎታውን ሳስበው የመጻፍ ልምዱ ፍሬ አፍርቶ ስናነብ በሚሰጠን ደስታና አቀራረብ አይቼዋለሁ፡፡
በነገረን ታሪክ ውስጥ የመምረጥ ችሎታው ከፊልም፣ ከማስታወቂያ ባለሙያነቱ እና ከውበት አድናቂነቱ የመነጨ እንደሆነ ያሳብቃል፡፡ ለምሳሌ መጽሐፉ ላይ ‹‹መተከል ጉባ ገበያ ውለው፤ ባልደረቦቹ ‹ለመዝናናት እንደር!› ሲሉት ኃላፊነቱን ተጠቅሞ በመከልከል ወደ ፓዊ ይዟቸው ተመለሰ፡፡ ሁሉም አኩርፈውታል፤ መዝናናት ፈልገዋል፤ ከልክሎ በሚነዳው መኪና ይዟቸው ሂዷል፡፡ በነጋታው አያልነሽ የምትመራው ኢህአፓ ገብታ የሚገደለውን ገድላ፤ የሚታፈሰውን አፍሳ መሄዷ ተሰማ፡፡ ትናንት ያኮረፉት መልሰው ‹የነፍስ አባታችን ተስፍሽ› አሉ፡፡››
እንደገና ‹‹ቆንዝላ በሚሰራበት ወቅት ደግሞ ባህር ዳር ሲዝናኑ አድረው ጥዋት ሲመለሱ፤ የተመደበለት መኪና ተቀየረና በሌላ መኪና ተሳፈረ፡፡ ሹፌሩ በጣም ዘገምተኛ ናቸው፡፡ ተስፋዬ ፈጣን ሹፌር ስለሆነ ቀምቶ ለመንዳት አስቦ ተቁነጠነጠ ግን አልቻለም፡፡ ትዕግስቱን እየተፈታተነው ባለበት ቅጽበት ከፊቱ እሱ ሊሳፈርበት የነበረው መኪና በጥይት ተመቶ ይጨሳል፡፡ ከውስጥ ያሉትን ፈረንጆችና ሐበሾች ኢህአፓ ጠልፋ ወሰደቻቸው፡፡ እሱ ግን በሹፌሩ ቀስ ብሎ መንዳት ተረፈ፡፡›› ሁለቱ አገላለጾች አቻ ኾነው ከታሪኩ ውስጥ ባይመረጡ ኖሮ ማስታወሻውን ሚዛናዊና የመምረጥ ችሎታውን ድንቅነት አያሳይም ነበር፡፡ ጥፋት በጥፋት ይመለሳል፡፡ በጎ ነገርም በበጎ ነገር ይመለሳል፡፡
የራሱን ታሪክ የሚጽፍ ሰው በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍ ያለ ተቀባይነት ያለው፤ በሥራው ምልዑ የኾነ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ ጋሽ ተስፋዬ መርጦ ጽፎልናል፤ ሳይሰስት ታሪኩን ለእኛ ለአንባብያን መጥኖ ለግሶናል፡፡ ጽፎ ማቅረብ፤ አቅርቦም ማሳመን ትልቅ አቅም ይጠይቃል፡፡  ይህንንም አሳይቶናል፡፡
2.አጓጊነት (Excitement)
Excitement is a very Enthusiastic and Eager. አጓጊነት በአተራረኩና በታሪክ አወቃቀሩ ልብ ሰቃይነት በጣም መጓጓት ነው፡፡
‹‹አሜሪካዊው ጸሐፊ፣ አርታኢ እና መምህር ዊልያም ዚንሰር (William Zinsser) ስለአጓጊነት እንዲህ ይላል “Memoir… may look like a casual end even random calling up of bygone events. It’s a deliberate construction” ማስታወሻ ሲጻፍ እንዲሁ እንደነገሩ ከትውስታ ማኅደር እየተፈተሸ የወጣ ይመስላል፡፡ ግን አይደለም፡፡ በእቅድ የተደረደረ ኹነት እንጂ፡፡
ግለ-ማስታወሻ ላይ አጓጊነት ማለት ግጭት ወይም ሴራ ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንስ አንባቢን እያባበሉ ከመጀመሪያ ገጽ እስከመጨረሻው እያዝናኑ፣ እያስገመቱ፣ እያጠየቁ፣ እያስደመሙ…  የሚወስዱበት መጀመሪያ የጠየቁትን ጥያቄ እስከመጨረሻው መልስ ሳይሰጡ መዝለቅ ነው፡፡ ታሪኩ ቢታወቅ እንኳ ከምናውቀው እውነት ሌላ እውነት አለ ብሎ አንባቢን ማሳመን፡፡ በዚህ ውስጥ ከ“ለምን” ይልቅ “እንዴት” የሚለው ጥያቄ ትልቅ ቦታ አለው፡፡
አንዳንዴ አጫጭር ልብወለድ ሲኾን አንዱ ካልሳበን ጥለነው ሌላኛውን ልናነብ እንችላለን፡፡ ይህ ግን የማስታወሻዎች ስብስብ እንደመኾኑ ከርዕስ ርዕስ ሁሉም ተያይዘውና ተሰናስለው የተቀመጡ መኾን አይጠበቅባቸውም፡፡ አንዱን ርዕስ አንብበን ቀጥሎ ያለውን የምናነበው ስለወደድነው ሳቢ ስለኾነ እንጂ፤ እንደልቦለድ በጣም ተያያዥ ስለኾነ አንዱ የአንዱን ታሪክ ያን ያህል ስለሚያጎድል አይደለም፡፡››
ቋሚ ደመወዝ የለመደ ሰው እንዴት ምንም የሚጨበጥ ነገር ሳይኖር ስራ ትቶ፣ በድፍረት ቤት ተከራይቶ በቀን ሁለት ዳቦ እየተመገበ መኖር ይችላል? በባዶ ሆድ የሰው ፊት ያታክታል፣ ዙረቱም ይሰለቻል፡፡ በአጣብቂኝ ችግር ውስጥ በነርስነት ሙያ ለህሊና የማይመቹ ስራዎችን ሰርቶ የዕለት ጉርስና ያመት ልብስን ማስታገስ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ራስን አስኮንኖ ኪስን ከመሙላት፤ ችግርን እየተጋፈጡ መኖርን መምረጥ በጣም ያጓጓል፡፡
የችግሮች መደራረብ የመውጫ መንገዶችን ያበዛቸዋል፡፡ ከአንድ ችግር ጋር ሲጋፈጥ መውጫ መንገዱ አስቀድሞ ያጓጓል፡፡ ሲራብ የሚጠግብብት፣ ሲጠማ የሚረካበት፣ ሲታሰር የሚፈታበት፣ ከቤት ኪራይ ሲሰደድ ሌላ ቤት የሚያገኝበት፣ በኃላፊነት ሲወስን ከሞት የሚተርፍበት፣ መንገድ ሁሉ ልብ ሰቃይ በገድላት መጻሕፍት የምናነበውን በእግዚአብሔር ተራዳኢነት የተፈፀመ የእውነተኛ ታሪክን በማርክሲሳዊው ሕይወት ውስጥ ያሳየናል፡፡    
3. ስዕላዊነት (Pictoriality)
Pictoriality is consisting of, or expressed by words and pictures. በታሪኩ ውስጥ ያሉ ኹነቶች ምስል ከሳች በሆኑ ቃላት መግለጽ ነው፡፡  
‹‹እውነት የትም አለ፤ ውበት ግን ይለያል፡፡ መረጃ የትም አለ፤ አቀራረብ ግን ይገዛል፡፡ ብዙ ሰው ብዙ እውነታ ሊኖረው ይችላል፡፡ ግን እውነቱ ትርጉም የሚኖረው አቀራረቡ ላይ  ነው። ግለ ታሪክ ዜና አይደለም፤ በእውነት ብቻ ሊታጨቅ አይችልም፡፡ ዘገባም አይደለም አንድን ኹነት ብቻ ይዞ መቼና የቱን ነገሮን አያቆምም፡፡ ከነገሩ እውነታነት ብቻ ሳይሆን አቀራረቡ አንባቢን መያዝ አለበት፡፡››
አጻጻፉ ሥዕላዊ ብቻ ሳይሆን የፊልም ስክሪፕት ጸሐፊነቱም ጎልቶ ታይቶበታል፡፡ ተንቀሳቃሽ ምስል (video) ማለት “በጣም ፈጣን ተንቀሳቃሽ ፎቶ ነው፡፡” ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች፡፡ ሰው በባህሪው ስልቹ ስለኾነ ችኮ የቆመ ጅብራ ነገር አይወድም፡፡ ጽሁፍ ሲሆን ደግሞ አንድ ነገር ላይ መልሶ መልሶ ሲሆን ማሰልቸቱ አይቀርም፡፡
‹በፊልም ትይዩ ትዕይንቶች ይኖራሉ፡፡ ባለታሪኮቹ ከዚህም ከዚያም ታሪካቸው ይታያል፡፡ ካስፈለገም በእነሱ ውስጥ ያለው ትዝታ (ፍላሽ ባክ)  በካሜራና በኤዲቲንግ ታግዞ ዛሬ ላይ ትናንትን ድሮን እናያለን፡፡ ከማዕበል  ማዶ ጽሑፍ ላይ እንዲህ ያለ ዛሬ ላይ ትናንትን፤ ትናንት ውስጥ ነገን ከትናት ወዲያን በፈጣን ታሪኮች ታጅቦ እናያቸዋለን፡፡ በአንድ ታሪክ ውስጥ ሌላ ታሪክ እናነባለን፡፡ ሲያስፈልግ ወደ ኋላ መለስ ብለን ለኛ ዕድሜ ድሮ የሆኑትን እናነባለን፡፡›
ጸሐፊውም ባለታሪኩም እሱ እንደመኾኑ የሕይወት መርከቡን ቀዛፊው ካፒቴንም ራሱ ነው፡፡ ማስታወሻውን ስናነበው በቃላቱ አማካኝነት ከካፒቴኑ ጋር ማዕበሉን አብረን እንድንቀዝፍ ያስገድደናል፡፡ የተዘረጋውን ለማጠፍ፤ የተከፈተውን ለመክደን የምንችለው መጨረሻው ገጽ ላይ መሄጃ ስናጣ፤ መርከቧም መልኅቋን ስትጥል ብቻ ነው፡፡ ቃላቶቹ አዕምሯችንን ከመያዝ አልፈው ሥዕል እየሰጡ እንደፊልም እንድመለከተው አስገድዶኛል፡፡ አስገድዶ ደፋሪ፣ አስገድዶ አሳሪ፣ አስገድዶ አስቀያሚ በበዛበት ዓለም ውስጥ አስገድዶ መካሪ፣ አስገድዶ አስተማሪና አስገድዶ አስነባቢ ከማዕበል ማዶን ዐየሁ፡፡
እንደማጠቃለያ
‹‹አሜሪካዊው የግለ ታሪክ ጽሁፍ አብዮት አስነሺ ደራሲው ጄሪ ዋክስለር (Jerry Waxler) ስለግል ማስታዋሻ ጥቅም እንዲህ ይላል፤ “The more memoires I read, the more lessons I learn, first about the litrary from, second about other people, and third about myself”  ብዙ ማስታወሻዎችን ባነበብኩ ቁጥር ብዙ እማራለሁ፤ አንድም ከሥነ-ጽሑፍ፤ አንድም ስለሌላ ሰው ሰውነት፤ አንድም ስለራሴ ግንዛቤ አግኝበታለሁ፡፡ በማለት ስለ ግለ-ማስታወሻ ያትታል፡፡››
የማዕበሉ ቀዛፊ ካፒቴን የሕይወት መርከቡን በማዕበል ውስጥ ቀዝፎ ወደቧ ላይ መልኅቁን የጣለበት መንገድ ግላዊ ጥበብ እና ዕድል በመለኮታዊ ኃይል (Divine Power) ተችረውት እንደኾነ ያሳያል። ይህ መለኮታዊ ኃይልም ወደ ካፒቴኑ ዘንበል ሊል የቻለው በማርክሲሳዊ ጥምቀት ባልጠፋችው ወሏዊ ደግነቱ ምክንያት ይመስለኛል። ይህንንም የማለቴ ድፍረት የመጣው እስከ ቀራኒዮ ኮረብታ ተከትሎት እንባ ሲያስነባው፣ የማያምንበትን ስለት ሲያስለው፣ ስለቱም ሲፈፀምለት ዐይቻለሁና ነው።
ማዕበሉን አንድ ኮረብታ ላይ ቁጭ ብዬ እንደፏፏቴ በሚምዘገዘገው ጽሑፉ ውስጥ እያዬሁ ደክሞኝ ነበር። ከኖረው ሰው በላይ የኑረቱ ተመልካች እንዴት ሊደክመኝ ቻለ?  ብዬ መልስ የማፈላለጊያ ጊዜ እንኳ ሳላገኝ መርከቧ መልኅቋን ጣለችና ቀዛፊውም እኔም አረፍን፤ ተመስገን ነው። እኔም ከስነ ጽሑፉ፣ ከሌላው ሰው ሰውነት፣ ከሀገር ፍቅር ስሜት፣ ከራሴ አሁናዊ ኹነት ጋር አገናዝቤ ተማርሁበት፡፡
ጋሽ ተስፋዬ ማሞ ወንድማገኝ ስለሰጠኸን ውድ ማስታወሻ እናመሰግናለን!!
ዋቢዎች
•   ጌታቸው ኃይሌ፣ በግል ሕይወቴ ከደረሰውና ካጋጠመኝ አንዳፍታ ላውጋችሁ፣ 2ተኛ ዕትም፣ ብራና መጻሕፍት መደብር፣ ጃጃው አታሚዎች፣ አዲስ አበባ፣ 2013 ዓ.ም፡፡
•    ቃል ኪዳን ኃይሉ፣ ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው?፣ የእስከዳር ግርማይ መጻሕፍ ዳሰሳ፤ ያልታተመ፡፡

ዮሀንስ አያሌው  በስራ ዘመናቸው ባንኩ ከነበረበት ችግር ማላቀቅ ችለዋል። የሐንስ ባንኩ ከነበረበት ኪሳራ በማንሳት ትልቁ የባንኩ ታሪክ ላይ ስማቸው ያኖሩ ናቸው።

Page 2 of 722