Administrator

Administrator

 መላው አለም ውጤታማነታቸው ከተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች ጋር ተመሳስለው የተሰሩና ለጤና ጎጂ የሆኑ ሃሰተኛ ክትባቶችን በህገወጥ መንገድ በድብቅ ለመሸጥና ትክክለኛ ክትባቶችን መዝረፍን ጨምሮ በርካታ “ኮሮና ነክ ወንጀሎችን” ለመፈጸም ያቆበቆቡ የተደራጁ ወንጀለኞችን ነቅቶ እንዲጠብቅ አለማቀፉ የፖሊስ ተቋም ኢንተርፖል አስጠንቅቋል፡፡
የተለያዩ አገራት ኩባንያዎችና የምርምር ተቋማት ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ጥቅም ላይ ለማዋል የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ በደረሱበትና አገራት ክትባቶችን ቀድመው ለማግኘት በሚሯሯጡበት እንዲሁም የግዢ ስምምነት በመፈጸም ላይ በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት፣ የተደራጁ ወንጀለኛ ቡድኖች ሃሰተኛ ክትባቶችን ለመቸብቸብ እንዲሁም ትክክለኛ ክትባቶችን ለመዝረፍ እየተዘጋጁ እንደሚገኙ መረጃ ደርሶኛል ብሏል ኢንተርፖል ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ።
ተቀማጭነቱ በፈረንሳይ የሆነው አለማቀፉ የፖሊስ ትብብር ተቋም ኢንተርፖል፣ በአባልነት ላቀፋቸው 194 የአለማችን አገራት በላከው የማስጠንቀቂያ መልዕክት፣ የተደራጁና ረጅም የወንጀል ሰንሰለት የፈጠሩ ወንጀለኞች ከኮሮና ክትባቶች ጋር በተያያዘ አካላዊም ሆነ በኢንተርኔት በኩል የሚካሄድ የወንጀል ድርጊት ሊፈጽሙ ስለሚችሉ የህግ አስከባሪ አካላት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተለያዩ የአለማችን አገራት ባልተጠበቀ ሁኔታ ለስግብግብ ወንጀለኞች መጠቀሚያ መልካም እድል ከሆነ መሰነባበቱን ያስታወሰው ተቋሙ፣ በቀጣይም ከጥራት በታች የሆኑ ሃሰተኛ ክትባቶችን በድብቅ አምርቶ መሸጥ፣ የክትባቶች ዝርፊያና ህገወጥ የክትባት ማስታወቂያዎችን ጨምሮ ኮሮና ተኮር የወንጀል ወረርሽኝ በስፋት ሊሰራጭ እንደሚችል ያለውን ስጋትም ገልጧል፡፡
ወንጀለኛ ቡድኖቹ ከዚህ ባለፈም ሃሰተኛ የኮሮና መመርመሪያ መሳሪያዎችን በህገወጥ መንገድ አምርተው ለገበያ የማቅረብ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ የጠቆመው ተቋሙ፣ የአለም አገራት መንግስታት፣ የጸጥታ ሃይሎች፣ ህግ አስፈጻሚና የደህንነት ተቋማት እነዚህን ወንጀለኞች ለመከላከልና በቁጥጥር ስር ለማዋል በንቃት እንዲሰሩና ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጥሪ አቅርቧል፡፡
መድሃኒቶችን በመሸጥ ስራ ላይ ከተሰማሩ 3 ሺህ ያህል ድረገጾች ላይ ባደረገው ምርመራ፣ ከ1 ሺህ 700 በላይ የሚሆኑት ለወንጀል የተቋቋሙ ወይም በቫይረስ አማካይነት የኢንተርኔት ጥቃት የሚያደርሱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ መቻሉን የሚናገረው ተቋሙ፣ ህብረተሰቡ በድረገጾች አማካይነት ከሚከናወኑና ሰዎችን ለሞት አደጋ ብሎም ለከፋ የጤና ችግሮች ከሚያጋልጡ የሃሰተኛ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ሽያጮች ራሱን እንዲያርቅም ምክሩን ለግሷል፡፡
የአሜሪካው የአገር ውስጥ ደህንነት ምርመራ ቢሮ በበኩሉ፣ ከሰሞኑ በአገሪቱ ሁለት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች እውቅና አግኝተው በስራ ላይ ይውላሉ ተብሎ ከመጠበቁ ጋር በተያያዘ አጭበርባሪዎች ይበራከታሉ ተብሎ በመገመቱ አዲስ ዘመቻ እንደሚጀምር ማስታወቁን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
ከዚህ በፊት ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባደረገው ዘመቻ ከጥራት በታች የሆኑ የፊት መከላከያ ጭንብሎችንና ለኮሮና ፈዋሽነቱ ያልተረጋገጠውን ክሎሮኪን የተባለ የወባ መድሃኒት አስመስለው ማምረትና ማከፋፈልን ጨምሮ ከ700 በላይ ኮሮና ነክ ወንጀሎችን መመርመሩን ያስታወሰው ቢሮው፣ ከመሰል ህገወጥ ንግድ የተገኘ 27 ሚሊዮን ዶላር መያዙንና በመሰል ድርጊቶች ላይ ተሰማርተው የተገኙ ከ70 ሺህ በላይ ህገወጥ ድረገጾችን መዝጋቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌሎች የኮሮና ቫይረስ ዜናዎች ደግሞ፣ ብሪታኒያ ፋይዘርና ባዮንቴክ የተባሉት ኩባንያዎች ያመረቱትና ከኮሮና ቫይረስን በመከላከል ረገድ 95 በመቶ አስተማማኝ እንደሆነ የተረጋገጠው የኮሮና ቫይረስ ክትባት በግዛቷ ውስጥ በጥቅም ላይ እንዲውል በመፍቀድ ከአለማችን አገራት ቀዳሚ መሆኗን የዘገበው ቢቢሲ፣ አገሪቱ ከኩባንያዎቹ 40 ሚሊዮን ክትባቶችን ማዘዟንና የአገሪቱ የመድሃኒት ቁጥጥር ተቋም ክትባቱ ከመጪው ሳምንት ጀምሮ ጥቅም ላይ መዋል ይችላል ሲል ፈቃድ መስጠቱንም ገልጧል፡፡ የጃፓን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መንግስት በበኩሉ፤ ባለፈው ረቡዕ ባሳለፈው ውሳኔ፣ መንግስት በአገሪቱ ውስጥ ለሚኖሩት 126 ሚሊዮን ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ክትባትን በነጻ እንዲያዳርስ መወሰኑን ያሁ ኒውስ የዘገበ  ሲሆን፣ የአገሪቱ መንግስት ሞዴርና ከተባለው የክትባት አምራች ኩባንያ ለ85 ሚሊዮን ሰዎች፣ አስትራዜንካ ከተባለው ክትባት ደግሞ ለ120 ሚሊዮን ሰዎች የሚሆን ክትባት ማዘዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ቢዝነስ ኢንሳይደር በበኩሉ፤ የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጁንግ ኡን በቻይና የተመረተና ውጤታማነቱ ያልተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ክትባት መከተባቸውን የዘገበ ሲሆን፣ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ቤተሰቦቻቸውም ክትባቱን ወስደዋል መባሉን አክሎ ገልጧል፡፡  ኢንተርናሽናል ኤስኦኤስ የተባለው ተቋም በ2021 የፈረንጆች አመት ለጎብኝዎችና መንገደኞች እጅግ አደገኛ የሆኑና ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ይኖርባቸዋል ያላቸውን የአለማችን አገራት ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ሊቢያ፣ ሶርያና አፍጋኒስታን ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
የፖለቲካ ነውጥ፣ ማህበራዊ አለመረጋጋት፣ የደህንነት ሁኔታ፣ የአደጋ ጊዜ ምላሽ አገልግሎቶች ሁኔታ እና የወንጀል ድርጊቶችን ጨምሮ በተለያዩ የደህንነት ስጋት መመዘኛዎች ተጠቅሞ በመገምገም፣ የአለማችን አገራትን የአመቱ የስጋት ደረጃ ይፋ ያደረገው ተቋሙ፣ ኢራቅና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የአራተኛና አምስተኛ ደረጃ መያዛቸውንም አመልክቷል፡፡
በአመቱ እጅግ አነስተኛ የስጋት ደረጃ ይኖራቸዋል ተብለው በሪፖርቱ የተጠቀሱት ሰባት የአለማችን አገራት በሙሉ የአውሮፓ አገራት ሲሆኑ፣ አይስላንድ፣ ዴንማርክ፣ ኖርዌይ፣ ፊንላንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ ስሎቫኒያና ሉግዘምበርግ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተጓዦች መይም መንገደኞች ላይ እጅግ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረባቸው ሶስቱ የአለማችን አገራት ብሎ ተቋሙ የጠቀሳቸው አገራት ሩስያ፣ ዩክሬንና ኦስትሪያ ሲሆኑ፤ በአንጻሩ አነስተኛ ተጽዕኖ ያደረሰባቸው ያላቸው አገራት ደግሞ ኒውዚላንድ፣ ታንዛኒያና ኒካራጓ ናቸው፡፡


በአለም ዙሪያ በየ100 ሰከንዱ 1 ህጻን በኤችአይቪ ቫይረስ እንደሚጠቃ እና ባለፈው የፈረንጆች አመት 2019 በመላው አለም 110 ሺህ ያህል ህጻናት በኤድስ ምክንያት ለሞት መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በአመቱ በመላው አለም 320 ሺህ ያህል ህጻናትና ወጣቶች በቫይረሱ መያዛቸውን ያስታወቀው ድርጅቱ፤ በቫይረሱ የሚያዙና ለሞት የሚዳረጉ ህጻናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ሲሆን የጸረ ኤች አይቪ ህክምና አገልግሎት በበቂ ሁኔታ እያገኙ እንዳልሆነም ገልጧል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ለህጻናት፣ ወጣቶችና ነፍሰጡር እናቶች የሚሰጡ የጸረ ኤች አይቪ ህክምና አገልግሎቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተስተጓጎሉ እንደሆነ የጠቆመው የድርጅቱ ሪፖርት፤ መንግስታት አገልግሎቶቹን ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸውም አመልክቷል፡፡
በ2019 የፈረንጆች አመት በመላው አለም 1.7 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በኤችአይቪ ቫይረስ መጠቃታቸውን ያስታወሰው የተመድ የዜና ድረገጽ በበኩሉ፣ በአመቱ በድምሩ 690 ሺህ ያህል ሰዎች ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ ለሞት መዳረጋቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡

 የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በቅርቡ ለንባብ ያበቁት “ኤ ፕሮሚስድ ላንድ” የተሰኘው መጽሐፍ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በ1.7 ሚሊዮን ቅጂዎች መሸጡንና በዚህም አዲስ የሽያጭ ክብረወሰን ማስመዝገብ መቻሉን ዴይሊ ሜይል ዘግቧል፡፡
መጽሐፉ በአሜሪካና ካናዳ ታትሞ ለገበያ በቀረበበት የመጀመሪያው ቀን ብቻ ከ887 ሺህ በላይ ቅጂዎች እንደተሸጡ ያስታወሰው ዘገባው፣ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ደግሞ በ1 ሚሊዮን 710 ሺህ 443 ቅጂዎች በመሸጥ አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገቡን ፔንጉዊን ራንደም ሃውስ የተባለው የመጽሐፉ አሳታሚ ድርጅት ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሽያጩ የወረቀት፣ የድምጽና የዲጂታል ቅጂዎችን እንደሚያጠቃልል የጠቆመው ዘገባው፣ በመጀመሪያ ዙር በ3.4 ሚሊዮን ቅጂዎች የታተመው “ኤ ፕሮሚስድ ላንድ” ከሰሞኑ በተጨማሪ ቅጂዎች እንደታተመና እስካሁን ድረስ ለህትመት የበቃው አጠቃላይ ቅጂ 4.3 ሚሊዮን መድረሱንም አክሎ ገልጧል፡፡

አለም በስልጣኔና በቴክኖሎጂ በረቀቀችበት በዛሬው ዘመን በመላው አለም ከ40 ሚሊዮን በላይ ሰዎች “የዘመናዊ ባርነት” ሰለቦች ሆነው እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
አለማቀፉ የስራ ድርጅት ባወጣው መግለጫ እንዳለው፣ በመላው አለም ከአስር ህጻናት አንዱ ወይም 150 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት ለዕድሜያቸው የማይመጥንና አደገኛ የግዳጅ የጉልበት ስራ በመስራት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ተጨማሪ 1 ሚሊዮን ያህል ህጻናትም በህገወጥ የሰዎች ዝወውር በቂ ክፍያ የማያገኙበትን ሥራ እንዲሰሩ ወይም ወሲባዊ ብዝበዛ እንዲፈጸምባቸው እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡
“የዘመናዊ ባርነት” ሰለቦች ከሆኑት 40 ሚሊዮን ያህል ሰዎች መካከል 25 ሚሊዮን ያህሉ የግዳጅ የጉልበት ስራ እንደሚሰሩና 15 ሚሊዮን ያህሉም ያለፈቃዳቸው ተገድደው ወደ ትዳር እንዲገቡ መደረጋቸውንም ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
የጉልበት ስራ፣ የግዳጅ ጋብቻ፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ በተለያዩ የጥቃትና የሃይል ድርጊቶች ዜጎችን “የዘመናዊ ባርነት” የሚያደርጉ አካላት፣ በየአመቱ 150 ቢሊዮን ዶላር ያህል ትርፍ ያለአግባብ በማካበት ላይ እንደሚገኙ ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ያስታወቀ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ በበኩላቸው፤ “የዘመናዊ ባርነት” ሰለቦች ሆነው ከሚገኙት የአለማችን አገራት ዜጎች መካከል 71 በመቶ የሚሆኑት ሴቶችና ልጃገረዶች መሆናቸውን በትዊተር ገጻቸው ባወጡት ጽሁፍ ገልጸዋል፡፡

 ኢስት አፍሪካ ኢንተርቴይመንትና ኢቨንት ኦርጋናይዘር ከፌደሬሽን ምክር ቤት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና 10ሩ ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተሳተፉበት ቁንጅና ውድድር ነገ  ከቀኑ 7፡30 ጀምሮ በሸገር ፓርክ እንደሚካሄድ ተገለጸ።
የቁንጅና ውድድሩን ክልላቸውን በመወከል ከአንድ እስከ ሶስተኛ በመውጣት የሚያሸንፉ የሰላምና የአንድነት አምባሳደር ሆነው ክልሎቻቸውን እንደሚገለግሉ የኢስት አፍሪካ ኢንተርቴይመንትና ኢቨንት ኦርጋናይዘር መስራችና ዋና ስራ አስኪጅ አቶ ሞቲ ሞረዳ ባለፈው ረቡዕ ረፋድ ላይ በሀያት ሬጀንዲ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀው ነገ በሚካሄደው ውድድር ላይ ሁለተኛና ሶስተኛ የሚወጡ ቆነጃጅት ሽልማትና አምባሳደርነታቸውን ከክብር እንግዶች እንደሚቀበሉም   ተናግረዋል።
ከየክልሉ 1ኛ የሚወጡ አሸናፊዎች ደግሞ 15ኛው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ዕለት ከኢፌደሪ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴና ከጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ (ዶ/ር) እጅ እንደሚቀበሉም ታውቋል።
የቁንጅና ውድድሩ ዋና አላማ አሁን አገራችን ያለችበትን በዘርና በሃይማኖት ተከፋፍሎ መባላትና መናቆር ያስከተለውን ችግር ለመቅረፍ ቆነጃጅቱ ለየክክላቸው ወጣቶች አንድነት፣ ፍቅርና ሰላም ላይ አበክረው እንደሚሰሩና በቀጣዩ አመት ለቀጣዮቹ አምባሰደሮች ሃላፊነታቸውን እስከሚያስረክቡ ድረስ ይሰራሉም ተብሏል።


 ሰምና ወርቅ ሚዲያና ኢንተርቴይመንት የሚያዘጋጀው ወርሃዊ የኪነ-ጥበብ ምሽት የዚህ ወር መሰናዶ “የሀገሬ ጥያቄ” በሚል ርዕስ የፊታችን ረቡዕ ህዳር 30 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 11፡30 ጀምሮ ጊዮን ሆቴል ውስጥ በሚገኘው ግሮቭ ጋርደን ዎክ ውስጥ ይካሄዳል።
ይህ ምሽት በኮቪድ 19 የምሽት መቋረጦች በኋላ የሚካሄድ የሰምና ወርቅ የመጀመሪያው መሰናዶ እንደሚሆን የመርሃ ግብሩ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ዓለሙ ተናግሯል።
በዕለቱ ወዳጄነህ ማህረነ (ዶ/ር)፣ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ አንጋፋዋ ከያኒ አለምፀሐይ ወዳጆ ፣ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፣ ረ/ፕ ነብዩ ባዬ፣ ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም፣ አርቲስት ሱራፌል ተካ፣ ኮሜዲያን አዝመራው ሙሉሰው፣ ጋዜጠኛ ሰለሞን ሀይለየሱስ፣ ገጣሚ ገዛኸኝ ጤራ እና ገጣሚ መንበረማርያም ሀይሉ ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል። የመግቢያ ዋጋው 100 ብር ሲሆን ትኬቶቹ በብሄራዊ ቴአትር የሰምና ወርቅ የመፅሐፍት አውደ ርዕይ ላይ እንደሚገኙም ታውቋል።

  ሰዓሊ ኪሩቤል መልኬ “ከእኔ እስከ ቤቴ”  በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የስዕል ዓውደ ትርዒት ሰኞ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ ይከፈታል።  
 በአውደ ርዕዩ መግለጫ ላይ እንዳሰፈረው በስራዎቹ የአልባሳትን ታሪካዊ አመጣጥ ለማሳየት አይምክርም፡፡ ይልቁንም ከዚህ ሰፊ ታሪክ ውስጥ ጨርቅ እንዴት የሥነ-ጥበብ አንድ ዘርፍ ሆኖ እንደመጣ ትንሽ ታሪካዊ ዳራውን ጥቆማ በመስጠት ከሥዕል ሥራው ጋር ያለውን ሐሣብ ያይዛል፡፡ ጨርቅን ከቀለም ጋር ወይም ከሌላ ቁስ ጋር በማዋቀርና በማዋሀድ የሚሰራውን፤ “Quilt Art” በመባል የሚታወቀውን ዘርፍ ከራሱ   አጋጣሚ በማዛመድ  የሚያሳይበት መሆኑንም  ባዘጋጀው ፅሁፍ አብራርቷል።
ሰዓሊ ኪሩቤል  መልኬ ስለሚያቀርባቸው ሥራዎች ሲገልፅ በተለያዩ ጊዜያትና ሐሳቦች ላይ ተሰርተው የተጠራቀሙ  መሆናቸውን ሲጠቅስ
…ቤቴ ሐሳቤ ነው በሚል የስዕሎችን ጉዞ አጠቃሎታል። “ከእኔ እስከ ቤቴ”  የሥዕልዓውደ ትርኢት በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ እስከ ታሕሳስ 23 ለዕይታ ይቀርባል።

  በአወዛጋቢው የ2020 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የገጠማቸውን ያልተጠበቀ መራራ ሽንፈት አሜን ብለው ለመቀበል አሻፈረኝ ሲሉ የሰነበቱት ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ከ4 አመታት በኋላ በሚካሄደው የ2024 ምርጫ ዳግም እንደሚወዳደሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ መናገራቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
የምርጫ ማጭበርበር ተፈጽሞብኛል በሚል ያቀረቧቸው ተደጋጋሚ ክሶች ሰሚ ያላገኙላቸውና እስካሁንም ድረስ  ሽንፈታቸውን መቀበላቸውን በይፋ ያላስታወቁት ትራምፕ፣ ባለፈው ማክሰኞ በዋይት ሃውስ ባደረጉት ንግግር በስልጣናቸው ላይ ለመቆየት የቻሉትን እያደረጉ እንደሚገኙና ካልሆነ ግን በቀጣዩ ምርጫ ተወዳድረው ወደ ነጩ ቤተ መንግስት እንደሚመለሱ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡
ትራምፕ በቀጣዩ ምርጫ ለመወዳደር ሃሳብ እንዳላቸው ለአንዳንድ ደጋፊዎቻቸውና አማካሪዎቻቸው በሚስጥር መናገራቸውን አልፎ ተርፎም የምርጫ ቅስቀሳቸውን የሚጀምሩት ተመራጩ ጆ ባይደን በዓለ ሲመታቸውን በሚያከናውኑበት ቀን እንደሆነ መግለጻቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ በምርጫው እንደሚወዳደሩ በይፋ ሲናገሩ ግን ይህ የመጀመሪያቸው መሆኑንም አክሎ ገልጧል።
በአሜሪካ ታሪክ በምርጫ ተሸንፈው ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ዳግም በሌላ ምርጫ ተወዳድረው ወደ ስልጣን የተመለሱ ብቸኛው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ግሮቨር ክሊቭላንድ መሆናቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ እ.ኤ.አ በ1884 አሸንፈው ስልጣን የያዙት ግለሰቡ በምርጫ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ እ.ኤ.አ በ1892 ዳግም በምርጫ አሸንፈው ወደ ነጩ ቤተ መንግስት መመለሳቸውን አክሎ ገልጧል፡፡
ከአወዛጋቢው ምርጫ ጋር በተያያዘ ቢቢሲ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው ዜና እንዳለው፣ የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዊሊያም ባር፣ የአገሪቱ ፍትህ መስሪያ ቤት ምርጫው ተጭበርብሯል ብሎ እንደማያምንና የትራምፕን ተጭበርብሪያለሁ ክስ የሚደግፍ ማስረጃ እንዳላገኘ ቢያስታውቁም፣ ትራምፕ ግን ዐቃቤ ሕጉ ይህን ባሉ በሰዓታት ልዩነት “ድምጼን ተሰርቄአለሁ” የሚሉ ፅሁፎችን በትዊተር ገጻቸው ላይ መለጠፋቸውን ገልጧል፡፡  (በር ነኣ አሃ በእድ በጎዳ ነኣ ሀርግያጋ ቤአነ ቤስ) - የወላይትኛ ምሳሌያዊ ንግግር


             በጥንት ጊዜ በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን፣ በአሜሪካው ፕሬዚዳንትና በራሺያው ፕሬዚዳንት ላይ የተቀለደ
አንድ ተረት ቢጤ ዕውነት ነበር፡፡ እነሆ፡-
የሁለቱ አገሮች ፕሬዚዳንቶች፤ ወታደራዊ ኃይላቸውን ያወዳድራሉ፡፡ የእኔ ይበልጥ፣ የእኔ ይበልጥ፣
ይፎካከራሉ። በመጀመሪያ የሩሲያው ፕሬዚዳንት፣ አሜሪካንንና የአሜሪካን ወታደራዊ ኃይል ሊጎበኙ ይሄዳሉ!
ከዚያም አንድ ጉዳይ ያነሳሉ፡፡
“የአንድ አገር ወታደራዊ ኃይል የሚለካው፤ ወታደሩ ለፕሬዚዳንቱ ባለው ታዛዥነት መጠን ነው!”
“እርግጥ ነው!” አሉ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት፡፡
“በል እንግዲያው ወታደሮችህ ምን ያህል ለአንተ ታማኝ እንደሆኑ አሳየኝ?”
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የሩሲያውን ፕሬዚዳንት ይዘው፣ ወደ ወታደሮቻቸው ይሄዱና አንዱን ወታደር
ጠርተው፤ ወደ አንድ ገደል አፋፍ ይወስዱትና፤
“በል ወደዚህ አዘቅት ገደል ተወርወር” ይሉታል፡፡
ወታደሩም፤
“አይ አላደርገውም” ይላል፡፡
“ለምን?” ይሉታል፡፡
“ጌታዬ፤ በእኔ ደሞዝ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች” አሉኝ፤ (I have a family to support!) ይላል፡፡
የሩሲያው ፕሬዚዳንት በአሜሪካኑ ወታደር ታዛዥ አለመሆን እየሳቁ፤
“ቆይ የእኔን ወታደር ታማኝነት አሳይሃለሁ!” ይሉና የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ወደ ሩሲያ ይዘውት ይሄዳሉ፡፡
ከዚያም አንዱን ወታደር ጠርተው፤
“ወደዚህ አዘቅት ገደል ተወርወር!” ይሉታል፡፡
ወታደሩም፤
“ታዛዥ ነኝ ጌታዬ!” ብሎ ወደ ገደሉ ይወረወራል፡፡
እንዳጋጣሚ ግን አንድ የዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ያርፍና ከሞት ይተርፋል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ወደሳቸው
እንዲመጣና ጥያቄ እንዲያቀርቡለት ይጠይቃሉ፡፡
ወታደሩ ተጠርቶ መጣ!
የአሜሪካው ፕሬዚዳንትም፤
“የእኔ ወታደር ወደ ገደል ተወርወር” ብለው፣ ‹የማስተዳድረው ቤተሰብ አለኝ› አለ፡፡ አንተስ እንዴት ልትወረወር ቻልክ?” አሉና ጠየቁት፡፡
ወታደሩም፤
“I too, have a family to support (እኔም የማስተዳድረው ቤተሰብ ስላለኝ ነው)” አለ፡፡
“እንዴት?” ቢሉት፤
“እኔ አልወረወርም ብል፤ እኔንም ቤተሰቤንም ነው የሚፈጁን!” ሲል መለሰ!
* * *
የአንድ ሰው ጥፋት ለቤተሰብና ለዘመድ አዝማድ ከሚተርፍበት ስርዓት ይሰውረን፡፡ ባለፈው ዘመን የመናገር ነፃነት ባልነበረበት ሁኔታ ውስጥ “አፍ-እላፊ” የሚባል ወንጀል ነበር - የአፍ ወለምታ! “ክብረ ነክ ንግግር” ነበር የሚባለው- ከወታደሩ ዘመን በቀደመው የንጉሱ ዘመን! አፍ - እላፊ ባለስልጣንን፣ መሪን፣ ሥርዓትን፣ አስተዳደርን ከመተቸት እስከ አገርን ማንቋሸሽ ድረስ የሚሰፋ ወንጀልን ያካትት ነበር፡፡ ልዩ ትርጉም የሚሰጠው አነጋገርም ያስቀጣ ነበር፡፡ ለምሳሌ፡- “ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም ሀቀኛ ኮሚኒስት ናቸው!” እያለ ቀኑን ሙሉ ይለፈልፍ የነበረ ንክ ሰው፣ ታስሮ ነበር! ወንጀሉ፤ “ማንም የሚያውቀውን ሀቅ እየደጋገምክ የምትናገረው ነገር ቢኖርህ ነው!” ተብሎ ነው! “አለፈልሽ ባሮ!” እያለም የባሮን ወንዝ አስመልክቶ መፈክር ያሰማ ሰው፤ ሽሙጥ ነው ተብሎ የታሰረበት አጋጣሚም ነበር!
ዋናው ጉዳይ ሰው ሲታፈን፤ መናገሪያ፣ መተንፈሻ…፣ ዘዴ መሻቱ አይቀሬ ነው የሚለው ዕውነታ ነው!
ያሰበ ጭምር ይቀጣል በሚባልበት ሥርዓት የተናገረ፤ መወንጀሉና መቀጣቱ አይገርምም! ሰብዓዊ መብትና ዲሞክራሲያዊ መብት በማይከበሩበት አገር ምሬቶች ይጠራቀማሉ፡፡ መውጫ ቀዳዳ ይፈልጋሉና ሥርዓት ወዳለው አመፅ አሊያም ወደ ሥርዓተ - አልበኝነት ሊያድጉ ይችላሉ፡፡ የገዢዎችን የመግዛት አቅም ይፈታተናሉ፡፡ ምላሽ የሌላቸው ጥያቄዎች ይበዛሉ!! ዓለም የጋዝ ታንክ ለመሙላት ሲሯሯጥ፣ ደሀ አገሮች ሆዳቸውን ለመሙላት ይፍረመረማሉ። “የምግብ ፍላጎት አለመሟላት ከነፃነት ረሀብ ጋር ከተዳመረ፤ የህዝቦች ህልውና ጥያቄ ውስጥ ይገባል” ይባላል፡፡ የኢኮኖሚ ህመምና የፖለቲካ ህመም ከተደራረቡ፣ ከማስታገሻ ያለፈ በሽታን ይፈጥራሉ!
ፍትሕ-አልባ ሁኔታን ይቀፈቅፋሉ። ሌብነት እንደ ሥራ ይቆጠራል፡፡ አንድ መገንዘብ ያለብን ነገር ግን፤ ሰላም -አልባ ሁኔታ ውስጥ ከገባን የሰረቅነውን የምንበላበት ጊዜም ይጠፋል! ያደለብነው ኪስ ያፈሳል! የገነባነው ቪላ ይፈርሳል! ለሌሎች የቆፈርነው ጉድጓድ፣ የእኛው መቀበሪያ ይሆናል!
 በድሮ ጊዜ አንድ ባለስልጣን እሥር ቤት ሲጎበኙ፣ እስር ቤቱን የማስፋፋት ሰፊ እቅድ መያዙን አስተዳዳሪው ያስረዷቸዋል። ባለስልጣኑም፤ “ጥሩ ሀሳብ ነው፡፡ በደምብ ገንቡና አስፋፉት፡፡ ዞሮ ዞሮ የእኛም የወደፊት ቤታችን ነው!” አሉ ይባላል፡፡
 ያሉት አልቀረም - ገቡበት! ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን፤ በአንድ ተውኔቱ ውስጥ ንጉሡ እሥር ቤት መርቀው ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር፤ “የአባታችን እርስተ - ጉልት የሆነውን ይህንን የሀገር ወህኒ ቤት መርቀን ስንከፍትላችሁ፤ በተለመደው ባህላችሁ እንድትተሳሰሩበት ነው” ይለናል፡፡
ዛሬ፤ ከፊውዶ-ቡርዥዋው ስርዓት ወደ ሶሻሊዝም፤ ከዚያም ወደ ካፒታሊዝም አድገናል እያልን፤
የግሎባላይዜሽን ቅርቃር ውስጥ የገባን ይመስላል፡፡ በጥናት ያልተደገፈ ሥርዓት፣ መላ-አጥ መንገድ ላይ በትኖናል ቢባል ማጋነን አይሆንም!
ከእነ ስማቸው እማማ ጦቢያ፤ የሚባሉ የዱሮ ሴት ወይዘሮ ነበሩ አሉ- ደርባባና ጨዋ!
“ከዚህ ከባሪያ የገላገልከኝ ለታ፣ ወዲያውኑ ብትገድለኝ ግዴለኝም” ይሉ ነበረ ሲፀልዩ፡፡
ባሪያ ያሉት ሄደና ሌላ መንግሥት መጣ!
ይሄኛውንም ማማረር ቀጠሉ፡፡
“ምነው እማማ፤ ከዚህ ከባሪያ ገላግለኝ ሲሉ ነበረ፡፡ ገላገለዎት፡፡ አሁን ደግሞ ምን ሆኑና ያማርራሉ?” ቢባሉ፤
“አሃ! ያኛውኮ ከፋም ለማም የጨዋ ባሪያ ነው! ይሄኛውኮ የረባ ጌታ እንኳ የለውም! ጌታውን ቢያውቅ የማንም መጫወቻ አያደርገንም ነበር!” አሉ ይባላል፡፡
አይ እማማ ጦቢያ፡፡ አሜሪካንን አላወቁ! እንግሊዝን አላወቁ! የረባ ጌታ ማን እንደሆነ አላወቁም! ከፊውዳሊዝም ወደ ካፒታሊዝም መሸጋገር፣ የጌታ አማራጭ የማግኘት ጉዳይ ብቻ ቢሆን እንዴት በታደልን ነበር! ጌቶቻችንን በቅጡ አለማወቅ፣ የነገ ዕቅዳችንን በግልፅ እንዳናይ እንዳደረገን ይኖራል! ከዚህ ያውጣን!!
ለችግሮቻችን ምላሽ ፍለጋ ወደ ሹሞቻችን ማንጋጠጥ፣ ዘላቂና ሁነኛ መፍትሔ አያመጣም! ችግሮቹ የራሳችን የመሆናቸውን ያህል መፍትሔም ከእኛ መፍለቅ ይኖርበታል፡፡ በዲሞክራሲያዊና በፍትሐዊ መንገድ ያላፈራናቸው አለቆች፤ መልካም አስተዳደርን ያጎናፅፉናል ብለን ማሰብ “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ” ነው፡፡
ለዕለት ኑሯችን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እንኳ ሸምተን ማደር እያቃተን፤ ነው፡፡ ያም ሆኖ ስለ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን አሀዞች ማውራት አልገደደንም፡፡
አለቆቻችን መፍትሔ-ሰጪ አካላት መሆን ካቃታቸው መሰንበታቸውን እያወቅን፣ ሁነኛ ምላሽ ካልሰጣችሁን እያልን እነሱን ደጅ እንጠናለን፡፡ እንደ ሲቪልም፣ እንደ ተቃዋሚ ፓርቲም ዕሳቤያችን ያው ነው! አሌ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የቤት-ጣጣ እያለብን፤ ነቅተን፣ በቅተን፣ ተደራጅተን፣ በአንድነት ፈጥረን የበሰለ መፍትሔ ከውስጣችን ማግኘትን ትተን፣ የሌላ ደጃፍ እናንኳኳለን!
የወላይታው ምሳሌያዊ አነጋገር ግንዛቤ የሚሰጠን እዚህ ላይ ነው፡- “የራሱን ልጅ አስከሬን አዝሎ፣ የታመመውን የሹም ልጅ ለመጠየቅ ይሄዳል!” ይለናል፡፡ ሹሞቹ ጤና መስለውት ነው!

Page 12 of 516