Administrator

Administrator


         በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ በሆኑት አቶ መኮንን ተካ የተዘጋጀው መጽሐፍ በሁሉም የመጽሐፍት መደብሮች ለገበያ ቀርቧል፡፡ መምህር መኮንን ተካ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህር ሲሆኑ ከዚህ መጽሐፍ በተጨማሪ ዝናቸው ከፍ ባሉ አለም አቀፍ የምርምር ጆርናሎች የተለያዩ
የምርምር መጣጥፎችን አበርክተዋል፡፡ ለ3ኛ ጊዜ የታተመና ጠለቅ ያለ ማሻሻያ የተደረገበት ይህ መጽሐፍ የሚከተሉትን ጉዳዮች ይዳስሳል፡-
- የሚዲያን ተጽዕኖና የማህበረሰብ ግንኙነትን በተመለከተ በቂ መረጃ ያቀርባል፣
- ስለ ሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ዝርዝር ፍልስፍናዎችንና የአሠራር መርሆዎችን ይተነትናል፣
- ለተለያዩ የሚዲያ ዘውጐች የሚሆኑ ዘገባዎች እንዴት መሰናዳት እንዳለባቸው ያብራራል፣
- የሃሳብ ነፃነትን፣ የሚዲያ ህጐችንና የጋዜጠኝነት አተገባበር ምን መምሰል እንዳለበት ሃሳብ ያቀርባል፣
- በሀገራችን የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት አተገባበር ላይ በንድፈ - ሀሳባዊ ቅኝት በመታገዝ አውዳዊ እውቀትን ያስጨብጣል፡፡
- መረጃና እውቀት እንዴት በጋዜጠኝነት መደራጀት እንዳለበት ያብራራል፣
- ከህትመትና ከአርትኦት ጋር በተገናኙ ርእሰ ጉዳዮች፣ ከጋዜጠኝነት አተገባበር አንፃር በቂ መረጃ ያቀርባል፡፡


* ታህሳስ 29 ቀን 1992ዓ.ም የመጀመሪያው "አዲስ አድማስ" ጋዜጣ፣ በመጀመሪያው ዕለት ቅዳሜ ለንባብ በቃ!!
*ላለፉት 20 ዓመታት በየሳምንቱ ቅዳሜ፤ እውነተኛና ትክክለኛ፣ ምሉዕና ሚዛናዊ ዜናዎችን…በመረጃ የበለፀጉ ፖሎቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘገባዎችን…ጠንካራ ትንታኔዎችን…በኪናዊ ውበታችው የላቁ ማህበራዊና ጥበባዊ ጽሑፎችን አስነብበናል!!
*አምስት አገራዊ ምርጫዎችን ዘግበን፣ ከአገራችንና ከአንባቢዎቻችን ጋር ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈናል፤ ለዘንድሮው ምርጫም እየተዘጋጀን ነው!!
*ድንቅ ጽሁፎችን በፍቅር እያበረከታችሁ ለዘለቃችሁ የአድማስ ብዕርተኞች ሁሉ፤ ባለውለታዎቻችን ናችሁ!!
*ለሁለት አስርት ዐመታት በፍቅር ያነበባችሁን ሁሉ እናመሰግናለን፤ እንወዳችኋለን!!
*ምርትን አገልግሎታችሁን ለማስተዋወቅ እኛና ለመረጣችሁ ድርጅቶች ሁሉ አክብሮታችንን እንገልጻን!!
*ዓላማችን መረጃንና ዕውቀትን በማክበር፤ በአዕምሮና በሥራ የሚበለጽግ፣ ራሱን ችሎ የሚያስብና የሚቆም፣ ምክንያታዊና አስተዋይ ትውልድ ይበረከት ዘንድ መትጋት ነው!!

Saturday, 22 February 2020 12:32

የልጆች ጥግ


       ውድ ልጆች፡- በቤት ውስጥ ሁሉም ነገር የየራሱ ቦታ አለው፡፡ ፍራፍሬ (ሙዝ፣ ብርቱካን፣ ወይን፣ ወዘተ) በቅርጫት ወይም በፍራፍሬ ቦውል ውስጥ ይቀመጣል:: የቆሸሸ ልብስ ደግሞ ቅርጫት ውስጥ ይጠራቀማል፡፡ የሕጻናት መጫዎቻዎች ተሰብስበው የሚቀመጡበት ሳጥን ወይም ካርቶን ይኖራቸዋል፡፡ ማናቸውንም ነገሮች በምትፈልጓቸው ጊዜ ብቻ  ነው አውጥታችሁ መጠቀም ያለባችሁ፡፡ ተጠቅማችሁ ስትጨርሱም… ወዲያውኑ እቦታቸው መመለስ አለባችሁ፡፡ ያለበለዚያ ግን ሌላ ጊዜ ስትፈልጓቸው በቀላሉ አታገኟቸው፡፡ አንዳንድ ነገሮች እየጠፋብችሁ የምትቸገሩት ለምን ይመስላችሁ? በትክክለኛ ቦታቸው ስለማታስቀምጧቸው ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉንም ነገር በቦታ በቦታው ማስቀመጣችሁን አትዘንጉ!  
ውድ ልጆች፡- ቤት ውስጥ የተበላሸ ወይም የተዘበራረቀ ነገር ካለ ወዲያውኑ አስተካክሉት፡፡ የሚያደናቅፍ ነገር ካያችሁ፣ ቶሎ ብላችሁ አንሱት፡፡ እናንተን ወይም ሌላ ሰው ሊጥል ይችላል፡፡ ውሃ ወይም ለስላሳ ወለሉ ላይ ከፈሰሰ ዝም ብላችሁ አትለፉት፤ አድርቁት፡፡ መሬት ላይ የወደቀ ሶፍት ወይም ወረቀት ከተመለከታችሁ አንስታችሁ የቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ ጨምሩት፡፡ እናንተ መስራት የምትችሉትን ነገር፣ ሌላ ሰው እንዲሰራላችሁ አትጠብቁ፡፡
ውድ ልጆች፡- ከት/ቤት ስትመለሱ፣ ዩኑፎርማችሁን ቀይራችሁ፣ አልጋ ላይ ወይም እዚህና እዚያ  መጣል ተገቢ አይደለም:: በትክክል አጣጥፋችሁ ማስቀመጥ  አለባችሁ:: ጫማና ካልሲያችሁንም እንደዚያው፡፡ መኝታ ቤታችሁንና የጥናት ክፍላችሁን ምንጊዜም ንፁህ አድርጉት:: ወላጆቻችሁ፤ “ክፍላችሁን አጽዱ” ብለው እስኪነግሯችሁ ድረስ አትጠብቁ፡፡ የራሳችሁን ሥራ ራሳችሁ ተወጡ፡፡
ውድ ልጆች፡- ታናናሽ ወንድሞችና እህቶቻችሁን ማጫወት፣ መምከርና ማገዝ እንጂ ማብሸቅና ማስለቀስ የለባችሁም:: ተገቢም አይደለም፡፡ የትም ቦታ ቢሆን ታላላቆቻችሁን አክብሩ፡፡ ቤተሰባችሁንም ውደዱ፡፡
እደጉ! ተመንደጉ!

Monday, 24 February 2020 00:00

ኮሮና ቫይረስ በሳምንቱ

   ከዕለት ወደ ዕለት መስፋፋቱንና ብዙዎችን ተጠቂ ማድረጉን የቀጠለው ኮሮና ቫይረስ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ በመላው አለም ከ75 ሺህ በላይ ሰዎችን ማጥቃቱንና ለሞት መዳረጉን አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
ወረርሽኙ በተቀሰቀሰባት ቻይና እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ 74 ሺህ 185 ሰዎች በቫይረሱ ሲጠቁ፤ የሟቾች ቁጥር ደግሞ 2004 መድረሱ ተነግሯል፡፡ ኢራንና ግብጽ በሳምንቱ አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች የተገኙባቸው ሁለቱ የአለማችን አገራት ሲሆኑ በኢራን 2፣ በግብጽ ደግሞ 1 ሰው በቫይረሱ መያዙ ተረጋግጧል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ በደቡብ ኮርያ ባለፈው ረቡዕ ብቻ 20 አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ የተጠቂዎች ቁጥር ወደ 51 ከፍ ማለቱንም አመልክቷል፡፡ በሺህዎች የሚቆጠሩ መንገደኞችን አሳፍራ በጃፓን የባህር ዳርቻ ለቀናት ታፍና በቆየችው መርከብ ውስጥ የነበሩት 542 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጠ ሲሆን የሩስያ መንግስት ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ቻይናውያን ወደ ግዛቱ እንዳይገቡ እገዳ መጣሉን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ እገዳው እስከ መቼ እንደሚቆይ የታወቀ ነገር የለም ብሏል፡፡
የአሜሪካ የንግድ ምክር ቤት ሰራሁት ያለውን ጥናት ጠቅሶ ዘ ኢንዲፔንደንት እንደዘገበው ደግሞ፣ በቻይና ከሚገኙት የአሜሪካ ኩባንያዎች መካከል ግማሹ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ እንቅስቃሴያቸው በከፍተኛ ሁኔታ መገታቱን መግለጻቸውና 78 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የሰው ሃይል እጥረት እንደገጠማቸው መናገራቸው ተወስቷል፡፡

Saturday, 22 February 2020 12:16

መልዕክቶቻችሁ

       የኤልቲቪ ‹‹ሌላው ገጽታ››?!

        እስካሁን በኤልቲቪ ‹‹ሌላው ገጽታ›› ፕሮግራም ላይ ለቃለ መጠይቅ ከቀረቡ እንግዶች ውስጥ የማየት ዕድል የገጠመኝ የጥቂቶቹን ብቻ ነው። የፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌውን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶና የማስታወቂያ ባለሙያው ጋዜጠኛ ሳምሶን ማሞን ቃለ መጠይቅ ነው፡፡ የዚህ ፕሮግራም ሁለተኛው ወይም የመጨረሻው ክፍሉ… ከጥያቄው ፎርማት እስከ ቅጣቱ (ቃሪያና ቆጭቆጫ መብላት) በጣም ያስገርመኛል፡፡ አንጋፋና ታዋቂ ሰዎችን በቴሌቪዥን ፕሮግራም በእንግድነት ጋብዞ፣ በቃሪያና ሚጥሚጣ መለብለብ ምን የሚሉት ሙያ ነው? በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ለእንግዳውም ሆነ ለተመልካቹ ብዙም የሚያዝናና አለመሆኑን ነው፡፡ (በነገራችን ላይ የተከበሩና የታወቁ ሰዎችን እየጋበዙ የማይመጥናቸው ቀልድና ጨዋታዎች ላይ ሳይወዱ በግድ የሚያሳትፉ የቲቪ ፕሮግራሞች እየበዙ ነውና ያሳስባል) የፕሮግራሙ አቅራቢ ጋዜጠኛ፤ ለእንግዶቿ ባትጨነቅ እንኳን ለራሷ ስትል የ‹ቃጠሎ› ጨዋታውን በሌላ ቁም ነገር ያለው ጨዋታ ብትለውጠው ይመረጣል - እሷም የጥያቄና መልሱ ተሳታፊ ናትና፡፡ ከጋዜጠኛ ሳምሶን ማሞ ጋር ባደረገችው ቆይታም ፊቷ ፍም መስሎ አይተናል፡፡ በየሳምንቱ እንዲህ እሆነች… እንዴት ልትዘልቀው ነው? ለጤናዋም ብታስብበትም ጥሩ ነው፡፡
       ሳሚ - ከሸገር

Saturday, 22 February 2020 11:59

መልዕክቶቻችሁ

   ከስህተት ውስጥ የፈለቀ አስደማሚ ማስታወቂያ!


           በአሜሪካ በምግብ አብሳይነት (Cook) የምትሰራ አንዲት እንስት ዕድል ቀናትና በገዛችው ሎተሪ ወደ ሀብት ማማ የሚያወጣ ብዙ ገንዘብ ደረሳት፡፡ የሚሊዮን ዶላር አሸናፊ ሆነች፡፡ በዚህም የተነሳ የሚዲያ ትኩረት ሳበች፡፡ አንዱ ታዋቂ የቴሌቪዥን ቻናልም ቃለ መጠይቅ አደረገላት፡፡ ይህቺ ባለ አዱኛ ከምግብ አብሳይነት ሙያዋ ውጭ በሌሎች አጠቃላይ ጉዳዮች ላይ እምብዛም ዕውቀትና ግንዛቤ የላትም፡፡ (በኛ አገር አባባል “ጨዋ” ናት)
የቴሌቪዥኑ ጋዜጠኛ በሎተሪ አሸናፊነቷ ዙሪያ ጥቂት ጥያቄዎችን ከጠየቃት በኋላ አንድ ለየት ያለ ጥያቄ አቀረበላት-  “What do you know about American president in general?”  (ስለ አሜሪካ ፕሬዚዳንት በአጠቃላይ ምን ታውቂያለሽ?) የሚል፡፡ የወጥ ቤት ባለሙያዋ እንስትም እንዲህ ስትል መለሰች፡- “I know only about General Motors›› (እኔ የማውቀው ስለ ጀነራል  ሞተርስ ብቻ ነው) ይሄን በቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት ሲከታተሉ የነበሩት የጀነራል ሞተርስ ፕሬዚዳንት ወደ ቴሌቪዥን ጣቢያው ደወሉና “ቃለምልልሱ በአየር ላይ ይቆይ፤ አሁን መጣሁ” አሉ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ቴሌቪዥን ጣቢያው የደረሱት የአዲስ (ብራንድ) ጀነራል ሞተርስ አውቶሞቢል ቁልፍ ይዘው ነበር፡፡
የመኪናውን ቁልፍ ለዚያች የሎተሪ አሸናፊና የወጥ ቤት ባለሙያ ከሸለሙ በኋላ “የአሜሪካ ፕሬዚዳንትን ስም የማያውቁ ዜጐች እንኳን እኛን ጠንቅቀው ያውቁናል” በማለት ተናገሩ - ለድርጅታቸው አስደማሚ ማስታወቂያ ሰሩ፡፡ ከተሳሳተ ምላሽ የተፈለቀቀ ምርጥ ማስታቂያ አይደል?!

            ጄፍ ቤዞስ 10 በመቶ ሃብታቸውን ለአየር ንብረት ለውጥ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል

         የናሚቢያ ቀዳማዊት እመቤት ሞኒካ ጄኒጎስ ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ 3 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ሃብታቸው በሙሉ ለበጎ አድራጎት እንዲውል መወሰናቸውን እንዲሁም የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ ከአጠቃላይ ሃብታቸው 10 በመቶ ያህሉን ወይም 10 ቢሊዮን ዶላር ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ተግባር እንደሚለግሱ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡
በአገራቸው የጾታ ልዩነትን ማጥፋትን ጨምሮ የተለያዩ የበጎ ምግባር ስራዎችን በመስራት የአፍሪካውያን ቀዳማዊ እመቤቶችን ገጽታ ለመገንባት እየጣሩ የሚገኙት ሞኒካ ጄኒጎስ፤ሃብታቸውን ለበጎ ምግባር ለማዋል መወሰናቸውን እንዳስታወቁ ዘገባው አመልክቷል፡፡ በሌላ ዜና ደግሞ አሜሪካዊው የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ፤ ከአጠቃላይ ሃብታቸው 10 በመቶ ያህሉን ወይም 10 ቢሊዮን ዶላር ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ተግባር እንደሚለግሱ ባለፈው ሰኞ ማስታወቃቸው ተነግሯል፡፡
የአማዞኑ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ጄፍ ቤዞስ አዲስ ባቋቋሙት ቤዞስ አርዝ ፈንድ የተባለ ፋውንዴሽን አማካይነት በአለማቀፍ ዙሪያ ለሚደረጉ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎች የ10 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት፡፡ የገንዘብ ድጋፉ ከሚደረግላቸው መካከል በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የሚሰሩ ተመራማሪዎች፣ አክቲቪስቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንደሚገኙበት የዘገበው ፎርብስ መጽሄት፣ ተፈጥሮን በመንከባከብ ላይ ትኩረት ላደረጉ ቅድሚያ ይሰጣል መባሉንም ገልጧል፡፡ የአለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ የሆኑት ጄፍ ቤዞስ አጠቃላይ የተጣራ ሃብታቸው 129.9 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስም ዘገባው አክሎ አስታውሷል፡፡

 ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋት ጋር በተያያዘ በቻይና የሩብ አመቱ የሞባይል ምርት በ50 በመቶ ያህል ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ፤ በአለማቀፉ የሞባይል ስልኮች ገበያ ላይ መቀዛቀዝ እንደሚከሰትና በ5 አመት ውስጥ ዝቅተኛው የሩብ አመት የሞባይል ሽያጭ ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በቻይናም ሆነ በሌሎች አገራት የሚገኙ ታላላቅ የሞባይል አምራች ኩባንያዎች ከቫይረሱ ስርጭት ጋር በተያያዘ ስራቸው መስተጓጎሉንና የሰው ሃይል እጥረት ማጋጠሙን ተከትሎ፣ የሩብ አመቱ የሞባይል ምርት መጠን በ12 በመቶ ያህል ሊቀንስ እንደሚችል መነገሩን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በሩብ አመቱ የሞባይል ሽያጩ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል ተብሎ የሚጠበቀው ኩባንያ አፕል ሲሆን ኩባንያው የሚያመርተው አይፎን ሞባይል፤ የሩብ አመት ሽያጭ በ10 በመቶ ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል፡፡
ተፎካካሪው የደቡብ ኮርያው ሞባይል አምራች ኩባንያ ሳምሰንግ በበኩሉ፤ የሽያጭ መጠኑ በ3 በመቶ ያህል ሊቀንስበት እንደሚችልም ዘገባው አመልክቷል፡፡

     የአሜሪካ መከላከያ ቢሮ ፔንታጎን በ13.27 ሚሊዮን ዶላር በአይነቱ አዲስ የሆነና “ገንስሊንገር” የሚል ስያሜ የተሰጠው ዘመናዊ በራሪ ጠመንጃ ለመስራት ማቀዱ ተነግሯል፡፡
የአሜሪካ የወታደራዊ ፕሮጀክቶች ተቋም ዳርፓ ተግባራዊ ሊያደርገው ያቀደው አዲሱ በራሪ ጠመንጃ ያለ ተኳሽ በአየር ላይና በምድር እየበረረ ጥቃት መፈጸም የሚችል መሆኑን የዘገበው ፎክስ ኒውስ፤ ለአዲሱ ጠመንጃ ምርምርና ምርት የሚውለው ገንዘብ እንዲመደብለት መጠየቁን አመልክቷል፡፡
አዲሱ በራሪ ጠመንጃ ምን ያህል መጠን እንዳለውና የሚጠቀመው ተተኳሽ ምን እንደሆነ በግልጽ አለመታወቁን የጠቆመው ዘገባው፤ ሰርጎገቦችን ለማጥቃት በሚደረጉ ዘመቻዎች ላይ ጥቅም ላይ እንደሚውልም አመልክቷል፡፡

      ከዕለታት አንድ ቀን የዱር አራዊቶች ተሰባስበው አያ አንበሶ ስለታመመ “እንዴትና መቼ እንደምንጠይቀው እንወያይ” እየተባባሉ ሃሳብ እንዲሰጥበት አንድ በአንድ ሃሳብ ይሰነዝራሉ፡፡
ዝሆን - “እንደሚታወቀወ አያ አንበሶ ለብዙ ዓመታት ጌታችንና ንጉሣችን ሆኖ የቆየ ባለ ግርማ ሞገስ መሪያችን ነው፡፡ ስለዚህ አሁኑኑ ሄደን እንጠይቀውና ልንረዳው የምንችለው ነገር ካለ በዐይናችን በብረቱ ዐይተን፣ ከራሱ ልሣን የምንሰማውን ችግሩን አድምጠን፤ የምናደርገውን እናድርግ” አለ፡፡
ቀጥሎ የአቶ ነብሮ ተራ ሆነ፤
“እኔም ጌታ ዝሆን ያለውን ነው የምደግፈው፡፡ ስንት ዘመን በሥነስርዓት ሲገዛንና ሲያስተዳድረን የኖረውን የዱር አራዊት ንጉሥ ቢታመም ማሳከም፣ ራበኝ ጠማኝ ቢል ማብላት ማጠጣት ይጠበቅብናል፡፡ ስለዚህ ወደዚያው እንሂድ ነው የምለው፡፡”
ቀጥሎ ዝንጀሮ ተነሳና፤
“ግዴላችሁም የአያ አንበሶን ነገር ከጥንት ከጠዋት ጀምራ መላውን የምታውቀው ጦጢት ስለሆነች እሷ የምትለውን ብንሰማ ደስ ይለኛል፡፡”
ተኩላ ቀጠለ፡-
“እኔም የአያ ዝንጀሮን ሃሳብ ነው የምደግፈው፡፡ ጦጢት የምትለውን እናዳምጥ፡፡”
ድኩላ በበኩሉ፤
“ግዴላችሁም ወዲህ ወዲያ ማለታችንን ትተን ቀጥታ አያ አንበሶ ቤት ሄደን ጡረታም መውጣት ይፈልግ እንደሆን፣ ድኖ ዳግመኛ መምራት ይሻም እንደሆነ… ከራሱ አንደበት እንስማ:: ስለዚህ ሳንውል ሳናድር ወደዚያው ሄደን እናረጋግጥ፡፡”
በማህል ጦጢት እየሮጠች መጣች፡፡
“ጦጢት ምን ትያለሽ?” ተባለች፡፡
“አንድ መልዕክተኛ እንላክና ሁኔታውን አጣርቶ ይንገረን” አለ አዞ፤ ከጦጣ በፊት፡፡
አዞን ተከትሎ ዘንዶ ተናገረ፤ “ከጦጣ በፊት መናገር መርጫለሁ፡፡ እዚህ ተቀምጠን ይሄ ይሁን ያ ይሁን ከምንል ቀጥ ብለን ሄደን በዐይናችን በብረቱ አይተን እንፍረድ” አለ፡፡
በመጨረሻ፤
“ጦጢት ምን ይሁን ትያለሽ ታዲያ?” ተባለች፡፡
ጦጢትም፤
“ግዴላችሁም ጊዜ ሰጥተን እንይ፡፡ ወይ አያ አንበሶ ይድናል፡፡ አሊያም እግዜር ካለልን ይሞታል፡፡ ብቻ አደራ አያ አንበሶ ያልኩትን እንዳይሰማ፡፡ ፀጥ እርጭ በሉ - አደራ፤ እኔ ግን ዕውነት ተናገሪ ካላችሁኝ… አያ አንበሶ ሲሞትም ይምረናል ብዬ አላምንም?”
አለችና እቅጩን ተናገረች፡፡
***
ክፋትና ጉልበት አለው ብለን የምናምነውን ሁሉ መፍራትና ባልሰማብኝ ብሎ መስጋት ያለ ነው፡፡ በተለይ የህገርና የህዝብ ጉዳይ ነው የምንለው ነገር ላይ ከሆነ ስጋታችን በጣም ይጨምራል፡፡ አንዳንዱ ጉዳዩን ከፖለቲካ ጋር ያዛምደውና ላብ ላብ ይለዋል፡፡ አንዳንዱ ምንም ይሁን ምን ስሜት አይሰጠኝም የሚል ይሆናል፡፡ ኑረዲን ኢሣ ያለውን ማስታወስ ይበጃል እዚህ ጋ፡-
“እኔ ምን አገባኝ የምትሉት ሀረግ
እሱ ነው ሀገሬን ያረዳት እንደበግ
ብዬ ግጥም ልፅፍ ተነሳሁኝና
…ምን አገባኝ ብዬ ቁጭ አልኩ እንደገና!”
ምን አገባኝ የማለት አባዜ አይጣል ነው!
ይሄ የእኔ ጉዳይ አይደለም እያልን የምንተወው ብዙ ነው፡፡ ይሄን ዓይነቱ አመለካከት ውሉ አድሮ ክፉውንም ደጉንም ደርቦ የመጨፍለቅ ችግር ላይ ይጥላል፡፡ እስከ ዛሬ በዲሞክራሲ፣ በእኩልነት፣ በወንድማማችነት፣ በፍትሐዊነት፣ በመተዛዘንና በመደጋገፍ ዙሪያ ያሳየነው ቸልተኝነት ዘለዓለማዊ እስኪመስል ድረስ ሲደጋገምብን የሚኖር ሆኗል፡፡ የፖለቲካ ህይወት “ይደገም አይደገም” የሚባል የፊልም ትርዒት አይደለም፡፡ ከማህበራዊ ሂደት ጋር ተስናስሎ ድርና ማጉን ለይቶ ማየት እስከማንችል ድረስ ሊወሳሰብ የሚችል ነው፡፡ ያልተመለሱ ጥያቄዎቻችን አያሌ ናቸው፡፡ ጊዜ እየረዘመ ሲሄድ የሚረሱም፤ የሚድበሰበሱም፣ ከናካቴው ደብዛቸው የሚጠፋም አያሌ ናቸው፡፡
በተለይ የኢኮኖሚ ጥያቄዎቻችንን በቅጡ አለማጤን ጣጣው የትየለሌ ነው፡፡ እንዳዲስ ደግመው ወደ ጠረጴዛው ብቅ የሚሉበት ሰዓት ግን ሊመጣ እንደሚችል አለመዘንጋትም፣ አለመዘናጋትም ደግ ነው፡፡ ሀገራችን ብዙ ታይቶ ጠፊ (Volatile) ክስተቶች ማስተናገዷ ከቶም አዲስ አይደለም፡፡ ጊዜና ቦታ እየመረጡ የሚመጡ ሂደቶችን በቅጡ አጥርቶ ማየት ይገባል፡-
እንደ ሼክስፒር፤
“ዛሬ ለወግ ያደረግሺው
ወይ ለነገ ይለምድብሻል
ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው
ወይ ይጠፋል ወይ ያጠፋል
ከርሞም የሠለጠነ እንደሁ
ተፈጥሮ ይሆናል ይባላል
…ማለት ያስፈልጋል፡፡ እንደ ዘበት በልማድ የጀመርናቸው ነገሮች ማቆሚያ እንዳያጡ ለከት ማበጀት ያሻል፡፡ ድክመቶቻችንን በወቅቱ እናሸንፍ፡፡ ስለ ትምህርት እንጨነቅ፡፡ ስለ ጤና እንጨነቅ፡፡ አስቦ ሂያጅ እንጂ የድንገቴ መንገደኞች አንሁን፡፡ ለዚህም በተቻለ፤ ጥብቅ ጥናት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
እንደ እስካሁኑ ያለ አንዳች እርምጃ ቸል የተባሉትን ብዙ ጉዳዮች ወቅታዊ መፍትሔ ከመስጠት ከመቆጠባችን የተነሳ እያደር ለሚገዝፉ ችግሮች እንደምንጋለጥ ልብ አንበል፡፡
“ለማናቸውም ድርጊትህ ጊዜ ምረጥ ጊዜ መስጠት ለማይገባው ነገር ጊዜ አትስጥ” እላለሁ፡፡”


Page 13 of 477