Administrator

Administrator

   ንጉሳዊው ሥርዓት ከዙፋኑ ላይ አልወረደም፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካም ለትጥቅ ካልሆነ ለፓርቲ ትግል አልታደለም፡፡ በ1953 የመፈንቀለ መንግስት ሙከራ የተደረገባቸው ቀዳሚው ኃይለስላሴ ያንን ክፉ ቀን አስታውሰው አንፃራዊ ነፃነትን ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም የሆነው ግን ተቃራኒው ነው፡፡ ንጉሳዊ አስተዳደሩ ፍፁም አምባገነናዊ እየሆነ ሔደ፡፡ ሜጫና ቱለማ የመረዳጃ ማኀበርን የመሰረቱት የኦሮሞ መብት ተቆርቋሪዎችም መጨረሻቸው የሚያምር አልነበረም፡፡ ብልጭ ያለው ትግል ለአፍታ አሸለበ፡፡
ይሁንና በእዚያው አላንቀላፋም፡፡ በ1960 (እ.ኤ.አ 1967) የብሔሮች ጭቆና ያገባናል ያሉ ወጣቶች የህቡዕ አደረጃጀትን ፈጥረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባርን መሰረቱ፡፡ በ”ሶርያ”ና በየመን ወታደራዊ ስልጠናን ወስደው ለማይቀረው ትግል የተዘጋጁት የምስጢራዊ ቡድኑ አባላት አዲስ አበባ ውስጥ መዋቅራቸውን ለመዘርጋትም እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡ “ሶርያ” የከረሙት የድሬዳዋ ተወላጆቹ መኸዲ መሐመድ እና ሙሣ ቡሽትም ተልእኳቸውን መሬት ለማውረድ አብሯቸው የሚኖረውን ሰው የሕቡእ አደረጃጀቱ አባል አደረጉ፡፡
አሊ መሀመድ ሙሣ ከሁለቱ ወጣቶች መረጃዎችን እየተቀበለ ለሌሎች ማድረስና ማደራጀት ላይ መሳተፉን ቀጠለ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ እያለም ነበር ድብቋ አሜሪካ ግቢ አካባቢ የሚኖርባት ቤት ድንገት የተንኳኳችው፡፡ በሩን ከፈተው፡፡ አንድ ሰው መኸዲ መሐመድን እንደሚፈልግ ነገረው፡፡ አብሮት የሚኖረውን ሰው ለመጥራት አላንገራገረም፡፡
መኸዲን ከፊቱ ያለውን ሰው አቤት አለው፡፡ 200 ብር ተልኮልህ እርሱን ለመስጠት ነበር ብሎ መልዕክተኛው እጁን ወደ ኋላ ኪሱ ላከ፡፡ የመዘዘው ግን የብር ኖቶችን አልነበረም፡፡ ሽጉጥ አውጥቶ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን መንግስት እንደሚያውቅ ተናግሮ፣ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲሔዱ አዘዛቸው፡፡ አሊ መሀመድ ሙሳ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የደህንነት ሰዎች እጅ መውደቁን ሲረዳ ማታ የምለብሰው ነገር ብቻ ልያዝ ብሎ ወደ ቤቱ ተመልሶ ገባ፡፡ ሳያመነታ በመስኮት አንድ ፎቅ ወደ ታች ዘሎ አመለጠ፡፡
አሊ መሃመድ ሙሳ የመድረክ ስሙን የአዘቦት መጠሪያው ያደረገ ድምፃዊ ነው፡፡ ግን ይኼም ታሪክ ከፖለቲካ አላመለጠም፡፡ በ14 ዓመት እድሜው የ”አፍራን ቀሎ” የሙዚቃ ቡድን አካል ከሆነው “ሂሪያ ጃለላ” የታዳጊዎች ስብስብ ጋር የመጀመሪያ ዜማው “ቢራ ዳ በርሄን” ሲጫወት “ፀሀይም አበራች አበቦቹም ፈኩ፤ አቤቱ አምላኬ እኔ ምን በደልኩ” ሲል አንጎራጉሯል፡፡ ታዳሚው በትንሹ ልጅ አጨዋወት ተማርኮ የላቀ አድናቆቱን ለገሰው፡፡ የመጀመሪያ ስራውም የአባቱን ስም አስረሳች፡፡ አሊ መሀመድ መባሉ ተረስቶ አሊ ቢራ በሚለው ናኘ፡፡ አሊ ትውልዱ ድሬዳዋ ነው፡፡ የአባቱ ስም መሀመድ ሙሳ ሲሆን የእናቱ ስም ደግሞ ፋጡማ አሊ ይባላል፡፡ አሊ፤ አሊ የተባለው አያቱን (የእናቱን አባት) ለማስታወስ ነው፡፡
ይሁንና የወይዘሮ ፋጡማን አባት ስም መጠሪያው ያደረገው አሊ ከእናቱ ስምን እንጅ ፍቅርን አልወረሰም፡፡ ገና በሕፃንነት እድሜው ወላጆቹ ፍች በመፈፀማቸው አባቱ ጋር ቀረ፡፡ የመሀመድ ሙሳ ገቢ አነስተኛ መሆን ደግሞ  ከአባቱም ነጠለው፡፡ አቶ መሀመድ ለአጎታቸው የትዳር አጋር ወይዘቶ ሜይሮ አሊ አደራ ሰጡ፡፡ ሜይሮ ከአቶ መሀመድ ቢሻሉ እንጂ የእሳቸውም የገቢ ምንጭ እንጀራ መሸጥ ነበር፡፡ እናም ታዳጊው አሊ እንጀራ የመሸጥ ኃላፊነት በለጋ እድሜው ወደቀበት፡፡ የአሊ ለስላሳ የህይወት ዜማ ጅማሮው ያኔ ነው፡፡”አለ ትኩስ እንጀራ አለ” እያለ የሚሸጥበት መንገድ ለዛ ያለው ነበረ፡፡ ከሰፊዋ ዓለም ያገኛት ትንሿ ቀዳሚ የሙዚቃ መድረክ እሷ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ዜማና ማንጎራጎር ለመደባት፡፡
አቶ መሀመድ ለራሳቸው የሚሆን ቁራሽ ቢያጡም ለልጃቸው ግን የቻሉትን ሁሉ ለማድረግ መፍጨርጨራቸው አልቀረም፡፡ በመሆኑም የእስልምና ትምህርትን እንዲከታተል አስመዘገቡት፡፡ ቁርዓን ሊቀራ ከዕኩዮቹ ጋር ዋለ፡፡ የአቶ መሀመድ ዓረብኛ መቻል ደግሞ ቋንቋውን አቀለለለት፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላም ተመረቀ፡፡ አሊን በሃይማኖታዊ አገልግሎት የጠበቁት አልታጡም፡፡ ልጅነቱን እየተሰናበተ የነበረው ታዳጊ ግን ለራሱ መሀንዲስ ሆኖ አቅጣጫውን ቀየሰ፡፡
ጓደኞቹ ወደ ነገሩት “አፍራን ቀሎ” የሙዚቃ ቡድን ሄዶም ተመዘገበ፡፡ አባልነቱ አንጋፋዎቹ የሙዚቃ ቡድኑ አባላት በደረሱለት ሶስት ዜማዎች ታጅቦ ከህዝብ ፊት አቆመው፡፡ “ቢራ ዳ በርሔ” በድሬዎች መንደር ተወዳጅ ሆነች፡፡ አላቆመምም፡፡ የተለያዩ የዓረብኛ፣ ሱዳንኛ እንግሊዝኛ ዜማዎችን እየተዋሰ የሚሰራቸው የኦሮምኛ ሙዚቃዎች ከዕድሜው በላይ የእውቅና ከፍታ ላይ ሰቀሉት፡፡ ይሁንና የድሬዳዋና “አፍራን ቀሎ”ን ፍቅር ፖለቲካ መረዘው፡፡ እነዛ አሊን የወደዱ የሙዚቃ አፍቃሪያንም ትንሹን ልጅ ከዓይናቸው አጡት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ስደትን መርጦ ወደ ጂቡቲ ጉዞ መጀመሩ ነበር፡፡
ይሁንና ጂቡቲ የነበሩ ወታደሮች ሕገ-ወጥ ነው ብለው ወደ እስር ቤት ወረወሩት፡፡
 የአምስት ወራት እንግልቱን ሲጨርስ አማራጭ አልነበረውም፤ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡
የትውልድ መንደሩ ግን የጠፋባትን ልጅ በደስታ አልተቀበለችውም፡፡ የንጉሱ የደህንነት ሰዎች አሊና ጓደኞቹን በፖለቲካ ክስ ወደ ማረሚያ ላኳቸው፡፡ በትንሹ ልብ ውስጥ የበቀለው የፖለቲካ ተሳትፎ ነፍስ የዘራው አሳሪዎቹ ወደ ጠቅላይ ግዛቱ መቀመጫ ሐረር በ1957 ካዛወሩት በኋላ ነበር፡፡ በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተጠርጥሮ የታሰረ አንድ ወጣት በፖሊሶች ይህ ቀረሽ የማይባል ግፍ ሲፈጸምበት ያስተውላል፡፡
በአሊ ገለጻ ተጠርጣሪው ወንጀሉን አለመፈጸሙ እሙን ቢሆንም፣ ፖሊሶች ግን የጭካኔ በትራቸውን ለአፍታ ሊያስቀምጡ አልወደዱም፡፡
በመጨረሻም ስቃዩ የከበደው ሰው ያላደረገውን ወንጀል አመነላቸው፡፡ አላመነቱም፡፡ በፍርድ ቤት አስወስነው በስቅላት ገደሉት፡፡ አሊ ከትንሿ የእሥር ክፍሉ ሆኖ ያን ሰው ሲያጣጥር አይቶታል፡፡ ኋላም ላይመለስ ሲያሸልብ እንደዛው፡፡ አሊ ቢራ በልጆቿ ላይ የምትጨክነው ኢትዮጵያ ትቅርብኝ ያልኩት ያኔ ነበር ይላል፡፡ የድሬዳዋው መልከ መልካም ወደ አዲስ አበባ ያቀናው ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላ በሰኔ ወር 1958 ነው፡፡
ብዙ አልቆየም፡፡ በአንድ አጋጣሚ ሲያንጎራጉር የተመለከቱት የክብር ዘበኛው ኮለኔል ጣሒር ኤልተሬ ወደ ክብር ዘበኛ ሙዚቃ ክፍል እንዲቀላቀል እድሉን አመቻቹለት፡፡ በ1959 አሊ መሀመድ ሙሳ በአገሪቱ ትልቅ የሚባለው የሙዚቃ ክፍል አባል ሆነ፡፡ ስራዎቹ አድናቆት ማግኘታቸው የትናንት አምሮቱን አልረታውም፡፡ በዚህ ምክንያትም በኦሮሞ የትግል ታሪክ ውስጥ ከግንባር ቀደሞቹ ተርታ በሚመደበው የሜጫና ቱለማ መረዳጃ ማህበር ውስጥ በሙዚቃው ድጋፍ ማድረግ ጀመረ፡፡ ለድሬዳዋው ፈናን ወግ አጥባቂው ክቡር ዘበኛ የሚመቸው አልነበረም፡፡ የሚያገኘው ገቢ ማነስ ተጨምሮበት ሙዚቃን አቁሞ አዋሽ ሌላ ስራ ጀመረ። ሙዚቃን ከአንገት በላይ ቢያኮርፋትም ልቡ ግን እሷው ጋር ነበር፡፡
“አዋሽ ነማ ሾኪሶ” የተሰኘ ስራውን ከህዝቡ ትውፊት ተውሶ ውብ አድርጎ የተጫወተው ከዛ መልስ ነው፡፡ ነፃነትን ናፋቂው አሊ፤ ከዚህ በኋላ ፊቱን ያዞረው ወደ ምሽት ክበቦች ነበር፡፡ በአብዮቱ ዋዜማ ሰሞን ጠመንጃ ያዥ አካባቢ በሚገኘው “ዋዜማ ክለብ” ሥራውን አሀዱ አለ፡፡ የጭቆና ምንጭ ነው ባለው ስርዓት ላይም በድፍረት ማዜሙን ቀጠለ፡፡ አሊ የናፈቀው አብዮት ዘገየ አንጂ አልቀረም፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዙፋን ተገርስሶ ወታደራዊው የደርግ ሥርዓት አራት ኪሉ ደረሰ፡፡ ንጉሳዊውን መንግስት አምርሮ የሚጠላው የድሬው ፈናንም፣ ባላባቱን የሚነቅፍ “አባ ለፋ” የሚል ሙዚቃውን ይዞ ብቅ አለ፡፡
አሊ ለውጥን ቢናፍቅም በመጣው ለውጥ ለመሰላቸት ግን አፍታ አልወሰደበትም፡፡ በመሆኑም በተለያየ መንገድ ለኦሮሞ ማንነት ሲታገሉ የነበሩና ዘግየት ብለው ኦነግን ከመሰረቱ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር በቅርበት መስራት መረጠ፡፡ እነዚህ ወገኖች ድሬዳዋ ያሉ የሙዚቃ ሰዎችን አምጥተህ ስልጠና ስጥልን ባሉት መሰረትም ስልጠና ሰጠ፡፡
 አሊ መሀመድ ሙሳ ወዲህ የኦሮሞን ማንነትና ባህል ለማስተዋወቅ እየታገለ ወዲያ በምሽት ቤቶች ስሙ መናኘት ጀመረ፡፡“ዛምቤዚ ክበብ” የተጀመረው ተወዳጅነት፣ ሜክሲኮ አቅራቢያ ባለው “ዲያፍሪክ” ሆቴል ገነነ፡፡ ማሕሙድ አህመድን የመሰሉ ተወዳጅ ድምፃዊ የያዘው በራስ ሆቴል የነበረው አይቤክስ ባንድም ከአሊ ቢራ ጋር መጣመርን መረጠ፡፡ ይህ አብሮነትም “አማሌሌ” የተሰኘ አልበሙን አዋለደ፡፡ አሊ በ1970ዎቹ አጋማሽ የእውቅና ማማ ላይ ቢደርስም የስዊድን ኤምባሲ ሰራተኛ ከነበረችው ባለቤቱ ብርጊታ አስትሮም ጋር ኑሮውን ሊያደላድል ወደ አሜሪካ መጓዙ ግን አልቀረም፡፡
ይህም ቢሆን ከሙዚቃው ሰማይ እንጂ ከኦሮሞ የትግል ጥያቄ አላራቀውም፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ “የኦሮሞ ነፃነት ግንባር” እና “የኦሮሞ እስላማዊ ነፃነት ግንባር” ያላቸውን ልዩነት በውይይት እንዲፈቱና በአንድነት እንዲታገሉ ያልተሳካ ሙከራ አድርጓል፡፡ አሊ በፖለቲካ ቡድኖች ገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች ላይ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ቢኖረውም፣ ይፋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ግን ኖሮኝ አያውቅም ይላል፡፡ ይልቁኑስ በውጪ ዓለምም ቢሆን በያዝ ለቀቅ ሙዚቃውን ገፋበት፡፡ እንዲህ ያለው ሕዝባዊ ቅቡልነትን የያዘ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ደግሞ በኢህአዴግ መራሹ መንግስት ላይ ጫና መፍጠሩ አልቀረም፡፡
በመሆኑም አሊን ወደ አገሩ መመለስ ትልቅ የፖለቲካ ፕሮጀክት ሆነ፡፡ የወቅቱ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ሳዶ የመሩት ተልዕኮ ከመግባባት ተደርሶበትም የሁለት አስርታት ስደተኛው ወደ አገሩ ተመለሰ፡፡ የአሊ መሀመድ ሙሳ ወደ አገር ቤት መመለስ በበርካታ ደጋፊዎቹ ነቀፌታን ቢያስከትልም፣ እርሱ ግን የመመለሱ አንዱ ምክንያት “በ1997 በነበረው የምርጫ ቅስቀሳ የአንድነት ኃይል የሚባሉት “ጨፍላቂ” አስተሳሰብን የያዙ ወገኖች በፖለቲካው ሜዳ ጎልቶ መታየት የፈጠረው ስጋት ነበር” ይላል፡፡
የድሬዳዋው ፈናን ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ ከጊዜው የትዳር አጋሩ ሊሊ ማርክስ ጋር በመሆን የ”ቢራ ፋውንዴሽን”ን በመመስረት በትምህርት ቤቶች አነስተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆች ልጆችን ለመርዳት ሰፊ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ አሊ በረጅሙ የሙዚቃ ዘመኑ እልፍ ጊዜ ሞትን ፊት ለፊት ገጥሟል፡፡
አስቀድሞ በጉበት ካንሰር ተይዞ በተደረገለት ቀዶ ጥገና በተአምር ከሞት አምልጧል፡፡ በሌላ ወቅትም የጭንቅላት ዕጢ ቀዶ ጥገና ተደርጎለት ዳግም ሞትን ረቷል፡፡ አሊ መሀመድ ሙሳ ለሶስተኛ ጊዜ የወገብ ቀዶ ጥገና ሲደረግለትም የከፋ የጤና ችግር ገጥሞት ነበር፡፡ ይሁንና ሞትን አሳፍሮ በበርካታ መድረኮች ላይ እየተገኘ ለህዝቡ የደስታ ርችት፤ ላመነበትም የትግል ቃፊር ሆኖ ዘለቀ፡፡
ለአሊ ቢራ ሙዚቃ ምሽጉ ናት፡፡ ነፃነትና እኩልነትን አሻግሮ የሚመለከትባት፡፡ በሙዚቃዎቹ ውስጥ ሁሌም የማናጣት የድብቅ ወዳጁም ለዚህ ምስክር ናት፡፡
አንዴ በውብ ሴት፣ ሌላ ጊዜ በጨረቃ፣ ሲያሻው በፀሀይ የሚመስላት፡፡ “ሲን በርባዳ ሆጉ”፣”ኦሮሞ ቦሩ”፣”ያ ሁንዴ አያና” እና “ገመቹ” ውስጥ ያች ውብ ተዚሞላታል፡፡ በአሊ ቢራ ሙዚቃዎች ላይ ትንታኔ የፃፈው ዘመድኩን ምስጋናው፤ በአሊ ሙዚቃዎች ውስጥ ያለችው ሴት ቅኔ ፍች “ኦነግ” ነው ይላል፡፡ የመሀመድ ሙሳ ልጅ በይፋ አይንገረን እንጂ ስለ ኦነግ አብዝቶ በስስት ተጫውቷል፡ በአደባባይ ስለ ኦሮሞ ህዝብ ያለውን አስተሳሰብ ተናግሯል፡፡
“አኒስ ቢያን ቀባ” (የአገር ፍቅር) እና “አዴ ኦሮሚያ” ( እምዬ ኦሮሚያ) ብሎ ኦሮሞን አምሳለ አገር አድርጎ አዚሟል፡፡
ዕውቁ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር መሀመድ ሀሰን፤ አሊን ድል አድራጊ የነፃነት አርበኛ ያደርጉታል፡፡
 ምክንያታቸውም ከአምሳ አመት በፊት ኦሮምኛን በማዜሙ ለእስርና ስደት የተዳረገው አሊ፤ ከ50 ዓመት በኋላ በአገሪቱ መሪዎች ፊት የሚሸለም ስመ ገናና ወደ ከመሆን መሸጋገሩ ነው፡፡ ገለፃቸው የሙዚቃና ፖለቲካን ድንበር ያፈርሳል፡፡ አሊንም እንደ ሙዚቀኛ ብቻ እንዳንመለከተው ያስገድዳል፡፡
(ከይነገር ጌታቸው (ማዕረግ) “ጠመንጃና ሙዚቃ” መጽሐፍ የተወሰደ)


 የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሃላፊ፤ ሩሲያ ከዩክሬን የእህል ኤክስፖርት ስምምነት ከወጣች ዓለምን መመገብ ፈታኝ እንደሚሆን አስጠነቀቁ፡፡
ሲንዲ ማክኬይን ሰሞኑን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ የፊታችን ሜይ 18 ቀን 2023 ዓ.ም የጊዜ ገደቡ እንደሚያበቃ የሚጠበቀው ስምምነት መታደስ ይኖርበታል፡፡
የእህል ኤክስፖርት ስምምነቱ ዩክሬን፣ ጦርነቱ እየተካሄደም ቢሆን፣ ብዙ ሚሊዮን ቶን ምግብ እንድታጓጉዝ አስችሏታል ተብሏል፡፡ ስምምነቱን ያሸማገሉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ቱርክ ነበሩ-ባለፈው ሃምሌ ወር፡፡ዩክሬን የበቆሎ፣ ስንዴና ገብስ ትልቋ ዓለማቀፍ ላኪ አገር ስትሆን፤ባለፈው ዓመት በዓለም ምግብ ፕሮግራም ከተከናወነው የስንዴ ግዢ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የተገኘው ከዩክሬን እንደነበር ታውቋል፡፡  “ስምምነቱን ማደስ አለባቸው፡፡ ካላደሱ በስተቀር እንኳን ዓለምን ቀርቶ ክልሉንም መመገብ አንችልም፡፡” ብለዋል፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሃላፊዋ፡፡ “እንደምታውቁት ዩክሬን የአውሮፓ የዳቦ ቅርጫት ነበረች፣ አሁን ግን ያ እየሆነ አይደለም፤ እናም እህሉን ከዚያ ማውጣት አለብን፤ ምክንያቱም ሌሎች አገራትን እየጎዳ ነው” ሲሉ አስረድተዋል፤ ሃላፊዋ፡፡
ስምምነቱ በአንድ ጊዜ የሚራዘመው ለ120 ቀናት ነው፤ ነገር ግን ሩሲያ በእህልና ማዳበሪያ ኤክስፖርቷ ላይ በገጠማት መሰናክል ሳቢያ፣ ሜይ 18 ከስምምነቱ እንደምትወጣ በመግለፅ፣ በዓለም ላይ  ሥጋት ጋርጣለች ተብሏል፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው፤ የሩሲያ፣ ዩክሬን፣ቱርክና የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ሃላፊዎች ስምምነቱን በማራዘም ሃሳብ ላይ ለመወያየት ባለፈው ሃሙስ በኢስታንቡል ተሰብስበው ነበር፡፡ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ላይ ግን አልደረሱም፡፡
“ጉዳዩ በእጅጉ ያስጨንቀኛል፡፡ የተቀረውንም ወገን ሁሉ ሊያስጨንቀው ይገባል፡” ብለዋል፤ ሃላፊዋ፡፡
“ሁሉም የዓለም መሪ” ስምምነቱ እንዲታደስና ግጭቱ እንዲቆም ሁኔታዎችን በማመቻቸት ያግዝ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል - የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሃላፊዋ ሲንዲ ማክኬይን፡:



 አዲስ ሃላፊ መቅጠሩ መሰማቱን ተከትሎ የቴስላ አክሲዮን በ2 በመቶ አድጓል

         ቢሊየነሩ ኢሎን መስክ ለትዊተር አዲስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መቅጠሩን ከትላንት በስቲያ ሃሙስ ያስታወቀ ሲሆን፤ አዲሷ የኩባንያው ሥራ አስፈፃሚ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ሃላፊነቱን ከባለ ሃብቱ ትረከባለች ተብሏል፡፡
“ለትዊተር አዲስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መቅጠሬን ሳስታውቅ በመጥለቅለቅ ስሜት ተሞልቼ ነው፡፡ በ6 ሳምንት ጊዜ ውስጥ ስራ ትጀምራለች!” ሲል  መስክ በግል የትዊተር ገፁ ፅፏል፡፡ የአዲሷን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ማንነት ግን ከመግለፅ ተቆጥቧል፡፡“የእኔ ሚና ወደ ዋና ሊቀ መንበርነትና ዋና የቴክኖሎጂ ሃላፊነት ይሻገራል” ያለው ኢሎን መስክ፤ በኩባንያው ውስጥ በዋና የቴክኖሎጂ ሃላፊነት በንቃት እንደሚሳተፍም አስገንዝቧል፡፡
ባላሃብቱ ባለፈው የካቲት ወር፣ በ2023 መጨረሻ ላይ ለትዊተር አዲስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ እንደሚቀጥር ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡መስክ የኤሌክትሪክ መኪኖች አምራቹ ቴስላ እንዲሁም የጠፈር መንኮራኩር አምራቹና የሳተላይት ኮሙኒኬሽን ተቋም የሆነው SateliteX  ዋና ሥራ አስፈፃሚም መሆኑ ይታወቃል፡፡
ባለፈው ህዳር ወር መጀመሪያ፣ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኩን በ44 ቢሊዮን ዶላር ከገዛ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ፣ ቢሊየነሩ ለዴልዌር ፍ/ቤት፣ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ የመሆን ፍላጎት እንደሌለው ተናግሮ እንደነበር ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
በሚያስገርም ሁኔታ ራሱ መስክ ፈጠረው የትዊተር አስተያየት መሰብሰቢያ ፖል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የትዊተር ተጠቃሚዎች፣ ባለሃብቱ ከሃላፊነቱ እንዲወርድ የጠየቁ ሲሆን እሱም ለአስተያየታቸው ተገዢ እንደሚሆን ቃል ገብቶ ነበር ተብሏል፡፡
 ቢሊየነሩ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኩን ገዝቶ መምራት ከጀመረ ወዲህ ኩባንያው ብዙ ምስቅልቅሎች እንደገጠሙት የሚያስታውሱ የቴክኖሎጂ ተንታኞች፤ ለትዊተር ጤናማ የወደፊት ጉዞ አዲስ ዋና ስራ አስፈፃሚ መቀጠሩን ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብለውታል፡፡
አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው፤ መስክ ለትዊተር አዲስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መቅጠሩን ማስታወቁን ተከትሎ፣ ባለፈው ሃሙስ፣ የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ቴስላ አክስዮን በ2 በመቶ  ገደማ አድጓል፡፡ የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ኩባንያው ባለ አክሲዮኖችም የመስክ ምን ያህል ትኩረት በትዊተር ላይ ይውላል ከሚለው አሳሳቢ ጉዳያቸው እፎይታ ያገኛሉ ተብሎ ተገምቷል፡፡
የቴስላም ሆነ የማናቸውም ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስፈፃሚ የመሆን ፍላጎት ፈፅሞ ኖሮኝ አያውቅም የሚለው ኢሎን መስክ፤ ራሱን ከዋና ሥራ አስፈፃሚነት ይልቅ እንደ ኢንጂነር መቁጠር እንደሚመርጥ ይገልፃል፡፡

 “አገሪቱ የህዝቡ እንጂ የሱዳን ሠራዊት አይደለችም” ፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ


     የሱዳን መደበኛ ጦር ሰራዊትና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ላለማድረስ የመጀመሪያውን ስምምነት በሳኡዲዋ የወደብ ከተማ ጂዳ መፈራረማቸውን የቻይናው CGTN የሳኡዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
የሱዳን ሲቪሎችን ከጉዳት ለመጠበቅ ባለፈው ሐሙስ የተፈረመው የጂዳ የቃል ኪዳን ዲክላሬሽን ስምምነት የተመቻቸው፣ በሳኡዲ አረቢያና በአሜሪካ መንግስታት መሆኑ ታውቋል፡፡
የሱዳን ህዝብን ጥቅም ማስቀደምና ለሲቪሎች በማናቸውም ጊዜያት ጥበቃን እንዲሁም የሰብአዊ እርዳታ ነፃ እንቅስቃሴን ማረጋገጥን በመሳሰሉ ሰብአዊ መርሆዎች ላይ የሚያተኩረው ዲክላሬሽኑ፣ ለጊዜው ምንም አይነት የተኩስ ማቆምን ባያካትትም፤ሁለቱ ሃይሎች በተጨማሪ ውይይት ለአጭር ጊዜ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንደሚሰሩ ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪ ውይይት ይደረስበታል ተብሎ የሚጠበቀው የአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት፤ ለሳምንታት ተቋርጠው የቆዩትን የውሃና ኤሌክትሪክ የመሳሰሉ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለነዋሪዎች ሊመልስ ይችላል ተብሏል፡፡ለአራት ሳምንታት ያህል በዘለቀውና በሱዳን የጦር ሰራዊትና በፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ መካከል ተባብሶ በቀጠለው የካርቱም ጦርነት፣ እስካሁን ቢያንስ 604 ሰዎች እንደ ሞቱና 5ሺ 127 ለጉዳት እንደተዳረጉ የዓለም ጤና ድርጅት ሰሞኑን አስታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቪኒ፤ የሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች የተኩስ ማቆም እንዲያደርጉ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የሱዳን ጄነራሎች በጦርነት የምትታመሰውን አገሪቷን እንደ ግል ጉዳያቸው ከመቁጠር እንዲቆጠቡም አስጠንቅቀዋል፡፡
“ህዝቡ እንደ አገር ባለቤትነቱ ሰላም አግኝቶ፣ መሪዎቹን እንዲመርጥ የተኩስ ማቆም ወሳኝ ነው” ያሉት የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት፤ “አገሪቱ የሱዳን ጦር ሠራዊት አይደለችም፤ የህዝቡ እንጂ፡፡” ብለዋል-በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት፡፡
ፕሬዚዳንቱ ይህን መልእክታቸውን ባለፈው ረቡዕ ያስተላለፉት በሱዳን፣  የሽግግር ሉአላዊ ም/ቤት ሊቀመንበር ልዩ ልዑክ፣ ዳፋላህ አል-ሃጂ አሊን፣ በሳምንቱ መጀመሪያ በኢንቴቤ ቤተ መንግስት ተቀብለው ካነጋገሩ በኋላ መሆኑን የኬንያው ዴይሊ ኔሽን ጠቁሟል፡፡ ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቪኒ የሱዳን አመራር የማንነት ፖለቲካ ውስጥ እንዳይገባም አስጠንቅቀዋል፡፡  



ከእለታት አንድ ቀን አንድ መጠጥ ቤት የነበረው ባላባት ነበረ። ይህ ሰው በጣም ስስታምና እምነተ-ቢስ ሰው ነበር።  በህልሙም በእውኑም  አግባብነት  የሌለው ትርፍ ከማግበስበስና ሀብታም ከመሆን በስተቀር የሚያስበው ነገር የለም። ሆኖም ምንም ያህል ጥረት ቢያደርግ በየዕለቱ እየደኸየ ነበር የመጣው። አንድ ቀን አንድ አጎቱ ሊጠይቁት መጡ። ለረዥም ጊዜ አልተገናኙም ነበር።
“ሥራ እንዴት ነው?” አሉ አጎቱ።
“ኧረ እንደው ምኑም አልሳካልህ ብሎኛል። በየቀኑ መደህየት ሆኗል የኔ ነገር። የቢራው በርሜል ውስጥ ውሃ ጨምሬ አቅጥኜ ልሸጠው ሞከርኩ።  ወይኑንም በውሃ አቅጥኜ አብዝቼ  ለመሸጥ ሞከርኩ፤ የመጨረሻ እርካሽ የሚባለውን ስጋና ቅጠላ ቅጠል ገዝቼ በውድ ለመሸጥም ሞክሬያለሁ። በተቻለኝ መጠንም ሂሳብ ስመልስ የተሳሳተ መልስ እየሰጠሁ ላጭበረብርም ሞከርኩ። ብዙ ብር አገኝ መስሎኝ ያልፈነቀልኩት ድንጋይ፣ ያልበጠስኩት ቅጠል አልነበረም። ያም ሆኖ አሁንም ከመደህየት አላመለጥኩም። ምን ችግር ውስጥ እንደገባሁና ምን አይነት የኮከብ ጠማማ እንዳለኝ አይገባኝም።”
“እኔ ግን አንተን ሀብታም የሚያደርግህ አንድ ዘዴ አውቃለሁ” አሉ አጎትየው። “ና ላሳይህ” አሉና ቢራውም፣ ወይኑም፣ ምግቡም ወደሚከማችበት ወደ ዋናው መጋዘን ይዘውት ሄዱ። ከዚያም በሩን በትንሹ ከፈት አድርገው “በል በቀዳዳው አሾልከህ እይ” አሉት።ባለመጠጥ ቤቱ ግን ምንም ነገር ከተለመደው ውጪ ሊታየው አልቻለም። “ኧረ ምንም አይታየኝም” አለ።
“እስቲ እግርህን በእግሬ ላይ አድርግ።  እጅህን ደግሞ እኔ ራስ ላይ አድርግና ለማየት ሞክር።” አጎቱ እንዳሉት አደረገ። ከዚያ እንደገና ወደ መጋዘኑ ተመለከተ። አይኑ ማመን አቃተው። ከመጋዘኑ መካከል ከወለሉ ላይ አንድ ወፍራም አጭር ቁዝር ሰውዬ ተቀምጧል። ምግቡን አሁንም አሁንም ይጠቀጥቃል። ኬክ በቅቤ፣ በጨው፣ በዱቄት ያሻምዳል። ከዚያም አሳማና  እንቁላል ይጎርሳል። ደሞ በዚያ ላይ ቢራ ይጨምርበታል። ደሞ ይጎሰጉስበታል።
“ማን ነው? ምንድን ነው ይሄ?” ሲል ጠየቀ ባለግሮሰሪው።
“ይሄ የቅቤ አምላክ ይባላል።” አሉ አጎትየው። “እነዚህ አማልክት ስስት ባለበትና እምነተ-ቢስነት በነገሰበት መጠጥ ቤት ሁሉ ይኖራሉ። ማጭበርበርና ዳተኝነት ባለበት ቦታ ሁሉ ይመጣሉ።”
“ግን እንደዛ ካለ ባህሪዬ እንዴት አድርጌ ማምለጥ እችላለሁ?”
“ማምለጥማ አትችልም። ደንበኞችህን ባታለልክ ቁጥር የቅቤ አምላክ አንተን ያታልልሃል። እርግጥ ነው ይህን አመልህን ትተህ ለደንበኞችህ ቀና አገልግሎት መስጠት ስትጀምር የቅቤ አምላክም ጥሎህ ይጠፋል። ግን ለደንበኞችህ በጣም ምርጥ ምግብ አቅርበህ ተመጣጣኝ ክፍያ መጠየቅ ይኖርብሃል። ይሄን መናኛ ምግብና የቀጣጠነ መጠጥ እያቀረብክ እንደምታደርገው ያለ ተግባር አማልክቱ እንዲሸሹ አያደርጋቸውም።”
ይህንን ብለው አጎትየው ትተውት ሊሄዱ ተነሱ። በቅርቡ ተመልሰው እንደሚጠይቁት ቃል ገቡለት። ከዚህ በኋላ አጎት አልተመለሱም። ባለ ግሮሰሪው ግን ሆቴሉን ማሻሻሉን ቀጠለ። ባሻሻለውም ቁጥር ትርፉ እየጨመረ መጣ። ሃብታም ሆነ፡፡ መጠጥ ቤቱ ጢም ብሎ ይሞላ ጀመር። የዚህን መጠጥ ቤት ምግብ ለመቅመስ ከሩቅም ከቅርብም በላተኛው ይፈላ ጀመር። ቢራው ይደነቅ ጀመር። ወይኑም ስሙ የተጠራ ሆነ።
ከዓመት በኋላ አጎትየው መጡ። ሁኔታው ሁሉ መለወጡንም አዩ። “እስቲ አሁን ወደ መጋዘንህ እንሂድ” አሉት።
እንደቀደመው ጊዜ አሾልከው ተመለከቱ። አሁን ከወለሉ ላይ የተቀመጠው አንድ ቀጫጫ፣ ደካማ፣ በሽተኛ መልክ  ያለው የቅቤ አምላክ ነው። ምግብ ለመብላት እየፈለገ ቅንጣት ታህል ጉርሻ ወደ አፉ ለማድረስ አቅም ያጣ ነው።
“አየህ” አሉ አጎት፣ “ታማኝነትና ጠንካራ ሰራተኝነት ባለበት ቦታ ሁሉ ዝር አይሉም። ይሄ መንፈስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሟች ነው። አንተ ወደ ጥንቱ የማታለል ተግባር እስካልተመለስክ ድረስ ወደዚህ ዝር አይልም።”
ባለግሮሰሪውም፡-
“ታማኝነትና ጠንካራ ሰራተኝነት የማታ የማታ ትርፋማ እንደሚያደርጉ ተገንዝቤያለሁ”” አለ።
***
በታማኝነትና በሠራተኝነት ላይ የሚያምን ግለሰብ፤ ኃላፊ፣ ባለስልጣን፣ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ድርጅት ማግኘት መታደል ነው። ትርፍ ከየትም ይምጣ ከየት መገኘት አለበት የሚል እምነት ደግ አይደለም። ውሎ አድሮ ከሰው ዘርፎም፣ ሰውን ገድሎ ቀምቶም ያገኙትን ትርፍ ትክክለኛ ሀብቴ ነው ማለትን ያስከትላል። የፖለቲካ የበላይነት ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተሄዱ ብዙ እኩይ ጉዳዮች ነበሩ። አሉም። ቢራው ላይ ወይም ወይን ጠጁ ላይ ውሃ እየጨመረ ሊያተርፍ እንደሞከረው ባለግሮሰሪ ብዙ ዓይነት የማማለያ መንገዶችን በመጠቀም ህዝቡን ለማጭበርበር የሞከሩ ብዙዎች ናቸው። ቋቱ ግን አልሞላም። የቅቤ አምላክ ውስጥ ውስጡን እየቦጠቦጠና እየሸረሸረ በአድልዎና በግፍ የተደበቀውን ሀብት ሁሉ ኦና እንዲቀር ያደርገዋል። ምልኪው ከባድ ነው፣ ሌሎችን በመበደል፣ ከሌሎች በመዝረፍ የሚካበት ሀብት መቅኖ የለውም። የኋላ ኋላ ወዳጅንም አርቆ፣ ሀብትንም አራቁቶ የራስን ህልውና ጭምር ወደማጣት ያመራል።
በሀገራችን የሚታየው የፖለቲካ ሙስናና የኢኮኖሚ ሙስና ተሳሳሪነትም፣ ተባባሪነትም ያላቸው ናቸው። በተለይ የፖለቲካ ስልጣንን ተገን አድርጎ የግል ወይም የድርጅት ኢኮኖሚያዊ ቋትን መሙላት የተለመደ ጉዳይ ነው። የማታ ማታ በገዛ ድርጅትም ሆነ በሌላ ባለጊዜ ወደ ዘብጥያ መውረድ እጅግ የታወቀ፣ እንደ ጸሐይ መግባት መውጣት የተረጋገጠ ሀቅ በመሆን ላይ ነው። አንድ የሀገራችን ፀሐፌ ተውኔት በአንደኛው ቴያትሩ ውስጥ ወህኒ ቤትን የገለጸው በንጉሥ አንደበት ነው። ንጉሡ  ወህኒ ቤቱን ሲመርቁ ባደረጉት ንግግር እንዲህ ይላሉ፡-
“የአባታችን ርስተ-ጉልት የሆነውን የሀገር ወህኒ ቤት መርቀን ስንከፍትላችሁ፤ እናንተም በተለመደው ባህላችሁ በመተሳሰብ እንድትተሳሰሩበት ነው”
እውነቱ ሁሌም ይሄው ነው። የፖለቲካውም የኢኮኖሚውም ማረፊያ ወህኒ ቤት ነው። የአባት ምርቃት ሆኖም ይሁን የሀበሻ የአጥንትና ደም ነገር፤ “በመተሳሰብ መተሳሰር” እስከዛሬ “የተለመደ ባህላችን” ሆኖ ቀርቷል። “ታማኝ ነው ያሉት የስለት እቃ ይሰርቃል” እንዲሉ ከመነሻው ስለ ዲሞክራሲያዊ ልእልና፣ ስለ ህዝባዊ ፍትህ፣ “አንድ ጥይት ስለማትተኮስባት” ሰላማዊ ሀገር፣ ነጻነቱን ካሰጡት አራስ ነብር ስለሆነ ህዝብ፣ በህዝብ ሀብት ስለበለጸጉ የቀድሞ ባለስልጣናት ሊያወጋ “ከዚህም ወዲያ ታላቅ መሪ፣ ከዚህም ወዲያ አማራጭ-የለሽ የፖለቲካ ድርጅት ኢትዮጵያ ከእንግዲህ አይኖራትም” ይባላል። አንድ ጀምበር ሳይሻገር ዲሞክራሲው የግሉ ዲሞክራሲ፣ ፍትሁም በአድልኦ የተሞላ የግሉ ፍትህ፣ ሰላሙም ጦር የሚሰበክበት፣ መሳሪያ የሚወለወልበት ከመንደር ቡድን እስከ ጎረቤት ሀገር የሚናቆርበት፣ የኢኮኖሚ ምዝበራውም ከስርዓታዊ-ዕዝ ኢኮኖሚ ወደ ፓርቲያዊ  አሊያም ባለስልጣናዊ ዕዝ-ኢኮኖሚ  Partisan Lords የፓርቲ- ባላባቶች የተፈጠሩበት ሆኖ ይገኛል።
ጊዜ ካለፈ አገር ከደቀቀች፣ ህዝብ ከተጎዳ በኋላ “በዚህ ባልፍ ኖሮ ድጡ አይጥለኝም ነበር” አይነት በውስጡ “አልተሳሳትኩም” የሚል አንድምታ ያለው ጸጸታዊ ማረሚያ ይቀርባል። የኢትዮጵያ አለመታደል፣ ከበቀልና ከጸጸት አዙሪት የማትወጣ ሀገር መሆኗ ነው። ጧቱን ይህን ባታደርግ  ጥሩ ነው ሲሉት፣ “ከእኔ ወዲያ  ፍልስፍና ላሳር ነው” ሲል ይቆይና “በግንዛቤ ችግር ምክንያት እስካሁን የሄድንበት መንገድ ሁሉ ስህተት ነበር። ዲሞክራሲያዊነትን ከማላላት  ማዕከላዊነትን ማጥበቅ፣ ከመብት ማክበር ይልቅ ጸጥታን ማስከበር ይሻላል ወዘተ” ወደሚል መደላደያ መሸጋገር እንግዳ አልሆኑም። አንዱን ቀዳዳ ሲያጥፉት ሌላ ቦታ እየተነደለ፣ አንዱን በር ሲዘጉት ሌላ እየተከፈተ ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረው የኢትዮጵያ ፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግር መላው እንደጠፋ ነው። ነውሩ በቀላሉ አይሸፈንም። ገበናው አደባባይ  ለመውጣት ጊዜ አይፈጅበትም። በሀገር ደረጃም ሆነ በመስሪያ ቤት ደረጃ መርከቡ ሲሰምጥ ከመርከቡ ከመውረድ ይልቅ ያልሰጠመው የመርከቡ ክፍል ላይ ለመቀመጥ መጋፋት እንደ ፖለቲካዊ ቅልጥፍና ከተቆጠረ ሰንብቷል። ለዚህ የሚሰጡ ወቅታዊ የሚመስሉ፣ በጥናት የተደገፉ የሚባሉ፣  በስብሰባ የጋራ መግለጫ የታጀቡ፣ በአዳዲስ መመሪያ የተቀነበቡ አያሌ ሽፋኖች ይቀርባሉ። ችግሩ ግን፤ “የሚዳቋ ጅራት፣ እርቃኗንም አይሸፍን፣ አምላክንም አያስመሰግን፤” እንደሚባለው መሆኑ ነው።

Saturday, 13 May 2023 20:28

ሂሩት በቀለ (1935 - 2015)

 ሂሩት በቀለ ከ50ዎቹ መጀመሪያ እስከ 80ዎቹ መጨረሻ ድረስ በጊዜው ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ጥቂት ስመጥር የሴት አርቲስቶች መሐከል አንዷና ተወዳጅ ድምፃዊ ስትሆን፤  የግጥምና የዜማ ደራሲም ነች:: ሂሩት የተጫወተቻቸው ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዎቿ አሁን ድረስ በህዝብ ዘንድ በጣም ተወዳጅና እንደውም ለብዙ አዳዲስ ወጣት ሴት አርቲስቶች መነሳሻና አቅም መፈተሻ መሆናቸው ግልጽ ነው።  
የህይወት ታሪክ
ሂሩት በቀለ  በእለተ ሰኞ መስከረም 28 ቀን 1935 ዓ.ም. ከእናቷ ከወ/ሮ ተናኜወርቅ መኮንንና ከአባቷ የመቶ አለቃ በቀለ ክንፌ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ቀበና ተወለደች:: እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስም ቀበና ሚሲዩን ት/ቤት[1] በመግባት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷ ተከታትላለች::
የስራ ዝርዝር
ሂሩት በትምህርት ቤት በነበረችበት ወቅት ለክፍል ጓደኞቿና ለሰፈሯ ልጆች ማንጎራጎር ታዘወትር ነበር:: ይህን ችሎታዋን የተመለከቱት ጓደኞቿም ወደ ሙዚቃው አለም እንድትገባ በተደጋጋሚ ያበረታቷትና ይገፏፏት ነበር:: በዚህ መሰረት  በ1951 ዓ.ም. ከቅርብ ጓደኛዋ ጋር በመሆን ወደ ምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል[2] በመሄድ በድምፃዊነት ተፈትና ለመቀጠር በቃች:: ብዙም ሳትቆይ ለመጀመሪያ ግዜ በተጫወተችው “የሐር ሸረሪት” በተሰኘው ዜማ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትንና ተቀባይነትን አገኘች:: ይሄኔ ነበር የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ክፍል አይኑን የጣለባት። ጥሎባትም አልቀረ፤ በ1952 ዓ.ም. ላይ ከምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል እውቅና ውጪ የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ሂሩትን በመጥለፍ  በጊዜው ኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ወደሚባለው የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ በመውሰድ በልዩ ኮማንዶዎች የ24 ሰዓት ጥበቃ እየተደረገላት ከወር በላይ ተደብቃ ቆየች:: ከአንድ ወር ያላሰለሰ ጥረት በኋላ የምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል ፍለጋውን ለማቋረጥ በመገደዱ፣ የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ክፍል ሂሩትን በይፋ በቋሚነት የሠራዊቱ የሙዚቃ ክፍል አባል አድርጎ ቀጠራት::
ሂሩት ከተጫወተቻቸው አያሌ ሙዚቃዎቿ መሀከል እንደ ህዝብ መዝሙር በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቀውና ከትንሽ እስከ ትልቅ በሀገር ፍቅር ስሜት እስካሁን የሚያዜመው “ኢትዮጵያ” አንዱ ነው::
ሂሩት በፖሊስ ሰራዊት የሙዚቃና የትያትር ክፍል ውስጥ በቅንነት ለ35 ዓመት አገልግላለች:: በእነዚህም 35 ዓመታት ውስጥ ከ200 በላይ ሙዚቃዎችን የተጫወተችና ለህዝብ ጆሮ ያደረሰች ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ በሸክላ የታተሙት ከ38 በላይ ሙዚቃዎች፣ በካሴት ደረጃ ደግሞ 14 ካሴቶች እያንዳንዳቸው 10 ዘፈኖችን የሚይዙ ለሙዚቃ አፍቃሪዎቿ አበርክታለች::
ሂሩት በሙዚቃ አለም በቆየችባቸው አያሌ አመታት ውስጥ ከብዙ ስመጥር ድምፃውያን ጋር በመሆን ስራዋን ለህዝብ አቅርባለች፤ ከነዚህም መሀከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል:- ማህሙድ አህመድ[3]: አለማየሁ እሸቴ[4]: ቴዎድሮስ ታደሰ: መልካሙ ተበጀ: ታደለ በቀለ: መስፍን ሀይሌ: ካሳሁን ገርማሞና ሌሎችም ይገኙበታል።
ሂሩት በቀለ ከ1987 ዓ.ም. በኋላ እራስዋን ከሙዚቃ አለም በማግለል፣ ጌታን እንደ ግል አዳኟ በመቀበል ሙሉ ጊዜዋንና ህይወቷን ለመንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት ከ28 ዓመት በላይ በአገር ውስጥና በውጭ አገር በመዘዋወር ስለጌታችን እየሱስ ክርስቶ ታላቅነት ላልሰሙ በማሰማት፣ አያሌ ወገኖች የእግዚአብሄርን መንገድ እንዲከተሉና ወደ ህይወት እንዲመጡ ምስክርነት በመስጠት፣ በጸሎት በመትጋት ጌታን በዝማሬ እያገለገለች ቆይታለች፡፡  
ሂሩት በቀለ በሙዚቃ አለም በነበረችበት ጊዜ ከፍተኛ አድናቆትንና ዝናን ያተረፈች እንዲሁም ደግሞ በመንፈሳዊ ህይወቷ ደስታንና የመንፈስ እርካታን ያገኘች ቢሆንም፣ የግል ህይወቷን በተመለከተ ግን ያላትን ትርፍ ግዜ ሁሉ ከልጆቿና ከቤተሰቧ ጋር ማሳለፍ እጅግ አድርጎ ያስደስታት ነበር::
ሂሩት ከሙዚቃ ስራዋና ከመንፈሳዊ ህይወቷ በተጨማሪ፥ በጨዋታ አዋቂነቷም ትታወቃለች፡፡ ሂሩት በቀለ 7 ልጆችና 10 የልጅ ልጆችን አፍርታለች::
ሽልማቶች
ሂሩት በቀለ በሙያዋ ላበረከተችው አስተዋጽኦ ከአገር ውስጥና ከውጭ ሀገር በርካታ ሽልማትና የእውቅና ምስክር ወረቀት ያገኘች ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ለመጥቀስ ያህል:
1ኛ) ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ እጅ ከወርቅ የተሰራ የእጅ አምባር እና የምስጋና ደብዳቤ
2ኛ) ከኢትዮጵያ ፖሊስ ሰራዊት ኮሚሽነር የከፍተኛ ስኬትና የላቀ አስተዋጽዎ ሽልማት ከምስክር ወረቀት ጋር
3ኛ) በሙዚቃው ዓለም ላበረከተችው ተሳትፎ ከፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ የብር ዋንጫና የምስጋና ደብዳቤ
4ኛ) በሙዚቃው ዘርፍ ለእናት ሐገሯ ላበረከተችው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም እጅ ሰርተፍኬት
5ኛ) ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በኢትዮጵያና በሱዳን ህዝቦች መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማደስ ላበረከተችው አስተዋፅኦ የእውቅና የምስክር ወረቀት
6ኛ) ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላበረከተችው የሙዚቃ አስተዋፅዖ ከኢትዮጵያ አብዮታዊ ጦር የፖለቲካ አስተዳደር የምስጋና ደብዳቤና ሽልማት
7ኛ) ከፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ የቲያትር እና ሙዚቃ ክፍል የ25-ዓመታት ከፍተኛ ስኬት እና የላቀ አስተዋፅኦ የምስክር ደብዳቤ ከፍተኛ ሽልማት ጋር
8ኛ) ከቀድሞ የሰሜን ኮርያ ፕሬዘዳንት ኪም ኢል ሱንግ እጅ ከወርቅ የተሰራ ሜዳልያ
9ኛ) ከኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነር: ለፖሊስ ሃይል ስፖርት ፌስቲቫል ላበረከተችው አስተዋፅኦ የእውቅና ሰርተፍኬት
10ኛ) ከመሰረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን: ላበረከተችው አስተዋፅኦ ልዩ እውቅና እና የምስጋና ሰርተፍኬት
11ኛ) ከወንጌል ብርሃን አለማቀፍ አገልግሎት ቤተክርስቲያን: በሃይማኖታዊ ህይወት ላሳየችው ትጋትና አስተዋፅኦ የምስጋና ሰርተፍኬት ይገኙበታል፡፡



የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስክሬኑን በነፃ አጓጉዟል


        ታዋቂው የክላርኔት መሳሪያ ተጫዋች ዳዊት ፍሬው ኃይሉ የቀብር ስነ-ስርዓት ነገ እሁድ ግንቦት 6 ቀን 2015 ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ይፈጸማል። የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴው ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ዛሬ ከሰዓት በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን  ጸሎተ ፍትሀት የሚደረግ ሲሆን እሑድ ጠዋት በሀገር ፍቅር ቴያትር ቤት በተዘጋጀ የሽኝት ስነ-ሥርዓት ስንብት ተካሂዶ፣ ቀትር 7፡00 ሰዓት ላይ ቀብር ስነ-ስርዓቱ እንደሚፈጸም አስታውቋል።
ዳዊት በቅርቡ ለስራ ጣሊያን ሀገር በሄደበት ወቅት ባረፈበት የሆቴል ክፍል ሕይወቱ አልፎ መገኘቱ ይታወሳል። በሙዚቃ የሙያ ዘመኑ 3 የሙዚቃ አልበም የሰራው ዳዊት ፍሬው፤ የአንጋፋው ድምጻዊ ፍሬው ኃይሉ ልጅ ነው።

 በደራሲ እታለም እሸቴ የተጻፈው “የመሐረቡ ምስጢር” የተሰኘ ረዥም ልብወለድ መጽሐፍ ለንባብ የበቃ ሲሆን፤ በመጪው ሳምንት ቅዳሜ ግንቦት 12 ቀን 2015 ዓ.ም ከጠዋቱ 4 ሰዓት ጀምሮ  በሐገር ፍቅር ቴአትር ቤት እንደሚመረቅ ታውቋል፡፡
በፖለቲካዊ ስላቅ ሥራዎቹ የሚታወቀው ሃማ ቱማ በመጽሐፉ ጀርባ ላይ ባሰፈረው አስተያየት፤ “ ---እኔ እንደ እታለም የረዥም ልብወለድ ታሪኮችን ጽፌ ለማቅረብ አልቻልኩም፡፡ እታለም ተራቀቅሁ፣ ከበድኩ፣ ተመጻደቅኹ በማይል ቋንቋ ከሦስት መቶ በላይ ገጾችን የሚያልፍና ከብዙኃኑ ህይወት ጋር የተሳሰረ ትረካን አስለምዳናለች፡፡ የተፈናቃዮችን ኑሮም እንኖረው ዘንድ በሚታመኑ ገጸባህርያት አማካኝነት አቅርባልናለች፡፡ --- እታለም ከዘመናችን የረዥም ልብወለድ ደራሲዎች አንዷና መነበብም ያለባት ናት እላለሁ፡፡”  ብሏል፡፡ ደራሲዋ ከዚህ ቀደም “ምንዳ” (2001 ዓ.ም)፣ “ህልመኛዋ እናት” (2004 ዓ.ም) ፣ “ተፈናቃይ ፍቅር” (2008 ዓ.ም) የተሰኙ ረዥም ልብወለድ መጻሕፍትን ለአንባቢያን አድርሳለች፡፡



የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አለባቸው አሞኜ በትላንትናው ዕለት በቢሯቸው ውስጥ መገደላቸው ተሰምቷል። ዋና ሥራ አስፈጻሚው በቢሯቸው ውስጥ ባለጉዳዮችን ተቀብለው በሚያነጋግሩበት ወቅት ባለጉዳይ ሆኖ ወደ ቢሮአቸው በገባ ሰው በተፈጸመባቸው ጥቃት ህይወታአው ማለፉ ነው የተነገረው። ግድያውን የፈጸመው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የካሳንቺስ አካባቢ ጣቢያ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት የቀጠና ኦፊሰር እንደሆነና በቁጥጥር ስር መዋሉንና ምርመራ እያጣራ  እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።


በአዲስ አበባና በሻሸመኔ ስራውን በይፋ ጀምሯል


       “ኮንሰርኒንግ ኦፍ ክርኤቲቭ ፕሮቫይዲንግ ኦሶሴሽን (ኮስፓ)” የተሰኘው ድርጅት ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ህፃናትን በማንሳትና በመንከባከብ እንዲሁም ወደ ትምህርት፣ ወደ ስራና ወደ ቤተሰብ መልሶ በመቀላቀል ስራ ላይ በይፋ መሰማራቱን አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ ትላንት ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም ረፋድ ላይ በጊዮን ሆቴል ዳሽን አዳራሽ ለሚዲያ ባለሙያዎች በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው ይህን ያስታወቀው፡፡
በበጎ አድራጎትና ማህበራት ኤጀንሲ በ2012 ዓ.ም በአገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጀትነት እንደተመሰረተና በአገር ወዳድ ምሁራን እንደተቋቋመ የተነገረለት ድርጅቱ፤ ከዓለም ባንክና ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራርሞ በአዲስ አበባና በሻሸመኔ ከተማ በይፋ ስራ መጀመሩም በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተብራርቷል፡፡
እንደ ሀላፊዎቹ ገለፃ፤ ኮስፓ የጎዳና ልጆችን ከጎዳና ላይ አንስቶ የማገገሚያ ማዕከል በማስገባት የአካልና የስነልቦና ህክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ልጆቹ ለጎዳና ህይወት የተዳረጉበትን ሥረ-መሰረት በመለየት፣ በልጆቹ ቤተሰብ ላይም ጥናትን መሰረት ያደረገ ስራ እንደሚሰራ ተገልጿል። በዚህም መሰረት ልጆቹ ከቤት የወጡት በኢኮኖሚ ችግር ነው በቤተሰብ ቀውስ፣ ወይስ በድርቅ፣ በጦርነትና ተያያዥ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮች የሚውለውን በጥናት በመለየት፣ ቤተሰባቸው ከዚህ ችግር ወጥቶ በኮስፓ ማዕከል በአዕምሮም በአካልም አገግመው የሚመለሱ ልጆቻቸውን እንዲቀበሉ ብሎም ድጋሚ ወደ ጎዳና እንዳይለቀቁ እስከማድረግ ድረስ በመስራት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ እንደሚሞከር ተብራርቷል።
ኮስፓ እ.ኤ.አ እስከ 2030 ዓ.ም ድረስ በሀገሪቱ አሉ ተብለው የሚገመቱ ከ150ሺህ በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በግማሽ ለመቀነስ እንደሚሰራ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፤ ተልዕኮውም በሂደት አገሪቱ ላይ የጎዳና ልጆች የማይታዩበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሆነ ጠቅሶ ይህ እንዲሳካ ለዚህም ትልሙ ስኬት የየከተሞቹ አስተዳደሮች ማህበረሰቡና ሚዲያው በጋራ አብሮ በትብብር እንዲሰራ ጥሪ አቅርቧል።
 ኮስፓ በአሁኑ ሰዓት 20 የጎዳና ተዳዳሪ ልጆችን አንስቶ በሻሸመኔ ማዕከሉ እየተንከባከበ ሲሆን በተለያዩ ከተሞች ስራውን የማስፋት እቅድ እንዳለውም ሃላፊዎቹ ገልጸዋል። ህፃናት ወደ ጎዳና የሚወጡበትን ሁኔታ ለመቀነስም በተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን  በትጋት እንደሚሰራ በመግለጫው ተብራርቷል።



Page 4 of 647