Administrator

Administrator

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ የቻይና ንጉስ፤ አማካሪ የሚሆነው ሁነኛ ሰው ይፈልግና አንድ አዋቂ ሊቅ አለና ወደ እሱ እንዲሄዱ፣ እንዲያሳምኑትና እንዲያመጡት ብልህ ባለሟሎችን ይልካቸዋል፡፡
ያ አዋቂ ሰው በአንድ ኃይቅ ዳርቻ ነው የሚኖረው፡፡ የንጉሡ ባለሟሎች ወደ አዋቂው ሰፈር ሄዱ፡፡ አዋቂውን ሰው አገኙትና፤ “እንደምነህ ወዳጃችን? ከንጉሡ መልዕክት ይዘን የመጣን ባለሟሎች ነን” አሉት፡፡
ሊቁ አዋቂ፤
“ምን ጉዳይ ገጥሟችሁ ወደኔ ዘንድ መጣችሁ?” ሲል ጠየቀ፡፡
ባለሟሎቹም፤
“ንጉሥ አስተዋይ፣ ታጋሽ፣ አርቆ አሳቢ፣ ዕውቀት የማይጠግብ ፈላስፋ ሰው ይፈልጋሉ፡፡ የመረጡትም አንተን ነው፡፡ ለዚህ ነው ወደ አንተ ዘንድ የመጣን” አሉት፡፡  
ሊቁ አዋቂም፤
“መምጣታችሁስ ደህና፡፡ ግን አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡፡”
ባለሟሎቹ፤
“መልካም ጥያቄህን ሰንዝር” አሉት
ሊቁ፤ “ጥያቄዬ፣ ንጉሡ ትክክለኛ አማካሪያቸው፣ እኔ መሆኑን በምን አወቁ? ዕውቀታቸው ትክክል ከሆነስ ለምን ለአማካሪነት አሰቡኝ?”
ባለሟሎቹ፤
“ነገሩ አልገባህም ማለት ነው፡፡ ንጉሡ የሚያምኑት ደመ - ነብሳቸውን ነው፡፡ ቀልባቸው የወደደውን! ያ ደግሞ አንተ ነህ፤ አለቀ” አሉት፡፡
ሊቁም፤ “ንጉሡ ቤተ መንግስት ውስጥ አንድ ከወርቅ የተሰራ ኤሊ አለ አይደለም?” ሲል ጠየቃቸው፡፡
“አዎን” አሉት፤ ስለ ኤሊው በማወቁ እየተገረሙ፡፡ ከዚያም አጠገባቸው እጭቃ ላይ የሚሄድ አንድ የውሃ-ኤሊ አሳያቸውና፤
‹‹ይሄን ኤሊ ተመልከቱ፡፡ ይሄ ኤሊ ንጉሡ ዘንድ ካለው የወርቅ ኤሊ ጋር ቦታ ትለዋወጣለህ ወይ? ተብሎ ቢጠየቅ ምን የሚል ይመስላችኋል?” ሲል ጠየቃቸው፡፡
ባለሟሎቹም፤
‹‹እምቢ የሚል ይመስለናል›› አሉት፡፡ ሊቁም፤ ‹‹በወርቅ ተለብጦ ጠረጴዛ ላይ ከመቀመጥ እዚሁ ሰፈሩ ውስጥ በሕይወት መኖሩን መረጠ፡፡ እንግዲህ የእኔም መልስ እንደዚያው ነው፡፡ እዚሁ ያለሁበት መሬት ላይ መኖርን እመርጣለሁ፤ በሉና ለንጉሡ ንገሩልኝ›› ብሎ አሰናበታቸው፡፡
*     *     *
ትክክለኛ ቦታቸውን የሚያውቁ ሰዎች ብልሆች ናቸው፡፡ ትክክለኛ ሰዎችን ለመምረጥና በትክክለኛ ቦታ ለማስቀመጥ የሚችሉ ሰዎችም እጅግ ብልሆች ናቸው፡፡ የራሳቸውን አቅምና ብቃት በአግባቡ መዝነው፡፡ “ይህ ቦታ ለእኔ አይሆንም፡፡ አልመጥነውም›› ለማለት የሚችሉ ሰዎች ራሳቸውንም፣ የሥራ ባልደረቦቻቸውንም፤ ህብረተሰብንም ከስህተት ያድናል፡፡
ዛሬ የህዝብ ጥያቄዎች ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ የህግ የበላይነትና የጉዳዩ ባለቤት መሆን ነው፡፡ በሀገራችን የመልካም አስተዳደርን ጉዳይ ስናነሳም አንዱ ችግራችን በሥራ መደቡ ላይ የተቀመጡ ሰዎች ወይ ብቃት ሲያንሳቸው፤ ወይ ቅንነት ሲያንሳቸው ወይ ደግሞ የማይችሉትን የሚችሉ መስለው ለመታየት፣ ያልሆነ ምስል ፈጥረው ሲገኙና ሥራን ሲበድሉ ነው፡፡ ከቶውንም የመልካም አስተዳደር ችግሩ እየተባባሰ ሲሄድ እኒሁ ሰዎች ስለ መልካም አስተዳደር መጉደል ጮክ ብለው እያወሩ መፍትሄ ሳያገኝ ሥር-የሰደደ በሽታ ሆኖ ቆይቷል። They shout at most against the vices they themselves are guilty of እንደሚሉት ነው ፈረንጆቹ፡፡ ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮህ እንደማለት ነው፡፡
ሁለተኛው ችግራችን ሙስና እና ሙስናን ለመሸፈን የሚደረግ ኃይለኛ የአስተዳደራዊና የተላላኪዎች መረብ መዘርጋት ነው፡፡ እከክልኝ ልከክልህ፣ ሸፍነኝ ልሸፍንህ ነው፡፡ በሀገራችን ስለ ሙስና ሲነገር እጅግ ብዙ ጊዜው ነው፡፡ ከመባባሱ በስተቀር ሁነኛ ለውጥ አልመጣም። ሙሰኞቹም ከዕለት ዕለት እየናጠጡ፣ የ‹‹አይደረስብንም” መተማመን እያበጁ፣ “በማን ይነካናል” ኩራት እየተደገጉ ይኖራሉ፡፡ ጉዳዮችን አጥርቶ ፍትሀዊ መፍትሄ የሚሰጥ በመጥፋቱ ነገሮች እየተጓተቱ ወደ ጤነኛ ዕድገት ከመሄድ ይልቅ አድሮ ጥሬ ወደ መሆን ያመራሉ፡፡ ኃላፊነት የመውሰድና የተጠያቂነትን መርህ አለመቀበል ወይም ተቀብሎ በሥራ ላይ አለማዋል፣ በስልጣን መባለግን ማስከተሉ መቼም አሌ የሚባል ነገር አይደለም፡፡ ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል አንዴ ከተጀመረ የሱስ ያህል የማይላቀቁት ጠንቅ ነው፡፡ “ከጅብ ጅማት የተሰራ ክራር ቅኝቱ ልብላው ልብላው ነው” የሚባለውን ተረት ልብ ይሏል። ከሁሉም የሚከፋው ደግሞ የመረጃ ማጥፋት ተግባር ነው፡፡ ብልሹ አሰራር ባለበት ቦታ የሰነዶች በቦታቸው አለመገኘት አይንቅም፡፡ ያን ብልሹ አሰራር በጥንቃቄ ፈትሾ፣ የውስጥ ቦርቧሪን ማግኘት ግድ ይሆናል፡፡ የውስጥ ቦርቧሪ እያለ መልካም አስተዳደርን መመኘት ምኞት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ወደ ራስ ማየትና ውስጥን መመርመር ትክክለኛውን የጥፋት ቦታ፣ ትክክለኛውን ቀዳዳ ለማግኘትና አፋጣኝና ቁርጠኛ መፍትሄ ወደ መፈለግ እንዲኬድ ያደርጋል፡፡ የምንሰጠው መፍትሄም የ“ከአንገት በላይ” መሆን የለበትም፡፡ በሥልጣን የባለገ መውረድ ካለበት መውረድ አለበት! ወለም ዘለም አያዋጣም፡፡ ከአንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም፣ ይሏልና፡፡ የችግርን ዕውነተኛ ገፅታ ካገኘን፣ የችግሩን ፈጣሪ ክፍሎችን ለይቶ ማውጣት አዳጋች አይሆንም፡፡ ምነው ቢሉ፤ “አይጢቱ ከሌለች ጉድጓዱ ኬት መጣ?” ብሎ መጠየቅ የአባት ነውና!

    የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ለሁለት “ሴት ቶፕ ቦክስ” አምራቾች፣ ለሦስት የግል ቴሌቪዥንና ለሦስት የኤፍ ኤም ሬዲዮ ብሮድካስተር ድርጅቶች ፈቃድ ሰጠ፡፡  
ባለፈው ረቡዕ በሸራተን አዲስ በተከናወነው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት፣ “ሴት ቶፕ ቦክስ” ለማምረት ከባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ከአቶ ዘርዓይ አስገዶም ጋር የተፈራረሙት ጣና ኮሙኒኬሽን ኃ.የተ. የግ.ማ እና ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሃይቴክ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ናቸው፡፡
የግል የቴሌቪዥን ብሮድካስት ፈቃድ የተሰጣቸው ሦስት ድርጅቶች፡- ፋና ብሮድካስት ኮርፖሬሽን፣ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልና አርኪ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ ኃ.ተ. የግ.ማ ናቸው፡፡ የግል ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ብሮድካስቲንግ ፈቃድ የተሰጣቸው ሦስት ድርጅቶች ደግሞ ኤዲስቴለር ትሬዲንግ ኃ.የተ.የግ.ማ (አሐዱ 94.3)፣ አርኪ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስና ዋን ላቭ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ ኃ.የተ. የግ.ማ (ሉሲ 107.8) ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ናቸው፡፡ በዕለቱ የተሰጠው ሦስት የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ፈቃድ፣ አሁን በአዲስ አበባና አካባቢያዋ አገልግሎት እየሰጡ ያሉትን ሰባት ጣቢያዎች ጋር ቁጥር ወደ 10 እንደሚያደርሰው ታውቋል፡፡
“ሴት ቶፕ ቦክስ” ማለት አሁን ያለው አናሎግ የቴሌቪዥን ስርጭት ወደ ዲጂታል ሲቀየር ስርጭቱን መቀበል የሚያስችል በቴሌቪዥን አናት ላይ የሚደረግ መሳሪያ ወይም በቴሌቪዥኑ ላይ የሚገጠም አንቴና ነው፡፡ መሳሪያው በዘጠኝ ወር ውስጥ ለአገልግሎት ይደርሳል ተብሏል፡፡ አቶ ዘርዓይ አስገዶም ንግግር ካደረጉ በኋላ የዕለቱ የክብር እንግዳ በምክትል ጠቅላይ ሚ/ር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል  ንግግር አድርገዋል፡፡ በዚሁ ወቅት አቶ ታደሰ ካሳ፤ “ሴት ቶፕ ቦክስ” አምራቾችን፣ አቶ ወልዱ ይመስል፤ የቴሌቪዥን ብሮድካስተሮችን እንዲሁም አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ፤ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ብሮድካስተሮችን በመወከል የተሰማቸውን ተናግረዋል፡፡

“የሰመጉን ሪፖርት አንቀበልም አላልንም”
   ባለፈው ጥቅምት 5 ቀን 2009 ዓ.ም ታትሞ በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ብፅአተ ተረፈ ጋር በተደረገው ቃለ ምልልስ፤ ‹‹ከፕሬዚዳንቱ ፅ/ቤት ሁለተኛ ሪፖርታችሁን ወደ ፅ/ቤታችን እንዳትልኩ ተብለናል›› ሲሉ የተናገሩት የፕሬዚዳንቱን ፅ/ቤት ስም የሚያጠፋና ፈፅሞ ያልተባለ ነገር ነው፤ አንድም ቀን ሪፖርታችሁን አንቀበልም ብለናቸው አናውቅም፤ ልንልም የምንችልበት ምክንያት የለንም፡፡ የፕሬዚንዳንቱ ፅ/ቤት ሁሉንም የሃገሪቱን ዜጎችና ተቋማት በእኩልነት የሚያገለግል ተቋም ነው፡፡
አቶ አለምነህ ረጋሳ  የፕሬዚዳንቱ የፅ/ቤት የፕሮቶኮልና ኮሚኒኬሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር፡፡

   በቴሌኮም ማስፋፋትና በኔትወርክ ዝርጋታ ስራ የተሰማራው ህዋዌ፤ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ለ‹‹መሰረት በጎ አድራጎት›› ድርጅት የትምህርት መሳሪያ ድጋፍ አደረገ፡፡  ድርጅቱ 4500 ደብተሮችን፣ 1500 እርሳሶችን፣ 1500 እስክርቢቶዎችንና ላጲሶችን ለግሷል፡፡ በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የድርጅቱ መስራችና ዳይሬክተር ወ/ሮ መሰረት አዛገ ህዋዌ ስላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው፣ ድጋፉ  ‹‹አንድ እሽግ ለአንድ ልጅ›› በሚል የሚያካሂዱትን የትምህርት ቁሳቁሶች አቅም ለሌላቸው የማከፋፈል ፕሮጄክት፣ በእጅጉ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡ በዕለቱ ከህዋዌ ያገኙት ድጋፍ በገንዘብ ሲተመን ከ50 ሺህ ብር በላይ እንደሆነ የገለፁት ወ/ሮ መሰረት፤ ድጋፉ ሌሎችም ድርጅቶች ማህበራዊ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ መነቃቃትን ይፈጥራል ብለዋል፡፡
ከድጋፉ ጎን ለጎን መሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት የተመሰረተበትን አምስተኛ ዓመት ያከበረ ሲሆን በአምስት አመት ጉዞው ያከናወናቸውን፣ ያሳካቸውንና ያለፋቸውን ፈተናዎች በዘጋቢ ፊልም ለታዳሚዎቹ አቅርቧል፡፡ የህዋዌ ተወካዮችም ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ በዕለቱ ቃል ገብተዋል፡፡ በመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት ጽ/ቤት በተካሄደው በዚህ ፕሮግራም ላይ ድርጅቱ አምባሳደር አርቲስት ሩታ መንግስተአብና አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር

      የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ ራድ አል ሁሴን በመጪው የአሜሪካ ምርጫ ሪፐብሊካንን በመወከል ለፕሬዚዳንትነት በመወዳደር ላይ የሚገኙት አነጋጋሪው ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ አሸንፈው ከተመረጡ አለማችን የከፋ አደጋ ላይ ትወድቃለች ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
አስፈሪና አሸባሪ አመለካከቶችን የሚያራምዱት ትራምፕ፤ ይህን አቋማቸውን የማይቀይሩና በምርጫው የሚያሸንፉ ከሆነ ለአለማችን ትልቅ ስጋት መሆናቸው አይቀሬ ነው ያሉት ዛይድ፣ በተለይም ትራምፕ ግርፋትን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው ማለታቸውንና በተጋላጭ ማህበረሰቦች ላይ ያላቸውን አሉታዊ አመለካከት ክፉኛ ተችተውታል፡፡
በየትኛውም አገር በሚካሄድ ማንኛውም አይነት የፖለቲካ ቅስቀሳ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌላቸው የገለጹት ዛይድ፣ ግርፋትን በሚያስፋፋና ተጋላጭ ማህበረሰቦችን የሰብአዊ መብቶቻቸው ተጠቃሚ እንዳይሆኑ በሚያደርግ መልኩ የሚቋጭ ምርጫ ሲያጋጥም ግን ዝም ማለት ተገቢ አይደለም ብለዋል፤ባለፈው ረቡዕ ጄኔቫ በሚገኘው የተመድ ዋና ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፡፡
ዛይድ በቅርቡ በሄግ ባደረጉት ንግግር ዘረኝነት የተጠናወታቸው አደገኛ ሰው ናቸው ሲሉ የትራምፕንና የሚከተሉትን ፖሊሲ በይፋ ተችተው እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሩስያ አምባሳደር በበኩላቸው፤ አንድ የተመድ ከፍተኛ የስራ ሃላፊ የውጭ አገራትን መሪዎችና መንግስታትን መተቸት አይጠበቅበትም ሲሉ የኮሚሽነር ዛይድን ንግግር መቃወማቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

     ባለፈው ሃምሌ ወር ከተቃጣበትና ከከሸፈው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጋር በተያያዘ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዜጎቹን ማሰሩን የቀጠለው የቱርክ መንግስት ባለፈው ማክሰኞም ተጨማሪ 125 የፖሊስ መኮንኖችን ማሰሩን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
የፖሊስ መኮንኖቹ እንዲታሰሩ የተወሰነባቸው ባይሎክ የተሰኘውንና በመፈንቅለ መንግስቱ ጠንሳሽ የሆነው ቡድን ደጋፊዎች የሚጠቀሙበትን የአጭር የጽሁፍ መልዕክት ማስተላለፊያ የሞባይል አፕሊኬሽን ሲጠቀሙ ተገኝተዋል በሚል መሆኑን ዘገባው ገልጧል፡፡
የመንግስት ሃይሎች ማክሰኞ ዕለት በመዲናዋ ኢስታንቡል የፖሊስ መኮንኖችንን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን  የጠቆመው ዘገባው፣ ከታሰሩት መካከልም 30 ያህሉ ምክትል የፖሊስ አዛዦች እንደሆኑ ገልጧል፡፡
የአገሪቱን የፍትህ ሚኒስትር ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው ባለፉት ወራት ከከሸፈው መፈንቅለ መንግስት ጋር ንክኪ አላቸው በሚል የተጠረጠሩ 32 ሺህ ያህል የወታደራዊ ሃይል መኮንኖች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ዳኞች፣ መምህራንና ሌሎች ባለሙያዎች ታስረዋል፡፡

  በህይወት ካሉ የቡድኑ መስራች አባላት አንዱ ነበር

      በህይወት ካሉ ጥቂት የአይሲስ መስራች አባላትና ከፍተኛ አመራሮች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለትና የሽብር ቡድኑ የፕሮፓጋንዳ ሃላፊ ሆኖ ሲሰራ የቆየው አቡ ሞሃመድ አል ፉርቃን መሞቱን ቡድኑ በድረ-ገጹ ባወጣው መግለጫ ማረጋገጡን ቢቢሲ ዘግቧል።
የአሜሪካ የመከላከያ ተቋም ፔንታጎን ባለፈው ወር ሶርያ ውስጥ ከምትገኘው ራቃ አቅራቢያ ባደረገው የአየር ጥቃት አቡ ሞሃመድ አል ፉርቃን መግደሉን ቢያስታውቅም፣ አይሲስ ግን ምንም አይነት ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቶ በሳምንቱ መጀመሪያ ሞቱን ማረጋገጡን ዘገባው ገልጧል፡፡
ቡድኑ ግለሰቡ መሞቱን እንጂ መቼ፣ የትና እንዴት እንደሞተ ያለው ነገር እንደሌለ የጠቆመው ዘገባው፣ ግለሰቡ የቡድኑን እንቅስቃሴ የተመለከቱ የፕሮፓጋንዳ መረጃዎችን በማዘጋጀትና በማሰራጨት እንዲሁም የቡድኑ ልሳናት የሆኑ ድረ-ገጾችንና መጽሄቶችን በበላይነት በመምራት ይሰራ እንደነበር አስታውሷል፡፡
አቡ ሞሃመድ አል ፉርቃን የአይሲስ የአመራር አካል የሆነው የሹራ ምክር ቤት አባል እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ቡድኑ የግለሰቡን ሞት ያረጋገጠው አንድ የአሜሪካ ተቋም የአይሲስ የፕሮፓጋንዳ ስራ እየተዳከመ መሆኑን በጥናት አረጋግጫለሁ ባለበት ወቅት መሆኑን

 - እየጋየ ያስቸገረውን ይህን ምርቱን በማቆሙ 17 ቢ. ዶላር ያጣል
                       - ደንበኞቹ በአስቸኳይ ስልኩን መጠቀም እንዲያቆሙ አሳስቧል

       በቅርቡ ለገበያ ያቀረበው የጋላክሲ ኖት 7 ምርቱ ባትሪው በቀላሉ የሚግልና እሳት የሚፈጥር ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ገብቶ የሰነበተው የደቡብ ኮርያው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሳምሰንግ፣ ችግሩን መፍታት ባለመቻሉ ከአሁን በኋላ ምርቱን ለማቆም መወሰኑን በሳምንቱ መጀመሪያ አስታውቋል፡፡
ኩባንያው በአለም ዙሪያ የሚገኙ ወኪሎቹንና የሞባይል መሸጫ መደብሮችን “ጋላክሲ ኖት 7 መሸጣችሁን አቁሙ፣ እኔም ማምረቴን እስከወዲያኛው አቁሜያለሁ፤ የሸጥኳቸውንም መልሼ እሰበስባለሁ” ሲል መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን፣ ጋላክሲ ኖት 7 ለገዙ ደንበኞቹም እሳት ሊፈጥርና አደጋ ሊያደርስባችሁ ስለሚችል አሁኑኑ መጠቀማችሁን አቁሙ በማለት አስጠንቅቋል፡፡
ባለፈው ወር በምርቱ ላይ የባትሪዎች መቃጠልና መፈንዳት አደጋ መከሰቱን በተመለከተ በርካታ ደንበኞች አቤቱታቸውን ማቅረባቸውን ተከትሎ ኩባንያው በአለም ዙሪያ የሸጣቸውን 2.5 ሚሊዮን የጋላክሲ ኖት 7 ስማርት ፎኖች መልሶ መረከቡን ያስታወሰው ቢቢሲ፤ችግሩን ለመፍታት ያደረገው ጥረት ባለመሳካቱ ምርቱን ማቆሙን ገልጧል፡፡ ጋላክሲ ኖት 7 የገዙ ደምበኞች የከፈሉት ገንዘብ እንደሚመለስላቸው አልያም በምትኩ ሌላ የፈለጉት የጋላክሲ ስማርት ፎን ሊቀየርላቸው እንደሚችል ኩባንያው ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሳምሰንግ ጋላክሲ ኖት 7 ማምረት ማቆሙን በይፋ ማስታወቁን ተከትሎ የኩባንያው የአክስዮን ድርሻ 8 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱንና በዚህም 20 ቢሊዮን ዶላር ማጣቱ የተነገረ ሲሆን፣ ኩባንያው በጋላክሲ ኖት 7 ቀውስ 17 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ሊያጣ ይችላል መባሉንም አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ኩባንያው በአመቱ አራተኛ ሩብ አመት 500 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ አገኛለሁ ብሎ አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ትርፉ በ85 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችልና በመጪው 2017 ከሞባይል ገበያ አገኘዋለሁ ብሎ ያቀደው ትርፍም በ22 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ባለሙያዎች ትንበያቸውን ሰጥተዋል፡፡
በጋላክሲ ኖት 7 ስማርት ፎኖች ላይ የታየው ችግር ኩባንያው በአለማቀፉ የስማርት ፎን ገበያ ያለውን ተቀባይነት ክፉኛ እንደሚጎዳውና የደንበኞቹን አመኔታ እንደሚያሳጣው የዘርፉ ተንታኞች መናገራቸውን የጠቆመው ቢቢሲ፣ የደቡብ ኮርያው የፋይናንስ ሚኒስትርም ኩባንያው ምርቱን ማቆሙ በወጪ ንግዱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር መናገራቸውን አስታውቋል፡፡ የአለማችንን የስማርት ፎን ገበያ 98.7 በመቶ ድርሻ የያዙት ሳምሰንግ እና አፕል ኩባንያዎች እንደሆኑ የዘገበው ዘ ስትሪት ድረገጽ በበኩሉ፣ የሳምሰንግ ወቅታዊ ቀውስ ለተፎካካሪው አፕል መልካም ዕድል እንደሚሆን መነገሩን ጠቁሟል፡፡

የኢስቶኒያ መንግስት ላቋቋመው ግዙፍ የሃይል ማመንጫ ተቋም በግብዓትነት የሚውል ቆሻሻ እጥረት በማጋጠሙ ከውጭ አገራት ከፍተኛ መጠን ያለው ቆሻሻ እየገዛ እንደሚገኝ ቢቢሲ ዘገበ፡፡
አገሪቱ ከቆሻሻ ሃይል ለሚያመነጨውና ኢሩ በተባለው አካባቢ ለሚገኘው ተቋም በቂ የሆነ ቆሻሻ በአገር ውስጥ ማግኘት ስላልቻለች፣ ከተለያዩ አገራት ቆሻሻ ለመግዛት መገደዷን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው አመት ብቻ 56 ሺህ ቶን ቆሻሻ ከውጭ አገራት ገዝታ እንዳስገባች ገልጧል፡፡
የሃይል ማመንጫው ባለፈው አመት ብቻ 245 ሺህ ቶን ቆሻሻ በጥሬ እቃነት መጠቀሙንና በአገር ውስጥ በቂ ቆሻሻ ባለመገኘቱ ሳቢያ ስራ ሊያቆም የሚችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ የአገሪቱ መንግስት ቆሻሻን ከውጭ አገራት በመግዛት ስራውን ለማስቀጠል መወሰኑንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
ለኢስቶኒያ መንግስት ቆሻሻ በመሸጥ ላይ ከሚገኙ አገራት መካከል ፊንላንድና አየርላንድ ይገኙበታል ያለው ዘገባው፣ ቆሻሻን ከውጭ አገራት ገዝቶ በማስገባት ሃይል የማመንጨት ኢንቨስትመንቱ አዋጪ እንደሆነ አንድ የአገሪቱ ባለስልጣን መናገራቸውንም አክሎ አስታውቋል፡፡

1 ቢሊዮን ዶላር ያህል ይፈጃል ተብሏል

    የአለማችን ረጅሙ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ የሆነው ቡርጂ ከሊፋ መገኛ የሆነቺው ዱባይ በእርዝማኔው አቻ የማይገኝለት ይሆናል የተባለውን ማማ መገንባት መጀመሯን በሳምንቱ መጀመሪያ አስታውቃለች፡፡
ኢማር ፕሮፐርቲስና ዱባይ ሆልዲንግ የተባሉት ሁለት ኩባንያዎች በጋራ የሚያሰሩት አዲሱ ማማ ግንባታው በአራት አመታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የዘገበው ሮይተርስ፣ማማው ምን ያህል እንደሚረዝም ግልጽ መረጃ አለመውጣቱን ገልጧል፡፡
ይሄም ሆኖ ግን ግንባታው የተጀመረው ማማ፣ 829.8 ሜትር ከሚረዝመው የአለማችን ቁጥር አንድ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ቡርጂ ከሊፋ የሚበልጥ እርዝማኔ እንደሚኖረው መረጃዎች መውጣታቸው እየተነገረ ሲሆን፣ ኢማር ፕሮፐርቲስ ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ በሰጠው መግለጫ ለማማው ግንባታ 1 ቢሊዮን ዶላር ያህል ወጪ እንደሚደረግ ማስታወቁን ሲቢቢ የዜና ወኪል አስታውሷል፡፡
ማማውን ዲዛይን ያደረገው ስፔናዊው አርክቴክት ሳንቲያጎ ካላትራቫ ቫልስ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ የከተማዋን ሙሉ ገጽታ ማሳየት የሚችል መሆኑንም አስታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአለማችን ረጅሙን ማማ ሆኖ የተመዘገበው በቶክዮ የሚገኘው ስካይ ትሪ የተባለው ማማ ሲሆን፣ 634 ሜትር ቁመት እንዳለው ዘገባው ገልጧል፡፡