
Administrator
“ጦርነት መፍትሄ አይኾንም፤ ከትናንት እንማር”
”--ጦርነት መፍትሄ አይኾንም፤ ከትናንት እንማር፤ ችግሮችን በውይይት እንፍታ፤ በሀገራችን ሰሜናዊ ክፍል ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ጦርነት ካደረሰብን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ገና በቅጡ እንኳ ባላገገምንበት በዚህ ወቅት፣ ዳግም ወደ ሌላ መጠነ ሰፊ የእርስ በርስ ግጭት መግባት፣ በሕዝባችን ላይ የሚያደርሰው ማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቡናዊ ጉዳት በእጅጉ የሚያሳስብ ነው። ጦርነት ከፍተኛ መጠን ያለው ሰብኣዊ እልቂትንና ቁሳዊ ውድመትን ከማስከተል በቀር፣ ለችግሮቻችን መፍትኄ እንደማያስገኝ ከቅርብ ጊዜው ተሞከሯችን መማር አለመቻላችን እጅግ አሳዛኝ ነው። በሀገር ውስጥ የሚካሄድ ጦርነት፣ የሀገር አንድነት ፀንቶ የቆመባቸውን የእሴት አምዶች በማፍረስ፣ የሕዝባችንን አንድነት የሚንድ በመኾኑ፣ ሁሉም አካላት ሁኔታውን ከማባባስ ተቆጥበው፣ ወደ ውይይት መምጣት የሚቻልበትን መላ ያፈላልጉ፡፡ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ፤ እጅግ አውዳሚና አክሳሪ ከኾነው ጦርነት፣ የችግር መፍትኄን ከመጠበቅ ይልቅ፣ በአስቸኳይ ወደ ውይይት ይምጡ።--”
(የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሰሞኑን ካወጣው መግለጫ የተወሰደ)
የቁጫ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፤ በመንግሥት አመራሮች በተቀሰቀሰ ግጭት ተፈጸመ ያለውን ጥፋትና ውድመት አወገዘ
አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ከነባሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሥልጣን መረከቡን ተከትሎ፣ ከክልሉ ዋና ከተሞች አመራረጥ ጋር በተያያዘ በቁጫ የምርጫ ክልል በተቀሰቀሰ አመጽና ረብሻ፣ ከፍተኛ ጉዳትና ውድመት መድረሱን የጠቆመው የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ)፤ ይሄንኑ በመንግሥት አመራሮች የተቀሰቀሰና የተመራ ነው ያለውን አመጽና ረብሻ በጽኑ አውግዟል፡፡
ከደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልል አደረጃጀትና ምስረታ ሂደት ጋር ተያይዞ፣ በቁጫ ምርጫ ክልል የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር አስመልክቶ የቁሕዴፓ አመራሮች፣ ትላንት ከሰዓት በኋላ 8 ሰዓት ላይ፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ጽ/ቤት አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በየጊዜው ሀገራችን የሚገጥማትን የፀጥታ ችግር እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ የቁጫ ምርጫ ክልል ሕዝብን እረፍት የሚነሱ ኃይሎች ላይ መንግስት የህግ የበላይነትን እንዲያሰፍን ፓርቲው ጠይቋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት፣ በተለያዩ ዞኖች ሲነሳ ለቆየው የክልል አደረጃጀት መንግስት ምላሽ እየሰጠ መሆኑን የሚገልጸው ፓርቲው፤ በዚህም ነባሩ ደቡብ ክልል ከአራት በላይ በሆኑ አዳዲስ ክልሎች እንዲዋቀር ተደርጓል ይላል፡፡
”ከእነዚህ አራቱ ክልሎች አንዱ የሆነውና በአሁኑ ወቅት በምስረታ ሂደት ላይ የሚገኘው “የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልል”፣ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ በተመዘገበው አብላጫ ውጤት፣ 6ቱ ዞኖች እና 5ቱ ልዩ ወረዳዎች በአንድነት በጋራ ክልል ለመተዳደር የወሰኑት ድምፅ በፌዴሬሽን ም/ቤት በመፅደቁ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት፣ ክልል ም/ቤት፣ ከሐምሌ 28 እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ የም/ቤት ጉባኤ፣ ለአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልል የስልጣን ርክብክብ አድርጓል፡፡” ብሏል፤ ፓርቲው፡፡
ም/ቤቱ፤አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልልን በ6 ክላስተር ከተሞች የአገልግሎት ተቋማትን ሸንሽኖ በተመረጡ ከተሞች የተደለደሉ የመንግሥት ተቋማትን ዝርዝር ይፋ ማድረጉን ያወሱት የፓርቲው አመራሮች፤ ይሄን ተከትሎም፣ ሐምሌ 29 ቀን 2015 ዓ.ም፤ “አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልል አደረጃጀት የጋሞ ሕዝብን ጥቅም የሚነካ በመሆኑ አንቀበልም” በማለት በቁጫ ምርጫ ክልል፣ በቁጫ ወረዳና በቁጫ ሰላምበር ከተማ አስተዳደር፣ በመንግስት አመራሮች የተመራ የረብሻና አመፅ ቅስቀሳ መደረጉን ይገልጻሉ፡፡
የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚና የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል የሆኑት የተከበሩ ረ/ፕሮፌሰር ገነነ ገደቡ፣ በአካባቢው የመንግስት አመራሮች የተቀሰቀሰና የተመራ ነው ባሉት አመፅና ረብሻ ስለደረሱት ጥፋቶች ሲያስረዱ፤”የቁጫ ሕዝብን ከወላይታ ዞን፣ ከጎፋ ዞንና ከደቡብ ኦሞ ዞን ሕዝብ ጋር የሚያገናኘውን የፌደራል አስፓልት መንገድ በመዝጋትና የሕዝብን ነፃ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ ወደ ቁጫ ሰላምበር ከተማ ቅዳሜ ገበያ የመጣው ገበያተኛ እንዲበተን፣ የፀጥታ ሃይሎች፣ በገበያተኞች ላይ ወከባና ድብደባ ፈጽመዋል” ብለዋል፡፡
”በረብሻው ያልተሳተፉ የሰላምበር ከተማ ነዋሪዎች በብሔር እየተለዩ፣ በቁጫ ብሔረሰብ አባላትና በቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አባላትና አመራሮች የንግድ ተቋማትና መኖሪያ ቤቶቻቸው ላይ በተፈፀመው የድንጋይ ውርወራ ውድመት ደርሷል” ያሉት የም/ቤት አባሉ፤ ”በረብሻው ከተሳተፉ ወጣቶች መካከልም የአንዱ ህይወት ማለፉ ተረጋግጧል፤ሌሎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ ሰዎች ላይ በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎችና በረብሻው በተሳተፉ ወጣቶች እንዲሁም በመንግስት አመራሮች ጥቃት ተፈጽሟል” ብለዋል፡፡
በቁጫ ምርጫ ክልል በመንግሥት ሃላፊዎች የተቀሰቀሰውንና የተመራውን የአመጽና ረብሻ እንቅስቃሴ ፓርቲያችን በፅኑ ያወግዛል ያሉት አመራሮቹ፤በአካባቢው ከፍተኛ ግጭትና ውድመት እንዲደርስ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ከቁጫ ሕዝብና ከፓርቲያችን ለክልሉና ለፌዴራል ፀጥታና ተጠሪ ተቋማት በቀረበው ጥቆማና አቤቱታ፣ የፌዴራል ፀጥታ ኃይል ወደ አካባቢው በፍጥነት ደርሶ ሕዝቡን ታድጎታል ብለዋል፡፡
”የተገኘው አንፃራዊ መረጋጋት አስተማማኝ ደረጃ እስኪደርስና አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልል ምስረታ ተካሂዶ በአካባቢው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እስኪሰፍን ድረስ፣ የፌዴራል ፀጥታ ኃይል የሕዝብን ሰላምና ደህንነት እንዲያስጠብቅ በመንግሥት በኩል ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው እንጠይቃለን” ብለዋል፤ አመራሮቹ በመግለጫቸው፡፡
አመፅና ረብሻው በቁጫ ወረዳና በቁጫ ሰላምበር ከተማ አስተዳደር እንዲነሳ የተፈለገው ያለ ምክንያት አይደለም የሚሉት የፓርቲው ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሃብታሙ ኃ/ሚካኤል፤ የቁጫን ህዝብ ማህበራዊ ዕረፍት በመንሳት ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ምስቅልቅል ለመዳረግና አካባቢውን የግጭት ማዕከል በማድረግ፣ የሕዝብን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመቀልበስ ነው ብለዋል፡፡
የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ከሌሎች አካባቢዎች ያመጧቸውን ወጣቶች ሳይቀር በዚህ ግጭትና ረብሻ ውስጥ አሳትፈዋቸዋል ያሉት ም/ፕሬዚዳንቱ፤ ግጭቱን በቁጫ የምርጫ ክልል እንዲነሳ ያደረጉትም በቁጫ ብሔረሰብ እንዲሁም በፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም በማለም ነው ሲሉ ወንጅለዋል፡፡
ሐምሌ 29 ቀን 2015 ዓ.ም፣ በቁጫ ወረዳና በቁጫ ሰላምበር ከተማ፣ በመንግሥት አመራሮችና በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች እንዲሁም በፖሊስ አባላት በተመራው አመፅና ረብሻ፣ የቁጫ ሕዝብን ከወላይታ፣ ከጎፋና ከደቡብ ኦሞ ዞን ሕዝቦች ጋር የሚያገናኘውን የፌዴራል አስፓልት መንገድ ዘግተውት እንደነበር ያስታወሱት የፓርቲው ም/ፕሬዚዳንት፤ በዚህም ሰላም ወዳዱን የቁጫ ሕዝብ ለዘመናት ጥብቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ከፈጠሩ፣ በአንድነትና በፍቅር ከሚኖሩ አጎራባች ሕዝቦች ለመለየትና እነዚህ አካባቢዎች በቁጫ ህዝብ ላይ እንዲነሳሱ በማድረግ፣ ከግጭት ለማትረፍ ታቅዶ የተፈፀመ ነው ብለዋል፡፡
ከክልል በታች ያሉ አደረጃጀቶች፣ ከአዲሱ ክልል ምስረታ በኋላ ምላሽ እንደሚያገኙ በፌዴሬሽን ም/ቤት አቅጣጫ መቀመጡን ያመለከተው ቁሕዴፓ፤ የቁጫ ሕዝብ ብሔር ማንነትና ራሱን በራሱ የማስተዳደር ህገመንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄው ለዘመናት የቆየና ጥያቄው ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ በክልል ደረጃ ምላሽ ማግኘት የሚገባው ጊዜ በማለፉ በይግባኝ ለፌደሬሽን ም/ቤት ቀርቦ ለምላሽ የተለያዩ ጥናቶች ሲደረጉ የቆየበት ከመሆኑ አንጻር፣ ከክልል አደረጃጀት ጥያቄ አስቀድሞ ምላሽ ሊሰጠው ይገባ ነበር ብሏል፤ ፓርቲው፡፡
በአጠቃላይ በቁጫ ሕዝብ ላይ ተጭነው ለቆዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የፌዴሬሽን ም/ቤት በራሱ ሥልጣንናና ተግባር ስር የነበረውን ኃላፊነት፣ በህግ አግባብም በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መመለስ አለመቻሉ በፈጠረው አጋጣሚ የቁጫ ሕዝብ ህገመንግስታዊ መብቶች ተጥሰው፣ በሌላው ወገን ፈላጭ ቆራጭነት፣ ህዝብን ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መጎሳቆል ከመዳረጉም በላይ፣ በራሱ መልክዓ ምድር ሠርቶ፣ ነግዶ፣ አርሶና አርብቶ እንዳይኖር ለተለያዩ ችግሮችና መከራዎች አጋልጦታል፤ ብሏል በመግለጫው፡፡
ፓርቲው በመግለጫው ለፌዴሬሽን ም/ቤት ባስተላለፈው መልዕክት፤የቁጫ ብሔረሰብ ማንነትና የራስ አስተዳደር የዞን መዋቅር ህገመንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች፣ በህገመንግስቱ በተቀመጠው አግባብ፣ መሰረት ፈጣን ምላሽ እንዲሰጠው አበክሮ ጠይቋል፡፡
በሌላ በኩል፤የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልል ምስረታን ተከትሎ፣ በቁጫ የምርጫ ክልል በመንግሥት አመራሮች በተነሳው ረብሻና አመፅ፣ ለሰው ህይወት ጥፋትና የንብረት ውድመት ተጠያቂ የሆኑና የቁጫ ምርጫ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር እንዳይገናኙ በማድረግ ጥቃት ፈጽመውባቸዋል የተባሉ አካላት ተጣርተው ለህግ እንዲቀርቡ ቁሕዴፓ በመግለጫው ጠይቋል፡፡
ፓርቲው አክሎም፤ የመንግሥት አካላት በመሩት ሁከት፣ የሰው ሕይወት ለጠፋበት የሟች ቤተሰብና በብጥብጡ የአካልና የንብረት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች፣ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ፣ ተገቢው ካሣ እንዲከፈልና የወንጀሉ ፈፃሚዎችም በቁጥጥር ሥር ውለው ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቋል፡፡
የወቅቱ ጥቅስ
“--በአሉታዊ-መነሻ ሳይሆን በአዎንታዊ-መነሻ ላይ ቆሜና የሀገሪቱን መዳን አስቀድሜ፣ እንዴት ልጓዝ? ብሎ የማሰብ ሆደ-ሰፊነት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ የተመቻቸ ሁኔታ አይፈጠርልኝም ብሎ የተስፋ-ቆራጭ መንገድ ከማሰብ የግድ መንገዱን መፍጠር አለብኝ ብሎ ቆርጦ መነሳት፤ ህዝብን ወደ በለጠ አዘቅት ከመምራት፣ አገርንም ይበልጥ ወደ ተወሳሰበ አደጋ ከመግፋት የሚገታ ብስለት ይሆናል፡፡--”
“ብላ ያለው ተጋግሮ ይጠብቀዋል ተሸከም ያለው ታስሮ ይጠብቀዋል”
በአንድ መንደር የሚኖር አንድ ድመት ያለው ሰው አለ፡፡ ድመቱ በመንደሩ እየተዘዋወረ በርካታ የድመት ወዳጆችና ውሽሞች አፈራ፡፡ አንድ ቀን አንዷ ድመት ዘንድ፣ ሌላ ቀን ሌላ ድመት ዘንድ እየተዘዋወረ ሲወሰልት ከረመ፡፡ በውጤቱም የመንደሩ ድመቶች ሁሉ አረገዙ፡፡ አያሌ ተፈለፈሉ። የሰፈሩ ሰው ሁሉ በድመቶች ብዛት ተጨናነቀ፤ መረረውና እድሩ ተሰበሰበ፡፡ ይሄንኑ ምሬቱን ተወያየ። በመካያው የአገር ሽማግሌዎች ተመርጠው ወደ ባለድመቱ ሄዱና እንዲህ አሉ፡-
“ጌታዬ፣ መቼም አንተ አስበህ ለተንኮል ያደረግኸው አይመስለንም፡፡ ሆኖም ችግሩ መፈጠሩ አልቀረም”
ሰውዬውም እንዲህ ለምድር ለሰማይ የከበዱ ሰዎች ላይ ምን ችግር ፈጠርኩባቸው በሚል ተሽቆጥቁጦ፤
“ምን ጥፋት አገኛችሁብኝ ጌቶቼ?” ሲል ጠየቀ፡፡
የሽማግሌዎቹ ተወካይም፡-
“አየህ ያንተ ድመት በሰፈሩ አንዲትም የቀረችው ድመት የለች፡፡ የድመት ማቲ ተፈለፈለ ተፈለፈለና በዚህ ምክንያት መንደሩ ሁሉ በድመት ተወረረ፡፡ አሁን ድመትህን ታስርልን ዘንድ ልንጠይቅህ ነው የመጣነው፡፡”
ሰውዬው፡-
“ታዲያ ምን ችግር አለ? እኔ እንደሚሆን አደርጋለሁዋ!” አለ፡፡ አመስግነውት ይለያያሉ፡፡
ባለድመቱ ሲያወጣ ሲያወርድ ይቆይና በመጨረሻ ውሳኔ ላይ ይደርሳል፡፡
ከጊዜ በኋላ በመንደሩ አንድ አደገኛ የእንስሳት ወረርሽኝ ይገባል፡፡ የሰፈሩ ትናንሽ ድመቶች በሙሉ ይረፈረፋሉ፡፡
ጭንቅ መጣ- ምክንያቱም አይጥ ደግሞ በተራው መንደሩን ወረረው፡፡ ሳሎን ከጓዳ የአይጥ መናኸሪያ ሆነ፡፡ የአገሩ ሽማግሌዎች እንደገና ወደ ባለ ድመቱ ይመጣሉ፡፡
ባለድመቱ፡- “አሁን ደግሞ ምን ተፈጠረ አባቶቼ?”
የሽማግሌዎቹ ተወካይም፡- “አንድ ችግር ገጠመን ወዳጄ፡፡ ያ የአንተ ድመት ከቤቱ መውጣት ካቆመ በኋላ አይጥ አላስቀምጥ አለን፡፡ አንድ ጊዜ ደግመህ ብትቸገርልንና ድመቱን ብትለቀው?”
ባለ ድመቱ፡- “አባቶቼ ያንንማ ለማድረግ ከእንግዲህ አልችልም፡፡”
የሽማግሌዎቹ ተወካይ፡- “ለምን ወዳጄ?”
ባለ ድመቱ፡- “ለአንዴም ለሁሌም እንዳያስቸግራችሁ ብዬ አኮላሸሁት!”
ሁሉም ጭንቅላታቸውን ያዙ፡፡ አዝነው መንገዳቸውን ሲቀጥሉ፣ ባለድመቱ ተጣራና አንድ ተስፋ ሰጣቸው፡-
“ጌቶቼ ሆኖም ድመቴ ስራ አልፈታም፡፡ ሊያግዛችሁ ይችላል”
ቆም ብለው፡- “በምን መንገድ ይረዳናል?”
ባለ ድመቱ፡- “የአማካሪነት አገልግሎት ስራ ጀምሯል- Consultant ሆኗል!!!”
***
የአማካሪው ዓይነት በበዛ ቁጥር ማ በጤና፣ ማ ተስፋ በቆረጠና በተኮላሸ አቋም እንደሚያማክር ለመለየት ያስቸግራል፡፡ አማካሪው ከግራ ከቀኝ መሯሯጡ ሲበዛ ማ “የመጣው ይምጣ!” በሚል እንደሚያቅድ፣ ማ በአቦ-ሰጡኝ እንደሚመራ፣ ማ አለቃውን የሚያስደስት መፈክር ማስገር እንደሚሻ፣ ማ እንደበቀቀን ከላይ የተነገረውን ብቻ በመደጋገም አዋቂ ለመምሰል እንደሚፍረመረም አበጥሮ ለማየት እጅግ ያዳግታል፡፡ በመንደር በሰፈሩ አንድ ሽለ-ሙቅ አጥቂ (fertile) ድመት ብቻ መኖሩንና የተፈለፈሉ ድመቶች እንደ አሸን መፍላት አሳሳቢ ሁኔታ መፍጠሩ፤ የትኩረቱን አቅጣጫ ሁሉ ከአይጦች መምጣት አንፃር እንዳይታይ አደረገው፡፡ ሁኔታው የአገር የቀዬውን አይን ማወሩ የሚገርመውን ያህል፣ የባለድመቱ ድመቱን የማኮላሸት ፈጣን እርምጃ ይብስ አስደንጋጭነቱን ያጎላዋል፡፡ ያ ሳይበቃ የመንደሩ ሰዎች፤ አይጦች መፈልፈል ሲጀምሩ፣ “እኛ እንዴት አይጦቹን ልናስወግድ እንችላለን?” የሚለውን ጥያቄ አላነሱም፡፡ የተለመደውን የድመቱን ጌታ እንደ መፍትሄ በማሰብ ወደሱዉ ያመሩት ሽማግሌዎች ብቸኛው መልስ አለመኖሩን ሲረዱ፣ የደረሰባቸው የሀሞት መፍሰስም፤ የማሳቁን ያህል፣ የድመቱ የአማካሪነት አገልግሎት ደግሞ ከተፍ አለ፡፡ “ባላጋባ ማጫፈር ያቅተኛል ወይ?” ዓይነት ተሳትፎ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የሀገራችንን የችግር መፍትሔ አሰጣጥ፣ የዕቅድ አወጣጥ፣ ድቀት አፈረጃጀትና አፈታት (Crisis management) ምን እንደሚመስል፣ ሌሎችንም ሁናቴዎች የሚያመላክት ሁኔታ ነው፡፡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ምስቅልቅል ሂደቶች እንደተለመደው በሹም-ሽር (appoint-demote) ፈጣን እርምጃ እንዳንገላገለው “ወተት ያጠጧት ውሻ፣ ቅቤ ሳትቀቡኝ አልሄድም ትላለች” እንዲሉ፤ የውስጥ አዋቂነትና ጠላት የማብዛት ስጋት መንገዶችን ሁሉ እያቆላለፉ መራመጃ ያሳጡ ይመስላሉ፡፡ ምንም እንኳ የምሩ ሰዓት አይቀሬ ቢሆንም፣ ጊዜያዊ መረጋጋትን (temporary stability) የሚሰጡ ሁኔታዎችን በማሰላሰል “አንገብጋቢ አይደለም” ብሎ እንደማለፍ ያለ አደገኛ መፍትሄ የለም፡፡ ዛሬ የሚፈጠርን ችግር ነገ እናስብበታለን ብለን አንዘልቀውም፡፡ ጉድጓዱን ሳይደፍኑ አይጢቱን የማሳደድ ዓይነት ብልሀት ሙስናን እንደማያስወግድ ሁሉ፤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ-ጉዳዮች ውስጥ ያሉ ጉድጓዶችን በቀና ልቡና ሳይደፍኑ መረጋጋት፣ መቻቻል፣ በራስ መተማመን በዋዛ የሚገኙ ነገሮች አይሆኑም፡፡ ከሁሉም ቀዳሚው አርቆ ማስተዋል ነው፡፡ የቤት ስራን ለመስራት የምንተጋውን ያህል፣ ኃላፊነትን ለመወጣት ሌት-ተቀን እንፍጨረጨራለን የምንለውን ያህል፣ አርቆ አስተዋይነትን በተገቢው መጠን መያዝ ይኖርብናል፡፡ ከዚህ ወይም ከዚያ እርምጃ ሀገር ምን ትጠቀማለች ማለትን ግንዛቤ ውስጥ ልናስገባ ያሻናል፡፡ ከምሁራንና ከረዥም ዕድሜ የልምድ ባለቤቶች የሚገኘውን ዕውቀት እንዴት በአግባቡ ለሀገር በሚበጅ ፈርጁ መጠቀም ይገባል ብሎ በብልህ ልቡና ማሰብ ይገባል፡፡
የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የመፏከቻና የመሻኮቻ መድረክ መፍጠር ሳይሆን፣ ያልተሄደበትን መንገድ እንዴት እናግኘው የማለትን ብልሀት መሻት ያስፈልጋል፡፡ በአሉታዊ-መነሻ ሳይሆን በአዎንታዊ-መነሻ ላይ ቆሜና የሀገሪቱን መዳን አስቀድሜ፣ እንዴት ልጓዝ? ብሎ የማሰብ ሆደ-ሰፊነት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ የተመቻቸ ሁኔታ አይፈጠርልኝም ብሎ የተስፋ-ቆራጭ መንገድ ከማሰብ የግድ መንገዱን መፍጠር አለብኝ ብሎ ቆርጦ መነሳት፤ ህዝብን ወደ በለጠ አዘቅት ከመምራት፣ አገርንም ይበልጥ ወደ ተወሳሰበ አደጋ ከመግፋት የሚገታ ብስለት ይሆናል፡፡ “የሞኝ ጀርባ ሲመታ የአስተዋይ ጀርባ ያመዋል” ይሏልና፤ ከህመማችን ተነስተን፤ የአተያያችን አቅጣጫ ቀናና አዎንታዊ መሆን እንደሚገባው አበክሮ ማስተዋል ነው፡፡
የሀገራችንን ሁኔታ “አንዴ ካመጣው ምን ይደረግ” በሚል ህሊና ለማለፍ አዳጋች ነው፡፡
“አይጣል ይሏል እንጂ ከጣለ ምን ይሏል
ከመቀነት ወጥቶ ብር ይኮበልላል”
ብለን ያላሳብ ለመተኛት የሚቻል ቢሆን መታደል ነበር፡፡ ሆኖም በተጨባጭ አካልንም አዕምሮንም የሚኮሰኩስ ሳንካ በየቢሮው፣ በየበሩ፣ በየማጀቱ ይጎረብጣልና ዐይንን መግለጥ ወይም ማፍጠጥ ብቸኛ አማራጭ ይሆንብናል፡፡ ለማንኛውም ተኝቶ ማደር አለመቻሉን ነው የምናጤነው፡፡
ስለ ተግባራዊ ዲሞክራሲያዊነት፣ ስለ እውነተኛ ፍትሀዊነት፣ ስለ ልባዊ መልካም አስተዳደርና ዕብለት-አልባ ስለሆነ የሀገር ዕድገት የምናወራ ከሆነ፤
“ብላ ያለው ተጋግሮ ይጠብቀዋል
ተሸከም ያለው ታስሮ ይጠብቀዋል”
ለሚል ዓይነት አሰራርና ተጨባጩን ሂደት እድል ለሚያስመስል ወገናዊ አካሄድ፣ ከቶም ቦታ ልንሰጠው አይገባም፡፡
ፈሳሽ ስዕል
ወንዜም ሞላ ቦይ
ምንጬም አትጉደይ
ከስሬ ስትፈልቂ
ራሴን እንዳይ
ምስሌ ይፍሰስብሽ
ፀድተሸ ብታጠሪኝ
ወንዜ ፍሰሽልኝ፡፡
ፍሰሽልኝ ወንዜ፤
ተቀላቅሎ ይኑር
ወዝሽና ወዜ፡፡
ጥያቄ ነን
ጥያቄ ነን
ለራሳችን
መልስ የሌለን፡፡
በሴኮንዶች ተጀምረን
በአመታት የምናድግ
በግዜ ጎርፍ
የምንጓዝ የምንከንፍ
መነሻ እንጂ
መድረሻ የለሽ ፍጡራን
ሄደን ሄደን…ሄደን
ጀማሪዎች የምንሆን
አውቀን አውቀን
መሃይማን፤
አድገን አድገን-
ህፃናት ነን!
ጥያቄ ነን!
የዓለም ሻምፒዮናውና ሦስቱ አሰልጣኞች
19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሳምንት በኋላ ቡዳፔስት ላይ እንደሚካሄድ ይታወቃ230ል። በሐንጋሪ የዓለም ሻምፒዮናው አዘጋጅ ኮሚቴ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከአትሌቶች ባሻገር ለአሰልጣኞችም የሜዳልያ ሽልማቶች ተዘጋጅተዋል። “በምንሸልማቸው ሜዳሊያዎች ስፖርትን፣ ጀግንነትንና ብሄራዊ ማንነትን ማስተሳሰር ግድ ይለናል። ስለዚህም በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አሰልጣኞች በሽልማት መድረክ ላይ ሜዳሊያዎችን ይቀበላሉ ብለዋል።" በቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮናው አዘጋጅ ኮሚቴ ዋና ስራ አስፈፃሚ ባላዝ ኔሜት።
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የተሳታፊ አትሌቶችን ዝርዝር ያስታወቀ ሲሆን፤ በሻምፒዮናው ከ202 አገራት የተውጣጡ ከ2100 በላይ አትሌቶች መመዝገባቸውን አረጋግጧል። ለዓለም ሻምፒዮናው ከ2 ወራት በላይ ዝግጅት ያደረገው የኢትዮጵያ ቡድን በሁለቱም ፆታዎች ቋሚ ተሰላፊዎችና ተጠባባቂዎችን ጨምሮ 48 አትሌቶች ማስመዝገቡን ለማወቅ ተችሏል። የአትሌቲክስ ቡድኑ ዝግጅት ፌዴረሽኑ ከክለቦች፤ ከአሰልጣኞች፤ ከማናጀሮችና ከአትሌቶች ተቀራርቦ በመሥራቱ በቡድን መንፈሱ የተጠናከረ ሆኗል። የቡድኑ ዝግጅት በስፖርት መሰረተ ልማቶች አለመሟላት አሳሳቢ ፈተና እንደገጠመው ግን መታዘብ ይችላል። ስፖርት አድማስ ከቡድኑ አሰልጣኞች ጋር ያደረጋቸው ቃለምልልሶች ከቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮና በኋላ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በቀጣይ በ2024 ለሚካሄደው የፓሪስ ኦሎምፒክ ብዙ መስራት ይጠበቃል፡፡
የአትሌቶች ማናጀርና አሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ ከሩጫ ዘመኑ በኋላ ወደ አሰልጣኝነት ሙያው በመግባት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስኬታማ ከሆኑ ባለሙያዎች አንዱ ነው። በአሰልጣኝነት ከ9 ዓመታት በላይ የሰራ ሲሆን ከግሎባል ስፖርት ኮምኒኬሽንና ከNN የሯጮች ቡድን ጋር በዓለም ሻምፒዮናው ተሳታፊ ይሆናል። ሁለቱ የአትሌቲክስ ተቋማት በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ 70 አትሌቶች (45 ሴቶች ናቸው) ጋር በመስራት ከፍተኛ እውቅናና ስኬት እያገኙ ናቸው። አሰልጣኝ ተሰማ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው ቡዳፔስት ላይ በግሎባል አትሌቲክስ ስር ከ45 በላይ አትሌቶች ተሳታፊ ይሆናሉ።
"ካለፉት ሻምፒዮናዎች በተለየ መልኩ ማናጀሮቹና አሰልጣኞቹ በአንድ ላይ መስራታቸው የቡድኑን የአንድነት መንፈስ አጠናክሮታል"
በኢትዮጵያ የማራቶን ቡድን ዝግጅት ዙርያ አሰልጣኞችና ማናጀሮች በልዩ ሁኔታ ተግባብተው ሲሰሩ ቆይተዋል። ለሻምፒዮናው የተደረገውን አጠቃላይ ዝግጅት አሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ ሲገመግም “የማራቶን ቡድኑን አጠቃላይ ዝግጅት በሴትም በወንድም የጀመርነው በ30 ኪ.ሜ የረጅም ርቀት ሩጫ ነው። አትሌቶቹ ከተለያዩ አሰልጣኞችና ማናጀሮች የመጡ ቢሆንም ለአገር አብረው መስራት እንዳለባቸው በመወሰን ነው ስራ የጀመርነው። የማራቶን አትሌቶቹ ከአራት የተለያዩ ማናጀሮች የተገኙ ናቸው። ከግሎባል አትሌቲክስ፣ ከጃኒ፣ ከገመዶ ከሁሴን፤ ከሃጂና ከጌታመሳይ የመጡ ቢሆንም አንድ ላይ ተቀላቅለው ሲሰሩ ቆይተዋል። የልምምዱን ሂደት ዲዛይን ያደረግነው ከአራት በላይ አሰልጣኞች ቁጭ ብለን ባደረግነው ምክክር ነው። የማራቶን ቡድኑ አብሮ በመስራቱ በአጠቃላይ ዝግጅቱ ጥሩ ነገር እያየን ነው። በሻምፒዮኖቹ ታምራት ቶላና በጎይተቶም ገብረስላሴ መሪነት ጥሩ ውጤት ለማምጣት እየሰራ እንገኛለን። ካለፉት ሻምፒዮናዎች በተለየ መልኩ ማናጀሮቹና አሰልጣኞቹ በአንድ ላይ መስራታቸው የቡድኑን የአንድነት መንፈስ አጠናክሮታል” ብሏል አሰልጣኝ ተሰማ እንደገለፀው ለማራቶን ቡድኑ የአንድነት መንፈስ መጠናከር የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት ጥያቄ ማቅረባቸው አስተዋፅኦ አድርጓል። ፌዴሬሽኑ ለቡድኑ ዝግጅት ሃሳብ ካቀረበ በኋላ አትሌቶች፤ ማናጀሮችና አሰልጣኞች ፈቃደኞች ነበሩ። ባለፈው የዓለም ሻምፒዮና በማራቶን የተመዘገበው የላቀ ውጤትም ለትብብሩ መነሻቸው ሆኗል። “ማራቶን የቡድኑ ስራ ነው። አብረህ ልምምድ ስትሰራ ረጅም ርቀት አብረህ ነው የምትጓዘው። ዞሮ ዞሮ አንድ ሰው ነው የሚያሸንፈው ግን በውድድሩ ውሃ መቀባበል አለ፣ አይዞሽ፣ አይዞህ መባባል አለ። ስለዚህ አትሌቶችን በዚህ አሰራር ላይ እንድንዘጋጅ ስንጠይቅ በጥሩ መንፈስ ተቀበሉት። ሁሉም አትሌቶች የአምናውን ውጤት ዘንድሮም ለማስመዝገብ ፍላጎት አላቸው።” ብሏል አሰልጣኙ ።
“ተሰላፊ አትሌቶች በይፋ መግለፃቸው በቡድኑ ላይ የተሰጠውን መተማመን ያመለክታል።”
የኬንያ የማራቶን ቡድን ቋሚ ተሰላፊዎች ከ2 ወራት በፊት ነው የታወቁት። በኢትዮጵያ በኩል ግን በቋሚ ተሰላፊዎችን ለመለየት አልተቻለም። ይህ ሁኔታ በቡድኑ አቋም ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ የለም ወይ? ለሚለው ጥያቄ አሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ ምላሽ ሲሰጥ “የማራቶን ቡድኑን ለመወሰን የአትሌቶች ወቅታዊ ብቃት ወሳኝ ይሆናል። እንደ አሰልጣኝ ብጠየቅ፤ በሻምፒዮናው እነ እገሌ ቢመረጡ ጥሩ ብቃት ያሳያሉ ብዬ ለመግለፅ አልቸገርም። አጠቃላይ ቡድኑን መጨረሻ ላይ የሚወስነው የቴክኒክ ኮሚቴና የፌዴሬሽን አመራር ነው።ሻምፒዮናው አንድ ሳምንት እስኪቀረው እነ እገሌ ይሰለፋሉ የሚል ነገር በኦፊሴላዊ መንገድ አልተገለጸም። በእኔ አስተያየት ይህ አትሌቶቹ ላይ የተወሰነ ጫና ሊፈጥር ይችላል። እኔ እመረጣለሁ እንትና ይመረጣል የሚለው ነገር ልምምዱን ወደ ፉክክር ይከተዋል። በጠቃላይ ቡድኑ በግልጽ አለመታወቁ የሚፈጥረው ተፅእኖ ሊኖር ይችላል። ከቤጂንግ ኦሎምፒክ ጀምሮ ያለኝ ልምድ የኢትዮጵያ ቡድን ውድድሩ አንድና ሁለት ቀን ሲቀረው የሚገለፅበት አሰራር ልክ አይመስለኝም። በሻምፒዮናነታቸው በቀጥታ የሚሳተፉትን አትሌቶችን ጨምሮ በሁለቱም ፆታዎች የሚሰለፉትን 8 ተሰላፊ አትሌቶች በይፋ መግለፃቸው በቡድኑ ላይ የተሰጠውን መተማመን ያመለክታል። በአትሌቶች የሚፈጥረውንም ጭንቀት ይቀንሰዋል።” በማለት ተናግሯል።
“ለመሸለምም ሆነ ለመሸለም በመጀመሪያ ሜዳው ሊኖረን ይገባል፡፡”
በዓለም ሻምፒዮናው ለኢትዮጵያ ቡድን ከተጋረጡ ስጋቶች አንዱ የቡዳፔስት ሞቃታማ አየር ንብረት ነው። አሰልጣኝ ተሰማ በዚህ ሁኔታ ላይ ሲናገር “የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች ብዙውን ጊዜ በነሐሴ ወር ላይ ነው የሚደረጉት። እኛ አገር የክረምት ወቅት ነው። በሌላው ዓለም በተለይ በአውሮፓ ደግሞ በጋ ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን የአየር ሁኔታ እንደተገመተው አይሆንም። በማራቶን በሁለቱም ፆታዎች ውድድሮች በማለዳ መደረጋቸው ይታወቃል። በዚያ ተንተርሰን ዝግጅታችን ላይ በተቻለን መልኩ የአየር ሁኔታወን የምንቋቋምበት ልምምድ እየሰራን ቆይተናል። አሁን ባለኝ መረጃ ቡዳፔስት ላይ የሙቀት ሁኔታ ከ29- 300C ይደርሳል እየተባለ ነው። አትሌቶችን ከሰዓት ላይ እያሰራን ቆይተናል። አምናም ኦሬጎን ላይ ሙቀቱ በጣም ያስቸግራል ሲባል ነበር። አጋጣሚ ሆኖ ግን ተፈጥሮን ማንም መቆጣጠር ስለማይችል ጥሩ አየር ሆኖ አስደናቂ ውጤት ተመዝግቧል። በአጠቃላይ የአየሩ ሁኔታ ለሁሉም አገሮች ነው፤ ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም። በውድድር ቦታ ላይ የሚገጥመንን ችግር በዝግጅት ማስተካከል አለብን በሚል ሰርተናል።” ብሏል።
በዘንድሮው ዓለም ሻምፒዮና ለአትሌቶች የሚሰጠው የሜዳልያ ሽልማት ለውጤታማ አሰልጣኞቻቸውም እንደሚበረከት እየተገለጸ ሲሆን የዓለም አትሌቲክስና ኦሎምፒክ የሚያስከብር ትልቁ ታሪካዊ ውሳኔ እንደሆነ አሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ ገልጿል። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ የማይረሳው ወርቃማ ታሪክ ያስመዘገቡ እንደሆነ ወልደመስቀል ኮስትሬ አይነት አሰልጣኖች ለታላላቆቹ አትሌቶች ትልቁን ስራ ከጀርባ ሆነው በመስራት የአንበሳውን ድርሻ እንደወሰዱ ያስታወሰው አሰልጣኙ ወደፊትም ውጤታማ አሰልጣኞችን በዚህ አይነት ማበረታቻ መፍጠር እንደሚቻል እምነት አለኝ ሲል አስረድቷል።በአለም አትሌቲክስ ላይ ስታየው አሰልጣኞች ይለፋሉ፣ ይደክማሉ ግን ዋጋውን የሚወስደው አትሌቱ ነው፡፡ ለአሰ“ልጣኞቹ የተሰጠ እውቅና ቢሰጣቸውም በቂ ግን አይደለም፡፡ የአለም አትሌቲክስ አሰልጣኞች ወደ ሜዳልያ ሽልማት ለማምጣት መስራቱ ትልቅ ምስጋና የሚቸረው ነው፡፡ አሰልጣኞች የተሻለ ስራ ለመስራት የሚነሳሱበት ይሆ” ናል፡፡
"ኢትዮጵያ በአለም አደባባይ ከፍ ብላ የምትታይበት ስፖርት ቀይ መብራት አብርቷል፡
፡ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ መንግስትም፣ ህዝብም፣ ባለሃብትም ማተኮር ያለበት በአትሌቲክስ ማዘውተሪያ ስፍራዎች ልማት ላይ ነው፡፡"
ከሽልማት ባሻገር ግን በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዮ ትኩረት መሠጠት የሚያስፈልገው በስፖርት መሠረተልማት ዙርያ መሆኑን አሰልጣኝ ተሰማ በጥብቅ ነው የሚያሳስበው። “ኢትዮጵያ በአለም አደባባይ ከፍ ብላ የምትታይበት ስፖርት ቀይ መብራት አብርቷል፡፡”ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ መንግስትም፣ ህዝብም፣ ባለሃብትም ማተኮር ያለበት በአትሌቲክስ ማዘውተሪያ ስፍራዎች ልማት ላይ ነው፡፡” በሚልም ተናግሯል።የማዘውተሪያ ስፍራዎች በጣም ያስፈልጉናል። አለበለዚያ የኢትዮጵያ አትሌቲክስን አደጋ ላይ ነው ያለው። በቂ “ማዘውተሪያ የለም፤ ትራክ የለም። የማራቶን ቡድን የሚሰራበት 20 ኪ.ሜ - 30 ኪ.ሜ የተዘጋጀ ቦታ የለንም። እስዛሬ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሚስተዳድረው አንድ ማዘውተሪያ ቦታ አለመኖሩ ያሳዝናል። ይህ መሰረተ ልማት ባልተሟላበት ሁኔታ ላይ ለአትሌቶችም ሆነ ለአሰልጣኞች የሚሰጠው የገንዘብ ሽልማትና ስጦታ ልጓጓለት አልችልም። ባለመሰጠቱም አልደነቅም። ምክንያቱም በመጀመሪያ የስፖርት መሰረተ ልማቱ አስፈላጊ ነው። ለመሸለምም ሆነ ለመሸለም በመጀመሪያ ሜዳው ሊኖረን ይገባል፡፡ አትሌቲክሱ ላይ ህፃናቶችና ታዳጊዎች የሚለማመዱበት የሚሰሩበት የስፖርት መሰረት ልማት ላይ ባለሃብቱም መንግስትም ተረባርቦ መስራት አለበት፡፡ ይህ ችግር ካልተቀረፈ በምንሳተፋቸው ውድድሮቹ ሚኒማ የማናሟላባቸው ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። የሜዳ እጥረት መኖሩ በአጭርና በመካከለኛ ርቀት አትሌቶች እንዳይኖሩ አድርጓል፡፡ በተለያዩ የአለም ክፍሎች ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የሚውለበለበው በአትሌቲክስ ነው፡፡ ስለዚህ ቅድሚያ ትኩረት መስጠት የሚገባን ለስፖርት መሰረተ ልማት ነው፡፡
የኢትዮ ኤሌክትሪክ አትሌቲክስ 10 አትሌቶችና ዋና አሠልጣኝ ቶሌራ ዲንቃ
የኢትዮ ኤሌክትሪክ የስፖርት ክለብ በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለሚሳተፉ 10 አትሌቶችና 1 አሰልጣኝ አሸኛኘት አድርጓል። የስፖርት ክለቡ ለዓለም ሻምፒዮናው ካስመረጣቸው አትሌቶች መካከል በማራቶን የዓለም ሻምፒዮንና የሻምፒዮናው ሪከርድ የያዘችው ጎይተቶም ገብረስላሴና በ10 ኪሜ የጎዳና ሩጫ የዓለም ሪከርድ ባለቤት የሆነችው ያለምዘርፍ የኋላው ይገኙበታል። ሌሎቹ አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ከፍተኛ ልምድ ያላቸው በሪሁ አረጋዊ፣ ሀጎስ ገብረሂወት፣ገብረፃዲቅ አብራሃ፣ ታደሰ ወርቁ፣ ፀጋዬ ጌታቸው፣ ያለምዘርፍ ሀብታም አለሙ፣ ሂሩት መሸሻና ሚዛን አለም ሲሆኑ፤ በአሰልጣኝነት ደግሞ ቶሌራ ዲንቃ ናቸው።የኢትዮ ኤሌክትሪክ የስፖርት ክለብ ባለፈው ሻምፒዮና በጎይተቶም አማካኝነት በማራቶን የወርቅ ሜዳልያ ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው። የክለቡ የስራ አመራር ቦርድ ቡዳፔስት ላይ አትሌቶቹ ከወርቅም ባሻገር ተጨማሪ የብርና ነሐስ ሜዳሊያዎችን ለኢትዮጵያ እንደሚያመጡ ተስፋ አድርጓል። የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ ውጤታማ አትሌቶችን በማሰባሰብ በሰጠው ትኩረትና ለኢትዮጵያ ቡድን ባደረገው ከፍተኛ አስተዋጽኦ በታዋቂ አሰልጣኞችና የፌዴሬሽን አመራሮች ሊመሠገን በቅቷል።
7 የዓለም ሻምፒዮናዎች፤ 3 ኦሎምፒኮች
አሰልጣኝ ቶሌራ ዲንቃ በአሰልጣኝነት ሙያ ውስጥ ከ14 ዓመታት በላይ ቆይቷል። የኦሮሚያ ፖሊስ ክለብ ሲመሰረት ከነበሩ አትሌቶች አንዱ ሲሆን ለ11 ዓመታት በኦሮሚያ ፖሊስ አትሌትነት አገልግሏል። ከዚያ በኋላ በኦሮሚያ ፖሊስ የስፖርት ክፍል ኃላፊነትና አሰልጣኝነት ሲሰራም ነበር። ከታዋቂ የኢትዮጵያ አትሌቶች መካከል በማራቶን የዓለም ሻምፒዮን የሆኑትን እነ ታምራት ቶላና ማሬ ዲባባን ከጅምሩ መልምሎ በማውጣት ለውጤት ያበቃ ነው። በተለይ የማራቶን ሻምፒዮኑን ታሞራ ቶላ ከቢሾፍቱ ክለብ አንስቶ ለ7 ዓመታት አሰልጥኖ ታላቅ ደረጃ አድርሶታል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደረጃ ደግሞ ከእነጥሩነሽ ዲባባ ጀምሮ አሁን እስካሉት ታላላቅ አትሌቶችን ከረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሽቦ ጋር በረዳት አሰልጣኝነት ስኬታማ ለማድረግ የቻለ ነው።አሰልጣኝ ቶሌራ ዲንቃ በዓለም ሻምፒዮና በኦሎምፒክ ከፍተኛ ልምድ ካላቸው አሰልጣኞች አንዱ ነው። ከ7 በላይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎችን፣ 3 የኦሎምፒክ መድረኮችን ተሳትፏል።አሰልጣኝ ቶሌራ ጠንካራ አትሌቶችን ከስር ጀምሮ መልምሎ በማውጣትና ለውጤት በማብቃት የተሳካለት ነው። ይህን አስመልክቶ ለስፖርት አድማስ ሲያብራራ “ከብዙ የኢትዮጵያ አትሌቶች ጋር ተሰሚነት እና ቀረቤታ አለኝ። ተስማምቼ፤ ተግባብቼ ነው የምንሰራው። አትሌቶቹን የምመለምልበት የራሴ መንገድ አለኝ። በውድድሮቹ ላይ ደረጃ ማግኘት ባይችሉም ጠንካራ ውጤት ያላቸውን፤ ከትምህርት ቤት ጀምሮ ጥሩ አቅም ያላቸውን ሯጮች በመመልመል ነው የምሠራው። ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አትሌቲክስ ክለብ በፊት በኦሮሚያ ፖሊስ የሚገኙ በርካታ አትሌቶችን መልምዬ ያወጣሁበት ልምድ ምሳሌ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል። እነ ታምራት ቶላ፣ ሹራ ደምሴ፣ ማሬ ዲባባ፣ አዱኛ ታከለ፣ ብርሃኑ በቀለና ሲሳይ ለማ የእኔ ምልምሎች ናቸው። በኢትዮ ኤሌክትሪክ ክለብ ለዓለም ሻምፒዮናው ከተመረጡ 10 አትሌቶች ከ800 ሜትር ሯጯ ሐብታም አለሙ በቀር ሁሉም አትሌቶች በእኔ የተመለመሉና የሚሰለጥኑ ናቸው። ታዳጊዎችን ከስር መልምሎ ለማሳደግ ብልሃት ያስፈልጋል። በኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ ከዓለም ሻምፒዮናው ቡድን 33 በመቶውን ማስመረጤ በተምሳሌትነት የሚያስጠቅስ ነው።
"በየትኛውም ክለብ የስራ አመራር ቦርድ በቂ በጀት በመሸፈን መስራት ይኖርበታል እንጅ በአትሌቶች ምልመላ ላይ እጁን ማስገባት የለበትም።"
ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የስፖርት ክለብ ሌሎች የአገሪቱ ክለቦች ምን ሊማሩ ይችላሉ በሚል ከስፖርት አድማስ ለቶሌራ ዲንቃ ጥያቄ ቀርቦለታል። “ማንኛውንም አስተዳደር አመራሩን ነው የሚመስለው። የስራ አመራር ቦርዱ፣ ፕሬዚዳንቱ፣ አሰልጣኙ ሁሉም የየራሱ የኃላፊነት ድርሻ አለው። በየሙያችን የተመደብንበት ኃላፊነት በተግባር መተርጎም ከሁላችንም ይጠበቃል። አንዱ በአንዱ ኃላፊነት ላይ ጣልቃ መግባት የለበትም። ሁሉም በሙያው ተማምኖ እንዲሰራ መደገፍ ያስፈልጋል። በየትኛውም ክለብ የስራ አመራር ቦርድ በቂ በጀት በመሸፈን መስራት ይኖርበታል እንጅ በአትሌቶች ምልመላ ላይ እጁን ማስገባት የለበትም። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከተመሰረተ ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም ለበርካታ ዓመታት ብዙ በጀት እያወጣ ውጤታማ አትሌቶችን ያቀፈ አልነበረም። ከእኛ በፊት ለክለቡ ብዙ ግምት አይሰጠውም ነበር። አልፎ አልፎ አንዳንድ አትሌቶች ወጥተዋል። እነ መሰለች መልካሙ ውዴ አያሌው… በአሁኑ ወቅት ግን ብዙ ለውጥ አድርጓል። በክለቡ ስምንት አሰልጣኞች መስራት ስንጀምር በአመላመሉ፣ በአሰራሩ ላይ ሙሉ በሙሉ ተሃድሶ ተደርጎ ነው። በአሁኑ ወቅት በኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለው የሥራ አመራር ቦርድ አትሌቶችን ለማሰባሰብ በተደረገው ጥረት ለአሰልጣኞቹ ሙሉ ድጋፍ ሰጥተዋል። ከኢትዮጵያ ክለቦች በሚሰጠው የደሞዝ ክፍያ አንደኛ ነው። ለአትሌቶቹ ከቤት ኪራይ አንስቶ የተሟላ ድጋፍ በመስጠት እየሰራ የሚገኝ አስተዳደር ነው። ጥሩ አመራር ካገኘህ የአትሌቲክስ ክለብን ማደራጀት፣ ማዋቀር፣ ጠንካራ አትሌት ማፍራት የአሰልጣኙ ስራ ነው። “ ሲል መልሷል።
የቶሌራ የዓለም ሻምፒዮና አስደሳችና አሳዛኝ ትውስታዎች
በአጭር ጊዜ አሰልጣኝነት ልምዴ ብዙ የሚያስደስቱ፣ የሚያሳዝኑ ታሪኮች ገጥመውኛል። በ2013 እ.ኤ.አ ላይ “በሞስኮ በተካሄደው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምዮና እነጥሩነሽ፣ መሰረት ደፋር፣ መሀመድ አማን ወርቅ ሜዳሊያዎች ያገኙበት ነበር። በለንደን ኦሎምፒክም የተመዘገበው አስደናቂ ውጤት ይታወሳል።
እነጥሩነሽ፣ መሠረት፣ ቲኪ ገላና አስደናቂ ውጤት ነበራቸው። በ2015 እ.ኤ.አ ላይ በቤጂንግ በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ደግሞ ያዘንኩባቸው ተሳትፎዎች ነበሩ። በ10ሺ ሜትር በወንዶችም በሴቶችም ዝቅተኛ ውጤት አስመዝግበን ነበር።
ከሁሉም ደግሞ የሚያስከፋው በ2011 እ.ኤ.አ ላይ በኮርያ ዴጉ በኢብራሂም ጀይልን በ10ሺ ሜትር በአንድ ወርቅ የተመለስንበት ነው። አሰልጣኝ በደስታውም በሀዘኑም በሁለቱም መሐል ነው የሚቆመው። በ2019 እ.ኤ.አ ላይ በዶሐው የዓለም ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር የተመዘገበው ውጤት ታሪካዊ ነበር። ሙክታር ኢድሪስ ሲያሸንፍ ሰለሞን ባረጋ ሁለተኛ ጥላሁን ኃይሌ አራተኛ ሆኖ ነው የጨረሰው።አሰልጣኝ ይደሰታልም፣ ይበሳጫልም ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ አሰልጣኝም አትሌትም እንቅልፍ አጥተው እ”ንደሚሰሩ ይታወቃል።
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የወደፊት አቅጣጫ ላይ ብዙ ጀግና አትሌቶች ያፈራች አገር በልምምድ ቦታ እጥረትና በትራክ አለመሟላት መሰቃየት የለባትም።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስን በአጭር ርቀት እና በዝላይ ውድድር ከብሔራዊ አትሌት ጀምሮ ያለፍኩበት ነው። አሁን “ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ የሚያስፈልገው ቋሚ መዋቅር ያለውና መሠረተልማት የተሟላለት ብሔራዊ ቡድን መገንባት ነው። ብዙ የአገራትን አትሌቶች በስልጠና ዘዴ መበላሸት ፣ በስፖርት ማዘውተሪያዎች አለመኖር፣ በተለያዩ የምልመላ መንገድ ላይ እየወደቁ ናቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ የስልጠና ቦታዎች ችግር በጣም አለብን። ይህን ሁሉ ዝግጅት እያደረግን ያለነው በዛ ውስጥ ሆነን ነው። የአካዳሚው ትራክ ባይኖር ኖሮ የኢትዮጵያ አትሌቶች አስፋልት ላይ እየሮጡ በትራክ ላይ ለመወዳደር ይገደዱ ነበር ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የኦሎምፒክ ኮሚቴው በጋራ ሆነው እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በጋራ መሰራት ይጠበቅባቸዋል። መንግስትን መገፋፋት አለባቸው። የስፖርት መሰረተ ልማት ችግሮች ካልተስተካከሉ በተተኪ አትሌቶች አሳሳቢ አደጋ እየተደቀነ ነው። አትሌቶች በተለያየ ቦታና ሁኔታ ነው እየሰለጠኑ የሚገኙት፡፡ የጋራ ውድድር ለማድረግ እየከበደም መጥቷል፡፡ ወጥ የሆነ የስልጠና መዋቅር መዘርጋት አለበት፡፡
የልምምድ መሥርያ ቦታ መጣበብ እያስጨነቀን ነው፡፡ እየተጠበባቅን ነው እየሰራን የቆየነው፡፡ ብዙ ጀግና አትሌቶች ያፈራች አገር በልምምድ ቦታ እጥረትና በትራክ አለመሟላት መሰቃየት የለባትም። ሕዝቡም መንግስትም ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡በተለይ የሚመለክተው የባህልና ስፖርት ሚኒስተር ነው። ባለድርሻ አካላት አስተባብሮ ለ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ ቶሎ ርምጃ መውሰድ ይጠበቃል። ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ በቂ የስፖርት መሠረተልማት ካልተገነባ በመካከለኛ ርቀት ውድድርሮችም አትሌቶችን ማፍራት የተቸገርንበት ሁኔታ ወደ ረጅም ርቀት ተሸጋግሮ የባሰ ጥፋት እንዳይ’መጣ ስጋት አለ፡፡
ባለፈው ሻምፒዮና ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎች ጨምሮ አራት ሜዳሊያዎች የሰበሰበው አሰልጣኝ ህሉፍ ይህደጎ
የቀድሞ አትሌትና የአሁኑ ውጤታማ አሰልጣኝ ህሉፍ ይህደጎ የተገኘው ከትግራይ ክልል አድዋ ከተማ ነው። ከዓመት በፊት በአሜሪካ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዋና አሰልጣኝነት 4 ሜዳልያዎችን 2 የወርቅ፣ አንድ የብርና 1 ነሐስ አግኝቷል። ቡዳፔስት በምታስተናግደው የዓለም ሻምፒዮና ላይ 6 አትሌቶችን በማስመረጥ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል። በ1500 ፍሬወይኒ ሃይሉ እና ብርቄ ሐየሎም፤ በ800 ሜትር ወርቅነሽ መሰለ፣ በ5ሺና በ10ሺ ሜትር ጉዳፍ ፀጋየ፣ ቀ5ሺ ሜትር ፍሬወይኒ ጸጋዬና ለምለም ሐይሉ ናቸው። አሰልጣኝ ህሉፍ ለዓለም ሻምፒዮናው ያደረገውን ዝግጅት አስመልክቶ ሲናገር “በዓለም አቀፍ ውድድር ውስጥ ስለሆነን ሁሌም ዝግጅት እናደርጋለን። ለዓለም ሻምፒዮናው ያደረግነው ዝግጅት ልዩ የሚያደርገው ከ1 ወር በላይ ከውድድር ውጭ ሆነን ልምምድ ስንሰራ በመቆየታችን ነው። በአጠቃላይ ግን አመቱን ሙሉ በጥሩ አቋምና ብቃት ዝግጅትና ልምምድ ስናደርግ ቆይተናል።” ብሏል
ጉዳፍ በመጀመሪያ በ10ሺ ሜትር ከምታደርገው ውድድር በኋላ ነው በ5ሺ ደግሞ የመሮጧ ነገር የሚወሠነው።
በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጠበቁ አትሌቶች አንዷ ጉዳፍ ፀጋይ ዋንኛዋ ናት። አትሌት ጉዳፍ ቡዳፔስት ላይ ሻምፒዮናነቷን ለማስጠበቅ ከመሮጧ ባሻገር፣ በ10ሺና በ5ሺ ሜትር ለመሳተፍ እንደምትችል ብዙዎች እየገመቱ ናቸው። አሰልጣኝ ህሉፍ በዚህ ዙርያ በሰጠው አስተያየት “በሻምፒዮናው ላይ ጉዳፍ ብቻ ሳትሆን እነ ጎይተቶም፣ ለተሰንበት፣ ታምራት፣ ሰለሞንና ሌሎችም አትሌቶች ይጠበቃሉ። ጉዳፍ በዚህ የዓለም ሻምፒዮና ላይ በሁለቱም ርቀቶች እንደምትሮጥ ስሟ ተመዝግቧል። ግን በመጀመሪያ በ10ሺ ሜትር ከምታደርገው ውድድር በኋላ ነው በ5ሺ ደግሞ የመሮጧ ነገር የሚወሠነው። ቡዳፔስት ላይ ሞቃታማ አየር ሊኖር ይችላል። ስለዚህም በሁለቱም ርቀቶች የመሳተፉ ነገር በተሟላ ብቃቷ ላይ ይወሰናል ። ሁለቱን ርቀቶች ለመሮጥ ይበልጥ አቅም ይኖራታል አይኖራትም እንደ አሰልጣኝ በውድድር ስፍራ ላይ ተመልክተን ነው የምንወስነው …”
“ሁሌም ተፎካካሪዎቻችን ኬንያውያን ናቸው”
በረጅም ርቀት ለኢትዮጵያ አትሌቶች ተፎካካሪዎች እነማን ይሆናሉ በሚል ጥያቄ ዙሪያ አሰልጣኝ ህሉፍ አስተያየት ሲሰጥ “ባለፈው የዓለም ሻምፒዮና ከኬንያ በልጠን 10 ሜዳልያዎች አምጥተናል። ሁሌም ተፎካካሪያችን ኬንያውያን ናቸው። በዓለም ሻምፒዮና ላይ የሜዳልያ ውጤትን የሚወስነው የሌሎች አገራት ተፎካካሪዎች ወቅታዊ ብቃት ነው። ኬንያውያን ዘንድሮ ያላቸውን ብቃት አጠናክረው እንደሚመጡ ነው የምገምተው። ኬንያ በተለይ ከባድ ተፎካካሪያችን ትሆናለች የምለው ከቡዳፔስት ሞቃታማ አየር ጋር በማያያዝ ነው። አምና የተሻለ ውጤት የነበረን የኦሬጎን አየር ቀዝቃዛ ስለነበር ነው። ከአዲስ አበባ አየር ጋር ይቀራረብ ነበር። ቡዳፔስት ላይ ከኦሬጎን ተቃራኒ አየር ነው የሚጠብቀን። ሞቃታማ ነው። በውድድሩ ሙቀት ከ28 እስከ 33 ዲግሪ እንደሚሆን ይገመታል። ካለፉት ሻምፒዮናዎች ያገኘነው ልምድ እንደሚያመለክተው ደግሞ ኬንያውያን በሞቃታማ አየር የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ። እንደ አሰልጣኝ የሙቀቱ ጉዳይ ያሰጋኛል”ሲል አሰልጣኝ ህሉፍ ተናግሯል።
ቡዳፔስት ላይ ምን ያህል ሜዳልያ ትጠብቃለህ ተብሎ የተጠየቀው ህሉፍ “በብዙ ምክንያት ያምናውን ውጤት ለመጠበቅ የሚከብድ ይሆናል፡፡ የኦሬጎን ሻምፒዮና የተካሄደው ሐምሌ ላይ ነው-------- ደግሞ በነሐሴ ነው፡፡ አምና ሰኔ አካባቢ ብዙም ዝናብ ሳይገባ ነው ትሬኒንግ ጨርሰን ወደ ዓለም ሻምፒዮናው የሄድነው፡፡ ሞቹ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ሙቀቱ የሚያሰጋን ቢሆንም ቡዳፔስት ላይ በአጠቃላይ ጥሩ ተፎካካሪ እንደምንሆን እጠብቃለሁ።” ሲል ተናግሯል
"ከሁሉም በማስቀደም ለአትሌቲክስ ተገቢውን መሰረተ ልማት እንዲዘረጋ ነው የምንጠይቀው።”
ወደ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ አሰልጣኝነት ከመጣ 6 ዓመት የሆነው ህሉፍ በቶኪዮ ኦሎምፒክና በኦሬጎን የዓለም ሻምፒዮና ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በዋና አሰልጣኝነት እየሰራ መቆየቱ ይታወቃል። በዚህ አጭር የአሰልጣኝነት ዘመኑ በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢ የሆነበት ጉዳይ የስፖርት መሠረተ ልማት በቂ አለመሆኑ ነው። “በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ትልቁ ፈተና የልምምድ ትራክ አለመኖር ነው። ከዓለም አትሌቲክስ ውጤታማ ከሚባሉ አገሮች አንዱ ብንሆንም ከልምምድ ትራክና ከስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ ጋር በተያያዘ በቂ መሰረተ ልማት አለመኖሩ በስፖርቱ ለምንገኝበት ደረጃ የማይመጥን ነው። ለዚህ ሻምፒዮና ባደረግነው ዝግጅት ወደ ትራክ እየገባን የነበረው ተራ በተራ፤ በልመናና በግፊያ ነው። የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ለዚህ አሳሳቢ ችግር መፍትሔ እንዲሰጡበት ጥሪ አቀርባሁ። ከሁሉም በማስቀደም ለአትሌቲክስ ተገቢውን መሰረተ ልማት እንዲዘረጋ ነው የምንጠይቀው።”
“የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ውሳኔ ለኢትዮጵያም ትምህርት ነው፡፡ አሰልጣኞቹ መበረታታት ያስፈልጋቸዋል፡፡”
በዓለም ሻምፒዮናው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አትሌቶችን ውጤታማ ላደረጉ አሰልጣኞች የሜዳልያ ሽልማት እንደሚሰጥ ተገልጿል። “የዓለም አትሌቲክስ ይህን አዲስ አሰራር በመፍጠሩ ትልቅ ቁምነገር ነው። ባሰለጠንካቸው አትሌቶች አራት አምስትም ሜዳሊያዎች ብታመጣ እንደ አሰልጣኝ የተለየ ሽልማት አይገኝበትም ነበር። ጥሩ የሜዳልያ ውጤት ቢኖርም የሚሰጥህ ሽልማት የሚያስደስት አይደለም። ሯጭ የሚያወጣው አሰልጣኝ ነው፡፡ ስለዚህም የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ውሳኔ ለኢትዮጵያም ትምህርት ነው፡፡ አሰልጣኞቹ መበረታታት ያስፈልጋቸዋል፡፡”
“በአዲስ አመት መግቢያ አትሌቶች ድል ሲያስመዘግቡ አዲስ ዘመን የመጣ ነው የሚመስለው፡፡”
የኢትዮጵያ አትሌቶች በአገሪቱ ሁኔታ ላይ የሚፈጥሩትን ስሜት እንዴት ትመለከተዋለህ የሚል ጥያቄ የቀረበለት አሰልጣኝ ህሉፍ “ስፓርት በተለይ አትሌቲክስ ለኢትዮጵያ በጣም ወሳኝ መስክ ነው፡፡ አገራችንን የሚያስጠራው አትሌቲክስ ነው፡፡ በአዲስ አመት መግቢያ አትሌቶች ድል ሲያስመዘግቡ አዲስ ዘመን የመጣ ነው የሚመስለው፡፡ ባለፈው ሻምፒዮና የትግራይ አትሌቶች ውጤታማ ሲሆኑ በዚያ ክልል ጦርነትና ሌሎች የከፉ ችግሮች ነበሩ። ከድል በኋላ ሁሉ ነገር ወደ ሠላም መጣ። እውነት ለመናገር አትሌቶቹ በመካከላቸው ምንም ችግር የላቸውም፡፡ የአትሌቶቹ አንድነት እኔም ይገርመኛል፡፡ ምንም ልዩነት የላቸውም። ከአንድ አካባቢ እንደመጡ ነው የሚሰሩት። ይህም ከቶኪዮ ኦሎምፒክ ጀምሮ ያየሁት ነው። በመጨረሻም የማስተላልፈው መልዕክት የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሌም ከአትሌቲክሱ ጀርባ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ከውጤት በላይ ቢኖር ብታደርግለት ትመኛለህ፡፡ ለአትሌቲክሱ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ በማንኛውም በሚሰጥህ አክብሮት ትረዳለህ ፡፡ ወደፊትም አክብሮታቸውን አብዝ ይስጠን፡፡ ከዚህ በመነሳት የስፖርት ማዘውተሪያዎቹ እንዲገነቡ ህዝባችን ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል”
“የአማርኛ ጥበበ ቃላት ቅኝት” ዛሬ በሀገር ፍቅር አዳራሽ ይመረቃል
በአንጋፋው ደራሲ ሃያሲና የኢኮኖሚ ባለሙያ አስፋው ዳምጤ የተሰናዳው “የአማረኛ ጥበበ ቃላት ቅኝት” የተሰኘ መፅሐፍ፣ ዛሬ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴአትር አዳራሽ ይመረቃል፡፡
መፅሐፉ፤ የዘመናት ታሪክን የሚያሳይ፤ የመቶ ዓመት የልብወለድ ታሪኮችን የሚተነትን ነው ተብሏል፡፡
በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ፣ ደራሲና መምህር ደረጀ ገብሬ፣ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ፣ ደራሲ ዘነበ ወላ፣ ደራሲና ሰዓሊ ዳንኤል ታዬ፣ ደራሲና አርታኢ ሁሴን ከድር እንዲሁም ኤርሚያስ ሁሴን ጥበባዊ ሥራዎቻቸውን ለታዳሚ የሚያቀርቡ ሲሆን፤ ይታገሱ ጌትነት ደግሞ መድረኩን ይመራዋል ተብሏል፡፡
አስታራቂ ሽማግሌ፣ የችግር ሐኪምና ፈዋሽ ነው”
“--እንደ እውነቱ ከሆነ ሰው በኃጢአት ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ ጥልና መገዳደል በየትኛውም ጊዜ፣ በየትኛውም ሀገር በየትኛውም ማኅበረሰብ ይከሠታል፣ ዛሬም በሀገራችን በተፈጠረው አለመግባባት ከባድ ችግር ተፈጥሮአል፣ የሚያስገርመው ነገር ቢኖር እንዴት እንደ ባህላችንና እምነታችን በቀላሉ በዕርቅና በይቅርታ ማስተካከል አቃተን የሚለው ነው፤ የዘመናችን ልዩ ነገር ይህ ነው፤ ለዚህም ብዙ የተለያየ ምክንያት ሊኖረው ይችላል፤ በሃይማኖት ዓይን ሲታይ ግን ለእግዚአብሔር ቃል የምንሰጠው ክብር በእጅጉ ስለተቀነሰ ነው የሚል ሆኖ ይገኛል፣ ይህ ዝንባሌ አሁን ላለውም ሆነ ለሚመጣው ትውልድ አደገኛ ስለሆነ የኦርቶዶክስ ሕዝበ ክርስቲያንም ሆነ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ሁሉ፣ ይህንን በጥልቀት ሊያጤኑትና ሊያርሙት ይገባል፡፡ ሽማግሌ የሀገር በረከት ነው፤ አስታራቂ ሽማግሌ የችግር ሐኪምና ፈዋሽ ነው፤ የፍቅርና የተግባቦት መሐንዲስም ነው፤ በእግዚአብሔርም ‘የሚያስታርቁ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው‘ ተብሎ ውዳሴ ተችሮአቸዋል፣ እነዚህን ሽማግሌዎች ተጠቅመን ችግሮቻችንን መፍታት ጊዜው የሚጠይቀው አስገዳጅ ጉዳይ ሆኖአል።”
(የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ
አቡነ ማትያስ፤ ለጾመ ፍልሰታ ካስተላለፉት መልዕክት የተወሰደ)
በአማራ ለተከሰተው ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለግለት 9 የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት አሳሰቡ
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውንና በርካታ ሠላማዊ ዜጎችን ለህልፈት ዳርጓል የተባለው ግጭት በእጅጉ እንዳሳሰባቸው የገለፁ የሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት፤ ግጭቱን ለመፍታት በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች የተጀመሩ የሰላም ጥረቶችና ስምምነቶች በክልሉም እንዲተገበሩ ጠየቁ። የክልሉን ሠላም ለማስጠበቅ በተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ወቅት የመንግስት የጸጥታ አካላት ያልተመጣጠነ ኃይል እንዳይጠቀሙና ብሔርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችና የጅምላ እስሮች እንዳይፈጸሙም ተቋማቱ አሳስበዋል።
በክልሉ ከወራት በፊት የተቀሰቀሰውና ሰሞኑን ተባብሶ የቀጠለው ግጭት ለንጹሃን ዜጎች ህልፈት ምክንያት መሆኑን ያመለከቱት ተቋማቱ፣ ግጭቱን ለማስቆም የሚወሰዱ እርምጃዎች የብዙሃንን ደህንነት፣ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶችእና ነጻነቶች አደጋ ላይ የማይጥሉ መሆን እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።
በአማራ ክልል በተፈጠረው ግጭት ስጋት እንደገባቸው የገለጹትና ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ መፈታት የሚችልበት መንገድ እንዲፈለግ ያሣሰቡት ዘጠኙ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት፣ የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት፣ የኢትዮጵያ ሴቶችና ሕፃናት ማህበራት ህብረት፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች፣ አዲስ ፓወር ሀውስ እና ሴታዊት ንቅናቄ የተሰኙት ድርጅቶች ናቸው።
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉና ስር እየሰደዱ መሆኑን የጠቆሙት ተቋማቱ የመንግስት የጸጥታ አካላት የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር ያለመ እንደሆነ የተነገረለትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚያስፈጽሙበት ወቅት ያልተመጣጠነ ኃይል ከመጠቀም እንዲታቀቡ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የሚወጡ መመሪያዎችና ደንቦች፤ ለዜጎች ተደራሽ በሆኑ አማራጮች በተከታታይ እንዲደርሱ ጠይቀዋል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ሂደት ውስጥ ብሔርን መሠረት ያደረጉ ማግለሎችና ጥቃቶች እንዳይስፋፉና የጅምላ እስሮች እንዳይከናወኑም ጥሪ አቅርበዋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው አርብ የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ፤ በአማራ ክልል ከተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ ጋር “ግንኙነት ያላቸው፣ ጉዳዮችን የሚያባብሱ፣ ስምሪት የሚሰጡ” የተባሉ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተጀመረ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማስታወቁ ይታወሳል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽመውን ጠቅላይ መምሪያ ዕዝን በዋና ሰብሳቢነት የሚመሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ባለፈው እሁድ በሰጡት መግለጫም፤ በቀጣይ ቀናት የሚወሰዱ እርምጃዎች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።
በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች በተከሰቱ ግጭቶች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፣ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችና ሌሎችም ጉዳቶች በክልሉ እንዳይፈጸሙ ከፍተኛ የመከላከል ስራዎች እንዲያከናወኑና የተጠያቂነት ስርዓት እንዲዘረጋ የጠየቁት ተቋማቱ፤ ግጭቱ በተከሰተባቸው የአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞችና አጎራባች አካባቢዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች ሰብአዊ እርዳታዎች በአግባቡ እንዲደርሱ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት መንስኤዎችና ዘላቂ መፍትሔው፤ በሚመለከታቸው አካላት ተለይቶ መቅረብ እንዳለበት በመግለጫቸው ያመለከቱት የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማቱ የሀገር ሽማግሌዎች የሲቪል ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የእምነት ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የበኩላቸውን ግፊት ማድረግ እንዳለባቸው አመልክተዋል። በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች የተጀመሩ የሰላም ጥረቶችና ስምምነቶች፤ በአማራ ክልል በሚንቀሳቀሱ ወገኖችና በፌዴራሉና በክልሉ መንግሥታት መካከል የሚተገበርበት ዕድል እንዲፈጠርም ጥሪ አቅርበዋል።
በመዲናዋ የግብረ-ሰዶም ተግባር ይፈፀምባቸዋል ተብለው በተጠረጠሩ ተቋማት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ተባለ
“ግብረሰዶማዊነት በሀገራችን ህግ ፍጹም የተከለከና በህግ የሚያስጠይቅ ተግባር ነው”
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ በከተማዋ የግብረሰዶም ተግባር ይፈፀምባቸዋል ተብለው በተጠረጠሩና ጥቆማ በተሰጠባቸው ሆቴሎች፣ ባሮችና ሬስቶራንቶች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የገለጸ ሲሆን፤ ከህብረተሰቡ ለሚደርሰው ጥቆማ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ጋር በቅንጅት በመሥራትም ላይ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡
ከነባሩ የሀገራችን ባህል፣ ወግ፣ የአኗኗር ስርዓትና ሃይማኖቶች ባፈነገጠ መልኩ የግብረ-ሰዶም ተግባር በሚያስፈጽሙ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ፔንሲዮኖችና መሰል የመዝናኛ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ከህብረተሰቡ በሚደርሰው ጥቆማ መሰረት፣ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ቢሮው አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ የግብረ-ሰዶም ተግባር መፈጸምና ማስፈጸም በኢትዮጵያ በሥራ ላይ ባሉ ሕጎች የተከለከለ መሆኑን ገልፆ፤ ይህንን አስጸያፊ በሰውም በአምላክም ዘንድ የተጠላ ድርጊት በሚፈጽሙና በሚያስፈጽሙ የመዝናኛ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ፣ ያለ አንዳች ርህራሄ ከፖሊስ ጋር በመተባበር፣ እርምጃ መውሰዱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክቷል።
በዚሁ መሰረት በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 አስተዳደር ውስጥ በሚገኝ “አበባ ገስት ሐውስ” በሚባል የመዝናኛ አገልግሎት መስጫ ተቋም ላይ፣ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት እርምጃ እንደተወሰደበት የጠቆመው ቢሮው፤ የተቋሙ ኃላፊም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑን አመልክቷል፡፡
በተመሳሳይ፤የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በሰጡት መግለጫ፤”ሀገራችን በህብረ ብሄራዊነቷ የምትታወቅና የተለያዩ ባህሎችና ወጎች ያሏት ሀገር ስትሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከማህበረሰቡ ወግና ባህል ያፈነገጡ ድርጊቶች እያጋጠሙ ነው” ብለዋል፡፡
ግብረሰዶማዊነት በሀገራችን ህግ ፍጹም የተከለከና በህግ የሚያስጠይቅ ተግባር መሆኑን የገለጸው ፖሊስ፤ በዚህ ተግባር ላይ በተሰማሩ ወገኖች ወይም ተቋማት ላይ መረጃን መሰረት አድርጎ፣ በህግ አግባብ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።
በዚህ ዓይነት ህገ-ወጥ ተግባር የሚጠረጠሩ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች፣ የሀገሪቷን ህግ አክብረው የመስራት ግዴታ እንዳለባቸውም ‹ፖሊስ አስጠንቅቋል፡፡
ከግብረሰዶም ፀያፍ ተግባር ጋር የተገናኘ መረጃና ጥቆማ ያለው ማንኛውም ሰው በአቅራቢያው በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በግንባር በመቅረብ፣ በነፃ የስልክ መስመር፡- 991 እና 987 እንዲሁም በ011-1- 11-01-11 እና 011-5-52-63-02 በመጠቀም መረጃና ጥቆማ መስጠት እንደሚችል የጠቆመው ቢሮው፤ አሁንም ህብረተሰቡ ይህንኑ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል።