Administrator

Administrator

· የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ስርአት የአምባገነኖች መደበቂያ ነው
        · ህዝብን ማሸነፍ የሚቻለው በፍቅርና በውዴታ ብቻ ነው

   በቅርቡ “መግባባት” ፖለቲካዊ እኩልነት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን! በሚል ርዕስ ለበርካታ አመታት ያደረጉት ፖለቲካዊ ምርምር ውጤት መፅሐፍ ፅፈው ለአንባቢያን ያቀረቡት የቀድሞ የኢዴፓ መስራች እና ፕሬዚዳንት እንዲሁም የቅንጅት ም/ሊቀ መንበር የነበሩት ዶ/ር ኢ/ር አድማሱ ገበየሁ ላፉት 12 ዓታት ከኖሩበት ስዊድን ሃገር ከሰሞኑ ለእረፍት አዲስ አበባ በመጡበት አጋጣሚ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አግኝቶ ከ1997 እስካሁን የመጣንበትን የፖለቲካ ሂደት የዳሰሰ ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ ዶ/ር ኢንጅነር አድማሱ ገበየሁ በሙያቸው የውሃ ምህንድስና ሊቅ ሲሆኑ በቅርቡም ወደ ሀገራቸው ተመልሰወ በሙያቸው እንዲሁም በሌሎች ማህበራዊ ዘርፎች ለማገልገል ፍላጎት እንዳቸው ይገልፃሉ፡፡ ዶ/ር ኢ/ር አድማሱ በሰፊው የሚታወቀውን የድል ምልክት የሆነውን የቅንጅቱን የሁለት ጣት የምርጫ ምልክት ሃሳብ በማመንጨትም ይታወቃሉ፡፡


    በ97 በተደረገው ምርጫ፣ ”ቅንጅት”ን በምክትል ሊቀ መንበርነት ሲመሩ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ላለፉት 12 ዓመታት ግን በሃገር ውስጥ አልነበሩም፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያለውን ፖለቲካዊ ሁኔታ አንዴት አገኙት?
እርግጥ ነው ከ97 በኋላ በቅርብ የለሁም፤ ነገር ግን በየጊዜው ሁኔታዎችን ማወቅ እፈልግ ነበር። የዲሞክራሲ ሥርአት በዚህ ሃገር፣ በብዙ ሰዎች የሚፈለግ ጉዳይ ነው። ብዙዎችም መስዋዕትነት የከፈሉበት ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን በቅርብም ይሁን በሩቅ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ እስካሁን መሻሻልን አላየሁም። ዲሞክራሲያችን እስካሁን መሻሻል አላሳየም፡፡ ይሄን መሻሻል የማምጣት ጉዳይ በዋናነት የህዝቡ ነው፤ ቀጥሎም ስለ ህዝብ ሆነው የሚንቀሳቀሱ ሚዲያዎች በተለይም ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ ጋዜጠኞች ከ97 በኋላ በሚፈለገው መጠን ዲሞክራሲን ማገልገል አልቻሉም። በእርግጥ ይሄ የእነሱ ጥፋት አይደለም፡፡ አመቺ ሁኔታ አልተፈጠረላቸውንማ ተወቃሽ አይደሉም፡፡ ሆኖም ዘርፉ ተመናምኖ ነው ያገኘሁት፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ ጋዜጠኞች በተደጋጋሚ ለእስርና ለስደት  ተዳርገዋል። ይሄ በሀገሪቱ ከባድ ጉዳይ ነው፡፡ በፖለቲካ ዘርፍ ህዝቡን ለማገልገል የተሰማሩ ወገኖች፣ ከገዥው ፓርቲ በስተቀር፣ ሃገራቸው እንዳልሆነች፣ ህዝቡም ወገናቸው እንዳልሆነ እንደ ባዕድ ተቆጥረው፣ምንም አይነት መፈናፈኛ አጥተው ቆይተዋል፡፡ ይሄ በዚህ አስራ ሦስት ዓመት ውስጥ የተፈፀመ እጅግ አሳዛኝ ታሪክ ነው፡፡ በአጠቃላይ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሚዲያዎች፣ የዲሞክራሲ ተቋማት፣ ሲቪክ ተቋማትና የዲሞክራሲ ምንጭ የሆነው ህዝቡ ራሱ በአሳዛኝ ሁኔታ ነው የቆዩት፡፡ ህዝቡ የሥልጣኑ ባለቤት መሆን አልቻለም፡፡ አስፈላጊ መድረኮች ተነፍገውታል፡፡ ይሄ አሳፋሪ ታሪክ ነው፡፡ እኔ በግሌ ውጪም ብኖር፣ በዚህ ጉዳይ እረፍት አጥቼ፣ ውስጤም ሲቆስል ነበር፡፡
አብዛኞቹ የቅንጅት አመራሮች ከእስር ከተፈቱ በኋላ ተበታትነዋል፡፡ አሁን ላይ ሆነው ሲያስቡት ችግሩ ምን ነበር ይላሉ?
እውነቱን ለመናገር ከ1997 በኋላ በመንግስት የተሰራው ሴራ እንዲህ ነው ተብሎ ሊገለፅ አይችልም። እርግጥ ነው ትልቁ ባለድርሻ መንግስት ይሁን እንጂ ሌላው የአንበሳውን ድርሻ የምንይዘው እኛ ተዋናዮቹ ነን። እንደ ህዝብ አነቃናቂ መሪ ወደ ኋላ ተመልሰን፣ ትንሽ በመሆናችን እኔ በበኩሌ ያሳዝነኛል፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ተሳታፊ በመሆኔ፣ በፈፀምኩት ጥፋት በግሌ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ምንም ይሁን ምክንያቱ እኛ የሚጠበቅብንን፣ የድርሻችንን አላደረግንም ነበር። በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እዚህ ያለውን መከራና ስቃይ መቅመስ ሲገባኝ፣ ለስደት መዳረጌም ውስጤን በጣም ጎድቶታል፡፡ ሆኖም ግን በአንድ በኩል በራሴ ኃላፊነት ስር ያሉ ቤተሰቦቼም ሆኑ ሌሎች ወገኖች ህይወታቸው እንዲቀጥል ማስቻሌ ደስ ይለኛል፡፡ በአጠቃላይ ግን በሀገር ደረጃ የሰራሁት ስህተት አመዝኖ ይታየኛል። ይህን ተረድቼም የበደልኩትን ለመካስ ባለኝ ሁሉ እታገላለሁ። በስደት እድሜዬ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ኅሊናዬ ስመለስ፣ ባለሁበትም ሆኜ አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ ብዬ ሞክሬያለሁ፡፡ ምንም ይሁን ምን እዚሁ የህዝብን ትንፋሽ እያዳመጡ፣ ከህዝብ ጋር አብረው መከራቸውን እያዩ፣ እየታሰሩ እየተፈቱ፣ የሚችሉትን ያህል የሰሩ ሰዎች በጣም የምቀናባቸው፣ በጣም የማከብራቸው ናቸው፡፡ ያንን ባለማድረጌ ትንሽ ቅስሜ ስብር ቢልም የሰሩትን ስራ ሁሉ ከማድነቅ ወደ ኋላ አልልም፡፡ ማድረግ ያለብኝን ግን ወደፊት አደርጋለሁ፡፡
የኢዴፓ መስራችና ሊቀ መንበር ነበሩ ---
ኢዴፓ መድህንን ፕሬዚዳንት ሆኜ ለሁለት የምርጫ ጊዜያት አገልግያለሁ፡፡ ዶ/ር ኃይሉ አርአያም ም/ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ኢዴፓንም ሆነ ሌሎች ፓርቲዎችን ያን ያህል በጥልቀት አልተከታተልኩም። ፓርቲዎችን በድምሩ ነበር የማያቸው፡፡ በአንድ በኩል ተቃዋሚን የሚወክል፣ በሌላ በኩል ገዥው ፓርቲ አድርጌ፣ በሁለት ዘርፍ ነበር በጥቅሉ የምከታተለው፡፡ እኔ አሁን ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ውጪ ነው ያለሁት። ይሄን የወሰንኩት በራሴው ምክንያት ነው፡፡ አንድ ሰው ከሃገሩ ከወጣ፣ በየዕለቱ እወክለዋለሁ ከሚለው ህዝብ ጋር ካልሆነ፤ በምንም መልኩ አመራርነትም አባልነትም አያስፈልገውም የሚል ነው እምነቴ፡፡ የፖለቲካ ስራ በህዝብ መሃል የሚከወን ነው፡፡ ምክንያቱም ባለቤቱ ህዝብ ነውና፡፡ ስለዚህ የሌለሁበትን የተቃውሞ ፖለቲካ፤ በጥልቀት አልተከታተልኩትም፡፡
ባለፉት 27 ዓመታት የዲሞክራሲ ሥርአት ግንባታ የት ደርሷል ይላሉ?
ዲሞክራሲያዊ ስርአት ተገንብቶ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው አይነት የፖለቲካ ስርአት ለመፍጠር ገና አልጀመርንም፡፡ ምክንያቱም ለመጀመሩ ምልክት የሚሆኑ ነገሮች በበቂ መጠን አልታዩም፡፡ ሃሳብን በነፃ መግለፅ ተግባራዊ ካልተደረገ ምን ፖለቲካ አለ? ሰዎች የሾሟቸውን እንኳ ለመቆጣጠር በነፃነት መደጀራት አለባቸው፡፡ ይሄ ተፈጥሯል? ምርጫ ራሱ የግል አይደለም። አንድ ፓርቲ በሚሊዮን ተደግፎ ከተመረጠ፣ የመረጡት 1 ሚሊዮኖች የፓርቲው እምነት አራማጆች ናቸው ማለት ነው። ይሄ ቀላል አይደለም፤ ስሜታቸው፣ ፍላጎታቸው፣ ግንዛቤያቸው---በመረጡት ፓርቲ ውስጥ አለ ማለት ነው፡፡ ይሄ በመሆኑ አንድ ማህበር ናቸው፡፡ በ97 ቅንጅትን ሚሊዮኖች ሲመርጡት፣ የማህበሩ አባል ሆኑ ማለት ነው፡፡ የፓርቲውን መብት መንግስት ጣሰ ማለት፣ የሚሊዮኖቹን ሃሳብና ፍላጎት ደፈጠጠ ማለት ነው፡፡
ብዙ ጊዜ በዓለም ላይ ያለው ዲሞክራሲ የሚቸገረው፣ የዲሞክራሲን የመጀመሪያ ትርጉም ትቶ፣ ሁለተኛውን ትርጉም በመያዝ ነው፡፡ ቀዳሚው የዲሞክራሲ ትርጉም፤ አንድ ዜጋ ራሱን በሚመለከት በሚሰጥ የውሳኔ ሂደት ውስጥ ራሱ ቀጥታ ወይም ተወካዩ መሳተፍ አለበት ይላል። ይሄ የዲሞክራሲ የመጀመሪያ ትርጉም ነው። ሁለተኛው ትርጉም፤ አብዛኛው በወሰነው ይፀናል፣ የጥቂቶቹ ድምፅ በብዙኃኑ ይገዛል ነው የሚለው፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ዲሞክራሲ የሚቸገሩት የመጀመሪያውን ትርጉም እየሳቱ ነው፡፡ በመፅሐፌ ለምሳሌ፣ ስለ አብላጫ ድምፅ የምርጫ ስርአት አስቀምጫለሁ፡፡ በዚህ ስርአት ውስጥ የሚንፀባረቀው ሁለተኛው የዲሞክራሲ ትርጉም ነው፡፡ አብላጫ የምርጫ ስርአት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዘንናል፡፡ አብዛኛው ማህበረሰብ የወከለውን ተወካይ በሚፈልገው ቦታ፣ በውክልና እንዳይቆምለት የሚያደርግ ነው፡፡ አሁን በአፍሪካ ውስጥ ብዙ አገሮች፣ ”ዲሞክራሲ - ዲሞክራሲ” ይላሉ እንጂ ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ ይህ የሆነው በአመዛኙ የያዙት የአብላጫ የድምፅ ስርአት ምርጫ ስለሆነ ነው። እንኳን ብዙ አይነት ማህበረሰብ ባለበት አፍሪካ፤ ለትንሽ አገርም ቢሆን አብላጫ የድምፅ ስርአት የሚበጅ አይደለም። አምባገነኖች ግን ይህን የምርጫ አይነት ይወዱታል። ምክንያቱም ሽፋኑን ምርጫ አድርገው፣ ያለ ነቀፌታ “ዲሞክራሲ ሰፍኗል” እያሉ፣ ውስጡን ግን የአንድ ፓርቲ ሰዎች እየተለዋወጡ፣ አለፍ ሲልም አንድ ሰው ብቻውን “ከስልጣኔ ሞት ያንሳኝ” በማለት የሙጥኝ ብሎ በንግስና ይቆያል፡፡ ይህ አይነቱን የምርጫ ስርአት ያመጣው ሰው፣ ከንጉስ ያነሰ ስልጣን የለውም። የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ስርአት፤ የአምባገነኖች መደበቂያ ሽፋን ነው፡፡ አስፈላጊው የምርጫ ስርአት “የመግባባት ዲሞክራሲዊ ስርአት” ነው፡፡
“መግባባት” የተሰኘው መጽሐፍዎ በዋናነት የሚያቀነቅነው ፖለቲካዊ ሃሳብ ምንድን ነው?
በመፅሐፉ ላይ የህግ የበላይነት፣ ዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጉዳዮች በጉልህ ተነስተዋል፡፡ የህግ የበላይነት ጉዳይ ለአንድ ስርአት ጉልህ ነው፡፡ ህፃናት ራሱ የሚጫወቱት ጨዋታ ሊቆይ የሚችለው፣ የጨዋታው ህግ እስከተከበረ ብቻ ነው፡፡ ህግ ሲፈርስ፣ ይበታተናል ይፈርሳል፡፡ በመንግስት ስርአት ውስጥም የህግ የበላይነት የዚህ አይነት ሚና አለው፡፡ ምናልባት በየጊዜው የሚጎረብጡ ህጎች ህግን ተከትለው ሊሻሻሉ ይችላሉ፡፡ የሚሻሻሉትም በህግ የበላይነት ስር ሆነው ነው፡፡ ህግና ስርአት አለ የሚባለው ወረቀት ላይ ስለሰፈረ ብቻ አይደለም፡፡ በተግባር መገለጥ አለበት። ከህግ የበላይነት ጋር ተያይዞ ደግሞ የሰብአዊ መብት፣ ሁላችንም በግላችን ያለን ተፈጥሮአዎ መብት ነው። የትኛውም ህግ ሊሽረው የማይችለው ነው፤ ሰብአዊ መብት፡፡ በህይወት መኖር፣ ከአካልና ህሊናዊ ጉዳት የመጠበቅ መብት፣ የሰብአዊ መብት ብለን ልንጠቅስ እንችላለን፡፡ ይሄን መብት የሚገፍ ሁሉ ህግ ነው ብለን ልንቀበል አይገባም፤ ልንታገለው ይገባል፡፡ መሻር አለብን። የሚገባንን የሰውነት ክብር የሚያኮስስ ሁሉ፣ መታገል አለብን፡፡ በመፅሐፌ ያነሳሁትም ይሄን ነው፡፡ ሌላው የዲሞክራሲ ጉዳይ ነው፡፡ የዲሞክራሲ ስርአት በምንም መልኩ፣ ሰብአዊ ክብራችንን ከነካ፣ የህግ የበላይነትን ከተጋፋ መታረም አለበት፡፡ ከህግ የበላይነትና ከሰብአዊ መብት ጋር የሚጋፋ ከሆነ ወትሮውንም ዲሞክራሲ አይደለም፡፡ ዲሞክራሲ፤ የእነዚህን ጥጋት ጠብቆ ነው መራመድ ያለበት፡፡ እነዚህ ሶስት አካሎች የራሳቸውን መስመር እየጠበቁ፣ የኛን የዜጎችን መብት መጠበቅ አለባቸው ነው፤ አጠቃላይ ትንታኔው፡፡ “መግባባት” ስንል፤ ሁለት ነገሮች በውስጡ አሉ፡፡ አንደኛ፤ ወደ አንድ የጋራ ነገር መምጣት ማለት ነው፡፡ ወደ መግባባት ለመምጣት ደግሞ ስርአት ነው የምናበጀው፡፡ መግባባት ማለት አንድ አይነት ሃሳብ መያዝ መቻል ማለት ሳይሆን ችግሮች በሚፈቱበት ሁኔታ ላይ ተቀራራቢ ወይም አንድ አይነት ሃሳብ ላይ መድረስ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የምርጫ ውጤት በመቀበል ላይ መግባባት ሲፈጠር “መግባባት” እንለዋን፡፡ “የመግባባት ዲሞክራሲ”፤ የህሊና ፍርድ ነው መነሻው፡፡
በመፅሐፍዎ መግባባትን ከምርጫ ጋር አያይዘው የሚገልጹበት ሁኔታ አለ፡፡ እስቲ ያብራሩልን?
በህግ የመምረጥ መብት የተሰጠው ሁሉ፣ የሚሰጠው ድምፅ ዋጋ ሁሉ፣ ከሁሉ እኩል ነው ካልን፣ ውጤቱም እኩል መሆን አለበት ነው - ፅንሰ ሀሳቡ፡፡ 100 ሰዎች የመረጡት እና 200 ሰዎች የመረጡት ድምፅ በእኩል መመዘን አለበት፡፡ ይህ ማለት 100 ድምፅ ያገኘው አንድ መቀመጫ ቢያገኝ፣ 200 ያገኘው ደግሞ 2 ማግኘት አለበት ማለት ነው፡፡ ይህ ቀመር ተግባር ላይ ሲውል፣ የ100ዎቹ መራጮች ድምፅ፣ መሬት ላይ አይወድቅም ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለውን የምርጫ ስርአት ነው ልንከተል የሚገባው፡፡ ይህን ሃሳብ ነው መፅሐፌ ላይ በሰፊው ያብራራሁት፡፡ የተመጣጠነ የምርጫ ስርአት፤ እያንዳንዱ ዜጋ የሚሰጠው ድምፅ ዋጋ እንዳለው ያረጋግጥለታል። ወደ “መግባባት ዲሞክራሲ” ለመግባት ተመጣጣኝ የምርጫ ስርአት ተግባር ላይ መዋል አለበት፡፡ ተመጣጣኝ የምርጫ ስርአት ከሌለ፣ “መግባባት” ዲሞክራሲ ውስጥ መግባት አንችልም፡፡ በሩ እሱ ብቻ ነው፡፡ “የመግባት ዲሞክራሲ” ቀመር የሚያስቀምጠው፣ ልክ የፓርላማው መቀመጫ በተመጣጣኝ የድምፅ ስርአት እንደሚያዘው ሁሉ፣ የመንግስት ስራ አስፈፃሚውም ወይም ካቢኔውም በዚሁ ቀመር ይዋቀር ነው የሚለው። የካቢኔ ቦታ ላይም በተመጣጣኝ የምርጫ ስርአቱ ቀመር መሰረት በስራ አስፈፃሚ ውስጥ በዚህ መንገድ ተመጣጣኝ ውክልና ካለ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ አስፈፃሚውን በሚገባ ለመቆጣጠር ያለው ስራም ሊሰራ ይችላል። በአብላጫ የምርጫ ስርአት ግን ዋናው የፓርቲውና የጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎነት ነው የሚጠበቀው፤ ምክንያቱም ስልጣን በሙሉ ተጠቅሎ እጃቸው ይገባል። በዚህ “መግባባት ዲሞክራሲ” ቀመር ግን ከስልጣን ለሁሉም እንደየመጠኑ ይከፋፈላል፡፡ ይህ ሲሆን ስራ አስፈፃሚው እየተከራከረ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ማለት ነው፡፡
ሁሉም አካል ከመንግስት የስልጣን እርከኖች እንዲሳተፍ በማድረግ፣ የኔነት ስሜትን ይፈጥራል ማለት ነው፡፡ አንድ ፓርቲ ብቻውን ሀገሪቱን እንደፈለገ የማድረግ እድል እንዳይኖረው ያደርጋል፡፡ ሌላው የመግባባት ዲሞክራሲ ጥቅሙ፣ አንድ ስርአት የሰራውን ተከታዩ እንዳያፈርስ ያግዛል፡፡ እኛ ደግሞ ይህን አይነቱን ስርአት ለመጀመር እድላችን ሰፊ ነው። ለምሳሌ አሜሪካ ይህ ሃሳብ ይተግበር ቢባል ለስንት መቶ አመታት የተሰፋውን ድሪቶ ማፍረስ ይከብዳል። እኛ ግን ብዙም ስላልደረትን በቀላሉ ከንፁህ ጨርቅ መልበስ መጀመር እንችላለን። በነገራችን ላይ ዶ/ር አብይ አህመድ ካነሷቸው ሃሳቦች፤ በትምህርት ጥራት ላይ ያላቸውን አቋም ወድጄዋለሁ። ትምህርት የግለሰቦችን ግንዛቤና ኃላፊነት የመሸከም አቅም ከፍ ስለሚያደርግ፣ ከፍተኛ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ነው። ትምህርት የሁሉም መንገድ ነው፡፡ የአስተሳሰብ መሰረትም ትምህርት ነው። ዶ/ር አብይ በዚህ ሃሳባቸው ልቤን ነክተውታል፡፡ ሁሌም ስጨነቅበት የነበረውን ነው የነኩልኝ፡፡
ብሔራዊ መግባባት እና እርቅ ተደጋግሞ የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ መግባባት ሲባል ምን ማለት ነው? እርቅስ ምንድን ነው? ማን ከማን ጋር ነው የሚታረቀው?
ማንኛውም ሰው መግባባትን መቀራረብን፣ መታረቅን ቢያነሳ፣ በጎ ነገሮች ስለሆኑ ጠቀሜታ አላቸው፡፡ እነዚህን በጎ እሳቤዎች ከዳር ለማድረስ የሚሰሩ ሁሉ በጎ እያደረጉ ነው እላለሁ፡፡ ለ18 ዓመታት ሳጠና እና ስከታተለው የነበረው አንዱ ጉዳይ፣ ይሄ የመግባባት ጉዳይ ነው። መተባበር፣ መተጋገዝ፣ መካተት አለመገለል፣ ስልጣን ለህዝብ የቀረበ መሆን የመሳሰሉት በጎ እሳቤዎች ናቸው፤ የመግባባት መርሆዎች፡፡ የእነዚህ ሃሳቦች መግነን ነው ዘለቄታ ያለው እርቅን የሚፈጥሩት፡፡ መግባባትና እርቅ፤ ከዚህ አንፃር ነው መተርጎም ያለበት፡፡ በጎ እሳቤን ለማጉላት፣ የቅሬታ ምንጮችን ማደብዘዝ ነው - የእርቅ መንገዱ፡፡
የፖለቲካ አደረጃጀቱ ከላይ ወደ ታች ሳይሆን ከታች መሰረት እየረገጠ፣ ወደ ላይ እየጠነከረ የሚሄድ መሆን አለበት፡፡ ይሄ ካልሆነ አመራሩ ሁሉ አሽከርና ሎሌ አይነት ነው የሚሆነው፡፡ የመግባባት ጉዳይ እነዚህን ሁሉ ያካትታል፡፡ ምክንያቱም የስር መሰረት ካልያዘና አፈንጋጭ ከሆነ፣ አፈር ሲባሉ ድንጋይ፣ ድንጋይ ሲባሉ ውሃ እንዳቀለቡት የሰናኦር ግንበኞች ነው የሚሆነው፤ አገሩ ሁሉ፡፡ መግባባትም መታረቅም፣ ከዚህ አንፃር ነው እኔ የምመለከተው፡፡ በጎ ነገርን ማቀንቀን ነው፤ ተስፋ ተፈላጊ ነገር ነው፤ ጨለምተኝነት ደግሞ ለዚህ እንቅፋት ነው፡፡
የዶ/ር አብይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣት እንዴት ይመለከቱታል?
በመጀመሪያ በመገናኛ ብዙኃን ያየሁት አቶ ለማ መገርሳን ነበር፡፡ አቶ ለማ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል መካከል ስለተፈጠረው ግጭት ንግግር ሲያደርጉ፣በጥንቃቄ ነበር ያዳመጥኩት፡፡ በንግግራቸው በጣም ነበር የተደመምኩትና የተደሰትኩት፡፡ ከክልል አልፈው፣ ኃላፊነት ተሰምቷቸው፣ ልክ እንደ አንድ ዳኛ፣ አመጣጥነው መናገራቸው አስደንቆኛል፡፡ በዚያው ቅፅበት ነው ሰውየው፤ ባህሪያዊ ፀጋ አላቸው ብዬ ያመንኩት፡፡ ወዲያው ነበር ፌስ ቡክ ገፄ ላይ ሙሉ ንግግሩን የለጠፍኩት፡፡ ሃሳባቸው ወርቅ ነበር። ተስፋዬን ነበር ያለመለሙት፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን ደግሞ የዶ/ር አብይን ንግግሮች፣ ከተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች፣ ማግኘትና ማዳመጥ ቻልኩ፡፡ ሰውዬው መልካም መልካሙን ነገር የማየት፣ የወደፊት ተስፋን አሻግሮ የመመልከትና ተስፋ ሰጪ ነገሮችን የመፈንጠቅ ልዩ ክህሎት አላቸው፡፡ በእንግሊዝኛም በአማርኛም ያደረጓቸውን የተለያዩ ንግግሮች ሰብስቤአቸዋለሁ፡፡ ሁሉም እንከን አልባ ንግግሮች ናቸው፡፡ በዚህ ሰውየውን ከጅምሩም ተስፋ ጥዬባቸው ነበረ፡፡ ከዚህ ተስፋ በመነሳት ልክ በፓርላማው ንግግር ሲያደርጉ፣ እኔም ንግግራቸውን ለፌስቡክ ተከታታዮቼ፣ በቀጥታ ሳደርስ ነበር፡፡ ንግግሩ በጎ በጎ ነገር ይበዛዋል፡፡ ተስፋ ፈንጣቂ ነበር፡፡ አቶ ለማ፣ ዶ/ር አብይ፣ አቶ ገዱ የያዙት ነገር ከባድ ትግል ነው፡፡ በነሱ አቅም ብቻ ከዳር ይደርሳል የሚል እምነት የለኝም። ያለንን ሁሉ አዋጥተን ልንረዳቸው ይገባል፡፡ ስልጣን ባይኖረን የዜግነት ግዴታችንን ተጠቅመን፣ ቢያጠፉ እየወቀስን፣ ቢያለሙ እያበረታን፣ የለውጡ አካል መሆን አለብን፡፡ ወቀሳው የሚያስፈልገው በድጋፍ ጭብጨባችን ደንዝዘው፣እንዳይዘናጉ ነው፡፡ ለነሱም ይረዳቸዋል፡፡
የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ  ፈተናዎች ምን ይመስልዎታል?
እኔ ብዙ ተስፋ ነው የሚታየኝ፤ ከተግዳሮቱ ይልቅ። ከኢህአዴግ ጎራ የነበሩ ሰዎች፣ ወደዚህ የለውጥ መንፈስ ያመጡናል ብዬ በህልሜም በእውኔም አስቤ አላውቅም፡፡ ከመጡበት ሂደት በላይ ከእንግዲህ የሚገጥማቸው ፈተና ያለ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ አላቸው፤ ይሄ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ አብዛኛው ከደገፋቸው ፈተና የሚመስሉትን በቀላሉ ማለፍ ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ ፍላጎቱ ያፈገፍጋል ተብሎ አይታሰብም። ትልቁ ፈተና  የኢትዮጵያን ህዝብ ልብ መግዛት ነው፡፡ ይህን ደግሞ አልፈውታል፡፡ በመሳሪያ ኃይል አይደለም የህዝብን ልብ የገዙት፡፡ በአንደበታቸው ነው፡፡ የመሳሪያ ኃይል ህዝብን ያሸብራል እንጂ  አያሸንፍም፡፡ ህዝብን ማሸነፍ የሚቻለው በፍቅርና በውዴታ ብቻ ነው። ህዝቡ ይህን ውጤት መጠበቅ አለበት፤ አለበለዚያ ሊቀለበስ ይችላል፡፡ እነሱ የያዙትን እንዲቀጥሉ ህዝብም እየደገፈ ወደ መጨረሻው ውጤት መሄድ አለበት፡፡ ህዝብ ነቅቷል፡፡ ደግ ደጉን የሚያበረክት ከሆነ፣ሁላችንም እንቅልፍ ወስዶን እናድራለን፡፡ ግን እንዳይቀለበስ አስተማማኝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ከጠ/ሚኒስትሩ  አመራር  ምን ይጠበቃል ይላሉ?
ካድሬያዊ የተበላሸ የአሰራር ሰንሰለትን ማጥፋት አለባቸው፡፡ ሃገሩን ማገልገል የሚፈልግ ምሁር ሞልቷል፡፡ ጨዋነት ደግሞ ወሳኝ ነው፤ ፖለቲካውን የጨዋ ያድርጉት፡፡ እነ ዶ/ር አብይ፤ በጨዋነት ፖለቲካውን እንደ ጀመሩት፣ ከላይ እስከ ታች የጨዋ ፖለቲካ ያድርጉት፡፡ ሌላውን ሁሉ ትተው ፖለቲካውን የጨዋ ያድርጉት፡፡ አመራሮች በህዝቡ የተመሰከረላቸው ጨዋዎች ከሆኑ፣ ቢማሩ ባይማሩ ግድ አይሰጥም፡፡       

   በሃገሪቱ ማንነትን መሠረት አድርገው የሚፈፀሙ ኢ-ሠብአዊ ድርጊቶችና መፈናቀሎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ያሳሰበው ሠማያዊ ፓርቲ፤ መንግስት ኃላፊነቱንም እንዲወስድ የጠየቀ ሲሆን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ፤ ከቤኒሻንጉል ተፈናቅለው ለወራት በባህርዳር ተጠልለው የሚገኙ ዜጎችን ሁኔታ እመረምራለሁ ብሏል፡፡
ጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ.ም ከ30 ዓመታት በላይ ከኖሩበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለጋንፎ ወረዳ የሠው ህይወት በጠፋበት ሁኔታ በሃይል የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆችን አስመልክቶ መግለጫ ያወጣው ሠማያዊ ፓርቲ፤ ማንነትን መሰረት አድርጎ የሚፈፀም በደል በአስቸኳይ እንዲቆም ለመንግስት ጥሪ አቅርቧል፡፡
በህዝቡ ላይ በደል ያደረሱ፣ ግድያ የፈፀሙና ያስፈፀሙ አካላትም ተጣርተው ተገቢውን ፍርድ እንዲያገኙ የጠየቀው ፓርቲው፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈፀመው መፈናቀል በመንግስት ባለስልጣናት ትዕዛዝ ነው የሚል ጥርጣሬ እንዳለውና መንግስት በባለስልጣናት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል፡፡ በመንግስት ሃላፊዎች ትዕዛዝ በተደጋጋሚ ማንነትን መሠረት አድርጎ የሚፈፀም ጥቃት አሣሣቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ያለው ፓርቲው፤ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እየተፈፀመባቸው ያሉ ማህበረሠቦችን አስፈላጊውን ከለላ በመስጠት መንግስት ከጥቃት የመከላከል ሃላፊነት አለበት ብሏል፡፡


            በ14 ዓመቱ ታዳጊ ላይ የብልት መሰለብና የአካል ጉዳት ያደረሰበት ተጠርጣሪ አልተገኘም

          ታዳጊው ለከፍተኛ ህክምና ወደ ጳውሎስ ሆስፒታል ይመጣል
                 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን፣ ድባጤ ወረዳ፣ ዝግህ ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ በካር ወንዝ በተባለ ቦታ ከብት በመጠበቅ ላይ የነበረው የ14 ዓመት ታዳጊ አበጠር ወርቁን ብልት በመስለብ ጥቃት ያደረሰበት ተጠርጣሪ እየተፈለገ ነው። የድባጤ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ንጋቱ ኢተፋ፤ ጉዳዩ ገና በምርመራ ላይ መሆኑንና ሰባት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ሰኞ ግንቦት 6 ቀን 2010 ዓ.ም በግምት ከቀኑ ከ7፡00 እስከ 8፡00 ባለው ጊዜ ውስጥ በካር በተሰኘው አካባቢ ታዳጊው ከብት ሲጠብቅ በነበረበት ወቅት አንድ ጫት በመቃም ላይ የነበረ ሰው አጠገቡ ሆኖ ለረዥም ሰዓት ሲያጫውተው እንደቆየና በድንገት ማጅራቱን ከመታው በኋላ ወድቆ ራሱን መሳቱን እንደነገራቸው የታዳጊው አጎት አቶ አያሌው አበረ ገልፀዋል፡፡ በአካባቢው ልማድ መሰረት የሰፈሩ ከብቶች የሚጠበቁት በተራ እንደሆነ የጠቆሙት የተጎጂው አጎት፤ በዕለቱም የከብት ጥበቃ ተራው የታዳጊው አባት እንደነበረና አበጠርም የአካባቢውን ከብቶች በመጠበቅ ላይ እንዳለ ጥቃቱ እንደደረሰበት ተናግረዋል፡፡
የፓዌ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ግርማ በየነ በታዳጊው ላይ ስለደረሰው የጉዳት መጠን ጠይቀናቸው ሲመልሱ፤ ህፃኑ ወደ ሆስፒታሉ ሲመጣ ብልቱ ተቆርጦ ፊቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቶና የመንጋጋ ስብራት ደርሶበት እንደነበር አስታውሰው፤ ለሶስት ቀናት በሆስፒታሉ ህክምና ቢደረግለትም በሆስፒታሉ ያለው ራጅ ብቻ በመሆኑና በሲቲ ስካን የጭንቅላቱ ሁኔታ መታዬት ስለነበረበት ወደ አንጎሉ ደም እንዳይፈስ በመስጋት ባህርዳር ወደሚገኘው ፈለገ ህይወት ሆስፒታል ሪፈር ተፅፎለት ለተሻለ ህክምና እንደሄደ ነግረውናል፡፡ የጉዳቱን መጠን በተመለከተም “ብልት ተቆርጦ ሲሄድ አንድ አካልን ማጣት ከባድ ጉዳት ነው፤ ፊቱም ላይ የደረሰው አደጋ ቀላል አይደለም” ያሉት ሜዲካል ዳይሬክተሩ፤ ሲቲ ስካን ተነስቶና ሙሉ ምርመራ ተደርጎ የሚገኘው ውጤት ነው በህክምና ሙያ በዋናነት የጉዳቱን መጠን የሚገልፀው ብለዋል፡፡ ታዳጊው በአሁኑ ሰዓት በባህር ዳር ፈለገ ህይወት ሆስፒታል ማህበራዊ አገልግሎት ዘርፍ በኩል አስፈላጊው ምርመራና ህክምና እየተደረገለት መሆኑን የልጁን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተሉ የሚገኙት በባህር ዳር ዩኒርቨሲቲ ረ/ፕሮፌሰር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ከፈለገ ህይወት ሆስፒታል ገልፀውልናል፡፡
የ14 ዓመቱ አበጠር ወርቁ ለእናቱ የመጀመሪያ ለአባቱ ሶስተኛ ልጅ እንደሆነ የገለፁት አጎቱ አቶ አያሌው አበረ፤ ምንም የማያውቅ ልጅ እንዲህ አይነት አሰቃቂ ጥቃት ሲደርስበት የወረዳው ፖሊስ የተወሰኑ ሰዎችን እያሰረ ከመፍታት ውጭ የተጠናከረ ምርመራ እያደረገና ትኩረት እየሰጠ አለመሆኑ እንዳሳዘናቸው ገልፀው ጉዳዩ በመንግስት ደረጃ ትኩረት አግኝቶ ህፃኑ ፍትህ እንዲያገኝና አጥፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
በፈለገ ህይወት ሆስፒታል ለልጁ ህክምናና ክትትል እያደረጉ የሚገኙት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የመጨረሻ አመት የቀዶ ህክምና ተማሪ ዶ/ር ሲሳይ ሙሉቀን በበኩላቸው፤ ህፃኑ የብልት መቆረጥ የጭንቅላትና የአይን ጉዳት እንዲሁም የጥርስ መውለቅና ተደራራቢ ጉዳቶች የደረሰበትና በስለት ፊቱ የተቆረጠ በመሆኑ የጉዳቱ መጠን ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው፣ በአፉና በአንገቱ አካባቢ ኢንፌክሽን የተፈጠረ በመሆኑ የአንቲ ባዮቲክ ህክምና እየተደረገለት ነው ብለዋል፡፡ ዶ/ር ሲሳይ አክለውም፤ ልጁ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየነቃ መሄዱን፣ በአተነፋፈሱ በኩል ትንሽ ችግር ስለገጠመው በኦክስጅን ታግዞ እየተነፈሰ መሆኑን ጠቁመው፤ ብልቱ ላይ ካቲተር ተገጥሞለት ህክምናው ቀጥሏል ብለዋል፡፡
ባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ የታዳጊውን ሙሉ ወጪ ሸፍነው ለማሳከም ቃል የገቡ ሲሆን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን ህፃኑ ጳውሎስ ሆስፒታል መጥቶ እንዲታከምና ወጪውን ሚኒስቴሩ እንደሚሸፍን መግለፃቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

 ባለፈው እትም ትዳርን ከመፍረስ ለማዳን ከሚረዱን ምክንያቶች አንዱን አስነብበናችሁዋል፡፡ የስነልብና ባለሙያዎች ትዳርን እንደአጀማመሩ ለማቆየት የሚረዱ በርካታ ጠቃሚ ነገሮችን የሚያማክሩ ሲሆን ለዚህ እትምም ለንባብ የተወሰኑትን መራርጠናል፡፡
አንድ መረጃ እንደሚጠቁመው በአሜሪካ 40-50% የሚሆኑ ትዳሮች የመፍረስ እድል ሲያጋ ጥማቸው በኢትዮጵያ ደግሞ በ30 አመት ውስጥ 45% ያህል ትዳር የመፍረስ እድል ያጋጥ መዋል የሚለው መረጃ የተገኘው ከ American Psychological Association ነው፡፡ ከሰሀራ በታች ባሉ 20/የአፍሪካ ሀገራት በ20/አመት ጊዜ ውስጥ ያለው ሁኔታ ሲታይ ትዳር ከመፍረስ ቆጠብ ያለ ነው ቢባልም ነገር ግን በትክክለኛው ጥናት ተደግፎአል ለማለት አይቻልም እንደ መረጃው እማኝነት፡፡
እንደአለምአቀፉ መረጃ ከሆነ ፍቺ የሚፈጸምባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከእነርሱም ውስጥ፡-
በትዳር ላይ መማገጥ፤
በገንዘብ አለመተማመን ወይንም አንዱ ለአንዱ በቂ ገንዘብ አለመስጠት፤
እርስ በእርስ ለመግባባት ችግር፤
ነጋ ጠባ በየእለቱና በየጊዜው መጨቃጨቅ፤
የሰውነት ቅጥ ያጣ ክብደት መኖር፤
አንዱ አንዱን የመናቅ፤ አስተዳዳሪ…ውሳኔ ሰጪ እኔ ነኝ የሚል ስሜት፤ እኩልነት ማጣት፤
እርስ በእርስ የመቀራረብ ችግር፤
ከሚገባው በላይ ነገሮችን የመጠበቅ፤
ካለእድሜ ጋብቻ፤
ልጅ አለመውለድ፤…ወዘተ
ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች ትዳር ጤናማ እንዳይሆን ሊያደርጉ ከሚችሉ መካከል ሲሆኑ መፍት ሔውን ለመፈለግ አስቀድሞ ግንዛቤው ቢፈጠር መልካም ነው ይላሉ ጥናት አቅራቢዎቹ፡፡
ባለፈው እትም ለትዳር መፍረስ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ አንዳንድ የተፈጠሩ ችግሮችን በሚ መለከት በምን መንገድ ማስወገድና ፍቅር እንደገና ማለት እንደሚቻል Mort-Fertel የተባሉት የስነልቡና ባለሙያ የጻፉትን አስነብበናችሁዋል፡፡ በዚህ እትም ደግሞ ትዳርን እንደጠበቀ ለማቆየትና ምናልባት ቢበተን ሊያስከትል የሚችለውን የጤና፤ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግር አስቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል ሌላው መንገድ መነጋገርና መነካካት ነው ይላሉ፡፡
መነጋገር እና መነካካት(Talk and Touch)
ባለሙያው እንደሚሉት አስቀድሞ በአንድ ነገር ግልጽ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ኑሮ ማለት በድርጊት እንዲሁም በንግግር አንዱ አንዱን በመነካካት የተደገፈ ነው፡፡ ለምሳሌም በ24 ሰአት ውስጥ ባልና ሚስቶች ምን ያህል መነጋገር እንዲሁም አንዳቸው አንዳቸውን በፍቅር መዳሰስ ይባቸዋል? ሁኔታውስ ምን ይመስላል? ለሚለው ሁልጊዜ ፊት ለፊት ተቀምጦ መነጋገር ወይንም ስራ በመፍታት አንዱ አንዱን መዳሰስ ይገባል ማለት አይደለም፡፡ ለዚህ ስርአት ወይም ህግ የለውም፡፡ እኔ እናገር ቁጭ ብላችሁ አድምጡኝ የሚያሰኝም አይደለም፡፡ ምናል ባትም በስልክ የድምጽ መልእክት ሊሆን ይችላል፡፡ አንተ/ቺ ስትናገር/ሪ የትዳር ጉዋደኛ ማዳመጥ ይችላል፡፡    
መንካት የተባለውም በንግግር ፈንታ በመንካት ተተካ እንጂ ከላይ ከተጠቀሰው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ ከሚወዱት ሰው ጋር ፍቅርን በመተቃቀፍ፤ ጸጉርን በማሻሸት ፤በመሳሳም በመሳሰሉት  የሚጋሩበት አይነት ነው፡፡ ይህ ምናልባትም በወሲብ ግንኙነት ጊዜ የሚደረገውን ሳይሆን በማናቸውም ጊዜ ፍቅርን ለመግለጽ የሚደረግ ነው፡፡
መነጋገር ሲባል በቀጥታ በእለት ተእለት ሕይወት ውስጥ ስለሚያጋጥም ነገር መሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌም…. ልጆቹን ከትምህርት ቤት አምጣ/ጪ…. የመብራት ወይንም የውሀ ክፍያ ክፈይ/ል… የመሳሰሉት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌም… ይህን ሕልም አየሁ …እኔ ይህንን ነገር እፈራዋለሁ/እወደዋለሁ…. ቀልድ ማውራት… በእለቱ ስላጋጠመ ነገር …የመሳሰሉት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
መነካካት ሲባልም …አንዱ አንዱ ትከሻ ላይ ደገፍ በማለት…ጸጉርን በመዳሰስ…ፊትን በመዳበስ …ሰውነትን መዳበስ  ….ማቀፍ …ሊሆን ይችላል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ተጋቢዎች በመካከላቸው የማይግባቡባቸው ነገሮች ካሉና አንደኛው ሌላውን በሚነካካበት ወይንም አስቂኝ በሆነ መልክ በሚያነጋግርበት ጊዜ ሌላኛው ወገን (ባል ወይንም ሚስት) ሊናደዱና ምላሹ የሚያስቆጣ ሊሆን ይችላል፡፡ Mort-Fertel የሚከተለውን የትዳር ልምድ ለንባብ ብለዋል፡፡
‹‹…አንድ ቀን እኔና ባለቤቴ በጋራ ቁጭ ባልንበት ለማናገርም ይሁን ለመንካት ስሞክር ተናደ ደችብኝ። እኔ ልዳብሳት ስሞክር እስዋ ሌላ ርእስ ታመጣና ወሬ ትጀምራለች፡፡ እኔ ምነው? የሚል ጥያቄ አነሳሁላት፡፡ የእስዋም መልስ የሚከተለው ነበር፡፡››
‹‹…እኔ በጣም ከባድ የሆነ በትዳር ሕይወታችን ያልተመቸኝ ነገር አለ፡፡ አንተ በቀላሉ ምንም እንዳልተፈጠረ በማስመሰል በመቀለድ በመነካካት ልታሳልፈው ትፈልጋለህ። ይህ ደግሞ ጭራሹንም ቀልድ ነው፡፡ አለችኝ፡፡ እኔም ጉዳዩ ምንድነው….እስቲ አስረጂኝ አልኩአት፡፡ እስዋም ከአሁን ቀደም የተነጋገርንባቸውን ቀላል ነገር ግን ማስተካከያ የሚፈልጉ ነገሮች እንደገና ነገረ ችኝ፡፡ አካሄድዋም እኔን እያታለልክ ነገሩን ችላ ብለኸዋል የሚል ነበር፡፡ እኔ ደግሞ የሚስተ ካከለውን ነገር በጋራ ተመካክረን እናደርገዋለን እንጂ የእኔ ብቻ ኃላፊነት አይደለም፡፡ ቢሆንም ደግሞ ፍቅራችንን ሊያደበዝዝ …አንዳችን በአንዳችን እንድንናደድ የሚያስችል መሆን የለበትም አልኩአት፡፡ በእውነቱ ባለቤቴ ይህንን አስተሳሰብ ከጭንቅላትዋ ለማስወገድ ጊዜ ፈጅቶባት ነበር። ስናገር አትስቅም፡፡ ስነካካት እጄን ትገፈትረዋለች፡፡ ስለዚህ ቢቸግረኝ የወሰድኩት እርምጃ የሚከተለው ነበር፡፡
‹‹…የምወድሽ ባለቤቴ …ምንም ሳትዘጊኝ በአስፈላጊው ጊዜ ሁሉ የምታነጋግሪኝ እና የማነጋግርሽ ከሆነ የምታቅፊኝ የምትነኪኝ ወይም ሳቅፍሽ ስነካሽ በአጸፋ ምላሽ የምትሰጪኝ ከሆነ በትዳርሽ ላይ አስገራሚ እና ጥሩ ለውጥ ታያለሽ፡፡ ይህ ካልሆነና እኔ ጥፋት ካለብኝ በፈለግሽው መንገድ እቀጣለሁ አልኩአት፡፡ ባለቤቴም ተስማምታ ፍቅር እንደገና ብለን ኑሮአችንን ቀጠልን፡፡››
አንድ ትንሽ እርምጃ ትልቅ ለውጥ ታመጣለች፡፡ ያሉት Mort-Fertel የሚከተለውን ምክር ሰጥተዋል፡፡  
ጥዋት ከመኝታህ ስትነሳ ከትዳር ጉዋደኛ ጋር አንድ ቁምነገር መጋራት እንዲሁም ቀልድ ቢጤ ጣል አድርጎ ተሳስሞ መለያየት ቀኑን ብሩህ ያደርገዋል ይላሉ የስነልቡና ባለሙያው፡፡ በእኩለ ቀንም ካለህበት/ሽበት በመሆን አዋዋልን መጠየቅ ስለቀጣዩ ጊዜ ፕሮግራም መነጋገር ያስፈል ጋል፡፡ ሁልጊዜ ቀልድ ይወራል ማለት ሳይሆን ቁምነገርም ማካፈል …ይሆናል ወይንም አይሆንም መባባልም ያስፈልጋል፡፡ የትዳር ጉዋደኛን እጅ በመያዝ ጉንጭን በመነካካት ትከሻን በመዳበስ በመደገፍ በመሳም በመሳሰሉት ሁኔታዎች ትዳር ሁልጊዜ እንዲታደስ ማድረግ ይቻ ላል፡፡ ምናልባትም ተገቢውን ትኩረት አላገኘሁም የሚል ስሜት ካለ በሆድ ይዞ ከማብሰልሰል ይልቅ በግልጽ በመነጋገር ትዳርን ከሚያጠቁር ነገር መከላከልና ማጽዳት ያስፈልጋል፡፡
Mort-Fertel  የትዳር ጉዋደኛሞች ሊያደርጉዋቸው የሚገቡ ወደ 50/የሚጠጉ ቁም ነገሮችን በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡ በጣም በጥቂቱ እናስነብባችሁ፡፡
በትዳር ጉዋደኛ ውሳኔ እምነት መኖሩን መግለጽ፤
የትዳር ጉዋደኛን ድንገት ከቢሮ ወይንም ከቤት በመሄድ መጎብኘትና ሳም ሳም በማድረግ መለየት፤
እለቱ ለትዳር ጉዋደኛ እንዴት እንደነበረ በኃላፊነት ስሜት መጠየቅ፤
የትዳር ጉዋደኛን በመለያየት ወይንም በመገናኘት ጊዜ እንዲሁም ከመተኛት በፊት መሳም፤
ባልተጠበቀ ጊዜ የትዳር ጉዋደኛን በመፈለግ ምንጊዜም እንደምታስባት/ቢው ማሳየት፤
የትዳር ጉዋደኛን ትከሻ ወይንም አንገት Massage ማድረግ ወይንም ማሸት፤
ከእራት በፊት ዳንስ ለማድረግ መገባበዝ፤
ችግርን ማዋየት እና ለሚሰጠው ምላሽ በፍቅር መንገድ ማመስገን፤
በመኝታ ጊዜ ባለትዳሮች እጃቸውን አንዳቸው ለአንዳቸው ሰጥተው ወይንም ተያይዘው ቢሆን እና የመሳሰሉትን መፈጸም የትዳር ጉዋደኛሞች ፍቅራቸው እንዲጸና ትዳርም እንዳይበተን ይረዳል፡፡  

• 736 ተጨዋቾች ይሳተፋሉ 1120 በመጀመርያ እጩ የቡድን ስብስብ በፊፋ ተመዝግበዋል፡፡
• 32 ቡድኖች በ10.43 ቢሊዮን ዩሮ የሚተመን የተጨዋቾች ስብስብ የሚገነቡ ይሆናሉ
• በዝውውር ገበያ የዋጋ ተመን ሊዮኔል ሜሲ ከአርጀንቲና 180 ሚሊዮን ዩሮ፤ ኪላን ማብፔ ከፈረንሳይ 120
ሚሊዮን ዩሮ ፤ ክርስትያኖ ሮናልዶ ከፖርቱጋል 120 ሚሊዮን ዩሮ
• ውድና ምርጥ 11 ተጨዋቾች ቡድን ከ900 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ያወጣሉ
• በተጨዋቾች ስብስብ ውዱ ቡድን ፈረንሳይ በ999.50 ሚሊዮን ዩሮ


    በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፉት 32 ብሄራዊ ቡድኖች እያንዳንዳቸው 35 ተጨዋቾች ያሉባቸውን የመጀመርያ እጩ የቡድን ስብስባቸውን ሰሞኑን ለፊፋ አስታውቀዋል፡፡ ብሄራዊ ቡድኖቹ በዓለም ዋንጫ የሚያሰልፏቸውን 23 ተጨዋቾች ያሉባቸውን የመጨረሻ የተጨዋቾች ስብስብ ውድድሩ ከመጀመሩ ከ10 ቀናት ቀደም ብሎ ማሳወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በትራንስፈር ማርከት ድረገፅ መሰረት በዓለም ዋንጫ በሚሳተፉ 32 ብሄራዊ ቡድኖች በመጨረሻ የተጨዋቾች ስብስብ የሚመዘገቡ 736 ተጨዋቾች በዝውውር ገበያው አጠቃላይ የዋጋ ተመናቸው እስከ 10.43 ቢሊዮን ዩሮ ነው፡፡ በዓለም ዋንጫው ሻምፒዮናነቷን ለማስጠበቅ በምትገባው ጀርመን ወሳኝ ይሆናል የተባለው ቶኒ ክሮስ፤ በአጥቂ መስመር ድንቅ ብቃቱን በማሳየት ለእንግሊዝ ብዙ ያገባል ተብሎ የሚጠበቀው ሃሪ ኬን፤ በቅርቡ ከገጠመው ጉዳት ካገገመ ብራዚልን በአምበልነት በመምራት ለ6ኛው የዓለም ዋንጫ ድል ያበቃታል ተብሎ የተወሳለት ኔይማር፤ በዓለም ዋንጫ ድል ስኬታማ በመሆን አርጀንቲናን ይክሳል የሚባለው ሊዮኔል ሜሲ፤ ከ2017 እኤአ ጀምሮ የዓለም ኮከብ ተጨዋች ሆኖ የሚገኘው ክርስትያኖ ሮናልዶ፤ ሊውስ ስዋሬዝ ከኡራጋይና በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ እና በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከፍተኛ አግቢነት የተሳካለት መሃመድ ሳላህ በኮከብ ተጨዋችነት እና በኮከብ ግብ አግቢነት እንደሚፎካከሩ እየተገመተ ነው፡፡ ሊሮስ ሳኔ ከጀርመን፤ ግራኔት ዣካ ከስዊዘርላንድ፤ ኬሌቺ ኢሄናንቾ ከናይጄርያ ፤ ማቲያ ቬሲኖ ከኡራጋይ፤ ማከስ ራሽፈርድ ከእንግሊዝ እንዲሁም ሮበርቶ ፈርሚሆ ከብራዚል በወጣት ኮከብ ተጨዋችነት የሚጠበቁ ሆነዋል፡፡ በየብሄራዊ ቡድኖቻቸው ባለመመረጣቸው፤ በጉዳት ምክንያት፤ በጡረታ በመሰናበታቸው እና ብሄራዊ ቡድኖቻቸው ባለመሳተፋቸው ደግሞ ዓለም ዋንጫው የሚያመልጣቸው ምርጥ ተጨዋቾች ጥቂት አይደሉም፡፡  ካሪም ቤንዜማና ሎረን ኮሰልኒ ከፈረንሳይ፤ አሌክስ ኦክስሌይ ቼምበርለይን፤ ጃክ ዊልሸርና ጆ ሃርት ከእንግሊዝ፤ ዳኒ አልቬስ ከብራዚል፤ማርዮ ጎትዜ ከጀርመን በመጀመርያው ተጨዋቾች ስብስብ  በብሄራዊ ቡድኖቻቸው ካልተጠሩት መካከል ይገኙበታል፡፡ ዝላታን ኢብራሞቪች ከስዊድን ዣቪ አርናንዴዝ ከስፔን በጡረታ ዓለም ዋንጫውን ከማይሳተፉ ተጨዋቾች የሚጠቀሱ ሲሆን እነ ሮሲ ከጣሊያን፤_እነ ሩበን ከሆላንድ ብሄራዊ ቡድኖቻቸው ለዓለም ዋንጫ ባለማለፋቸው ታላቁ የስፖርት መድረክ ያመለጣቸው ናቸው፡፡
ከፍተኛ የዋጋ ግምት ያላቸው ተጨዋቾች
ከ21ኛው የዓለም ዋንጫ ጋር በተያያዘ በዝውውር ገበያ ከፍተኛ የዋጋ ግምት ያላቸው ተጨዋቾች ከ1 እስከ10 ባለው ደረጃ በቅደም ተከተል ሲቀመጡ እንደሚከተለው ነው፡፡ ሊዮኔል ሜሲ ከአርጀንቲና 180 ሚሊዮን ዩሮ፤ ኪላን ማብፔ ከፈረንሳይ 120 ሚሊዮን ዩሮ ፤ ክርስትያኖ ሮናልዶ ከፖርቱጋል 120 ሚሊዮን ዩሮ ፤ ኬቨን ዴብርዋኒ ከቤልጅዬም 100 ሚሊዮን ዩሮ ፤ ኤዲን ሃዛርድ ከቤልጅዬም 100 ሚሊዮን ዩሮ ፤ አንቶኒዮ ግሬዝማን ከፈረንሳይ 100 ሚሊዮን ዩሮ ፤ ፊሊፕ ኩቲንሆ ከብራዚል 90 ሚሊዮን ዩሮ  ፤ ፖል ፖግባ ከፈረንሳይ 90 ሚሊዮን ዩሮ ፤ ሉዊስ ስዋሬዝ ከኡራጋይ 85 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም ሮሜሉ ሉካኩ ከቤልጅዬም በ85 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡
በ80 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመናቸው ዴል አሊ ከእንግሊዝ፤ ሮበርት ሎውንዶውስኪ ከፖላንድ፤ቶኒ ክሮስ ከጀርመን፤ ኡስማን ዴምቤሌ ከፈረንሳይ፤ መሃመድ ሳላህ ከግብፅ እንዲሁም ራሂም ስተርሊንግ ከእንግሊዝ ይጠቀሳሉ፡፡ በ75 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመናቸው ደግሞ ሊሮይ ሳኔ ከጀርመን፤ ሰርጂዮ አግዌሮ ከአርጀንቲና እንዲሁም ኢስኮ ከስፔን  ሲሆኑ በ70 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመን ደግሞ ሳል ኑጎዌዝ ከስፔን፤ ኮኬ ከስፔን ፤ ገብሬል ጂሰስ ከብራዚል፤ ክሪስትያን ኤርክሰን ከስዊዘርላንድ እንዲሁም ጎንዛሎ ሄግዌን ከአርጀንቲና ይገኙበታል፡፡
ከዚህ በታች የቀረበው ደግሞ በዓለም ዋንጫ ከሚሰለፉ 736 ተጨዋቾች  መካከል በክለብ ደረጃ በሚያገኙት ሳምንታዊ ደሞዝ ከ1 እስከ 10ኛ የሚኖራቸው ደረጃ ነው፡፡
ኔይማር (ብራዚል) 509.26 ሺ ዩሮ በሳምንት
ክርስትያኖ ሮናልዶ (ፖርቱጋል) 421.6ሺ ዩሮ  
ሊዮኔል ሜሲ (አርጀንቲና)421.6ሺ ዩሮ  
ሜሱት ኦዚል (ጀርመን) 403.75 ሺ ዩሮ  
ኪላይን ሚባፔ (ፈረንሳይ) 357ሺ  ዩሮ  
ሊውስ ስዋሬዝ (ኡራጋይ) 331.5 ሺ ዩሮ  
ፖል ፖግባ (ፈረንሳይ)  331.5 ሺ ዩሮ  
ሰርጅዮ አግዌሮ (አርጀንቲና) 254.15 ሺ ዩሮ  
ቶኑ ክሮስ (ጀርመን) 229.5 ሺ ዩሮ  
ሰርጂዮ ራሞስ (ስፔን ) 229.5 ሺ ዩሮ  
ባለ ከፍተኛ ዋጋና  ምርጥ 11
የ21ኛው ዓለም ዋንጫ ባለ ከፍተኛ ዋጋና  ምርጥ 11 ተጨዋቾች ቡድን ከ900 ሚሊዮን ዩሮ በላይ እንደሚያወጣ በድረገፁ ያሰፈረው www.transfermarkt.co.uk ነው፡፡ ትራንስፈርማርከት  የዓለም እግር ኳስ የተጨዋቾች ዝውውር ገበያ ታሪክ፤ተመንና የዋጋ ውጣውረድ በማስላት የሚሰራ ታዋቂ ድረገፅ ነው፡፡ የዓለም ዋንጫ ባለ ከፍተኛ ዋጋና ምርጥ 11 ተጨዋቾች  ድረገፁ የመረጠው በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፉት 32 ብሄራዊ ቡድኖች ከሚያሰልፏቸው 736 ተጨዋቾች ነው፡፡ ይህ ቡድን አሰላለፉ 4-3-3 ወይምን 4-3-2-1 እንደሚሆን ድረገፁ ቢያመለክትም ዋና አሰልጣኙ ማን እንደሆነ ግን አልጠቆመም፡፡  
ከዚህ በታች ከ900 ሚሊዮን ዩሮ በላይ የሚያወጣው ቡድን አባላት የቀረበ ሲሆን በመቀጠል ደግሞ የዓለም ዋንጫውን ከፍተኛ የዝውውር ገበያ የዋጋ ተመን  በሚሊዮን ዩሮ ያስመዘገቡ  ተጨዋቾችን ያገኛሉ፡፡
ግብ ጠባቂ
ዴቪድ ዴ ጊያ (ስፔን)    50,00 Mill. €
ተከላካዮች
ማርኩዊኖስ (ብራዚል) 55,00 Mill. €
ራፋኤል ቫርኔ (ፈረንሳይ)     40,00 Mill. €
ማርሴሎ  (ብራዚል)    40,00 Mill. €
ዳንኤል ካርቫሃል (ስፔን)    45,00 Mill. €
አማካዮች
ፖል ፖግባ (ፈረንሳይ)90,00 Mill. €
ቶኒ ክሮስ (ጀርመን) 80,00 Mill. €
ኬቨን ዴብርዋኒ (ቤልጅዬም) 110,00 Mill. €
አጥቂዎች
ክርስትያኖ ሮናልዶ (ፖርቱጋል) 120,00 Mill. €
ሊዮኔል ሜሲ (አርጀንቲና) 180,00 Mill. €
አንቶኒዮ ግሪዝማን (ፈረንሳይ) 100,00 Mill. €

ጥንት ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ዐረብ ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡ የከሰሱት ሶስት ሴቶች ናቸው፡፡ ያለአግባብ ፈቶናል፣ በድሎናል፣ ብለው ነው አቤቱታ ያቀረቡት፡፡
ዐረቡ ቀርቦ እያንዳንዳቸውን፤ “ለምን እንዳባረርካቸው አስረዳ?” ተባለ፡፡
ዐረቡም፤
“የመጀመሪያዋ ሚስቴ ጠዋት ማታ ጭቅጭቅ አበዛችብኝ!” አለ፡፡
“ምን ብላ ጨቀጨቀችህ?” አሉ ዳኛው፡፡
“ነገ ትፈታኛለህ፤ አላምንህም ትላለች፡፡ ሲሰለቸኝ እንደውም ‹ዛሬ ነው የምፈታሽ› ብዬ አስወጣኋት!”
“መልካም፡፡ ሁለተኛዋንስ?”
“ሁለተኛዋ ደግሞ የትላንትናዋን ሚስትህን እንዴት ፈታሃት? እያለች ነጋ - ጠባ ትነተርከኛለች፡፡ ‹አንቺ ስለትላንት ምን አገባሽ? የዛሬን በሰላም ኑሪ› ብላት አሻፈረኝ አለች፤ አባረርኳት!”
“ሶስተኛዋስ?”
“እሷ ደግሞ ‹ለነገ አታስብም› ትለኛለች፡፡ ‹የዛሬን መደሰት ብቻ ነው ፍላጎትህ፡፡ ነገም እኮ መኖር አለብን› ትላለች፡፡ ‹ዝም ብለሽ የዛሬን ተደሰች› ብላት እምቢ አለች - አባረርኳት!”
ዳኛው የሚስቶቹንም ቃል ከሰሙ በኋላ፣ “ፍርድ ቤቱ ሁኔታውን ካየና ግራ ቀኙን አመሳክሮ ከመረመረ በኋላና በተለይም ለማንኛዋም ባለቤትህ ምንም ንብረት አለማካፈልህን በማመንህ፣ አሁን ለሁሉም ካሳ ክፈል ብትባል ስለሚከብድህ፤ ሶስቱንም አግብተሃቸው እንድትኖር ተወስኗል!”
ዐረቡም፤
“ክቡር ፍርድ ቤቱ ትላንትን፣ ዛሬና ነገን አግብተህ ኑር ነው የሚለኝ?”
“አዎን፡፡ ውሳኔው እንደዚያ ነው፡፡”
“ባይስማሙልኝስ?”
“እሱን ስንደርስ እናየዋለን!”
“ነገም አላችሁ ማለት ነው?”
“ፍርድ ቤቱን አትዳፈር! የታዘዝከውን ፈፅም” አሉ ዳኛው በቁጣ፡፡
*   *   *
ፍትህና የፍትህ አካላት ነገር ሁሌም እንዳሳሰበን አለ፡፡ የተከማቹ ፋይሎች ጉዳይ፣ የቀጠሮዎች መራዘም ልማድ፤ እንደጤናማ ሂደት መቆጠር ከጀመረ ዘመናት አልፈዋል፡፡ “የፍርድ ቤት ሙግት አለብኝ” ይሉ የነበሩት አያት ቅድመ - አያቶቻችን ህይወት ዛሬ ይታያል ማለት ጊዜና ሁኔታን ያላገናዘበ ትዝብት ሆኖ ይሰማናል - anachronistic እንዲሉ፡፡ ያም ሆኖ ወደ ትላንት ተመልሰን እየኖርን ነው ባንልም፣ የትላንት ድባብ ስር እንድንጠለል የሆንን ይመስላል፡፡ የጥንት ፍርድ ቤቶች ዋና ሥራ የመሬት ሙግት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ዳኞች ‹በጓሮ በር ሙክት ያስጎትታሉ›፤ ጉቦና እጅ መንሻ ምስሳቸው ነው ይባላል፡፡
“ተወኝ ዳኛ አዳኜ፣ የበግ መግዣም የለኝ እጅ እጄን የሚያዩ ብዙ ልጆች አሉኝ” ተብሎ የተገጠመው ቢቸግር ነው፡፡ ዛሬ ስሙ ሙስና የተባለው ጉቦ፤ የቤት ስሙ “ቢዝነስ”፣ “ኮሚሽን”፣ “የሥራ ማንቀሳቀሻ - ጉዳይ ማስፈፀሚያ” መሆኑ አይገርምም፡፡ “ጠበቃ ማንን ያዝክ?” እገሌን። “በጣም ጥሩ ሰው ይዘሃል፡፡ እሱ ዳኞቹን አሳምሮ ያውቃል!” ሙስና ፈርጁ ብዙ ነው፡፡ የፖሊስ ጣቢያ እስረኛ ስልኩ ተወስዶበት፤ በፖሊሱ ሞባይል ወደዘመዶቹ ለመደወል ብዙ ብር የሚከፈልበት አገር ፍትሕ እንዴት እንደሚገኝ ግራ ይገባል፡፡ ይህ ማለት ግን ሀቀኛና ጠንካራ አካላት የሉም ማለት አይደለም -ይዋጣሉ ነው ችግሩ! የሚገርመው በየመስሪያ ቤቱ ሲዘርፍ የከረመው ሁሉ አንደኛ የፍትህ ተቆርቋሪ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ ዙሪያ - ገባው፣ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ “ሌባ! ሌባ!” እያለ እየጮኸ ሳር - ቅጠሉን የሚግጥ ነው! ከቤተ - ሰባዊ የኮንትሮባንድ ንግድ ጀምሮ እስከ ኩባንያዊ ሽቀላ ድረስ አገሩን ያምሳል፡፡ ዛሬ ለበላይ አካል የሚያስፈልገው ጥያቄ የት ቦታ ሙስና አለ? ሳይሆን፤ የት ቦታ ሙስና የለም? የሚለው ነው፡፡ የመፍትሄው ቁልፍ ጥያቄ፤ የበላይ አካልን እገሌ ከእገሌ ሳይሉ መፈተሽ ነው፡፡ ሀቀኛ ጥናት ማካሄድ ነው። በሽርክና የተገባባቸው ንግዶችን፣ የኮንስትራክሽን እንቅስቃሴዎችን፣ በልማት ስም የሚሰሩ ደባዎችን ደፍሮ ማጣራትና ማጥራት ነው! አንድ ፀሐፊ እንደጠየቀው፤ “ይሄ የበላይ አካል ማለት የብዕር ስም ነው እንዴ?” ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ የበላይ አካል ምስጢር መሆን የለበትም፡፡ በተማሪው ለመተማመን፣ አስተማሪውን መመርመር ነው፡፡ የፍትህ የበላይ አካላት፣ የኢኮኖሚ የበላይ አካላት፣ የፖለቲካ የበላይ አካላት፣ የትምህርት የበላይ አካላት … ሁሉም የበላይ ጠባቂ አላቸው፡፡ ሥረ - ነገራችን እንግሊዞች እንደሚያቀርቡት ጥያቄ “Who guards the guards?” ዓይነት ነው፡፡ “ጠባቂዎቹን ማን ይጠብቃቸዋል?” እንበልና ላዕላይ ጠባቂውንም በጥበብ እንመርምር፡፡

ሁሴን አዳል መሐመድ (ዶ/ር)

    ብሔር ወይስ ብሔረሰብ?
የቀበሌ፤ ወረዳ፤ ዞን ወዘተ ሕዝብ፤ ሕዝብ ነው፤
የብሔረሰብ ሕዝብ፤ ሕዝብ ነው፡፡
የብሔር ሕዝብ፤ ሕዝብ ነው፤
የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ሕዝብ ነው፡፡
ሕዝብ = አገር
አገር = ሕዝብ
ብሔር/ብሔረሰብ ሕዝቦች እያሉ በደፈናው ማነብነብና መጻፍ በአገራችን የተለመደ ነገር ሆኗል፡፡ የማህበረሰባዊ ጽንሰ ሓሳብ መግለጫዎች የሆኑት ሁለቱ ቃላት፤የአገራችን ፖለቲካ ንድፈ-ሓሳብ ማጠንጠኛ እንዲሆኑ በመደረጉ የማንም ባለ ወቅት ፖለቲከኛ ሰው፤ የፖለቲካ አፍ መፍቻ ይሁኑ እንጂ ከአገራችን ሕዝብ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር በእነዚህ ሁለት ቃላት መኻል ያለው አንድነትና ልዩነት በትክክል የሚታወቅ አይመስልም፡፡ ይህ ሆኖ እያለ ግልጽ ካልሆነ ጽንሰ-ሓሳብ ላይ ተነስቶ ቃላቱን የሕገ መንግሥት አንቀጽ አድርጎ እስከ መሄድ የተደረሰው በድፍረት መሆኑ በእጅጉ ያስገርማል፡፡
ብሔር/ብሔረሰብ፤ የማርክሲስት/ሌኒኒስት የማህበረሰብ ዕድገት ታሪክ፣ ቁስ አካልነት፣ ፍልስፍና ጽንሰ-ሐሳብ ሲሆን አንዱ ወይም ሌላው የሚገለጸው ከህብረተሰብ ታሪክ ወቅት ጋር ባለው ተዛምዶ፣ በአንድ የተወሰነ የታሪክ ወቅት የሚኖር ማህበረሰብ በማለት እንጂ በግል ስሜት አይደለም፡፡ ብሔረሰብን በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ማለትም በፊውዳላዊ ወይም ቅድመ ካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ደረጃ ውስጥ የሚገኝ ማህበረሰብ እንደሆነ ሲገልጹ፤ ብሔር ደግሞ ከፊውዳሊዝም መክሰም በኋላ ከካፒታሊዝም ማደግ ጋር ተያይዞ የተዋሃደና በከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ያለ፣ የጋራ ኢኮኖሚ ሕይወት ያለው ማህበረሰብ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ ጽንሰ-ሐሳብ አኳያ አሁን በአንድ ክፍለ ዘመን እየኖሩ ካሉት የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ሕዝቦች የትኛው፣ በየትኛው የታሪክ ወቅት እየኖረ ነው? ኢትዮጵያ አሁን በስንት የታሪክ ወቅት ውስጥ ትገኛለች? ብሔሩ የየትኛው አስተዳደር ክልል ሕዝብ ነው? ብሔረሰቡስ? ደቡብ፤ ኦሮሞ፤ አማራ፤ ትግራይ፤ ሱማሌ፤ አፋር፤… ብሔር ወይም ብሔረሰብ ለመሆን አሟልተው የተገኙት መስፈርት ምንድን ነው? የትኛው በፊውዳሊዝም ስልተ-ምርት ይገኛል? ወደ ካፒታሊስት ስልተ-ምርት እየገሰገሰ ያለ ወይም የሚያደርገውን ሽግግር ያጠናቀቀው የትኛው ነው? እያንዳንዱ መልስ የሚያሻው ጥያቄ ነው፡፡ ስለ ፌደራሊዝምና ዲሞክራሲያዊ ብሔረተኝነት የሚኖረን ዕውቀት፣ ከማነብነብ እልፍ እንዲል ከፈለግን፣በሁለቱ ላይ የጠራ ግንዛቤ መያዝ ያስፈልገናል፡፡
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (ቀ.ኃ.ሥ.ዩ) ታጋይ ተማሪዎች የተራገበው፣ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ያልተመሰረተው የማርክሲስት/ሌኒኒስት፣ የብሔር/ብሔረሰብ ጽንሰ-ሓሳብ፣ የሜዳ ትግል ስልት የመረጡትን ወጣቶች፣ በአገራችን ታሪካዊ ጠላቶችና ባልነቃ ብሶተኛ ሕዝብ ድጋፍ፣ ለሁለት አስርተ ዓመታት ጫካ ውስጥ አክርሞ፤ በጦር ሜዳ ያልተሰውቱን ታጋዮች፣ ለቤተ መንግሥት ከማብቃቱ በስተቀር በጽንሰ-ሓሳቡ ላይ የጠራ ግንዛቤ ባለመያዙ፣ ለችግሩ መቋጫ የሚሆን መፍትሔ እስከ አሁን አልተገኘም፡፡ አገራችን ሌላ ዙር ትርምስ የሚጠብቃት ይመስላል፡፡ በደርግ ላይ ድል መቀዳጀት፣ አጼ ምኒልክ ቤተመንግሥት ካስገባ በኋላ፣ ቀ.ኃ.ሥ.ዩ ተጠንስሶ፣ ጫካ ውስጥ ተደፍድፎ፣ የፈላውን ያልጠራ ጽንሰ-ሓሳብ የመንግሥት/ገዥ ፓርቲ የፖለቲካ ሰነድ በማድረግ፣ ማንኛውንም ሓሳብ ሳያቅማሙ የሚቀበሉ ዜጎችን ከየብሔረሰቡ ተወላጆች አስጠግቶ በመጋት፣ በእነርሱ መንኩራኩርነት ለማስፋፋት የተደረገው የትግል እንቅስቃሴ፤ ሕዝባችንን ለእንግልት፤ አገራችንን ለውርደት አጋልጧል፡፡
በቅጡ ካልተረዱት ጽንሰ-ሓሳብ በመነሳት የጠባብ ብሔረተኝነት ትግል አስፈላጊነትን በእንጭጭ አእምሯቸው በመቀበል፣ ለአገራችን ታሪካዊ ጠላቶችና የገዥ መደብ ዝንባሌ ለነበራቸው ቡድኖች ፍላጎት ማሳኪያ በረሐ ገብተው፣ የተደናበረው ትግል ትሩፋት ተቋዳሽ ሆነው ከቆዩ በኋላ፣ ዘግይተውም ቢሆን ሁኔታዎችን በሰከነ አእምሮ ማገናዘብ የቻሉ፣ ራሳቸውን ወደ ዳር ያገለሉ፣ አንዳንድ የቀድሞ ወጣቶች/የአሁኖቹ አዛውንቶች፣ ላሳለፉት የዜሮ ድምር የበረሐ ትግል ፍጻሜ፣ በየተራ እየተጸጸቱ ንስሐ በሚገቡበት በአሁኑ ጊዜ፣ “ጉድ ሳይሰማ አይታደርም” እንዲሉ፣ የአገራችንን የመከራ ዘመን ለማራዘም መጥበብ በማይችል ብሔረሰብ ስም ጭምር የጠባብ ብሔረተኝነት ትግል ጥንስስ የሚጠነስሱ፣ የማህበረሰብ ክፍሎች ብቅ ብቅ ማለታቸው አስደንጋጭ ነው፡፡
እዮሃ! እዮሃ!
የጎመኑ ዘመን ውጣ፤ የጮማው ግባ እንዲሉ፤
የብሔረሰብ ፓርቲ ዘመን ይሻር፤
የርዕዮተ ዓለም ፓርቲ ዘመን ይንገሥ፡፡
--እንደ ማለት፣ የጠባብ ብሔረተኝነት ገመድ በመጓተት፣ አገራችን ከአንዱ የዘመን አሮንቃ ወጥታ በሌላ የዘመን አሮንቃ! ውስጥ እንድትርመጠመጥ ይተጋሉ፡፡ በወዳጅና ጠላትነት ሁልጊዜ በደም ስንፈላለግ እንድንኖር ይሻሉ፡፡ ቀጥሎ የቷን “ብሔር”፣ “ህብረተሰባዊ ዕረፍት ለማሳጣት” ነው፡፡ እሺ ቀጥሎስ? ወደ ቀድሞ ገናናነታችን የሚመልሱን ሠረገላዎች፣ የብሔረሰብ ፓርቲዎች ይሆኑ እንዴ? በርካታ ብሔረሰቦች ሕዝቦች በሚኖሩባት ውድ አገራችን፣ የሚፈጠር የፖለቲካ አስተሳሰብ ቅኝት፣ ሁሉንም የአገሪቱን ዜጎች ሊያሳትፍ ከሚችል የጋራ ርዕዮተ ዓለም አውድ ይልቅ በብሔረሰቦች ልዩነቶች ላይ እንዲመሰረት የሚደረግበት ምክንያት ምንድን ነው? እርግጥ ነው፤ የፖለቲካ አስተሳሰብ ቅኝትን በርዕዮተ ዓለም አውድ ላይ እንዲያተኩር ማድረግ የፖለቲከኛን የአስተሳሰብ ከፍታና በሰፊ የፖለቲካ ስነ ምህዳር ውስጥ በነጻ መወዳደርን ይጠይቃል፡፡ ይህ አቅም በሌለበት፤ ዘወትር በኪራይ ሰብሳቢነት ለመኖር በጠባብ ብሔረተኝነት የፖለቲካ አንቀልባ መታዘል፣ አዋጭ የፖለቲካ አማራጭ ይሆናል፡፡   
ኤሎሄ ኤሎሄ፤
ለማ ሰበቅታኒ፡፡
ከእንግዲህ ወዲያ የብሔረሰብ ፓርቲ ስህተት፣ ያለፈ ታሪካችን አካል ሆኖ መቅረት እንጂ መቀጠል የለበትም። ምንም እንኳ ለጠባቦች የኪራይ መሰብሰቢያ፣ጊዜያዊ የንግድ ፈቃድ ወረቀት ሆኖ ቢያገለግልም ያለፈው ስህተት ያስከተለው ዕዳ፣ የብሔረሰቡ ሕዝብ ዕዳ ብቻ ከመሆን አልፎ ለሌሎች ብሔረሰብ ሕዝቦች በአጠቃላይ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተረፈ የጋራ ዕዳ ነው፡፡ እርግጥ የአማራ ብሔረሰብ ሕዝብ በይበልጥ ስለመጎዳቱ አስረጂዎች በግልጽ እየቀረቡ ይገኛል፡፡
የብሔረሰብ ፓርቲ፤ ዘመን ተሻጋሪ፣ መልካም ውርስ አይደለም፡፡ ጠባቦችን ላለፈው ስህተታቸው ንስሐ ለማስገባት ግፊት ማድረግ እንጂ ፈለጉን በመከተል አዳዲስ የብሔረሰቦች ፓርቲዎችን መፍጠር ለምንወዳት አገራችን፤ ኢትዮጵያ አንድነት መቀጠል አይረባንም፡፡ አገራችን ተነጣጥለው የቆሙ ብሔረሰቦች ሕዝቦች የሏትም፡፡ ለምሳሌ በአማራ ሕዝብ ስም ጠባብ የብሔረሰብ ፓርቲ አቋቁሜ እታገላለሁ የሚል ቡድን ቢነሳ፣ ሁኔታው ከማስደንገጥ አልፎ ያስፈራል፡፡ ይህ የማይቀር የሚሆነው ሌሎች ከጠባብነት ሐዲድ መውጣት ተስኗቸው፣ ያንኑ የጠባብነት ገመድ ነክሰው ባሉበት እየረገጡ ከቀጠሉ ብቻ እና ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡ ያኔ! ለአማራ ሕዝብ መጥበብ የሕልውና ጥያቄ ስለሚሆንበት የጠባብ ቡድን ዓላማን መሸከም የግድ ይላል፡፡ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ፤ ለኢትዮጵያ አንድነት ዘብ የሚቆም ትምክተኛ ሕዝብ በመባል በጠባብ ቡድን ኃይሎች ሲጠራ የኖረ ታላቅ ሕዝብ፤ እሱነቱን እንደ ባዶ ስልቻ አቅልሎ ወደ እዚህ ዝቅተኛ ደረጃ መድረስ ግድ ከሆነበት የጠባብነት ትግሉን ፈር ለማስያዝ፣ በመጀመሪያ የአማራ ሕዝብን አገር ወሰን ዳርቻ ማስመር፤ ብሎም ከዳር ድንበሩ ውጭ ስለሚኖረው የአማራ ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ሁነኛ አቅጣጫ ማስቀመጥ ግድ ይለዋል፡፡
“የእኛ ቡድን ብሔር መሬት ያን ሁሉ ያጠቃልላል”፤ “ጨቋኟ የአማራ ብሔር፣ ህብረተሰባዊ ዕረፍት አታገኝም” እያለ ሲወተውት የነበረ ጠባብ ቡድን፤ በምስጢር የነደፈው የአስተዳደር ክልሎች አወቃቀር ለአገራችን እንደ ማይበጅ አንዳንድ ነባር የቡድኑ አባላት በጸጸት ስሜት ምስክርነት እየሰጡ ነው፡፡ የኤርትራ ከእናት አገሯ መገንጠል፤ አገራችን የባህር በር ማጣት፣ ኢሕአዴግ የፈጸመው ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት/ንዝህላልነት መሆኑን ሳያወላውሉ በማውገዝ፣ ላለፈ ክረምት ቤት ከሚሠሩ ነባር ታጋዮች ጎን ለጎን፣ ልቦና የማይገዙ ደቀ-መዝሙሮች መኖራቸው ያስገርማል፡፡
ፌደራሊዝምና ዴሞክራሲያዊ ብሔረተኝነት፤ “የአገራችን ሕልውናና የአብሮነት መሰረቶች” ናቸው የሚለውን ጥርት ያለ ሐቅ የሚክድ ዜጋ ያለ ይመስል፣. ዘወትር ንግግር በማሳመር፣ እምቧ ከረዩ የሚሉ አንዳንድ የመንግሥት/የገዥ ፓርቲው ባለስልጣናት አሉ፡፡ ችግሩ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ አለመተግበሩ ስለመሆኑ መናገር ድክመት መስሎ ይታያቸዋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ብሔረተኝነት ያለ መከባበርና መዋደድ አይመጣም፡፡ በፌዴራሊዝምና ዴሞክራሲያዊ ብሔረተኝነት ዙሪያ በአገራችን የነበረው ያለፈ ዘመን መልካም ገጽታ፤ በአሁኑ የአስከፊ ዘመን መስታወት ውስጥ በግልጽ እየታየ ለመሆኑ ከዚህ በላይ ማስረጃ የለም፡፡ እስካሁን ድረስ በአገራችን የሰፈነውን የአተገባበር ጉድለት መንስዔ፤ ዓላማና ግብ እንደዚሁም ፋይዳ የሚያውቁት ምስጢረኞቹ ብቻ ነበሩ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የምስጢሩ እሽግ ፖስታ ተከፍቶ በመነበቡ ምክንያት ምስጢሩ ለአብዛኛው ዜጎች ግልጽ ሊሆን በመቻሉ፣ ሕዝቡ በዕውቀት ላይ ለተመሰረተ ትግል ተነሳስቷል፡፡
ባለፉት 27 ዓመታት አገራችን ክፉኛ አዘቅት ውስጥ የወደቀችበት ችግር መንስኤው የፌደራሊዝም ቅርጸ-መንግሥት መዘርጋቱ ሳይሆን የፌደራሊዝም ስርዓቱን ያዋቀርንበት መርህ-አልባ የአወቃቀር ንድፍ ነው፡፡ ጥቂት መገለጫዎችን እስቲ እንይ፡
አንዳንዴ ቋንቋን ወሳኝ መስፈርት በማድረግ ማህበረሰቦች የምንነት ጥያቄ ይዘው እንዲቀርቡ በማድረግ ለቀረበ የምንነት ጥያቄ አስቸኳይ ምላሽ ይሰጣል፤ አዲስ የአስተዳደር ክልል ወዲያውኑ ይፈጠራል ወይም ማህበረሰቦች ወደ አንዱ ክልል ይካተታሉ፤
ቋንቋውን ባይችልም ተካትቶ ሲያበቃ፣ ቋንቋ እንዲማር የሚወሰንበትም አለ፤
ቋንቋው ጭራሽ በመጥፋቱ የተነሳ በሚናገሩት ቋንቋ ብቻ ከሌላው ምንነታቸውን መለየት የሚያስቸግሩትን የማህበረሰብ ክፍሎች፤ በመንግሥት ድጋፍ፤ የምንነት መጠሪያ ስም አውጥተው ከነባር የማህበረሰብ ዘውግ እንዲለያዩ ይደረጋል፤  
የምንነት ጥያቄ ማቅረብ የሚያስጠይቅበት እና የምንነት ጥያቄ እንዲቀርብ ግፊት የሚደረግበት ክልል ጎን ለጎን አለ፡፡
“ከልጅ ልጅ ቢለዩ በሞት ይለዩ” የሚሉ ማህበረሰቦች ደግሞ ጆሮ ዳባ ልበስ ይባላሉ፡፡
በማይመስለን ክልል ተቀርቅረናልና፣ መልሱን፣ የሚሉ ማህበረሰቦች ደግሞ መከራ ይከፍላሉ። ማህበረሰቦቹ ይመስለናል የሚሉት ክልላዊ አስተዳደር፤ አንዴ አሳልፎ ለሌላው ስለሰጣቸው ፊት ይነሳቸዋል፤ የወሰዳቸው ክልል ደግሞ መብታቸውን በመጠየቅ፣ ክፉኛ አሳጡኝ በሚል “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ድርቅና ነገሮችን ሁሉ ያጠብቅባቸዋል፡፡ መብትን መጠየቅም ስለሚያስጠይቅ ማህበረሰቦቹ በ”እከክልኝ፣ ልከክልህ”ተደጋግፎት ይሰቃያሉ፡፡
ማህበረሰቦቹ በሰሚ ዕጦት፣ ከሁለት የወጣ ጎመን ሆነው በመንከራተት፣ከመጠውለግ ወደ መድረቅ ተጠግተዋል፡፡ የወልቃይት፤ የራያ ሕዝቦች ችግር ይኸው ነው፡፡
ብሔረሰባዊ ምንነት ተፈጥሯዊ የሆነና ማንኛውም ሰው ከተገኘበት ብሔረሰብ ጋር አብሮ የሚወለድ ወይም በማህበራዊ መስተጋብር በሚፈጠር አጋጣሚ ወይም በምርጫ የሌላውን ብሔረሰብ ምንነት በመያዝ ሊገኝ እንደሚችል ተቀባይነት ያገኘ መርህ ነው፡፡ ከዚህ መርህ አንጻር የአንድ ብሔረሰብ ቋንቋ ተናጋሪ መሆን ብቻውን ለብሔረሰባዊ ምንነት አያበቃም፡፡ ቋንቋ ብቻውን ብሔረሰባዊና አገራዊ ምንነትን ገላጭ ዋና መስፈርት ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ በሚናገሩት ቋንቋ ብቻ ማህበረሰቦችን፣ የዚህ ብሔረሰብ አባላት ናቸው ማለት ቋንቋ የሚጋሩ የሁለት ጎረቤት አገሮች ማህበረሰቦችን፣ የአንድ አገር ዜጎች ናቸው ማለት ያለመቻል ያህል ነው፡፡
ለሚቀርቡ የምንነት ጥያቄዎች በርካታ መስፈርቶችን ተጠቅሞ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የማህበረሰቡን ታሪካዊ ዳራ አጥንቶ፤ በማህበረሰቡ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ፤ በጥንቃቄ ተመልክቶ፣ በወቅቱ መልስ የማይሰጥ ከሆነ፣ እንዲሁም አድሏዊ አሰራር ካለ፤ የቃልና የተግባር አንድነት እጥረት አጋጥሟል፤ ተቀባይነት አግኝቷል የሚባለው መርህ ተጥሷል ማለት ነው፡፡ ለምንነት ጥያቄ መልስ በሚጠብቅ ማህበረሰብና ጉዳዩ በሚመለከተው ውሳኔ ሰጭ አካል መኻል፣ የጥቅም ግጭት የወለደው ቅራኔ ይታያል፡፡ እቅጩን ለመናገር ደጋግሞ መነገር ያለበት ጉዳይ በአገራችን የደረሰው ህብረተሰባዊ ችግር መንስዔው ለድብቅ የቡድን ፍላጎት ማሳኪያ ሲባል፣ በፌደራሊዝም ስም፣ ሕዝቡን በቋንቋ ግድግድ አጥር አካልሎ በማናቆር የተፈጠረው የመልካም አስተዳደር ችግር ነው፡፡ ሕዝቡ የሚያነሳቸው ኢ-ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍል፤ ሙስናና ሌሎች ጥያቄዎች፣ በተዋረድ የሚገኙ የዋናው ችግር መገለጫዎች ናቸው፡፡
በብዝህነት ላይ ሲያተኩር ለሕዝቦች አንድነት ዝቅተኛ ትኩረት የሰጠው በብሔረሰብ ምንነት መስፈርት ላይ የተመሰረተው አዲሱ የአስተዳደር ክልሎች አወቃቀር፣ ወደ ፊት የሚያስከትለውን ችግር ባለማጤን ማህበረሰቦችን ያለ ይሁንታቸው ለዘመናት አብሮ በመኖር በጋራ ከመሰረቱት የማህበረሰብ ዘውግ በማፈናቀል ለያይቷቸዋል፡፡ የአካባቢ አስተዳደር አወቃቀሩ በአካላዮቹ ራዕይ መሰረት፤ በቋንቋ ልዩነት ላይ የተገነባ በመሆኑ ዜጎችን በአገራቸው የሚኖሩ ባይተዋሮች አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ሆኖ እያለ አዲሱ የአስተዳደር ክልሎች አወቃቀር ተበታትነው የቆዩ የብሔረሰብ ሕዝቦችን አንድ ላይ በማሰባሰብ በብሔረሰቦች ሕዝቦች መካከል ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ያስቻለን ህብረተሰባዊ ዕድገት ነው በማለት ይቀለዳል! “ዓሳን ከባሕር አውጥቶ ማንሳፈፍ፣ ለጭልፊት ርሕራሄ ይመስላታል” እንዲሉ አበው! ዳሩ ግን ምንም ያህል ጠቃሚ ይሁንም አይሁንም፤ አዲሱ የአካባቢ አስተደደር ክልል አወቃቀር የተከናወነው ከሕዝብ ውሳኔ ውጭ ነበር፡፡ የባለራዕዮችን ውሳኔ ዝም ብሎ እንዲቀበል ነው የተደረገው፡፡ ሕዝቡ ከክልል ስያሜ አሰጣጥ ጀምሮ አልመከረበትም፡፡ ክልሎች በመነሻው ላይ በቁጥር ተሰየሙ፤ ቀጥሎ ስም ሲወጣ እያንዳንዱ ስም እንዴት እንደወጣ ሕዝቡ አያውቅም። በመጨረሻም ያስከተለው ውጤት ታየ፡፡ አብዛኛው ዜጋ የስነልቦና ጉዳቱን ተሸክሞ፣ ከዚህ የተሻለ ቀን በተስፋ እየጠበቀ ነው፡፡   (ይቀጥላል)


    በህክምና ባለሙያው ቸርነት ገብረ ክርስቶስ የተፃፈው በህክምና ላይ የሚያጠነጥን “ዲባቶ” የተሰኘ መፅሐፍ ለንባብ በቃ፡፡
መፅሐፉ በዋናነት በህክምናው አለም ያሉ የአካሚና የታካሚ እውነቶችን በስነ ፅሑፍ ለዛ እያዋዛ እውቀትና ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ነው ተብሏል፡፡ በ371 ገፆች የተቀነበበው መፅሐፉ በ160 ብር እና በ20 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡  

 በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ የመገናኛ ብዙኃን ሽልማት ሊካሄድ መሆኑን የሽልማት አዘጋጁ ዋይጂኤስ መልቲ ሚዲያ አስታወቀ፡፡ የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ በብሮድካስት ባለስልጣን እውቅና እንዳገኘ የገለፁት የድርጅቱ ኃላፊዎች፤  የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ነሐሴ 26 ቀን 2010 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡
በዕለቱም በህትመት፣ በብሮድካስትና በድረ ገፅ መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉና የተመረጡ ጋዜጠኞች እንደሚሸለሙ ተገልጿል፡፡ ተሸላሚዎች የሚመረጡት በዘርፉ የካበተ ልምድና ብቃት ባላቸው የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ዳኝነት እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሽልማቱ አዘጋጅ ዋይጂኤስ መልቲ ሚዲያ ከአሁን በፊት የተለያዩ የኪነ ጥበብ መድረኮችን በማዘጋጀት የሚታወቅ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በብስራት ኤፍ ኤም ሬዲዮ ላይ “ማራኪ” የተሰኘ ፕሮግራም የሚያቀርብ ድርጅትም ነው፡፡

የእውቁ ፖለቲከኛና መሐንዲስ ኢ/ር ዘለቀ ረዲ፣ “የ21ኛው ክ/ዘመን መሳፍንትና ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የማስቀጠል ፈተና” የተሰኘው መፅሐፍ የፊታችን ሰኞ ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ይመረቃል፡፡
በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የመፅሐፉ  ዳሰሳ (review)፣ እንዲሁም ከመፅሐፉ የተመረጡ ክፍሎች የሚቀርቡ ሲሆን ውይይትም ይደረጋል ተብሏል፡፡