Administrator

Administrator

“እኔ በቁሜ ብሸለምም ሽልማቱ ለሌሉት ባልደረቦቼም ነው” (አርቲስት ዙፋን)

“ቆንጆ ቆንጆ ሴቶች ፈልጉ” ተብሎ ነው፤ተመርጬ የተቀጠርኩት
· ተወዛዋዥነት ለዘመናት ተንቆ የኖረ ሙያ ነው ትላለች

  የ50 ዓመት የኪነ ጥበብ ጉዞሽ እንደሚዘከር ቀደም ብሎ መረጃ ነበረሽ? በሰማሽ ወቅት ምን አልሽ? የአንጋፋ አርቲስቶችን የረዥም ዘመን የኪነጥበብ አገልግሎት መዘከር የተለመደ ይመስላል፡፡ ትክክል ነኝ?
የተሰማኝን ነገር እንኳን ልነግርሽ አልችልም፡፡ እግዚአብሄር እራሱ ሲፈቅድ ነው ሁሉም የሚሆነው፡፡ እኔ በቁሜ እያለሁ ይሄ በመደረጉ ከምነግርሽ በላይ ደስ ብሎኛል (በስሜት  እያለቀሰች) ምክንያቱም የውዝዋዜ ሙያ እንደ ሙያ፣ ሙያተኛውም እንደ ሙያተኛ ሳይቆጠር ዘመናት አልፈዋል፡፡ መጀመሪያ የ50ኛ ዓመት በዓሉ ሊከበር የነበረው መስከረም 27 ነበር፡፡ በመንግስት ስብሰባዎች ምክንያት ወደ ጥቅምት ሁለት ተዛወረ፤ ከዛ በኋላ እንደገና ወደ ጥቅምት 11 ተዛውሮ፣ እናትና ልጁ ሲፈቅዱ (ክርስቶስንና ማሪያምን ማለቷ ነው) ያው በዚህ ቀን በልዩ ሁኔታ ተከበረ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ባህልና ቱሪዝምን ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ የብሔራዊ ቴአትር የባህል ማዕከል ሰራተኛ የሆነችውን ወ/ሮ ብርሃንንም አመሰግናታለሁ፤ ብዙ ደክማለች ለዚህ በዓል፡፡ ድካምና መሰላቸት ሳይሰማት ለዚህ ክብር አብቅታኛለች፡፡ ለዚህ ክብረ - በዓል ብዙ የለፉትን ሌሎችንም ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ፡፡
የውዝዋዜ ሙያና ሙያተኛው በተለየ ሁኔታ የማይከበሩበት ምክንያት ምን ነበር ?…
እኔ እንግዲህ መንታ አርግዤ እንደተገላገልኩ የምቆጥርባቸው ሁለት ነገሮች አሉኝ፡፡ ሙያውና ሙያተኛው እንደሙያተኛ አለመቆጠራቸውና ክብር አለማግኘታቸው አንዱ ያረገዝኩት ሃሳብ የነበረ ሲሆን ሁለተኛው የምንሰራው ብሔራዊ ቴአትር ይሁን እንጂ እኛ ተወዛዋዦች  የመንግስት አልነበርንም፡፡ ስለዚህ የጡረታ መብት አልነበረንም፡፡ ከዚያ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተን፣ የማዘጋጃ ቤት አንድ አርቲስት ህይወቱ አልፎ፣ ስንቱ በሳንጃ ተወግቶ ነው ጡረታችንን ያስከበርነው፡፡ ለ4 ወር ታስረን ሁሉ ነበር፡፡ በደምና በህይወት የተገነባ መብት ነው፡፡ የተወዛዋዡን ጉዳይ በተመለከተ ምንም ክብር አልነበረም፡፡ ቴአትር የሰራ፣ ዘፈን የዘፈነ፣ አሁን ዘመን ያመጣውን ፊልም የሰራ ጭምር ሲሸለም ታያለሽ፡፡ የኛን ሙያ ስታይና ስታስቢው ያሳለፍነው መከራ ይከብዳል፡፡ ከእኛ በፊት የነበሩ የዘርፉ ባለሙያዎች፤ በትንሽ ብር ደሞዝ ሀብት ንብረት ሳያምራቸው፣ ለሙያው ፍቅር ሲሰሩና መስዋዕትነት ሲከፍሉ ኖረዋል፡፡ ቀጣዮቹ እኛ ነን፤ ከኛም በኋላ የመጡ አሉ፡፡ ስለዚህ በተሰጠሽ ሙያ ተተኪን ታስተምሪያለሽ፤ ታሰለጥኛለሽ፤ ራስሽም ታገለግያለሽ፡፡ ለምን ብትይ… ያለፉት ለእኛ አስተምረዋል አገልግለዋል፡፡ በሌላ በኩል ተወዛዋዥ የሚሰራው ውዝዋዜ ብቻ አይደለም፡፡ ሁለገብ ነው፤ ቴአትርም ዘመናዊና ባህላዊ ውዝዋዜም… ብቻ ብዙ ነገር ይሰራል፡፡ ይህን ሁሉ የሚሰራው ሙያተኛ ግን አንድም ቀን ስሙ ሲጠራና ሲወደስ አትሰሚም፤ ሲሸለምም አታይም፡፡ ውዝዋዜ የዕድሜ፣ የጉልበትና የወጣትነት ስራ ነው፡፡ ለምን ስሙ አይነሳም? ለምን አይሸለምም? የሙዚቃ ማህበራት፣ የቲያትር ማህበራት፣ የፊልም ሰሪዎች ማህበራት አሉ፤ የውዝዋዜ ግን የለውም፡፡
እነዚህ ሁሉ ነገሮች ይቆጩሽ ነበር?
በጣም ይቆጨኝ ነበር… በጣም! እኔ እንደሚታወቀው፤ ለሚዲያም ቅርብ አይደለሁም፤ ግን አንድ ቀን እድል ገጥሞኝ ይህን ቁጭት እንደምናገረው እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ ይሄው እግዚአብሔር ፈቅዶ፣ 50ኛ ዓመት ክብረ በዓሉ ሲከበር በደንብ ተናገርኩት፡፡ አንደኛ በእንዲህ መልኩ በውዝዋዜ ጥበብ 50 ዓመት ሰርታለች ተብዬ፣ ክብረ በዓሉ መዘጋጀቱ አንዱን አረገዝኩ ያልኩሽን ሃሳብ እንደመገላገል ነው፡፡ ሽልማቱ፣ ክብረ በዓሉና ዝግጅቱ የእኔ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት በዘርፉ ብዙ ሰርተው፣ ምንም ክብርና ሞገስ ሳያገኙ ላለፉት ሁሉ ነው፡፡ አንድ ሰው ግጥም ይጽፋል፣ ሌላው ዜማ ሊደርስ ይችላል፡፡ አቀናባሪው ሙዚቃውን ያቀናብራል፡፡ ከዚያ በኋላ ተወዛዋዡ መድረክ ላይ ይውረገረግበታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ተቀናጅተው ነው አድማጭ ተመልካችን በቁጥጥር ስር የሚያውሉት፡፡ እንደ ጆሮ ሁሉ አይንም እኮ ሙዚቃን ማየት ይፈልጋል፡፡ ቪሲዲ የሚሰራው ለዚህ አይደለም እንዴ? ውዝዋዜ ለሙዚቃ የጀርባ አጥንት እኮ ነው፡፡
ከዚህ በፊት የተሸለሙ ተወዛዋዦች የሉም?
እርግጥ ባህልና ቱሪዝም እንዲሁም የኢትዮጵያ የባህል ማዕከል ይህን ሲያደርጉ የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡ ለአርቲስት መርአዊ ስጦት፣ ለአርቲስት ደስታ ገብሬም ሲዘጋጅላቸው ነበርኩኝ፡፡ ነገር ግን ደስታ ገብሬ ማለት የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች ባህልና ውዝዋዜ በአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ በአፍሪካና በክልል ስታስተዋውቅ ዘመኗን የጨረሰች ናት፡፡ ወዲህ ደግሞ ስትጨፍር አይን የምታፈዝ፣ አጥንት አላት የላትም እየተባለ የምታከራክር ትልቅ ባለሙያ፡፡ ከዚህ አንጻር አንደኛ በህይወት እያለች ባለመሸለሟ፣ ሁለተኛ ደግሞ በዝግጅቱ ቀን ብዙ ሰው ባለመምጣቱ በጣም ቅር ተሰኝቼ ነበር፡፡ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ አበባ ማስቀመጥ፤ ወዲህ ወዲያ ማለት ጥቅም የለውም፡፡ እንደኔ በቁሙ ያለ ሰው፤ እንዲህ አይነት ክብር ሲደረግለት ግን እጅግ ያስደስታል፡፡
ያንቺ የ50ኛ ዓመት ክብረ በዓል ምን ይመስል ነበር? …
ከጅምሩ ልጆቼና የልጆቼ ጓደኞች ቀኑ ደርሶ ዝግጅቱ ሲጧጧፍ፣ እኔ በሌሊት ፀጉር ቤት ሄጄ ፀጉሬን ተሰርቼ ስመጣ፣ በራሴ መኪና እንደምሄድ ነበር የማውቀው፡፡ ልጆቼም የራሳቸው መኪና አላቸው፡፡ እናም በእናንተ ታጅቤ ስለምሄድ፣ መኪናችሁን አዘጋጁ፤ አገር ልብስም አዘጋጁና ልበሱ ብያቸው ነበር፡፡ ከፀጉር ቤት እንደመጣሁ ትንሿ ልጄ፤ “ማሚዬ፤ ዛሬ እኔ ነኝ ፕሮቶኮል፤ ተረጋጊ” አለችኝ፡፡  
ወደ ብሔራዊ የመጣሽው ግን በራስሽ መኪና ሳይሆን በሽንጠ ረጅም ሊሞዚን ነበር-----
ልክ ነው ልነግርሽ ነው፡፡ ከዚያ በቃ ገባሁ፤ ለበስኩና “በሉ እንዳናረፍድ እንውጣ” ስላቸው፣ “ቆይ ማሚ ትንሽ እንቆይ፤ ከዝግጅቱም ቦታ እየደወሉ ነው፤ እኛም በስልክ እየተገናኘን ነው” ይሉኛል፡፡ ልክ ወደ ውጭ ስወጣ፣ የ “ዋዜማ” ድራማ ካሜራ ማንን አየሁት፡፡ እንዴ እዚህ ምን ይሰራል ብዬ ገረመኝ፡፡ “ለምን እዚህ መጣህ ሳሚ?” አልኩት “ማሚዬ፤ ካንቺ ጋር ከቤትሽ ጀምሮ አብሬ መሄድ ፈልጌ ነው” አለኝ፡፡ እኔ አዳራሽ እንዲመጣ ነበር የጠራሁት፡፡ ለካ ከልጄ ጋር ተነጋግረው ኖሯል፡፡ ስወጣ ፎቶ እንዲያነሳኝ ተጠርቶ ነው፡፡ ከዚያ ለባብሼ ጨርሼ ስወጣ፣ ያን ሊሞዚን ተገትሮ አየሁት እልሻለሁ፡፡ ልጆቼና ቤተሰቦቼ ናቸው ሰርፕራይዝ ያደረጉኝ፡፡ ልጆቼ፣ ቤተሰቤና የልጆቼ ጓደኞች፤ በአበባ የታጀበውን ሊሞዚን ከበው እልልል ይባላል፡፡ በጣም ነው ያለቀስኩት! (አሁንም እያለቀሰች)
በደስታ ስሜት ----?
አዎ! አንደኛ ይህን ሁሉ ሳያዩ ያለፉ ተወዛዋዥ አስተማሪዎቼን አስቤ አለቀስኩ፡፡ እኔ የደረስኩበት አልደረሱም፤ ቢያንስ በህይወት ቢኖሩ ጡረታ ይወጡ ነበር፡፡ ለሙያው እየተሰጠ ያለውን ክብር ያዩ ነበር፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች እንዲሁም ቤተሰቤና ልጆቼ ባደረጉት ነገርም በጣም ተደሰትኩኝ፡፡ ከዚያ እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም፡፡ ማልቀስ ሲያንሰኝ ነው፡፡ በብሔራዊ ቴአትር፣ የአገር ፍቅር--- የባንዲራ ፍቅር------ የብሔር ብሔረሰብ ፍቅር… ያስተማሩን፣ ከአገራችን ወጥተን በዚያው እንዳንቀር፣ አገራችንን እንድንወድ ያደረጉን አንጋፋዎቹ አልፈዋል፤ ይህንን አላዩትም (አሁንም ለቅሶ…) እኔ በህይወት ቆሜ ብሸለምም ሽልማቱ የእነሱም ነው፡፡ በህይወት እያሉ በየጓዳው ተረስተው የቀሩ፣ በውጭም በስደት ህይወታቸውን የሚገፉ፣ ለሙያው መስዋዕትነት የከፈሉ ብዙ አሉ፤ ሽልማቱ የእነሱም ጭምር ነው፡፡
ሽልማትሽ ምን ነበር?
ብዙ ነገር ተሸልሜያለሁ፤ ወርቅ፣ ብርና የተለያዩ ነገሮችን ተሸልሜያለሁ፡፡ ከ “ዋዜማ” ድራማ አዘጋጆችና ተዋንያን፣ እንደ አዋርድ የሚሰጥ ሽልማት ተበርክቶልኛል፡፡ ከተለያዩ አርቲስቶችም በርካታ ሽልማት አግኝቻለሁ፡፡ ከሽልማቱ ይበልጥ የሚያኮራው ደግሞ እያንዳንዱ ሰው፤ ስለኔ የሚያወራውና የሚሰጠው ምስክርነት ነበር፡፡ “አልጋነሽ ማለት ይህቺ ናት፤ እሷ ማለት እንዲህ ናት---” ተብሎ በቁምሽ ስትሰሚ፤ከዚህ በላይ ደስታ የለም፡፡ ይህ ክብረ በዓል ተከታዮቻችንን ያበረታታል፤ ለሙያቸው ፍቅር እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡
ከብሔራዊ ቴአትር ጡረታ የወጣሽው መቼ ነው?
ጡረታ የወጣሁት 2001 ዓ.ም አካባቢ ነው፡፡ አሁን በግሌ ብዙ ስራዎችን በመስራት ላይ እገኛለሁ፡፡
በመሃል ግን ውጭ ቆይተሽ መጥተሻል፡፡ የሄድሽው ለስራ ነበር ወይስ ለእረፍት?
ጡረታ እንደወጣሁ አሜሪካ ሄጄ፣ ሁለት ዓመት ቆይቼ ነው የተመለስኩት፡፡ እንደተመለስኩም፤ በየሻሽ ወርቅ በየነ የተዘጋጀ “ደመነፍስ” የሚባል ቴአትር አስተባብር ነበር፡፡ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ እየሰራሁ ነው ያለሁት፤እግዚብሔር ይመስገን፡፡
በአሁኑ ወቅት “ቃቄ ወርዲዮት”፣ “ዋዜማ” ---- ላይ እሰራለሁ፡፡ ይኼው ለብሔራዊ ቴአትር 60ኛ ዓመት ክብረ በዓል ዝግጅትም እየሰራን ነው፡፡ እኔ ጡረታ ብወጣም ከቤቱ አልወጣሁም፡፡ ብሔራዊ ቴአትር፤ ለእኔ አባቴም እናቴም፣ለእዚህ ሁሉ ያበቃኝ ስለሆነ ከዚህ መራቅ አልፈልግም፡፡ ከታላቆቼም ከታናሾቼም… በቤቱ ካሉ የአስተዳደር ሰራተኞችም ጋር ተዋድጄ ነው የምኖረው፡፡
እስኪ ወደ ኋላ ልመልስሽ ----- ትውልድና እድገትሽ የት ነው?
ተወልጄ ያደግሁት ጎጃም ውስጥ ነው፡፡ በጣም ትንሽ ሆኜ ነው አዲስ አበባ የመጣሁት፡፡ እዚሁ ነው ያደግኩት፡፡ የጎጃም ተወላጅ ሆኖ አዲስ አበባ የሚኖር ሰው አግብቶ በልጅነቴ ይዞኝ መጣ፡፡ ያው እንደሚታወቀው፣ በዛን ዘመን ልጅ ሆነሽ ትዳሪያለሽ፤ ለአቅመ ሄዋን እስክትደርሺ ባልሽ ጋ ታድጊያለሽ፤ እኔም በዚህ መልኩ አግብቼ ሊያስተምረኝ አመጣኝ፤ አልተመቸኝም፤ ወደ አገሬ ተመለስኩኝ፡፡ ከዚያ ብዙ ሳልቆይ አክስቴ አዲስ አበባ አመጣችኝ ግን የሚያስተምረኝ አልተገኘም፡፡ ከዚያ ወደ ብሄራዊ ቴአትር መጣሁና ተቀጠርኩኝ፡፡ ዋናው ነገር በአሁኑ ሰዓት ደስ የሚለኝ፤ እኔ ያላገኘሁትንና የተቆጨሁበትን ትምህርት፤ በወንድሞቼ፣ በልጆቼ፣ በዘመዶቼ ተወጥቼዋለሁ፡፡ አሁን ያስተማርኳቸው ፕሮፌሰር፣ ዶክተር ወንድሞች አሉኝ፡፡ ልጆቼንም አስተምሬያለሁ፤ ሁሉም በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት፡፡
ብሔራዊ ቴአትር እንዴት ተቀጠርሽ?
ያን ጊዜ የባህልም የዘመናዊም ተወዛዋዥ እንዲኖራቸው አርቲስት አውላቸው ደጀኔ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ በባህሉ በኩል የራሳቸው ተወዛዋዦች እንዲኖራቸው ሲፈቀድላቸውም “ቆንጆ ቆንጆ ሴቶች ፈልጉ” ተብሎ፤ተፈልጌ ነው ተመርጬ የተቀጠርኩት፡፡
ያው መልክሽም ቁመትሽም የሰጠ ሆኖ ተገኘሽ?    እንዴታ! መልክና ቁመና፣ ቅጥነት ጭምር መስፈርት ነበር፡፡ በወቅቱ ስንፈተን ደግሞ ዝም ብሎ ፈተና እንዳይመስልሽ፡፡ እስከ ላይ እስከ ጭንሽ ድረስ ልብስሽን ገልበሽ፣ አንዲት ጠባሳ በሰውነትሽ ላይ ካለ፣ አታልፊም፡፡ ፈታኙ በወቅቱ አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ ነበር፡፡ ጠባሳው ብቻ ሳይሆን አቋቋምሽም ይታያል፤እግርሽ ቀጥ ያለ መሆን አለበት፤ወልገድ ሸፈፍ ካልሽ አለቀልሽ፡፡
 የበረራ አስተናጋጆች  እንደሚመለመሉት ማለት ነው?
እንደዚያ ነው! ከባድ ነበር ፈተናው፡፡ ከዚያ ስድስት ልጆች ተመረጥን፡፡ የሚገርምሽ ስድስታችንም በህይወት አለን፡፡
እስኪ እነማን እንደነበራችሁ ----- የሌሎቹን ስም ንገሪኝ?
አልማዝ ሀይሌ (ማሚ)፣ አሰለፈች በቀለ፣ ወይንሸት በላቸው፣ አበበች ገ/ሚካኤል፣ አሰለፈች  ገሰሰ፣ አልጋነሽ ታሪኩ ነን፡፡ ፍቅርተ ጌታሁን ሰባተኛ ናት፡፡ አሰለፈች ገሰሰና አሰለፈች በቀለ ውጭ ነው የሚኖሩት፤ ሌሎቻችን እዚሁ አለን፡፡ አሁን ለብሔራዊ ቴአትር 60ኛ ዓመት፣ ወገባችንን ስናውረገርግ ለማየት ያብቃሽ እንግዲህ፡፡
ብሔራዊ ቴአትር በስንት ዓመትሽ ነበር የተቀጠርሽው?
ምናልባት 16 ዓመት ቢሆነኝ ነው፤ በጣም ልጅ ነበርኩኝ፡፡
ውዝዋዜ ያቆምሽው መቼ ነው?
ለ24 ዓመት በውዝዋዜ ከሰራሁ በኋላ ነው ያቆምኩት፡፡ ለምን አቆምሽ ብትይ…በድሮ ጠቅላይ ግዛት፣ በአሁኑ ክ/ሀገር ስትሄጂ፣ ውዝዋዜም ቴአትርም ይዘሽ ሄደሽ ነው የምትሰሪው፡፡ ስለዚህ ባህል ትሰሪያለሽ፤ መሀል ላይ ቴአትር ትሰሪና ከዚያ በባህል ትዘጊያለሽ፡፡ ወይም ባህልና ዘመናዊ፣ ከቴአትር ጋር ይዘሽ ትሄጂና በዘመናዊ ዳንስ ትዘጊያለሽ… እንዲህ ነበር የሚሰራው፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ የብሄር ብሄረሰቦችን ስራ እንሰራለን፤ ፈረንጅ ቋንቋችንን ስለማያውቀው፣ማይም የሚሰራበትም ጊዜ አለ፡፡
በዚህን ወቅት መጀመሪያ የውብሸት ወርቃለማሁ ድርሰት የሆነውን “አንድ ለሶስት” ድራማ ሰርቻለሁ፤ “ሀሁ በስድስት ወር” ላይ የለማኝ ገፀ ባህሪ፣ “እናታለም ጠኑ” የጉሊት ሽንኩርት ነጋዴ፣ “ሀኒባል” ላይ ወታደር፣ “ቴዎድሮስ” ላይ የንግስቲቱ ገረድ ሆኜ ------ ተጫውቻለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ በመዋቅር ዝውውር ወደ ቴአትር ክበብ ገባሁ፡፡
በማስተባበር ደረጃ እነ “ደመነፍስ”ን አስተባብሬያለሁ፡፡ በ “ገመና” አንድ ላይም የቃልኪዳን አክስት ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ አሁን “ዋዜማ” ድራማ ላይ ታማሚዋ ጥሩዬን ሆኜ እየሰራሁ ነው፡፡ ገና ያልታየ “የኔ ዘመን” ፊልም ላይ እየተወንኩ ነው፤ በቅርቡ ተጠናቅቆ ይመረቃል፡፡ “ይግባኝ” ላይም ዳኛ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡
እኔ የምለው ----“ይግባኝ”፣ “የባላገር ፍቅር”፣ “በእንቅልፍ ልብ“፣ “ዋናው ተቆጣጣሪ”፣ የተሰኙት ቴአትሮች ላይ የተወንሽው ወደ ቴአትር ክፍል ከተዛወርሽ በኋላ ነው?
ልክ ነው ግን አሁን ጠፋብኝ እንጂ በማስተባበርም በመተወንም ብዙ ሰርቻለሁ፡፡ “ስሌት” ፊልም ላይም ተውኛለሁ፡፡
ብሔራዊ ቴአትር ውስጥ መኪና የገዛሽ የመጀመሪያዋ አርቲስት አንቺ ነሽ ይባላል፡፡ ይሄ እውነት ነው?
ልክ ነው፤ በ1966 መስከረም 19 ቀን ነው መኪናዬ ከሞኤንኮ የወጣው፤አዝዤ ነው ያስመጣሁት፡፡ በደርግ ጊዜ እሱ መኪና ነዳጅ ይበላል ተብሎ እንዲገባ አይፈቀድም ነበር፤ ላለፉት 40 ዓመታት ነድቼዋለሁ፡፡ አሁን 41ኛ ዓመቱን ይዟል፤እሱ ቀለም እንዲቀባ ጋራዥ ገብቷል፡፡ አሁን ልጆቹ ለልደቴ ኮሮላ መኪና ገዝተውልኝ ነው የምነዳው፡፡ ከብሔራዊ ቴአትር የመጀመሪያ መኪና ገዢ ብሆንም ከሃገር ፍቅር አሰለፈች አሽኔና ዘነበች ታደሰ (ጭራ ቀረሽ) ቀድመውኝ ገዝተው ነበር፡፡
ስንት ልጆች አሉሽ?
ሶስት ሴቶች ልጆች አሉኝ፡፡ በጥሩ ሁኔታ ነው ያሳደግኋቸው፡፡ አንዷ ዲፕሎማና ዲግሪዋን ይዛ የራሷን ስራ ትሰራለች፡፡ አንዷ አግብታ፣ አንድ ልጅ ወልዳለች፤ ሆስተስ ናት፡፡ አንዷም አግብታ አሜሪካ ነው የምትኖረው፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡



    ከ2000 በላይ የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልሶችን የያዘውና በድጋሚ ተሻሽሎ የታተመው “ምን ያህል ያውቃሉ” የተሰኘ መፅሐፍ ለ6ኛ ጊዜ ታትሞ ለንባብ በቃ፡፡ በቁምነገር መፅሔት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ በጋዜጠኛ ታምራት ኃይሉ የተሰናዳው የጠቅላላ እውቀት መፅሀፍ፤ በቴክኖሎጂ፣ በኢኮኖሚ፣ በስነ-ፅሁፍ፣ በህክምና፣ በህግ፣ በታሪክ፣ በጠፈር፣ በቱሪዝም፣ በስፖርትና በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ለማወቅ ተችሏል፡፡
 መፅሀፉ ለታዳጊም ሆነ ለአዋቂዎች እድሜ ሳይገድብ እውቀትን ለማስፋፋት ይረዳል የተባለ ሲሆን በየጊዜው እየተሻሻለና አዳዲስ ነገሮችን እያካተተ እንደሚሄድ ታውቋል፡፡መፅሀፉ በ193 ገፆች ተቀንብቦ፣ በ48 ብር ከ65 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡  

አንዳንድ ዕውነተኛ ክስተቶች ሲቆዩ ተረት ይመስላሉ፡፡ የሚከተለው እንደዚያ ዓይነቱ ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን፣ ከዓመታት በፊት፣ እዚሁ እኛ አገር የቀበሌና የከፍተኛ የሶስት ወር የሂሳብ ሪፖርት፣ ይሰማ ነበር ይባላል፡፡ በዚህ ስብሰባ ምክንያት የታሠሩ አንድ ሰው ለእሥር መዝጋቢው የነገሩት ነው፡፡ እንዲህ አሉ፤ “ሪፖርቱን ይሰማ ዘንድ የቀበሌው ነዋሪ ግዴታ አለበት፡፡”
በዚሁ መሰረት የዚያን ዕለት የቀበሌው ህዝብ ግልብጥ ብሎ ወደቀበሌው አዳራሽ መጥቷል፡፡
ሰብሳቢው -
“እንደለመደው የቀበሌያችንን የፋይናንስ ሪፖርት እናዳምጣለን” አሉ፡፡
ይሄኔ እኔ፤
“ከዚያ በፊት እኔ አንድ አስተያየት አለኝ” አልኩ፡፡
ዕድል ተሰጠኝ፡፡
(በዚያን ዘመን ገዢ የነበረው መንግሥት - “የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ” ነበር የሚባለው፡፡ የሽማግሌው አስተያየት ይህን ስም በተመለከተ ነበር)
“በተሰጠኝ ዕድል በመጠቀም የመንግሥታችን ስም “ጊዜያዊ” የሚለው ልክ አይደለም፡፡ ይሄን ሁሉ ዓመት አስተዳድሮን ዘላቂ የማይሆንበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ “ጊዜያዊ” የሚለውን እንሰርዝና ዘላቂ እናድርገው” አልኩ፡፡
ህዝቡ በሁለት ተከፍሎ ሙግት ገጠመ፡፡ የጠዋቱ ስብሰባ እስከ ከሰዓት ዘለቀ፡፡ ሰብሳቢው ተናደዱና፤
“ስብሰባው ለሌላ ቀን ተዛውሯል” አሉና በተኑት፡፡
ከዚያ እኔም እንደሌላው ሰው ወደ ቤቴ እየሄድኩ ሳለሁ
“ትፈለጋለህ” ብለው ወደ እሥር ቤት አመጡኝ፡፡ ምን አጠፋሁ? ብል፤ “የፋይናንስ ስብሰባ አደናቅፈሃል!” አሉኝ… ካሉ በኋላ ወደ መዝጋቢው ፍርጥም ብለው ዞረው፤ “ይሄውልህ ወዳጄ፤ ይሄ መንግሥት ለምን ዕድሜ ጨመርክልኝ ብሎ አሠረኝ፡፡ ባጭሩ መቀጨት ነው እንዴ የሚፈልገው?” አሉ፡፡
***
ብዙ መንግሥታት የሚበጃቸውን አያውቁም፡፡ የሚጠቅማቸውን ሲመከሩ፣ በግድ ምክሩ ከራሴ ወገን ካልመጣ በሚል ይመስላል፤ አሻፈረኝ፣ አልሰማም ይላሉ፡፡ አንድ የትምህርት ሚኒስቴር ሹም እንዳሉት ነው፡፡ አንድ ጊዜ አንድ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ኃላፊው አልሰማ እያሉ ሲያስቸግሩት፤
“ይሆናል ሲሉዎት አይሆንም
አይሆንም ሲሉዎት ይሆናል፤
የርሶ ነገር ምን ይሻላል?”
ሲል ፃፈላቸው፡፡
ኃላፊው የመለሱለት፤
“ተጣጥሮ መሾም ነው!” የሚል ነበር፡፡
ይህ ዕውነታ ዛሬም የሚከሰት ነው፡፡ ልዩነቱ ዛሬ በግልፅ ሹሞቹ እንቢታቸውን አለመግለፃቸው ነው፡፡ አለመሰማማት ክፉ አባዜ ነው፡፡
የምክሩን ምንነት እንጂ የመካሪውን ማንነት ብቻ ማየት ከጥንት ጀምሮ ጐጂ ባህል ነው፡፡ ምክሩን አውቆና መርምሮ፣ ጠቃሚውንና ጐጂውን መለየትም ያባት ነው፡፡ ሁሉም ነገር ሂደት መሆኑን አለመርሳት ብልህነት ነው፡፡
አዲስ ሃሳብን እንደጠላት ማየት የዋህነት ነው፡፡ ሁሌ በአንድ ሀዲድ ላይ መሄድ ለውጥን ያርቃል እንጂ አያቀርብም፡፡ ፕሮጄክቶች ሥራ ከመጀመራቸው በፊት፣ ዕቅዶች ከመተግበራቸው በፊት፣ የሚቀርቡ የሥጋት አስተያየቶችን ለእንቅፋትነት የተሰነዘሩ አድርጐ ማየት በተለይ ከተለመደ፤ አደገኛ ነው፡፡ የሚያመላክተውም የአሉታዊነት ኃይልን (Negative Energy) ነው፡፡
አለመቀበልን “እኔ ያልኩት ብቻ ነው ልክ” ማለትን፣ አልፎ ተርፎም ፍርደ ገምድልነትን ነው የሚያመጣው፡፡ ያ ደሞ ፀረ - ዲሞክራሲ ነው፡፡ ሥራዎች ከተሠሩ በኋላ “ይፍረሱ”፣ “እንደገና ይስተካከሉ”፣ “መጀመሪያም ፕላኑ ችግር ነበረበት” ማለት ጊዜን፣ የሰው ኃይልን፣ ገንዘብና ንብረትን ማባከን መሆኑን መቼም ማንም ጅል አይስተውም፡፡  ብዙ ተብሏል፡፡ አልተሰማም፡፡ ሆኖም መንግሥት ባይሰማስ እኛ ምን እናድርግ? ብሎ ማሰብም ደግ ነው፡፡ ሁሌ መንግሥትን በመጠበቅ ህዝብ ተባብሮ መሥራት የሚችለውን ተሳትፏዊ ተግባር አለመፈፀምም ደካማነት ነው፡፡ ለምሳሌ በ1966 ዓ.ም ድርቅ ወቅት የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች፤ ወሎና ትግራይ ድረስ በራሳቸው ወጪ ሄደው ህዝቡን ለመታደግ ጥረዋል፡፡ ዛሬም እንደዚያ ማሰብ ጠቃሚ ነው፡፡ ህዝብ በረሃብ ሲጐዳ እጅን አጣምሮ መቀመጥ፤ “ያንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት” የሚለውን መዘንጋት ነው፡፡ ችግሩ ያገር ነውና አገር መረባረብ አለበት፡፡ ህዝብ የሚቻለውን ማድረግ አለበት፡፡ አለበለዚያ “ሁሉ ፈረስ ላይ ከወጣ ማን መንገድ ያሳያል” ይሆናል፡፡

     በኢንተርኔት ነጻነት ከ12 የአፍሪካ አገራት የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች ቻይና የኢንተርኔት ነጻነት በመገደብ 1ኛ ናት
    የኢንተርኔት ነጻነት በአለማቀፍ ደረጃ ለአምስት ተከታታይ አመታት እያሽቆለቆለ እንደሚገኝና ኢትዮጵያም የኢንተርኔት ነጻነት ከሌለባቸው የአለማችን አገራት አንዷ መሆኗን “ፍሪደም ሃውስ” የተባለው አለማቀፍ ተቋም ሰሞኑን ባወጣው አመታዊ ሪፖርት አስታወቀ፡፡ተቋሙ በ65 የአለማችን አገራት ላይ ያካሄደው የ2015 የኢንተርኔት ነጻነት ጥናት ሪፖርት፣ ከአለማችን አገራት የከፋ የኢንተርኔት ነጻነት የተንሰራፋባት ቻይና መሆኗን ጠቁሞ፣ ጥናቱ ካካተታቸው 12 የአፍሪካ አገራት መካከልም ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ነጻነት የመጨረሻውን ደረጃ ትይዛለች ብሏል፡፡
2.9 በመቶ የኢንተርኔት አገልግሎት ሽፋን ባለባት ኢትዮጵያ፣ የማህበራዊ ድረ ገጾችና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አፕሊኬሽኖች እንዲሁም ፖለቲካዊና ማህበራዊ ይዘት ያላቸው ጽሁፎች ይታገዳሉ፣ ጦማርያንና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ተጠቃሚዎችም ይታሰራሉ፣ ፕሬሱም ነጻ አይደለም ብሏል፡፡
በአገሪቱ የኢንተርኔት አቅርቦትና ተደራሽነት ችግሮች እንዳሉ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የአገልግሎት መቆራረጥና አዝጋሚነት በስፋት እንደሚያጋጥምና በአይሲቲው ዘርፍ ለሚሰማሩ ገለልተኛ ተቋማትና ስራ ፈጣሪዎች የሚሰጠው ዕድልም እጅግ ውስን ነው ብሏል፡፡የ2007 አገራዊ ምርጫ መቃረቡን ተከትሎ በርካታ ተጽዕኖ ፈጣሪ ዜናዎች እንዳይሰራጩ ታግደዋል፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድረገጾችም አገልግሎት እንዳይሰጡ ተደርገዋል ያለው ሪፖርቱ፤ ከ100 በላይ ድረገጾችም አሁንም ድረስ ታግደዋል፤ መንግስት በኢንተርኔትና በሞባይል በሚደረጉ ግንኙነቶች ላይ የሚያደርገውን ክትትልና ስለላ አጠናክሮ ቀጥሏል ብሏል፡፡
መንግሥት በበኩሉ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚሰነዘሩ ተመሳሳይ ትችቶችን ማስተባበሉ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በቅርቡ እንደገለፀው፤ የኢንተርኔት ስርጭትና አጠቃቀምን ለመቆጣጠር የሚያስችል ህግ ይፀድቃል፡፡
ኢትዮጵያ በርካታ ጋዜጠኞችን በማሰር ቀዳሚ ከሆኑት የአለማችን አምስት አገራት አንዷ ናት ያለው ሪፖርቱ፣ ከ2014 እስከ 2015 ባለው ጊዜም፣ መንግስት ሃሳባቸውን በገለጹ ጦማርያንና በድረገጽ ጋዜጠኞች ላይ የሚያደርሰውን እንግልትና እስራት አጠናክሮ ቀጥሏል ሲል ገልጿል፡፡የ2015 የኢንተርኔት ነጻነት ሪፖርት እንደሚለው፤ ጥናት ከተደረገባቸው 65 የአለማችን አገራት መካከል ነጻ የተባሉት 18 ሲሆኑ፣ 28 አገራት የተወሰነ የኢንተርኔት ነጻነት እንዳለባቸው፣ 19 አገራት ደግሞ  የኢንተርኔት ነጻነት እንደሌለባቸው ተረጋግጧል፡፡


“የእህል ምርት፣ ከአምና የበለጠ እንጂ ያነሰ አይሆንም”…ግብርና ሚኒስቴር “እንደ ኢትዮጵያ በድርቅ የተጐዳ የለም፤ 15 ሚሊዮን ሰው ሊራብ ይችላል”…ለጋሾችየዝናቡ መጠን ካለፈው ዓመት በ40 በመቶ ቀንሷል

ባለፉት 30 ዓመታት ባልታየ ከፍተኛ ድርቅ ሳቢያ፣ የተረጂዎች ቁጥር 15 ሚሊዮን ሊደርስ ደሚችል የተገለፀ ሲሆን ግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ፤ የዘንድሮ የእህል ምርት ከአምናው የበለጠ ይሆናል አለ፡፡ በኤሊኖ ምክንያት፣ እንደ ኢትዮጵያ በድርቅ የተጐዳ አገር ካለመኖሩም በተጨማሪ፣ ካለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር የተረጂዎች ቁጥር ከ3 ሚሊዮን ወደ 8 ሚሊዮን እንደጨመረ መንግስትና ለጋሾች በጋራ ገልፀዋል፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላም የተረጂዎች ቁጥር 15 ሚ. ሊደርስ ይችላል ብለዋል - ለጋሾች፡፡ ግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ፣ ትናንት በሰጠው መግለጫ፣ ድርቁ ከባድ ቢሆንም፣ ከፍተኛ የእህል አምራች አካባቢዎች ላይ ብዙ ጉዳት አልደረሰም ብሏል፡፡ ዘንድሮ ምን ያህል እህል እንደሚሰበስብ፣ በስታትስቲክስ ኤጀንሲ ጥናት ይካሄዳል ያሉት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ፤ ጥቅል የሀገሪቱ የእህል ምርት እንደማይቀንስ ግን በጥቅል ዳሰሳ

ለሳተላይት ሥርጭቱ ከ12ሚ. ብር በላይ ዓመታዊ በጀት ጸድቋል

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በሀገር ውስጥና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ፣ ምእመና ድምፅዋን የምታሰማበትና መረጃ የምትሰጥበት የ24 ሰዓት የቴሌቪዥን አገልግሎት እንድትጀምር ቅዱስ ሲኖዶስ ወሰነ፡፡
ከጥቅምት 12 ጀምሮ የዓመቱን የመጀመሪያ የምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ በማካሔድ ላይ የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የቴሌቪዥን አገልግሎቱን ለማስጀመር ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ዓመታዊ በጀት ከትላንት በስቲያ ማጽደቁ ታውቋል፡፡
በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የብዙኃን መገናኛ ድርጅት በሚል ተዋቅሮ ሥራ አስኪያጅ በመሠየምና እስከ 22 ሠራተኞችን በመቅጠር የሚጀምረው አገልግሎቱ፤ ዝግጅቱንና ቀረጻውን በሀገር ውስጥ በማከናወን በሳተላይት እንደሚሠራጭ ተገልጿል፡፡
 በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ የሚመራውና ዘጠኝ አባላት ያሉት የብዙኃን መገናኛ ቦርድ፣ የሳተላይት ሥርጭት አገልግሎቱን የሚሰጠው የኮሚዩኒኬሽን ኩባንያ በመምረጥ ሥራውን ለመጀመር እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡
በሚዲያ ጥቅም፣ አሠራርና የወደፊት አቅጣጫ ለምልአተ ጉባኤው አባላት ማብራሪያ የሰጡት የቦርዱ አመራሮች፤ የሳተላይት ሥርጭቱ መካከለኛው ምሥራቅን፣ ደቡብ አውሮፓን፣ ሰሜንና ምሥራቅ አፍሪቃን እንደሚያካልልና ለተቀረው ዓለም ዝግጅቱን በኢንተርኔት በመጫን እንደሚያስተላልፍ አስረድተዋል፡፡
 በሀገር ውስጥና በዓለም ዙሪያ ከ50 ሚሊዮን ያላነሱ አገልጋዮችና ምእመናን ያሏት ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ ተከታዮቿን ለማስተማርና ለመጠበቅ የምትችልበት ተጨማሪ ሚዲያ ካላመቻቸች በተለይም ተረካቢውን ወጣት ትውልድ ለመድረስ እንደሚያስቸግራት፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡
 የሚዲያ ጥናት እና የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴውን በማስተባበርና የውጭ ተሞክሮዎችን በመዳሰስ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩት አቡነ ሳሙኤል፣ የቴሌቪዥን አገልግሎቱ ቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረተ እምነቷን፣ ሥርዐቷን፣ ትውፊቷንና ታሪኳን ለማስተማር፤ ቅዱሳት መካናቷንና ቅርሶቿን ለማስተዋወቅ፤ ለጥናትና ምርምር ለማነሣሣት፤ በየአህጉረ ስብከቱ የተሠሩ መልካም ሥራዎችን በማቅረብ የምእመኑን ድጋፍ ለማግኘት እንደሚረዳት “ሚዲያ እና ዓለምአቀፋዊ አስተሳሰብ” በሚል ርእስ ባቀረቡት ጽሑፍ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዘንድሮና ቢያንስ በ7 በመቶ ያድጋል ተብሏል

     አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ፤ ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት የ2015 የኢኮኖሚ ዕድገት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስና ባለፉት ስድስት አመታት ከተመዘገቡት የአካባቢው
የኢኮኖሚ ዕድገቶች ዝቅተኛው እንደሚሆን መተንበዩን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ተቋሙ ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ባደረገው የአካባቢው የግማሽ አመት የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ እንዳለው፣ አምና 5 በመቶ የነበረው የኢኮኖሚ ዕድገት ዘንድሮ ወደ 3.75 በመቶ ዝቅ እንደሚል የሚጠበቅ ሲሆን፣ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ መቀነስ በምክንያትነት ከተጠቀሱት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከልም የነዳጅና የሸቀጦች ዋጋ መቀነስ እንዲሁም በቻይና ኢኮኖሚ ላይ የታየው መቀዛቀዝ ይገኙበታል፡፡ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት የዘንድሮ የኢኮኖሚ ዕድገት ከአገር አገር የተለያየ እንደሚሆን የጠቆመው ተቋሙ፤ ኮትዲቯር፣ ኢትዮጵያና ታንዛኒያን የመሳሰሉ አገራት ዘንድሮና በቀጣዩ አመት የ7 በመቶ እና ከዚያ በላይ ዕድገት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል ብሏል፡፡የነዳጅ ዋጋ ከ2014 አጋማሽ ጀምሮ ከግማሽ በላይ መቀነሱ፣ ናይጀሪያ እና አንጎላን የመሳሰሉ የነዳጅ ላኪ አገራትን በተለየ ሁኔታ ተጎጂ አድርጓል ያለው ተቋሙ፤ ዛምቢያ፣ ጋና እና ደቡብ አፍሪካን የመሳሰሉ የሚኒኔራል ላኪ አገራትም በሸቀጦች ዋጋ ቅናሽ ክፉኛ እንደተጎዱ ገልጧል፡፡ከቅርብ አመታት ወዲህ በአለማችን ፈጣን ዕድገት ከሚያስመዘግቡ አካባቢዎች ተርታ መሰለፍ የቻለው ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት መንግስታት፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ቅናሹ የሚያስከትላቸውን አሉታዊ ተጽዕኖዎች ለመቋቋም የሚያስችሉ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እንዲያደርጉም አይ ኤም ኤፍ አሳስቧል፡፡

       የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ ጸሃፊ አህመድ ሻሂድ ሰሞኑን ባወጡት ሪፖርት፣ የኢራን መንግስት በዚህ አመት ብቻ ከ1ሺህ በላይ ሰዎችን በስቅላት ለመግደል አቅዷል ማለታቸውን ፎክስ ኒውስ ዘግቧል፡፡
የኢራን መንግስት በተለያዩ ምክንያቶች በስቅላት የሚገድላቸው ሰዎች ቁጥር ባለፈው አመት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ያሉት ሻሂድ፣ የአገሪቱ መንግስት ካለፈው ጥር ወር አንስቶ 700 ያህል ሰዎችን በስቅላት መግደሉን ተናግረዋል፡፡ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ አለማቀፍ ህጎችን በመጣስ፣ ሁለት ወጣት ጥፋተኞችን በስቅላት የገደለው የኢራን መንግስት፤ በሌሎች  ወጣቶች ላይም ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈጸም እየተዘጋጀ መሆኑን የጠቆሙት ሻሂድ፣ ስቅላት የተፈረደባቸው አብዛኞቹ ወጣቶች በሰው ላይ ያደረሱት ጉዳት የለም፤ አደንዛዥ ዕጽ በመጠቀም ስለተወነጀሉ ብቻ ነው ቅጣቱ የተጣለባቸው ብለዋል፡፡የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች፤ ኢራን አለማቀፍ ህጎችን በመጣስ የራሷንና የውጭ አገራትን
ጋዜጠኞች ታንገላታለች በሚል በተደጋጋሚ ሲተቹ መቆየታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ሻሂድም
ብዙ ጋዜጠኞች አመለካከታቸውን በማንጸባረቃቸውና ዘገባ በመስራታቸው ብቻ በአገሪቱ መንግስት
የከፋ ቅጣት እየተጣለባቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በማህበራዊ ድረገጾች፤ ዜናዎችንና የተለያዩ ጽሁፎቻቸውን በማሰራጨታቸው ብቻ የሞት ቅጣት የተጣለባቸው ጋዜጠኞችም እንዳሉ ሻሂድ ገልጸዋል፡፡ ተቀማጭነቱን በኒውዮርክ ያደረገው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄም፤ ባለፈው የፈረንጆች አመት መጨረሻ ከ30 በላይ ጋዜጠኞች
በኢራን እስር ቤቶች ውስጥ እንደሚገኙ ማስታወቁን ዘገባው አክሎ ገልጿል፡፡

ለ35 አመታት የዘለቀው የ1 ልጅ ብቻ ፖሊሲ፣
ከ400 ሚ. በላይ ወሊዶችን አስቀርቷ
    ቻይና ዜጎቿ አንድ ልጅ ብቻ እንዲወልዱ የጣለችውንና ከ35 አመታት በላይ የዘለቀውን አስገዳጅ የስነህዝብ ፖሊሲ በማሻሻል፣ ሁለት ልጆችን መውለድ እንደሚችሉ የሚፈቅድ አዲስ ህግ ልታወጣ መወሰኗን ከትናንት በስቲያ ማስታወቋን ቢቢሲ ዘገበ፡፡የአገሪቱን የወሊድ መጠን ለመቀነስና የህዝብ ቁጥር ዕድገቱን ለመግታት ታስቦ የተቀረጸው “የአንድ
ልጅ ብቻ” ውለዱ ብሄራዊ ማዕቀብ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት እ.ኤ.አ ከ1979 ጀምሮ ባሉት
አመታት፣ በአገሪቱ ሊከሰቱ ይችሉ የነበሩ 400 ሚሊዮን ያህል ወሊዶች  መምከናቸውን ዘገባው
ጠቁሟል፡፡በአገሪቱ በእድሜ የገፉ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱ፣ ቻይና ተተኪ ትውልድ እንዳታጣ
ስጋት መፍጠሩን ተከትሎ፣ መንግስት የወሊድ ገደቡን እንዲያሻሽልና ዜጎች ተጨማሪ አንድ ልጅ
መውለድ እንደሚችሉ ለመፍቀድ እንዳነሳሳው ተገልጧል፡፡አንድ ልጅ ብቻ ውለዱ የሚለውን ህግ ጥሰው ሌላ ልጅ ጸንሰው የተገኙ ቻይናውያን ሴቶች፤ ጽንሱን እንዲያጨናግፉ ይገደዱ እንደነበር እንዲሁም ከስራቸው ይፈናቀሉና የተለያዩ ቅጣቶች ይጣሉባቸው እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡

   ታዋቂው የኮምፒውተርና ስማርት ፎን አምራች ኩባንያ አፕል፣ ባለፉት 12 ወራት የሸጣቸው አይፎን ስልኮች ቁጥር ክብረ ወሰን ማስመዝገቡንና ይህን ተከትሎም በታሪኩ ከፍተኛ የሆነውን የ53.4 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ እንዳገኘ ማስታወቁን ዘ ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡አፕል ባለፉት 12 ወራት ያገኘው አጠቃላይ ገቢ 233.7 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ ይህም ኩባንያው በሳምንት ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ወይም በእያንዳንዷ ሰከንድ ከ1ሺህ 693 ዶላር በላይ ትርፍ ማግኘቱን ያሳያል ብሏል፡፡ኩባንያው እስካለፈው መስከረም ወር በነበሩት ሶስት ወራት ገቢው በ22 በመቶ በማደግ 51.5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ያስታወቀው አፕል ኩባንያ፤ በያዝነው ሩብ አመት ከ75.5 እስከ 77.5 ቢሊዮን ዶላር ሽያጭ አስመዘግባለሁ ብሎ
እንደሚጠብቅም ገልጿል፡፡ባለፉት ሶስት ወራት 48 ሚሊዮን አይፎን ስልኮችን እንደሸጠ የጠቆመው ኩባንያው፣ በተጠቀሰው ጊዜም ሽያጩ የ22 በመቶ እድገት ማሳየቱን አስታውቋል፡፡