
Administrator
በመዲናዋ 15 ሆቴሎች የኮከብ ደረጃቸውን ተነጠቁ
ለአንጋፋው አርቲስት ኪሮስ ኃ/ሥላሴ ዛሬ የምሥጋናና እውቅና መርሃ ግብር ይካሄዳል
አርቲስት ኪሮስ ኃ/ሥላሴ ከ1975 ጀምሮ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በትያትር ጥበባት በቢኤ ዲግሪ ተመርቆ ሀገር ፍቅር ቴአትር ተመደበ። የወጣትነቱንና ጉልምስና እድሜውን በዚያ አሳለፈ። ሀገር ፍቅር ቴአትር ለኪሮስ ኃ/ሥላሴ መ/ቤቱ ብቻ ሳይሆን ትዳሩም ሕይወቱም ጭምር ነው። ከባለቤቱ አርቲስት ፀዳለ ግርማ ጋር ትዳር የመሰረተውና ልጆች ያገኘው ከሀገር ፍቅር ቴአትር ነው።
ኪሮስ ኃ/ሥላሴ ከመደበኛው ስራ ጡረታ ይውጣ እንጂ ዛሬም ሀሳብና ውሎው፣ ማህበራዊ ሕይወቱ ሀገር ፍቅር ቴአትር ነው። “ሳልሳዊው ባልንጀራ” ፣ “የቬኑሱ ነጋዴ “ ፣ “ናትናኤል ጠቢቡ” ፣ “ጣውንቶቹ “ ፣ “አሉ” ፣ “ባልቻ አባነፍሶ” ን የመሳሰሉ ትያትሮች ላይ በተዋናይነት ተሳትፏል። በርካታ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ ተውኗል። ሀገር ፍቅር ቴአትር እና የአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮን በተለያዩ ጥበባዊ ሀላፊነቶች መርቷል። በሚሊኒየሙ ጊዜ የአዲስ አበባ ሚሊኒየም ጽ/ቤትን በሊቀመንበርነት መርቷል።
ኪያ ወደ ሀገር ፍቅር ቴአትር የተመደበበት ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በትያትር ጥበባት በመጀመሪያ ዲግሪ ማስመረቅና በየጥበብ ቤቶች መመደብ የጀመረበት ወቅት ስለነበረ፣ በወቅቱ በነባሮቹ አንጋፋ የጥበብ ሰዎችና በወጣቶቹ ምሩቃን መካከል የተፈጠረውን መጓተት ለማርገብና ዘመናዊውን እውቀት በልምድ ከካበተው ችሎታ ጋር አቀናጅቶ ለመስራት የኪሮስ ሚና ትልቅ ነው።
በአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ኃላፊነቱ ወቅትም ወጣቶች የተለያዩ የትያትር ክበባትና ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው ተሰጥኦዋቸውን ወደ መድረክ እንዲያመጡ የኪያ አበረታች አቀራረብ ግዙፍ ነው። ከወጣቶች ጋር እንደ ወጣት፣ ከአዛውንቶቹ ጋርም እንደ እነሱ መሆን የሚችል በሁሉም የተወደደና የተመሰገነ ብቁ የጥበብ ሰው ነው። በዚህም “ኪሮስ” የሚለው ስሙ ቀርቶ በወዳጆቹ ዘንድ “ኪያ” መጠሪያ ስሙ ሆኗል።
ተስፋ የኪነጥበብ ኢንተርፕራይዝ እና የኪሮስ ኃ/ሥላሴ ልጆች ሕብረት ፈጥረው በዛሬው ዕለት መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 9:30 ሰዓት ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴአትር አዳራሽ ደማቅ የክብርና የምስጋና መርሐ ግብር አዘጋጅተውለታል።
በመርሃ ግብሩም፦
ሙዚቃ (በሀገር ፍቅር ቴአትር እና መሐሪ ብራዘርስ ባንድ) ከታዋቂ ድምጻውያን ጋር፤ በስሙ የተዘጋጀና በታዋቂ ተዋንያን የሚቀርብ አጭር ድራማ፤ በፖሊስ ሰራዊት የማርሽ ባንድ ልዩ ልዩ ጣዕመ ዜማዎች፤ ዶኩመንታሪ (ሕይወቱንና ስራዎቹን የሚዘክር) እና ሌሎች መርሐ ግብሮች ይቀርባሉ።
የአርቲስት ኪሮስ ኃ/ሥላሴ ወዳጆችና አድናቂዎች በሰዓቱና በቦታው ተገኝታችሁ ኪያን በጋራ እንድናመሰግነውና እንድናከብረው፣ ልጆቹ እና ተስፋ የኪነጥበብ ኢንተርፕራይዝ በአክብሮት ጋብዟችኋል፡፡
“ዛፉ ሲወድቅ ዝንጀሮዎቹ ይበተናሉ” - የቻይናዎች አባባል “ቁልቋል የወደቀው ቅርንጫፍ ስላበዛ ነው” - የትግሪኛ ተረት
የተረት - አባት የሆነው ኤዞፕ እንዲህ ይለናል፡፡
ከእለታት አንድ ቀን ተኩላዎች ተመካከሩና መልክተኞች ወደ በጎች ላኩ፡፡
የተኩላዎቹ ልዑካን እበጎች መንደር ደረሱ፡፡ በጎች ተኩሎች መጡብን ብለው ተሸሸጉ፡፡ አድፍጠው ጋጣቸው ውስጥ አድብተው ተቀመጡ፡፡ ተኩሎቹ ግን ረጋ ብለው፣ አደብ ገዝተው፣ “በጎች አትደንግጡ፤ እንደምን ዋላችሁ” አሉ፡፡
“ለድርድር ነው የመጣነው” አሉ ተኩሎቹ፡፡
በጎቹ ቀስ በቀስ ከተደበቁበት ወጡ፡፡
“እኛ በድርድር እምናለን”
“እህስ? ምን እግር ጥሏችሁ መጣችሁ? ምን የድርድር ሃሳብ ይዛችሁ መጣችሁ” አሉ በጎች
“አንድ የቸገረ ነገር ገጥሞን ነበርና ልናዋያችሁ ፈልገን ነው”
“ምንድነው? ከተመካከርን የማይፈታ ምንም ነገር አይኖርም፡፡ ዋናው ተቀራርቦ መነጋገር ነው፤ ንገሩን፡፡”
ተኩሎችም፤
“እግዚአብሄር ይስጥልን፡፡ የቸገረን ነገር ምን መሰላችሁ? ይኸው ከተፈጠርን ጀምሮ ከውሾች ጋር ነጋ- ጠባ እንታገላለን፡፡ የችግራችን መነሻም መድረሻም ውሾች ናቸው፡፡ እርኩስ ውሾች እኛን ባዩ ቁጥር ይጮሃሉ፡፡ ይተነኩሱናል፡፡ ሰፈር ይረበሻል፡፡ ለእኛና ለእናንተ ወዳጅነትና ሰላም ዋናዎቹ እንቅፋቶች ውሾች ናቸው፡፡”
በጎችም፤
“ታዲያ ምን እናድርግ? ምን ዘዴ ብንፈጥር እንቅፋቶቹን ማስወገድ እንችላለን”
ተኩሎችም፤
“እናንተ እሺ ካላችሁማ ዘዴ አይጠፋም ነበር”
“እኮ ዘዴ ካለ ንገሩና?”
“ለጌታችሁ ንገሩ፡፡ ውሾች እንዳልተመቿችሁ ሰላምም እንደነሷችሁ አስረዱ፡፡ ይባረሩልን በሉ”
“ይሄማ ቀላል ነው፡፡ እንነግረዋለን”
በዚህ ተስማሙና ተኩሎቹ ሄዱ፡፡
በጎቹ ውሾቹ እንዲባረሩ ለጌታቸው አመለከቱ፡፡ ጌታቸውም ስንት ዘመን ቤት ደጁን ሲጠብቁ የኖሩትን ውሾች ከቤት አስወጥቶ አባረራቸው፡፡
ከዚያን ቀን በኋላ የዋሆቹ በጎች የዘመናት ጠባቂዎቻቸውን አጡ፡፡ ተንኮለኞቹ ተኩሎች እየተዝናኑ፣ በጎቹን አንድ በአንድ እየለቀሙ፣ በሏቸው፡፡
***
የድርድርን ትርጉም አለማወቅ እርግማን ነው፡፡ ከማን ጋር ነው የምደራደረው? ተደራዳሪዩስ ሊደራደረኝ ያሰበው ምን አስቦ ነው? ጠላቴ እንኳ ቢሆን ድርድሩ ያዋጣኛል ወይ? ከቅርብ ጊዜ ግቤ አንፃር ምን እጠቀማለሁ? ከዘላቄታ ግቤ አንፃርስ ምን እጠቀማለሁ? ትላንትና ምን ዓይነት ግንኙነት ነበረኝ? ዛሬስ? ዛሬን በዛሬው ክስተት መዳኘት እንዴት እችላለሁ? ብሎ ማሰብ የአባት ነው፡፡
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአሜሪካው ጄኔራል ማካርተር በፈሊፒንስ የአሜሪካ ጦር አዛዥ ተደርጎ ሲሾም አንድ ረዳት መኮንን አንድ መጽሐፍ ይሰጠዋል፡፡ መጽሐፉ ከዚህ ቀደም የነበሩት አዛዦች የተዋሉባቸውን ጦርነቶች ዝርዝር የያዘ ነው፡፡ ማካርተር “የዚህ መጽሐፍ ስንት ቅጂ አለ?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ረዳቱም፤ “ስድስት አለ” አለው፡፡ ጄኔራሉም፤ “መልካም፤ በል ስድስቱንም መጻሕፍት ሰብስበህ አቃጥልልኝ፡፡ እኔ የትላንትና ውሎዎች ባሪያ መሆን አልፈልግም፡፡ ችግር ሲከሰት እዛው ወዲያውኑ መፍትሄ እሰጠዋለሁ፡፡ መጽሐፍቱን በሙሉ አቃጥልና ሁኔታዎች በተከሰቱ ሰዓት እንደ ሁኔታው ግዳጅህን ፈጽም” አለው፡፡ ታሪክ የራሱ ዋጋ ቢኖረውም ይህንን እንደ ተመክሮ መውሰድ ተገቢም ደንብም ነው፡፡ በትላንት ለመመካት ከሆነ ግን የግብዝ አመድ- አፋሽ መሆን ነው!
“ነበርን ማለት ግን ከንቱ ነው፤ ተውነው መጀነኑ በቅቶን
ጉራ መንዛት መዘባነን፣ የሚያዛልቅ ዘዴ ባይሆን” ይለናል ኦቴሎ የሼክስፒሩ፣ በፀጋዬ ገ/መድህን ብዕር ልሳን! ስለታሪክ ስለትላንት ማውራት ሳይሆን ዛሬን ማሸነፍ ነው የፖለቲካ ፋይዳው፡፡ ይሄን ያወቁ ላቁ! ይሄን የናቁ ወደቁ! እንደማለት ነው፡፡
ከ1966 ጀምሮ የተከሰቱ የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች አበሳዎች፣ እከሌ ከእከሌ ሳይባል በትንሹ አስር መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የተንተራሱ ይመስላሉ፡፡ ከአበሳዎቹ አንደኛው/በትንሽ በትልቁ መከፋፈል፣ ያለመስዋእትነት ድል መመኘት፣ ውሎ አድሮ ጧት የማሉበትን ማታ መካድ፡፡ “ዕምነት ሲታመም ሺ ወረቀት መፈራረም” ነው፡፡ 2ኛው/ለባላንጣቸው ሰርጎ - ገብነት መጋለጥ ነው፡፡ 3ኛው /እርስ በርስ አለመከባበር፣ አለመተሳሰብ፡፡ 4ኛው/ የመስመር ጥራት አለመኖር፤ ርዕዮተ-ዓለማዊ ብስለት ማጣት፡፡ 5ኛው/በትንሽ ድል መወጣጠርና በትንሽ ሽንፈት መፍረክረክ፡፡ 6ኛው/ተጋጣሚን መናቅና ወሬን /አሉባልታን እንደ አቋም መውሰድ፡፡ 7ኛው/ የጊዜን ፋይዳ በትክክል መረዳት፣ ባልፈውስ? አለማለትና የኃይል ሚዛን የማን ነው አለማለት፣ ከተፈፀመም አለመመዘን፣ ይሄ ዓላማ ባይሳካ ምን ሁለተኛ ዘዴ ቀይሻለሁ? ብሎ አለመዘጋጀት፡፡
8ኛው/ ባለፈው ያደረግነው የት አደረሰን? ታሪኩ ተተንትኖ ተገምግሞ ሳያልቅ በነዚያው ተዋንያን ተውኔቱ መቀጠሉ 9ኛው/ እምቢ አላረጅም ማለት ነው፡፡ አዲሱ ያሸንፈኛል አለማለት “the new is invincible የሚለውን መርሳት፤ “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ማለት፡፡ 10ኛው/እኔ ባልሆንስ መፍትሄው? ሌላ ቢኖርስ? ከኔ የተሻለ አለ ብሎ ፈጽሞ አለማሰብ!
ከነዚህ ሁሉ ይሰውረን፡፡ እነዚህን ሁሉ ከልብ ከመረመርን ፓርቲዎቹ ሁሉ የቆሙት በአንድ ወይም በሁለት ቡድን ህብለ ሰረሰር (Spinal cord) ዙሪያ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ የሚሆነው
“ከተኳሾቹም - አሉ በልዩ
ማህል - አገዳ የሚለያዩ”
በምንልበት አገር ነው፡፡ ከፖለቲካ ንቃት- ባህሉ (ትምክህቱ፣ ጥበቱ፣ ዕምነቱ፣ የፖለቲካ ጥንቆላው፣ ሟርቱ ወዘተ) ባለበት አገር ልማድን አለመመርመር ጦሱ ብዙ ነው፡፡ አጠቃላይ የፖለቲካ ተመክሮአችን ገና አልተፈተሸም፡፡ “ዳሩ ሲነካ መሀከሉ ዳር ይሆናል” ይላል ያበሻ አባባል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ግንዱ ሲመታ ቅርንጫፉና ቅጠሉ መርገፉ አይቀሬ ነው፡፡ ቻይናዎቹ “ዛፉ ሲወድቅ ዝንጀሮዎቹ ይበተናሉ” የሚሉን መሰረታዊ ነገር የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ “ቁልቋል የወደቀው ቅርንጫፍ ስላበዛ ነው” የሚለውም የትግሪኛ ተረት አዙረን ስናየው እንደ ቻይናዎቹ ነው፡፡
‘የትዝታዬ ማሕደር’ በቅርቡ ይመረቃል
“ዳግላስ ጴጥሮስ” በሚለው የብዕር ስሙ የሚታወቀውና በርካታ መጣጥፎችን ያስነበበው ደራሲ ጌታቸው በለጠ፤ ‘የትዝታዬ ማሕደር’ በሚል ርዕስ ያዘጋጀውን በሕይወቱ ዙሪያ የሚያጠነጥን መጽሐፍ በመጪው ሳምንት መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ያስመርቃል፡፡
የጌታቸው በለጠ ግለ-ታሪክ መፅሐፍ በ448 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን፤ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያሳለፈውን ሕይወቱን የሚተርክ ነው ተብሏል፡፡ ‘የትዝታዬ ማሕደር’ በ1ሺ ብር ለገበያ የቀረበ ሲሆን፤ በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ ታዋቂ ደራሲያንና የቅርብ ወዳጆቹ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ ከእነዚህም መካከል ዶ/ር ንጉሴ ተፈራ፣ ደራሲ አበረ አዳሙ፣ ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል፣ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ ደራሲ ጌታቸው በለጠ፣ የደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገለ ሲሆን፤ በማህበራዊና ኪነ ጥበባዊ ሂሶቹም ይታወቃል፡፡
የአገራዊ ለውጡ ሰባት ዓመታት፤ በተቃዋሚዎች ዕይታ
• አገሪቱ በታሪኳ ከባዱን ዘመን ያለፈችበት ጊዜ ነው
• ዕድገቱ የት ላይ እንደተስተዋለ ለማረጋገጥ አዳጋች ነው
• ያለፉት ሰባት ዓመታት “የክስረት ዓመታት” ናቸው
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ እነሆ ድፍን ሰባት ዓመታት ተቆጠሩ፤ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሃላፊነት የተረከቡት። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ብዙ ተስፋ ሰጪ ለውጦች ታይተዋል፡፡ ብዙ ተግዳሮቶችና ተስፋን የሚያጨልሙ ክስተቶች ታልፈዋል፡፡ ቀላል የማይባሉ ስኬቶች የተመዘገቡትን ያህል፣ በእርስ በርስ ጦርነቶችና ግጭቶች የበርካታ ዜጎች ህይወት አልፏል፡፡ ከፍተኛ ሃብትና ንብረት ወድሟል፡፡ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ተፈጥሯል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ሰሞኑን የአገራዊ ለውጡ 7ኛ ዓመት በመንግሥትም በህዝብም ተከብሯል፤ በውይይትና በድጋፍ ሰልፍ፡፡ በተለይ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ በተካሄዱ ውይይቶች፣ ባለፉት 7 የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶች እየተዘረዘሩ ተዘክረዋል፡፡ ሁሉም የመንግሥት አመራሮች በሁሉም ዘርፎች አስደማሚ ስኬቶች መመዝገባቸውን ነው ሲገልጹ የሰነበቱት፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ይሄን አይቀበሉም፡፡ ያለፉት ሰባት ዓመት ለእነሱ የስኬትና የዕድገት ጊዜያት ሳይሆኑ፤ የጦርነት፣ የግጭት፣ የችግርና የመከራ ወቅቶች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት፣ ያለፉትን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር የሰባት ዓመት ጉዞ ፓርቲያቸው በጥልቀት እንደገመገመ ተናግረዋል። ይህን የሰባት ዓመታት ጉዞ፤ “ለኢትዮጵያ የመከራና ስቃይ ዓመታት ነበር” ይሉታል፡፡ “ምናልባትም አገሪቱ በታሪኳ ከባዱን ዘመን ያለፈችበት ጊዜ ነው” ሲሉም ያክላሉ፡፡
“ብልጽግና ፓርቲ አገሪቱ በዕድገት ጎዳና፣ በከፍታና በአብሮነት መንገድ ‘እየተጓዘች ነው’ ቢልም፣ አባባሉ ግን ከዕውነታ የራቀ ነው” የሚሉት መጋቢ ብሉይ፤ “የአገሪቱ ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ እየወደመ ነው፤ ለጦርነት በግብዓትነት እየዋለ ነው። ትልልቅ የተፈጥሮ ገጸ በረከቶቿን ባዕዳን እየተቀራመቱት ነው። የአገሪቱ ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት እየተደፈረ ነው” ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡
የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው፤ ከአጼ ኃይለስላሴ የስልጣን ዘመን ጀምሮ የተለያዩ መንግሥታት ሲወጡና ሲወርዱ መቆየታቸውን አውስተው፣ “በ27 ዓመቱ የኢሕአዴግ አስተዳደር ተሳታፊ የነበሩ አመራሮች፣ አሁን ላይ በተቃራኒው ያለፈውን አገዛዝ ይወቅሳሉ። እኛ እየተራብን ባለንበት ሁኔታ፣ ማርና ወተት የሚፈስባት አገር ነች እየተባለ ነው፤ ይሉናል” ሲሉም ይሳለቃሉ፡፡ እውነቱ ግን በአገሪቱ ብዙ ረሃብተኞች መኖራቸው ነው ባይ ናቸው፡፡
በአዲሱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምም፣ በተጨባጭ በዜጎች ኑሮ ላይ የታየ ለውጥ እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ እንደውም “በዓለም አቀፍ ደረጃ ከምንታወቅባቸው ደረጃዎች እየወረድን መጥተናል” ብለዋል፡፡ በመንግስት ባለሥልጣናት በአገሪቱ ወደ 8 ነጥብ 4 በመቶ የሚጠጋ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳለ ይነገራል የሚሉት አቶ ሙላቱ፤ “ዕድገቱ የት ላይ እንደተስተዋለ ለማረጋገጥ አዳጋች ነው” ይላሉ፡፡ አያይዘውም፣ “የዕድገት አንዱ ማረጋገጫ ተደርጎ የሚጠቀሰው የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት ነው። እኔ የኮሪደር ልማቱን አልቃወምም። ልማት መካሄድ አለበት። ነገር ግን ይህ ልማት የሚካሄደው የዜጎችን ጥያቄ፣ አጠቃላይ ሕግና ስርዓትን ባገናዘበ መልኩ ስለመሆኑ በደንብ የተፈተሸ አይመስለኝም።” ብለዋል፡፡
“ያለፈው የኢሕአዴግ መንግስት ‘ልማታዊ መንግስት ነኝ’ ይላል። በልማት ምክንያት ያለአግባብ ቤቱ የፈረሰበት አንድ ዜጋ መብቱን መጠየቅ አይችልም ነበር። ፍርስራሹን ይዞ ነበር ወደሚሄድበት የሚሄደው። ምክንያቱም ልማታዊ መንግስት ዴሞክራሲን አያውቅም። የአሁኑ ግን ከኢሕአዴግም የባሰ ነው።” ሲሉ ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
መጋቢ ብሉይ አብርሃም፣ የአገሪቱ የሰላምና ደህንነት ሁኔታ ባለፉት ሰባት ዓመታት ምን እንደሚመስል ሲናገሩ፤ “ኢትዮጵያ በታሪኳ በእርስ በርስ ግጭት የተወጠረችበት ጊዜ አልነበረም። አሁን ላይ ግን በመላ አገሪቱ ሰላም የለም። ብልጽግና ዜጎች ከቤታቸው በሰላም ወጥተው በሰላም እንዳይመለሱ የሚያደርግ ፖሊሲ ይዟል። ከዚህም ባለፈ በአገራቸው የባይተዋርነት ስሜት እንዲሰማቸውና የዜግነት መብታቸው እንዳይከበር አድርጓል።” ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡
በዚህ ሃሳብ አቶ ሙላቱም ይስማማሉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወታደሮች የሚሰለጥኑት ኢትዮጵያን ከባዕድ ወራሪ ሃይል ለመጠበቅ ሳይሆን የእርስ በርስ ጦርነትን ለመፋለም መሆኑን ጠቅሰው፣ “ዜጎች በጠራራ ጸሐይ ታግተው እየተሰወሩ ነው” ብለዋል። ለዚህ ጉዳይ በማስረጃነት ያቀረቡት፣ ከሳምንታት በፊት ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በአውቶቡስ ሲጓዙ የነበሩ ዜጎች በታጣቂዎች ታግተው የገቡበት እስካሁን ድረስ አለመታወቁን ነው። “በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ላይ የሕግ የበላይነት የለም” የሚሉት አቶ ሙላቱ፤ “አገር የሚኖረው ሕገ መንግሥቱን አክብሮ የሚያስከብር መንግስት ሲኖር ነው፤ ይህ ከሌለ ግን ማንም ጉልበት ያለው ሃይል፣ አገሪቷ ላይ እየፈነጨባት ሊኖር ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰው የባይቶና ዓባይ ትግራይ (ባይቶና) ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ክብሮም በርሀ፣ ያለፉትን ሰባት የለውጥ ዓመታት የገለጹት፣ “ጦርነት፣ ስደት፣ ድህነትና ሞት የበዛባቸው” በማለት ነው። አቶ ክብሮም የጠ/ሚኒስትሩን የአስተዳደር ዘመን የገመገሙት ፓርቲያቸው ከሚንቀሳቀስበት ትግራይ ክልል አንጻር ሲሆን፣ “ያለፉትን ሰባት ዓመታት ትግራይ በጦርነት አሳልፋለች። ከጦርነት ፕሮፓጋንዳ የጦርነትን የጥፋት አዝመራ ወደ መሰብሰብ የተሸጋገርንበት ጊዜ ነበር” ይላሉ። በዚህም ምክንያት በትግራይ ክልል ትምህርት መቋረጡን፣ የሕክምና አገልግሎት መጥፋቱን፣ እንዲሁም የግብርና ስራ መቆሙን ይገልጻሉ፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች ሳቢያ፣ በርካታ የክልሉ ወጣቶች በሕገ ወጥ መንገድ በገፍ እየተሰደዱ መሆናቸውን የጠቆሙት ሊቀ መንበሩ፤ በአጠቃላይ የጠ/ሚኒስትሩ ሰባት የአስተዳደር ዓመታት ለትግራይ ክልል ጥሩ እንዳልነበር ገልጸዋል፡፡
መጋቢ ብሉይ፣ ባለፉት ሰባት ዓመታት አገሪቱ ለተጋፈጠቻቸው ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች፣ እሳቸው “ጠባብ ብሔረተኛነት” ሲሉ የጠሩት ፖለቲካዊ እሳቤ መንሰራፋቱን በምክንያትነት ይጠቅሳሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጡ ማግስት የታዩ አዎንታዊ ለውጦችን ሲያስታውሱም፤ “መንግሥት በእስር ላይ የነበሩ ጋዜጠኞችን ከእስር ፈትቷል፤ በሌሉበት ክስ ተመስርቶባቸው ቅጣት የተበየነባቸው ጋዜጠኞች ቅጣቱና ክሱ ተነስቶላቸው ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ጥሪ አቅርቧል፤ በአገር ውስጥ እንዳይታዩ ክልከላ የተጣለባቸውና መቀመጫቸውን በውጭ አገራት ያደረጉ ድረ ገጾችና መገናኛ ብዙኃን ዕግዱ ተነስቶላቸዋል። ይህንን እንቅስቃሴ የተመለከተው ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (CPJ) በወቅቱ ድጋፉን የገለጸ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የፕሬስ ቀን እንድታከብር ተመርጣ ነበር።” ይላሉ፡፡ “ይሁንና ብዙም ሳይዘልቅ የፖለቲካ ምሕዳሩ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እየተዘጋ ያለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ነጻ ጋዜጠኝነት የታፈነበትን ጊዜ ለማሳለፍ ተገድደናል” ብለዋል፣ የኢሕአፓ ተቀዳሚ ፕሬዚዳንቱ።
አቶ ሙላቱ ገመቹ፣ ከመጋቢ ብሉይ ሃሳብ ጋር የሚቀራረብ ዕይታቸውን ሲገልጹ፤ “ከሰባት ዓመታት በፊት ከነበረው የዴሞክራሲና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሁኔታ አንጻር፣ በአሁኑ ወቅት ምህዳሩ እየጠበበ መጥቷል” ይላሉ፡፡
መጋቢ ብሉይ፣ ያለፉትን ሰባት ዓመታት “የክስረት ዓመታት ናቸው” ሲሉ ይገልጹዋቸዋል፡፡ “አሁን ላይ የሰባት ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸውን የሚያከብሩበት ሳይሆን፣ ራሳቸውን ፈትሸው ከስልጣን የሚወርዱበት ወቅት ነበር። ያንን በብልጽግና ፓርቲ አላየንም።” ብለዋል። ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በአንድ የውይይት መድረክ ላይ “እኔ አሻግራችኋለሁ” በማለት ተናግረው ነበር፤ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋምና የአገሪቱን መጻዒ ዕድል የሚወስን ፍኖተ ካርታ እንዲቀረጽ ለሚጠይቁ ወገኖች ምላሽ ሲሰጡ። መጋቢ ብሉይ አብርሃም፣ ይህንን የጠ/ሚኒስትሩን ቃል ሙሉ በሙሉ የፖለቲካ ተዋናዮች ማመናቸው “ስሕተት” እንደነበር ይናገራሉ፡፡
“ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘አሻግራችኋለሁ’ ሲሉ፣ ‘ያሻግሩናል’ ብለን የጠበቅነው ከጠባብ ብሔረተኝነት፣ አንድነታችንን ከማያስከበረው ሕገ መንግስት ነበር። እርሳቸው ግን ከጠባብ ብሔረተኛነት አላሻገሩንም፤ ሕገ መንግስቱ አልተሻሻለም። እንዲያውም ህወሓት/ኢሕአዴግ ከፈጸማቸው ስሕተቶች፣ የባሱ የመብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል።” ሲሉ ተችተዋል፡፡ ይህ ጉዳይ በእጅጉ የከነከናቸው የሚመስሉት መጋቢ ብሉይ ነገሩ በስፋት ሲያብራሩት፤ “እኛ የፖለቲካ ሃይሎች ማድረግ ይገባን የነበረው በአጠቃላይ ለእነርሱ ጉዳዩን ሙሉ በሙሉ አምነን መስጠት ሳይሆን፣ በጋራ ፍኖተ ካርታ መቅረጽና የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ከተፈለገ፣ ከእነርሱ ጋር ቁጭ ብለን መወያየት ነበር። ነገሮችን ግራና ቀኝ አልመረመርንም።” ሲሉ ራሳቸውን ጨምሮ የተቃዋሚውን ጎራ ወቅሰዋል፡፡
“ያጋጠመንን መልካም ዕድል በአግባቡ አልተጠቀምንበትም” የሚሉት ተቀዳሚ ፕሬዚዳንቱ፤ “አሁንም ቢሆን አልረፈደም። ቆም ብሎ ሁኔታዎችን ማጤን፣ ይህቺ አገር ከቀውስ የምትወጣበትን ዘዴ መፈለግ ከሁላችንም ይጠበቃል።” ሲሉ የመፍትሔ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡
የኦፌኮው አቶ ሙላቱ፣ እንደ አገር ከታሪክ ስሕተታችን መማር አልቻልንም ባይ ናቸው፡፡ “የአገራችን ችግር የኢኮኖሚ ችግር አይደለም። የማሕበራዊ ችግርም የለብንም። ያልተገራና ያልዘመነ ፖለቲካ ነው የእኛ ችግር። ፖለቲካችንን ካላዘመንነው፣ ችግራችን ቀጣይ ይሆናል።” ብለዋል፤ በማጠቃለያ አስተያየታቸው፡፡
አቶ ክብሮም በርሀ ደግሞ፣ በመጪዎቹ ጊዜያት በሰበብ አስባቡ የተጓተተው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ተደርጎ፣ የትግራይ ክልል ወደቀደመ ሰላሙ እንዲመለስ፣ የፌደራል መንግሥቱን ጨምሮ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
እስራኤል ከአየር መንገድ ጋር አዲስ ፕሮጀክት ልትጀምር ነው
“ከኢትዮጵያ ጋር የንግድ ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች”
እስራኤል ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር አዲስ ፕሮጀክት ልትጀምር ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረገውን የንግድ ትብብርና ግንኙነት የሚያጠናክረው እንደሚሆን ተጠቁሟል።
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ዶ/ አብርሃም ንጉሴ ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ገልጸዋል። በአሁኑ ጊዜ ከ122 በላይ የእስራኤል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙም አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡
ኩባንያዎቹ በአግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ በጨርቃጨርቅ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ በኢኮሲስተም እና የመሳሰሉ ዘርፎች ላይ በመስራት ላይ እንደሚገኙ ያብራሩት አምባሳደሩ፤ እስራኤል የኢትዮጵያን ምርት በማስገባት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች መሆኗንም አመልክተዋል። “ጤፍን ወደ እስራኤል በማስገባት ቀዳሚነቱን ይዘናል። ቡና እና ሰሊጥ፣ እንዲሁም ሌሎች የጥራጥሬ እህሎችም ወደ እስራኤል ይገባሉ” ብለዋል።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከእስራኤል የቴክኖሎጂ ምርቶችን እንደምታስገባ የጠቆሙት አምባሳደር ዶ/ር አብርሃም፤ ከዚህም ባሻገር በሁለቱ አገራት መካከል የቴክኖሎጂ ተሞክሮ ልውውጥ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
“በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ በኩል፣ በጣም ጥሩ የሆነ ግንኙነት አለ። ባለፈው ህዳር ወር የእስራኤል መንግስት አራት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤክስፐርቶችን በመላክ፣ ኢትዮጵያ አሁን የምታካሂደውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ሲስተምና ኢኮሲስተም የበለጠ ለማጠናከር እየተሰራ ነው” ብለዋል፡፡
በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ በማሳለጥ በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድ የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር አብርሃም፤ እስራኤል ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር “ኤሮስፔስ” የተሰኘ ፕሮጀክት በቅርቡ እንደሚጀመር ጠቁመዋል፡፡ “የእስራኤል አውሮፕላን ኢንዱስትሪ፣ የኢትዮጵያን የመጓጓዣ አውሮፕላኖች ወደ ካርጎ የመለወጥ ፕሮጀክት ነው።” ሲሉም አብራርተዋል፡፡
የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ሂደቶች የተጠናቀቁ መሆናቸውን አምባሳደሩ አመልክተዋል። “በሁለቱም አገሮች የንግድ ልውውጥ ሲደረግ፣ በአራት ሰዓት ውስጥ በሁለቱ አገራት መካከል የደርሶ መልስ ጉዞ ለማካሄድ ይቻላል። የበለጠ ለማጠናከር ደግሞ እየሰራን ነው።” ሲሉ ተናግረዋል።
አምባሳደር ዶክተር አብርሃም ንጉሴ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ባለፈው የፈረንጆቹ ነሐሴ ወር 2024 ዓ.ም ነበር።
የአዋቂዎች የትምባሆ አጠቃቀም ላይ ለውጥ መታየቱ ተገለጸ
በአገር አቀፍ ደረጃ የአዋቂዎች የትምባሆ አጠቃቀም መጠንን ለመቀነስ ሰፋፊ ስራዎችን መስራት ይገባል ተብሏል። ከትምባሆ አጫሽነት ጋር የተገናኙ ጉዳቶች መጠን እየቀነሰ ስለመምጣቱ ተገልጿል።
ባለፈው ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በኤሊሊ ሆቴል በተዘጋጀ መድረክ ላይ በ2016 ዓ.ም. የዓለም አቀፍ የአዋቂዎች ትምባሆ አጠቃቀም ጥናት (GATS) ይፋ ተደርጓል። በዚህ መድረክ ላይ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ በሆናቸው አገር አቀፍ የአዋቂዎች ትምባሆ አጠቃቀም (GATS 2024) ጥናት፣ ከፍተኛ የሆኑ ለውጦችን ስለመገኘቱ ተነግሯል። ይሁንና አሁንም ሰፋፊ ስራዎች እንደሚጠበቅ ተመላክቷል፡፡
አገር አቀፍ የአዋቂዎች ትምባሆ አጠቃቀም የ2016 ጥናት፣ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የትምባሆ ተጠቃሚዎች ቁጥር 5 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ዓመት ጥናት ደግሞ ወደ 4 ነጥብ 6 በመቶ “ቀንሷል” ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል፤ በGATS 2016 በተጠናው ጥናት፣ ሰዎች በሚሰሩባቸው የስራ ቦታዎች የነበረው ለትምባሆ ሁለተኛ ወገን አጫሽነት መጋለጥ (Second and smoker) 29 ነጥብ 3 በመቶ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2024 ጥናት ግን ወደ 19 ነጥብ 8 በመቶ ስለመቀነሱ ተጠቅሷል፡፡
ይህን በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት እየተዛመተና በሰው ልጆች ጤና እና ማሕበራዊ ኑሮ፣ ብሎም ኢኮኖሚ ላይ ችግር እየፈጠረ ያለን ጉዳይ ለመግታት ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ባለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት ሰፋፊ ስራዎችን ሲሰራ እንደቆየ በዚህ መድረክ ላይ ተነግሯል። ከእነዚህም መካከል የትምባሆ ቁጥጥር መመሪያ ቁጥር 77/2013ን እና የትምባሆ ምርት አወጋገድ መመሪያ ቁጥር 1003/2016 TEA፣ ከዚህ በተጨማሪም አገር አቀፍ የትምባሆ ቁጥጥር አስተባባሪ ኮሚቴ በማቋቋምና የስምንት ዓመት አገር አቀፍ የትምባሆ ቁጥጥር ስትራቴጅክ ዕቅድ በመንደፍ ስራዎች ሲሰሩ እንደቆዩ ለማወቅ ተችሏል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ አዲስ አበባን ከትምባሆ ጭስ ነጻ ማድረግ፣ ሌሎችን ነጻ ለማድረግ “ይጠቅመናል” በሚል ዕሳቤ ባለፉት 5 ዓመታት አዲስ አበባን ከትምባሆ ጭስ “ነጻ ማድረግ” የሚል ንቅናቄ ተቀርጾ መተግበሩ ከፍተኛ የሆነ ውጤት እንዳስገኘ ተገልጿል፡፡ በሌሎችም ክልሎች በተሰሩ ተከታታይ የትምባሆ ቁጥጥር ስራዎች ለውጥ መታየቱ በጥናት ጭምር “ተረጋግጧል” ተብሏል።
የተለያዩ መረጃዎችና ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ በዓለም በየዓመቱ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በትምባሆ ምክንያት ይሞታሉ። ከእነዚህም ውስጥ 12 ሚሊዮን ቀጥተኛ አጫሽ ሳይሆኑ ለጭሱ ብቻ ተጋላጭ በመሆን የሚጎዱ ናቸው፡፡
ከዚህም ባለፈ፣ ሰዎች ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የመጠቃት ዋነኛ ምክንያት የሆነውና ቁጥራቸው በማይናቅ ሁኔታ እየጨመረ ከመጣባቸው ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው ሲጋራ ማጨስና ሌሎች የትምባሆ ምርቶችን መጠቀም ጋር የተያያዘ መሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ሲነገር ቆይቷል። ሲጋራ ማጨስና ሌሎች የትምባሆ ምርቶችን መጠቀም በሱስ ለማስያዝ፣ ለአደገኛ የሳንባ በሽታ ወይም ካንሰር፣ ለልብ በሽታ መዳረግ፣ ለጽንስ መጎዳት፣ በሚጨስበት አካባቢ በሚኖሩና በማያጨሱ ሰዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የጤና መታወክና ሌሎችንም በሽታዎች እያስከተለ ይገኛል፡፡
በዚህ መድረክ ላይ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ደጉማ፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሃይሉ፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ ለኢትዮጵያ የ28.5 ሚ. ዩሮ ድጋፍ አደረገ
ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዋን ለመደገፍ ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ (AFD) 28.5 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አገኘች። የድጋፍ ስምምነቱ 25 ሚሊዮን ዩሮ የበጀት ድጋፍና 3.5 ሚሊዮን ዩሮ የቴክኒክ ድጋፍን ያካትታል ተብሏል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ እንደገለጹት፤ ይህ ድጋፍ የኢትዮጵያን የመንግሥትና የግል ሽርክና፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ማሻሻያና የፋይናንስ ዘርፍ ተደራሽነትን ለማጠናከር ይረዳል። በተጨማሪም፤ ለውጤታማ ፖሊሲ ትግበራና ተቋማዊ አቅምን ለማሳደግ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል።
የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ (AFD) ዳይሬክተር ሚስተር ሉዊስ-አንቶይን ሶሼት በበኩላቸው፤ ኤጀንሲው የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ለውጥ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ድጋፍ አስተዳደርን፣ ኢኮኖሚያዊ ዘላቂነትንና የመንግሥት ዘርፍ ቅልጥፍናን ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አዲስ ዘመናዊ አውሮፕላን---
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፣ በ3.6 ሚሊዮን ዶላር የገዛትን አዲስ ዘመናዊ አውሮፕላን ሰሞኑን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተረክቧል፡፡ አውሮፕላኗ 14 ሰው የመያዝ አቅም ያላት ሲሆን፤ የተደራጀ የአውሮፕላን ማረፊያ በሌለባቸው ገጠራማ አካባቢዎች በቀላሉ ማረፍ እንደምትችልም የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እህት ኩባንያ የሆነው ትራንስ ኔሽንስ ኤር ዌይስ ሥራ አስኪያጅ፣ አቶ አሚር አብዱልወሃብ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግረዋል፡፡
“ሴስና ካራቫን ኤክስ” የሚል ስያሜ ያላት አዲሷ አውሮፕላን፤ ሚድሮክ በማዕድንና በእርሻ ዘርፍ የሚሰራቸው ሥራዎችን ለማሳለጥ ተጨማሪ አቅም እንደምትፈጥርም ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም አውሮፕላኗ ለጎብኚዎችና ለአገልግሎት ፈላጊዎች የቻርተር አገልግሎት እንደምትሰጥም ተናግረዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ራይድ ተፈራረሙ
በ5 ዓመት ውስጥ ለ300ሺ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከሃይብሪድ ዲዛይንስ (ራይድ) ጋር ለአምስት ዓመታት የሚቆይ፣ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር የስራ ስምምነት ተፈራረሙ። ስምምነቱ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችልና ለአምስት አመት የሚቆይ መሆኑም ተመላክቷል።
በመድረኩ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እንደገለፁት፤ በሃገር ደረጃ የስራ ዕድል ፈጠራን ለማሳዳግ በትኩረት እየተሰራ ነው። ይህ ስምምነትም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር፣ የአገልግሎት ዘርፉን ከማዘመን ባሻገር ፍትሀዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የማይተካ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። ስምምነቱ ሚኒስቴሩ በሚዘረጋው የስራ መስመር መሰረት በህጋዊ መንገድ ብዙ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ ሲሆን፤ በሁሉም ክልሎች ስራ ላይ እንዲውል አቅጣጫ መውጣቱን ተናግረዋል።
የሃይብሪድ ዲዛይንስ (ራይድ) መስራችና ስራ አስፈፃሚ ሳምራዊት ፍቅሩ በበኩላቸው፤ ኩባንያቸው የስራ እድል ለመፍጠርና ስራ የለም የሚባለው ነገር እንዲቆም በርካታ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። እስካሁን ለ120 ሺ ዜጎች የስራ እድል እንደተፈጠረ የገለፁት ስራ አስፈፃሚዋ፤ ይህ ስምምነትም በሚቀጥሉት አምስት አመታት 300ሺ ለሚሆኑ ወጣቶችና ሴቶች የስራ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።