Administrator

Administrator

Monday, 09 September 2019 11:51

አገራዊ አባባል

• ዕዳ አለኝ ብለህ አትቸገር ዕዳ የለኝም ብለህ አትክበር አይታወቅም የአምላክ ነገር
• ያለ ፍቅር ሰላም፤ ያለ ደመና ዝናብ፡፡
• የሀገሬ ሰዎች ተጠንቀቁ የሰረቁት ስጋ ያስይዛል መረቁ፡፡
• ያመሰገኗት ቅል ባፏ ታፈሳለች፡፡
• መታረቃችን ስለማይቀር፣ ስንጣላ በልክ ይሁን፡፡
• የማይቀርልህን እንግዳ አጥብቀህ ሳመው፡፡
• የጅብ ፍቅር እስኪቸግር፡፡
• በቅሎ ግዙ ግዙ፣ አንድ አሞሌ ጨው ላያግዙ፡፡
• ካለ ፈጣሪ አሟጠሽ ጋግሪ፡፡
• አሳቀኝ ገንፎ ከእራቱ ተርፎ፡፡
• ዓሳውም እንዳያልቅ ውሃውም እንዳይደርቅ፡፡
• አሳዳጊ ለበደለው ፊትህን አትስጠው፡፡
• አሽከሩን አይዳኝ በገናውን አይቃኝ፡፡
• አቅለው ብለው ቆለለው፡፡
• አቀማመጥ ያላወቀ ከባልና ሚስት መሀል ይቀመጣል፡፡
• አባቱን አያውቅ አያቱን ናፈቀ፡፡
• አባት ካነሰው ምግባር ያነሰው፡፡
• አባይ ስለቱ ደስ ማሰኘቱ፡፡
• አባይ አንተ ያየኸኝ ከደረት፣ እኔ ያየሁህ ከጉልበት፡፡

Monday, 09 September 2019 11:43

የግጥም ጥግ

  ጨለማ

       ጨለማዬ
ነውሬን ሸክፎ
እርቃኔን አቅፎ
ሸሽጎ ደብቆ
አኑሮኝ ነበረ
ግና
ብርሀን ይሉት ጠላት
በጨለማዬ ላይ ብርሀኑን አብርቶ
ይኸው ጉድ ሆኛለሁ
ገመናዬ ሁሉ አደባባይ ወጥቶ፡፡
(ዳዊት ጸጋዬ)

Monday, 09 September 2019 11:52

የሙዚቃ ጥግ

 • ሙዚቃ፤ የዝምታ ስኒን የሚሞላ የወይን ጠጅ ነው፡፡
 ሮበርት ፍሪፕ
• ሰዓሊያን ስዕላቸውን በሸራ ላይ ይስላሉ፡፡ ሙዚቀኞች ግን ስዕላቸውን በዝምታ ላይ ይስላሉ፡፡
 ሊዎፖልድ ስቶኮውስኪ
• ሙዚቃ ሕይወት ነው፡፡ ለዚያ ነው ልባችን ምት ያለው፡፡
 ያልታወቀ ሰው
• ከእያንዳንዱ ተወዳጅ ዘፈን ጀርባ ያልተነገረ ታሪክ አለ፡፡
 ኩሻንድዊዝደም
• ሙዚቃ፤ ውብ፣ ቅኔያዊ ነገሮችን ለልብ የመተረኪያ መለኮታዊ መንገድ ነው፡፡
 ፓብሎ ካሳልስ
• ደስተኛ ስትሆን ሙዚቃውን ታጣጥማለህ፡፡ ስታዝን ግጥሞቹን ትረዳለህ፡፡
 ፍራንክ ኦሽን
• የሙዚቃ እውነተኛ ውበት፣ ሰዎችን ማስተሳሰሩ ነው፡፡
 ሮይ አየርስ
• ሙዚቃ የአዕምሮ መድሃኒት ነው፡፡
 ጆን ሎጋን
• ብቸኛው እውነት ሙዚቃ ነው፡፡
 ጃክ ኬሮስ
• ሙዚቃ ሚዛኔ ነው… የሕይወቴ ማዕከል፡፡
 ማንዲ ፓቲንኪን
• ህይወት ያለ ሙዚቃ ስህተት ነው፡፡
 ፍሬድሪክ ኒቼ
• ለእኔ ህይወት ያለ ሙዚቃ ባዶ ነው፡፡
 ጄን ኦስተን
• ሙዚቃ ዓለምን ይለውጣል፤ ምክንያቱም ሰዎችን መለወጥ ይችላልና፡፡
 ቦኖ


Monday, 09 September 2019 11:46

የፍቅር ጥግ


 • ራሳችን ወላጅ እስክንሆን ድረስ የወላጅ ፍቅርን በቅጡ አናውቀውም፡፡
  ሄነሪ ዋርድ ቢቸር
• የተበላሹ አዋቂዎችን ከማቃናት ይልቅ ጠንካራ ሕጻናትን መፍጠር ይቀላል፡፡
 ፍሬድሪክ ዳግላስ
• ልጆቻቸውን የማይወዱ አባቶች አሉ፤ የልጅ ልጁን የማይወድ አያት ግን የለም፡፡
 ቪክቶር ሁጎ
• ፍቅር የልጅ ጨዋታ አይደለም፤ ትልቅ ሃላፊነት ነው፡፡
 ሼክ አፊፍ
• ልጆቼን በምወድበት መንገድ ማንንም ወድጄ አላውቅም፡፡
 ኬቲ ሳጋል
• ሕጻናትን እወዳለሁ፡፡ እኔም በአንድ ወቅት ሕጻን ነበርኩ፡፡
 ቶም ክሩዝ
• የእናት ልብ የሕጻን የት/ቤት ክፍል ነው፡፡
 ሄነሪ ዋርድ ሊቸር
• ሕጻናት ሕይወትህን ተፈላጊ ያደርጉልሃል፡፡
 ኢርማ ቦምቤክ
• ወላጅነት… መጪውን ትውልድ የመምራትና ያለፈውን ትውልድ ይቅር የማለት ጉዳይ ነው፡፡
 ፒተር ክሬቶስ
• ወላጅነት የሕይወት ዘመን ሥራ ነው፤ ልጅ አድጓል ተብሎ አይቆምም፡፡
 ጄክ ስሎን
• ምድርን ከአያቶቻችን አይደለም የወረስነው፤ ከልጆቻችን ነው የተዋስነው፡፡
 የአሜሪካውያን አባባል
• ትልቁ የተፈጥሮ ሃብታችን የልጆቻችን አዕምሮ ነው፡፡
 ዋልት ዲዝኒ
• እያንዳንዱ ሕጻን ሰዓሊ ነው፡፡
 ፓብሎ ፒካሶ

Monday, 09 September 2019 11:43

ሃሳብዎን በነፃነት ይስጡ!

 ውድ አንባቢያን፡- ከዚህ በታች የቀረቡት መጠይቆች ከመስከረም 2011 ዓ.ም አንስቶ እስካሁን ባሉት ጊዜያት የተፈፀሙ ወይም የተከናወኑ ጉ ልህ አገራዊ ሁነቶችን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ዓላማውም የአዲስ አድማስ አንባቢያን የዓመቱን ምርጥ፣ ተወዳጅ፣ አሳዛኝና አስደንጋጭ ክስተቶች በተመለከተ ሀሳባቸውን ወይም አስተያየታቸውን መሰብሰብ ነው፡፡ ምላሽ በመስጠት የተለመደ ትብብራችሁን ታደርጉ ዘንድ እንጠይቃለን፡፡ እናመሰግናለን፡፡
 
1. የዓመቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ የክልል ፕሬዚዳንት
2. የዓመቱ ስኬታማ የመንግስት ተቋም
3. የዓመቱ አሳፋሪ የመንግስት ተቋም
4. የዓመቱ ተስፋ የሚጣልበት የዲሞክራሲ ተቋም
5. የዓመቱ አስደማሚ የመንግስት ስኬት
6. የዓመቱ ስኬታማ አገራዊ ንቅናቄ
7. የዓመቱ አስደንጋጭ ክስተት
8. የዓመቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ አክቲቪስት
9. የዓመቱ ምርጥ የፖለቲካ (የመንግስት) መሪ
10. የዓመቱ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ጣቢያ
11. የዓመቱ ተወዳጅ የሬዲዮ ጣቢያ
12. የዓመቱ ምርጥ ኢ-ል ብወለድ መጽሐፍ
13. የዓመቱ ተወዳጅ የኪነ ጥበብ ምሽት
14. የዓመቱ የሰላምና የፍቅር አርአያ
15. የዓመቱ ምርጥ የቴሌቪዥን ድራማ
16. የዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ አልበም
17. የዓመቱ ምርጥ ጋዜጠኛ
18. የዓመቱ አሳፋሪ የፖለቲካ ውዝግብ
19. የዓመቱ ምርጥ የበጎ አድራጎት ድጋፍ

        ዕድሜ------------------------- ፆታ ------------------------ የትምህርት ደረጃ -------------------------
 በፖ.ሳ.ቁ 12324 ልትልኩልን ወይም ዝግጅት ክፍላችን ድረስ በመምጣት በአካል
ልታደርሱን ትችላላችሁ፡፡
አድራሻ፡- ግቢ ገብርኤል፣ ፓላስ ኮሜርሻል ሴንተር፤ 6ኛ ፎቅ
ለተጨማሪ መረጃ፡- በ0911 201357 ይደውሉ

በመናገር ብቻ ያሰቡትን ሁሉ መፍጠር፣ ቅንጣት ላባ በማወዛወዝ ብቻ ያሻቸውን ማድረግ፣ የሚመኙትንም መሆን የሚቻልበት ተዓምረኛ ዓለም ውስጥ ነው አሉ፡፡
መቼም፣ ሁሉም የምትሃት ዓለም ሰው፣ አንድ አይነት አይደለም፡፡ የናት ሆድ ዥጉርጉር ይባል የለ፡፡ እናማ አንዷ ታዳጊ የተዓምር ዓለም ልጃገረድ፣ ያልተለመደ ነገር ማድረግ ጀመረች፡፡
በመናገር ብቻ ያሰበችውን ነገር ሁሉ ከመፍጠር ይልቅ፣ የተፈጠሩ ነገሮችን እየመረመረች ስም ታወጣላቸው ጀመር፡፡ ላባ በማወራጨት፣ ያሻትን ከማድረግ ይልቅ፣ ጓሮ ውስጥ እንጨትና ብረት መግጠምና መፍታት አማራት፡፡ ምኞት ብቻ ሳይሆን ችሎታም እፈልጋለሁ አለች፡፡ ተዓምረኞቹን ግራ አጋባቻቸው፡፡ ቤተሰብ ተጨነቀ፡፡ ጎረቤት ተንሾካሾከ፡፡ የሰፈር መጠቋቆሚያ ሆነች፡፡ አንዳንዶቹ ጠሏት፡፡ አንዳንዶቹ መዓት ልታመጣብን ነው ብለው ወነጀሏት፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ፈረዱባት፡፡
ከተዓምር ዓለም ተባረረች፡፡ ሁሌ ብርሃን፣ ሁሌ ምቾት፣ ሁሌ እርጋታ ከሆነበት አለም ተወረወረች፡፡ ተወርውራ፣ ጭቃ ላይ ወደቀች፡፡ የጥቅምቱ ብርድ አንቀጠቀጣት፡፡ ጨለማ ዋጣት፡፡
እንዲህ ሆና ነው፤ ወዲህና ወዲያ ስትንገላታ ቆይታ፣ አንድ ትንሽ መኖሪያ ቤት ያጋጠማት፡፡ በር ከፍታ አየች፡፡ መብራት አለ፡፡ ወደ መታጠቢያ ቤት ስትገባም፣ አምፖል በርቷል፡፡ ተገረመች፡፡ እዚህ ምትሃት የሌለበት ዓለም ውስጥ፤ ድቅድቅ ጨለማን የሚያጠፋ እንደዚህ አይነት ተዓምር አልጠበቀችም፡፡
ለካ፣ የነዚህ ምትሃትም ቀላል አይደለም አለች፡፡ ምትሃት ባይሆንም፣ ከምትሃት አይተናነስም፡፡ እያንዳንዱ ክፍል ውስጥ ፀሐይ ፈጥረዋል፡፡
የገላ መታጠቢያ ቧንቧ ስትከፍት ውሃው ሿ ብሎ ወረደ፡፡ ተደነቀች፡፡ ለካ ተአምረኛ ያልሆነ ዓለም ውስጥም ተዓምር መስራት ይቻላል፡፡ በየቤታቸው ዝናብ ማዝነብ ይችላሉ ብላ ተደነቀች፡፡
*   *   *
በጨለማ ውስጥ ብርሃን ባይኖርም፣ ጨለማ ውስጥ መቅረት ማለት አይደለም፡፡ ብርሃንን መመኘት ብቻ ሳይሆን፣ የየራሳችንን ቤት የሚያፈካ፣ አገርን የሚያደምቅ ብርሃን መስራት እንደሚቻል አለመዘንጋት ነው፡፡
አዎ፣ ከከፍታ እጅግ ወርደናል፡፡ በጭቃ ላይ ወድቀን በማጥ ተጠምደን መራመድ አቅቶናል፡፡ ከፊት የሚራመዱ ሰዎች ታሪክ በሰሩበት አገር፣ ከዓለም ሁሉ የኋላ ሆነናል፡፡ በድህነትና በችግር ተብረክርከናል፡፡ ኑሮ ከብርድ የከፋ ሲሆን የማንቀጥቀጥ ያህል ሊያንገበግበን ይገባል፡፡ ነገር ግን አንርሳ፡፡ በእያንዳንዱ ሕፃንና ታዳጊ አእምሮ፣ ተዓምር የሚያሰኝ እውቀት አቅም ነው፡፡
የእያንዳንዱ ወጣት፣ ምትሃትን የሚያስንቅ የፈጠራ፣ የሙያና የስራ አቅም ነው፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያዊ መልካምን መመኘት፣ ከፍታን መውደድ ማጣጣም፣ ወደ ከፍታ መጓዝ፣ ከከፍታም ወደ ከፍታ እየላቀ በስኬት ላይ ስኬትን እየደመረ ትንግርት የመስራት ብቃትን መቀዳጀት ይችላል፡፡
ድንቅ ብርሃን፣ ድንቅ አገርና ድንቅ ሕይወት፤ በእያንዳንዳችን ውስጥ መኖሩን ልብ እንበል፡፡ መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን!!

Saturday, 31 August 2019 13:48

ምርቃት

(… አይነቱ ብዙ ነው)
ለማኙ ይመርቅሃል፡፡ አሮጊቷ ይመርቁሃል፡፡ ሆቴል ተከፍቶ ይመረቃል፡፡ ከኮሌጅ ትመረቃለህ፡፡ የደሞዝ ቦነስ ይመረቅልሃል፡፡ ቅቅል በልተህ የመረቅ ጭማሪ ታስመርቃለህ፡፡
በገጠር ሰዎች ስም የሚሸቅል አንድ ጩሉሌ የዕርዳታ ድርጅት ደግሞ የደከመ የቦኖ ውሃ ያሰራል:: ከዛም የወረዳው አስተዳዳሪ በክብር እንግድነት ተጋብዞ፣ ከፊት ተቀምጦ፣ ወደ መድረክ ቀርቦ፣ ስለ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፣ ስለ መልካም አስተዳደር ስለ ዴሞክራሲ፣ ስለ ሰላማዊ ምርጫ፣ ስለ ጸረ ሰላም ኃይሎች፣ ስለ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ስለ በጥልቀት መታደሰ አልተገናኝቶ ነገር ለፍልፎ፣ በአጀብና በጭብጨባ ቦኖው ወዳለበት ቦታ ሄዶ፣ የባህል ቀሚስ ከለበሰች ጩጬ ልጅ መቀስ ተቀብሎ፣ የጩጬዋን ጉንጭ አገላብጦ ስሞ፣ ሪባኑን ሁለት ቦታ ቆርጦ፣ ቧንቧውን ከፍቶ ውሃውን ቀምሶና ሕዝቡን አስጨብጭቦ ቦኖውን ይመርቀዋል፡፡
ደሞዝ የማይበቃቸው፣ ኑሮ ያካለባቸው አራት የኢቲቪና አዲስ ዘመን ጋዜጠኞች ዳጎስ ያለ ውሎ አበል ተከፍሏቸው ይመጡና፣ ነገርየውን እንደ ትልቅ ልማታዊ ዜና አካብደው ይዘግቡታል:: መጨረሻ ላይ 47 ገጽ የሚሞላው Evaluation Report በExternal Consultant  ተረቅቆ ‹‹በዚህ ቦኖ መሰረት ሳቢያ ሆዱን የሚያመው አበሻ በ16% ቀነሰ፣ ሴቶች ታጥበው ቀሉ ወደ ጅረት ወርደው ውሃ የሚቀዱበት ሰዓት ስላጠረላቸው ጤና ጣቢያ ሄደው መውለድ ጀመሩ፤ ሕጻናት ወፈሩ፣ Climate Changeን ለመከላከል በተዘዋዋሪ ተጽእኖ ፈጠረ…›› ምናምን የሚል ጆካ ሪፖርት ተጽፎ፣ ሴቶችና ሕጻናት ውሃ ጠጥተው ፈገግ ሲሉ የተነሱት ፎቶ ተጨምሮበት ለፈረንጅ ይላካል፡፡
(ይሄኛው ምርቃት ግን የተለየ ነው)
***
ልጅቷ አንድ የግል ኮሌጅ ውስጥ ሰቃይ የነርሲንግ ተማሪ ነበረች፡፡ Bird Chick ያስባሏት 3 ነገሮች አሏት፡፡ ቀይ ነች፡፡ ከኋላ ነፍፍ ነገር ነች፡፡ ቦርጭ የላትም፡፡ ሌላው ውብቷ የቦዲ፣ የቃርያ ጅንስ፣ Victoria’s Secret ሊፕ ግሎስ፣ ከፓኪስታን ወይዘሮ ጭንቅላት ላይ ተቆርጦ የመጣ Human Hairና ፊቷ ላይ የለደፈችው የFair and Lovely ክሬም ድምር ውጤት ነው፡፡
(…እንደ ዱሮ ደራሲ ልብን የሚያርደው፣ ብርሃን የሚረጨው፣ አሎሎ መሳይ ኩሩው ዓይኗ፣ ሰልካካው አፍንጫዋ፣ የሮማን ፍሬ የሚመስለው ዲምፕላሙ ጉንጯ፣ እንደ ሲዳማ በቆሎ እሸት መጠንና ቅርጹን ሳይስት የተደረደረው ሃጫ በረዶ የመሰለው ነጭ ጥርሷ፣ እንደ ብስል እንጆሪ ብሉኝ፣ ብሉኝ ግመጡኝ ግመጡኝ የሚለው ከንፈሯ፣ ጥቁረቱ ሃርን የሚያስንቅ፣ ጀርባዋ ላይ ተዘናፍሎ እንደ ዘንዶ የተጠመለለው ጸጉሯ እንደ ታንክ አፈ ሙዝ ቀጥ ብለው የተሰደሩት ጡቶቿ… ምናምን ብለን እንዘግባት እንዴ?)
የማታ እየተማረች የቀን አንድ የግል ሆስፒታል ውስጥ በተለማማጅነት ገብታ መስራት ጀመረች:: በሥራም፣ በቅልጥፍናም፣ በተግባቢነትም እሳት የላሰች ስለነበረች እንደተመረቀች እዛው አስቀሯት፡፡ የማታ የዲግሪ ትምህርቷ ቀጠለች፡፡ ታማሚውም፣ አስታማሚውም፣ አካዳሚውም ሁሉም የሚወዷት ጎበዝ ነርስ ሆነች፡፡ ‹‹ካይን ያውጣሽ›› ተባለች፡፡
ለሶስት ዓመታት ከሰራች በኋላ ‹‹በቃኝ›› ብላ ሥራ አቆመች፡፡ የሥራ ልምድም ሳትጠይቅ፣ ቻውም ሳትል ጥላ ጠፋች!
***
ሥራዋን ለቅቃ ከጠፋች በኋላ በስድስተኛው ወር ወደ ሆስፒታሉ ሄደች፡፡ ሃኪሞቹን በምሳ ሰዓት ላይ የሚበሉበት ካፌ ውስጥ አገኘቻቸው፡፡
‹‹አንቺ አለሽ እንዴ?››
‹‹ስልክ አታነሺም?››
‹‹ትገርሚያለሽ!››
‹‹እንዴት ነሽ ግን?››
‹‹ጠፋሽ››
‹‹ተስማማሽ››
ምናምን ተባባሉና ለምን ሥራ እንደለቀቀች፣ አሁን ምን እየሰራች እንደሆነ ጠየቋት፡፡ ‹‹አሁን በግሌ እየሰራሁ ነው - አሪፍ ነገር ጀምሬያለሁ፡፡››
‹‹ምን?››
‹‹አትላስ አካባቢ ጫት ቤት ከፍቻለሁ:: በጣም ቢዝነስ አለው፡፡ አሁን ለምዷል፡፡ ግን ገና አልተመረቀም፡፡ እናም ቅዳሜ ከሰዓት ጀምሮ መጥታችሁ እንድትመርቁልኝ ልንገራችሁ ብዬ ነው የመጣሁት›› አለችና ለያንዳንዳቸው የምረቃ ጥሪ ካርድ አደለቻቸው፡፡
(ደርቀው ቀሩ!)
አንዱ የገባው ዶክተር ‹‹ያዋጣል ብለሽ ነው?››
‹‹ቀላል! ፀዳ ያለ ሰው ነው እሚመጣበት፡፡ በክላስ የሚቅሙ ነጋዴዎችና ኮንትራክተሮች አሉ፤ በጣም ቢዝነስ አለው፡፡ ኪራዩ ትንሽ ውድ ነው፤ በወር ሰላሳ ሺ ብር ነው የተከራየነው፡፡ አንድ እዚህ ሲታከም ከተዋወቅኩት ሰውዬ ጋራ ነው በሼር አብረን የከፈትነው፡፡ ግን ገበያ አለው፤ ሺሻው ብቻ ኪራዩንና የሰራተኞችን ወጪ ይችላል፡፡”
‹‹እና ህክምናውን ተውሽው!›› ጠየቋት - ሽማግሌው ሀኪም፡፡
‹‹ውይይይ ዶክተርዬ፤ ሁሌ በሽተኛ ማየት አይደብርም? ኑሮ ራሱኮ በሽታ ነው! በዛ ላይ የሰው አመል እንኳንስ ታሞ እንዲሁም አልተቻለም፡፡… እኔ ድሮም ፈታ ያለ ነገር ነው እሚመቸኝ፡፡ ጭንቀታም ፊት አልወድም፡፡ … ደሞ ደሞዙስ? ደሞዝ ነው እንዴ? አንተ እራስህ መች አለፈልህ? ያንን ሁሉ አመት ተምረህ ተምረህ፣ ስንቱን በሽተኛ ፈውሰህ አድነህ ምን ተረፈህ? ስም ብቻ እኮ ነው የተረፈህ::… ሰው ቁጭ ብሎ ስልክ ብቻ ተደዋውሎ፣ አየር ባየር  ከብሮ ያድራል፡፡ አንተ የሰው ሆድ ቀድድህ እየሰፋህ፣ ‹ዳነልኝ ወይንስ ሞተብኝ?› የሚል ጭንቅ ነው የተረፈህ፡፡››  
የሥራ ሰዓት ደረሰ፤ ተለያዩ፡፡… ሃኪሞቹ ከራሳቸው ጋር መሟገት ጀመሩ፡፡
(ከኢዮብ ምህረትአብ ዮሐንስ
 “ቼ በለው!” መጽሐፍ የተቀነጨበ)

 ሱዳን የተመድ ሰላም አስከባሪ ከዳርፉር እንዲወጣ ጠየቀች

          አዲሱ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ፣ አሜሪካ፣ ሱዳንን ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር ውስጥ እንድታስወጣ ጥረት ማድረግ መጀመራቸውን እንዳስታወቁ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአሶሼትድ ፕሬስ በሰጡት መግለጫ፤ ሱዳንን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የተጀመረው ጥረት ስኬታማ ይሆን ዘንድ ሽብርተኝነትን የሚደግፉ አገራት በሚል በአሜሪካ ከተመዘገቡት አገራት ተርታ ማስወጣት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት በመጠቆም፣ ይህንን እውን ለማድረግ፣ ከአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ማስታወቃቸውን  ዘገባው አመልክቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ1993 በዝርዝሩ ውስጥ የተካተተችው ሱዳን፣ ከአሜሪካ የሽብርተኝነት ዝርዝር ውስጥ መውጣቷ ለውጭ ኢንቨስትመንት በሯን እንድትከፍትና እጅግ ወሳኝ የሆነውን የገንዘብ አቅርቦት ከአለም ባንክና አይኤምኤፍ ለማግኘት እድል የሚሰጣት በመሆኑ፣ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ መናገራቸውንም አመልክቷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ ሱዳን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፣ በዳርፉር የሚገኘውን የሰላም አስከባሪ ጦር በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እንዲያስወጣ መጠየቋን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በተመድ የሱዳን አምባሳደር ኦመር ሞሃመድ ሲዲግ፣ ባለፈው ሰኞ ለጸጥታው ምክር ቤት ባቀረቡት አቤቱታ፣ የሰላም ማስከበር ተልዕኮው የሚያበቃበት ጊዜ ላይ መድረሱን በመጠቆም፣ ተመድ በዳርፉር አካባቢ መንግስት፣ የጦር መሳሪያዎችንና ወታደሮችን እንዳያንቀሳቅስ የጣለውን እገዳ ሊያነሳ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
የጸጥታው ምክር ቤት ባለፈው ሰኔ ወር ባደረገው ስብሰባ፣ ሱዳን በጸጥታ ችግር ውስጥ በመግባቷ በዳርፉር የሚገኘው የሰላም አስከባሪ ጦር ከአካባቢው የሚወጣበት ጊዜ እንዲራዘም መወሰኑን ያስታወሰው ዘገባው፤ እ.ኤ.አ በ2003 በዳርፉር የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ ወደ አካባቢው የገቡ 5 ሺህ 600 ሰላም አስከባሪ ወታደሮች አሁንም በዳርፉር እንደሚገኙና የአፍሪካ ህብረት ግን በዳርፉር ያለው ሁኔታ ገና ባለመረጋጋቱ የሰላም አስከባሪው እንዲወጣ የቀረበውን ጥያቄ ተገቢ አይደለም ሲል መተቸቱን አመልክቷል፡፡

 ባለፈው ሰኞ በሊቢያ የባህር ዳርቻ በደረሰ አደጋ፣ 40 አፍሪካውያን ስደተኞች ለሞት መዳረጋቸውን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ ባለፉት ስምንት ወራት ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ አገራት ለመግባት ሲሞክሩ ለሞት የተዳረጉ ስደተኞች   ቁጥር 900 መድረሱን አመልክቷል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በሊቢያ የባህር ዳርቻ በደረሰው የጀልባ አደጋ 60 ያህል ስደተኞች ከሞት መትረፋቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ አብዛኞቹም የሱዳን፣ የግብጽና የሞሮኮ ዜጎች መሆናቸውን ገልጧል፡፡ ባለፈው ወር በዚያው አካባቢ በደረሰ ተመሳሳይ አደጋ፣ 150 ስደተኞች ለሞት መዳረጋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ባለፈው አመት ብቻ በሜዲትራኒያን ባህር በደረሱ አደጋዎች ከ2 ሺህ 240 በላይ አፍሪካውያን ስደተኞች የገቡበት ሳይታወቅ መቅረቱን አመልክቷል፡፡

 ባለፈው አመት የፎርብስ መጽሄት ከፍተኛ ተከፋይ ሴት የፊልም ተዋንያን ዝርዝር ውስጥ በአንደኛ ደረጃ ላይ የነበረችው ታዋቂዋ የሆሊውድ የፊልም ተዋናይት ስካርሌት ጆሃንሰን፣ ዘንድሮም በ56 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ክብሯን ማስጠበቋ ተነግሯል፡፡ በአመቱ 44.1 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘችው ሌላዋ የፊልም ተዋናይት ሶፍያ ቬርጋራ በሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ያስታወቀው ፎርብስ፤ ሬሲ ዊዘርስፑን በ35 ሚሊዮን ዶላር ሶስተኛ ደረጃን መያዟን አመልክቷል፡፡
ኒኮል ኪድማን በ34 ሚሊዮን ዶላር፣ ጄኔፈር አኒስተን በ28 ሚሊዮን ዶላር፣ ኬሊ ኩኮ በ25 ሚሊዮን ዶላር፣ ኤልሳቤት ሞስ በ24 ሚሊዮን ዶላር፣ ማርጎት ሪቤ በ23.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ቻሊዜ ቴሮን በ23 ሚሊዮን ዶላር፣ ኤለን ፖምፒዮ በ22 ሚሊዮን ዶላር እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ የፊልም ተዋንያን መሆናቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በተመሳሳይ መረጃ ደግሞ ቴለር ስዊፍት የአመቱ ከፍተኛ ተከፋይ ሴት ሙዚቀኛ መሆኗንና ድምጻዊቷ ባለፉት 12 ወራት ጊዜ ውስጥ በድምሩ 185 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን ፎርብስ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
ቢዮንሴ ኖውልስ 81 ሚሊዮን ዶላር፣ ሪሃና 62 ሚሊዮን ዶላር፣ ኬቲ ፔሪ 57.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ፒንክ 57 ሚሊዮን ዶላር፣ አሪያና ግራንዴ 48 ሚሊዮን ዶላር፣ ጄኔፈር ሎፔዝ 43 ሚሊዮን ዶላር፣ ሌዲ ጋጋ 39.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ሴሌን ዲዮን 37.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ሻኪራ 35 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት እንደ ቅደም ተከተላቸው እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም ፎርብስ አስታውቋል፡፡

Page 13 of 455