Administrator

Administrator

   1ኛ. ፍፁም የማላሸንፈውን ነገር እንድተው እንዲያደርገኝ
                 2ኛ. የማሸንፈውን ነገር ዳር እንዳደርስ ድፍረት እንዲሰጠኝ
                 3ኛ. በአንደኛውና በሁለተኛው መካከል ያለውን ልዩነት እንዳውቅ እንዲረዳኝ

     በጥንት ዘመን በህንድ አገር የሚነገር አንድ ዝነኛ አፈ - ታሪክ እንዲህ ይላል፡፡
ከሂማሊያ ተራራ ግርጌ በሚፈሰው በታወቀው የጋንጀስ ወንዝ ዙሪያ የሚኖሩ የተለያዩ ዓይነት ሰዎች ነበሩ ይባላል፡፡ ከልዩነታቸው ሁሉ በተለየ የሚያጨቃጭቃቸው የውሃ ሀብታቸው ነበር፡፡ ሁሉም ስለ ውሃቸው ጉዳይ ከመንደሩ ብልህ አዛውንት ፊት እየቀረቡ በየጊዜው ይከራከራሉ፡፡
“የእኛ ውሃ ከተራራ አለት መካከል የሚፈልቅ በመሆኑ ጥራት አለው፡፡ ከዚያ ሌላ በመጠጥም ቢሆን በማናቸውም አቅጣጫ ከሚፈሰው ውሃ ብዛት አለው፡፡ ስለዚህ ለጋንጀስ ወንዝ ትልቅ አስተዋፅኦ ያለን እኛ ነን፡፡” ይላሉ፡፡
ከሂማሊያ ተራራ በተቃራኒው አቅጣጫ የሚኖሩት ሰዎች ደግሞ፤
“የለም፤ የተሻለ ውሃ ያለን እኛ ነን፡፡ የእኛ ውሃ ብዙ ማዕድን ያለው፣ በጥንታዊነቱም የታወቀ፣ የበለፀገ ሀብት ያለው፣ ዙሪያ ገባውን እያራሰ፣ የሜዳውን መስክ እያረሰረሰና መስኩን እያለመለመ፣ ለከብት ግጦሽ ጭምር የሚያገለግል ነው፡፡ ዋና ተጠቃሚ መሆን ያለብን እኛ ነን” ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
ከሁለቱ ወገኖች የሚለዩት ከሂማሊያ ጀርባ የሚኖሩት ሶስተኛዎቹ ሰዎች፤
“የእኛን ውሃ የሚያክል በፍፁም የለም! ምክንያቱም የኛ ውሃ ፀበልነት አለው፡፡ ቅዱስ ነው፡፡ ስንቱ ቢስ - ገላ፣ ስንቱ ሽባ፣ ስንቱ በሽተኛ የሚፈወስበት ነው፡፡ አገር የሚድነው በእኛ ውሃ ነው፡፡ ስለዚህም የተሻለ አስተዋፅኦ ስላለን የተሻለ ጥቅም ይገባናል” ይላሉ፡፡
በአራተኛ ወገን ቆመው የሚከራከሩትና ከሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ የሚፈሰው ወንዝ ዙሪያ የሚኖሩት ሰዎች በበኩላቸው፤
“ከማናችሁም የተሻለ ገባር፣ ወንዝ ያለን እኛ ነን፡፡ ለምን ብትሉ የእኛ ውሃ ገስጋሽ ነው፡፡ ኃይል አለው፡፡ ትልቁን የጋንጀስ ወንዝ እየገፋ፣ አቅም እየሰጠ፣ የሚያንቀሳቅሰቀው የእኛ ውሃ ነው!” አሉ፡፡
እንግዲህ የአራቱም ወገኖች ክርክር ዳኝነት እንዲያገኝ የሚጠበቀው ከመንደሮቹ አባት ከብልሁ አዛውንት ነው፡፡ አንዳቸው በጥራት አንዳቸው በማዕድን ይዞታ፣ አንዳቸው በፈዋሽነት፣ አንዳቸው በፍጥነትና በኃይል የተሻልን ነን በሚል የተሻለ ጥቅም ጠየቁ፡፡
የመንደሩ ብልህ አዛውንት ሁሉንም ካዳመጡ በኋላ፣ ሰፈራቸው ላይ ወጥተው፤
“ኑ ተከተሉኝ” አሉና ከመንደሩ ርቀው የጋንጀስ ወንዝን ተከትለው ጋለቡ፡፡ አራቱም ወገኖች እየጋለቡ ተከተሉ፡፡ መንደሮቹን ወደ ኋላ እየተዉ ፍፁም ከማይታዩበት ሌላ አካባቢ ሲደርሱ አዛውንቱ ወረዱና፤
“ይሄ ማን የሚባለው ወንዝ ነው?” ሲሉ አራቱንም ወገኖች ጠየቁ፡፡
“የጋጀስ ወንዝ ነዋ!” ሲሉ መለሱ፤ ሁሉም በአንድ ድምፅ፡፡
አዛውንቱም፤ “መልካም፡፡ በሉ አሁን እያንዳንዳችሁ የየራሳችሁን መንደር ውሃ ከዚህ ወንዝ ውስጥ አውጡና አሳዩኝ!” ሲሉ ጠየቁ፡፡ አንዳቸውም የኔ ነው የሚሉትን ውሃ ሊያሳዩ አልቻሉም፡፡ የሁሉም መንደር ውሃ አንድ ጋንጀስ ሆኗል፡፡
*         *       *
ሁሉም ገባር ወንዞች ተቀላቅለው ወደ አንድ ትልቅ ወንዝ ይፈስሳሉ፡፡ ማናቸውንም ከሌላው መለየት የማይቻልበት ደረጃም ይደርሳሉ፡፡ የእኔ መንደር ውሃ ከሌላው መንደር ውሃ ይበልጣል የሚለውን አስተሳሰብ የጋንጀስ ወንዝ ይዞት ሄዷል፡፡ ሁላችንም ስለ ትልቅ ስዕል ማሰብ ስንችል አገር እናድናለን፡፡ ትልቁ የጋንጀስ ወንዝ ትናንሾችን ገባር ወንዞች ሁሉ ጠቅልሎ፣ አንድ ወንዝ ሆኖ መፍሰስ፣ የአንድን ትልቅ አገር ህልውና ምስል ይሰራልናል፡፡
ፍትሕም፣ ዲሞክራሲም፣ መልካም አስተዳደርም፣ የፖለቲካ ጥራትም፣ ንፁህ እጅም አንድ ላይ በአግባቡ ሲፈስሱ፣ አገር የመንቀሳቀስ ኃይልና አቅም ታገኛለች፡፡ የእኔ አስተዋፅኦ ይበልጣል ብሎ ተገዳድቦ መለያየት የአንድነት ፀር ነው፡፡ አገርን ይሸረሽራል፡፡ አቅምን ያኮስሳል፡፡
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤
“የአበሻ መኪና አነዳድ በሌላው መንገድ
መገድገድ፣ የአበሻ ንግድ የሌላውን ንግድ ማሽመድመድ›› የሚለን፤ ይሄንኑ ሀቅ ለማፀህየት ነው!
ተነጣጥለን ልዩነትን በማስፋት የትም አንደርስም፡፡ ኅብር ልንፈጥር የምንችለው ዜማችን አንድ ሲሆን ነው፡፡ ፍቅራችን ከልብ ሲሆን ነው፡፡ ከልብ መደማመጥ ስንችል ነው፡፡ ልዩነት ቢኖረን እንኳን በሠለጠነ ጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት አሊያም ተከባብሮ መቀመጥ ስንችል ነው፡፡ ለዚህ ቁልፉ በመቻቻል ማመንና በተግባር ማሳየት መቻል ነው፡፡ ትዕግሥት ፍርሃት አለመሆኑን የምናውቀውን ያህል፤ አጉል ድፍረትና አጉራ-ዘለል ፖለቲከኝነት ወንዝ እንደማያሻግር ማወቅ ያስፈልጋል…
ዛሬ ‹‹በቆሼ ሠፈር›› የደረሰውን አሰቃቂ አደጋ በሐዘንና በቁጭት እናስበዋለን፡፡ አደጋን አስቀድመን ለማሰብ እንችል ዘንድ የህዝብን ፍርሃትና ሥጋት አለመናቅ ዋና ነገር ነው፡፡ ቅን ልቦና ቢኖረን መልካም ነው፡፡ የሕዝብን ደግ ማሰብ፣ የልብ ትርታውን ለማዳመጥ፣ ኑሮውን መመርመር ተገቢ ነገር ነው። ለቅድመ ጥንቃቄ ይጠቅመናል፡፡ አደጋ ከደረሰም በኋላ በኅብረት መረባረብን ህዝብን ለመታደግ አቅምና ልብን መስጠትን፤ ህዝብን ማስተባበርን ሆነኝ ብሎ ማሰብ፣ ከዚያም የሚገኘውን ትምህርት ማጤን፣ አፋጣኝ መፍትሔ ለማግኘትም ሳይነጣጠሉ መጣር ያሻል፡፡ የአገር ጉዳይ ነውና አገር አደጋውን መቋቋሚያ ማሽኖችን ማቅረብ አለባት፡፡ የክሬኖችንና የመቆፈሪያዎችን እጦት መቋቋም ካቃተን የአደጋ አደጋ አለብን፡፡ ወይ ህዝብን ለመርዳት ፈቃደኝነት ማጣት አለ፡፡ አሊያም የችግራችን ጥልቀት አሰቃቂነት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል ማለት ነው፡፡ ለወገን መድረስ ይጠበቅብናል፡፡ ጊዜ እየመረጥን ሳይሆን ሁልጊዜ!! ተከታዩ ጉዳይ የተጎዳውን ህዝብ ማቋቋምና ሌላ ቦታ ለማስፈር ምን አርምጃ እንውሰድ የሚለው ነው፡፡ የሚመለከተው ክፍል ይህን ያስብበታል ብለን እንገምታለን፡፡ አደጋው ድንገተኛና በችግር ላይ ችግር የፈጠረ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ አገራችን አንዴ በጎርፍ አንዴ በድርቅ፣ አሁን ደግሞ በናዳ፣ መጠቃቷን እናያለን፤ ችግር ፈቺ ዘዴንና ቅድመ ዕቅድን  የማዘጋጀትን ሥራ አቅም በፈቀደ መሥራት አለብን፡፡ አገራችን የችግር ቋት መሆኗን ደጋግመን አውስተናል፡፡ የፖለቲካውን፣ ኢኮኖሚውንና የማኅበራዊውን ድርብርብ ችግር በቅደም ተከተል የምንፈታበትን ዘዴ ካላዘጋጀን ወደ ባሰ ማጥ ልንገባ እንችላለን፡፡ አቅምን አግዝፎ ማየትም፣ ከልኩ በታች አቀጭጮ ማየትም አደጋ ነው፡፡ ስለዚህ ፀሎተኛው እንዳለው፤ አምላክን የምለምነው ሶስት ነገሮች፡-
1ኛ/ ፍፁም የማላሸንፈውን ነገር እንድተው እንዲያደርገኝ
2ኛ/ የማሸንፈውን ነገር ዳር እንዳደርስ ድፍረት እንዲሰጠኝ
3ኛ/ በአንደኛውና በሁለተኛው መካከል ያለውን ልዩነት እንዳውቅ እንዲረዳኝ ነው ማለት ብልህነት ነው፡፡
አደጋ ለደረሰባቸው ሁሉ ፅናቱን እንዲሰጣቸው እንመኛለን!!

Saturday, 18 March 2017 15:06

ከልብ አዝነናል!!

“ቆሼ” እየተባለ በሚጠራው ሥፍራ በደረሰው አደጋ በርካታ ወገኖቻችን ለህልፈት በመዳረጋቸው የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለፅን፣ ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መፅናናትን እንመኛለን፡፡ በተመሳሳይ በጋምቤላ ክልል፣ የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ታጣቂዎች በፈፀሙት ጥቃት ህይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያውያን ጥልቅ ሀዘናችንን እየገለፅን፣ ለቤተሰቦቻቸው ፅናቱን እንመኛለን!! ታፍነው የተወሰዱትን 43 ህፃናትን
ለማስመለስም መንግስት የማያወላውል ቁርጠኝነቱን እንደሚያሳይም ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ለአገራችን መልካሙን ዘመን ያምጣልን!!
                   አዲስ አድማስ - የእርስዎና የቤተሰብዎ

Monday, 20 March 2017 00:00

ማረሚያ

    ባለፈው ሳምንት የጋዜጣው ዕትም “በማዕተብ ጉዳይ ከመምህሩ ጋር የተጋጨው ተማሪ ራሱን አጠፋ” በሚል ርዕስ በወጣው ዜና ላይ ተማሪው የጅማ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ኮሌጅ ተማሪ እንደሆነ የተገለፀው በስህተት ሲሆን ተማሪው በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ በሚተዳደር “የጅማ መምህራን ኮሌጅ” ይማር የነበረ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡ ለተፈጠረው ስህተት ውድ አንባቢያንንና የጅማ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብን ልባዊ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

    በአዲስ አበባ፣ የካ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 12፣ ልዩ ስሙ አባዶ ቁጥር 1 እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የተሠራችው የደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ  ቤተ ክርስቲያን፣ ሕገ ወጥ ግንባታ በሚል በደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱ በከፊል የፈረሰባቸው መኾኑን የገለጹ ካህናትና ምእመናን፣ የድረሱልን ጥሪ አሰሙ፡፡
በከተማው መልሶ ማልማት ወደ አካባቢው የሔዱት ነዋሪዎቹ፣ ሥርዓተ አምልኰ የሚፈጽሙበት ቤተ ክርስቲያን ተቸግረው መቆየታቸውንና ከአራት ወራት በፊት፣ ከግለሰቦች በስጦታ ባገኙት ቤትና ቦታ ላይ በሀገረ ስብከቱ ፈቃድ በቅድስት አርሴማ ስም ቤተ ክርስቲያን ተክለውና አስባርከው በመገልገል ላይ እንደነበሩ ካህናቱና ምእመናኑ ገልጸዋል፡፡500 ካሬ ሜትር ስፋትና 30 ቆርቆሮ ቤት ያለውን ቦታ ለመኖርያና ለእርሻ ይገለገሉበት የነበሩት ግለሰቦች፣ በስማቸው ተመዝግቦ ግብር ይገብሩበት እንደነበርና ሕጋዊ ባለይዞታዎች ለመኾናቸው የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዳላቸው ካህናቱና ምእመናኑ ጠቅሰዋል፤ ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያ በስጦታ ሲያበረክቱም፣ በውል ተቀባይነት የተረከቡት፣ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የተወከሉ የመሥራች ኮሚቴው ካህናት መኾናቸውን አስረድተዋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤትም፣ የነዋሪዎቹን ማመልከቻና በአባሪነት ያቀረቧቸውን ማስረጃዎች መሠረት በማድረግ፣ ቤተ ክርስቲያን ለማነጽ ይቻል ዘንድ የወረዳው አስተዳደር ጽ/ቤትና የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ በደብዳቤ መጠየቁን አውስተዋል፡፡
ኾኖም፥ የወረዳው አስተዳደር፣ ከኹለት ሳምንት በላይ አንዳችም ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቷል፤ ያሉት ካህናቱና ምእመናኑ፣ ዝምታውን እንደ ይኹንታ በመቁጠር፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የታዘዘላቸውን ጽላት አስገብተው መንፈሳዊ አገልግሎት መጀመራቸውን ገልጸዋል፤ የግለሰብን ቤት በቀጥታ
ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መጠቀም ስለሚከብድም፣ ዲዛየኑንና ቆርቆሮውን መቀየራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን በማከናወን ላይ ሳሉም፣ የወረዳው የደንብ ማስከበር ጽ/ቤት፣ የንብረት ማስቀመጫ ኮንቴይነሩ ብቻ ሲቀር ሌላውን አፍርሶ ንብረቱን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ማስገባቱን፣ ስምንት ካህናትም መደብደባቸውንና የመሥራች ኮሚቴው አባላትም ለአራት ቀናት ታስረው
እንደነበር ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡የታሰሩት ከተፈቱ በኋላ፣ ጉዳዩ በሕግ ታይቶ ባለመብት መኾናቸው እስኪረጋገጥ፣ ያለው ንብረት ቁልፉ ተከብሮ እንዲቀመጥ በፍርድ ቤት የእግድ
ትእዛዝ ቢያስወጡም፣ አጥሩና ምእመናኑ ለጥላ የሚገለገሉበት ሸራ፥ በደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱ መፍረሱን፤ ዶማ፣ አካፋ፣ ድጅኖ የመሳሰሉ መሣሪያዎችም መወሰዳቸውን፤ ዘወትርም ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው እንዳለ ዘርዝረዋል፡፡“ሕገ ወጥ ብንኾን፣ በሕግ እንጠየቃለን እንጂ ኢሰብአዊ በኾነ ኹኔታ ሊደበድቡንና ዘወትር እያስፈራሩን ሊቀጥሉ አይችሉም፤” ያሉት አንድ ካህን፣ መንግሥት ስለ እምነት ነጻነት ከሚናገረው አንጻር፣ “እነዚኽ ሰዎች እነማን እንደኾኑ ለመናገር እንቸገራለን፤” ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡በአኹኑ ወቅት በመቅደስነት የሚገለገሉበት፣ የንብረት ማስቀመጫ ኮንቴነር መኾኑን ጠቅሰው፣ ለአራት ወራት የተቀደሰበት ቤተ ክርስቲያን እንዳይፈርስና ተረጋግተው ማገልገል እንዲችሉ፣ ለክፍለ ከተማ አስተዳደሩ የደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ትእዛዝ እንዲሰጥላቸው፣ ለከንቲባው ጽ/ቤት መጠየቃቸውን አመልክተዋል፤ ጉዳዩ በፍ/ቤት ለመጋቢት 27 ለውሳኔ መቀጠሩንም አስታውቀዋል፡፡   ስለጉዳዩ የደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱን አስተያየት በስልክ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ፣ ጥሪ ባለመመለሱ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡





    አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ከትናንት በስቲያ በሸራተን ሆቴል በላኪነት፣ በአስጎብኚነት፣ በማማከርና በገንዘብ አስቀማጭነት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ደንበኞቹ የሰርተፍኬትና በሦስት ደረጃ የዋንጫ ሽልማት ሰጠ፡፡
የፕላቲኒየም ተሸላሚ የሆኑት ድርጅቶች ካቤ ፒኤልሲ፣ የይርጋጨፌ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየን፣ ሐግቤስ ፒኤልሲና ግሪንላንድ ፒኤልሲ ሲሆኑ ሌሎችም የወርቅና የብር ዋንጫ ተሸልመዋል፡፡
አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ በአብዛኛው በኅብረት ስራ ማህበራት፣ እድሮች፣ አነስተኛ የብድር አቅራቢ ተቋማትና ግለሰቦች የተመሰረተ ሲሆን የባለአክሲዮኖቹም ቁጥር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከ300,000 በላይ ይሆናል፡፡
ባንኩ ከጊዜ ወደ ጊዜ የቅርንጫፍ ስርጭቱን በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ለንግድ ስራ ምቹ በሆኑ ቦታዎች እያስፋፋ ሲሆን ሞባይልና ኢንተርኔት አገልግሎት ጨምሮ፤ ሁሉንም ቅርንጫፎቹን በመረጃ መረብ በማገናኘት ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ታውቋል፡፡



የዘንድሮ የአድዋ በዓልን አስመልክቶ ለአራተኛ ጊዜ የተካሔደው ከአዲስ አበባ አድዋ ‹‹ጉዞ አድዋ 4›› የእግር ጉዞ ከጥር 9 ጀምሮ የካቲት 23 ቀን 2009 ዓ.ም በደማቅ አቀባበል በአድዋ ከተማ መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡ የእግር ጉዞውን በስኬት ያጠናቀቁ ተጓዦችን በደማቅ ስነስርዓት ለመቀበል
የፊታችን ሰኞ መጋቢት 11 ቀን ከምሽቱ 11፡45 ጀምሮ በአምስት ክሎ ብሔራዊ መዚየም ቅጥር ግቢ በሚገኘው ሉሲ ሬስቶራንት አዳራሽ፣ ልዩ ልዩ ኪናዊ ዝግጅቶችና የእራት ምሽት ተዘጋጅቷል፡፡
ለዘንድሮው ጉዞ አድዋ መሳካትና በሀገር አቀፍ ደረጃ የዓድዋ ክብረ በዓል ደማቅ እንዲሆን የላቀ ሚና ያበረከቱ የሚዲያ ተቋማትና ግለሰቦች የክብር አቀባበሉ ሥነስርዓት ተካፋይ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
‹‹ጉዞ ዓድዋ›› በቀጣይ ዓመታት የአፍሪካ ተጓዦችን በእግር ጉዞው ለማሳተፍ ያለውን እቅድም በይፋ የሚገልጽበት ምሽት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

 

  የቀድሞ የህፃናት አምባ ውስጥ አድገው በተለያዩ የስራ መስክ በተሠማሩ ግለሠቦች የተቋቋመው ‹‹ትምህርት ለተቸገሩ በጎ አድራጎት ማህበር›› መጋቢት 10 ቀን 2009 ዓ.ም የገቢ ማሠባሠቢያ ፕሮግራም ያካሂዳል፡፡
ከ3 መቶ በላይ የትምህርት እድል ማግኘት ያልቻሉ ህፃናትን በኮተቤ ኪዳነምህርት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በከፈተው ትምህርት ቤት በማስተማር የሚታወቀው ማህበሩ፤ በአሁኑ ወቅት ይህን በጎ ተግባር ለማከናወን የአቅም ውስንነት ስላጋጠመው የእርዳታ ማሠባሠቢያ መርሃ ግብር ለማዘጋጀት መገደዱን አስታውቋል።
በዚህም መሰረት መጋቢት 10 ቀን 2009 ዓ.ም ከላምበረት አዲሱ መናኸሪያ ተነስቶ እስከ ኮተቤ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን የ3.5 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ በማዘጋጀትና የሙዚቃ ዝግጅትን አካቶ የገቢ ማሠባሠቢያ ሰፊ ፕሮግራም እንደሚያደርግ አስታወቆ፤ በእለቱ ድጋፍ እንዲደረግለት ጥሪ አድርጓል፡፡

 በጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ኮሌጅ የ2ኛ ዓመት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተማሪ፣ የሆነው ወጣት በአንገት ማዕተብ ጉዳይ ከመምህሩ ጋር ተጋጭቶ “የትምህርት ውጤቴ ተበላሸ” በሚል ራሱን አጠፋ፡፡
ተስፋዬ ገመዳ የተባለው ተማሪ የስነ ልቦና ሳይንስ መምህሩ በቡድን ያዘዙትን አሳይመንት ስራ አዘጋጅቶ በመድረክ ላይ ሊያቀርብ ሲል መምህሩ፣ “በአንገትህ ላይ ያደረከውን ማተብ ወይ አውልቅ ወይም ሸፍነው” ሲሉት ተማሪው፤ “ይህ የእምነቴ መገለጫ ነው፤ ያዘዙኝን ማድረግ አልችልም” የሚል ምላሽ እንደሰጣቸውና መምህሩም “ያዘዝኩህን ማድረግ ካልቻልክ የሰራኸውን ማቅረብ አትችልም” በማለታቸው ስራውን ሳያቀርብ መቅረቱንና ከመድረኩ ወርዶ በእጁ የያዘውን የቡድን  ስራ ሪፖርት በንዴት ቀዳዶ መቀመጡን የአይን እማኞች አስታውሰዋል፡፡ በወቅቱ ተማሪው ክፍለ ጊዜውን አቋርጦ ከክፍሉ መውጣቱንና ተመልሶ  ሊገባ ሲል መምህሩ አትገባም ብለው እንደከለከሉትና፣ ተማሪውም ስሜታዊ ሆኖ ከመምህሩ ጋር ለፀብ መጋበዙን፣ ተማሪዎችም በመሃል ገብተው እንደገላገሏቸውና የአካዳሚክ ዲኑ በቦታው ተገኝተው ስለተፈጠረው ችግር ተማሪዎችን በመጠየቅ፣ ፀቡን ማረጋጋታቸውን ተማሪዎች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ ቀን እንደተለመደው ተማሪው የስነልቦና ክፍለ ጊዜ ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ክፍል ሲገባ መምህሩ በድጋሚ ከክፍል እንዳስወጡት፣ ተማሪውም ለአካዳሚክ ዲኑ አቤቱታ ማቅረቡንና ዲኑም የትምህርቱ የመጨረሻ ክፍል ጊዜ ስለሆነ ‹‹በቃ ተወው በውጤትህ ላይ ምንም ለውጥ አያመጣም›› ብለው አረጋግተው እንደሸኙት፣ የተማሪው የቅርብ ጓደኞች ገልፀዋል፡፡
በኋላም ፈተና እንዲወስድ የተፈቀደለት ሲሆን የተለጠፈውን የፈተና ውጤት ሲመለከት ግን “No Grade” (ምንም ውጤት የለም) የሚል ስለነበር ወዲያው በንዴት ወደ ተከራየበት ቤት በማምራት የዚያኑ እለት ራሱን ግቢ ውስጥ ባለ የማንጎ ዛፍ ላይ  ሰቅሎ ማጥፋቱን የቅርብ ጓደኞቹ ገልፀዋል፡፡
ፖሊስና የአካባቢው ህብረተሰብ በቦታው ደርሶ ከተሰቀለበት ሲያወርዱት ነፍሡ ከስጋው  እንዳልተላቀቀችና ወደ ሆስፒታል በመሄድ ላይ ሣለ ህይወቱ ማለፉን የጠቆሙት ምንጮች፤ የቀብር ሥነስርዓቱም ከትናንት በስቲያ በትውልድ አካባቢው በሰሜን ምዕራብ ሸዋ፣ ደገሞ ወረዳ መፈፀሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አስከሬኑን ለቤተሰብ ያደረሱት መርማሪ ፖሊስ ዮሐንስ መገርሳ፤ ተማሪው ከመምህሩ ጋር በመጣላቱ ራሱን  እንዳጠፋ ጥርጣሬ መኖሩንና የሆስፒታል የምርመራ ውጤት በማስረጃነት እየተጠበቀ መሆኑን ጠቁመው፣ ጉዳዩ ገና በመጣራት ላይ ነው ብለዋል - ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፡፡

 ከቻይና ስመ-ጥር የጫማ አምራች ኩባንያዎች አንዱ የሆነውና ከአምስት አመታት በፊት በኢትዮጵያ ፋብሪካውን ከፍቶ የማምረት ስራ የጀመረው ሁጂያን ግሩፕ፤ ኢንቨስትመንቱን ለማስፋፋትና ለ100 ሺ ሰዎች ተጨማሪ የስራ ዕድል ለመፍጠር ማቀዱን አስታወቀ፡፡
ሁጂያን ግሩፕ ለ6 ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያን ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩንና ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ያስታወሱት የኩባንያው ፕሬዚዳንት ዣንግ ሁዋሮንግ፤ 100 ሺህ ያህል አዳዲስ የስራ ዕድሎችን የመፍጠርና ካፒታሉን ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር የማሳደግ ዕቅድ እንዳለው መግለጻቸውን ፒፕልስ ዴይሊ ድረገጽ ዘግቧል፡፡
ኩባንያው በኢትዮጵያ በከፈተው ፋብሪካ እያመረተ ለውጭ ለገበያ የሚያቀርባቸው የጫማ ምርቶች፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልጅ የሆነቺው ኢቫንካ ትራምፕ ያቋቋመቺውን ኢፖኒመስ የተባለ ኩባንያ ጨምሮ በበርካታ የአውሮፓ አገራት ኩባንያዎች ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፋቸውንም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

 ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው ለፍ/ቤቱ ተናግረዋል
                                      
       ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በኃይል ለማስወገድ ሙከራ አድርገዋል እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ድንጋጌዎች ተላልፈዋል በሚልና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ክስ የተመሰረተባቸው ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ለፍ/ቤት ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም፡፡
አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር መረራ ጉዲና የካቲት 24 ቀን 2009 ዓ.ም በነበራቸው ቀጠሮ፣ የተከሰሱት በወንጀል ህጉ ስለሆነና ተከሳሹ ከዚህ ቀደም የነበራቸው የፖለቲካ ታሪክ፣ ከቤልጂየም ሲመለሱ እንደሚታሰሩ እየተነገራቸው እንደመጡና ከሀገር የመኮብለል ፍላጎት የሌላቸው መሆኑ ታይቶ እንዲሁም የስኳር ህመምተኛ በመሆናቸው በዋስትና ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀው እንደነበር ይታወሳል፡፡
አቃቤ ህግም የተጠረጠሩበት ወንጀል ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በኃይል የመናድ ሙከራ በመሆኑ በዋስትና ቢወጡ መረጃ ሊያሸሹ ይችላሉ በሚል የዋስትና ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡
የግራ ቀኙን አስተያየት የመረመረው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፤ ተጠርጣሪው በተከሰሱበት የህግ አንቀፅ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከ15 ዓመት በላይ ወይም በእድሜ ልክ አሊያም በሞት ሊያስቀጣ የሚችል በመሆኑ ዋስትናውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡
በችሎቱ ማጠናቀቂያ ላይ ዶ/ር መረራ የምናገረው አለኝ ብለው ሲፈቀድላቸው፡-
“ከእነ ጀነራል መንግስቱ ነዋይና ጀነራል ታደሰ ብሩ ዘመን ጀምሮ ከአንድ ትውልድ በላይ ገዳዮችና ሟቾች፣ ታሳሪዎችና አሳሪዎች በበዙበት የሀገራችን የፖለቲካ ድራማ ውስጥ በመቆየት አንድ ከሆዱ በላይ ለሀገሩ የሚያስብ ምሁር ማድረግ እንዳለበት ሁሉ፣ ከአርባ አምስት አመታት በላይ ለሀገሩ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ በታማኝነት መታገሌ እየታወቀ ወደ ጎን መገፋቴን፤ ለሁላችንም የምትሆንና በእኩልነት የምታስተናግደን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትፈጠርና ነፃ የፍትህ ስርአት በሀገራችን እንዲሰፍን ላለፉት 25 ዓመታት በመታገሌ መከሰሴ አንሶ የሀገሪቱ ፓርላማ አባል ጭምር የነበርኩት ሰው፣ ለተራ ወንጀለኛ የሚፈቀድ የዋስ መብት በመከልከሌ የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን ለራሴ ብቻ ሳይሆን እኛም ሆንን ልጆቻችን በሰላም ይኖሩበታል በምንለው መከረኛ ሀገራችንና አላልፍለት ብሎ ለታመሰው ለመላው መከረኛ ህዝባችን ጭምር መሆኑ እንዲታወቅልኝ ነው” የሚል ንግግር አድርገዋል፡፡