Administrator

Administrator

  ኤመርሰን ማንጋግዋ ቃለ-መሃላ ፈጽመው ስልጣን ተረክበዋል

   ላለፉት 37 አመታት ዚምባቡዌን የመሩትና የአገሪቱ የጦር ሃይል ስልጣኑን በጊዜያዊነት መረከቡን ተከትሎ፣ ለቀናት ሲያንገራግሩ ቆይተው ባለፈው ማክሰኞ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው የለቀቁት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፤ በጦር ሃይሉ ባለስልጣናት ያለመከሰስ ዋስትና እንደተሰጣቸው ሮይተርስ ከትናንት በስቲያ ዘግቧል።
ሙጋቤ “እስከ ዕለተ ሞቴ በአገሬ ምድር ላይ መኖር እፈልጋለሁ፤ ቀሪ ዘመኔን በስደት መገፋት አልሻም፤ ስለሆነም ለእኔም ሆነ ለባለቤቴ ደህንነት ዋስትና ከተሰጠኝ ስልጣኔን እለቃለሁ” በሚል ለጦሩ መደራደሪያ ሃሳብ መላካቸውን ተከትሎ፣ እሳቸውም ሆኑ ባለቤታቸው ግሬስ በአዲሱ መንግስት ደህንነታቸው እንደሚጠበቅላቸው ቃል እንደተገባላቸው አንድ የአገሪቱ የጦር ሃይል ባለስልጣን መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሙጋቤ ጡረታቸው እንደሚከበርላቸውና የመኖሪያ ቤት ክፍያና የጤና ዋስትናን የመሳሰሉ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን እያገኙ፣ ቀሪ ህይወታቸውን ከቤተሰባቸው ጋር በሰላም እንዲገፉ ሁኔታዎች ይመቻቹላቸዋል መባሉን ዘገባው የጠቆመ ሲሆን፣ ዘ ጋርዲያን በበኩሉ፤ ሙጋቤ ከሶስት አስርት አመታት በላይ በዘለቀው የስልጣን ዘመናቸው፣ የግል ሃብት ለማካበት ያልዳዱና ከአገር ውጭ ምንም አይነት ሃብትም ሆነ ንብረት እንደሌላቸው ዘግቧል። ሚስታቸው ግሬስ በአንጻሩ፤ የከብት እርባታና የወተት ምርቶች ማቀነባበሪያን ጨምሮ በርካታ ንግዶችን እንደሚያከናውኑም አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ዋዞዌ በተባለው የአገሪቱ የገጠር መንደር ውስጥ የሚገኘው የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ ንብረት የሆነ እርሻና የከብት ማድለቢያ ድርጅት፣ ባለፈው ረቡዕ በመቶዎች በሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች መዘረፉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ .
በቀድሞው የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ከስልጣናቸው መባረራቸውን ተከትሎ፣ወደ ደቡብ አፍሪካ የተሰደዱትና ከሁለት ሳምንታት ቆይታ በኋላ ባለፈው ረቡዕ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው የ75 አመቱ ኤመርሰን ማንጋግዋ፤ በትናንትናው ዕለት ቃለ መሃላ ፈጽመው ስልጣን ይዘዋል፡፡
አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ በበኩሉ፤ ዚምባቡዌ የከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንደመዘፈቋ፣ አዲሱ የአገሪቱ መንግስት ከወጪ፣ ከውጭ ብድርና ከሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አፋጣኝ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚገባው ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ማንጋግዋ በበኩላቸው ተቀዳሚ ስራቸው ኢኮኖሚውን ማቃናት እንደሆነ ተናግረዋል። የሙጋቤን ከስልጣን መልቀቅ ተከትሎ በርካታ የውጭ አገራት ኢንቬስተሮች ወደ አገሪቱ ለመግባት ፍላጎት እያሳዩ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ይህም የዶላር እጥረትን ለመቅረፍና ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር የያዙትን ዕቅድ በማሳካት ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

ከጥንታውያን ፋርሶች ተረቶች አንዱ የሚከተለውን ይላል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ መንደር ውስጥ የሚኖር እጅግ ሞገደኛና አስቸጋሪ ወጣት ነበር፡፡ ይህ ወጣት ልጃገረዶችን እየደበደበ ያስቸግራል፡፡ ንብረታቸውን ይቀማል፡፡ ወደ ቤታቸው በጊዜ እንዳይገቡ አግቶ ያስቀምጣቸዋል፡፡ አባቱ አንቱ የተባለና የሚፈራ በመሆኑ፣ ደፍሮ የሚናገረውና ተው የሚለው ቤተሰብ የለም፡፡
ይኼ ወጣት፣ ከልጃገረዶችም አልፎ ወጣት ወንዶችን ያስፈራራል፡፡ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ ያደርጋል፡፡ እያስፈራራ ፍራንክ ይቀበላል፡፡ ደብተር ይነጥቃል፡፡ ለሞገደኛ ተግባሩ ተባባሪ እንዲሆኑ ያስገድዳቸዋል፡፡
ይኼ ወጣት በወጣት ሴቶችና ወንዶች ላይ የሚፈፅመው ጥፋት አልበቃ ብሎት፤ አረጋውያንና አሮጊት ሴቶች እያስፈራራ፣ ቁልቁል ይሄዱ የነበሩትን ሽቅብ፤ ሽቅብ ይሄዱ የነበሩትን ቁልቁል፣ ያስኬዳቸው ነበር። ይህ ሞገደኛ የሰፈር ወጣት፣ ለወላጆቹ ጥፋቱ ተነገረ፡፡ ተው ተባለ፡፡ አሻፈረኝ አለ። ለትምህርት ቤት ዳይሬክተሩ  እንዳይነገር ትምህርቱን ጥሎ ከወጣ ቆይቷል፡፡ እንዲህ በሞገደኝነት እየተቀናጣ ብዙ ጊዜ ሲያስቸግር ከረመ፡፡
አንድ ቀን የሰፈር ልጆች ተሰበሰቡና፤
“እስከመቼ ይሄ ሞገደኛ ሲጫወትብን ይኖራል? አንድ ነገር ማድረግ ይገባናል” ማለት ጀመሩ፡፡
የሞገደኛውን ወጣት የዱሮ ዝና ያስታወሱ አፈገፈጉ፡፡
“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ያሉትም አያመልጥም፤ በጋራ እናሳየዋለን፤ አሉ፡፡
ሁለተኞቹ ወገኖች፤ ሰፈሩን ዙሪያውን ከበን እንያዘው ተባባሉ፡፡ የሞገደኛውን ቤት ከበቡ፡፡ እንደተከበበ ያወቀው ወጣት እቤቱ አጠገብ ካለ ትልቅ ባህር ዛፍ ላይ ወጣ፡፡ ጫፉ ላይ ተቀመጠ፡፡
ተከትሎት ዛፉ ላይ የሚወጣ ጀግና ጠፋ፡፡ ስለዚህ መላ መምታት ተያዘ፡-
አንዳንዶች - እዛው እንዳለ በድንጋይ እንውገረው - አሉ፡፡
አንዳንዶች - የለም ዝም ብለን ብንጠብቀው ሲርበው ይወርዳል-አሉ፡፡
ሌሎች - ቀላሉ መንገድ ለፖሊስ ነግረን እንዲያስወርደው ማድረግ ነው አሉ፡፡
ተቃራኒዎቹ፤ ፖሊስ እጅ ከፍንጅ ሲያጠፋ አልያዝኩትም፤ ዛፍ ላይ መውጣት ወንጀል አይደለም፤ ማስረጃ ሰብስቡ ነው የሚለን አሉ፡፡
ደግሞ ሌሎቹ - ዛፉን ብንቆርጥበት ይወድቃልኮ! አሉ፡፡
የሰፈሩ ወጣቶች ይሄን ይሄንን ሲመክሩ፤ ሞገደኛው ወጣት ድንገት መውረድ ጀመረ፡፡ አካባቢው ሁሉ ፀጥ አለ፡፡ ወጣቶቹ ሲወርድ ምን እንዲያደርጉ ግራ ተጋቡ፡፡ ግማሾቹ ገለል ማለት ጀመሩ፡፡ ግማሾቹ ዱላ አዘጋጁ፡፡ ከፊሎቹ ድንጋይ ያዙ!
ዛፉ ወገብ ላይ ሲደርስ፤
“ለፖሊስ እጄን ልሰጥ ነው፡፡ እንደማትነኩኝ ቃል ግቡልኝ” አላቸው፡፡
“ውረድ ማንም አይነካህም” አሉት፡፡ ፖሊስ ተጠርቶ መጣ፡፡ ወጣቱ ወርዶ እጁን ሰጠ፡፡
“ለዚህ ለዚህ ለምን በፊት እንደዚህ አላደረግህም?” አሉት፡፡
“እንዳስቸገርኳችሁ ጀምሬ እንዳስቸገርኳችሁ ለመጨረስ ስለፈለግሁ ነው!” አላቸው፡፡
*      *     *
መሪዎች አሻፈረኝ ሲሉ ህዝቦች ልክ ያገቧቸው ዘንድ የዲያሌክቲክ ህግ ግድ ይላል፡፡ አምባ - ገነን መሪነት ከአፍ እስከ ገደፏ የሆነችው አፍሪካ፤ በጉልበት ወደ ሥልጣን የሚመጡ፣ በጉልበት ሥልጣን ላይ የሚቆዩና ያለ ጉልበት ከስልጣን አንወርድም የሚሉ መሪዎች ተለይተዋት አያውቁም፡፡ በእርግጥ ከስልሳዎቹ እስከ ዛሬ የአፍሪካ ብቻ ሳይሆኑ የላቲን አሜሪካም መሪዎች አምባገነናዊ ባህሪያቸው አንድ ዓይነት ነው፡፡ ሁሉም ስለ ህዝብ ጥቅም እያወሩ ህዝብን ረግጠው ይገዛሉ፡፡ ሁሉም ስለ ህዝብ ጥቅም እያወሩ የህዝብን ሀብት ይመዘብራሉ፡፡ ሁሉም ስለ ህዝብ ጥቅም፣ ስለ መልካም አገዛዝ፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ ሰላም፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ብሄራዊ ብልፅግና፣ ስለ ሰላም፣ ስለ አብሮ መኖር… ወዘተ ያወራሉ፡፡ ድርጊታቸው ግን ተፃራሪ ነው! ከአፍሪካ ካውንዳ፣ ኢዲ አሚን፣ ሞቡቱ፣ ኦማዱ፣ ቦካሳ፣ አራፕሞይ፣ ሳሙኤል ዶ፣ መንግሥቱ ኃ/ማርያም፣ አሚን፣ ኬንያታ፣ ንጉማ፣ ቦንጎ፣ ሲያድ ባሬ፣ አልባሺር፣ ሴኩ ቲሬ፣ ሀሰን ጉሌድ፣ ካሙዚ ገንዳ፣ ሙጋቤ፣ የሚጠሩት ስሞች ሁሉ ቦታ ቢለዋወጡ ስለ አንድ ሰው የምናወራ ያህል አንድ ናቸው፡፡ የካምቦዲያው ፓል ፖት፣ የቺሊው ፒኖሼ፣ የፓራጉዋዩ ስትሮስነር፣ የፖላንዱ ጃሬ ሴልስኪ፣ የአርጀንቲና ዱዋርቴ፣ የስፔኑ ፍራንኮ ወዘተ… ሁሉም ያው ናቸው! አምባገነን አምባገነን ነው! ምንም ቦቃ አይወጣለትም - በጉልበት ይወጣል፣ በጉልበት ይኖራል፤ በመጨረሻ በጉልበት ይወርዳል!
ሐማ ቱማ የተባለው ኢትዮጵያዊ ፀሀፊ ስለ አካፋና ኢትዮጵያውያን (of spades and Ethiopians) በተባለው የግጥም መድበሉ What is in a name (ከስሙ ምን አለህ? እንደማለት ነው) እንዲህ ይለናል፡-
“… ሌሮይ ጆንስ አልከው ኢማሙ ባራካ
ጆሴፍ ዴ ሲሬ ሴሴኮ ዋዛባንጋ፤
ሊዎፖልድ ሆነ አማዱ
ኬራኩ ሆነ መንግሥቱ፤
አሚን ቦካሣ ቦንጎ
ሐቢብ ሞይ አሊያም ሳሚዶ፤
ስሙ ይቀያየር እንጂ
ሎሌማ ያው ሎሌ’ኮ ነው
ገዳይ ምንጊዜም ገዳይ ነው!
ስማቸውን ብትለዋውጥ
ወይ ቢቀያየር መልካቸው
ሎሌ ሁሌም ሎሌ ነው
ነብሰ - ገዳይ ያው ገዳይ ነው!!
ሁሉን የሚያስረው ሰንሰለት፣
ጫፉ ሌላ ቦታ ነው
አንተ ከሰሙ ምናለህ
ጠማማውን ጭንቅላት እየው እንጂ አዟዙረህ!
እየው ቦታውን ለዋውጠህ!”
ይለናል፡፡ የአምባገነን ስሙና መልኩ እንጂ ሥራውና ሤራው አንድ ነው፡፡
“አምባገነኖች መውረድ ከማይችሉበት የነብር ጀርባ ላይ ሆነው ወደፊትና ወደኋላ ይጋልባሉ፡፡ ነብሮቹ ግን ከቀን ቀን እየራባቸው ይሄዳሉ” ይላሉ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትርና ፀሐፊ፤ ዊንስተን ቸርችል። ሁሉም አምባገነኖች እናታቸው አንድ ናት! አንዳቸውም ከአንዳቸው አወዳደቅ አይማሩም! የታላላቅ ሰዎችን ማንነት፣ ማክበርና ማስከበር ከብዙ ደካማ አገዛዝና ውድቀት ያድናል፡፡ ትልቅን ለማክበር ዝግጁ መሆን፣ ወደ ትልቅነት መንገድ መጀመር ነው፡፡ ተገፍትረው እስኪወድቁ የሚጠብቁ ያልታደሉ መሪዎች ናቸው፡፡ ታላላቅ ሰዎቻቸውን የሚያዋርዱና የሚንቁ መጨረሻቸው አያምርም! ትልቅን ለመሸፈንና እንዳይታይ ለመጋረድ መሞከር የጅል ጥረት ነው! “ጀምበር በእበት አይመረግም” የሚለው የጉራጊኛ ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ዕውነት ነው!

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ አጠቃላይ የሃብት መጠኑ 21 ቢሊዮን ብር መድረሱን የገለፀ ሲሆን በተለያዩ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ለተሰማሩ ባለሀብቶች የሰጠው የብድር መጠንም 10.9 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ አስታውቋል፡፡
የባንኩ የባለአክሲዮኖች 18ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ህዳር 9 ቀን 2010 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ባከናወነበት ወቅት በቀረበው ሪፖርት ላይ
እንደተጠቀሰው፤ በበጀት ዓመቱ ከታክስ በፊት  681.5 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡ ተጠቅሷል፡፡
አመታዊ ትርፉም ካለፈው አመት አንፃር የ48.6 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ የጠቆመው ባንኩ፤ ባለፈው ዓመት 50 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በአዲስ አበባና ክልል ከተሞች መክፈቱንም አስታውቋል፡፡ በአጠቃላይም የቅርንጫፎቹን ብዛት 180 ማድረሱንና 73 አዳዲስ የካርድ ገንዘብ ከፋይ ማሽኖችን (ATM) በተለያዩ ሆቴሎችና ቅርንጫፎች መትከሉን አመልክቷል፡፡ ባንኩ አገልግሎቶቹን በራሱ ህንፃ ላይ ለማከናወን የግዥና የግንባታ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን በጉባኤው ላይም ለቀጣይ ሶስት ዓመታት ባንኩን በበላይነት የሚመሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት መምረጡን አስታውቋል፡፡

 ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ጓደኛሞች በአንድ ጫካ ውስጥ አቋርጠው በጣም ረዥም መንገድ እየሄዱ ነበር፡፡ መንገዱን ከመጀመራቸው በፊት፤
አንደኛው - እንግዲህ አደራ መንገድ ነውና የሚያጋጥመን አይታወቅም፡፡ ስለዚህ እንማማል፡፡
ሁለተኛው - ገና ለገና ችግር ያጋጥመናል ብለን ነው የምንማማለው? ማናቸውንም መከራ ልንችል፣ ካስፈለገም በምድር ላይ ለሚያጋጥመን ሞትም እንኳ ቢሆን፤ መስዋዕትነት ልንከፍል ከልባችን የተነሳን ጓደኛሞች፤ እንዴት እንዲህ በአንድ ጊዜ አለመተማመን ደረጃ እንደርሳለን? የማይተማመኑ ጓደኛሞች ነን ወይም ነበርን ማለት ነው?
አንደኛው - አይደለም ወዳጄ፤ ጠዋቱን ወዳጅነታችንን ስንጀምር አገር አማን ነበር፡፡ ያለ ህግ፣ ያለ መመሪያ፣ ያለ ፊርማ ነበር ሁሉንም የጠነሰስነው! አሁን ግን ጊዜው ከፋ፡፡ ከጓደኞቻችን መካከል እነማን ትተውን እንደጠፉ፣ እነማን በቃን ብለው ነገር - ዓለሙን እንደተዉት፣ እነማንስ ወኔያቸው እንደከዳቸው አስታውስ! አሁን የእኛም መጨረሻ ምን እንደሆነ በማይታወቅበት ሁኔታ መማማል መምጣቱ አያስገርምም!
ሁለተኛው - እንግዲህ ካልክ ይሁን! እኔ ግን አላመንኩበትም
ምርጫ የሌላቸው ጓደኞች ተማማሉ፡፡
“የከዳ ክህደቱ በልጅ ልጆቹ ይድረስ ተባባሉ!”
ከዚህ በኋላ መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ጫካው ውስጥ እንደገቡ በድንገት አንድ አውሬ መጣባቸው።
“በል ወዳጄ መሳሪያህን አቀባብል” አለው፡፡
ጓደኛው ግን ምን ጊዜ አመለጠ ሳይባል ሮጦ ዛፍ ላይ ወጥቷል፡፡
ያለ አጋዥ የቀረው ጓደኛ፤ ከዚህ ቀደም በሚያውቀው ዘዴ በመጠቀም፣ መሬት ላይ ትንፋሹን አጥፍቶ እንደሞተ ሰው ሆኖ ለጥ አለ፡፡
አውሬው የሞተ ሬሳ አይበላ ኖሮ፤ መጥቶ አሽትቶት አሽትቶት ቀስ እያለ ርቆ ሄደ፡፡
አውሬው ሙሉ በሙሉ ከአካባቢው ርቆ፣ ከዐይን ከተሰወረ በኋላ፤ ዛፍ ላይ ወጥቶ የነበረው ጓደኛው ወደ መሬት ወርዶ የተኛው ጓደኛው ጋ መጥቶ፤
“ለመሆኑ አውሬው ወደ ጆሮህ ቀርቦ ምን ነገረህ?” ሲል ጠየቀው፡፡
የተኛው ጓደኛም፤
“እጅግ አስገራሚ ነገር ነው የነገረኝ!”
“ምን አለህ በሞቴ?” ሲል ሰፍ ብሎ ጠየቀው፡፡
“እሱማ ያለኝ ከእንግዲህ በህይወትህ አደጋ ሲያጋጥምህ የሚከዳ ወዳጅ ጋር መንገድ እንዳትጀምር! መንገድ ከመጀመርህ በፊት ጓደኛ የምትመርጥበትን ቅድመ - ሁኔታ አጥርተህ ዕወቅ!” አለኝ፡፡ አንተ ባንዳ መሆንህ የገባኝ አውሬውን ካገኘሁ በኋላ ነው! በል ደህና ሰንብት ወዳጄ። ጊዜው ደግ ሲሆን አገኝሃለሁ!” ብሎት ሄደ፡፡
*      *     *
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤
“ዕምነት ሲታመም
ሺ ወረቀት መፈራረም” ይለናል፡፡
የላይኛው ተረት መንፈስ በቅጡ ገብቶታል ማለት ነው!
አለመተማመንና ጥርጣሬ አብዮት የሚባለው መሰረታዊ ለውጥ ከመጣ ጀምሮ፤ ውስጣችን በቅሎ ያደገ ክፉ አባዜ ነው! ከዚህ ይሰውረን! የኢኮኖሚ ጥርጣሬ፣ የፖለቲካ ጥርጣሬ፣ የባህል ጥርጣሬ ወዘተ… ለዘመናት ሲፈታተኑን የኖሩ ሳንካዎቻችን ናቸው፡፡ እነዚህ ጥርጣሬዎች አንድም ከመንግስት የተወለዱ፣ ሁለትም ከአብዮተኞቻችን የተቀፈቀፉ፣ ሦስትም በህዝብ የረዥም ጊዜ ትግል የፈለቁ ናቸው! ምንም ያህል ዘመን ስንጠራጠር ብንኖር፤ አንዳንድ ዕውነቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው፣ ህሊናዊና ነባራዊ ሁኔታዎች ሲሟሉ፣ ከመከሰት ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ቀናቸውን ቆጥረውና ጊዜያቸውን ቀምረው ከተፍ ይላሉ፡፡
ደራሲ ከበደ ሚካኤል፤
“… እንዲሁም በዓለም ላይ፣
አለ አንዳንድ ነገር፤
በዚህ ቢሉት በዚያ
ከመሆን የማይቀር!”
የሚሉን አይቀሬ ነገሮች በምንም መንገድ ከመፈፀም እንደማይቀሩ ሲያስገነዝቡን ነው!
መንገዶች ወደ ግባቸው የሚያደርሱን ነባርና ተዓማኒ በመሆናቸው ነው! ሁሉንም ቀና ያድርግልን!
ሰው መምረጥና የአገር አጋዥ መፈለግ ዛሬ ግዴታችን ነው! የፈጀውን ጊዜ ይፍጅ እንጂ አማራጭ የሌለው ነው!
በውስጣችን በአስተሳሰብ የበሰሉ፣ ሆደ-ሰፊ፣ በልምድ የበለፀጉ ብርቱ ብርቱ ሰዎች አሉ፡፡ የሽማግሌነት ድልድዮቻችን ናቸው፡፡ አደባባይን ያዩ ዘንድ ዕድል እንሰጣቸው፡፡
የሮበርት ብራውንን ግጥም የተረጎመው ሰዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታም፤
“…አለ በውስጣችን
ዕውነት ፍፁም ሆና የምታበራበት፤
ደግሞም ማወቅ ማለት
ከውጪ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ የበራውን እንዲወጣ ማድረግ”
የሚለን ይሄንኑ ሲያፀኸይ ነው!!
ከበረታን መተማመን አያቅተንም፡፡ በቂ የጥርጣሬ ጊዜ አሳልፈናል፡፡ በቂ የሌሎች መሣሪያ የመሆን የመበለጫ ዕድሜ ቆጥረናል፡፡ ዛሬ ግን እንደ ሁሉም ነገር የማብቂያ ሁኔታ ደርሷል፤ ብንል፤ ላለመዘናጋት በር ለመክፈት የበሰልን የሆንበትና ዐይናችንን የከፈትንበት ወቅት መጥቷል ብንል የማጋነን አይሆንም! ደጋግመን፤ “የማይተማመን ባልንጀራ ወንዝ ለወንዝ ይማማላል” የሚለውን ተረት፤ ከአንጀታችን ማሰብ ነው፡፡ ያኔ ለውጥ በእጃችን ላይ መሆኑን እንገነዘባለን!! “የበላን አብላላው፣ የለበሰን በረደው” መባሉንም አንርሳ!! እነሆ ለውጥ የተዘጋጁትን ከግትሮቹ፣ በጎቹን ከተኩላዎቹ መለየት ታላቅ አገራዊ ግዴታ ነው!!

 • ሄኒከን ከ20ሺ በላይ አርሶ አደሮች ጋር በአጋርነት ይሰራል
          • 60 በመቶ የቢራ ገብስ ከውጭ ተገዝቶ የሚገባ ነው
                          
    በፍጥነት እየተስፋፋ የመጣው የኢትዮጵያ የቢራ ኢንዱስትሪ፣ የቢራ ገብስ ፍጆታው በከፍተኛ መጠን ማደጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት 63 ሺህ ቶን የገብስ ብቅል ይጠቀም የነበረው የቢራ ኢንዱስትሪው፤ አሁን ከ120 ሺህ ቶን በላይ ይጠቀማል፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ ደግሞ 200 ሺህ ቶን ገብስ ያስፈልገዋል ተብሎ ይገመታል።
ይህን ከፍተኛ ፍላጎት ለማሟላትም ሀገሪቱ ገብስ ከውጭ ሀገራት ለማስገባት በየዓመቱ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ታወጣለች ይላል- በገብስ ምርት ጉዳይ ላይ የሚሰራው ሚስታራ ባዮተች ኩባንያ፡፡ የሀገሪቱን የቢራ ገብስ ፍላጎት በእጅጉ እንዲጨምር ካደረጉት የቢራ ኩባንያዎች ውስጥ በዓለም አቀፍ የቢራ ኢንዱስትሪ ከ145 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው፣ በ192 የዓለም ሀገራት፣ ከ25 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ያፈራው ሄኒከን አንዱ ነው፡፡
በዋሊያ፣ በሶፊ ማልት፣ በሐረር፣ በበደሌ፣ በክለር እና በሄኒከን ቢራ ምርቶቹ በአገር ውስጥ በስፋት የሚታወቀው ሄኒከን ኩባንያ፤ በአሁን ወቅት 28 በመቶ የገብስ ፍላጎቱን ከሀገር ውስጥ እያሟላ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ በኢትዮጵያ የ9.2 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት  ያለው ሄኒከን፤ የገብስ ፍላጎቱን ከሀገር ውስጥ ለማሟላት የተከተለው ስልት ደግሞ ራሱ መሬት ወስዶ፣ የገብስ እርሻ ከማስፋፋት ይልቅ ለቢራ ገብስ ማብቀል ተስማሚ የሆኑ አካባቢዎችን በጥናት በመለየት፣ አርሶ አደሮች የተሻሻለ ዝርያ አምርተው እንዲያስረክቡት አጋር በማድረግ ነው፡፡ ከ4 ዓመት በፊት በተጀመረው በዚህ የእርሻ ቴክኖሎጂን በማስፋፋት የማህበረሰብ ገቢን ማሳደግ ፕሮጀክቱ፤ በቀጥታ ከ20ሺ 894 ገበሬዎች ጋር አብሮ እየሰራ ሲሆን በተጨማሪም 30ሺ ያህል ገበሬዎችን የተሻሻሉ የገብስ ዝርያዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ይገልፃል፡፡
ቀድሞ አርሶ አደሮች የሚጠቀሟቸው የገብስ ዝርያዎች በሄክታር ከ15-18 ኩንታል ብቻ ምርት የሚሰጡ እንደነበር የጠቆመው ኩባንያው፤ አሁን ከጀርመንና ከፈረንሳይ ያስገባቸው Traveler እና Grace የተባሉ የገብስ ዝርያዎች የኢትዮጵያን አርሶ አደሮች በሄክታር ከ50 ኩንታል በላይ ምርት አንዲያገኙ እያስቻላቸው መሆኑን ይገልፃል፡፡ ኩባንያው ይህን ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊያደርግባቸው ከመረጣቸው የሃገሪቱ ገብስ አብቃይ አካባቢዎች መካከል ደግሞ ምዕራብ አርሲ ዞን፣ አርሲ ዞን እና ባሌ ዞን ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በአርሲ ዞን በቆጂ አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮችም በዚህ ፕሮጀክት ከታቀፉ በኋላ ምርታማና የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማግኘታቸው ዓመታዊ ምርታቸውና ገቢያቸው ከፍተኛ ጭማሪ ማሣየቱን ያስረዳሉ፡፡
ከእነዚህ መካከል የ6 ሚሊዮን ብር ካፒታል ባለቤት የሆኑት አርሶ አደር ፋዬ ተሠማ አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ፋዬ እንደሚሉት፤ ቀድሞ እስከ 18 ኩንታል በአንድ ሄክታር የሚያገኙት ምርት፣ አሁን በተሻሻሉ ዝርያዎች ከ60 ኩንታል በላይ ማግኘት እየቻሉ መሆኑን ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል። በየአመቱም በሚሊዮን ብር የሚገመት የገብስ ግብይት ከሂኒከን ኩባንያ ጋር እየፈፀሙ እንደሆነ የሚጠቅሱት አርሶ አደሩ፤በቀጣይም ምርታቸውን አሣድገው የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን እቅድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡  
ሄኒከን አንዱን ኩንታል በአንድ ሺህ ሃያ ብር እንደሚረከባቸውና ይህም በገበያ ላይ ካለው ዋጋ ጋር ተመጣጣኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ድጋፍም እንደሚያደርግላቸው ገልጸዋል፡፡ ኩባንያው በበኩሉ፤ በቀጣይም ከእነዚህ 20 ሺህ አርሶ አደሮች በተጨማሪ በጎንደር፣ በጎጃምና በደቡብ አካባቢ ካሉ አርሶ አደሮች ጋር ተመሳሳይ ፕሮጀክት ዘርግቶ ለመስራት እቅድ እንዳለው አስታውቋል፡፡  
በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ ከ4 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች በ1.1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ገብስ እያመረቱ ቢሆንም ከዝርያዎች አለመሻሻል ጋር ተያይዞ የሃገሪቱን የገብስ ምርት ፍላጎት ማሟላት ባለመቻላቸው ቢራ ፋብሪካዎች፣ 60 ከመቶ የሚሆነውን የቢራ ገብስ ከውጭ ሃገራት ነው የሚያስገቡት - በውጭ ምንዛሪ፡፡ በኢትዮጵያ በቢራ ኢንዱስትሪው ከተሰማሩት መካከል ቢጂአይ፣ ዲያጆ፣ ዳሸን፣ ሄኒከን፣ ሐበሻ፣ ዘቢደር እና ራያ ቢራ ተጠቃሽ ናቸው፡፡


    ታዋቂው ሰዓሊ ሊዮናርዶ ዳቬንቺ ከ500 አመታት በፊት የሳለውና የእየሱስን ምስል የሚያሳየው ጥንታዊ ስዕል፣ ኒውዮርክ ውስጥ በተካሄደ ጨረታ በ450 ሚሊዮን ዶላር መሸጡና ሽያጩ ክብረ ወሰን የተመዘገበበት መሆኑ ተዘግቧል፡፡
“መድሃኒያለም” በመባል የሚታወቀውና የአንድ ግለሰብ ንብረት ሆኖ የቆየው ይህ ስዕል፤በ100 ሚሊዮን ዶላር መነሻ ዋጋ ለጨረታ ቢቀርብም በስተመጨረሻ በ450 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ስሙ ላልተጠቀሰ አሸናፊ መሸጡን ክርስቲ የተባለው አጫራች ኩባንያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
አንድ ሩስያዊ ግለሰብ በ2013 ዓ.ም በ127 ሚሊዮን ዶላር ገዝቶት የግል ንብረቱ አድርጎት የነበረው ይህ ጥንታዊ ስዕል፤ ሰሞኑን የተሸጠበት ዋጋ፣ እስካሁን ድረስ በዓለማችን የስዕል ሽያጭ ታሪክ ከፍተኛው እንደሆነ የዘገበው ቢቢሲ፤ ከዚህ በፊት ከፍተኛ ዋጋ የተሸጠው ስዕል የታዋቂው ሰዓሊ ቫንጎ ስዕል እንደነበረም አስታውሷል፡፡

  ከወቅቱ የግብጽ ዝነኛ እንስት ድምጻውያን አንዷ የሆነቺው ሼሪን አብደል ዋሃብ ባለፈው አመት በተካሄደ አንድ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ አባይን ውሃ የሚያንቋሽሽ ንግግር በማድረጓ በአገረ ግብጽ የሙዚቃ ሥራዋን በመድረክ ላይ እንዳታቀርብ መታገዷ ተዘግቧል፡፡
ይህቺው ዝነኛ ግብጻዊት አቀንቃኝ የሙዚቃ ስራዎቿን በምታቀርብበት ኮንሰርት ላይ “የአባይን ውሃ አልጠጣሽም” የሚል ርዕስ ያለውን ዘፈን እንድትጫወት ከአድናቂዎቿ ጥያቄ በቀረበላት ወቅት፣ “ምን ማለታችሁ ነው… የአባይን ውሃ ከጠጣሁ እኮ፣ በጥገኛ ትላትሎች በሚከሰተው ሺስቶሞሲያሲስ የተባለ በሽታ እያዛለሁ” ብላ መመለሷንና አድናቂዎቿንም የአባይን ውሃ እንዳይጠጡ መምከሯን የዘገበው ቢቢሲ፤ይህን ተከትሎ በአገሪቱ የሙዚቃ ማህበር ከኮንሰርት ስራ መታገዷን አመልክቷል፡፡
የ37 አመቷ ዝነኛ ድምጻዊት “የህልውናችን መሰረት በሆነው በታላቁ ወንዛችን አባይ ላይ ያልተገባ ንቀት አሳይታለች፣ ስለሆነም በዚህ ህገ ወጥ ተግባሯ የተነሳ ለተወሰነ ጊዜ በየትኛውም የግብጽ የሙዚቃ መድረክ ላይ ስራዎቿን እንዳታቀርብ አግደናታል” ሲል ማህበሩ ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ይህን ተከትሎ ድምጻዊቷ በዱባይ ባቀረበቺው ኮንሰርት ላይ በአባይ ወንዝ ላይ ያልተገባ የንቀት ንግግር ማድረጓን በማመን፣ “ያልሆነ ነገር ዘባርቄ ስላስቀየምኳችሁ ተወዳጇን አገሬን ግብጽንና ግብጻውያን ወገኖቼን በሙሉ ከልቤ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ስትል በይፋ መጸጸቷን አስታውቃለች፡፡

Saturday, 18 November 2017 13:37

የሙጋቤ ማምሻ…

 በስተመጨረሻም…
ሙጋቤ ወደ ራሳቸው ተኮሱ!
ዚምባቡዌን ላለፉት 37 ዓመታት ያስተዳደሩት፣ ከመንበረ ስልጣናቸው የሚያነሳቸው ሞት ብቻ እንደሆነ ሲናገሩ የኖሩት፣ ወንበራቸውን ለሚስታቸው ሲያደላድሉ የከረሙት፣ የ93 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፣ ተቀናቃኛቸውን መትተው ለመጣል ወስነው የመዘዙትን ጠመንጃ ምላጭ ሳቡት፡፡
ሙጋቤ ተሳስተዋል፤ የጠመንጃው አፈ ሙዝ ወደ ራሳቸው ግንባር መዞሩን ልብ ሳይሉ ነበር ምላጩን የሳቡት!
ኖቬምበር 6 ቀን…
ቀጣዩዋ የአገሪቱ መሪ ሊያደርጓት ያሰቧት የባለቤታቸው የቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ ዋነኛ ተቀናቃኝ የሆኑትንና ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩትን ኤመርሰን ማናጋግዋን ከስልጣናቸው ማባረራቸውን በይፋ አስታወቁ፡፡
ከሁለት ቀናት በኋላም፣ “አዞው” በሚል ቅጽል ስማቸው የሚታወቁትና ቀጣዩ  የአገሪቱ  መሪ  ለመሆን ከቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ጋር የሚፎካከሩት ተባራሪው ምክትል ፕሬዚዳንት፤ ”ሙጋቤ ነፍሰ ገዳዮችን አሰማርቶብኛል፣ ለደህንነቴ ስል አገር ጥዬ ተሰድጃለሁ” ሲሉ አስታወቁ፡፡
ሙጋቤ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ክፉኛ በተጎዳበትና የፖለቲካ ውጥረቱ በተባባሰበት ወሳኝ ወቅት፣ ሚስታቸውን ለስልጣን ለማብቃት በመጓጓት የ75 ዓመቱን የፓርቲ ጓዳቸውን ኤመርሰን ማናጋግዋን ከስልጣንና ከአገር ማባረራቸው በፓርቲያቸው ዛኑፒኤፍ ውስጥ አስደንጋጭ የመሰንጠቅ አደጋን አስከተለ፡፡
የሙጋቤ ባለቤት ቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ ወይስ ተባራሪው ምክትል ፕሬዚዳንት ማንጋግዋ፣ ማንኛቸው ስልጣኑን ይረከቡ? የሚለው ጉዳይ፣ ዛኑፒኤፍ ፓርቲን ሲያወዛግብ ነበር የከረመው፡፡
የሙጋቤን እርምጃ ተከትሎ የዚምባቡዌ የቀድሞ የጦር መኮንኖች ማህበር ባወጣው መግለጫ፣ የምክትል ፕሬዚዳንቱን መባረር አውግዞ፣ በሚስታቸው በኩል ስልጣናቸውን ለማስቀጠል የጓጉትን ሙጋቤን ከእነሚስታቸው ከፓርቲው አባልነት ማባረሩን በይፋ አስታወቀ፡፡
በዚምባቡዌ ውጥረቱ እየተባባሰ መቀጠሉን ያጤነው የአገሪቱ መከላከያ ሃይል ዋና አዛዥ ጄኔራል ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ ባለፈው ሰኞ ለሙጋቤ በላኩት መልዕክት፣ “ተቀናቃኞችን በማባረር ወንበርዎን ለሚስትዎ የማስረከቡን አካሄድ የሚገፉበት ከሆነ፣ ወታደሩ በጉዳዩ ጣልቃ እንደሚገባ ይወቁ” በማለት አስጠነቀቁ፡፡
ሙጋቤ ሰምተው ዝም አሉ፤ ወታደሩ ረቡዕ ማለዳ ያለውን አደረገ፡፡
እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ወታደሮችን ያሳፈሩ የጦር መኪኖች በዚምባቡዌ ርዕሰ መዲና ሃራሬ ጎዳናዎች ላይ ሲመላለሱ ታዩ፡፡ የጦር መኪኖቹ ፓርላማውን ጨምሮ ቁልፍ በተባሉ ህንጻዎች ዙሪያ ሰፈሩ፡፡ ሃራሬ ጸጥ ረጭ፣ ጭው ጭር አለች፡፡ ጥይት እና ወታደር ብቻ ሳይሆን ፍርሃት እና ስጋት የጫኑ ታንኮች ከተማዋን ተመላለሱባት፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋር፣ አንድ ወሳኝ ነገር እየተከናወነ ነበር፡፡
ባለፈው ረቡዕ ማለዳ…
የዚምባቡዌ መንግስት የቴሌቪዥን ጣቢያ፣ ሰዓቱን ጠብቆ ይተላለፍ የነበረውን የወትሮውን መደበኛ ፕሮግራም ስርጭት ድንገት አቋረጠና፣ ያልተገመተ ሰበር ጉድ ማሰማቱን ቀጠለ፡፡
የአገሪቱ የመከላከያ ሃይል፣ ዚምባቡዌን ላለፉት 37 ዓመታት ከነበረችበት የሮበርት ሙጋቤ መዳፍ ፈልቅቆ ማውጣቱን፣ አገሪቱን የመምራት ስልጣኑን በመረከብ ሙጋቤንና ክብርት እመቤት ግሬስን በመኖሪያ ቤታቸው ማሰሩን ይፋ አደረገ፡፡
ሮበርት ሙጋቤና ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ፤ ጠባቂ ተመድቦላቸው በመኖሪያ ቤታቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ያስታወቁት ጄኔራሎቹ፤ ”የወታደሩ አላማ መፈንቅለ መንግስት አካሂዶ ስልጣን መንጠቅ አይደለም፤በሰውዬው ዙሪያ ተጠልለው የአገሪቱንና የህዝቧን ደም ሲመጥጡ የኖሩ ስግብግብ ወንጀለኞችን አነፍንፎ መያዝና ለፍርድ ማቅረብ እንጂ፤ ስለዚህ ተረጋጉ!” ሲሉም የጦር ሃይሉ መኮንኖች ለህዝቡ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
ዚምባቡዌ ይህን ሰበር ጉድ ስትሰማ፣ ብዙ ለየቅል የሆነ ነገር ሆነች - በድንጋጤ ክው አለች፤ በደስታ ፈነጠዘች፣ በጭንቀት ተወጠረች፣ በእፎይታ ተነፈሰች…
ቢቢሲ ረቡዕ ማለዳ በሃራሬ የሆነውን ነገር ሲዘግብ፤ ”የተቀላቀለ ስሜት የታየበት” ነበር ያለው። “የወታደሩ ያልተጠበቀ እርምጃ አገሪቱን ለ37 ዓመታት ያህል ከማቀቀችበት የአንድ ሰው አገዛዝና የኢኮኖሚ ድቀት ነጻ የሚያወጣ የትንሳኤ ዘመን ጅማሬ ነው” ያሉ ዜጎች የመኖራቸውን ያህል፣ ወታደር የገባበት ነገር እንደዋዛ እይቋጭም ብለው የሰጉ ብዙዎች መሆናቸውንም ዘገባው አመልክቷል።
ወታደሩ በሃይል ስልጣን መያዙን ተከትሎ “ጄኔሬሽን 40” የተባለውና የቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ ቀንደኛ ደጋፊ እንደሆነ የሚነገርለትን የገዢው ፓርቲ አካል የሆነ ቡድን ተሰሚነት ያላቸው አባላት ማሰር መጀመሩ እየተነገረ ሲሆን፣ አንዳንዶችም የሙጋቤ ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ግን፣ ረቡዕ ዕለት ከሙጋቤ ጋር በስልክ ተገናኝተው ማውራታቸውንና በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እንደገለጹላቸው አስታውቀዋል፡፡ ሲኤንኤን በበኩሉ፤ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዘገባው፣ ሙጋቤ ከጦር ሃይል አዛዡ ጋር ድርድር ሲያደርጉ የሚያሳይ ፎቶግራፍ፣ ደጋፊያቸው እንደሆነ በሚነገርለት ሄራልድ የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ ላይ ታትሞ መውጣቱን አመልክቷል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ረቡዕ ዕለት በሰጠው መግለጫ፣ “በዚምባቡዌ እየሆነ ያለው ነገር መፈንቅለ መንግስት ይመስላል፤ ጦሩ አገሪቱን ወደ ቀውስ ከሚያመራ ነገር መቆጠብና ህገ መንግስታዊ ስርዓት እንዲመለስ ጥረት ማድረግ ይገባዋል” ብሏል፡፡
የእንግሊዟ ጠ/ ሚ ቴሬሳ ሜይ፤ በዚምባቡዌ እየሆነ ያለው ነገር ተስፋ ሰጪ ቢሆንም፣ በግርግር መሃል ግን ሌላ ጨቋኝ ሃይል ስልጣን እንዳይይዝ ያሰጋል ሲሉ ጭንቀታቸውን ገልጸዋል፡፡
የዚምባቡዌ ጉዳይ ከተቀረው የአፍሪካ አገራት በተለየ መልኩ ደቡብ አፍሪካን አስጨንቋታል። የዚምባቡዌ ኢኮኖሚ በ2008 ክፉኛ በቀውስ መመታቱን ተከትሎ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች ወደ ደቡብ አፍሪካ በመሰደድ አሁንም ኑሯቸውን በመግፋት ላይ ይገኛሉ፡፡ ወቅታዊው የዚምባቡዌ ቀውስ ከተባባሰ፣ ደቡብ አፍሪካ ከአቅሟ በላይ የሆነ ስደተኛ ለመቀበልና በጎረቤቷ ጦስ የባሰ ቀውስን ለማስተናገድ ትገደዳለች፤ ይህ እንዳይሆንም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለች ሰላም ለማውረድ እየሰራች ነው ተብሏል፡፡
የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማህበረሰብ አባል አገራት ተወካዮችና የደቡብ አፍሪካ ሚኒስትሮች ልኡካን ቡድን መሪዎች፤ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በሚደረግበትና አገሪቱን ከባሰ ቀውስ መታደግ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ለመምከር ከትናንት በስቲያ ወደ ሃራሬ አቅንተዋል፡፡
በወታደሩ እጅ ላይ የወደቀቺው የዚምባቡዌ ቀጣይ ዕጣ ምን ሊሆን እንደሚችል ተንታኞች የተለያየ ግምት እየሰጡ ሲሆን ከብዙዎች ዘንድ የሚደመጠው ግን በሙጋቤ ተባርረው አገር ጥለው የተሰደዱት ምክትል ፕሬዚዳንት ማንጋግዋ ወደ አገራቸው ተመልሰው ስልጣን የመያዝ ዕድል ይኖራቸዋል የሚለው ግምት ነው፡፡
ወታደሩ ከሙጋቤና ከስደተኛው ማንጋግዋ ጋር ድርድር እያደረገ እንደሚገኝና ድርድሩም ማንጋግዋ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ፣ ሙጋቤ መልሰው እንዲሾሟቸውና ስልጣን እንዲለቅቁ ለማድረግ፣ በስተመጨረሻም ፓርቲው መሪውንና ፕሬዚዳንቱን እንዲመርጥ ለማድረግ ሳይሆን እንደማይቀር ተነግሯል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በውጭ አገር የካንሰር ህክምናቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት ታዋቂው የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሞርጋን ሻንጋራይ፣ ወደ አገራቸው ተመልሰው፣ተቃዋሚዎችን ያቀፈ ንቅናቄ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ግምታቸውን የሰጡም አልታጡም፡፡ ዚምባቡዌ ባለፉት 10 ዓመታት በከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ መዝለቋን የዘገበው ቢቢሲ፤ የገንዘብ እጥረት መባባሱን፣ የመገበያያ ገንዘቧ የመግዛት አቅም እጅግ በጣም መዳከሙንና የስራ አጥነቱ በዚህ ዓመት 90 በመቶ መድረሱን አመልክቷል፡፡
አምና ብቻ የ18 አገራት ምርጫ፣ በኢንተርኔት አማካይነት ተዛብቷል
ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016 ብቻ በ18 የተለያዩ የአለማችን አገራት በተካሄዱ ምርጫዎች በኢንተርኔት አማካይነት በተደረጉ ጣልቃ ገብነቶች የመራጮች ድምጽ አሰጣጥ መዛባቱ ተነግሯል፡፡
ፍሪደም ሃውስ የተባለው ዓለማቀፍ ተቋም ባወጣው ሪፖርት እንዳለው፤ በ2016 ምርጫ በተካሄደባቸው 18 አገራት ውስጥ መንግስታት፣ ቡድኖች፣ ተቃዋሚዎችና የማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎች በኢንተርኔት በሚያሰራጯቸው መረጃዎች አማካይነት በመራጮች ድምጽ አሰጣጥና በምርጫ ውጤቶች ላይ መዛባት እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡
በ65 የአለማችን አገራት ላይ የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ተቋሙ ባወጠው ሪፖርት፤ በአመቱ የ30 የአለማችን አገራት መንግስታት ከምርጫ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ተቃውሞዎችን የሚያፍኑ መልዕክቶችን በስፋት በማሰራጨት ተግባር ላይ ተጠምደው ሲሰሩ እንደነበር ተረጋግጧል፡፡
በአመቱ የተጠናከረ የኢንተርኔት ጣልቃ-ገብነትና አፈና ከተካሄደባቸው አገራት መካከል ቻይናና ሩስያ እንደሚገኙበት የጠቆመው ተቋሙ፤ ቱርክ፣ ፊሊፒንስ፣ ሶርያና ኢትዮጵያም በዝርዝሩ ውስጥ መካተታቸውን ጠቅሷል፡፡

    ሶስት የተለያየ መጠን ያላቸው የሲኒማ አዳራሾችን የያዘውና ብስራተ-ገብርኤል በሚገኘው ላፍቶ ሞል ላይ የተደራጀው “እንይ ሲኒማ”፤ ዛሬ ከቀኑ 10፡00 ጀምሮ በይፋ ተመርቆ ስራ እንደሚጀምር፣ የሲኒማ ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍሬዘር ተሾመ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ለሲኒማ ቤቱ የምርቃት ስነ-ስርዓት “እርቅ ይሁን” የተሰኘው ፊልም ለእይታ ይበቃል ተብሏል፡፡ ሲኒማ ቤቱ፡- 3 አዳራሾች ያሉት ሲሆን ትልቁ አዳራሽ ሲኒማ 1፡- 240 ወንበሮች፣ ሲኒማ 2፡- (መካከለኛው) 160 ወንበሮች እና ሲኒማ 3፡- (ትንሹ) 145 ወንበሮች እንዳሉት አቶ ፍሬዘር  ገልፀዋል፡፡
ዘወትር ቅዳሜና እሁድ ሲኒማ ቤቱ የህፃናት ፊልምና መዝናኛዎችን እንደሚያዘጋጅ የተጠቆመ ሲሆን ከ3 ወራት በኋላም ጥራት ያላቸው ቴክኖሎጂዎችን ገጥሞ፣ የሆሊውድ ፊልሞችን ለእይታ እንደሚያበቃ ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
በምርቃት ስነ -ስርዓቱ ላይ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የባህልና ቱሪዝም ሀላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይታደማሉ ተብሏል፡፡

    የደራሲ ሰዓዳ መሀመድ “ደባሎቼና ሌሎችም” የተሰኘ አዲስ የአጭር ልቦለዶች ስብስብ መፅሀፍ ገበያ ላይ ዋለ፡፡ ሰባት አጫጭር ልቦለዶችን ያካተተው መፅሀፉ፤ ከሰባቱ አምስቱ የደራሲዋ ስራዎች ከዚህ ቀደም ከሌሎች ደራሲያን ስራዎች ጋር በጋራ  ታትመው የነበሩ ሲሆን ሁለቱ  አዲስ እንደሆኑ ታውቋል፡፡ በ130 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ በ60 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
በሌላ በኩል፣ የፊታችን አርብ ህዳር 15 ቀን 2010 ዓ.ም ከ11፡30 ጀምሮ “ፍቅር የተራበ” የተሰኘው ቴአትር በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የሚታይ ሲሆን ገቢው በህመም ላይ ለምትገኘው ደራሲ ሰዓዳ መሀመድ የሚውል በመሆኑ ሁሉም ሰው ቴአትሩን በመታደም ደራሲዋን እንዲረዳ ጥሪ ቀርቧል፡፡