Administrator

Administrator

የተጠቃሚዎቹ ቁጥር 1.79 ቢ. ደርሷል
     ታዋቂው የማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ ባለፈው መስከረም በተጠናቀቀው የዘንድሮው ሶስተኛ ሩብ አመት 2.4 ቢሊዮን ዶላር ማትረፉንና 7.01 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን ባለፈው ሳምንት አስታወቀ፡፡
ፌስቡክ የሩብ አመት ትርፉ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ166 በመቶ እድገት በማሳየት 2.4 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን እንዳስታወቀ የዘገበው ስካይ ኒውስ፤ትርፋማ እንዲሆን ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያበረከተው ከሞባይል አገልግሎት ማስታወቂያ ያገኘው ገቢ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር 1.79 ቢሊዮን መድረሱን ያስታወቀው ኩባንያው፤ በሞባይል ብቻ ፌስቡክ የሚጠቀሙ ደምበኞቹ ቁጥርም 1.66 ሚሊዮን መድረሱን አመልክቷል፡፡
ኩባንያው በቀጣዩ አመት ኢንቨስትመንቱን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያስፋፋ ማስታወቁንዘገባው ጠቅሶ፣ ከእነዚህ ኢንቨስትመንቶች መካከልም በድሮኖች አማካይነት ለገጠር አካባቢዎች የኢንተርኔት አገልግሎት ማዳረስ አንዱ እንደሆነ መጠቆሙን አስረድቷል፡፡

በዩክሬን የሚገኝ አንድ የኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ መጠሪያ ስማቸውን አይፎን 7 ብለው ላስቀየሩ የመጀመሪያዎቹ አምስት ደምበኞቹ አዲሱን ስማርት ፎን፣አይፎን 7 እንደሚሸልም ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት፣ የመጀመሪያው ወጣት ስሙን በይፋ ማስቀየሩን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የ20 አመቱ ዩክሬናዊ ወላጆቹ ያወጡለትን ኦሌክሳንደር ቱሪን የተባለ ስም በአይፎን 7 መቀየሩን ባለፈው አርብ ማስታወቁን ተከትሎ፣ ኩባንያው ቃል የገባለትንና 850 ዶላር የሚያወጣውን አዲሱን የአፕል ምርት አይፎን 7 ስማርት ፎን ሸልሞታል ተብሏል፡፡ወጣቱ በሚመለከተው የአገሪቱ የህግ አካል ስሙን ለማስቀየር ወጪ ያደረገው 2 ዶላር ብቻ በመሆኑ ከተሸለመው አይፎን ዋጋ አንጻር አትራፊ ነው ብሏል ዘገባው፡፡
ዩክሬናዊው ለሽልማት ብሎ ያጸደቀውን አይፎን 7 የሚለውን አዲሱን ስሙን፣ ወደፊት ወደነበረበት በመቀየር በቀድሞ ስሙ ሊጠራ እንደሚችል መናገሩን የጠቆመው ዘገባው፤ ወጣቱ ስሙን መቀየሩ ቤተሰቦቹንና ጓደኞቹን አስደንግጧል ብሏል፡፡

  20ኛ ዓመቱን ለማክበር በዝግጅት ላይ የሚገኘው ወጋገን ባንክ፣ባለፈው ዓመት ባደረገው እንቅስቃሴ ከታክስ በፊት 478.5 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ፡፡
ባንኩ ከትናንት በስቲያ ባካሄደው 23ኛ መደበኛና 12 ድንገተኛ ዓመታዊ የባለአክሲዮኖች ጉባዔ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አርአያ ገ/እግዚአብሔር ባቀረቡት ሪፖርት፣ አምና (2015/16) ባደረገው እንቅስቃሴ ታክስ፣ መጠባበቂያና ሌሎች ውጪዎች ከተቀነሰ በኋላ 375.6 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
ለመንግሥት 102.9 ሚሊዮን ብር ግብር መክፈላቸውን፣ የተገኘው ትርፍ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ6.6 በመቶ ብልጫ ማሳየቱንና ከእቅዱ 92 በመቶ ማሳካቱም ተጠቁሟል፡፡  
ካቻምና 1.5 ቢሊዮን ብር የነበረው የባንኩ የተከፈለ ካፒታል፣ አምና 1.8 ቢሊዮን ብር መድረሱንና ጠቅላላ ካፒታሉም ወደ 2.8 ቢሊዮን ብር ማደጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት ካቻምና ከነበረው 13.7 ቢሊዮን ብር አምና ወደ 16.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የተሰበሰበ ተቀማጭ ገንዘብ 11.8 ሚሊዮን ብር ሲሆን የመደበኛ ብድር መጠንም የግምጃ ቤት ሰነድ ግዢን ሳይጨምር 7.6 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ባንኩ እ.ኤ.አ በ2025 በአፍሪካ ከሚገኙ 10 ስመጥርና ተፎካካሪ ባንኮች አንዱ የመሆን ራዕዩን ለማሳካት እየተጋ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል፣ የሰው ኃይል ብቃትን ለማጎልበት፣ የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋትና የኢንፎሜሽን ቴክኖሉጂ አቅሙን ለማሳደግ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡  
የባለአክሲዮኖች ቁጥር 2,456 የደረሰ ሲሆን ባንኩ በአሁኑ ሰዓት 3,385 ሠራተኞችን በሥሩ ያስተዳድራል፡፡ ወጋገን፤ ስታዲየም አካባቢ በማስገንባት ላይ ያለው ባለ 23 ፎቅ፣ ዘመናዊ የዋና መ/ቤት ሕንፃ፣75 በመቶ መጠናቀቁ ተጠቁሟል፡፡

 ቅዳሜ ጥቅምት 5 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ፤ “የጌዴኦ ዞን ከተሞች ነደዱ” በሚል ርዕስ የቀረበውን ዘገባ ይመለከታል፡፡ በመጀመሪያ በጌዴኦ ዞን በተከሰተ ግጭት ምክንያት በጠፋው የሰው ህይወትና በወደመው ንብረት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልፃለን፡፡
የተፈጠረውን ክስተት ተከትሎ ከላይ በተጠቀሰው ርዕስ የወጣው ዘገባ ሚዛናዊነት የጎደለው፣ የሌላውን ክብርና ዝና የሚነካ እንዲሁም በሀሰት የወነጀለና መረጃ በማዛበት ጭምር የቀረበ በመሆኑ በስህተት የተገለጹ የምንላቸውን እንደሚከተለው እናቀርባለን፤
ዲላ ከተማ ያሉ ባለአክሲዮኖች የከተማ መሬት እንደነበራቸውና የእነርሱ መሬት ላይ ጨፌ ዩኒየን እንደተሰጠ ተደርጎ የተዘገበው በፍጹም በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሰረተ ሲሆን ትክክለኛው መረጃ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
የይርጋጨፌ ቡና ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን ኃ.የተ ሰኔ 14 ቀን 1994 ዓ.ም ተመስርቶ ነሐሴ 16 ቀን 1994 ዓ.ም ሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ያገኘ ድርጅት ነው፡፡ ዩኒየኑ በ1997 ዓ.ም የዲላ ማዘጋጃ ቤት፣ ባለሀብቶችና ማህበራት የከተማ ቦታ ወስደው እንዲያለሙ መጋበዙን ተከትሎ፣ ግንቦት 18 ቀን 1997 ዓ.ም የልማት ቦታ እንዲሰጠው ጥያቄ ቢያቀርብም  አፋጣኝ ምላሽ ባለማግኘቱ፣ በድጋሚ ታህሳስ 14 ቀን 1998 ዓ.ም ጥያቄ አቅርቧል፡፡ የቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ በወቅቱ የኢንቨስትመንት መሬት ላይ ውሳኔ ይሰጥ የነበረው የዞኑ የሊዝ ኮሚቴ፣ ዩኒየኑን ጨምሮ ለስምንት (8) የተደራጁ አካላት በጥያቄያቸው መሰረት ቦታ በሰጠበት ወቅት ለዩኒየኑ 5,368 ካሬ ሜትር መጋቢት 9 ቀን 1998 ዓ.ም ወስኖ፣ ውሳኔው እንዲፈጸም መጋቢት 11 ቀን 1998 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ፣ ለዲላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት አመራር በመስጠቱ፣ ማዘጋጃ ቤቱም በደብዳቤው መነሻ የካቲት 1 ቀን 1999 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ፣ “ለኢንቨስትመንት የወሰዱትን ቦታ የሊዝ ክፍያ ፈጽመው እንዲያለሙ ለማሳወቅ” በማለት የሊዝ ክፍያ ለዩኒየኑ ሲያሳውቅ፣ ዩኒየኑ የተጠየቀውን ገንዘብ ብር 146,000 (አንድ መቶ አርባ ስድስት ሺህ) በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲላ ቅርንጫፍ፣ ገቢ አድርጓል፡፡
የሌሎች የነጋዴዎች ማህበራት ማለትም የሰባቱ ማህበራት ቦታ ተሰጥቷቸው ወደ ልማት የገቡ ቢሆንም ዩኒየኑ ቦታ ላይ ያረፉ የማ/ቤቱ ሱቆች ፈርሰው ቦታው ባለመጽዳቱ ከሦስት ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ እንደሌሎቹ ማህበራት ወደ ልማት ሳይገባ ቆይቷል፡፡ አሁን ከዩኒየኑ ጋር ክርክር የገጠመው ማህበር ጥቅምት 10 ቀን 2001 ዓ.ም ሳሬንደም የገበያ ማህበር አክስዮን ማህበር በሚል ስያሜ ተመስርቶና የንግድ ፈቃድ ጥቅምት 16 ቀን 2001 ዓ.ም የኢንቨስትመንት ቦታ ጥያቄ ለዞኑ አስ/ጽ/ቤት ማቅረቡን ተከትሎ፣ ጽ/ቤቱም በበኩሉ ለዲላ ከተማ አስ/ጽ/ቤት ህዳር 17 ቀን 2004 ዓ.ም ድጋፍ እንዲደረግላቸው ደብዳቤ መጻፉን በፍ/ቤት ክርክር ወቅት ከነበረው የመረጃ ልውውጥ ለመረዳት ችለናል፡፡
ሆኖም የዞን አስ/ጽ/ቤት ቀደም ሲል ለሳሬንደም የገበያ ማዕከል አ/ማ እንዲያለሙት የድጋፍ ደብዳቤ የጻፈለት ቦታ ቀደም ሲል ለይርጋጨፌ ዩኒየን ተሰጥቶ የነበረ መሆኑን ማረጋገጡን በመግለጽ፣ ለአዲሶቹ አልሚዎች በአቅራቢያው ሌላ ቦታ እንዲፈለግ የካቲት 16 ቀን 2001 ዓ.ም ለዲላ ከተማ አስ/ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ አመራር ሰጥቷል። የከተማው የከንቲባ ጽ/ቤት ደግሞ የካቲት 17 ቀን 2001 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ፣ የከተማ መሬት ለሚያስተዳድረው ለዲላ ከተማ ማ/ቤት ከዞን አስ/ጽ/ቤት የተሰጠውን አመራር አስተላለፈ። የዲላ ማ/ቤት የተሰጠውን አመራር ወደ ጎን በመተው፣ ከዩኒየኑ ቦታ በመቁረስ፣ ጋይድ ማፕ በማዘጋጀት ሚያዚያ 20 ቀን 2001 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የዩኒየኑን ቦታ ለሳሬንደም ለመስጠት የአፈጻጸም መመሪያ እንዲሰጠው የዲላ ከተማ አስተዳደርን ጠየቀ፡፡ ከተማ አስተዳደሩም ለማ/ቤቱ ካስተላለፈው አመራር የሚቃረን ጥያቄ ማስቆም ሲገባው፣ እንደአ መጣጡ ለዞኑ አስተዳደር ሲያስተላልፍ፣ የዞኑም አስተዳደር ጥያቄውን ተቀብሎ በማስተናገድ፣ ግንቦት 11 ቀን 2001 ዓ.ም አስቀድሞ ለዩኒየኑ የተሰጠውን ቦታ አሁን ደግሞ ለሳሬንደም በሚሰጥበት ሁኔታ በመስማማት ውሳኔ ሀሳብ አደራጅቶ፣ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ አቀረበ፡፡ በዚህ ወቅት ጉዳዩ ለክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት የቀረበው፣ በክልሉ የመሬት አስተዳደር ላይ ችግር በመኖሩ ውሳኔ ይሰጥ የነበረው በክልል መስተዳድር ም/ቤት ነበር፡፡ የክልሉ ካቢኔ ሰኔ 26 እና 27 ቀን 2001 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ፣ ቀደም ሲል በዞኑ የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ፣ ቦታውን የማልማት መብት አስቀድሞ የተሰጠው ባለመብት መኖሩን የማያመላክት በመሆኑና የውሳኔ ሀሳቡ የቀረበው ደግሞ ከፍተኛ የመንግስትና የህዝብ ኃላፊነት ከተሰጠው የዞን አስ/ጽ/ቤት መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት፣ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ተቀብሎ በማጽደቅ ለተፈጻሚነቱ ሰኔ 29 ቀን 2001 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ለዞኑ አስተዳደር አሳወቀ፡፡ ከዚህ በመቀጠል የዞኑ አስተዳደር ሐምሌ 2 ቀን 2001 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ለከተማ አስ/ጽ/ቤት አመራር ሰጠ፡፡
ዩኒየኑም የማልማት መብት ባገኘበት ቦታ ላይ ሕገወጥ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን መረጃ ሲደርሰው፣ ሐምሌ 24 ቀን 2001 ዓ.ም ከተፈቀደለት ይዞታ እንዳይነካበት ማሳሰቢያ ደብዳቤ በመጻፍ፣ ቦታውም ጸድቶ ለልማት እንዲዘጋጅ እንዲደረግለት ጠየቀ፡፡ የሕገ ወጥ እንቅስቃሴ መረጃ የደረሰው የጌዴኦ ከተማ ልማት መምሪያ ሐምሌ 30 ቀን 2001 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ፣ ማ/ቤቱ ከህገ ወጥ ተግባሩ እንዲቆጠብ አስጠነቀቀ፡፡ ይሁን እንጂ የመምሪያውን ተግሳጽ ለመስማት ማ/ቤቱ ዝግጁ አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ ዩኒየኑ ተስፋ ባለመቁረጥ አስተዳደራዊ ትኩረት እንዲሰጠው ተደጋጋሚ ጥረት አደረገ፡፡ በዚህ ሁሉ አቤቱታ መሃል ጥር 25 ቀን 2002 ዓ.ም ቦታው ከዩኒየኑ ተቆርሶ ለሳሬንደም መሰጠቱ ተሰማ፡፡ ከዚህ በኋላ አስተዳደራዊ መፍትሄ በመጥፋቱ ዩኒየኑ ጉዳዩን ወደ ጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመውሰድ ግንቦት 19 ቀን 2002 ዓ.ም በተላለፈው ውሳኔ ማ/ቤቱ፣ የዞኑን ሊዝ ኮሚቴው ውሳኔ በሕግ ተገድዶ እንዲፈጽም ታዘዘ። በዚሁ ውሳኔ ዩኒየኑ ከሦስት ዓመታት በፊት የሊዝ ክፍያ በፈጸመበት ሙሉ ይዞታ መጠን (5,368 ካሬ ሜትር) ላይ መብቱን በፍ/ቤት ውሳኔ አረጋገጠ፡፡ ከዚህ በመቀጠል ሰኔ 10 ቀን 2003 ዓ.ም በሙሉ ይዞታ ላይ (5,368 ካሬ ሜትር) ካርታ ተሰርቶ በመሰጠቱ ፍርዱ ተፈጸመ፡፡ በሕገ ወጥ መንገድ የተሰጠው የሳሬንደም ካርታ ሰኔ 15 ቀን 2003 ዓ.ም መሰረዙን ለሳሬንደም ለራሱና ለሌሎች የመንግሥት አካላት ተገለጸ፡፡
ከዚህ በኋላ ጉዳዩ ወደ ቀጣይ የክልልና የፌደራል ፍ/ቤቶች በሂደት አምርቶ፣ በመጨረሻም በፌደራሉ ጠ/ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ለተከራካሪው ወገን ተወሰነ፡፡ ጉዳዩ ወደ አፈጻጸም ክርክር ሲደርስ የመንግሥት ትኩረት አግኝቶ ክትትል ይደረግበት ስለነበር፣ ከዞኑ ከፍ/ቤት ጀምሮ እስከ ክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩ እንደ ፍርዱ መፈጸም የማይቻል በመሆኑ አማራጭ መንገድ በመከተል እልባት ሲሰጡ ቆይተው፣ የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ግን የሥር ፍ/ቤት የአፈጻጸም ክርክር ላይ የሰጠውን ብይን መስከረም 23 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት ሻረ፡፡
“ዩኒየኑ ፍርዱን በይሁንታ መቀበል አልቻለም፡፡ በዚህም ለበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋት፣ለበርካታ ንብረት ውድመት የዳረገው ግጭት እንደቀሰቀሰ ምንጮች ይናገራሉ” በሚል የቀረበው ፍጹም ሐሰትና ተራ ውንጀላ ነው፡፡
የይርጋ ጨፌ ቡና ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን፣ በጌዴኦ ዞን በሚገኙ 27 ሁለገብ ኅ/ሥራ ማህበራት በታቀፉ ከ46,000 በላይ በሆኑ አርሶ አደሮች፣ በኢፌዴሪ ኅብረት ሥራ ማህበራት ማቋቋሚያ አዋጅ ከ14 ዓመታት በፊት የተቋቋመና በሀገር ልማትና ገጽታ ግንባታ የራሱን ከፍተኛ ሚና እየተወጣ ያለ ትልቅ ተቋም ነው፡፡ የዩኒየኑ ቦርድ፣ ማኔጅመንት እና ሰራተኞች ኃላፊነት የሚሰማቸውና የድሃውን አርሶ አደር ኑሮ ለማሻሻል ሌት ተቀን የሚታትሩ ከመሆናቸው የተነሳ፣ ለአልባሌ አስተሳሰብና ድርጊት ጊዜ የሌላቸውና ይህን የመሰለ አስከፊና ህገ ወጥ ድርጊት ለመፈፀም ተቋማዊ አጀንዳ አንግበው የሚንቀሳቀሱ አይደሉም፡፡ የቦታ ክርክሩንም ጉዳይ በተመለከተ በህጋዊ መንገድ ብቻ መፍትሄ እንደሚገኝ በመተማመን ሁሉንም ህጋዊ አማራጮች በሙሉ አሟጦ እየተጠቀመ ያለ ተቋም እንጂ በእንደዚህ ዓይነት ያልተገባ ድርጊት የመሳተፍ ፍላጎትም ሆነ ታሪክ የለውም፡፡ ስለዚህ ይህ መሰረተ ቢስ ውንጀላ ተገቢነት የሌላው በመሆኑ እንቃወማለን፡፡

ድምፃዊ ሔኖክ መሀሪ፤ ‹‹እውድሻለሁ›› በተሰኘው ዘፈኑ በ”ምርጥ የአር ኤንድ ቢ” እና የ”ሶል” አፍሪካዊ ድምፃዊ በመሆን፣ የ”ኦልአፍሪካ ሚዩዚክ አዋርድ” (አፍሪማ 2016) አሸናፊ ሆነ፡፡ ባለፈው እሁድ በናይጄሪያ ሌጎስ ከተማ በተካሄደው የሽልማት ስነስርዓት ላይ ሔኖክ ባሸነፈበት ዘርፍ 7 ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ የናይጄሪያ ድምፃዊያን፣ ሁለት ደቡብ አፍሪካዊያን፣ አንድ ሩዋንዳዊና አንድ ማላዊ ድምፃዊያን ፉክክር አድርገው የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ ሄኖክ ማሸነፉን ገልጾ፣ሆኖም አሸንፋለሁ ብሎ እንደላልጠበቀ ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡  
ጃኖ ባንድ ‹‹ዳሪኝ›› በተሰኘው ዘፈን፣ በ”ምርጥ ሮክ” እና “ምርጥ ቡድን”፣ ድምፃዊት ፍቅር አዲስ ነቅአጥበብ ደግሞ ‹‹ምስክር›› በተሰኘው ዘፈኗ፣”የምስራቅ አፍሪካ ምርጥ ሴት ድምፃዊት” እንዲሁም ድምፃዊ አንተነህ ምናሉ ‹‹ዋዮ›› በተሰኘው ዘፈኑ፣ “ተስፋ የተጣለበት ድምፃዊ” እና “ምርጥ የሬጌ አቀንቃኝ” በሚሉ ዘርፎች ታጭተው የነበረ ሲሆን ማሸነፍ ግን አልቻሉም፡፡
ውድድሩ 50 በመቶ በሙዚቃ ባለሙያ ዳኞች ነጥብ የሚሰጠው ሲሆን 50 በመቶው በህዝብ ምርጫ የሚገኝ ነጥብ መሆኑን የጠቆመው ድምፃዊ ሄኖክ፤ቅስቀሳ በተጀመረ ሰሞን ፌስቡክ መዘጋቱ ፈታኝ ቢሆንም ተስፋ ባለመቁረጥ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ባደረገው ቅስቀሳና ዳኞች በሰጡት 50 በመቶ ነጥብ ማሸነፉ እንዳስደነገጠው አልደበቀም፡፡ ድምፃዊት ፀደንያ ገ/ማርቆስ ‹‹ሀርየት›› ለተሰኘው ፊልም በሰራቸው የማጀቢያ ሙዚቃ፣ባለፈው ዓመት (2015 አፍሪማ አዋርድ) “የምስራቅ አፍሪካ ምርጥ ሴት ድምፃዊት” በሚል ዘርፍ ማሸነፏ አይዘነጋም፡፡  
 በ34 የተለያዩ ዘርፎች አርቲስቶችንና የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን አወዳድሮ አሸናፊዎችን ለሽልማት የሚያበቃው “አፍሪካ ሚዩዚክ አዋርድ”፤ በአህጉሪቱ ትልቁ ሽልማት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የሽልማት ውድድሩ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን ዘንድሮ 2714 አፍሪካዊያን አርቲስቶች ተመዝግበው እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሌጎስ በተካሄደው በዚህ የሽልማት ስነስርዓት ላይ ከ2500 በላይ ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ አፍሪካዊያን እንግዶች ታድመው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

“እውነተኛ ለውጥ ነው የማመጣው … የኦባማ አይነት እንዳይመስላችሁ”

ማክሰኞ ማታ ወደ እንቅልፌ የሄድኩት ሄላሪ ክሊንተን እንደምትመረጥ እርግጠኛ ሆኜ ነበር። ጠዋት ባለቤቴ ትራምፕ እየመራ ነው ስትለኝ ደንብሬ ተነሳሁኝ፡፡ የደነበርኩት ጆሮዬን ማመን ስለተሳነኝ ነው፡፡ የምርጫውን ሂደት ስከታተል ነው የከረምኩት፡፡ ምንም እንደማይመለከተኝ አውቃለሁ፡፡ እኔ አፍሪካ ውስጥ እንጂ አሜሪካ ያለሁ ሰው አይደለሁም፡፡ በራሴ ሜዳ የምወክለው ሰው ስለሌለኝ በሌላ ሀገር ገብቼ እንደ መቀላወጥ ነው፡፡ ግን ህልም አለኝ፡፡ ሰው ነኝ፡፡ እንደ ማንኛውም ሰው ምርጫ አለኝ፡፡
ወደ ቴሌቪዥኑ ሄጄ ከቁርስ በፊት ተቀመጥኩኘ። ትራምፕ ድምፁን እየሰበሰበው ነው፡፡ ከእሱ ምርጫ ጣቢያና ከሂላሪ ምርጫ ጣቢያ ዘገባው እየተለዋወጠ ይሰራጫል፡፡ ከዘገባው ይበልጥ በሁለቱም ምርጫ ጣቢያ የተሰበሰቡ የደጋፊ ፊቶች፣ እየተከሰተ ስላለው ነገር እውነቱን ይናገራሉ፡፡ የሂላሪ ደጋፊዎች በማዘን ላይ ናቸው፡፡ በዲሞክራቶቹ ሀዘን እኔ መደሰት ጀመርኩኝ፡፡ ከዚህ ቀደም ሪፐብሊካንም ዲሞክራትም ሲመረጥ የምደግፈው አልነበረኝም። ግን ደግሞ ኦባማ ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት ሲመረጥ ደስተኛ ነበርኩኝ፡፡
ለኦባማ ስደግፍ ምክንያቴ ምን ነበር? … ግልፅ ነው፤ ጥቁር በመሆኑ ምክኒያት ብቻ ነበር፡፡ በብቃቱ አይደለም፡፡ ብቃቱ ለእኔ የቆዳ ቀለሙ ላይ የሚገኝ ይመስለኝ ነበር፤ መሳሳቴ እስኪገባኝ ስምንት ዓመት ማለፍ ነበረበት፡፡ የቀለም ዘረኛ ነበርኩኝ፤ ያኔ። ግን ፕሬዚዳንትነት ከቀለምም ሆነ ከድጋፍ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ እውነት ነው፤ ለምርጫ ምክኒያቱ፡፡ ኦባማ ታላቅ የንግግር ጥበብ አዋቂ ነው። ስምንት ዓመት በተለያየ መድረክ ላይ ሲናገር ተሰምቷል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶም ረጅም ንግግር ሲያደርግ ሰምቼዋለሁ፡፡ ግን ማውራት ነው እንጂ ሌላ ለውጥ አላመጣም፡፡
“Change we can” - የምርጫ መቀስቀሻው ሃረግ ነበረች፡፡ ለውጡ ወደ ምን እንደሆነ ግን አልታወቀም ነበር፡፡ አሁን ለይቷል፡፡ ቴሌቪዥኑ ላይ ማፍጠጤን ቀጠልኩኝ፡፡ የሂላሪ የምርጫ ውጤት 208 ላይ ቆሟል፡፡ የትራምፕ 245 ደረሰ። በጉጉት እየተጠበቀ ያለው የፔንስልቫኒያ እስቴት የምርጫ ድምፅ ነው፡፡ የሂላሪ የእድገት ግዛት ነው፡፡
ለእኔ የትራምፕ መመረጥ ምንድነው የሚፈይደው? ከሚለው ጥያቄ ጋር ተፋጠጥኩኝ። የሚፈይደው ነገርማ አለ፡፡ የአሜሪካ ፖለቲካ በአናቱ ከተዘቀዘቀ፣ የሀገሬም ፖለቲካ ቢያንስ ጥርሱ መውለቁ አይቀርም፡፡ የሀገሬ ፖለቲካ ከሂላሪ ፖለቲካ ጋር ብዙ ዝምድና አለው፡፡ የሂላሪ ፖለቲካ ከማንነት ፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለሴቶች፣ ለብሄር ብሔረሰቦች፣ ለማይኖሪቲዎች .. ወደሚል አዝማሚያ ያጋደለ ነው፡፡ ክፍልፋይን የሚያበረታታ እንጂ ወደ አንድነት የሚያመራ አይደለም፡፡
በሂደት እንደተረዳሁት ሁሉም ፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የፈለገ አይነት የፖለቲካ ጥያቄ ከማንነት ጥያቄ ይበልጥ የኢኮኖሚ መንስኤ ያለው ነው፡፡ ፍትሐዊ ሀብት የማፍራትና ፍትሀዊ የመከፋፈል ጉዳይ ነው … ሁሉም ጥያቄ ሲጠቃለል፡፡
ኦባማ ጥቁር መሆኑ ወይንም ሄላሪ ሴት መሆኑዋ ለኢኮኖሚ ኢ-ፍትሃዊነቱ መፍትሄ መሆን እስካልቻለ ድረስ የማንነት ጥያቄ አስፈላጊ አይደለም፡፡ መጀመሪያ የሰውነት ጥያቄ ነው፡፡
እንዲህ እያልኩ በማሰብ ውጤቱን መከታተል ቀጠልኩኝ፡፡ የሂላሪ ደጋፊዎች ከተቋም ጋር የተጋጩና ተቋሞችን በአጠቃላይ የሚጠሉ ስለመሆናቸው አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ ቀርቦ ሲናገር ሰማሁት፡፡ ባለሙያውን አውቀዋለሁ፡፡ በክሊንተን መንግስት ውስጥ የኢኮኖሚ አማካሪ ሆኖ ይሰራ የነበረ ሰው ነው፡፡
ሮበርት ራይሽ ይባላል። ለሮበርት ራይሽ መሰረታዊና ጤናማ ኢኮኖሚ፣ የመካከለኛ ገቢ የህብረተሰብ ክፍልን የሚያሳድግ ነው፡፡ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የሚፈጥር፣ የሚያጠነክርና የሚጠብቅ ስርዓት “ቅዱስ” ነው ብሎ ያምናል፡፡ ስለዚህ ምናልባት ህዝቡ ከተቋማቱ ጋር የተጣላው እነዚህ መብቶቹን የሚያስጠብቁ ስላልሆኑ ነው ብሎ ሀሳቡን ሰነዘረ፡፡ ሌሎችም ተራ በተራ እየተለዋወጡ የተለያዩ አስተያቶችን ይሰጣሉ። በአጠቃላይ ግን በቴሌቪዥን መስኮት የሚታዩት ሁሉ የደስታ ድባብ ውስጥ አልነበሩም፡፡  
በተለይ ምሁራኑ በተለያየ አቅጣጫ መበሳጨታቸውን እየገለፁ ነው፡፡ በቴሌቪዥን የሚታዩ ተንታኞች ግን ከህዝቡ ጋር ናቸው ወይንስ አይደሉም? አልኩኝ፡፡ ህዝብ ከተጣላው ተቋም ጋር ነው የሚሰሩት? … እሺ ምሁራንና ተንታኞቹስ ከተቋማቱ ጋር ያብሩ፤ ጋዜጠኞቹ ግን ምን ነክቷቸው ነው? … ለካ በፋውንዴሽን ታቅፈው ነው መረጃ የሚያጠናቅሩት፡፡ ከህዝቡ ጋር የቆመ ታዲያ ማነው? እንግዲህ ለህዝቡ የቆመው ማን እንደሆነ በግልፅ እየታየ ነው፡፡ ከህዝብ ፍላጎት ጋር የቆመው የምርጫ ሳጥኑ ብቻ ነበር፡፡ በምርጫ ሳጥኑ ውስጥ የተከማቸው ድምፅ ደግሞ የዶናልድ ትራምፕን ስም አጭቆ ይዟል፡፡
“Popular Vote” የሚል ነገር በቴሌቪዥኑ አንድ ጫፍ ተፅፏል፡፡ በ Popular Vote ላይ ያለው ቁጥር በሳጥኑ ውስጥ ካለው ይለያል፡፡ በጎዳና ላይ ወሬ ሂላሪ ተመርጣለች፡፡ በተጨባጩ የድምፅ መስጫ ሳጥን ውስጥ ግን የሴትየዋ ድምፅ ጎድሏል፡፡ በፕሮፓጋንዳ ምርጫ እሷ አሸንፋለች፡፡ እውነትና ፕሮፓጋንዳ ግን በህዝብና በተቋማት መሀል ያለውን ርቀት መልሰው ማንፀባረቃቸው የሚደንቅ አይደለም?
ከአንድ ወዳጄ ጋር ስለ ምርጫ ስናወራ የነገረኝ ቀልድ ትዝ አለኝ፡፡ በሰዎች መሀል ትራምፕን እንደሚደግፍ አንዱ የአሜሪካ ዜጋ ሲያወራ፣በዙሪያው ያሉ ሁሉ “እንትን የነካው እንጨት አደረጉት፡፡ “እንዴት እንደዚህ አይነት መሀይም፣ ዘረኛና ተሳዳቢ ሰው ትመርጣለህ?!” ብለው አዋከቡት፡፡ ግራ አጋቡት፡፡ ከከበበው ነቀፋ ለመራቅ ወጥቶ ሊሄድ ሲል ከታቃወሙት መሀል መሪ ሆኖ ሲጮህ የነበረው ከኋላው ተከትሎ በጆሮው፣ “እኔም ትራምፕን ነው የምመርጠው … ግን ሰው ፊት እንደዛ ብዬ አልናገርም … ሊያጠቁህ ይችላሉ” ብሎ ሹክ አለው፤ሲል አጫወተኝ፡፡ ከዚህች ቀልድ በላይ “Popular Vote”ን የገለጠልኝ ማስረጃ የለም፡፡ በቴሌቪዥኑ መስኮት የሪፐብሊካን የምርጫ ዘመቻ ዋና አቀናጁ፣ ጆን ፓዴስታ ብቅ ብሎ፣የሂላሪን ደጋፊዎች፤“ወደ ቤታችሁ ተመልሳችሁ ተኙ” ሲል ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ደጋፊዎቿ እያለቀሱ  ተበታተኑ፡፡
አሁን ትኩረት ሁሉ ወደ ሪፐብሊካኑ ጎራ ሆነ። እኔም የታሪክ አንድ አካል የመሆን ስሜት ለምን እንደተሰማኝ ማወቅ ፈልጌያለሁኝ፡፡ … ለምንድነው እኔም ፖለቲከኛ የምጠላው፡፡ ትራምፕ የቢዝነስ ሰው እንጂ ፖለቲከኛ አለመሆኑ ደጋግሞ ሲገለፅ ይሰማል። እንዲያውም ልሂቃን ከሚባሉት ጋር እንደማይቆም ይነገራል፡፡ “የአሜሪካ ህዝብ በአብዛኛው እኮ መሀይም ነው … ትራምፕን ቢደግፉ አይግረምህ፤ እንደ አውሮፓ ህዝብ ጥልቅ ነገር አይገባውም” ያለኝ አንድ ምሁር ትዝ አለኝ፡፡ አሁን ትራምፕ ሊመረጥ መሆኑን ሲሰማ ምን ይል ይሆን? ስል አሰብኩኝ፡፡
በእርግጥ ግን ዲሞክራሲና እውቀት ምንና ምን ናቸው፡፡ መሀይም ህዝብ፤ የሚፈልገውን መሪ አያቅም ማለት ነው? … አንድን ብቁ የሚለውን ሰው ለመምረጥ ሰው መሆን ብቻ በቂ አይደለም እንዴ? የፖለቲካ ውድድር በእርግጥ የኦሎምፒክ ውድድር አይደለም፡፡ አንድ ማራቶን ውድድር ላይ ተካፍሎ ያሸነፈውን ለማወቅ፣ ምርጫና ክርክር አያስፈልገውም፡፡ ግልፅ ነው፡፡ የሰው ብቃት በአካል ተገልፆ ሲታይ ክርክር አይፈጥርም፡፡
አንድ የምርጫ እጩ ለህዝቡ የሚሆን እውነትን ሲያቀርብስ? … አዎ ያከራክራል፡፡ ስለሚያከራክር ነው የድምፅ ብልጫ ያስፈለገው፡፡ ድምፁን በምርጫ ሳጥን ከቶ መቁጠር ያስፈለገው ክርክሩን ለመክፈል ነው፡፡ ህዝብ የሚመርጠውን አያውቅም ከተባለ ዲሞክራሲ የማይሰራ ፅንሰ ሀሳብ ነው እንደ ማለት ነው፡፡
መሀይም ቢሆንም ተመረጠ፡፡ የተሰበሰበው ህዝብ በጩኸት ደስታውን ገለፀ፡፡ የሚዲያ ተቋማቱ “የተከሰተው የፖለቲካ ስርዓት መሬት መንቀጥቀጥ ነው” ይላሉ ደጋግመው፡፡ ልክ ፀሐይ በምዕራብ የወጣች ይመስላል እንዲህ ሲሉ። መገረማቸው የመነጨው ከትምክህታቸው መሰለኝ። የማያውቁትን ህዝብ እናውቀዋለን ብለው ደመደሙ፡፡ ድምዳሜው ስህተት መሆኑ ሲገለፅ የሚሰጥ ትንታኔ ማቅረብ ጀመሩ፡፡
ከዚህ ቀደም መሀይምነትን ከሀይማኖተኛ ፅንፈኝነት ጋር በማያያዝ ነበር ትንታኔ የሚሰጡት፡፡ ወይንም “ካፒታሊዝምን ሊያፈርስ የመጣ ኮሚኒስት ነው” በማለት ነበር የሚወነጅሉት፡፡ ግን ንግድን የሚያበረታታ ፅንፈኛ ወይንም ታክስን እቀንሳለሁ የሚል ኮሚኒስት ለሀሜት አይመችም፡፡ ከዚህ ቀደም የቡሽ አስተዳደር ያማረራቸው ሪፐብሊካኖች (ያውም ቀይ አንገት ነጮች) ጥቁሩን ኦባማን በአንድ ድምፅ መርጠውታል፡፡ አሁን ደግሞ ጥቁሩ ሰው የሚፈልጉትን አልሰማ ሲል ለወጡት፡፡ ምንም ፍረጃ አያስፈልገውም፡፡ ከፑቲን ጋር ለመስራት መፈለጉም የህዝቡን ድምጽ አላሳጣውም፡፡  
… ብቻ ውጤቱ ታወቀ፡፡ ትራምፕ በከፍተኛ (278) ድምጽ ተመረጠ፡፡ ሂላሪ ስታለቅስ ቆይታ ደጋፊዎቿን ለማሰናበት መጣች፤ “ዋናው አሜሪካ ናት … ከትራምፕ ጋር መስራት አለብን” አለች፡፡ ዶናልድ ማሸነፉን ሲያውቅ ለደጋፊዎቹ ያደረገውን ንግግር ተሸናፊዋም ደገመችው፡፡ ልዩነትን መግጠም ላይ አተኮሩ፡፡ ስንጥቁ ግን በቀላሉ የሚገጥም አይመስልም፡፡ ኦባማም ብቅ ብሎ፣ከወዲሁ የሽግግር ሂደቱን አቀላጥፎ፣ ለዶናልድ ስልጣኑን ለማስረከብ እንደጓጓ ተናገረ፡፡
ቀኑን ሙሉ ቴሌቪዥን ላይ የተከልኩትን አይኔን ነቀልኩኝ፡፡ ትራምፕን ከክርክሩ ጀምሮ እደግፈው ነበር፡፡ ድጋፌ የመነጨው እውነትን የሚናገር መስሎ ስለተሰማኝ ነው፡፡ የሚመስል ሁሉ አይሆንም የሚሉኝ ብዙ ናቸው፡፡ መምሰል መጀመር ራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ወደ መሆን እና ወደ ለውጥ የመጓዣ ብቸኛው መንገድ ነው፡፡
“እውነተኛ ለውጥ ነው የማመጣው … የኦባማ አይነት ለውጥ እንዳይመስላችሁ” ብሏል፤ ሰውየው።
የምርጫ ውድድሩ የመጀመሪያ ሂደት ላይ … ገና የሪፐብሊካን እጩ ለመሆን በመወዳደር ላይ ሳሉ አንድ የጋዜጣ አምደኛ፤ “ትራምፕ የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩ ሆኖ ከተመረጠ የምፅፍበትን የጋዜጣ አምድ እበላዋለሁ …” ብሎ ፎክሮ ነበር፡፡
እንግዲህ ከእጩነት አልፎ ሰውየው ፕሬዚዳንት ሆነ፡፡ የጋዜጣ አምዱን ቀርቶ የህገ መንግስቱን ድርሳን በአጠቃላይ እየቀደደ ቢበላውም ይህ ሁነት የሚለወጥ አይሆንም፡፡

    በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች የሰብዓዊ ድጋፍ ይፈልጋሉ
በየመን የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የጦርነትና የአየር ድብደባዎች ሰለባ ሊሆኑ በሚችሉበት እጅግ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የአለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በየመን የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፤ የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የጠቆመው መግለጫው፣ ድርጅቱ በየመን በሚካሄዱ የአየር ጥቃቶችና የምድር ጦርነቶች ሳቢያ አቋርጦት የነበረውን ስደተኞችን ወደአገራቸው የመመለስ ስራ እንደገና መጀመሩንም አስታውቋል፡፡
የድርጅቱ የጅቡቲ፣ የኢትዮጵያና የየመን ቢሮዎች በጋራ ባደረጉት እንቅስቃሴ፤ ሆዴዳ በተባለው የየመን አካባቢ የነበሩ 672 ስደተኞችን ከአካባቢው የማስወጣት ስራ መስራታቸውን የጠቆመው መግለጫው፣ ተጨማሪ 150 ስደተኞችም በትናንትናው ዕለት ጅቡቲ ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ እንደሚደረግ ገልጿል፡፡

የጸረ-ትራምፕ ተቃውሞው ከ27 በላይ ከተሞችን አዳርሷል
    በዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሪፐብሊካኑን ወክለው የተወዳደሩት ዶናልድ ትራምፕ ማሸነፋቸውን የሚገልጸው የምርጫ ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባለፈው ረቡዕ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ተባብሶ መቀጠሉ እየተዘገበ ነው፡፡
የትራምፕን በምርጫ ማሸነፍ በመቃወም ወደ አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎች በአስር ሺህዎች እንደሚቆጠሩ የዘገበው ሲኤንኤን፤ ረቡዕ ዕለት የተጀመረው ተቃውሞ ወደ በርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች መዛመቱንና እስከ ሃሙስ ድረስም ከ25 በላይ በሚሆኑ የአገሪቱ ከተሞች ተቃውሞ መደረጉን ጠቁሟል፡፡
ተቃዋሚዎቹ ትራምፕ ስልጣን መያዛቸው አግባብ አለመሆኑንና አገር የመምራት ብቃት እንደሌላቸው በመግለጽ፣ ፎቶግራፋቸውን ከማቃጠልና በተለያዩ ተቋማት ላይ ጥፋት ከማድረስ አልፈው በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎችም የምርጫ ውጤቱ እንዲሰረዝና ሄላሪ ክሊንተን ስልጣን እንዲይዙ እስከመጠየቅ መዝለቃቸውን ዘ ጋርዲያን ትናንት ዘግቧል፡፡
ረቡዕ የጀመረው ተቃውሞ ሃሙስም ወደ ዴንቨር፣ ሚኒያፖሊስ፣ ፖርትላንድ፣ ኦክላንድና ሌሎች የአሜሪካ ከተሞች መስፋፋቱን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፣ በፖርትላንድ 4 ሺህ ያህል ተቃዋሚዎች አደባባይ በመውጣት በፖሊስ መኮንኖችና በመደብሮች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውንና ፖሊስም ከ29 በላይ ሰዎችን ማሰሩን ገልጧል፡፡
በዴንቨርም 3 ሺህ ያህል አሜሪካውያን ተቃውሞ ማድረጋቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን በቀጣይም ተቃውሟቸውን ለመቀጠልና የትራምፕን አሸናፊነት እንደማይቀበሉ የሚገልጹ ድርጊቶችን ለመፈጸም እያቀዱ ነው ሲል ዘ ጋርዲያን ትናንት ዘግቧል፡፡
በዋሽንግተን ሰፋ ያለ ተቃውሞ ለማድረግ ታስቦ በፌስቡክ የተከፈተው ዘመቻ እስከ ሃሙስ ተሲያት ድረስ፣ 30 ሺህ አባላትን ማፍራቱን የጠቆመው ዘገባው፤ ተቃውሞውን የሚደግፉ የቡድኑ አባላት ቁጥር በየሰዓቱ በሺህዎች እያደገ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
አሜሪካ በትራምፕ አሸናፊነት በተከፉ ተቃዋሚዎች ብትጥለቀለቅም፣ በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት አንዳቸው ሌላኛቸውን ሲያብጠለጥሉና ሲወነጅሉ የከረሙት ተመራጩ ዶናልድ ትራምፕና ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ግን፣ ሃሙስ በዋይት ሃውስ ተገናኝተው ልዩነትን ያሸነፈ ውይይት አድርገዋል ተብሏል፡፡
ኦባማና ትራምፕ 90 ደቂቃ በፈጀው ውይይታቸው፤ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በሚደረግበት ሁኔታና በሌሎች ብሄራዊና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች ዙሪያ መምከራቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡


     አዴፓ በሃገሪቱ አንድ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ እንዲፈጠር ለተቃዋሚዎች፣ ለምሁራንና ለህዝቡ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን በሚቀጥሉት 6 ወራት ይህን ውጥን እውን ለማድረግ በትጋት እንደሚሰራም አስታውቋል፡፡
‹‹ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ መፍጠር የወቅቱ ቀዳሚና አንገብጋቢ ጥያቄ ነው›› በሚል ፓርቲው ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ፤ ኢዴፓ የራሱን ጠቅላላ ጉባኤ ለማዘጋጀት ኮሚቴ አቋቁሞ እየተንቀሣቀሰ መሆኑን በመግለፅ ህዝቡ ድጋፉን እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ‹‹ህዝቡ ባልተደራጀና ባልተቀናጀ ሁኔታ በሃይልና በነውጥ ጭምር እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚፈለገውን ለውጥ ሊያመጣ አይችልም›› ያለው ፓርቲው፤ ከዚህ ስጋት በመነሣት ኢዴፓ  ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ምሁራን የህዝቡን ትግል በአግባቡ የሚመራ ጠንካራ ፓርቲ ለመፍጠር ተግተው መስራት አለባቸው ብሏል፡፡
ቀጣዮቹን 6 ወራት በመጠቀምም ፓርቲው ተጠናክሮ ሊመጣ የሚያስችለውን ጥረት ሁሉ እያደረገ መሆኑን በመግለፅ፤ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ህዝብ፣ መንግስትና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ድጋፍ እንዲያደርጉለት ጠይቋል፡፡
መንግስት አንድ ጠንካራ ፓርቲ እንዲፈጠር ተገቢውን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ያለው ኢዴፓ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጣዊ ድክመታቸውን በሃቅ በመገምገምና፣ ራሳቸውን በጥራት በማጠናከር፣ ከእርስ በእርስ መጠላለፍና መነቋቆር ወጥተው አንድ መሆን አለባቸው ብሏል፡፡
‹‹ኢዴፓ በዚህ አጀንዳ እውን መሆን የሚሠጠው ትኩረት ከፍተኛ ነው›› ያለው መግለጫው፤ የፓርቲን ደንብና መመሪያ እንዲሁም ፕሮግራም ከማሻሻል ጀምሮ የፓርቲውን ስያሜ እስከመቀየርና የተናጥል ህልውናውን እስከ ማክሰም የሚደርስ እርምጃ ለመውሠድ ዝግጁ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ይህን የሚያደርገውም አንድ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ በመፍጠር መሆኑን የጠቀሰው ኢዴፓ፤ የሃገሪቱ ምሁራንም ዳር ቆመው ከመታዘብና ከመተቸት ፓርቲዎችን በእውቀታቸውና በገንዘባቸው እንዲደግፉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በሃገሪቱ የተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ረግቦ እውነተኛ የብዙሃን ፓርቲ ስርአት የሚፈጠርበት ሁኔታ እንደሚኖር ፓርቲው ያለውን ተስፋ በመግለጫው አመላክቷል፡፡

• 42 ሺህ ተሳታፊዎች
 • የቻይናዋ ኦሎምፒክ ሻምፒዮን ዢን ዋንና የደቡብ አፍሪካው ማራቶን ሯጭ ሄነሪክ ራማላ
 እንግዶች ናቸው
   • 6ሺ በቀይ መነሻ 36ሺ በአረንጓዴ መነሻ
      • 500 አትሌቶች፤ 250 ቱሪስት ሯጮች፤ 20 አምባሳደሮች፤30 የአካል ጉዳተኞች፤ 500 የበጎ
         ፍቃድ አገልጋዮች እንዲሁም 30 አርቲስቶች
          • ባለፈው ዓመት ከ750 ውጭ ቱሪስት ሯጮች 1.803 ሚ ዶላር የኢኮኖሚ አስተዋፅኦ

    በቀጣይ ሳምንት መነሻ እና መድረሻውን በመስቀል አደባባይ  አድርጎ በሚካሄደው 16ኛው ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 42 ሺህ ስፖርኞች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ የታላቁ ሩጫ ዲያሬክተር ለዝግጅት ክፍላችን በላኩት መግለጫ እንዳስታወቁት ‹‹መስቀል አደባባይ ትልቁ ምልክታችን ነው፡፡ ውድድሩን በዚህ እንድናደርግ ስለተፈቀደልን ትልቅ ደስታ ይሰማናል፡፡ ከስራችን ውስጥ አንዱና ዋንኛው የአገራችንን ገፅታ መገንባት ነው›› ብለዋል፡፡ የ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው መነሻው በመስቀል አደባባይ ሆኖ በስታዬም፤ በሜክሲኮ፤ በአፍሪካ ህብረት አደባባይ፤ ሳር ቤት፤ ቄራ፤ ጎተራ ማሳለጫ፤ ላንቻ፤ መሳለሚያ በማድረግ በመስቀል አደባባይ ይፈፀማል፡፡
በ2008 እኤአ በቤጂንግ ኦሎምፒክ በ3ሺ መሰናል የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃችውና በቻይና የናይኪ ክለብ ፕሬዝዳንት የሆነችው የቻይናዋ አትሌት ዢን ዋን እና ታዋቂው የረጅም ርቀት፤ የማራቶን ሯጭ የሀጎነው የደቡብ አፍሪካው ሄንድሪክ ራማላ በክብር እንግድነት የሚገኙ ሲሆን ታዋቂው የደቡብ አፍሪካ የብሮድካት ኩባንያ ሱፕር ስፖርት የ52 ደቂቃዎች ስርጭት እንደሚሰራ ታውቋል፡፡
የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው በሁለት ምድብ በተካፋፈለ አዲስ አሯሯጥ መደረጉ ልዩ ያደርገዋል፡፡ የመጀመርያዎቹ በቀይ መነሻ የሚሮጡትና ከ1 ሰአት ባነሰ ጊዜ ውስጥ 10 ኪሎ ሜትሩን የሚጨርሱ ሲሆን ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች በደረሰን መረጃ በዚሁ ምድብ ለመሮጥ የተመዘገቡት ብዛታቸው 6000 ነው።  በሌላ በኩል በሁለተኛው ምድብ በአረንጓዴ መነሻ ለመሮጥ 36ሺ ተሳታፊዎች መመዝገባቸውን ያመለከቱት አዘጋጆቹ፤ በዚህ ምድብ ውድድሩን ለመጨረስ ከ1 ሰአት በላይ ጊዜ የሚወስድባቸውና በፌስቲቫል መልኩ የተለያዩ ትርኢቶችን እያሳዩና እየተዝናኑ የሚሮጡ እንደሚገኙበት ገልፀዋል፡፡
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቢሮ ለስፖርት አድማስ በላከው መግለጫ እንደተጠቆመው ዘንድሮ በውድድሩ ላይ 500 አትሌቶች በዋናው ውድድር ተሳታፊ ሲሆኑ ከ300ሺ ብር በላይ ለሽልማት መዘጋጀቱ ታውቋል፡፡ በአጠቃላይ በ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው ከሚሳተፉት 42ሺ ተሳታፊዎች መካከል 15ሺ ያህሉ በግል፤ 24ሺ በተለያዩ ድርጅቶች፤ 600 በሞባይል ባንኪንግ ለተሳትፎ መመዝገባቸውን የጠቀሰው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መረጃ፤ 20 የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፤ 30 የአካል ጉዳተኞች፤ 500 የበጎ ፍቃድ አገልጋዮች እንዲሁም 30 አርቲስቶች ‹‹ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ›› የሚለውን ዓላማ በማንገብ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫውን ለሶስት አመታት አብይ ስፖንሰር የሆነው ቶታል ኢትዮጵያ ሲሆን ከ15 በላይ የተለያዩ ስፖንሰሮችን ያሰባሰበ ውድድር እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል በ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው  ከውጭ አገር የሚመጡት ተሳታፊዎች ብዛት 250 ሲሆኑ ለመጀመርያ ጊዜ የቻይና ስፖርተኞችም እንደሚገኙ  ታውቋል፡፡ ዘንድሮ የውጭ አገር ተሳታፊዎች ብዛት የቀነሰው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መውጣቱን ተከትሎ የብዙ አገራት ኤምባሲዎች ለዜጎቻቸው በሰጡት ማስጠንቀቂያ ተሳትፏቸውን ለመሰረዝ በመወሰናቸው ነው፡፡
ይሁንና የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር በቱሪዝም ገቢ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የላቀ አስተዋፅኦ እንዳለው  በሊድስ ቢኬትዩኒቨርስቲ የተሰራው አንድ ጥናት ማረጋገጡን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በዩኒቨርስቲው ለካርኒጄ ሪሰርች ኢንስትቲዩት The Economic Impact of International Tourists attending the 2015 Great Ethiopian Run በሚል ርእስ በዶክተር ኢያን ሪቻርድስ የተሰራው ጥናት እንዳመለከተው ባለፈው ዓመት በ15ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር 750 የውጭ አገር ዜጎች ተሳትፈው በተለያዩ ወጭዎች እና ለበጎ አድራጎት በሰጡት መዋጮ ከ1.803 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ አድርገዋል። በጥናታዊ ሪፖርቱ ላይ በዝርዝር እንደተገለፀው 750ዎቹ ቱሪስት ሯጮች ለሆቴል፤ ለአየር ትኬት በተለያዩ ሁኔታዎች በድምሩ 803ሺ ዶላወጭ ሲያደርጉ ከመካከላቸው 38 በመቶ ያህሉ በበጎ ፍቃድ የገቢ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ በመሳተፍ 1 ሚሊዮን ዶላር አዋጥተው ለተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች እንዲበረከት አድርገዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የ2009 የፕላን ኢንተርናሽናል የልጆች ውድድር የዛሬ ሳምንት በወጣቶችአካዳሚ እንደሚካሄድም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የልጆች ውድድሩ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ዋዜማ ሲካሄድ  በሶስት የእድሜ መደቦች ከ11 ዓመት በታች፤ ከ8 አመት በታ እና ከ5 ዓመት በታች ተካፍሎ ሲደረግ ከ4500 በላይ ህፃናና ታዳጊዎችን በማሳተፍ እንደሆነ ታውቋል፡፡