Administrator

Administrator

በሳኡዲ አረቢያ አንድን ውሻ በከፍተኛ ሁኔታ አሰቃይተው ገድለዋል በሚል ተከሰው ፍርድ ቤት የቀረቡ ሁለት ወጣቶች የ5 አመት እስር ወይም የ500 ሺህ የሳኡዲ ሪያል መቀጣታቸውን አረብ ኒውስ ዘገበ፡፡
ወጣቶቹ ከሳምንታት በፊት ውሻውን በከፍተኛ ሁኔታ ሲደበድቡና ሲያሰቃዩ ቆይተው ለሞት እንደዳረጉት የሚያሳየውና በአንደኛው ወጣት ሞባይል የተቀረጸው አስር ደቂቃ ያህል የሚረዝም የቪዲዮ ፊልም በማህበራዊ ድረገጾች አማካይነት በስፋት መሰራጨቱን ተከትሎ፣ ድርጊቱ ከፍተኛ ተቃውሞ ማስነሳቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ፖሊስ ወንጀለኞቹን ተከታትሎ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል፡፡
ፖሊስ ወንጀለኞቹ መኪና እያሽከረከሩ ውሻውን በመሬት ላይ በመጎተት ሲያሰቃዩት እንደነበር በሚያሳየው በዚህ ቪዲዮ ላይ የታየውን የመኪናዋን ታርጋ ቁጥር በመመዝገብ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ተከታትሎ በሪያድ በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ዘገባው አስረድቷል፡፡
የአገሪቱ የግብርና ሚኒስትር ጃቢር አል ሸሪ፤ ወጣቶቹ በውሻው ላይ የማሰቃየት ወንጀል መፈጸማቸው በመረጋገጡ፣ በአገሪቱ ህግ እና የባህረ ሰላጤው አገራት ባወጡት እንስሳትን የማሰቃየት ወንጀል ህግ መሰረት፣ ፍርድ ቤት ቀርበው ቅጣት እንደተጣለባቸው አስታውቀዋል፡፡

በእቴጌ ጣይቱ ሆቴል ላይ የደረሰውን የቃጠሎ አደጋ ለመታደግ በተደረገው ርብርብ ላይ ተሳታፊ ለነበሩ አካላት “ምስጋና” የሚቀርብበት ምስጋና የተሰኘ ልዩ የኪነ ጥበብ ዝግጅት በጣይቱ ሆቴል ግቢ ውስጥ ተከፈተ፡፡ ከጥር 14 እስከ ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ ይቆያል በተባለው በዚሁ የኪነ ጥበብ ፕሮግራም ላይ የተለያዩ ሰዓሊያን የስዕል ስራዎች ለዕይታ ቀርበዋል፡፡ ከስዕል ኤግዚቢሽኑ በተጨማሪ ልዩ የሰርከስ፣ የሙዚቃ ትርኢትና ሥነ ግጥሞች የሚቀርቡ ሲሆን ለህፃናት የታሪክ ነገራ እና የስዕል ስራዎች ስልጠናም እንደሚሰጥ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረፃዲቅ ሀጎሽ ፕሮግራሙን መርቀው በከፈቱበት  ወቅት እንደተናገሩት፤ ታሪካዊውንና ጥንታዊውን ሆቴል ከቃጠሎው አደጋ ለመታደግና የህዝብ ሀብት የሆነውን ሆቴል  ለማዳን ህብረተሰቡ ያደረገውን ተጋድሎ እናደንቃለን ብለዋል፡፡ ሆቴሉ በቋሚነት የቀድሞ ይዘቱንና ታሪካዊነቱን በጠበቀ መንገድ እንዲታደስ የሚደረግበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑንና ሆቴሉን ከፀሐይና ከዝናብ ለመከላከል የሚያስችል ጊዜያዊ ጥገናው በሆቴል አስተዳደሩ መጀመሩን አመልክተዋል፡፡

በድምፃዊ ዘለቀ ገሰሰና በአቶ አዲስ ገሰሰ የተሰራው የታዋቂው የሬጌ አቀንቃኝ የቦብ ማርሌ ሐውልት ከሁለት ወር በኋላ በሚደረግ ታላቅ ሥነ-ስርዓት እንደሚቆም አዘጋጆቹ ገለፁ፡
ድምፃዊ ዘለቀ ገሰሰ ለአዲስ አድማስ እንደተናገረው፤ ሐውልቱ ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በነበሩት አቶ አርከበ እቁባይ በተሰየመውና ገርጂ ኤምፔሪያል ሆቴል ፊት ለፊት በሚገኘው የቦብ ማርሌ አደባባይ ላይ ለማቆም ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡
ሚያዚያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም የዳግማይ ትንሳኤ ዕለት በሚደረገው ታላቅ ኮንሰርትና የሀውልት ማቆም ሥነ-ስርዓት ላይ ሪታ ማርሌን ጨምሮ የቦብ ማርሌ ሁለት ልጆች እንደሚገኙና ልጆቹ በኮንሰርቱ ላይ እንደሚዘፍኑ ተገልጿል፡፡
ቀደም ሲል ሃውልቱ በሚከበረው የቦብ ማርሌ የልደት በዓል ወቅት እንዲቆም ታስቦ የነበረ መሆኑን የተናገረው ድምፃዊ ዘለቀ ገሰሰ የቦብ 70ኛ ዓመት የልደት በዓል በጃማይካ ኪንግስተን ከተማ እንዲከበር በመወሰኑና የቦብ ቤተሰቦችም ለበዓሉ ወደ ስፍራው በማምራታቸው ፕሮግራሙ ተሰርዞ ለዳግማይ ትንሳኤ እንዲካሄድ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ የቦብማርሌ 70ኛ ዓመት የልደት በዓል ዓመቱን ሙሉ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበርም ድምፃዊው ጨምሮ ገልጿል፡፡  

በእውነት ፊልም ፕሮዳክሽን የተሰራውና በወንድወሰን ይሁብ ተደርሶ በእውነት አሳሳህኝና በደራሲው የተዘጋጀው “የገጠር ልጅ” የተሰኘው ፊልም ነገ ከቀኑ 11፡30 በብሔራዊ ቲያትር በሚካሄድ ሥነ ስርአት ይመረቃል፡፡ ቤተሰቦቿን ለመርዳት ወደ አረብ አገር በስደት ሄዳ ወደ ሀገሯ የተመለሰች አንዲት ወጣት የሚደርስባትንና የሚያጋጥማትን አሳዛኝ የህይወት ፈተና የሚያሳየው ልብ አንጠልጣይ ፊልም ሙሉ ቀረፃው የተካሄደው በአዲስ አበባ ከተማና ሰንዳፋ አካባቢ መሆኑን የፊልሙ ፕሮዲዩሰሮች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ በፊልሙ ላይ ተሻለ ወርቁንና ሰለሞን ሙሔን ጨምሮ ከ90 በላይ ወጣትና አንጋፋ ተዋንያን የተሳተፉበት መሆኑ ተገልጿል፡፡

በደራሲ ቃልኪዳን ኃይሉ የተፃፈውና “ለምን አትቆጣም?” የተባለው አዲስ መፅሐፍ ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል እንደሚመረቅ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አስታውቋል፡፡

ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ሰንዳፋ ከተማ “ዋን ስቶፕ ሲኒማ” የተሰኘ ዘመናዊ ሲኒማ ቤት ባለፈው ሳምንት ተመርቆ አገልግሎት ጀመረ፡፡ ሲኒማ ቤቱ በ1.7 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ሲሆን ለከተማዋና ለአካባቢው ነዋሪዎች አማራጭ የመዝናኛ ማዕከል ይሆናልም ተብሏል፡፡ ሲኒማ ቤቱ እስከ 500 የሚደርሱ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም እንዳለው ተገልጿል፡፡ በከተማው ከንቲባ አቶ ዘገዬ ካሳ የዛሬ ሳምንት ተመርቆ የተከፈተው ዋን ስቶፕ ሲኒማ፤ ለአገሪቱ የፊልም ኢንዱስትሪ እድገት የበኩሉን ድርሻ እንደሚያበረክት የድርጅቱ ባለቤት አቶ ዘላለም ተመስገን ተናግረዋል፡፡

Saturday, 24 January 2015 13:27

ሞኝ እንደነገሩት

ሞኝ እንደነገሩት
“ፍቅር ያሸንፋል” ስትለኝ አምኜህ
በጦርነት ሁሉ ልሰለፍ አብሬህ
ደብተሬን ቀድጄ
አድርቄ ወጥሬ ጋሻ ሰርቼበት
ብዕሬን ፈልፍዬ ጦር አስቀርጬበት
ጠላትን ወግቼ
ለፍቅር ደምቼ…
ካቀረቀርኩበት ቀና ብል የለህም
ያሸንፋል ባልከኝ አንተ አልተሸነፍክም
እኔ ነኝ ብቻዬን ፍልሚያውን አውጄ
ጦሬን አበጅቼ
እኔው ተማርኬ ራሴን የሰጠሁ
ሙሉው ጦርነቴን
ሙሉ መሸነፌን
ሙሉ መሰጠቴን
ያንተ ድርሻ ቢኖር ልቤን የሰወረው
“ፍቅር ያሸንፋል” ማለትህ ብቻ ነው፡፡
    (ከብሩክታዊት ጐሳዬ “ፆመኛ ፍቅር”
    የተሰኘ የግጥም መድበል የተወሰደ)

Saturday, 24 January 2015 13:24

ፀሎቴ

እንዳላዝን … እንዳልባባ
ለኔ ሲሉ፡- እያነቡ
የኔን ዕንባ
 እኔኑ
በኔው፡- ዕንባ
እያሉኝ እሹሩሩ … እሹሩሩ
ለኔ ሲሉ ፡- ሁልዜም እንደኖሩ
እስከዛሬም .. የሚኖሩ  
ነበሩ፡፡
እንዳላዝን … አባብለውኝ
እንዳልስቅም ፡- አዝነውልኝ
ከርቱዕ አንደበታቸው
ዕንባዬ ፈሶ ከዕንባቸው
ለኔ ብለው
እውነት ለኔ ብለው
የኔን ቁስል ቆስለውልኝ
የኔን ህልም ታመውልኝ፣ ታመውልኝ፡፡
ሞቴንም እንዳይሞቱልኝ
ፀሎት ላይ ነኝ
ለኔ ሲሉ፡- ያልሆኑትን እንዳይሆኑልኝ
(1994 ዲላ)

Saturday, 24 January 2015 12:51

የፖለቲካ ጥግ

ፖለቲካ፤ ለፖለቲከኞች ሊተው የማይችል ትልቅ ቁምነገር ነው     ወደሚል ድምዳሜ ደርሻለሁ፡፡
ቻርልስ ደጐል
* በዲሞክራሲ ሥርዓት አንደኛው ፓርቲ ሁልጊዜ ዋና ጉልበቱን     የሚያውለው ሌላኛው ፓርቲ አገር ለመምራት ብቁ አለመሆኑን     ለማረጋገጥ በመሞከር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሁለቱም ይሳካላቸዋል፡፡ ደግሞም     ትክክል ናቸው፡፡
ኤች ኤል ሜንኬን
* ዲሞክራሲ በመጠኑ የምትጠላውን     እጩ እንድትመርጥ የሚፈቅድልህ ሥርዓት ነው፡፡
ሮበርት ባይርኔ
* ፖለቲከኞችና ዲያፐር (የሽንት ሁለቱም በተመሳሳይ ምክንያት በየጊዜው መለወጥ አለባቸው፡፡
ያልታወቀ ፀሐፊ
* ፖለቲከኛ ነገ፣ በሚቀጥለውሳምንት፣ በሚቀጥለው   ወር፣ በሚቀጥለው ዓመት የሚከሰተውን ነገር የመተንበይ ችሎታ ያስፈልገዋል፡ከዚያም በኋላ ያልተከሰተበትን ምክንያት የማስረዳት ችሎታ ሊኖረው ይገባል፡፡
ዊንስተን ቸርችል
* የፖለቲካ ቀልድ ችግሩ፣ የቀለድንባቸው ፖለቲከኞች መመረጣቸው ነው፡፡
ያልታወቀ ግለሰብ
* ፖለቲካ፤ ውሳኔዎች አስፈላጊነታቸው እስኪያበቃ ድረስ የማቆየት ጥበብ     ነው፡፡
ሔንሪ ኪውይሌ
* ልታሳምናቸው ካልቻልክ አደናግራቸው፡፡
ሃሪ ኤስ ትሩማን
* ሰላማዊ ትግል እውን እንዳይሆን የሚያሰናክሉ፣ የትጥቅ ትግልን አይቀሬ ያደርጉታል፡፡
ጆን ኤፍ ኬኔዲ
* ፖለቲካ እጅግ ውድ እየሆነ ከመምጣቱ የተነሳ ለመሸነፍ እንኳን ብዙ ገንዘብ ይፈልጋል፡፡
ዊል ሮጀርስ

Saturday, 24 January 2015 12:47

አስገራሚ የቃላት ፍቺዎች

ተሞክሮ
 ሰዎች ለስህተታቸው የሚሰጡት ስም
አቶሚክ ቦምብ
 ሁሉንም ፈጠራዎች የሚያወድም ፈጠራ
አድርባይ
ድንገት ወንዝ ውስጥ ቢገባ ገላውን መታጠብ የሚጀምር ሰው
ወንጀለኛ  
ከመያዙ በቀር ከሌላው ሰው የማይለይ
ሃኪም
 በሽታህን በክኒን ገድሎልህ፣ አንተን በክፍያ የሚገድልህ ሰው
አለቃ
 ስትዘገይ ቀድሞህ የሚገባ፣ ስትቀድም የሚዘገይ
ኮሚቴ  
በግላቸው ምንም መስራት የማይችሉ ሰዎች በጋራ ምንም መስራት እንደማይቻል ለመወሰን በአንድ ላይ የሚቀመጡበት
ክላሲክ
ሰዎች የሚያወድሱት ግን የማያነቡት መፅሃፍ
የጉባኤ አዳራሽ
 ሁሉም ሰው የሚናገርበት፣ ማንም የማያዳምጥበትና በመጨረሻም ሁሉም የማይስማሙበት ስፍራ
ተስፈኛ
 ከአይፍል ማማ ላይ እየወደቀ ሳለ መሃል ላይ “አያችሁ ገና አልተጎዳሁም” የሚል ሰው
ስስታም
ሃብታም ሆኖ ለመሞት በድህነት የሚማቅቅ ሰው
ፈላስፋ
ሲሞት እንዲወራለት በህይወት ሳለ ራሱን የሚያሰቃይ ጅል
ወዘተ
ሌሎች በትክክል ከምታውቀው በላይ ታውቃለህ ብለው እንዲያምኑ ማድረጊያ ዘዴ