Administrator
“ስውር ስፌት ቁ.2” ተመረቀ
በጋዜጠኛ፣ ገጣሚና ተርጓሚ ነቢይ መኰንን የተጻፈው “ስውር ስፌት ቁ.2” የግጥም መድብል ትናንት ምሽት
በዋቢ ሸበሌ ሆቴል አዳራሽ ተመረቀ፡፡የኪነጥበብ ቤተሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት
በተከናወነው የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ፣ ገጣሚውን ጨምሮ አንጋፋና ወጣት ገጣሚያን ስራዎቻቸውን ለታዳሚው
አቅርበዋል፡፡
ገጣሚ ነቢይ በመኰንን ከዚህ በፊት “ጥቁር፣ ነጭ ግራጫ ግጥሞች” እና “ስውር ስፌት ቁ.1” የግጥም መፃህፍት
ለአንባቢ ያበረከተ ሲሆን፣ በታዋቂዋ አሜሪካዊት ደራሲ ማርጋሬት ሚሼል የተጻፈውን “Gone With The
Wind” የተሰኘ ተወዳጅ የረጅም ልቦለድ መጽሃፍ፣ “ነገም ሌላ ቀን ነው” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ተርጉሞ
በማቅረብ ይታወቃል፡፡
“ስውር ስፌት ቁ.2” በመጽሃፍት መደብሮችና በአዟሪዎች እየተሸጠ ይገኛል፡፡
“የጭቃ ጅራፎች” ነገ ይመረቃል
“መንገድ ተዘረጋ
መንገድ ተቀየሰ
በተራማጅ እጦት
መልሶ ፈረሰ!...”
በገጣሚ አክሊሉ ገብረ መድህን የተጻፈው “የጭቃ ጅራፎች” የተሰኘ የግጥም መጽሃፍ፣ ነገ ከምሽቱ 11፡30 ሰዓት
በዋቢ ሸበሌ ሆቴል አዳራሽ ይመረቃል፡፡
በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 50 የገጣሚው የግጥም ስራዎች የተካተቱበት መጽሃፉ 92 ገጾች
ያሉት ሲሆን በተለያዩ መጽሃፍት መደብሮችና አዟሪዎች ዘንድ በ20 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
የጥበብ አፍቃሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በሚገኙበት የመጽሃፉ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ፣ አንጋፋና
ወጣት ገጣሚያን ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡
የ“ነጻ አርት ቪሌጅ” የስዕል ትርዒት ዛሬ ይከፈታል
“ነጻ አርት ቪሌጅ” በማካሄድ ላይ የሚገኘው ‘ነጻ ሃሳብ’ የተሰኘ የሥነ ጥበብ ፌስቲቫል አካል የሆነው የስዕል ትርዒት ዛሬ ከቀኑ 9 ሰዓት በ“ነጻ አርት ቪሌጅ” ይከፈታል፡፡ነጻ አርት ቪሌጅ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ እንዳለው፣ ከዛሬ ጀምሮ ለተመልካች ክፍት በሚሆነው በዚህ የስዕል ትርኢት ላይ በ30 ሰዓሊያን የተሰሩ የሥነ ጥበብ ስራዎች ለእይታ ይቀርባሉ፡፡
ከግቢ ‘በሮች’ ወደ መንደር ‘በሮች’…
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…ግድግዳው ላይ ያለው ቀን መቁጠሪያ ተለወጠ? እኛ አገር ዘመን መለወጥ ማለት ግድግዳ ላይ ያለውን ቀን መቁጠሪያ መለወጥ ከሆነ እየሰነበተ ነዋ! የምር እኮ…ዘንድሮ “ሲጋራ አቆማለሁ…” “ቂማ አቆማለሁ…” “መጨለጥ አቆማለሁ…” የሚል አንድም ወዳጅ አልገጠመኝም፡፡ ወዳጆቼ ‘ሲፑ’ና ‘ቂማው’… ይሄን ያህል ተስማምተዋችኋል እንዴ! “ነገር እየሰማሁና እያየሁ ከምቃጠል ሳላይና ሳልሰማ እየቃምኩና እየጠጣሁ ብቃጠል ይሻለኛል!” ያልከን ወዳጃችን ጭራሽ እየወፈርክ ሄድክሳ! እውነትም “አለማየትና አለመስማትን የመሰለ ነገር የለም…” ምናምን የሚል የጥናት ውጤት የሆነ ቦታ ሊኖር ይችላል፡፡ ሀሳብ አለን…እንዲህ መፋጠጥ በተለመደበት ዘመን በየምግብ ቤቱ “ሌላው ተመጋቢ የሚመገበውን እየተንጠራሩ ማየት የተከለከለ ነው…” ምናምን የሚል ማስታወቂያ ይለጠፍልንማ!! ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሰዎቹ ምን የሚሉ ይመስለኛል መሰላችሁ… “አየሻት ስቴክ እኮ ነው የምትበላው!” “ታዲያ ስቴክ ብትበላ ምን አለበት?” “ምን አለበት! አንድ ብልቃጥ የጥፍር ቀለም ዓመት ተኩል የምታብቃቃ፣ ስቴክ የምትበላበት ከየት አምጥታ ነው! ይሄኔ አንዱን ሼባ ይዛ ይሆናል፡፡”
ሌላው ቡድን ዘንድ ደግሞ ምን ይባላል መሰላችሁ… “ስማ ያንን ችጋራም ምን እንደሚበላ አየኸው!” “ምንድነው የሚበላው?” “በእናትህ በቅዳሜ ምድር ክክ ምናምን ይበላል!” “የፈለገውን ቢበላ ምናለበት!” “የምን መፈለግ ነው! ችጋራም ነው እንጂ! የሚሠራው ቢዝነስ ቀላል መሰለህ! ልጄ ከሰዎቹ ጋር ተለጥፎ…” እናላችሁ…ልንመገብ ገብተን ስለሌሎች ተመጋቢዎች… “ከዕለታት አንድ ቀን…” ምናምን ታሪኮች የምናበዛ ሰዎች በርክተናል፡፡ የምር ግን…ነገሬ ብላችሁ እዩልኝማ…አሥር ጠረጴዛ ዘሎ ያሉ ሰዎች ያለ አጉሊ መነጽር እያሻገሩ አጎራረሳችሁንና አዋዋጣችሁን ‘ሲገመግሙ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) እኔ የምለው…አጎራረሳችን የትኛው ካምፕ ውስጥ እንዳለን ያስነቃብናል እንዴ! ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… አዲስ አበባ በራሷ አነሳሽነት ነዋሪዎቿን ‘በመደብ’ እየለየች ነው፡፡
ልክ ነዋ…‘ንጥጥ’ ያሉ ሀብታሞች በተወሰኑ አካባቢዎች፣ ‘ምጥጥ’ ያሉ ቺስታዎች ደግሞ በየስርቻው! ሟርት አያስመስልብኝና እንዲህ አይነት ነገሮች እየበዙ በሄዱ ቁጥር የኋላ፣ ኋላ አሪፍ አይሆንም፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አሁን ‘የምንፈራው’ የሀብታሞቹን መኮሳተር (ለመኮሳተርስ ሲያዩን አይደል!) የጥበቃዎችን ግልምጫ ነው፡፡ ስሙኝማ…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው… አንዳንድ ሰዎች ‘መለዮ ሲለብሱና ዱላ ቢጤ መወዝወዝ ሲጀምሩ’ … አለ አይደል…የሚናፍቃቸው ዱላውን የሚያሳርፉበት ጀርባ ነው እንዴ! አሀ…በሰፈር ደረጃ ያሉ አንዳንዶቹን እኮ ስታዩዋቸው…አለ አይደል… በዓይናቸው እናንተን እያዩ በልባቸው… “ይሄ እንዲህ ትከሻውን እያሳየ የሚንጎማለለውን ቀልጥሞ፣ ቀልጥሞ መጣል ነበር!” እያሉ የሚያስቡ ይመስላችኋል፡፡
እና ‘መረጋጋት’ን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ልክ ነዋ…ዱላው ‘እዛኛው እጅ’ ላይ የገባ ዕለት “…ይቅርታ እለምናለሁ፣ ጥፋቴን አውቄያለሁ…” ምናምን አይነት የአድማጮች ዘፈን ምርጫ አይሠራም! እኔ የምለው…ካወራን አይቀር…እዚቹ ከተማ ‘ጌትድ ኮሚዩኒቲስ’ የሚባሉ ግቢዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ሙሉ መንደሮቹ ራሳቸው ግማሽ የእግር ኳስ ሜዳ በሚያካክሉ በሮች እየተከረቸሙ ነው፡፡ (ቀስ ብሎ ደግሞ ሙሉ አውራጃን ዓመት ሙሉ ቀጥ አድርገው ‘መቀለብ’ በሚችል ገንዘብ የሚገዙ መኪኖች በሚያልፉባቸው መንገዶች “ዝር ትሉና!” እንዳንባል መፍራት ነው!) እናላችሁ…ቀደም ሲል የመኖሪያ ግቢ በር ላይ ነው “ማንን ፈልገህ ነበር?” የምንባለው፡፡ አሁን ግን በታጠሩት መንደሮች ዋና በር ላይ ነው “ወዴት ነው!” የምንባለው፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በፊት እኮ የሀብታምና የድሀ መኖሪያ የሚለየው እንዲህ በመንደር ሳይሆን በቤቶቹ ትልቅነት ምናምን ነበር፡፡ እዚህ ጋ ቅልጥ ያለ ቺስታ እንደ ባለቤቷ ጠጅ ያንጋደዳት ጎጆ ውስጥ እየኖረ፣ ከፊት ለፊቱ ደግሞ የፊታውራሪ እከሌ የተንጣለለ ግቢ ይገኛል፡፡
(በነገራችን ላይ ፊትአውራሪ የሚለው መጠሪያ እየጠፋ መሄዱ የፊት አውራሪነት ባህሪይም አብሮ እየጠፋ ነው ማለት አይደለም፡፡ እንደውም ባይብስበት ነው!) እናላችሁ…ፈራንካው ያላቸው ሰዎች መንደሮቻቸውን በትላልቅ የብረት በሮች እንደሚዘጉት ሁሉ፣ ባለፈረንካዎችና ‘ባለድርሻ አካላቱ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) በሁሉም በኩል ራሳቸውን በትላልቅ ‘የብረት በር’ እየከለከሉ ነው፡፡ ለምሳሌ…የፈረንካ ሰፈር ትኩስ ሀይሎች ሲገናኙ የሚያወሩት ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… “ፌስቡክ ፍሬንዶቼ አራት ሺ ሰባት መቶ ሆኑ!” “ዋው! የእኔ ገና ሦስት ሺህ ናቸው፡፡ በቀደም ፍሬንድ የሆነችኝ…አንድ ምን የመሰለች ልጅ በፌስቡክ አግኝቻለሁ፡፡“ “ዩ ዶንት ሴይ! ከስቴትስ ነው?” “ኖ እዚሁ ነች…” “ኋት! ዩ ሚን ሺ’ዝ ሎካል!” “ብታያት እንዲህ አትልም ነበር፡፡ ምን የመሰለች ቺክ መሰለችህ! እንደውም ፕሮፋይል ፒክቸሯን ላሳይህ…” ከዛማ ሳምሰንግ ጋላክሲ ኤስ ፋይቭ ምናምን ይወጣል፡፡ ‘እዚህኛው ሰፈር’ ደግሞ ‘ፌስ’ ገና ከ‘ቡክ’ ጋር ሳይያያዝ ከሰው ልጅ አካል አንዱ የሆነበት ቺስታው መንደር ምን የሚባባሉ ይመስለኛል መሰላችሁ… “ስማ ከዚያች ልጅ ጋር እንዴት ናችሁ…” “የቷ!” “የቷ ትላለህ እንዴ! ያቺ ቀበሌ ሸማቾች ምናምን የምትሸጠው…” “ምን ታደርግ አንተ…እኔ ልጄ ስንት ሀሳብ አለብኝ! ሥራ ፍለጋ ስንከራተት ሁለት ዓመት እንዳለፈኝ አታውቅም!” “አትበሳጭ፣ ግዴለህም ለደግ ነው፡፡” “የምበላው እያጣሁ ለደግ…” ይልና መሀል ላይ ያቋርጣል፡፡ ‘ትርፍ’ ሊናገር ነበራ! አንድ ሁለቴ ያማትብና “…ይልቅ የማነበው አሮጌ መጽሐፍ ካለህ…” ምናምን እየተባለ ይቀጥላል፡፡እናላችሁ…እነሱ በ‘ቴክስት ሜሴጅ’ የፈለጉትን ቢባባሉ ያው የለመዱት ነው፡፡
እኛ ግን… አንዳንዱ የእኔ ቢጤ ‘ፋራ’ እንትናዬውን “ስዊቲ፣ አይ ላቭ ዩ ቬሪ ማች!” በሚል ሁሉም ሰው በሚገባው የፈረንጅ አፍ ግጥም አድርጎ ይጽፋል፡፡ አሀ…በእንግሊዝኛ ጥየቄ ማቅረብ ነገሩን ሁሉ ‘አሪፍ’ ያስመስለዋላ! ለነገሩ…“ስዊቲ!” “ሀኒ!” “ማይ ኤንጅል!” ምናምን ነገሮች በእኛ አፍ አያምሩማ! “ዳቦ ፍርፍር እየበሉ በእንግሊዘኛ ማወራት አያምርም…” የሚል ሰው የሆነ ቦታ ያለ አይመስላችሁም! (ስሙኝማ…አንዳንድ በፈረንጅኛ አፍ እንኳን የሚያነጥሱት ሰበሰቧቸው ቦታዎች ብቅ ማለታችን አይቀርም፡፡ እናላችሁ…በፈረንጅ አፍ ሲያወሩ ቋንቋው ላይ የሚያደርሱበት የኃይል ጥቃት ሶሪያና ኢራቅ አጠገብ ብንሆን ኖሮ ሌላ የዓለም ጦርነት ዋዜማ ሊሆን ይችል ነበር፡፡ አሀ… የአትክልት ተራ “ማዳም ጉድ ኦራንጅ…” አጠገብ እንኳን አይደርሱም! በዚህ ላይ ቅልጥ ያሉ ‘የብልግና’ ቃላት መሸለያ እየመሰላቸው ሲደጋግሙት ፈረንጅ ምን ያህል ይሳቀቅ ይሆን ያሰኛል! ከዓመታት በፊት በዕድሜ ‘ሲክስቲዋን’ ፉት ብለው ወደ ‘ሰቨንቲዋ’ የሚጠጉ እናት በ‘ታይታቸው’ ኋለኛ በኩል ‘ባይት ሚ’ (Bite me!) ተብሎ የተጻፈበት ለብሰው መሃል ከተማ ሲዘንጡ ማየቴ ትዝ ይለኛል፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ…በመንደር ትላልቅ በሮችም፣ በፌስቡክ ‘ፍሬንዶችም፣’ በ“ባይት ሚ” ምናምን አካሄዳችንም እያማረበት አይመስልም፡፡ የ‘ቦተሊካው’ ነገር አልበቃ ብሎ የሚለያዩን ነገሮች እየበዙ ሲሄዱ…አለ አይደል… ነገርዬው የትላልቅ በሮች ጉዳይ መሆኑ እንዳያበቃለት መፍራት ነው፡፡ከግቢ ‘በሮች’ ወደ መንደር ‘በሮች’…ተስፋ የሚሰጥ ‘ዕድገት’ አይደለም፡፡ ደህና ሰንብቱልኝማ!
ኢቦላ የላይቤሪያን ህልውና አደጋ ላይ ጥሎታል
- 160 ባለሙያዎች ህክምና ሲሰጡ በኢቦላ ተይዘው፣ ግማሽ ያህሉ ሞተዋል
- 2 ሺህ 46 ዜጎቿ በቫይረሱ ተይዘዋል፤ 1ሺህ 224 ሞተዋል
- የአገሪቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ተቃውሷል
በላይቤሪያ በከፍተኛ ፍጥነት በመስፋፋት ላይ የሚገኘው የኢቦላ ቫይረስ፣ የአገሪቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በማቃወስ ብሄራዊ ህልውናዋን አደጋ ላይ የጣለ ከፍተኛ ችግር የሆነበት አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱን ቢቢሲ ዘገበ፡፡የአገሪቱን የመከላከያ ሚኒስቴር ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ለ14 አመታት በዘለቀውና እ.ኤ.አ በ2003 በተቋጨው የእርስ በርስ ግጭት 250 ሺህ ያህል ዜጎቿ የሞቱባትና በመሰረተ ልማት አውታሮቿ ላይ ከፍተኛ ውድመት የደረሰባት ላይቤሪያ፣ አሁን ደግሞ ኢቦላ እንደ ሃገር መቀጠሏን ጥያቄ ውስጥ የሚከት የህልውና ፈተና ሆኖባታል፡፡ በቅርቡ በአገሪቱ የተቀሰቀሰው የኢቦላ በሽታ ከጊዜ ወደጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ መምጣቱን የጠቆመው ዘገባው፣ በበሽታው ከተጠቁ 2ሺህ 46 የአገሪቱ ዜጎች መካከል 1ሺህ 224 ያህሉ ተህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን ገልጧል፡፡“ኢቦላ ለላይቤሪያ ብሄራዊ ህልውና እጅግ አደገኛ ስጋት እየሆነ ነው፡፡ በፍጥነት በመሰራጨት ላይ የሚገኘው ይህ በቀላሉ የሚተላለፍ ገዳይ ቫይረስ፣ በአገሪቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ፈጥሯል፡፡” ብለዋል የላይቤሪያ የመከላከያ ሚኒስቴር ብሮዊን ሳሙካይ፣ ባለፈው ማክሰኞ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት፡፡
በሽታው በአገሪቱ ክፍተኛ ጥፋት እያደረሰ እንደሚገኝ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በቂ የጤና መሰረተ ልማት ያልተሟላላት የላይቤሪያ የጤና ተቋማት በበሽታው ተጠቂዎች መጣበባቸውንና ተገቢውን የህክምና አገልግሎት መስጠትና የቫይረሱን ስርጭት መግታት የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን አስረድተዋል፡፡ አለማቀፉ ማህበረሰብ በላይቤሪያ ለተከሰተው የኢቦላ ችግር የሰጠው ምላሽ እጅግ አናሳ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ላይቤሪያ ከፍተኛ የሆነ የጤና መሰረተ ልማት አውታሮች፣ የህክምና ቁሳቁስ፣ የህክምና ባለሙያና የገንዘብ እጥረት እንዳለባት የገለጹት ሚኒስቴሩ፣ ይህም አገሪቱ በፍጥነት እየተሰራጨ ያለውን የኢቦላ በሽታ ለመግታት እንዳትችል እንዳደረጋት ተናግረዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የላይቤሪያ ልኡክ በበኩሉ፣ የአገሪቱ የህክምና መስጫ ተቋማት በተገቢው ሁኔታ ያልተደራጁ መሆናቸው በቂ ህክምና ለመስጠት አለማስቻሉን ገልጾ፣ ተገቢውን ስልጠና ሳይወስዱና ጥንቃቄ ሳያደርጉ የህክምና ስራቸውን ሲያከናውኑ የነበሩ 160 የጤና ባለሙያዎች በሽታው መያዛቸውንና ግማሽ ያህሉም ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን አስታውቋል፡፡ላይቤሪያ ችግሩ ከተከሰተባቸው ሌሎች የምዕራብ አፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር፣ በሽታውን በመግታት ረገድ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ስራ አለመስራቷን ጠቆሞ፣ በቫይረሱ የተጠቁ ዜጎችን ለማከም በጤና ተቋማት የአልጋ እጥረት መኖሩንም ገልጧል፡፡የአለም የጤና ድርጅትም፣ በላይቤሪያ የተከሰተውን የኢቦላ በሽታ ችግር ለመፍታት ትኩረት ሰጥተው በመስራት ላይ ለሚገኙ አለማቀፍ ድርጅቶች፣ የጀመሩትን ጥረት በሶስትና አራት እጥፍ እንዲሳድጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
“ሊፋን ሞተርስ” ኢትዮጵያን የምሥራቅ አፍሪካ ማዕከል ሊያደርግ አቅዷል
ኢትዮጵያ ጦርነት የሌለባት ሰላማዊ አገር በመሆኗ፣ ሕዝቧም ቀማኛ፣ ዘራፊና ነጣቂ ባለመሆኑ ኢትዮጵያን የምሥራቅ አፍሪካ ማዕከል አድርገን እየሠራን ነው ሲሉ የሊፋን ሞተርስ ሥራ አስኪያጅ ሚ/ር ፍራንክ (በቻይናዊ ስማቸው ሊዩ ጂያንግ) ገለፁ፡፡ ሚ/ር ፍራንክ ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለ - ምልልስ፤ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋ ነው፣ ስርቆት፣ ዝርፊያ፣ቅሚያና ነጠቃ የለበትም፡፡ ለዚህም ሕዝቡን፣ ደንበኞቻችንንና መንግሥትን በጣም እናመሰግናለን” ብለዋል፡፡ ወደፊት ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ጐረቤት አገራት የመኪና ምርቶችን ለመላክ ኢትዮጵያን ማዕከል አድርገው ለመስራት ማቀዳቸውን በመግለጽም በዱከም ኢስተርን ዞን፣ በ400 ሚሊዮን ዶላር ዘመናዊ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ እየገነቡ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ እስካሁን 3,500 መኪኖች መሸጣቸውን የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ፤ ወደፊት እንደገበያው ሁኔታ በዓመት 5,000 መኪኖችና ከዚያም በላይ ለመገጣጠም ማቀዳቸውን ገልፀዋል፡፡
የዘንድሮው የመኪና ሽያጭ ገበያ በተለያዩ ምክንያቶች የጠበቁትን ያህል ባይሆንም ወደፊት እንደሚሻሻል የጠቆሙት ኃላፊው፤ ለገበያው አለመጨመር ዋነኛው ችግር ኢትዮጵያውያን ከአዲስ መኪና ይልቅ አሮጌ መግዛት ስለሚወዱ ነው ብለዋል፡፡ “አሮጌ መኪና የመጠቀሚያ ጊዜ ወሰን ስለሌለው አሁን በጐዳና ላይ የሚታዩት አብዛኞቹ አሮጌ መኪኖች ከ30 ዓመት በላይ ያገለገሉ ናቸው፡፡ በዚህም የነሳ የተቃጠለ ጋዝ በመልቀቅ አካባቢን ይበክላሉ፤ ከፍተኛ የድምጽ ብክለት ይፈጥራሉ፣ የመኪና አደጋ የመፍጠር ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህም በላይ የአረንጔዴ ልማት ኢኮኖሚ ፖሊሲን ስለሚፃረሩ መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ችግር እንዳለባቸው ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ “የውጭ ምንዛሪ ችግር የለብንም፤ ምክንያቱም እኛ ወኪል ሳንሆን በ160 አገሮች ቅርንጫፍ ያለው የቻይናው ሊፋን ግሩፕ አካል ነን፡፡ ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲኖር፣ ሌሎች ድርጅቶች ከ6 እስከ 8 ወር ሲጠብቁ፣ እኛ ከ15 ቀንና ቢበዛ ከሁለት ወር በላይ አንጠብቅም፡፡ ትንሽ ችግር የገጠመን በኤክሳይዝ ታክስ ነው፡፡
ለእኛ የተለየና ስሌቱም ግልጽ ስላልሆነ ትንሽ ቅሬታ ፈጥሮብናል፡፡ ነገር ግን ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት፣ ከኢንዱስትሪና ከውጭ ሚ/ር መ/ቤቶች ጋር እየተነጋገርንና እየተወያየን ስለሆነ በቅርቡ ውሳኔ እንደሚያገኝ ተስፋ አለኝ” ብለዋል፡፡ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች እየበዙ ስለሆነ ውድድሩን እንዴት ለመቋቋም እንዳሰቡ ተጠይቀው፤ “የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች መጨመር አያስጨንቀንም፡፡ ምክንያቱም፣ አንደኛ በኢትዮጵያ ገበያ ለመቆየት ወስነን ከፍተኛ ካፒታል እያፈሰስን ነው፡፡ ሁለተኛ፣ በዘመናዊ መኪና ደረጃ ሊፋን ኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ በመግባት የመጀመሪያው ብራንድ ነን፡፡ ከሌላ ኩባንያ ጋር ሆነን ኢትዮጵያ የገባነው በ2007 ቢሆንም ከ2009 ጀምሮ ለብቻችን መገጣጠም በመጀመር፣ ከሕዝቡ፣ ከደንበኞችና ከመንግሥት ጋር እንዴት መሥራት እንዳለብን የ7 ዓመት ልምድ አካብተናል፡፡ “ሌላው ደግሞ መኪና መሸጥ ብቻ ሳይሆን ከሽያጭ በኋላ የእኛን ያህል ሰርቪስ የሚሰጥ እንደሌለ ደንበኞቻችን ይመሰክራሉ፡፡ ለሰርቪስ ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ መለዋወጫ ነው፡፡ ምንም ዓይነት እጥረት እንዳያጋጥም ለመለዋወጫ 10 ሚሊዮን ብር መድበናል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ደንበኞቻችን ይመርጡናል ብለን እናምናለን” በማለት አስረድተዋል፡፡
“ዓመቱ ለኢንቨስትመንት አመቺ ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ”
- ዶ/ር አረጋ ይርዳው (የሚድሮክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ)
በኩባንያችን በኩል ባለፈው አመት የተከናወኑት ተግባራት በሙሉ አመርቂ ነበሩ፡፡ በተለይ በቴክኖሎጂ ግሩፑ አካባቢ ጥሩ ስራ ነው የተሠራው፡፡ በቀጣይ ደግሞ በተለይ የመብራት አገልግሎቱ መሻሻልና የባቡር ዝርጋታው መጠናቀቅ፣ በሀገራችን ያለውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መልካም ያደርጉታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በአጠቃላይ 2007 እና ከዚያ በኋላ ያለው ዘመን ለኢንቨስትመንቱ አመቺ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ቴክኖሎጂ ግሩፑን በተመለከተ የወርቅ ምርት የመሳሰሉትን ሥራዎች እያስፋፋን ነው፡፡ የምናስፋፋበትም ምክንያት እስከዚያ መብራቱም ይደርሳል ብለን ስለምናስብ ነው፡፡ በአጠቃላይ በአገራችን የሚታየው ነገር ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ በተረፈ ለኢትዮጵያ ህዝብ ዘመኑ የሰላም፣ የጤናና የብልጽግና እንዲሆን እመኛለሁ፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነት እና ኢትዮጵያ
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በአዲስ አበባ ሲያካሂድ የቆየውን የ10 ቀናት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔው ዛሬ ያገባድዳል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ኢሳ ሃያቱ ያለፈውን ሳምንት ከጉባኤው ጎን ለጎን የተለያዩ የጉብኝት ፕሮግራሞች ነበራቸው፡፡ ከሳምንት በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በመገናኘት ውይይት አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የእድገት እንቅስቃሴዎች እና የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ባላት ሁኔታ ያተኮር ነበር፡፡ በውይይቱ የተሳተፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ማዘጋጀት እንደምትችል ሲያስረዱ፤ ኢሳ ሃያቱ በበኩላቸው ኢትዮጵያ መስፈርቱን አሟልታ ብታዘጋጅ ደስተኛ ነኝ ብለዋል፡፡
የአህጉሪቱን ታላቅ የስፖርት መድረክ ማዘጋጀት ክብር እንደሆነ የገለፁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ቤታችሁ ነው ሲሉ ለካፍ ፕሬዝዳንት ነግረዋቸዋል፡፡ ካሜሮናዊው ኢሳ ሃያቱ ባለፈው ሃሙስ ደግሞ ከአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ፕሬዝዳንት ንኮሳዛና ዳላሚኒ ዙማ ጋር ስብሰባ የነበራቸው ሲሆን በአዲስ አበባ የሚገኘውን የካፍ እግር ኳስ አካዳሚም ጎብኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በመስተንግዶው፣ በትራንስፖርት አቅርቦት፤ በፀጥታና ደህንነት ብቁ ብትሆንም የጐደሉት ስታድዬሞች ነው፡፡ የአዲስ አበባ እና የባህር ስታድዬሞች ውድድሩን ለማስተናገድ የሚበቁ መሆናቸውን የተናገሩት የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ጁነዲን ባሻ ናቸው፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክልልሎች እየተገነቡ ያሉ ስታድዬሞች በግንባታቸው የመጨረሻ ምእራፍ ላይ እንደሚገኙ በመግለፅ የኢትዮጵያ መንግስት ውድድሩን ለማዘጋጀት የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ የ2017 31ኛው አፍሪካ ዋንጫን ማዘጋጀት ባይፈቀድልን በ2019 እና በ2021 እኤአ የሚካሄዱት 32ኛው እና 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫዎችን ለማስተናገድ እንጠይቃለን ብለዋል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በአዲስ አበባ ዓመታዊ ጉባኤውን ሲያካሂድ በሴቶች እግር ኳስ፤ በአህጉራዊ ተቋም የማህበረሰብ ድጋፍ እንቅስቃሴዎች፤ በማርኬቲንግ እና የቴሌቭዥን ስርጭት ዙርያ፤ በቻን ውድድር ዝግጅቶች፤ በፉትሳል እና የባህ ዳርቻ ላይ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ ተከታታይ ስብሰባዎችን አድርጓል፡፡ በ2019 እና በ2021 እኤአ ለሚደረጉት 32ኛው እና 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫዎች ለማዘጋጀት ፍላጎት ያላቸው እያንዳንዳቸው በ30 ደቂቃ ገለፃቸው ተፎካክረዋል፡፡ አምስቱ ተወዳዳሪ አገራት አልጄርያ፤ ካሜሮን፤ ጊኒ ፤አይቬሪኮስት እና ዛምቢያ ናቸው፡፡ የሁለቱ አፍሪካ ዋንጫዎች አዘጋጆች የኮንፌደሬሽኑ አባል አገራት በሚያካሂዱት ምርጫ ዛሬ ይገለፃሉ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በ2017 እኤአ ላይ ለሚደረገው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫን ሊቢያን በመተካት ስለሚያዘጋጀው አገር ለሚወስነው ውሳኔ ማመልከቻ የሚገባበት ቀን 10 ቀን ቀርቶታል፡፡ ውሳኔው መቼ እንደሚተላለፍ ግን የታወቀ ነገር የለም፡፡
ይህን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት 9 አገራት አመልክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ፤ ግብፅ፤ ጋና፤ ማሊ፤ ዚምባቡዌ፤ ኬንያ ለብቻዋ እና ከኡጋንዳ ሩዋንዳ እና ከታንዛኒያ ጋር በመጣመር መስተንግዶውን ጠይቀዋል፡፡ ኢትዮጵያና ተፎካካሪዎቿ የአፍሪካ ዋንጫን ከመሰረቱት አገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ በ1962 እኤአ ላይ 3ኛውን፤ በ1968 እኤአ 6ኛውን እንዲሁም በ1976 እኤአ ላይ 10ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ማዘጋጀቷ ይታወቃል፡፡ ለማስተናገድ እየጠየቀች ያለችው ለ4ኛ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫውን ለማካሄድ ነው፡፡ኢትዮጵያ በ10 የአፍሪካ ዋንጫዎች ተሳትፎ አድርጋ አንድ ጊዜ ሻምፒዮን ሁለት ጊዜ ሶስተኛ ደረጃ እንዲሁም ለአምስት ጊዜ ለግማሽ ፍፃሜ መድረስ ችላለች፡፡የምዕራብ አፍሪካዋ አገር ማሊ የተሟላ መሰረተ ልማቶች ስላሉኝ ውድደሩን ማስተናገድ ይገባኛል ትላለች፡፡ ኬንያ ደግሞ የአፍሪካ ዋንጫውን ለማዘጋጀት ሁለት አማራጮች ይዛ ነው የቀረበችው፡፡ አንደኛው አማራጭ ውድድሩን በተናጠል ማስተናገድ ነው፡፡ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ከምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ አባል አገራት ሩዋንዳ፤ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ ጋር ለጣምራ አዘጋጅነት ማመልከቷ ነው፡፡
የኬንያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ይህን በጣምራ የማዘጋጀት ፍላጎት ከሳምንታት በፊት ይፋ ሲያደርጉ ከሩዋንዳ እና ከኡጋንዳ ፈጣን ምላሽ አላገኙም ነበር፡፡ ታንዛኒያም በተናጠል የማዘጋጀት ፍላጎት ነበራት፡፡ በ2002 እኤአ ላይ የማዘጋጀት እድል ተሰጥቷት መሰረተልማቶቿን በሚያስፈልገው የጊዜ ገደብ ባለማጠናቀቋ እድሏ በጣምራ ውድደሩን ላዘጋጁት ናይጄርያ እና ጋና ተላልፎባት ነበር፡፡ በ2010 እኤአ ላይ የአፍሪካ ዋንጫውን ለማዘጋጀት ተወዳድራም በድጋሚ አልተሳካላትም፡፡ ዘንድሮ ግን ዚምባቡዌ በ2017 እኤአ ላይ የአፍሪካ ዋንጫን ማስተናገድ ይገባኛል ብላ በከፍተኛ ደረጃ ዘመቻ እያደረገች ነው ከተሳካላት በ2034 እኤአ ላይ የዓለም ዋንጫን በአፍሪካ ምድር ለሁለተኛ ጊዜ እንዲስተናገድ እንቀሳቀሳለሁ የሚል እቅዷን ይፋ አድርጋለች፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት የአፍሪካ ዋንጫን ማዘጋጀት የሚፈልጉ አገራት የማሸነፍ ከፍተኛ እድል እንዳላቸው የተወራላቸው የመስተንግዶ ፍላጎታቸውን የገለፁት ጋና እና ግብፅ ናቸው፡፡ በቂ ስታድዬሞች፤ ምቹ ትራንስፖርት እና የእግር ኳስ እድገት ያላት ጋና ቅድሚያ ግምት ተሰጥቷታል፡፡
በአንፃሩ በአፍሪካ ዋንጫ ስኬታ ግንባር ቀደም የሆነችው ግብፅ እንደጋና ሁሉንም መስፈርት በሟሟላት ለፉክክሩ ብትቀርብም በፀጥታ ችግር የመመረጥ እድል እንደማይኖራት ይገለፃል፡፡ እነማን አዘጋጆች ነበሩ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከላይ ከተዘረዘሩት አገራት አዘጋጁን የማይመርጥ ከሆነ በምትክነት ውድድሮችን የማስተናገድ እድል ያላትን ደቡብ አፍሪካ ሊመርጥ እንደሚችል ይገለፃል፡፡ባለፉት 60 ዓመታት የተካሄዱትን 29 የአፍሪካ ዋንጫውን አንዴና ከዚያም በላይ ለማዘጋጀት የቻሉት 18 አገራት ናቸው፡፡ እኩል አራት ግዜ በማዘጋጀት የመጀመርያውን ስፍራ የሚወስዱት ግብፅ እና ጋና ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው ሶስት ጊዜ ማስተናገድ የቻሉት ሁለት አገራት ደግሞ ኢትዮጵያ እና ቱኒዚያ ናቸው፡፡ እያንዳንቻቸው ሁለት ጊዜ የውድደሩ አዘጋጅ በመሆን ደግሞ 4 አገራት ናይጄርያ፤ ሞሮኮ፤ ደቡብ አፍሪካ እና ሱዳን ተሳክቶላቸዋል፡፡ 10 አገራት ደግሞ የአፍሪካ ዋንጫን አንድ ጊዜ ያዘጋጁ ሲሆን እነሱም አልጄርያ፤ አንጎላ፤ ቡርኪናፋሶ፤ ካሜሮን፤ አይቬሪኮስት፤ ኢኳቶርያል ጊኒ፤ ጋቦን፤ ማሊ፤ ሴኔጋል እና ሊቢያ ናቸው፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ እንዴት ይዘጋጃል? የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነት ብቁ የሚላቸው አገራት በሆቴል እና መስተንግዶ፤ ቢየያንስ አራት አለም አቀፍ ደረጃ የጠበቁ ስታድዬሞች ከእነ ልምምድ ስፍራቸው፤ በቂ የአየር እና የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት፤ አስተማማኝ ደህንነት እና ፀጥታን በዋና መስፈርቶቹ ይመለከታል፡፡ በ2013 እኤአ ላይ ደቡብ አፍሪካ ያዘጋጀችው 29ኛው አፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ከ31 ዓመት መራቅ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈችበት ነበር፡፡ ደቡብ አፍሪካ ይህን አፍሪካዋንጫ ያዘጋጀችው ለዓለም ዋንጫ ያቀረበቻቸው መሰረተ ልማቶችና ልምዶች በቂ በመሆናቸው ነበር፡፡ ሊቢያ በነበራት የፀጥታ ጉድለት ከውድድሩ አዘጋጅነት ተሰርዛ ደቡብ አፍሪካ መተካቷ የተሳካ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ከ38 ዓመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ እንዲሁም በታሪክ ለአራተኛ ጊዜ ማስተናገድ ብትችል ከደቡብ አፍሪካ መሰናዶ ብዙ ልትማር ያስፈልጋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ለ2010 ለዓለም ዋንጫ የነበሩ እና ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የአዘጋጅ ኮሚቴ የቦርድ አባላት በማሰባሰብ ውድድሩ ከመዘጋጀቱ ቢያንስ ለ2 ዓመት ተንቀሳቅሳለች፡፡ ይሄ ብሄራዊ የአዘጋጅ ኮሚቴ ሚኒስትሮች፤ ዲኤታዎች፤ ባለሃብቶች፤ ታዋቂ ሰዎች፤ ትልልቅ እና ባለታሪክ ስፖርተኞች እና ሌሎችንም ያካተተ እና እስከ 30 አባላት በቦርድ አባልነት የሰሩበት ነው፡፡ ከዚሁ ቦርድ ስር ደግሞ ቢያንስ አምስት የተለያዩ ኮሚቴዎች ይኖራሉ፡፡
የውድድር አካሄድን፤ ፀጥታ እና ደህንነትን፤ የፋይናንስ ጉዳዮችን፤ የማርኬቲንግ እና የንግድ ተግባራትን፤ የሰው ሃይል ምደባን፤ የሆቴል እና የትራንስፖርት አቅርቦትን እንዲሁም የሚዲያ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነትን ያንቀሳቅሳሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካ 29ኛውን አፍሪካ ዋንጫ ስታስተናግድ ከመንግስት የበጀት ድጋፍ፤ ከካፍ የገንዘብ አስተዋፅኦ፤ ከስፖንሰርሺፕ እና ከተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ገቢ ነበረው፡፡ የውድድር ማካሄጃ፤ የአስተዳደር ስራዎች፤ የጉዞ እና የሆቴል አገልግሎት እና ሌሎች ተግባራትን በማከናወን ወጭዎች ይኖሩታል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስኮንፌደሬሽን ለአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ አገር 6.2 ሚሊዮን ዶላር ያበረክታል፡፡ በሁሉም አዘጋጅ ከተሞች የውድድሩ ብሄራዊ ኮሚቴ አብሮ የሚሰራበት ምክር ቤት፤ ከአምስት በላይ ከብሄራዊ ኮሚቴው ጋር ተፈራርመው የሚሰሩ የመንግስት ተቋማት፤ ለ16 ብሄራዊ ቡድኖች በአዘጋጅ ከተሞች ሙሉ የስልጠና ሜዳ እና ከስታድዬም ከ5 እስከ ሰላሳ ደቂቃ ጉዞ ያላቸው የማረፊያ ሆቴሎች፤ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሟሉ ቢያንስ አምስት ስታድዬሞች፤ ከ200 በላይ ከብሄራዊ ኮሚቴው ጋር የሚሰሩ ሰራተኞች፤ ከ2500 በላይ ውድድሩን የሚያስተናግዱ በጎፍቃደኞች ፤የውድድሩ ኦፊሴላዊ ድረገፅ ፤ ውድድሩን የሚገልፅ መርህ ፤ የውድድሩ መለያ የሆነ ምልክት እና ሎጎ፤ በከፍተኛ ደረጃ ውድድሩን የሚያስተዋውቁ ባነሮች፤ ቢልቦርዶች እና ፖስተሮችም አንድ የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ አገር በተሰካ መንገድ ለማስተናገድ የሚያከናውናቸው ስራዎች መሆናቸውን በደቡብአፍሪካ የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሪፖርት መረዳት ይቻላል፡፡ አፍሪካ ዋንጫን በማስተናገድ ለሌሎች አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች በቂ ተመክሮ እና አቅም ይገነባል፡፡ የስፖርቱን አስተዳደር ሁለገብ አቅም ያሳድጋል፡፡ አለም አቀፍ ትኩረት ይገኝበታል፡፡ የስፖርት መሰረተ ልማቶች እንዲስፋፉ ምክንያት ይሆናል፡፡ የስፖርት እድገትን ለማቀላጠፍ ያግዛል፡፡
ከባህር ወጥታ ጤዛ ላሰች
(በባር ወጣችም አወናሰችም) - የጉራጌ ተረት
ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት በባልትናባለሙያ ነኝ የሚሉ ወይዘሮ በአንድ ከተማ ይኖሩ ነበረ ይባላል፡፡ አንድ ቀን “ዛሬ የምሠራው ገንፎ ነው፡፡ ጐረቤት ሁሉ ይጠራ” ብለው አዘዙ፡፡ ጐረቤቱ ሁሉ ተጠራና የገንፎው ግብዣ ተጧጧፈ፡፡ የዱሮ ጊዜ የገንፎ አበላል እንደዛሬ በማንኪያ አልነበረም፡፡ ሁሉም እጁን ታጥቦ ክብ ክብ ሠርቶ የሚችለውን ያህል መጉረስ ነው፡፡ ሴትዮዋ ባለሙያነታቸውን ደጋግመው እየተናገሩ እየፎከሩ፤ “ብሉ እንጂ ጐረስ ጐረስ ነው እንጂ!” እያሉ ያበረታታሉ፡፡ በየክቡ እየዞሩ፤ “እህስ እንዴት ነው ገንፎዬ” ይላሉ፡፡
እንደ ዕውነቱ ከሆነ ገንፎው በጣም ቀጥፎ፣ እጅግ ላቁጦ ጣት ላይ የሚጣበቅ ነው፡፡ አንደኛ ጐረቤት “እንዴ ድንቅ ነው፤ የእርሶ ሙያ ምን ይጠረጠራል” አለ ወደ ሁለተኛው ቀርበው “እህስ ገንፎዬ እንዴት ነው?” ሁለተኛ ጐረቤት - “አይ እጅ! እንዲህ ያለ ሙያ ከየትም አይገኝ!” ሴትዮዋ የበለጠ እየተኩራሩ ወደ ሶስተኛው ዞሩ፤ “እህስ ገንፎዬን እንዴት አገኘኸው?” ይሉታል፡፡ እሱም እንደሌሎቹ የድርሻውን ውዳሴ በመስጠት፤ “ገንፎ ከበሉ አይቀር ይሄን ዓይነቱን ነው! እንደው እንዴት አርገው ቢያገነፉት ነው እሜቴ እንዲህ ያማረልዎ?” ይላል፡፡ በመጨረሻ ወደ አንድ ውሸት የማይወድ አንደበተ - ቀና፣ ቁምነገረኛ ሰው ዘንድ መጥተው፤ “እህስ ወዳጄ ገንፎዬ እንዴት ነው?” ሰውዬው ዝም አለ፡፡ “ምነው ዝም አልክ? አልጣፈጠህም እንዴ?” ብለው አጠንክረው ጠየቁት፡፡ ሁሉ ሰው የሰውዬውን መልስ ይጠብቃል፡፡ ሰውዬው ጉሮሮውን አጠራና፤ “ኧረ እሜቴ፤ እንደው መጣፈጡ ቀርቶ እጄን በለቀቀኝ!” አላቸው፡፡
***
“ዕውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር” እጅግ ወሳኝ ነው፡፡አገር ያድናል፡፡ ህዝብን ከግርታ ያወጣል፡፡ በአንፃሩ መሸነጋገል ከቶም የአገር ጠር ነው፡፡ በይሉኝታም ይሁን በፍርሀት፣ አውቀን በድፍረትም ይሁን ሳናውቅ በስህተት፤ መሸነጋገልና መወዳደስ፤ “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” ነው፡፡ በትክክል ያልሰራነውን ሠርተሃል ተብለን አደባባይ ወጥተን መፎከር ኋላ ደብቁኝ ደብቁኝን ያመጣል፡፡ እንደ እሜቴ ገንፎ ነውና! ለረዥም ዘመን በታዋቂ - ተደናቂነት፣ አሊያም በሥልጣን መከታ፤ ሲሸነግሏቸው እየተኩራሩ የኖሩ አያሌ ናቸው፡፡ “እናቷ መራቂ ልጅቷ አሜን ባይ” እንደሚባለው መሆኑ ነው፡፡ (Yes-men of Athens እንዲሉ ፈረንጆች) ዛሬም ዕውነተኛውን ዲሞክራሲ ከሐሳዊው ዲሞክራሲ መለየት አለብን፡፡ ሀቀኛውን ፍትሕ ከአስመሳዩ ፍትሕ አጥርተን መጓዝ አለብን፡፡
መልካም አስተዳደርን ከብልሹው አስተዳደር ነጥለን ዕቅጩን መናገር አለብን፡፡ በአደባባይ ስለ ፀረ ሙስና እየተናገርን ዙሪያ መለስ የሙስና አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀን ከሆነ ጉዱ መለየት አለበት፡፡ በምንንቀሳቀስበት የሥራ ሂደት ውስጥ ሁሉ “የነካነው ሁሉ ወርቅ ይሆናል” ብለን ደርሶ ሚዳስ እንሁን ብንል፣ ውሎ አድሮ የምንጋለጥበት ሰዓት ስለሚመጣ እያንዳንዷን እርምጃችንን በጥንቃቄ ብንመዝን ይሻላል፡፡ ዕውነቱን በትክክል ተናግሮ የወደፊት መንገድን አርሞ መጓዝ እንጂ መገበዝ ወንዝ አያሻግርም፡፡ ኢኮኖሚው እጅግ ያዘቀዘቀው ህዝብ “እንኳን እናቴ ሞታ እንደውም አልቅስ አልቅስ ይለኛል” እያለ መሆኑን እንገንዘብ፡፡ አገር ያለህዝብ ድጋፍ ወደፊት አትራመድም፡፡
ህዝብን አክብሮ፣ ያለ አንዳች ሽንገላ መታደጊያውን ሰዓት እንወቅ፡፡ ህዝብ አብሮ ለመጓዝ ዝግጁነቱን ያሳየበትን ወቅት በትክክል ለይቶ መጠቀም ብልህነት ነው፡፡ ቸገረኝ ሲል እህ ብሎ ማዳመጥ ትክክለኛ የአመራር መርህ ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ብሶትንም ሆነ ፖለቲካዊ እሮሮን ሰምቶ በአመቸው መንገድ ሁሉ መፍትሔ መስጠት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው፡፡ ወቅቱን ያላወቀ ወይም ያልተገነዘበ አካሄድ “ከባህር ወጥታ ጤዛ ላሰች” እንደተባለው ይሆናል፡፡ አሁንም አሁንም እናስተውል፡፡ 2007 ዓ.ም የማስተዋያ ዓመት ይሁንልን!
በጋምቤላ ግጭት የተጠረጠሩ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው
ሸፍተው የነበሩ የዞኑ የፖሊስ ልዩ ሃይል አዛዥና የሚሊሽያ አባላት እጃቸውን ሰጡ
በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጎደሬ ወረዳ፣ በመዠንገር ዞን በተቀሰቀሰውና አሁንም ድረስ በአንዳንድ ቦታዎች በቀጠለው ግጭት እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ የክልሉ ባለስልጣናት ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው፡፡ በአዲስ አመት ዋዜማ የተቀሰቀሰውና ከ40 በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ግጭት መነሻ ከመሬት ባለቤትነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ለአዲስ አድማስ የገለፁት ምንጮች፤ “ደገኞች መሬታችንን ይልቀቁ” የሚሉ የአካባቢው ተወላጆችና አንዳንድ የክልሉ ባለስልጣናት በመንግስት ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የሰፈራ ፕሮግራም ተገን በማድረግ ነባር ይዞታ ያላቸውን ነዋሪዎች በማፈናቀላቸው ግጭቱ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው ተወላጆችና ከሌሎች አካባቢዎች በመጡ ነዋሪዎች መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየና በየጊዜው የሚያገረሽ ግጭት እንዳለ የሚታወቅ ሲሆን፣ በቅርቡ የተከሰተው ግጭት ሊቀሰቀስ እንደሚችል የፌደራል መንግስት በደረሰው መረጃ መሰረት፣ በአፈ ጉባኤ ካሳ ተክለብርሀን የተመራ ቡድን ከክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በመተባበር በአካባቢው የማረጋጋት ስራ ቢሰራም፣ በዞኑ ያሉ አንዳንድ የፖሊስና የሚሊሺያ አባላት “መሬታችንን ይልቀቁ” የሚለው ሃሳብ እንዲሰርፅ በማድረጋቸው ግጭቱ እንደተፈጠረ ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
ግጭቱ ከተፈጠረ በኋላም የዞኑን የፖሊስ ልዩ ሀይል አዛዥ ጨምሮ የፖሊስና የሚሊሽያ አባላት ሸፍተው ጫካ መግባታቸውን የተናገሩት ምንጮች፤ በአሁኑ ወቅት አዛዡና ሌሎች ጥቂት አባላት እጃቸውን ለመንግስት ሃይሎች እንደሰጡ ገልፀዋል፡፡ በአካባቢው የተከሰተው ግጭት ሁነኛ መፍትሔ ካልተበጀለት፣ በአቅራቢያ ወደሚገኙ ሌሎች አካባቢዎች ሊዛመት ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት መፈጠሩን ያመለከቱት ምንጮቹ፤ ከወራት በፊት ማንነታቸው ያልታወቀ የታጠቁ ሰዎች ዲማ ተብሎ በሚጠራው የክልሉ አካባቢ አስር ሰላማዊ ዜጎችን ገድለው መሰወራቸውን ገልፀዋል፡፡ በአካባቢው የተከሰተው ግጭት ከክልሉ የፀጥታ ሃይሎች ቁጥጥር በላይ በመሆኑ፣ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሃይል ጣልቃ ገብቶ የማረጋጋት ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡