Administrator
“ሰው ይጫኑብህ ግንድ ቢሉት፣ ግንድ ከተጫነኝ ሰው ያነሳልኛል፤ ሰው ከተጫነኝ ማን ያነሳልኛል” አለ
ከእለታት አንድ ቀን አንድ የፐርሺያ ንጉሥ ሁለት ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ ፈረደባቸው ይባላል፡፡ በመጨረሻም፤
“የሞት ፍርዱ ከመፈፀሙ በፊት የፈለጋችሁትን ተናገሩ” ሲል እድል ይሰጣቸዋል፡፡
አንደኛው፤ “ምንም የምናገረው የለኝም” አለ
ሁለተኛው፤ ንጉሡ ምን ያህል ፈረሳቸውን እንደሚወዱት ስለሚያውቅ፤
“ንጉሥ ሆይ የአንድ ዓመት ጊዜ ከሰጡኝ ፈረስዎ ወደሰማይ እየከነፈ እነዲሄድ ላስተምረው እችላለሁ” አላቸው፡፡
ንጉሡ በሰማይ ላይ የሚከንፍ ፈረስ እየጋለቡ ሲሄዱ ታያቸው፡፡ ካሁኑ ነሸጣቸውና ይቁነጠነጡ ጀመር፡፡
“ይሁን አንድ ዓመት ሰጥተንሃል፡፡ ፈረሱን አምጥተው እንዲያስረክቡህ አደርጋለሁ” አሉ፡፡
የመጀመሪያው እሥረኛ በምንም አይነት ፈረስ እንደማይበር ስለሚያውቅ ፈረስ አስተማሪውን እሥረኛ ጓደኛውን እንዲህ ሲል ጠየቀው፤
“ወዳጄ፤ ፈረስ በሰማይ እንደማይበር አሳምረህ ታውቃለህ፡፡ እንዲህ ያለ የዕብድ ሀሳብ ከየት አምጥተህ ነው ቃል የገባኸው፡፡ የመሞቻችንን ጊዜ ከማራዘም በስተቀር ምን ይፈይድልሃል?”
ፈረስ አስተማሪውም፤
“አይምሰልህ ወዳጄ፤ ነፃነቴን የማገኝባቸውን አራት ዕድሎች ራሴ መስጠቴ ነው”
አንደኛው እሥረኛም፤
“አራቱ ዕድሎች ምን ምን ናቸው?” ሲል በመጓጓት ጠየቀው፡፡
ፈረስ አስተማሪው፤ እንዲህ ሲል ዘረዘረለት፡-
1ኛ ወይ በዚህ ዓመት ውስጥ ንጉሡ ሊሞቱ ይችላሉ
2ኛ እኔም ልሞት እችላለሁ
3ኛ ወይ ደሞ ፈረሱም ሊሞት ይችላል
4ኛ ደሞስ ማን ያውቃል እኔ ፈረሱ በሰማይ እንዲበር ላስተምረው እችል ይሆናል
***
አበው ጠበብት ሦስት አይነት ጊዜ አለ ይሉናል፡፡ አንደኛው ረዥም ጊዜ የሚባለው ነው፡፡ ረዥም ጊዜ በትዕግሥት በጥንቃቄ እቅዶቻችንን ሁሉ ቀምረን የምንጓዝበት ጊዜ ነው፡፡ ሁለተኛው ተገደን የምንገባበት ጊዜ ነው፡፡ (Forced Time የሚሉት ነው ፈረንጆች፡፡) ይሄ አጭርና ጉዳያችንን ተጣድፈን፣ ተወጥረን በግዴታ ወደ ተግባር የምናስገባበት ነው፡፡ ሦስተኛው የፍፃሜ ጊዜ ነው፡፡ እቅዶችን የምንፈፅምበትና ግባችንን የምንመታበት ነው፡፡ እነዚህን ጊዜያት ወደ አገር መንዝረን ስናያቸው “ከእቅድ በላይ አመረትን”፣ “ከታሰበው ገዜ ቀደም ብለን ግባችንን መትተናል”፣ “ሥር-ነቀል ለውጥ አካሂደን ሰፊውን ህዝብ የአብዮቱ ተጠቃሚ አድርገነዋል”… ወዘተ በማለት አያሌ መፈክሮችን ስናሰግር መክረማችንን እንድንመረምር ግድ ይለናል፡፡ በእርግጥ ግን ያቀድነውን እቅድና ጊዜያችንን በአግባቡ አጣጥመን ለአንዳች ፋይዳ በቅተናልን? ተጀምረው የተቋረጡ “እንደ እገሌ ህንፃ አቁሞ ያስቀርሽ!” “እንደ እገሌ መንገድ ያሽመድምድህ!” “እንደ አገሬ መብራት ድፍን ያርገኝ ብለህ ማል እስቲ!” “እንደ ዛሬው ውሃ ድርቅ ያርገኝ በል እስቲ!” “እንደ ኔትወርካችን ይበጣጥሰኝ! በል…” እስከመባባል ድረስ በምፀት፣ በስላቅና፣ በለበጣ ህይወት ውስጥ የምንጓዘው ከቶም እቅዳችን በጊዜው ተከናውኖ ነውን? ያሰኘናል፡፡
ናፖሊዮን ቦናፓርት “የተነጠቅነውን ቦታ ለማስመለስ እንችላለን፣ ያጠፋነውን ጊዜ ግን በጭራሽ” ይለናል፡፡ የበለጠ የከፋው ደግሞ ስለባከነው ሰዓት በመገማገም የምናባክነው ሰዓት ነው፡፡ ባለፈው መንግሥት “የኮሚቴዎችን መብዛትና እንዴት እንደሚቀነሱ የሚያጠና ኮሚቴ ፍጠሩ!!” እንደተባለው ነው፡፡
“ጊዜ የሥልጣን እጅ ነው፣ የሚያውቅ ሎሌው ያረገዋል
የተጃጃለውን ግና፣ ሎሌው አርጐ ይገዛዋል” ይለናል ገጣሚው፡፡ ይህን ልብ እንበል፡፡
የሙሰኞች መናኸሪያ የሆነችው አገራችን የጊዜ ሌቦችም መደበቂያ መሆኗንም አንዘንጋ፡፡ ሙስና ከየትም የሚከሰት ተዓምት ሳይሆን የሰው ልጆች ራሳቸው ጊዜን እያዩ የሚፈፅሙት እኩይ ተግባር ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ የሚያጠፋም ሰው፣ የሚያለማም ሰው ነው፡፡ ሰው የምንለው ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ነው”
“ለመቶ አምሳ ጌታ፣
ስታጠቅ ስፈታ
ነጠላዬ…
አለቀ በላዬ”
ካለችው የበታች አካል ጀምሮ፤
“የእባብ መርዝም እንደዚያው፤ ሁሌም የሚፈለፈለው
ንጉሡ አናት ላይ ካለው፤ ከዘውዱ ወይራ ቅጠል ነው”
እስከሚለው ቄሣራዊ አገዛዝ ድረስ፤ የሙስና ፖለቲካዊ ዘይቤ መገለጫ ነው፡፡
ሰውም እንደ ሐምሌት፤
“…በምናውቀው ስንሰቃይ፣ የማናውቀውንም ፈርተን
በህሊናችንም ማቅማማት፣ ወኔያችንንም ተሰልበን… መሆን ወይም አለመሆን?...” እያለ ስለበደሉ ማውጠንጠንን ኑሮ ብሎታል፡፡ ወዳጅም ሰው፣ ባላንጣም ሰው፣ ደጋፊም ሰው፣ ተቃዋሚም ሰው፣ የበላይም ሰው፣ የበታችም ሰው ሰው ነው….
“ሰው ይጫኑብህ ግንድ?” ቢሉት፣
ግንድ ከተጫነኝ ሰው ያነሳልኛል፤
ሰው ከተጫነኝ ማን ያነሳልኛል?!” አለ፤ የሚለው የጉራጌ ተረት፤ ይሄንኑ በብርቱ ያፀኸያል!
ከዲላ ዩኒቨርሲቲ የተሰጠ ምላሽ
አዲስ አድማስ ጋዜጣ በጥቅምት 1 ቀን 2007 ዓ.ም እትሙ በነፃ አስተያየት አምድ ስር ’’በዲላ ዩኒቨርሲቲ ያዘኑት የተማሪ ወላጆች’’ በሚል ርዕስ ታትሞ የወጣውን ፅሁፍ ተመልክተናል፡፡ ከዚህ ፅሁፍ መገንዘብ እንደቻልነው ዝግጅት ክፍሉ ሊታረሙ ይገባል ብሎ በአስተያየት መልክ ማሳሰቡ በግርድፉ ሲመዘን መልካም ነው ብሎ መውሰድ ይቻል ይሆናል፡፡ ይሁን እንጅ ፅሁፉ የአንድ ወገንን አስተያየት ብቻ ይዞ መውጣቱ አግባብ ነው ብለን አናምንም፡፡ ምንጊዜም ለለውጥ ዝግጁ የሆነ ግለሰብ ወይም ተቋም በገንቢነታቸው የሚሰጡትን አስተያየቶች መውሰድ አለበት፡፡ ተቋማችንም ከዚህ የተለየ አቋም የለውም፡፡
ፀሀፊው በፅሁፉ ካሰፈራቸው አስተያየቶች ለአብነት እየጠቀስን ብንመለከት ‘’ዩኒቨርሲቲው በጣም ሞቃት ስለሆነ ተማሪዎች ’’ሰመራ’’ በማለት በሰየሙት ----’’ የሚለው ገለፃ ከመጠየቅ ስንፈት የመጣ ስህተት ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ኦዳያኣ ግቢ በተለምዶ ’’ሰመራ’’ ተብሎ ይጠራ የነበረው፣ ከከፍተኛ ሙቀቱ የተነሳ ሳይሆን ግቢው ገና ስራ እንደጀመረ (1999 ዓ.ም) የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በጊዜያዊነት (ለአንድ ወሰነ ትምህርት) በዚያ ግቢ በትውስት ተቀብሎ ስላስተማረ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በዚህ ፅሁፍ ላይ ያስተዋልነው ነገር ቢኖር ጋዜጣው (ፀሃፊው) ራሱም እንዳስቀመጠው ለፅሁፉ መነሻ የሆነው መኪና ላይ ያገኛቸው ግለሰቦች መሆናቸውን ይጠቅስና ደግሞ ወደ ታች ወረድ ብሎ በቦታው ተገኝቶ ራሱ ያየው እንደሆነ ያወራል፣ ደግሞ ከዛው ሳይወጣ ስለ ቅበላ ማውራቱን ትቶ አምና ተከሰተ ስለሚለው ነገር ያወራል፡፡ ይህ የሚያሳየን እርስ በርሳቸው የተጣረሱ እና የማጣራት ስራ ያልተሰራባቸው ስህተቶችን ነው፡፡
በፅሁፉ ውስጥ ደረቅ እንጀራ አቅራቢዎች በዱቤ ያቀርቡ እንደነበረና አስተዳደሩ ሲቀየር ገንዘባቸውን ሳይቀበሉ በክስ ሂደት ላይ እንዳሉ ተገልጿል፡፡ ዩኒቨርሲቲው መክሰስም ሆነ መከሰስ የሚችል በአዋጅ የተቋቋመ ህጋዊ ተቋም መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የተነሳው ጉዳይ ግን ተጋኖ የሚቀርብ አይደለም፡፡ ዩኒቨርሲቲውም እንጀራ በዱቤ የገዛባቸው ጊዜያት የሉም፡፡
እነዚህ በአብነት የተጠቀሱት ስህተቶች የተከሰቱት ፀሀፊው የዩኒቨርሲቲውን የአስተዳደር አካላት ሳያነጋግር በፅሁፉ ላይ እንደተጠቀሰው በግለሰቦች አስተያየት ላይ ብቻ በራሱ መላምቶች ተመርኩዞ በመፃፉ ነው፡፡ ግለሰቦቹ የተሰማቸውን አስተያየት የመስጠት መብታቸው በህገመንግስታችን የተቀመጠ ዴሞክራሲያዊ መብት በመሆኑ ለምን ሰጡ ብለን ክርክር የምንገጥምበት ጉዳይ አይኖረንም፡፡ በተመሳሳይ ፀሀፊው ዩኒቨርሲቲያችን ላይ ያዩትን (የማየት እድሉ ከነበራቸው) ጠንካራም ሆነ ደካማ ጎን የመፃፍ መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ፅሁፍ ሲጻፍ በተባራሪ ወሬ ሳይሆን በተጨባጭ ማስረጃ ተመርኩዞ፣ ግራ ቀኙን አይቶ ሁለቱንም ወገን አነጋግሮ፣ ቢቻል በአካል አረጋግጦ መሆን እንዳለበት የጋዜጠኝነት ስነምግባሩም ሆነ የፕሬስ ህጋችን የሚጠይቁት ግዴታ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ዝግጅት ክፍሉም ይህንን ሀቅና ሀገራዊ መርህ እንደሚያምንበት እሙን ይሆናል ብለን እንገምታለን፡፡
ከዚህ አንጻር ፅሁፉ የሁለት ወገንን ሀሳብ ያላካተተ መሆኑ ከመጀመሪያው ሚዛናዊነቱን ጥያቄ ውስጥ እንደሚከተው አከራካሪ አይሆንም፡፡ አጠቃላይ ጉዳዮችን ለማብራራት ያህል ግን በእኛ በኩል በያዝነው ዓመት በተቻለ መጠን የተማሪዎቻችንን አቀባበል ስነስርዓት ምቹ በሆነ መንገድ ለማከናወን የተቻለንን ጥረት አድርገናል፡፡ ይህ ማለት ግን ምንም እጥረት የለውም ለማለት አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር ፅሁፉ ላይ የተጠቀሱት በተለይ ደግሞ የተመደበው አንድ አውቶብስ ብቻ ነው የሚለውን ብንወስድ ከእውነት የራቀ አስተያየት ነው፡፡ በእኛ በኩል ያሉንን ተሽከርካሪዎች በተገቢው መንገድ አሰማርተን፣ አሽከርካሪዎች ለምሳ በሚል እንኳን አገልግሎት እንዳያቋርጡ በሽፍት እንዲጠቀሙ አድርገን አገልግሎት ሰጥተናል፡፡ እዚህ ላይ እንደ አስተያየት ሰጪው ግለሰብ ሲታይ፣ ምን አልባት በግለሰቡ አመለካከት ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከህግ አንጻርና እንደ ጋዜጠኛ ሲታይ፣ ግለሰቡ የሰጡትን አስተያየት በመያዝ ከጉዞ ቀርቶም ቢሆን በአካል ተገኝቶ ሁሉንም ጥያቄዎችም ሆነ አስተያየቶች አጣርቶ መሄድ ይጠበቅበት ነበር (ያውም ራሱ ጋዜጠኛው ’’ሰዎቹ ስለዩኒቨርሲቲው የሚናገሩት ፈፅሞ ለማመን የሚያዳግት ነው፤--- ሰዎቹ እንደሚሉት ይሆናል ብዬ ስለማልገምት---’’ እያለ!)፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም ሌሎች የተሸከርካሪ አማራጮች ማለትም የባጃጅና የጋሪ አገልግሎት ተከለከልን ለሚለው አስተያየት ከምን አንጻር እንደሆነ ሊመዘን ይገባ ነበር፡፡ ከአሁን በፊት ከነበሩን የተማሪ አቀባበል ስነስርዓቶች በርካታ ልምዶችን ወስደን ለማስተካከል ጥረት አድርገናል፡፡ በፊት ካየናቸው እጥረቶች አንዱ፣ ተማሪዎቻችን በሚገቡበት ወቅት ለከፍተኛ ወጪ መዳረጋቸው እና አልፎ አልፎም የእቃ መጥፋት ሁኔታ ያጋጥማቸው የነበር መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ አመት ተቋማችን ከከተማው ፖሊስና ትራፊክ ፅ/ቤት ጋር ቅንጅት በመፍጠር አውቶብሶች ወደ መናሃሪያ ከመሄዳቸው በፊት ወደ ዩኒቨርሲቲያችን እየገቡ የጫኗቸውን ተማሪዎች እንዲያወርዱ በመደረጉ፣ከአሁን በፊት ሲያጋጥሟቸው የነበሩ በርካታ ችግሮች ተቀርፈዋል፡፡ አልፎ አልፎ ወደ ግቢ መግባት ያልቻሉ አውቶብሶች ሲኖሩ ደግሞ ወደ ዩኒቨርሲቲያችን መገንጠያ ሲደርሱ እንዲያቆሙ እየተደረገ፣ በተቋማችን ተሸከርካሪዎች ተማሪዎቻችንን የምናስገባበት አሰራር ነበር ተግባራዊ የተደረገው፡፡ ይህ ደግሞ ተማሪዎቻችን ለወጪ እንዳይዳረጉና ከተለያዩ ተፅዕኖዎች ነፃ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ተግባር ደግሞ የሚያስመሰግን እንጅ የሚያስነቅፍ አልነበረም፡፡ በተቃራኒው በአቀበባል ስነስርዓቱ እረክተው ቢሮ ድረስ ቀርበው ያመሰገኑ ወላጆችም እንደነበሩ ልንገልፅ እንወዳለን፡፡
ሌላው በፅሁፉ የቀረበው ጉዳይ የተቋማችን የአጥርና አጠቃላይ የግንባታዎች ሁኔታ ነው፡፡ ከዚህ አንጻርም ጸሀፊው እንከን የለሽና ሚዛናዊ ይሆን ዘንድ በአካል ማየትና እውነታውን ከተቋሙ በኩል የማረጋገጥ ግዴታም ነበረበት፡፡ ከላይ እንደገለጽነው በዚህ በኩልም ምንም እንከን የለብንም የሚል አቋም የለንም፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በአጠቃላይ በሀገራችን በሚገኙ የትምህርት ተቋማት ከፍተኛ የግንባታ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ይህ መልካም እድል ከገጠማቸው ተቋማት አንዱ የእኛ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለተቋማችን እና ለአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ ገፀ በረከታችን ነው፡፡
የአጥርም ሆነ ሌሎች ግንባታዎችን በተቻለ ፍጥነት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ ተቋማችን ብቻ ሳይሆን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም የዞን እና የከተማ አስተዳደሩን ጨምሮ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው በጋራ እየተረባረብን እንገኛለን፡፡
ፀሀፊው ያልተገነዘበው አንዱ ነገር፣ ዩኒቨርሲቲያችን 13 ወር ሙሉ የመማር ማስተማር ስራ የሚያከናውንና በ2006 ዓ.ም የክረምት መርሃ ግብርም በርካታ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ የቆየ ሲሆን የክረምት ተማሪዎችን ከሸኘ በኋላም መደበኛ ተማሪዎችን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት አድርጓል፡፡ ይህም በመሆኑ ምንም አይነት ተዘግቶ የከረመና ፀሀፊው በከፍተኛ ግነት ነገሩኝ ያላቸው ግለሰቦች እንደገለፁት፣ በአቧራ ተሞልቶ ተባይ አስከሚያፈራ የደረሰ መኝታ ቤትና የተበለሻሹ ግብዓቶች የመኖራቸው ጉዳይም ትክክል አለመሆኑን ታዝበናል፡፡
ይልቁንም ለእያንዳንዱ የተማሪ መኝታ ክፍል ህንጻዎች የጽዳት ባለሙያዎችና ተቆጣጣሪዎች ያሉበት፣ ተማሪዎቹም ከመግባታቸው በፊት አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት በማከናወን ተማሪዎቻችንን የተቀበልን መሆናችን ልብ እንዲባል እንፈልጋለን፡፡
ተማሪዎች እንደማንኛውም የተሻለ ምቾት ሊመርጥ እንደሚችል ግለሰብ ሁሉ የታሸገ ወይም የቀዘቀዘ ውሃ ገዝተው ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ይህ እውነታ በከፍተኛ ሁኔታ ተኳሽቶ፣ ምንም አይነት ውሃ በግቢ ውስጥ እንደሌለና ተማሪዎችም እግራቸውን እንኳን የሚታጠቡበት አጥተው እንደተቸገሩ አድርጎ ማቅረቡ፣ ከአንድ ጋዜጠኛ የማይጠበቅ ስነምግባር ነው፡፡ በነገራችን ላይ በቅርቡ ለሁሉም ህንጻዎች የሚዳረስ፣ ከዚህ በፊት ከሚጠቀሙበት የተሻለ መጠንና ጥራት ያለው ውሃ ተገኝቶ፣ የሙከራ ስርጭት ተደርጎ፣ በየህንጻው ላይ ያሉ የመፀዳጃ ቤቶች ክፍት እንደሚሆኑ እየገለፅን፣ ጸሀፊው ሰባት መቶ ሜትር ሄደው ጫካ ይፀዳዳሉ ብሎ ላቀረበው ሃሳብ፣ ከህንፃዎች ውጪ ጊዜያዊ መፀዳጃ ቤቶችን በመገልገል ላይ ያሉ በመሆኑ የፀሀፊው ሃሳብ እኛን አይገልፀንም፡፡ በአካል ተገኝቶ ለማየት እንደሚቻለው ሁሉ በኦዳያኣ ግቢ (በፀሐፊው አገላለፅ ’’ሰመራ’’ ግቢ) ውስጥ ተማሪዎችም እንደሚመሰክሩት፣ጭቃ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡ መኝታ ቤቶችን ከመንገድ፣ መማሪያ ክፍሎችን ከመንገድና እርስ በርሳቸው የሚያገናኙ የድንጋይ ንጣፍ መንገዶች (ኮብል ስቶን መንገድ) ተሰርተዋል፡፡ ከከተማው አስተዳደር ጋር ተያይዞም ፅሁፉ ላይ የተቀመጠው ጉዳይም ሚዛናዊነቱን የጠበቀ አይደለም፡፡ ከተማ አስተዳደሩም ሆነ የከተማው ማህበረሰብ ዩኒቨርሲቲውን አይፈልገውም የሚለው ጫፍ የወጣ ዘገባ ማስቀመጥም ከግዴለሽነት የሚመነጭ ካልሆነ በስተቀር አንድም የከተማው ማህበረሰብ ተጠይቆ አልፈልግም ባላለበት ሁኔታ መንገደኞችን አነጋግሮ ጥርጣሬ አለኝ ብሎ ማስቀመጥ፣ አጠቃላይ ማህበረሰቡን ካለመረዳት የሚመነጭ በመሆኑ ከህግም አንጻር ሲታይ ተገቢ ያልሆነና ሊያስጠይቅ የሚችል ጉዳይ እንደሚሆን ይሰማናል፡፡
የአካባቢው መስተዳድርና ማህበረሰብም ከዩኒቨርሲቲው ተጠቃሚ እንደሆኑ አጥብቀው የሚያምኑና የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ በአፅንኦት ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ነገር ግን ከአፍራሽነት የሚመነጭ፣ ተቋሙንና ማህበረሰቡን ለማቃረን የማለም እቅድ ካልሆነ በስተቀር ይህንን በአካል ቀርቦ ተቋሙ ለማህበረሰቡ እየሰጠ ያለውን ድጋፍና ተተግብረውም የመጡትን ለውጦች አይቶ በመገምገም ሚዛናዊ ፅሁፍ መፃፍ ይቻል እንደነበረ ግልፅ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ዩኒቨርሲያችን የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ እንደሚያደርጉት በግንባታም ይሁን በአጠቃላይ የትምህርት ስራ እንቅስቃሴ ራዕዩን ለማሳካት በተሻለ እንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ እንዲታወቅና በዚህ የልማት እንቅስቃሴ ወቅት የሚከሰቱ መጠነኛ ችግሮችን እያጎላን ልማታችንን ከማደናቀፍ በዘለለ ጠንካራ ጎኑንም በማየትና መጠነኛ ችግሮችን በጋራና በንቃት እየቀረፍን መጓዝ እንዳለብን የጋራ ስሜት መያዝ የተቋማችን ብቻ ሳይሆን የሚዲያዎች ሚናም እንደሆነ ስለምናምን፣በእናንተ በኩል ይህ ሚዛናዊነቱን ያልጠበቀ ፅሁፍ ቢቻል ሁሉንም ጉዳዮች ከሚመለከታቸው የተቋማችን ኃላፊዎች ጋር በመገናኘትና ሁሉንም ተግባር በአካል በመጎብኘት እውነቱን እንድታረጋግጡ እንጋብዛለን፡፡ከአዘጋጁ፡ ዩኒቨርሲቲው ከላይ እንደገለጸው የተማሪ ቤተሰቦችን ቅሬታ ብቻ ሳይሆን የዩኒቨርሲቲውን አካል ምላሽ ማካተት ተገቢ እንደነበር እናምናለን፡፡ ሆኖም በአካል ተገኝተን ሁኔታውን ለማየት በቂ ጊዜ ስላልነበረን ጋዜጣውን ወደ ማተሚያ ቤት እስከላክንበት የመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ በሁለት የዩኒቨርሲቲው ስልኮች በመደወል ምላሽ የሚሰጠን አካል ለማግኘት የጣርን ቢሆንም ስልኩን የሚያነሳ ባለመኖሩ ሙከራችን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ እንዲያም ሆኖ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ሳምንት ከተማሪ ቤተሰቦች ለተሰነዘረው ቅሬታ ከላይ የቀረበውን ምላሽ በጽሁፍ ስለላከልን ከልብ እናመሰግናለን፡፡
መንግሥት የአሸባሪዎች የጥቃት ስጋት እንደሌለ አስታወቀ
“ኢቦላ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቷል የሚባለው ሃሰት ነው”
የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ክፍሉ ጠንካራና ህብረተሰቡን ያማከለ በመሆኑ ከአልሸባብም ሆነ በሌሎች ሀገሮች ከሚደገፉ አሸባሪዎች ሊደርስ የሚችል ጥቃት እንደማይኖር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አረጋገጠ፡፡
ሰሞኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲው አማካኝነት በቦሌ አካባቢ አልሸባብ ጥቃት ሊፈፅም እንደሚችል መረጃው ደርሶኛል በማለት ዜጐቹ በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በድረገፁ መልእክት ማስተላለፉ የሚታወስ ሲሆን በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ጉዳይ ዳይሬክተር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ በበኩላቸው፤ “የሀገሪቱ ፀጥታ የተጠናከረ ነው፤ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ስጋት አይግባው” ብለዋል፡፡
የሀገሪቱን ደህንነት የምንጠብቀው በተለያዩ ጊዜያት በሚሰጡ የጥቃት ማስጠንቀቂያዎች አይደለም ያሉት አምባሳደሩ፤ የፀጥታ ሃይሉ የህብረተሰቡን ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነቱን ለመወጣት እለት ከእለት በጥንካሬ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በትናንትናው እለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ለዲፕሎማቶችና ለአለማቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች በሰጠው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የኢቦላ ታማሚ እንደሌለ አረጋግጧል፡፡
ሰሞኑን በማህበራዊ ድረ-ገፆች ኢትዮጵያ ውስጥ በጥቁር አንበሳና በቅዱስ ያሬድ ሆስፒታል የኢቦላ ታካሚዎች አሉ በሚል የተሰራጩ መልእክቶች ከእውነት የራቁ መሆናቸውን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡
ከተለያዩ ወገኖች የሚቀርቡ ጥቆማዎች በስልክ መስመር 8335 ላይ እያስተናገደ መሆኑን የጠቆመው መስሪያ ቤቱ፤ የኢቦላ ታማሚ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢገኝ እንደማይደበቅና ሀገሪቱ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደሆነ ገልጿል፡፡
በሽታው ሀገር ውስጥ ቢገባ እንኳን በብቃት ምላሽ ለመስጠት ጠንካራ ዝግጅት መደረጉንም ጠቁሟል፡፡
ፕ/ር መስፍን በአውስትራሊያ የእድሜ ዘመን ስኬት ሽልማት ይቀበላሉ
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ተቀማጭነቱ በአውስትራሊያ የሆነው ‘ዲሞክራሲ ፎር ኢትዮጵያ ሰፖርት ግሩፕ’ የተሰኘ ቡድን ያዘጋጀውን የእድሜ ዘመን ስኬት ሽልማት ለመቀበል ሰሞኑን ወደ አውስትራሊያ መሄዳቸውን ምንጮቻችን ገለጹ፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በአገሪቱ ሁሉን አቀፍ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ለማስቻል ለረጅም አመታት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ያለው ቡድኑ፣ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት በማሰብ ሽልማቱን እንዳበረከተላቸው አስታውቋል፡፡
ፕሮፌሰሩ ሽልማቱን ከመቀበላቸው በተጨማሪ፣ ከነገ ጀምሮ በሚልቦርን፣ በሲድኒ፣ በብሪስባኔና በሌሎች የአውስትራሊያ ከተሞች ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በአገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
በሰብዓዊ መብቶች፣ በታሪክ፣ በጂኦግራፊና በልማት ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ የተለያዩ መጽሃፍትንና የጥናት ወረቀቶችን የጻፉትና ለረጅም አመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በተለያዩ የመንግስት ድርጅቶች ያገለገሉ ፕ/ር መስፍን፣ ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ መስራቾች አንዱ ሲሆኑ፣ ለተለያዩ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማካሪ ሆነው ሲሰሩ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
የጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤ የቀብር ሥነ-ስርዓት ዛሬ ይፈፀማል ተብሎ ይጠበቃል
በኬንያ በስደት ላይ ሳለ በጥቂት ቀናት ህመም ህይወቱ ያለፈው የጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤ የቀብር ስነ ስርዓት በዛሬው እለት በትውልድ ሀገሩ ይርጋጨፌ ይፈፀማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተለያዩ የግል የህትመት ውጤቶች ላይ ለረጅም አመታት በጋዜጠኝነት ሙያ ሲሰራ የቆየውና “ማራኪ” የተሰኘ መፅሄት አሳታሚ የነበረው ጋዜጠኛ ሚሊዮን፤ ባደረበት ድንገተኛ ህመም ባለፈው ሰኞ ህይወቱ ያለፈ ሲሆን ትላንትና ምሽት አስከሬኑ አዲስ አበባ እንደሚገባና ይርጋጨፌ ወደሚገኙት ቤተሰቦቹ ተልኮ በዛሬው እለት የቀብር ሥነ ስርአቱ ይፈፀማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ታውቋል፡፡
ጋዜጠኛው ናይሮቢ ኬንያታ ሆስፒታል ለ15 ቀናት በህክምና ሲረዳ መቆየቱን የጠቆሙት ምንጮች፤ ሃኪሞች ታይፎይድና ከሆድ ውስጥ ደም መፍሰስ ጋር የተያያዘ ህመም አጋጥሞት እንደነበር መግለፃቸውን አመልክተዋል፡፡
የጋዜጠኛው ህይወት ካለፈ በኋላ በገንዘብ እጥረት ለ4 ቀናት በኬንያታ ሆስፒታል የአስክሬን ማቆያ ውስጥ መቀመጡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጋዜጠኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ አንተነህ አብርሃም፤ ሟች ሚሊዮን የማህበራቸው ግንባር ቀደም አባል ስለነበር በኃላፊነት ስሜት አስከሬኑን ወደ ሀገር ቤት ለማምጣት በተደረገው ጥረት ውስጥ መሳተፋቸውን፤ አስከሬኑን እንድታመጣም የሟችን እህት ከሌሎች ተባባሪዎች ጋር ሆነው ገንዘብ በማዋጣት ወደ ኬንያ መላካቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
አስከሬኑን ለማስመጣት በተደረገው ጥረት የገንዘብ እጥረት አጋጥሞ እንደነበር የጠቆሙት አቶ አንተነህ፤ ለሆስፒታል መከፈል የነበረበትን 1600 ዶላር የምስራቅ አፍሪካ የጋዜጠኞች ህብረት እና አርቲክል 19 ተባብረው መክፈላቸውንና አስፈላጊውን የመጓጓዣ ሰነድ በማስፈፀምም ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል፡፡
ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤ ለረጅም አመታት ከቀድሞ “ኢትዮጵ” ጋዜጣ ጀምሮ በተለያዩ የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች ላይ ሲሰራ የቆየ ሲሆን ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ አገር ጥሎ እስከወጣበት ነሐሴ መጨረሻ ድረስ ”ማራኪ” የተሰኘች በማህበራዊና በኪነጥበባዊ ጉዳዮች ላይ የምታተኩር መፅሄት ያሳትም እንደነበር ይታወቃል፡፡
ጋዜጠኛው በ2005 ዓ.ም “ወሲባዊ ውስልትና (ዘ አዲስ አበባ)” የተሰኘ መፅሃፍ ፅፎ ለአንባቢያን አድርሷል፡፡
የ30 አመቱ ጋዜጠኛ ሚሊዮን፤ ከሀገር ከመሰደዱ በፊት ማተሚያ ቤቶች “ማራኪ” መፅሄትን አናትምም እንዳሉትና ገቢ ያገኝበት የነበረ ስራው በመቋረጡ በችግር ላይ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ገልፆ ነበር፡፡ ጋዜጠኛ ሚሊዮን የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበር፡፡
“በግፊት ወደ ስልጣን እንደመጣሁት በግፊት መውረድ አልፈልግም” - ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈውራ
የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር በመሆን ላለፉት 10 ወራት ያገለገሉት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው፤ ከተወሰኑ የዳያስፖራ የፓርቲው ድጋፊ ሰጪ አመራሮችና የካቢኔ አባላት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ከኃላፊነታቸው እንደለቀቁ ተናገሩ፡፡
ለዳያስፖራዎች ክብር እንዳላቸው የገለፁት ኢ/ር ግዛቸው፤ የተወሰኑ የዳያስፖራ የፓርቲው ድጋፍ ሰጪ አባላት አገር ውስጥ ባለው አመራር ጣልቃ በመግባት ማዘዝ እንደሚፈልጉ ጠቁመው ለፓርቲው የገንዘብ ድጋፍ ስለሚያደርጉ ብቻ ፓርቲውን የእነሱ ወኪል ለማድረግ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡
“መውረድ አለብህ ብለው ጥያቄ ማቅረባቸውን አልቃወምም፤ ነገር ግን ተቃውሞዋቸውን በተቋማዊ መንገድ ማቅረብ አለባቸው” የሚሉት ኢንጂነር ግዛቸው፤ “እዚህ ቦታ ሰላማዊ ሰልፍ አድርግ፣ እዚያ ቦታ ህዝባዊ ስብሰባ ጥራ እያሉ የሚያዙትን አልቀበልም” ብለዋል፡፡ “የሚሰጡትን ገንዘብ እንደ በጎ አድራጎት ማየት የለባቸውም፤ እንደ ግዴታ መውሰድ አለባቸው፤ እኔ ለእስርም ሆነ ለሞት ቅርብ እንደሆንኩት ሁሉ እነሱም ገንዘብ የማዋጣት ግዴታ አለባቸው እንጂ በገንዘብ እጅ ለመጠምዘዝ መሞከር የለባቸውም” ሲሉ ተናግረዋል - ኢንጂነሩ፡፡
“ግንኙነታቸውም ግለሰባዊ በመሆኑ ይህንን እቃወማለሁ” የሚሉት ኢንጂነሩ፤ እኔን ከስልጣን የማውረድ መብት ያለው ጠቅላላ ጉባኤው ቢሆንም አተካሮ ውስጥ ገብቼ ፓርቲውን ላለመጉዳት ስል በገዛ ፈቃዴ መልቀቁን መርጫለሁ ብለዋል፡፡ አክለውም “አንዷለም አራጌ ታስሮ አንተ እቤት ቁጭ የማለት ሞራል አለህ ወይ? በሚል ግፊት ወደ ስልጣን እንደመጣሁ በግፊት መውረድ አልፈልግም” ብለዋል፡፡
ከተወሰኑ የካቢኔ አባላት ጋር ያለመግባባት የተፈጠረው ከመኢአድ ጋር ለመዋሃድ በተደረገው ሙከራ መሆኑንም ኢ/ር ግዛቸው ገልፀዋል፡፡ ውህደቱ መኢአድ ውስጥ ባለ ችግር ምክንያት ሊሳካ አልቻለም ብለዋል፡፡
ለውጥ በህዝባዊ አመፅም ሆነ በትጥቅ ትግል ይመጣል ብለው እንደማያምኑ የገለፁት ኢንጅነሩ፤ በቀጣዩ ምርጫ ለመወዳደርም ሆነ ላለመወዳደር ገና እንዳልወሰኑ ተናግረዋል፡፡
‹‹...ጥሩ ቤተሰብ መፍጠር ...ጥሩ አለምን መፍጠር...››
ህጻናትን በፍቅርና በሰላም ማሳደግ የሚቻለው ይበልጡኑ ወላጆች ኃላፊነት የሚሰማቸው እና ጥሩ ምሳሌ ሲሆኑ ነው፡፡ ቤተሰብህን በተሸለ ደረጃ መምራት ማለት አለምን በተሸለ ደረጃ ለመምራት ዝግጁ መሆን ማለት ነው የሚለው የጠበብት ንግግር ተግባራዊ እንዲሆን ሁሉም ልብ ሊለው የሚገባ ነገር ነው፡፡ ወላጅ ልጅን በማስተናገዱ ረገድ እራሱን ሊጠይቅ ከሚገባቸወ ነገሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
* እኔ ወላጅ ከሆንኩኝ ልጄን በትክክል ለመርዳት የሚያስችል በቂ ጊዜ ሊኖረኝ ይገባል? ወይንስ በተጣበበ ጊዜ የማደርገው ነገር ትክክል ነው?
* ለመሆኑ ማድረግ የሚገባኝን እያደረግሁኝ ነውን?
* የትኛው ትምህርት ቤት ባስተምረው ጥሩ ይሆናል?
* ልጄን በሚያዝናና መንገድ እየረዳሁ ነውን? ወይንስ?
* በማደርገው ነገር ውስጤን በትክክል አምነዋለሁኝ? ወይንስ እየተጠራጠርኩ ነው?
የሚሉትንና ሌሎችንም ጥያቄዎች ለራስ በማቅረብ ልጆችን በተገቢው መንገድ ማሳደግ በሁሉም ወላጅ እና ቤተሰብ እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ላይ የሚጠበቅ ግዴታ ነው፡፡
የኢፌዲሪ ህገመንግስት አንቀፅ 35 ማንኛውም አንድ ህፃን ሊኖረው የሚገቡ መብቶች ብሎ የሚከተሉትን በዝርዝር አስቀምጧል፡-
ሀ) በህይወት የመኖር፣
ለ) ስምና ዜግነት የማግኘት ፣
ሐ) ወላጆቹን ወይም በህግ የማሳደግ መብት ያላቸውን ሰዎች የማወቅና የእነሱንም እንክብካቤ የማግኘት፣
መ) ጉልበቱን ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅ፣በትምህርቱ፣በጤናውና በደህንነቱ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ስራዎችን እንዲሰራ ያለመገደድ ወይም ከመስራት መጠበቅ፣
ሠ.. በትምህርት ቤቶች ወይም በህፃናት ማሳደጊያ ተቋሞች ውስጥ በአካሉ ከሚፈፀም ወይም ከጭካኔና ኢሰብአዊ ከሆነ ቅጣት ነፃ የመሆን፣ከላይ ከተጠቀሱት ድንጋጌዎች መካከል ተራቁጥር (መ) እንዲሁም (ሠ) ህፃናትን ከተለያዩ አካላዊ ብሎም ስነልቦናዊ ጥቃቶች ለመከላከል ታስቦ የወጣ ነው፤እንደ ኢፌዲሪ ሴቶች ህፃናት እና ወጣቶች ሚንስ..ር አገልለፅ ለጥቃት ተጋላጭ ሆኑ የሚባሉት ህፃናት...
‹‹አስፈላጊው እንክብካቤ የማይደረግላቸው እንዲሁም ደህንነታቸው በተለያየ ምክንያት አደጋ ላይ የወደቀና ህገመንግስቱ የደነገገላቸውን መብት መጠቀም ያልቻሉ ህፃናት ናቸው›› children advocacy center የሚለው ሕጻናትን ተንከባክቦ በማሳደግ ረገድ ለዚህ እትም መረጃ ያደረግነው ጽሁፍ ሲጀምር ተከታዮቹን ነጥቦች ይዘረዝራል፡፡
* ከትዳር አጋራችን ጋር የሚኖረን ጥሩ ያልሆነ ግንኙነት፣
* የኢኮኖሚ ችግር ፣
* ከእፅ እና ከአልኮል ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲሁም፣
* በልጅነት ተከስቶ ያለፈ ጥቃት፣
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ለሚያደርሱት ጥቃት እንደ መንስኤ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የቱንም ያህል ልጃቸውን የሚወዱ ወላጆች እን..ን ቢሆኑ እንደችግር ለተጠቀሱት ነጥቦች ትእግስትን ወይንም መቻልን ያጣሉ፡፡ children advocacy center የህፃናት ጥቃትን ለመከለላከል የሚያስችሉ መንገዶች ብሎ ካስቀመጣቸው ሀያ ነጥቦች ውስጥ የተወሰኑትን ሀሳቦች እናስነብባችሁ፡
1/ጥሩ ምሳሌ ወይም አርአያ መሆን፣ ወላጆች ለሁሉም የቤተሰብ አባላት ተገቢውን ቦታ እና ክብር ሊሰጡ ይገባል፤ ልጆችን ትህትና በተሞላበት መንገድ ማነጋገር ተገቢ ነው፡ አግባብ ያልሆነ ምግባር ሲያሳዩም እነሱን ሳይሆን ድርጊታቸውን እንዳልወደዱት ከመንገር ባለፈ ፈፅሞ ልጆችን ለመምታት እንዳይሞክሩ ይመከራል፡፡፡
መምታት ወይም ሌሎች አካላዊ እርምጃዎችን መውሰድ ልጆች ሀይለኝነትን እንዲማሩ ያደርጋል፡፡ የተሳሳቱ መስሎ ተሰማዎት ይቅርታ ይጠይቁ ይህን በማድግዎ ለልጆ መልካም ባህሪን ያወርሳሉ፡፡
2/ልጅዎን ጓደኛ ማድረግ፣ልብ ይበሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ነገሮችን በቁጣ እና በንግግር ብቻ ማለፍ አለመግባባትን ለማቅለል ይረዳል፡፡ ልጆች የወላጆቻቸውን ደስታ እና ጥሩ ፊት ሲያዩ መልካም ምግባር ይኖራቸዋል ስለዚህ ከልጆችዎ ጋር መዝናናትን አሊያም የእግር ጉዞ ማድረግን ያዘውትሩ፡፡
ይህን መሰል ድርጊቶች ድካምን ለመቀነስ ብሎም ከልጆችዎ ጋር የሚኖርዎትን ግንኙነት ለማጠንከር አይነተኛ መንገድ ነው፡፡
3/ልጆችን ማመስገን ወይም ማበረታታት፣ መጥፎ ቃላት ልጆች ዋጋቢስ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡ ጉዳቱም የእድሜ ልክ ነው፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ቀና ይሁኑ፡፡ ምን ያህል በእሱ/በእሷ ደሰተኛ እንደሆኑ እና በእርስዎ ዘንድ ያላቸውን ቦታ ለልጆቾ አዘውትረው ይንገሯቸው፡፡
4/እርምጃ መውሰድ ወይም ሌሎች እስኪጀምሩ አለመጠበቅ፣በስራ ቦታ እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች የህፃናት ጥቃትን በሚመለከት እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርብዎታል፡፡ ስለ ጉዳዩ ይበልጥ ባወቅን ቁጥር ድርጊቱን ለማቆም በይበልጥ እንተጋለን፡፡
5/በጎ ፈቃደኛ መሆን ፣ ጊዜዎን በህፃናት ጥበቃ እንዲሁም ለልጆች ድጋፍ የሚሰጡ ፕሮግራሞችን ለመደገፍ ያውሉት፡፡
6/ በህፃናት ማቆያ ማእከል ውስጥ ማገልገል፣ ጊዜዎን የተጎዱ እና ጥቃት የደረሰባቸው ህፃናትን ለሚንከባከብ ማእከል የበጎፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ያውሉት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ህፃናትን ከሚረዱ ማእከላት ጋር ህብረት በመፍጠር አብረው ይስሩ ፡፡
7/ ስለህፃናት ጥቃት እንዲሁም መከላከያ መንገዶቹ በቂ ግንዛቤ መያዝ፣
8/ ወላጆቻቸውን ላጡ ህፃናት ወላጅ መሆን ፣ ይህን ማድረግ ቀላል አይደለም ነገርግን አንድ ህፃን ደህንነቱ ሲጠበቅ የሚሰማውን ሲያዩ እርካታዎ ከፍያለ ነው፡፡
9/ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ እና በህፃናት ደህንነት ላይ ከሚሰሩ አካላት ጋር መስራት፣
10/ የትኞቹ ህፃናት በይበልጥ ለጥቃት ተጋላጭ እንደሆኑ መረዳት፣ ምንም እን..ን የህፃናት ጥቃት ዘር እና ባህል ሳይለይ በሁሉም ህብረተሰብ ክፍል የሚከሰት ቢሆንም አብዛኛዎቹ አካላዊ ጥቃቶች የሚከሰቱት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ባለቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ነው፡፡
የአእምሮ ህመም እንዲሁም የአካል ጉዳት ያለባቸው ታዳጊ ህፃናት ደግሞ ለድርጊቱ በይበልጥ ተጋላጭ ናቸው፡፡
11/ የጥቃቱን መገለጫዎች ለይቶ ማወቅ፣
በህፃናት ላይ የሚደርሱ አካላዊ እንዲሁም ፆታዊ ጥቃት መገለጫዎችን ለይቶ ማወቅ ድርጊቱን ለማወቅ በይበልጥ ይረዳል፡፡
12/ ለልጆች አስፈላጊ የሆኑ ስጦታዎችን አስቀድሞ ማዘጋጀት፣ ይህን ማድረግ ለልጆች ያለንን ፍቅርና እንክብካቤ ከመግለፅ አልፎ እነርሱን ለማሳደግ ምን ያህ እግጁ እንደሆንን ያሳያል፡፡
“አፈር ብላ” የግጥም መድበል ይመረቃል
በዳንኤል ቢሰጥ እቴቴ የተፃፉ ግጥሞች የተካተቱበት “አፈር ብላ” የተሰኘ የግጥም መድበል፤ ሰሞኑን ገበያ ላይ ውሏል፡፡ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሽሙጦችና ፍልስፍና ነክ ግጥሞች እንዲሁም አገራዊ ፉከራና ሽለላ ቀመስ ግጥሞች የተካተቱበት መፅሃፉ፤ ፈገግና ዘና የሚያደርጉ ርእሰ ጉዳዮችንም ይዳስሳል፡፡
በ100 ገፆች ተቀንብቦ የተዘጋጀው “አፈር ብላ” የግጥም መድበል፤ በ25 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ መፅሃፉ የፊታችን ሰኞ ከቀኑ 10፡30 ጀምሮ በሩሲያ የሳይንስና የባህል ማዕከል (ፑሽኪን አዳራሽ) ይመረቃል ተብሏል፡፡
“ዳነ” የጉራጊኛ ቪሲዲ ለገበያ ቀረበ
በጉራጊኛ ዘፈኑና በማራኪ ውዝዋዜው የሚታወቀው የድምፃዊ መላኩ ቢረዳ “ዳነ” የተሰኘ አዲስ የጉራጊኛ ቪሲዲ ሰሞኑን ለገበያ ቀርቧል፡፡ የ14 ዘፈኖችን ቪዲዮ ያካተተው ይኸው ስራ፤ አብዛኞቹ ግጥሞችና ዜማዎች በራሱ በድምፃዊው የተሰሩ ሲሆን ቅንብሩ በዘሪሁን ሳህለማሪያም፣ ያሬድ አስናቀ፣ አሸናፊ ከበደና በሰለሞን ኢብራሂም ነው የተሰራው፡፡
ድምፃዊው በቪሲዲው ውስጥ “ትግርኛ ምት በጉራጊኛ”፣ “አውዳመት አማርኛ በጉራጊኛ ስልት”፣ “ጐንደር በጉራጊኛ”፣ “ሱዳንኛ በጉራጊኛ” እና “ትዝታ በጉራጊኛ” የሚሉትን በማካተት ለየት ባለ ሁኔታ የቀረበ ሲሆን ከዚህ ቀደም “ትዊስት በጉራጊኛ” የተሰኘ ቪሲዲ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡ አዲሱ ቪሲዲ በዚያዳ ሪከርድስ ታትሞ እየተከፋፈለ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ድምፃዊ መላኩ ቢረዳ በአሁኑ ሰዓት በዮድ አቢሲኒያ የባህል ምግብ ቤት አዳራሽ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ሚስቴን ቀሙኝ” ፊልም ነገ ይመረቃል
በደራሲና አዘጋጅ ሙሉዓለም ጌታቸው ተሰናድቶ፣ በበርሄ ገ/መድህን ፕሮዱዩስ የተደረገው “ሚስቴን ቀሙኝ” የተሰኘ ኮሜዲ የፍቅር ፊልም፤ ነገ በመላ አገሪቱ በሚገኙ የግል ሲኒማ ቤቶች እንደሚመረቅ ፕሮዱዩሰሩ አቶ በርሄ ገ/መድህን ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
በሜርሲ መልቲ ሚዲያ ፕሮዳክሽን ለእይታ የሚቀርበውን ይሄን ፊልም ሰርቶ ለማጠናቀቅ አንድ አመት እንደፈጀ የገለፁት ፕሮዱዩሰሩ፤ ከ600 ሺህ ብር በላይ እንደወጣበትና የ1ሰዓት ከ42 ደቂቃ ርዝማኔ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
በፊልሙ ላይ ዮሐንስ ተፈራ (ዳረማኛ)፣ ቃልኪዳን ጥበቡ፣ ሰገን ይፍጠር፣ ካሳሁን ፍሰሃ (ማንዴላ)፣ አስራት ታደሰ፣ ፋንቱ ማንዶዬ፣ እንዳልካቸው ሰበታና ሌሎችም ወጣትና አንጋፋ ተዋንያን ተሳትፈውበታል ተብሏል፡፡