Administrator
ህፃናት ለእግዚአብሔር የፃፏቸው ደብዳቤዎች
ውድ እግዚአብሔር፡-
ትልቋ እማማ ወደ ቤቷ ስትሄድ ከእኛ ጋር የምትሆን ሌላ እማማ ልትልክልኝ ትችላለህ?
ሶፊ - የ4 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
አባቢ ዶክተር እንድሆን ይፈልጋል፡፡ እኔ ደሞ አልፈልግም፡፡ አንተ ግን ሳይንቲስት እንድሆን ትፈቅድልኝ የለ?
ብሩክ - የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ዳዲን ካየሁት ብዙ ጊዜ ሆኖኛል፡፡ ማሚን ስጠይቃት የሄደበትን አታውቀውም፡፡ አንተ ጋ መጥቷል እንዴ?
ጆሲ - የ5 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
በዚህ ዓመት ከክፍላችን አንደኛ የሚወጣው ማነው? ለእኔ ብቻ በጆሮዬ ንገረኝ፡፡
ሄለን - የ5 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ታላቅ እህቴ፤ ማሚ ያስቀመጠችውን ቸኮላት ሰርቃ ስትበላ አየኋት፡፡ ለማሚ ልንገርባት ወይስ አንተ ትቆጣታለህ?
ዴቭ - የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
አንተ ጋ ትምህርት ቤት የለም አይደል! አለ እንዴ?
ሳሚ - የ7 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ከክፍላችን ልጆች ሁሉ ቀድሜ መሮጥ እንድችል ታደርገኛለህ? እርግጠኛ ነኝ ትችላለህ፡፡
ፊሊፕ - የ5 ዓመት ህፃን
የፍቅር ጥግ
የሴትን ልብ ለማግኘት እርግጠኛው መንገድ ተንበርክኮ ማለም ነው፡፡
ዳግላስ ጄሮልድ
(እንግሊዛዊ ፀሃፌ ተውኔት)
ማናቸውንም የፍቅር ጉዳዮች አላስታውስም። ሰው የፍቅር ጉዳዮችን በምስጢር ነው መያዝ ያለበት፡፡
ዋሊስ ሲምፕሰን
(ትውልደ-አሜሪካ እንግሊዛዊ መኳንንት)
መጀመሪያ ማፍቀር እንጂ መኖር አልፈልግም፡፡ መኖር የምሻው እግረመንገዴን ነው፡፡
ዜልዳ ፊትዝጌራልድ
(አሜሪካዊ ፀሃፊ)
ከሁሉም ዓይነት ሴቶች ጋር ፍቅር ይዞኛል። ወደፊትም ሙሉ በሙሉ በዚሁ ለመቀጠል አቅጃለሁ፡፡
ቻርልስ
(የዌልስ ልኡል)
በፀደይ ወራት የጎረምሳ ህልም በስሱ ወደ ፍቅር ሃሳብ ይገባል፡፡
አልፍሬድ ቴኒሰን
(እንግሊዛዊ ገጣሚ)
ፍቅር እንደ ሲጋራ ነው፤ ከጠፋብህ እንደገና ትለኩሰዋለህ፡፡ ነገር ግን ፈፅሞ እንደ መጀመሪያው አይጥምም፡፡
አርኪባልድ ፐርሲቫል ዋቬል
(እንግሊዛዊ ወታደር)
ጓደኝነት ክንፍ አልባ ፍቅር ነው፡፡
ሎርድ ባይረን
(እንግሊዛዊ ገጣሚ)
ከማፈቅረው ሰው ጋ መሄድ ፍላጎቴ ነው፡፡ ወጪውን ማስላት አልፈልግም፡፡ ጥሩ ይሁን መጥፎ ማሰብ አልሻም፡፡ ያፍቅረኝ አያፍቅረኝ ማወቅ አልፈልግም፡፡ ከማፈቅረው ጋ መሄድ ፍላጎቴ ነው፡፡
ቤርትሎት ብረሽት
(ጀርመናዊ ፀሐፌ ተውኔትና ገጣሚ)
ፍቅር ከድህነትና ከጥርስ ህመም በቀር ሁሉንም ነገሮች ያሸንፋል፡፡
ማ ዌስት
(አሜሪካዊ ተዋናይና ኮሜዲያን)
ፍቅር ደስታ መሆኑ የቀረው ምስጢር መሆኑ የቀረ ጊዜ ነው፡፡
አፍራ ቤኸን
(እንግሊዛዊ ደራሲና ድራማ ፀሃፊ)
የአልማዝ ስጦታውን እስከ መመለስ የሚያደርስ ጥላቻ ለወንድ ኖሮኝ አያውቅም፡፡
Zsa Zsa Gabor
(ትውልደ - ሃንጋሪያዊ አሜሪካዊ ፊልም ሰሪ)
የፖለቲካ ጥግ
(ስለ ጠላት)
ጠላቶችህን ሁልጊዜ ይቅር በላቸው፣ ስማቸው ግን ፈፅሞ አትርሳ፡፡
ሮበርት ኬኔዲ
(አሜሪካዊ ፖለቲከኛ)
ጠላቶቼን ይቅር ማለት አይጠበቅብኝም፤ ሁሉንም ገድያቸዋለሁ፡፡
ራሞን ማርያ ናርቫዝ
(ስፔናዊ ጄነራልና ፖለቲከኛ)
ጠላቶቼ እውነት እንዳላቸው መቀበል አልወድም።
ሳልማን ሩሽዲ
(ትውልደ - ህንድ እንግሊዛዊ ደራሲ)
ጠላትህን በስትራቲጂ መናቅ፣ በታክቲክ ግን ማክበር አለብህ፡፡
ማኦ ዜዶንግ
(ቻይናዊ ፖለቲከኛ)
በወዳጆችህ ትከበራለህ… በጠላቶችህ ትታወቃለህ። እኔ በእጅጉ የታወቅሁ ነበርኩ፡፡
ጄ. ኤድጋር ሁቨር
(አሜሪካዊ የወንጀል ጥናት ባለሙያና የመንግስት ባለስልጣን)
ዝናና እውቅና ለጠላቶች ያጋልጣል፡፡
ሲ.ኤል.አር.ጀምስ
(የትሪኒዳድ ፀሃፊ፣ የፖለቲካ ንድፈ ሃሳብ ቀማሪ)
ከአስተዋይነት የበለጠ ጠቃሚ መሳሪያ፣ ከድንቁርና የከፋ ጎጂ ጠላት የለም፡፡
አቡ አብደላህ መሃመድ
አል-ሃሪቲ-አል-ባግዳድ-አል-ሙፊድ
(ኢራቃዊ ምሁርና የህግ ባለሙያ፤ በ10ኛው ክ/ዘመን የኖረ)
ገንዘብ ወዳጆችን መግዛት አይችልም፡፡ ነገር ግን የተሻለ የጠላት መደብ ሊያስገኝልህ ይችላል፡፡
ስፓይክ ሚሊጋን
(ትውልደ-ህንድ እንግሊዛዊ ፀሃፊ፣ ተዋናይና ተረበኛ)
ሰላም የሚፈጠረው ከትላንት ጠላቶች ጋር ነው፡፡ ሌላ ምን አማራጭ አለ?
ሺሞን ፔሬስ
(የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር)
አይዟችሁ፤ “ስንዴው ከሳምንት በኋላ ጂቡቲ ይደርሳል”
መንግስት፣ በየጊዜው “የምስራች” እያለ የሚነግረንን ወሬ ማመን ቢቀርብን ይሻላል። ግን፣ መስማትና ማመን ለምዶብናል፡፡ መልካም ነገር ስለምንመኝ ይሆን፤ “ለማመን” የምንቸኩለው? መንግስት አዲስ ወሬ ሲያበስረን እንሰማዋለን፤ “የዛሬውስ እውነት ሊሆን ይችላል” ብለን እናምነዋለን፡፡ ሌላው ይቅርና፤ “ኢትዮጵያ በእህል ምርት ራሷን ችላለች” ሲለን እንኳ አምነነዋል። በየጎዳናው የምናየው ድህነትና በየጓዳው የሚያጋጥመን የኑሮ ችግር በጣም ከባድና አሳዛኝ እንደሆነ ብናውቅም፤ የምስራች ሲበሰር ቶሎ ለማመን ዝግጁ ነን።
ምን ዋጋ አለው? ዳቦ ቤቶች በስንዴ እጥረት እንደ ዘንድሮ ተቸግረው አያውቁም፡፡ ባለፈው ጥቅምት ወር ገደማ ነው ነገሩ የተጀመረው። “አዝመራው ጥሩ ምርት ይዟል” ተባለ በደፈናው፡፡ ግን በዚሁ ተደፋፍኖ አልቀረም፡፡ በእህል አይነት እየተዘረዘረ፤ ከነመጠኑ በኩንታል እየተጠቀሰ “ከፍተኛ የእህል ምርት ይሰበሰባል” የሚል የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን ሪፖርት ወጣ። ይህን ሪፖርት ተከትሎ፤ የእህል ንግድ ድርጅት መግለጫ ለመስጠት ቀናት አልፈጀበትም። ስንዴ ከውጭ ለመግዛት ነው ወራት የሚፈጅበት፡፡
የእህል ገበያ ድርጅት ሃላፊዎች፤ የእህል ምርት በብዛት እንደሚሰበሰብ በመጥቀስ ታህሳስ ወር ላይ በሰጡት መግለጫ፤ የእህል ዋጋ አሽቆልቁሎ ገበሬዎች ተጎጂ እንዳይሆኑ እንሰጋለን በማለት ጭንቀታቸውን አስረድተዋል።
እንዲያውም፣ የእህል ዋጋ ገና ካሁኑ የመቀነስ አዝማሚያ ጀማምሮታል በማለት የተናገሩት የድርጅቱ ሃላፊዎች፣ ለምሳሌ የጤፍ ዋጋ በኩንታል 20 ብር ቀንሷል በማለት ማስረጃ አቅርበዋል፡፡ የአንድ ኪሎ የጤፍ ዋጋ ላይ የሃያ ሳንቲም ቅናሽ መታየቱ እንደ ትልቅ ነገር መወራቱ አያስገርምም? ይሄም ብቻ አይደለም፡፡ በየአመቱ ከታህሳስና ከጥር ወር በኋላ የእህል ዋጋ እንደሚጨምር እንዴት ይዘነጉታል? ለዚያውም “የእህል ንግድ” ላይ የተሰማሩ ሃላፊዎች ናቸው!
ለማንኛውም የእነሱ ጭንቀት፣ የእህል ምርት “ተትረፍርፎ” ገበያ ላይ ዋጋው እንዳይወድቅ ነው። ደግነቱ፤ ችግር የለም፡፡ ችግር አይፈጠርም። የእህል ንግድ ድርጅት አለልን፡፡ ሃላፊዎቹ፤ እህል በመግዛትና በመሰብሰብ በገበያ ላይ ዋጋው እንዳያሽቆለቁል ለማድረግ እንደተዘጋጁ ገልፀዋል - በታህሳስ ወር።
በእርግጥ እንደዚህ ቢያስቡ አይገርምም። የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን መረጃዎች ሲታዩ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረተው ስንዴ በተለይ ባለፉት ስድስት አመታት በእጅጉ ጨምሯል። በ2001 ዓ.ም የስንዴ ምርት 25 ሚሊዮን ኩንታል፤ በ2004 ዓ.ም ደግሞ 29 ሚሊዮን ኩንታል እንደነበር ይገልፃል የባለስልጣኑ መረጃ። አምና በከፍተኛ የምርት እድገት 34 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ እንደተሰበሰበ አመታዊው የባለስልጣኑ ሪፖርት ያመለክታል። ዘንድሮ ደግሞ አርባ ሚሊዮን ኩንታል።
ሪፖርቶቹ እውነተኛ ከሆኑ፣ የስንዴ ምርት በሁለት አመታት ውስጥ በ11 ሚሊዮን ኩንታል ጨምሯል ማለት ነው። የ45% እድገት ቀላል አይደለም፡፡ አስደናቂ ነው፡፡ “ምርት ተትረፈረፈ” ያስብላል፡፡
ግንቦት 20 በሚከበርበት እለት ደግሞ ተጨማሪ ትልቅ ስኬት ተበሰረ፡፡ ለተከታታይ አመታት በተመዘገበው የግብርና እድገት ዘንድሮ ኢትዮጵያ በእህል ምርት ራሷን ችላለች በማለት ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ ተናግረዋል፡፡ ድንቅ ነው፡፡
የእህል ምርት እየጨመረ መምጣቱ አይካድም፡፡ ጥሩ ነው፡፡ “ኢትዮጵያ በእህል ምርት ራሷን ችላለች” ብሎ መናገር ግን ሌላ ነገር ነው፡፡ ያለ መንግስት ድጐማ ኑሯቸውን መቀጠል የማይችሉ 6.5 ሚሊዮን ችግረኛ የገጠር ነዋሪዎች አሉ፡፡ ያለ ውጭ እርዳታ በህይወት መቆየት የማይችሉ 6.5 ሚሊዮን ረሃብተኞች መኖራቸውን ደግሞ ዩኤን ገልጿል፡፡ በድምሩ 13 ሚሊዮን
ተረጂዎች ያሉባት አገር “በእህል ምርት ራሷን ችላለች” ሲባል ምን ትርጉም አለው?
የመንግስት ብስራት ግን በዚህ አላቆመም፡፡ የስንዴ ምርት በእጅጉ እያደገ መሆኑን በመጥቀስ፤ “ኤክስፖርት ይደረጋል” በማለት የመንግስት ባለስልጣናት ሲናገሩ ከርመዋል፡፡ የሆይ ሆይታው ተከፋይ የሆኑት የእህል ንግድ ድርጅት የስራ ሃላፊዎች፤ ከዚህ “ብስራት እና “ስኬት” የተለየ ነገር አልተናገሩም፡፡ እንዲያውም የተወሰነ ያህል ቁጥብነት አሳይተዋል፡፡ ባለፈው አመት ምን እንደሰሩና ለዘንድሮ ምን እንዳቀዱ የድርጅቱ የስራ ሃላፊዎች ሲዘረዝሩ እንመልከት፡፡
በ2005 ዓ.ም ወደ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ስንዴ በ4.5 ቢሊዮን ብር ከውጭ ሀገር በመግዛት ገበያውን ለማረጋጋት እንደተቻለ ለዋልታ የገለፁት ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ብርሃኑ ሃይሉ፤ ዘንድሮ በቂ ስንዴ ስለተመረተ ከውጭ አገር ገዝተን አናስመጣም አላሉም፡፡ ግን እንደሌላው ጊዜ በፍጥነት ስንዴ ለመግዛትም ውሳኔ አላስተላለፉም።
ከ2005 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር በ2006 ዓ.ም የሚሰበሰበው የስንዴ ምርት በ4 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚበልጥ የተናገሩት የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ፤ የስንዴ እጥረትንና የዋጋ ንረትን ለማቃለል ታስቦ ከውጭ እየተገዛ የሚመጣው ስንዴ ዘንድሮ በግማሽ እንደሚቀንስ ገልፀዋል፡፡ አምና ከውጭ ተገዝቶ የመጣው ስንዴ ከ5 ኩንታል በላይ ስለሆነ ዘንድሮ 2.5 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡
“ዘንድሮ ከውጭ ገበያ የሚገዛው ስንዴ በግማሽ እንደሚቀነስ ነው ዋና ስራ አስኪያጁ ያመላከቱት” ብሏል ፋናቢሲ በታህሳስ 28 ቀን ዘገባው።
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን መረጃ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ሆይሆይታ እና የእህል ንግድ ድርጅት ሃላፊዎች ውሳኔ ውሎ አድሮ መጨረሻው አላማረም፡፡
ገና የካቲት ወር ላይ ነው በስንዴ እጥረት የአገሪቱ ዳቦ ቤቶች መቸገር የጀመሩት፡፡ እንደታሰበው በ2.5 ሚሊዮን ኩንታል ግዢ ብቻ የስንዴ እጥረትን ማቃለል እንደማይቻል በግልጽ እየታየ የመጣው፤ ስራ ፈትተው በራቸውን የሚዘጉ ዳቦ ቦቶቹ ሲበራከቱ ነው፡፡
ለዚህም ነው የኋላ ኋላ አራት ሚሊዮን ኩንታል ለመግዛት የተወሰነው፡፡ ለነገሩ ቀደም ሲል የታሰበው 2.5 ሚ ኩንታል ስንዴ፤ ቶሎ ተገዝቶ አልመጣም። ለጊዜው በቂ ስንዴ ተመርቷል ስለተባለ ከውጭ አገር ገዝቶ ማስመጣት የሚያስቸኩል ጉዳይ አልሆነባቸውም፡፡
አሁን እንደምታዩት፤ የስንዴ እጥረት አፍጥጦ ወጥቷል፡፡ የመንግስት እና የእህል ንግድ ድርጅት ሆይሆይታ በመጨረሻ “ዳቦ አልቋል” ወደሚል ችግር አደረሰን፡፡ ነገር ግን የመንግስት ባለስልጣናትም ሆኑ የድርጅቱ ሃላፊዎች በተሳሳተ ግምት የስንዴ እጥረት እንደፈጠሩና ጥፋት እንደሰሩ አምነው አይቀበሉም፡፡
“የስንዴ እጥረት ተፈጠረ፤ ዱቄት ጠፋ፣ ዳቦ አለቀ” የሚል ቅሬታ ሲቀርብባቸው፤ “የአቅርቦት እጥረት የለም፤ ችግሩ የስርጭት ነው” የምትል የተለመደች ምላሽ ይሰጣሉ፡፡
የስርጭት ችግርምኮ የነሱ ጥፋት ነው፡፡ ግን ይሄንን ለማሰብ ጊዜ የላቸውም። በወሬ ብቻ የስንዴ እጥረትን የሚያስወግዱ ስለሚመስላቸው፤ ሌላ ነገር አይታያቸውም፡፡ “የአቅርቦት እጥረት የለም” የሚል ወሬ አላዋጣ ሲል ነው፤ የተስፋ ቃል መናገር የሚጀምሩት፡፡ “አይዟችሁ፡፡ ከሳምንት በኋላ ስንዴው ጅቡቲ ይደርሳል” በማለት በተስፋ እንድንጠብቅ ሰሞኑን ነግረውናል፡፡
ለመብላት የጠፋ ቅቤ ስሞት በአፍንጫዬ ይፈስሳል፤ አለ ዶሮ
(በቁም ያልረዳ ዘመድ ሲሞቱ አርባ ይደግሳል)
ከዕለታት አንድ ቀን ሶስት ሰዎች አንድ ጫካ እያቋረጡ ሳሉ፣ አንዲት የወፍ ጫጩት ከዛፍ ላይ ጎጆዋ ወድቃ መሬት ላይ ያገኙዋታል፡፡
አንደኛው - “ቤቴ ወስጄ እንደ ዶሮ ጫጩት አሳድጋታለሁ” አለ፡፡
ሁለተኛው - “ለጥናትና ምርምር ትጠቅማለች፡፡ ወደ ላቦራቶሪ ወስደን ለባለሙያ እንስጣት” አለ፡፡
ሶስተኛው - “የለም ጎበዝ፤ ወደገበያ ወስደን እንሽጣት” አለ፡፡
በዚህ ክርክር ብዙ ከተሟገቱ በኋላ በዚያው አካባቢ የሚኖር አንድ ፈላስፋ አዋቂ ስላለ ወደሱ ዘንድ ሄደው ዳኝነት ሊጠይቁ ተስማሙ፡፡ ወፊቱን ይዘው አዋቂው ቤት ሄዱ፡፡
“ምን ልርዳችሁ ምን ላግዛችሁ?” አለና ጠየቃቸው፡፡ ተወካያቸው እንዲህ ሲል አስረዳ፡-
“ከዛፍ ጎጆዋ የወደቀች ወፍ አግኝተናል፡፡ አንዱ ቤቴ ወስጄ ላሳድጋት አለ፡፡ አንዳችን ለቤተ-ምርምር እንስጣት አልን፡፡ አንዳችን ገበያ ተወስዳ ትሸጥ አልን፡፡ ማንኛችን ነን ትክክል?”
ፈላስፋውም ጥቂት ካሰበ በኋላ፤
“ወዳጆቼ ሆይ! ለዶሮ ጫጩት የሚሆነው ኑሮ ለወፍ ጫጩትም ይሆናል ብሎ ያሰበ ተሳስቷል፡፡ ሁሉም የየራሱ ኑሮ ነው ያለው፡፡ አሳድጎስ ምን ሊያደርጋት ነው? ዓላማ ቢስ ይሆናል! ቤተ-ምርምር እንውሰዳት ያለውም ተሳስቷል፡፡” ለወፊቱ የሚጠቅማት ነገር የለምና፡፡ ወደገበያ ወስደን እንሽጣት ያለውም ከዚች ጫጩት ሽያጭ ማንኛችሁ ምን ያህል ልትጠቀሙ ነው? የማያዋጣ ጥቅም ከመፈለግ አለማድረጉ ይመረጣል” አላቸው፡፡
“እንግዲያስ ምን አድርጉ ትለናለህ?” አሉና ጠየቁት፡፡
ፈላስፋውም፤
“ከሁሉም የሚሻለው ወፊቱን ወደ ጎጆዋ መመለስ ነው፡፡ ኑሮዋን መልሱላት፡፡ ሰላሟን ስጧት፡፡ የተፈናቀለን ሰው እንደምታቋቁሙ ሁሉ ለወፊቱም እንደዚያ አስቡላት” ብሎ አሰናበታቸው፡፡
* * *
ያለዓላማ ጉዞ ከንቱ ነው፡፡ ያለቅርስና ያለበቂ መሰረታዊ ጥቅም ነፃ-ገበያን መመኘት የጫጩት አትራፊነት ምኞት ነው፡፡ ያለብስለት ጥናትና ምርምር፣ ያለብቁ ባለሙያ ዕድገት ዘበት ነው፡፡ ኑሮው ካልተመለሰለት፣ ደሀ ጎጆው ካልተመለሰ፣ ልማቱ ከደረቀ፣ እሳቱ ካልሞቀ ተስፋው ይሞትበታል፡፡ ኑሮው መለወጥ አለበት፡፡ መታገዝ አለበት፡፡ ገቢና ወጪው መመጣጠን መቻል አለበት፡፡ ውሎ አድሮ ገቢው ይጨምር ዘንድ መንገዱ ሊጠረግለት ይገባል፡፡
ዛሬ እንደፋሽን የተያዘው ህገ-ወጥ ብልፅግና ነው፡፡ ሀገራዊ ስሜት ያለጥርጥር እየቀጨጨ ነው፡፡ ደምብና ሥርዓትን መጣስ እንደፋሽን ተይዟል፡፡ ድህነትን መቀነስ እንደአፍ አመል ሆኖ ይነገራል እንጂ በበሰለ መልኩ ህዝብ ውስጥ አልሰረፀም፡፡ ግማሽ ጎፈሬ፣ ግማሽ ልጩ የሆነ ካፒታሊዝም ከፋይዳው ማነስ ግራ ማጋባቱ ይብሳል፡፡ የምሁሮቻችን የድህነትን አሽክላ ለማስወገድ ዝግጁ አለመሆን፣ ከስራ አጥነት መዘዝ ጋር ተዳምሮ፣ ከአረንቋው እንዳንወጣ እያደረገን ነው፡፡ አዙሪቱ እጅግ ጥምዝምዝና ተደጋጋሚ ነው፡፡ “ከእለት እንጀራና ከትክክለኛ ምርጫ የትኛው ይሻላል?” ዓይነት አጣብቂኝ የድህነት የቤት ጣጣ ነው፡፡ ሀብት እኩል ባልተከፋፈለበት አገር ምርጫ 100% ተሳካ ሲባል አይገርምም ይላሉ ለበጠኛ አበው - ባለሙያዎች እንዲህ ግራ-ገብ ነገር ሲበዛባቸው፡፡ ከሁሉም ይሰውረን ማለት ትልቅ ፀሎት ነው፡፡
የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ኢ-አድሎአዊነትና ቀናነትን ይጠይቃል፡፡ የብዙሃን ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረት አስፈላጊነት አጠያያቂ ያለመሆኑን ያህል፤ ሁሉም ፓርቲዎች እኩል መሆናቸውን፣ በታሪክ የብቻውን ካሳ የሚያገኝ አንድም ፓርቲ መኖር እንደማይገባ፣ እርስ በእርስ መወዳደራቸው የዕድገት ማሺን መሆኑ እጅግ ግልፅ ሊሆን ይገባል፡፡ ሁሉም ፓርቲዎች ያለጭቦ መሳተፋቸውና መወከላቸው፣ የሲቪል ቡድኖችም ሊሳተፉበት ማስፈለጉ ገሀድ ጉዳይ ነው፡፡ በማግለል እንጂ በማሳተፍ የምናወጣው ነገር እንደሌለ ልብ ማለት ተገቢ ነው፡፡
ኑሮ ዛሬ ነው፡፡ ነገ ምኞት ነው፡፡ ህይወት በእጅ ባለበት ሰዓት የሚኖር እንጂ በምኞት የሚታቀድ አይደለም፡፡ ዛሬ መኖር መቻል አለበት፡፡ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች በቀላሉ መገብየት አለባቸው፡፡ ቀን በቀን እየናረ የሚሄደውን የኑሮ ውድነት ሳንገታ ዕድገትን ብናልም ምኞት ብቻ ነው፡፡ ለመብላት የጠፋ ቅቤ ስሞት በአፍንጫዬ ይፈስሳል፤ አለ ዶሮ የሚበላው ለዚህ ነው፡፡
ኢትዮጵያና ግብጽ በ7 ነጥቦች ላይ ተስማሙ
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝና የግብጹ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ ከትናንት በስቲያ በኢኳቶሪያል ጊኒ ማላቦ ከተማ ተገናኝተው አዲስ ስምምነት ላይ መድረሳቸው የተዘገበ ሲሆን፤ የጋራ ጥቅምን ባስጠበቀ መልኩ ለመስራትና ከወዲሁ አስፈላጊ ዝግጅቶችን በመጀመር በሶስት ወራት ውስጥ የጋራ ስብሰባ ለማድረግ መስማማታቸውን የግብጽ መንግስት ገለፀ፡፡
የሁለቱ አገራት መሪዎች ውይይት ስኬታማ እንደሆነ በመጥቀስ፣ የኢትዮጵያና የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሰጡት የጋራ መግለጫ፤ የአባይ ወንዝን በሚመለከት የግብጽ ህልውናና የኢትዮጵያ የልማት ፍላጎትን መሰረት በማድረግ ለመስራት ተስማምተናል ብለዋል፡፡ በአባይ ወንዝ እና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ መሪዎቹ ተወያይተው በ7 ነጥቦች እንደተስማሙ ሚኒስትሮቹ ገልፀው፤ ለሁለቱ አገራት ጥቅም የሚበጀውን የውይይትና የትብብር መርህ እናከብራለን የሚል ነጥብ በቀዳሚነት ጠቅሰዋል፡፡
እያደገ የመጣውን የውሃ ፍላጎት ለማሟላትና የውሃ እጥረትን ለመቋቋም የሚያስችል የገንዘብ አቅም የሚያስገኙ ክፍለ አህጉራዊ ፕሮጀክቶችን ለመዘርጋት ቅድሚያ እንሰጣለን ብለው እንደተስማሙም ሚኒስትሮቹ ተናግረዋል፡፡
ሶስተኛው የስምምነት ነጥብ፣ የአለም አቀፍ ህግ መርሆዎችን እናስከብራለን የሚል ነው፡፡ ይሁን እንጂ፤ ሁለቱ አገራት “የአለም አቀፍ ህግ መርህ” በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያየ ትርጓሜ በመስጠት እንደሚወዛገቡ የሚታወቅ ሲሆን፤ ለዚህ አወዛጋቢ ጉዳይ እልባት የሚሰጥ አዲስ ሃሳብ አልመጣም፡፡ በግብጽ በኩል፤ ከ90 አመት በፊት ግብጽና እንግሊዝ እንዲሁም ከ50 ዓመታት በፊት ሱዳንና ግብጽ የተፈራረሟቸው ስምምነቶች መከበር አለባቸው የሚል መከራከሪያ ይቀርባል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ብዙዎቹ የአባይ ተፋሰስ አገራትን ያላሳተፉ የድሮ ስምምነቶች ተቀባይነት የላቸውም፤ የአባይ ተፋሰስ አገራት የፈረሙበት አዲስ ውል ሊከበር ይገባል የሚል መከራከሪያ ይቀርባል፡፡
ጠ/ሚ ሃይለማርያም እና ፕ/ት አልሲሲ የተስማሙበት አራተኛው ነጥብ፤ ሱዳንን ጨምሮ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የተቋቋሙት የሶስትዮሽ ኮሚቴን የሚመለከት ነው፡፡ በግብጽ ተቃውሞ ሳቢያ ኮሚቴው ስራ እንደቆመ የሚታወቅ ሲሆን፤ አሁን የኮሚቴውን ስራ በአፋጣኝ መልሶ ለማስጀመር ተስማምተናል ሲሉ ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተናግረዋል፡፡ አለማቀፍ የባለሙያዎች ኮሚቴ ያቀረባቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች ለማስተግበር እንዲሁም በቀጣይ የግድቡ ግንባታ ሂደት ላይ በሚካሄድ ጥናት የሚገኙ ውጤቶችን በጸጋ ለመቀበል መስማማታቸውም ተገልጿል፡፡
አምስተኛው ነጥብ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ሃላፊነትን የሚጥል ሲሆን፤ የግድቡ ግንባታ በግብጽ የውሃ አጠቃቀም ላይ ማናቸውም ችግር እንዳይፈጠር በፅናት እጥራለሁ ይላል፡፡ የግብጽ መንግስት ላይ ሃላፊነትን የሚጥለው 6ኛ ነጥብ ደግሞ የኢትዮጵያን የልማት ፍላጎት ከግምት ውስጥ ከሚያስገባ ገንቢ ውይይት ላለማፈንገጥ ቃል እገባለሁ የሚል ነው፡፡
ሱዳንን በሚጨምረው የሦስትዮሽ ኮሚቴ ስር በቅንነት ለመስራትም ሁለቱ መሪዎች ተስማምተዋል፤ በ7ኛው ነጥብ፡፡
የሁለቱ መሪዎች ውይይት ግልጽነት የተመላበት ነበር ያሉት የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሜህ ሾክሪ፤ ውይይቱና ስምምነቱ ለሁለቱ አገራት ግንኙነት ትልቅ ስፍራ አለው፤ በመተማመንና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ከፍተናል ብለዋል፡፡
የህዳሴ ግድብ በግብጽ የውሃ አጠቃቀም ላይ ችግር እንዳይፈጥር ኢትዮጵያ ምን ማድረግ ትችላለች ተብለው የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ የግድቡ ዲዛይን የተሰራው ምንም አይነት ችግር ሊያስከትል በማይችል መልኩ ነው፤ ከዚህም በተጨማሪ አገራቱ በተስማሙት መሰረት በጉዳዮቹ ዙሪያ በጋራ መወያየትና መፍትሄ ማበጀት ይችላሉ ብለዋል፡፡
ለአልሸባብ ወደ አክራሪነት መለወጥ ኢትዮጵያ ተጠያቂ ናት መባሉን መንግስት አጣጣለ
አልሸባብ ፅንፈኛ ድርጅት የሆነው ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ ጦር ሰራዊት በማዝመቷ ነው በማለት ኒው አፍሪካን መጽሔት የዘገበ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የአልሸባብ ታጣቂዎች አፍጋኒስታን ሄደው ስልጠና የወሰዱት ገና ድሮ ነው በማለት ዘገባውን አጣጣለ፡፡
አልሸባብ በዩጋንዳ እና በኬኒያ በፈፀማቸው ጥቃቶች ሳቢያ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ውስጥ ስጋት መፍጠሩን በመጥቀስ ነው መጽሔቱ አልሸባብን የሚመለከት ሰፊ ዘገባ ያቀረበው፡፡
ዜጐች በሄዱበት ሁሉ በፍተሻ መከራቸውን እያዩ እንደሆነ መጽሔቱ ገልፆ፤ በኬኒያ እና በዛንዚባር የቱሪዝም ገቢ ክፉኛ አሽቆልቁሏል፤ የኬኒያ መንግስት የመከላከያ በጀቱን ለመጨመር ተገዷል፡፡
አልሸባብ ወደ አክራሪነት የተለወጠው፤ በ2006 የኢትዮጵያ መከላከያ ሀይል በአሜሪካ ድጋፍ ወደ ሶማሊያ በመዝመቱ ነው ሲልም መጽሔቱ ኢትዮጵያን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ በመጽሔቱ የቀረበው ውንጀላ መሰረተ ቢስ ነው ሲል ያጣጣለው የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ኢትዮጵያ አልሸባብን አዳከመች እንጂ ወደ አክራሪነት እንዲለወጥ አላደረገችም በማለት ሰፊ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ እንዲህ አይነቱ ውንጀላ በተደጋጋሚ የሚሰነዘር መሆኑን ሚኒስቴሩ ጠቅሶ፤ ነገር ግን ምንም አይነት ማስረጃ የማይቀርብበት መሰረተ ቢስ ውንጀላ ነው ብሏል፡፡
በሶማሊያ እየገነነ የነበረው የእስልምና ፍርድ ቤቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጦር በመመታቱ አይደለም አልሸባብ ያቆጠቆጠው፡፡ እንዲያውም የፍርድ ቤቶች ምክር ቤት ሶማሊያ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ በነበረበት ወቅትና ከዚያ በፊት ወደ አፍጋኒስታን ለስልጠና ተልከው በነበሩ ቡድኖች ናቸው አልሸባብን የመሰረቱት ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡
የእስልምና ፍርድ ቤቶች ህብረት ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አውጆ እንደነበር ሚኒስቴሩ አስታውሶ፤ ያንን ጥቃት ለመከላከል የተወሰደው ወታደራዊ እርምጃ ተገቢ ነበር ብሏል፡፡
ወታደራዊ እርምጃ የወሰድነውም፤ አለም አቀፍ ህጐችን በማይጥስ መንገድና ከሶማሊያ የሽግግር መንግስት በተደረገልን ግብዣ ነው ብሏል - ሚኒስቴሩ፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ሶስት አመት ሶማሊያ ውስጥ በቆየበት ወቅት ምንም አይነት ድጋፍ ከአሜሪካን እንዳልተሰጠውም ጠቅሷል፡፡
የሸራተን ሰራተኛ ማህበርና ማኔጅመንቱ እንዲደራደሩ ተወሰነ
የሸራተን ሠራተኛ ማህበርና ማኔጅመንቱ ለድርድር እንዲቀርቡ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ ባለፈው ማክሰኞ የወሰነ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ አደራዳሪ እንዲመደብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
የሸራተን ሆቴል ጠበቃ አቶ ተካ አስፋው፤ ክሱ እንዲሰረዝና ያለ አደራዳሪ ራሳቸው እንዲደራደሩ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡
ላለፉት 6 ወራት የሸራተን ሰራተኛ ማህበር ማኔጅመንቱ በህብረት ስምምነቱ ላይ እንዲደራደር ጥያቄ ሲያቀርብ ቢቆይም ማኔጅመንቱ ለድርድር ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ ለኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን የእገዛ ጥያቄ ማቅረቡን እንዲሁም ጉዳዩ ከፌዴሬሽኑ አቅም በላይ በመሆኑ ለኢሰማኮ ደብዳቤ መፃፉንና ኢሰማኮ ለማኔጅመንቱ የአምስት ቀን ጊዜ መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ማኔጅመንቱ የተሰጠውን የአምስት ቀን የጊዜ ገደብ ከጨረሰ በኋላ የኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኑ ለአሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ ክስ መስርቶ፣ ባለፈው ማክሰኞ የፌዴሬሽኑ ጠበቃ አቶ ሰኢድ ይመርና የማኔጅመንቱ ጠበቃ የቀድሞው የስፖርት ፌዴሬሽን ም/ፕሬዚዳንት አቶ ተካ አስፋው በተገኙበት ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
ቦርዱ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፤ አደራዳሪ እንዲመድብ ትዕዛዝ እንደሚያስተላልፍ ገልጿል፡፡
በጉዳዩ ላይ ፌዴሬሽኑ በአደራዳሪነት እንዲገባ የኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኑ ጠበቃ አቶ ሰኢድ ይመር የጠየቁ ሲሆን የሸራተን ሆቴል ጠበቃ አቶ ተካ አስፋው ጥያቄውን ተቃውመውታል፡፡ “በጭራሽ መደረግ የለበትም፤ ፌዴሬሽኑ በአደራዳሪነት ገባ ማለት በእሳት ላይ ቤንዚን እንደማርከፍከፍ ይቆጠራል” ብለዋል - አቶ ተካ፡፡ የፌዴሬሽኑ ጠበቃ አቶ ሰኢድ በበኩላቸው፤ “በህግ አምላክ! ህጋዊ ሰውነት ያለውን ድርጅት በዚህ መልኩ መዝለፍ በህግ ያስቀጣዎታል” ሲሉ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ቦርዱ አቶ ተካ ከንግግራቸውን እንዲታቀቡ አድርጓል፡፡
የሠራተኛ ማህበሩና ማኔጅመንቱ ለድርድር ቀርበው እስከ ሀምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም የደረሱበትን ሁኔታ ለቦርዱ ሪፖርት እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
በእለቱ ጉዳዩን ለመከታተል ከመጡት በርካታ የሸራተን ሰራተኞች መካከል አብዛኞቹ እንደገለፁልን፤ ሰራተኞች ችግራቸውን በሚዲያ ከገለፁ በኋላ፣ ሥራ አድረው ጠዋት ወደ ቤት ለሚሄዱ ሰራተኞች የሚቀርበው ሰርቪስ (የትራንስፖርት አገልግሎት) የቆመ ሲሆን በህመም፣ በጋብቻና በዘመድ ሞት ምክንያት አስፈቅዶ የቀረ ሰው ሰርቪስ ቻርጅ አይከፈለውም ተብሎ በድርጅቱ ሰሌዳ ላይ እንደተለጠፈም ጠቁመዋል፡፡
“የኪችን ሰራተኛ 350 ብር፣ የላውንደሪ ሰራተኛ፣ 400 ብር፣ የጥበቃ ሰራተኛ 450 ብር፣ እንግዳ ተቀባይ 700 ብር፣ አስተናጋጅ 450 ብር ደሞዝ እያገኘ በችግር ምክንያት የቀረን ሰው ሰርቪስ ቻርጅ አንከፍልም ማለት አሳፋሪ ነው” ብለዋል ሰራተኞቹ፡፡ የኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኑ ጠበቃ አቶ ሰኢድ ይመር በበኩላቸው፤ በሰራተኞቹ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ አግባብ ባለመሆኑ ድርጅቱ ከዚህ ድርጊቱ እንዲታቀብ ለቦርዱ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
ሰራተኞቹም የተወሰደው እርምጃ በህብረት ስምምነቱ የሌለና አዲስ የመጣ በመሆኑ ድርጅቱ የወሰደውን እርምጃ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ መሰረት እንዲያነሳ ጠይቀዋል፡፡
ስለቀጣዩ የማህበሩና ማኔጅመንቱ ድርድር የጠየቅናቸው የሰራተኛ ማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ሳሙኤል፤ ጉዳዩ በፍ/ቤት የተያዘ መሆኑን ጠቅሰው፤ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
“...ልጆች ቢኖሩንም...ዛሬ...ብቻችንን ነን...”
“...እኔና ባለቤቴ ከተጋባን እነሆ ሀምሳ ሶስት አመታችን ነው፡፡ የመጀመሪያ ልጃችን ሴት ስትሆን እሱዋም እድሜዋ ወደ ሀምሳ ሁለት ደርሶአል። በጠቅላላውም ወደ አስራ አንድ ልጅ የወለድን ሲሆን የመጨረሻ ልጃችን ሀያ አምስት አመት ሆኖአታል፡፡ በነበረው ሁኔታ ከቤተሰብ የተወረሰ ሀብት እና እኛም በየበኩላችን የሰራነው ተጨማምሮ ልጆቻችንን በደንብ አሳድገን ዛሬ ሁሉም የየራሳቸውን ሀብትና ንብረት ይዘዋል፡፡ እንዲያውም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በውጭ ሀገራት ኑሮአቸውን መስርተዋል፡፡ ሀገር ውስጥ ያሉትም ቢሆኑ ያገቡትም አግብተው ያላገቡትም ቢሆኑ ቤት እየተከራዩ ወጥተው እነሆ ዛሬ እኔና ባለቤቴ ብቻችንን እንኖራለን፡፡ በስልክም ይሁን በአካል እንደጠያቂ ከመጠየቅ ወይንም ስንፈልጋቸው አቤት ከማለት ውጭ በቀጥታ የምናገኘው ልጅ የለንም፡፡ ሁሉም የራሳቸውን ኑሮ መስርተዋል፡፡ እናም ጊዜው አልፈቅድ ብሎ እንጂ ልጅ ምንጊዜም አይጠላም። ታዲያ ...አሁን ...ልጆቻችንን ስንጠይቅ እኛ እንደእናንተ ጊዜ ብዙ ልጅ አንወልድም ዛሬ ጊዜው ተሸሽሎአል...በልክ ነው የሚወለደው...ይሉናል፡፡ በእርግጥ አጥግቦ አብልቶ...አልብሶ እና አስተምሮ ማሳደግ ካልተቻለ ዝም ብሎ መውለድም አስቸጋሪ ይሆን ይሆናል...”
ወ/ሮ ይርገዱ ተዋበ ከአዲስ አበባ
ወ/ሮ ይርገዱ የሰባ አመት እድሜ ባለጸጋ ናቸው፡፡ ዛሬ ለሚመለከታቸው ግን ምናልባት ወደ ሀምሳዎቹ መጨረሻ እንጂ ሰባ አመት አይመስሉም። ምክንያቱንም ሲጠየቁ የሰጡት መልስ “...እኔ ልጆቼን ለማሳደግና ቤቴን ለማስተዳደር ስል እስከዛሬ ድረስ ያለእረፍት እንቀሳቀስ ነበር፡፡ ምናልባትም እሱ እንደ ስፖርት ሆኖ ይሆናል...” የሚል ነበር መልሳቸው፡፡ በእርግጥም አልተሳሳቱም፡፡ ብዙ ልጅ እንደመውለዳቸውም ስለአለመጎዳታቸውን ሲገልጹ ...ምንጊዜም ልጅ የሚወልዱት በሆስፒታል እንጂ በቤት ውስጥ አለመሆኑን እና የተማሩ በመሆናቸውም እራሳቸውን ለመርዳት አለመቦዘናቸውን ነው፡፡ ወ/ሮ ይርገዱ የሊሴ ፍራንሴ እና የንግድ ስራ ኮሌጅ ተማሪ ነበሩ፡፡ በእርግጥ አሉ ወ/ሮ ይርገዱ “...በእርግጥ ወደመጨረሻ የተወለዱትን ሁለት ልጆች ስወልድ ችግር ገጥሞኝ ነበር፡፡ አንዱዋም በሰባት ወርዋ የተወለደች ስትሆን ሌላዋ ደግሞ የተለያዩ የጤና ጉድለቶች ነበሩባት። እናም በከፍተኛ ሁኔታ እንክብካቤ ተደርጎ እና በሐኪሞችም ያላሳለሰ ክትትል ሰው ሆነው ዛሬ ጥሩ አቋም ላይ ይገኛሉ” ብለዋል፡፡
ከወ/ሮ ይርገዱ ታሪክ መለስ በማለት በዘመኑ ያሉትን ወላዶች አነጋግረናል፡፡ በክሊኒክ ክትትል ሲያደርጉ ካገኘናቸው መካከል የምትከተለው እናት ትገኝበታለች፡፡
“...ወ/ሮ ኤልሳቤጥ እባላለሁ፡፡ አሁን አንድ ልጅ አለኝ፡፡ የወለድኩት በኦፕራሲዮን ስለሆነ ለመውለድ የሚፈቀድልኝ ጊዜ ገና ስለሆነ እንጂ እኔ ልጅ መውለድ እፈልጋለሁ፡፡
ጥ/ እስከስንት ልጅ መውለድ ትፈልጊያለሽ?
መ/ እኔ እስከ አራትም ይሁን አምስት ልጅ ብወልድ ደስተኛ ነኝ፡፡
ጥ/ ባለቤትሽ በዚህ ይስማማል?
መ/ በእርግጥ እሱ እስከሶስት ይላል... እኔ ግን ልጅ እወዳለሁ፡፡
ጥ/ የማሳደግ ሁኔታውስ እንዴት ነው?
መ/ እኔ እማምነው ልጆች በረከት ናቸው በሚለው ነው፡፡ ልጅ ሲወለድ የራሱን ነገር ይዞ ይመጣል በሚለው ስለማምን ብወልድ ደስ ይለኛል።
ጥ/ ይህ ስሜት ከምን የመጣ ይመስልሻል?
መ/ አባቴ ቀደም ብሎ ስለሞተ እኛ ቤት እኔና ወንድሜ ብቻ ነን የተወለድነው፡፡ በአንድ ወቅት ወንድሜ ሲታመም እኔ የማዋራው ሰው እንኩዋን አጥቼ ነበር፡፡ እህት ወንድም ቢኖረኝ ኖሮ እያልኩ አስብ ነበር፡፡ እናም ከዚያ በመነሳት ልጄ ብቻዋን እንድትሆን ስለማልፈልግ ይመስለኛል፡፡
ሌላው እንግዳችን አባት ነው፡፡ የእርሱ ሀሳብ ደግሞ በፍጹም ከወ/ሮ ኤልሳቤጥ ይለያል፡፡
“...እኔ ቢኒያም ጌታቸው እባላለሁ፡፡ አንድ ልጅ አለኝ፡፡ እድሜውም ወደሶስት አመት ደርሶአል፡፡ እኔ ልጅ እንዲበዛ አልፈልግም፡፡
ጥ/ ለምን?
መ/ የልጅን ቁጥር መወሰን አስፈላጊ ነው። ልጅን መውለድ ማለት ወልዶ በማሳደግ ደረጃ ብቻ መወሰን ያለበት አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ ወደ ወላጆቻችን አኑዋኑዋር ስንመለስ የምንታዘበው ነገር አለ፡፡ እነእርሱ በዘመናቸው መሬት... ቤት... ሌላም ሌላም ሀብት የነበራቸው ሲሆን ልጅ እየወለዱ ያለሀሳብ አስተምረው አሳድገው ሲያልፉም ለእኛ መቋቋሚያ አውርሰው ይሆናል፡፡ በእርግጥ ይህ የሁሉም ሰው አኑዋኑዋር ባይሆንም በነበረው ልምድ የጎረቤት ልጅ የራስ ልጅ ተደርጎ የሚወሰድበት ሁኔታ ስለነበር ሀብታሙ ከደሀው ጋር ተጋግዞ እንዲሁም አንዱ አንዱን እረድቶ በሚያሰኝ ሁኔታ አድገናል፡፡ ዛሬ ግን ያለው ሁኔታ ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ ወላጅም እንደድሮው ያለ አኑዋኑዋር የለውም...እርስ በእርስ መተጋገዙም ቢሆን እስከዚህ የሚታይ አይደለም፡፡ ስለዚህ አንድ ወላጅ የሚያሳድገውን ብቻም ሳይሆን ወደፊት የወለደው ልጅ እንዴት እንደሚኖር ማሰብም ይጠበቅበታል ብዬ አምናለሁ፡፡
ጥ/ ልጅን በኑሮው ማቋቋም አስፈላጊ ነው ብለህ ታስባለህ?
መ/ ቢያንስ ቢያንስ የወለድኩት ልጅ በደንብ ተምሮ አድጎ ...ወደፊት ምን ሊሰራ እንደሚችል ማመላከት ...ምናልባትም የስራ ፈጠራን ማሳየት... ብችል እራሴ ስራ ፈጥሬ የወለድኩት ልጅ እንዲያስፋፋው ማድረግ ይጠበቅብኛል ብዬ አምናለሁ፡፡
ጥ/ በአንድ ልጅ ተወስኖ መቅረት ነው? ወይንስ?
መ/ አ.አ.ይ፡፡ አንድ ልጅ ጨምረን ሁለት እንደሚሆኑ ከባለቤቴ ጋር ተስማምተናል፡፡
ሌላዋ እንግዳ ወ/ሮ ሳራ ትባላለች፡፡ ያገኘናት ለእራስዋ የህክምና ክትትል ለማድረግ ከሄደችበት ክሊኒክ ነው፡፡
“...እኔ ሁለት ልጆች አሉኝ፡፡ እድሜያቸውም ትልቅዋ ስምንት አመት ሲሆን ትንሹ ደግሞ ስድስት አመቱ ነው፡፡
ጥ/ ከባለቤትሽ ጋር ...ሁለት ልጅ ይበቃናል ብላችሁ ወስናችሁዋል?
መ/ ልጅ ብንጨማምር ደስ ይለን ነበር፡፡ ነገር ግን የማሳደግ ሁኔታው እጅግ አስመርሮናል፡፡
ጥ/ ኢኮኖሚው ነው... ወይንስ?
መ/ አ.አ.ይ... ኢኮኖሚውን እንደብልሀቱ ልናደርገው እንችል ነበር፡፡ ነገር ግን የሚረዳኝ ሰው በማጣቴ ሁለቱን ልጆች ለማሳደግ በጣም ተሰቃይቻለሁ፡፡ ሰራተኛ እንደልብ አይገኝም። ቢገኙም ባልታሰበ ሁኔታ ትተው ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህ ...ግማሽ በግማሽ ከስራዬ እየቀረሁ ማለት በሚያስችል ሁኔታ ልጆቼን አሳድጌያለሁ፡፡ ከዚህ በሁዋላ ያ ሁኔታ እንዲደገም አልፈልግም እንጂ ቢያንስ ቢያንስ አንድ ሴት ልጅ ብደግም እፈልግ ነበር፡፡
ጥ/ ልጆችን ለመንከባከብ ከስራ መቅረት ያንቺ ብቻ ድርሻ ነበር ወይንስ የባለቤትሽም?
መ/ እንደሁኔታው ሁለታችንም እየተጋገዝን ነው ልጆቻችንን ያሳደግነው፡፡ እንደስራው ክብደትና ሁኔታ እየተነጋገርን ነበር ያንን የምናደርገው፡፡ ከእኔና እሱ በተጨማሪም ቤተሰቦቻችንም እያገዙን ነው የተወጣነው።
በመቀጠል ሀሳቡን የሰጠን አባት ነው፡፡ አቶ ክፍሎም ገብረሕይወት ይባላል፡፡ የአንድ ልጅ አባት ነው፡፡ ልጁ ወደሶስት አመት ይሆነዋል፡፡
ጥ/ አንተ እና ባለቤትህ ሌላ ልጅ የመውለድ እቅድ አላችሁ?
መ/ ልጅ መውለድ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን እራሳችንን ማደራጀት ስላለብን ቆም ማለት ፈልገናል፡፡
ጥ/ እራስን ማደራጀት ሲባል ምን ማለት ነው?
መ/ የምንወልዳቸውን ልጆች በሚገባ አስተምረን በብቃት ለማሳደግ እንድንችል እራሳችንን ማስተማር... ኑሮአችንን ማደራጀት... የመሳሰሉት ስለሚያስፈልጉን ባለቤቴም ሁለተኛ ዲግሪዋን እኔም ሶስተኛውን ዲግሪዬን በመስራት ላይ እንገኛለን፡፡ ይሄንን ካስተካከልን እኛ እያደግን ስለምንሄድ የምንወልዳቸውም ልጆች በጥሩ ሁኔታ ያድጋሉ የሚል እምነት አለን፡፡
በስተመጨረሻ የተነሳውን ፍሬ ሀሳብ የሚጠቀልሉልን የህክምና ባለሙያ ዶ/ር ዳንኤል አስፋው ናቸው፡፡
የቤተሰብ እቅድ ዘዴን መጠቀም የሚያስፈልገው በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት እንደሚያስረዳው ልጆችን አራርቆና ጤናማ በሆነ መንገድ ለማሳደግ ቤተሰብ የተወሰኑ ልጆችን የመውለድ እቅድ እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡ በሕክምናው፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚው እና ከወቅቱ ሁኔታ ጋር በተያያዘ አስገዳጅ ነገሮች መኖራቸው ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ከኢኮኖሚ አቅም በላይ መውለድ የልጆችን አስተዳደግ ጥራት ሊቀንስ ይችላል፡፡ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ገንዘብ አለን ተብሎም ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ልጆች መውለድም አይመከርም፡፡ ይሄም ከህክምናው አገልግሎት ይሁን ከኢኮኖሚው እንዲሁም ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የማይታረቅ ውሳኔ ይሆናል፡፡ የቤተሰብ እቅድ ሲባል አለምአቀፋዊ ትኩረት ያለው አሰራር ነው፡፡ ቤተሰብ ሲባል ደግሞ አንድ ተቋም ሲሆን ያ ተቋም የራሱ የሆነ ቪዥን እና ሚሽን ያለው እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ የዚህም ውጤት በትዳር አለም በእቅድ የተወሰኑ ልጆችን ወልዶ አስተምሮ እና አንጾ በማሳደግ ለሀገር ብቁ ዜጋን ማስረከብ ነው። በቀጣይም የመልካም ዜጋ መተካካት በሀገር ላይ እንዲፈጠርና ወገን እንዲጠቀም ...ሀገር እንድታድግ የሚያስችል አካሄድ ነው፡፡
“የጀበና ሙሽሮች” የቡናና የኪነጥበብ ፌስቲቫል ተከፈተ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከልና ኤልሰን ፕሮሞሽን በመተባበር ያዘጋጁት “የጀበና ሙሽሮች” የተሰኘ የቡናና የኪነጥበብ ፌስቲቫል በትላንትናው እለት በብሔራዊ ቴአትር የተከፈተ ሲሆን ፌስቲቫሉ እስከ ነገ እንደሚቆይም ታውቋል፡፡ የተለያዩ ክልሎች የቡና አፈላል ስርዓታቸውን ከነ አቀራረቡና ሙሉ ስርዓቱ ወክለው በተገኙበት በዚህ ፌስቲቫል ላይ የኢፌድሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ሰኢድ እና የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክቡር ዶ/ር ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡ “”ቡና ከእለት የእለት ህይወታችን ጋር የተገናኘ ቢሆንም በደንብ አናውቀውም፤ ይህን ቡና ለራሳችን በደንብ ለማስተዋወቅ ታስቦ የተዘጋጀ ፌስቲቫል ነው” ብሏል - ፕሮሞተር ዮናስ ታደሰ፡፡ በአሜሪካ የአቦል ቡናና የመርካቶ ገበያ መስራች የሆኑት አቶ ታምሩ ደገፋና ከፈረንሳይ የመጡት ወ/ሮ አለም ፀሐይ ንባብ፤ የኢትዮጵያን ቡና በያሉበት እንዴት እንደሚያስተዋውቁ በፌስቲቫሉ መክፈቻ የገለፁ ሲሆን፤ አቶ ታምሩ ደገፋ በአሜሪካ ለታዋቂው ሙዚቀኛ ለማይክል ጃክሰን በአንድ ወቅት ስለ ኢትዮጵያ ቡና ሰፊ ማብራሪያ እንዳደረጉለት ተናግረዋል፡፡ ፌስቲቫሉ እስከ ነገ የሚቆይ ሲሆን የአማራ፣ የትግሬ፣ የኦሮሞ፣ የጉራጌና የሌሎች ብሔሮች የቡና ስርዓት ለእይታ ቀርቦ እየተጐበኘ ነው፡፡