Administrator

Administrator

ቅሬታቸውን ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሓላፊዎች ገልጸዋል

የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ በኾኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የቤተ ክርስቲያኒቱን እምነትና ሥርዐት እንዲማሩ፣ ዕውቀታቸውንና ገንዘባቸውን በማቀናጀት ሞያዊ ድጋፍ እንዲያበረክቱ በማስተባበር ላይ የሚገኘውን ማኅበረ ቅዱሳንን በአሸባሪነት በመፈረጅ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ አማካይነት ጠቅላላ ሀብቱና ንብረቱ የሚታገድበት ውሳኔ እንዲተላለፍ በመንግሥትም በኩል እርምትና ርምጃ እንዲወሰድበት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የአድባራት አስተዳዳሪዎች መግለጫ አውጥተውበታል በተባለው ስብሰባ ጉዳይ ኹለት የቅ/ሲኖዶስ አባላት ለከፍተኛ የመንግሥት ሓላፊዎች ቅሬታቸውን ማሰማታቸው ተገለጸ፡፡
የቅ/ሲኖዶሱን ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስንና በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና የጅማ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን በስም የጠቀሱት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች፣ ሊቃነ ጳጳሳቱ ቅሬታቸውን ያቀረቡት ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሓላፊዎች እንደኾነ ቢገልጹም የሓላፊዎቹን ስም ከማሳወቅ ተቆጥበዋል።
ቤተ ክርስቲያኒቱ በፀረ ሙስናና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ከመንግሥት ጋራ የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት በቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መወሰኗን ሊቃነ ጳጳሳቱ አስታውሰው፣ በዚህም መሠረት ለሙስናና ብክነት የተጋለጡ አሠራሮችን ለማረምና ለማስተካከል ጥረት እያደረገች ቢኾንም ባለሥልጣናቱ ከማን ጋር መሥራት እንዳለባቸው በትክክል አለመለየታቸውንና ግንኙነቱም ሙሰኞችን በአይዟችኹ ባይነት የሚያበረታታ እንደኾነ መናገራቸው ተጠቅሷል፡፡
ሊቃነ ጳጳሳቱ ቅሬታቸውን በዚህ መልኩ ለባለሥልጣናቱ ለማቅረብ ያስገደዳቸው የአድባራት አስተዳዳሪዎቹ፣ ‹‹ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን ለአድማ ያነሣሣል፤ በሀገርና በቤተ ክርስቲያን ላይ ሁከትና ሽብር እንዲፈጠርና ሰላም እንዲደፈርስ ያደርጋል›› ባሉት በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የሚወሰደው አስተዳደራዊ ርምጃ በፀረ ሽብር ሕጉ መሠረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቁበት መግለጫቸው ነው፡፡
የመንግሥት የተለመደ እገዛ እንዳላቸው በአጽንዖት የጠቀሱት አስተዳዳሪዎቹ በዚሁ መግለጫቸው፣ መንግሥት በፀረ ሽብር ሕጉ ታሳቢነት ገለልተኛ ኦዲተር መድቦ በማኅበሩ ላይ የሀብትና ንብረት ቁጥጥር የማካሔድ ድጋፉ እንዳይለያቸው ያስተላለፉት ጥሪ በሌላቸው ሕጋዊነትና ውክልና የቀረበ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በራስዋ መንገድ ማከናወን በሚገባት ተግባር ላይ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነትን የሚጋብዝና ለውጭ ተጽዕኖ አሳልፎ የሚሰጥ እንደኾነ ተመልክቷል፡፡
በመንበረ ፓትርያርኩ ከተገኙት የመንግሥት ሓላፊዎች ጋራ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ እንደተካሔደ በተገለጸው የኹለትዮሽ ውይይት፣ ማኅበረ ቅዱሳንን በመቃወም ሰበብ የወጣው የአስተዳዳሪዎቹ መግለጫ ዋነኛ ዓላማ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ወስና የምታካሒደውን የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ሒደት መጋፋት ነው ተብሏል፡፡  መላውን የሀገረ ስብከቱን አድባራት አገልጋዮች  ለመወከል የማይበቁ ጥቂት ግለሰቦችን በመያዝ ይደረጋል የተባለው ይኸው እንቅስቃሴም ‹‹የት እንደሚያደርስ እናየዋለን›› የሚሉ ንግግሮች ጭምር ከሊቃነ ጳጳሳቱ የተሰሙበት እንደነበር ምንጮቹ አስታውቀዋል፤ ጉዳዩም በመጪው ግንቦት በሚካሔደው የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ዓቢይ መነጋገርያ መኾኑ እንደማይቀር ተጠቁሟል፡፡
ከሀገረ ስብከቱ አድባራት የተውጣጡ ናቸው የተባሉ አስተዳዳሪዎች ያደረጉት ስብሰባ፣ አስተባባሪዎቹ ከፓትርያርኩ ተሰጥቶናል ከሚሉት ፈቃድ በቀር በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ዘንድ በይፋ የታወቀና የተፈቀደ እንዳልነበረ ምንጮቹ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳንን በሁከትና ሽብር ለሚከሱ በቂ ሕጋዊነትና ውክልና የላቸውም ለተባሉ አካላት ፓትርያርኩ የሰጡትን የስብሰባ ፈቃድ፣ በቅርቡ ማኀበሩ አገር አቀፍ የአብነት መምህራን የምክክር ጉባኤ  እንዳያካሒድ ከተጣለበት እገዳ ጋር ያነፃፀሩ ታዛቢዎች፣ ሁኔታው የፓትርያርኩን ርምጃዎች መርሕ አልባነት የሚያጋልጥ ነው ይላሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር መተዳደርያ ደንብ ያለውና ግልጽ ተልእኮ ይዞ የሚንቀሳቀሰው ማኅበር፣ህልውናና አገልግሎት በግልጽ አስተዳደራዊ ጫና ውስጥ መግባቱን  እንደሚያመለክት ታዛቢዎቹ ያምናሉ፡፡
ከመዋቅር፣ ከሀብትና ንብረት ቁጥጥር ጋራ በተያያዘ በማኅበሩ ላይ የሚቀርቡት ውንጀላዎች፣ በፀረ አክራሪነት ስም የሚናፈስበትን ፕሮፓጋንዳ በማጠናከር ፖሊቲካዊ ርምጃ እንዲወሰድበት ፍላጎት ያላቸውን አካላት ምኞት በጉልሕ እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡ ማኅበሩ ሃይማኖቱን የሚጠብቅ፣ ቤተ ክርስቲያኑን የሚከባከብና ሀገሩን የሚወድ ብቁ ዜጋ ለማፍራት ያለውን ዓላማ የሚረዱ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ምእመናንና የመንግሥት አካላትም የተቃዋሚዎቹን አቋምና መግለጫ በጥንቃቄ እንዲመለከቱትም አሳስበዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖናና ትውፊት ውጭ ነው በተባለ የሌላ እምነት አስተምህሮ የተነሳ  በኮሌጁ ደቀ መዛሙርት መካከልና በደቀ መዛሙርቱ ምክር ቤት አባላት ውስጥ ያለው ግንኙነት ውጥረት ውስጥ እንደገባ እየተገለጸ ነው፡፡
ከኮሌጁ ውጭ ከሚገኙና በቅ/ሲኖዶስ ከተወገዙ ግለሰቦችና ቡድኖች ጋር የዓላማና የጥቅም ግንኙነት መሥርተዋል በተባሉ ጥቂት ደቀ መዛሙርት አማካይነት በኮሌጁ ውስጥ ከመንጸባረቅ አልፎ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ነው የተባለው ይኸው አስተምህሮ፣ አስተዳደራዊ መፍትሔ እንዲበጅለት የደቀ መዛሙርቱ ምክር ቤት ጥር 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ለኮሌጁ አስተዳደር ያቀረበው ጥያቄ እስከ አሁን ምላሽ አለማግኘቱ  ውጥረቱን የበለጠ እንዳባባሰው ለአዲስ አድማስ የደረሰው መረጃ አመልክቷል፡፡
የአስተምህሮው ውዝግብ አፋጣኝ መፍትሔ አለማግኘቱ ከደቀ መዛሙርቱ አልፎ የምክር ቤት አባላትን ለሁለት እንደከፈለ ተገልጧል፡፡ ኮሌጁንና ደቀ መዛሙርቱን በቅንነትና በትጋት ለማገልገል በደቀ መዛሙርቱ ጠቅላላ ጉባኤ የተመረጠውና ከፍተኛ ሓላፊነት የተጣለበት የደቀ መዛሙርቱ ምክር ቤት፣ ‹‹ከልማቱ ጥፋቱ አመዝኗል›› ያሉት ጸሐፊውና አንድ የአመራር አባሉም ራሳቸውን ማግለላቸው ታውቋል፡፡
‹‹ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖናና ትውፊት ውጭ የኾነ የኑፋቄ ትምህርት ሲዘራ ድምፀ ተዓቅቦ ከማድረግ ባሻገር ችግር አለባቸው ከሚባሉት ደቀ መዛሙርት ጎን ተሰልፈው ኮሌጁንም ኾነ ሓላፊነት የሰጠንን ደቀ መዝሙር በቅንነት እንዳናገለግል የአንዳንድ መማክርት አባላት ተግባር አውኮናል›› ያሉት ሁለቱ አባላት፤ በዚህ ሳምንት ለኮሌጁ ዋና ዲን ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ፣ ምክር ቤቱ የችግሩ ተባባሪ በመኾኑ ከሓላፊነቱ ታግዶ ጉዳዩ እንዲጣራና እምነታቸውና ሥነ ምግባራቸው በተመሰከረላቸው ደቀ መዛሙርት እንዲተካ ጠይቀዋል፡፡
‹‹የቤተ ክርስቲያንን እንጀራ እየበሉ፣ በጀቷን አውጥታ እያስተማረቻቸው የሌላ እምነት የሚያራምዱ›› ያሏቸውን ወገኖች አጥብቀው እንደሚቃወሙ የገለጹ የደቀ መዛሙርት ተወካዮች በበኩላቸው፣ ኮሌጁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖናና ትውፊት ለመጠበቅና ለማስፋፋት የቆመ  በመኾኑ አስተዳደሩ፣ በቃል፣ በድምፅና በጽሑፍ የሚቀርቡለትን ማስረጃዎች መርምሮ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል፡፡

          ለችግር የተጋለጡ ህፃናትን እና በለጋ እድሜያቸው ተደፍረው ወይም ተገደው የልጅ እናት የሆኑ ሴቶችን ለመርዳትና የተሻለ ህይወት እንዲኖራቸው ለማድረግ ታስቦ ከሁለት ዓመታት በፊት የተቋቋመው መሠረት የበጎ አድራጎት ድርጅት በድርጅቱ የበጎ ፍቃድ አገልጋዮች ተነሳሽነት “በጎ ፍቃደኝነት” የሚል መሪ ቃል ያነገበ ልዩ ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ሊያካሂድ ነው፡፡
መጋቢት 21/2006 ዓ.ም በሐርመኒ ሆቴል በሚካሄደው በዚሁ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ባለሀብቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የድርጅቱ ድጋፍ ሰጪ አካላትና ሌሎች የድርጅቱ አጋሮች እንደሚገኙበት አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡
“እኛው ለእኛው በእኛው” በሚል መሪ ቃል እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኘው ይኸው ድርጅት ምንም አይነት ቋሚ የገቢ ምንጭ ሳይኖረው ጠንካራ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 280 ህፃናትንና 125 ሴቶችን በመርዳት ላይ የሚገኝ ድርጅት እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ህብረተሰቡ የህፃናቱን እና የሴቶችን ህይወት ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ በሚደረገው እንቅስቃሴ ያለውን በመለገስ ሃላፊነቱን እንዲወጣ የድርጅቱ መስራች እና ዳይሬክተር ወ/ሮ መሰረት አዛገ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

       ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው ለማረሚያ ቤቶች የሚውል መፃሕፍት ማሰባሰብ ዛሬ ይጀመራል፡፡ ለቀጣዮቹ 30 ቀናት በሚቆየው የመፃሕፍት ማሰባሰብ ሥራ መጽሐፍ መለገስ የሚፈልጉ ፈቃደኞች በተመረጡ ቦታዎች እንዲያስቀምጡ በጎ ፈቃደኛዋ ጥሪ አድርጋለ ች፡፡ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል፣ ብሄራዊ ቴአትር ጀርባ የሚገኘው ጃፋር መጽሐፍ መደብር፣ ሜጋ መጽሐፍት መደብር ቢሮ እና ፒያሳ እናት ህንፃ ፊት ለፊት የሚገኘው አብዲ መጸሐፍ መደብር መጽሐፎቹን ለማስቀመጥ የተመረጡ ቦታዎች እንደሆኑ ነርስ ሊንዳ በቀለ ገልፃለች። በ2004 ዓ.ም ብሄራዊ ቴአትር መግቢያው መጽሐፍ የሆነ ፕሮግራም አዘጋጅታ ወደ ሶስት ሺህ ያህል መጽሐፍትን በመሰብሰብ ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዳስገባች የገለፀችው በጎ ፈቃደኛዋ፤ በ2005 ዓ.ም ከኅብረተሰቡ ገንዘብ በማሰባሰብ ጋሞ አካባቢ ለሚገኙ የገጠር ት/ ቤቶች የመማሪያ መጽሐፍትን በቅናሽ በመግዛት ማስረከቧን ተናግራለች፡፡ ዘንድሮም በጎ ፈቃደኞች የሚለግሷቸውን መጸሐፍት ለቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንደምታስረክብ ገልፃ፤ ሁሉም ሰው ካለው መጽሐፍ ላይ እንዲለግስ ጥሪ አቅርባለች፡፡ በጎ ፈቃደኛዋ በየዓመቱ የምታካሂደውን የመጽሐፍ ማሰባሰብ ሥራ “መጽሐፍት ለሁሉም በሁሉም ስፍራ” በሚል መርህ እንደምታከናውንም ጨምራ ገልፃለች፡፡

በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር እና በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ትብብር የመፅሀፍ አውደርዕይ መዘጋጀቱን የደራሲያን ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ገ/ክርስቶስ ሃ/ሥላሴ አስታወቁ፡፡ አውደርዕዩ ከመጋቢት 15 እስከ 21/2006 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን ከዳግማዊ ምኒሊክ ት/ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው ቦታ ላይ እንደሚካሄድም ተገልጿል፡፡ በአውደ ርዕዩ ላይ መጽሐፍት በታላቅ ቅናሽ ለሽያጭ እንደሚቀርቡ የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ የአውደርዕዩ መክፈቻ እለት ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በብሄራዊ ሙዚየም አዳራሽ በርካታ ደራሲያንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት “በርናባስ” በተሰኘ ልብወለድ መጽሐፍ ላይ ሂሳዊ ውይይት ይካሄዳል ተብሏል።

በደራሲ ለማ ደገፋ የተፃፉት “ከመሩ አይቀር”፣ “ካደጉ አይቀር”፣ “ጂሩፍ ጂሬኛ” እና “የህይወት ውቅር” መፃሕፍት ዛሬ ረፋድ ላይ በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል እንደሚመረቁ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አስታወቀ፡፡ “ካደጉ አይቀር” የተሰኘው ባለ 220 ገፅ መጽሐፍ የሰውን አዕምሮ በማልማት የሚገኝ ትሩፋት ላይ የሚያተኩር ሲሆን “ከመሩ አይቀር” የአመራርን ምንነት፣ የመሪን ማንነትና የመሪ ተግባራትን በማንሳት ትንታኔ ይሰጣል ተብሏል፡፡ መጽሀፉ 145 ገፆች እንዳሉትም ታውቋል፡፡ “የህይወት ውቅር” የተሰኘው የለማ ደገፋ ሶስተኛ ተመራቂ መጽሐፍ፤ 316 ገፆች ያሉት ሲሆን ስለመንፈሳዊ ህይወት የሚገደው የትኛውም ሰው የሚማርበትና መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት በማድረግ የተሰናዳ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ “ጂሩፍ ጂሬኛ” የተሰኘው መጽሐፍ 367 ገፆች እንዳሉትም የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በደራሲ ገስጥ ተጫኔ እና በቀድሞው የኢትዮጵያ ምድር ጦር ሰራዊት ወታደሮችና ሲቪል ማህበራት ትብብር የተዘጋጀው “የቀድሞው ጦር” የተሰኘ የታሪክ መፅሐፍ ዛሬ ይመረቃል፡፡ የመጽሀፍ ምርቃቱ ዛሬ ጠዋት በዮርዳኖስ ሆቴል የሚከናወን ሲሆን 747 ገፆች እንዳሉትና በ250 ብር ለገበያ እንደቀረበ ደራሲ ገስጥ ተጫኔ ተናግረዋል፡፡ “የቀድሞው ጦር” ለደራሲው ዘጠነኛ መፅሀፋቸው ሲሆን ከዚህ በፊት “የናቅፋው ደብዳቤ”፣ “እናት አገር”፣ “የፍቅር ቃንዛ”፣ “ነበር” ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት፣ የማክዳ ንውዘትና ሌሎችንም ለአንባቢያን አድርሰዋል፡፡

“የሎሚ ሽታ” ፊልም ፕሮዱዩሰር የሆነው ማቭሪክ ፕሮሞሽን፤ ከኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጋር በመሆን በኢቴቪ 3 “ማቭሪክ ፊልሞች የኢትዮጵያ” የተሰኘ የአማርኛ ፊልሞች ብቻ የሚታዩበት ፕሮግራም ጀመረ፡፡
“ፊደል አዳኝ” በሚለው ፊልም ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የጀመረው ፕሮግራሙ፤ በየሳምንቱ ቅዳሜ ከ4፡30 እስከ 6፡30 የሚተላለፍ ሲሆን ሰኞ በተመሳሳይ ሰዓት በድጋሚ ይቀርባል፡፡ የማቭሪክ ፕሮሞሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ፌቨን ታደሰ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ከዚህ ቀደም የውጭ ሃገር ፊልሞች የሚታዩበትን “ታላቁ ፊልም”ን መነሻ ያደረገው ፕሮግራማቸው፤ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ 10 ያህል የአማርኛ ፊልሞችን ካቀረበ በኋላ ባለሙያዎች በሚሰጡት የግምገማ ውጤት መሰረት አሸናፊው ፊልም ይሸለማል። በፕሮግራሙ የሚቀርቡ ሁሉም ፊልሞች፣ የሲኒማ ቤት የዕይታ ጊዜያቸውን ጨርሰው የወረዱ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሸንቁጥ አየለ የተጻፈው “ህቡዕ ጣት” የተሰኘ ልቦለድ መፅሀፍ ለንባብ በቃ፡፡ ሃሳቡን በማብላላት እና የወቅቱን ሁኔታ ለማገናዘብ ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደው መፅሀፉ፤ 206 ገፆች ያሉት ሲሆን በአህጉራዊና አገራዊ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን እንደሆነና በተለይም የኢትዮጵያን ውስጣዊ ልዩነት በዙሪያዋ ያሉ ጠላቶቿ እንደ መሳሪያ በመጠቀም የራሳቸውን አላማ ሊያሳኩ የሚታትሩበትን ሁኔታ ያስቃኛል ተብሏል፡፡ በ45 ብር ለገበያ የቀረበው መፅሀፉ፤ የደራሲው ሁለተኛ ሥራ ሲሆን ከዚህ ቀደም “የተስፋ ክንፍ” የተሰኘ መፅሐፍ እና መቼቱን ባህርዳር ያደረገ “ማዕበል” የተሰኘ ፊልም በመፃፍና በመተወን ለእይታ አብቅቷል፡፡

ሚዩዚክ ሜይ ደይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ባሳተመው “የኮሌጅ ቀን ግጥሞች” መጽሓፍ ላይ ነገ ከቀኑ 8 ሰዓት ውይይት ሊያደርግበት መሆኑን አስታወቀ፡፡ ሬድዮ ፋና አካባቢ በሚገኘው ብሔራዊ ቤተ መፃሕፍት የሚካሄደውን የሦሥት ሰዓታት ሥነጽሑፋዊ ውይይት የመኘሻ ሃሳብ በማቅረብ የሚመሩት የሥነጽሑፍ ባለሙያው አቶ ገዛኸኝ ፀጋው ናቸው፡፡

          የዋልያዎቹን  ዋና አሰልጣኝ ለመቅጠር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የተከተለው የአሰራር ሂደት ከዓለም አቀፍ ልምዶች አንፃር እንደዘገየ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በብዙ የዓለም አገራት የብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኞች ቅጥር ቢያንስ በ4 ቢበዛ በ5 ሳምንታት ውስጥ የሚፈፀም ቢሆንም ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሚሆን ዋና አሰልጣኝ አፈላልጎ ለመቅጠር እስካሁን 8 ሳምንታት ቢያልፉም ሂደቱ አልተጠናቀቀም፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለዋና አሰልጣኙ ቅጥር  ካወጣው ማስታወቂያ  በኋላ ለሁለት ሳምንት   ምዝገባ ተካሂዶ ከመላው ዓለም 27 አሰልጣኞች ያመለከቱ ሲሆን የስም ዝርዝራቸውና ዜግነታቸው ከሳምንት በፊት ታውቋል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በመስፈርቶቹ 27ቱን አሰልጣኞች በማወዳደር ሲሰራ 1 ሳምንት ያለፈው ሲሆን የመጨረሻ እጩዎችን  ማንነትና ብዛታቸውን አልገለፀም፡፡  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን የሚረከበው አዲሱ አሰልጣኝ መቼ  እንደሚታወቅ ፤  የቅጥሩ  ውል እንዴት እና መቼ እንደሚፈፀም፤ ለምን ያህል ግዜ በሃላፊነቱ እንደሚቆይ፤ ምን ያህል ወርሃዊ ደሞዝ እንደሚከፈለውና ፌደሬሽኑ ክፍያውን እንዴት ሊከፍል እንዳሰበም በይፋ የታወቀ ነገር የለም፡፡
የፌደሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ከሳምንት በፊት ለመገናኛ ብዙሃናት በላከው መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ለማሰልጠን ፍላጎት ያሳዩ አሰልጣኞች ከመላው ዓለም ከሚገኙ 15 አገራት የተሰባሰቡ ናቸው ፡፡  ከፈረንሳይ፣ ከጀርመን፣ ከቤልጅዬም፣ከቱርክ፣ ከቦስኒያ፣ ከስፔን እና ከቡልጋርያ ከእያንዳንዳቸው አንድ አሰልጣኝ፤ ከጣሊያን፣ከኢትዮጵያ፣ ከስዊድን፣ ከሆላንድ፣ ከሰርቢያ፣ ከፖርቱጋል፣ ከብራዚል እና ከሮማኒያ ከእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት አሰልጣኞች እንዲሁም ከአርጀንቲና ሶስት አሰልጣኞች አመልክተዋል፡፡ እነዚህ አመልካች 27  አሰልጣኞች  በቅጥሩ ለመወዳደር ለፌደሬሽኑ ያስገቡት የስራ ልምድ እና ብቃትን በዝርዝር ባይገለፅም በእግር ኳስ ዙርያ መረጃ በሚገኝባቸው ድረገፆች ስለ ስራ ታሪካቸው ብዙ እውቅና ያላቸው ገሚሱ ናቸው፡፡  ስለ አሰልጣኞቹ መረጃ ማግኘት የተቻለው አንዳንዶቹ በኢትዮጵያ ከመስራታቸው በተያያዘ፤ አንዳንዶቹ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በክለብ እና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ስላላቸው የስራ ልምድ በተለያዩ ድረገፆች ግለታሪካቸው ተፅፎ በመገኘቱ ነው፡፡  ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ክለቦችን በማሰልጠን ልምድ ኖሯቸው ለዋናው ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ማመልከቻ ያስገቡት የደደደቢት አሰልጣኝ የነበሩት የቱርኩ ሜሜት ታይፉን እና አሁን የመብራት ኃይል ክለብ አሰልጣኝ ሆነው የሚሰሩት የቡልጋርያው ሎርዳን ስቶይኮች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን አሰልጥነው የሚያውቁት እና በድጋሚ ቡድኑን ለመረከብ ያመለከቱት ደግሞ የጣሊያኑ ዲያጎ ጋርዚያቶ እና የቤልጅዬሙ ቶም ሴንትፌይት ናቸው፡፡ ቤልጅማዊው ቶም ሴንትፌይት ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ቅጥር ሳይፈፀምላቸው ለሙከራ እንዳሰለጠኑ የሚታወስ ሲሆን አሁን ብሄራዊ ቡድኑን ለመረከብ ከሁሉም ቀድመው ፍላጎታቸውን በሱፕር ስፖርት በመግለፅ የሚጠቀሱ ሆነዋል፡፡
የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት መግለጫ  እንዳመለከተው የቅጥር ማመልከቻቸውን ካቀረቡት 27 እጩ አሰልጣኞች መካከል ኢትዮጵያዊያን የሆኑት ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ የመጀመርያው ከ3 የውድድር ዘመናት  በፊት በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ አሰልጣኝነት  የፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው እና አሁን በሱዳኑ ክለብ አልሃሊ ሼንዲ በረዳት አሰልጣኝነት በመስራት ላይ የሚገኘው ውበቱ አባተ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ አስቀድሞ በስኮትላንዳዊው ኢፌም ኦኑራ የዋና አሰልጣኝነት ዘመን  የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የፉትቦል ዲያሬክተር ሆኖ የሰራውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የአሰልጣኝነት ትምህርት የተከታተለው ዮሃንስ ተሰማ ናቸው፡፡  በአውሮፓ ታዋቂ ክለቦች ተሰልፈው ውጤታማ ከመሆን አልፈው በአውሮፓ፣ በአፍሪካና፣ በእስያ የሚገኙ ብሔራዊና ወጣት ቡድኖችን እንዲሁም ክለቦችን በማሰልጠን ለሻምፒዮንነት ክብር የበቁ ሙያተኞች  እንዳመለከቱ የገለፀው የፌደሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት ክፍል ፤ ብሄራዊ ቡድኑን ተረክቦ ለውጤት ለማብቃት ያላቸውን ፍላጎት በተለያያ መንገድ መግለፃቸው የሚያበረታታ ነው ብሏል፡፡ ከእጩ አሰልጣኞቹ መካከል ከ30 ዓመታት በላይ የማሰልጠን ልምድ ያላቸው፤ በዓለም አቀፍ ውድድሮች አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡ እንደሚገኙበት የተገለፀ ሲሆን የጥቂቶቹ የትምህርት ዝግጅት በዲፕሎማ ከመወሰኑ በስተቀር አብዛኞቹ ከመጀመሪያ ዲግሪ በላይ ያላቸው፤ በአውሮፓው እግር ኳስ ማህበር የመጀመሪያ ደረጃ የአሰልጣኝነት ብቃት ማረጋገጫ የያዙና የፕሮፌሰርና የኢንስትራክተርነት ማዕረግ የተሰጣቸው ሙያተኞች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡  
የእግር ኳስ ፌደሬሽን ብሄራዊ ቡድኑን  ባለፈው 2 ዓመት ከ6 ወር በዋና አሰልጣኝነት የመሩትን ሰውነት ቢሻው  በተሻለ ለመተካትና ለውጥ ለመፍጠር በሚል ካሰናበተ ሁለት ወር ቢሆነውም በምትክነት ለመቀጠር ማመልከቻ ካስገቡት 27 አሰልጣኞች በስራ ልምዳቸው አለመሻላቸውን ለመረዳት አያዳግትም፡፡ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን  ከ31 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈ፤ ለ20ኛው ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ለሚደረገው የመጨረሻ ማጣርያ ምእራፍ ለመገባት ከበቁ 10 የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች አንዱ ለመሆን የበቃ፤ በአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ወይም ቻን ውድድር በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈ፤ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ከዓመቱ ምርጥ ሶስት ብሄራዊ ቡድኖች አንዱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡  
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በሃላፊነት ለመረከብ ካመለከቱት 27ቱ አሰልጣኞች መካከል ስፖርት አድማስ የተወሰኑትን ለማስተዋወቅ ከዚህ በታች ያለውን አጭር መግለጫ አቅርቧል፡፡ እነዚህን አስር 10 አሰልጣኞች ለስፖርት አፍቃሪው ማስተዋወቅ የተቻለው ስለባለሙያዎቹ የሚገልፁ በቂ መረጃዎችን በተለያዩ ድረገፆች  በማፈላለግ ማግኘት ስለተቻለ ነው፡፡


ፋቢዮ ሎፔዝ የ50 ዓመት ጣሊያናዊ ናቸው። በትልልቆቹ የጣሊያን ሴሪኤ ክለቦች አትላንታና ፌዬሬንቲና በአማካሪነት አገልግለዋል፡፡ ከ2007 እ.ኤ.አ ጀምሮ ለ6 የውድድር ዘመናት ከ6 በላይ የዝቅተኛ ሊግ ክለቦችን ያሰለጠኑ ሲሆን በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ብዙም ልምድ የላቸውም፡፡


ሃንስ ሚሸል እድሜያቸው 49  ሲሆን በዜግነታቸው ጀርመናዊ ናቸው፡፡ በተጨዋችነት ዘመናቸው ግብ ጠባቂ ነበሩ፡፡ ከ2001 እ.ኤ.አ ጀምሮ ወደ ማሰልጠን ስራ ገብተዋል፡፡ በአሰልጣኝነት ስራ ዘመናቸው በቻይና ሀ-20 ቡድን ረዳት አሰልጣኝ፣ ከ2007 እ.ኤ.አ ጀምሮ ለ3 ዓመት በሩዋንዳ  እግር ኳስ ፌደሬሽን የቴክኒክ ዲያሬክተር፣ በ2011 የፊልፒንስ ሀ-25 ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ ሆነው ከተቀጠሩ በኋላ አድገው ባለፉት 3 ዓመታት ደግሞ የዋናው ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ነበሩ፡፡ በስፖርት ሳይንስና በማኔጅመንት ባችለር ዲግሪ ያላቸው ሲሆን በታላላቆቹ የዓለማችን ክለቦች ሪያል ማድሪድ፣ አርሰናል፣ ካይዘስላውተርን፤ ሪቨር ፕሌት ሌሎችም  በአሰልጣኝነት የስራ ልምምድ በመስራት አስደናቂ ልምድ አላቸው፡፡



ዲያጐ ጋርዚያቶ በትውልድ ፈረንሳዊ ቢሆኑም በዜግነት ጣሊያናዊ ናቸው፡፡ አሁን የ64 ዓመት አዛውንት የሆኑት እኝህ አሰልጣኝ በተጨዋችነት ዘመናቸው የተከላካይ መስመር ተሰላፊ ነበሩ፡፡ ከ1984 እ.ኤ.አ ጀምሮ በአሰልጣኝነት ማገልገል ሲጀምሩ የፈረንሳይ ዝቅተኛ ሊግ ክለቦችን ሲያሰለጥኑ ቆይተው ትልቁን ኃላፊነት የተረከቡት በ2001 እ.ኤ.አ ላይ የኢትዮጵያ ሀ 20 ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆነው ሲመደቡ ነበር። በዚሁ ጊዜም የኢትዮጵያን ወጣት ቡድን በአርጀንቲና ለተደረገው 14ኛው የዓለም ወጣቶች ዋንጫ እንዲሳተፍ አብቅተዋል። የኢትዮጵያ ሀ-20 ቡድን ዋና አሰልጣኝነት ከለቀቁ በኋላ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በክለብ ደረጃ ሲሰሩ ቆይተው በ2007 እ.ኤ.አ ላይ የቶጐ ብሔራዊ ቡድን ተረክበው ነበር፡፡ በቶጎ አሰልጣኝነት የቆዩት ግን ለ2 ወራት የስራ ጊዜ ነበር፡፡ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ትልቅ ውጤት በማስመዝገብ የተደነቁ ሲሆን ለሁለት ጊዜያት ያሰለጠኑትን የዲ ሪፖብሊክ ኮንጎውን ቲፒ ማዜምቤ  በ2009 እ.ኤ.አ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ እንዲያሸንፍ አድርገዋል፡፡ በ2012 እ.ኤ.አ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮትጵያ ተመልሰው በነበረ ጊዜ ዋና ብሔራዊ ቡድኑን በሃላፊነት ቢይዙም በአወዛጋቢ ሁኔታዎች ቢይዙም ከ2 ወራት በኋላ ተሰናብተዋል፡፡



ኤርኒስት ብራንድተስ የ58 ዓመቱ ሆላንዳዊ በተጨዋችነት ዘመናቸው የተከላካይ መስመር ተሰላፊ ነበሩ፡፡ በሆላንድ ብሔራዊ ቡድን ከ1977 -85 እኤአ በመጫወት ልምድ ከማግኘታቸውም በላይ በ1978 እ.ኤ.አ ላይ አርጀንቲና ባስተናገደችው ዓለም ዋንጫ ለመጫወት የበቁ ናቸው፡፡ ከ1993 እ.ኤ.አ ወዲህ በአሰልጣኝነት ማገልገል የጀመሩ ሲሆን በተለይ በትልቁ የሆላንድ ክለብ ፒኤስቪ አይንድሆቨን በረዳት አሰልጣኝነት ለ9 ዓመታት ሰርተዋል፡፡ በአፍሪካ ደረጃ የተወሰነ የስራ ልምድ ያላቸው ሲሆን ለ2 ዓመታት የሩዋንዳውን ክለብ ኤፒአር ካሰለጠኑ በኋላ ባለፈው ዓመት ደግሞ የታንዛኒያው ክለብ ያንግ አፍሪካንስ አሰልጥነው ነበር፡፡


ዞራን ፍሊፖቪች የ69 ዓመቱ ፖርቱጋላዊ አሰልጣኝ ናቸው፡፡ በተጨዋችነት ዘመናቸው ከሚጠቀስ ታሪካቸው ከ1970-78 በዩጎዝላቪያ ብሄራዊ ቡድን የአጥቂ መስመር ተሰላፊ ሆነው ማሳለፋቸው ነው። በአሰልጣኝነት ስራ የጀመሩት በ1988 እ.ኤ.አ ጀምሮ ሲሆን ለ2 ዓመት የፖርቱጋሊ ትልቅ ክለብ ቤነፊካ አሰልጣኝ ሆነው ከመስራታቸው በላይ በ1999 እኤአ በጣሊያኑ ክለብ ሳምፕዶርያም አገልግለዋል።  ከዚያም ተጫውተው ወዳሳለፉበት ታዋቂው ክለብ ስታር ቤልግሬድ በመመለስ ለ3 ዓመት በአሰልጣኝነት አገልግለው በ2007 እ.ኤ.አ  የሞንቴኔግሮ ቡድንን በመምራት  ለ2 ዓመት አገልገለው ከዚያ ወዲህ  ስራፈት ናቸው፡፡

ጐራን ስቴቫኖቪች የ47 ዓመቱ ሰርቢያዊ በተጨዋችነት ዘመናቸው የአማካይ መስመር ተሰላፊ ነበሩ፡፡ ከ1983 ጀምሮ ለስምንት አታመት ለፓርቴዝያን ቤልግሬድ የተጫወቱ ሲሆን በ1985 እ.ኤ.አ የዩጐዝላቪያ ብሔራዊ ቡድን አባል ነበሩ፡፡ ከ2001 እ.ኤ.አ ወዲህ በአሰልጣኝነት መስራት ጀምረው ከ2003-2006 እ.ኤ.አ የሰርቢያና ሞንቴኔግሮ ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ ሆነው ካገለገሉ በኋላ በ2009 እ.ኤ.አ ላይ በቀድሞ ክለባቸው ፓርቴዝያን ቤልግሬድ ረዳት አሰልጣኝ ሆነው ተቀጥረዋል፡፡ በ2013 ደግሞ በዚሁ ክለብ ዋና አሰልጣኝ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በአፍሪካ ልምድ ያላቸው ሲሆን በ2011 እ.ኤ.አ ላይ የጋና ብሔራዊ ቡድንን ለማሰልጠን በደቡብ አፍሪካ በተደረገው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፈዋል፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን የቻይና ሱፕር ሊግ ክለብ በሃላፊነት ተረከበው የነበረ ቢሆንም ክለቡ ወደ ዝቅተኛ ሊግ በመውረዱ ተሰናብተው ያለፉትን ወራት ያለ ስራ ቆይተዋል፡፡


ስቴፈን ኮንስታንቲን የ51 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ከ1994 እ.ኤ.አ ጀምሮ ለአሰልጣኝነት እየሰሩ ናቸው፡፡ 4 ብሔራዊ ቡድኖችን ለማሰልጠን ከሌሎቹ አመልካቾች የላቀ ልምድ ያላቸው ሲሆን  በ1999 እ.ኤ.አ ለሁለት ዓመት ኔፓልን፣ ከ2003 ጀምሮ ለ3 ዓመታት ህንድን፣ ከ2007 ጀምሮ ለአንድ ዓመት ማላዊን እንዲሁም በ2011 የሱዳን ብሔራዊ ቡድን በዋና አሰልጣኝነት መርተዋል፡፡ በአሰልጣኝነት የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሮፌሽናል ፍቃድ ያላቸው ሲሆን በስነልቦና እና በአካል ብቃት ስልጠና ምርጥ ተብለው ሁለት ጊዜ የተሸለሙ፤ በምግብ ሳይንስ ዲፕሎማ ያላቸው እና የአሰልጣኞች አሰልጣኝ ተብለው በፊፋ እውቅና ያላቸው ኢንስትራክተር ናቸው፡፡