Administrator

Administrator

Saturday, 14 December 2013 12:39

ስለ ይቅር ባይነት

አባቴ ሆይ፤ የሚሰሩትን ያውቃሉና ይቅር በላቸው፡፡
ካርል ክራዩስ (የኦስትሪያ ፀሐፊ)
ጠላቶችህን ምንጊዜም ይቅር በላቸው፤ ስማቸውን ግን ፈጽሞ እንዳትረሳ፡፡
ሮበርት ኬኔዲ (አሜሪካዊ ፖለቲከኛ)
እኔ ጠላቶቼን ይቅር ማለት አይጠበቅብኝም፤ ሁሉንም ገድዬ ጨርሻቸዋለሁ፡፡
ራሞ ማርያ ናርቫዝ (ስፔናዊ ጄነራልና ፖለቲከኛ)
ታላቅ ሰው የትላንት ጉዳቶቹን እያሰበ አይብከነከንም፡፡
(ዩሪፒደስ (ግሪካዊ ፀሐፌ ተውኔት)
ለቡጢህ ምላሽ የማይሰጠህን ሰው ተጠንቀቀው! እርሱም ይቅር አይልህ፤ ለራስህ ይቅርታ እንድታደርግም አይፈቅድልህ፡፡
ጆርጅ በርናንድ ሾው (አየርላንዳዊ ፀሐፌ ውኔት)
ሌሎችን ተጠያቂ እንደምታደርግ ራስህን ተጠያቂ አድርግ፤ ለራስህ ይቅርታ እንደምታደርግ ሌሎችንም ይቅር በል፡፡  
የቻይናውያን አባባል
ሰው አንዴ ከተፀፀተ በኋላ ጥፋቱን ፈጽሞ አስታስታውሰው፡፡
የሂብሩ አባባል
የፈለገ ቢሆን ከአምስት ዓመት በላይ ሰው ላይ ቂም አልይዝም፡፡  
ዊሊያም ኬኔዲ (አሜሪካዊ ፊልም ፀሐፊናደራሲ)
እግዚአብሔር ይቅር ይበልሽ፤ እኔ ግን ፈጽሞ ይቅር ልልሽ አልችልም፡፡
ቀዳማዊት ኤልዛቤት (እንግሊዛዊት ንግስት)
እውነትን ውደድ፤ ለስህተት ግን ይቅርታ አድርግ፡፡
ቮልቴር (ፈረንሳዊ ፀሐፊና ፈላስፋ)

Saturday, 14 December 2013 12:32

ለቡጊ

በግሬ ጣራ መርገጥ
ሙዚቃ ሲጋልብ መውጣት መውረድ መፍረጥ
ዓይኔን ማገላበጥ
መርበትበት መንቀጥቀጥ
መላጋት መንገድገድ እንደሰከረ ሰው
የናፈቀኝ ይህ ነው፡፡
ተነስቼ ልዝለል
ቡጊ ቡጊ ልበል…
ቡጊ ቡጊ ቡጊ
    ከበሮ ሲያጋፍት ሙዚቃ ሲያናፋ
ልብሴን ጥዬ ልጥፋ
ልራቆት አብጄ
ልብረር ካለም ሄጄ
ሙዚቃ በጥላው ይምጣ ይሸፍነኝ
ሁሉንም ያስረሳኝ፡፡
እንደ እሳት ቦግ ቦግ
መውለብለብ መንተግተግ
መቃጠል መሞት ነው
ይህ ነው፣ ዳንሴ ይህ ነው፡፡
ልቤን ይነሳኛል
ዛር ይሰፍርብኛል
ልወርውር እጆቼን
    ሙዚቃን እንደ ኳስ ልለጋው በግሮቼ
ልዝለል ተነስቼ፤
ቡጊ ቡጊ ልበል
መሬት ልንከባለል
ልዝለል ጮቤ ልምታ
ያቃዠኝ አንዳፍታ፤
ቡጊ ቡጊ ቡጊ
ገብረክርስቶስ ደስታ

የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገነባው ሁለገብ የስፖርት አካዳሚ እና የመወዳደርያ ስፍራ 42 በመቶ መጠናቀቁ ተገለፀ፡፡ ከ530 ማሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚሆንበትን አካዳሚው የሚገነባው አፍሮፅዮን ኮንስትራክሽን ሲሆን አማካሪው ሺጌዝ ኮንሰልታንሲ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው የዘንድሮውን የከፍተኛ ትምህርት የስፖርት ፌስቲቫል በዚሁ ሁለገብ የስፖርት አካዳሚና የመወዳደርያ ስፍራ እንደሚያስተናግድም ታውቋል፡፡ የስፖርት ፌስቲቫሉ ከመጀመሩ 10 ቀናት ቀናት ቀደም ብሎ የአካዳሚው የመጀመርያው የግንባታ ደረጃ ይጠናቀቃል፡፡ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዓመታዊ የስፖርት ፌስቲቫል ከየካቲት 1 እስከ 16 ሲከናወን ድረስ 34 ዩኒቨርስቲዎች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በ12 የስፖርት ዓይነቶች የሚካፈሉ ከ6 ሺ በላይ ስፖርተኞች በማሳተፍ ይወዳደሩበታል፡፡

የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በሁለገቡ የስፖርት አካዳሚና የመወዳደርያ ስፍራ እያስገነባቸው ካሉት የስፖርት መወዳደርያዎች መካከል ሶስትና ሁለት ውድድሮችን ማስተናገድ የሚችሉ አምስት የእጅና ቅርጫት ኳስ ሜዳዎችን ጨምሮ ሁለት የሜዳ ቴኒስ፣የዋና እና የእግር ኳስ ሜዳ ይገኙባቸዋል። ከእነዚህ 5 የስፖርት መወዳደርያ ሜዳዎች የሁለቱ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ የቀሪዎቹ ደግሞ 85 በመቶ የግንባታ ስራው መጠናቀቁ ተገልጿል። በግንባታ ላይ ከሚገኙት የስፖርት መወዳዳርያዎች 25 ሺ ተመልካቾችን ማስተናገድ የሚችለው የእግር ኳስ ሜዳ እንዲሁም የሜዳ ቴኒስና የዋና መወዳደርያዎች የግንባታ ስራ 50 በመቶ የተከናወነ ሲሆን እስከ ጥር ወር መጨረሻ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቁ ይጠበቃል፡፡ የሁለገብ የስፖርት አካዳሚና የመወዳደርያ ስፍራ ግንባታው በዩኒቨርሲቲው ለሚሰጠው የመጀመርያና ሁለተኛ ድግሪ የሰውነትና ጤና ማጎልመሻ ትምህርት አገልግሎት የሚውሉ 10 የመማርያ ህንጻዎችም ግንባታን ያካትታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን የተቋቋመበት ዋና ዓላማ በአዲስ አበባ ከተማ ሊደርሱ የሚችሉትን እሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎችን ነዋሪውንና ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ፣ አደጋን አስቀድሞ ለመከላከልና ከተከሰተም ፈጥኖ በመቆጣጠርና በማረጋጋት የነዋሪውን ደህንነት (Safety) እንዲጠበቅ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህ ተልዕኮው መሰረት ህዳር 25 ቀን 2006፣ ከቀኑ 9፡15 ገደማ፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ቦታው ጆንያ ተራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የገበያ ማዕከል የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ፣ የእሳት አደጋው ከተከሰተው በላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉ ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ የእለቱን አደጋ አስመልክቶ ጋዜጣችሁ ባለፈው ቅዳሜ ህዳር 28 ቀን 2006 እትሙ ላይ “ከንቲባ ድሪባ የእሳት ቃጠሎ ተጐጂዎችን አቤቱታ አጣራዋለሁ አሉ” በሚል ርዕስ፣ የተቋማችንን ተልዕኮ በሚያሳንስና ገጽታችንን በሚያበላሽ እንደዚሁም ተቋማችንን ከህዝብ ጋር በሚያጋጭ መልኩ፣ መልካም እይታና ሚዛናዊነት የጐደለው ስሜትን ብቻ ያስተናገደ ዘገባ ማቅረባችሁ መስሪያ ቤታችንን አሳዝኗል፡፡ በዘገባችሁ ላይ አንዳንድ ነጋዴዎች፤ “የእሳት አደጋ ሰራተኞች ከበላይ አካል መመሪያ አልተላለፈልንም በሚል ሰበብ ቆመው ሲያዩ ነበር” ለተባለውኧ በማናቸውም እሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎችን ምክንያት መተኪያ የሌለውን የሰውን ህይወትና ንብረት ማዳን ሰብአዊ አገልግሎት ጭምር ከመሆኑም ባሻገር፣ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተቋቋመበት ዋናው አላማ ነው፡፡

ማናቸውንም አደጋ ፈጥኖ ለመቆጣጠር ባለሙያዎችም ሆኑ በየደረጃው የሚገኙ የመስሪያ ቤቱ የስራ ሃላፊዎች፤ በአደጋው ስፍራ የሚገኙ በመሆኑና ስራው ላይም በቀጥታ የሚሳተፉበት አሰራር እንጂ የሰው ህይወትና ንብረት ለማዳን የማንም አካል ትዕዛዝ ወይም ፈቃድ ተጠይቆ አያውቅም፤ ወደፊትም አይጠየቅም፡፡ አንዳንድ የመስሪያ ቤታችን ሰራተኞች ጉቦ ጠይቀዋል ለተባለውም፣ እንደዚህ አይነት አሉባልታ ቀደም ሲልም ሆነ አሁን በግለሰቦች የሚነገር ሲሆን ይህንኑ ለማጣራት በሚደረገው ሂደትም የጋዜጣ ዝግጅት ክፍላችሁን ጨምሮ “ሲሉ ሰማን” ከማለት ውጪ ተጨባጭ መረጃ አልቀረበም፡፡ ይሁን እንጂ ስራችን በህዝብ ፊት የሚሰራ በመሆኑ፣ ተጨባጭ መረጃዎች ካሉ ከህግ አካላት ጋር ተባብረን የምንሰራ መሆኑን ማረጋገጥም እንወዳለን፡፡ ሌላው አደጋዎች ሰፋ ሲሉ ሌሎች ተባባሪ ተቋማትንና የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያጋብዙ በሆነ ጊዜ ሁሉ በትብብር ስንሰራ ቆይተናል፡፡ በዚህ የእሳት አደጋም የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ፤ ኤርፖርቶች ድርጅት እንዲሁም የፀጥታ ኃይሎችና የአካባቢውን ህብረተሰብ በማሳተፍ፣ በሁሉም ቅርንጫፍ ጣቢያዎቻችን የሚገኙ የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪዎችንና አምቡላንሶችን ከበቂ ባለሙያዎች ጋር በማሰማራትና ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ አደጋው የከፋ እንዳይሆን ማድረግ ተችሏል፡፡

ጋዜጣችሁ ባቀረበው ዘገባ ግን የአደጋ መቆጣጠር ሰራተኞቻችንም ጭምር የአደጋው ሰለባ በመሆን አደጋውን ለመቆጣጠር ያደረጉትን ጥረት ለማየት አልፈለገም፡፡ ስለዚህም የላክነውን ይሄን ጽሑፍ በጋዜጣችሁ ላይ በማስተናገድ ላቀረባችሁት ዘገባ ማስተካከያ እርምጃ እንድትወስዱ እያሳሰብን፣ ይህ ሳይሆን ቢቀር የህግ አግባቦችን ለመጠቀም የምንገደድ መሆኑን እንገልፃለን፡፡ አማኑኤል ረዳ ኃይሉ (ኮ/ር) ም/ዋና ዳይሬክተር ከአዘጋጁ፡- ባለፈው ቅዳሜ የጋዜጣችን ዕትም፤ “ከንቲባ ድሪባ የእሳት ቃጠሎ ተጐጂዎችን አቤቱታ አጣራዋለሁ አሉ” በሚል ርእስ የወጣው ዘገባ፣ ጋዜጠኞቻችን አደጋው በደረሰበት ስፍራ ተገኝተው ተጐጂዎች ለከንቲባው ያቀረቡትን አቤቱታ በመስማት፣ ተጐጂዎችን በማነጋገርና ፎቶግራፍ በማንሳት የተጠናቀረ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን ደውለን የሚመለከተውን ኃላፊ በማነጋገር፣ በጉዳዩ ላይ የሰጡትን ምላሽ አካተን ማውጣታችንን ይታወሳል፡፡

  • የፓርቲው አመራሮች በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ሀዘናቸውን ገልፀዋል

የታላቁን የነፃነት ታጋይ የኔልሰን ማንዴላን ህልፈት ተከትሎ፣ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) ከትላንት በስቲያ ከሰዓት በኋላ የሀዘን መግለጫ ፕሮግራም በጽ/ቤቱ ያካሄደ ሲሆን በፕሮግራሙ ላይም ስለኔልሰን ማንዴላ የነፃነት ትግል፣ ከኢትዮጵያ ጋር ስለነበራቸው ቁርኝትና ከማንዴላ ምን ትምህርት ይወሰድ በሚሉት ዙርያ ንግግር ተደርጓል፡፡ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ከፕሮግራሙ ቀደም ባሉት ቀናት ደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ በመሄድ፣ በኔልሰን ማንዴላ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን መግለፃቸውን የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ፓርቲው ወር በገባ በሶስተኛው ቀን በሽብርተኝነት ወንጀል ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የሚገኙትን እነ አንዷለም አራጌን እንደሚያስብ የጠቆሙት የፓርቲው ዋና ፀሃፊ አቶ አስራት ጣሴ፤ የኔልሰን ማንዴላን የሀዘን መግለጫ ታህሳስ ሶስት ቀን ያደረገው ማንዴላ በነፃነት ትግል፣ በእነ አንዷለም ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳረፉ መሆናቸውን ለመጠቆም እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

“ማንዴላን ደቡብ አፍሪካ ወልዳ ብታሳድገውም ኢትዮጵያ ደግሞ አስተምራና ከሞት አትርፋ ለደቡብ አፍሪካ አበርክታዋለች” ብለዋል-ፀሃፊው፡፡ ማንዴላ ኢትዮጵያ ውስጥ በትምህርት ላይ እያሉ የደቡብ አፍሪካ ነጭ መሪዎች ለግል ጠባቂው ጉታ ዲንቃ፣ ጉቦ ከፍለው ሊያስገድሏቸው እንደነበር ያስታወሱት አቶ አስራት፤ ሆኖም ጉታ ዲንቃ ምስጢሩን ለማንዴላ አስተማሪ በመንገራቸው ከሞት መትረፋቸውን ጠቅሰው፣ ይህ ምስጢር ወጥቶ ከሞት ባይተርፉ ኖሮ ኢትዮጵያም፣ አፍሪካም ሆነ ዓለም ማንዴላ ስለሚባል ሰው አያውቅም ነበር ብለዋል፡፡ በ25 አመታቸው አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስን (ANC)ን ተቀላቅለው፣ በ46 ዓመታቸው ለእስር የተዳረጉ የነፃነት ታጋይና የመቻቻል ተምሳሌት ኔልሰን ማንዴላ፤ በሮቢን ደሴት ለ27 ዓመት በእስር ተሰቃይተው ከወጡና አፓርታይድ ከወደቀ በኋላ እ.ኤ.አ በ1994 የመጀመሪያው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡

ማንዴላ፤ “ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን እንዳስተማሩና ያሰሯቸው ሰዎች ላይ የቂም በቀል እርምጃ ከመውሰድ እርቅና መግባባትን በመምረጣቸው አለም በአንድ ድምፅ ተስማምቶ “ተምሳሌት” ብሏቸዋል ያሉት አቶ አስራት፤ ከ1ሺ በላይ ሽልማቶችና የማዕረግ ስሞች፣ 85 የክብር ድግሪዎች፣ የ45 የአለም ከተሞች የክብር ነዋሪነት፣ እንዲሁም ማንዴላ የተወለዱበት የልደት ቀናቸው ጁላይ 18 በተባበሩት መንግስታት ውሳኔ “የማንዴላ ቀን” ተብሎ ተሰይሞላቸዋል፤ ይህ ሁሉ የተገኘው ለነፃነት በተከፈለ መስዋዕትነት ነው ብለዋል አቶ አስራት ጣሴ፡፡

“እነአንዷለም ሽብርተኞች ተብለው ታስረዋል፤ ግን ሽብርተኞች አይደሉም፤ የነፃነት ትግል ቄስና ደብተራ ናቸው” ያሉት አቶ አስራት፤ ኔልሰን ማንዴላም በእንግሊዞች “አሸባሪ” ተብለው እንደነበር አስታውሰው፤ እነ አንዷለምም በቅርቡ የነፃነት ታጋይነታቸውን አለም እንደሚያውቀው ተናግረዋል፡፡ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሊቀመንበር አቶ አበባው መሀሪ ያደረጉት ንግግር ደግሞ በኔልሰን ማንዴላና በአፄ ሚኒልክ ላይ ያተኮረ ሲሆን ልክ እንደ ኔልሰን ማንዴላ ሁሉ አፄ ምኒልክም በኢትዮጵያ ውስጥ የመቻቻልና የአንድነት መንፈስ እንዲኖር ያበረከቱትን አስተዋፅኦ አስታውሰው፤ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የጥላቻና የጐሪጥ መተያየት ፖለቲካ አውግዘዋል። አቶ አበባው አክለውም፤ በምኒልክ ዘመን መቻቻልና አንድነት በመኖሩ የውጭ ጠላትን ማሸነፍ መቻሉን የገለፁ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ማንዴላ ይቅር ባይነትና መቻቻል ካልመጣ፣ ለአገሪቱም ሆነ ለህዝቧ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

በሊንኬጅ አርት ሪሶርስ ሴንተር አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚካሄደው የፊልም ፌስቲቫልና የፊልም ውድድር ባለፈው ሳምንት

ተካሂዶ አሸናፊዎች ተሸለሙ፡፡
ድርጅቱ ዘንድሮ ለስምንተኛ ጊዜ ባካሄደው ዝግጅት ፊልሞችን በእስር ዘርፎች አወዳድሯል፡፡
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝምና ከደራሲያን ማህበር የተውጣጡ አምስት የፊልም ባለሞያዎች፣

ፊልሞቹን በተለያዩ ሲኒማ ቤቶች በመመልከት ዳኝተዋል፡፡
ባለፈው ሰኞ በብሔራዊ ቲያትር በተከናወነው የመዝጊያና የሽልማት ስነስርዓት ላይ ይፋ እንደተደረገው “ኒሻን” ፊልም

በሶስት ዘርፎች አሸናፊ ለመሆን በቅቷል - በዓመቱ ምርጥ ፊልም፣ ምርጥ ዳይሬክተርና ምርጥ ሲኒማቶግራፊ፡፡



በወርሃ ታህሣሥ፣ 2001 ዓ.ም ነው … አንዲት ቀይ የቤት መኪና፣ ስድስት ኪሎ ከሚገኘው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

ዋናው ግቢ፣ በአንደኛ በር በኩል ወጥታ ቁልቁል ወደ አራት ኪሎ አቅጣጫ ከነፈች፡፡ የጣሊያኖችን የግፍ ጭፍጨፋ

ከሚዘክረው ሀውልት ጋ ሥትደርስ፣ ወደ ማርቆሥ ቤተክርሥቲያን ታጠፈችና አሁንም ቁልቁል ወደ አፍንጮ በር

ተተኮሰች፡፡ ሰዓቱ፣ 11፡45 አካባቢ እንደነበረ አሥታውሣለሁ፡፡ ቀዩዋ መኪና፣ የዩኒቨርሲቲው አንድ አንጋፋ መምህር

እያሽከረከሯት ወደ ፒያሳ አመራች፤ የመምህሩን አምስት የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ብትጭንም፣ ከ12፡30 በፊት፣

አሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሴዝ ግቢ የማድረስ ሀላፊነት ተጥሎባታል፡፡ ቀይዋ መኪና ከተቆረጠው ሰዓት በፊት ጥቂት

ደቂቃዎችን ቀድማ ከተባለው ቦታ አደረሠችን፡፡
የአሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሴዝ ግቢ፣ ከያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በወጡ ሙዚቀኞች እንደተቋቋመ በተነገረለት “ሃራ

ሳውንድ ባንድ” አማካኝነት፣ ሞቅ ደመቅ ብሎ ይታያል፡፡ በመሣሪያዎች ብቻ የተቀናበሩ ጣዕመ ዜማዎች ይንቆረቆራሉ፡፡

ውጭ ላይ የተሠናዳው መድረክ፣ በህዝበ አዳም ተሞሽሯል፡፡ አሁን ጨለማው ዐይን ያዝ ከማድረግ አልፏል፤ ትላልቅ

ፓውዛ መብራቶች መድረኩን በብርሃን አድምቀውታል፡፡ የሙዚቃ ቅንብሩ በስፋት መደመጥ ያዘ፡፡ አንድ ገጣሚ መድረኩ

ላይ ወጥቶ በመሣሪያ ቅንብር ከሚወጣው ጣዕመ ዜማ ጋር በወጉ ተለክቶ የተሠፋ የሚመሥል የሰውነት እንቅስቃሴ

ማሣየት ጀመረ፡፡ የውዝዋዜው ሥልት፣ ከሙዚቃው ምት ጋር በእርጋታ እየተዋሀደ ከለብታ ወደ ሞቅታ ሲዛወር፣

የገጣሚው አንደበት ተከፈተ፡፡
ከዚያ ሥልጡን አንደበት ውስጥ የሚወጡ የተመጠኑ የስንኝ ቋጠሮዎች፣ በተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች ምጣኔ ዜማ

ታጅበው ሲለቀቁ፣ በታላቅ ኪናዊ የመንፈስ ከፍታ ወደ ሰማየ ሰማያት የሚያርጉ ይመስሉ ነበረ፡፡ እኔ በበኩሌ ግጥም፣

ከዋሽንት ባለፈ በተለያዩ ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ቅንብር ታጅቦ ሲቀርብ ሣይ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ በመድረኩ ላይ

የተለያዩ ወጣት ገጣሚያን፣ ከሙዚቃው ምት ጋር የስንኞቻቸውን ምት እያዋደዱ በውዝዋዜ ሞሽረው ታዳሚውን

ማስኮምኮም ቀጥለዋል፡፡ መሀከል ላይ ይመስለኛል፣ የቀዩዋ መኪና አሽከርካሪ፣ አንጋፋው የዩኒቨርሲቲ መምህርም

መድረኩን ተቆጣጠሩት፤ ገጣሚው ፕሮፌሰር፣ ከወጣቶቹ ባልተናነሰ፣ እንደውም ካንዳንዶቹ በተሻለ ቆሞ ሲያሥተምር

የዋለ ወገባቸውን ከሙዚቃው ሥልት ጋር አዋደው ማወዛወዝ ጀመሩ፡፡ ግጥማቸውንም ከሙዚቃው ሥልት ጋር እያዋሀዱ

አቀነቀኑት፡፡ ይህ ቀን፣ በኢትዮጵያ የሥነ ጽሁፍ ታሪክ፣ ሥርዓት ባለው መልኩ ግጥም በጃዝ የቀረበበት ዕለት ተብሎ

ሊመዘገብ ይችላል፡፡
የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ እንደማስታውሰው ከሆነ፣ በዕለቱ ግጥሙን በመሣሪያዎቹ ቅንብር ጣዕመ ዜማና በራሡ ሥልታዊ

ውዝዋዜ አጅቦ በማቅረብ መድረኩን የሟሸው ገጣሚ አበባው መላኩ ይመስለኛል፡፡ “ይመስለኛል”ን ያመጣሁት፣

የመጀመሪያው የመድረክ አሟሺ አበባው ነው ወይስ ደምሰው መርሻ? ባለ “አሻራ”ዋ ምሥራቅ ተረፈ ናት ወይስ ሰዓሊዋ

ምህረት ከበደ? ወይስ ደግሞ “ለግጥም ጥም ጠብታ” የበቃው ፍሬዘር አድማሱ? የሚለውን ቀዳሚ ሰው በውል ማስታወስ

ባለመቻሌ ነው፡፡ “እየሄድኩ አልሄድኩም” የሚሉት የቀዩዋ መኪና አሽከርካሪ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ግን መሀከል ላይ

ማቅረባቸው፣ ብዙ ጥርጣሬ አልፈጠረብኝም። ለማንኛውም ግን፣ ስድስቱ ገጣምያን የዕለቱ ባለ ታሪኮች እንደነበሩ

ለመጠቆም መፈለጌን ብታውቁልኝ አልጠላም፡፡
በርግጥ፣ ግጥም በጃዝ ሥርዓት ባለው ቡድናዊ አደረጃጀት ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበው በ2001 ዓ.ም ነው ቢባልም፣ ለዚህ

የቡድን ዝግጅት ከመብቃቱ በፊት ሌሎች ሙከራዎች እንደነበሩ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እስከ አሁን በተገኙ

ማስረጃዎች መሰረት፣ በ2000 ዓ.ም በብሔራዊ ትያትር አበባው መላኩ “ቅናት” የተሠኘ ግጥሙን በሲዲ በቀረበ የሙዚቃ

ቅንብር አጃቢነት ለተመልካች ማቅረቡ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዕለት ከታዳሚው ከፍተኛ አድናቆት እንደተቸረው ተነግሯል፡፡

አበባው፣ በብሔራዊ ትያትር መድረክ ግጥሙን ከተቀናበረ ሙዚቃ ጋር ያቀርብ ዘንድ ንቃትና ብርታት የሆነው “ደግ

አይበረክትም” የተሠኘው የግጥም ሲዲው ዝግጅት ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡
እንግዲህ፣ ግጥምን በጃዝ መድረክ የሚያቀርበው የቡድን አባላት በአሊያንሥ ኢትዮ-ፍራንሴዝ ዝግጅትና በኋላም

በተለያዩ መድረኮች ግጥም በጃዝ ማቅረቡን እየሠለጠነበት መጣ፡፡ ቡድኑ፣ ከታዋቂው የፒያኖ ተጫዋች ግርማ ይፍራሸዋ

ጋር በጣሊያን የባህል ማዕከል ያቀረበው ዝግጅት፣ የወደፊቱን የከፍታ ዘመን አመላካች ነበረ ማለት ይቻላል፡፡ በቦሌ

ሮክና በሸራተን አዲስ መድረኮች ላይም ኢትዮጵያዊ ግጥም በጃዝ ተሞሽሮ ይቀርብ ዘንድ የቡድኑ የላቀ ትጋትና ጥረት

ቀጠለ፡፡ በ2003 ዓ.ም፣ ወር በገባ የመጀመሪያው እሮብ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል መድረክ ላይ ከመለከት ባንድ ጋር በኋላም

ከአቢሲኒያ ባንድ ጋር በመተባበር ግጥም በጃዝ እየሸመኑ ማቅረብ ተወዳጅ ኪነት እየሆነ መጣ። የዋቢ ሸበሌው የአንድ

ዓመት የግጥም በጃዝ ጉዞ ሲስተናበር የነበረው በቸርነት ወልደ ገብርኤል፣ በደምሰው መርሻና በአበባው መላኩ እንደነበረ

ያሠባሠብኳቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚሁ ዓመት ወደ ኋላ ላይ ግሩም ዘነበና ሜሮን ጌትነት የቡድን አባላቱን

እንደተቀላቀሉ ሰምቻለሁ፡፡
አሁንም የግጥም በጃዝ መድረኮች፤ የታዳሚን ቀልብ እየገዙ፣ የኪነት ልክፍት ያለበትን እያፈዘዙ፣ የገነገኑ ሀገራዊ

ሰንከፎችን እየመዘዙ የስኬት ጉዟቸውን ተያያዙት፡፡ በ2004 ዓ.ም፣ ግጥም በጃዝ በራስ ሆቴል መድረኮች ላይ አብቦ

ይፈካ ዘንድ ጊዜው ፈቀደ፡፡ ወር በገባ የመጀመሪያው እሮብ የራስ ሆቴል ትልቁ አዳራሽ፣ በታዳሚዎች መጣበብ ጀመረ።

የሆቴሉ ሰፊ ግቢ ሊሸከመውና ሊያስተናግደው ከሚችለው በላይ በሆኑ ረዣዥም ሰልፎች ይፈተን ዘንድ ግድ አለው፡፡

አዳራሹ፣ ከ800 በላይ የሚሆኑ ታዳሚዎች ጢም ብለው ሞልተው ይፈሡበታል፡፡ የሚገርመው ግን ይህ ሁሉ ታዳሚ

የሚርመሰመሰው ዝግጅቱ የሚቀርበው በነፃ ሥለሆነ እንዳይመሥልዎ! 50 ብር የመግቢያ ዋጋ ለመክፈል የተሠለፉ

የግጥም በጃዝ እድምተኞች፣ አዳራሹ እየሞላባቸው ሲመለሱ ማየት የየዕለቱ ክሥተት ሆኗል፡፡
የራስ ሆቴሉ ግጥምን በጃዝ መድረክ አሠናጂ የቡድን አባላት፣ ለግዜው “ጦቢያ ግጥም በጃዝ” በሚል ሥያሜ፣ ድርጅት

ከፍቶ የኢትዮጵያን ግጥም በጃዝ አፍክቶ ማቅረቡን ተያይዞታል፡፡ በራስ ሆቴል መድረክ ወር በገባ በመጀመሪያው ዕለተ

እሮብ፣ ለጥበብ ሱሰኞች ምሣቸውን እያደረሠ ይገኛል። የቡድኑ የጥበብ ጉዞ ሥርዓት ባለው መንገድ እየተጓዘ፣

ለተከታታይ 28 ወሮች በመድረክ ላይ ነግሷል፡፡ ቡድኑ፣ ዝግጅቱን በተከታታይ ማቅረብ የጀመረበትን ሁለተኛ ዓመትም

ለማክበር በቅቷል፤ በዚሁ በዓል ላይ፣ የተመረጡ ዝግጅቶች፣ “ጦቢያ ግጥም በጃዝ” (ቅጽ አንድ) በሚል ስያሜ በዲቪዲ

አሣትሞ በ50 ብር ዋጋ ለጥበብ ወዳጆች ማቅረቡ ይታወቃል፡፡ በነገራችን ላይ በራስ ሆቴል መድረክ በጃዝ የሙዚቃ

ቅንብር ተከሽነው የሚቀርቡት ግጥሞች ብቻ አይደሉም፤ ስሜት ኮርኳሪ፣ መሣጭና እውቀት አጋሪ የሆኑ ወጐችና

ዲስኩሮችም ሢቀርቡ አይቻለሁ፡፡ እንደውም፣ በጦቢያ ግጥምን በጃዝ ቢሮ ውስጥ በተገኘ መርሐ ግብር መሠረት፣

በየዕለት መድረኩ 5 ገጣምያን፣ 1 ወግ ተራኪ እና1 ዲስኩር አቅራቢ የኪነት ቤተኞች ሥራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ

ይታወቃል፡፡
የዛሬ የጦቢያ ግጥም በጃዝ ቡድን ተጠሪዎች፤ አበባው መላኩ፣ ምሥራቅ ተፈራ፣ ደምሰው መርሻ፣ ምህረት ከበደ፣ ግሩም

ዘነበና ሜሮን ጌትነት ሲሆኑ፣ አብዛኞቹ፣ በዘመነኛ ትንታግ ገጣሚነታቸው ይታወቃሉ፤ በመካከላቸው በትወናም

የተጨበጨበላቸው ይገኛሉ፡፡ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ አብዛኞቹ የቡድን አባላት በተለያዩ መድረኮች በግጥም

ተናግረዋል፤ ለግጥም ተዋድቀዋል፤ ስለ ግጥም አንብተዋል፤ ስለ ግጥም ቆመዋል፤ ለግጥም ጦም አድረዋል፡፡ ዛሬ ግን

በግጥም እያሠቡ፣ በግጥም ትውልድ ይሞግታሉ፤ በግጥም ተከብረው፣ በግጥም በልተው አድረዋል፡፡
ዛሬ ይህ ቡድን፣ ከተለያዩ ኤምባሲዎችና ከተለያዩ ድርጅቶች የአብረን እንስራ ጥሪ ይቀርብለታል። በታወቁ ተቋማት

ስፖንሰርነት፣ የተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮችን ይወጣ ይዟል፡፡ ለምሣሌ በመጋቢት ወር 2005 ዓ.ም፣ ከያኒው ሰርክ

የሚጠበብበት ተፈጥሮ፣ ህልውናዋ አደጋ ላይ መውደቁን ለማጠየቅ፣ በብሔራዊ ትያትር መድረክ “ጥበብ ለተፈጥሮ”

በሚል ርዕስ የተደነቀ ዝግጅት አቅርቧል፤ በዕለቱ የቀረቡት ግጥሞች በ80 የፖሊስ የማርሽ ባንድ አባላት ታጅበው

እንደነበረ ይታወሣል፡፡
ዛሬ፣ “ጦቢያ ግጥም በጃዝ” የቡድን አባላት፣ የራስ ሆቴልን መድረክ በጥበብ አድምቀው የሚሞሸሩት፣ በራሣቸው

“የመንፈስ ከፍታ” ያህል ብቻ በመንጠቅ አይደለም፤ የተለያዩ ገጣሚዎችን፣ ወግ አራቂዎችን፣ ዲስኩር አቅራቢዎችን ወዘተ

በመጋበዝ አዳዲስ ጥበበ ቃላት እንዲከሸኑ ሥርዓት ዘርግተዋል እንጂ፡፡ ለዚህ ነው፣ ከእግረ ተከል የኪነት ባለሟሎች

እስከ ጉምቱ የጥበብ አያቶች ድረስ በመድረክ ላይ ሢዘምኑ የሚታየው፤ በእውነትና በእውቀት እየተመሙ፣ ኪናዊ ውበት

ሲያፈልቁ የሚገኘው፡፡
ዛሬ ግጥም በጃዝ መድረክ የሚደነቅና የሚወደድ ውበት ብቻ ሣይሆን የሚናፈቅ ሕይወትም እየሆነ ያለ ይመሥላል፡፡

ዛሬ፣ 50 ብር ከፍለው የሚታደሙ አድናቂዎች ብቻ አይደለም የሞሉት፤ የዓመታት ወጪ ሸፍነው የቡድኑ አባል ለመሆኑ

የሚታትሩ ጭምር ተመዝግበዋል እንጂ፡፡ ዛሬ ቡድኑ፣ ጥበብን የሚያቀርብበት የነፃ አዳራሽ መንግሥት ይፍቀድልኝ

አይልም፤ እንደውም በየወሩ ለመንግሥት በሺዎች የሚቆጠር ብር ይገብራል እንጂ፤ “ግብር አይደለም ዕዳ” እንዲል

የገቢዎች ሚኒስቴር፡፡
ምን አለፋዎት … ግጥም በጃዝ መድረክ ላይ በሃበሻ ግጥም፣ የሀበሻ እውነትና እውቀት በጥበባዊ ሥልት ተፈታትቶ

በምርጥ የቃላት ጡብ፣ ሢገጣጠም ያያሉ (እመኑኝ እያጋነንኩ አይደለም-በፍፁም)፡፡ ከሃበሻ የኑሮ ልማድ ውስጥ

እውነቱና እውቀቱ በብልሃት ይተነተናሉ-በግጥም፡፡ ከእውነቱና ከእውቀቱ የተጠነፈፈው ማንነቱ በቃላት ምታት መድረክ

ላይ ሢሠጣ፣ ታዳሚው እየሣቀ ይተክዛል፤ እያጨበጨበ ይቆዝማል፡፡ ግጥሞቹ፣ ወጉና ዲስኩሩ በሀበሻ የመንፈስ ክር

የተሣሠሩ ሽንፈቶቹን፣ ቁጭቶቹን፣ ህልሞቹን ይናገራሉ፤ ከሀገር እውቀቶቹና እውነቶቹ ጋር እየተጣቀሡም፣ የዘመን

መንፈስን እያሥጠቀሡ፣ ገዝፈውና በዝተው ይቀነቀናሉ፡፡ የአዳሚም የታዳሚም መንፈስ ከፍ ብሎ ይንሣፈፋል፤ ዝቅ

ብሎም ይነፍሣል … እኔ በበኩሌ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመምህርነትም በተማሪነትም ያጣሁትን የመንፈሥ ልዕልና በዚያ

አዳራሽ ውስጥ የተጐናፀፍኩ አይነት ነው የሚሠማኝ፡፡ የሀበሻ ግጥም፣ ወግና ዲስኩር በተቀናበረ ሙዚቃ ታጅበው

እውነት፣ እውቀትና ውበት በሚያፈልቁበት በዚህ አዳራሽ፣ የሰዓታት ሰላም ያገኘሁ ይመሥለኛል፡፡
እስኪ በራሥ ሆቴል አዳራሸ ከሚቀርቡ ዝግጅቶች መካከል የቅርቡን (ህዳር 4 ቀን 2006 ዓ.ም) የጥበብ ድግሥ

በጨረፍታ ልጠቁማችሁ። እንደተለመደው ትልቁ አዳራሽ ከአፍ እስከ ገደፉ ጢም ብሏል፡፡ የውጭ ሀገር የመገናኛ

ብዙኃን ባልደረቦች ትላልቅ መቅረፀ ምሥል ካሜራዎችን ተሸክመው ዝግጅቱን ለመቅረጽ ከወዲያ ወዲህ ሽር ጉድ

ይላሉ፡፡ “ነፃ አውጪ ባንድ” በመሣሪያ የተቀነባበሩ ጣዕመ ዜማዎችን ያሠማሉ፡፡ የመድረክ አጋፋሪው፣ ዝነኛው ተዋናይ

ግሩም ዘነበ ወደ መድረኩ ጐራ እያለ በአስገምጋሚ ድምፁ መርሐግብሩን ያሥተዋውቃል፡፡
በዚህ ዕለት፣ የሸገር ሬዲዮ ባልደረባው ስመ ጥሩ የመድረክ ሰው ተፈሪ ዓለሙ፣ የሁለት ትውልዶችን ብጭቅጫቂ ኑሮ በ

“ስውር-ስፌት” እየጠቀመ ያለው (“ጠ” ጠብቃ ትነበብ) የአዲስ አድማሱ ዋና አዘጋጅ ገጣሚ ነቢይ መኮንን፣ ሢያሻው

በግጥም መናገር የሚችለው ታዋቂው ሰዓሊና ቀራፂ በቀለ መኮንን፣ የዕለቱን መድረክ “የመንፈስ ከፍታ” አግዝፎ የናኘው

ገጣሚ በረከት በላይነህ፣ ለግጥም ወይም ስለ ግጥም ሕይወተን እየከፈለ ያለ የሚመሥለኝ ገጣሚ ደምሰው መርሻ፣ መሪር

ሰዋዊ ግዙፍ ጥያቄዎች በተራኪ ግጥም እንዴት በብልሃት ሊቀርብ እንደሚችል በገቢር ያሣየው ገጣሚ ፈቃዱ ጌታቸው፣

ይህ ትውልድ ከሃገሩ አልፎ ዓለምን የመሞገት ብቃት እንዳለው በአንድ የወግ ጽሁፉ ማሣመን የቻለው የ“ፋክት”

መጽሔቱ አምደኛ ሚካኤል ዲኖ እና በተለያዩ መድረኮች ዝናን ያተረፉት የ“ፋቡላ ኪነጥበብ” አባላት የራስ ሆቴልን

አዳራሽ በሀበሻ የጥበብ አየር ሞልተውት አምሽተዋል፡፡ የታዳሚውን ስሜትና የመንፈሥ እርካታ እንዲህ ነው ማለት

ይከብደኛል፤ የአጋነንኩ ይመስልብኛልና! እራስዎት ጠይቀው ቢያረጋግጡ ይሻላል፡፡ አዘጋጆቹ፣ የ“ጦቢያ ግጥም በጃዝ”

ቡድን አባላት ብራቮ!

Saturday, 07 December 2013 13:01

እንኳን ለዓመት ጉድ አበቃን!

ዘንድሮም ልክ በዓመቱ፣ እንደአምናና እንደ ሃቻምና
የሐምሌ ጐርፍ ሞላና፣ ይኸው ለዓመት ጉድ
በቃና …
አደጋ ባሕል ከሆነን፣ እስቲ እግዚአብሔር ይመስገና፣ …
ዝግጁው ማዘጋጃ ቤት፣ ዜና መግለጫ ለማውጋት
እንደጥምቀተ ባሕር ወግ፣ የዓመቱን ጐርፍ ለማውሣት
ደረሰ ፍል ውሃ ሜዳ፣ በጋዜጦች አጀብ ብዛት
ለዓመቱ ዜና ገብ ቂጥ፣ “ካሜራ ማን ዙም-ኢን ዙም አውት”
ዘንድሮ ለማወዳደር፣ ከሀቻምናው የዝናብ መዓት
የዓመቱን ፋንፋር ለሕዝቡ፣ በቴሌቪዥን ለመንፋት! …
አደጋ ባሕል ከሆነን፣ እስቲ እግዚአብሔር ይመስገና፤
እኛም ለዓመት ጉድ በቃና፤ …
ከተማው በዶፍ ታጠበ፣ ዝናብ ሳይሆን መዓት ጣለ
ዘቀጠ ተብከለከለ
ቤት ንብረት ተግበሰበሰ፣ ገደል መቀመቅ ተጣለ
መኪናው እንደ አሻንጉሊት፣ ከምድር በላይ ተንጣለለ
ተዋጠ ተጥለቀለቀ፣ ጣራና ፎቅ ግቻ አከለ
ወረደ መዓት ወረደ
ሰማይ ቁልቁል ተቀደደ
እንደ ኦሪት ውሃ ጥፋት፣ አራዳ በማጥ ተናደ
የቤት እንስሳው ንብረቱ፣ ስንቱ አስከሬን ተወሰደ
ከእንጦጦ ፍልውሃ ሜዳ፣ ቄራ እንጦሮጦስ ወረደ
አጠበው ምድሩን ጠረገው፣ ዛፍ ግንዱን እየማገደ
ፎቁን ተሸክሞት ሄደ! …
አቤት ጉድ እየተባለ፣ እንዲያው ብቻ በደፈና
አዲስ አበባ ያለ ዕቅድ፣ ከዓመት ዓመት በጥገና
የዘለቄታ መፍትሔው፣ በአስተማማኝ ሳይጠና
በማዘጋጃ ቤት ዲስኩር፣ የተናደው ፎቅ ላይ ቀና
ለአዲስ ጥናት በአዲስ እቅድ፣ላይ ነን እኮ እየተባለ
ጋዜጣም ምሱን ሸለለ
ቴሌቪዥን ተቀበለ
ሬዲዮም ተንበለበለ
ዘንድሮም ልክ በዓመቱ፣ አዲሳባ ጉድ ተባለ!
ዝነኛው የአቃቂ ውሃም፣ ከጊንፊሌ ጋር ፏለለ
ስንቱን ሰው በልቶ ቤት ነዶ
ለዓመት ምሱ ሕዝቡን ማግዶ
እንደ ቅድመ ታሪክ ዘንዶ
ደሞ ለዓመት ያብቃን ብሎ፣ ተንጐማሎ እየኮራ
እየተወሳለተ ዝናው፣ በጋዜጣ በካሜራ
እያስገመገመ ሄደ፣ እንደሞላ እንደ ተፈራ! …
አደጋ ባሕል ከሆነን፣ እስቲ እግዚአብሔር ይመስገና፤
እኛም ለዓመት ጉድ በቃና፤ …
ዝግጁው ማዘጋጃ ቤት፣ ዜና መግለጫ ለማውጋት
ደረሰ ላጋር ቁልቁለት፣ በጋዜጦች አጀብ ብዛት፣
ካሜራ ማን ዙም-ኢን ዙም አውት! ራዲዮ ማይክሮፎንክን አጉላ
ፊንፊኔም ጥማድ ቀበና አቃቂም ድምር ቡልቡላ
የዓመት መዓቱን ወረደ ሞላ ፈላ ሰው ተበላ!
የቀበሌ አዋጅ እምቢልታ
የእሳት አደጋ ኡኡታ
አስከሬን ጠፋ ዕድር ውጡ፣ ዋይታ ጡሩምባ ቱልቱላ
የእግዜር ቁጣ የእግዜር ዱላ! …
እንደ አምልኮ ጣኦት ልማድ፣ እንደ ባሕሎች አሸክላ
ለአዲሳባ ውሃ ግብር፣ የሰው ልጅ እየተቀላ
ክረምት በመጣ ቁጥር፣ ዓማን ዘራፍ ይባላላ! …
አደጋ ባሕል ከሆነን፣ እስቲ እግዚአብሔር ይመስገና፤
እንኳን ለዓመት ጉድ በቃና!
ጸጋዬ ገብረ መድኅን

 

በወጣትና አንጋፋ ከያንያን በየወሩ የሚቀርበው “ግጥም በጃዝ” 29ኛ ዝግጅቱን የፊታችን ረቡዕ ከምሽቱ 11፡30 ጀምሮ በራስ ሆቴል አዳራሽ እንደሚያቀርብ አዘጋጆቹ ገለፁ፡፡ በምሽቱ የጥበብ ዝግጅት ላይ ገጣሚ ነቢይ መኮንን፣ ሰዓሊና ቀራጺ በቀለ መኮንን፣ አበባው መላኩ፣ ሜሮን ጌትነትና ገዛኸኝ ፀጋው ግጥም ሲያቀርቡ፤ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ወግ፣ በኃይሉ ገብረመድሕን ደግሞ ዲስኩር ያቀርባሉ ተብሏል፡፡ የዝግጅቱ መግቢያ በነፍስ ወከፍ 50 ብር ነው፡፡

በሻሸመኔ ከተማና አቅራቢያዋ ኪነጥበብ አፍቃሪዎች የተቋቋመው “ከአድማስ ፊት” የኪነጥበብ ማህበር 45ኛ ዝግጅቱን ነገ ከቀኑ 7 ሰአት በሻሸመኔ የባህል አዳራሽ እንደሚያቀርብ አስታወቀ፡፡ የዕለቱ የክብር እንግዳ በ “ትናንሽ ፀሐዮች” እማ ጨቤን ሆና የምትተውነው አርቲስት ሰብለ ተፈራ ነች። በነገው ዝግጅት የጭውውት፣ የግጥም፣ የዘፈን፣ የመነባንብ ሥራዎች ይቀርባሉ፡፡ ማሕበሩ ካሁን በኋላ በየወሩ በተለያዩ የጥበብ ዘርፎች ውድድር እያካሄደ ለአሸናፊዎች የሚሸልም ሲሆን የነገው ውድድርም በኮሜዲ ዘርፍ እንደሚሆን ማሕበሩ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ ከ“አድማስ ፊት” የተመሰረተበትን 6ኛ ዓመት በ50ኛ ዝግጅቱ በመጪው ሰኔ ለማክበር እየተዘጋጀ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከዓመቱ ምርጥ የአፍሪካ ሶስት ብሄራዊ ቡድኖች አንዱ መሆኑን አስታወቀ፡፡ አስቀድሞ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በዓመታዊ የኮከብ ተጨዋቾች ምርጫው በሁለት ዘርፎች 3 ኢትዮጵያውያን በእጩነት እንደጠቀሳቸው ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ ስኬት በማግኘት በአገሪቱ እግር ኳስ ላይ ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሯል። የዋልያዎቹ ስብስብ በ2013 የአፍሪካ ምርጥ ቡድኖች የመጨረሻ እጩ ሆኖ የቀረበው ከምእራብ አፍሪካዎቹ ቡድኖች ናይጄርያ እና ቡርኪናፋሶ ጋር ነው፡፡ ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፍ በ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ የበቃው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ20ኛው ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻው ጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ በ2014 እኤአ በደቡብ አፍሪካ በሚስተናገደው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ እንደሚሳተፍም ይታወቃል፡፡ በካፍ ዓመታዊ ኮከብ እግር ኳስ ተጨዋች ምርጫ በመላው ዓለም ከሚጫወቱ አፍሪካዊ ፕሮፌሽናሎች በእጩነት ከቀረቡት 25 ተጨዋቾች ሳላዲን ሰኢድ ሲጲጁ በሌላው በአፍሪካ ብቻ በሚጫወቱ ከቀረቡት 23 እጩዎች ደግሞ አዳነ ግርማና ጌታነህ ከበደ ተካትተዋል፡፡ የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋቾች ምርጫ ላይ በተለያዩ ዘርፎች ያሸነፉት የሚሸለሙት ከወር በኋላ በናይጄርያ ሌጎስ በሚካሄድ ስነስርዓት ይሸልማሉ፡፡ በተያያዘ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በወጣቶች ላይ በማተኮር ጠንክረን ከሰራን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዕድገት በጣም ተጠናክሮ ይቀጥላል በማለት ለፊፋ ድረገፅ በሰጡት ምላሽ ተናግረዋል፡፡ ፊፋ በድረገፁ በሰውነት ቢሻው ላይ ያተኮረ ዘገባውን ሲሰራ ዋና አሰልጣኙን ቀድሞ የባይሎጂ መምህር እና የእግር ኳስ ተማሪ መሆናቸውን ጠቅሶ ነበር፡፡ ‹‹መምህርነት እና የእግር ኳስ አሰልጣኝነት ተመሳሳይ ሙያ መሆናቸው እጅግ በጣም ጠቅሞኛል፡፡ አስተማሪነቴን ካቆምኩ በኋላ በመጀመርያ በአገር አቀፍ ደረጃ በርካታ የእግር ኳስ ስልጠና ኮርሶችን ወስድኩ ፡፡ ከዚያም የካፍ እና የፊፋ ኮርሶችንም ተከታትያለሁ፡፡ በውጭ አገርም የትምህርት ኮርሶችን አግኝቻለሁ፡፡ አሁን ሙያዬ መምህርነት አይደለም የማስተምረው እግር ኳስን ሆኗል ›› በማለት አሰልጣኝ ሰውነት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ኢንተርናሽናል ውድድሮችን የጀመርነው ለአፍሪካ ዋንጫ እና ለዓለም ዋንጫ የማለፍ ግቦችን በማቀድ ነበር፡፡ ግቦቻችን ለማሳካት በጣም ጠንክረን መስራት እንዳለብንም በመገንዘብ ቀን ከሌሊት ልምምድ አድርገናል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ መሻሻልን ለመረዳት ብዙ እንደማያስቸግር ለፊፋ ድረገፅ ዘገባ ያስረዱት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ‹‹ዋናው ምስጥር በርትቶ መስራት እና ሁሉም ተጨዋቾች በአንድ አይነት አስተሳሰብ እንዲሰሩ ማስቻል ነው፡፡ የቡድናችን ጥንካሬ ያለው አንድነት እና ትስስር ነው፡፡›› ብለዋል የኢትዮጵያን እግር ኳስ ቀጣይ እድገት ብሩህ ለመናድረግ መሰራት ስላለበት ሲናገሩ‹‹ በወጣቶች ደረጃ ወርደን በመስራት የኳስ ተሰጥኦ ያላቸውን ልጆች ማሳደግ አለብን፡፡ በሚቀጥሉት ሁለት እና ሶስት አመታት በርካታ ምርጥ ችሎታ ያላቸውን ተጨዋቾች ማሰባሰባችን አይቀርም፡፡ በእነሱ ላይ አተኩረን ከሰራን የብሄራዊ ቡድናችን ጥንካሬ ይቀጥላል፡፡›› ብለዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የ2013 የዓለም ኮከብ እግር ኳስ ተጨዋቾች ምርጫ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ከሮናልዶ ወይም ከሜሲ የቱ ያሸንፋል በሚል የተፈጠረው ክርክር ትኩረት እንደሳበ ነው፡፡ አንዳንድ ዘገባዎች ፉክክሩ በክርስትያኖ ሮናልዶ፤ ሊዮኔል ሜሲ እና ፍራንክ ሪበሪ መካከል እንደሚሆን እየገለፁ ናቸው፡፡ እንደውም በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ኤጀንሲያ ኒውስ የተባለ ታዋቂ የስፔን ሚዲያ አሸናፊውን ደርሸበታለሁ ብለው ዘግቧል፡፡ እንደኤጀንሲያ ኒውስ መረጃ ሜሲ ለአምስትኛ ጊዜ የዓለም ኮከብ ተጨዋች ሆኖ የወርቅ ኳሱን እንደሚሸለም ተገልፆ፤ ክርስትያኖ ሮናልዶ፤ ፍራንክ ሪበሪ ፤ አንድሬስ ኢንዬስታ እና ዝላታን ኢብራሞቪች እስከ አምስተኛ ደረጃ እንዳገኙ ታውጇል፡፡ ከግብ ጠባቂዎች በምርጥ 11 ቡድኑ ለመካተት የቀረቡ 5 የመጨረሻ እጩዎች ከሳምንት በፊት ይፋ ሲደረጉ ጣሊያናዊው የጁቬንትስ ግብ ጠባቂ ጂያንሉጂ ቡፎን፤ ስፔናዊው የማድሪድ ግብ ጠባቂ ኤከር ካስያስ፤ ቼካዊው የቼልሲ ግብ ጠባቂ ፒተር ቼክ፤ ጀርመናዊው የባየር ሙኒክ ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኑዌር እንዲሁም ስፔናዊው የባርሴሎና ግብ ጠባቂ ቪክቶር ቫልዴዝ ናቸው፡፡ ለዓመቱ ምርጥ ጎል ለሚሸለመው የፑሽካሽ አዋርድ 10 ተጨዋቾች በአስር ምርጥ ጎሎቻቸው በእጩነት ሲቀረቡ የኔይማር እና የኢብራሞቪች ጎሎች ይገኙበታል፡፡ በፊፋ ድረገፅ የተሰጡ ድምፆች ከተሰበሰቡ በኋላ ለመጨረሻ ፉክክር የሚበቁ ሶስት የዓመቱ ምርጥ ጎሎች የሚታወቁት ሰኞ ነው፡፡ በዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ ምርጫ ለመፎካከር የቀረቡ አስር እጩዎች ካርሎ አንቸሎቲ፤ ራፋ ቤኒቴዝ፤ አንቶኒዮ ኮንቴ፤ ቪሰንቴ ዴልቦስኬ፤ አሌክስ ፈርጉሰን፤ ጁፕ ሄንየስ፤ የርገን ክሎን፤ ጆሴ ሞውሪንሆ፤ ሊውስ ፊሊፕ ስኮላሬ እና አርሰን ቬንገር ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ ተጨዋች ሆኖ ለማሸነፍ የበቃው አይቮሪኮስታዊው ያያ ቱሬ ነው፡፡ የማንችስተር ሲቲ ወሳኝ አማካይ ተጨዋች የሆነው ቱሬ በቢሲሲ የዓመቱ አፍሪካዊ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ ከመመረጡ ባሻገር ለፊፋ የወርቅ ኳስ ሽልማት የታጨ ብቸኛው አፍሪካዊ ነው። ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ በተካሄደው የቢቢሲ የዓመቱ ኮከብ ተጨዋች ምርጫ ላይ በመጨረሻ እጩነት ከቀረቡት ተጨዋቾች ናይጄሪያውያኑ ጆን ኦቢ ሚኬል እና ቪክቶር ሞሰስ እንዲሁም የዛምቢያው ጆናታን ፕሪቶፕያ ይገኙበት ነበር፡፡