Administrator

Administrator

     የታዋቂው ሞታውን ሪከርድስ ኩባንያ ፕሬዚዳንትና የአለማችን ትልቁ ሙዚቃ አሳታሚ ኩባንያ የዩኒቨርሳል ሚዩዚክ የኧርባን ሚዩዚክ ፕሬዚዳንት የሆነችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኩባንያ ስራ አስኪያጅ ኢትዮጵያ ሃብተማርያም፣ በቢልቦርድ የ2016 የአለማችን ምርጥ 100 የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ስራ ስኪያጅ ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ተካትታለች፡፡
በአለማችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ የተሳካ ተግባራት የፈጸሙ የዘርፉ ኩባንያዎችን የሚመሩ ሴት የስራ አስፈጻሚዎችንና ማናጀሮችን እየመረጠ በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ቢልቦርድ፣ ሰሞኑንም ኢትዮጵያ ሃብተማርያምን ጨምሮ በአሳታሚነት፣ በአከፋፋይነትና በሌሎች ተያያዥ መስኮች የተሰማሩ ኩባንያዎችን የሚመሩ የአመቱ 100 ምርጥ ሴቶችን ዝርዝር አውጥቷል፡፡ የ37 አመት እድሜ ያላት ኢትዮጵያ ሃብተ ማርያም በምትመራቸው የሙዚቃ ኩባንያዎች አማካይነት በአመቱ ባከናወነቻቸው ተግባራት፣ ከአለማችን ምርጥ የሙዚቃ ኩባንያ መሪ ሴቶች ተርታ መሰለፏን ቢልቦርድ በድረገጹ ባስነበበው መረጃ ገልጧል፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 የታላቁ የአለማችን የሙዚቃ ኩባንያ ሞታውን ሪከርድስ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን የተሾመችው ኢትዮጵያ፤ ስቲቪ ዎንደርን ጨምሮ ከአለማችን ታላላቅ ድምጻውያን ጋር ስኬታማ ስራዎችን በማከናወን ወደ ፕሬዚዳንትነት ማደግና በዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ኩባንያ የኧርባን ሚዩዚክ ፕሬዚዳንት ሆና መስራት መቻሏ ተነግሯል፡፡
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2014 በዚሁ የቢልቦርድ የአለማችን ምርጥ 100 የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ተካትታ እንደነበርም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ስልጠናና የቴክኒክ ድጋፍ እንሰጣለን ብለዋል

   በዓለም ታዋቂና ቀዳሚ ከሆኑት የኬክና ዳቦ አምራች ድርጅቶች አንዱ የሆነው ቤከልስ በቅርቡ ከተከፈተው ራማዳ አዲስ ሆቴል ጋር በመተባበር፣ ደረጃውን የጠበቀ ኬክና ዳቦ ለአዲስ አበባ ነዋሪ ሊያቀርብ ነው፡፡
ታዋቂው ጀርመናዊ ሼፍ ባስቲያን ኤቬርሰማን ትናንት በራማዳ አዲስ ሆቴል፣ ትክክለኛ ኬክና የዳቦ መጋገሪያ ቁሶችን (ዱቄት የተለያዩ ዓይነት ቸኮሌቶች…) በማቅረብ፣ ከተለያዩ ሆቴሎች ለተጋበዙ እንግዶች በመጋገር አሳይቷል፡፡
አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ከተማ በመሆኗ ጥራት ያለውና ደረጃውን የጠበቀ ኬክና ዳቦ ማቅረብ አለብን ያሉት ሚ/ር ባስቲያን፤ ከ5 ኮከብ ሆቴሎች ጀምሮ አነስተኛ ኬክና ዳቦ መጋገሪያዎች፤ ትክክለኛውን ቁስ እንዲጠቀሙ፣ ለሁሉም የኬክና ዳቦና ዘርፍ ኢንዱስትሪ የቴክኒክ ድጋፍ፣ ጥራት ያለውት ምርት….. እናቀርባለን ብለዋል፡፡
ማንኛውም ሆቴልና ኬክና ዳቦ መጋገሪያ ትክክለኛውን ጥሬ ዕቃ ከራማዳ አዲስ ሆቴል ጋር በመነጋገር ሊያገኝ እንደሚችል ተገልጿል፡፡

     የሆላንድ ካር ኩባንያ ግማሽ ባለሀብት የሆኑት ኢ/ር ታደሰ ተሰማ፤ በኩባንያቸው ላይ እየተደረገ ያለውን ምርመራ በተመለከተ ለጠ/ሚኒስትሩና ለፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቤቱታ አቀረቡ፡፡
ባለሀብቱ ህዳር 27 ቀን 2009 ዓ.ም ለዋና ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬና ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በፅሁፍ ባቀረቡት አቤቱታ፤ “በፍ/ቤት የኪሳራ ውሳኔ የተላለፈበትን ሆላንድ ካር ኩባንያ በተመለከተ የኪሳራውን ሂደት እንዲያከናውኑ በተሾሙት መርማሪ ዳኛ ላይ እምነት አጥቻለሁ›› ብለዋል፡፡
ባለሀብቱ እየተፈፀመ ነው ያሉት በስልጣን አለአግባብ መጠቀምና ሙስና እንዲጣራላቸው ጠይቀዋል - በአቤቱታቸው፡፡
በዘጠኝ ነጥቦች ዘርዝረው እየተፈፀሙ ናቸው ያሏቸውን ስህተቶች ያቀረቡት ባለሀብቱ፤ ኪሳራ አጋጥሞታል የተባለው ኩባንያቸው በአንድ ወቅት በሀገሪቱ ካሉ ኩባንያዎች ከፍተኛ ግብር ከፋይ የነበረና ታማኝ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ተብሎ የተሰየመ ድርጅት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡  ሆላንድ ካር፤ ዶክ፣ አባይ፣ አዋሽ፣ ተከዜና ናኦሚ የተሰኙ አውቶሞቢሎችን በአገር ውስጥ በመገጣጠም ይታወቅ እንደነበር ይታወሳል፡፡

  አቢሲኒያ ባንክ በቅርቡ ባደረገው የባለአክሲዮኖች 20ኛ መደበኛና 11ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤዎች ላይ ለግብረሰናይ ድርጅቶች እንዲለገስ የተወሰነውን የግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለተመረጡ 7 ግብረሰናይ ድርጅቶች ሰጠ፡፡
ባንኩ ባለፈው ሳምንት በቅርቡ ለተቀዳሚ ደንበኞች ማስተናገጃ በከፈተው ልዩ ሐበሻ ቅርንጫፍ በተደረገው የርክክብ ሥነ ስርዓት ላይ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ አስማረ ባደረጉት ንግግር፣ ባንካችን ከምስረታው ጀምሮ ላለፉት 20 ዓመታት ከበርካታ የግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር አብሮ በመስራት ማኅበራዊ ግዴታውን ሲወጣ ቆይቷል ብለዋል፡፡
በዕለቱ ድጋፍ የተደረገላቸው 7 ግብረሰናይ ድርጅቶች፡- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የ200 ሺህ ብር፣ መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል የ100 ሺህ ብር፣ ለዓለም የሕፃናት ዕርዳታ ድርጅት 60 ሺህ ብር፣ ርዕይ ለትውልድ የ50 ሺህ ብር፣ ነህምያ ኦቲዝም ማዕከል የ40 ሺህ ብር፣ የጎንደር መልሶ ማቋቋምና ልማት ማኅበር የ25 ሺህ ብር፣ ፍሬገነት ኪዳን ለህፃናት የ25ሺ ብር ቼክ ከባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ከአቶ መሰረት ታዬ እጅ ተቀብለዋል፡፡
“ከተመሰረትን አጭር ጊዜ ቢሆንም ይዘን የተነሳነው ራዕይ ትልቅ ነው፡፡ በ2020 ዓ.ም (ከ11 ዓመት በኋላ ማለት ነው) 10 ሺህ ህፃናት ራዕይ ኖሯቸው አገር የሚቀይሩ ትልቅ ቦታ የሚደርሱ ዜጎችን መፍጠር ነው” ያሉት የርዕይ ለትውልድ ፕሬዚዳንት፤ የድርጅቱ ዓላማ፣ ከተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ በመጠየቅ የድሃ ቤተሰብ ልጆች ምግብ እንዲበሉ ማድረግ፣ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችና ዩኒፎርምም ማቅረብ ነው ብለዋል፡፡

Monday, 05 December 2016 10:02

የፍቅር ጥግ

 · አንድ ላይ መሆን የቱንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆን ግዴለኝም፤ ለብቻ ከመሆን በላይ የከፋ ነገር የለም፡፡
    ጆሴፊኔ አንጄሊኒ
· የትም ብሄድ ልዩነት የለውም፤ ሁልጊዜ ወዳንተ መመለሺያ መንገዱን አውቀዋለሁ፡፡ አንተ አቅጣጫ ማመላከቺያ ኮከቤ ነህ፡፡
   ዲያና ፒተርፍሬዩንድ
· “እወድሻለሁ” - የሁሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻ ይኸው ነው፡፡
   ኤፍ. ስኮት ፊትዝጌራልድ
· ሁለመናዬ ሁሉመናሽን ይወደዋል፡፡
   ጆን ሌጀንድ
· ፍቅር፤ ለሰው ልጅ ብዙዎቹ ህመሞች ድዌዎች ፈውስ ነው፡፡
   ዊሊያም ሜኒንገር
· እውነተኛ የፍቅር ታሪኮች መጨረሻ የላቸውም፡፡
   ሪቻርድ ባች
· ፍቅር እሳት ነው፡፡ ነገር ግን ልብህን ያሙቀው አሊያም ቤትህን ያቃጥለው መገመት አትችልም፡፡
   ጆአን ክራውፎርድ
· በዓይኖችህ ሳይሆን በልብህ አፍቅር፡፡
   ድሬክ
· በፍቅር ስሜት ብቻ ነው የማምነው፡፡
   ካርሴና ካፑር ክሃን
· መፈቀር ብ ቻ አ ይደለም የ ምሻው፤ መ ፈቀሬም እንዲነገረኝ ጭምር እንጂ፡፡
   ጆርጅ ኢሊዮት
· በህይወት ውስጥ አንድ ደስታ ብቻ ነው ያለው- ማፍቀርና መፈቀር፡፡
   ጆርጅ ሳንድ

Monday, 05 December 2016 09:59

ስናውቃቸው የሚገርሙን!!

 · አንድ ፓውንድ (453.6ግራም) ማር ለማምረት፣ አንድ ንብ 2 ሚሊዮን አበቦችን መቅሰም ይኖርበታል፡፡
· የዓለም የህዝብ ቁጥር እ.ኤ.አ በ2080 ወደ 10.8 ቢሊንዮ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
· በህይወት ዘመናችን ሁለት የዋና ገንዳዎች የሚሞላ ምራቅ እናመርታለን፡፡
· መዝለል የማይችል ብቸኛው አጥቢ እንስሳ ዝሆን ነው፡፡
· እንደ ጣት አሻራ ሁሉ እያንዳንዱ ሰው የተለያዩ የምላስ አሻራዎች አሉት፡፡
· የሲጋራ መለኮሽያ ላይተር የተፈለሰፈው ከክብሪት በፊት ነው፡፡
· የተራራ አንበሶች ማፏጨት ይችላሉ፡፡
· ቢራቢሮዎች ምግባቸውን የሚቀምሱት በእግሮቻቸው ነው፡፡
· ዶልፊኖች የሚተኙት አንድ ዓይናቸውን ገልጠው ነው፡፡
· የጥርስ መቦረሽያ ‹‹ኮልጌት›› በስፓኒሽ ቋንቋ ‹‹ሂድና ራስህን ስቀል›› ማለት ነው፡፡
· አንድ አማካይ ሰው በህይወት ዘመኑ 6 ወራትን ቀይ የትራፊክ መብራት ወደ አረንጓዴ እስኪለወጥ ይጠብቃል፡፡
· የሰው ልጅ ተኝቶ ሳለ፤ በአማካይ 70 የተለያዩ ነፍሳትንና
10 ሸረሪቶችን ይበላል ወይም ወደ ሆዱ ያስገባል፡፡
· ሰው እስትንፋሱን በመግታት ነፍሱን ማጥፋት
አይችልም፡፡

Monday, 05 December 2016 09:57

የማሰላሰያ ጥግ

 ለመጨረሻ ጊዜ አዲስ ነገር የሞከራችሁት መቼ ነው?
መኖር የምትችሉት ለ1 ዓመት ብቻ ቢሆን፣ ምን ለማሳካት ትፈልጋላችሁ?
ዓይናችሁን ስትጨፍኑ ምን ታልማላችሁ?
ስለራሳችሁ እጅግ አድርጋችሁ የምትወዱት ምንድን ነው?
ህይወታችሁን እንደ ፊልም ብትቆጥሩት፣ ርዕሱን ምን ትሉታላችሁ?
ራሳችሁን በ5 ቃላት እንዴት ትገልጹታላችሁ?
በጣም የምትኮሩበት ነገር ምንድ ነው?
ህይወት ትላንት ምን አስተማረቻችሁ?
ምን መጥፎ ልማዶችን ማቆም ትፈልጋላችሁ?
እናንተን ልዩ የሚያደርጋችሁ ምንድ ነው?
በጣም የምትፈልጉት ነገር ምንድን ነው?

ባለፈው 1 ዓመት የታተሙ መፃህፍት ይወዳደራሉ
     በረዥም ልቦለድ፣ በግጥምና በልጆች መፃህፍት ዘርፍ የሥነ ፅሁፍ ሥራዎች ተወዳድረው ሊሸለሙ ነው።
ኖርዝ ኢስት ኤቨንትስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃህፍት ኤጀንሲ ጋር በትብብር ያዘጋጁት ሆሄ የሥነፅሁፍ ሽልማት ፕሮግራም፤ አሸናፊ ደራስያንን ከመሸለም ባሻገር የንባብ ባህል እንዲስፋፋ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ላበረከቱ ክበባትንና ቤተ መፃህፍትም የሚመሰገኑበትና ዕውቅና የሚያገኙበት ይሆናል ተብሏል፡፡
የሽልማት ፕሮግራሙ አዘጋጆች ከትናንት በስቲያ በጎተ ኢንስቲትዩት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ለውድድር የሚቀርቡት መፃህፍት ከመስከረም 1 ቀን 2008 እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ የታተሙ መሆን አለባቸው፡፡ ተወዳዳሪ መፃህፍቱ በዳኞች ኮሚቴ በተዘጋጀላቸው መስፈርቶች መሰረት የሚመዘኑ ሲሆን በዳኞች ኮሚቴ ከሚሰጠው ውጤት በተጨማሪ አንባቢያን በነፃ የስልክ መልዕክትና በድረ ገፅ የሚሰጡት ድምፅም የተወሰነ ነጥብ ይኖረዋል ተብሏል። አጠቃላይ ውጤቱ የሚታወቅ ይሆናል፡፡
በውድድሩ መሳተፍ የሚፈልጉ ደራሲያን ከታህሳስ 4-19 2009 ዓ.ም ሞርኒንግ ስታር ሞል ላይ በሚገኘው የድርጅቱ ቢሮ፣ በጎታ ኢንስቲቲዩትና በቡክላይት መፅሀፍ መደብር መመዝገብ እንዳለባቸው የጠቆሙት አዘጋጆቹ፤ የሽልማት ስነ ስርዓቱ በሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡


      እናት የማስታወቂያ ስራዎች ድርጅት ከጀርመን የባህል ማዕከልና ከወመዘክር ጋር በመተባበር “አማካሪው አልፍሬድ ኤልግ በምኒልክ ቤተ-መንግስት” በሚል ርዕስ በዮናስ ታረቀኝ ወደ አማርኛ በተተረጎመው ታሪካዊ መፅሀፍ ላይ በነገው ዕለት ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በወመዘክር አዳራሽ ውይይት ይካሄዳል፡፡
ለውይይቱ የመነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት አቶ ብርሀኑ ደቦጭ ሲሆኑ በውይይቱ የመሳተፍ ፍላጎት ያለው ሁሉ እንዲገኝ ተጋብዟል፡፡

የኖቤል ተሸላሚዎችን አነጋግረዋል
     የአመቱ የኖቤል የስነጽሁፍ ተሸላሚ በመሆን የተመረጠውና “ስራ ስለሚበዛብኝ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ አልገኝም” በማለቱ የዓለማችን መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው አሜሪካዊው ድምጻዊና የሙዚቃ ግጥም ደራሲ ቦብ ዳይላን፣ ባለፈው ረቡዕ ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር በዋይት ሃውስ እንዲገናኝ የቀረበለትን ግብዣ ባለመቀበል በስነስርዓቱ ላይ ሳይገኝ መቅረቱ ተዘግቧል፡፡
ኦባማ የዘንድሮ የኖቤል ተሸላሚ አሜሪካውያንን ከሽልማት ስነስርዓቱ በፊት በዋይት ሃውስ ለማግኘት ባለፈው ረቡዕ በያዙት ቀጠሮ፣ ሌሎች ተሸላሚዎች በስፍራው ቢገኙም ልማደኛው ዳይላን ግን ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የውሃ ሽታ ሆኖ በመቅረት ዳግም የመገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሊሆን እንደበቃ የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ይጠቁማል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ዳይላን ተሸላሚ መሆኑ ይፋ የተደረገ ሰሞን፣ “ከምወዳቸው ገጣሚያን አንዱ የሆነው ዳይላን ሽልማቱ ይገባዋል” በማለት የእንኳን ደስ አለህ መልዕክት ያስተላለፉለት ሲሆን  እ.ኤ.አ በ2012 ታላቁን የአገሪቱ የነጻነት ሜዳይ ሽልማት አበርክተውለት እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡
ምንም እንኳን ዳይላን ባይገኝም፣ ኦባማ በዕለቱ የፊዚክስ ኖቤል ተሸላሚዎቹን ዳንካን ሃልዳኔን  ማይክል ኮስተርሊዝን፣ የኢኮኖሚክስ ተሸላሚውን ኦሊቨር ሃርትን እንዲሁም የኬሚስትሪ ተሸላሚውን ሰር ጄ ፍሬዘር ስቶዳርትን  በዋይት ሃውስ በክብር ተቀብለው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈውላቸዋል፤ ለስራቸውም እውቅና ሰጥተዋቸዋል፡፡