Administrator

Administrator

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል

   የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍሊፕ ሃሞንድ በእንግሊዝና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ በማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረገ ጉብኝት ለማድረግ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ ከትናንት በስቲያ በድረ-ገጹ አስታወቀ፡፡ባለስልጣናቱ ኢትዮጵያን የመጎብኘት እቅድ እንዳላቸው ያስታወቁት፣ ባለፈው ረቡዕ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የመከሩት የእንግሊዝ የአገር ውስጥ ጉዳይ ቢሮ ሁለተኛ ቋሚ ጸሃፊ ኦሊቨር ሮቢንስ መሆናቸውን ቢገልጽም፣ ጉብኝቱ የሚከናወንበትን ጊዜ በተመለከተ ግን ያለው ነገር የለም፡፡ ሁለቱ የእንግሊዝ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙትና እንግሊዛዊ ዜግነት ያላቸው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈቱና በቆንስላ ተወካዮች የሚጎበኙበት ሁኔታ እንዲመቻች የሚጠይቅ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ቢልኩም መንግስት ግን ይህ ነው የሚባል ምላሽ አለመስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ጉብኝቱ ዴቪድ ካሜሩን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ላይ ከወጡ ወዲህ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡበት የመጀመሪያው ጉብኝት ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር እ.ኤ.አ በ2004 ኢትዮጵያን ጎብኝተው እንደነበር ይታወሳል፡፡

    ሪንጊንግ ቤልስ የተባለው የህንድ የሞባይል ቀፎዎች አምራች ኩባንያ፣ በዓለማችን የስማርት ፎን ገበያ እጅግ ርካሽ ዋጋ የተተመነለትን ፍሪደም 251 የተባለ አዲስ የሞባይል ቀፎ ምርቱን በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ለገበያ እንደሚያቀርብ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ፡፡ከጥቂት ወራት በፊት የተቋቋመው ኩባንያው፣ለዚህ የሞባይል ቀፎ 7.3 ዶላር የመሸጫ ዋጋ የተመነለት ሲሆን የሞባይል ቀፎው 8 ጊጋ ባይት ሚሞሪ ያለውና በፊቱና በኋላው ሁለት ካሜራዎች የተገጠሙለት ነው ተብሏል፡፡ ኩባንያው በቅርቡም በአገሪቱ የ4ጂ የሞባይል ቀፎ ገበያ እጅግ እርካሹ ዋጋ የተተመነለትን ምርቱን ለገበያ ማብቃቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ አዲሱን የሞባይል ቀፎውን የመገጣጠም ስራውን እንደጀመረና ምርቱን በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ለአገር ውስጥ ገበያ ያቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድቷል፡፡
ህንድ በአለማችን የሞባይል ቀፎ ገበያ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ በአገሪቱ አንድ ቢሊዮን ያህል የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች እንዳሉም ገልጧል፡፡

   በምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አገራት የሚገኙ 1 ሚሊዮን ያህል ህጻናት የኤሊኖ ክስተት ባስከተለው ድርቅ ሳቢያ የከፋ የምግብ እጥረት ተጠቂዎች መሆናቸውንና አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ዩኒሴፍ አስታወቀ፡፡ በአካባቢው አገራት የሚገኙት እነዚህ ህጻናት የምግብና የውሃ እጥረት እንዳለባቸውና የክብደት መጠናቸው እየቀነሰ እንደሚገኝ የጠቆመው ተቋሙ፣ የምግብ ዋጋ መናር ቤተሰቦች ሳይመገቡ እንዲውሉና ንብረቶቻቸውን ሽጠው ምግብ እንዲገዙ እያስገደዳቸው ነው ብሏል፡፡መንግስታት ችግሩን ለመቋቋም የራሳቸውን ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፣ በህጻናቱ ላይ የተከሰተው የከፋ የምግብ እጥረት አሳሳቢ ነው ተብሏል፡፡ሌሴቶ፣ ዚምባቡዌና አብዛኞቹ የደቡብ አፍሪካ አገራት ድርቁን ተከትሎ አስቸኳይ እርዳታ እንደሚፈልጉ ማስታወቃቸውን የዘገበው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፣ በኢትዮጵያም የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር በዚህ አመት ከ10 ሚሊዮን ወደ 18 ሚሊዮን ከፍ ይላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጧል፡፡ማላዊ ባለፉት 9 አመታት የከፋ በተባለው የምግብ እጥረት እንደተጠቃች ያስታወሰው ዘገባው፣ 15 በመቶ ያህል ህዝቧ የርሃብና የከፋ የምግብ እጥረት ችግር እንዳንዣበበበት አክሎ ገልጧል፡፡

“ትራምፕ በምርጫው አሸንፎ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አይሆንም!...” ባራክ ኦባማ
             “በአሜሪካ ታሪክ እጅግ ቀሽሙ ፕሬዚዳንት ኦባማ ነው!...” ዶናልድ ትራምፕ
    ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማና በመጪው የአሜሪካ ምርጫ ሪፐብሊካንን ወክለው ለመወዳደር በምርጫ ክርክር ተጠምደው የሰነበቱት አነጋጋሪው የሪልስቴት ከበርቴ ዶናልድ ትራምፕ የቃላት ጦርነት ውስጥ መግባታቸው ተዘገበ፡፡
ኦባማ ባለፈው ሰኞ ካሊፎርኒያ ውስጥ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ትራምፕ በምርጫው አሸንፈው ቀጣዩ የአሜሪካ መሪ ሊሆኑ አይችሉም፤ ምክንያቱም አገርን መምራት ዕቃ ዕቃ ጨዋታ አይደለም! የአገሬ ህዝብ እንዲህ ያለ ሰው እንዲመራው እንደማይፈቅድ ስለማውቅ፣ ትራምፕ አሸንፎ ፕሬዚዳንት እንደማይሆን አምናለሁ ሲሉ መተቸታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡“የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆን፣ የቶክ ሾው መምራት አይደለም!... በምርጫ ማሸነፍም፣ ሰፊ ማስታወቂያ የመስራትና የገበያ ጥናት የማድረግ ጉዳይ አይደለም፡፡ ከባድ ተልዕኮ ነው!...” ብለዋል ኦባማ የትራምፕን አካሄድ በመተቸት፡፡ኦባማ ይሄን ማለታቸውን ተከትሎም፣ በምርጫ ክርክር ተወጥረው የሰነበቱት ዶናልድ ትራምፕ፤ በነጋታው ረቡዕ ለኦባማ ትችት መረር ያለ የአጸፋ ምላሽ መስጠታቸውን ሲኤን ኤን ዘግቧል፡፡“በአሜሪካ ታሪክ እጅግ ቀሽሙ ፕሬዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ ነው!... እሱ የሚሰራውን ነገር የማያውቅ፣ የአገር መሪ ነኝ የሚል ቀሽም ሰው ነው!... በ2012 ምርጫ በዕጩ ተወዳዳሪነት ብቀርብ ኖሮ፣ ኦባማን በቀላሉ ዘርሬ ስልጣኑን እይዝ እንደነበር ቅንጣት ታህል አልጠራጠርም!” ብለዋል ትራምፕ፡፡

ቫይረሱ በ39 አገራት ተሰራጭቷል
    የዓለም የጤና ድርጅት፤ ነፍሰጡሮችን በማጥቃት የጭንቅላት መጠናቸው አነስተኛና የአእምሮ እድገታቸው ውስን የሆኑ ህጻናት እንዲወለዱ የሚያደርገውን ዚካ ቫይረስ ለመዋጋት ለሚከናወኑ ስራዎች 56 ሚ ዶላር ያስፈልጋል ማለቱን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ገንዘቡ በተለይ በደቡብ አሜሪካ አገራት በመስፋፋት ላይ ለሚገኘው ዚካ ቫይረስ በአፋጣኝ ክትባት ለመፍጠር፣ በቫይረሱ የተጠቁትን ለመመርመርና በጉዳዩ ዙሪያ ዘላቂ መፍትሄ የሚያመነጩ ምርምሮችን ለማድረግ እንደሚውል የጠቆሙት የድርጅቱ ጄኔራል ዳይሬክተር ማርጋሬት ቻን፣ ቫይረሱ ወደ 39 የአለማችን አገራት በመስፋፋቱ በአፋጣኝ መፍትሄ መፈለግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ የሚፈለገውን ገንዘብ ከአባል አገራትና ከለጋሾች አገኛለሁ ብሎ እንደሚጠብቅ የገለጹት ቻን፣ ሰሞኑን ቫይረሱ ክፉኛ ወደተስፋፋባት ብራዚል አምርተው ድርጅቱ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እያከናወነ የሚገኘውን ስራ እንደሚገመግሙና ከአገሪቱ የጤና ሚኒስትር ጋር በጉዳዩ ዙሪያ እንደሚወያዩም ተናግረዋል፡፡

    በኢትዮጵያ የህብረት ስራ ማህበራት ታሪክ 50 ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ማህበራቱ በስርአት ተደራጅተው፤ በፖሊሲ ታቅፈው ሥራ ከጀመሩ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አልሆናቸውም፡፡ በአሁኑ ሰዓት የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመርና ወደ ውጪ በመላክ ለአገሪቷ ገቢ ያስገባሉ፡፡ ምርጥ 10 ከሆኑት ቡና ላኪዎች ውስጥ አብዛኞቹ የህብረት ሥራ ማህበራት ናቸው፡፡ ነገር ግን የሚጠበቅባቸውን ያህል እየሰሩ አይደለም ይባላል፡፡ በሌላ በኩል ለማህበራቱ ተገቢው ትኩረት አልተሰጠም የሚል ቅሬታ ይሰነዘራል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ማህሌት ኪዳነወልድ፤ የፌደራል ህብረት ሥራ ማህበር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩርን በማህበራቱ እንቅስቃሴ፣ችግሮችና የወደፊት ትልሞች ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡  
የማህበራቱ አላማ ምንድን ነው?
እንግዲህ ማህበራት ለአርሶ አደሩ፣ ለአርብቶ አደሩ፣ እንዲሁም ለዝቅተኛው ማህበረሰብ ትልቅ ጠቀሜታ አላቸው፡፡ የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር፣ አርሶ አደሩ ላመረተው ምርት ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ፣ በገጠር የፋይናንስ ስርአት ቅርፅ እንዲይዝ… በአጠቃላይ የአንድ አገር ኢኮኖሚ እድገት ዘላቂ እንዲሆን ከተፈለገ፣ የማህበራቱ ሚና በተለይም በግብርናው ዘርፍ መተኪያ የለሽ ነው፡፡
አጠቃላይ እንቅስቃሴያችሁ ምን ይመስላል?
እንግዲህ በአጠቃላይ ማህበራቱ ከ15.8 ቢ. ብር በላይ ካፒታል አላቸው፡፡ ከ802ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡ በተለይም የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመርና ወደ ውጪ በመላክ ለአገሪቷ ገቢ ያስገባሉ፡፡ በተለይ በቡናና ሰሊጥ ምርቶች፡፡ ምርጥ 10 ከሆኑት ቡና ላኪዎች ውስጥ አብዛኞቹ የህብረት ሥራ ማህበራት ናቸው፡፡
ከዚያም በላይ መንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በመቅረፅ ሚናቸውን በማያሻማ መልኩ አስቀምጧል፡፡ እንግዲህ ይህን ያልኩት ጠቀሜታቸውን በአጭሩ ለማሳየት ነው፡፡ ሆኖም የሚጠበቅባቸውን ያህል እየሰሩ አይደለም፡፡ በርካታ ቀሪ ነገሮች አሉ፡፡ በፖሊሲው ላይ እንደተቀመጠው ከሆነ፣ አሁን የምናየው ውጤት በቂም ብቁም አይደለም፡፡ ትልቅ የአመለካከት ችግር አለ፡- በአመራሩ፣ በተደራጀው ክፍል፣ በአደራጁ… በሁሉም በኩል፡፡ አንዳንዱ ማህበራቱን የደርግ ሶሻሊስት ስርአት ማስፈፀሚያ አድርጎ የማሰብ፣ የደሃ መሰብሰቢያ እንዲሁም ከእድርና ከእቁብ የተለየ ተቋም አድርጎ ያለማየት ችግሮች አሉ፡፡ ይህ ችግር ማህበራቱ ማግኘት ያለባቸውን ድጋፍ እንዳያገኙ እያደረገ ነው፡፡ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግር አለባቸው፡፡ መጋዘን የላቸውም፡፡ መስሪያ ቦታ፣ ቢሮ የለም፡፡ ይህንን ማቅረብ ያለበት አካልም የዝግጅት ችግር አለበት፡፡ ፖሊሲው አንድ ሆኖ፣ ከክልል ክልል አፈፃፀሙ ይለያያል፡፡ ወደ ዞንና ወረዳ ስትወርጂ ደግሞ ችግሩ እጅግ የከፋ ነው፡፡ ሌላው ነገር ብድር ነው፡፡ በቂ ብድር የለም፤ የብድር ጉዳይ ትልቅ ማነቆ ነው፡፡ ማህበራቱ ብድር የሚያገኙበት ማእቀፍ የለም፡፡ ስለሆነም ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ማበርከት ያለባቸውን አስተዋፅኦ አላበረከቱም፡፡ በተጨማሪም ብዙዎቹ ማህበራት በኮሚቴ እንጂ በባለሙያ አይመሩም፡፡ ምርቱ ተወዳዳሪ ቢያደርጋቸውም ወደ ተግባር የሚቀይር ባለሙያ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እንግዲህ ፖሊሲውን በማስፈፀም የመሰረተ ልማት ችግርን ለመፍታት እየሰራን ነው፡፡ ፋይናንስ አካባቢ ግን ገና መታየት አለበት፡፡ አማራጮች ሊቀመጡ ይገባል፡፡
መንግሥት ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት አልሰጠም እያሉኝ ነው?
መንግሥት በፖሊሲ ማእቀፍ ያስቀመጠው አቅጣጫ፣ የሰጠው ትኩረት አለ፡፡ ትኩረት ስንል ከፌደራል እስከ ክልል ነው፡፡ እንግዲህ መንግስት ስንል፤ ክልል፣ ዞን፣ ወረዳ፣ ቀበሌ እያለ ይወርዳል፡፡ ያው ትኩረት አሰጣጡ ከክልል ክልል ይለያያል፡፡ ትኩረቱ በእርግጥ በቂ አይደለም፡፡ እንደውም ወደ ታች ከክልል ወረዳ እያለ ሲወርድ… ጭራሽ የለም ማለት ይቻላል፡፡ አንዳንዱ ክልል የህብረት ስራ ጉዳይን የመጨረሻ አጀንዳው ያደርገዋል፡፡ እንግዲህ በGTP2 የተሻለ ነገር ለማየት ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በተለይ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከማህበር አገልግሎትና ብዛት እንዲሁም ከተማዋ ዋና የገበያ ማእከል ከመሆኗ አንፃር፣ ለማህበራት የሰጠው ትኩረት እጅግ አናሳ ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ማህበራቱ ከዘይትና ስኳር ስርጭት ጋር በተያያዘ በረጅም ሰልፍና አንዳንዴም የለም በማለት ነው የሚታወቁት …?
ህብረት ስራ ማህበራት በዋናነት የሚደራጁት ለዘይት፣ ስኳርና ዱቄት ብቻ አይደለም፡፡ በርካታ ምርቶችን ያቀርባሉ፤ በተለይ ግብርናው ላይ፡፡ ምንድነው --- መንግስት በድጎማ የሚያቀርባቸው እነዚህ ምርቶች ላይ የአቅርቦትና የፍላጎት ያለመጣጣም ችግር አለ፡፡ ስለሆነም አነስተኛ ገቢ ላለው ህብረተሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ በማህበራት በኩል ያቀርባል፡፡ በመዲናዋ ከ130 የሚበልጡ ማህበራት አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከ30 በማያንሱት ላይ ኪራይ ሰብሳቢነት ሊታይ ይችላል፡፡ በጓሮ በር እያወጡ የሚሸጡ መኖራቸው አይካድም፤ተከታተለንም እርምጃ እየወሰድን ነው፡፡ ነገር ግን በጅምላ መጥላትና መንግስት ለራሱ ጥቅም ያደራጃቸው ተቋማት አድርጎ ማየቱ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህንን ነው እንግዲህ ቅድም የአመለካከት ችግር አለ ያልኩሽ፡፡ የማህበራቱ መልካም ስራ አብሮ መነሳት አለበት፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ፒያሳ፣ ማህበራቱ አንድ ኪሎ የቁርጥ ስጋን ከ80-90 ብር ይሸጣሉ፡፡ ሌላ ቦታ ከ180-200 ብር ሲሸጥ እያየን ነው፡፡ 1 ኪሎ ሽንኩርት ከ6-7 ብር ይሸጣሉ፡፡ በሌላው ገበያ 12 እና 14 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ማህበራቱ ከ30 እስከ 120 በመቶ የዋጋ ልዩነት አላቸው፡፡
እንግዲህ ማህበራቱ ባለፈው ዓመት 4.5 ቢ. ብር ምርት ሸጠዋል፡፡ ከ30 እስከ 120 በመቶ የዋጋ ልዩነት አላቸው ካልን፣ በአማካይ ወስደን በ60 ብናበዛው እንኳን ብዙ ሚሊዮን ብሮች ተጠቃሚ ኪስ ገብቷል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሀብት ክፍፍሉን ፍትሃዊ ያደርገዋል፡፡
ወደተለያዩ የውጭ አገራት በመሄድ ተሞክሮ ወስዳችኋል፤ ተሞክሮው ምን ይመስላል?
እነ ጃፓን፣ ኦስትሪያ፣ ታይላንድ፣ ማሌዢያና አውሮፓ… ለህብረት ስራ ማህበራት የድጋፍ ማእቀፎች አሏቸው፡፡ የፋይናንስ ችግርን ለመፍታት የተለየ ባንክ ፣ የተለየ የፖሊሲ ማእቀፍ አላቸው፡፡ ለምሳሌ ደቡብ ኮሪያ ሦስት አይነት ባንክ አላት፡- ንግድ ባንክ፣ ህብረት ስራ ባንክና ፖሊሲ ባንክ ናቸው፡፡ የትኛውም ማህበር የገንዘብ እጥረት ሲገጥመው ቢዝነስ ፕላን አቅርቦ ብድር ያገኛል፡፡ የሚሰራበት ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ግብር ነፃ ነው፡፡ ሌላም ሌላም፡፡ በእኛ ሀገር አንዳንዱ አዋጁ ላይ አለ፤ ነገር ግን አተገባበር ላይ ችግር አለ፡፡ አንዳንድ አዋጆችም ማሻሻያ እንዲደረግባቸው እየጠየቅን ነው፡፡ ማህበራቱ የዜጎቻቸውን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆን አለባቸው፡፡ መንግስታት ሲቀያየሩ የኢኮኖሚ እድገትን የሚያስቀጥሉ ሊሆኑ ይገባል፡፡
ከ5 እና 6 ዓመታት በፊት አውሮፓና አሜሪካ የፋይናንስ ችግር ሲገጥማቸው ማህበራት ግን ሳይነኩ ወጥተዋል፡፡ ጃፓን ግብርናዋ የሚመራው በህብረት ስራ ነው፡፡ ሰሞኑን ያዘጋጀነው ኤግዚቢሽንና ባዛር ከነሱ በወሰድነው ተሞክሮ፣ የገበያ ትስስርን ለመፍጠር ያለመ ነው፡፡ በሌሎች አገራት ማህበራት በ50 እና 60ሺ ካሬ ላይ ያረፈ ትልልቅ የገበያ ማዕከላትም አሏቸው፡፡ እንግዲህ ቅድም 13.3 ሚ. ዜጎች የማህበራት አባል ናቸው ብዬሻለሁ፤ ይህንን ቁጥር በ5 ቤተሰብ እንኳን ብናበዛው እያወራን ያለነው ስለ 60ሚ. ህዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ከተፈለገ የአመለካከት ችግሮች ተቀይረው የሚገባቸውን ትኩረት ሊያገኙ ይገባል፡፡ በእርግጥ ማስተዋወቁ ላይ እኛ ዘንድም ክፍተት አለ፡፡ በቀጣይ የምንሰራበት ይሆናል፡፡
በአሁኑ ወቅት ስንት የህብረት ሥራ ማህበራት አሉ?
ከ71 ሺህ በላይ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት፣ ከ353 ሺህ በላይ የህብረት ስራ ዩኒየኖች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ከ13.3 ሚ. በላይ ዜጎች የህብረት ስራ ማህበራት አባል ናቸው፡፡

    የተባበሩት የአረብ መንግሥታት ንብረት የሆነው ፍላይ ዱባይ አየር መንገዱ ከወር በፊት በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት ባደረገው እንቅስቃሴ ስኬታማ እንደነበር አስታወቀ፡፡
 አየር መንገዱ በዓመቱ ውስጥ 81,530 በረራዎችን በማድረግና 9.04 ሚሊዮን ተሳፋሪዎችን በማጓጓዝ፣ 27.4 ሚሊዮን ዶላር ያገኘ ሲሆን የተጓዞቹ ብዛት ከ2014 ጋር ሲነፃፀር በ1.8 ሚሊዮን ሰዎች ብልጫ (25 በመቶ መጨመሩን) እንዳለውና ለ4ኛ ዓመት ትርፋማ መሆኑን ገልጿል፡፡
አጠቃላይ ገቢው 1.33 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ከ2014 ጋር ሲነፃፀር የ11 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በአንዳንድ መዳረሻ መስመሮች በሚፈጠሩ እገዳዎች ብዙ መስተጓጎሎች መፈጠራቸውንና ከአዳዲስ የበረራ መስመሮች ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ግፊትና ጫና እንደነበረበትም አመልክቷል፡፡
የፍላይ ዱባይ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሚ/ር ጋኢዝ አል ጋኢዝ፤ አጠቃላይ የንግድ ሁኔታው ፈታኝ ቢሆንም የዕድገት ታሪካችንን በመጠበቅ ዓመቱን በስኬት አጠናቀናል ብለዋል፡፡ 

“ዘ ዊክንድ” በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀውና ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ አለማቀፍ ዝናን በማትረፍ ላይ የሚገኘው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ፣ በሳምንቱ መጀመሪያ በተካሄደው የዘንድሮው የግራሚ ሽልማት ስነስርዓት በሁለት ዘርፎች ተሸላሚ ሆኗል፡፡
በዘንድሮው የግራሚ ሽልማት በሰባት ዘርፎች ለሽልማት ታጭቶ የነበረው አቤል ተስፋዬ፤ ሎሳንጀለስ ውስጥ በተከናወነው 58ኛው የግራሚ ሽልማት ስነስርዓት ላይ፣ “ቤስት ኧርባን ኮንቴምፖራሪ አልበም” እና “ቤስት አር ኤንድ ቢ ፐርፎርማንስ” በተሰኙት ሁለት ዘርፎች አሸናፊ በመሆን ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡
“ቢዩቲ ቢሃይንድ ዘ ማድነስ” የተሰኘው አልበሙ በ“ቤስት ኧርባን ኮንቴምፖራሪ አልበም”፣ “ኧርንድ ኢት” የተሰኘው ስራው ደግሞ  በ“ቤስት አር ኤንድ ቢ ፐርፎርማንስ” ዘርፎች ለሽልማት እንዳበቁት የተዘገበ ሲሆን፣ ባለፈው ሰኞ ምሽት በተካሄደው የሽልማት ስነስርዓቱ ላይ የሙዚቃ ስራዎቹን ለተመልካቾች አቅርቧል፡፡
በዘንድሮው የግራሚ ሽልማት ካሸነፉት ድምጻውያን መካከል ቴለር ስዊፍት፣ ኬንድሪክ ላማር እና ኤሚ ዋይንሃውስ ይገኙበታል፡፡

Saturday, 20 February 2016 09:44

የዘላለም ጥግ

(ስለ ዲሲፕሊን)
- ዲሲፕሊን በግብና በስኬት መካከል ያለ
ድልድይ ነው፡፡
ጂም ሮህን
- አንድ ጊዜ ቁርጠኝነቱ ካለህ ያሰብክበት
ለመድረስ ዲሲፕሊንና ተግቶ መስራት
ይኖርብሃል፡፡
አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ
- ያለ ዲሲፕሊን ህይወት ጨርሶ የለም፡፡
ካታሪን ሄፕበርን
- ማህበራዊ ሚዲያ ጊዜህን እንዳይሰርቅብህ
ዲሲፕሊን ያስፈልግሃል፡፡
አሌክሲስ ኦሃንያን
- በራስ መተማመን የሚመነጨው
ከዲሲፕሊንና ከልምምድ ነው፡፡
ሮበርት ኪዮሳኪ
- ስኬት የሚለካው ባለህ ዲሲፕሊንና
በውስጣዊ ሰላምህ ነው፡፡
ማይክ ዲትካ
- ጥሩ ዲሲፕሊን ቢኖረኝ ኖሮ ወደ ሙዚቃ
ሙያ እገባ ነበር፡፡
ክሊንት ኢስትውድ
- ዲሲፕሊን ማለት የምትፈልገውን ነገር
ማስታወስ ነው፡፡
ዴቪድ ካምቤል
- አንዳንድ ሰዎች ዲሲፕሊንን እንደ ሥራ
ይቆጥሩታል፡፡ ለእኔ በነፃ እንድበር
የሚያደርገኝ የስርዓት ዓይነት ነው፡፡
ጁሊ አንድሪውስ
- የስኳር በሽታ ዲሲፕሊንን አስተምሮኛል፡፡
ሶንያ ሶቶማዮር
- ጥቂት ሰዎች ጀግና ሆነው ይወለዳሉ፡
፡ ብዙዎች የሚጀግኑት በልምምድና
በዲሲፕሊን ኃይል ነው፡፡
ፑብሊዩስ ፍላቪዩስ ቬጄቲዩስ ሬናቲዩስ
- ዲሲፕሊን? የቃሉን ትርጉም አላውቀውም፡፡
ሊያም ጋላግሄር
- አማፂ ለሆነ ሰው ዲሲፕሊን ከባድ ነው፡፡
ጆናታን ዊንተርስ

    ስሙ ያልታወቀ ፀሐፊን ጠቅሶ አንድ የኛ ፀሐፊ ያቀረበውን ለዛሬ ተረት እናርገው
ዐጼ ቴዎድሮስ አንድ ቀን አንድ የሚያምኑትን ዘበኛ ይዘው፣ አልባሌ መስለው ከጨለመ በኋላ በሠፈሩ ይዞሩ ጀመር፡፡ በየጐጆው እየተጠጉ ያደምጡ ነበር፡፡ እኩሉ ያልተኛ እኩሉም ተኝቶ፡፡ ከዝያ ወዲያ ካንድ ወታደር ጐጆ ተጠግተው ቢያደምጡ ባልና ምሽት በግብረ - ሥጋ ሲጣሉ ሰሙ፡፡ ወንዱ ይለምናል፡፡ ሴቲቱ አይሆንም ትላለች፡፡ ከዝያ ወዲያ ወንድየው፤
“በማርያም”፣ በሥላሴ፣ “በጻድቃን በቅዱሳን” እያለ ቢለምን፤ ሴትዮዋ፣
“እምቢ አይሆንም” ትላለች፡፡
ሰውየው፤
“ኧረ በሥላሴ ይሁንብሽ?”
“በጭራሽ ስልህ? አሻፈረኝ አልኩኮ!”
“በጻድቃን በቅዱሳን?”
“ሰውየው፤ እምቢ ማለት አይገባህም?”
ሰውየው የመጨረሻ ሙከራ አደረገ፡፡
“በይ በቴዎድሮስ ሞት…” አላት፡፡
“ቴዎድሮስማ ከሚሞት፣ ጐንደር አይታረስም” አለችና ፈቀደች፡፡
ንጉሡ ይሄንን ከሰሙ በኋላ እየሳቁ ወደ አዳራሻቸው ገቡና፣ ያን አብሮአቸው የነበረ ዘበኛ፤ ያችን ጐጆ እንዳታሳስትህ አስተውላት ብለውት ነበረና በነጋታው ያንን ዘበኛ፤
“ባልና ሚስቱን ጠርተህ አምጣቸው” ብለው ሰደዱት፡፡
ባልና ሚስቱም፤
“ምን ተገኘብን ይሆን?” ብለው እየተንዘፈዘፉ፣ እየተንቀጠቀጡ መጡና ከጃንሆይ ፊት ቆሙ፡፡
ንጉሡም፤
“እንዴት አደራችሁ?” አሉ፡፡
እነዚያም እየተብረጀረጁ ሳይሰሙ ቀርተው ኖሮ ባጠገባቸው የቆመ ቢነግራቸው በግንባራቸው ተደፍተው እጅ ነስተው ቆሙ፡፡
ቀጥለውም ንጉሡ፤
“ትላንት ማታ በምኝታ ጊዜ ከቤታችሁ ሆናችሁ ተናገራችሁ?” ብለው ጠየቋቸው፡፡
“ጃንሆይ የተናገርነው የለም፡፡ ጠላት ነገር ሠርቶብን እንደሆነም ያጋጥሙኝ፤ ድኻ ወታደር ባሪያዎ ነኝ፡፡”
“ከመኝታችሁ ላይ ጥቂት የተናገራችሁት ነገር እንዳለ አስበህ ንገረኝ አይዞህ” አሉት፡፡
እሱም ሰውነቱን አጠናከረና አስቦ፣ ያንን ምሽቱ ያደረገችውን ነገር ነገራቸው፡፡ ንጉሡም ሳቁ፡፡ ሴቲቱም አፈረች፡፡
***
“በኃይለስላሴ አምላክ ተወኝ!”፣ “በንጉሥ ይዤሃለሁ ተወኝ”፣ “በህግ አምላክ” ዱሮ ቀረ፡፡ የንጉሥ ስም ተጠርቶ አትንካኝ፣ አትምታኝ፣ መብቴን አትንካ፣ ማለት ጥንት የተለመደ ነበር፡፡ ዛሬ ያ ልማድ ቀርቷል፡፡ ማንም አይሰማም፡፡ ነገሥታቱ በህዝቡ የየዕለት ህይወት ውስጥ ይገቡ ነበር፡፡ የመፈራታቸውም መጠን ወሰን የለውም፡፡ ዛሬ ህጉ እየተለወጠ፣ ዘመኑ ጤና እያጣ መጥቷል፡፡
ዛሬ ከሽማግሌው ይልቅ ወጣቱ ጤና አጥቷል፡፡ በቀላሉ ይሸነፋል፡፡ የትምህርት አቅሙ ደካማ በመሆኑ ዕውቀቱ አገም ጠቀም ነው፡፡ ከመማር ማማረር የሚመርጠው እየበረከተ፤ የሚያመረው እየሳሳ መጥቷል፡፡ ቁርጠኝነት ጠፍቷል፡፡ ለሱስ ተገዥነት የማያጠያይቅ አደጋ ነው፡፡ የወሲብ ማጠናከሪያ ዕንክብል ካዋቂው ይልቅ የለጋው ወጣት ማዳበሪያ ሆኗል፡፡ ዛሬ በሪህ በሽታ የሚያዘው ወጣቱ ሆኗል፡፡ ንቅዘት (degeneration)  የወቅቱ ትዕዛዝ ይመስላል፡፡ ይቅር ይበለን እንጂ ምን ይባላል፡፡ እጅግ አሳሳቢ ነው!
“አረጋዊውን ባንቀልባ፣ ከምንሸከም እንኮኮ
ጐልማሳውን ከወኔ ጣር፣ ካልፈታን ከፍርሃት ምርኮ” የሚለን ነው ፀጋዬ ገ/መድህን፡፡
ሌላው ጣራችን ዲሞክራሲ ነው፡፡ ማንም መንግሥት፣ ገዢ ፓርቲ ወይም ተቃዋሚ ድርጅት ልብ ሊል የሚገባው ዲሞክራሲ የትግል ሂደት ውጤት እንጂ መና እንዳልሆነና አሸናፊ ከተሸናፊ ጋር የመቻቻል ግዴታ እንዳለበት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ስለባለጋራዎቻችን ኡምቤርቶ ኢኮ የሚለንን ማዳመጥ እጅግ ተገቢ ነው፤
“መልካም ምግባር የሚከሰተው የባለጋራዎቻችንን መኖር በመካድ ሳይሆን፣ ባላጋሮቻችንን በቅንነት በመረዳት፣ በነሱ ቦታ ሆነን ነገሮችን በመመልከት ነው፡፡ ሌሎችን በቅንነት መረዳት ማለት ልዩነትን ሳንክድ ወይም ቸል ሳንል፣ የአድልኦ አስተያየቶችን ማስወገድ ማለት ነው”
አንድ የሀገራችን ፀሐፊም “መቻቻል መቻል ነው፡፡ መቻል ሳይኖር መቻቻልን ማሰብ ከባድ ነው” ይለናል፡፡ ትላንት ያሳደግነውን ቂም በቀል ነቅለን መጣል አለብን፡፡ ከዓመት ዓመት አንድ ዓይነት መላ ምት እየተለምን፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በአቦ ሰጡኝ መጓዝ፣ ባለበት ሂድ እንጂ ወደፊት አያራምደን፡፡ One step forward two steps back እንደሚሉት እንዳይሆን እንጠንቀቅ፡፡ አንድ ወደፊት ሁለት ወደኋላ ጐታች ጉዞ ነው፡፡ የለማውን ግብ ለማድረስ ሙስና ማነቆ ከሆነ፣ የለማውን ፍሬ ሳንበላ ኢ - ፍትሐዊነት ካገደን፣ የለማውን ወደበለጠ ደረጃ እንዳናደርስ “የአብዬን እከክ ወደምዬ ልክክ” እንቅፋት የሚሆንብን ከሆነ አካሄዳችን ውሽልሽል ነው፡፡ ዕድገታችን ቁልቁል ነው፡፡ በወጉ ያልተንከባከብነው ዕድገት ለወሬ እንጂ ለተግባር አይመችም፡፡ ከጐረቤቶቻችን በዚህ በዚህ እንበልጣለን፤ በዚህ በዚህ እንሻላለን፤ በዚህ በዚህ በአብዛኛው አብረን እየተጓዝን ነው፣ ማለት በተጨባጭ ዕድገትና ማንነታችንን አያሳይም፡፡ ይልቁንም፤ “ተንከባክባ ያላሳደገችውን ልጅ፣ የእከሌ ልጅ እኩያ ነው ትላለች” የሚለውን ተረት ነው የሚያረጋግጥ!