Administrator

Administrator

  ባለፈው የፈረንጆች አመት 2019 በመላው አለም በአውሮፕላን አደጋ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከአንድ አመት በፊት ከነበረው ከግማሽ በላይ ቅናሽ ማሳየቱን ሮይተርስ ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡
ቲ70 የተሰኘውና ተቀማጭነቱ በሆላንድ የሆነው የአቪየሽን ዘርፍ አማካሪ ተቋም ሰሞኑን ያወጣውን አመታዊ ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ በአመቱ በመላው አለም 86 የንግድ አውሮፕላኖች አደጋ እንዳጋጠማቸውና በአደጋዎቹ በድምሩ 257 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአመቱ ለሞት ከተዳረጉት ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ድርሻ የሚይዙት ባለፈው መጋቢት ወር ላይ በተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ለሞት የተዳረጉት 157 ሰዎች መሆናቸውንም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 በመላው አለም የተከሰቱት አስከፊ የአውሮፕላን አደጋዎች 13 እንደነበሩና በአደጋዎቹ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥርም 534 እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡ የፈረንጆች አመት 2017 በታሪክ እጅግ አነስተኛው የአውሮፕላን አደጋ ክስተት የተመዘገበበት እንደነበር ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ በአመቱ የተከሰቱት አስከፊ የአውሮፕላን አደጋዎች ሁለት ብቻ እንደነበሩና የሟቾች ቁጥር 13 ብቻ እንደነበርም አክሎ ገልጧል፡፡


  የሁሉም ከፍተኛ ባለስልጣናት ደመወዝ እንዲቀነስ መመሪያ ሰጥተዋል

              የዛምቢያው ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ የራሳቸውን ጨምሮ የሁሉም ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ደመወዝ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀነስ የሚያስገድድ ጥብቅ ውሳኔ ማሳለፋቸውን አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በድህነት በሚማቅቁባት አገር ውስጥ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከሚገባቸው በላይ ደመወዝ እየተከፈላቸው ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የእሳቸውን ጨምሮ የሁሉም የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ደመወዝ እንዲቀነስ መመሪያ ማስተላለፋቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በመመሪያው መሰረት፤ ፕሬዚዳንት ሉንጉን ጨምሮ በከፍተኛ የደመወዝ እርከን ውስጥ የሚገኙ ቁልፍ የአገሪቱ ባለስልጣናት ከደመወዛቸው ላይ እስከ 20 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ ይደረግባቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፤ ቅናሹ በእየ እርከኑ እስከ 10 በመቶ እንደሚደርስም አመልክቷል፡፡
የመንግስትን ወጪ ለመቀነስ ታጥቆ የተነሳው የፕሬዚዳንት ሉንጉ መንግስት፤ በቀጣይም ከፍተኛ ባለስልጣናት ለስብሰባና ለሌሎች ጉዳዮች ወደ ውጭ አገራት የሚያደርጉትን ጉዞ እንዲያቋርጡ አዲስ ትዕዛዝ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም የተነገረ ሲሆን ከደመወዝ ቅናሹና ከመሰል ቁጠባዎች የሚገኘው ገንዘብ ድሃ ዜጎችን ለመደጎም ለታሰቡ ፕሮጀክቶች እንደሚመደብ ተጠቁሟል፡፡

   የፈረንጆች አዲስ አመት የመጀመሪያዋ ቀን በሆነችው ባለፈው ረቡዕ ብቻ በመላው አለም 392 ሺህ ያህል ልጆች ተወልደዋል ተብሎ እንደሚገመት ተመድ አስታውቋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ተቋም ዩኒሴፍ ይፋ ያደረገውን መረጃ ጠቅሶ አልጀዚራ አንደዘገበው፤ በዕለቱ በህንድ 67 ሺህ 385፣ በቻይና 46 ሺህ 299፣ በናይጀሪያ 26 ሺህ 39 ህጻናት እንደተወለዱ ይገመታል፡፡
ባለፉት ሶስት አስርት አመታት ዕድሜያቸው አምስት አመት ሳይሞላቸው ለሞት የሚዳረጉ ህጻናት ቁጥር ከግማሽ በላይ መቀነስ  ቢያሳይም፣ የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር በአንጻሩ በአዝጋሚነት መቀነሱን ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በመላው አለም በፈረንጆች አመት 2018 በተወለዱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሞቱ ህጻናት ቁጥር 2.5 ሚሊዮን እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው.፤ ከእነዚህ መካከልም ከ35 በመቶ በላይ የሚሆኑት በተወለዱበት እለት ይህቺን አለም በሞት እንደተለዩዋትም አክሎ ገልጧል፡፡

  የመንግሥቱ ኃ/ማርያም ወዳጅ…
ጌታቸው ኃ/ማርያም የኢሠፓ አባል ነበር:: በስራው ላይ ግን ይህ ፍጹም አይንፀባረቅም ነበር፡፡ ጌታቸው እና ሊቀመንበር መንግስቱ ኃ/ማርያም ይቀራረባሉ፡፡ ትውውቃቸው የሚጀምረው ጅማ እንደነበርም ይነገራል:: ሊቀመንበሩ ጌታቸውን ያቀርቡታል፡፡ በጉዟቸው ሁሉ አብሯቸው ነው፡፡
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ፡፡ በዓሉ ግርማ፤ ፀጋዬ ኃ/ማርያም በተሰኘው ገጸ ባህሪው ጋዜጠኛው ለሊቀመንበሩ ያለውን ፍቅር እንዲህ ገልጾታል፡- “ተርገብጋቢ ወንዳወንድ ድምጽ፤ እንደ መብረቅ ቦግ የሚል ከልብ የመነጨ ፈገግታ፤ ቅስምን ድንገት የሚሰብር ልባዊ ትህትና:: ሰውየው ባማረ ሚሊተሪ ዩኒፎርም ነበሩ፡፡ ሳያቸው በራስ የመተማመን ድፍረት ተሰማኝ:: የሀገር መሪዎች እንደ ማንኛውም ሰው ተራ ሟች መሆናቸው ቢታወቅም ሲያይዋቸው የሆነ ፍቅር፣ አክብሮትና ፍርሃት፣ እና ድፍረት ለምን በሰው ሆነው ይታዩኛል፡፡ ምናልባት የሀገርና የህዝብ ክብርና ኩራት ቃል ጠባቂና አስከባሪ ባለአደራ ስለሆኑ ይሆናል:: የሆነው ሆኖ በዚህ ምክንያትም ይሁን በሌላ ባለስልጣናትን ማክበር በጣም እወዳለሁ:: ይህንን ጸባዬን በማየት የሥራ ባልደረቦቼ “ይኼው እንግዲህ ባለስልጣን ሲያይ ጭራውን ሊቆላ ነው ይላሉ:: እኔ ግን ጭራዬን የምቆላ ሰው አይደለሁም፡፡ ቆልቼስ የት ልደርስ?”
ዝናቡ ዘነበ አልኩ እንጂ ሰማዩን
አላስለቀስኩት
ኢህአዴግ አዲስ አበባን በተቆጣጠረ ሰሞን መላው ጋዜጠኛ በማዘጋጃ ቤት ለግምገማ ይቀመጣል፡፡ ያ ዘመን ደግሞ የመገማገም፣ የመወነጃጀልና የመሰዳደብ ዛር የነገሰበት ነበር:: የኢህአዴግ ካድሬዎች በልባቸው የቋጠሩትን አላማ ይዘው፣ ተለጣፊና አለሁ ባይ ጋዜጠኞች ያቀበሏቸውን ወንጀሎች ሰንቀው ተሰይመዋል:: ጌታቸው ላይ አንድ ወንጀል ቀረበ፡፡ ከኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ጋር ውጪ ሀገር ሄዶ ሲዘግብ የነበረውን ሁኔታ አስታውሰው እንዲህ ሲሉ ወነጀሉት “ኮሎኔሉ ከአውሮፕላን ሲወርዱ ዝናብ ዘነበ የሚል ዘገባ ሰርተሃል፣ ምን ማለት ፈልገህ ነው?” ሲሉ ጠየቁት እሱም እንዲህ ሲል መለሰ የሚፈራ አለመሆኑን እያስረዳ ቀጠለ “እኔ ጌታቸው ኃ/ማርያም የዘነበውን ዝናብ ዘነበ አልኩ እንጂ ሰማዩን አላስለቀስኩት” ሲል መለሰ፡፡ ሁሉም በድፍረቱ ተገረሙ፡፡ ውንጀላው ብዙዎችን አላሳመነም ከኢህአዴጉ ካድሬ ውጪ፡፡ ይሁንና ከሚወደው ሙያው ሳይወድ 1983 ላይ ተሸኘ፡፡ ተሰናበተ፡፡ የእሱ መሰናበት የጐዳው ጌታቸውን ብቻ አልነበረም፤ በሁለት እግሩ ለመቆም ይንገዳገድ የነበረውን የሀገራችንን የሚዲያ ዕድገትና ጋዜጠኞችን ጭምር እንጂ፡፡   
“ሞገደኛው ጋዜጠኛ”
መንግስቱ ገዳሙ ሞገደኛ የሚል ስያሜ የተሰጠው ከሙያዊ ሕይወቱ በመነጨ ሞጋች ስለነበር ነው፡፡ ጽሑፎቹ የሕዝቡን እውነተኛ ሕይወት የሚዳስሱ፣ ችግሩንና በደሉን ከፍላጐቱ ጋር የሚያመለክቱ ነበሩ፡፡ በተለይም የሥርዓቱን ንቅዘት በመዋጋት የሚደርስበት አሳርና መከራ ከሙያው አላገደውም፡፡ መንግስቱ “የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የገና ዳቦ” ናቸው ሲል ብዙ ጊዜ ተናግሯል፡፡ የሞገደኛው ጋዜጠኛ መንግስቱ ገዳሙ ገድል ብዙ ነው:: በመንግስቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግስት ወቅት የፒያሳን ሕዝብ በመኪና እየተዘዋወረ ቀስቅሷል:: ሁኔታው ሲለወጥ በሲዳሞ የአራት ወራት ግዞት ደርሶበታል፡፡ በአያሌ የሕዝብ አመጾች እየተሳተፈ ስላስቸገረም በየፖሊስ ጣቢያው ታስሮ የሻማ ከፍሏል፡፡
መንግስቱ ገዳሙ አንጋፋ ጠጪ በመባል የሚታወቅ ሲሆን ለምን እንደሚጠጣ ሲጠየቅ፤ “እኔ እኮ ለምን እንደምጠጣ እናንተ ደንቆሮዎች አይገባችሁም፤ የእኔ አእምሮ ከተራው ሰው አእምሮ በጣም የላቀ ነው፡፡ ስለዚህ ከእናንተ ጋር ለመነጋገር ያንን ከፍተኛ አእምሮዬን በአልኮል ኃይል ነው ወደ እናንተ ደረጃ ላወርድ የምችለው” በማለት መናገሩ ይታወሳል፡፡
ከጽሑፉና ከንግግሩ ባሻገር መንግሥቱ ገዳሙ በእለታዊ ድርጊቱ ስርዓቱን ይቃወም ነበር፡፡ ለምሳሌ አንዲት አህያ ጆሮዋ ላይ ብር ለጥፎ በየመጠጥ ቤቱ እየዞረ፣ አስተናጋጆቹ እንዲታዘዟት ያደርግ ነበር፡፡ በዚህም የጊዜው ባለስልጣኖች በገንዘብ እንጂ በአስተሳሰብ ከአህያ እንደማይሻሉ ለማስረዳት ያደረገው ነው ተብሏል፡፡ አህያዋን ይዟት በየቦታው ሲዞር “ምንድን ነች?” ብለው ሲጠይቁትም “የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባልደረባ ነች” እያለ ይመልስ እንደነበር ይወሳል፤ በዚያ ዘመን ማስታወቂያውን በአህያ እየዞረ የሚያስነግረው ብሔራዊ ሎተሪ፤ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥር ነበር፡፡ አህያዋም የባለስልጣኖች ተምሳሌት ነበረች፡፡ “
ከማን አንሼ” በምትሰኝ መጽሐፉ ላይ አንድ ሰው እጅ እንዲነሳት የተደረገችው ክራቫት ያሰረች አህያ፤ የወቅቱን የፓርላማ አባላት ለመሳደብ ሆን ብሎ ያዘጋጃት ናት ይባላል፡፡
***
“ዜና እያነበብኩ በጥይት ተመታሁ…”
ወቅቱ 2008 ክረምት ላይ ነበር፣ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተቃውሞ ድምጾችና ግርግሮች በብዛት የሚታዩበት ሰሞን፡፡ ከእነዚህ ቦታዎች አንዱ ደግሞ ጐንደርና አካባቢው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም በአብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው በዚሁ ጊዜ ነበር፡፡ “ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ በቁጥጥር ስር ውሏል” የሚል ዜና እና መግለጫ የእለቱ ዋና ዜና ሆኖ ጊዜ ተመድቦለታል:: የእለቱ ተረኛ ዜና አንባቢ ደግሞ መሰለ ገ/ህይወት፡፡
ዜና ማንበቡን ጀመረ፡፡ ወዲህ ደግሞ ደባርቅ ከተማ ላይ አንድ አርሶ አደር ዜናውን በከፍተኛ ንዴት ትኩረት ሰጥቶ መከታተሉን ቀጠለ፤ መሰለም ይህንን መግለጫ ማንበቡን ቀጥሏል:: አርሶአደሩ ግን የመሰለን ዜና መስማትና መቋቋም አቃተው፡፡
ክላሹን አነሳ፤ አቀባበለ፤ ወደ ቴሌቪዥኑ ተኮሰ፡፡ መሰለን ያገኘ ያክል እፎይታ ተሰማው:: ዜናው ተቋረጠ፡፡ “ይህንን የነገረኝ አንድ የቅርንጫፍ ባልደረባችን ነው:: በዚህም ምን ያክል ኢቲቪ ይጠላ እንደነበርና ለእኛ ያላቸው አመለካከት ከባድ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ ይህንን ጉዳይ ስሰማ በጣም ነው የደነገጥኩት፡፡ መሰለ በጥይት ተመታ እየተባለም ረጅም ጊዜ ይወራ ነበር፡፡
***
“ለ8 ቀን ኒሻን የሸለሙኝ አርበኛ”
እነዚህ የተቃውሞና የጥላቻ ድምጾች እንዳሉ ሁሉ፣ በተቃራኒው ደግሞ አድናቆቱም ከፍተኛ ነበር፡፡ “አንድ አባት አርበኛ በጣም እንደሚያደንቁኝ ከነገሩኝ በኋላ የሚሰጡኝ ግራ ሲገባቸው፣ በጣሊያን ወረራ ላይ የተሸለሙትን ኒሻን “ለስምንት ቀን አድርገህ መልስልኝ” ብለውኛል፡፡
የተለያዩ ስድቦችና በፎቶሾፕ የተሰሩ አስቂኝ ፎቶዎች…በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች እከታተል ነበር፡፡
ኢቲቪ የመንግስት አፍና የስርዓቱ ማንጸባረቂያ ስለሆነ ህዝቡ ዜናውን እኛ የምናዘጋጀው ይመስለው ነበር፡፡” እኔ ተቋሙ የቀጠረኝ የተሰጠኝን ማንኛውንም ዜና ለማንበብ እንጂ መርጬ “ይሄን አላነብም፤ ይሔኛው ደግሞ ይቅርብኝ” የማለት መብት የለኝም፡፡…
***
“ከመንግስቱ ኃ/ማርያም ኮበለሉ…”
ግንቦት 13/1983 ዓ.ም በኢትዮጵያ ራዲዮ ለሚገኙ ጋዜጠኞች እንደማንኛውም ቀን ሆና የቆየችው እስከ ረፋዱ 5፡00 ሰዓት ድረስ ብቻ ነበር፡፡ ምንም አዲስ ነገር አልነበረም፡፡ ምንም እንኳን ጦርነቱ በአዲስ አበባ ዙሪያ እንደቀጠለ ቢሆንም፡፡
በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ አብዱልሀሺዝ ይባላሉ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ራዲዮ መጡና ጌታቸው ኃ/ማርያምን አናገሩት:: እንዲህም አ፡- “ዛሬ፤ በተለይም ራዲዮ ዜና አንባቢዎች የትም አትሄዱም፤ የሚጠበቅ ዜና አለ” ብለው ተናግረው ወጡ:: ግቢው ግራ ገባው:: ጋዜጠኞቹም ይህንን አዲስ ዜና ማን ያነበው ይሆን? እያሉ መጠባበቅ ጀመሩ:: ምናልባትም የራሳቸውን የሞት ፍርድ ማንበብም ሊሆን ይችላል፤ ግን ደግሞ የሆነ መሬት አንቀጥቅጥ ዜና እንዳለ አምነዋል፡፡ የዚህ ዜና ታሪክ አካል መሆን ሁሉም ይፈልጋሉ:: ሰዓቱ እየሄደ ነው፡፡ ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ሆነ፡፡ “ጣቢያው እንዳይዘጋ፤ ጠብቁ” የሚል ትእዛዝ ድጋሚ ተላለፈ፡፡
አለምነህ ይህን ዜና ለማንበብ ከሁሉም በላይ ጓጓ፡፡ ዳሪዮስ ሞዲ ልምድ ስላለው እሱ ሊያነበው ይችላል በሚል ፍርሃት አለምነህ ዳሪዮስ ሞዲን በቅርብ ርቀት ይከታተለው ጀመር፡፡ ነጋሽ መሐመድም ቢሆን ሊያነበው እንደሚችል ሲያስብ ይበልጡን ፈራ፡፡
አለምነህ ዋሴ ሁሉንም በአይኑ ሲፈልግ ዳሪዮስ ሞዲን አጣው፡፡ በአካባቢው አለመኖሩንም ሲያይ ደስታው ወደር አልነበረውም፡፡ ሰዓቱ 6፡30 ሆኗል፡፡
ዜናውን የሚያመጡት ሰዎች ገቡና በቀጥታ ወደ ስቱዲዮ መውረድ ጀመሩ፡፡ አለምነህ ተከትሎ ገባ፤ እሱ ሊያነበው እንደሚችልም እርግጠኛ ሆነ፡፡ ነገር ግን ወደ ስቱዲዮ ሲጠጉ፣ ዳሪዮስ ሞዲ ከስቱዲዮ ሆኖ ቀድሞ ገብቶ “አድማጮች ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በጉጉት የሚጠበቅ ዜና አለ” ብሎ እያስተዋወቀ ነበር:: ይሄንን ታላቅ ዜና አለምነህ በልምድ ማነስ ምክንያት (ዳሪዮስ ስቱዲዮውን ቀድሞ ይዞት ኖሮ) ለማንበብ ሳይታደል ቀረ፡፡ “የሚያስቅ ሀዘን” ብሎ ይገልጸዋል ይህንን ልዩ አጋጣሚም - አለምነህ ዋሴ፡፡ ዜናውም “መንግሥቱ ኃ/ማርያም በዛሬው እለት ከስልጣን ወርደው ከኢትዮጵያ ውጪ ሄደዋል” የሚል ነበር፡፡ (እንግዳ፣ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን)
ምንጭ፡-
(“የጋዜጠኞች ወግ” በግዛቸው አሻግሬ)

*ታህሳስ 29 ቀን 1992 ዓ.ም የመጀመሪያው “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ፣ በመጀመሪያው ዕለተ ቅዳሜ ለንባብ በቃ!!
* ላለፉት 20 ዓመታት በየሳምንቱ ቅዳሜ፤ እውነተኛና ትክክለኛ፣ ምሉዕና ሚዛናዊ ዜናዎችን… በመረጃ የበለፀጉ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘገባዎችን…ጠንካራ
ትንታኔዎችን… በኪናዊ ውበታቸው የላቁ ማህበራዊና ጥበባዊ ጽሑፎችን አስነብበናል!!
* አምስት አገራዊ ምርጫዎችን ዘግበን፣ ከአገራችንና ከአንባቢዎቻችን ጋር ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈናል፤ ለዘንድሮው ምርጫም እየተዘጋጀን ነው!!
*ድንቅ ጽሁፎችን በፍቅር እያበረከታችሁ ለዘለቃችሁ የአድማስ ብዕርተኞች ሁሉ፤ባለውለታዎቻችን ናችሁ!!
* ለሁለት አስርት ዓመታት በፍቅር ያነበባችሁን ሁሉ እናመሰግናለን፤ እንወዳችኋለን!!
*ምርትና አገልግሎታችሁን ለማስተዋወቅ እኛን ለመረጣችሁ ድርጅቶች ሁሉ አክብሮታችንን እንገልጻለን!!
* ዓላማችን መረጃንና ዕውቀትን በማክበር፤ በአዕምሮና በሥራ የሚበለጽግ፣ ራሱን
ችሎ የሚያስብና የሚቆም፣ ምክንያታዊና አስተዋይ ትውልድ ይበረክት ዘንድ መትጋት ነው!!

                                መልካም የገና በዓል!!!

 ሊጠናቀቅ የሶስት ቀናት ዕድሜ ብቻ በቀረው የፈረንጆች አመት 2019 አለማችን ብዙ ክፉና ደጎችን አስተናግዳለች፡፡ እጅግ አሳዛኝና አስደንጋጭ ነገሮች በተፈጸሙበት፣ በርካታ በጎና አስደሳች ነገሮች በተሰሙበት፣ ብዙዎችን ጭንቀትና ፍርሃት ውስጥ የከተቱ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክስተቶች በተስተናገዱበት የተገባደደው የፈረንጆች አመት 2019፤ የአለማችን መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ሰጥተው ከዘገቧቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል የተወሰኑትን መራርጠን እነሆ ብለናል፡፡
የተቃውሞና የአመጽ ማዕበል
የተገባደደው የፈረንጆች አመት 2019 ሰበብ ምክንያቱም ሆነ አላማና ግቡ ይለያይ እንጂ ከአፍሪካ እስከ እስያ፣ ከአውሮፓ እስከ መካከለኛው ምስራቅና አሜሪካ አለማችን በያቅጣጫው በተቃውሞ ስትናጥ የከረመችበት የተቃውሞና የአመጽ አመት ነበር፡፡ ከሊባኖስ እስከ ባርሴሎና፣ ከእንግሊዝ እስከ ጣሊያን፤ አለማችን ዙሪያ ገባውን በተቃውሞ እሳት ስትለበለብ ነው አመቱን የገፋችው፡፡
ቦሊቪያውያን በቅርቡ በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፤ “የህዝብን ድምጽ አጭበርብረው አሸናፊነታቸውን አውጀዋል” ያሏቸውን ፕሬዚደንት ኢቮ ሞራሌስ፤ ለመቃወም እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው፣ አደባባይ በመውጣት ከፖሊስ ሲተናነቁና በተቃውሞ ማዕበል አገሪቱን ሲያጥለቀልቋት ከርመዋል፡፡
በቺሊ ባለፈው ጥቅምት ወር የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ መደረጉን ተከትሎ፣ ጉዳዩ ያስቆጣቸው የአገሪቱ ዜጎች፤ የመዲናዋን ሳንቲያጎ ጎዳናዎች በማጥለቅለቅ ተቃውሞ ከማሰማት አልፈው መደብሮችን መዝረፍና አውቶብሶችን ማቃጠላቸውን ተያያዙት፡፡
 የህዝቡ ቁጣ ያሳሰበው የአገሪቱ መንግስትም ነገሩ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማጽደቅ ሁኔታዎችን ለማረጋጋት ደፋ ቀና ሲል ከርሟል፡፡
የኢኳዶር መንግስት ለአስርት አመታት ያህል በነዳጅ ዋጋ ላይ ሲያደርግ የዘለቀውን ድጎማ ማንሳቱን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ዜጎች በተቃውሞ ጎዳናዎችን ያጥለቀለቁትም ሆነ በሆንግ ኮንግ በታሪኳ አይታው በማታውቀው ማብቂያ የሌለው፣ ለወራት የዘለቀ ተቃውሞ የታመሰችው በዚሁ የ2019 አመት ነው፡፡
የአለማችን አገራት በተቃውሞ የሚታመሱበት ሰበብ እየቅል ቢሆንም፣ በተደጋጋሚ ለተቃውሞ ምክንያት ሆነዋል ብሎ ሮይተርስ ከጠቀሳቸው ዋነኛ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው - ኢኮኖሚ፡፡ ኢኳዶር፣ ቤሩት፣ ሃይቲና ኢራቅን ጨምሮ በአመቱ በበርካታ አገራት የተቀሰቀሱት ተቃውሞዎች፤ ዜጎችን ባስቆጡ የመንግስታት ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎች ሳቢያ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በአወዛጋቢ የስራ ፈቃድ አዋጅ ተጀምሮ ሌሎች ጥያቄዎችን እያግተለተለ ላለፉት አምስት ወራት የዘለቀውን የሆንግ ኮንግ ተቃውሞ ጨምሮ በተለያዩ አገራት ዜጎችን ለተቃውሞ ያስወጣ ሌላኛው ምክንያት ተብሎ የተጠቀሰው ደግሞ የፖለቲካዊ ነጻነት ወይም የሉአላዊነት ጥያቄ ነው፡፡ የስፔን መዲና ባርሴሎናን ጎዳናዎች በመቶ ሺዎች በሚጠጉ ካታሎናውያን ያጥለቀለቀው የጋለ የተቃውሞ ሰልፍም ለአመታት ከዘለቀ የመገንጠልና ራሱን የቻለ ሉአላዊ አገር የመፍጠር ጥያቄ ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው ሮይተርስ ያስነበበው፡፡ መንግስት በሙስና ተጨማልቋል፤ ሹመት በዝምድናና በውግንና ሆኗል፤ ባለስልጣናት ከዜጎች በሚዘርፉት ሃብት የግል ካዝናዎቻቸውን እየሞሉ ነው የሚሉና መሰል የሙስና ምሬት የወለዷቸው ተቃውሞዎች ከተቀሰቀሱባቸው አገራት መካከልም ሊባኖስ፣ ኢራቅና ግብጽ እንደሚገኙበትም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በአመቱ በተለያዩ የአለማችን አገራት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎችን አደባባይ ያስወጣው ሌላኛው የተቃውሞ ሰበብ ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ ነው፡፡ መንግስታት ለአየር ንብረት ለውጥ በቂ ትኩረት እንዲሰጡ የሚጠይቁ በርካታ ተቃዋሚዎች፤ ከአሜሪካ እስከ እንግሊዝ፣ ከጀርመን እስከ ስፔን፣ ከኦስትሪያ እስከ ፈረንሳይና ኒውዚላንድ ጎዳናዎችን ያጥለቀለቁትም በዚሁ አመት ነበር፡፡
አፍሪካ
የተገባደደው አመት 2019 አፍሪካ ከአወዛጋቢ ምርጫዎች እስከ አሰቃቂ የስደት አደጋዎች፣ ከተፈጥሮ አደጋዎች እስከ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ቀውሶች በርካታ ጉልህ ክስተቶችን ያስተናገደችበት ነበር፡፡ ከሶስት አስርት አመታት በላይ ሱዳንን አንቀጥቅጠው የገዙት ኦማር አልበሽር፤ መሬት በሚያንቀጠቅጥ ህዝባዊ ተቃውሞ ከመንበረ ስልጣናቸው ወርደው ወደ እር ቤት የተሸኙበት፤ የዚምባቡዌው መሪ ሮበርት ሙጋቤ፤ ከስልጣን ወርደው ወደ መቃብር የተሸኙበት ታሪካዊ አመት ነበር - 2019፡፡
የደቡብ አፍሪካውን የመጤ ጠልነት ጥቃት ጨምሮ አፍሪካ በአመቱ ካስተናገደቻቸው አሳዛኝ ክስተቶች መካከልም፣ በወርሃ መጋቢት በሞዛምቢክ የተከሰተውና ብዙዎችን ለሞትና ለመፈናቀል የዳረገው ሳይክሎን ኢዳይ የተባለው ጎርፍ እንዲሁም በዚምባቡዌና በማላዊ የተከሰቱት አደገኛ የተፈጥሮ አደጋዎች የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በምስራቃዊ አፍሪካ ከፍተኛ ዝናብ 2.8 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ተጎጂ ማድረጉ ይነገራል፡፡
ከሁለት አስርት አመታት በላይ ተኳርፈው የኖሩትን ኢትዮጵያና ኤርትራ ባልተገመተ ሁኔታ ወደ ሰላም ያመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የኖቤል የሰላም ተሸላሚ በሆኑበትና አገራችን ሳተላይት ያመጠቀችበትን አዲስ ታሪክ የጻፈችበት የ2019 አመት፣ አፍሪካ ካስተናገደቻቸው ሌሎች በጎ ክስተቶች መካከል የሚጠቀሰው ጉዳይም በምዕራብ አፍሪካ አገራት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት ለዳረገው የኢቦላ ቫይረስ መድሃኒት የመገኘቱ የምስራች አንዱ ነበር፡፡
ምርጫ
2019 ዩክሬን፣ እንግሊዝ፣ ፖላንድ፣ ኢራቅ፣ አፍጋኒስታን እና ሲሪላንካን ጨምሮ በአለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ አገራት ምርጫ ያከናወኑበት አመት እንደነበር ያስታወሰው ዘጋርዲያን በበኩሉ፣ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምጽ በመታጣቱ ለሶስተኛ ጊዜ ምርጫ ለመመስረት የተዘጋጀችውን እስራኤል ምርጫ በተለየ ሁኔታ ጠቅሶታል፡፡
በአመቱ ናይጀሪያ፣ ቦትሱዋና፣ ሴኔጋል፣ ናሚቢያ፣ ሞዛምቢክና ጊኒ ቢሳኡን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ አገራት ምርጫ የተከናወነ ሲሆን፣ እንደተለመደው አብዛኞቹ አገራት ምርጫን ተከትሎ በሚፈጠር ብጥብጥና ተቃውሞ በርካታ ዜጎቻቸውን በሞት ያጡበት እንደነበር ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
ስደት
ተመድ ባለፉት አስር አመታት የ23 በመቶ ጭማሪ ያሳየው የአለማችን ስደተኞች ቁጥር፣ በፈረንጆች አመት 2019 በመላው አለም የስደት ህይወትን በመግፋት ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር 272 ሚሊዮን መድረሱን ያስታወቀውም ባለፈው ወር ባወጣው አለማቀፍ የስደት ሁኔታ አመላካች ሪፖርቱ ነበር፡፡
በፈረንጆች አመት 2019 በአውሮፓ 82 ሚሊዮን፣ በሰሜን አሜሪካ 59 ሚሊዮን በሰሜን አሜሪካና ምዕራብ እስያ አገራት ደግሞ በተመሳሳይ 49 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የስደት ህይወትን በመግፋት ላይ እንደሚገኙ የጠቆመው ተመድ፤  ከአለማችን 272 ሚሊዮን ስደተኞች መካከል ግማሽ ያህሉ በአስር አገራት ውስጥ እንደሚኖሩም ገልጧል፡፡
ብዙ ዜጎቿ የተሰደዱባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ህንድ ናት ያለው ሪፖርቱ፤ 18 ሚሊዮን ህንዳውያን አገራቸውን ጥለው በመሰደድ በሌሎች አገራት ኑሯቸውን እየገፉ እንደሚገኙም አመልክቷል፡፡ ከአለማችን የህዝብ ቁጥር እድገት ይልቅ የአለማችን ስደተኞች ቁጥር እድገት ብልጫ እንዳለው የገለጸው ሪፖርቱ፣ በተገባደደው የፈረንጆች አመት በስደት ላይ ከሚገኙት 272 ሚሊዮን ስደተኞች መካከል 48 በመቶው ሴቶች መሆናቸውንም አስታውቋል፡፡
አለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት ከቀናት በፊት ባወጣው አመታዊ ሪፖርት እንዳለው፣ በአመቱ በአለማችን የተለያዩ ክፍሎች 3 ሺህ 170 ያህል ስደተኞች ድንበር አቋርጠው የስደት ጉዞ በማድረግ ላይ እያሉ ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል፡፡
በአመቱ በስደት ላይ ሳሉ ለሞት ከተዳረጉ ስደተኞች አመካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደተለያዩ የአውሮፓ አገራት ለመጓዝ ሲሞክሩ የነበሩ አፍሪካውያን ስደተኞች መሆናቸውንና በአመቱ በወር 10 ሺህ ያህል ስደተኞች ከአፍሪካ ቀንድ ወደ የመን ተሻግረዋል ተብሎ እንደሚታመንም ድርጅቱ አስታውሷል::
አስከፊ የተፈጥሮ አደጋዎች
2019 የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተላቸው በርካታ የተፈጥሮ አደጋዎች በተለያዩ የአለማችን አገራት በርካቶችን ለሞትና ለመፈናቀል አደጋ የዳረገበት አመት እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአመቱ 10 የተፈጥሮ አደጋዎችን አስተናግዳ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ጉዳት የደረሰባት አሜሪካን ጨምሮ በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ በርካታ አገራት ኢኮኖሚያቸው ክፉኛ መጎዳቱን የጠቆመው የአለም የሜትሪዮሎጂ ኤጀንሲ፣ ለአብነትም በሞዛምቢክ የተከሰተውንና በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ጉዳት ያደረሰውን የጎርፍ አደጋ ያስታውሳል፡፡
መስከረም ወር ላይ ባህማስን የመታው ሃሪኬን ዶሪያን፣ በነሃሴ ወር ቻይና ውስጥ ተከስቶ 72 ሰዎችን ለሞት የዳረገው ታይፎን ሌኪማ፣ በጥቅምት ወር ላይ በጃፓን ተከስቶ 80 ሰዎችን የገደለው ታይፎን ሃግቢስ፣ በሰኔ 90 ህንዳውያንንና ከ160 በላይ ጃፓናውያንን ለሞት የዳረጉት የሃይለኛ ሙቀት ክስተቶች፣ 900 የአፍሪካ አገራት ዜጎችን ለሞት የዳረገው ሳይክሎን ኢዳይ እንዲሁም በ14 የአፍሪካ አገራት 45 ሚሊዮን ሰዎችን ለተረጂነት የዳረገው ድርቅ አለማችን ካስተናገደቻቸው በርካታ የተፈጥሮ አደጋዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የትራምፕ መከሰስ
አመቱ እየተገባደደ ባለበት የመጨረሻው ወር ላይ ከተከሰቱና የመገናኛ ብዙሃንን ቀልብ ከሳቡ የአመቱ ጉልህ አለማቀፋዊ ክስተቶች ተርታ የሚሰለፈው ሌላው ጉዳይ ደግሞ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መከሰስ ነው:: የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀምና የምክር ቤቱን ስራ በማደናቀፍ እንዲከሰሱና ከስልጣናቸው እንዲወርዱ በአብላጫ ድምጽ መወሰኑን ተከትሎ ነበር፣ ትራምፕ በአገሪቱ ታሪክ ሴኔት ፊት ቀርበው ክሳቸውን እንዲከላከሉ የተወሰነባቸው ሶስተኛው ፕሬዚዳንት ሆነው በታሪክ መዝገብ ላይ የሰፈሩት፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የዩክሬን አቻቸው ቭላድሚር ዘለንስኪን በቀድሞው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምርጫ ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን እና በልጃቸው ላይ የሙስና ምርመራ እንዲያደርጉ በመደለልና ጫና በማድረግ ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም፤ እንዲሁም ከዚህ ጋር በተያያዘ ለሚደረግባቸው ምርመራ መረጃዎችን ባለመስጠትና የምክር ቤቱን ስራ በማደናቀፍ እንዲከሰሱ በቀረበባቸው የውሳኔ ሃሳብ ዙሪያ፣ ለአስር ሰዓታት ያህል ከተደረገ ክርክር በኋላ ነበር፣ የምክር ቤቱ አባላት ፕሬዚዳንቱ  እንዲከሰሱና ሴኔት ፊት ቀርበው የቀረቡባቸውን ክሶች እንዲከላከሉ በአብላጫ ድምጽ የወሰኑት፡፡
ሴኔቱ የተገባደደውን አመት ሸኝቶ ከሳምንታት በኋላ ዳግም ተገናኝቶ በጉዳዩ ዙሪያ በመምከር ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም፣  ትራምፕ ስልጣናቸውን የሚለቅቁት ከሴኔቱ አባላት ሁለት ሶስተኛው የድጋፍ ድምጽ ከሰጡበት ብቻ ነው፡፡  ሴኔቱ ሪፐብሊካን የሚበዙበት እንደመሆኑ ግን በፕሬዚዳንቱ ላይ ውሳኔው የመተላለፉ ዕድል አነስተኛ እንደሆነ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው::  ብዙዎች እንደገመቱት ሳይሆን ቀርቶ፣ ሴኔቱ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከስልጣን እንዲሰናበቱ ውሳኔ የሚያስተላልፍ ከሆነ፣ ምክትላቸው ማይክ ፔንስ በመጪው አዲስ አመት ስልጣኑን ተረክበው እስከ ቀጣዩ 2021 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አገሪቱን ያስተዳድራሉ ተብሏል፡፡
በሞት የተለዩ ዝነኞች
ከፖለቲካው መስክ የዚምባቡዌው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፣ የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ዣክ ሲራክ እና የግብጹ አቻቸው ሞሃመድ ሙርሲ ከዚህ አለም በሞት የተለዩበት 2019፣ አለማችን በተለይ በመዝናኛው መስክ ስማቸውን በደማቁ ለማስጻፍ የቻሉ በዛ ያሉ ዝነኞችን በሞት ያጣችበት አመት እንደነበር ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡
የአሜሪካን ትልቁ የክብር ሽልማት የፕሬዚደንቱ የነጻነት ሜዳይ የተቀበሉትና የኖቤል የስነጽሁፍ ተሸላሚዋ አሜሪካዊት ደራሲ ቶኒ ሞሪሰን ባለፈው ነሃሴ ነበር በተወለዱ በ88 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት የተለዩት፡፡
አለማቀፍ ዝናን ያተረፈው ኤርትራዊው ራፐር ኒፕሲ ሃስል ባልታወቁ ሰዎች በተተኮሰበት ጥይት በ33 አመቱ ከዚህ አለም በሞት በተለየበት፣ በተገባደደው የፈረንጆች አመት 2019 ይህቺን አለም በሞት ከተለዩት ሌሎች የአለማችን ዝነኞች መካከል የሚጠቀሰው ደግሞ በአውሮፕላን አደጋ ለሞት የተዳረገው አርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ተጫዋች ኢሚሊያኖ ሳላ ነው፡፡
በአመቱ ከዚህ አለም በሞት ከተለዩ ሌሎች ስመጥር የአለማችን ሰዎች መካከልም ታዋቂው ፈረንሳዊ የሙዚቃ ቀማሪና የጃዝ ፒያኒስት ሚሼል ሌግራንድ፣ የቀድሞው የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ያሱሺሮ ናካሶኔ፣ የአይሲሱ መሪ አቡበከር አል ባግዳዲ፣   የቀድሞ የህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱሻማ ስዋራጅ፣ የቀድሞው የአርጀንቲና ፕሬዚዳንት ፈርናንዶ ዲ ላ ሩኣ ይገኙበታል፡፡
ሌሎች ጉልህ ክስተቶች
የጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ግድያ፣ ቦሪስ ጆንሰንን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመረጠውን የእንግሊዝ መንግስት አመቱን ሙሉ ወጥሮ ይዞት የዘለቀውና ከጫፍ የደረሰ የሚመስለው የአገሪቱ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት የመውጣት ዕቅድ፣ የኢራን የአንግሊዝን የነዳጅ ታንከር መቆጣጠሯ፣ ተካርሮ የቀጠለው የአሜሪካና የቻይና የንግድ ጦርነት፣ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው የቦይንግ አውሮፕላን መከስከስ፣ የአሸባሪው ቡድን አይሲስ መሪ አቡበከር አልባግዳዲ መገደሉ፣ የሜሲ ለ6ኛ ጊዜ የባሎንዶር የወርቅ ኳስ ተሸላሚ መሆን እና የአማዞን ጫካ ቃጠሎም በአመቱ አለማችን ካስተናገዳቻቸውና የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስበው ከከረሙ ሌሎች በርካታ ጉልህ ክስተቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡


 የደቀ መዝሙርነት ካባ የለበሰ አንድ ሰው ሁልጊዜ ማለዳ በቅርብ ወደሚገኝ አንድ መናፈሻ ይሄድና የዛፎቹን አበቦች ይመለምላል። እጅና ዓይኖቹ አበቦቹን ሲያገኙ ይስገበገባሉ፡፡ አጠገቡ ያገኘውን አበባ  በሙሉ ይቀጥፋል፡፡ አበቦቹን የሚፈልጋቸው ለአንድ የሞተ ምስል፣ ከድንጋይ ለተቀረፀ ምስል ሊያቀርባቸው መሆኑ ግልጽ ነው። ለማለዳው ፀሐይ የተጋለጡት አበቦች ያምራሉ። ሲቀጥፋቸው ደግሞ በሃይል እየመነጨቀ ነው፤ ርጋታ አይታይበትም፡፡ ለሚያመልከው ጣኦት፣ ለሞተ የድንጋይ ምስሉ ብዙ አበባ ይፈልጋል፡፡
በአንድ በሌላ ቀን የተወሰኑ ወጣት ልጆች አበባ ሲቀጥፉ ተመለከትኩ። እነዚህኞቹ አበቦቹን የፈለጓቸው ለጣዖታቸው አይደለም መሰል ያለ ርህራሄ እየቀነጠሱ ይጥሏቸዋል። እናንተስ እንዲህ አድርጋችሁ አታውቁም? ግን ለምንድነው የምታደርጉት? በመንገዳችሁ ያገኛችሁትን ቀንበጥ እየቀነጠሳችሁ ወዲያ ትጥላላችሁ፡፡ እንዲህ አይነት ሃሳብ የለሽ ተግባር እንደምትፈጽሙ አስተውላችሁ ታውቃላችሁ? በእድሜ የገፉ ሰዎችም ይህን ይፈጽማሉ:: እነሱም ውስጣዊ ጭካኔያቸውን፣ ለህያው ነገሮች ያላቸውን ንቀት የሚገልጡበት የራሳቸው መንገድ አላቸው። ስለ ርህራሄ ያወራሉ፤ የሚሰሩት ነገር በሙሉ ግን አፍራሽ ነው፡፡
አንድ፣ ሁለት አበባ ቀንጥሳችሁ ፀጉራችሁ ላይ ብትሰኩ ወይም ለምትወዱት ሰው ብታበረክቱ ምንም ላይባል ይችላል። ዝም ብሎ ቀነጣጥሶ መጣሉን ግን ምን አመጣው? ትላልቅ ሰዎች ምኞታቸው ያስከፋል፤ በጦርነት ይገዳደላሉ፤ በገንዘብ ይጠፋፋሉ። የተደበቀ ተግባራቸውን የሚገልጡበት የተለያየ መንገድ አላቸው፡፡ ወጣቶች ደግሞ የእነሱን ፈለግ እየተከተሉ ነው፡፡
ወጣቶችም ሆንን ሽማግሌዎች የርህራሄ ስሜት የለንም፡፡ ለምን? ፍቅርን ስለማናውቅ ነው?
ቀላል ፍቅር ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ውስብስቡ የወሲብ ፍቅር ወይም የእግዚአብሄር ፍቅር ሳይሆን ፍቅር ብቻ - ለስላሳ መሆን፤ በሁሉም ነገር ለስላሳ አቀራረብን መጠቀም:: ወላጆቻችሁ በጣም ስራ ስለሚበዛባቸው ቤት ውስጥ ይህን ቀላል ፍቅር አታገኙትም፤ በቤታችሁ ይህን እውነተኛ ፍቅር፣ ለስላሴ ስለማታገኙ እዚህ ስትመጡ ይህን ስሜት አልባነታችሁን ይዛችሁ ነው፡፡ ይህን ስሜት ንኩነት እንዴት ማምጣት አለባቸው ማለት አይደለም፡፡ የደንብ እገዳ ሲኖርባችሁ ትፈራላችሁ፡፡ ሰዎችን፣ እንስሳትን፣ አበቦችን እንዳትጎዱ የሚያደርጋችሁን ስሜት ንኩነት እንዴት ህያው ማድረግ ይቻላል?
በዚህ ሁሉ ነገር ተማርካችኋል? መማረክም አለባችሁ፡፡ ስሜት እንዲኖራችሁ ፍላጎት ካላደረባችሁ ሙት ናችሁ - አብዛኞቹ ሰዎችም እንዲህ ናቸው። በቀን ሶስት ጊዜ ቢበሉም፣ ልጆች ቢያፈሩም፣ መኪና ቢያሽከረክሩም፣ ምርጥ ልብሶች ቢለብሱም እንደ ሙት ናቸው፡፡
ስሜት ንኩ መሆን ምን ማለት እንደሆነ ታውቃላችሁ? ለነገሮች ርህራሄ ማሳደር ነው፡፡ የሚሰቃዩ እንስሳትን መታደግ፣ በባዶ እግራቸው የሚሄዱ ሰዎች እንዳይጎዱ ከመንገድ ላይ ድንጋይና ምስማሮችን ማንሳት ነው፡፡ ለሰዎች፣ ለአዕዋፋት፣ ለአበቦች፣ ለዛፎች መራራት ነው፤ የእናንተ ስለሆኑ ሳይሆን የነገሮችን ድንቅ ውበት በንቃት ስለተመለከታችሁ ብቻ። ይህን ስሜታዊነት እንዴት ማምጣት ይቻላል?
ጥልቅ ስሜት ሲኖራችሁ አበቦችን አትቀጥፉም፣ ነገሮችን የማጥፋት ሰዎችን የመጉዳት ፍላጎት አይኖራችሁም፤ እውነተኛ አክብሮትና ፍቅር ይኖራችኋል፡፡ በሕይወት አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች መካከል ዋነኛው ፍቅር ነው፡። ፍቅር ስንል ምን ማለታችን ነው? አንድን ሰው የምታፈቅሩት በምላሹ ፍቅር ሽታችሁ ከሆነ በእርግጠኝነት ይህ ፍቅር አይደለም:: ማፍቀር ማለት በምላሹ ምንም ሳይጠይቁ በልዩ የፍቅር ስሜት ውስጥ መሆን ነው፡፡ በጣም ጎበዞች ልትሆኑ፣ ፈተናዎቻችሁን በሙሉ ልታልፉ፣ የዶክትሬት ዲግሪ አግኝታችሁ ትልቅ ቦታ ልትይዙ ትችላላችሁ፡፡ ይህ ስሜታዊነት፣ ይህ የፍቅር ስሜት ከሌላችሁ ግን ልባችሁ ባዶ ይሆናል፣ ህይወታችሁን በሙሉ ትሰቃያላችሁ፡፡
ስለዚህም ልብ በዚህ የፍቅር ስሜት መሞላት አለበት፡፡ ልባችሁ በፍቅር ሲሞላ አታጠፉም፣ ርህራሄ የለሽ አትሆኑም፣ ጦርነቶች አይኖሩም:: ደስተኞች ትሆናላችሁ፡፡ ይህ ፍቅር  እንዴት እውን ሊሆን ይችላል? ፍቅር ከአስተማሪው፣ ከመምህሩ መጀመር እንዳለበት እርግጥ ነው። መምህሩ ስለ ሂሳብ፣ ስለ ጆግራፊ ወይም ስለ ታሪክ መረጃ ከሚሰጣችሁ ይልቅ በልቡ ይህን የፍቅር ስሜት አሳድሮ ስለ ፍቅር ቢናገር፣ ከመንገድ ላይ ድንጋይ ቢያነሳና በሰራተኛው ላይ የስራ ጫና ባይደራርብ፣ ሲናገር፣ ሲሰራ፣ ሲጫወት፣ ሲመገብ፣ ከእናንተ ጋር ሲሆንም ሆነ ብቻውን፤ይህ ስሜት ተሰምቶት --- ስሜቱንም የሚገልጽ ከሆነ እናንተም ፍቅር ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ፡፡
ንፁህ ቆዳ፣ ቆንጆ ፊት ሊኖራችሁ ይችላል፤ የሚያምር ልብስ ልትለብሱ ወይም ታላቅ አትሌት ልትሆኑ ትችላላችሁ፤ በልባችሁ ፍቅር ከሌለ ግን ከሚገባው በላይ አስቀያሚዎች ናችሁ፡፡ ስታፈቅሩ ፊታችሁ ጨፍጋጋ ይሁንም ቆንጆ ያበራል። በህይወት እንደ ፍቅር ያለ ምንም የለም፡፡ ስለ ፍቅር ማውራት፣ ስሜቱን መጎናፀፍ፣ መንከባከብ፣ እንደ ሃብት መያዝ አስፈላጊ ነው:: አለበለዚያ ይጠፋል - ምክንያቱም ዓለም በጣም ጨካኝ ነው፡፡
በወጣትነታችሁ የፍቅር ስሜት ከሌላችሁ፣ ሰዎችን፣ እንስሶችን፣ አበቦችን በፍቅር ካልተመለከታችሁ በዕድሜ ከፍ ስትሉ ሕይወታችሁን ባዶ ሆኖ ታገኙታላችሁ፤ ብቸኞች ትሆናላችሁ፤ ፍርሃት ጥላውን ያጠላባችኋል፡፡ ልባችሁ በዚህ ልዩ የፍቅር ስሜት በተሞላ ጊዜ ጥልቀቱን፣ ደስታውን፣ ፍንደቃውን በተጎናፀፋችሁ ቅጽበት ዓለም ተለውጣ ትታያችኋለች፡፡       
ምንጭ፡- (በተስፋሁን ምትኩ ከተተረጎመው “ውስጣዊን ማንነት ማወቅ” መጽሐፍ የተወሰደ፤1999 ዓ.ም)

Saturday, 28 December 2019 13:55

የልጆች ጥግ

ውድ ልጆች፡- “ማን እንደ ቤት” ሲባል ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? አያችሁ… የራስ ቤት ውስጥ እንደፈለጉ መሆን ይቻላል፡፡ ይመቻል፡፡ በደንብ ከሚያውቋችሁ… ሰዎች ጋር ነው የምትኖሩት
- ከቤተሰባችሁ ጋር!! ጠዋት ላይ ፀጉራችሁ ተንጨባርሮ፣ ፊታችሁን ሳትታጠቡ ሊያያችሁ ይችላሉ፡፡ ግን ችግር የለውም - ቤተሰቦቻችሁ ናቸው፡፡ ገላችሁን እየታጠባችሁ ስትዘፍኑም ይሰሟችኋል አንዳንዴም ያልታጠበ ካልሲያችሁ ይ ሸታቸዋል፡፡ ቢ ሆንም ም ንም አይሏችሁም፡፡ ቤተሰቦቻችሁ ናቸዋ!! ግን አብራችሁ ስትኖሩ… ጥሩ ባህርይ ሊኖራችሁ እንደሚገባ አትርሱ! በአንድ ቤት ውስጥ በጋራ ነው የምትኖሩት፡፡ የየራሳችሁ መኝታ ክፍል ወይም አልጋ ሊኖራችሁ ይችላል:: ሌሎች በጋራ የምትጠቀሙባቸው ነገሮችም ይ ኖራሉ፡፡ ዋ ናው ነ ገር መ ልካም ባህርይ ማሳየትና ቤተሰባችሁን ማክበር ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ቤተሰቡን ደስተኛ ያደርገዋል፡፡
መልካም ሳምንት!!
(Good Manners with Family)

Saturday, 28 December 2019 13:52

የዝነኛ ሴቶች ጥግ

• ‹‹ስኬቴን ሳስብ በእጅጉ የሚያስደስተኝ፣ በባርሴሎና ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ማሸነፌ፣ ለአገራችን ሴት አትሌቶች አዲስ ምዕራፍ መክፈቱ ነው፡፡”
   አትሌት ደራርቱ ቱሉ
• ‹‹ለታማሚዎቼና ለተማሪዎቼ የሚጠበቅብኝን አገልግሎት በጥሩ ሁኔታ ለመስጠትና አገሬን የተሻለች ጤናማ አገር ለማድረግ በውስጤ ቁርጠኛ አቋም አለኝ”
   ዶ/ር የወይን ሃረግ ፈለቀ (ፕሮፌሰር፤ የሕክምና ዶክተር)
• ‹‹ድንቅ ተተኪ ትውልድ ለመፍጠር፣ ድንቅ ሴቶች በእናትነትም ሆነ በመሪነት ያስፈልጉናል፡፡››
   ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ (ነርስ፤ የማህበረሰብ ልማት መሪ)
• ‹‹ሁላችንም፣ እኛ ብቻ እናሳካው ዘንድ ለአንድ የተለየ ዓላማ ታስበን መፈጠራችንን ማወቅ ይገባናል፡፡ እኔ፤ ከዚህ ዓይነቱ ነፃነትን የሚያቀዳጅ ዕውቀት ብዙ ተጠቅሜያለሁ፡፡››
    ዘሪቱ ከበደ (ድምጻዊት)
• ‹‹አባቴ ዩኒቨርሲቲ እንድገባ መፍቀዱን የሰሙ ሰዎች በጣም ነበር የተገረሙት:: ‹ሴትን ልጅ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመላክ የፈቀድከው አብደህ ነው?!› በማለት
ሀሳቡን ተቃወሙ፡፡››
   ሳምያ ዘካርያ (የግብርና ስታትስቲሽያን)
• ‹‹ሴቶች ሕይወታቸውን ለማሻሻልና ህልማቸውን ለማሳካት ይችሉ ዘንድ ኀይለኛና ደፋር እንዲሆኑ እሻለሁ፡፡
   ብሩታዊት ዳዊት (የኢኮኖሚ ባለሙያ)
• ‹‹እናንተም… ወንዶች የገነኑበት ሙያ ውስጥ ገብታችሁ ልትገኑበት እንደምትችሉ አትጠራጠሩ፡፡ ለምን አውሮፕላን አብራሪነት አሊያም ጠ/ሚኒስትርነት
አይሆንም? ምንም የማይቻል ነገር የለም!››
    ካፒቴን አምሳለ ጓሉ (አውሮፕላን አብራሪ)


Page 6 of 464