Administrator

Administrator

Monday, 03 November 2014 07:56

ኢቦላ በአሃዝ ሲገለፅ

የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ የኢቦላ በሽታ ስርጭት በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ነው፡፡ የድርጅቱ ሪፖርት ቀጣዮቹን መረጃዎች ይፋ አድርጓል፡፡
8.033       እስከ አሁን በኢቦላ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች
3865     በኢቦላ በሽታ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች
233    በኢቦላ በሽታ ህይወታቸውን ያጡ የጤና ባለሙያዎች
400     በበሽታው የተያዙ የጤና ባለሙያዎች
21    በኢቦላ ቫይረስ የተጠቃ ሰው የበሽታውን ምልክቶች የሚያሳይባቸው ቀናት
        ***        
የየአገራቱ የጤና በጀት
በአሜሪካ የነፍስ ወከፍ አመታዊ የጤና በጀት     $ 8895
በላይቤሪያ     “    “    “    $ 65
በሴራሊዮን     “    “    “$ 96
በጊኒ        “    “    $ 32
በኢትዮጵያ     “    “    $ 18        
የዓለም ጤና ድርጅት ሌሎች መረጃዎች
በኤችአይቪ በየሳምንቱ - 4795 ሰዎች ይሞታሉ
በተቅማጥ    በየሳምንቱ -2828   ሰዎች ይሞታሉ
በኢቦላ     በየሳምንቱ -10ሺ ሰዎች ይሞታሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡   

        በኢትዮጵያ ከ104 ሺ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች ይገኛሉ
         የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ትብብር ቢሮ ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት፣ በየዕለቱ ከ200 በላይ ኤርትራውያን ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ መግለጹን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ፡፡
በኤርትራ መንግስት አስተዳደር የተማረሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች አገራቸውን ጥለው መሰደዳቸውን ያስታወሰው የተመድ ሪፖርት፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን አደገኛ ድንበር እያቋረጡ በህገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ካለፈው መስከረም ወር አንስቶ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ነው ብሏል፡፡ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከ3ሺህ 500 በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የገለጸው የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ትብብር ቢሮ ሪፖርት፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ቁጥር ከ104 ሺህ በላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡
የስደተኞችን ቁጥር እንዲጨምር ያደረገው ምክንያት በሪፖርቱ እንዳልተገለጸ የጠቆመው ዘገባው፤ይሄም ሆኖ ግን አንዳንድ የመብት ተሟጋች ቡድኖች ኤርትራውያን በአገሪቱ መንግስት የሚደርስባቸው ጭቆና እየከፋ መምጣቱ ለስደቱ መባባስ በምክንያትነት እንደሚያስቀምጡት ገልጧል፡፡

  • በ“ክልሉ ባለፉት ሶስት አመታት ብቻ 5ሺህ ያህል ሰዎች ታስረዋል”
  • የእንግሊዝ ጋዜጦች ኢትዮጵያ በየአመቱ የሚሰጣትን ከ9 ቢ. ብር በላይ እርዳታ ተቃውመውታል
  • የኢትዮጵያ መንግስት የእነአምነስቲን ሪፖርት መሰረተ ቢስ ነው ይላል

        በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ሶስት አመታት 5ሺህ ያህል ሰዎች ኦነግን ትደግፋላችሁ፣ መንግስትን ትቃወማላችሁ በሚል ጥርጣሬ  ክስ ሳይመሰረትባቸው እንደታሰሩና በርካቶችም ለስቃይና ለሞት እንደተዳረጉ “አምነስቲ” የገለጸ ሲሆን የእንግሊዝ ጋዜጦች በየአመቱ፣ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ እርዳታ ተቃውመውታል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተቋማት የሚያወጡት ሪፖርት፤ የውጭ ሃይል ጣልቃገብነትን የሚያራምድ መሰረተ ቢስ ውንጀላ ነው ይላል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት፤ የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሞ ተወላጆች ላይ የሚፈጽመው በደል እየከፋ መምጣቱንና ሰላማዊ ተቃውሞ ባደረጉ ዜጎች፣ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና በተማሪዎች እንዲሁም በክልሉ በሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ በጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ እስር፣ ስቃይና ግድያ እንደሚፈጸም ገልጿል፡፡
በክልሉ በርካቶች ለእስር የተዳረጉት ሌሎች ሰዎች መንግስትን እንዲቃወሙ አነሳስታችኋል በሚል እንደሆነ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ የተጠርጣሪዎች ቤተሰቦችም ጥቃት እንደሚደርስባቸው አስታውቋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የጦር ካምፖች ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ታስረው እንደሚገኙና አብዛኞቹም ከጠበቆችና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እናዳይገናኙ እንደተከለከሉ ሪፖርቱ አብራርቷል፡፡
አለማቀፋዊና ክልላዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማት በአፋጣኝ በጉዳዩ ጣልቃ ሊገቡና በክልሉ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ገለልተኛ የሆነ ምርመራና ማጣራት ሊደረግባቸው ይገባል ብሏል አምነስቲ፡፡
በተያያዘ ዜና የእንግሊዝ መንግስት ከፍተኛ እርዳታ ከሚሰጣቸው አገራት ኢትዮጵያ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ትናንት የዘገበው ቴሌግራፍ፣ ባለፈው አመት ብቻ ከ329 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ እርዳታ መቀበሏን ጠቅሶ የጸጥታ ሃይሎች ዜጎችን ለሚያሰቃዩባት ኢትዮጵያ እርዳታ መሰጠቱን ተቃውሟል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በየአመቱ ከእንግሊዝ የሚያገኘውን ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ እርዳታ ለልማት ማዋል ሲገባው ዜጎችን ለመጨቆን እያዋለው ይገኛል ያለው ጋዜጣው፣ ድርጊቱን አውግዞታል፡፡ ዴይሊ ሜይልም በተመሳሳይ ሁኔታ እንግሊዝ ባለፉት ሶስት አመታት ብቻ ለኢትዮጵያ 1 ቢሊዮን ፓውንድ በእርዳታ መስጠቷን አስታውሶ፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርት በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በመንግስት ሃይሎች ለእስራት፣ ለሞትና ለስቃይ እየተዳረጉ እንደሚገኙ ማስታወቁን ገልጧል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የሚገኙትን የአዳማና ሞጆ አካባቢዎች የሚሸፍን የዲጂታል ቶፖግራፊ ካርታ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ካርታ ስራዎች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
ኤጀንሲው ጃይካ ከተባለው ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት ጋር በትብብር የሚሰራው ዲጂታል ቶፖግራፊ ካርታ፣ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አዲሱ ካርታ ኤጀንሲውን ወደ ዲጂታል የአሰራር ዘዴ እንደሚያሸጋግረው ተጠቁሟል፡፡ የአዳማና ሞጆ አካባቢዎች ለፕሮጀክቱ ስራ የተመረጡት ትላልቅ ፕሮጀክቶችና ሰፋፊ የልማት ስራዎች የሚከናወኑባቸው ስፍራዎች በመሆናቸውና ለአዲስ አበባ ከተማ ያላቸው ቅርበት ስራውን በወቅቱ ለማጠናቀቅ ይረዳል በሚል እንደሆነ ታውቋል፡፡

እስከ 16 አመት የሚደርስ እስር ሊፈረድበት ይችላል

የ21 አመቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ወጣት ሮቤል ፊሊጶስ፤ የአሜሪካ ፖሊስ ባለፈው ሚያዝያ ወር በቦስተን ማራቶን ውድድር ላይ በተከሰተው የቦንብ ጥቃት ዙሪያ በሚያደርገው ምርመራ ሃሰተኛ መረጃ ሰጥቷል፤ ምርመራውን ሆን ብሎ አስተጓጉሏል በሚሉ ሁለት ክሶች ባለፈው ማክሰኞ በቦስተን ፌደራል ፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋተኛ መባሉ ተዘገበ።
ፍንዳታው ከደረሰ ከሶስት ቀናት በኋላ፣ የቦንብ ጥቃቱ ፈጻሚ ነው ተብሎ በሚጠረጠረው ዞካር ሳርኔይ የተባለ ግለሰብ ክፍል ውስጥ የነበሩ ማስረጃዎችን አሽሽተዋል ከተባሉ ሶስት ሰዎች ጋር እንደነበር የተጠረጠረውና የግለሰቡ ጓደኛ የሆነው ወጣት ሮቤል ፊሊጶስ፣ በመጭው ጥር ወር መጨረሻ በቀረቡበት ክሶች በእያንዳንዳቸው እስከ ስምንት አመት የሚደርስ የእስራት ቅጣት ሊጣልበት እንደሚችል ተነግሯል፡፡
ሮቤል በወቅቱ አደንዛዥ ዕጽ ተጠቅሞ ስለነበር፣ በክፍሉ ውስጥ ስለተፈጠረው ነገር ማስታወስ ባለመቻሉ እንጂ ሆን ብሎ አልዋሸም ያሉት የሮቤል ጠበቆች፣ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል፡፡
ሶስት ሰዎችን ለሞት፣ ከ260 በላይ ሰዎችንም ለመቁሰል አደጋ የዳረገውን የቦንብ ጥቃት ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረው ዞካር ሳርኔይ፣ በመጪው ጥር ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ የጠቆመው ዘገባው፤ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ ሞት የሚደርስ  ቅጣት ሊጣልበት እንደሚችል ታውቋል፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩና የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ “በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን የፖለቲካ እንቅስቃሴ” በተመለከተ አሜሪካ ውስጥ ላለፉት ስድስት ወራት ጥናት ሲያደርጉ ቆይተው በቅርቡ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ በአሜሪካ ስለነበራቸው ቆይታ፣ ስለ ጥናታቸው፣ እንዲሁም በሃገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ከፍተኛ ሪፖርተር አለማየሁ አንበሴ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ እንዲህ ቀርቧል፡፡

ላለፉት ስድስት ወራት አሜሪካ ቆይተው ነው የመጡት፡፡ የጉዞዎ አላማ ምን ነበር?
“ናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዲሞክራሲ” በተባለ የአሜሪካ ተቋም ውስጥ ጥናት ሳደርግ ነው የቆየሁት፡፡ ዲሞክራሲ እና የኢትዮጵያ ዳያስፖራን በተመለከተ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚደረገው ዲሞክራሲያዊ ትግል ውስጥ ያላቸውን ሚና ማየት ነበር የጥናቱ ዓላማ፡፡ የአሜሪካ ዋና ከተማ ዲሲ ውስጥ የኢትዮጵያ ሁለተኛ ዋና ከተማ በሚመስል ደረጃ ነው ኢትዮጵያውያኖች ያሉት፡፡ እዚያ አካባቢ ፖለቲካው ያገባናል ብለው የሚንቀሳቀሱትን አግኝቻለሁ፡፡ እንደ ሲያትል፣ ሳንዲያጎ፣ ላስቬጋስ፣ ሳንፍራንሲስኮ፣ ሚኒሶታ፣ ዳላስ፣ ፊላደልፊያ በመሳሰሉት የአሜሪካ ከተሞች ተዛዙሬም ኢትዮጵያውያንን አነጋግሬያለሁ፡፡ በዚያውም ለፓርቲያችን ድጋፍ ለማሰባሰብ ሞክሬያለሁ፡፡ ከሞላ ጎደል በውጭ ያለው ዳያስፖራ በሀገሩ ፖለቲካ ላይ እንዴት ነው? የሚለውን ነው ያየሁት፡፡ በ“ኢሳት” እና በ“ቪኦኤ” እንዲሁም በ“ኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ” ላይ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በተመለከተ በስፋት ቃለምልልሶችንና ክርክሮችን ለማድረግ ሞክሬያለሁ፡፡ መጨረሻ ላይም አሜሪካውያንና ኢትዮጵያውያን በተገኙበት መድረክ ላይ የጥናት ውጤቱን አቅርቤአለሁ፡፡
መሰረታዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት ከኢትዮጵያ መንግስት፣ በውጭው ዓለም ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ምን ይጠበቃል በሚሉት ሶስት መሰረታዊ ነገሮች ላይ ነው አስተያየት ለማቅረብ የሞከርኩት፡፡
በወቅቱ ፕሬዚዳንት ኦባማ፣ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎችን ሰብስቦ ሲያነጋግር፣ እኔ ጥናት ያቀረብኩበት ዲሞክራቶች የሚመሩት ናሽናል ዲሞክራቲክ ኢንስቲቲዩት፣ እንዲሁም ዊልሰን ሴንተርና ፍሪደም ሴንተር የሚባሉ ተቋማት በጋራ የአፍሪካ ሲቪል ማህበረሰብ አባላትን ሰብስበው ነበር፡፡ በጣም ሰፊ ስብሰባ ነው፡፡ በመድረኩ ላይም ስለ አፍሪካ መሰረታዊ ችግሮች ማለትም ስለ ምርጫ፣ ስለ ፍትህ፣ ስለ ሰብአዊ መብት አከባበር… ሃሳቦች ተንፀባርቀው ውይይት ተደርጓል፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይም በተናጋሪነት ተሳትፌያለሁ፡፡ እንግዲህ እነዚህን ስራዎች ስሰራ ነው የቆየሁት፡፡
በዳያስፖራው ላይ ባካሄዱት ጥናት ምን ውጤት አገኙ?
ምንም ጥያቄ የለውም፤ ከዳያስፖራው ጋር በሁለት ነገሮች ላይ መግባባት ያስፈልገናል፡፡ እንደሚታወቀው ያለ ዳያስፖራው ድጋፍ መንቀሳቀስ ይከብዳል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው የፖለቲካ ምህዳር፣ ከሃገር ውስጥ የፋይናንስ ድጋፍ ማግኘት የሚቻልበት ደረጃ ላይ አይደለንም፡፡ የዳያስፖራው ድጋፍ ያስፈልገናል፡፡ ዳያስፖራው ግን ድጋፉን ሲሰጠን ውሃ ልኩን ካላወቀ፣ ሃገር ውስጥ የሚደረገው ትግል መልኩን ሊስት ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገውን ሰላማዊና ህጋዊ ትግል፣ ዳያስፖራው በውጪ ደረጃና ሚዛን ካየው እንዲሁም እንደዚያ ተንቀሳቀሱ ካለ፣ አገር ውስጥ በዚያ ደረጃ መንቀሳቀስ ስለማይቻል፣ ብዙ ተስፋ የመቁረጥ ዝንባሌ ይከሰታል፡፡ ይሄንንም በጥናቴ ተመልክቻለሁ፡፡ ሌላው ደግሞ ዳያስፖራው በሚሰጠው ድጋፍ መጠን በሚፈልገው አቅጣጫ ግፋበት የማለት ዝንባሌ ይታያል፤ እሱም ያስቸግራል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን አስቸጋሪው ዳያስፖራው በተለይ በብሄር የመከፋፈሉ ነገር ነው፡፡ በብሄር ብሄረሰቦች ጥያቄ ዙርያ ዳያስፖራው ሃገር ውስጥ ካለነው በበለጠ ተከፋፍሏል፡፡   ምን ዓይነት ዲሞክራሲያዊ ለውጥ መምጣት አለበት በሚለው ላይ ሀገር ውስጥ ያሉት ተቃዋሚዎችም ሆኑ ዳያስፖራው ስምምነት ላይ ካልደረሱ፣ ለዲሞክራሲ የሚደረገውን ትግል ወደፊት ለመግፋት ይቸግራል፡፡ በዳያስፖራው እና በሃገር ውስጥ ባለው ተቃዋሚ መካከል ኢትዮጵያ እንዴት ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ትሂድ በሚለው ላይ መግባባት መፍጠር ያሻል፡፡
ዳያስፖራው በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በሃይማኖትም ጭምር እስከ መከፋፈል ደርሷል በማለት የሚተቹ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ በጥናትዎ ምን ታዘቡ?
ከሃይማኖት ይልቅ በፖለቲካው ውስጥ ያለው ክፍፍል፣ በተለይ በብሄረሰቦች ጥያቄ ዙርያ ሁለት ፅንፍ አለ፡፡ መሃል መንገድ ላይ የሚሰባሰቡ ኃይሎች ተፈጥረው፣ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ ሊወስን የሚችል ዲሞክራሲያዊ ትግልን መልክ ማስያዝ እስካልቻሉ ድረስ ያለማጋነን የሁለት ፅንፎች እስረኛ እንሆናለን፡፡ አንዱ ኢትዮጵያ የሚባል ነገር አልሰማም ይላል፤ ሌላው ደግሞ የኢትዮጵያዊነት ሰርተፍኬት ሰጪም ከልካይም እኛ ነን ባይ ነው፡፡ ያ ደግሞ አገር ውስጥም ይንፀባረቃል፡፡ እነዚህ ነገሮች መልክ እንዳይዙ ያደረጉት የገዥው ፓርቲ ቀጥታም ሆነ ስውር እጆች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በሃገር ደረጃ ያለባት ፈተናም ይሄን የማለፍ እና ያለማለፍ ነው፡፡
ይሄ የዳያስፖራው ሁኔታ ሀገር ውስጥ ባሉ ተቃዋሚዎች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ምንድን ነው?
በዚህ ምክንያት በአጠቃላይ ትግሉ ተጎድቷል፡፡ ክርር ወዳለው መስመር የመሰባሰብ ችግር አለ፡፡ አብዛኛው ሰውም በዚህ ሃይል ስር ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሃገር ውስጥ ባለው ትግል ላይ ተፅዕኖ አለው፡፡ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂው ገዥው ፓርቲ ነው፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩን ባጠበበ ቁጥር ወደዚህ መሰሉ እንቅስቃሴ ብዙዎች መግባታቸው አይቀርም፡፡ ብሄረሰቦች እየተቻቻሉ፣ የተሻለች ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያን እንዳይፈጥሩ ያደረገው ገዥው ፓርቲ ነው፡፡ የገዥውን ፓርቲ አቅጣጫ መለወጥ ካልቻልን የትም አንደርስም፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩን የማስተካከል ኃላፊነት በግድም ሆነ በውድ የገዥው ፓርቲ ነው፡፡ በዳያስፖራው አካባቢ ላለው የከረረ ፖለቲካ ምንጩ ምንድን ነው? የሚለውን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ዋናው ምንጭ የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበቡ፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ የሚካሄድበት መድረክ መፈጠር ያለመቻሉ፣ ነፃ ሃሳብ የሚንሸራሸርበት ሚዲያ አለመኖሩ፣ በቀላል ቋንቋ ገዥው ፓርቲ “ስልጣን ወይም ሞት?” በሚለው አቋሙ መቀጠሉ ነው ይሄን የፈጠረው፡፡ ትግሉን ወደ ውጪ ያስወጣው እኮ ራሱ ገዥው ፓርቲ ነው፡፡ ጋዜጠኞችን፣ ፖለቲከኞችን የሚያሳድደውና ሰው ወደ ውጭ እንዲያይ የሚያደርገው ገዥው ፓርቲ ነው፡፡ አገር ውስጥ ያለው ነገር ቢስተካከል የኢትዮጵያ ፖለቲካን ትግል ይዞ አሜሪካ ወይም አውስትራሊያ አሊያም ሌላ ሃገር የሚሄድበት ምክንያት የለም፡፡ ይሄ አካሄድ ደግሞ ገዥውን ፓርቲም ቢሆን እየጠቀመው አይደለም፡፡ በዋናነት የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲሰደድ ያደረገው ገዥው ፓርቲ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዳይሰደድ ከፈለገ፣ እዚህ ያለውን የፖለቲካ ምህዳር መክፈትና ማስፋት አለበት፡፡
በአብዛኛው በዳያስፖራው አካባቢ የሚደረገው ትግል እየሰፋ የሚሄድበትና በዚያው መጠን ፖለቲካው የሚከርበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚለውን ብዙ ሰው እየረሳ ነው፡፡ እዚህ ያለው የፖለቲካ ምህዳር ስለጠበበ፣ ስለማያሰራ፣ ወጣቶችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ፖለቲከኞችን ስለሚያሳድድ ውጪ እየሄዱ እየተደራጁ፤ ውጪም ብቻ ሳይሆን ጫካም እየሄዱ እየተደራጁ፣ ባገኙት መንገድ ትግሉን መቀጠል ስለሚፈልጉ ነው፡፡
የዳያስፖራው ትግል ሃገር ውስጥ ባለው ስርአት ላይ ተጨባጭ ተፅዕኖ የመፍጠርና ለውጥ የማምጣት አቅም አለው ብለው ያስባሉ?
ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚደረገው ትግል ካልራቀ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ተጨባጭ የሆነ ለውጥ ማምጣት የሚችልበት እድል አለው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገውን ትግል በሃብት ሊረዳ ይችላል፡፡ በእውቀት፣ በዲፕሎማሲና በብዙ መንገድ ሊረዳ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ባለስልጣናትም ጭምር አሁን የሚደረገውን የዳያስፖራውን ትግል እንደቀላል እያዩት አይደለም፡፡ ዳያስፖራው እኮ ምናልባትም የእነሱም የመጪው ጊዜ መኖሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት፣ ብዙ ወጪ እያወጡ ዳያስፖራ ውስጥ ኑሮአቸውን ለመመስረት እየሞከሩ ነው፡፡ የደርግ ባለስልጣናት ዛሬ ኑሮአቸው ዳያስፖራ ውስጥ ነው፡፡ ባለስልጣናት በሚሄዱበት ሃገር ምን እየገጠማቸው እንደሆነ እያየን ነው፡፡ እኛን በሃገራችን መኖር እንዳንችል አድርጋችሁ እናንተ እዚህ መቀመጥ አትችሉም እየተባሉ ነው፡፡ እነ ጁነዲን ሳዶ እኮ እየተደበቁ ነው የሚኖሩት፡፡ ሃገር ውስጥ ለሰሩት ወንጀል ምናልባት በህግ ልንጠየቅበት እንችላለን እያሉ ይጨነቃሉ፡፡ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይም የዳያስፖራው ሚና ቀላል አይደለም፡፡ በዓመት 4.5 ቢሊዮን ብር ወደ ሃገር ውስጥ ይልካሉ፡፡
በቅርቡ በአሜሪካ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከባንዲራ ጋር በተያያዘ ስለተፈጠረው ሁኔታ ምን ይላሉ?
የባንዲራው ጉዳይ ውስጥ ብዙ መግባት አልፈልግም፡፡ ኢህአዴግም ቢሆን ከማንም በላይ የባንዲራ ጠባቂ ነኝ ሊል የሚችል ድርጅት አይደለም፡፡ በተለይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ስለባንዲራ ምን ይሉ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ኢህአዴግ ያን ያል  የባንዲራ አስከባሪ መሆን አይችልም፡፡ ዋናው ነገር ኤምባሲዎች አካባቢ እንደዚያ ያለ ነገር ገፍቶ ከቀጠለ በአጠቃላይ ጥሩ ምልክት አይደለም፡፡ የሃገሪቱ ያለመቻቻል ፖለቲካ እዚያ ድረስ ሄዶ ሁላችንንም በማያስከብር መልኩ እየተንፀባረቀ ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ ምህዳርን በመዝጋትና በማፈን ብዙ ነገሮችን አደርጋለሁ የሚለውን ደጋግሞ ቢያስብበትና ጩኸቱንም ቢሆን እዚሁ ሃገር ቤት ብንጯጯህ ይሻላል፡፡
ዳያስፖራው በተቻለው ሁሉ አሜሪካ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ተፅዕኖ እንድታሳርፍ ሲጥር መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ በሰጡት መግለጫ፤ “ወዳጅነታችን ተጠናክሯል፣ ውጤታማ ውይይትም አድርገናል” ብለዋል፡፡ በዚህ ዙሪያ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?
የአሜሪካ መንግስት ባለስልጣናት ፍቅራቸውና ሌላ ነገራቸው ብዙም አያሳስበኝም፡፡ እኔ የሚያሳስበኝ የቤት ስራችንን መስራትና አለመስራታችን ነው፡፡ እኔ ፖለቲካል ሣይንስ በተለይም የውጪ ፖሊሲ ላይ አስተምራለሁ፤ እናም “አሜሪካኖች ቋሚ ጥቅም እንጂ ቋሚ ፍቅር የላቸውም፡፡” ለምሣሌ የግብጽ መንግስት ገና መናጋት ሲጀምር “በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ወዳጃችን ነው” እያሉ ሲቀባጥሩ ነበር፡፡ ኋላ ላይ ግን ኦባማ “ሠላማዊ ተቃዋሚን መግደል ወንጀል ነው” ብሎ ተናገረ፡፡ ከዚያ በኋላ ጨዋታው ተቀየረ፡፡ ስለዚህ ዋናው ነገር ኢትዮጵያውያን በጋራ ትግሉን ማጠናከራቸው ነው፡፡ ያ ከሆነ የአሜሪካ መንግስት ትግሉን የማይደግፍበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ አሁን ሁለቱን መንግስታት ያወዳጀው የሽብር ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ በግልጽ ይታወቃል፡፡ በፀረ-ሽብር ጨዋታ ውስጥ ተጠላልፈው ገብተው እያደረጉ ያለው ነገር ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ዋናው እኔን የሚያስጨንቀኝ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሃይሎች፣ የኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሃይሎችና የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱን የቤት ስራ እየሰራ ነው? ለራሱ መብት፣ ክብርና ነፃነት እየታገለ ነው ወይ? የሚለው ጉዳይ ነው፡፡
ካነሱት አይቀር አሁን ያለውን የተቃዋሚ ሃይሎች ፖለቲካ፣ የህዝቡን ፍላጐት እና የገዥው ፓርቲን ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል?
 ሁሉም ፓርቲ የአቅሙን ያህል እየሰራ ነው፡፡ የመከፋፈል ፖለቲካው ግን አሁንም ቀጥሏል፡፡ ብዙ ፓርቲዎች የ97ቱን የመሠለ እንቅስቃሴ መፍጠር አልቻሉም፡፡ ያን ጊዜ ቢያንስ ሁለት ስብስቦች መፍጠር ተችሎ ነበር፤ አሁን ግን ሙከራዎች ቢኖሩም ወደፊት የሚያስኬድ አይመስልም፤ ክፍፍሉ አሁንም አለ፡፡ ነገር ግን ነፃና ፍትሃዊ የሚባለው አይነት የምርጫ ስርአት ከተዘረጋ ምንም ጥርጥር የለውም፣ ኢህአዴግ በአንድ ወር እንቅስቃሴ ይሸነፋል፡፡ ይሄን በሰሞኑ የመምህራን ስልጠና ላይም ተናግሬዋለሁ፡፡ ኢህአዴግን ለማሸነፍ ቀላል ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ኢህአዴግ በአንድ በኩል ተቃዋሚዎች ተዳክመዋል ይላል፤ መቼም ሰይጣን አይደለም ተቃዋሚዎችን የሚያዳክመው፤ ኢህአዴግ ራሱ ነው፡፡ አሞሌና ዱላ ይዞ የሚዞረው ኢህአዴግ ነው፡፡ በአሞሌ ያልወደቀ በዱላ ይወድቃል፡፡ ኢህአዴግ አሞሌና ዱላ ይዞ መዞር ካቆመ፣ እሱን ማሸነፍ ትልቅ ነገር አይደለም፡፡ ይልቁንስ ከዚያ በኋላ ሃገር ለመምራት ተቻችሎ፣ ተግባብቶ የጋራ የፖለቲካ አጀንዳ ቀርፆ ለመንቀሳቀስ ይቻላል ወይ የሚለው ነው እኔን የሚያሳስበኝ፡፡
ኢህአዴግን ለማሸነፍ ያስቸግራል የሚል ግምት ግን የለኝም፡፡ ዋናው ኢህአዴግ የራሱን ዳኛ ይዞ ወደ ጨዋታ ሜዳ አለመግባቱ ነው፡፡ አሁን ዳኛም ተጫዋችም ነው፡፡ ሁልጊዜ ዳኛም ተጫዋችም ሆኜ እቀጥላለሁ ካለ ግን ምናልባትም እኛም ኢህአዴግም የማንፈልገው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈጠር ይችላል፡፡
በአንድ በኩል ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አይደለም የሚል ትችት ከተቃዋሚዎች ሲሰነዘር ይደመጣል፡፡ እነዚያው ፓርቲዎች ግን ባላመኑበት ምርጫ ሲሳተፉ እንመለከታለን፡፡ ቦርዱ ገለልተኛ አይደለም ካሉ በኋላ በምርጫው መሳተፍ ተገቢ ነው ይላሉ?
ሁለት ነገር ነው ያለው፡፡ ተቃዋሚ ስንል ህዝብ ተቃዋሚ ናቸው ብሎ የሚያምንባቸውን ነው እንጂ ኢህአዴግ የሚቀልባቸውን ማለት አይደለም፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ይህ አይነቱ አዙሪት እንዲያበቃ በጋራ “አንሳተፍም” የሚል አቋም መያዝ አለባቸው፡፡ ብዙ ጊዜ እንዲህ ያለ ሃሳብ ማግኘት ያስቸግራል፡፡ አንዱ ትልቁ ችግር ይሄ ነው፡፡ ለምሣሌ በ2002 ምርጫ መድረክ አካባቢ የተሠባሰብነው ወደ ምርጫ ያለመግባት ሃሳብ ነበረን፤ ነገር ግን መኢአድ የስነምግባር ደንቡን በመፈረሙ፣ የተቃዋሚዎችን የጋራ አቋም ስላላገኘን፣ ጨዋታው ከሚበላሽብንና የፖለቲካ ትርፍ ቢገኝ ብለን ገባንበት እንጂ ውጤት ያመጣል ብለን አይደለም፡፡ የ97 ምርጫን ካየን፣ ህብረት በጨዋታው ሜዳ ላይ ተደራድሯል፡፡ የሚፈለገውን በአንድነት ገፍተን ባናገኝም የተወሰኑ ጥቃቅን ነገሮች ተሻሽለዋል፡፡
የሚዲያ አጠቃቀምን ማንሳት እንችላለን፡፡ በወቅቱ ኢህአዴግ የቆመበት መሬት እስኪከዳው ድረስ የገፋነው በሱ ነው፡፡ የ2002 ምርጫ ላይ ግን መግባቱ ጥቅም አልነበረውም፡፡ አሁንም የተቃዋሚዎች ሙሉ አቋምና ውሣኔ እስካልተገኘ ድረስ አንዱ ገብቶ ሌላው ሲቀር አስቸጋሪ ነው፡፡ አንዳንዴ መቀመጫም ባናገኝ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት የምንገባበት አጋጣሚም አለ፡፡ ሌላው ሁለት ምርጫ ላይ ያልተሳተፈ ይሰረዛል የሚል ህግ አለ፤ ያንን በመፍራትም ይገባል፡፡
አሁንስ የ8 ወር እድሜ ለቀረው የ2007 ብሔራዊ ምርጫ የተቃዋሚዎች ዝግጅት ከኢህአዴግ አንፃር እንዴት ይታያል?
ተቃዋሚዎች ዝግጅት ይኖራቸዋል፤ ነገር ግን ዋናው ጉዳይ የፖለቲካ ምህዳሩ እስካልሰፋ የትም አይደረስም፡፡ የ2007 ምርጫን ከአሁኑ ገምግም ከተባልኩ፣ ምናልባት ኢህአዴግ የተወሰኑ የመቀመጫ ፍርፋሪዎችን ለተቃዋሚዎች ለቆ እንደገና አሸነፍኩ ሊል ይችላል፡፡ ያ ማሸነፍ ለኢትዮጵያም፣ ለኢህአዴግም ለሁሉም የሚጠቅም አይመስለኝም፡፡ ምንጊዜም ህዝብን ተስፋ አታሳጣ፤ ህዝብን ተስፋ ካስቆረጥከው ተስፋ የቆረጠ ስራ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ አሁንም ሃገር ውስጥም ሆነ ውጪ ብዙ ነገሮች ጤናማ አይደሉም፡፡
ቀደም ብለው እንደነገሩኝ፤ በአሜሪካ ቆይታዎ ኢሣት ቴሌቪዥን ላይ ሰፊ ቃለ ምልልስና አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ ጣቢያውን የ“አሸባሪዎች” ልሣን ነው በማለት የፖለቲካ ድርጅቶች ከጣቢያው ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲገቱ አስጠንቅቋል፡፡ ከዚህ አንፃር ጉዳዩ ስጋት ውስጥ አልከተትዎትም?
“ኢሣት” እንግዲህ የኢህአዴግ ወዳጅ ሃገር በሚባለው አሜሪካ በነፃ ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ ጣቢያ ነው፡፡ ድጋፍ ከማህበረሰቡ እያሰባሰበ ነው የሚሠራው፡፡ እዚያ ጣቢያ ላይ መረራ የራሱን አስተያየት ነው የሰጠው እንጂ የኢሣትን ፕሮፓጋንዳ አይደለም ያንፀበረቀው፡፡
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ነው አስተያየቴን የሰጠሁት፡፡ ኢሣት ጠመንጃ የለውም፣ የትጥቅ ትግልም እያካሄደ አይደለም፡፡
 ስለዚህ እኔ እንደ ከባድ ነገር አላየውም፡፡ በነገራችን ላይ የኢህአዴግ ባለስልጣናትም አልፎ አልፎ አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥንን ባያፍን እኮ “ኢሣት” ጋ የምሄድበት የተለየ ምክንያት የለኝም፡፡ የውጪ ሚዲያ ጋ እንዳንሄድ ከፈለገ፣ የሀገር ውስጡን ይስጠን፡፡ መረራ “ኢሣት”ን ባይጠቀም ሌሎች ብዙ ሺህ ምሁራን ይጠቀሙበታል፡፡ እንደሚታወቀው የኛ ፓርቲ የሽብር ፕሮጀክት የለውም፤ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ነው የሚታገለው፡፡ “ኢሳት” ላይ የምናገረው ሃገር ውስጥ ባለው ቴሌቪዥን ጣቢያ እንድናገር እድል ቢሰጠኝ የምናገረውን ነው፡፡ እኔ ውጪም ሆነ ውስጥ ቋንቋዬ አንድ ነው፡፡

(ዘልኤ አይቤ ጋዬ - ዎሬ አይቤ ቁፌ) የወላይታ ተረት

ከላፎንቴን ታሪኮች አንዱ እንዲህ ይለናል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን የሰማይ ቁጣ በእንስሳት ላይ እየመጣ ነው ስለተባለ የዱር እንስሳት ተሰብስበው ማ አጠፋ? ማ አጠፋ? በመባል ጥፋተኛውን አጋልጠው ለመስጠት አውጫጪኝ ይቀመጣሉ፡፡ እንስሳት ሁሉ ለረሀብ ተጋልጠው የእርስ በርስ ፍቅራቸው ሁሉ ሞቷል፡፡ ሁሉ ተኮራፍፏል፡፡ ተኩላ ከተኩላ እርግብ ከእርግብ እንኳ አይነጋገሩም! ከመጣው መዓት ለመዳን ሁላችሁም ሀሳብ ስጡ ተባለ፡-
አንበሳ ወንበሩን ያዘና በሊቀመንበርነት፡-     
“ወዳጆቼ ሆይ! የሰማይ ቁጣ ጥፋተኞች ላይ መውረዱ ደንብ ነው፤ አንቃወመውም፡፡ ነገር ግን ሁሉ ኃጢያት እኩል አይደለምና የበለጠና የከፋ ኃጢያት የሰራውን መለየት ይኖርብናል! ያ ጥፋተኛ ቅጣቱን ሲቀበል ለእኛ ስርየት፣ መዳኛ ይሆንልናል! ህሊናችንን ሳናጭበረብር ዕውነቱን እንናገር፡፡ እኔ በበኩሌ  ጥቂት ያስቀየሙኝን በጎች በልቻለሁ - አንዳንዴም እረኞቻቸውንም የቀመስኩበት ጊዜ ነበረ፡፡ ወድጄ አይደለም ስላስቀየሙኝ ነው፡፡ ይህ ጥፋት ነው ካላችሁ ሞት ይፈረድብኝ፡፡ ብቻ ዋናው ነገር ሌሎቻችሁም ኃጢያት ኃጢያታችሁን ተናዘዙ፡፡ ድርሻ ድርሻችሁን ውሰዱ፡፡ ከዚያ የከፋ ጥፋት የሰራውን እንለያለን፡፡ (It is only fair that all should do their best
to single out the guiltiest)”
ከዚያ ቀበሮ ተነሳና
“ንጉሥ ሆይ! ለእንደ ርሶ ያለ የተከበረ የዱር አራዊት ጌታ፤ በግ መብላት በጭራሽ ሀጢያት ሊሆን አይችልም፡፡ እነዚህን ባለጌና ልክስክስ በጎች መብላት ፈፅሞ ሊያስጠይቅ አይገባም፡፡ እረኞችም ቢሆኑ በእኛ ላይ ሲዶልቱ የሚኖሩ ናቸውና የእጃቸውን ነው ያገኙት” ብሎ ተቀመጠ፡፡ ጭብጨባው ቀጠለ፡፡
ቀጥሎ ማንም በነብር፣ በድብና በመሳሰሉት ክቡር እም ክቡራን ይቅርታ - የለሽ ወንጀል ላይ ምንም ሀሳብ ሳያነሳ ጭራሽ እንዲህ ያለ የተቀደሰ ተግባር የፈፀመ ከዚህ የለም፤ እየተባለ ውዳሴው ተዥጎደጎደ፡፡
በመጨረሻ አህያ ተነሳች፡-
“አንድ ቀን አንድ ሰፊ የሣር መስክ ሳቋርጥ ረሀብ አንጀቴን ቢመዠርጠኝ የምላሴን ያህል ቅንጣት ሳር ግጬ አልፌያለሁ፡፡ ያንን ሳር የመጋጥ መብት እንደሌለኝ በእርግጥ አውቃለሁ” አለች፡፡
ሁሉም እጃቸውን እያወጡ በአህያ ላይ የእርግማን መርግ ይጭኑባት፣ ይወርዱባት ጀመር፡፡ አንድ የተማረ፣ ብዙ ያነበበ የሚባል ተኩላም ተነስቶ፤
“ከዚህ በላይ በዓለም ላይ ኃጢያት ተሰርቶ አያውቅም፡፡ የኃጢያቶች ሁሉ ኃጢያት የሰው ሣር መጋጥ ነው! የሁላችንንም ኃጢያት ልትሸከም የሚገባት ይህቺ አህያ ናት! ቁጣውም እሷ ላይ መውረድ አለበት፡፡ የተንኮል ሁሉ ደራሲ እሷ ናት! ፎ! የሰው ሳር እንዴት ይጋጣል?! ስለዚህ ሞት ነው የሚገባት! ሆኖም አንድ ሀቅ ልጨምር ብሎ በግጥም ቀጠለ፡፡
“ሀብታም ሆንክ ደሀ፣
ክክቡር ነህ የተባልክ ወይ ከንቱ ቁጥር
ሁልህ ይደርስሃል የተራህ ሥፍር
ችሎት ይቀባሃል፣ ወይ ነጭ ወይ ጥቁር!”
                                              *         *         *
ፍሬድሪክ ኒች “ከመጥፎ ሥራ ጋር አብሮ ከመኖር ከመጥፎ ህሊና ጋር አብሮ መኖር ይከብዳል” ይላል፡፡ በሌላው ላይ በጅምላ ስምምነት፣ በመንገኝነት መፍረድ ትልቅ ኃጢያት ነው፡፡ ውሎ አድሮ እንቅልፍ መንሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከህሊና ጋር በእፎይታ ማደር፣ ያለ አንዳች ወንጀለኝነት ስሜት አንገትን ቀና አድርቶ ለመሄድ መቻል ታላቅ ጸጋ ነው፡፡ የራስን አሳር የሚያህል የተቆለለ ወንጀል አድበስብሶ አንዲትን ቀጭን ሽፋን አጋኖ በሌላው ላይ መደፍደፍ አገር ገዳይ ነው! ህዝብ አሰቃይ ነው፡፡
“በክፉ ሰዓት የእናት ልጅ አይታመንም!” ይላል አበሻ ሲተርት፡፡ በክፉ ሰዓት የማ ባህሪ መቼ እንደሚቀየር አይታወቅም፡፡ በክፉ ሰዓት የትኛው ወዳጅ ተገልብጦ ጠላት እንደሚሆን አይታወቅም፡፡ ብዙ የፌሽታ ጊዜ ጓደኞች ጊዜ ከምበል ሲል አብረው ይከነበላሉ! ዕበላ - ባዮች፣ አቋም - የለሾች፣ አድር-ባዮች፣ አሥጊና አጥፊዎች ናቸው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ስለሆነም ለህዝብም ለአገርም አይበጂም!
በጥንታዊት ቻይና የዌይ ግዛተ - መንግስት አንድ ለንጉሱ ታማኝ ሚሱ ሳይ የሚባል ባለሟል ነበር፡፡ የግዛቱ ህግ “የንጉሱን ሰረገላ በሚስጥር የነዳ ሰው እግሩ ቆረጣል” ይላል፡፡ ያ ታማኝ ሰው እናቱ ትታመምና ልትሞት ታጣጥራለች፡፡ ሊደርስላት የንጉሡን ሰረገላ ምንም አይሉኝም ብሎ እየነዳ ሄደ፡፡ ንጉሡ ይሄን ሲሰሙ “አይሱ ሳይ! እጅግ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ነው፡፡ ለእንቱ ሲል እግሮቹን እንደሚያጣ ረሳ!” አሉ፡፡ ታማኝ ሰዎች ታማኝነታቸው የት ድረስ መብት እንደሚሰጣቸው የረሱ‘ለት ራሳቸውን ያጣሉ ነው ትምርተ - ታሪኩ (Lesson/Moral of the story እንዲሉ ፈረንጆች፡፡)
የሀገራችን ፕሮጀክት ቀራጮች፣ ንድፈ - ሀሳብ አንጓቾች (theoreticians) አማካሪዎች፣ ስትራቴጂስቶች፣ ቀዳሽ ዳሳሾች በእርግጥ ከልባቸው ለህዝብና ለአገር ተቆርቁረው ነው ወይ ሥራውን የሚሰሩት ብሎ መፈተሸ የአባት ነው! ማ በተዘዋዋሪ ወገንተኛ ነው? ማ ልታይ ልታይ እያለ ከሙሰኞች ጋር የተሰለፈ ነው? ማ አፍአዊ፣ ማ ልባዊ ነው? ማ አጉራሽ አልባሽነትን እንደትራንስፎርሜሽን እያስቆጠረ ነው? ውስጣችንን እንፈትሽ፡፡ አንደበተ - ርቱዑን ከበቀቀኑ እንለይ፡፡
ፖለቲካችን፣ ኢኮኖሚያችን፣ ማህበራዊ ግንኙነታችን በአስመሳይ ሰዎች ሲታጠር ህይወታችን ጉድፍ የተሞላ፣ በደል የበዛው፣ ዕድገታችን ሀሳዊ፣ ፍቅራችን ነውር ያጎደፈው፣ ተስፋችን ጨለግላጋ፣ የጋራ ቤታችን የተራቆተ እንደሚሆን ገሀድ ነው፡፡ ምን እየዘራን ምን እያጨድን እንደሆነ በቅጡ ልብ እንበል፡፡ “ንግድ ምንድንነው? ትንባሆ፤ ትርፉ ምንድን ነው? - ሳል” የሚለውን የወላይትኛ ተረት አበክረን እናስምርበት!

ጥቃቱ ከአይሲስ ጋር ሊያያዝ ይችላል እየተባለ ነው
ባለፈው ረቡዕ ማለዳ በካናዳ ርዕሰ መዲና ኦትዋ በሚገኘው የአገሪቱ የጦርነት መታሰቢያ አደባባይና በፓርላማ ውስጥ በተከሰተውና ሁለት ሰዎችን ለህልፈት በዳረገው የተኩስ ጥቃት ዙሪያ የተጀመረው ምርመራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ሲ ኤን ኤን ዘገበ፡፡
ሚካኤል ዜሃፍ ቢቤው የተባለ የታጠቀ ግለሰብ፣  የአገሪቱን የጦርነት መታሰቢያ አደባባይ በመጠበቅ ላይ በነበሩ ሁለት ወታደሮች ላይ ተኩስ በመክፈት አንደኛውን የገደለ ሲሆን፣ ከሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ሌሎች ሶስት ወታደሮችን ካቆሰለ በኋላ የግለሰቡ ህይወት ማለፉን ዘገባው ገልጧል፡፡
ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት በአገሪቱ ፓርላማ ተገኝተው ለምክር ቤቱ አባላት ንግግር እያደረጉ የነበሩት የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ስቴፈን ሃርፐር ጉዳዩን በተመለከተ ረቡዕ ምሽት በሰጡት መግለጫ፣ አገሪቱ በመሰል ጥቃቶችና ነውጦች እንደማትሸበር ገልጸው፣ ጥቃቱ ካናዳ ከአጋሮቿ ጋር በመሆን ጽንፈኝነትን ለመዋጋት የያዘችውን አቋም የበለጠ እንድታጠናክር የሚያደርግ ነው፤ ጽንፈኞች እንደፈለጉ የሚፈነጩበት ምቹ ቦታ አያገኙም ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥቃቱን የፈጸመው ሚካኤል ዜሃፍ ቢቤው የተባለ ግለሰብ መሆኑን ከመግለጽ ባለፈ ማንነቱንም ሆነ ድርጊቱን ለመፈጸም ያነሳሳውን ምክንያትና አላማውን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ያልሰጡ ሲሆን፣ ስለአሸባሪው ተጨማሪ መረጃ ለማግኘትና ሌሎች ተባባሪዎች እንዳሉት ለማጣራት የተጀመረው ምርመራ በጥቂት ቀናት ውስጥ ውጤት ያስገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡በወሩ መጀመሪያ ላይም የካናዳ መንግስት በኢራቅ የሚገኙ የአይሲስ ታጣቂዎችን ለማጥቃት በሚደረገው ዘመቻ ላይ ለመሳተፍ እቅድ እንዳለው ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው ሰኞ አንድ የአገሪቱ ወታደር አሸባሪ ተብሎ በተጠረጠረ ግለሰብ ሞንትሪያል ውስጥ በመኪና ተገጭቶ መገደሉን ተከትሎም፣ አገሪቱ ያለባትን የሽብር ስጋት መጠን ከዝቅተኛ ወደ መካከለኛ ደረጃ ከፍ ማድረጓን አስታውሷል፡፡
ካናዳ አይሲስ የተባለውን ጽንፈኛ ቡድን ለመዋጋት በተጀመረው አለማቀፍ እንቅስቃሴ እንደምትሳተፍ በይፋ ማስታወቋንና በቡድኑ ላይ ለሚደረገው የአየር ድብደባ ላይ የሚሳተፉ ስድስት ተዋጊ ጀቶችን ለመላክ መወሰኗን ተከትሎ ጥቃቱ መከሰቱ፣ ጉዳዩ ከአይሲስ ጋር ተያያዥ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ መፍጠሩን ዘገባው አስታውቋል፡፡አይሲስ ካናዳውያንን ለሽብር ጥቃት እየመለመለ እንደሆነ በቅርቡ ማስታወቁን ያስታወሰው ዘገባው፤ የአገሪቱ መንግስት ባለፈው ነሃሴ ወር ላይ ባወጣው ሪፖርትም፣ 130 ያህል ካናዳውያንም ወደሌሎች አገራት በመሄድ ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር መቀላቀላቸውንና ከእነዚህ ውስጥም 30 የሚሆኑት በሶርያ በሚካሄደው ጦርነት ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚገመት ማስታወቁን ገልጧል፡፡
በአገሪቱ መሰል የሽብር ጥቃቶች በጂሃዲስቶች ሊሰነዘሩ እንደሚችሉ ይገመት እንደነበር የጠቆመው ሲ ኤን ኤን፤ አሜሪካም መረጃ አግኝቻለሁ በማለት በቅርቡ በካናዳ በሚገኘው ኤምባሲዋና ቆንስላዋ ላይ ያለውን የደህንነት ሁኔታ በጥብቅ መከታተል መጀመሯን አስታውሷል፡፡አይሲስም ሆነ ሌሎች ቡድኖች ለጥቃቱ ሃላፊነት አለመውሰዳቸውን የገለጸው ዘገባው፣ የአገሪቱ የደህንነት መስሪያ ቤትም አይሲስ ወይም ሌሎች የሽብር ቡድኖች ከጥቃቱ ጋር በቀጥታ እንደሚያያዙ የሰጠው መግለጫ በይፋ ባያስታውቅም፣ በጉዳዩ ላይ ጥብቅ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ቢቢሲ በበኩሉ፤ በካናዳ የተለያዩ የጽንፈኛ ቡድኖች አባላትና ግለሰቦች አክራሪነትን መስበክ ከጀመሩ መቆየታቸውን በመጥቀስ፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ብጥብጦችን መፍጠር እንደሚገባ ብዙዎችን ማሳመን መቻላቸውን ዘግቧል፡፡ የአገሪቱ ፖሊስ 90 ተጠርጣሪዎችን ያሳተፉና ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዙ 63 የብሄራዊ ደህንነት ጉዳዮችን በመመርመር ላይ እንደሚገኝ ባለፈው ሳምንት ማስታወቁንም አስታውሷል፡፡




* ተኩስ ሊያቆምና ያገተውን ሊፈታ ተስማምቷል የተባለው ቦኮ ሃራም፣ ግድያና ጠለፋውን ቀጥሏል

   ቦኮ ሃራም የተባለው የናይጀሪያ አሸባሪ ቡድን፣ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የሸሪያ ህግ ተግባራዊ እንዲሆን የማስቻል አላማውን ለማሳካት ባለፉት አምስት አመታት፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶችን እንደፈጸመና ከ5ሺህ በላይ ናይጀሪያውያንን እንደገደለ ይነገራል፡፡
ቡድኑ ባለፈው ሚያዝያ ወር ቺቦክ ወደተባለችው ከተማ ድንገት ብቅ ብሎ የፈጸመው ድርጊት ግን፣ ያልተጠበቀና ብዙዎችን ያስደነገጠ ነበር፡፡ የታጠቁ የቦኮ ሃራም ወታደሮች፣ አገር አማን ብለው ወደ ትምህርት ቤታቸው በመጓዝ ላይ የነበሩ 276 ልጃገረዶችን አፍነው፣ ወዳልታወቀ ስፍራ አጋዙ፡፡
ይህ ድርጊት የአገሪቱን መንግስት፣ የልጃገረዶቹን ወላጆችና የቺቦክ ከተማ ነዋሪዎችን ብቻ ሳይሆን፣ መላውን ናይጀሪያዊና አፍሪካውያንን ብሎም አለምን አስደነገጠ፡፡ መገናኛ ብዙሃን ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተው አስተጋቡት፡፡ በአሸባሪው ቡድን የታገቱት ናይጀሪያውያን ልጃገረዶች ዕጣ ፋንታ ብዙዎችን አስጨነቀ፡፡
የተወሰኑ ልጃገረዶች ለማምለጥ ቢችሉም፣ እንደታገቱ ያሉት 219 ያህል ልጃገረዶች ጉዳይ ይህ ነው የሚባል እልባት ሳያገኝ ስድስት ወራት አለፉ፡፡ የአገሪቱ መንግስት ያሰረብኝን ታጣቂዎቼን ካልፈታ፣ ልጃገረዶቹን ለባርነት እሸጣለሁ በማለት ሲዝት የቆየው ቡድኑ፤ የሽብር ጥቃት መፈጸሙን አጠናክሮ እንደገፋበት ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
“አላህ ልጃገረዶቹን መሸጥ እንዳለብኝ ነግሮኛል፡፡ እሸጣቸዋለሁ፡፡” ብሏል የቦኮ ሃራም መሪ ነኝ ያለ ግለሰብ ከሶስት ሳምንታት በፊት በይፋ፡፡የናይጀሪያ መንግስትም ለታገቱት ዜጎቹ ጉዳይ ተገቢውን ትኩረት አልሰጠም የሚል ትችት ሲሰነዘርበት ቆይቷል፡፡ የአገሪቱ የጦር ሃይል አባላት የሆኑ ወታደሮችም፣ መንግስት የቡድኑን ጥቃት በተገቢው ሁኔታ ለመመከት የሚያስችል ድጋፍ እያደረገላቸው አለመሆኑን መናገራቸውን የዘገበው ሲኤንኤን፣ የአሜሪካ መንግስት እገታው ከተፈጸመ ከአንድ ወር በኋላ፣ ልጃገረዶቹን የሚያፈላልጉ 80 አሜሪካውያን ወታደሮችን ወደ ቻድ መላኩን አስታውሷል፡፡በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ግን፣ የናይጀሪያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተስፋ ሰጪ መግለጫ አወጡ፡፡ የአገሪቱ መንግስት ከአሸባሪው ቡድን ጋር ባለፈው ሳምንት በቻድ የተኩስ አቁም ስምምነት መፈጸሙንና ቡድኑ ያገታቸውን ልጃገረዶች ለመልቀቅ መስማማቱን አስታወቁ፡፡
በጀርመን መዲና በርሊን ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የናይጀሪያው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሚኑ ዋሊ በበኩላቸው፤ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ስምምነት ላይ መደረሱንና ልጃገረዶቹ በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚለቀቁ በእርግጠኝነት ተናግረዋል፡፡
“አሸባሪ ቡድኑ ልጃገረዶቹን እስከ መጪው ሰኞ ለመልቀቅ ተስማምቷል” ብለዋል፡፡ የናይጀሪያ መንግስት ቃል አቀባይ ማይክ ኦሜሪም፤ የታገቱት ልጃገረዶች በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ሲኤንኤን እንደዘገበው፣ ቦኮ ሃራም በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ድረስ የራሱን መግለጫ አለማውጣቱ ብዙዎችን አጠራጥሯቸዋል፡፡ የአለማቀፍ ፖለቲካ ተንታኞችም በሁለቱ ሃይሎች መካከል የተደረሰውን ስምምነት በጥርጣሬ እንደሚያዩት አስታውቀዋል፡፡
ቡድኑ እስላማዊ መንግስት የመመስረት ዓላማውን ለማሳካት በጦርነት ሊቀጥል ይችላል የሚሉት እነዚሁ ተንታኞች፣ ስምምነቱን ያደረገውም የበለጠ ለመደራጀትና ራሱን ለማጠናከር የሚሆን ጊዜ ለመግዛት ሲል እንደሚሆን ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡
መንግስት ከቡድኑ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት መፈጸሙን ቢያስታውቅም፣ የቦኮ ሃራም አባላት እንደሆኑ የተነገረላቸው ታጣቂዎች ግን በሁለት መንደሮችና በአንድ ከተማ ላይ በከፈቱት ተኩስ ስምንት ያህል ሰዎችን ሲገድሉ፣ ሌሎች ልጃገረዶችንም አግተዋል፡፡

Saturday, 25 October 2014 10:47

የፀሃፍት ጥግ

* ደራሲ ልብወለድ ሲፅፍ ህያው ሰዎችን መፍጠር አለበት፡፡ ገፀባህርያትን ሳይሆን ህያው ሰዎችን፡፡ ገፀባህርያት አስቂኝ ስዕሎች ናቸው፡፡
ኧርነስት ሄሚንግዌይ
* የፃፍኩት ነገር ፅሁፍ ከመሰለ ደግሜ እፅፈዋለሁ፡፡ በእንግሊዝኛ የድርሰት አፃፃፍ ትምህርት ላይ የተማርነው ነገር የታሪኩን ድምፀትና ዜማ እንዲረብሽ አልፈቅድም፡፡
ኢልሞር ሊኦናርድ
* መፃፍ፡፡ እንደገና መፃፍ፡፡ ሁለቱም ከሌሉ  ደግሞ ማንበብ፡፡ ሌላ አቋራጭ መንገድ አላውቅም፡፡
ላሪ ኤል ኪንግ
* ለረዥም ልብወለድ ህጎች የሉም፡፡ ኖረውም አያውቁም፡፡ ሊኖሩም አይችሉም፡፡
ዶሪስ ሌሲንግ
* ዘይቤ ማለት ዘይቤዎችን በሙሉ መርሳት ነው፡፡
ጁሌስ ሬናርድ
* ፀሐፍት ሁለት ጊዜ ነው የሚኖሩት፡፡
ናታሊ ጎልድበርግ
* የመጨረሻው ዓረፍተነገር እስካልተፃፈ ድረስ የመጀመሪያው ዓረፍተነገር ሊፃፍ አይችልም፡፡
ጆይስ ካሮል አትስ
* ምክርን ተጠንቀቅ - ይሄኛውንም ጭምር፡፡
ካርል ሳንድበርግ
* ቀስቃሽ ሰዓት አልፈልግም፡፡ ሃሳቦቼ ከእንቅልፍ ይቀሰቅሱኛል፡፡
ሬይ ብራድበሪ
* ፅሁፍ የተባለ ነገር ሁሉ ልክፍት ይመስለኛል፡፡ ልትገቱት አትችሉም፡፡
ዊሊያም ካርሎስ ዊልያምስ
* ሁልጊዜ መፃፍ የምጀምረው በንፁህ ወረቀትና በቆሻሻ አዕምሮ ነው፡፡
ፓትሪክ ዴኒስ
* መፅሐፍ የሃሳብ መያዣ ብቻ ነው - ልክ እንደጠርሙስ፡፡ ዋናው ጉዳይ መፅሃፉ ውስጥ ያለው ቁም ነገር ነው፡፡
አንጄላ ካርተር