Administrator

Administrator

 “የደሞዝ ጭማሪው ለሌላው ሲደርስ ለጋዜጠኛው አልደረሰም” ጋዜጠኞች

“ጭማሪው ሰሞኑን በቦርዱ ተወስኗል፤ በቀጣዩ ወር ይደርሳቸዋል” አቶ ሽመልስ ከማል

 

“ድርጅቱ በደመነፍስ ይመራል የሚለው አጉል አሉባልታ ነው” የፕሬስ ድርጅት ሥ/አስኪያጅ

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስር የሚታተሙት አዲስ ዘመን፣ ኢትዮጵያን ሄራልድ፣ በሪሳ እና አል-አለም ጋዜጠኞች በመስሪያቤታቸው የመልካም አስተዳደር እጦት እየተማረሩ መሆኑን ገለፁ፡፡ መንግስት በድርጅቱ ውስጥ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር እያወቀ ምላሽ አለመስጠቱ እንዳሳዘናቸው ጋዜጠኞቹ ተናግረዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ለመንግስት ሰራተኞች የተደረገው የደሞዝ ጭማሪ ለጋዜጠኞች አለመድረሱን የገለፁት ሰራተኞቹ፤ ላለፉት አራት ዓመታት የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው እያገለገሉ ያሉት አቶ ሽመልስ ከማል አንድም ቀን ሰብስበው አወያይተዋቸው እንደማያውቁ በምሬት ገልፀዋል፡፡

“ድርጅቱ በዚህ ዓመት ይህን እሰራለሁ ብሎ ያስቀመጠው ግብ የለም፣ ጋዜጠኛው የሚመራው ብቃት በሌለው ስራ አስኪያጅ ነው፣ ይህንንም በስብሰባ ለራሳቸው ለስራ አስኪያጁ ተናግረን ችግሩን የሚያጣራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ያጣራውን ለሚመለከተው አካል ቢያቀርብም የተሰጠ ምላሽ የለም” ብለዋል - ጋዜጠኞቹ፡፡ የቦርዱ ሰብሳቢ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል በበኩላቸው፤ አንድም ቀን አወያይቶን አያውቅም የሚለው ፍፁም ሀሰትና የተሳሳተ መረጃ መሆኑን ገልጸው፣ በየጊዜው ከጋዜጠኞችና ከኤዲተሮች ጋር እንደሚወያዩና በኤዲተሮችና ዋና አዘጋጆች ፎረም ላይ የተለያዩ ሃሳቦች እየተነሱ በምክክር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

“ከሰራተኛው መካከል የራሳቸው ጥቃቅን የጥቅም ግጭት ያላቸው አንዳንድ ግለሰቦች የሚነዙት አሉባልታ እንደ አጠቃላይ የሰራተኛው ችግር ተደርጎ መነሳቱ መሰረተ ቢስ ነው” ብለዋል - አቶ ሽመልስ፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰብስቤ ከበደን በጉዳዩ ዙሪያ አነጋግረናቸው በሰጡት ምላሽ “ድርጅቱ በእቅድና በፕሮግራም እንደሚመራ በቢሮ ተገኝቶ አሰራሩን ማረጋገጥ ይቻላል” ያሉ ሲሆን፣ አንዳንድ የግል ችግር ያለባቸው ግለሰቦች የድርጅቱንና የአመራሩን ስም ለማጥፋት ሆን ብለው የሚነዙት ተጨባጭ ያልሆነ ወሬ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ድርጅቱ ችግር ቢኖርበት ኖሮ ሰራተኛውን የሚያወያይበት የስብሰባ መድረክ እያዘጋጀ አያወያይም ነበር” ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ በቅርቡ አጠቃላይ ስብሰባ ተጠርቶ ከሰራተኞች የተለያዩ አስተያየቶች መሰጠታቸውንና በውይይት መድረኩ ላይ የተነሱትን አንዳንድ ክፍተቶች እንደግብአት በመጠቀም የአሰራር ማስተካከያ እየተደረገ እንደሆነ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

ጋዜጠኞቹ በበኩላቸው ለመልካም አስተዳደር እጦቱ እንደዋና ማሳያ ያቀረቡት የድርጅቱ ህንፃ በሁለት ዓመት ተገንብቶ ይጠናቀቃል ቢባልም አራት አመት ፈጅቶ እንኳን አሁንም ይቀረዋል፣ የሰራተኛ የቅጥር ሁኔታው ግልፅነት የለውም፣ ሹፌር ሳይቀር በፍሪላንስ የሚቀጠርበት ሁኔታ አለ፣ የደሞዝ ጭማሪና የእድገት ሁኔታ በአድሎአዊ አሰራር የተተበተበ ነው፤ በዚህም የተነሳ ለጋዜጦቹ አለኝታ የሚባሉ ወደ 50 ሰራተኞች ባለፈው ዓመት ለቀዋል፤ ዘንድሮም የለቀቁ አሉ በማለት ተናግረዋል፡፡ መንግስት ይህን ሁሉ ችግር ያውቃል፤ ግን ማስተካከያ አልተደረገም ብለዋል፡፡ ፕሬስ ውስጥ በሲቪል ሰርቪስና በቦርድ የሚተዳደር ሁለት ዓይነት ሰራተኛ መኖሩን ጋዜጠኞቹ ገልጸው፣ በሲቪል ሰርቪስ የሚመራው ሰራተኛ ጭማሪው ሲደርሰው የእኛ ዘግይቷል ብለዋል፡፡

“በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ጋዜጠኞች ደሞዝ የፕሬሱ ጋዜጠኞች ይበልጥ ነበር” ያለው አንድ ቅሬታ አቅራቢ ጋዜጠኛ፤ ኢዜአዎች ፕሬስ አቻ ድርጅት ሆኖ እንዴት ደሞዝ ይበልጡናል በሚል ላነሱት ጥያቄ በአፋጣኝ ምላሽ ተሰጥቷቸው ደሞዛቸው መስተካከሉን አስታውሶ፤ የእኛ አቻ ድርጅት በሆነው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) በቅርቡ እስከ 200 ፐርሰንት የደሞዝ ጭማሪ ቢደረግም በእኛ ድርጅት ምንም የተባለ ነገር ባለመኖሩ ጋዜጠኛው በድርጅቱ ተስፋ እየቆረጠ ነው ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ጭማሪውን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፤ በሲቪል ሰርቪስ የሚተዳደሩት የሚከፈላቸው በመንግስት በመሆኑ እንደማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ ጭማሪው ቀድሞ እንደረሳቸው አምነው፣ ሆኖም በቦርድ ለሚተዳደሩት ጋዜጠኞች የሚከፈለው ድርጅቱ ከማስታወቂያና ከጋዜጣ ሽያጭ ከሚያገኘው ገቢ ላይ በመሆኑና ስኬሉ ስለሚለያይ ቦርዱ ተወያይቶ ውሳኔ እስኪሰጥበት ሲጠበቅ እንደነበር አብራርተዋል፡፡ “ውይይቱ ተጠናቅቆ ቦርዱ ከትላንት በስቲያ ስለወሰነላቸው ጭማሪው በቀጣዩ ወር ይደርሳቸዋል” ብለዋል - ሥራ አስኪያጁ፡፡

በስብሰባው ላይ የአመራር ብቃት የለዎትም፤ ቦታውን ይልቀቁ በሚል ከጋዜጠኞች ቅሬታ ስለመቅረቡ አቶ ሰብስቤን ጠይቀናቸው፤ “እኔ ስብሰባ ላይ እንዲህ የሚባል ትችት አልቀረበብኝም” ያሉት አቶ ሰብስቤ፤ እርግጥ በስነ-ምግባርም ሆነ በእውቀት ብቃት የሌለው አንድ ጋዜጠኛ “ቦታውን ልቀቅ” ብሎ በግል ተናግሮኛል፤ ጋዜጠኛው አሁን ስራ ለቋል” ብለዋል፡፡ ብዙ ጋዜጠኞች ከድርጅቱ ይለቃሉ ስለሚባለው አንስተንባቸው በሰጡት ምላሽ፤ “ከጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ ጋዜጠኞች ይለቃሉ፣ የተሻለ ደሞዝ ሲያገኙ የትኛውም መ/ቤት እንደሚልቁት ሁሉ እዚህም ይለቃሉ፤ በዚያው ልክ እኛም እንቀጥራለን” ብለዋል፡፡ ሰራተኞቹ፤ የመልካም አስተዳደር ችግሩ በአስቸኳይ ካልተቀረፈ፣ እንደአቻ ድርጅት ማግኘት የሚገባንን የደሞዝ እድገት ካላገኘንና አድሎአዊ አሰራር ካልቀረ ድርጅቱን ለመልቀቅ እንገደዳለን ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ በበኩላቸው፤ በድርጅቱ ውስጥ መሻሻሎችን ለመፍጠርና ወደ ኮርፖሬት አደረጃጀት ለመቀየር ስራዎች ተሰርተው በመጠናቀቅ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

              የአፍሪካ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ መንግስት በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን እንዲፈታና በቅርቡ አገራቸውን ጥለው የተሰደዱ ጋዜጠኞችም፣ ወደ አገር ቤት ተመልሰው ስራቸውን የሚቀጥሉበትን ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥር ጠየቀ፡፡ አለማቀፉ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን ባለፈው ረቡዕ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በኢትዮጵያ የሚታየው የፕሬስ ነጻነት ጥሰት፣ የጋዜጠኞች እስርና ስደት ያሳስበኛል ብሏል፡፡ “በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነትን የሚጥሱ ተግባራት መከናወናቸው መቀጠሉ እንዲሁም የሚታሰሩና አገር ጥለው የሚሰደዱ ጋዜጠኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ያሳስበናል” ያሉት የአፍሪካ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ጋርባ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከመገኛኛ ብዙሃን ጋር ሃቀኛ ውይይትና ምክክር በማድረግ፣ ራሳቸውን ተቆጣጥረው በአግባቡ እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታዎችን እንዲፈጥር ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡በኢትዮጵያ ብሄራዊ ጋዜጠኞች ህብረትና በምስራቅ አፍሪካ የጋዜጠኞች ማህበር አዘጋጅነት በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው የምርመራ ጋዜጠኝነት አውደ-ጥናት ላይ የተሳተፈውና ከምስራቅ አፍሪካ የጋዜጠኞች ማህበርና ከአለማቀፉ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን የተወከሉ 3 አባላት ያሉት የልኡካን ቡድን፣ ከመንግስት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መምከሩንም የፌዴሬሽኑ መግለጫ አስታውሷል፡፡

ከአካባቢው አገራት በበለጠ ሁኔታ ጋዜጠኞች የሚታሰሩትና የሚሰደዱት በኢትዮጵያና በኤርትራ እንደሆነ ለሚኒስትሩ የገለጹት የልኡካን ቡድኑ አባላት፣ የኢትዮጵያ መንግስት በእስር ላይ የሚገኙትን ሁሉንም ጋዜጠኞች እንዲፈታና በስደት የሚገኙትም ወደአገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ እንዲያመቻች መጠየቃቸውን ጠቁሟል፡፡ አቶ ሬድዋን በበኩላቸው ለልኡካን ቡድኑ በሰጡት ምላሽ፣ በቅርቡ አገር ጥለው የተሰደዱት ጋዜጠኞች ክስ እንዳልተመሰረተባቸውና ከአገር የሚያስወጣቸው ምክንያት እንደሌለ ፤ የአገሪቱ መንግስትም ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን ለማስከበር ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ መናገራቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡ የአፍሪካ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን በ40 የአህጉሪቱ አገራት ውስጥ የሚገኙ ከ50ሺህ በላይ ጋዜጠኞችን እንደሚወክል፣ አለማቀፉ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

      ሆቴሉ የብድርና የኮንትራት ማናጅመንት ስምምነቶችን ነገ ይፈራረማል

ግንባታው ከ18 ወራት በኋላ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል የተባለው የአለማቀፉ ኢንተርኮንቲኔንታል ግሩፕስ አካል የሆነው “ክራውን ፕላዛ ሆቴል”፤ በአዲስ አበባ በአገልግሎት ላይ ከሚገኘው “ክራውን ሆቴል” የስያሜ ኮፒ ራይት መብት ጥያቄ ቀርቦበት ፍ/ቤት የንግድ ስያሜ እግድ አስተላልፎበታል፡፡ “ክራውን” የሚለው ስያሜ በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ፅ/ቤት የተመዘገበና በስራ ላይ የሚገኝ እንደሆነ የጠቆመው “ክራውን ሆቴል”፤ ስያሜው ለሌላ አካል መሰጠቱ ተገቢ አይደለም ሲሉ ለፍ/ቤቱ ይግባኝ ብሏል፡፡ “ክራውን ሆቴል” የሚለው የንግድ ምልክት በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ፅ/ቤት ተመዝግቦ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከ20 አመታት በላይ አስቆጥሯል የሚለው ለይግባኝ ሰሚ ፍ/ብሔር ችሎት የቀረበው የሆቴሉ ማመልከቻ፤ ውሳኔው “ክራውን ሆቴል” በሁለት አስርት ዓመታት ያገኘውን ስምና ዝና እንዲሁም ገበያውን አዲሱ ሆቴል እንዲሻማበት የሚያደርግ ነው ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት “ክራውን ሆቴልን” ሳያማክር ሚያዚያ 28 ቀን 2006 ዓ.ም የዓለም አቀፍ ኢንተርኮንቲኔንታል ፕሩፕስ አካል ሆነው ሆቴል “ክራውን ፕላዛ” የሚለውን ስያሜ መፍቀዱ አግባብ አይደለም ሲል ይግባኝ የጠየቀው ክራውን ሆቴል፤ ፍ/ቤቱ አዕምሯዊ ንብረት ፅ/ቤት የሰጠው ውሳኔ የይግባኝ ባይን በንግድ ምልክቱ የመጠቀም ህጋዊ መብት በእጅጉ የጎዳ መሆኑን ፍ/ቤቱ ተገንዝቦ የፅ/ቤቱን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ በመሻር ስሙ በድጋሚ የተሰጠው ሆቴል “ክራውን ፕላዛ” በሚለው የንግድ ምልክት መጠቀም አይችልም የሚል ውሳኔ እንዲሰጥለት በሰኔ 23 ቀን 2006 ዓ.ም ለፍ/ቤቱ በፅሁፍ አመልክቶ ነበር፡፡ ፍ/ቤቱም መስከረም 7 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት፤ ይግባኝ ባይ መስከረም 5 ቀን 2007 ዓ.ም በቃለ መሃላ በተደገፈ አቤቱታ እግድ መጠየቃቸውን አስታውቆ በሰጠው ትዕዛዝ፤ ሌላ ተለዋጭ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ፅ/ቤት የሰጠው ውሳኔ አፈፃፀም ታግዷል ብሏል፡፡

የይግባኝ ቅሬታውን ለመስማትም ለጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ፅ/ቤት የንግድ ምልክትና ኢንስፔክሽን ዋና የስራ ሂደት ጊዜያዊ ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ፅጉ፤ የፍ/ቤቱ እግድ ትዕዛዝ እንደደረሳቸው አረጋግጠው፣ ጉዳዩ በፍ/ቤት የተያዘ በመሆኑ ምንም አይነት አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ፣ ነገር ግን ጽ/ቤታቸው የፍ/ቤቱን እግድ እንደሚያስከብር ገልፀዋል፡፡ አለማቀፍ የሆኑ የሆቴልም ሆነ ሌሎች ኩባንያዎች ስያሜና የንግድ አርማ የሃገራችን ኩባንያዎች በምን አግባብ ነው እንዲጠቀሙ የሚደረገው ስንል የጠየቅናቸው ዳይሬክተሩ፤ “ባለ ኩባንያው የንግድ ምልክቱን ያስመዘግባል፤ በንግድ ምልክቱ ዙሪያም ተቃዋሚ ካለ እንዲቀርብ የጋዜጣ ማስታወቂያ ይወጣል፤ ካልቀረበና በምርመራ ከተረጋገጠ ይሰጠዋል፤ በዚህ መንገድ ነው የሚስተናገደው” ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል የስትራክቸር ግንባታ ስራው ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁ የተገለጸው “ክራውን ፕላዛ ሆቴል”ን የሚያስገነባው ፀሜክስ ሆቴሎችና ቢዝነስ ኃ/የተ/የግ ማህበር ከአለም ባንክ ጋር የ19 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት የሚፈራረም ሲሆን በፀሜክስ እና በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ግሩፕ መካከል ደግሞ የሆቴል ማናጅመንት ኮንትራት ውል ስምምነት በነገው ዕለት ይፈራረማል ተብሏል፡፡

                  የ4.5ቢ. ዶላር ድጋፍ አድርገዋል የኩዌት አሚር የተከበሩ ሼክ ሳባህ አል-አህመድ አል-አልጃበር አል-ሳባህ ሃይማኖትና ጎሳ ሳይለዩ ለዓለም ህዝብ ባደረጉት የተለያዩ ድጋፎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ)፣ “የሰብአዊ በጎ አድራጎት ስራዎች መሪ” በማለት እንደሸለማቸው የኩዌት አምባሳደር አስታወቁ፡፡ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ህብረትና በዩጋንዳ የኩዌት አምባሳደር ሺድ አልሃጅሪ፣ በጽ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ አሚሩ ሊሸለሙ የቻሉት፣ ባላቸው መልካም አመለካከትና ቅን አስተሳሰብ የህዝቦችን ህይወት ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስና በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ያሉ ህዝቦችን ለመርዳት ያደረጉትን ሰብአዊ ስራ ለማጉላትና እውቅና ለመስጠት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሚሩ ያደረጉት ሰብአዊ ድጋፍ 4.5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አምባሳደሩ ጠቅሰው፣ 2.5 ቢሊዮን ዶላሩ የአፍሪካ ድርሻ ነው ብለዋል፡፡ ጥቃቅንና መካከለኛ ቢዝነሶች ለመደገፍና ለማበረታታት 500 ሚሊዮን ዶላር፣ ምስራቃዊ ሱዳንን እንደገና ለመገንባት 100 ሚሊዮን ዶላር፣ ለፍልስጤም ስደተኞች ድጋፍ 34 ሚሊዮን ዶላር፣ ለአፍሪካ ህብረት የጤና ክሊኒክ ማስፋፊያ 5 ሚሊዮን ዶላር፣ በአፍሪካ ለሚደረጉ የልማት ፕሮጀክቶች 1 ቢሊዮን ዶላር፣ በአፍሪካ ለሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች 1 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን በአጠቃላይ ለ13 የሰብአዊ በጎ አገልግሎት ሥራዎች 4.5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ መስጠታቸው ታውቋል፡፡ ስለኢትዮጵያና ኩዌት ግንኙነት የተጠየቁት አምባሳደሩ፤ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ረዥም ዘመን ያስቆጠረ መሆኑን ጠቅሰው፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ ግንኙነቱን ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዳደረሱት በማስታወስ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ ግንኙነቱ እንዲቀጥል ባደረጉት ጥረት፣ ሁለቱ አገራት 14 የሁለትዮሽ ስምምነቶች መፈራረማቸውን ገልፀዋል፡፡ በኩዌት ባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን በተመለከተ መንግስታቸው ምን እርምጃ እንደወሰደ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ “ኩዌት በህግ ተቋም የምትተዳደር አገር ስለሆነች፣ ፖሊስና ፍርድ ቤቶች ህጉን ለማስከበር በከፍተኛ ሁኔታ ይሰራሉ፤ የኩዌት ህግ ለማንም አያደላም፤ የአገሩም ሆነ የውጭ ዜጎች እኩል ነው የሚዳኙት፡፡” ብለዋል አምባሳደር ራሺድ አልዛድሪ፡፡ በኩዌት 80ሺ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡

             ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት ከኒውዮርክ አፍሪካን ሬስቶራንት ዊክ ጋር በመተባበር ባወጣው በኒውዮርክ ሲቲ የሚገኙ ምርጥ አስር የአፍሪካውያን ሬስቶራንቶች ዝርዝር ውስጥ፣ የኢትዮጵያውያኑ ሬስቶራንቶች ‘ንግስተ ሳባ’ እና ‘ባቲ’ ተካተቱ፡፡ በኒውዮርክ ሲቲ የአፍሪካውያን ምግቦችን በማቅረብ ከሚታወቁት ከ50 በላይ ሬስቶራንቶች መካከል፣ በሚያዘጋጇቸው ምግቦች ጣዕም፣ በመስተንግዶ፣ በውስጣዊ ድባብና ዘላቂነት በሚሉ መስፈርቶች ከተመረጡት 10 ሬስቶራንቶች መካከል የኤርትራውያኑ ‘ምጽዋ’ም ይገኝበታል፡፡

ከታዋቂው ታይምስ አደባባይ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውና በሼፍ ፊሊጶስ መንግስቱ ባለቤትነትና አስተዳዳሪነት የሚመራው ንግስተ ሳባ፣ የኢትዮጵያውያንን ባህላዊ ምግቦች እያጣጣሙ ከወዳጅ ዘመድ ጓደኛ ጋር ለመጨዋወት ተመራጭ ቦታ እንደሆነ የገለጸው ፎርብስ፤ የሚያቀርበው ጣፋጭ ኬክም ልዩ መገለጫው እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ በባህላዊ የቤት ማስጌጫዎች የተዋበው ይሄው የኢትዮጵያውያን ሬስቶራንት፤ በተለያዩ የአሜሪካ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ የዘገባ ሽፋን እንዳገነ ፎርብስ አስታውሷል፡፡ በአዲስ አበባ በተወለደችው ህብስት ለገሰ ባለቤትነት የሚንቀሳቀሰው ባቲም፣ ጣፋጭ የኢትዮጵያውያን ምግቦችን በአስደናቂ መስተንግዶ ለደንበኞቹ በማቅረብ እንደሚታወቅ ፎርብስ ገልጿል፡፡ የሴኔጋሎቹ “ፖንቲ ቢስትሮ”፣ “ካፌ ሪዮ ዲክስ” እና “ሌኖክስ ሳፋየር”፣ የደቡብ አፍሪካዎቹ “ማዲባ” እና “ቶላኒ ኢተሪ ኤንድ ዋይን”፣ የናይጀሪያው “ቡካ” እንዲሁም የአይቬሪኮስቱ “ፋራፊና ካፌና ላውንጅ”ም፣ በኒውዮርክ ሲቲ ምርጥ 10 የአፍሪካውያን ሬስቶራንቶች ዝርዝር እንደተካተቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአዲስ አበባና በአምስት ክልሎች ባቋቋሟቸው የፌስቱላ ሆስፒታልና የህክምና ማዕከላት ከ40ሺህ በላይ ለሚሆኑ ታማሚዎች የህክምና እርዳታ በመስጠት የሚታወቁት የዶ/ር ካትሪን ሃምሊን 90ኛ ዓመት የልደት በዓል፣ ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ ሪትዝካርልተን ይከበራል፡፡ የፕሮግራሙን አዘጋጆች በመጥቀስ ታዲያስ መጽሄት ከኒውዮርክ እንደዘገበው፣ ዶ/ር ሃሚሊን በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ልዩ መልዕክት እንደሚያስተላልፉና በወሊድ ምክንያት የሚፈጠሩ የጤና ችግሮችን ለማጥፋት ርብርብ እንዲደረግ ያስተላለፉትን ጥሪ ተቀብለው የራሳቸውን ድጋፍ ለማድረግ የሚፈልጉ በርካታ ታዋቂ ግለሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ዝግጅቱን እንደሚታደሙ ይጠበቃል፡፡ የዶ/ር ሃምሊን የ90ኛ አመት የልደት በዓል፣ የተከበሩ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬን ጨምሮ ከአገር ውስጥና ከሌሎች የአለም አገራት የተጋበዙ እንግዶች በተገኙበት ባለፈው ጥር ወር በአዲስ አበባ መከበሩን የጠቆመው ዘገባው፤ ዶ/ር ሃምሊን ፌስቱላን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ላለፉት 55 አመታት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሷል፡፡ በአዲስ አበባና በክልሎች የፌስቱላ ሆስፒታልና የህክምና መስጫ ማዕከላትን በማቋቋም በአገሪቱ ከፍተኛ የጤና ችግር ሆኖ የቆየውንና ተገቢ ህክምና ያልነበረውን ፌስቱላን ለማጥፋት ይዘው ለተነሱት ታላቅ ራዕይ መሳካት እገዛ የሚያደርገውን የአዋላጅ ነርሶች ኮሌጅ ለማቋቋም ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ተጠቃሽ ሰው መሆናቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡ ፌስቱላ በአፍሪካ ከአስራ ሁለት ሴቶች በአንዷ ላይ የሚከሰት አሳሳቢ የጤና ችግር እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

Monday, 22 September 2014 14:20

ሃይማኖት አለሙ አረፈ

          ታዋቂው ተዋናይና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ሃይማኖት አለሙ፣ ባደረበት ህመም ህክምና ሲከታተል ቆይቶ በትናንትናው ዕለት አረፈ፡፡በአዲስ አበባ ከተማ የተወለደውና በሆለታ ያደገው ሃይማኖት አለሙ፤ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የተከታተለ ሲሆን፣ በሚኒሶታ ዩኒቨርሲቲ በትወና ጥበብ በከፍተኛ ማዕረግ በመመረቅ የመጀመሪያ ዲግሪውን እንዲሁም በስነጥበባት ሁለተኛ ዲግሪውን ተቀብሏል፡፡ለረጅም አመታት በአሜሪካ የኖረውና በበርካታ ቲያትሮችና ፊልሞች ላይ በተዋናይነት በመስራት የሚታወቀው ሃይማኖት፣ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ፣ አስታር አድቨርታይዚንግ በተባለው አለም አቀፍ የማስታወቂያና የኮሙኒኬሽን ተቋም ዋና ጸሃፊ ሆኖ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና በራክማኖቭ ኮሌጅ የትወና ጥበብ ያስተማረው ሃይማኖት፤ በብሔራዊ ትያትር በስራ አስኪያጅነት ያገለገለ ሲሆን በዚሁ ትያትር ቤት በበርካታ ትያትሮች ላይ ተውኗል፡፡ የትወና ብቃቱን ካሳየባቸው ትያትሮች መካከል የታዋቂው ባለቅኔና ፀሐፌ ተውኔት ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን “እናት ዓለም ጠኑ” እና “ሀሁ በስድስት ወር” ተጠቃሽ ሲሆኑ “ቴዎድሮስ” በተሰኘው ትያትር ላይ በመተወንም ይታወቃል፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ሃይማኖት የሼክሰፒርን “ሃምሌት” የተሰኘ ትያትርም አዘጋጅቷል፡፡

       በዶ/ር አቡሽ አያሌው የተዘጋጁት “አልፋና ኦሜጋ” ቁጥር 2 እና ቁጥር 3 መጽሐፎች ሰሞኑን ለንባብ በቁ፡፡ አዘጋጁ በ“አልፋና ኦሜጋ ቁጥር 1” መጽሐፍ፤ ስለ ሰዎችና ዩኒቨርስ የመጀመሪያና የመጨረሻ ምስጢራት ሰፊ ትንታኔ በመስጠት የጀመሩትን ሃሳብ በቁጥር ሁለትና በቁጥር ሶስት መጽሐፋቸው በስፋት እንዲቃኙት ለማወቅ ተችሏል፡፡ “አልፋና ኦሜጋ” ቁጥር ሁለት፤ ስለ እኛና ስለ ዩኒቨርስ የመጀመሪያና መጨረሻ ምስጢራት አልበርት አንስታይንና ስቴፈን ሐውኪንግ ደርሰውበታል ስለተባለው እውነት፣ ስለ 666 አስገራሚ የዩኒቨርስ ቁጥርነት፣ በድንገት ፈነዳ ስለተባለው መንፈሳዊ እሳት፣ በመንፈሳዊ ሃይል ስለተሞላው ጨለማ፣ በአስገምጋሚው እሳት ውስጥ ተፈጠረ ስለተባለው ሰማይና ምድር እንዲሁም የአልበርት አንስታይንን መሳጭ የህይወት ታሪክ ያካተተ ሲሆን በ125 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ “አልፋና ኦሜጋ” ቁጥር ሶስት መጽሐፍ ደግሞ በተለይ ከሞት በኋላ ህይወትና የፈጣሪ መኖር በኳንተም ፊዚክስ ስለመረጋገጡ፣ በነፍስ ላይ ስለተካሄዱ ልዩ ልዩ ሳይንሳዊ ጥናቶች፣ የፈጣሪን ህልውና በማያዳግም መልኩ ስላረጋገጡ 15 ትልልቅ ፍልስፍናዎች፣ በፈጣሪ መኖር ስለሚያምኑ የዓለማችን 13 ምርጥ ሳይንቲስቶች እንዲሁም ስለ ገነት፣ ገሃነም፣ መላዕክት፣ ዲያቢሎስና ፈጣሪ፤ ሳይንስ የደረሰበትን እውነታ ያስቃኛል ተብሏል፡፡ በ224 ገፆች የተቀነበበው መፅሃፉ፤ በ100 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ

ባለፈው ዓመት የያዝናቸውን የስራ እቅዶች ከሞላ ጐደል ማከናወን ችለናል፡፡ ለአዲሱ አመት የተላለፉም አሉ፡፡
በአጠቃላይ 2006 መጥፎ አመት አልነበረም፤ ጥሩ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡
በአዲሱ ዓመት ሁሉም ሰው ሃላፊነት እንዲወስድ እጠይቃለሁ፡፡ ሃላፊነትን መውሰድና መወጣት ቀላል ነገር
ይመስላል እንጂ ከባድ ነው፡፡ ለምሣሌ ስለ መኪና አደጋ ችግር ሲነሳ ጥፋቱ ሁሌም በአንድ ወገን (ሹፌሩ) ላይ
ብቻ ነው የሚደመደመው፡፡ ሃላፊነቱ ለአንድ ወገን ብቻ እየተሰጠ ስለሆነ በዚህ ረገድ ውጤታማ መሆን
አልተቻለም፡፡ ነገር ግን መንገደኛው (እግረኛው)፣ የእንስሳት መንገድ አጠቃቀም፣ የመኪናው ቴክኒካዊ ብቃት
የመሳሰሉትን ሁሉ የሚመለከት ነው፡፡ መንግስትም ሃላፊነቱን እኔ ብቻ እወስዳለሁ ሣይል ወደ ህብረተሰቡም
ማውረድ አለበት፡፡ ያ ካልሆነ የምንመኘው ነገር ውጤታማ ላይሆን ይችላል፡፡
2006 ዓ.ም እውነቱን ለመናገር ለስፖርቱ ጥሩ አልነበረም፤ በአትሌቲክስም ሆነ በእግር ኳሱ፡፡ በዚህ ዘርፍም
ለውጥ እንዲመጣ ሁሉም የየራሱን ሃላፊነት ወስዶ ግዴታውን በሚገባ መወጣት አለበት፡፡ አዲሱ ዓመት
የእድገትና የብልፅግና እንዲሆን መልካም ምኞቴ ነው፡፡

አሜሪካ 300 ወታደሮች ወደ ላይቤሪያ ልትልክ ነው

እንግሊዛዊቷ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ሩት አትኪንስ ሰሞኑን በኦክስፎርድ ለ60 በጎ ፍቃደኞች ሊሰጥ የታቀደውን
የኢቦላ ቫይረስ የሙከራ ክትባት በመውሰድ የመጀመሪያዋ በጎ ፈቃደኛ እንደሆነች መሆኗን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የሙከራ ክትባቱን የሚወስዱ በጎ ፈቃደኞች እንደሚፈለጉ በቢቢሲ ሬዲዮ መስማቷን የገለፀችው አትኪንስ፣
በምዕራብ አፍሪካ ሁኔታው በጣም አሳዛኝ ስለሆነና የዚህ ክትባት ሂደት አካል መሆን ትልቅ ውጤት ለማምጣት
በሚደረገው ጥረት ማበርከት የምችለው ትንሹ ነገር እንደሆነ በማሰብ፣ ክትባቱን በበጎፈቃደኝነት ለመውሰድ
ወስኛለሁ” ብላለች፡፡
ክትባቱ ከኢቦላ ቫይረስ ትንሽ የዘረመል ንጥረ ነገር ብቻ የያዘ በመሆኑ ተከታቢው በበሽታው እንደማይያዝ
የተገለፀ ሲሆን በኦክስፎርድ የጄነር ኢኒስቲቲዩት ዳይሬክተርና የሙከራ ክትባቱ መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አድርያን
ሂልም፤ “ይሄ ክትባት ማንንም ኢቦላ ያስይዛል የሚል ቅንጣት ስጋት የለም” ብለዋል፡፡
ክትባቱን ለመወጋት ስታስብ የደህንነቷ ጉዳይ እንዳላስጨነቃት የተናገረችው ሚስ አትኪንስ፤ የ15 ዓመት ታዳጊ
ልጇ የኢቦላ ቫይረስ ተሰጥቷት የምትሞት መስሎት እንደነበርና እንዳረጋጋችውም ገልፃለች፡፡
ብዙ ጊዜ አዲስ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ ከማግኘቱ በፊት ለዓመታት በሰዎች ላይ ሙከራ ሲደረግ
ይቆይ ነበር ያለው ቢቢሲ፤ በምዕራብ አፍሪካ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ አጣዳፊነት ግን ይሄ የሙከራ ክትባት
በአስደናቂ ፍጥነት ጥቅም ላይ እንዲውል ጥረቱ እንዲጠናከር አድርጓል ብሏል፡፡
በሰዎች ላይ የሚደረገው ሙከራ ውጤታማ ሆኖ ከተገኘ፣ ክትባቱ በፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ላይ በቫይረሱ
በተጠቁ አካባቢዎች የሚገኙ የጤና ሰራተኞችን ከበሽታው ለመከላከል ጥቅም ላይ እንደሚውል ታውቋል፡፡
ያን ጊዜ ግን ለ10ሺ ሰዎች ያህል የሚሆን ክትባት እንደሚያስፈልግ የተገለፀ ሲሆን በምዕራብ አፍሪካ ክፉኛ
የተጠቁ አካባቢዎች ላይ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችን ከቫይረሱ ለመከላከል ጥቅም ላይ ይውላል ተብሏል፡፡
ክትባቱ እየተሰራ የሚገኘው ግላክሶስሚዝክላይን በተባለ ኩባንያና በአሜሪካ ብሔራዊ የጤና ተቋም ሲሆን፣
የእንግሊዝ ዓለምአቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ የምርምር ተቋማት ለሙከራ ክትባቱ የገንዘብ
ድጋፍ እንዳደረጉ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የኢቦላ ቫይረስን ለመከላከል እገዛ የሚያደርጉ 3ሺ ወታደሮችን
ወደ ላይቤሪያ የመላክ ዕቅድ እንዳላቸው ባለፈው ማክሰኞ አስታወቁ፡፡ ኦባማ ይሄን ያስታወቁት የላይቤሪያዋ
ፕሬዚዳንት አለን ጆንሰን ሰርሊፍ በሽታውን ለመከላከል እገዛ ያደርጉላቸው ዘንድ ለኦባማ በቀጥታ ያቀረቡትን
ጥያቄ ተከትሎ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የአሜሪካ ወታደራዊ ሃይል የህክምና ማዕከሎችን ግንባታ በመቆጣጠርና የጤና ሰራተኞችን በማሰልጠን
ለላይቤሪያ መንግስት እገዛ እንደሚያደርግ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በምዕራብ አፍሪካ ለተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ፈጣን ያልሆነ ምላሽ ትችት ሲሰነዘርበት
፣ቆየቱ ይታወቃል፡፡
በበሽታው ክፉኛ የተጠቁት የምዕራብ አፍሪካ አገራት ሴራሊዮን፣ ላይቤሪያና ጊኒ ሲሆኑ ወረርሽኙ ከ2400 በላይ
ሰዎችን ለህልፈት እንደዳረገ ተጠቁሟል፡፡ ከእዚህ የሞት አደጋ ውስጥ ግማሹ የተከሰተው በላይቤሪያ ነው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት፤ አገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎችን በቫይረሱ ልታጣ እንደምትችል በቅርቡ
አስጠንቅቋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኃላፊዎች፣ በጄኔቫ በሚያካሂዱት ስብሰባ ለወረርሽኙ
በተሰጠው ዓለም አቀፍ ምላሽ ላይ እንደሚወያዩ ቢቢሲ ጠቁሟል፡፡
የጋና ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ባለፈው ሰኞ ወረርሽኙን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤
“በምዕራብ አፍሪካ ለተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ከፍተኛና ፈጣን የውጭ እርዳታ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡