Administrator

Administrator

Saturday, 24 June 2017 11:25

ቆቅ ሆነን

እየው ኖርን ሳንዋደድ፣ እድሜም ገፋ እንደ ዘበት፣
ለሰው ይምሰል ጥላችንም፣ እንደፍቅር ተወራለት፡፡
ባንድ ማድ፣ እየበላን እየጠጣን፣
ለሚያየን አስጎምጅተን፣ እያስቀናን፤
አለን ሳንተኛ፣ ሳናንቀላፋ፣
እኛው በኛ፣ ስንጋፋ፡፡
ቆቅ ሆነን፣ ስንጠባበቅ፣
ደግሞ- የዋህ መስለን ስንሳሳቅ፤
ብዙ…. ብዙ! ዘመን፣ ተቆጠረ፣
ቂም ሳይፈታ፣ እንደከረረ!፡፡
      ጋሻው ሙሉ

Saturday, 24 June 2017 11:23

እግዜር ግንበኛ ነው

የናንተን አላውቅም፣ እኔ ግን እላለሁ
እውነቱን ለእግዚአብሔር፣ እመሰክራለሁ፡፡
ጥሩ! አድርጎ እሚያንጽ፣ እግዜር ግንበኛ ነው
ያለ ጭስ ፋብሪካ፣ ሰውን ገጣጠመው፡፡

     በአምስት የስነ ልቦና ምሩቃን ከአንድ አመት በፊት የተቋቋመው ‹‹አብርሆት›› የስነ-ልቦና አገልግሎት ማዕከል በሳለፍነው ሳምንት በይፋ ተመርቆ ስራ ጀመረ፡፡ ማዕከሉ አራት ክፍሎች ያሉት ሲሆን እነዚህም የህፃናትና የወጣቶች የአዕምሮ ህመምና የጋብቻ፣ የሚዲያ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የስልጠና እና በአደጋ ምክንያት ሰዎች የንግግር ክህሎታቸውን ሲያጡ የሚታከሙበት የንግግር ህክምና ዲፓርትመንቶች እንደሆኑ ታውቋል። በተለይ የህፃናትና የታዳጊዎች ዲፓርትመንት የአዕምሮ እድገትና የንግግር መዘግየትን ጨምሮ ሌሎች እክሎችን ምርመራና ምዘና በማድረግ ህክምና ይሰጣል ተብሏል፡፡ የስነ-ልቦና ጉዳይ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት፣ የስነ ልቦና መንስኤዎችና ወሳኝ መፍትሄዎች ደግሞ በጥናትና ምርምር ክፍሉ ይከናወናል ተብሏል፡፡
ስልጠናን በተመለከተ ማዕከሉ ለተቋማት፣ ለግለሰቦችና በተለይ የስነ-ልቦናና የአዕምሮ ችግር በቤተሰባቸው ውስጥ ላለ ወላጆችና አሳዳጊዎች በየደረጃው እንደሚሰጥም ከማዕከሉ መስራቾች አንዱ የሆኑት አቶ ሄኖክ ኃይሉ ገልፀዋል፡፡ ከሱስ፣ ከአዕምሮ ህመምና ከተያያዥ ችግሮች ጋር ያሉ ህሙማን ተኝተው መታከምና ማገገም የሚያስፈልጋቸው ከሆነም ለ“ቤዛ” እና “ስጦታ” ከተባሉ የስነ- አዕምሮ ህክምና ማዕከላት ጋር ማዕከሉ ባደረገው ስምምነት የሚታከሙበት ሁኔታ መመቻቸቱም ተገልጿል፡፡
ከሙያው ጋር ለ30 ዓመት እንደሚተዋወቁ የገለፁት ረዳት ፕሮፌሰር ፍሬው ከፍያለው፤ ወጣቶቹ ማዕከሉን ለማቋቋም ከፈቃድ ማውጣት ጀምሮ የገጠማቸው ውጣ ውረድ አልፈው ለዚህ መብቃታቸውን አድንቀው፤ በስራቸው ታማኝና ጠንካራ ሆነው ህዝብን በሀቅ እንደሚያገለግሉ እመተማመናለሁ ያሉ ሲሆን ወደፊትም በሚችሉት መጠን ማዕከሉንና ወጣቶቹን ለመደገፍ ቃል ገብተዋል፡፡ ‹‹አገራችን ላይ ሙያ ተሸጦ የሚተረፍበት ደረጃ ላይ አልተደረሰም›› ያሉት መስራቾቹ፤ “እኛም ሙያ ሸጠን ለማትረፍ ሳይሆን በዘርፉ ያለውን ከፍተኛ ክፍተት በአቅማችን ለመሙላት በጣም መጠነኛ በሆነ ክፍያ አገልግሎቱን ለመስጠት ማዕከሉን አቋቁመናል” ብለዋል፡፡

   በደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ ማንሳት ስራ ላይ ተሰማርቶ የቆየው ሮዝ ቢዝነስ ግሩፕ በሀገር ውስጥ ያመረታቸውን ባለ ሶስት እግር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለገበያ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው የጃፓን ቴክኖሎጂን የታጠቁ፣ ባትሪያቸውን በኤሌክትሪክ በመሙላት ብቻ የሚጓጓዙ፣ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎችን ደብረ ዘይት አካባቢ በገነባው ፋብሪካው ማምረቱን የኩባንያው ባለቤት አቶ ሮቤል እስጢፋኖስ አስታውቀዋል፡፡
ፋብሪካውን ከአንድ ዓመት በፊት መገንባት እንደጀመሩ የጠቆሙት አቶ ሮቤል፤በአሁኑ ወቅት በአንድ ሰዓት አንድ የኤሌክትሪክ ባለ ሶስት እግር መኪና ማምረት እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ለ4 ሰዓት በተሞላ ባትሪ መቶ ኪሎ ሜትር ድረስ መንዳት ያስችላል ያሉት ባለቤቱ፤ ኤሌክትሪክ ለመሙላትም 7 ብር ብቻ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡
ተሽከርካሪው በዋናነት ከከተማ ውጪ ላሉ አካባቢዎች የሚያገለግል ሲሆን ለሰፋፊ ግቢ የውስጥ ለውስጥ እንቅስቃሴ፣ ለሽርሽር እንዲሁም ለተለያየ ዓይነት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚውል ነው ተብሏል፡፡ ሹፌሩን ጨምሮም 7 ሰዎች የመያዝ አቅም አለው፡፡
ኩባንያው ተሽከርካሪውን ከኢትዮጵያ አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ ገበያ ለማቅረብ ማቀዱንም ባለቤቱ ባለፈው ሰኞ፣ በተሽከርካሪው የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ ተናግረዋል፡፡
የኩባንያው መነሻ ካፒታል 24.9 ሚሊዮን ብር መሆኑንና ለ105 ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩን የጠቀሱት አቶ ሮቤል፤የተሽከርካሪውን ዋጋ በተመለከተ ገዥዎች ሲመጡ ብቻ ቢያውቁት ይሻላል በሚል ከመግለፅ ተቆጥበዋል፡፡   

 በስራ ፈጠራ፣ አዲስ ቴክኖሎጂ በመፍጠርና በመቅዳት የተለያየ ውጤታማ ደረጃ ላይ የደረሱ ስኬታማ ሰዎች ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት “የአሸናፊነት ጉዞ ወደ ስራ ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ መቅዳት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂ ማፍለቅና ኢንተርፕረነርሺፕ” የተሰኘ የኮሌጅ ቶክ ሾው ሊጀመር ነው፡፡ ቶክ ሾውን የሚያቀርበው ኤዲቲ የንግድ ፕሮሞሽን አገልግሎት ሲሆን ይህ ቶክ ሾው የሚካሄደው ከሰኔ 2009 እስከ ሰኔ 2010 ለአንድ ዓመት እንደሆነ አዘጋጁ ገልጻል፡፡
ኮሌጅ ቶክ ሾው ዝግጅቱ በአዲስ አበባ በሚገኙ 13 የመንግስትና የግል ቴክኒክና ሞያ ኮሌጆች እንደሚካሄድም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዋና አላማው በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ኮሌጆች በተለያዩ ደረጃዎች የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ተመርቀው ሲወጡ ቴክኖሎጂን በመቅዳት፣ አዲስ በመፍጠርና በመመራመር የራሳቸውን ስራ ውጤማ ሆነው እንዲሰሩ፣ የሚገጥማቸውን ችግሮች በምን መልኩ ማለፍ እንዳለባቸውና በአጠቃላይ ውጤታማነት ዙሪያ ልምድ ካላቸው ሰዎች ልምድ እንዲቀስሙ ማድረግ ነው ተብሏል፡፡

     ከሁለት ዓመታት በፊት ተከፍቶ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ጌትፋም ኢንተርናሽናል ሆቴል ባለ 5 ኮከብ ደረጃን አገኘ፡፡ ሁኔታውን አስመልክቶ ሰሞኑን በሆቴሉ በተካሄደው ሥነ ስርዓት ላይ እንደተገለፀው፤ ሆቴሉ ዓለም አቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለደንበኞቹ ሲሰጥ ቆይቶ በቅርቡ በተካሄደ ፍተሻና ቁጥጥር መስፈርቱን አሟልቶ የተገኘ በመሆኑ ባለ 5 ኮከብ ደረጃ ተሰጥቶታል፡፡ የሆቴሉ ባለቤት አቶ ጌታሁን በሻህ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ሆቴሉ አሁን ላለበት ደረጃ እንዲበቃ ቤተሰቦቻቸውና መላው ሠራተኞች የከፈሉት መስዋዕትነት ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ ሆቴሉ ባለ 5 ኮከብ ደረጃ ያለው መሆኑ ለእሳቸውም ሆነ ለሆቴሉ ሠራተኞች ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረላቸው ጠቅሰው፤ በቀጣይም ደንበኞቻቸውን በጥራትና በብቃት ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

 የሚከተለውን የፃፉልን እጓለ ገብረ ዮሐንስ ናቸው፡፡
“የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ነው፡፡
 በግሪክ ሜቶሎጂ የሚገኝ አንድ ትልቅ ተረት አለ፡፡
(ይህም ስለ ፕሮሚሴቭስ የሚነገረው ነው፡፡ ትልቅ ምሥጢር በውስጡ ደብቆአል፡፡ ፕሮሚሴቭስ በሚል አርእስት የቀድሞውን ተረት መሠረት በማድረግ፣ ኤስሂሎስ የሚባለው ትራጀዲን የፈጠረ ባለቅኔ፣ አንድ ትሪሎጂ - ማለት ሦስት ድራማዎች ጽፎአል፡፡ እሱን በመከተል ሸሊ ባይረን ጌቴ ጽፈዋል፡፡ የፕሮሚሴቭስ መንፈስ በአውሮፓ የመንፈስ ታሪክ ውስጥ መካከለኛውን መሥመር የያዘ ነው፡፡ አሁን የጠቀስናቸው ሰዎች በአውሮፓ የሥነ ጽሑፍ ጠፈር ላይ በጣም ጐልተው የሚታዩ ከዋክብት ናቸው፡፡)
የፕሮሚሴቭስ ተረት እንደሚቀጥለው ነው፡፡ ፕሮሚሴቭስ በከፊል አምላክ፣ በከፊል ሰው የሆነ ሕላዌ ነበር፡፡ በከፊል አምላክ እንደመሆኑ ዐሥራ ሁለቱ የግሪክ አማልክት በኦሉምቦስ ተራራ ሆነው ስለ ሰውና ስለ ዓለም አስተዳደር ሲመክሩ ይሰማ ነበር፡፡ በከፊል ሰው እንደመሆኑ የሰው ሥቃይና መከራ በጣም ያሳዝነው፣ ይጸጽተው ነበር፡፡ ሰው ቤት ንብረት ሳይኖረው በበረሃ፣ በጫካ፣ በዱር፣ በገደል፣ በዋሻ፣ በቁር፣ በሀሩር እንዲኖር ተፈርዶበት ነበር፡፡ ይህ መሆኑ አማልክት መክረው ዘክረው፣ ለሰው የዕውቀት ምንጭ የሆነውን ብርሃንን የሰጡት እንደሆን ከዕለታት ባንድ ቀን ሰጭነታቸውን ክዶ፣ በነሱ ላይ በመነሳት የሚያምፅ መሆኑን በመረዳት፣ ብርሃንን ከሰዎች ደብቀው ከማይደርሱበት ቦታ በመሠወራቸው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሰዎች በጭለማና የርሱ ተከታይ በሆኑት ችግሮች ሥር ሲሰቃዩ ይኖራሉ፡፡
ይህ የሰዎች መራራ ዕድል ወገናቸው በሚሆን በፕሮሚሴቭስ ላይ ርህራሄ አሳድሮበት፣ ብርሃንን አማልክት አርቀው ከደበቁበት ሰርቆ ለሰዎች ወስዶ ሰጠ፡፡ ያን ጊዜ ማናቸውም ነገር ግልጽ ሆኖ ታያቸው፡፡ በብርሃን ምክንያት ጥበብና ማናቸውም የዕውቀት ስልት ስለተገለጸላቸው፣ ራሳቸውን ከገዛ ራሳቸው በተገኘው ዘዴ ለማስተዳደር ጀመሩ፡፡
ፕሮሚሴቭስን ግን ለሰዎች ብርሃንን ሰጥቶ፣ በጐ በመሥራቱ አማልክት ቀንተው፣ በብርቱ ስቃይ ይቀጣ ዘንድ አዳኝ ከማይደርስበት ገደል ላይ ከቋጥኝ ድንጋይ ጋር በሰንሰለት ተቆራኝቶ፣ አሞራ ለዘለዓለም እንዲበተብተው ፈረዱበት፡፡
*   *   *
ከፕሮሚሴቭስ ዕጣ -ፈንታ ይሰውረን፡፡ ይህ ፕሮሚሴቭስ የሰውን ዕድል ለማሻሻል የሚታገሉት የዕውቀት ሰዎች፣ የመምህራንና የሊቃውንት ምሳሌ ነው፡፡ እሱ ብርሃንን አማልክት ከደበቁበት ቦታ ወስዶ ለሰው እንዳበረከተ ፣ የዕውቀት ሰዎችም ዕውቀት በመለኮታዊ ምሥጢርነት ከሰው ተደብቃ ስትኖር ሳለ በብዙ ትግል አግኝተው፣ ከገዛ ራሳቸው አሥርፀው የወገኖቻቸውን ዕድል ለማሻሻል ያበረክታሉ፡፡ ዋጋቸውም ሌላ ሳይሆን ስቃይ መከራ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ሶክራቲስ በመርዝ ተገድሎአል፡፡ ጆርዳኖ ብሩኖ የጧፍ ቀሚስ ተጐናጽፎ በእሳት ተቃጥሎአል፡፡
እነዚህ ሰዎች እንደ ጧፍ መብራት ማለት ናቸው፡፡ ራሳቸው ነደው ተቃጥለው ያልቃሉ። ለሌሎች ግን ብርሃን ይሰጣሉ፡፡ የፕሮሜሴቭስ ምሳሌ አንድ ትልቅ ሕግ ጉልህ አድርጐ ያሳያል። ይህም “ዕውቀት በሥቃይ የሚገኝ ነው” (Learn through suffering) የሚል ነው፡፡  
ልጆቻችንን ይህን ለሌሎች ስንል መታገል፣ መስዋዕት  ማድረግ እንደምን እናስተምር? ብርሃን የሚያመጡ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ ዕውቀትን ለሀገር ለማጎናፀፍ የሚጥሩ መምህራን ያሹናል፡፡ የዕውቀት ብርሃን ለመጪው ትውልድ ታትሮ ለማስተላለፍ፣  ልብና ልቡና ይፈልጋል፡፡ አረፍ ብሎ ወዴት እያመራን ነው ብሎ መጠየቅን ግድ ይላል፡፡ ዕውቀት ከትምህርት ብቻ የሚገኝ አይደለም፡፡ ከኑሮአችን፣ ከልምዳችን፣ ከትግላችን እንጂ፡፡ ይህ ወረድ ብሎ አፈሩን መዳሰስን፣ ህዝቡን ማግኘትን፣ የልብ ትርታውን ማወቅን ይጠይቃል፡፡ ምን ጎደለው? ስለዚህ ጉዳይ ግንዛቤ አለ ወይ? በምን ዓይነት መንገድ የጎደለውን ዕውቀት ለማሟላት እችላለሁ? ማለትን ይጠይቃል፡፡ መንገዱን ካገኙ በኋላም፤ ጧት ማታ ሳይታክቱ መታተርን ይጠይቃል፡፡ ይህን ከልብ ካደረግን አገር መውደድ ገብቶናል፡፡ ያንድ ሰሞን ሞቅ ሞቅ ብቻ አገርን ከገባችበት ማጥ አያወጣትም፡፡ “ኦሆ በሀሊ፣ ያርጓጅ አናጓጅ፣ በደመቀበት ቦታ ሁሉ የሚያጨበጭብ አንድም የተለየ ነገር ለማስገኘት አይችልም” ይላሉ ዶክተር እጓለ፡፡ ሉቃስን በመጥቀስም እንዲህ ይሉናል፡- “ውሰብአ አቴናሰ ወእለ ይነግድ ኲሎሙ ህየ በእደ ትካዘ አልቦሙ ዘእንበለ ዳእሙ ለአፅምኦ ወነቢብ ዘሐዲስ”። አቴናውያን አዲስ ነገር ከመስማት ወይም ከመናገር በስተቀር ሌላ ምኞት አልነበራቸውም። ባለው ላይ ቆሞ አዲስ ነገር ለማግኘት የሚጣጣር ሰው ሁል ጊዜ ወደፊት ይሄዳል - ማለት ነው፡፡
እንደ አቴናውያን፤ በአለው ላይ ቆመን አዲስ ነገር ለማግኘት የምንጣጣር ከሆነ ወደፊት እንሄዳለን። ትምህርትንና ዕውቀትን መሰረቱ ያደረገ ትውልድ ከፈጠርን የራሱን ጥያቄ፣ የራሱን ነገ ራሱ ይወልዳል። የሚኖርበት ቤት ሲጠበው ቤቱን ራሱ አስፋፍቶ ይሰራዋል፡፡ ሁሉን እኛ እናድርግልህ ካልነው - ሁሉን ቀላቢ እንሁንለት ካልን፤ ዞሮ ዞሮ ተቀላቢ ትውልድ ነው የምናፈራው፡፡ ፈረንጆቹ እንደሚሉት - Spoon – Feeding mentality ይጠቀልለዋል - የአጉሩሱኝ አስተሳሰብ እንደማለት ነው፡፡
ለወጣቱ፤ የመንግሥቱ ለማን ግጥም “መርፌ - ትሰራለህን” ማንበብና በዚያ አቅጣጫ መጓዝ የአባት ነው፡፡ በየትኛውም አቅጣጫ! ወጣቱ በሥነ ምግባር ረገድ፣ የሰውን ፀባይና ችሎታ በሚመረምር መልኩ አዕምሮው መታነፅ አለበት፡፡ ዕውቀትን መሰረት ሳያደርግ ለትግል ብቻ ብናዘጋጀው፣ የፕሮፓጋንዳ ወይም የአጀንዳ ማስተላለፊያ አሸንዳ ቱቦ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ በታሪክም የታየ ነው፡፡ በማህበራዊ ኑሮው የእያንዳንዱ መብትና ተግባር የሚጠበቅበት፣ “ሰው በንፁህ ተምኔቱ መሰረት በሰላም ተደስቶ የሚገኝበትን ሕግ” ይዞ መጓዝ እንዳለበት ሊረዳ ይገባል፡፡ ህይወት እንደ ጂኦሜትሪ ትምህርት በቀጥታ መሥመር የተሞላና የተለካ አይደለም፡፡ ቀላል ሂሳብም አይደለም። እንዴት እንደሚገነባ፣ ከራሱ ህይወት ተነስቶ እንዴት ለማደግ እንደሚችል፣ ትምህርትን ባሰላሰለ መልኩ ማጤን እንጂ “ሳይገሉ ጎፈሬ፣ ሳያረጋግጡ ወሬ” መሆን የለበትም፡፡ እስከ ዛሬ አጭር ተመልካች፣ አጭር ተጓዥ ሳናደርገው (Myopic) አልቀረንም፡፡ አጭር ግቦች አጭር ያደርጉናል!
አንድ ደራሲ እንደሚለው፤ “… የውጪ ጉዳዮችን ካገር ውስጥ ኃይሎች አሰላለፍ፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ከጥበብ ሽግግርና ከውጪ ርዳታ፣ የቋንቋ መዘበራረቅና ጉራማይሌነትን ከባህላዊ ድቀት፣ የሐሳብ ነፃነትን ከጋዜጣ፣ ራዲዮና አጠቃላይ ውይይት ምህዳር መጥበብ ጋር…” የሚያነፃፅር ወጣትም ሆነ አዋቂ ያስፈልገናል፡፡
ወጣቱ አገሩን ያውቅ ዘንድ ጥልቅ አስተሳሰብ፣ ረዥም ርዕይና በግብረገብ የታነፀ ድፍረትና መስዋዕትነት ያስፈልገዋል፡፡ የሀገራዊነት፣ የወገን አሳቢነት፣ የኢ-ራስ - ወዳድነት፣ የሁሉን - አውድም አስተሳሰብ አለመያዝ፣ ሁሉን - ረጋሚ ያለመሆን አመለካከት፣ ኢ-ፅንፋዊነት ወዘተ እንደ መርህም፣ እንደ ኑሮም ሊሰርፁበት ይገባል፡፡ አለበለዚያ አፋሮች እንደሚሉት፤ “አገሩን የማያውቅ ሰው፣ መሬትን እየረገጠ መሬትን ይረግማል” ይሆናል፡፡   

ደሞዛቸው በወር 800 ሪያል ይሆናል
ከሁለት ወራት በኋላ 2800 ኢትዮጵያውያንን በቤት ሠራተኝነት ወደ ሣኡዲ አረቢያ ለመላክ የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን በጅዳ የሚገኘው ቆንፅላ ፅ/ቤት አረጋግጦልኛል ሲል ሣኡዲ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
150 ያህል ሰራተኛ በአዲስ አበባ ባለ 5 እና ባለ 10 ብር ካርድ እጥረት የተፈጠረው በከተማዋ የካርድ ተጠቃሚዎች በመበራከታቸው መሆኑን ኢትዮ- ቴሌኮም አስታወቀ፡፡ ለካርዶቹ መጥፋት ከተጠቃሚው መብዛት ባሻገር የስርጭት ችግር መኖሩን ለአዲስ አድማስ የጠቆሙት የኢትዮ-ቴሌኮም የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ አብዱራሂም አህመድ፤ አከፋፋዮች እጥረት አለ ሲባል አጋጣሚውን ተጠቅመው ዋጋ ለመጨመር ሰው ሰራሽ እጥረት መፍጠራቸውን ገልፀዋል፡፡
በሳምንት 50 ሚሊዮን  የባለ 5 እና 10 ብር ካርዶች ፍጆታ ላይ ይውሉ እንደነበር የጠቆሙት አቶ አብዱራሂም፤ በአሁን ወቅት ከ100 ሚሊዮን በላይ ካርድ እንደሚቀርብ ሰው ሰራሽ እጥረቱን ማሳያም ነው ብለዋል፡፡
ችግሩን በአፋጣኝ ለማቃለል 140 ሚሊዮን ባለ 5 እና 140 ሚሊዮን ባለ 10 ብር ካርዶች በውጭ ሀገር አሳትሞ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ላይ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አብዱራሂም፤  ችግሩ ከሰኞ ጀምሮ እንደሚቀረፍም አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ከ89 ዋና የካርድ አከፋፋዮች፣ 600 ንኡስ አከፋፋዮችና ከ120 ሺህ ቸርቻሪዎች ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር ካርዶቹን ለተጠቃሚዎች እንደሚያደርስ ሃላፊው አስረድተዋል፡፡  
ከሠሞኑ በአዲስ አበባ በርካታ አካባቢዎች ባለ 5 እና ባለ 10 ብር የሞባይል ካርዶችን ለማግኘት አስቸጋሪ እንደነበር ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሠጡ ተጠቃሚዎች አስታውቀዋል፡፡ መልማይና ላኪ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ መንግስት የሥራ ፈቃድ አግኝተው ሠራተኞቹን ለመላክ በዝግጅት ላይ ናቸው ተብሏል፡፡ ወኪሎቹ በአሁኑ ወቅት ሰራተኞቹን ወደ ሣኡዲ ለመላክ የሣውዲ መንግስት ይሁንታ ብቻ እየተጠባበቁ መሆኑን ተገልጿል፡፡  
በቤት ሠራተኝነት የሚላኩት ወጣቶች በቤት አያያዝና ተያያዥ ሙያዎች በቂ ስልጠና እንደተሰጣቸውና ስለ ሣኡዲ ባህልና አኗኗርም ግንዛቤ እንዳገኙም ታውቋል፡፡
ወርሃዊ ደሞዛቸውም 800 የሳኡዲ ሪያል መሆኑን የጠቀሰው ዘገባው፤ የመጀመሪያ የስራ ውላቸው ለ3 ወራት የሚቆይ ሆኖ፤ በሂደት ይራዘማል ተብሏል፡፡
በቅርቡ የኢትዮጵያ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የሣኡዲ መንግስት የሠራተኛ ጉዳይ ሚኒስቴር በቤት ሠራተኞች ጉዳይ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
በዚህ ስምምነት ከተካተቱት ጉዳዮች መካከል የሣኡዲ መንግስት ለሠራተኞች ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግ፣ ሰራተኞች በህጋዊ ኤጀንሲዎች ብቻ መላክ እንዳለባቸው፣ የኢትዮጵያ መንግስት ለሠራተኞች በቂ ስልጠና ሰጥቶና ጤንነታቸው የተሟላና ለስራ ብቁ መሆናቸውን አረጋግጦ እንዲልክ የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ግርማ ሸለመ፤ በሳኡዲ ጋዜጣ የወጣው መረጃ በሳኡዲ የተገኘ እንጂ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል የቀረበ አለመሆኑን ጠቅሰው ብዙም ስለጉዳዩ መረጃ የለንም ብለዋል፡፡ በስምምነቶች መሠረት እየተከናወኑ ያሉ ዝግጅቶች መኖራቸውንም ኃላፊው አክለው ገልፀዋል፡፡

   የተስፋ ብልጭታዎችና የወደፊት አቅጣጫዎች ክፍል 2

    የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከልን አስመልክቶ በክፍል 1 ያቀረብነው ዘገባ ከ224 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የሆነባቸውን የስፖርት መሰረተ ልማቶች የግንባታ ሂደቶች በመጠኑ የሚዳስስ ነበር፡፡ በክፍል ሁለት የማሰልጠኛ ማዕከሉን ሳይንሳዊ የስልጠና መንገዶች፤ የአሰልጣኞችን የሙያ እና የብቃት ደረጃ  የሰልጣኞች ምልመላ እና ተያያዥ ሁኔታዎችን  እንመለከታለን፡፡   የማሰልጠኛ ማዕከሉን ፍሬያማነት በማንሳት ከተለያዩ አቅጣጫዎች የምንገመግመው ሲሆን የሰልጣኞችን ተስፋና የአሰልጣኞችን የብቃት ደረጃን ማሻሻል ጥያቄ እናነሳለን፡፡ ይህን ልዩ ዘገባ ለመስራት በጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል የትምህርት፣ የስልጠናና የውድድር ዘርፍ ዲያሬክተር ከሆነው አሰልጣኝ ጎሳ ሞላ ፤ በአጭርና መካከለኛ ርቀት እንዲሁም የአንዳንድ የሜዳ ላይ ስፖርቶች አሰልጣኝ ከሆኑት ንጉሴ አደሬ እና ከከፍታ ዝላይ ሰልጣኝ ማልጎኝ ዊል ጋር ቃለምልልሶች አድርገናል፡፡ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት  ኃይሌ ገብረስላሴ ጋርም ተጨማሪ ውይይት የነበረን ሲሆን በማሰልጠኛ ማዕከሉ ዙርያ የተሰሩ የጥናት ፅሁፎችን መርምረናል፡፡  መልካም ንባብ፡፡
እንደመግቢያ
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው በኢትዮጵያ መንግስት በቢሊዮን የሚተመን በጀት ወጥቶባቸው የተገነቡ የስፖርት መሰረተ ልማቶች አድናቆት የሚገባቸው ናቸው፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፤ የጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከልና ሌሎች ተቋማት የቀድሞ ውጤታማ እና ባለታሪክ አትሌቶች የነበራቸውን ህልምና ፍላጎትን ያሳኩ መሰረተ ልማቶች በመሆናቸው ነው ፡፡
ይሁንና አካዳሚውና የማሰልጠኛ ማዕከሉ የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን የሚሆኑ ምርጥ ስፖርተኞችን ማፍራት ዋንኛ ዓላማቸው መሆን እንዳለበት የሚያሳስበው ኃይሌ፤ የስፖርት መሰረተ ልማቶቹ ተገንብተው ስራ ከጀመሩ በኋላ በሚከተሉት ራዕይና ዓላማ ዓለም አቀፍ ተፎካካሪነትን  ከግምት ውስጥ ባስገባ የአመራር ደረጃ መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው፣ በሚሰጧቸው አገልግሎቶች ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉበት አሰራር እንዲኖራቸው፤  በአስተዳደራቸው የስፖርቱን ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ መስራት እንዳለባቸው ይናገራል፡፡
በርግጥም የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፤ የጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከልና ሌሎችም የስፖርት መሰረተ ልማቶች ተቀብለው በሚያሰለጥኗቸው ስፖርተኞች ብቻ በመወሰን ታጥረው መቀመጥ የለባቸውም፡፡ ቢያንስ የመሮጫና የልምምድ ትራኮቻቸው፣ የእግር ኳስና የሌሎች ስፖርቶች ሜዳዎች ተገቢውን የቁጥጥር መርሃ ግብር በመዘርጋት ለሁሉም ክፍት መሆን አለባቸው፡፡
ኃይሌ በአስተያየቱ የስፖርት መሰረተ ልማቶች በሚሰጡት አገልግሎት የገቢ ምንጮችን እንዲፈጥሩ፤  በአስተዳደራቸው ልምድ ያላቸው ታላላቅ ስፖርተኞች እና ባለሙያዎችን እንዲያሳትፉ፤ በባለቤትነት የሚያስተዳድራቸው የስፖርት አካል ብቻ እንዲሆን፤ የነባርና የቀደም አትሌቶች አስተዋፅኦ እንዲጠናከር መደረግ አለበትም ይላል፡፡ በተለይ የገቢ ምንጮችን በመፍጠር ረገድ በሆላንድ፤ በጣሊያን፤ በጀርመንና በእንግሊዝ ያሉ ተመክሮዎችን በመንተራስ ከጅምሩ የተገነቡት የስፖርቱ መሰረተ ልማቶች በዚያ የሚሰራውን መከተል እንደሚኖርባቸው ሲያመለክት ብሄራዊ ቡድኖች ማዕከሉን ሲገለገሉ የሚያንቀሳቅሳቸው ፌደሬሽን ክፍያ እንደሚፈፅም እና ይህ አሰራር በየደረጃው እንደሚሰራበት ጠቁሞ፤ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል በተመጣጣኝ ክፍያ የስፖርት መሰረተልማቶቹን አገልግሎት እንዲያገኝባቸው መስራት ተገቢ ነው ብሏል፡፡
የማዕከሉ አሰልጣኞች እና ሳይንሳዊ ስልጠና መንገዶች
በጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል የትምህርት፣ የስልጠናና የውድድር ዘርፍ ዲያሬክተር የሆነው አሰልጣኝ ጎሳ ሞላ ነው፡፡ በማዕከሉ ሁለገብ እንቅስቃሴዎች ያለፉትን 7 አመታት ያገለገለው አሰልጣኝ ጎሳ፤ በስፖርት ሳይንስ በተለይ በአትሌቲክስ ስፖርት በመጀመርያ ከባህርዳር ከዚያም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲዎች ሁለት ዲግሪዎችን ተቀብሏል፡፡
አሰልጣኝ ጎሳ ሞላን ጨምሮ በጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል ላይ  እየሰሩ የሚገኙት 20 አሰልጣኞች ናቸው፡፡ ከመካከላቸው ሶስቱ በስፖርት ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል፡፡ 17ቱ አሰልጣኞች ደግሞ በስፖርት ሳይንስ የመጀመርያ ዲግሪ ያላቸው ሲሆኑ ከእነሱ መካከል  በማዕከሉ ውስጥ እያገለገሉ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በመስራት ላይ የሚገኙት አምስቱ ናቸው፡፡ ሃያዎቹ አሰልጣኞች በማዕከሉ ለሚገኙት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልጣኞች ውጤታማ እና ተመጣጣኝ ስራ ለማከናወን በቂ ናቸው ለማለት አይቻልም፡፡ ከስልጠናው ባሻገር በፊዝዮሎጂ፤ ስነ ምግብና ስነ ልቦና የሚሰሩ ባለሙያዎች ስብስብ ያካተተ አደረጃጀት ወሳኝ እንደሆነ መታወቅ አለበት ፡፡ የአሰልጣኞቹ ብዛት፤ የሙያ ብቃት፤ የትምህርት ደረጃና ልምድ ዓለም አቀፍ ደረጃ በጠበቀ ሁኔታ በማዋቀር የሚሰራበት አዲስ አቅጣጫ ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ከሆኑት ከብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፤ ከአትሌቲክስና ከሌሎች የስፖርት ፌዴሬሽኖች ጋር በአጋርነት በመንቀሳቀስ መተግበር የሚቻል ይመስለኛል፡፡
አሰልጣኝ ጎሳ ሞላ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው የማዕከሉ አሰልጣኞች በየጊዜው የሙያ ማሻሻያዎች፤ ስልጠናዎችን በመከታተል ብቃታቸውን የማሳደግ ባህል እያዳበሩ መጥተዋል፡፡ በአትሌቶች ላይ ለሚሰሯቸው ስልጠናዎች ወቅቱን የጠበቁ መረጃዎች በቅርበት የሚወስዱ በመሆናቸው  በተለያዩ ምርምሮች እና ጥናቶች የመሳተፍ ፍላጎትና አቅም እየፈጠሩ ይገኛሉም ብሏል፡፡   በርግጥ በማዕከሉ ከሚሰጡ ስልጠናዎች ጋር በተያያዘ ጥናትና ምርምር የሚደረጉባቸው አሰራሮች መሰረት እየያዙ መምጣታቸው የሚያበረታታ ነው። ሆኖም ግን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው የሚሰሩበት ፖሊሲ አለመኖሩ ዘላቂ ስኬት የሚመዘገብባቸውን ሁኔታዎች የሚያዳክማቸው ሆኗል፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች ከሚሰሩ ብሄራዊ ቡድኖች፤ ከክለብ እና ክልል ቡድኖች፤ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ዩኒቨርስቲዎች፤ ከነባር እና ልምድ ካላቸው ትልልቅ አትሌቶች እና አሰልጣኞች፤ ከኦሎምፒክ ኮሚቴ፤ ከፌደሬሽኖች ጋር በአጋርነት በመስራት የማዕከሉን ፍሬያማነት በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ይቻላል፡፡
ማዕከሉ በሚያከናውናቸው ተግባራት እንደትልቅ ተቋም መንቀሳቀስ ይገባዋል፡፡ ለወጣት ስፖርተኞች የስራ እድል መፍጠር እና ስፖርቶችን ማስፋፋት እንደገዘፈ ውጤት ከመቁጠር መውጣት አለበት፡፡ ሰልጣኞቹ የዓለም እና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ለመሆን የሚበቁ፤ በተለያዩ ስፖርቶች የላቁ ውጤቶችን የሚያስመዘግቡ፤ ሪከርዶችንና የውጤት ክብረወሰኖችን በማሳካት ታሪክ የሚሰሩ መሆን አለባቸው፡፡  የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እና የጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል በስፖርት ዩኒቨርስቲ ደረጃ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል የሚለው ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ፤ ተቋማቱ በስፖርቱ ምርምርና ጥናት የሚያደርጉ፤ የአሰልጣኞች አሰልጣኝ የሆኑ ባለሙያዎችን የሚያፈሩ፤ ምርጥ እና ኤሊት አትሌቶችን የሚያፈልቁ፤ ከዓለም እና ከኦሎምፒክ ሻምፒዮኖች ጋር በተለያዩ መዋቅሮች ተቀናጅተው የሚሰሩ መሆን እንዳለባቸው ያሳስባል፡፡ ሁለቱም የስፖርት ተቋማት ዓላማቸው ለዓለም አቀፍ ውድድሮች በአካልና በአዕምሮ ከፍተኛ ብቃት ያላቸው፤ ስነ ምግባራቸውን የጠበቁ ምርጥና ወጣት ስፖርተኞች ማፍራት፤ ለባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት፣ ለስፖርቱ ጥራት አስተዋፅኦ የሚሆኑ የጥናትና የምርምር ስራዎች ማካሄድና ውጤቶችን ማሰራጨት እንዲሁም ለተለያዩ ስፖርቶች የዕውቀት ማዕከል መሆን ነው፡፡
በርግጥ አሰልጣኝ ጎሳ ሞላ  ለስፖርት አድማስ እንደተናገረው በማዕከሉ በሚሰጡ ስልጠናዎች  በሳይንሳዊ አሰራሮች እየተጠናከሩ መምጣታቸው ከላይ የተጠቀሱትን ዓላማዎች ለመተግበር የሚያግዙ አበረታች ጅማሮዎች ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የሰልጣኞች ምልመላ በመስፈርት ላይ የተመረኮዘ መሆኑ የማዕከሉን አሰራር ሳይንሳዊ እንደሚያደርገው አሰልጣኝ ጎሳ ሲያስረዳ፤ ‹‹የትኛው አትሌት ለየትኛው ስፖርት መግባት ይችላል››  በሚል አስተሳሰብ እንሰራለን በማለት ነው፡፡ በማዕከሉ በኩል የአትሌቲክስ ሰልጣኞች የሚመለመሉት   በየዓመቱ በየክልሉ ተዘዋውሮ በማፈላለግ በሚከናወኑ ተግባራት ነው። በተለይ ለአትሌቲክስ ከ17 ዓመት በታች እድሜ ያላቸው ታዳጊና ወጣቶች ይፈልጋሉ፡፡ ምልመላውን የሚያከናውኑት የማዕከሉ አሰልጣኞች  በአትሌቲክስ አሰልጣኝነት በመስራት ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው በስልጠና እንለውጣቸዋለን ብለው የሚያስቧቸውን አትሌቶች በየክልሉ የሚያፈላልጉበት አሰራር በተሻለ መዋቅር ማደግ ይኖርበታል፡፡ አሰልጣኝ ጎሳ ሞላ የምልመላውን ሂደት ሲገልፅ በዕጩ ሰልጣኞች ምልመላ የሚሰማሩ ባለሙያዎቹ ታዳጊዎችና ወጣቶችን በቅርበት ያላቸውን አቅምና የአካል ብቃት እንደሚገመግሙ፤ ይህን ሂደትም በፎቶ እና በቪድዮ ምስሎች አስደግፈው በሙሉ ሃላፊነት ለማዕከሉ እንደሚያቀርቡም ይገልፃል፡፡ በአሰልጣኞቹ አማካኝነት ከየክልሉ በእጩ ሰልጣኝነት የተመለመሉት  ወደ አካዳሚው ከመግባታቸው በፊት ሌላ ፈተና ይጠብቃቸዋል፡፡  የባለሙያዎች ኮሚቴ ምልመላውን ባከናወኑ አሰልጣኞች የሚቀርቡ መረጃዎችን በጥልቀት ይመረምሯቸዋል፡፡ በመጨረሻም በአዳሪነት ገብተው ተከታታይ ስልጠናዎች ለ4 ዓመታት  ወስደው እንዲመረቁ ይደረጋል፡፡ከዓለም አቀፍ ተመክሮዎች መገንዘብ እንደሚቻለው ምርጥ ፐሮፌሽናል አትሌት በማሰልጠኛ ማዕከል ለማፍራት በትክክለኛው ሳይንሳዊ የስልጠና ሂደት ከ8-12 ዓመት ይወስዳል። በአጠቃላይ አንድ ሰልጣኝ ፕሮፌሽናል አትሌት ለመሆን 10 ዓመታትን መሰልጠንና መማር አለበት። ይህንን በጥሩነሽ ማዕከል ለመተግበር በሚያስብ ፖሊሲ መንቀሳቀስ ተገቢ መሆኑን እዚህ ጋር መጠቆም ግድ ይላል፡፡
በሌላ በኩል  ማዕከሉ ሳይንሳዊ አሰራሮችን እንደሚከተል የሚያመለክት ማስረጃ ስልጠናዎች በእቅድ መመራታቸው ነው አሰልጣኝ ጎሳ ሞላ ማብራሪያውን ይቀጥላል፡፡ እያንዳንዱ ሰልጣኝ ዓመታዊ የእቅድ መርሃ ግብር እንደሚወጣለት፤ ስልጠናን የመቀበል አቅም እና የእድሜ ደረጃን ከግምት ውስጥ እንደሚያስገባ፤ በየእለቱ፤ በየሳምንቱ የሚሰጡት ስልጠናዎች በማማከል የሚነደፉ ናቸው። በተጨማሪም ስልጠናውን በእቅድ ከመምራት ባሻገር ለአትሌቱ ዓመታዊ ግብ በማስቀመጥ መስራታችን ምን ያህል ለሳይንሳዊ አሰራር ትኩረት እንደሰጠን የሚያመለክት ነው የሚለው አሰልጣኝ ጎሳ፤ በተለያዩ የስልጠና ደረጃዎች ለእያንዳንዱ ስፖርተኛ በየስፖርት አይነቱ ዓመታዊ ግብ የሚቀመጥለት ወቅታዊ ብቃቱን በማገናዘብ  እዚህ መድረስ አለበት ተብሎ ነው ብሏል፡፡  በአጠቃላይ በማዕከሉ የስልጠና እቅዶቹ ፤ የልምምድ መርሃ ግብሮች፤ የሚመዘገቡ ውጤቶች እና ተያያዥ አሃዛዊ መረጃዎች በሰነድ እና በዲጂታል ማህደር ከስር በስር የሚከማቹ መሆናቸው ተጠናክሮ መሄድ ያለበት ልምድ ነው ፡፡ የማዕከሉን የስልጠና ሂደት ለመተንተን እና በተለያየ አቅጣጫ ለማስላት የሚያግዝ ሳይንሳዊ አሰራር ነው፡፡
ስልጠናዎች በተለያዩ ወቅቶች መከፋፈላቸውም የሚጠቀስ ሳይንሳዊ የስልጠና ሂደት ሲሆኑ፤ የመደበኛ ዝግጅት ወቅት፤ የቅድመ ውድድር ወቅት እና የውድድር ወቅት በመከተል የሚካሄዱት የስልጠና ሂደቶች ልዩ ውጤት የሚያስገኙ ይሆናሉ፡፡ በሳምንት ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ለሁሉም አትሌቶች 10 የልምምድ መርሃ ግብሮች ያሉ ሲሆን፤  በጠዋት እና ከሰዓት ተከፋፍለው ሰልጣኞች የስልጠናውን ጫና ተቋቁመውና በቂ እረፍት አድርገው እንዲሰሩም ይደረጋል፡፡ የአትሌቱን መቶ ፐርሰንት ብቃት በየደረጃ መለካት የሚቻለው በእነዚህ ወቅቶች ጠብቆ መስራት ሲቻል ነው የሚለው አሰልጣኝ ጎሳ፤ በአጠቃላይ ከላይ በተጠቀሱት ሳይንሳዊ የስልጠና ሂደቶች የሚነደፉት የስልጠና መርሃ ግብሮች በተለያዩ ዲፓርትመንቶች ከፀደቁ በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆኑ በማመልከት ነው፡፡  ከዓመታዊ እቅድ እና ግብ ባሻገር አሰልጣኙ እና ሰልጣኝ አትሌቱ ተስማምተው እየሰሩ መሆናቸውን ተከታተለው የሚያረጋግጡበት መዋቅርም ተዘርግቷል፡፡ አትሌቱ እዚህ እደርሳለሁ ሲል አሰልጣኙም እዚህ አደርሰዋለሁ በሚል ተስማምተው ይሰራሉ፡፡ በየስልጠናው ክፍል  በእቅድ እና በተቀመጠው ግብ መሰረት እንቅስቃሴ መኖሩን የሚመረምሩ ሃላፊዎች አሉ፡፡ በየወቅቱ የውስጥ ምዘናዎች ይደረጋሉ፡፡ ምዘናዎቹ የአካል ብቃት፤ ወቅታዊ አቋም እና የፉክክር ደረጃ የሚፈተሽባቸው ሲሆን አትሌቱ በየጊዜው ስለሚያሳየው ማሻሻያ ክትትትል ለማድረግ የሚያመች ሌላ ሳይንሳዊ አሰራር ነው፡፡ በማዕከሉ የሚሰጡት ስልጠናዎች በሳይንሳዊ መንገድ መካሄዳቸው ከላይ የተዘረዘሩት ስኬቶች ምስጥር እንደሆኑ የሚያስገነዝበው አሰልጣኝ ጎሳ ሞላ፤ ሰልጣኞች በየእለቱ በሚያልፉባቸው የስልጠና መርሃ ግብሮች ምርጥ ውጤት ለማግኘት ጥረት የሚያደርጉበትን ባህል በማዳበራቸው ወደተለያዩ ውድድሮች ሲገቡ በሪከርድ ስኬት እና በሜዳልያ ውጤት የሚደነቁበትን ታሪክ በተደጋጋሚ የሰሩበትን እድል ፈጥሮታል ብሏል፡፡
በአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት የምልመላ ሂደት ያሉትን ዓለም አቀፍ ተመክሮዎች በማጥናት መገንዘብ የሚቻለው የጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል ብዙ ክፍተቶች እንዳሉት ነው። የመጀመሪያው አሳሳቢ ክፍተት ብዙዎቹ ሰልጣኞች ለማዕከሉ የሚመለመሉት በአገር አቀፍ ደረጃ  በሚካሄዱ ውድድሮች ክልብ ወይም ክልል ወክለው ከተሳተፉ በኋላ መሆኑ ነው። በማሰልጠኛ ማዕከል ሳይንሳዊ አካሄድ ሰልጣኞች መመልመል ያለባቸው ምንም አይነት የውድድር ተመክሮ ሳይኖራቸው መሆን ነበረበት፡፡ ከ6-10 በሚሆን እድሜያቸው በየትውልድ ስፍራቸው በሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ያልፋሉ፡፡ ከዚያም ከ10-14 በሚሆን እድሜያቸው መደበኛ የስፖርት ስልጠናዎችን ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸው ጎን ለጎን ያዘወትራሉ። ከእነዚህ ሂደቶች  በኋላ ወደ ማዕከሉ እንዲገቡ መደረግ አለበት።
ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ የስልጠና ሂደቶች በአካዳሚ፣ በማሰልጠኛ ማዕከል፣ በክለብና በክልል ደረጃ ወጥ የሚሆኑበት መዋቅር ካልተዘረጋ ውጤታማ አንሆንም ይላል፡፡ የላቀ ብቃትንና ውጤት የሚያስመዘግብ ፕሮፌሽናል አትሌት ለማፍራት የሚችለው ከስር ተነስቶ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በሚያሳትፍ ብሄራዊ መመሪያ በመስራት ነው ብሎ፤ በቀድሞ አትሌቶች በአዲስ መልክ ተደራጅቶ የሚንቀሳቀሰው ፌዴሬሽን የነበሩ አሰራሮች እና አመለካከቶች ለመቀየር ቢቸገርም አንዳንድ ስርነቀል ለውጦች ለመፍጠር እየሞከረ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ አትሌቶች የሚያልፉበት የስልጠና ሂደት፤ አሰልጣኞች የሚሰሩባቸው የስልጠና መንገዶች ሁሉ ወጥ አለመሆናቸው ዋናው ፈተና እንደሆነባቸው የሚያስገነዝበው ኃይሌ፣ በዛሬው ትውልድ የአትሌቶች ጥረት እና ትጋት ያነሰ መሆኑን በማስተካከል የአካዳሚና የማሰልጠኛ ተቋማት ሰልጣኞችን የመመልመል ሂደት ከዚያም ለሚሰጡ ስልጠናዎች ስኬት የሚያመች መዋቅር መፍጠር እንደሚገባ ያስገነዝባል፡፡
ለአካዳሚ ወይንም ለማሰልጠኛ ማዕከል የሚሆኑ ሰልጣኞች ተገቢውን የዕድሜ ደረጃና የዕድገት ሂደት ጠብቀው የሚደርሱ መሆን እንዳለባቸው ከዚሁ ጋር በማያያዝ ያስገነዝበው ኃይሌ፤ ከቀበሌ ወደ ዞን ከዚያም በከተማ እና በክልልና በክለብ  ደረጃ በሚዘረጉ መዋቅሮች እና የስልጠና ሂደቶች ስርዓቱን ጠብቀው የሚያልፉ ሰልጣኞችን በመመልመል ውጤታማ ስራ መከናወን ይቻላል ብሎ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰራበት ወጥ የአትሌቲክስ መመርያ የመዘጋጀቱን አስፈላጊነት ጠቁሟል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ይህን ታሳቢ በማድረግ ዳጎስ ያለ አገር አቀፍ የአትሌቲክስ መመርያ ሲያዘጋጅ ቆይቶ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ እየደረሰ ይገኛል፡፡ መመርያው ከፍተኛ ልምድ ባላቸው የአትሌቲክስ ባለሙያዎች በየክልሉ የተደረጉ ጥናቶችና ቅኝቶች መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ሲሆን አትሌት፤ ክለብ፤ አሰልጣኝ እና ስልጠና ምን መሆን አለበት ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ በስልጠናው የእድሜ ገደብ፤ የእድገት ደረጃ እና የአሰራር ሂደት በዝርዝር የሚቀመጥበት ሰነድ ነው። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ኃይሌ ገብረስላሴ ይህን የአትሌቲክስ መመርያ አስመልክቶ ለስፖርት አድማስ በሰጠው አስተያየት በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተደጋጋሚ በተደረጉ ውይቶች፤ በቀረቡ ትችቶች እና ግምገማዎች ተጠናክሮ ለህትመት በሚበቃበት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የሚገኝ ሲሆን በየአምስት አመቱ እየዳበረ እና እየተሻሻለ የሚሄድ ነው ብሏል፡፡
የማዕከሉ ፍሬያማነት ሲለካ
የጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ጉልህ አስተዋፅኦና መነቃቃት መፍጠሩን በተለያዩ ማስረጃዎች ማመልከት እንደሚቻል ለስፖርት አድማስ በዝርዝር ያስረዳው አሰልጣኝ ጎሳ ሞላ፤ በአጭር እና መካከለኛ ርቀት ሩጫዎች እንዲሁም የሜዳ  ላይ ስፖርቶች በአገር አቀፍ ደረጃ የነበረውን ያነሰ ትኩረት መቀየሩን፤ ብዙም ትኩረት በማይሰጣቸው ስፖርቶች ክለቦች እና የክልል ፌደሬሽኖች ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማነሳሳቱን ይጠቃቅሳል፡፡ በሜዳ ላይ ስፖርቶች፤ በአጭር እና በመካከለኛ ርቀት ተተኪ እና ውጤታማ አትሌቶች እያፈሩ ስለመሆናቸው የማዕከሉ ሰልጣኞች በክለቦች እና በክልል ፌደሬሽኖች ተፈላጊ እየሆኑ እንደመጡ በመግለፅም የማዕከሉን ፍሬያማነት ሊያመላክት ሞክሯል፡፡
ከወር በፊት በአዲስ አበባ በተካሄደው 46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአጭርና መካከለኛ ርቀት፤ በዝላይና በውርወራ ስፖርቶች ከተመዘገቡ 10 ክብረወሰኖች ገሚሱን በማዕከሉ ያለፉ ሰልጣኞች ማስመዝገባቸውንና የሜዳልያ ውጤቶችንም በብዛት ማግኘታቸውን የገለፀው አሰልጣኝ ጎሳ ፤  በታዳጊ እና ወጣት ውድድሮች ላይም የማዕከሉ ሰልጣኞች በተለያዩ ጊዜያት  ስኬታማ ሆነዋልም ይላል፡፡ በሌላ በኩል ሰልጣኞች በማዕከሉ ሆነው ከማዕከሉም ወጥተው አገርን በመወከል በዓለም አቀፍ ውድድሮች ውጤታማ መሆናቸውንም በማስረጃነት አንስቷል። በ2015 እኤአ ላይ ቤጂንግ ባስተናገደችው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ3ሺ ሜትር መሰናክል የተሳተፉት ጅግሳ ቶሎሳ እና ሃይለማርያም አማረ በማዕከሉ 4 ዓመታትን ሰልጥነው የተመረቁ ናቸው፡፡ በተለይ ሃይለማርያም አማረ በሪዮ 31ኛው ኦሎምፒያ ለመሳተፍ የበቃ መሆኑ ትልቅ ውጤት ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በማዕከሉ በሁለተኛና ሶስተኛ  አመት ሰልጣኝነት የሚገኙ ስፖርተኞች በየክለቦቹ ተሰራጭተው ጠንካራ ውጤት ማስመዝገባቸው ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ማዕከሉ በኮንደሚኒዬም ቤቶች ከ2002 ዓ.ም መስራት ከጀመረበት ጊዜ እንስቶ እስከ 2009 እኤአ ድረስ 445 አትሌቶች  በማስመረቅ ለተለያዩ ክለቦች እና  ቡድኖች አዘዋውሯል፡፡ 113  አትሌቶች  በተለያዩ የእድሜ ደረጃዎች እና የስፖርት ዓይነቶች ለብሄራዊ ቡድን የተመረጡ ሲሆን 31 ወንድና 26 ሴት አትሌቶች በአህጉራዊ ውድድሮች፤   13 ወንድና 11 ሴት አትሌቶች  ደግሞ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ሊሳተፉ በቅተዋል፡፡
በርግጥ የማዕከሉን ፍሬያማነት ከላይ በተዘረዘሩት መረጃዎች ለማመልከት ቢቻልም ግን ሌሎች አሳሳቢ ነገሮች ተጋርጠዋል፡፡ በተለይ ማዕከሉ አሁን ባለበት ደረጃ በተለያዩ የዕድሜ ደረጃ ለሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖች ተፎካካሪና ውጤታማ አትሌቶችን በሚጠበቅበት ደረጃ እያቀረበ አይደለም። ወደ ማሰልጠኛ ማዕከሉ ከሚቡት 50 በመቶ ያህሉ በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ ይወጣሉ፤ ወደ ክለቦች ሲዛወሩ በማዕከሉ ከነበሩበት የስልጠና ደረጃ ወርደው ይሰራሉ፤ በአገር አቀፍ ውድድሮች ያለወቅታቸው እየገቡ ባክነው ይቀራሉ። የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኃይሌ ገ/ሥላሴ በዚህ ዙርያ አስተያየት ሲሰጥ፣ ማዕከሉ ፍሬያማነቱን ለመለካት ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩን መጥቀስ እንዳማይኖርበት አመልክቶ የሚጠበቀው ውጤት የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ለመሆን የሚበቁ ስፖርተኞችን ማፍራት ነው ይላል፡፡
ምናልባትም የማዕከሉ ሰልጣኞችን በአገር አቀፍ ውድድሮች እያገኙ ያሉት ውጤት የሚያበረታታ ቢሆንም በተሟላ መሰረተ ልማት በሚያሰለጥናቸው ስፖርተኞች  ውጤታማ የሆነበትን እድል ከሌሎች ክለቦች ጋር በማነፃፀር እንደስኬት መቁጠሩ ተገቢ አለመሆኑን ሳያስገነዝብ አላለፈም፡፡ በተያያዘ የማዕከሉ ሰፖርተኞች እንደ ክለብ በአገር አቀፍ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉበት ሁኔታ መቀየር እንዳለበት የሚመክሩም አሉ የመንግስት ክለብ ተብሎ መወዳደር ተገቢ አለመሆኑን ለመጠቆም ነው፡፡
በከፍታ ዝላይ ሰልጣኝ የሆነው ማልጎኛ ዊልና ተስፋው
በጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል ባደረግኩት  ጉብኝት ከሰልጣኞች አንፃር ብዙ ያደረግኩት ቅኝት እና ውይይት አልነበረም። የሰልጣኞቹን መመገቢያ፤ መኖርያ እንዲሁም የመማርያ ክፍሎችን ተዘዋውሬ ተመልክቼ ነበር። የማዕከሉ ሰልጣኞች ራሳቸውን የሚያስተዋውቅ ወጥ የስፖርት ትጥቅ (ዩኒፎርም) ቢለብሱ ጥሩ ነው፡፡ የስፖርት መሰረተ ልማቶቹን በመንከባከብ፤ በመፀዳጃ ቤት አካባቢ ያሉ የፍሳሽ ችግሮችን በመቆጣጠር በሚመሩበት ዲስፕሊን አርዓያ መሆን እንዳለባቸው ግን ሳልጠቅስ አላልፍም፡፡
ከሰልጣኞቹ መካከል ግን አንዱን በማነጋገር ምን አይነት ስፖርተኛ ከማዕከሉ እየወጣ መሆኑን ለመገንዘብ ሞክሪያለሁ፡፡ የከፍታ ዝላይ ሰልጣኝ የሆነው ማልጎኝ ዊል ነው፡፡ በመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ላይ ጋምቤላ ክልልን ወክሎ  በመሳተፍ  ስፖርተኛነቱን ጀምሮ ዛሬ  በማዕከሉ የ2ኛ ዓመት ተማሪ ሆኖ እየሰራ ይገኛል፡፡   
በማዕከሉ በምከታተለው ስልጠና ከፍተኛ ለውጥ እያሳየሁ እና እያደግኩ ነው በማለት ለስፖርት አድማስ የሚናገረው ማልጎኝ ተስፋው ተመርቆ ከወጣ በኋላ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚሳተፍበትን ደረጃ በማሳካት ክብረወሰን እስከማስመዝገብ ነው፡፡ በ46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በከፍታ ዝላይ 1.95 ሜትር በማስመዝገብ  የብር ሜዳሊያ ያገኘው ማልጎኝ፤ በከፍታ ዝላይ የኢትዮጵያ ሪከርድ የሆነው 2.07 ሜትር እና በዓለም አቀፍ ውድድር ለመካፈል የሚያበቃው ሚኒማ ደግሞ 2.10 ሜትር መሆኑን ጠቅሶ በማዕከሉ ባሳለፈው የሁለት ዓመት ቆይታ 1.95 ሜትር መዝለሉ ወደ እነዚህ የውጤት ደረጃዎች የሚደርስበትን ሁኔታ የሚጨበጥ እንዳደረገውም ተናግሯል፡፡  ከ4 ዓመታት በኋላ ከማዕከሉ ተመርቆ ሲወጣ አገሩን በዓለም አቀፍ መድረክ መወከል እንደሚችል ምናልባትም በከፍታ ዝላይ የዓለም ክብረወሰንን ለመስበር  እንደሚችል እርግጠኛ እየሆነ መጥቷል፡፡
አሰልጣኝ ንጉሴና ሙያቸውን የማሳደግ ጥያቄያቸው
አሰልጣኝ ንጉሴ አደሬ በማዕከሉ የአጭርና መካከለኛ ርቀት  እንዲሁም የሜዳ ላይ ስፖርቶች አሰልጣኝ ሆነው  እያገለገሉ ናቸው፡፡  በሜዳ ላይ ስፖርቶች  እንዲሁም በአጭርና በመካከለኛ ርቀት ቀድሞ ከነበሩት የተሻሉ ስፖርተኞችን ማዕከሉ በማውጣት  እየተሳካለት መሆኑን ለስፖርት አድማስ የተናገሩት አሰልጣኙ፤ በስራቸው የሚከተሏቸው የስልጠና ሂደቶች  የሙያ ብቃታቸውን  በሚያሳድጉበት አቅጣጫ እየወሰዳቸው መሆኑን ይመሰክራሉ።  ከኮተቤ የመምህራን ማሰልጠኛ በስፖርት ሳይንስ ተመርቀው ከዚያ በአሰልጣኝነት ሙያቸው በማገልገል ከ15 ዓመታት በላይ እንደሆናቸው፤ ከጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማዕከል በፊት በኦሮሚያ ክልል እና በለገጣፎ የአትሌቲክስ ቡድኖች በሙሉ ሃላፊነት የሰሩበትም ልምድ እንዳላቸው ፤ በ800፣ በ1500 ሜትር በዝላይ እና በውርወራ ያሰለጠኗቸው ስፖርተኞች በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድር በመሳተፍም እንደተሳካላቸው አሰልጣኝ ንጉሤ አደሬ ይናገራሉ፡፡ በተለይ በኦል አፍሪካን ጌምስ እንዲሁም በዓለም ወጣቶች ኦሎምፒክ በቻይና ናይጂንግ 2015 ላይ ዋና አሰልጣኝ ሆነው በመስራት አመርቂ ውጤት አግኝተዋል፡፡
በአትሌቲክስ ስፖርት አሰልጣኝነት የሶስተኛ ደረጃ 3 ሰርተፍኬት አለኝ የሚሉት አሰልጣኝ ንጉሴ ግን በማዕከሉ ቆይታቸው የብቃት ደረጃቸውን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ስልጠናዎች የሚያሳድጉበት እድል እንዲፈጥርላቸው ይጠይቃሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ ሆኖ ለመስራት   ደረጃ 4 የአሰልጣኝነት ማዕረግ ማግኘት ይኖርብኛል በማለት  ለስፖርት አድማስ የተናገሩት አሰልጣኝ ንጉሴ፤  ለዚህ አይነት የአሰልጣኝነት ደረጃ በመብቃት የተሻለ ለመስራት አቅም እንዳላቸው ለማስገንዘብ በማዕከሉ በሚገኝ ቢሯቸው ተገኝተን ስራቸውን እንድንታዘብ አድርገው ነበር።  በርግጥም የአሰልጣኝ ንጉሴ አደሬን ቢሮ ለጎበኘ  በአጭርና በመካከለኛ ርቀት እንዲሁም በሌሎች የሜዳ ላይ ስፖርቶች በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ጉልህ ለውጥ ለማምጣት እየሰሩ እንደሆነና ስኬታማ ለመሆን ፍላጎት እንዳላቸው ለመረዳት አይቸገርም፡፡ የሰልጣኞቻቸውን የልምምድ ፕሮግራሞች፣ የውጤት ታሪክና የመሻሻል ሂደቶች በየዕለቱ እየመዘገቡ በአጀንዳቸው ያሰፍራሉ። በቢሯቸው በተለያዩ ቦታዎች በተቀመጡ ቦርዶችና ግድግዳዎች ላይ የተለያዩ ቻርቶች፣ ግራፎች እና ሌሎች  አሀዛዊ መረጃዎች ለጥፈዋል፡፡ ተገቢውን የሙያ ማሻሻያ  የሚያገኙ ከሆነ ያለጥርጥር በኢትዮጵያ አትሌቲክስ በአጭርና መካከለኛ ርቀት፣ እንዲሁም በሜዳ ላይ ስፖርቶች የላቁ ውጤቶችን እንደሚያስመዘግቡ በልበ ሙሉነት መመስከር ይቻላል፡፡
በተለይ ከስልጠና ስራቸው ጎን ለጎን ከአሰላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በአትሌቶች አመጋገብ ላይ ልዩ ጥናትና ምርምር እያደረጉ መሆናቸውም የሙያ ማሳደግ ጥያቄያቸውን ተገቢነት የሚያመለክት አብይ ማስረጃ ነው፡፡ አትሌቶች የተጠና የአመጋገብ ስርአት እንዲኖራቸው ለማስቻል ነው፡፡
ይቀጥላል

  የቻይና የጠፈር ተመራማሪዎች በቀጣዩ አመት ወደ ጨረቃ በሚያደርጉት ቼንጅ ፎር የተባለ የጠፈር ምርምር ተልዕኮ፣ በጨረቃ ላይ ድንች ለማብቀል ማቀዳቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ተመራማሪዎቹ ዕጽዋትና ነፍሳት በጠፈር ላይ መራባት የሚችሉበትን ዕድል ለመፍጠር የሚያደርጉት ምርምር አካል ነው በተባለው በዚህ ዕቅድ፤ በምርምሩ የሚገኙ ውጤቶች የሰዎችን በጠፈር ላይ የመኖር ዕድል ለመፍጠር ለሚከናወኑ ስራዎች በግብዓትነት እንደሚያገለግሉ ተነግሯል፡፡
በ2015 ለእይታ በበቃው ዘ ማርቴን የተሰኘ የሳይንስ ፊክሽን ፊልም ላይ ማርስ ውስጥ ብቻውን የቀረን አንድ ገጸባህሪ ወክሎ የሚጫወተው ታዋቂው የፊልም ተዋናይ ማት ዴመን፣ ህይወቱን ለማዳን የድንች ማሳ ሲያዘጋጅ እንደሚታይም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Page 1 of 340