Administrator

Administrator

ታዋቂው ፎርብስ መጽሔት በአጠቃላይ ዕድገትና በትርፋማነት አለምን ይመራሉ ያላቸውን የ2017 ቀዳሚ ኩባንያዎች ዝርዝር ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ዳማክ ፕሮፐርቲስ የተባለው የተባበሩት አረብ ኤሜሪትስ የሪልስቴት ኩባንያ የአንደኛነት ደረጃን ይዟል፡፡ፎርብስ የኩባንያዎችን የሽያጭ፣ የትርፍ፣ የሃብት መጠንና የገበያ ዋጋ መሰረት በማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ባደረገው በዚህ የቀዳሚ ባለዕድገት ኩባንያዎች ደረጀ ዝርዝር 1ኛ ደረጃን የያዘውና በ2016 የ1.9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘው ዳማክ ፕሮፐርቲስ፣ በመላው መካከለኛው ምስራቅ ሰፋፊየግንባታ ፕሮጀክቶችን እንደሚሰራ ተነግሯል።
መርሴድስ ቤንዝን ጨምሮ ከ50 በላይ የተለያዩ ውድ መኪኖችን በማከፋፈል የሚታወቀውና በ2016 28.03 ሚሊዮን መኪኖችን በመሸጥ ከፍተኛ ገቢ ያገኘው የቻይና ግዙፉ የመኪና አከፋፋይ፣ ቻይና ግራንድ አውቶሞቲቭ ሰርቪስስ፣ በፎርብስ ዝርዝር የ2ኛነት ደረጃን ይዟል፡፡በሪልስቴት ዘርፍ የተሰማሩት ግሪንላንድ ሆልዲንግስ እና ሜልኮ ኢንተርናሽናል የ3ኛ እና የ4ኛ ደረጃን ሲይዙ፣ ሸቀጣሸቀጦችን ለተጠቃሚዎች በማድረስ ዘርፍ የተሰማራው ኤስኤፍ ሆልዲንግስ የተባለ ኩባንያ በበኩሉ፣ 5ኛው የአለማችን ቀዳሚ የእድገት ገስጋሽ ኩባንያ ሆኗል፡፡ፎርብስ ከዚህ በተጨማሪም በዓመቱ እጅግ ከፍተኛ ከበሬታንና ታማኝነትን ያገኙ የዓለማችን ኩባንያዎች ደረጃ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ 351 ሺህ ሰራተኞችን ቀጥሮ የሚያሰራውና በ2016 ዓ.ም የ90 ቢሊዮን ዶላር ሽያጭ አስመዝግቦ፣ 6.4 ቢሊዮን ዶላር ያተረፈው  የጀርመኑ ሲመንስ ኩባንያ

ቀዳሚነቱን ይዟል፡፡
የፈረንሳዩ የጎማ አምራች ሚሼሊን ግሩፕ እና አልፋቤት ጎግል ከፍተኛ ተአማኒነትን በማግኘት ከዓለማችን ኩባንያዎች ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን

መያዛቸውን የገለጸው ፎርብስ፤ የጃፓኑ ኒንቲዶ አራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ጠቁሟል፡፡

 የመከላከያ ሠራዊት ግጭቱን ሙሉ በሙሉ እንዲያስቆም ተጠየቀ

     ሰማያዊ ፓርቲ እና የመላ ኢትዮጵያዊያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፤ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢ የተፈጠረውን ግጭት፣ አጣሪ ኮሚቴ ልከው ማጣራታቸውን ያስታወቁ ሲሆን ግጭቱን ያባባሰው የአንድ ባለሀብት መገደል ነው ብለዋል፡፡ መንግስት በበኩሉ፤ በፓርቲዎቹ ሪፖርት ላይ አስተያየት መስጠት አልችልም ብሏል፡፡
ሁለቱ ፓርቲዎች የሁኔታውን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ አጣሪ ኮሚቴ ወደ ግጭቱ አካባቢ ልከው ጉዳዩን  ማጣራታቸውን፣በዚህም ግጭቱ ወደ ከፋ ደረጃ እስኪሸጋገር ድረስ የፀጥታ ኃይሎች ጣልቃ ገብተው የማረጋጋት ስራ አለመስራታቸውን ማረጋገጣቸውንም ሰሞኑን ባቀረቡት ሪፖርት አስታውቀዋል፡፡
ግጭቱ ከመስከረም 2 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በዋናነት የተባባሰበት ምክንያት በምስራቅ ሃረርጌ አወዳይ ከተማ፣አንድ የሶማሌ ተወላጅ ባለሀብት ላይ ግድያ ከተፈጸመ በኋላ መሆኑን የጠቆመው አጣሪ ኮሚቴው፤ ይህን ተከትሎ በከተማዋ በተነሳው ብጥብጥም፣በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ቤታቸውን ማቃጠል፣ ንብረታቸውን መዝረፍና ግድያ መፈፀሙን ተረድቻለሁ ብሏል፡፡
በዚህ አላስፈላጊ ግጭት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች፤ በቂ ምግብና አልባሳት፣ እንዲሁም  የመኝታ ፍራሽ እንደማያገኙ፣ በዚህም የተነሳ በባዶ መጋዘን በደረቅ ወለል ላይ እንደሚተኙ አጣሪ ኮሚቴው ማረጋገጡን የገለፁት ፓርቲዎቹ፤ በምግብና በንፁህ ውሃ እጥረት የተነሳ ህፃናት ለተቅማጥ በሽታ መዳረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡  
መንግስት ለደረሰው ሰብአዊ ውድመት ተጠያቂ መሆኑን በመግለጫቸው ያስታወቁት ፓርቲዎቹ፤ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ፣ለሞቱት ቤተሰቦች የሞራል ካሣ እንዲከፍልና ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው ወገኖች፣ በአፋጣኝ መቋቋሚያ ሰጥቶ፣ ወደተረጋጋ ኑሮአቸው እንዲመለሱ ጠይቀዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊትም ግጭቱን በአስተማማኝ ደረጃ እንዲያስቆም በመጠየቅ፣ ለወደፊትም ይህ ዓይነቱ የዜጎችን መብት የሚጥስ ድርጊት እንዳይደገም  ጥሪ አቅርበዋል - ፓርቲዎቹ፡፡
እያንዳንዱ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊና ዓለም አቀፍ ግብረሠናይ ድርጅቶች፣የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ለማቋቋም የበኩላቸው ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን ያሉት ፓርቲዎቹ፤ በእነሱ በኩልም ድጋፍ የሚጠይቁ ደብዳቤዎችን ለተመረጡ አካላት ለማሰራጨት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ለተጎጂዎች እርዳታ የሚሰባሰብበትን የባንክ ሂሳብ ቁጥርም በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል፡፡
ፓርቲዎቹ በግጭቱ ላይ አደረግነው ባሉት ማጣራት ላይ ተመስርተው ያወጡትን  ሪፖርት በተመለከተ ከአዲስ አድማስ አስተያየት የተጠየቁት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፤ “ሪፖርቱ ባልደረሰን ሁኔታ የመንግስትን አቋም ለመግለፅ እቸገራለሁ” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ፤ የግጭቱን መንስኤና ጉዳት አስመልክቶ ያጠናቀረውን የምርመራ ሪፖርት በዚህ ወር ያቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን የፌደራል መንግስቱም በዋናነት ይሄን ሪፖርት እየተጠባበቀ መሆኑን በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡

 “የክልሉን ህዝቦች አንድነት ለማበላሸት የተወጠነ ሴራ ነው”

      ሰሞኑን በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች በተቀሰቀሰው ተቃውሞ  የ8 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን የገለጸው የክልሉ መንግስት፤የተቃውሞ እንቅስቃሴው እየተጠናከረ የመጣውን የክልሉን ህዝቦች አንድነት ለማበላሸት የተወጠነ ሴራ ነው ብሏል፡፡   
ባለፈው ረቡዕ  በአምቦ፣ ወሊሶ፣ ሻሸመኔ፣ ዶዶላ፣ ሃረር - ጨለንቆና በኬ ከተሞች ተቃውሞ የተደረገ ሲሆን ከ20 ሺህ በላይ ህዝብ ተሳትፎበታል ሲሉ የአይን እማኞች በገለፁት የሻሸመኔው የተቃውሞ እንቅስቃሴ የ5 ሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ መንግስት አስታውቋል፡፡  
በተጨማሪም በምዕራብ ሃረርጌ ዞን ቦኬ ወረዳ በተካሄደ ሰልፍ ላይም የ3 ሰዎች ህይወት ማለፉን የገለጸው  የክልሉ መንግስት፤ አጥፊዎችን ተከታትዬ ለህግ አቀርባለሁ ብሏል፡፡
ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ደግሞ በወሊሶና በአምቦ ከተሞች ተቃውሞ አይሎ መስተዋሉን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በተቃውሞ  ሰልፎቹ ላይ በስፋት ከተደመጡ መፈክሮች መካከልም፤ “አቶ ለማ መገርሳ ፕሬዚዳንታችን ነው፤ ከጎኑ እንቆማለን!”፣ “የታሰሩ የኦፌኮ አመራሮች ዶ/ር መረራ እና በቀለ ገርባ ይፈቱ”፣ “የወገኖቻችን መፈናቀል ይቁም!” የሚሉና የመንግስት ለውጥን የሚጠይቁ ይገኙበታል ብለዋል፤ ምንጮች፡፡
በአምቦ የተካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሳታፊ ብዛት የላቁ ናቸው የሚሉት ምንጮች፤ ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ መላው የከተማዋ ነዋሪዎች የተሳተፉበት ነው የሚመስለው ብለዋል፡፡
በሰሞኑ የኦሮሚያ ከተሞች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የኦህዴድ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የክልሉ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብይ አህመድ፤ በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግስት እየሰራ ያለው ስራ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ እንዲሁም አንድነትን እያጠናከረ መምጣቱን ጠቁመው፣ “አፍራሽ ኃይሎች” ለኦሮሞ ህዝብ ጥቅም የቆሙ በማስመሰል፣ ወጣቱን በስሜት አነሳስተው፣ ሰላማዊ ሰልፍ በመጥራት የተጀመሩ ስራዎችን ለማክሸፍ እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል፡፡ ህዝቡ የእነዚህን አካላት ጥሪ እንዳይቀበልም ዶ/ር አብይ ጠይቀዋል፡፡
የተቃውሞ እንቅስቃሴዊቹ በተደረጉበት ወቅት የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ያለጦር መሳሪያ ህዝቡን ወደየቤቱ እንዲመለስ ሲመክሩና ሲያግባቡ መታየታቸውን ጉዳዩን አስመልክቶ ለቪኦኤ መረጃ የሰጡ የአይን እማኞች አስረድተዋል፡፡
በሻሸመኔ እና በበኬ ከደረሰው የሞት አደጋ በስተቀር በሌሎቹ ከተሞች የተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች በሰላም መጠናቀቃቸውን የየአካባው ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

 የቅማንት ህዝበ ውሣኔ ከተደረገባቸው 8 ቀበሌያት መካከል በ7ቱ፣በነባሩ አስተዳደር እንቀጥላለን የሚለው አብላጫውን ድምጽ ሲይዝ፣በአንድ ቀበሌ ደግሞ በቅማንት አስተዳደር ስር የሚለው አብላጫ ድምፅ ማግኘቱን የምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡
ህዝበ ውሣኔውን አስመልክቶ ሪፖርታቸውን ለፌደሬሽን ም/ቤት ያቀረቡት የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፀሃፊና የፅ/ቤቱ ሃላፊ አቶ ነጋ ዲፊሣ፤ በጭልጋ ወረዳ ስር የምትገኘው “የኳበር ሎምዬ” ቀበሌ ላይ የተደረገው ህዝብ ውሣኔ፣ በቅማንት አስተዳደር ስር እንካለል የሚለው አብላጫ ድምፅ በማግኘቱ፣ ቀበሌው በቅማንት አስተዳደር ስር እንደምትካለል ያረጋገጡ ሲሆን ቀሪዎቹ ሠባት ቀበሌዎች በነባሩ አስተዳደር ስር ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
ህዝበ ውሣኔ ገና ያልተካሄደባቸው ቀሪ አራት ቀበሌዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፤ የአማራ ክልል አስተዳደር በጉዳዩ ላይ ከቀበሌዎቹ ህዝብ ጋር ውይይት አካሂዶ ሲያጠናቅቅና ህዝበ ውሳኔው እንዲካሄድ የክልሉ አስተዳደር ለፌዴሬሽን ም/ቤት ጥያቄ ሲያቀርብ የሚፈፀም መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በስምንቱ (8) ቀበሌያት በተካሄደው ህዝበ ውሣኔ ድምፅ ለመስጠት ከተመዘገበው 23 ሺህ 283 መራጭ መካከል 89 በመቶው ወይም 20 ሺህ 824 ነዋሪዎች ድምፅ መስጠታቸውን በአቶ ነጋ ሪፖርት ላይ ተጠቁሟል፡፡ ከምርጫ ቦርድ በዚህ መልኩ የቀረበለትን ሪፖርት የገመገመው የፌዴሬሽን ም/ቤትም ውጤቱን አፅድቆታል፡፡

ኢቴል አድቨርታይዚንግና ኮሙኒኬሽን ከቱርኩ መንግስታዊ ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው “8ኛው አዲስ ቢዩልድ ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን የንግድ ትርዒት” ትናንት በሚሊኒየም አዳራሽ የተከፈተ ሲሆን እስከ ሰኞ እንደሚቆይ ታውቋል፡፡
የአዘጋጅ ድርጅቱ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ወ/ሮ ሃይማኖት ተስፋዬ ባለፈው ማክሰኞ በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ “የኮንስትራክሽን መሳሪያዎችና ቴክኖሎጂዎች” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው  የንግድ ትርዒት ዓላማ፤ የኮንስትራክሽን መሳሪያዎችና
ቴክኖሎጂዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የደረሱበትን ደረጃ በዘርፉ ለተሰማሩ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች በማስተዋወቅ፣ አምራችና ገዢን ማገናኘት ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ኤግዚቢሽን ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ12 አገሮች ማለትም፣ ከቱርክ ከጀርመን፣ ከኢጣሊያ፣ ከቤልጂየም፣
ከቻይና፣ ከቱኒዚያ፣ ከሳዑዲ ዐረቢያ፣ ከተባበሩት ዐረብ ኢመሬትስ፣ ከቡልጋሪያና ከአሜሪካ የተውጣጡ 125 ድርጅቶች፣ አገሮቻቸው የደረሱበትን የመጨረሻ ቴክኖሎጂ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡

  የምድር አውሬ ሁሉ መሰብሰቢያና መናገጃ አንድ ገበያ ነበር ይባላል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አውሬ ሁሉ እገበያ ሲውል አያ ጅቦ ግን ሳይሄድ ቀረ፡፡ የማታ ማታ ገበያተኛ ሲመለስ ከጎሬው ወጣና ከመንገድ ዳር ተቀመጠ፡፡ ገበያ ምላሽ ሲሆን እንኮዬ ዝንጆሮ ስትመጣ፣ የገበያውን አዋዋል ጠየቃት፡፡ እንደምትቸኩል ነግራው፣ ጦጢትን ጠይቃት አለችው፡፡ ጦጢትን ጠየቃት፡፡ እሷም፤ እንኮዬ ሚዳቋን ጠይቅ ብላው ሄደች፡፡ ሚዳቆን ጠየቃት፡፡ እቸኩላለሁ፤ እንኮዬ አህዪትን ጠይቃት አለችው፡፡
በመጨረሻው አህዪት መጣች፡፡ ገበያው እንዴት ዋለ? አላት፡፡ “ቆይ ቁጭ ብዬ ላጫውትህ!” ብላ ተቀመጠች፡፡ ሁሉን ካወራችለት በኋላ፤ “እንደኔ ይሄን ገደል እመር ብለሽ ማለፍ ትችያለሽ?” አለና ጠየቃት፡፡
“አሳምሬ!” አለችው፡፡
አጅሬ የሞት ሞቱን እንጣጥ ብሎ ዘለለው፡፡ አህዪት ግን እዘላለሁ ብላ ወርዳ ተከሰከሰች፡፡ አያ ጅቦ ሆዬ፤ ታች ወርዶ ሆዷን ዘንጥፎ ይበላ ጀመር፡፡ ይሄኔ ውሻ ከአፋፍ ብቅ አለች፡፡ ስታስተውል አበላሉ አስጎመዠትና፣ ምራቋ ጠብ ጠብ ሲል አናቱ ላይ አረፈ፡፡፡ ቀና ብሎ ቢያይ፤ ውሺት አለች፡፡
“በይ ነይ ውረጂና እየመተርሺ አብይኝ” አላት፡፡
“እሺ ጌታዬ” ብላ ወርዳ እየመተረች ስታበላው ቆይታ፤ አያ ጅቦ ዞር ሲልላት የአህዪትን ልብ ዋጥ ስልቅጥ አደረገችው፡፡ ጅቦ መለስ ብሎ ቢያይ ልቧን አጣው፡፡
ውሾን፤
“ልቧ ወዴት ሔደ?” ብሎ ጠየቃት፡፡
“ልብ ባይኖራት ነው እንጂ ልብማ ካላት አንተ ዘንድ መጥታ መቼ ትቀመጥ ነበር?” አለችው፡፡
አያ ጅቦ ግን፤ “ቅድም አይቼው ነበር፡፡ ታመጪ እንደሆን አምጪ፡፡ አለበለዚያ፤ አንቺንም እበላሻለሁ” አላት፡፡
“ምነው አያ ጅቦ፤ እኔን በቅቤና በድልህ አጣፍጠህ ነው እንጂ፣ እንደ አህዪት ደረቁን ትበላኛለህ?” አለችው። ሆዳሜ ዕውነት መሰለውና፤
“ቅቤውና ድልሁ ከየት ይመጣል?” አለና ጠየቃት፡፡
“ከእመቤቴና ከጌታዬ ቤት እኔ ሄጄ አመጣዋለኁ” አለችው፡፡
“ሄደሽ የጠፋሽ እንደሆነ ማ ብዬ እጠራሻለሁ?”
“እንኮዬ ልብ-አጥቼ፤ ብለህ ትጠራኛለህ!”
“በይ እንግዲያውስ ሄደሽ አምጪ” አላት፡፡
“እሺ ታዛዥ ነኝ!” ብላ ሄደች፡፡
ሄደችና ቅርት አለችበት፡፡
“ኧረ እንኮዬ ልብ-አጥቼ” እያለ ተጣራ፡፡
“ከእመቤቴና ከጌታዬ ቤት ለምን ወጥቼ!” ብላ፤ የስድብ ወርጂብኝ አወረደችበት፡፡
ከጊዜ በኋላ ግን ውሺት ስትልከሰከስ፤ አያ ጅቦ ያዛት፡፡ ዐይኗ ፈጠጠ፡፡
አያ ጅቦም “ዐይንሽ በምን እንዲህ አማረ?” አላት፡፡
“ጌታዬ፤ በአሥር የአጋም እሾህ ተነቅሼ ነዋ!” አለችው፡፡
“እባክሽ እኔንም ንቀሺኝ?”
ውሺት፤ አጋም እሾህ ሰብራ አመጣችና ዐይኖቹን ትጠቀጥቃቸው ጀመር፡፡
“ኧረ አመመኝ ውሺት”
“ሲያጌጡ ይመላለጡ ነው! ማማር እንዲያው ይገኝ መሰለህ?”
ብላ ሁለቱንም ዐይኑን አሳወረችው፡፡ ከዚያም ሠንጋ ጥለው፣ በጎድን ተዳቢት የሚደባደቡ ሰዎች ጋ ልውሰድህ ብላ ለገበሬዎች አሳልፋ ሰጥታ አስገደለችው!
*    *    *
“ያሰቡትንና ያቀዱትን ቸል ሳይሉና ሳይታለሉ ከፍፃሜ ማድረስ፣ የአስተዋይ ተግባር ነው፡፡ እኩይ ያልሆነ ጓደኛ መያዝ፣ ነገርን ሳያመዛዝኑና ሳያሰላስሉ ፈጥኖ ማመንና መቀበል የሚያስከትለውንም አለማሰብ፣ ከየዋህነትና ከቂልነት አስቆጥሮ ከጥቃት ያደርሳል፡፡ አታላይ ለጊዜው በመብለጥለጥ ምኞቱን ቢያረካም የፈፀመው ደባ እንደሚደርስበት የጅቡን አወዳደቅ መመልከት ይበቃል፡፡ ከእንስሳትም ውስጥ በአስተዋይነታቸውና በብልህነታቸው የሚመሰገኑ ፍጥረታት ይገኛሉ፡፡ እነሆ ውሻይቱ፤ በዘዴ ከአደጋ ከአመለጠች በኋላ፤ ኃይለኛ የሆነ ጠላቷን አሞኝታ ከሞት አደጋ አድርሳዋለች”፡፡ (ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወ/መስቀል) አቅደን በዕንጥልጥል የተውነው ስንት ጉዳይ ነበረን? የማያዋጣ ጓደኛ ምን ያህል ጊዜ ያዝን? ምን ያህል ደባዎች ተፈፀሙብን? ከዚያስ ምን ያህል ተማርን? እነዚህን ጥያቄዎች ደጋግመን ብንጠይቅ፣ ብዙ ችግሮችን ለማስወገድ እንችላለን!
አብዛኞቹ ግለሰቦች በፓርቲ የፖለቲካ ህይወታቸው የመታለል እጣ ይገጥማቸዋል፡፡ በትልቅነታቸውና ሆይ ሆይ በሚባሉበት ሰዓት፣ ከቶም መውደቅ የሚል ነገር እንዳለ ትዝ አይላቸውም! በታሪክ የነበሩ መሪዎች፣ የፖለቲካ ኃላፊዎች፣ ታላላቅ ሰዎች እንዴት ወደቁ? የእኔስ አካሄድ ምን ይመስላል? አለማለት፤ ቢያንስ የዋህነት ነው! ከታሪክ አለመማር ነገን ለመገመት አለመቻል ነው፡፡ ነገን አለመገመት የራስን ፍፃሜ አለማጤን ነው፡፡ ስለሆነም የድንገቴ አወዳደቅ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ማጣፊያው ያጥራል! በደጉ ሰዓት ያላቆዩዋቸው ጓደኞች፣ በክፉው ሰዓት አይኖሩምና፤ የማታ ማታ አጋዥ ደጋፊ ማግኘት አዳጋች ይሆናል፡፡ ህዝብ የደገፈን ሲመስለን ጥንቃቄ ስለማናደርግና የእኔው ነው ብለን ስለምንኮፈስ ነው! ሲመሽብን ግን በምን ያህል ፍጥነት እንደሚተፉን፣ በምን ያህል ፍጥነትስ ገፍትሮ እንደሚጥለን ሳንገነዘብ ከአደባባይ ሸንጎ እንወገዳለን። የሚገርመው ስንወድቅም ህዝብ ከድቶናል ብለን አለማመናችን ነው!! ከአንገት በላይ ፍቅር ከአንገት በላይ ይቀራል! የህዝብን መሠረተ-ነገር አለማጤን ክፉ ማጥ ውስጥ ይከታል!!
ማንኛውም ነገር ያረጃል፡፡ ያፈጃል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ፍቅርም እንደዚያው ነው፡፡ ትላንት የደምና የመስዋዕትነት ጓዶች የነበሩ ዛሬ በኢኮኖሚ ተፅዕኖ፣ አዳዲስ ወዳጅ በማፍራት፣ ሀቀኛ የነበረው ዓላማ ጊዜውን ጨርሶ በአዳዲስ ህሊናዊና ነባራዊ ሁኔታ ሲዋጥ፤ አሊያም የህዝብ ብሶትና ምሬት መቆሚያ መቀመጪያ ሲያሳጣው ወይም አጠቃላይ ሁኔታው ምቾት ሲነሳንና፤ ከውጪም ከውስጥም ስንወጠር፤ የዱሮው እኛነታችን ያከትማል፡፡ ከጥንት ወዳጆቻችን ጋር በሰላም ከተለያየን እሰየው ነው! በተቃራኒው ሆድና ጀርባ ሆኖ መለያየት ከመጣ ግን ወደማናውቀው ጠብ፣ መጠላለፍ እና መጠፋፋት ደረጃ እንደርሳለን! ከዚህ ይሰውረን!
ከነገራችን ሁሉ እጅግ አሳሳቢ፤ ነግ በእኔን አለማወቃችን ነው!! እኔ የተሻልኩ ስለሆንኩኝ እንደሱ አልወድቅም፣ ማለት ሁሌም እንዳታለለን አለ፡፡ ይልቁንም የወደቀውን ሰው ወንበር መሻማት፣ እሱ ባያውቅበት ነው የሥልጣንን አያያዝ፣ እያሉ፣ እዚያው ገደል ውስጥ መውደቅ የተለመደ ሆኗል! አይጣል ነው! ታማኝነትን ከአድር-ባይነት አለመለየት እርግማን ነው! ዘላቂነትን ከዘልዓለማዊነት ጋር ማምታታት የባሰ መርገምት ነው። “ጓደኛህን ሲያማ ለእኔ ብለህ ስማ!” የሚለውን ተረት አንርሳ፡፡
“ትላንትና ሞቼ፣ ቀረሁ ሳልቀበር
እኔም የፈራሁ፣ ይሄንኑ ነበር!”… የሚለውን ግጥምም ልብ እንበል፡፡ አለመቀደም መልካም ነገር ነው። ቀድሞ መመታት እንዳለ ግን አንዘንጋ! ትላንት አለቃ የነበረው ዛሬ ምንዝር ሲሆን ማላገጡንና መሳለቁን ትተን፣ ይህ ሂደት የት ያደርሰን ይሆን? ብለን እንጠይቅ፡፡ ሁኔታዎች ካልተሻሻሉ፣ ነገሩ ሁሉ እየከፋ ይሄዳል፡፡ ጥንት “ወሎ መሰደድ ልማዱ ነው” ያሉ ባለሥልጣናት፤ እራሳቸው መቀመቅ ወርደዋል፡፡ “ገበያ እንዴት ዋለ?” ቢለው፤ “አንዱ በአንዱ ሲስቅ” የሚለው ተረት ትምህርት ካልሆነን፤ ከምን ልንማር ነው?!

ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ለ2010 የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ በሁለቱም ፆታዎች 10 እጩዎችን ሰሞኑን ይፋ ሲያደርግ በውድድር ዘመኑ በ10ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን የበቃችውና በ2016 የዓለም ኮከብ አትሌት የነበረችው  አልማዝ አያና በሴቶች ምድብ ከአስሩ እጩዎች አንዷ ሆናለች፡፡
አይኤኤኤፍ ሰሞኑን በሁለቱም ፆታዎች ይፋ ያደረገውን የእጩዎች ዝርዝር ከ6 አህጉራት በተውጣጡ የዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ኤክስፐርቶች ፓናል መምረጡን ያስታወቀ ሲሆን በውድድር ዘመኑ በለንደኑ 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በዳይመንድ ሊግ ውድድድሮች ለተመዘገቡ ውጤቶች ትኩረት እንደሰጠ ለመረዳት ይቻላል፡፡
በሴቶች ምድብ ከተያዙት አስር አጩዎች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ አልማዝ አያና በቅርቡ በኢቢሲ የስፖርት ሽልማት የዓመቱ ምርጥ ሴት አትሌት ተብላ እንደተሸለመች የሚታወስ ሲሆን በአይኤኤኤፍ ማህበር የ2017 የአለም ምርጥ አትሌት ምርጫ በእጩነት የቀረበችው በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ እንዲሁም በ5ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ በመጎናፀፏ፤ እንዲሁም በርቀቱ የዓመቱን ፈጣን ሰዓት 30፡16.62 በሆነ ጊዜ በማመዝገቧ ነው፡፡ ዋና ተፎካካሪዎቿ ይሆናሉ ተብለው የተጠበቁት በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በየስፖርት መደባቸው የወርቅ ሜዳልያዎች ያገኙትና የዳይመንድሊግ ሻምፒዮኖቹ ናቸው፡፡
በተለይ በውድድር ዘመኑ በ5ሺ ሜትር የዓመቱን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበችና በምንም ውድድር ያልተሸነፈችው፤ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ እንዲሁም የዳይመንድ ሊግ አሸናፊዋ ሄለን ኦቡሪ ከአልማዝ አያና የኮከብ አትሌትነቱን ክብር ለመንጠቅ ከፍተኛ ግምት ሲሰጣት፤ የደቡብ አፍሪካዋ ካስተር ሴማንያ በ800 ሜትር በውድድር ዘመኑ ባለመሸነፍ፤ የዓለም ሻምፒዮን ሆኖ የወርቅ ሜዳልያ በመውሰድ እና የዳይመንድ ሊግ ዋንጫን በማንሳት እንዲሁም በ1500 ሜትር በዓለም ሻምፒዮና ተጨማሪ የነሐስ ሜዳልያ በመውሰድ ነው፡፡
በከፍታ ዝላይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና የዳይመንድ ሊግ ድርብ አሸናፊ ማሪያ ላሳኢታካኔ፤ በ100 ሜትር መሰናክል የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና የዳይመንድ ሊግ ድርብ አሸናፊ አውስትራሊያዊቷ ሳሊ ፓርሰን፤ በዲስከስ ውርወራ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና የዳይመንድ ሊግ ድርብ አሸናፊ የክሮሽያዋ ሳንድራ ፔርኮቪች፤ በዝርዘመት ዝላይ የዓለም ሻምፒዮን የሆነችው አሜሪካዊቷ ብሪትኔ ሪስ፤ በምርኩዝ ዝላይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና የዳይመንድ ሊግ ድርብ አሸናፊ ግሪካዊቷ ኤካቴሪን ስቴካንዲ፤ በሄፕታተሎን የዓለም ሻምፒዮን የሆነችው ቤልጅማዊቷ ናፊ ሳቱ እንዲሁም በመዶሻ ውርወራ የሚስተካከላት ያጣችው ፖላንዳዊቷ አንቲታ ዋልደርሽዚያክ ሌሎቹ ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡በሌላ በኩል በወንዶች ምድብ በ2017 የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ላይ ከቀረቡት አስር እጩዎች መካከል የአምና አሸናፊ ዩሲያ ቦልት አለመካተቱ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ ዩሴያን ቦልት የሩጫ ዘመኑን ያበቃ በዚሁ የውድድር ዘመን ሲሆን በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ100 ሜትር የነሐስ ሜዳልያ ማግኘቱ ብቻ እንደ ትልቅ ውጤት ቢጠቀስ ነው፡፡በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ፤ በ5ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ ያገኘውና የዳይመንድ ሊግ ያሸነፈው እንግሊዛዊው ሞፋራህ የማሸነፍ እድል ሊኖረው ይችላል፡፡ በከፍታ ዝላይ ሙታዝ ኢሳ ከኳታር፤ በመዶሻ ውርወራ ፓል ፋጄክ ከፖላንድ፤ በምርኩዝ ዝላይ ሳም ኬንድሪክስ ከአሜሪካ፤ በ1500 ሜትር ኤልያህ ማንጎኒ ከኬንያ፤ በርዘመት ዝላይ ሉቮ ማናዮናጋ ከደቡብ አፍሪካ፤ በ110 መሰናክል ኦማር ኤምሲሎይድ ከጃማይካ፤ በስሉስ ዝላይ ክሪስትያን ቴይለር አከሜሪካ፤ በ400 ሜትር ዋይደን ቫን ኒኪሪክ ከደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በጦር ውርወራ ጆሃነስ ቬተር ከጀርመን ሌሎቹ እጩ ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በድረገፁ እንዳመለከተው ከ6 ሳምንታት በኋላ በ2017 ኮከብ አትሌትነት የሚመረጡ አሸናፊዎችን ለመሸለም በመጀመርያ በሚቀጥሉት 9 ቀናት አስሩን እጩዎች ወደ 3 እጩዎች ለመለየት በሶስት የዓለም አትሌቲክስ ባለድረሻ አካላት ድምጽ ይሰበሰባል። የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማህበር ምክር ቤት 50 በመቶ እንዲሁም የአይኤኤኤፍ ቤተሰቦች የሚባሉት አባል ፌዴሬሽኖችና የተለያዩ ኮሚቴዎች አባላት 25 በመቶ የድምፅ ምርሻ በመያ የሚሰጡትን ድምፅ በኢሜል የሚያቀርቡ ሲሆን የዓለም አትሌቲክስ አድናቂዎች እና የአትሌቶች ደጋፊዎች ደግሞ በቀሪው 25 በመቶ የድምፅ ድርሻ በአይኤኤኤፍ ድረገፅ www.iaaf.org እንዲሁም ለእያንዳንዱ አስር እጩዎች በአይኤኤኤፍ ዎርልድ አትሌቲክስ ክለብ www.facebook.com/WorldAthleticsClub/ በተከፈቱ የኢንተርኔት ማህበረሰብ ገፆች ላይ በመስጠት ይሳተፉበታል።  በሶሻል ሚዲያዎቹ ላይ በፌስቡክ የየእጩዎቹን ልዩ ገፅ ላይክ በማድረግ በትዊተር ገፅ መልሶ ሪቲዊት በማድረግ ድምፅ ይሰጣል ማለት ነው፡፡
ባለፈው ዓመት በተካሄደው 29ኛው የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ የዓለም ኮከብ አትሌት ሽልማት ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አልማዝ አያና በሴቶች ምድብ ማሸነፏ የሚታወስ ሲሆን  በሽልማቱ ታሪክ 6ኛውን ክብር ለኢትዮጵያ  ያስገኘችበት ነበር። በ1998 እኤአ ኃይሌ ገብረስላሴ፤ በ2004እና በ2005 እኤአ ለሁለት ተከታታይ ጊዚያት ቀነኒሳ በቀለ፤ በ2007 እኤአ መሰረት ደፋር እንዲሁም በ2015 እኤአ ገንዘቤ ዲባባ የዓለም ኮከብ አትሌት የተባሉ የኢትዮጵያ አትሌቶች ናቸው፡፡ አልማዝ አያና በ30ኛው የዓለም ኮከብ አትሌት ሽልማት በድጋሚ ከተመረጠች በሽልማቱ ታሪክ ሁለት ጊዜ ያሸነፈች  ብቸኛዋ ሴት እንዲሁም 7ኛዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት ትሆናለች፡፡
በ2016 የአይኤኤኤፍ የዓለም ኮከብ አትሌት ምርጫ ላይ በሴቶች ምድብ አልማዝ አያና ያሸነፈችው በ31ኛው ኦሎምፒያድ በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ስትጎናፀፍ የዓለም እና የኦሎምፒክ ሪከርድ በማስመዝገቧ፤  በተጨማሪ በ5ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳልያ በማግኘቷ እንዲሁም  በ2016 የአይኤኤኤፍ ዳይመንድ ሊግ ደግሞ በ3ሺ እና 5ሺ ሜትር 4 ውድድሮች አድርጋ በሰበሰበችው 50 ነጥብ የዳይመንድ ሊግ ዋንጫ እና የ43ሺ ዶላር ተሸላሚ ለመሆንም በመብቃቷ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ የግልም ሆነ የመንግስት… አንድም ሆስፒታል ደረጃውን መቶ በመቶ ባሙዋላ መልኩ የተደራጀ አይደለም፡፡
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በወጣው እትም የህክምና ባለሙያዎች የህግ ተጠያቂነት በአለም አቀፍ ደረጃ ምን መልክ አለው? በአገራችንስ? የሚሉትን ነጥቦች ለንባብ ብለናል፡፡ በዚህ ዙሪያ የሚነሱ የመጨረሻ ሀሳቦችን ከህግ ከባለሙያው አቶ አበበ አሳመረ ማብራሪያ እናገኛለን። በኢትዮጵያ በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ በኩል የሚደርሱ ችግሮች ይህን ይመስላሉ የሚል ጥናት ባይኖርም የደረሱ ችግሮች ግን የሉም ማለት አይደለም።  ባለፉት ሁለት ሳምንታት የወጣውን እትም ያነበቡ የአንድ ቤተሰብ አባል በልጃቸው ላይ የደረሰውን ገጠመኝ በጽሁፍ ልከውልናል፡፡ እንደሚከተለው ነው፡፡  
‹…ሁኔታው ያጋጠመው በቅርብ ነው፡፡ ነሐሴ 2009/ ዓ/ም፡፡ ሕጻኑ በእድሜው 10/አመት ነው፡፡ ክስተቱ ሲያጋጥም ለእረፍት ከአያቱ ቤት ሰሚት ከሚባለው ስፍራ ነበረ፡፡ ከአባቱ እናት ጋር ሆኖ የፍልሰታን ጾም እየጾም ቁርባን ይቆርባል፡፡ አንድ ቀን ግን ያልታሰበ ሁኔታ ያጋጥ ማል፡፡ በድንገት ልጁ ታመምኩ አለ፡፡ ትኩሳት መድከም የመሳሰሉት ነገሮች ይታዩበታል፡፡ ቀረብ ወደሚለው ሐኪም ቤት ይወስዱታል፡፡ ከሐኪም ቤቱም የተገኘው መልስ የጨጉዋራ ሕመም መሆኑንና የሚመገበውን እና የማይመገበውን ምግብ ነግረው የጨጉዋራ መድሀኒት ይሰጡታል፡፡ ይህ ሕጻን እውን የጨጉዋራ በሽታ ያዘው? እንዴት? እየተባለ በቤተሰብ ውስጥ ሀሳቡ እየተንገዋለለ እሱም ህመሙ ምንም ሳይሻለው እንዲያውም እየባሰበት ሁለት ቀን አደረ፡፡ በሶስተኛው ቀን ግን ልጁ ምንም አይንቀሳቀስም፡፡ ዛለ፡፡ አይናገርም፡፡ ትኩሳቱ እጅግ ከፍ ብሎአል፡፡ እንደገና ወደሌላ ሐኪም ቤት ተወሰደ፡፡ የተገኘው መልስ እጅግ አስደንጋጭ ነበር። ትርፍ አንጀቱ በጊዜው ሕክምና ስላላገኘ ፈንድቶአል (rupture) አድርጎአል የሚባል ነበር፡፡ ቤተሰብ በሙሉ ተደናገጠ። ሐኪሞቹም እጅግ አዘኑ፡፡ ነገር ግን መሞቱ ካልቀረ ይከፈትና ይሞከር ተብሎ ከሁለት ሰአት በላይ የፈጀ ኦፕራሲዮን ተደርጎ አሁን ደህና ነው፡፡ ከመሞትም ተርፎአል፡፡ ለዚህ ጉዳይ ተጠያቂው ማነው? በሚል ሀሳቡን ለተለያዩ ሐኪሞች  አንስተን ነበር፡፡ የሐኪሞቹ መልስ ግን አስገራሚ ነበር፡፡
ግማሾቹ …በእርግጥ የጨጉዋራና የትርፍ አንጀት ሕመም ስሜት ይመሳሰላል፡፡ ለዚህም ነው ሐኪሙ ጨጉዋራ ነው ያለው አሉ፡፡
ሌሎቹ ደግሞ…ልጁ ሕጻን ስለሆነና በትክክል ስሜቱን መግለጽ ስለማይችል ሐኪሙ ሊሳሳት ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የሚያጋጥም ነገር ነው የሚል ነበር መልሳቸው፡፡
አልፎ አልፎ ግን አ..አ…ይ፡፡ ቢሆንም …ሐኪሙ  አስቀድሞ ከመወሰኑ በፊት መጠራጠርና በተገቢው መንገድ ምርመራ እንዲካሄድ ማድረግ ነበረበት ያሉም አሉ፡፡
እንግዲህ በእንዲህ ያለው አጋጣሚ እድል ካልቀናና ተገቢው ሐኪም ካልተገኘ የስንት ሰው ሕይወት እንደሚቀጠፍ መገመት ይቻላል፡፡ የህክምና ስህተት ማለት እንደሌሎች የስራ ዘርፎች ስህተት በቀላሉ ሊተካ ወይንም ሊታረም የማይችል የሰው ሕይወት ጉዳይ ነው። የአንድ ሰው ሕይወት ካለፈ በሌላ ሊተካ አይችልም። ሐኪሙ ቢከሰስ ቢወቀስ እንኩዋን ያ ያለፈ ሕይወት ሊመለስ አይችልም፡፡ አበቃ፡፡ ስለዚህ ይህ ነገር በደንብ ቢታሰብበት ጥሩ ይመስለኛል፡፡ የህክምና ባለ ሙያው በደንብ እውቀቱን ቢያደረጅ እንዲሁም አገልግሎት መስጫ ተቋማቱ በደንብ ቢጠናከሩ እና የአሰራር ዘዴያቸው ግልጽ እንዲሆን አስቀድሞ መሰራት ያለበት ነገር ቢሰራ ለአገልጋዩም ለተገልጋዩም ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡
የታማሚው አባት
አቶ አበበ አሳመረ እንደሚገልጹት በቅድሚያ የሙያ ኃላፊነት የሚባለውን ነገር ስንመለከት ማስረጃው ተቀባይነት አለው ወይ? ከየት ነው መምጣት ያለበት? ማንነው ይህንን ማስረጃ ለመስጠት በሕግ ስልጣን ያለው? …ወዘተ የሚል የማስረጃ ሕግ ስለሌለን ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር እያየ ማስረጃ እየመዘነ ውሳኔ እየሰጠ ይገኛል፡፡ ወደፊት ግን መጀመር ያለበት አሰራር አለ፡፡ …ለምሳሌ በሌሎች አገሮች የሙያ ማህበራት አንዱ ሚናቸውና ኃላፊነታቸው የሙያ ኃላፊነት ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎችን ማስተቸት ነው፡፡ ይህም …
በስራ ላይ ያለው ሕግ የጎደለው ነገር ካለ እንዲመለከቱትና እንዲሻሻል ጥያቄ ለማቅረብ ይረዳል፡፡
የማህበር አባላትን በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ እንዲያገኙና በአሰራራቸው እንዲጠነቀቁ እንዲሁም ትምህርት እንዲያገኙ ለማድረግ ይረዳል፡፡
ፍርድ ቤቶች በተመሳሳይ ጉዳይ የሚቀርብላቸውን የኃላፊነት መጉዋደል በሚመለከት ቀደም ብሎ የተሰራውን ስራ ወይንም የተወሰነውን ውሳኔ ሲያዩ የህጉን አተረጉዋጎም፣ የማስረጃ አሰባሰብ እንዲሁም እንዴት እንደተመዘነ በሚመለከት ሁሉ የተኬደበትን አሰራር ለማጤንና ለማገናዘብ እንዲረዳቸው ያግዛል፡፡
ከሕክምና አገልግሎት ጋር በተያያዘ የህግ ስራ ለሚሰሩ ማንኛቸውም አካላት ፣ለፖሊሲ አውጭዎች አሰራር ይረዳል፡፡
ከዚህ ውጭ ግን ልንመለከተው የሚገባን ነገር አለ ብለዋል አቶ አበበ፡፡ በሕክምና ሙያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዘርፎችም ላይ የመገናኛ ብዙሀን የሚያደርሱት የተጋነነ የመረጃ አሰጣጥ በሙያው የተሰማራውንም ሌላውንም ተገልጋይ እኩል የሚጎዳበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ ያህል የሚከተለውን ገጠመኝ ላስታውስ ብለዋል የህግ ባለሙያው አቶ አበበ አሳመረ፡፡
‹…በአንድ ወቅት ከአንዲት ታካሚ ሆድ ውስጥ የፈሳሽ ማምጠጫው ፋሻ ወይንም ጎዝ ተረሳ፡፡ ወደህግ ሲቀርቡ ሶስቱም ሐኪሞች ጥፋተኛ ነን አሉ፡፡ ነገር ግን አለቃቸው በሰጠችው አስተያየት የባለሙያ እጥረት ፣የተቋማቱ የአደረጃጀት አለመሟላት የመሳሰ ሉት ሁሉ አብረው መታየት እንዳለባቸው ነው፡፡ አንድ ሐኪም መስራት ከሚገባው ሰአት በላይ እንዲሰራ ሲገደድ እንደሰው መድከምና መሳት ሊገጥመው ይችላል፡፡ ይህ ለምን ይደረጋል እንዳይባል …ታካሚው ቁጥሩ ከሐኪሙ በላይ ስለሆነ እና በወቅቱ ካልተሰራለት ሊሞት ስለሚችል ቢያንስ እንደምንም ይታይ የሚል ውሳኔም፣ ስምምነ ትም ተደርጎ ሐኪሙ በቅንነት እንዲያየው የተቻለው ሁሉ ይደረጋል፡፡ በዚህ መሀል አንድ ሐኪም አብዛኛውን ሰው አድኖ ግን አንድ ሰው ቢሞትበት ለፍርድ ከመቅረብ ባሻገርም በመገናኛ ብዙሀን በተጋነነ ሁኔታ ለህዝብ አቅርቦ ማሳጣት ሚዛኑን አያጣም ወይ? በሕግ ከሚችለው በላይ በከበደ መልኩ የሚዳኝና በመገናኛ ብዙሀኑም ብዙ የሚባል ከሆነ አንድ ሐኪም እኔ መስራት የሚገባኝ በቀን ይህን ያህል ታካሚ ማየት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በላይ አልችልም ብሎ ጋዋኑን አስቀምጦ ቢወጣ እስትሬቸር ላይ የሚሞተው ሰው ቁጥር ይጨምራል፡፡ የሚል ነበር፡፡
አቶ አበበ እንደሚሉት አንድ የህክምና አሰጣጥ ስህተት ተፈጠረ ሲባል ነገሩን ከብዙ አቅጣጫ መመልከትና መመርመር ይገባል፡፡ የትጋ ነው ስህተቱ የተፈጠረው? በባለሙያው ግድየለሽነት ወይንም የእውቀት ማነስ ነው? ወይንስ በተቋሙ የአሰራር ዘዴ መበላሸት ነው? …ወዘተ ይህንን ለማረጋገጥ የሰከነ አካሄድን ይጠይቃል፡፡ ካለበለዚያ ግን የህክምና ባለሙያው አስቀድሞውኑም ትምህርቱን ወይንም ሙያውን እንዳይመርጠው እስከማድረግ ድረስ የሚያደርስ የተሳሳተ አካሄድ ሊፈጠር ስለሚችል መጠንቀቅ ይፈልጋል፡፡ እንደ አቶ አበበ ማብራሪያ በኢትዮጵያ የግልም ሆነ የመንግስት አንድም ሆስፒታል ደረጃውን መቶ በመቶ ባሙዋላ መልኩ የተደራጀ አይደለም፡፡
በሌሎች አገሮች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በሕክምና ተቋማት አደረጃጀት አለመስተካከልም ይሁን በባለሙያው አሰራር ስህተት ምክንያት በሚፈጠሩ ስህተቶች የተነሳ በሕክምና ባለሙያውና በታካሚው መካከል የሚፈጠሩ ቅርበቶች ሊሻክሩ ይችላሉ፡፡ ሐኪሙም ሁልጊዜ ኃላፊነትን የሚያስብ ከሆነ በቀጥታ በትክክል ሊያድን የሚችለውን መድሀኒት ከማዘዝ ይልቅ መጠራጠርን በማብዛት በኃላፊነት ላለመጠየቅ ሲባል …ይህ ቢሆንስ…ይህ ባይሆንስ ስለሚል የተለያዩ ላቦራቶሪዎች ውጤት እንዲቀርብለት ማዘዝ የመሳሰሉትን እርምጃዎችን ሊወስድ ይችላል፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ሕመምተኛው አፋጣኝ ውሳኔን እንዳያገኝ …እንዲሁም ለተለያዩ ወጪዎችም ሊዳረግ ይችላል፡፡
አቶ አበበ አሳመረ በማጠቃለያቸው የተናገሩት ‹‹…ሐኪሞች ሳይጨነቁና ሳይፈሩ በራስ በመተማመን የሚሰሩ ከሆነ ተገልጋዩም በደንብ ይጠቀማል፡፡ ስለሆነም በኃላፊነት የሚጠየቁ ባለሙያዎች የሚከፍሉት ካሳ የተጋነነ እና ሕይወትን የሚፈታተን መሆን የለበትም። ሆን ተብሎ የተፈጸመ ጥፋት ካልሆነ በቀር ወደወንጀል ኃላፊነት መውሰድም ባይኖር ጥሩ ነው፡፡ ባጠቃላይም ማህበራቱ ተጠናክረው ሌላው አለም እንደሚንቀሳቀሰው ቢንቀሳቀሱ እንዲሁም በዘርፉ የተለያዩ ጥናቶች ማለትም ከኢንሹራንስ ከሕግ አሰራር የመሳሰሉት ሁሉ መሰረት ተደርገው ጥናቶች ቢካሄዱ በቀጣይ ለሚኖረው አሰራር ይጠቅማል፡፡›› ብለዋል፡፡ 

የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር፣ የአገሪቱ የጦር ሃይል አባላትና ወታደሮች ፌስቡክን ጨምሮ በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች ላይ ፎቶ ግራፋቸውንና ሌሎች ጽሁፎቻቸውን እንዳይለጥፉ የሚከለክል ህግ እያወጣ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ሚኒስቴሩ ይህንን ህግ ለማውጣት ያነሳሳው፣የደህንነትና የመረጃ ማፈትለክ ስጋት እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ ወታደሮቹ የሚለጥፏቸው ፎቶ ግራፎችና ሌሎች ጽሁፎች የት አካባቢና የትኛው የጦር ሰፈር ላይ እንደሚገኙ ለጠላት ሃይል ወታደራዊ መረጃ ሊሰጡ ይችላሉ መባሉን አመልክቷል፡፡ ህጉ ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ ተግባራዊ
ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም የጠቆመው ዘገባው፤ የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴርም በ2015 ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ አብዝተው ማህበራዊ
ድረገጽ በሚጠቀሙ ወታደሮቹ ጉዳይ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገብቶ እንደነበር አስታውሷል፡፡


የኖቤል የሽልማት ተቋም የ2017 የኖቤል አሸናፊዎችን ዝርዝር ከያዝነው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ ይፋ በማድረግ ላይ ሲሆን፣ እስካሁንም የፊዚክስ፣ የኬሚስትሪ፣ የህክምና እና የስነጽሁፍ ዘርፍ ተሸላሚዎች ታውቀዋል፡፡
ተቋሙ ባለፈው ሰኞ ይፋ ባደረገው ቀዳሚው የዓመቱ የኖቤል የህክምና ዘርፍ ተሸላሚዎች ዝርዝር፣ ሰርካዲያን ሪትም በተባለ የዘርፉ ምርምር የላቀ ፈጠራ ያበረከቱት ሶስቱ አሜሪካውያን ተመራማሪዎች፡-  ጄፍሪ ሲ ሃል፣ ማይክል ሮስባሽ እና ማይክል ደብሊው ያንግ አሸናፊዎች መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
ማክሰኞ ዕለት ይፋ የተደረገው የፊዚክስ ዘርፍ ተሸላሚዎች ዝርዝር በበኩሉ፡- ሌዘር ኢንተርፌርኖሜትር ግራቬቲሽናል ዌቭ በተባለው የፊዚክስ መስክ የላቀ የምርምር ውጤት ያበረከቱት ጀርመናዊው ሬነር ዌስ እና አሜሪካውያኑ ተመራማሪዎች ባሪ ሲ ባሪሽ እና ኪፕስ ኤስ ትሮን የዘርፉ አሸናፊዎች እንደሆኑ አስታውቋል፡፡
ሬነር ዌስ የ1 ሚሊዮን ዶላር ሽልማቱን ግማሽ ሲወስድ፣ ሌሎቹ ሁለት ተመራማሪዎች ቀሪውን ገንዘብ እኩል እንደሚካፈሉ ተቋሙ አስታውቋል፡፡
የዓመቱ የኖቤል የኬሚስትሪ ዘርፍ ተሸላሚዎችን ባለፈው ረቡዕ ይፋ ያደረገው ዘ ሮያል ስዊድሽ አካዳሚ ኦፍ ሳይንስስ፣ እጅግ ረቂቅ የሆኑ ደቂቀ አካላትን በከፍተኛ ሁኔታ አጉልቶ የሚያሳይ ማይክሮስኮፕ የፈጠሩትና የባዮ ኬሚስትሪ መስክ ምርምርን ወደላቀ ደረጃ ያሳደገ ነው የተባለለት የዚህ የፈጠራ ውጤት ባለቤቶች የሆኑት ስዊዘርላንዳዊው ጃክ ዶቼት፣ እንግሊዛዊው ሪቻርድ ሄንደርሰን እና አሜሪካዊው ጆኣኪም ፍራንክ የዘርፉ አሸናፊዎች መሆናቸውን አስታውቋል፡፡  
“ዘ ሪሜንስ ኦፍ ዘ ዴይ” እና “ኔቨር ሌት ሚ ጎ” በሚሉት ተወዳጅ ልቦለድ መጽሐፍቱ የሚታወቀው እንግሊዛዊው ደራሲ ኢካዙኦ ሺጉሮ፤ 830 ሺህ የእንግሊዝ ፓውንድ የሚያስገኘው የዘንድሮ የኖቤል የስነ ጽሁፍ ዘርፍ ተሸላሚ መሆኑን ተቋሙ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
እ.ኤ.አ በ1954 በጃፓኗ ናጋሳኪ የተወለደው ደራሲው፣በረቀቀና ጥልቅ ስሜትን በሚጭር አጻጻፉ ዓለማቀፍ ዝናን እንዳተረፈ ያስታወቀው ተቋሙ፤ ሁለቱ ተወዳጅ ስራዎቹ በፊልም መልክ ተሰርተው ለእይታ መብቃታቸውን ተከትሎም ዝናው የበለጠ በዓለም ዙሪያ መናኘቱን አመልክቷል።
የአልፍሬድ ኖቤል መታሰቢያ የሆነው የኢኮኖሚክስ ዘርፍ የ2017 ተሸላሚ በበኩሉ፤ ከነገ በስቲያ ስቶክሆልም ውስጥ በሚከናወን ስነስርዓት በይፋ እንደሚገለጽ ይጠበቃል፡፡