Administrator
“የሚገርም ተሰጥኦ የታደለ ታላቅ አርቲስት”
ከአዘጋጁ፡- የድምፃዊ ኢዮብ መኮንን ድንገተኛ ህልፈትን ተከትሎ በፌስቡክ ላይ ከወጡ በርካታ አስተያየቶች ጥቂቶቹን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ ለባለቤቱ፣ ለቤተሰቡና ለወዳጅ ዘመዶቹ መፅናናትን እንመኛለን፡፡
ከጥቂት አመታት በፊት አንድ የበጎ አድራጎት ትርኢት ላይ ለመሳተፍ፣ ከዘፋኞች ጋር ወደ ደሴ ተጉዤ ነበር፡፡ የተሣፈርንበት አውቶብስ ጉንጫቸውን በጫት አሎሎ በወጠሩ ዘፋኞች ተሞልቷል፡፡ ዘፋኞቹ ሲሻቸው ይተራረባሉ፣ሲሻቸው ይጮሃሉ፣ይጨፍራሉ፡፡ የአውቶብሳችን ሽማግሌ ሹፌር ሳይቀር፣አልፎ አልፎ መሪውን እየለቀቀ በማጨብጨብ፣ በ ‹‹ቅወጣ›› ከዘፋኞች እንዳማያንስ በማሳየት ላይ ነበር፡፡ በጫቱም፣በጭፈራውም የሌለበት ድምጻዊ ኢዮብ መኮንን ብቻ እንደሆነ ተመለከትሁ፡፡ በእርጋታ ተቀምጦ፣ በአውቶብሱ መስኮት አሻግሮ የሚሮጡ የግራር ዛፎችን ይመለከታል፡፡ ልዩነቱ ግልጽ ነበር፡፡
ድሮ ድሮ፣ ኢዮብ መኮንን አቤሴሎም የሚዘናፈል ረጅም ጸጉር ያለው ጎልማሳ ነበር፡፡ ድንገት ጸጉሩን ተሸለተ፣ ከጸጉሩ ጋር የጥንት ባህርይውን አራገፈ። ጭምት፣ መንፈሳዊና በመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር የነደደም ምዕመን ሆነ፡፡
በተገናኘን ቁጥር፣ኢዮብ ስለእምነት እንድንወያይ ይፈልጋል፡፡ ብዙ ጊዜ እምነት የሚያጠብቅ ሰው አንዳች ችግር ይኖርበታል ብዬ አስብ ነበር፡፡ ኢዮብ ግን እጅግ መልካም ሊባል በሚችል ሕይወቱ፣ ይሄንን አመለካከቴን ውድቅ አድርጎብኛል፡፡
የዛሬ ሳምንት ገደማ ኢዮብ ዘፈን በመሥራት ላይ ነበር፡፡ እና ለአንድ ዜማው ግጥም እንድሠራለት ጋበዘኝ፡፡ ከዚህ በፊት የሞከርኳቸው የዘፈን ግጥሞች ስለከሸፉብኝ ግብዣውን ለመቀበል አመነታሁ፡፡ ግን ደሞ ወዲያው፣በኢዮብ ድምጽ ግጥሜ ተዘፍኖልኝ ለማየት ጓጓሁ፡፡ ውሀ ልማት አካባቢ፣ሌክስ ፕላዛ ሕንጻ ሥር መኪናው ውስጥ ቁጭ ብለን ዜማዎችን ማድመጥ ጀመርን፡፡ ዘፈኑ ውስጥ ያሉት ሐሳቦች አብዛኞቹ ወደ መዝሙር ያዘነብላሉ፡፡ ኢዮብ ዘፈኑን ለፈንጠዝያ ሳይሆን ለስነምግባር ግንባታ ሊጠቀምበት ፈልጓል፡፡ አንድ በጣም ልብ የሚበላ የሶማሌ ዘፈን አስደመጠኝ፡፡
‹‹ሶማሊኛ ትችላለህ እንዴ?>>
‹‹አዎ፣ትግርኛም አውቃለሁ!››
‹‹የት ተማርከው?>>
‹‹አስመራ፣ የወታደር ልጅ መሆኔን አትርሳ››
ከዘፈን ውጭ ምን ታደርጋለህ?
‹‹ኦን ላይን፣ጊታር እየተማርሁ ነው፡፡ ቆይ ላሳይህ››…ላፕቶፑን ለኮሰና ጥቂት አስጎበኘኝ፡፡ ከዛ ከመኪናው ስወርድ የመኪናው እጀታ ስለማይሠራ ወርዶ ከውጭ ከፈተልኝ፡፡ ኢዮብ ብዙ ብሮችን መቁጠር የሚችል ልጅ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ እንኳን መኪናውን የመኪናውን እጀታ ማስቀየር አልፈለገም፡፡ ምናልባት፣ዓመት በአልን ጠብቆ ልብስ የሚቀይር ብዙ ሰው ባለበት አገር ውስጥ፣መኪና መቀያየሩን እንደ ኃጢአት ቆጥሮት ይሆናል፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላ ልኡል የተባለ ዘፋኝ ጓደኛዬ፣ የኢዮብን በድንገት መውደቅ ሲነግረኝ ወደ ቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል ሄድኩ፡፡ ዘፋኞችና አዘጋጆች መጠበቂያው ክፍል ላይ ተደርድረው ይተክዛሉ፡፡ ዘሪቱ፣ ዳግማዊ አሊ፣ እቁባይ በርሄ፣ አጃቸውን አገጫቸው ላይ ጭነው፣ ተቀምጠዋል። የኢዮብ ባለቤት ወዲያ ወዲህ እየተንቆራጠጠች ታነባለች፡፡
ዛሬ ደግሞ ይሄው ሞቱን ሰማሁ፡፡ኢዮብ!!! በጠፈሩ ውስጥ፣ ያለግብ ከሚዞሩ ኮረቶች፣ ያለ ምክንያት ከሚበሩ ኮከቦች በቀር ምንም የለም ብዬ እንደማምን ታውቃለህ፡፡ ይሁን እንጂ ለዛሬ እንኳ፣ የኔ እምነት ከሽፎ ያንተ እምነት እውነት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ በምድር ለገጠመህ መራራ እጣ ሰማያዊ ካሳ (ጉማ) እንድታገኝ እመኛለሁ፡፡
(በዕውቀቱ ስዩም ከፌስ ቡክ)
ኢዮብ የስራ ባልደረባዬ ብቻ ሳይሆን የቅርብ ጓደኛዬም ነበር፡፡ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት በፋራናይት ክለብ አብረን ሰርተናል፡፡ ይሄ ቅርብ ግንኙነት እንዲኖረን አድርጐናል፡፡
እኔና ኢዮብ የወንድማማቾች ያህል ነበር። የአስር ዓመት ጓደኝነት ከዚያ ውጭ ምን ሊሆን ይችላል? የኢዮብ ሞት ለእኔ ያልጠበቅሁትና በጣም አስደንጋጭ ነበር፡፡ ወደ ኬንያ ለህክምና ሲሄድ ተሽሎት ወደ አገሩ እንደሚመለስ ጽኑ እምነት ነበረኝ፡፡ ኢዮብ ከእንግዲህ አብሮን እንደማይኖር የሰማሁትን ዜና አሁንም ድረስ አምኖ መቀበል አዳግቶኛል፡፡ ኢዮብ የሚገርም ተሰጥኦ የታደለ ታላቅ አርቲስት ነበር፡፡ ይሄን ተሰጥኦውን ገና በቅጡ ሳይጠቀምበት ህይወቱ አለፈ፡፡ ብዙ አስደናቂ ችሎታዎቹን ለማየት በምንጠብቅበት ሰዓት ነው ሞት የቀደመው፡፡ አሁን ምን ማለት አይቻልም - እግዚአብሔር ነፍሱን በሰላም እንዲያሳርፍለት ከመፀለይ በቀር፡፡
(ድምፃዊ ሸዋንዳኝ ኃይሉ)
ይሄንን ባለተሰጥኦ ድምፃዊ ለማወቅና ለመተዋወቅ የቻልኩት አንድ ግሩም ወዳጄ ሥራውን በዳላስ፣ ቴክሳስ ሲያስተዋውቅለትና በመስከረም ወር 1997 ዓ.ም ለኮንሰርት ባመጣው ጊዜ ነበር፡፡ ኢዮብ ያኔ “እንደ ቃል” የተሰኘው አዲሱ አልበሙ ወጥቶ ስለነበር ዝናው መናኘት ጀምሯል፡፡ “ኢትዮ - ሬጌ” የተባለ አዲስ የሙዚቃ ዘይቤ ለኢትዮጵያ በተለይ ለዳያስፖራው ያስተዋወቀ አዲስ ዘፋኝ በሚል ነበር የሚታወቀው፡፡ ከዜማው የበለጠ የዘፈን ግጥሞቹ ማራኪ ነበሩ፡፡ ፍቅርን፣ መከባበርንና ትሁትነትን በዘፈኖቹ ሰብኳል፡፡ ኢዮብን በሞት ብናጣውም ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ባበረከተው ታላቅ አስተዋጽኦና በትሁት ባህርይው ዘላለም ሲታወስ ይኖራል፡፡
ዳኒ (ከዋሺንግተን ዲሲ)
ከሁለት ዓመት በፊት ኢዮብ በኒውዮርክ ያቀረበውን ኮንሰርት የመታደም ዕድል አግኝቼ ነበር። ገና በመጀመሪያውና ብቸኛ በሆነ አልበሙ ዝነኛ ለመሆን የበቃ አርቲስት ነው፡፡ ያለጊዜው ህይወቱ ማለፉ በጣም ያሳዝናል፡፡
ቢኒያም ጌታቸው (ከአሜሪካ)
የቅርብ ጓደኛው አልነበርኩም፡፡ እኔን ጨምሮ በአብዛኛው ሰው ዘንድ ይወደድ እንደነበር ግን አውቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ተወዳጅ የነበረ ወጣት የሬጌ አቀንቃኝ አጥታለች፡፡ እግዚአብሔር ነፍሱን በመንግስተ ሰማያት ያኑርለት፡፡ ለቤተሰቡ መጽናናትን እመኛለሁ፡፡
ለማ ገብረማርያም (ከኢትዮጵያ)
ልብን የሚያላውስ ዘፋኝ ነበር፡፡ አዲስ አበባ እያለሁ ኮንሰርቶቹንና በምሽት ክለብ የሚያቀርባቸውን ሥራዎች ታድሜያለሁ፡፡ በተለይ በክለብ H20 እና በፋራናይት በሚያስገርም ድምፁ መድረኩን የቀወጠባቸውን ሌሊቶች ፈጽሞ አልረሳቸውም፡፡ የእሱ ሞት በተለይ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ትልቅ እጦት ነው፡፡ ሁላችንም አዲሱን አልበሙን እንጂ ሞቱን አልጠበቅንም ነበር፡፡ በጣም አስደንጋጭ ዜና ነው፡፡
አለማየሁ ጨቡዴ (ከኩዌት)
በአዲስ አበባ ኮንሰርቶቹን ተከታትያለሁ፡፡ በምሽት ክበቦች ሲዘፍን ታድሜያለሁ፡፡ ዘፈኖቹን በመኪና ውስጥ፣ እቤቴና ቢሮዬ እሰማቸዋለሁ። በዘፈኖቹ ተለክፌ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ ጂም አብረን ስንሰራ ከስፖርት በኋላ ስቲም ውስጥ እናወራለን፡፡ በጣም አሪፍ ሰው ነበር - ለጨዋታና ለጓደኝነት የሚመች፡፡ ሁላችንም ነን ያጣነው፡፡ የእሱ ሞት ለሁላችንም ትልቅ ጉዳት ነው፡፡
ብሩክ ኢትዮ (አዲስ አበባ)
አሁንም ድረስ ከድንጋጤ አልወጣሁም፡፡ እኔና ኢዮብ የፌስቡክ ጓደኛ የሆንነው ሙዚቃውን ከሰማሁ በኋላ ነው፡፡ የዓለም ተጓዦች የሆኑ ሰዎች ሲዲውን ይዘውት ስለነበር ከእነሱ ተውሼ ነው ያደመጥኩት፡፡
በቅርቡ ካሊፎርኒያ ለኮንሰርት በመጣ ጊዜ “All night pressure” የተባለው የእኔ ባንድ እንዲያጅበው ተስማምተን ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ አልተሳካም፡፡ የሁለተኛ አልበም ቀረፃችንን ለመጨረስ ውጥረት ውስጥ ነበርን፡፡
ከኢዮብ ጋር ባወራንባቸው ጥቂት ጊዜያት ሃቀኛ ነፍስ እንደነበረውና ሲበዛ ደግ መሆኑን ለመገመት አልቸገረኝም፡፡ የግጥሞቹ ትርጉም ባይገባኝም ድምፁና አዘፋፈኑ ውብና አይረሴ ነበር፡፡ ሙዚቃ ክልልና ድንበር ተሻጋሪ ለመሆኑ ይሄም ተጨማሪ አብነት ነው፡፡ በዚህ ሰዓት በጣም አዝኛለሁ፡፡ ለባለቤቱና ቤተሰቦቹ መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ። በዚህ የሀዘን ጊዜ በፀሎት ከጐናችሁ መሆኔን ለመግለፅ እፈልጋለሁ፡፡
ክሪስ ኤሊስ (ኦሬንጅ ካንቲ፣ ዩኤስኤ)
==============
ድምጻዊ እዮብ መኮንን ዘውዴ ከአባቱ ከአቶ መኮንን ዘውዴ ይመኑ እና ከእናቱ ወ/ሮ አማረች ተፈራ የምሩ ጥቅምት 12 ቀን 1967 ዓ.ም በጭናቅሰን ገብርኤል ጅጅጋ ከተማ ተወለደ፡፡ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በጅጅጋ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ከፊል የሁለተኛ ደርጃ ትምህርቱን ደግሞ ከወላጅ አባቱ ጋር ወደ አስመራ በመሄድ የተከታተለ ሲሆን፤ቀሪውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ወደ ጅጅጋ በመመለስ ተምሯል፡፡ በ1991 ዓ.ም. በአጋጣሚ ወደ አዲስ አበባ የሚያመጡ ፈቃደኛ ሰዎች በማግኘቱ እራሱን ያስተዳድርበት የነበረውን የፎቶግራፍ አንሺነት ሥራን ትቶ፣ በ24 ዓመቱ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው የያኔው ፋልከን ክለብ ድምጻዊነቱን “ሀ” ብሎ ጀመረ።
ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ አልበሙን እስካወጣበት 2000 ዓ.ም ድረስ የሌሎች ድምጻውያንን ሥራዎች፣በዋነኝነት የአሊ ቢራን እና የቦብማርሊን ዘፈኖችን ሲያቀነቅን የቆየ ሲሆን በነዚህ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ውጭ ወደ ዱባይም በመመላለስ በድምጻዊነቱ ሰርቷል፡፡ በጥቅምት 2000 ዓ.ም በአብዛኛው በሬጌ ስልት የተዘጋጀው “እንደቃል” የተሰኘው የመጀመሪያ አልበሙ ከተለቀቀ አጭር ጊዜ በኋላ፣ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን በማትረፍ እስካሁን ድረስ በከፍተኛ መጠን በመደመጥ ላይ ይገኛል፡፡ በአዲስ ጣዕም የመጣው “እንደቃል” አልበም በኢትዮጵያ ውስጥ የሬጌ ሙዚቃ ይበልጥ ይወደድ ዘንድ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሯል።
ከዚህ አልበሙ በኋላ በሀገር ውስጥ እና ከሃገር ውጪ በአውሮፓ እና በአሜሪካ የሙዚቃ ዝግጅቶችን እያቀረበ ቆይቷል፡፡ በአዲስ አበባ የተለያዩ የሙዚቃ ቦታዎች ላይም ለረጅም ጊዜያት በቋሚነት የራሱን ዘፈኖች ለአድናቂዎቹ በመድረክ ሲያቀርብ ነበር፡፡ ሁለተኛ አልበሙንም በመሥራት ላይ የነበረ ሲሆን በድንገት እስኪታመም ድረስ ሙሉ ትኩረቱ በዚሁ ሥራው ላይ ነበር፡፡ ድምጻዊ እዮብ መኮንን ነሐሴ 7 ቀን 2005 ዓ.ም በድንገተኛ የስትሮክ ህመም መኖሪያ ቤቱ ደጃፍ ላይ የወደቀ ሲሆን፤ህመሙ ጠንቶ እራሱን ሳያውቅ በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል የህክምና ክትትል ሲደረግለት ቆይቶ በወዳጅ ዘመዶቹ ርብርብ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ናይሮቢ ኬንያ ሄዶ፣ በአጋካን ሆስፒታል ሕይወቱን ለማትረፍ ጥረት ቢደረግም በታመመ በአምስተኛ ቀኑ ነሐሴ 12 ቀን 2005 ዓ.ም. ምሽት በ38 ዓመቱ ሕይወቱ አልፏል፡፡
ድምጻዊ እዮብ መኮንን ባለትዳር እና የአንድ ልጅ አባት ነበር። የድምጻዊ እዮብ መኮንን የቀብር ስነ-ስርዓት ባለፈው ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2005 ዓ.ም ቤተሰቦቹ፣ወዳጅ ዘመዶቹ እና አድናቂዎቹ በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።
ደራሲዋ በመፅሃፍ ሽያጭ 95ሚ. ዶላር አፈሰች
ኢ.ኤል ጄምስ ትባላለች፡፡ ፎርብስ መጽሔት ባወጣው የደራሲዎች አመታዊ ሽያጭ ዝርዝር አንደኛ ሆናለች - “50 ሼድስ ኦፍ ግሬይ” በተሰኘ መፅሃፏ፡፡ ከዚ መፅሃፍዋ ያገኘችው የገንዘብ መጠን 95 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ መጽሐፉ በሦስት ተከታታይ ክፍል (Trilogy) የሚተረክ ሲሆን በስምንት ወር ውስጥ ሰባ ሚሊዮን ኮፒ ተሸጧል፡፡ መጽሐፏን ወደ ፊልም ለመቀየር በሲኒማ ሰሪዎች ተጠይቃ በመስማማቷ ተጨማሪ አምስት ሚሊዮን ብር ትርፏ ላይ ታክሎላታል፡፡ በ2014 ፊልሙ ሲኒማ ቤቶችን ያናውጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከዚህች ሴት ደራሲ (ኢ.ኤል ጄምስ) ድንገተኛ ስኬት በፊት ከፍተኛ ሻጭ የነበረው ጄምስ ፓተርሰን ነበር፡፡ ዘንድሮ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል፡፡ ሴቷ ደራሲ በአራት ሚሊዮን ብር በልጣ አስከትላዋለች፡፡ ለአራት ተከታታይ አመታት የያዘውን ደረጃም ነጥቃዋለች፡፡ ጄምስ ፓተርሰንን “አሌክስ ክሮስ” እና “ማክሲመም ራይድ” በተሰኙ ድርሰቶቹ ድፍን አለም ያውቀዋል፡፡ በአመት አምስት መጽሐፍት ጽፎ (አምርቶ) ለማሳተም በመብቃቱ ይጠቀሳል፡፡ እሱን በመከተል ሶስተኛ ደረጃ ላይ ያለችው ሱዛን ኮሊንስ ናት፡፡ 55 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ ከመጽሐፏ ሽያጭ አግኝታለች፡፡ መጽሐፏ “ዘ ሀንገር ጌምስ” ይሰኛል፡፡ ወደ ፊልምም ተቀይሯል፡፡ በዚሁ አመት የ”ሀንገር ጌምስ” ተከታይ የሆነው ፊልም “ዘ ሀንገር ጌምስ ካቺንግ ፋየር” የሲኒማን አለም እንደሚነቀንቅ ይጠበቃል፡፡
“ማይክልን የገደለው የህመም ፍርሀቱ ነው”
ታላቁ የፖፕ ሙዚቃ ንጉስ ማይክል ጃክሰን ከሞተ አራት አመት ሆነው፡፡ የሟቹ ቤተሰብ ግን አሁንም የሞቱ ምክያኒያት አልተዋጠልኝምና ይመርመርልኝ ማለቱን ቀጥሏል፡፡ ምርመራው በአንደኛነት ያነጣጠረው የሙዚቃ ንጉሱን የልብ ጤና ይከታተል በነበረው ዶክተር ኮንራድ ሙሬ ላይ ነው፡፡ የክሱ አይነት፡- በስህተት ነብስ ማጥፋት (involuntary manslaughter) እና የታማሚውን የጤና ሁኔታ ያላገናዘበ ንዝህላልነት የሚል ነው፡፡ በዚህ ፍርድ ሂደት ላይ የማይክል ጃከሰን የቀድሞ ሚስት (ዴቢ ሮው) በእንባ እየታጠበች ስለ ሟቹ ባሏ ባህሪ ተናዝዛለች፡፡ ትዝታዋን በመመርኮዝ የሰጠችው ምስክርነት የዚህ ሳምንት ትኩስ ዜና ሆኖ ሰንብቷል፡፡
ዴቢ ስለ ማይክል ምን መሰከረች?
“ማይክል ምንም አይነት ህመምን የማስተናገድ አቅም የሌለው ሰው ነው፡፡ ማመን በሚያስቸግር ደረጃ ህመምን ይፈራል፡፡ ህመምን ለማስወገድ ምንም አይነት መድሀኒት ይወስዳል፡፡ ዶክተሮቹም ለዚህ ፍርሐቱ መሳሪያ ሆነውለታል” ብላለች፡፡ ዴቢ ሮው ከማይክል ጃክሰን ጋር የተዋወቀችውም እዛው ሀኪም ቤት ነበር - የማይክልን ቆዳ በሽታ ከሚያክመው ከዶክተር አርኖልድ ክላይን ጋር በምትሰራበት ወቅት፡፡ እዛ ተዋውቀው ተጋቡ፡፡ በጋብቻ ጥምረት ሦስት አመት አብረው ኖሩ፡፡ ከ1996-1999 … የመጀመሪያዎቹን ሁለት ልጆቹን የወለደችለትም ዴቢ ሮው ናት፡፡ በፍርድ ቤት በሰጠችው ምስክርነቷ፡- ማይክል፤ ለቀዶ ጥገና ብቻ የሚወሰድ ማደንዘዣ ለእንቅልፍ ሲል ይወጋ እንደነበር ተናግራለች፡፡
“… ከሞት ይልቅ እንቅልፍ የማጣቱ ነገር በበለጠ ያስጨንቀው ነበር” ትላለች ዴቢ፡፡ “ምክንያቱም ያለ እንቅልፍ በመድረክ ላይ ሙዚቃዎችን ማቅረብ ስለማይችል ነው”
ለቀዶ ጥገና የሚወሰደውን ማደንዘዣ በ1997 (በፈረንጆቹ አቆጣጠር) መጠቀም ከማዘውተሩ በፊት … የሌላ ህመም ማጥፊያ መድሐኒት ሱሰኛ ነበር፡፡ በ1993 የፔፕሲን ማስታወቂያ ለመስራት ቀረፃ በሚያደርግበት ወቅት በተፈጠረ አደጋ፣ የራስ ቅሉ ላይ የቃጠሎ አደጋ ባጋጠመው ጊዜ ህመሙን ለማስወገድ “ዲሜሮል” የተሰኘ ማደንዘዣ ይወስድ ነበር፡፡ የዚህን መድሐኒት ሱስ መላቀቅ ሳይችል በላዩ ላይ “ፕሮፖፎል” የተባለውን ማደንዘዣ ለእንቅልፍ ሲል ደረበበት፡፡ የእነዚህ የህመም ማጥፊያ መድሐኒቶች መደራረብ በ2009 አለምን ላስደነገጠ ሞቱ ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ሚስቱ በምስክርነቷ ፍንጭ ሰጥታለች፡፡ ዴቢ ሮው የከሳሹ ቤተሰቦች (በተለይ የማይክል ጃክሰን እናት ካተሪን) ከቀጠሩዋቸው ጠበቆች የሚቀርቡላትን መስቀለኛ ጥያቄዎች በፍርዱ ቀጣይ ሂደቶች እንደምትመልስ ይጠበቃል፡፡
ዓመታዊው የሸራተን የስዕል አውደ ርዕይ ይቀርባል
በየዓመቱ በነሐሴ ወር የሚዘጋጀው የሸራተን የስዕል አውደ ርዕይ ሊቀርብ ነው፡፡ “Art of Ethiopia 2013” በሚል ርዕስ የሚቀርበው አውደ ርዕይ፤ በኢትዮጵያ ያሉ የጥበቡ ፈርጀ ብዙ ገፅታዎችን የሚያሳዩ 500 ያህል ሥዕሎች ይቀርቡበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከነዚህ ስራዎች ከመቶ አስር እጅ በቅርፃ ቅርፅ ላይ ያተኩራል የተባለለት ትልቅ አውደ ርዕይ፤ በሚቀጥለው ዓርብ ነሐሴ 24 ቀን 2005 ዓ.ም ተከፍቶ እስከ ነሐሴ 27 በየእለቱ ከቀኑ 4 ሰዓት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ለህዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡ በዝግጅቱ 450 ሰዓሊዎች ስራዎቻቸውን እንዲታይላቸው አቅርበው “የምርጦቹ ምርጥ” ለአውደርዕዩ መቅረቡንና ከነዚህም ሩቡ እጅ የሴት ሰዓሊያን ስራ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሸራተን አዲስ ላለፉት አምስት ዓመታት በየዓመቱ ታላቅ የስዕል አውደርእይ እያሳየ ይገኛል፡፡ አውደርእዩ በአዲስ አበባ የሚገኙ የስዕል ትምህርት ቤቶችን ለማጠናከር ያለመ ነው፡፡
8ኛው የበደሌ ስፔሻል የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል በባህዳር
ስምንተኛው የበደሌ ስፔሻል “የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል በህዳር 2006 ዓ.ም እንደሚካሄድ ሊንኬጅ ማስታወቂያ ህትመትና ፕሮሞሽን አስታወቀ፡፡ ከህዳር 16 እስከ ህዳር 23 የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል፣ “አፍሪካዊያን የራሳቸውን ታሪክ እስኪናገሩ የቅኝ አገዛዝ ታሪክ ቅኝ ገዢዎችን ያደምቃል” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን 70 ያህል ዶክመንተሪ፣አጭር፣ፊቸር እና አኒሜሽን ፊልሞች ይቀርቡበታል፡፡ “African panorama” “Cinema Landmarks” “Contemporary Cnema”, “Regional /Ethiopia Focus” እና “Community Focus” የተሰኙ ፊልሞች የሚቀርቡበት ፌስቲቫል፣ ሽልማቶችም ይኖሩታል ተብሏል፡፡
“ላማ ሰበቅታኒ” ለንባብ በቃ
በፀሐፌ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ የተደረሰው “ላማ ሰበቅታኒ” የረዥም ልቦለድ መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ “Fantasy” የተሰኘውን የአፃፃፍ ስልት ተከትሎ የተጻፈው መጽሐፍ 174 ገፆች ያሉት ሲሆን የታተመው በ”እማይ ፕሪንተርስ” ነው፡፡ የመጽሐፉ ዋጋ 40 ብር ከ50 ሣንቲም ነው፡፡
ደራሲ ውድነህ ክፍሌ “የቼዝ አለም”፣ “ባቢሎን በሳሎን” ፣ “የታፈነ ጩኸት” እና በሌሎችም ተውኔቶቹ የሚታወቅ ሲሆን ከዓለም አቀፍ አዕምሮአዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የ2000 ዓ.ም “ምርጥ የትያትር ደራሲ” ተብሎ መሸለሙም አይዘነጋም፡፡
“እዩና እመኑ” የመዝሙር ቪሲዲ ነገ ይመረቃል
ጥንታዊውና ታሪካዊውን የአቡነ መልከፄዴቅ ገዳም ይበልጥ ለማስተዋወቅና ለቱሪስቶች ለማስጐብኘት እንዲሁም ለመርዳት በአርቲስቶች የተሰራው “እዩና እመኑ” ቪሲዲ ነገ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል አዳራሽ ይመረቃል፡፡
ትዕግስት ግርማ፣ ይገረም ደጀኜ፣ መሰረት መብራቴና ሌሎች ታዋቂ አርቲስቶች የተሳተፉበት ቁጥር አንድ “እዩና እመኑ” ከዚህ በፊት ተመርቆ ለገበያ ከቀረበ በኋላ በተደረገው ገዳሙን የማስተዋወቅ ስራ እስካሁን የ13 አገራት አምባሳደሮች፣ ሀይሌ ገ/ስላሴና የጀርመኑ ፕሬዚዳንት የጐበኙት ሲሆን ዘወትር ቅዳሜ ከ33-40 መኪና ጐብኚዎች ወደ ስፍራው እንደሚጓዙ ተጠቁሟል።
በአቡነ መልከ ፄዴቅ ገዳም እጅግ አስገራሚ ከሆኑት መስህቦች መካከል የሰው ሬሳ ከአመታት በኋላ አለመበስበሱ፣ ያለቀለም መርገጫ በእጣን መዓዛ ብቻ የሚሰራ ማህተም፣ ከ800 ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው ደወል እና ሌሎችም እንደሚገኙበት ይታወቃል፡፡
“እንግዳ ነፍስ” ፊልም ሰኞ ይመረቃል “ጃንኖ” ፊልም በአዲስ አበባ መታየት ጀመረ
በአሊ ይመር ተጽፎ የተዘጋጀውን “እንግዳ ነፍስ” ፊቸር ፊልም ሰኞ ምሽት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር እንደሚያስመርቅ ዙምባራ ፊልም ፕሮዳክሽን አስታወቀ፡፡ በፊልሙ ላይ መንትዮችን ጨምሮ 45 ያህል ተዋንያን እንደተሳተፉበት የጠቀሰው ድርጅቱ፣ፊልሙን ሠርቶ ለማጠናቀቅ አንድ ዓመት እንደፈጀ አስታውቋል፡፡
በሌላም በኩል “ጃንኖ” የተሰኘ ፊልም የ95 ደቂቃ ፊልም በአዲስ አበባ መታየት ጀመረ፡፡
በሐዋሳ ተሰርቶ በዚየው ከተማ ሰኔ 26 ተመርቆ የነበረው ፊልም ባለፈው እሁድ በአለም፣ በዋፋ፣ በዮፍታሔ፣ በሴባስቶፖል፣ በኢዮሃ፣ በሆሊሲቲ ሲኒማ ቤቶች ታይቷል፡፡
ፊልሙን ፋሲል አስማማው ጽፎ ፕሮዲዩስ ያደረገው ሲሆን በደረጄ ደመቀ ዳይሬክተርነት ዘነቡ ገሠሠ፣ እንቁሥላሴ ወ/አገኘሁ፣ አልጋነሽ ታሪኩ፣ ናርዶስ አዳነ፣ ተመስገን ታንቱ፣ ይልፋሸዋ መንግስቴ ደረጄ ደመቀና ሌሎችም ተውነውበታል፡፡
ከ40 ዓመት በፊት በደብረታቦር ከተማ የተነበቡ የዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ጽሁፎች...
ሰሞኑን፣ ወደ ዝግጅት ክፍላችን አንድ በእድሜ ብዛት ንትብ ያለ ባለ 34 ገጽ መጽሔት መጣልን። ክፍለሀገር ከሚኖር፣ የእነ ፈቃደ አዘዘ የቀድሞ ተማሪ እጅ ከ40 ዓመት በላይ የቆየው ‹‹ቴዎድሮስ›› የተሰኘው ይኽ መጽሔት፣ ደብረታቦሩ ከተማ በሚገኘው፣‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት›› በ1964 ዓ.ም. በሰቴንስል ተባዝቶ እንደተሰራጨ ታውቋል፡፡
በወቅቱ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለአንድ ዓመት የማስተማር አገልግሎት የመስጠት ግዴታ ስለነበረባቸው፣ የያኔዬው የ22 ዓመቱ ትንታግ ወጣትፈቃደ አዘዘና ሌሎች 6 ጓደኞቹ፣ በዳግማዊ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የማስተማር ‹‹ሰርቪስ›› ይወጡ ዘንድ፣ የዛሬው የደቡብ ጎንደር መስተዳድር ዞን ዋና ከተማ በሆነው ደብረታቦር፣ ከትመው ነበረ፡፡ እናም፣ መጽሔቱ፣ በዚያ የአንድ ዓመት የማስተማር ቆይታቸው ወቅት ያዘጋጁት ሲሆን፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ የቀረቡ መጣጥፎች፣ ዜናዎች፣ ለፈገግታ ያህሎች፣ የአካባቢ ገለጻዎች፣ ግጥሞች፣ የካርቱ ሥዕሎች ወዘተ. ቀርበውበታል፡፡
ታዲያ በመፅሄቱ ላይ በንባብ ከቀረቡ ፅሁፎች መካከል፣በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማስተማርና መመራመር ከጀመሩ፣ ዘንድሮ 40ኛ ዓመታቸውን የደፈኑት የዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ፅሁፎችም ይገኙበታል። “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” በሚል ርዕስ ያቀረቡት መጣጥፍ፣ በወቅቱ በተማሪዎች ንቅናቄ ሲስተጋባ የነበረው የብሄር/የጎሳ ፖለቲካ የደረሰበት ጫፍና የወደፊት ጦስ አቀንቅኗል፡፡ “ታዲያኮ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት ቀርቶ ‹አጅባሬ ነኝ!›፣ ‹ካሳንችሴ ነኝ!› ወዘተ. ማለት ሊመጣ ነው፡፡ በአባትና ልጅ መሀከል ልዩነት አይፈጠር ብላችሁ ነው? ወይስ ተፈጥሯል? የሚለውን ገለፃ ከዛሬ ነባረ ሁኔታ ጋር በንፅፅር ስናየው የትንቢት ቃልም ይመስላል፡፡
“መቼ ሆን?” በሚል ጥያቄያዊ ርዕስ ለዘብ ብለው የቀረቡ የአስተውሎት ምልከታዎች ፣ስለ ደብረታቦር ከተማና ህዝብ ማህበረ ባህላዊና ኢኮኖሚያዎ ሁኔታ ይጠቁማሉ፡፡ የምልከታዎቹ ዋጋ ግን፣የትናንሽ የገጠር ከተሞችን ጭምር ማህበረ ባህላዊ የኑሮ መልኮች፣የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ክስተቶችን ወዘተ በወቅቱ የመዘገብን አስፈላጊነት ከማመልከታቸውና ከማንቃታቸው ጭምር ሊመዘዝ ይችላል፡፡ ዛሬ ላይ የደብረታቦር ከተማና ህዝብ የለውጥ ሁኔታን ቃኝቶ ምልከታውን ለሚያከፈለን ፀሐፊም መልካም አጋጣሚ ነው እንላለን፡፡ ለማንኛውም ከመፅሄቱ እንደወረደ የቀረቡትን ፁሁፎች እንደሚከተለው አቅርበናል፤
ድር ቢያብር አንበሳ ያስር
በማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ አንድ ሰው ብቻውን ኢምንት ነው፡፡ ሀይል የለውም፡፡ ስርዓት አይኖረውም፡፡ አላማውም ግላዊ ነው፡፡ ብቻውን ከመቶ ኪሎ ጤፍ እንደ አንዲቱ የጤፍ ቅንጣት ነው። ጤፍ ብቻዋን አታጠግብም፡፡ ሰውም ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡ ከሰው ከተባበረ ግን እራሱን ሊያሻሽልና ሊጠብቅ፣ ባላንጋራውን ሊያጠቃ ይችላል፡፡ ሥራውም እንደ አንዷ ጤፍ ሳይሆን እንደምንበላው እንጀራ አንጀት አርስ ይሆናል፡፡
ታድያ ምነው የሰው ልጆች ልብ ተራራቀ? ምነው ተከፋፈለ? ምነው ሕብረትን ጠላ? ለምንስ በጠቅላላው በሰው ልጅ ወንድማማችነት እንደመመስረት የጎሳ ዝምድና ይመሰረታል? ለምን ወገን ይለያል? ሀገር የጋራ ነው ተብሏል፡፡ ታዲያኮ ዝምድናውም የጋራ ነው ማለት ነው፡፡ ፍቅሩ የሁሉ ነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን አሁን የሚታየው ድርጊት ህሊናን የማያስደስትና አንጎልን የሚያናውጥ ነው፡፡
ጠለቅ ብለን ስንመለከት ብዙ ጅል ነገር እናገኛለን፡፡ አማራና ትግሬ ወገን መርጦ፣ ና ጉራጌ ተከፋፍሎ፣ ጋምቤላና ኩናማው ተለያይቶ ደም እንዳየች ውሻ በተገናኘ ቁጥር (‹‹ሲጣላ››) ሥራው እንዴት ይሠራ? እንዴት ለትምህርት እናስብ? እንዴት ለአንዲቷ ለመከረኛዪቱ እናት እናስብላት? ልባችን ለየብቻ ሆነ፡፡ ሥራችን ለየብቻ ሆነ፡፡ በመሀከል ግን ተጎዳን፡፡ እሷንም እንደማቀቀች ጎባጣ አሮጊት፣ ቀንታ (ቀና ብላ) ዓለሟን እንዳታይ ዓይኗን አጠፋነው፡፡
የሚገርመው ደግሞ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ይህ ልዩነቱ እየጠበበ ነው የሚሄደው፡፡ አማራው እንደገና ጋይንት፣ ቡልጋ፣ እስቴ፣ ደብረማርቆስ ወዘተ. እያለ ወገን ይለያል፡፡ ጋላውም አሩሲ፣ ሰላሌ፣ በቾና ወለጋ ወዘተ. እያለ ይከፋፈላል፡፡ ትገሬውም እንደዛው፡፡ ሌላውም እንደዛው፡፡ ካፍንጫችን እርቀን ስናስብ ደግሞ ቀስ እያለ በትውልድ መንደር የሚደረግ ልዩነት ሊመጣ ሞቆብቆቡን እንረዳለን፡፡ የአጅባርና የአስፋው ግራር፣ የአራት ኪሎና የስድስት ኪሎ ወዘተ. ልጆችስ እየተፈላለጉ ይጣሉ የለ? ታዲያኮ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት ቀርቶ ‹‹አጅባሬ ነኝ!››፣ ‹‹ካሳንችሴ ነኝ!›› ወዘተ. ማለት ሊመጣ ነው፡፡ በአባትና ልጅ መሀከል ልዩነት አይፈጠር ብላችሁ ነው? ወይስ ተፈጥሯል?
ይህ ሁሉ የሚመጣው የስልጣኔን ጮራ፣ የትምህርትን ውጋገን ካለማገኘትና ከዚህም በላይ እውነተኛ የሀገር ፍቅር ከማጣት ነው፡፡ ስለዚህ ያገሬ ሰው ስማኝ፣ ተባበር፡፡ አትበታተን፡፡ ጠላትህን አታስደስት፡፡ ከተባበርክ እንኳን ረሃብን፣ ድንቁርናን እና ሌሎች ልዩ ልዩ በሽታዎችን ማጥፋት ትችላለህ፡፡
ተራራውን ብትገፋው ይገፋልሃል፡፡ ወደመሬት ማውረድ ወደሰማይ ማውጣት፣ ማስጠምም ማዳንም ያንተው ይሆናሉ፡፡ አትፍራ ሁሉም የሚፈልግ ህብረት ነው፡፡ አንድነትህን የሚጠላ የለም፡፡ ልብህን ይክፈተው፡፡ ብርታቱን ይስጥህ፡፡
ፈቃደ አዘዘ
የሰርቪስ መምህር
(በግል ምክንያት ሆሄ አልተጠበቀም)
መቼ ይሆን?
የደብረ ታቦር ሕዝብ መኪና በበጋ ሲመጣ በእልልታ መቀበሉ የሚቀረው?
ደብረ ታቦር መብራትና መንገድ ውሃና በቂ የሕክምና ጣቢያ የሚኖራት?
አንድ ብልህ ነጋዴ በላመነት የሚሰሩ ቦርሳዎችና ሻንጣዎች ኢንዱስትሪ የሚያያቋቁመው?
የደብረ ታቦር ጠላና ጠጅ የሚበላሸው?
የሚሲዎን ሀኪም ቤት አዋቂ ዶክቶሮች አስመጥቶ ሀብታም ደኃ ሳይል በትክክል የሚያክመው?
የደብረ ታቦር የ‹‹ቴዎድሮስ›› ቡድን (የእግር ኳስ) የቤጌምድር አሸናፊ (ሻምፒዎን) ሆኖ አዲስ አበባ የሚመጣው?
ፍርድ ቤት የሚመላለሰው ተሟጋች ቁጥር የሚቀንሰው?
እማማ የኔ ገላ የሚወፍሩት?!!!!!!!!
ተማሪዎችና መምህራን በጓድ ተከፋፍለው በትርፍ ጊዜያቸው ሕዝቡን በየቤቱ ሄደው የሚያስተምሩት?
የበኣል ቀናት ተቀንሰው የሥራ ቀናት የሚጨመሩት?
‹‹ፋርጣ ብር ቢያጣ ነገር አያጣ›› የሚባለው አነጋገር ዋጋ የሚያጣ?
በየመንገዱ፣ በየሜዳው፣ በየአጥር ጥጉና በየዱሩ መጸዳዳት የሚቀረው?
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጭነት መጫኛ አውሮፕላን ሰው ማመላለሱን የሚተወው?
የደብረ ታቦር ተማሪዎች ለኮርስ መስገብገባቸውን ትተው በትምህርታቸው ለመግፋት የሚያስቡት?
አዝማሪዎች በቀን በቀን ብር አምጡ ማለት የሚተዉት?
የሰርቪስ መምህር - ፈቃደ አዘዘ
1964፣ ደብረ ታቦር