
Administrator
የሚዳቋ ጅራት እርቃኗንም አይሸፍን አምላክንም አያስመሰግን
ከእለታት አንድ ቀን አንድ መጠጥ ቤት የነበረው ባላባት ነበረ። ይህ ሰው በጣም ስስታምና እምነተ-ቢስ ሰው ነበር። በህልሙም በእውኑም አግባብነት የሌለው ትርፍ ከማግበስበስና ሀብታም ከመሆን በስተቀር የሚያስበው ነገር የለም። ሆኖም ምንም ያህል ጥረት ቢያደርግ በየዕለቱ እየደኸየ ነበር የመጣው። አንድ ቀን አንድ አጎቱ ሊጠይቁት መጡ። ለረዥም ጊዜ አልተገናኙም ነበር።
“ሥራ እንዴት ነው?” አሉ አጎቱ።
“ኧረ እንደው ምኑም አልሳካልህ ብሎኛል። በየቀኑ መደህየት ሆኗል የኔ ነገር። የቢራው በርሜል ውስጥ ውሃ ጨምሬ አቅጥኜ ልሸጠው ሞከርኩ። ወይኑንም በውሃ አቅጥኜ አብዝቼ ለመሸጥ ሞከርኩ፤ የመጨረሻ እርካሽ የሚባለውን ስጋና ቅጠላ ቅጠል ገዝቼ በውድ ለመሸጥም ሞክሬያለሁ። በተቻለኝ መጠንም ሂሳብ ስመልስ የተሳሳተ መልስ እየሰጠሁ ላጭበረብርም ሞከርኩ። ብዙ ብር አገኝ መስሎኝ ያልፈነቀልኩት ድንጋይ፣ ያልበጠስኩት ቅጠል አልነበረም። ያም ሆኖ አሁንም ከመደህየት አላመለጥኩም። ምን ችግር ውስጥ እንደገባሁና ምን አይነት የኮከብ ጠማማ እንዳለኝ አይገባኝም።”
“እኔ ግን አንተን ሀብታም የሚያደርግህ አንድ ዘዴ አውቃለሁ” አሉ አጎትየው። “ና ላሳይህ” አሉና ቢራውም፣ ወይኑም፣ ምግቡም ወደሚከማችበት ወደ ዋናው መጋዘን ይዘውት ሄዱ። ከዚያም በሩን በትንሹ ከፈት አድርገው “በል በቀዳዳው አሾልከህ እይ” አሉት።ባለመጠጥ ቤቱ ግን ምንም ነገር ከተለመደው ውጪ ሊታየው አልቻለም። “ኧረ ምንም አይታየኝም” አለ።
“እስቲ እግርህን በእግሬ ላይ አድርግ። እጅህን ደግሞ እኔ ራስ ላይ አድርግና ለማየት ሞክር።” አጎቱ እንዳሉት አደረገ። ከዚያ እንደገና ወደ መጋዘኑ ተመለከተ። አይኑ ማመን አቃተው። ከመጋዘኑ መካከል ከወለሉ ላይ አንድ ወፍራም አጭር ቁዝር ሰውዬ ተቀምጧል። ምግቡን አሁንም አሁንም ይጠቀጥቃል። ኬክ በቅቤ፣ በጨው፣ በዱቄት ያሻምዳል። ከዚያም አሳማና እንቁላል ይጎርሳል። ደሞ በዚያ ላይ ቢራ ይጨምርበታል። ደሞ ይጎሰጉስበታል።
“ማን ነው? ምንድን ነው ይሄ?” ሲል ጠየቀ ባለግሮሰሪው።
“ይሄ የቅቤ አምላክ ይባላል።” አሉ አጎትየው። “እነዚህ አማልክት ስስት ባለበትና እምነተ-ቢስነት በነገሰበት መጠጥ ቤት ሁሉ ይኖራሉ። ማጭበርበርና ዳተኝነት ባለበት ቦታ ሁሉ ይመጣሉ።”
“ግን እንደዛ ካለ ባህሪዬ እንዴት አድርጌ ማምለጥ እችላለሁ?”
“ማምለጥማ አትችልም። ደንበኞችህን ባታለልክ ቁጥር የቅቤ አምላክ አንተን ያታልልሃል። እርግጥ ነው ይህን አመልህን ትተህ ለደንበኞችህ ቀና አገልግሎት መስጠት ስትጀምር የቅቤ አምላክም ጥሎህ ይጠፋል። ግን ለደንበኞችህ በጣም ምርጥ ምግብ አቅርበህ ተመጣጣኝ ክፍያ መጠየቅ ይኖርብሃል። ይሄን መናኛ ምግብና የቀጣጠነ መጠጥ እያቀረብክ እንደምታደርገው ያለ ተግባር አማልክቱ እንዲሸሹ አያደርጋቸውም።”
ይህንን ብለው አጎትየው ትተውት ሊሄዱ ተነሱ። በቅርቡ ተመልሰው እንደሚጠይቁት ቃል ገቡለት። ከዚህ በኋላ አጎት አልተመለሱም። ባለ ግሮሰሪው ግን ሆቴሉን ማሻሻሉን ቀጠለ። ባሻሻለውም ቁጥር ትርፉ እየጨመረ መጣ። ሃብታም ሆነ፡፡ መጠጥ ቤቱ ጢም ብሎ ይሞላ ጀመር። የዚህን መጠጥ ቤት ምግብ ለመቅመስ ከሩቅም ከቅርብም በላተኛው ይፈላ ጀመር። ቢራው ይደነቅ ጀመር። ወይኑም ስሙ የተጠራ ሆነ።
ከዓመት በኋላ አጎትየው መጡ። ሁኔታው ሁሉ መለወጡንም አዩ። “እስቲ አሁን ወደ መጋዘንህ እንሂድ” አሉት።
እንደቀደመው ጊዜ አሾልከው ተመለከቱ። አሁን ከወለሉ ላይ የተቀመጠው አንድ ቀጫጫ፣ ደካማ፣ በሽተኛ መልክ ያለው የቅቤ አምላክ ነው። ምግብ ለመብላት እየፈለገ ቅንጣት ታህል ጉርሻ ወደ አፉ ለማድረስ አቅም ያጣ ነው።
“አየህ” አሉ አጎት፣ “ታማኝነትና ጠንካራ ሰራተኝነት ባለበት ቦታ ሁሉ ዝር አይሉም። ይሄ መንፈስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሟች ነው። አንተ ወደ ጥንቱ የማታለል ተግባር እስካልተመለስክ ድረስ ወደዚህ ዝር አይልም።”
ባለግሮሰሪውም፡-
“ታማኝነትና ጠንካራ ሰራተኝነት የማታ የማታ ትርፋማ እንደሚያደርጉ ተገንዝቤያለሁ”” አለ።
***
በታማኝነትና በሠራተኝነት ላይ የሚያምን ግለሰብ፤ ኃላፊ፣ ባለስልጣን፣ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ድርጅት ማግኘት መታደል ነው። ትርፍ ከየትም ይምጣ ከየት መገኘት አለበት የሚል እምነት ደግ አይደለም። ውሎ አድሮ ከሰው ዘርፎም፣ ሰውን ገድሎ ቀምቶም ያገኙትን ትርፍ ትክክለኛ ሀብቴ ነው ማለትን ያስከትላል። የፖለቲካ የበላይነት ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተሄዱ ብዙ እኩይ ጉዳዮች ነበሩ። አሉም። ቢራው ላይ ወይም ወይን ጠጁ ላይ ውሃ እየጨመረ ሊያተርፍ እንደሞከረው ባለግሮሰሪ ብዙ ዓይነት የማማለያ መንገዶችን በመጠቀም ህዝቡን ለማጭበርበር የሞከሩ ብዙዎች ናቸው። ቋቱ ግን አልሞላም። የቅቤ አምላክ ውስጥ ውስጡን እየቦጠቦጠና እየሸረሸረ በአድልዎና በግፍ የተደበቀውን ሀብት ሁሉ ኦና እንዲቀር ያደርገዋል። ምልኪው ከባድ ነው፣ ሌሎችን በመበደል፣ ከሌሎች በመዝረፍ የሚካበት ሀብት መቅኖ የለውም። የኋላ ኋላ ወዳጅንም አርቆ፣ ሀብትንም አራቁቶ የራስን ህልውና ጭምር ወደማጣት ያመራል።
በሀገራችን የሚታየው የፖለቲካ ሙስናና የኢኮኖሚ ሙስና ተሳሳሪነትም፣ ተባባሪነትም ያላቸው ናቸው። በተለይ የፖለቲካ ስልጣንን ተገን አድርጎ የግል ወይም የድርጅት ኢኮኖሚያዊ ቋትን መሙላት የተለመደ ጉዳይ ነው። የማታ ማታ በገዛ ድርጅትም ሆነ በሌላ ባለጊዜ ወደ ዘብጥያ መውረድ እጅግ የታወቀ፣ እንደ ጸሐይ መግባት መውጣት የተረጋገጠ ሀቅ በመሆን ላይ ነው። አንድ የሀገራችን ፀሐፌ ተውኔት በአንደኛው ቴያትሩ ውስጥ ወህኒ ቤትን የገለጸው በንጉሥ አንደበት ነው። ንጉሡ ወህኒ ቤቱን ሲመርቁ ባደረጉት ንግግር እንዲህ ይላሉ፡-
“የአባታችን ርስተ-ጉልት የሆነውን የሀገር ወህኒ ቤት መርቀን ስንከፍትላችሁ፤ እናንተም በተለመደው ባህላችሁ በመተሳሰብ እንድትተሳሰሩበት ነው”
እውነቱ ሁሌም ይሄው ነው። የፖለቲካውም የኢኮኖሚውም ማረፊያ ወህኒ ቤት ነው። የአባት ምርቃት ሆኖም ይሁን የሀበሻ የአጥንትና ደም ነገር፤ “በመተሳሰብ መተሳሰር” እስከዛሬ “የተለመደ ባህላችን” ሆኖ ቀርቷል። “ታማኝ ነው ያሉት የስለት እቃ ይሰርቃል” እንዲሉ ከመነሻው ስለ ዲሞክራሲያዊ ልእልና፣ ስለ ህዝባዊ ፍትህ፣ “አንድ ጥይት ስለማትተኮስባት” ሰላማዊ ሀገር፣ ነጻነቱን ካሰጡት አራስ ነብር ስለሆነ ህዝብ፣ በህዝብ ሀብት ስለበለጸጉ የቀድሞ ባለስልጣናት ሊያወጋ “ከዚህም ወዲያ ታላቅ መሪ፣ ከዚህም ወዲያ አማራጭ-የለሽ የፖለቲካ ድርጅት ኢትዮጵያ ከእንግዲህ አይኖራትም” ይባላል። አንድ ጀምበር ሳይሻገር ዲሞክራሲው የግሉ ዲሞክራሲ፣ ፍትሁም በአድልኦ የተሞላ የግሉ ፍትህ፣ ሰላሙም ጦር የሚሰበክበት፣ መሳሪያ የሚወለወልበት ከመንደር ቡድን እስከ ጎረቤት ሀገር የሚናቆርበት፣ የኢኮኖሚ ምዝበራውም ከስርዓታዊ-ዕዝ ኢኮኖሚ ወደ ፓርቲያዊ አሊያም ባለስልጣናዊ ዕዝ-ኢኮኖሚ Partisan Lords የፓርቲ- ባላባቶች የተፈጠሩበት ሆኖ ይገኛል።
ጊዜ ካለፈ አገር ከደቀቀች፣ ህዝብ ከተጎዳ በኋላ “በዚህ ባልፍ ኖሮ ድጡ አይጥለኝም ነበር” አይነት በውስጡ “አልተሳሳትኩም” የሚል አንድምታ ያለው ጸጸታዊ ማረሚያ ይቀርባል። የኢትዮጵያ አለመታደል፣ ከበቀልና ከጸጸት አዙሪት የማትወጣ ሀገር መሆኗ ነው። ጧቱን ይህን ባታደርግ ጥሩ ነው ሲሉት፣ “ከእኔ ወዲያ ፍልስፍና ላሳር ነው” ሲል ይቆይና “በግንዛቤ ችግር ምክንያት እስካሁን የሄድንበት መንገድ ሁሉ ስህተት ነበር። ዲሞክራሲያዊነትን ከማላላት ማዕከላዊነትን ማጥበቅ፣ ከመብት ማክበር ይልቅ ጸጥታን ማስከበር ይሻላል ወዘተ” ወደሚል መደላደያ መሸጋገር እንግዳ አልሆኑም። አንዱን ቀዳዳ ሲያጥፉት ሌላ ቦታ እየተነደለ፣ አንዱን በር ሲዘጉት ሌላ እየተከፈተ ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረው የኢትዮጵያ ፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግር መላው እንደጠፋ ነው። ነውሩ በቀላሉ አይሸፈንም። ገበናው አደባባይ ለመውጣት ጊዜ አይፈጅበትም። በሀገር ደረጃም ሆነ በመስሪያ ቤት ደረጃ መርከቡ ሲሰምጥ ከመርከቡ ከመውረድ ይልቅ ያልሰጠመው የመርከቡ ክፍል ላይ ለመቀመጥ መጋፋት እንደ ፖለቲካዊ ቅልጥፍና ከተቆጠረ ሰንብቷል። ለዚህ የሚሰጡ ወቅታዊ የሚመስሉ፣ በጥናት የተደገፉ የሚባሉ፣ በስብሰባ የጋራ መግለጫ የታጀቡ፣ በአዳዲስ መመሪያ የተቀነበቡ አያሌ ሽፋኖች ይቀርባሉ። ችግሩ ግን፤ “የሚዳቋ ጅራት፣ እርቃኗንም አይሸፍን፣ አምላክንም አያስመሰግን፤” እንደሚባለው መሆኑ ነው።
ሂሩት በቀለ (1935 - 2015)
ሂሩት በቀለ ከ50ዎቹ መጀመሪያ እስከ 80ዎቹ መጨረሻ ድረስ በጊዜው ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ጥቂት ስመጥር የሴት አርቲስቶች መሐከል አንዷና ተወዳጅ ድምፃዊ ስትሆን፤ የግጥምና የዜማ ደራሲም ነች:: ሂሩት የተጫወተቻቸው ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዎቿ አሁን ድረስ በህዝብ ዘንድ በጣም ተወዳጅና እንደውም ለብዙ አዳዲስ ወጣት ሴት አርቲስቶች መነሳሻና አቅም መፈተሻ መሆናቸው ግልጽ ነው።
የህይወት ታሪክ
ሂሩት በቀለ በእለተ ሰኞ መስከረም 28 ቀን 1935 ዓ.ም. ከእናቷ ከወ/ሮ ተናኜወርቅ መኮንንና ከአባቷ የመቶ አለቃ በቀለ ክንፌ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ቀበና ተወለደች:: እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስም ቀበና ሚሲዩን ት/ቤት[1] በመግባት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷ ተከታትላለች::
የስራ ዝርዝር
ሂሩት በትምህርት ቤት በነበረችበት ወቅት ለክፍል ጓደኞቿና ለሰፈሯ ልጆች ማንጎራጎር ታዘወትር ነበር:: ይህን ችሎታዋን የተመለከቱት ጓደኞቿም ወደ ሙዚቃው አለም እንድትገባ በተደጋጋሚ ያበረታቷትና ይገፏፏት ነበር:: በዚህ መሰረት በ1951 ዓ.ም. ከቅርብ ጓደኛዋ ጋር በመሆን ወደ ምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል[2] በመሄድ በድምፃዊነት ተፈትና ለመቀጠር በቃች:: ብዙም ሳትቆይ ለመጀመሪያ ግዜ በተጫወተችው “የሐር ሸረሪት” በተሰኘው ዜማ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትንና ተቀባይነትን አገኘች:: ይሄኔ ነበር የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ክፍል አይኑን የጣለባት። ጥሎባትም አልቀረ፤ በ1952 ዓ.ም. ላይ ከምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል እውቅና ውጪ የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ሂሩትን በመጥለፍ በጊዜው ኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ወደሚባለው የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ በመውሰድ በልዩ ኮማንዶዎች የ24 ሰዓት ጥበቃ እየተደረገላት ከወር በላይ ተደብቃ ቆየች:: ከአንድ ወር ያላሰለሰ ጥረት በኋላ የምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል ፍለጋውን ለማቋረጥ በመገደዱ፣ የፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ክፍል ሂሩትን በይፋ በቋሚነት የሠራዊቱ የሙዚቃ ክፍል አባል አድርጎ ቀጠራት::
ሂሩት ከተጫወተቻቸው አያሌ ሙዚቃዎቿ መሀከል እንደ ህዝብ መዝሙር በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቀውና ከትንሽ እስከ ትልቅ በሀገር ፍቅር ስሜት እስካሁን የሚያዜመው “ኢትዮጵያ” አንዱ ነው::
ሂሩት በፖሊስ ሰራዊት የሙዚቃና የትያትር ክፍል ውስጥ በቅንነት ለ35 ዓመት አገልግላለች:: በእነዚህም 35 ዓመታት ውስጥ ከ200 በላይ ሙዚቃዎችን የተጫወተችና ለህዝብ ጆሮ ያደረሰች ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ በሸክላ የታተሙት ከ38 በላይ ሙዚቃዎች፣ በካሴት ደረጃ ደግሞ 14 ካሴቶች እያንዳንዳቸው 10 ዘፈኖችን የሚይዙ ለሙዚቃ አፍቃሪዎቿ አበርክታለች::
ሂሩት በሙዚቃ አለም በቆየችባቸው አያሌ አመታት ውስጥ ከብዙ ስመጥር ድምፃውያን ጋር በመሆን ስራዋን ለህዝብ አቅርባለች፤ ከነዚህም መሀከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል:- ማህሙድ አህመድ[3]: አለማየሁ እሸቴ[4]: ቴዎድሮስ ታደሰ: መልካሙ ተበጀ: ታደለ በቀለ: መስፍን ሀይሌ: ካሳሁን ገርማሞና ሌሎችም ይገኙበታል።
ሂሩት በቀለ ከ1987 ዓ.ም. በኋላ እራስዋን ከሙዚቃ አለም በማግለል፣ ጌታን እንደ ግል አዳኟ በመቀበል ሙሉ ጊዜዋንና ህይወቷን ለመንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት ከ28 ዓመት በላይ በአገር ውስጥና በውጭ አገር በመዘዋወር ስለጌታችን እየሱስ ክርስቶ ታላቅነት ላልሰሙ በማሰማት፣ አያሌ ወገኖች የእግዚአብሄርን መንገድ እንዲከተሉና ወደ ህይወት እንዲመጡ ምስክርነት በመስጠት፣ በጸሎት በመትጋት ጌታን በዝማሬ እያገለገለች ቆይታለች፡፡
ሂሩት በቀለ በሙዚቃ አለም በነበረችበት ጊዜ ከፍተኛ አድናቆትንና ዝናን ያተረፈች እንዲሁም ደግሞ በመንፈሳዊ ህይወቷ ደስታንና የመንፈስ እርካታን ያገኘች ቢሆንም፣ የግል ህይወቷን በተመለከተ ግን ያላትን ትርፍ ግዜ ሁሉ ከልጆቿና ከቤተሰቧ ጋር ማሳለፍ እጅግ አድርጎ ያስደስታት ነበር::
ሂሩት ከሙዚቃ ስራዋና ከመንፈሳዊ ህይወቷ በተጨማሪ፥ በጨዋታ አዋቂነቷም ትታወቃለች፡፡ ሂሩት በቀለ 7 ልጆችና 10 የልጅ ልጆችን አፍርታለች::
ሽልማቶች
ሂሩት በቀለ በሙያዋ ላበረከተችው አስተዋጽኦ ከአገር ውስጥና ከውጭ ሀገር በርካታ ሽልማትና የእውቅና ምስክር ወረቀት ያገኘች ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ለመጥቀስ ያህል:
1ኛ) ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ እጅ ከወርቅ የተሰራ የእጅ አምባር እና የምስጋና ደብዳቤ
2ኛ) ከኢትዮጵያ ፖሊስ ሰራዊት ኮሚሽነር የከፍተኛ ስኬትና የላቀ አስተዋጽዎ ሽልማት ከምስክር ወረቀት ጋር
3ኛ) በሙዚቃው ዓለም ላበረከተችው ተሳትፎ ከፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ የብር ዋንጫና የምስጋና ደብዳቤ
4ኛ) በሙዚቃው ዘርፍ ለእናት ሐገሯ ላበረከተችው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም እጅ ሰርተፍኬት
5ኛ) ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በኢትዮጵያና በሱዳን ህዝቦች መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማደስ ላበረከተችው አስተዋፅኦ የእውቅና የምስክር ወረቀት
6ኛ) ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላበረከተችው የሙዚቃ አስተዋፅዖ ከኢትዮጵያ አብዮታዊ ጦር የፖለቲካ አስተዳደር የምስጋና ደብዳቤና ሽልማት
7ኛ) ከፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ የቲያትር እና ሙዚቃ ክፍል የ25-ዓመታት ከፍተኛ ስኬት እና የላቀ አስተዋፅኦ የምስክር ደብዳቤ ከፍተኛ ሽልማት ጋር
8ኛ) ከቀድሞ የሰሜን ኮርያ ፕሬዘዳንት ኪም ኢል ሱንግ እጅ ከወርቅ የተሰራ ሜዳልያ
9ኛ) ከኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነር: ለፖሊስ ሃይል ስፖርት ፌስቲቫል ላበረከተችው አስተዋፅኦ የእውቅና ሰርተፍኬት
10ኛ) ከመሰረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን: ላበረከተችው አስተዋፅኦ ልዩ እውቅና እና የምስጋና ሰርተፍኬት
11ኛ) ከወንጌል ብርሃን አለማቀፍ አገልግሎት ቤተክርስቲያን: በሃይማኖታዊ ህይወት ላሳየችው ትጋትና አስተዋፅኦ የምስጋና ሰርተፍኬት ይገኙበታል፡፡
የታዋቂው የክላርኔት ተጫዋች ዳዊት ፍሬው የቀብር ስነ-ስርዓት እሁድ ይፈጸማል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስክሬኑን በነፃ አጓጉዟል
ታዋቂው የክላርኔት መሳሪያ ተጫዋች ዳዊት ፍሬው ኃይሉ የቀብር ስነ-ስርዓት ነገ እሁድ ግንቦት 6 ቀን 2015 ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ይፈጸማል። የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴው ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ዛሬ ከሰዓት በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ጸሎተ ፍትሀት የሚደረግ ሲሆን እሑድ ጠዋት በሀገር ፍቅር ቴያትር ቤት በተዘጋጀ የሽኝት ስነ-ሥርዓት ስንብት ተካሂዶ፣ ቀትር 7፡00 ሰዓት ላይ ቀብር ስነ-ስርዓቱ እንደሚፈጸም አስታውቋል።
ዳዊት በቅርቡ ለስራ ጣሊያን ሀገር በሄደበት ወቅት ባረፈበት የሆቴል ክፍል ሕይወቱ አልፎ መገኘቱ ይታወሳል። በሙዚቃ የሙያ ዘመኑ 3 የሙዚቃ አልበም የሰራው ዳዊት ፍሬው፤ የአንጋፋው ድምጻዊ ፍሬው ኃይሉ ልጅ ነው።
“የመሐረቡ ምስጢር” ለንባብ በቃ
በደራሲ እታለም እሸቴ የተጻፈው “የመሐረቡ ምስጢር” የተሰኘ ረዥም ልብወለድ መጽሐፍ ለንባብ የበቃ ሲሆን፤ በመጪው ሳምንት ቅዳሜ ግንቦት 12 ቀን 2015 ዓ.ም ከጠዋቱ 4 ሰዓት ጀምሮ በሐገር ፍቅር ቴአትር ቤት እንደሚመረቅ ታውቋል፡፡
በፖለቲካዊ ስላቅ ሥራዎቹ የሚታወቀው ሃማ ቱማ በመጽሐፉ ጀርባ ላይ ባሰፈረው አስተያየት፤ “ ---እኔ እንደ እታለም የረዥም ልብወለድ ታሪኮችን ጽፌ ለማቅረብ አልቻልኩም፡፡ እታለም ተራቀቅሁ፣ ከበድኩ፣ ተመጻደቅኹ በማይል ቋንቋ ከሦስት መቶ በላይ ገጾችን የሚያልፍና ከብዙኃኑ ህይወት ጋር የተሳሰረ ትረካን አስለምዳናለች፡፡ የተፈናቃዮችን ኑሮም እንኖረው ዘንድ በሚታመኑ ገጸባህርያት አማካኝነት አቅርባልናለች፡፡ --- እታለም ከዘመናችን የረዥም ልብወለድ ደራሲዎች አንዷና መነበብም ያለባት ናት እላለሁ፡፡” ብሏል፡፡ ደራሲዋ ከዚህ ቀደም “ምንዳ” (2001 ዓ.ም)፣ “ህልመኛዋ እናት” (2004 ዓ.ም) ፣ “ተፈናቃይ ፍቅር” (2008 ዓ.ም) የተሰኙ ረዥም ልብወለድ መጻሕፍትን ለአንባቢያን አድርሳለች፡፡
ሥራ አስፈፃሚው በቢሯቸው ተገደሉ
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አለባቸው አሞኜ በትላንትናው ዕለት በቢሯቸው ውስጥ መገደላቸው ተሰምቷል። ዋና ሥራ አስፈጻሚው በቢሯቸው ውስጥ ባለጉዳዮችን ተቀብለው በሚያነጋግሩበት ወቅት ባለጉዳይ ሆኖ ወደ ቢሮአቸው በገባ ሰው በተፈጸመባቸው ጥቃት ህይወታአው ማለፉ ነው የተነገረው። ግድያውን የፈጸመው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የካሳንቺስ አካባቢ ጣቢያ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት የቀጠና ኦፊሰር እንደሆነና በቁጥጥር ስር መዋሉንና ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
“ኮስፓ” የተሰኘ ድርጅት ህፃናትን ከጎዳና በማንሳት ሥራ ላይ መሰማራቱን አስታወቀ
በአዲስ አበባና በሻሸመኔ ስራውን በይፋ ጀምሯል
“ኮንሰርኒንግ ኦፍ ክርኤቲቭ ፕሮቫይዲንግ ኦሶሴሽን (ኮስፓ)” የተሰኘው ድርጅት ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ህፃናትን በማንሳትና በመንከባከብ እንዲሁም ወደ ትምህርት፣ ወደ ስራና ወደ ቤተሰብ መልሶ በመቀላቀል ስራ ላይ በይፋ መሰማራቱን አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ ትላንት ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም ረፋድ ላይ በጊዮን ሆቴል ዳሽን አዳራሽ ለሚዲያ ባለሙያዎች በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው ይህን ያስታወቀው፡፡
በበጎ አድራጎትና ማህበራት ኤጀንሲ በ2012 ዓ.ም በአገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጀትነት እንደተመሰረተና በአገር ወዳድ ምሁራን እንደተቋቋመ የተነገረለት ድርጅቱ፤ ከዓለም ባንክና ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራርሞ በአዲስ አበባና በሻሸመኔ ከተማ በይፋ ስራ መጀመሩም በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተብራርቷል፡፡
እንደ ሀላፊዎቹ ገለፃ፤ ኮስፓ የጎዳና ልጆችን ከጎዳና ላይ አንስቶ የማገገሚያ ማዕከል በማስገባት የአካልና የስነልቦና ህክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ልጆቹ ለጎዳና ህይወት የተዳረጉበትን ሥረ-መሰረት በመለየት፣ በልጆቹ ቤተሰብ ላይም ጥናትን መሰረት ያደረገ ስራ እንደሚሰራ ተገልጿል። በዚህም መሰረት ልጆቹ ከቤት የወጡት በኢኮኖሚ ችግር ነው በቤተሰብ ቀውስ፣ ወይስ በድርቅ፣ በጦርነትና ተያያዥ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮች የሚውለውን በጥናት በመለየት፣ ቤተሰባቸው ከዚህ ችግር ወጥቶ በኮስፓ ማዕከል በአዕምሮም በአካልም አገግመው የሚመለሱ ልጆቻቸውን እንዲቀበሉ ብሎም ድጋሚ ወደ ጎዳና እንዳይለቀቁ እስከማድረግ ድረስ በመስራት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ እንደሚሞከር ተብራርቷል።
ኮስፓ እ.ኤ.አ እስከ 2030 ዓ.ም ድረስ በሀገሪቱ አሉ ተብለው የሚገመቱ ከ150ሺህ በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በግማሽ ለመቀነስ እንደሚሰራ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፤ ተልዕኮውም በሂደት አገሪቱ ላይ የጎዳና ልጆች የማይታዩበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሆነ ጠቅሶ ይህ እንዲሳካ ለዚህም ትልሙ ስኬት የየከተሞቹ አስተዳደሮች ማህበረሰቡና ሚዲያው በጋራ አብሮ በትብብር እንዲሰራ ጥሪ አቅርቧል።
ኮስፓ በአሁኑ ሰዓት 20 የጎዳና ተዳዳሪ ልጆችን አንስቶ በሻሸመኔ ማዕከሉ እየተንከባከበ ሲሆን በተለያዩ ከተሞች ስራውን የማስፋት እቅድ እንዳለውም ሃላፊዎቹ ገልጸዋል። ህፃናት ወደ ጎዳና የሚወጡበትን ሁኔታ ለመቀነስም በተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በትጋት እንደሚሰራ በመግለጫው ተብራርቷል።
በአዲስ አበባ የመንግስት መ/ቤቶች የስራ ሰዓትን ወደ 16 ሰዓት ለማራዘም እየተሰራ ነው- ተባለ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙ የመንግስት የስራ ተቋማት አገልግሎት የሚሰጡበትን ሰዓት ከ8 ሰዓት ወደ 16 ሰዓት ለማራዘም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተነግሯል፡፡ መ/ቤቶቹ አገልግሎታቸውን እስከ ምሽት ድረስ እንዲሰጡ የማድረጉ ተግባር የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴም ያነቃቃል ተብሏል፡፡የከተማ አስተዳደሩ የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ባካሄዱት የጋራ ውይይት ላይ ይፋ የተደረገው እቅድ እንደሚያመለክተው፤ በከተማዋ የሚታየውን የተገልጋዮችን ችግርና መጉላላት ለመቅረፍ የሚቻልበት መንገድ እየተፈለገ ነው፡፡
የመንግስት መ/ቤቶች ለተገልጋዮች በሚሰጡት አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እየቀረቡ መሆኑን የሚጠቁመው ዕቅዱ፤ ይህን ቅሬታና ችግር ለመፍታት የአገልግሎት ሰዓቱን ወደ 16 ሰዓት ማራዘም እንደ አንድ መፍትሄ መወሰዱንና ይህም ለመተግበር እየተሰራ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።በዚሁ የመንግስት ስራን ወደ 16 ሰዓት ለማራዘም በተያዘው እቅድ ሰራተኞች በፈረቃ የሚሰሩበት ሁኔታ ሊመቻች እንደሚችልና አሰራሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞችን አዋጅ የማይጥስ እንደሚሆንም ተነግሯል፡፡ የከተማው አስተዳደር የመ/ቤቶቹን የአገልግሎት ሰዓት የማራዘም ፈቃዱን ተግባራዊ ለማድረግ ጥናት እያካሄደ መሆኑንና በመጪው በጀት ዓመት ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
50ኛው የዓለም አካባቢ ጥበቃ ቀን በተለያዩ መርሃ ግብሮች ሊከበር ነው
50ኛው የአለም አካባቢ ጥበቃ ቀን ከግንቦት 25-27 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ጎልፍ ክለብ ጋርደን ውስጥ ይከበራል፡፡
“የፕላስቲክ ብክለትን እንግታ” በሚል መሪ ቃል ለ3 ቀናት በሚከበረው በዚሁ በዓል ላይ አንድ መቶ የሚደርሱ በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ የተሰማሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚሳተፉበት የአለም አካባቢ ቀን ኤክስፖ 2015 እንደሚከናወን አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንና ካሪቡ ኤቨንትስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት በጋራ በሚያዘጋጁት በዚሁ ፕሮግራም ላይ የምድራችን አየር ንብረቷን የሚበክሉ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ከመጠቀም እንቆጠብ በሚል ሰፋ ያለ ትምህርታዊ ዝግጅቶች እንደሚኖሩትም ተገልጿል፡፡ በዚህ ዝግጅት ላይ ምድራችንና አየር ንብረቷን የማይበክሉ (Eco frindely) የሆኑ ምርቶችንና አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ የግሉ ዘርፍ ተቋማት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ባለ ድርሻ መንግስታዊ የሆኑ አካላት እንዲሳተፉም አዘጋጆቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ቴክኖ ሞባይል አዳዲስ የስፓርክ 10 ሲሪይስ ስልኮቹን ይፋ አደረገ
ቴክኖ ሞባይል፤ አዳዲስ የስፓርክ 10 (Tecno Spark 10) ሲሪይስ ሞዴል ምርቶቹን ትናንት ይፋ አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ70 በላይ በሚሆኑ አለማቀፍ ገበያዎች ላይ በተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘው ቴክኖ ሞባይል፤ ትናንት በተከፈተውና ለሁለት ቀናት በሚቆየው ዝግጅት፤ የስፓርክ 10፣ ስፓርክ 10ሲ እና ስፓርክ 10 ፕሮ ሞዴሎችን ለገበያ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡ ስልኮቹ ዘመናዊ የፊትለፊት ካሜራ ያላቸውና ተገልጋዮች ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችሉ መሆናቸውም በዚሁ የምርት ማስተዋወቂያ ስነስርዓት ላይ ተገልጿል፡፡
ትራንስሚሽን ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (ቴክኖ ሞባይል) ጎሮ አካባቢ በሚገኘው የአይሲቲ ፓርክ ባስገነባው ዘመናዊ ፋብሪካው የተለያዩ ዓይነት የስልክ ምርቶችን በመገጣጠም ለሀገር ውስጥና ለውጭ አገር ገበያዎች የሚያቀርብ ተቋም ነው፡፡
ብርሃን ባንክ ከ51 በላይ ወለሎች ያሉት ህንጻ ሊያስገነባ ነው
ለዋና መሥሪያቤቱ ህንጻ ያሸነፈውን ዲዛይን ይፋ አደረገ
ብርሃን ባንክ ከ51 በላይ ወለሎች ያሉት ህንጻ ሊያስገነባ ሲሆን፤ ለዋና መሥሪያቤቱ ህንፃ ግንባታ ዲዛይን ለማሠራት ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ አሸናፊ ሆኖ የተመረጠውን ዲዛይን ይፋ አደረገ።
ባንኩ ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ላይ 16 ኩባንያዎች የተሳተፉ ሲሆን ተሳታፊዎቹ ካቀረቧቸው ዲዛይኖች መካከል አሸናፊ የሆነው ዲዛይን ግንቦት 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ምሽት በተካሄደ ፕሮግራም ላይ ይፋ ተደርጓል።
ባንኩ በሰንጋ ተራ አካባቢ በተረከበው 5400 ካሬ ሜትር መሬት ላይ ለሚያስገነባው ህንፃ MAE ኮንሰልቲንግ ኤንድ ኢንጂነርስ በተባለው ድርጅት የቀረበው ዲዛይን አሸናፊ ሆኖ ተመርጧል። በተመረጠው ዲዛይን መሠረት የሚገነባው የባንኩ ዋና መሥሪያቤት ህንፃ ከ 51 በላይ ወለሎች ይኖሩታል ተብሏል፡፡
በዴጃው ኮንሰልቲንግ የተሰራው የህንፃ ዲዛይን ሁለተኛ ደረጃ አሸናፊ ሲሆን ፣ በአዲስ መብራቱ ኮንሰልቲንግ ኤንድ ኢንጂነርስ የቀረበው ዲዛይን ደግሞ ሦስተኛ ወጥቷል።