Administrator

Administrator

 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2019 እኤአ ላይ ካሜሮን ለምታስተናግደው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚያደርገውን የምድብ ማጣርያ ከወር በኋላ ቢጀምርም፤ አስፈላጊውን የተሟላ ዝግጅት በተያዘው እቅድ መሰረት ለማከናወን አልቻለም። አዲሱ ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለስፖርት አድማስ እንደገለፁት በመጀመሪያ ምርጫቸው ለብሔራዊ ቡድኑ 29 ተጨዋቾችን በመመልመልና የአንድ ወር የዝግጅት እቅዳቸውን ለፌደሬሽኑ ከሳምንት በፊት አቅርበው ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ፤ ከጥሎ ማለፍ እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ በተያያዘ ባሉት የጨዋታ መደራረቦች ሳቢያ እቅዳቸውን ሊተገብሩ አልቻሉም፡፡ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ባስተላለፈው ውሳኔ ግን ከጋና ጋር ከሚደረገው ጨዋታ በፊት ዋልያዎቹን ለ10 ቀናት ብቻ እንዲያዘጋጁ ወስኖባቸዋል፡፡ ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለፌደሬሽኑ ያቀረቡትን የ1 ወር የዝግጅት እቅድ እንዳብራሩት፤ 3 የወዳጅነት ጨዋታዎችን ከከተማ ውጭ ለማድረግ፤ የተለያዩ የልምምድ መርሃ ግብሮችን ለመስራት፤ የተጨዋቾችን የጤና ሁኔታዎችና ወቅታዊ አቋም በመገንዘብ ቡድኑን ለማዋሃድና የመጨረሻ ቡድናቸውን ዝርዝር ለማሳወቅ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ ይሁንና የክለቦች መልካም ፈቃደኝነት ባለመኖሩ የዝግጅት ጊዜው ከ1 ወር ወደ አስር ቀናት እንዲያጥር እንዲሁም የወዳጅነት ጨዋታዎች ብዛትም ከ3 ወደ አንድ እንዲቀነስ ግድ ሆኗል፡፡
ለ6 ወራት ያለአንዳች ውድድር ተበትነው የቆዩት  ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫው የምድብ ማጣርያ በምድብ 6 ከጋና፤ ከኬንያና ከሴራሊዮን መደልደላቸው ይታወቃል፡፡ ከወር በኋላ የመጀመርያ ጨዋታቸውን  የሚያደርጉት ከሜዳ ውጭ ከጋና ብሄራዊ ቡድን ጋር ይሆናል፡፡ ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለስፖርት አድማስ በሰጡት አስተያየት የብሄራዊ ቡድኑ ባለቤት ህዝቡ እና ሁላችን ነን ብለው፤ በቴክኒክ ኮሚቴ ፀድቆ የቀረበውን የ1 ወር የዝግጅት እቅዳቸውን የፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ወደ 10 ቀናት ለማሳጠር መወሰኑን በመቃወም በከፍተኛ ደረጃ መከራከራቸውን አስገንዝበዋል፡፡ ፌደሬሽኑ፤ የክለብ አሰልጣኞች እና አመራሮች፤ ሚዲያ እና ህዝቡ ለብሄራዊ ቡድኑ የሚሰጠውን ትኩረት ለማሳደግ   በጋራ  እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ያቀረቡት ዋና  አሰልጣኙ፤ የዝግጅት እቅዶች ተለዋዋጭ መሆን የለባቸውም ሲሉም ያሳስባሉ፡፡ ክለቦች በጠቅላላ ጉባኤ በጋራ የደረሱበት ስምምነት ላይም በድጋሚ ምክክር በማድረግ እንዲሰሩም ይመክራሉ፡፡
በሌላ በኩል ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ የሚያደርገው ተሳትፎ በተወሰነ መልኩ ጫና መፍጠሩ አይቀርም የሚሉት ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኮንጎው ክለብ ኤኤስ ቪታ ጋር በሜዳው የሚያደርገው ሁለተኛ ጨዋታም ከዋልያዎቹ የጨዋታ መርሃ ግብር የሚደራረብበት ሁኔታ እንደሚያስጨንቃቸውም ጠቁመዋል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያውን ከሜዳ ውጭ ከጋና ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ መጀመራቸው ፈታኝ እንደሚሆን ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ ሲያስገነዝቡ የ10 ቀናት ዝግጅቱ ሙሉና ውጤታማ ቡድን ለመገንባት እንደሚያስቸግራቸው አልሸሸጉም፡፡ በብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ አጀማመር ስኬታማ ለመሆን በተለዋጭ እቅዶች እየተንቀሳቀስኩ ነው ግን ብለዋል፡፡ በተለይ የጋና ብሄራዊ ቡድን በቅርብ ጊዜያት ያደረጋቸውን ሦስት ጨዋታዎች ቪዲዮ በጥልቀት እንደተመለከትን በተለያዩ የዓለም ሀገራት ያሉ የጋና ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች እንቅስቃሴም ስከታተል ቆይቻለሁ ብሏል፡፡ ከምድብ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ ከመደረጉ 1 ሳምንት በፊት ከኡጋንዳ  ብሄራዊ ቡድን ጋር የሚያደርጉት የወዳጅነት ጨዋታ ቋሚ ተሰላፊዎቻቸውንና፤ አጠቃላይ የቡድኑን ስብስብ ለመለየት የምጠቀምበት ይሆናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለአዲሱ ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የብሄራዊ ቡድኑን ሙሉ ሃላፊነት  ካስረከባቸው  ሳምንታት አልፈዋል፡፡  በውል ስምምነቱ እንደተጠቀሰው የዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ሆነው ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የሚሰሩ ሲሆን፤ በ2019 እኤአ ላይ ካሜሮን ለምታስተናግደው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ማብቃት እንዳለባቸው ተገልፆላቸዋል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለዋና አሰልጣኙ ውላቸው በስምምነት እስካልተቋረጠ ድረስም ከስልክ፣ መኪና እና ሹፌር እንዲሁም የጤና መድህን ወጭዎችና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ጋር በወር ያልተጣራ 100000 ብር ደመወዝ እንደሚከፍላቸው ይታወቃል፡፡ ከሳምንት በፊት የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ኮሚቴ እና ስራ አስፈፃሚው ባፀደቀላቸው መሰረት ዋና አሰልጣኙ ሁለት ረዳት አሰልጣኞች የቅዱስ ጊዮርጊሱ ምክትል አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ እና የመከላከያ አሰልጣኝ በለጠ ገብረኪዳን ናቸው፡፡  ፀጋ ዘአብ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ሆኖ ሲመደብ፣ ይስሃቅ ሽፈራው የብሄራዊ ቡድኑ ወጌሻ እንዲሁም ዶክተር አያሌው የቡድኑ ሃኪም ሆነው ይሰራሉ፡፡ የስነ ልቦና እና የስነ ምግብ ባለሙያዎችን የፌደሬሽኑ የህክምና ኮሚቴ ከስራ አስፈፃሚው ጋር በመመካከር የሚያሳውቁ ይሆናል፡፡
ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ትውልዳቸው በምዕራብ ሸዋ ዞን ኮደዱላ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ሲሆን፤ ለበርካታ ዓመታት እግር ኳስን ተጫውተዋል፡፡ ላለፉት 24 ዓመታት በተለያዩ ክለቦች በአሰልጣኝነት ያገለገሉ ናቸው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ባንኮች፣ መከላከያ፣ ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ ክለቦችን  በማሰልጠን  ሰፊ ልምድ ያካበቱ ሲሆን የፕሪሚዬር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት ባይችሉም ጠንካራ ቡድን  በሚገነቡበት አሰራራቸው ይታወቃሉ፡፡ በ1995 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን በማሰልጠን የሰሩ ሲሆን ለሦስት ዓመት ከሉሲዎቹ ጋር ሲያሳልፉ ለሦስተኛ ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፉ በማድረግም ውጤታማ ነበሩ፡፡
ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከፌደሬሽኑ ጋር ውሉን በፈረሙበት ወቅት ለ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ብቻ ሳይሆን ሩብ ፍፃሜ መግባት ዕቅዳቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተለያየ ምክንያት ከብሄራዊ ቡድኑ ያገለሉ ተጫዋቾችንም ወደ ቡድኑ ሊመለሱ  እንደሚችሉም አስታውቀው ነበር፡፡ ይህን አስመልክቶ ዋና አሰልጣኙ ለስፖርት አድማስ በሰጡት አስተያየት ከቀድሞ ተጨዋቾች ወደ ብሄራዊ ቡድኑ እንዲመለስ በተለይ ጥረት ያደረጉት የቅዱስ ጊዮርጊሱን አዳነ ግርማ በማነጋገር ነበር፡፡ ‹‹አዳነን  ወደ ቡድኑ እንዲመለስ ስጠይቀው በቅርበት አግኝቼው ነው። ሁሌም ለአገሩ ለማገልገል ፍላጎት እንዳለው ገልፆልኝ በተለያዩ የግል ምክንያቶች  ግን ወደ ቡድኑ ለመመለስ እንደሚከብደው አስረድቶኛል፡፡ እኔም ሙሉ ለሙሉ አቋሙን ተረድቼ ውሳኔውን ተቀብያለሁ›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ለብሄራዊ ቡድን በመጀመርያ ምርጫ የጠሯቸውን ተጨዋቾች ስም ዝርዝር እስካሁን ያላሳወቁት ዋና አሰልጣኙ፤ በውጭ ካሉ ተጨዋቾች በተለይ በግብፅ የሚገኙት የአጥቂ መስመር ተሰላፊው ኡመድ ኡክሪና አማካዩ ሽመልስ በቀለ ለብሄራዊ በድኑ ለመሰለፍ መልካም ፈቃዳቸውንና ጉጉታቸውን መግለፃቸውንም ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2019 እኤአ ካሜሮን ወደምታስተናግደው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው የምድብ ማጣርያ በምድብ ስድስት የሚገኙ ሌሎቹ ቡድኖች ወደ ካምፕ ገብተው በመሰባሰብ ባይሆንም በተለያያ መንገድ ዝግጅቶቻቸውን ከጀመሩ ሳምንታት ተቆጥረዋል። በተለይ ኬንያ ለምድብ ማጣርያው ከፍተኛ ትኩረት የሰጠች ሲሆን የመጀመርያውን የወዳጅነት ጨዋታ ከሳምንት በፊት ከማላዊ ብሄራዊ ቡድን  በናይሮቢ አድርጋ ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡ የሃራምቤ ኮከቦች የሚባለውን የኬንያ ብሄራዊ ቡድን በዋና አሰልጣኝነት የሚመሩት ስታንሊ አኩዋምቢ ናቸው፡፡ ሰሞኑን ለዴይሊ ኔሽን በሰጡት አስተያየት በአፍሪካ ዋንጫ እና የቻን ውድድር በሚኖራቸው ዝግጅቶች ስኬታማ መሆን የሚቻለው የፌደሬሽን እና የፕሪሚዬር ሊግ አስተዳደር ትብብርና ድጋፍ ሲሰጡ ነው ብለዋል፡፡ ለብሄራዊ ቡድኑ ጠንካራ እና የተሟላ ዝግጅት ሲባል የፕሪሚዬር ሊጉ አስተዳደር በጨዋታዎች መርሃ ግብር ላይ የተወሰኑ ሽግሽጎችን እንዲያደርግ የጠየቁት ስታንሊ አኩዋምቢ፤ ክለቦች ወሳኝ ተጨዋቾቻቸውን በአስፈላጊው ወቅት በመልቀቅ እንዲተባበበሩ እና በየወሩ ቢያንስ  የወዳጅነት ጨዋታ ፌደሬሽኑ እንዲያዘጋጅላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በሌላ በኩል ከምድቡ ሰፊ የማለፍ እድል እንደያዘ የሚነገርለት የጋና ብሄራዊ ቡድን በዋና አሰልጣኝነት የሚመሩት ኩዋሲ አፒያህ ሲሆኑ ወደ ሃላፊነቱ የመጡት ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ አሰልጣኙ የጋና ህዝብ በአፍሪካ ዋንጫ እና በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን አምበሉ  አሰሞሃ ጊያንም ተመሳሳይ መልዕክት ነበረው፡፡ አሳሞሃ ጊያን ለጋና ክሮኒክል በቅርቡ በሰጠው አስተያየት በጋና ፕሪሚዬር ሊግ እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያሉ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች  ለብሄራዊ ቡድኑ ቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸው መክሯል፡፡ ከ2012 እስከ 2014 የጋና ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት ኩዋሲ አፕያህ በድጋሚ ጥቋቁር ክዋክብቶችን እንዲመሩ ሲመረጡ የሁለት ዓመት የቅጥር ኮንትራት  ተፈራመዋል፡፡ የጋና ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫው ሻምፒዮን እንዲያደርጉ እና ለ2018 የራሽያ ዓለም ዋንጫ እንዲያሳልፉ የጋና እግር ኳስ ፌደሬሽን ይፈልጋል፡፡

                 የምድብ 6 ጨዋታዎች

• ጁን 9 ፤ 2017 እኤአ ጋና ከኢትዮጵያ - ሴራሊዮን ከኬንያ
• ማርች 23፤ 2018 እኤአ ኢትዮጵያ ከሴራሊዮን - ኬንያ ከጋና
• ሴምፕተምበር 5 ፤ 2018 እኤአ ጋና ከሴራሊዮን - ኢትዮጵያ ከኬንያ
• ሴፕቴምበር 9፤ 2018 እኤአ ሴራሊዮን ከጋና - ኬንያ ከኢትዮጵያ
• ኦክቶበር 12 ፤ 2018 እኤአ ኢትዮጵያ ከጋና - ኬንያ ከሴራሊዮን
• ኖቬምበር 9፤ 2018 እኤአሴራሊዮን ከኢትዮጵያ - ጋና ከኬንያ

 የታንዛኒያ መንግስት በሃሰተኛና በተጭበረበሩ የትምህርት ማስረጃዎችና የኮሌጅ ሰርተፍኬቶች አማካይነት በተለያዩ የመንግስት የስራ መደቦች ላይ ተቀጥረው ሲሰሩ የተገኙ 9 ሺህ 900 የአገሪቱ ሰራተኞችን ከስራ ገበታቸው ማባረሩ ተዘግቧል፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆን ሙጉፋሊ ሙስናን ለመዋጋት በብሄራዊ ደረጃ ያወጁት ዘመቻ አካል በሆነው በዚህ እርምጃ፣ በመላ አገሪቱ በተከናወነ ምርመራ፣ በሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ተቀጥረው ሲሰሩ የተገኙት ከ9 ሺህ 900 በላይ የመንግስት ሰራተኞች በአስቸኳይ ከስራ እንደዲባረሩ መደረጋቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
በተከናወነው የመንግስት ሰራተኞች የትምህርት ማስረጃ ማጣራት ስራ፣ የ1ሺህ 500 ያህል ሰራተኞች ትክክለኛ የትምህርት ማስረጃዎች በተጭበረበረ መልኩ እንደገና ተስተካክለው ለብዙ ሰራተኞች የትምህርት ማስረጃ ሆነው እንደቀረቡ መረጋገጡንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ባለፈው መጋቢት ወር ላይ በተከናወነ ተመሳሳይ ምርመራ፣ በስራ ገበታቸው ላይ ለሌሉ 20ሺ ገደማ ሰራተኞች ደመወዝ እንደሚከፈላቸውና በዚህም አገሪቱ በየአመቱ በአማካይ 82 ሚሊዮን ፓውንድ  እንደምታጣ መረጋገጡንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

የአውሮፓ ህብረት፤ እንግሊዝ ከህብረቱ አባልነት ለመውጣት ያከናወነቺውን ህዝበ ውሳኔ ተፈጻሚ ለማድረግና ጠቅልላ ለመውጣት በቅድሚያ 100 ቢሊዮን ዩሮ እንድትከፍል የሚያስገድድ መመሪያ ሊያወጣ እየተዘጋጀ ነው የተባለ ሲሆን፣ የብሬግዚት ሚኒስትሩ አገራቸው የተባለውን ክፍያ እንደማትፈጽም አስታውቀዋል፡፡
ህብረቱ እንግሊዝን ይህን ያህል ገንዘብ ለማስከፈል ማቀዱን ፋይናንሺያል ታይምስ ጋዜጣ ሰሞኑን መዘገቡን ተከትሎ፣ ሚኒስትሩ ዴቪድ ዴቪስ እንግሊዝ ክፍያውን አትፈጽምም ሲሉ በይፋ ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የእንግሊዝ መንግስት ይህን ያህል ገንዘብ እንዲከፍል ከአውሮፓ ህብረት በይፋ የቀረበለት ጥያቄ እንደሌለ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ የተባለውን ክፍያ እንድንከፍል የሚያስገድዱ ህጎች እንዳሉና እንደሌሉ በዝርዝር ከመወያየት በዘለለ 100 በሊዮን ዩሮ አንከፍልም ሲሉም አክለዋል፡፡  
ህብረቱ እንግሊዝን 100 ቢሊዮን ዩሮ ያህል ገንዘብ ለማስከፈል ያቀደው ከአባልነቷ በመውጣቷ ሳቢያ የሚከሰቱ ወጪዎችን ለማካካስ ነው መባሉን የጠቆመው ዘገባው፣ የገንዘብ ክፍያው እንዲፈጸም ጥያቄውን ያነሱት አገራትም ፈረንሳይና ጀርመን ሊሆኑ ይችላሉ መባሉንም ገልጧል፡፡

  የኡጋንዳ ፖሊስ ባለፈው ረቡዕ የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀንን ለማክበር በመዲናዋ ካምፓላ ወደሚገኙ ጎዳናዎች ከወጡ የአገሪቱ ጋዜጠኞች መካከል ስድስቱን ማሰሩን ኒውስዊክ ዘግቧል፡፡
የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን የት ይከበር በሚለው ጉዳይ ላይ በኡጋንዳ የጋዜጠኞች ማህበር አመራሮች መካከል ልዩነት መፈጠሩን ተከትሎ፣ የተወሰኑ የማህበሩ አባላት ዕለቱን ለማክበር ወደ አደባባይ ወጥተው በአመራሮቻቸው ላይ ተቃውሟቸውን ባሰሙበት ወቅት የከተማዋ ፖሊስ “ሰልፉን ለማካሄድ ህጋዊ ፈቃድ አላገኛችሁም” በሚል ስድስት ያህል ጋዜጠኞችን ማሰሩን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የከተማዋ ፖሊስ በፕሬስ ነጻነት ቀን በጋዜጠኞች ላይ የወሰደው እርምጃ የመንግስት ባለስልጣናትን ማስቆጣቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለስልጣናቱ ባስተላለፉት ፈጣን ትዕዛዝ ጋዜጠኞቹ ክስ ሳይመሰረትባቸው በሰዓታት ልዩነት ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ የተባለው አለማቀፍ ተቋም ባለፈው ሳምንት ባወጣው የ2017 የአለማችን አገራት የፕሬስ ነጻነት ደረጃ  መሰረት፤ ኡጋንዳ በፕሬስ ነጻነት ከአለማችን 180 አገራት 112ኛ ደረጃን መያዟንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

  በፌስቡክ የማህበራዊ ድረገጽ በኩል ጽንፈኝነትን የሚያስፋፉና አንባቢያንን የሚያሸብሩ መልዕክቶችን የሚያሰራጩ ተጠቃሚዎችን የሚያድኑና እርምጃ የሚወስዱ ተጨማሪ 3 ሺህ ተቆጣጣሪ ሰራተኞችን ቀጥሮ ሊያሰማራ እንደሆነ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን ወደ ጽንፈኝነት የሚስቡና የፍርሃትና የመሸበር ስሜትን የሚፈጥሩ መልዕክቶችና ቪዲዮዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተበራከቱ መምጣታቸውን ተከትሎ፣ የኩባንያው መስራች ማርክ ዙከርበርግ ጉዳዩን ለመግታት በማሰብ፣ ተጨማሪ ተቆጣጣሪዎችን ቀጥሮ ወደ ስራ እንደሚያስገባ ባለፈው ረቡዕ አስታውቋል፡፡
ተጠቃሚዎች መሰል መልዕክቶችንና ቪዲዮዎችን በፌስቡክ ላይ ሲያገኙ በአፋጣኝ ለኩባንያው 4ሺህ 500 ያህል ተቆጣጣሪዎች ጥቆማ መስጠት የሚችሉበት አሰራር ተቀይሶ እየተሰራበት እንደሚገኝ የተነገረ ሲሆን ኩባንያው ድርጊቱን በፈጸሙ ተጠቃሚዎች ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንደሚወስድም ተነግሯል፡፡
ፌስቡክ በየሳምንቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መሰል ጥቆማዎችና የቅሬታ መልዕክቶች እንደሚደርሱት የዘገበው ዘ ጋርዲያን፣ እነዚህን በርካታ ጉዳዮች አጣርቶ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንዲችል እስከ አመቱ መጨረሻ ድረስ ተጨማሪ 3 ሺህ ያህል ተቆጣጣሪዎችን ለመቅጠር ማቀዱንም ገልጧል፡፡

 አቶ ዳጂ ጃራ ኩምቢ በተባሉ ባለሀብት በአዳማ ከተማ ወንጂ መታጠፊያ ላይ የተሰራውና 55 ዘመናዊ የመኝታ ክፍሎች ያሉት ደንበል ቪው ኢንተርናሽናል ሆቴል ዛሬ ይመረቃል፡፡ ሆቴሉ ሁሉም ነገር የተሟሉለት ሱትስ፣ 2 ደሉክስ ቲውን፣ 21 ደሉክስ ስታንዳርድ፣ 13 ሲንግል ስታንዳርድና 12 ሲንግል ክፍሎች ሲኖሩት፣ ከ30 እስከ 300 ሰዎች ማስተናገድ የሚችሉ 4 አዳራሾች አሉት፡፡ ክፍሎቹ፣ ቲቪ፣ ስልክ፣ ጠረጴዛና ወንበር፣ ሶፋ፣ ሻወር፣ ነፃ ዋይፋይ … ያሉት ሲሆን እንግዶችን የሚያረካ አገልግሎትና መስተንግዶ ለመስጠት እየተጠባበቀ ነው ተብሏል፡፡

   ‹‹ለሠራተኞቻችን በምንሰጠው ልዩ ትኩረት እንለያለን››
                      
     በእንግዶች፣ በሠራተኞችና አብረውት በሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ተመራጭ እንዲሆን በትጋት እንደሚሰራ የጠቆመው ሳፋሪ አዲስ ሆቴል፤ የዛሬ ሁለት ሳምንት በይፋ ሥራ እንደሚጀምር ተገልጿል።
የሳፋሪ አዲስ ሆቴል ልዩ አማካሪ አቶ ዜናዊ መስፍንና የሆቴሉ ማኔጅመንት አባላት ባለፈው ማክሰኞ በቦሌ መንገድ ከቴሌ ዝቅ ብሎ በሚገኘው የሆቴሉ አዳራሽ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የሆቴሉ ዓላማ ልዩ አገልግሎት በመስጠት በሆቴል ኢንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግና የአገሪቱን ቱሪዝም ገጽታ መቀየር ነው ብለዋል፡፡
በ1,3000 ስኩዌር ሜትር ላይ ያረፈው የዚህ ሆቴል ግንባታ 6 ዓመት እንደፈጀ የጠቀሱት የሆቴሉ ልዩ አማካሪ አቶ ዜናዊ፣ አሁን ዝግጅቱን አጠናቅቆ ግንቦት 5 በይፋ ስራ ይጀምራል ብለዋል፡፡
ሳፋሪ ማለት እንደ ወርቅ፣ አልማዝ፣ ፐርልና መሰል ማዕድናት የከበረ ድንጋይ ስያሜ ነው ያሉት ልዩ አማካሪው፤ ላለፉት 30 ዓመታት በወርቅና የከበሩ ድንጋዮች ንግድ ላይ ተሰማርተው የቆዩት የሆቴሉ ባለቤት አቶ ፍስሐ አባይ፣ ለሥራቸው ክብርና ማስታወሻ ይሆን ዘንድ ሆቴሉን ‹‹ሳፋሪ›› ብለው መሰየማቸውን ገልጸዋል፡፡
ሆቴሉ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ 64 ደሉክስ፣ 8 ባለ ሁለት አልጋ (ትዊንስ)፣ 26 ሱትና 24 ስታንዳርድ የመኝታ ክፍሎች ሲኖሩት፣ ረዥም ጊዜ የሚቆዩ እንግዶች፣ ምግባቸውን የሚያዘጋጁባቸው 8 አፓርትመንት ክፍሎች ከተሟላ የወጥ ቤት ዕቃዎች ጋር ተደራጅተው ይጠብቋቸዋል፡፡
2 ሬስቶራንቶችና 3 ባሮች ያሉት ይኼው ሆቴል፤ ከ20-50 ሰዎች ማስተናገድ የሚችሉ አራት አዳራሾች ያሉት ሲሆን በሆቴሉ ላረፉ እንግዶችና ለውጭ ተጠቃሚዎች የጂምናዚየምና የስፓ  (ስቲም፣ ሳውና፣ ጃኩዚ ማሳጅ) አገልግሎት በባለሙያ ይሰጣል፡፡  ለወንዶችና ለሴቶች የፀጉር ውበት፣ የእጅና የእግር ጥፍር ማስዋቢያ አገልግሎት እንደሚሰጥም ታውቋል፡፡
ሆቴሉ፣ 60 መኪኖችን ማቆም የሚችል ስፍራ ሲኖረው፤  ቦታው በሆቴሉ ለሚያርፉና ለውጭ እንግዶች ይበቃል ወይ? ተብለው የተጠየቁት አቶ ዘናዊ ሲመልሱ፤ ‹‹ሆቴሉ ቢዝነስ ስታይል ነው። በርካታ መኪና ማቆሚያ የሌላቸው የዚህ ዓይነት ሆቴሎች በአሜሪካም ሆነ በሌሎች አገራት በብዛት አሉ›› ብለዋል፡፡
በግንባታ ወቅት ለ700 ሰራተኞች የሥራ ዕድል እንደፈጠረ የጠቀሱት ልዩ አማካሪው፤ ‹‹ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ከ200-230 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ ሳፋሪ አዲስ፤ ለሠራተኞቹ የላቀ ልዩ ትኩረት ይሠጣል›› ብለዋል፡፡
እኛን ልዩ ከሚያደርጉን ነገሮች አንዱ፣ ከእንግዳውም በላይ ለሰራተኞቻችን የምንሰጠው የቅድሚያ ትኩረት ነው፡፡ ምክንያቱም በማኔጅመንቱ አስተዳደር ደስተኛ ያልሆነ ሰራተኛ፤ እንግዶችን በጥሩ ሁኔታ አያስተናግድም፡፡ ስለዚህ ሠራተኞቹ፣ የባለቤትነት ስሜት ተሰምቷቸው፤ ‹‹ሆቴሉ የኛ ነው›› ብለው እንዲቀበሉ፣ ከደሞዝና ከደረጃ ዕድገት በተጨማሪ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን ያገኛሉ፡፡ የስራ ላይና ከውጭ አገር ባለሙያ አስመጥተን ሥልጠና እንሰጣቸዋለን፡፡ በዚህ ዓይነት የሠራተኞችን ፍልሰት እንቀንሳለን ብለን እናምናለን›› ብለዋል- አቶ ዜናዊ፡፡
‹‹ከሠራተኞች 40 በመቶ ያህሉ ከዚህ በፊት ምንም ዓይነት የሆቴል ሥራ ልምድ የሌላቸውና እኛው እዚሁ ያሰለጠንናቸው ናቸው፡፡ የቀጠርናቸው ሰራተኞች ከትምህርና ከሥራ ልምድ ባሻገር ከ7 የሚበልጡ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች አቀላጥፈው የሚናገሩ ናቸው›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ምናልባትም በአዲስ አበባ የመጀመሪያው እንደሆነ የሚነገርለት ግዙፍና እጅግ ዘመናዊ መሳሪያዎች የተገጠሙለት የላውንደሪ ክፍሉ፤ ለሠራተኞች ዩኒፎርም፤ ለእንግዶችና ለውጭ ተጠቃሚዎች አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል፡፡

 በጋዜጠኛ ደራሲና የቋንቋ መምህር ደሳለኝ ማሰሬ የተሰነደው ‹‹የፍቅር ሳቅ›› የግጥም ስብስብ መፅሀፍ ገበያ ላይ ዋለ፡፡ መፅሀፉ ወጣቱን መሰረት ባደረጉ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ከ60 በላይ ግጥሞችን ማካተቱ የመፅሀፉ አዘጋጅ ጋዜጠኛ የቋንቋ መምህርና ደራሲ ደሳለኝ ማስሬ
ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ በ96 ገፅ የተቀነበው መፅኀፉ በ40 ብር ከ50 ሳንቲም እየተሸጠ ሲሆን ደራሲው በቅርቡ ለንባብ የሚያበቃው የቋንቋ መፅሀፍ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑንም ገልጿል፡፡

 70ኛው ግጥምን በጃዝ ረቡዕ ግንቦት 2 ቀን 2009 ዓ.ም ከምሽቱ 12 ሠዓት ጀምሮ በራስ ሆቴል ይካሄዳል፡፡
በዚህ ምሽት ላይ የስነፅሁፍ ምሁሩ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ ገጣሚ ተርጓሚና ጋዜጠኛ ነብይ መኮንን፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብት፣ ፍቃዱ ተ/ ማርያም፣ ይታገሡ ጌትነት እና ኤልያስ ሽታሁን ይሣተፋሉ ተብሏል፡፡ በእለቱ በሽመልስ አበራ እና እታፈራሁ መብራቱ የተዘጋጀ አጭር ተውኔት እንደሚቀርብም ተጠቁሟል፡፡

  አራቱ የ1980ዎቹ ኮከብ ድምፃውያን ከሮሃ ባንድ ጋር ዘፈኖቻቸውን ያቀርባሉ

    ግንቦት 12ቀን 2009 ዓ.ም በግዮን ሆቴል ይካሄዳል በተባለው በዚህ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ በወቅቱ ‹‹ሁሉም ቢተባበር›› በሚለው የጋራ ዜማቸው ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፉትና የ1980ዎቹ አራት ምርጥ ድምፃውያን፡- አረጋኸኝ ወራሽ፣ ፀሐዬ ዩሐንስ፣ ፀጋዬ እሸቱና ንዋይ ደበበ እንደሚሳተፉበት የኮንሰርቱ አዘጋጅ ከትናንት በስቲያ በአዚማን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ገልፀዋል፡፡
የኮንሰርቱ አዘጋጅ ታምር ማስታወቂያ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን መለሰ እንደገለፀው፤ የሙዚቃ ኮንሰርቱ በአገራችን ዘመናዊ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የነበራቸው ድምፃውያን ከሮሃ ባንድ ጋር በመሆን ያን ዘመን የሚያስታውሱ ሥራዎችን በሺዎች ለሚቆጠሩ አድናቂዎቻቸው ያቀርባሉ፡፡
የሙዚቃ ኮንሰርቱ ከተለመደው የሙዚቃ ኮንሰርት የተለየ መሆኑን የገለፀው አቶ ሰለሞን፤ ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ‹‹ወርቃማው ዘመን›› እየተባለ በሚጠራው የ1980ዎቹ ዓመታት ያለፉ በዘመኑ ምርጥ የተባሉ የሙዚቃ ሥራዎችን ሲያጣጥሙ የነበሩ አድናቂዎች ከሚወዷቸው ድምፃውያን ጋር የሚገናኙበትን እድል የሚፈጥር መሆኑ ዋንኛው ነው ብሏል፡፡ ድምፃውያኑ ከሮሃ ባንድ ጋር በጋራ በሚያቀርቡት በዚህ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ ከ10ሺ በላይ ታዳሚዎች ይገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከኮንሰርቱ ገቢ 10 በመቶ አገር በቀል ለሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች ለመስጠት መታሰቡንም አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡
ከኮንሰርቱ መጠናቀቅ በኋላ የኢትዮጵያን ዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክ የሚያስታውስና በተለይም በ1970ዎቹና 80ዎቹ መጨረሻ ድረስ ባለው ጊዜ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚዘጋጅ የአንድ ሰዓት ትኩል ዘጋቢ ፊልም እንደሚዘጋጅና ሲዲውም ከኮንሰርቱ መጠናቀቂያ በኋላ በሚዘጋጅ የምስጋና ፕሮግራም ላይ እንደሚመረቅ የኮንሰርቱ አዘጋጆች በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ የሚዘጋጀው ኮንሰርት ከተጠናቀቅ በኋላ በ3 ዋና ዋና የክልል ከተሞች ተመሳሳይ የሙዚቃ ኮንሰርት ለማዘጋጀት ዕቅድ መያዙንም አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡