Administrator

Administrator

 በዳንኤል ዓለሙ የተዘጋጀው “ይህን ያውቁ ኖሯል?” የተሰኘ የጠቅላላ ዕውቀት መጽሐፍ ሰሞኑን በገበያ ላይ ዋለ፡፡ በአምስት ምዕራፎች የተከፋፈለው መጽሐፉ፤ የዓለም አስደናቂ ሪከርዶች፣ የፖለቲካውና የስፖርቱ ዓለም አስገራሚና አስደናቂ እውነታዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መረጃዎችን ይዟል፡፡ በ224 ገጾች የተሰናዳው መጽሐፉ፤ በ50 ብር ከ70 ሳ. ለገበያ ቀርቧል፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም “ፈተናን የማሸነፍ ጥበብ”፣ “ስኬታማ የፍቅር ህይወት”፣“ገንዘብና ጭንቀት”፣ “ራስን የመለወጥ ምስጢር” እና “ይህን ያውቁ ኖሯል? ቁ.1” የሚሉ መጻህፍትን ማሳተሙን ጠቁሟል፡፡
በደራሲ ድርቡ አደራ የተጻፈው “ሌባ ሻይ” ልብ ወለድ መፅሐፍም ለንባብ የበቃው ባሳለፍነው ሣምንት ነው፡፡ በ400 ገጾች የተቀነበበው መጽሐፉ፤ በ80 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ጸሐፊው ቀደም ሲል “ሐምራዊት”፣ ሽንብሩት” እና “ዲና” የሚሉ መጽሐፍትን ማሳተሙ ይታወሳል፡፡
ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ስለ ህዋ ሳይንስ ግንዛቤ ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀውና “አስትሮኖሚ ለልጆች” የተሰኘው መጽሐፍም ከሳምንቱ የህትመት ትሩፋቶች አንዱ ሆኗል፡፡ በፊዚክስ የማስተርስ ድግሪ እንዳለው በጠቆመው አክመል ተማም የተሰናዳው መጽሐፉ፤ ዩኒቨርስ፣ጋላክሲዎችና ሶላር ሲስተም በሚሉ ሶስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ የቀረበ ሲሆን በ28 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ የትምህርት ባለሙያው አክመል፤ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና ለሌሎች “ዩኒቨርስ” የተሰኘ መጽሐፍ አሳትሞ ማቅረቡም ታውቋል፡፡

የገጣሚ ደምሰው መርሻ በሙዚቃ የተቀናበሩ የግጥም ሥራዎች “ያልታየው ተውኔት” በሚል ርዕስ በሲዲ የተዘጋጀ ሲሆን የፊታችን ረቡዕ ከ11 ሰዓት ጀምሮ በሂልተን ሆቴል ይመረቃል፡፡
17 ግጥሞችን ታዋቂው ሙዚቀኛ ጆርጋ መስፍን ያቀናበረለት ሲሆን 1 ግጥም ደግሞ በጥላሁን ጊዮርጊስ (ፒጁ) መቀናበሩን ገጣሚው ጠቅሶ፣ኤርምያስ ዳኜ የሁሉንም ሚክሲንግ እንደሰራለት ተናግሯል፡፡
የሲዲውን ሽፋን ሰዓሊ ዳንኤል ታዬ ሰርቶልኛል ብሏል- ገጣሚው፡፡   
በሒልተን ሆቴል በሚካሄደው የግጥም ሲዲ የምረቃ ሥነሥርዓት ላይ አንጋፋው ሃያሲ አብደላ እዝራ በግጥሞቹ ላይ ሒሳዊ ዳሰሳ የሚያቀርብ ሲሆን ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም፣ አርቲስት ፈለቀ አበበና ሌሎችም ለታዳሚያን የግጥም ሥራዎችን ያቀርባሉ ተብሏል፡፡ ደምሰው መርሻ በተለያዩ የጥበብ መድረኮች ላይ ግጥሞቹን አዘውትሮ በማቅረብ የሚታወቅ ተወዳጅ ገጣሚ ሲሆን የ“ግጥም በጃዝ” ቡድንም አባል ነው፡፡

Saturday, 13 June 2015 15:31

የፍቅር ጥግ

ልክ ነገ እንደሌሌ ያህል አፍቅር፡፡ ነገ ከመጣ ደግሞ እንደገና አፍቅር፡፡
ማክስ ሉሳዶ
መልካም ትዳር የደግነት ውድድር ነው፡፡
ዲያኔ ሳውዬር
ደስተኛ ትዳር ሁልጊዜ አጭር የሚመስል ረዥም ጭውውት ነው፡፡
አንድሬ ማውሮይስ
በጋብቻ ውስጥ ደስታን ማግኘት ሙሉ በሙሉ የዕድል ጉዳይ ነው፡፡
ጄን ኦዩስተን
(Pride & Prejudice)
“ፍቅር”፤ አንድ ሰው መጥቶ ትርጉም እስኪሰጠው ድረስ ተራ ቃል ነው፡፡
ያልታወቀ ደራሲ
አንዱ ጉንጭ ይሰጣል፤ ሌላው ይስማል፡፡ አንዱ ገንዘብ ይሰጣል፤ ሌላው ያጠፋል፡፡
ጆርጅ በርናርድ ሾው
ጋብቻ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ባለቤታቸውን (ግማሽ ጐናቸውን) እንዲቆጣጠሩ ህጋዊ መብት ለግለሰቦች የሚሰጥ ዓይነት ፈቃድ ነው፡፡
ጄስ ሲ ስኮት
ሁሉም ጋብቻዎች ትዳሮች መንግስተ ሰማያት ነው ይላሉ፡፡ ግን እኮ ነጐድጓድና መብረቅም የሚፈጠሩት እዚያው ነው፡፡
ክሊንት ኢስትውድ
ሰዎች በትዳር የሚዘልቁት ስለፈለጉ እንጂ በሮች ቁልፍ ስለሆኑባቸው አይደለም፡፡
ፖል ኒውማን
ማንም ሴት፤ እናቱን የሚጠላ ወንድ ፈጽሞ ማግባት እንደሌለባት በደንብ አውቃለሁ፡፡
ማርታ ጌልሆርን
ትዳር የተሃድሶ ትምህርት ቤት አይደለም፡፡
ኦን ላንደርስ
ደስተኛ ወንድ የወደዳትን ሴት ያገባል፡፡ የበለጠ  ደስተኛ ወንድ ደግሞ ያገባትን ሴት ይወዳል፡፡
ሱዛን ዳግላስ
የደስታን በሮች የሚከፍተው እናት ቁልፍ ፍቅር ነው፡፡
ኦሊቨር ዌንዴል ሆልሜስ
ትዳር ደስተኛ አያደርግህም፤ አንተ ነህ ትዳርህን ደስተኛ የምታደርገው፡፡
Drs. Les and Leslie Parrott 

  ለደራሲው 10ኛው መጽሐፉ ነው
   “ዴርቶጋዳ” በተሰኘው የመጀመሪያ ልብ ወለድ መፅሃፉ ከፍተኛ ተነባቢነትና ዕውቅናን የተቀዳጀው ወጣቱ ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ፤ “ሜሎስ” የተሰኘ አዲስ ልብ ወለድ መጽሐፍ ሰሞኑን ለንባብ ያበቃ ሲሆን 10ኛ መጽሃፉ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በ280 ገፆች የተቀነበበውን መጽሐፍ፤የዲዛይንና ህትመት ሥራ ያከናወነው ራሱ ደራሲው ያቋቋመው ዴርቶጋዳ ማተሚያ ድርጅት ነው፡፡ “ሜሎስ” በ60 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
ይስማዕከ ከዚህ ቀደም “የወንድ ምጥ”፣ “ዴርቶጋዳ”፣ “የቀንድ አውጣ ኑሮ”፣ “ራማቶሓራ”፣ “ተልሚድ”፣ “ተከርቸም”፣ “ዣንቶዣራ”፣ “ክቡር ድንጋይ” እና “ዮራቶራድ” የተባሉ መጽሐፍትን ያሳተመ ሲሆን  አብዛኞቹም በከፍተኛ ቅጂ በመሸጥ ለአሳታሚውም ሆነ ለጸሃፊው ዳጎስ ያለ ገቢ ማስገኘታቸው ይታወቃል፡፡ በተለይ “ዴርቶጋዳ” በጠቅላላው ወደ 200ሺ የሚጠጉ ቅጂዎች በመታተም በኢትዮጵያ የሥነጽሁፍ ህትመት ታሪክ አዲስ ሪከርድ ማስመዝገቡን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አንዳንድ የሥነጽሁፍ ባለሙያዎችና ሃያሲያን፣ ደራሲው ከመጀመሪያው ሥራው በኋላ ያወጣቸው ተከታታይ  መጻህፍት እያሽቆለቆሉ መምጣታቸውን ቢናገሩም እስካሁን በሥራዎቹ ላይ የሰላ ሂስ የሰነዘረ ወይም ሂሳዊ ጽሁፍ ያቀረበ የለም፡፡

  - አንድ ደብዳቤው ከ3 አመታት በፊት 3ሚ ዶላር ተሽጧል
   ታዋቂው የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አንስታይን በተለያዩ ጊዜያት የጻፋቸው ደብዳቤዎች በቀጣዩ ሳምንት ሎሳንጀለስ ውስጥ ለጨረታ እንደሚቀርቡና ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ ይሸጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘ ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
ለጨረታ የሚቀርቡት ደብዳቤዎች በአንስታይን የእጅ ጽሁፍ የተጻፉና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ እንደሆኑ የጠቆመው ዘገባው፣ ከደብዳቤዎቹ መካከልም አንስታይን ለልጆቹና ሃንስ እና ኤድዋርድ እንዲሁም ለቀድሞ የትዳር አጋሩ ሜሊቫ ማሪክ የጻፋቸው ይገኙበታል ብሏል፡፡
አልበርት አንስታይን በደብዳቤዎቹ ፈጣሪን፣ ፖለቲካን፣ ታሪክን፣ ሳይንስንና ሌሎች ጉዳዮቹን የተመለከቱ ሃሳቦቹን እንዳንጸባረቀና የሳይንቲስቱን የአመለካከት ጥልቀት የሚያሳዩ አስገራሚ ሰነዶች እንደሆኑ፣ ጨረታውን ያዘጋጀው የሎሳንጀለስ አጫራች ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጆሴፍ ማዳሌና ተናግረዋል፡፡
አንስታይን ሃይማኖትን በተመለከተ የጻፈውና ጎድ ሌተር በመባል የሚታወቀው ደብዳቤ እ.ኤ.አ በ2012 ለጨረታ ቀርቦ በ3 ሚሊዮን ዶላር መሸጡንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

 የዚምባቡዌው ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ፤ የእንጀራ ልጅ ረስል ጎሬራዛ ባለፈው የካቲት በመዲናዋ ሃራሬ ማንነቱ ያልተገለጸን ግለሰብ በመኪናው ውስጥ ገድሏል በሚል ተከሶ ፍርድ ቤት መቅረቡንና ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ 800 ዶላር እንዲከፍል እንደተፈረደበት ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ የበኸር ልጅ የሆነው የ31 አመቱ ጎሬራዛ፣ በሃራሬ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ ድርጊቱን መፈጸሙን በማመን እንደተጸጸተ ገልጾ፣ ይቅርታ እንዲደረግለት ጠይቋል። ፍርድ ቤቱም የመንጃ ፈቃዱን ነጥቆ እስር ቤት ሊወረውረው ቢያስብም፣ መጸጸቱን አይቶ በገንዘብ ቅጣት ብቻ እንዳለፈው አስታውቋል፡፡
ግለሰቡ በእስር አለመቀጣቱ በርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎችን እንዳስደነገጠ የገለጸው ዘገባው፣ በተመሳሳይ ወንጀል የተከሰሱ ሌሎች ወንጀለኞች በሁለት አመታት እስር እንደተቀጡ አስታውሷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ማስተላለፉን ተከትሎ የእስር ቤቱ ሃላፊዎች ተከሳሹን በደንቡ መሰረት ከፍርድ ቤቱ ወደ ነበረበት እስር ቤት በመውሰድ የተቀጣውን የገንዘብ ቅጣት ከከፈለ በኋላ እንዲለቀቅ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ፣ የመንግስት የደህንነት አካላት ሊከላከሏቸው እንደሞከሩም ዘገባው አክሎ ገልጧል።

 - በእስር ቤቱ የ150 አመት ታሪክ ሲያመልጡ የመጀመሪያዎቹ ናቸው
  - ድንበር አቋርጠው ወደ ካናዳ ሳይገቡ አልቀሩም ተብሏል
     የኒውዮርክ አገረ ገዢ አንድሪው ኮሞ ባለፈው አርብ ሌሊት ዳኔሞራ በተባለችው ከተማ ከሚገኝ እስር ቤት ያመለጡትን ሁለት ነፍሰ ገዳዮች በተመለከተ መረጃ ለሰጣት ሰው፣ ግዛቲቱ 100 ሺህ ዶላር ወሮታ እንደምትከፍል ማስታወቃቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ሪቻርድ ማት እና ዴቪድ ስዊት የተባሉት እነዚህ አደገኛ ነፍሰ ገዳዮች ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግለት በዚህ እስር ቤት የ150 አመታት ታሪክ አምልጠው መጥፋት የቻሉ የመጀመሪያዎቹ ታራሚዎች ናቸው ያለው ዘገባው፤የታሰሩበትን ክፍል የብረት ግድግዳ በመቁረጥ በፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ውስጥ ለውስጥ ሾልከው እንዳመለጡ ገልጧል፡፡
“እነዚህ ነፍሰ በላዎች አሁንም የከፋ ወንጀል ከመፈጸም ወደኋላ የማይሉ ናቸው” ብለዋል፤አገረ ገዢው አንድሪው ኮሞ፣ ምናልባትም እስረኞቹ ድንበር አቋርጠው ወደ ካናዳ ሳይገቡ እንዳልቀሩ ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሁለቱ እስረኞች ማምለጣቸውን ተከትሎ፣ ፖሊስ በአካባቢው የሚገኙ ጎዳናዎችን ዝግ አድርጎ ጉዳዩን በጥብቅ መመርመሩንና  በግዛቲቱ የሚደረገው የደህንነት ፍተሻና ፍለጋ በከፍተኛ ሁኔታ ተጧጡፎ መቀጠሉን የገለጸው ዘገባው፣ ከ200 በላይ ፖሊሶችም በአነፍናፊ ውሾችና በአየር ላይ አሰሳ በታገዘ እስረኞቹን የማደን ስራ መጠመዳቸውን አስረድቷል፡፡
ሪቻርድ ማት አንድን ግለሰብ በማገትና በመግደል ወንጀል ተከሶ የ25 አመታት የእስር ቅጣት ላይ እንደነበርና፣ ዴቪድ ስዊትም አንድን የፖሊስ ሃላፊ በመግደሉ የእድሜ ልክ እስር ፍርደኛ እንደነበር ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

- በብጥብጡ ከ70 በላይ ሰዎች ሞተዋል
ከሁለት አመታት በፊት አልማስሪ እና አልሃሊ በተባሉት የግብጽ እግር ኳስ ቡድኖች ደጋፊዎች መካከል በፖርት ሲቲ ስቴዲየም የተከሰተውንና ከ70 በላይ ሰዎች የሞቱበትን ብጥብጥ በማነሳሳት የተከሰሱ 11 ግብጻውያን የሞት ቅጣት እንደተጣለባቸው ሲ ኤንኤን ዘገበ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በካይሮ የተሰየመው ችሎት በግብጽ የእግር ኳስ ታሪክ አስከፊው የተባለለትንና ህጻናትን ጨምሮ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉበትን ይህን ብጥብጥ በማነሳሳታቸው የሞት ቅጣት ከጣለባቸው ከእነዚሁ 11 ግለሰቦች በተጨማሪ፣ በብጥብጡ ተሳትፈዋል ባላቸው ሌሎች 40 ሰዎች ላይም የእስር ቅጣት ጥሏል፡፡
ተመልካቾቹ እርስበርስ በድንጋይ፣ በካራና በገጀራ በአስከፊ ሁኔታ የተጨፋጨፉበት ይህ ከፍተኛ ብጥብጥ መከሰቱን ተከትሎ፣ ግብጽ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ስታዲየም እንዳይገቡ እገዳ መጣሏንና ጨዋታዎች በዝግ ስቴዲየም ሲከናወኑ መቆየታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ በሂደትም የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ተመልካቾች ብቻ ወደ ስቴዲየም እንዲገቡ መፈቀዱን ገልጧል፡፡
በግብጽ ከዚያ በኋላም የእግር ኳስ ደጋፊዎች ብጥብጥ መከሰቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው የካቲት ወር ላይም የዛማሌክ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ባስነሱት ብጥብጥ 19 ሰዎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን አክሎ ጠቁሟል፡፡

      ከትናንት በስቲያ በድምቀተ የተከፈተው 3ኛው ሆቴል ሾው ኢትዮጵያ 2007 የሆስፒታሊቲ ቱሪዝም ፎረምና ኤክስፖ ነገ ይዘጋል ሲሉ የኦዚ ቢዝነስና ሆስፒታሊቲ ግሩፕ መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አስታወቁ፡፡
ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ አቶ ቁምነገር ተከተል በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር በሰጡት መግለጫ፤ ነገ ለአካባቢ ጥበቃ የሚቆረቆሩና የሚጨነቁ ሆቴሎች ተወዳድረው አሸናፊውን በመሸለም የንግድ ትርኢትና ኤክስፖው ይዘጋል ብለዋል፡፡
ለሦስተኛ ጊዜ ከሰኔ 4 ጀምሮ በሚሊኒየም አዳራሽ ሲካሄድ የቆየው የንግድ ትርኢትና ኤክስፖ  ዓላማ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው፣ በአፍሪካ ታዋቂ የሆነና በኢትዮጵያዊ ባህላዊ መሠረት ላይ የተገነባ የሆስፒታሊቲና የቱሪዝም መድረክ መፍጠር ነው ያሉት አቶ ቁምነገር፤ ባለድርሻ አካላት መድረክ ፈጥረው በዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት በአገር ውስጥ የሚታዩ ኢንዱስትሪ ነክ ጉዳዮችን ለመዳሰስ፣ አዳዲስ አሰራሮችን ለመጋራትና ለልምድ ልውውጥ አመቺ ሁኔታ መፍጠር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በ3ኛው ሆቴል ሾው ኢትዮጵያ ከኢጣሊያ፣ ፈረንሳይ፣ ዩ.ኤስ.ኤ፣ ታይላንድ፣ ቱርክ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ ዱባይና ቻይና የመጡ 145 አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች፣ የቢዝነስ ሀሳቦች (አይዲያ) የያዙና የገበያ አፈላላጊ ኩባያዎች እየተሳተፉ እንደሆነ ታውቋል፡፡
በንግድ ትርኢትና ኤክስፖው ላይ ሁለት ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚቀርብ የጠቀሱት ማኔጂንግ ማናጀሩ፣ ትናንት ቤልጂየማዊው የ “ሄድ ኳተር ማጋዚን” ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣ የኢትዮጵያን የሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሑፍ ማቅረባቸውን፣ ዛሬ ደግሞ ደቡብ አፍሪካዊው የቢዝነስ ቱሪዝም  ኩባንያ ፕሬዚዳንት፤ የኢትዮጵያ የስብሰባ የኢንሼዬንቲቭ፤ (ኮንፈረንስ፣ ኤግዚቢሽን ወይም ኤቨንት) እምቅ የቱሪዝም ገበያ ዕድሎችና አጠቃቀማቸው በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀርባሉ፡፡ እስካሁን በኢትዮጵያ ስብሰባዎች የሚካሄዱት በመንግስት አዘጋጅነት ብቻ ሳይሆን ቢዝነሱ ራሱ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት እንዳለበት ጠቅሰው፤ ለምሳሌ ቢልጌት 2 ሚሊዮን ዶላር መድቦ በኤድስ ላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤ እንዲያዘጋጅ ዕድሉ ለግል ኮንፈረንስ አዘጋጅ ድርጅቶች ቢሰጥ፣ የአዘጋጅቱን ኃላፊነት የወሰደው ድርጅት በኤድስ በብዛት የተጎዳችው አፍሪካ ስለሆነች ስብሰባውን በአፍሪካ ለማድረግ ወስኖ በየትኛዋ አገር ይካሄድ? ብሎ ሲፈልግ፣ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ማዘጋጀት እንደምትችል ታውቆ ከቢዝነሱ የሚገኘው ገቢ (ማይስ MICE) መጠቀም በምትችልበት አሰራር ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀርባሉ ብለዋል፡፡  የንግድ ትርኢቱና ኤክስፖው በተከፈተበት ሥነ-ሥርዓት በሚቀጥለው ዓመት በመጋቢት ወር ስራ የሚጀምረው የስብሰባ፣ ኢንሴንቲቭ፣ ኮንፈረንስ (ኮንግረስ) ኤግዚቢሽን (ኢቨንት) አዘጋጅ ማይስ MICE ምሥራቅ አፍሪካ 2008 ፎረምና ኤክስፖ መቋቋሙን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ክቡር ሬድዋን ሁሴንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ ተወልደ ወ/ማርያምን በመወከል አቶ ኢሳያስ ወ/ማርያም ይፋ አድርገዋል፡፡
ነገ ቨ3ኛው ሆቴል ሾው ኢትዮጵያ 2007 የንግድ ትርኢትና ኤክስፖ ከመዘጋቱ በፊት በተለያዩ ሆቴሎችና ሪዞርቶች መካከል የሙያ ውድድርና የልምድ ለውውጥ እንደሚካሄድ፣ እንዲሁም በዲዛይንና ግንባታ ወቅት ለአካባቢ ጥበቃ ክብካቤ ከፍተኛ ትኩረት በሰጡ ሆቴሎችና ሪዞርቶች መካከል ውድድር ተካሂዶ አሸናፊዎቹ እንደሚሸለሙ አቶ ቁምነገር ተከተል አስታውቀዋል፡፡  

ኮካኮላ ኢትዮጵያ ከተለያዩ የአዲስ አበባ ት/ቤቶች ከተውጣጡ 50 ታዳጊ ተማሪዎች ጋር “በራስ ለመተማመን ቢሊዮን ምክንያቶች አሉን” በሚል መርህ ባለፈው ረቡዕ በሻላ መናፈሻ ዘመቻ ጀመረ፡፡
“በራስ ለመተማመን ቢሊዮን ምክንያቶች” በሚል መሪ ቃል ኮካኮላ በመላው አፍሪካ የጀመረው ዘመቻ አካል ሲሆን ዓላማውም ወጣት አርቲስቶች የተለያዩ ችግሮችን አልፈው ለስኬት የበቁበትን ተሞክሮ ለታዳጊዎች በማካፈል የአህጉሩን ቀና አስተሳሰብና አስደናቂ ታሪኮች በመሰብሰብ፣ የአፍሪካን ልዩ ታሪኮች ለማክበር መንገድ መክፈት እንደሆነ የኮካኮላ ኢትዮጵያ ማናጀር ሚ/ር ኬንጐሪ ማቻሪያ ገልፀዋል፡፡
ድርጅቱ ከተለያዩ የሕይወት ዘርፎች አራት ተፅዕኖ ፈጣሪ አርቲስቶች ያጋጠሟቸውን ፈታኝ ችግሮች እንዴት አልፈው ለስኬት እንደበቁ ለኢትዮጵያ ታዳጊዎች እንዲያካፍሉ የመረጠ ሲሆን እነሱም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያተረፈችው ዲዛይነር ማኅሌት አፈወርቅ (ማፊ)፣ በኢትዮጵያ የሬጌ አልበም ያወጣው ስኬታማ ሙዚቀኛ ዮሐንስ በቀለ (ጆኒራጋ) ከፍተኛ እውቅና ካላቸው ሴት ዲጄዎች አንዷ የሆነችው የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ማርሼት ፍሰሐ (ዲጄ የሚ) እና አካል የሚያደክም በሽታ ቢኖርበትም በፅናት ተቋቁሞ ለስኬት የበቃውና በአነቃቂ ንግግሮቹ የሚታወቀው ሰዓሊ ብሩክ የሺጥላ ናቸው፡፡
በዝግጅቱ ወቅት ታዳጊዎች በተለያዩ ምድቦች ተከፋፍለው እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ከተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ ዝነኞቹ ጋር ተነጋግረዋል፡፡ ይህም ታዳጊዎች ውጤታማ አርአያ ሞዴሎች ለማግኘት ልዩ ዕድል የፈጠረላቸው ከመሆኑም በላይ የሥራ ፈጠራ፣ ከባድ ሥራ፣ የሕይወት ተድላና ስኬት በቀላሉ እንደማይገኝ የሚያሳይ እውነታ ተምረውበታል ብለዋል የኮካኮላ ኃላፊ፡፡