Administrator

Administrator

በመጀመሪያ ለመላው ኢትዮጵያዊያን በጭንቅም ውስጥ ቢሆን እንኳን አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ። 2014ን እንደ ፖለቲከኛ ከፖለቲካዊ ሁኔታው ነው የምመለከተው። ዓመቱ እንደ ሀገር ከፈረሱ ጋሪውን ለማስቀደም የሞከርንበት ነው። ምን ማለቴ መሰለሽ… ቅድሚያ ለችግሮቹ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሳንሰጥ ሌሎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ችግሮቻችን ከኋላ ወደፊት ለመፍታት የሞከርንበት ነው። 2012ም፣ 2013ም እንደዛው ነበር።
በእኔ እምነት ፖለቲካው ሲቃና ነው ኢኮኖሚው፣ ማህበራዊ ህይወታችንም ሆነ ሃይማኖታዊ ጉዟችን በትክክል የሚሄደው። እኛ ለዘመናት የታገልነውን ዘውግን ወይም ዘርን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ እሳቤን በቆራጥነት ካልገታነው በስተቀር እንደ ሀገር ሁሉ ነገራችንን ነው የሚያቆመው የሚል እምነት ነው ያለን። እናም 2014 ይህንን ዋናውን ችግር አልፈን፣ ሌሎች ተከትለው የሚመጡ በሽታዎችን ለመፍታት የሄድንበት ዓመት ነውና በዚህ መልኩ ነው የምገልጸው።
ስለዚህ በ2015 ዓ.ም ሀገራዊ ምክክሩን የእውነት አድርገን መጀመሪያ መፈታት ያለበትን ማለትም ሁሉ ቦታ ላይ እየገባ ችግር የሚፈጥርብንን ፖለቲካውን ፈትተን ወደ ሌሎች የምንሄድበት   ዓመት እንዲሆን ነው ምኞቴ።  በሌላ በኩል 2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ ብዙ ነገር ቢሞከርባትም እንኳን የማትፈርስ ሀገር መሆኗን ያሳየችበት  ዓመት ነው። አየሽ ኮሮና ቫይረስ ነበረ፣  ወረራ ነበረ፣ የውጪ ጣልቃገብነት ነበረ፣ አንበጣ ነበረ፣ የጎርፍ አደጋና በጣም በርካታ ፈተናዎች  ነበሩ።
ታዲያ ይንን ሁሉ ልንሻገር የቻነው ኢትዮጵያ የተሰራችበትና እንደ ሀገር  የተሸመነችበት ድርና ማግ የዋዛ ባለመሆኑ ነው። በመጨረሻም አዲሱ ዓመት የሰላምና የጤና ይሁንልን ለማለት እወዳለሁ። መልካም አዲስ ዓመት።

 የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል
       - የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በኢትዮጵያ ለ10 ቀናት ይቆያሉ ተብሏ


         በኢትዮጵያ ዳግም ያገረሸው ጦርነት ቀጠናውን እንዳያበጣብጥ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የመከላከል እርምጃ እንዲወስድ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ያቋቋመው አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት መርማሪ ኮሚሽን ጠየቀ።
ኮሚሽኑ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፤ ዳግሞ ያገረሸው ጦርነት ወደ ሌሎች አገራት ተዛምቶ ቀጠናውን እንዳያበጣብጥ የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብሏል።የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥና ጦርነቱ ተስፋፍቶ ቀጠናውን እንዳያናጋ የፀጥታው ምክር ቤት የመከላከል እርምጃ እንዲወስድ የጠየቀው ኮሚሽኑ፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ምክር ቤቱ ጉዳዩን ዋንኛው አጀንዳው እንዲያደርገውም አሳስቧል።
የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመምከር የጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ተገቢነት ያለው መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ጦርነቱን አቁመው ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል።
በተያያዘ ዜና፤ ከቀናት በፊት አዲስ አበባ የነበሩት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር የህውሃት ታጣቂ ሃይሎችን ከመንግስት ጋር ለማደራደር የሚቻልበትን መንገድ መፈለግ ላይ ናቸው ተብሏል። ባለፈው እሁድ ነሐሴ 29 ቀን2014 ዓ.ም አዲስ አበባ የገቡት ልዩ መልዕክተኛው እስከ መስከረም 5 ቀን 2015 ድረስ እንደሚቆዩም ተገልጿል።
ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ጦርነቱን አቁመው የሰላም ንግግርና ድርድር እንዲጀምሩ የሚያሳስብ መልዕክት ይዘው መምጣታቸው የተነገረላቸው ልዩ መልዕክተኛው፤ በቆይታቸው ከመንግስት ባለስልጣናትና ሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር እንደሚወያዩ ተጠቁሟል።
የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የፕሬዚዳንት ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑኩ አምባሳደር ማይክ ሀመር ባለፈው ግንቦት ወር ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ከተሸሙወዲህ ለሁለት ጊዜያት ያህል ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን ከአውሮፓ ህብረት አቻቸው አኔት ዌበር፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ሃናቴት እና ከካናዳና ጣሊያን አምባሳደሮች ጋር በመሆን ወደ መቀሌ አቅንተው ነበር። የማይክ ሐመር የመቀሌ ጉዞ በሁለቱ ወገኖች  መካከል የሰላም ድርድር እንዲጀመር ያደርጋል የሚል ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም፤ ህውሃት ነሐሴ 18 ቀን2014 ዓ.ም የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ ዳግም ጦርነቱን በመቀስቀሱ ሳቢያ የሰላም ተስፋውን አጨልሞታል።የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት  በአሁኑ ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ዳግም ጦርነት ውዱ  የሰው ህይወት በመቀጠፉ የተሰማውን ሀዘን እየገለፀ፣ ሁኔታውን ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመመለስ  ህዝብና መንግስት እንዲሁም ተፋላሚ ሀይሎች ሊጀምሩ ያቀዱት  የድርድር ሂደት ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ እናምናለን ብሏል፡፡
 ‹‹ዳግም ያገረሸው ግጭት ተባብሶና ሰፍቶ የሚቀጥል ከሆነ ከሰው ልጅ ህይወት መጥፋት በተጨማሪ ለከባድ ሰብዓዊ ቀውስና የንብረት ውድመት የሚያጋልጥ መሆኑ ባለፉት ዓመታት የተከሰተው የጦርነት ጠባሳ ህያው ምስክር ነው›› ይላል ምክር ቤቱ ትላንት ያወጣው መግለጫ፡፡
በመሆኑም ከጦርነትና ግጭት ትርፍ ሊያገኝ የሚችል የህብረተሰብ አካል ያለመኖሩን ከግምት በማስገባት ከጥቂት ሳምንታት በፊት ተሰንቆ የነበረው የሰላም  ሂደት በአስቸኳይ እንዲጀመር የመገናኛ ብዙሃን ስለ ሰላምና አብሮነት ትኩረት ሰጥተው እንደሚገባ መክሯል
ሆኖም መገናኛ ብዙሃን  ወቅቱን አስመልክተው የግጭት መረጃዎችን ለህዝብ በሚያደርሱበት ጊዜ በምክር ቤታችን የጸደቀውንና ማንኛውም ጋዜጠኛ ሊከተላቸው የሚገቡ የስነ ምግባር ደንቦችን በማክበር መሆን ይኖርበታል ሲልም አስታውሷል ምክር ቤቱ፡፡  ‹‹የሚዲያ ተቋማት በዚህ ወቅት  በተቀናጀ መልኩ የሀገርና የህዝብ ደህንነት ላይ በማተኮር  እንዲሁም የህዝቦችን ለዘመናት የኖረውን አብሮነት በማስቀደም ተጨማሪ ግጭትና መራራቅ እንዳይፈጠር ተግተው ሊሰሩ የሚገባበት ሰዓት ነው›› ብሏል፡፡
ካገረሸው ጦርነት ጋር ተያይዞ ለህዝብ የሚቀርቡ  ዘገባዎችን ከፍ ባለ የሀላፊነት መንፈስ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ሊዘነጋ አይገባም፤ በተለይም መገናኛ ብዙሃን ጦርነቱን የሚያባብሱ፣ ጥላቻን የሚሰብኩና ሰብአዊ ክብርን የሚያዋርዱ የአደባባይ መግለጫዎችን በተመለከተ በኢፌዲሪ ህገ መንግስት የተደነገጉትን ክልከላዎች ማክበር አለባቸው ያለው መግለጫው በዘገባዎቻቸው ማናቸውንም የህብረተሰብ ክፍል በዘር፣ በብሔር፣ በፆታ፣ በሃይማኖት ወይም በፖለቲካዊ አስተሳሰብን አስመልክቶ ጥላቻን የሚያበረታታ እንዲሁም ንቀትን ወይም መገለልን ሊፈጥር የሚችል ቋንቋን ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚገባ በምክር ቤቱ በፀደቀው የሥነ ምግባር ደንብ ላይ መስፈሩን አስታውሷል፡፡
‹‹የፕሬስ ነፃነት ከሙያ ስነ ምግባር ጋር የተቆራኘ ነው፤ በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን የጋራ ሰላምንና ወዳጅነትን ለማሳደግ እጅግ የተለየ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከሕዝቦች፣ ከብሔረሰቦች ወይም ከሃይማኖቶች ጋር በተያያዘ በሚነሱ አለመግባባቶች ወይም ግጭቶች ላይ የሚሠሩ ዜናዎች፣ አስተያየቶች ወይም የሚሰነዘሩ ሃሳቦች እውነታዎቹ በተገቢው ሁኔታ ከተረጋገጡ በኋላ መቅረብ ያለባቸው ሲሆን ትኩረታቸው በመፍትሄው ላይ ሆኖ የሕዝቦችን ትስስር፣ ወዳጅነትና ሰላምን ለማስፈን በሚያስችል መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይ በህዝቦች መካከል የመነሳሳት ስሜቶችን ሊፈጥሩ የሚችሉ የጦር ሜዳ  ፎቶግራፎችንና አሰቃቂ ምስሎችን ከማሳተም ወይም ከማሰራጨት መታቀብ አለባቸው፡፡››ብሏል ምክር ቤቱ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነፀ በሃላፊነት ስሜት ህዝብን  የሚያገለግል ሚዲያ በሀገራችን  እንዲጎለብት የሚሰራ ሲሆን ከ60 በላይ የመንግስትና  የግል መገናኛ ብዙሃን፤ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙህን እንዲሁም የጋዜጠኞች የሙያ ማህበራትን በአባልነት ያቀፈ ተቋም ነው፡፡


  “አዲስ ዓመት ብሩህ ነው፤ ተስፋ አለ፡፡ ምንም ውጣ ውረድ ቢኖር፣ ይሄን ባዛርና ኤግዚቢሽን ዞር ዞር ብሎ በማየት ስሜትን ማነቃቃት
ያስፈልጋል፡፡ መኪና የት አቆማለሁ ብላችሁ ሳትጨነቁ ኤግዚቢሽን ማዕከልን ጎብኙ፤ ተዝናኑ፤ ቀኑን ሙሉ ዲጄ አለ፡፡ ከ11 ሰዓት በኋላ ደግሞ ባንዶች ሙዚቃ ያቀርባሉ፡፡--”

         የኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅና የማርኬቲንግ መምሪያ ስራ አስኪያጅ አቶ ተክሉ አባተ፣ ዘንድሮ ለአዲስ ዓመት ራሱ ማዕከሉ ባዘጋጀው ኤግዚቢሽንና ባዛር እንዲሁም በአጠቃላይ በመሥሪያ ቤታቸው የሥራ እንቅስቃሴ ዙሪያ ሰሞኑን ከአዲስ አድማስ ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል፡፡ እነሆ፡-


       የዘንድሮ የእንቁጣጣሽ ኤግዚቢሽንና ባዛር ምን ይመስላል?
ድርጅታችን እስካሁን ድረስ ኤግዚቢሽንና ባዛሮችን፣ ኩነቶችን ለሚያዘጋጁ ተቋማት ወይም ሶስተኛ ወገኖች ነበር በጨረታ አወዳድሮ የሚሰጠው፡: ከገና 2014 ጀምሮ ግን የትንሳኤ በዓልንና የአዲስ ዓመትን ባዛር በራሱ አቅም እያዘጋጀ ይገኛል፡፡ ይህም በነጋዴውና በሸማቹ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ ምክንያቱም ድርጅታችን በራሱ ሲያዘጋጅ ትርፍን ከገንዘብ ብቻ ሳይሆን ከነዋሪው እርካታ አንጻርም ነው የሚያየው፡፡ ከዚህ ቀደም በፕሮግራም አዘጋጆች የነበረው ከፍተኛ የዋጋ ጫና፣ ሸማቹም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በመፍጠሩ የዋጋ ማሻሻያ አድርገናል፡፡ ይሄን ተከትሎ ከሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ ነው፣አብዛኛዎቹ ቦታዎች ተይዘው ያለቁት፡፡ በተጨማሪም፤ ዘንድሮ የሚታየውን ከፍተኛ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ለማርገብ በማሰብ፣በተለይ የበዓል ፍጆታዎችን ለማህበረሰቡ  በቅናሽ ለማቅረብ  36 የሚጠጉ ቦታዎችን ለሸማቾችና ለህብረት ስራ ማህበራት፣ እንዲሁም ለጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት በነፃ እንዲጠቀሙበት አመቻችተናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ እስካሁን ሰባት የሚደርሱት ገብተዋል፤ እስከ በዓል መዳረሻ ደግሞ ቀሪዎቹ ይገባሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ቦታ በነፃ የተሰጣቸው ማህበራት ምን ያህል የዋጋ ማሻሻያ አድርገዋል? አንዳንዴ ባዛሮች ላይ የዋጋ ቅናሽ እንደተደረገ ቢነገርም፣ እውነቱ ግን ከወትሮውም የበለጠ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎ ያጋጥማል፡፡ ከዚህ አንጻር  የዋጋ  ቁጥጥር ታደርጋላችሁ?
ከሌላ ቦታዎች አንፃር መጠነኛ የሆኑ የዋጋ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ ዋጋውን መቆጣጠር ባንችልም፣ ቦታውን በነፃ ስለሰጠናቸው፣ ሌላው ነጋዴ ከሚሸጠው ያነሰ እንዲሸጡ  ተነጋግረናል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታም ሸማቹ ከእነዚህ ማህበራት በብዛት ሲገዛ አያስተዋልን ነው፤የዋጋ ቅናሽ በማድረጋቸው፡፡  
ማዕከሉ ለምንድን ነው አሰራሩን ቀይሮ ኤግዚቢሽንና ባዛር ራሱ ማዘጋጀት የጀመረው?
ይሄ ማዕከል  ፕሮግራሞችን እንደሚያዘጋጅ በአዋጅ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩት አመራሮች የሚከተሉት የራሳቸው አሰራር ይኖራል፡፡ እኛ ግን እንደመጣን  የተሳታፊውን ማህበረሰብ ሀሳብ በመውሰድ መረጃ አሰባሰብን፡፡ ባገኘነው መረጃ መሰረትም፤ ተከታታይ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ሲደረግ መቆየቱ ተግዳሮት እንደሆነና ይህም በተዘዋዋሪ በሸማቹ ማህበረሰብ ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን አረጋገጥን፡፡ ይህን እንዴት መፍትሄ እናበጅለት በሚለው ዙሪያ እየመከርንበት ሳለ፣ የገና 2014 ዓ.ም ባዛርን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ዋጋ ያቀረበልን ኤቨንት አዘጋጅ፣ በወቅቱ በነበረው ሀገራዊ ሁኔታ ሳቢያ፣ ፍቃድ ያገኘው በዓሉ አስር ቀናት ብቻ ሲቀረው ስለነበር፣ ፕሮግራሙን ማዘጋጀት አልቻለም ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ተቋማችን ፈጣን ውሳኔ በመስጠት በዘጠኝ ቀናት ውስጥ የመጀመሪያውን ኤግዚቢሽንና ባዛር ራሱ አዘጋጀ፡፡ እናም ኤግዚቢሽኑ ውጤታማ ነበር፡፡ የነጋዴው ማህበረሰብም ከዚህ በኋላ እናንተ እንድታዘጋጁት እንፈልጋለን የሚል ሀሳብ በሰጠን መሰረት፣ አሁንም እየሰራን እንገኛለን፡፡
ባዛሮችና ኤግዚቢሽኖች ከዚህ ቀደም በግል ድርጅቶች ሲዘጋጁ ብዙ ጎብኚዎችን ለመሳብና ትርፋማ ለመሆን ሲሉ ዝግጅቱን ለማድመቅና ማራኪ ለማድረግ ብዙ ይጥራሉ፤የማስተዋወቅ ስራዎችም በስፋት ይሰራሉ፡፡ እናንተስ?
 የአዲስ ዓመት ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ ከሌላው ጊዜ በተለየ በጣም ብዙ ማሻሻያዎችን አድርገናል፡፡ የመጀመሪያው በጣም ባለቀ ሰዓት ላይ  ያዘጋጀነው ስለነበር፣ የማስተዋወቅ ስራ ለመሥራት በቂ ጊዜ አልነበረንም፡፡ አሁን ግን ብዙ ልምድ ወስደን ቀደም ብለን ነው በቴሌቪዥንና በሬዲዮ እንዲሁም በመኪና በመዘዋወር የማስተዋወቅ ስራውን የጀመርነው፡፡ እዚህ ያለው ደግሞ ከዚህ በኋላ ነው ይበልጥ እየደመቀ የሚመጣው፡፡ ይሄ ወቅት ማህበረሰባችን  ለመሸመት ብቻ ሳይሆን ጎብኝቶ፣ ራሱንና  ልጆቹንም አዝናንቶ የሚሄድበት ነው፡፡ ኤግዚቢሽኑ  ትልቁ የበዓል ድምቀት እንደመሆኑ በጉጉት የሚጠበቅም ነው፡፡
አሁን አገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ፤ ጦርነት፣የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት አንጻር፣ ኤግዚቢሽኑ ከወትሮው ሊቀዘቅዝ ይችላል ብላችሁ አልሰጋችሁም?
ኤግዚቢሽን ማዕከል በዓይነቱ ብቸኛው ተቋም ነው፤ ቀደም ብዬ እንዳልኩት የከተማው ነዋሪ  ምርትና አገልግሎት ለመሸመት ብቻ ሳይሆን ለመዝናናትም ጭምር ስለሚመጣ፣ በዓል በዓል የሚለው ድባብና ግርግሩ፣ በተለይ ከአስራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው የሚታየው፡፡  በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን፣ ማህበረሰባችን ለምዶታልና ይመጣል፡፡ ባሉት ቀጣይ ቀናትም የበለጠ እየደመቀ ይመጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዓል ነው..መጪው የትምህርት ጊዜ ነው፤ ወላጆች ለልጆቻቸው የትምህርት መሣሪያዎችን ይገዛሉ፤ ልጆቻቸውን ያዝናናሉ … ቤታቸውን በአዲስ ነገር ያስውባሉ፤ ይሄ በየዓመቱ  ተለምዷል…. ተስፋ ሰንቀን እንደ አዲስ የምነንሳበት አዲስ አመት ስለሆነ፣ ከሌላው ጊዜ በተለየ ይደምቃል፤ማህበረሰቡም ይጠብቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ብቸኛው የባዛርና ኤግዚቢሽን ማዘጋጃ ሥፍራ መሆኑ የራሱን ተወዳዳሪነትና የተጠቃሚውን የማማረጥ ዕድል አይጎዳውም?
ኤግዚቢሽን ማዕከል ብቸኛው ላይሆን ይችላል፡፡ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አቅጣጫ የተሰጠበትና በሲኤምሲ አካባቢ እየተገነባ የሚገኝ አዲስ “አፍሪካን ኮንቬንሽን ሴንተር” የተሰኘ ማዕከል ሲጠናቀቅ ይከፈታል፡፡ እዛም ላይ እኛ ትልቅ ባለድርሻ ነን፡፡ የዚህ ተቋም መኖር አማራጮችን ለተጠቃሚ ያመቻቻል፤ ጤናማ የሆነ ፉክክርም ይፈጥራል፡፡  
ወደፊትም ኤግዚቢሽን በማዘጋጀት ትቀጥላላችሁ ማለት ነው ---?
አዎ በማዘጋጀቱ እንቀጥላለን፤ምክንያቱም ከመግቢያ ትኬት ጀምሮ ከፍተኛ የዋጋ ማሻሻያዎችን አድርገናል፡፡ የማህበረሰቡን እርካታ አስጠብቀን መሄድ እንፈልጋለን፡፡ ስለዚህ ማዘጋጀቱን እንቀጥልበታለን፡፡ በዓመት ውስጥ በርካታ ኹነቶች አሉን፡፡ ያንን የሚያዘጋጁ ተባባሪ አዘጋጆችም አሉ፤እነሱም ይቀጥላሉ፡፡ ሆኖም የአዲስ ዓመትን፣ የገናንና የፋሲካን ባዛር ማዕከሉ ማዘጋጀቱን ይቀጥልበታል፡፡ ነገር ግን በማኔጅመንት በኩል የመንግስትና የባለድርሻ አካላት ጥቅም ተነክቷል ይሻሻል ከተባለና ከተገመገመ ደግሞ ለሦስተኛ ወገን እንሰጣለን፡፡
በመጨረሻ የአዲስ ዓመት ምኞትዎን መግለጽ ይችላሉ---
አዲስ ዓመት ብሩህ ነው፤ ተስፋ አለ፡፡ ምንም ውጣውረድ ቢኖር፣ ይሄን  ባዛርና ኤግዚቢሽን ዞር ዞር ብሎ በማየት ስሜትን ማነቃቃት ያስፈልጋል፡፡ መኪና የት አቆማለሁ ብላችሁ ሳትጨነቁ ኤግዚቢሽን ማዕከልን ጎብኙ፤ ተዝናኑ፤ ቀኑን ሙሉ ዲጄ አለ፡፡
ከ11 ሰዓት በኋላ ደግሞ ባንዶች ሙዚቃ ያቀርባሉ፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡ ወደ ማዕከሉ እንዲመጣ እጋብዛለሁ፡፡ አዲሱ ዓመት የሰላምና የብሩህ ተስፋ ይሆንልን ዘንድ እመኛለሁ፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን  የቅዳሜ ሹር ለት  ቤተሰብ ተሰብስቦ፣ የፆመ የሚገድፍበት፣ ያልፆመም በግድ ተቀስቅሶ ገበታ የሚቀርብበት ሌሊት፣ አንድ አመለኛና አስቸጋሪ ልጅ፣ እንደ ሁልጊዜው ከሰው ፊት ምንትፍ ያደርጋል፡፡
የዚያን ዕለት ሌሊት በእንግድነት የተገኘ ጥቁር እንግዳ አለ፡፡
አባትና እናት፣ ያ አመለኛ ልጅ ያስቸግራል ብለው በየደቂቃው ስቅቅ ይላሉ፡፡ ዶሮው መጣ፡፡ ለየሰው በቁጥር እየለዩ እናት አወጡ፡፡ አመለኛው ልጅም ደርሶታል፡፡ ግን አመል ነውና ፋንታውን ዋጥ ስልቅጥ አድርጎ በእጁ እመር እያለ፣ የእንግዳውን ዕንቁላል ላፍ አደረገ፡፡
አባት፡-
“ኧረ ይሄ ባለጌ፣ የእንግዳውን ድርሻ ትወስዳለህ?”
እናት
(በምንተፍረት)
“ግዴለም ይብላ ተውት፣ ልጅ አደል? አለኮ፣ለእንግዳው አወጡለት፡፡”
እንግዳውም በሀፍረት ልሳን፡-
“ኧረ ግዴለም አትቆጡት! የእኛ ቤት ልጅ´ኮ ሙሉ ድስቱን ነው አንስቶ ይዞ የሚሮጠው!” አለ
ይሄኔ አባት፤
“አይ ለሱስ ደህና አድርገን ቀጥተነዋል፡፡”
***
በዓላት እንደ ድምቀታቸው ቀላል የኢኮኖሚ ጠባሳ  ሳይተው አያልፉም፡፡ በተለይ ከነሐሴ 12-13ቱ ቡሄ እስከ እንቁጣጣሽ፣ አልፎም እስከ መስቀል፣ እንደየ ብሔረሰቡ የፌሽታ አከባበር ስርዓት የዋዛ ጉዳት አይደለም የሚያደርሱት።
ከበዓላቱ በተጨማሪ ደግሞ መስከረም የትምህርት ቤት መከፈቻ ወቅት መሆኑ፣ የየቤተሰቡን ኢኮኖሚ መጫኑና ኪስን ማጎድጎዱ፣ የየዓመቱ የሂሳብ ስሌት የሚያስታውሰው ነው፡፡
ሌላው ቀርቶ ለክረምት እረፍት ቤተሰቡን ለማየት ከውጪ የሚመጣው ሰው ብዛት እንኳ የዋዛ አይደለም፡፡ ሁሉም የየትውልድ ቀዬውን ባሕላዊ እሴትና ማዕድ ተቋድሶ ወደመጣበት ይመለሳል፡፡
ከበዓላቱ ሁሉ ግን እንደ መስከረም ደማቅና በፀደይ የተከበበ፤ ጨፍጋጋውን ክረምት ለማሰናበት ፀሐይ ፏ ብላ የምትበራበት፣ የአዲስ ዘመን ብስራት፣ በአየር  ጠባዩ ለውጥ የሚነገርበት፣ ልጆች አበባ ስለው ከቤት ቤት እየዞሩ፣ ለየዘመድ አዝማዱ የሚሰጡበት ወዘተ የለም፡፡
ገጣሚና ፀሐፌ ተውኔት መንግሥቱ ለማ፤
“…ማን ያውቃል እንዳለው፣ ለድንጋይስ ቋንቋ፣
ለሚቆረጥ ዛፍ፣ እንዳለው ጠበቃ ?
ማን ያውቃል?
የመስቀል ወፍና፣ የዐደይ አበባ
 ቀጠሮ እንዳላቸው፣ መስከረም ሲጠባ?!...”
ማለታቸውን ይኸው ለዘመናት እየደጋገምን እንለዋለን፡፡
በአዲስ ዘመንና ወቅት አዳዲስ አበቦች ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ልቦች፣ አዳዲስ ሃሳቦች፣ አዳዲስ ራዕዮች፣ አዳዲስ የህይወት ቅኝቶች፣ እንዲያብቡ ተስፋችን ህልቆ-መሳፍርት የለውም፡፡ አዲስ ዓመት የአዲስ ህልውና መፀነሻና ማደጊያው ነው የምንለውም ለዚህ ነው፡፡
አንድ የአገራችን ገጣሚ ለእንቁጣጣሽ ለገናና ለጥምቀት በዓል የገጠመው የሚከተለው ግጥም፣ ለየዘመኑ ያገለግላል፡፡ እነሆ፡-
ያበባነቴ አበባ
በአበባነቴ አበባ፣ ማዞሬን ዛሬ ሳስበው፣
እንደቀን-ጥንጥን ተዳውሮ፣ ዛሬ ለሆንኩት ሁሉ
ንጥረ-ነገሩ እሱው ነው!
ትላንትና አላለቀም
የአበባ ጅምር ነው እንጂ፣ ረግፎ መሬት አልወደቀም፡፡
ዘመን ማለት የዕድሜ ቁጥር
የእንቁጣጣሾች ጀማ ነው፣ ያልባለቁ አበቦች ድምር፡፡
ያላለቁ እምቡጦች ቀመር!
የአበባነቴ አበባ ነው፣ የየዕለቱ ዕድሜ ስፍር፡፡
የአምና ጀምበር ጠልቃ አትቀር
በዘንድሮ በኩል ልትሰርቅ፣ ተሻግራም ነገ ልትጨርር
 የአበቅቴን ውል ልታሻግር
ያው ትኖራለች ከኛው ጋር፡፡
ያም ሆኖ፣ የጥንቱ አበባ፣ አሁን/ጠውልጎ እንዳላየው
የየዓመታቱን ጉንጉን ሐር፣ በንቡጥ ቀለም ነው  ምፈትለው!
የትላንት እኔን ሰርቄ
ለዛሬው እኔ አበድሬ
ለነገም ወለድ ቋጥሬ
ከዓመት ወደ ዓመት በቅዬ፣
አድራለሁ አበባ አዙሬ
ሌላው ቢቀር  የቅን-ልቤን፣ ለቅሜ የራሴን ፍሬ!
(ለእንቁጣጣሽ ለገናና ለጥምቀት በዓል) 2014 ወዘተ--
ለማንኛውም የዘንድሮን የመስከረም እንቁጣጣሽና የብርሃነ-መስቀል በዓል በሰላም በፍቅር ያድርሰን!
መልካም አዲስ ዓመት!
መልካም የመስቀል በዓል!
አዲስ አድማስ ጋዜጣ የትፍሥሕት እና የፌሽታ ጊዜ ይመኝላችኋል!!

     “በኤጀንሲያችን ኔትዎርክ የለም የሚባል ነገር ታሪክ እየሆነ ነው”


      ኢትዮ ቴሌኮምና የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ፤ የአገልግሎት ክፍያን በቴሌብር እንዲፈጸም የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከትላንት በስቲያ የፈጸሙ ሲሆን አገልግሎቱም ተግባራዊ መደረጉ ታውቋል፡፡
አገልግሎቱ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲን የአሰራር ስርዓት በማዘመን ባለጉዳዮች ያለምንም ውጣ ውረድና እንግልት፣በኦንላይን አገልግሎት እንዲስተናገዱ በማድረግ፣ቀላል ፈጣን፣ ምቹና አስተማማኝ የሆነውን ቴሌብር ተጠቅመው፣የአገልግሎት ክፍያቸውን በቀላሉ እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል ተብሏል። ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በሸራተን አዲስ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩና የሰነዶች ማረጋገጫ ምዝገባ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሙሉቀን አማረ የስምምነት ውሉን ተፈራርመዋል።
የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጄንሲ በአሁኑ ወቅት 15 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች፣ 27 ልዩ ልዩ አገልግሎቶች እንዲሁም ከ7 ሺ በላይ ደንበኞች ያሉት ሲሆን፣ በቀን በአማካይ ከ6.5 ሚሊዮን ብር በላይ የአገልግሎት ክፍያ እያስተናገደ እንደሚገኝ ታውቋል። አዲስ በተተገበረው አሰራር መሰረት፤ባለጉዳዮች በኤጀንሲው አገልግሎት ካገኙ በኋላ በሚላክላቸው ወይም በሚሰጣቸው የክፍያ ማዘዣ ቁጥር በመጠቀም የመኪና ሽያጭ ውል፣ የስጦታ፣ የውክልና፣ የብድር፣ የማህበር ምስረታና ቃለ ጉባኤ የመሳሰሉ የአገልግሎት ክፍያዎችን በቀላሉ በቴሌብር መተግበሪያ ወይም በአጭር ቁጥር (*127#) በመፈጸም አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ኢትዮ ቴሌኮም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ኩባንያው በቅርቡ ሁሉን አካታች የፋይናንስ አገልግሎት የጀመረ ሲሆን እነሱም፡- #ቴሌብር መላ (የግለሰብ ደንበኞች፣ ነጋዴዎች እንዲሁም ወኪሎች የአነስተኛ ብድር አገልግሎት በቴሌብር አካውንታቸው አማካኝነት የሚያገኙበት)፣ #ቴሌብር እንደኪሴ (የቴሌብር ደንበኞች በአካውንታቸው ላይ ያላቸው ቀሪ የሂሳብ መጠን በቂ ባልሆነበት ጊዜ የሚጠቀሙበት) እንዲሁም #ቴሌብር ሳንዱቅ (ደንበኞች ከወለድ ነጻ ወይም የተለያየ የወለድ መጠን የሚታሰብባቸው የቁጠባ አይነቶችን የሚጠቀሙበት) ሲሆኑ፤ ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቶቹን ከዳሸን ባንክ ጋር በአጋርነት በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል።
ከመንግስት መ/ቤቶች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የቀድሞው ውልና ማስረጃ፣ የአሁኑ ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ባደረጉት ንግግር፤ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የጀመሩት አዲስ አሰራር በየቀኑ አገልግሎት የሚሰጧቸውን ከ7 ሺህ በላይ ደንበኞች የሚያስደስት እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ “ዕድሜ ለቴሌኮም፣ በአሁኑ ወቅት በተቋማችን ኔትዎርክ የለም የሚባል ነገር ታሪክ እየሆነ ነው” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮቴሌኮም የኤጀንሲውን አገልግሎት በማዘመንና በማቀላጠፍ ረገድ ለተጫወተው ጉልህ ሚና፣ በተቋሙና በደንበኞች ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው፤ “ደንበኛ እንዲህ ስለ አገልግሎታችን ብቃት ሲናገር እንዴት ልብ ያሞቃል መሰላችሁ!” በማለት፤ የኢትዮ ቴሌኮም ባለድርሻ አካላትን “እንኳን ደስ ያላችሁ” ብለዋል።
በአገሪቱ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ የሆነው 40 በመቶ ብቻ መሆኑን ያነሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤”የፋናንስ አገልግሎት ለሁሉም” በሚል መሪ ቃል ኩባንያቸው በጀመረው እንቅስቃሴ ይሄን ክፍተት ለመሙላት እየጣረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
“አንድ ባንክ ዓመቱን ሙሉ ከሰጠው የብድር አገልግሎት ይልቅ እኛ በጥቂት ቀናት በቴሌብር የሰጠነው የብድር አገልግሎት ይበልጣል፤” ያሉት ወ/ት ፍሬህይወት፤”ይሄ ልቤን ያላሞቀው ምን ሊያሞቀው ይችላል?” ብለዋል፤በደስታ ተሞልተው፡፡

  አድማስ ዩኒቨርስቲ 14ኛውን ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባኤውን ዛሬ ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በማግኖሊያ ሆቴል ያካሂዳል። ዩኒቨርስቲው ለዘንድሮው ጉባኤ የመረጠው የጥናትና ምርምር ርዕስ “የከፍተኛ ትምህርት ጥራት፣ ጥናትና ምርምር እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ” የተሰኘ ሲሆን ለአንድ ሀገር ወሳኝ የሆነውን የትምህርት ጥራትና ከዩኒቨርስቲዎች ተልዕኮ አንዱና ዋነኛው የሆነውን የማህበረሰብ አገልግሎት ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካ ቀንድን የሚዳስስ የጥናትና ምርምር ወረቀት በጉባኤው እንደሚቀርብ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ሞላ ጸጋ (ዶ/ር) ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል።ፕሬዚዳንቱ አክለውም ባለፉት 13 ዓመታት ዩኒቨርስቲያቸው የትምህርት ጥራቱን ማዕከል ያደረገና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ጉባኤ ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውሰው በዚህ ረገድ ሃላፊነታቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል። በዘንድሮውም የጥናትና ምርምር ጉባኤ ከላይ በተመረጠው ርዕስ ዙሪያ ምሁራን ጥናትና ምርምር ስራቸውን እንዲያቀርቡ በመጋበዝና ከቀረቡት ውስጥ የተሻለ ይዘት ያላቸውን በማወዳደር ለጉባኤው ማቅረባቸውን የገለጹት ሞላ ፀጋ (ዶ/ር) በዚህም ዘርፍ እየታየ ያለውን ክፍተት ለመሙላት መፍትሄ ጠቋሚ የሆኑ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። በዚህ ጉባኤ ላይ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎችና  ከባለ ድርሻ አካላት ተወከሉ ሃላፊዎች እንደሚታደሙ ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል።አድማስ ዩኒቨርስቲ በአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ካምፓሶቹ ከ20 ዓመታት በላይ በርካታ ዜጎችን በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በማስተማር በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ባለሙያ ከማድረጉም በላይ በሀገሪቱ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት በመሙላት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ያለ ተቋም ነው ተብሏል።

 ጆርካ ኢቨንት ኦርጋናይዘር ከATX ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ (አፍሪካ ቴክ ኤክስፖ) የፊታችን ረቡዕ ጳጉሜ 2 ከረፋዱ 4፡00 ጀምሮ በስካይላይት ሆቴል ይከፈታል።
በተከታታይ ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ኤክስፖ በቴሌኮም፣ በፋይናንሻል ክፍያ፣ በማህበራዊ ሚዲያ፣ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ፣ በሶፍትዌር ግንባታ፣ በኤሌክትሮኒክስ፣ በሶላር ቴክኖሎጂ፣ በሳይበር ደህንነት፣ በባንክና ኢንሹራንስ፣ በሜትር ታክሲ፣ በኮንሲዩመር ቴክኖሎጂና በግብርና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ዘርፎች የተሰማሩ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉበት ታውቋል፡፡
 መንግስት ለቴክኖሎጂው ዘርፍ የሰጠውን ልዩ ትኩረት ታሳቢ በማድረግና ይህንንም  ፖሊሲ ውጤታማ ለማድረግ እንደተዘጋጀ በተነገረለት በዚህ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ፤ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጪ ኩባንያዎች እንደተሳተፉበትና በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አዘጋጁ ጆርካ ኢቨንት ኦርጋናይዘር አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርና በኢንቨስትመንት ኮሚሽን እውቅናና አድናቆት የተቸረው  የቴክኖሎጂ ኤክስፖ፤ በእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሀገር ገፅታ ግንባታ፣ በኢኮኖሚ ግንባታ እንዲሁም ለዜጎች የስራ ዕድል ፈጠራ አዎንታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥር ነው ተብሏል፡፡
በመክፈቻው ዕለትም ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢኖቬሽንና ቴክሎጂ ሚኒስቴር፣ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ከኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ከሌሎችም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተጋበዙ ሚኒስትሮችና ተወካዮች እንዲሁም የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች እንደሚገኙም ታውቋል።

አሌክስ ዴ ዎል የተባለ ፀሐፊ “አዲስ ተግዳሮት በአፍሪካ ቀንድ” በሚል ዐቢይ ርዕስ ሥር- “አፍሪካ ቀንድ እና ቀይ ባሕር”- በሚል ንዑስ ርዕስ የሚከተለውን አስፍሯል። ምንጊዜም የማይበርደው የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ዛሬም ለያዥ ለገራዥ እንዳስቸገረ አለ።
የአፍሪካ ቀንድ በታሪክ ራሱን እንደ አንድ ክልል አረጋግጦ ተቀምጦ አያውቅም። በአካላዊና በሰብዓዊ መልክዐ-ምድር ረገድ እጅግ መጠነ- ሰፊ ሲሆን፣ የክርስቲያኑንም የሙስሊሙንም ህብረተሰብ በማይተናነስ ቁጥር የሚነካ ነው። ህዝቦቹ´ኮ አፍሪካ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከሕንድ ውቂያኖስ፣ በቅርቡ ደግሞ ከአውሮፓና ከአሜሪካ የተሳሰረ ነው። ያም ሆኖ እንደ አፍሪካ  ቀንድ ህዝብ ራሱን አያይም። ይልቁንም የአፍሪካ ቀንድ ከግዛቱ ውጪ ባሉ ሰዎች ነው በቅጡ የሚገለጠው። በተለይም በዓለም ታላላቅ ኃይሎች እንደ ችግር ፈጣሪ እየተቆጠረች ነው። የዛሬዋ አፍሪካ ቀንድ አሳሳቢ አባዜ፣ በዓለም አቀፉ የሥልጣን ትግል የደምበኛና የአቅራቢ ዓይነት እንዳይሆን ነው። ያ ደግሞ የገዛ ራስዋ ያልሆነ ጣጣ ነው።
የአፍሪካ ቀንድ ዋንኛ ዕዳ መልክዐ ምድራዊ አቀማመጡ ነው። የስዊስ ካናል በ1869 እ.ኤ.አ ሲከፈት ቀይ ባሕር ከዋና ዋናዎቹ የንግድ ደም ስሮች አንዱ ሆነ። የዓለም ኃያላን መንግስታትም የባሕር መርከብ እንቅስቃሴ ደህንነት ጉዳይ ዋና ጉዳያቸው ሆነ እንጂ ውስጡን የማስተዳደሩ ነገር አላሳሰባቸውም ነበር። በግዛቱ አዲስ የጂኦ - ስትራቴጂ ፍላጎት ባደረ ቁጥር እንደ ሁልጊዜው ያንኑ ዓይነት ውጥረት ይከሰታል። ይሄ በ1950ዎቹ በስዊስ ካናል ላይ በቀዝቃዛው ጦርነት ጅማሮ ላይ ታየ። እንደገና ደግሞ በ1970ዎቹ የዐረብና እስራኤል ጦርነት ሊፋፋም አናቱ ላይ ሲደርስና በኃያላን ፍጭት፣ በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድና በየመን ሲያጥጥ ፈጥጦ ወጥቷል።
ከዚያ የተከተለው እንግዳ የሆነ ታሪካዊ ሲላሲሎ ነው። አሊያም አፆለሌ ልንለው የምንችለው አዙሪት ነው! ለሩብ ምዕተ ዓመት ያህል የግዛቱ አገሮች የራሳቸውን አጀንዳ ሲያቀነቅኑ ነበር። ዓለም አቀፍ ፍላጎቱ ባይቆምም የስትራቴጂው ፋይዳ እየቀነሰ መጥቶ የሰብዓዊ ደህንነት -ማለትም እንደረሃብን ማቆምና ጅምላ ጭፍጨፋን መግታት አጀንዳ ሆኑ። ያም አሁን እያተለወጠ ነው። የኤደን ባሕረ-ሰላጤ ከአስርት ዓመታት በፊት፣ ለአጭር ጊዜ በሶማሊያ ድንበር በባህር ዘራፊዎች ስጋት ላይ ወድቆ ነበር።
አሁን ደግሞ የባሰ ቁም ስቅል የሚታይበት ጊዜ መጥቷል። የዐረባዊ ፔኒንዙላው አልቃይዳ የየመንን የተወሰነ የባሕር ዳርቻ ተቆጣጠረ። የመርከብ ኢንሹራንስ አሳሳቢ ነው። በሳውዲ የሚመራው የአገሮች ኅብረት፣ በየመኑ እርስ በርስ ጦርነት ጣልቃ መግባቱ አልቀረም። ሊፈረካከስ የደረሰውን ሁኔታ ይብስ ለማናጋት ለሱማሌ ተስፈንጣሪ ቡድኖች ገንዘብ ይረጫሉ። የኤርትራንም መነጠል ለማፍረስ የወታደራዊ ሰፈር ይመሰርታሉ።
የአዳዲስ ጦርነት መቀፍቀፍ ስጋት እያኮበኮበ ነው። የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ውጥረትና ወታደራዊ አየር እየነፈሰበት ነው። በወታደራዊ ንቅናቄ በተነሳሳች በአዲስ መልክ ልብ በገዛች ኤርትራና በተቆጣች ኢትዮጵያ መካከል የሚኖረው ጠብ መጫር ሊናቅ አይገባውም። ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ዓለማቀፋዊ ትኩረት እየሳቡ ነው፡-
አንደኛው- የባህር ደህንነት ጉዳይ ነው። ከሞላ ጎደል የአውሮፓና ኢስያ የንግድ እንቅስቃሴ በቀይ ባሕር ላይ የሚያልፍ ነው። በዓመት 700 ሚሊዮን ዶላር ያህል ነው። ቀላል አይደለም!
ሁለተኛው- በኃይል የተደገፈ ከባድ ጽንፈኝነት መኖሩ ነው- የአልሻባብ አደጋ የዋዛ አይደለም። የአፍሪካ ሕብረት ለዚህ የሰጠው ምላሽ የጸረ-ሽብርተኞች መቋቋሚያ ኃይል ነው። ያም በሰላም ጠባቂዎች ኃይል መልክ ነው።
እነዚህ አሸባሪዎችን ሲዋጉ በአንጻሩ ሳውዲና ኳታር ዋሐቢዝምን ለማስፋፋት የሙስሊም ጽንፈኝነትን ማጠናከሪያ ብር ያፈስሳሉ።
የመጨረሻና ሦስተኛው ጉዳይ ስደት ነው። ከሶርያውያንና ከአፍጋኖች ቀጥሎ ግፈኛ መንግስታቸውን በመሸሽ ከአገር የሚሰደዱና አውሮፓ የሚገቡ ህዝቦች ኤርትራውያን ናቸው። በተስፋ መቁረጥ የአውሮፓ ህብረት ለኤርትራ ዕርዳታ ይሰጣል። ቀቢፀ ተስፋ ነው ግን! ምንም ካለማድረግ ይሻላል ነው ነገሩ።
የአፍሪካ ኅብረት ይሄንን ስትራቴጂያዊ ገዋ መድፈን አለበት። የባህረ-ሰላጤውን ኅብረት ምክር ቤት ጋር አጋርነት  ፈጥሮ መንቀሳቀስ አለበት!

Saturday, 27 August 2022 11:47

የግንቦት 7 ልዩ ኮማንዶ

ወያኔዎችን ምን እንዳስጨነቃቸው አላውቅም። ያደረጉትን ለምን እንደሚያደርጉትም አልገባኝም። ከቤተሰቦቼ መሃል ከአባቴ በስተቀር ሌላ ማንም እስር ቤት እንዳይጎበኘኝ አድርገዋል። ጉብኝቱንም በሳምንት አንድ ቀን ቅዳሜ ብቻ እንዲሆን ወስነዋል። የተሰጠን ጊዜም ግማሽ ሰዓት ብቻ ነው።
ማንም ሌላ እስረኛ እንዲህ አይነት ገደብ የለበትም። አባቴ ሊጎበኘኝ ሲመጣ እንደሌላው ጎብኚ ከሌሎች ጠያቂዎች ጋር አልቀላቀልም። እኔም ከሌሎች እስረኞች ጋር ተቀላቅዬ አልጎበኝም። አባቴና እኔ የማንገናኘው የቃሊቲው አስተዳዳሪ ቢሮ ውስጥ መሆኑን ቀደም ብዬ ተናግሬለሁ። በየሳምንቱ አባቴን ለማግኘት ስንቀሳቀስ ሃምሳ ሜትር እርዝማኔ የሌለው መንገድ፣ መኪና ቀርቦልኝ እንደምወሰድም ጠቅሻለሁ።
ከሁሉ ያልገባኝ ነገር በመኪና መወሰዱ ሳይሆን የሚደረገው ጥንቃቄ ነው። መሳሪያ የያዘ ወታደር መኪናው ውስጥ አብሮኝ መግባቱ የተለመደ አሰራር ሊሆን ይችላል። እስረኛ ያለአጃቢ ስለማይንቀሳቀስ። ከዚህ አልፎ ግን እኔ በምንቀሳቀስበት ቀንና ሰዓት መንገዱን በሙሉ ከእስረኛ ብቻ ሳይሆን ከራሱ ከቃሊቲ ፖሊሶች ማጽዳት ለምን እንደፈለጉ ወይም እንደተገደዱ ነው አልገባ አለኝ።
ቅዳሜ ቀን ቃሊቲ በጣም ብዙ እንቅስቃሴዎች የሚታይበት ቀን ነው። ብዙ እስረኛ በቤተሰብ የሚጠየቀው ቅዳሜ ቀን ነው። እስረኛውም ገንዘብ የሚያገኘውም የሚያጠፋውም ቅዳሜ ነው። አሳሪዎቼ ብቻ ከነገሩኝ ተነስቼ ሳይሆን አንድ ቅዳሜ እኔም በመኪና ስወሰድ ያየሁት ነው። ትርምስ ነው። ወደ ላይ ወደ ታች የሚሉ ሸቀጥ የያዙ በወታደሮች የታጀቡ ሴትና ወንድ እስረኞች አይቻለሁ። ፖሊሶች ምግብ የሚበሉባቸውና ቡና የሚጠጡባቸው ዳስ ነገሮች በፖሊሶች ተሞልቶ አይቻለሁ። ይህን ያየሁት አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
ከዛ ቀን ውጭ በምንቀሳቀስበት ወቅት በምሄድበት መንገድ ወፍ ዝር እንዳይል ይደረጋል። መኪናው ወደ አስተዳደሩ ቢሮ እስከሚዞር በርቀት ዋናውን የግቢውን በር ማየት እችላለሁ። በዛ መንገድ ላይ እንኳን እስረኛ ፖሊስም እንዳይታይ ተደርጎ ነው የሚያንቀሳቅሱኝ። አንዳንድ ጊዜ ከታሰርኩበት ግቢ በራፍ ላይ እንድቆም ተደርጎ መንገዱ በሙሉ መጽዳቱን ብርሃኔ ጠይቆ ነው መኪና ላይ የምጫነው።
በዚህ ጉዞ አልፎ አልፎ ብርሃነና ሌሎች ፖሊሶች የሚጨቃጨቁበት ሁኔታ ይፈጠራል። መንገዱ ጸድቷል ተብሎ ስንወጣ ከሆነ አሳቻ ስፍራ ብቅ ብቅ የሚሉ ፖሊሶች ነበሩ። እኔን ለማየት እንደሚፈልጉ ግልጽ ነው። ወደ መኪናው እያዩ የሚጠቋቆሙበትን ሁኔታ አይቻለሁ። ብርሃነ እነዚህን ፖሊሶች ወደ ወጡበት እንዲመልሱ ትእዛዝ ይሰጣል። እነሱም በፈቃደኝነት እሺ ብለው አይመለሱም። ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸውም በዝግታ እያጉረመረሙ ይመለሳሉ።
ሴት ፖሊሶች ተሰብስበው ቡና የሚጠጡበትን በቆርቆሮ የተሰራ ዳስ አልፈን ነው ወደ አስተዳደሩ ቢሮ የምንሄደው። አንድ እለት ብርሃነ እዛ ክፍት ዳስ ውስጥ ቡና ይዘው የሚያያቸውን ፖሊሶች በተመለከተ፣
“እኛ ወደዚህ ስንመጣ ነው እንዴ የእነዚህ ሴቶች የቡና ሱስ የሚቀሰቀሰው፤አሁን ስንወርድ እኮ  ቦታው ባዶ ነበር።” አለ። መኪና የሚነዳው የብርሃነ አገር ሰው ሴቶቹን በተመለከተ የሰጠው ኋላ ቀር አስተያየት አስደነገጠኝ። ከእነዚህ ቡና ከሚጠጡ ሴት ፖሊሶች መሃል በድፍረት ወታደራዊ ሰላምታ የምትሰጠኝ አንዲት ፖሊስ ነበረች። ማንም ቢያያት አትፈራም። እንዴት ዝም ይሏታል እያልኩ፣ በፈገግታ ሰላምታዋን ተቀብዬ አልፍ ነበር።
እኔንም ለማንቀሳቀስ ወያኔ በሚያደርገው ጥንቃቄ በመገረም ጉዳዩን በዝርዝር ለእንግሊዝ መንግስት ጎብኝዎቼ ነገርኳቸው።
“የግንቦት 7 ልዩ ኮማንዶ ከቃሊቲ መንጭቆ ያወጣኛል ብለው ይሰጋሉ መሰለኝ፤ ሲያንቀሳቅሱኝ ከምክንያት ያለፈ ጥንቃቄ ያደርጋሉ” አልኩ። በመሃከላችን ተቀምጦ የነበረው የደህንነት ሰው ተናደደ።
ጥንቃቄ የሚደረገው ስጓጓዝ ብቻ አይደለም። ከውጭ ሰው አምጥተው እታሰርንበት ግቢ ውስጥ የሚያሰሩት ነገር ካለ፣ “እቤት ውስጥ ግቡ” እንባላለን። ስራው እስኪያልቅ ይቆለፍብናል። ሽንት ቤትና እጅና እቃ መታጠቢያው ገንዳ አካባቢ የሚሰራ ስራ ካለም እንዲሁ ይቆለፍብናል።
ቃሊቲ ከገባሁ በኋላ ብዙ ጊዜ የተለያዩ የጤና መታወኮች ገጥመውኛል። መጀመሪያ ሰሞን የቃሊቲ እስር ቤት ሃኪሞች እንዲያዩኝ አልተፈቀደላቸውም ነበር። ለተብርሃን ተፈልጋ መጥታ ነው፤ እንደገና ለተቀሰቀሰብኝ ኪንታሮት በሽታ መድሃኒት የሰጠችኝ። እሷ ስትመጣ አሰፋና ዳዊት እቤት ውስጥ ይዘጋባቸዋል። ለተብርሃን ምርመራ የምታደርግልኝ ግቢው ውስጥ እደጅ ነው። የኪንታሮት ምርመራ ደጅ ማድረግ አልቻለችም። የነገርኳትን ብቻ ሰምታ መድሃኒት አዘዘችልኝ።
ከለተብርሃን በኋላ አስናቀች የምትባል የጤና መኮንን ተተካች። አስናቀች የቃሊቲ ሃኪም ናት። ስሟን ያወቅሁት ከተዘጉበት ክፍል በቀዳዳ አሾልቀው ካዩዋት ቁራኛዎቼ ነው። አስናቀች የትግራይ ተወላጅ አይደለችም። እንደ ለተብርሃን ሩህሩህ መሆኗ ያስታውቃል። ከበሽታዬ አልፋ እንደ ለተብርሃን ስለ ሌላ ነገር ግን አታናግረኝም። እንኳን ለሌላ ወሬ ከህክምና ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ለመናገርም ድፍረት ያላት አትመስልም። ፖሊሶቹን፤ “ከዚህ ዞር በሉ፤ ሃኪምና በሽተኛ ብቻቸውን መሆን (ፕራይቬሲ) ያስፈልጋቸዋል” አትላቸውም። “ለምንድነው እዚህ ካፊያ እያካፋ፣ እውጭ ምርመራ የማደርግለት” አትልም።
ቃሊቲ ከአምስት ጊዜ በላይ ጥርሴን በጣም ታምሜአለሁ። በህመሙ የተነሳ ፊቴ በተደጋጋሚ ክፉኛ አብጧል። ተስቦ፣ ቁርጠት፣ ተቅማጥ፣ የመሳሰሉት የጤና መታወኮች በተደጋጋሚ ገጥመውኛል። አንድ ሰሞን  ጉንፋን ደንበኛው አድርጎኝ ነበር። ሁሉም በሽታ በህመም ማስታገሻና በጸረ ባክቴሪያ መድሃኒት እንዲታለፍ ተደርጓል።
ጥርሴ እንዲነቀልልኝ በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቤአለሁ። የሰማኝ አልተገኘም። የሚታዘዝልኝንም መድሃኒት በአንዴ ለመስጠት ፈቃደኛ  አይደሉም። ሰአቱ በደረሰ ቁጥር ጠዋት፣ ምሳ ሰዓትና እራት ሰዓት ላይ እየተቆነጠሩ ይሰጡኛል። ይህ አሰራር ቀድሞ ያልነበረ አሰራር ነው። ማታ ማታ እነ አብርሃም በሩን ቆልፈው ከሄዱ ለኔ ብለው አይመለሱም። በዚህ የተነሳ የህመም ማስታገሻ መድሃኒት ታዞልኝም መድሃኒቱ በእጄ ስለማይሰጠኝ እየተሰቃየሁ ማደር እጣዬ ነው።
እኔን ውጭ አውጥቶ ከሌላ ሃኪም ጋር ማገናኘት የማይታሰብ ነው። ቁራኛዎቼ ለትንሹም ለትልቁም ቃሊቲ ወደ አለው የጤና ክሊኒክና በአካባቢው ወዳለ ጤና ጣቢያ ይወስዳሉ። ከዛም አልፎ እስከ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተወስደው ህክምና አግኝተዋል። ምንም ያህል ቢያመኝ ይህንን መብት ወያኔዎች ለኔ አልሰጡም።
አስናቀችም አንድም ቀን የሃኪምነት የሥነምግባር ግዴታዋን ተጠቅማ “ሌላ ቦታ ተወስዶ ይመርመር” የሚል ጥያቄ አቅርባ አታውቅም። የደረት ማዳመጫውንና የደም ግፊት መለኪያውን ይዛ መጥታ እዛው ጸሃይ ወይም ዝናብ ላይ የምታደርገውን አድርጋ ትሄዳለች። የደም ግፊቴን ስትለካ ግን ግፊቱ በትንሹም ቢሆን ከፍ የሚያደርግ ነገር ታስከትልብኝ እንደነበር ሳትረዳ ተለያየን።
ሌላው ከወያኔ ጥብቅ ቁጥጥር ጋር ተያይዞ የተነፈግኩት መብት ጸጉር የመስተካከል መብት ነው። እኔ ይህን መብት እንዳልጠይቅ በታፈንኩበት ወቅት ቦርሳዬ ውስጥ ያገኟትን የጸጉርና የጢም ማስተካከያ ተሰጥቶኛል። የራሴ ማስተካከያ ባይኖረኝ ኖሮ በጠርሙስ ይላጩኝ ነበር? ወይም ማስተካከያ ይገዙልኝ እንደነበር የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው።
ቃሊቲ እንደገባሁ በዚህ ጸጉር ማስተካከያ ዳዊትና አሰፋን ጠይቄ ጸጉሬን እንዲያስተካክሉኝ ማድረግ ጀምሬ ነበር። በዛውም እነሱንም ተራ በተራ በዚሁ ማስተካከያ አስተካክላቸዋለሁ። እርስ በርስ በመጨቃጨቃቸው የተነሳና ጠባያቸውም እየተበላሸ ስለሄደ ሁለቱንም ማስተካከሌን አቆምኩ። እንዲያውም “ደጁን ማያ ሰበብ ይሆናችኋል። እነ ብርሃነ እየወሰዱ ሌላ ጋር እንድትስተካከሉ ያድርጉ” አልኳቸው። አሳሪዎቻቸውም ሳይወዱ በግድ እነአሰፋን ሌላ ዞን እየወሰዱ ማስተካከል ጀመሩ። ተስተካክለው እስኪጨርሱ ሌላ እስረኛ ማስተካከያው ክፍል እንዳይገባ ይደረግ ነበር። እነ ዳዊት ለአስተካካዮቹ አንድ ቃል እንዳይተነፍሱ ብርሃነ ወይም በሪሁ እዛው ተቀምጠው፣ ጠብቀው ሲጨርሱ ይዘዋቸው ይመለሳሉ።
ቁራኛዎቼ የትም ቦታ ሲወሰዱም በሻምበል በሪሁ ወይም በሻለቃ ብርሃነ ታጅበው ነው። ለህክምና እንደሚወሰደው እንደሌላው እስረኛ፣ ከሌላው እስረኛ ጋር ተቀላቅለው በአንድ መኪና አይሄዱም። የሚንቀሳቀሱት ለብቻቸው አንድ መኪና ተመድቦላቸው ነው።
ቤተሰብ ጥየቃም ሲሄዱ በሪሁ ወይም ብርሃነ ሳያጅቧቸው አይሄዱም። በተለይ የአሰፋ ቤተሰቦች የሚመጡበትን አስቀድመው ስለማይናገሩ እነ ብርሃነ ተፈልገው እስከሚገኙ ቤተሰቦቹ ለረጅም ሰዓታት የሚጉላሉበት ጊዜ ነበር። ዳዊት በሶስት ዓመት ዘመዶቹ ሊጎበኙት የመጡት አንድ ጊዜ ብቻ ስለሆነ ችግር አልነበረበትም። አንዷንም ጊዜ ቢሆን ዘመዶቹ ብዙ ተንገላተው የደም እንባ አንብተው ነው ሊያገናኙት የቻሉት። አሰፋና ዳዊት ከምግብ ጠባቂዎች ጋር በቀጥታ እየተገናኙ ምግባቸውን እንዳይቀበሉ የተደረገው ከመጋቢዎች ጋር እንዳያወሩ ተፈርቶ ነው።
ይህንና ሌሎችም ፈጽመው ቅጥ ያጡ ቁጥጥሮች ለማድረግ ወያኔ ለምን እንደተገደደ እስከ ዛሬ ለኔ ሚስጥር ነው።
(ከአንዳርጋቸው ጽጌ “የታፋኙ ማስታዎሻ” መጽሐፍ የተቀነጨበ፤2012 ዓ.ም)

Page 10 of 627