Administrator

Administrator

 የተመድ ማዕቀብ ያልገታት፣ የአለማቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ውግዘት ያላስጨነቃት፣ የአሜሪካ ዛቻና ማስፈራሪያ ያላስበረገጋት ሰሜን ኮርያ፤ የሚሳኤልና የኒውክሌር ሙከራዎቿን በተጠናከረ መልኩ እንደምትገፋባቸውና በየሳምንቱ በቋሚነት የሚሳኤል ሙከራ ለማድረግ ማቀዷን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሰሜን ኮርያ በቀጣይም ተጨማሪ የሚሳኤል ሙከራዎችን በመደበኛነት ለማካሄድ ማቀዷን ለቢቢሲ የተናገሩት የአገሪቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃን ሶንግ ሪዮል፤ አሜሪካ ይህንን በመቃወም በእኛ ላይ ወታደራዊ እርምጃ የምትወስድ ከሆነ እልቂት የሚያስከትል የኒውክሌር የአጸፋ እርምጃ እንወስዳለን፤ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጦርነትም ይቀሰቀሳል ማለታቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡ ባለስልጣኑ ይህን ማለታቸውን ተከትሎ፣ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሉ ካንግ በሰጡት መግለጫ፤ አገራቸው ውጥረትን የሚያባብሰውን የሰሜን ኮርያን ድርጊትና ሃሳብ እንደምትቃወም ያስታወቁ ሲሆን ቻይና የሰሜን ኮርያ የኒውክሌርና የሚሳኤል ፕሮግራም በእጅጉ እንዳሳሰባት መግለጻቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ለረጅም ጊዜያት የዘለቀው የሰሜን ኮርያና የአሜሪካ ወታደራዊ ውጥረት ባለፉት ሳምንታት እየተባባሰ መቀጠሉን ያስታወሰው ዘገባው፤ አሜሪካ የባህር ሃይል ቡድን ወደ ኮርያ ልሳነምድር መላኳን ተከትሎ፣ ራሴን ለመከላከል ተዘጋጅቻለሁ ያለቺው ሰሜን ኮርያ፣ ባለፈው ቅዳሜ የጦር ሃይል አቅሟን የሚያሳይ ትርዒት ማቅረቧንና በነጋታውም የከሸፈ የሚሳኤል ሙከራ ማድረጓን ጠቁሟል፡፡

 አሜሪካ እ.ኤ.አ በ1993 በሞቃዲሾ ታጣቂዎችን ለመደምሰስ ከተካሄደውና 18 የልዩ ሃይል ወታደሮቿንና ሁለት የጦር ሄሊኮፕተሮቿን ካጣችበት ጦርነት በኋላ ሰሞኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ መላኳን ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡
ከአሜሪካ 101ኛ የአየር ወለድ ክፍለ ጦር የተመረጡት ወታደሮች፣ ለሶማሊያ ብሄራዊ የጦር ሃይል አልሻባብን በተሻለ ሁኔታ መታገል የሚችልበትን አቅም የሚፈጥር ወታደራዊ ስልጠና እና የማስታጠቅ ስራ እንደሚሰሩ አንድ የአሜሪካ ወታደራዊ ቃል አቀባይ መናገራቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ በሶማሊያ ሰፋ ያለ ወታደራዊ ሚና መጫወት የሚያስችል እቅድ ማጽደቃቸውንና ይህም በአልሻባብ ላይ የተጠናከረ የአየር ድብደባ ጥቃት ዘመቻ ለማካሄድ የታለመ እንደሆነም ዘገባው አክሎ ጠቁሟል፡፡
አዲሱ ሶማሊ-አሜሪካዊ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ ፎርማጆ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ፣ ተቀማጭነቱን በሶማሊያ አድርጎ ምስራቃዊ አፍሪካን በሽብር በሚያተራምሰው ጽንፈኛው ቡድን አልሻባብ ላይ አዲስ የማጥቃት ዘመቻ ማወጃቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

 ከሊቢያ በመነሳት ሜዲትራንያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት የጀልባ ጉዞ ላይ የነበሩ 28 የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ህገወጥ ስደተኞች፣ ሳባርታ ከተባለቺው የሊቢያ የጠረፍ ከተማ አቅራቢያ ሞተው መገኘታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ጀልባዋ ጉዞዋን ጀምራ ጥቂት እንደሄደች በደረሰባት አደጋ መሰበሯን የጠቆመው ዘገባው፤ በርሃብና በውሃ ጥም ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉት 28 ስደተኞች አስከሬንም በአንድ ሊቢያዊ አሳ አጥማጅ መገኘቱን የሊቢያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የደህንነት ክፍል ኮማንደር የሆኑት አህማይዳ ካሊፋ አምስላም ባለፈው ማክሰኞ ማስታወቃቸውን ገልጧል፡፡ በባህር ጉዞ ላይ የነበረቺው ጀልባ ሞተሯ ተበላሽቶ ከቆመች በኋላ ምግብና ውሃ በማጣት ለህልፈተ ህይወት ከተዳረጉትና አራቱ ሴቶች ከሆኑት ስደተኞች መካከል አብዛኞቹ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት ዜጎች መሆናቸውን የጠቆሙት ባለስልጣኑ፤ የቀብር ስነስርዓታቸውም በሊቢያ በሚገኝ የህገወጥ ስደተኞች መካነ መቃብር እንደተፈጸመ ተናግረዋል፡፡
ሊቢያ በአፍሪካውያን ስደተኞች ዘንድ ወደ አውሮፓ አገራት ለመግባት ተቀዳሚዋ የጉዞ መስመር መነሻ መሆኗን የጠቆመው ዘገባው፤ ባለፉት 3 አመታት ውስጥ ብቻ ከ150 ሺህ በላይ አፍሪካውያን ስደተኞች በሊቢያ በኩል ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ ጣሊያን መግባታቸውን አስታውሷል፡፡

በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የቅንጦት መኪኖችን በማምረት የሚታወቀው ቴስላ የተባለው ኩባንያ፣ ለረጅም አመታት በታዋቂው ጄኔራል ሞተርስ ኩባንያ ተይዞ የቆየውን የአሜሪካ ቁጥር አንድ ሃብታም የመኪና አምራች ኩባንያነት ደረጃ መረከቡ ተዘግቧል፡፡
ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ አጠቃላይ የሃብት መጠኑ 51.54 ቢሊዮን ዶላር የደረሰውና በቢሊየነሩ ኤለን ሙስክ የተቋቋመው ቴስላ፤ 50.22 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ያለውን ጄኔራል ሞተርስ ኩባንያ በመብለጥ የአሜሪካ ቁጥር አንድ የመኪና አምራች ኩባንያ ለመሆን መብቃቱን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ከ13 አመታት በፊት የተቋቋመው ቴስላ ኩባንያ የሃብት መጠኑ ከጄኔራል ሞተርስ ቢበልጥም በገበያ ድርሻ ግን አነስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ ቴስላ በአሜሪካ የመኪና ገበያ ያለው ድርሻ 0.2 በመቶ ብቻ ሲሆን ጄኔራል ሞተርስ በበኩሉ፣ 17.3 በመቶ የገበያ ድርሻ እንዳለው ገልጧል፡፡
ቴስላ በ2016 ያመረታቸው መኪኖች 76 ሺህ ያህል ብቻ እንደነበርና ይህ ቁጥር ከጄኔራል ሞተርስ በእጅጉ ያነሰ  እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ ጄኔራል ሞተርስ በአመቱ 546 ሺህ ያህል መኪኖችን መሸጡን አስታውሷል፡፡ ቢሊየነሩ ኤለን ሙስክ፣ ኩባንያውን የበለጠ በማስፋፋትና የማምረት አቅሙን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ፣ በቀጣዩ አመት ግማሽ ሚሊዮን ለማድረስ ማቀዳቸውም ተነግሯል፡፡

 አገሪቱ በምግብ እጥረት፣ በዋጋ ግሽበትና በፖለቲካዊ ቀውስ እየማቀቀች ነው

      በምግብ እጥረት ችግር ለተጠቁ ዜጎቹ ምላሽ መስጠት ያቃተው የቬንዙዌላ መንግስት፣ ከሚያስተዳድረው የነዳጅ ኩባንያ የአሜሪካ ቅርንጫፍ ካዝና ወጪ ያደረገውን 500 ሺህ ዶላር ገንዘብ፣ ለፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዓለ-ሲመት ማከናወኛ እንዲውል በስጦታ መልክ ማበርከቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ቬንዙዌላ ሲትጎ ፔትሮሊየም በተባለው ኩባንያ በኩል፣ ይህንን ገንዘብ ለትራምፕ በዓለ-ሲመት ማድመቂያ ማዋሏን የሚያረጋግጥ መረጃ ባለፈው ረቡዕ ይፋ መደረጉን የጠቆመው ዘገባው፤ ይህ መረጃ የወጣው የምግብ እጥረትና የዋጋ ግሽበት እየተባባሰ ከመጣው የዜጎች ተቃውሞና የእርስ በእርስ ግጭት ጋር ተደማምረው፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ከፋ ቀውስ እየከተቱት እንደሆነ በሚነገርበት ወሳኝ ወቅት ላይ መሆኑ ትኩረት ስቧል ብሏል፡፡
ከነዳጅ ገቢ ማሽቆልቆልና ከህዝባዊ አመጽ ጋር በተያያዘ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ የምትገኘዋ ቬንዙዌላ፤ ከሶስት ወራት በፊት የተከናወነውን የልዕለ ሃያሊቷን አሜሪካ ድግስ ለማድመቅ ይህን ያህል ገንዘብ ማውጣቷን የሚያረጋግጠው የፌዴራል የምርጫ ኮሚሽን መረጃ ብዙዎችን እያነጋገረ እንደሚገኝም ዘገባው ገልጧል፡፡
የቬንዙዌላ የገንዘብ ስጦታ ለትራምፕ በዓለ-ሲመት ማድመቂያ የገንዘብ ስጦታ ካበረከቱ አንዳንድ ታዋቂ የአሜሪካ ኩባንያዎች ስጦታ በእጅጉ እንደሚልቅ የጠቆመው ዘገባው፤ ከእነዚህ ኩባንያዎች መካከልም 250 ሺህ ዶላር የሰጠው ፔፕሲ እና 150 ሺህ ዶላር የሰጠው ዎልማርት እንደሚገኙበት አመልክቷል፡

ፌደሬሽኑ ለውጥ የሚፈጠረው ቀስ በቀስ ነው ይላል፡፡
                      
       ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢትዮጵያ  ፕሪሚዬር ሊግና ከፍተኛ ሊግ ስፖርታዊ ጨዋነት ተጓድሏል፡፡ በየስታድዬሙ  የተለያዩ የስርዓት አልበኝነት ችግሮች በተደጋጋሚ እያጋጠሙ ናቸው፡፡ በየስታድዬሞቹ ስርዓት አልበኛ ደጋፊዎች የሚፈጥሯቸው ሁከቶች እና ግርግሮች ሰላማዊ ስፖርት አፍቃሪዎች ለጉዳት እየዳረጉ ከመሆናቸውም በላይ ወደ ስታዬሙ እየተሳበ የሚመጣውን ተመልካች አጓጉል ስጋት ውስጥ እየከተቱ ናቸው፡፡ ምርጥና  አንጋፋ ተጨዋቾችም  ክብረነክ በሆኑ ስድቦች የሚከፉባቸው አጋጣሚዎች እየበዙ መጥተዋል፡፡ ጨዋታዎችን የሚመሩ ዳኞች ለአስከፊ ጥቃት እና ሞራል የሚነኩ ስድቦች እየተደረጉ ሲሆን  ፖሊሶች እና የፀጥታ ኃላፊዎች በየረብሻዎቹ ዋና ተጠቂዎች እየሆኑም ናቸው፡፡ ስታድዬሞች እና አካባቢያቸው ያሉ ንብረቶች ላይም ውድመት እየተከሰተ ነው፡፡
የአዳነ  ተማፅኖ
ከሳምንት በፊት በአዲስ አበባ በተካሄደው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ላይ ስፖርት አድማስ ካስተዋላቸው ገጠመኞች መነሳት ይቻላል፡፡ በካታንጋ አካባቢ የቡና እና የጊዮርጊስ ደጋፊዎች በሁለተኛው ግማሽ የፈጠሩት ሁከት ነበር፡፡ ደጋፊዎች የስታድዬሞቹን ወንበሮች በመነቃቀል ተወራውረው በንብረት ላይ ውድመት አድርሰዋል፡፡  ለተወሰኑ ደቂቃዎች የተስተዋለው ሁከት የስታድዬም ተራ አስከባሪ የሆኑ ደጋፊዎች  እና ፌደራል ፖሊሶችን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የዘፈቁ ነበር፡፡ በሌላ በኩል የደርቢ ጨዋታውን ይመራ የነበረው የመሃል ዳኛ፤ የየክለቦቹ አሰልጣኞች እንዲሁም ተጨዋቾች በየጊዜው በአንዳንድ ስርዓት የሌላቸው ደጋፊዎች ሲሰደቡ እና  በተለያዩ ስም አጥፊ ስድቦች ሲዘለፉ ነበር፡፡ ከሁሉ የሚያሳዝነው ግን  በቀኝ ጥላ ፎቅ የተቀመጡ የተወሰኑ የቡና ደጋፊዎች የቅዱስ ጊዮርጊሱን አዳነ ግርማ በመጥፎ ስድቦች በጋራ እየጮሁ ያስቀየሙበት አጋጣሚ ነው፡፡ አዳነ ግርማ ለስፖርት አድማስ በሰጠው አስተያየት የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በተመሳሳይ ጥፋቶች ላይ ሃላፊነቱን ወስዶ መንቀሳቀስ እንዳለበትና ጥቂት ስርዓት አልበኛ ደጋፊዎች በስታድዬሙ ለሚፈጥሩት ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደለው ተግባር ላይ የማያዳግም ቅጣት እንዲተላለፍባቸው  ተማፅኗል፡፡ በርግጥም በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ያገለገሉ አንጋፋና ምርጥ ተጨዋቾች የሚሰደቡበት አጋጣሚ በአዳነ  ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ቡናው ጋቶች ፓኖም ፤ የደደቢቱ ብርሃኑ ፋዲጋ ፤ የመብራት ሃይሉ ዳዊት እስጢፋኖስ፤ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አበባው ቡጣቆ….እና ሌሎችም ተጨዋቾች በጥቂት ስርዓት አልበኛ ደጋፊዎች የሚሰደቡባቸው አጋጣሚዎች እየበዙ መምጣታቸው የሚያሳስብ ነው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ስታድዬም ተጨዋቾችን ብቻ ሳይሆን፤ የክለብ አመራሮችና የፌደሬሽን ሃላፊዎችን እንዲሁም  ዳኞችን መሳደብ የጥቂት ስርዓት አልበኛ ደጋፊዎች ልማደኛ ተግባር መሆኑ የስፖርት ቤተሰቡን አሳስቦታል፡፡  
አዳነ ግርማ ለስፖርት አድማስ አስተያየት ሲሰጥ ‹‹ለስፖርታዊ ጨዋነት ኃላፊነቱን ወስደን  በጋራ መስራት ያስፈልጋል›› ያለ ሲሆን አንዳንድ ከባድ ስርዓት አልበኝነቶች  እንዳይደገሙ አስተማሪ ቅጣቶችን ለማስተላለፍ የፌደሬሽኑ የዲስፕሊን ኮሚቴ በትኩረት መስራት እንደሚኖርበት አስገንዝቦ፤ በተጨዋቾች ላይ የሚደርሱ የጥቂት ስርዓት አልበኛ ደጋፊዎች ስድቦችን ለመከላከል ብዙ መሰራት አለበት ይላል፡፡ ‹‹ጠንካራ የተጨዋቾች ማህበር ቢኖር እንደዚህ አይነት ክስተቶችን በተለያዩ መንገዶች መፍትሄዎች እንዲገኝባቸው ይሰራ ነበር። ይሁንና ማህበሩ ህልውና ያለው አይመስልም፡፡   በጉዳዩ ባለመስራቱ የተጨዋቾችን ብሶት የሚሰማ እየጠፋ ነው፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽን የተጨዋቾች ወኪል ሆኖ ችግሮችን ለማጥፋት መስራት አለበት ›› በማለት አዳነ ግርማ ምክሩን ይሰጣል፡፡
‹‹ለብሄራዊ ቡድን ወሳኝ ጎሎችን ሳገባ የሚደሰተው መቶ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡
በሞራል እና በቁርጠኝነት ክለቤንም ሆነ ብሄራዊ ቡድን እንደማገለግልም ይታወቃል፡፡ ስለዚህ በየጊዜው  መሰደብ ሳይሆን መመስገን እና መከበር አለብኝ ›› የሚለው አዳነ ግርማ ‹‹ እድገቴ በስርዓት ነው፤ በእግር ኳስ ዛሬ ላለሁበት ደረጃ የደረስኩት እና የምታወቀው በትጋት በመስራቴ ነው ፡፡ ሁሌም ባደረግኩት ማልያ በፍላጎት እና በእልህ ነው የምጫወተው ፡፡ ለምታጠቀው ማልያም ሟች ነኝ›› ሲልም ለስፖርት አድማስ ይናገራል፡፡ ይህ ባህርይው ብዙውን ጊዜ ለተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች የማይመች ሆኖ ለስድብ እየዳረገው መሆኑ የሚገርም ነው፡፡ ተምሳሌት ሊሆን ሲገባው፡፡ ባለትዳር እና የአምስት እና የ3 ዓመት እድሜ ያላቸው ህፃናት አባት የሆነው አዳነ ግርማ በስታድዬም የመሰደቡ ነገር  ቤተሰቡን ሁሉ እያሳቀቀበት መሆኑንም ለስፖርት አድማስ ሲገልፅ፤ ሜዳ ላይ እየተጫወተ ሲሰደብ ከዓላማው ባይዘናጋም እሱን ብለው የሚመጡ ቤተሰቦቹ እና ሌሎች ወዳጅ እና ዘመዶቹ በስታድዬም ገብተው መረበሻቸው እያስከፋው መሆኑን በማስረዳት ነው፡፡
ክበረነክ ስድቦች የቤተሰብ እና የሙያ ክብርን ከሟጉደፋቸውም በላይ ረጅም ዘመን ግልጋሎት ለሚሰጡ ተጨዋቾች ሞራል መነካት ምክንያት ነው። ስድብን ከስታድዬም ለማጥፋት ሁሉም የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚኖርባቸውም ይመክራል፡፡
ስታድዬም ውስጥ ስሰደብ እንደውም እልህ ውስጥ እገባና የተሻለ ለመንቀሳቀስ እሞክራለሁ የሚለው አዳነ፤  ደጋፊዎች ሰደቡኝ ብዬ እሰጥ አገባ ውስጥ አልገባም፤ ተሳዳቢነት ወይም ጥል ያደግኩበት ባህርይ አይደለም፡፡ ብዙ የሚያደንቀኝ የሚያከብረኝ ደጋፊ በመኖሩ በትጋት የምሰራ የእነሱን ደስታ ለማግኘት ነው ሲልም ተናግሯል። ከኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ለእኔ ልዩ ክብር እና አድናቆት ያላቸው ጥቂት አይደሉም በየጊዜው፤ በየመንገዱ ሲያገኙ በጣም ያበረታቱኛል ስለዚህ የተወሰኑ ጥቂት ደጋፊዎች ስታድዬም ሆን ብለው በመግባት የሚሳደቡበት ሁኔታ ሁሉንም ስፖርት ቤተሰብ የሚወክል ተግባር እንዳልሆነ መታወቅ ይኖርበታልም ብሏል፡፡ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ምክንያት በሆኑ ስፖርተኞች ሙያተኞችና ደጋፊዎች ላይ አስተማሪ የሆነ ቅጣት ተግባራዊ አደርጋለሁ የሚለው ፌደሬሽን እን አደና ለሚያቀርቡት ጥሪ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል፡፡ አሁን 31 ዓመቱ የሆነው አዳነ ግርማ ከታዳጊ ፕሮጀክት ጀምሮ እግር ኳስን በክለብ ደረጃ ሲጫወት ከ15 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ለሃዋሳ ከነማ ለ3 የውድድር ዘመና የተጫወተ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ላለፉት 10 ዓመታት ሲጫወት 4 ጊዜ የፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮነት ክብሮችን ተጎናፅፏል፡፡የብሄራዊ ቡድን ተጨዋችነት በታዳጊ፤ በወጣት ቡድን ፤ በኦሎምፒክ እና በዋና ብሄራዊ ቡድን ደረጃ ነው የተጫወተው ለ11 ዓመታት ለብሄራዊ ቡድኑ ሲጫወት 36 ጨዋታዎችን አስቆጥሮ 8 ጎሎችን በስሙ አስመዝግቧል፡፡
የጋቶች መሰደብና  ተለዋዋጭ ውሳኔዎች
በስታድዬም ውስጥ በሚገቡ ጥቂት ስርዓት አልበኛ ደጋፊዎች ሰለባ ከሆኑ ተጨዋቾች ሌላኛው የኢትዮጵያ ቡናው ጋቶች ፓኖም  ይገኝበታል፡፡ ባለፉት 5 ዓመታት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 29 ጨዋታዎችን አድርጎ 7 ጎሎች በስሙ ያስመዘገበው የ22 ዓመቱ ጋቶች ፓኖም በየስታድዬሙ ለደጋፊዎች ስድብ ከተጋለጡ ተጨዋቾች ግንባር ቀደም ተጠቃሹ ነው፡፡  በኢትዮጵያ ኘሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት የውድድር መርሀ ግብር ድሬዳዋ ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና መጋቢት 07/2009 ዓ.ም ጨዋታቸውን ባካሄዱበት ወቅት የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች በተከሰተው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲስኘሊን ኮሚቴ ይጠቀሳል፡፡ የዲስፕሊን ኮሚቴው ጨዋታ የመሩት ዳኞችና ኮሚሽነሮች ያቀረቡትን ሪፖርት መርምሮ ባሳለፈው ውሳኔ የድሬዳዋ ከነማ እግር ኳስ ደጋፊዎች በኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች ጋቶች ፓኖም ላይ ፀያፍና በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በእጅጉ የተወገዘ ድርጊት መፈፀማቸው አረጋግጧል፡፡  ስለሆነም  የድሬዳዋ ከነማ እግር ኳስ ክለብ 75,000 ብር/ሰባ አምስት ሺህ ብር/ የገንዘብ ቅጣትና ቀጣዩን የኘሪሚየር ሊግ ጨዋታ ያለደጋፊ እንዲጫወት ወስኖ ነበር፡፡ በተመሳሳይ በዕለቱ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ የወጣው የኢትዮጵያ ቡናው ጋቶች ፓኖም በፈፀመው ጥፋት የድሬዳዋ ከነማ ደጋፊዎች የፈጠሩበትን የስነልቦና ጫና ከግምት ውስጥ በማስገባት የአንድ ጨዋታ ቅጣት ማስተላለፉና፤ የድሬዳዋ ከነማው የህክምና ባለሙያ አስራት ለገሠ ደግሞ በእለቱ ለፀብ የሚያነሳሳ ድርጊት በመፈፀሙ ምክንያት አራት ጨዋታዎች እንዲታገድና ብር 5,000/አምስት ሺህ ብር/ እንዲቀጣ መወሰኑን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ አስታውቆ ነበር፡፡
ይሁንና ከላይ የተጠቀሱት ውሳኔዎች በማግስቱ በሌላ ውሳኔ ተቀይረዋል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፒሊን ኮሚቴ የድሬዳዋ ከነማ እግር ኳስ ክለብ  ባቀረበው አቤቱታ ምክንያት ጉዳዩ በይግባኝ ሰሚ ቋሚ ኮሚቴ ታይቶ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ድረስ በዲሲፒሊን ኮሚቴ የተላለፈው ውሳኔ በክለቡ ላይ ተፈፃሚ እንደማይሆንና በዝግ ስታድየም የሚካሄድ ጨዋታ አፈፃፀም ከውሣኔው በኋላ በሊግ ኮሚቴ የሚታይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከፍተኛው ሊግ እና የዲስፕሊን ኮሚቴው
በከፍተኛ ደረጃ ስፖርታዊ ጨዋነት ከተጓደለባቸው የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ውድድሮች አንዱ የከፍተኛ ሊግ ነው፡፡ ለዚህ ከሰሞኑ የበአንድ ጨዋታ የተፈጠረው ረብሻ እና በፌደሬሽኑ ዲስፕሊን ኮሚቴ የተላለፈው ርምጃ በማስረጃነት ማቅረብ ይቻላል፡፡ መጋቢት 29/2009 በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ17ኛ ሳምንት ውድድር ሀድያ ሆሳዕና ከሻሸመኔ ከተማ ሆሳዕና ላይ ጨዋታቸውን ባካሄዱበት ወቅት የተፈጠረውን ከስፖርታዊ ጨዋነት የወጣ ሁከትና ብጥብጥ በማጣራት የዲሲኘሊን ኮሚቴ በክለቦች እና በተጫዋቾች ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ በእዚሁ መሠረት የሀድያ ሆሳዕና እና የሻሸመኔ ከተማ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች በፈጠሩት ሁከትና ብጥብጥ ጨዋታው ለ15 ደቂቃዎች እንዲቋረጥ ምክንያት በመሆናቸው ክለቦቹ እያንዳንዳቸው ብር 25,000/ሀያ አምስት ሺህ ብር/ እንዲቀጡ ወስኗል፡፡ ከዚህ ቅጣት በተጨማሪም ዋና ዳኛውን የተማታው እና ተጫዋቾች አደጋ እንዲያደርሱበት ያነሳሳው የሻሸመኔ እግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ያሬድ አበጀ ከማንኛውም አይነት የእግር ኳስ ስፖርት እንቅስቃሴ ለአንድ ዓመት እዲታገድና የብር 15,000/አስራ አምስት ሺህ ብር/ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፎበታል፡፡  ዋና ዳኛውን ለመደብደብ ሙከራ ያደረገው የቡድኑ አምበል አብዮት ወንዲፍራው የተጋጣሚውን ቡድን ተጫዋች በመማታቱና አርአያነት ማሳየት ሲገባው ከሜዳ አልወጣም በማለቱ ለስድስት ወራት እንዲታገድና የ10,000ብር/አስር ሺህ ብር/ ቅጣት የወሰነበት ሲሆን፤ በሀይሉ አባተ፣ አሸናፊ ከበደ፣ ሰለሞን ሽታ የተባሉት የሻሸመኔ ከተማ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች ዋና ዳኛውን ለመደብደብ ከመሞከር አልፈው በሀይሉ በስለት፤ አሸናፊና ሰለሞን ደግሞ በድንጋይ አደጋ ለማድረስ በመሞከራቸውና ከፍተኛ የዲሲኘሊን ጥፋት በመፈፀማቸው እያንዳንዳቸው ለስድስት ወራት ከጨዋታ እንዲታገዱና የ15,000 ብር/አስራ አምስት ሺህ ብር/ ቅጣት እንዲከፍሉ ወስኖባቸዋል፡፡ በዲሲኘሊን ኮሚቴ የተላለፈውን የቅጣት ውሳኔ በ10 ቀናት ውስጥ ለፌዴሬሽኑ ገቢ ካልሆነ ክለቦቹ በቀጣዮቹ የውድድር ኘሮግራሞች እንዳይሳተፉ የሚደረግ መሆኑንም የዲሲኘሊን ኮሚቴው በውሳኔው አስታውቋል፡፡
ቀስ በቀስ ለውጥ መፍጠር - የፌደሬሽኑ እቅድ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በ2009 አከናውናቸዋል ካላቸው እቅዶቹ መካከል በየደረጃው በሚካሄዱ ውድድሮች የሚስተዋለውን የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር እንዲሻሻል ማድረግ መሆኑን በሪፖርቱ አስታውቆ የነበረ ሲሆን  ለውጥ የሚፈጠረው ቀስ በቀስ ነው በማለት የፌደሬሽኑ የፅህፈት ቤት ሃላፊ እና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ወንድምኩን አላዩ ለስፖርት አድማስ ተናግሯል። የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ባስቀመጠው እቅድ መሰረት ችግሮችን ለመፍታት እንዲቻል ጥናት በማካሄድና ወጥ እቅድ በማዘጋጀት ከመንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በትብብር ሰርቷል የሚለው የፅህፈት ቤት ሃላፊው፤ ጥናቱን መሰረት በማረግ የዲስፕሊን መመርያው መሻሻሉን፤ የክልል ፌዴሬሽኖችን እና የጸጥታ ኮሚቴዎችን በማጠናከር በየደረጃው የሚካሄዱ ውድደሮችን በመምራት እገዛ እንዲኖራቸው ማስቻሉን በክለቦች የተመዘገበ የደጋፊ ማህበር እንዲኖራቸው በማድረግ ስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ሲፈጠር ተጠያቂ የሚሆኑበትን ስርአት ለመዘርጋት እየተሞከረ መሆኑን አብራርቷል። ክለቦችን በማሳተፍ ወጥ እና ለስፖርታዊ ጨዋነት ምክንያት የማይሆን አመታዊ የውድድር ስርአት እና ፕሮግራም በማዘጋጀት ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራ የሚገልፀው ፌደሬሽኑ በውድድር ዘመኑ መጀመርያ ላይ አገር አቀፍ ውይይቶች መካሄዳቸውንና በክልሎች ደረጃ በአምስት የተለያዩ ከተሞች ምን ይደርግ በሚል ውይይት መደረጉን ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች  መዘጋጀታቸው አቶ ወንድምኩን ገልጿል፡፡ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች እና መፍትሄዎች በሚል ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የተዘጋጀው ጥናት ለሚመለከታቸው ሁሉ መዳረሱን አቶ ወንድምኩን ገልፆ፤ በቢልቦርድ፤ በባነር በበራሪ ወረቀቶች የተለያዩ የማስተማርያ እንቅስቃሴዎች መሰረጋቸውንም አመልክቷል፡፡ ስለሆነም በ2009 ዓ.ም ካለፈው የውድድር ዘመን በተሻለ የስፖርታዊ ጨዋነት ላይ መሻሻሎች እንደታዩ የፌደሬሽኑ እምነት ቢሆንም ጠንከር ያሉ እንቅስቃሴዎች ባለመኖራቸው የጎላ ውጤት ሊመዘገብ አልቻለም ለማለት ግን አያዳትም፡፡  በ11 የተለያዩ የውድድሮች ዓይነቶች  ገቢ ማሳባሰቢያ እና ወቅታዊ ውድድሮችን ሳይጨምር 1669 ጨዋታዎችን በ8385 ዳኞች ኮሚሽነሮች እና ሌሎች ሙያተኞች በመመደብ በብቃት መምራት እንዲሁም የውድድር የዲሲፒሊን መመሪያ የስፖርታዊ ጨዋነትን ችግር የማይሸከም እና ችግሮች እንዳይደገሙ አስተማሪ የሆኑ እርምቶችን እንደሚወስድ ፌደሬሽኑ በሪፖርቱ በዝርዝር ቢያመለክትም ያን ያህል የሚያመረቃ ስር እንዳልተሰራ ይስተዋላል፡፡
በውድድር ዘመኑ ከሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ የክለብ አመራሮችና፣ የዳኞችና፣ የአሰልጣኞችን፣ የተጨዋቾችን፣ የደጋፊዎችን  ባለድርሻ አካላትን እና የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ዙርያ ገና ብዙ ስራዎች ያስፈልጋሉ፡፡ በየደረጃው የሚከሰተውን የስፖርታዊ ጨዋነት ችግርን ለማሻሻል ሚዲያ በመጠቀም ግንዛቤ እንዲፈጠር በተያዘው እቅድ መስራ ተገቢ ነው፡፡ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር የሚያደርሱ እና የተሳሳተ ውሳኔ የሚሰጡ ዳኞች ላይ አስተማሪ የሆነ ቅጣት ተግባራዊ እንደሚያደርግ የገለፀው ፌደሬሽኑ በየጊዜው ይህን አቋሙን በሚለዋወጡ ውሳኔዎች ማበላሸት የለበትም፡፡ ፌዴሬሽኑ የሚሰጣቸው ወሳኔዎች ፈጣን፣ ፍትሀዊ፣ ወቅታዊ እና ችግር ፈቺ እንዲሆኑ የሚፈልግ ሲሆን፤ በየውድድሮቹ ማጠናቀቂያ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር የነበረባቸውን ክለቦች በመለየት አስተማሪ የሆነ እርምት መውሰዱም በተያዘው እቅድ መሰረት ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል፡፡
ወደፊት ምን መደረግ ይኖርበታል…
በስታድዬም የሚፈጠሩ የስርዓት አልበኝነት ችግሮችን ለማጥፋት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ መነሳት ይኖርባቸዋል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ እና የዲስፕሊን ኮሚቴው በሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎች ብቻ ለውጥ መፍጠር አይቻልም፡፡ በሚዲያዎች ላይ የሚቀርቡ ዘገባዎች፤ ክርክሮች፤ መካሰሶች፤ መወነጃጀሎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በጥንቃቄ መስራት ይገባል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚታየው የደጋፊዎች እንቅስቃሴ የተወሰኑ ችግሮችን ሲፈጥርም በገሃድ የሚስተዋል በመሆኑ በዚያ አቅጣጫ ያሉ ችግር ፈጣሪ ሁኔታዎችን መርምሮ ማየት ተገቢ ነው፡፡
የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮችን መቅረፍ ካልተቻለ እና እየተባባሱ ከሄዱ የስፖርቱን እድገት ከማስተጓጎላቸውም በላይ፤ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን በማባባስ እና በታዳጊዎች ደረጃ ያሉትን ሁኔታዎች ተስፋ ቢስ በማድረግ አሉታዊ ተፅኖዎችን ያሳድራል፡፡ ስድብ፤ ዘረኝነት፤ ጥላቻና አንባጓሮን ከስታድዬም ለማጥፋት ባለድርሻ አካላት በስፋት መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ከሚከወኑ ተግባራት ባሻገር ክለቦች፤ የደጋፊዎች ማህበራት፤ የፀጥታ ሃይሎች በየጊዜው በስፖርታዊ ጨዋነት ዙርያ የምክክር መድረኮችን እያዘጋጁ መስራት አለባቸው፡፡ በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ ያተኮሩ ልዩ ልዩ የስልጠናና እና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችም ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው መታወቅ ይኖርበታል፡፡

 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚያዘጋጀው 6ኛው የሐዋሳ ግማሽ ማራቶን ነገ የአፍሪካን ትልቁን የኢንዱስትሪ ፓርክ እየገነባች በምትገኘው የሐዋሳ ከተማ ይካሄዳል፡፡ የግማሽ ማራቶን ውድድሩ ለአምስት ዓመታት ከተካሄደ በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት አልተከናወነም ነበር። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሐዋሳ ከተማ አስተዳደር እና ከCCECC ከተባለው የኮንስትራክሽ ተቋራጭ ኩባንያ  ጋር በመተባበር የግማሽ ማራቶን ውድድሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አድርገዋል፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮያ ለሚቀጥሉት 3 ዓመታት የግማሽ ማራቶን ሩጫ እና ተያያዠ ውድድሮችን በስኬት ለማካሄድ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
በ6ኛው የሐዋሳ ግማሽ ማራቶን  በዋናው የ21 ኪሜ ውድድር ከ25 ክለቦች የተውጣጡ ከ150 በላይ ምርጥ አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን ከ25 በላይ የጎዳና ላይ ሩጫ ስፖርተኞች ከተለያዩ አገራት በመምጣት ይሳተፉበታል፡፡  በተያያዘም የ7 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ  ሩጫ እና የህፃናት ውድድር  የተዘጋጀ  ሲሆን  ከ4500 በላይ ተሳታፊዎች ይኖራቸዋል፡፡ የግማሽ ማራቶን ውድደሩ በአገር ውስጥ ለሚገኙ አትሌቶች የውድድር እድል የሚፈጥር በመሆኑና የሐዋሳ ከተማን የልማት እና የቱሪዝም እንቅስቃሴ በማስተዋወቅ ውጤታማ  እንደሚሆን ተጠብቋል፡፡ ከአዲስ አበባ 275 ኪሎሜትር ርቃ የምትገኘው  የሐዋሳ ከተማ  በ1700 ሜትር ከፍታ  ላይ ናት፡፡ ከተማዋ የ57 ዓመታት እድሜ ያላት ስትሆን በፈጣን እድገት ላይ የምትገኝ እና ከ500ሺ በላይ ህዝብ የሚኖርባት  ናት፡፡

 በእርግዝና ወይንም ከወሊድ በሁዋላ የሚገጥም ድብርት ስያሜ ነው Postpartum Depression የሚባለው። ባለፈው እትም ያስነበብናችሁ ይህ በእናቶች ላይ የሚደርስ ከባድና ያልታወቀ ችግር በዚህ እትም እልባት ያገኛል። ዶ/ር ባልካቸው ንጋቱ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና ዶ/ር አታላይ አለም የአእምሮ ሐኪም የሰጡትን ጠቃሚ ሃሳብ እንዲሁም ሁለት እናቶች ከሰጡት ምስክርነት ጋር ለንባብ አቅርበነዋል።
“እኔ የሁለት ልጆች እናት ነኝ። እርግዝና ሲከሰት ወይንም ልጅ ሲወለድ እናትየው ስለሌላ ነገር እንዳታስብና በሰላም በደስታ የምትወልደውን ልጅ እንድታስብ እንዲሁም ቤተሰብዋ ቁጥሩ እየጨመረ ሲሄድ ማድረግ የሚገባትን ነገር ከባለቤትዋ እና ከቤተሰብዋ ጭምር በተረጋጋ ሁኔታ ዝግጅት እንድታደርግ መንገዱ ሊከፈትላት ይገባል ። ነገር ግን ይህ መሆኑ ቀርቶ እንዲያውም በፊት ከነበረው ይበልጥ ሌላ የሀሳብ ጫና የሚያድርባት ከሆነ ሁኔታው አስቸጋሪ ይሆናል። እኔ በተለይም የመጀመሪያ ልጄን በወለድኩበት ጊዜ ልገልጸው የማልችለው የጭንቀትና የድብርት ስሜት ነበረኝ። በሆነው ባልሆነው ነገር እበሳጭ ነበር። ሆድ ይብሰኝ ነበር። የዚህ ምክንያት ደግሞ ባለቤቴ ስለእኔ እርጉዝ መሆን ምንም ግድ የማይሰጠው እና ከእራሱ ፕሮግራም ውጭ ስለእኔም ሆነ ስለሚመጣው ልጅ ምንም የማይጨነቅ መሆኑ ነበር።
በእርግጥ ጠዋት ይወጣል ማታ ይገባል። ነገር ግን በትክክለኛው መንገድ ባለቤ ልጅ ወለደችልኝ ብሎ እንክብካቤ አላደረገልኝም። በቅርቤ አልተገኘም። ስለዚህ አብረውኝ ያሉት ሰዎች ሁሉ ምንም ቢያደርጉልኝ ልወዳቸው አልቻልኩም። ያስጠሉኛል። ልክ እሱ ሲመጣ የነበረኝ ጭንቀት ሁሉ ይለቀኛል። ነገር ግን እቤቱ ከገባም በሁዋላ ወደእኔ ቀረብ ብሎ ማጽናናት ወይንም የደስታዬ ተካፋይ የመሆን ነገር... ልጁን ታቅፎ የማየት ሁኔታ ስላልነበረው ተመልሼ በጣም አዝን ነበር።ይህንን ነገር ለቤተሰቤ ፊት ለፊት ስላልተናገርኩኝ እናን ጨምሮ እህቶቼ መላው ቤተሰቡ ስለእኔ አልተጨነቀም ነበር። ለእኔ አጥሚት መስራት ገንፎ ማቅረብ በስተቀር ምን ያስፈልግሻል? ምን ሆነሻል? የሚያስደስትሽ ነገር ምንድነው? የሚለውን ነገር እነሱም አልጠየቁኝም። ምክንያቱም ስለዚህ ነገር ምንም የሚያውቁት ነገር የለም። እኔም እራሴ ከባለቤጋር በተያያዘ ያለውን ነገር በሙሉ እጅግ አድርጌ ከመጥላት በስተቀር ለማንም ምንም መናገር አልቻልኩም። ምክንያቱም የደረሰብኝን ነገር ስላላወቅሁት ነው።
ሁለተኛውን ልጄን ስወልድ ግን በተቻለ መጠን ቀደም ባለው ጊዜ የደረሰብኝ ነገር እንዳይደርስብኝ ተጠንቅቄ ነበር። የሚያስደስቱኝን ነገሮች ከባለቤም ሆነ ከቤተሰቤ ሳልጠብቅ በእራሴ ለመወጣት በደንብ አድርጌ ነበር የተዘጋጀሁት። የኢኮኖሚ ችግር እንዳይገጥመኝ እቁብ ሰብስቤ ገንዘብ ያዝኩ። የምመገባቸውን ነገርች አስቀድሜ አዘጋጀሁ። ቤን ቀለም አስቀባሁ። የአልጋ ልብሶቼን ፒጃማዎቼን ሁሉ አስቀድሜ አዘጋጀሁ። ምክንያቱም ይህንን ሁሉ ስጠይቀው ባለቤ ምንድነው ብትወልጂ... በፊት በነበረው አትጠቀሚም? የምን ወጪ ማብዛት ነው እያለ እሱ ግን አንድ ቀን እንኩዋን ሳያቋርጥ እየጠጣና እየሰከረ ጭምር ይመጣ ስለነበር ያንን ጊዜ በፍጹም አልረሳውም። ድብርቱን በሐኪም ብርታት ተላቅቄአለሁ። ቂሙን ግን አልተላቀቅሁም። ስለዚህ ከዚህ በሁዋላ አልደግመውም በማለት እራሴ በራሴ ሁሉን ነገር አዘጋጅቼ ልጄን ወለድኩ።
ቤተሰቤ እንደእንግዳ ተስተናግዶ እንዲሄድ እንጂ ከጉዋዳዬ እንዲገቡ አልፈቀድሁም። ምክንያቱም በመጀመሪያው ስወልድ በሌለ ኢኮኖሚ እነእሱም ከቁጥር በላይ ሆነው እየተሰበሰቡ ባዶዬን ነበር ያስቀሩኝ። ስለዚህ ከእና በስተቀር የቀሩት እየመጡ እንዲሄዱ እንጂ ሌላ ኃላፊነት ውስጥ እንዲገቡ አልፈቀድሁም። ይህንን ደግሞ ለእናም ፊት ለፊት ነግሬአት እሱዋም ተስማምታ በፍቅር እና በክብር ቁጭ ብላ አረሰችኝ። ባለቤም... አ... ሀ... አሁን አድገሻል... ጭቅጭቅም አቁመሻል... ሲለኝ የፌዝ ሳቅ እየሳቅሁ ተወጣሁት። ስለዚህ ሴቶቹን እምመክረው በመጀመሪያ ሲያረግዙ ጀምሮ ይህ ድብርት የሚባለው በተለያየ ምክንያት ሊከሰት እንደሚችል ነው። ከሆነ ደግሞ ወደሐኪም መሔድ ነው። ከዚህ ውጭ ግን ሁሉም ቢቻል ተግባብቶ... ካልተቻለ ደግሞ ረጋ ባለ መንፈስ አስፈላጊ ለሆነው ነገር ሁሉ ቅድመ ዝግጅት ቢያደርጉ ከችግሩ አስቀድመው እራሳቸውን ያላቅቃሉ። ከዚህ በተጨማሪ ግን ትልቁን ምክር መስጠት የምፈልገው ለባሎች ነው። ከእኔ ጉዳይ ስነሳ ባሎች አባቶች ሚስቶቻቸው ሲወልዱ ትልቁን ሚና ሊጫወቱ ይገባል።
ባሎች... ሚስቶቻቸው ሲወልዱ ጊዜ ሰጥተው እቤት ውስጥ በመገኘት... ባለቤቱ በመውለዱዋ አመስግኖ... ሸልሞ... ወዘተ... እናትየውን የሚያስደስት ነገር ማድረግ ይጠበቅበታል። እናትየው ልጅ በመውለድዋ ምክንያት ባልዋ የሰጠውን ክብደት በማየት... ለእርስዋ ያለውን ፍቅር የምታረጋግጥበት ወቅት በመሆኑ ከወለደች በሁዋላ ለሚፈጠረው የመንፈስ ጭንቀት አትጋለጥም። ስለዚህ ሚስት በምትወልድበት ጊዜ ባልየው በተቻለ መጠን በቅርብዋ መገኘት... ምን በላች... ምን ጠጣች... እስከሚለው ድረስ ቢንከባከባት... ሚስት በጣም ስለምትደሰት ለአእምሮ ጭንቀት ወይንም ድብርት አትጋለጥም ብዬ አስባለሁ። በእኔ ላይ የደረሰው ከመውለድ በሁዋላ የአእምሮ ጭንቀት ምክንያቱ ባለቤ ለእኔ ተገቢውን ድጋፍ አለማድረጉ ነው ብዬ አምናለሁ።”
 በእምነት ሲሳይ ከፒያሳ
ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰተው ድብርት መገለጫዎቹ ብዙ ነገሮች ናቸው።
አንዳንድ እናቶች በወሊድ ወቅት በሰውነታቸው ላይ ለውጥ ያያሉ። ለምሳሌም በሰውነት ውስጥ ያለው የሆርሞን መጠን ሲቀንስ ወይንም የደም መጠን ማነስ ወይንም ግፊት መጨመርና የመሳሰሉት ነገሮች ለድካምና ለጸባይ መለዋወጥ ሊዳርጋቸው ይችላል። ይህ ባለበት ሁኔታ እናቶች በአካባቢያቸው ያሉ ሰዎች እንክብካቤና ድጋፍ ሲቀንስ ደግሞ ጉዳቱን ያባብሰዋል።
ሴቶች ብዙውን ጊዜ ማለትም በእርግዝና ጊዜ እንኩዋን ሳይቀር ስለውበታቸው ይጨነቃሉ። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ከወሊድ በሁዋላ እራስን ዞር ብሎ ማየት የሚያቅትበት ሁኔታ ይስተዋላል። ይህ ሲሆን ጤናማ ስላልሆነ አብሮ ያለ ሰው ምንድነው ምክንያቱ ብሎ መጨነቅ ይጠበቅበታል። ምክንያቱም ወላድዋ ስለመልክና ቁመናዋ መጨነቅ ካቆመችና ምንም ስሜት የማይሰጣት ከሆነ በህይወትዋም ላይ መወሰን አለመቻልዋን እንዲሁም ስጋት የመሳሰሉት ነገሮች እየጎሉ መምጣታቸውን ያሳያል ። ይህ መሆኑ ደግሞ ጭንቀትን የሚያባብስ ነው።
በቤት ውስጥ ስራን ለመስራት ድጋፍ የሚያደርግ ሰው አለመኖር ፣የኑሮ አጋርን ድጋፍ ማጣት ባል፣ በባህርይው አስቸጋሪ የሆነ ቀደም ብሎ የተወለደ ልጅ በቤት ውስጥ ካለና ካለእናቱ የሚዳኘው ሲጠፋ... በወላድዋ ላይ ጭንቀት ብስጭት እንዲሁም ድብርት ያስከትላል ።
አንድ ቤተሰብ ልጅ ለመውለድ ሲያስብ አስቀድሞ ስለኢኮኖሚው ጥያቄ ማንሳት ትክክለኛ እና ተገቢ ነው። የኢኮኖሚው ጉዳይ ሊያሳስብ የሚገባው እናትየው በምትወልድበት ጊዜ እሱዋን ጨምሮ ስለሚኖረው መስተንግዶ እና ከዚያም በሁዋላ ልጁ በምን እንደሚያድግ አስቀድሞ መጨነቅ ተገቢ በመሆኑ ነው። ይህ ጥያቄ መልስ የማያገኝ ከሆነ ባለው ሁኔታ እንዴት መኖር እንደሚቻል አስቀድሞ እቅድ ሊኖር ይገባል። ይህ ሳይሆን ከቀረነገሮች ሳይሙዋሉ ስለሚቀሩ እናትየው መበሳጨት እና መጨነቅዋ ወይንም መደበርዋ ግድ ነው።
ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ አንዲት እናት የደረሰባትን እንደሚከተለው አካፍላናለች።
 “እኔ ከመውለዴ በፊት ከባለቤ ጋር ብዙ ተነጋገርን። እባክህን ገንዘብ ሳይኖረን ሁለተኛ ልጅ ምን ያደርግልናል? ብዬ ስጠይቀው... ተይው... በቃ ይወለድ... የሚገጥመንን ምን ታውቂያለሽ? አለኝ። እኔም እየፈራሁ በጣም እያሰብኩ እንደምንም የእርግዝና ጊዜዬ አለቀ። ከዚያም ልክ ወልጄ ገና ከሆስፒታል ሳልወጣ ባለቤ ከመስሪያ ቤቱ በፖሊስ ተይዞ በሕግ ቁጥጥር ስር ዋለ። ምን አድርጎ ነው? ሲባል የመስሪያ ቤቱ አሽከርካሪ ስለነበር ከአሁን ቀደም በሄደበት የመስክ ስራ ሕገ ወጥ ሰዎችን ከነንብረታቸው በመኪናው ላይ ጭኖ ገንዘብ ሲሰራ በመገኘቱ ተከሶ ስለ ነበር በዋስ ተለቆ ሲከራከር ቆይቶ ውሳኔ የተሰጠበት ወቅት ነው።እኔ ደግሞ ይህንን ሁሉ ታሪክ አላውቅም። በሁዋላ ግን መለስ ብዬ ሳስበው እርግዝናው 7/ወር ካለፈው በሁዋላ ይህ ጽንስ ሊቋረጥ አይችልም? ብሎ ጠይቆኝ ከፍተኛ ጸብ መፈጠሩን አስታወስኩ። በጊዜው ለእኔ ሕይወት ምንም ግድ የለህም... አንተ ብትከለክለኝ እንኩዋን ለምኜም ቢሆን አሳድጋለሁ እንጂ አሁንማ ምንም አይደረግም ብዬዋለሁ። ወልጄ ስወጣ ባልተቤ እስር ቤት ነበር። የሶስት ወር እስራትና የተወሰነ ገንዘብ ቅጣት ተጥሎበት ነበር። በቃ... ትልቅ ችግር ውስጥ ነበር የወደቅሁት። ለሊት ተነስቼ ብጮህ ደስ ይለኛል። ሰው ማየት አስጠላኝ። የሽንት ጨርቅ ነጠላ መቅደድ ሆነ። የሚበላው በሰው በዘመድ ትብብር ሆነ። ከዚያ ወደ አንድ ወር ገደማ ሲሆነኝ ተመልሼ ሆስፒታል ነበር የገባሁት። በጣም ታመምኩ። ሐኪሞቹ ግን ድብርት ነው አሉኝ። አክመው አዳኑኝ። በጣም ብዙ ምክር ተሰጠኝ። እንዲህ እንዲህ እያልኩ ስቸገር ስሰቃይ እሱም የእስር ጊዜውን ጨርሶ ወጣ። ቀኑም አለፈ። አሁን ደህና ነን። ነገር ግን ሰው በሕይወቱ የሚመጣውን ለውጥ አስቀድሞ ቢገምት እና ቢጠነቀቅ መልካም ነው እላለሁ።”
 ሃና ተስፋዬ /ከአቧሬ
ቀጥሎ የተጠቀሱት ነጥቦች አንባቢ ልብ ሊላቸው የሚገቡ ናቸው። ከወሊድ በሁዋላ፡-
... የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ እንቅልፍ ማጣት ፣ጥልቅ የሆነ ብስጭት፣ የፍቅር ግንኙነት መቀነስ ፣የደስተኝነት መጠን መቀነስ ፣በጣም ከፍተኛ የሆነ የድካም ስሜት፣ የእፍረት ስሜት ፣የጥፋተኝነት ስሜት መጨመር፣ የፀባይ መለዋወጥ፣ ከልጅ ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠር አለመቻል፣ እንዲሁም በእራስ ወይንም በተወለደው ልጅ ላይ ጉዳት ለማድረስ መሞከር... ወዘተ የሚታይ ከሆነ ያቺ እናት ድብርት (Postpartum Depression ) ይዟታል ማለት ነው።
ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚታየው ድብርት (Postpartum Depression ) ምክንያቱ
እርግዝናውና ጽንሱ የተፈለገ መሆን ያለመሆን ፣
ከትዳር ጉዋደኛ ጋር ያለው ግንኙነት ፣
ከሴት አማት ጋር ያለው ግንኙነት ፣
የገቢ መጠን ማነስ... ረሀብ፣
በወሊድ ጊዜ የሚጠብቁት ነገር ሳይሳካ ሲቀር፣
ድጋፍ ማጣት እና ስሜትን የሚጎዱ ችግሮች የደረሱባቸው ሴቶች ላይ በአብዛኛው ይታያል። ከዚህ በተጨማሪም... አንዲት ሴት ከወለደች በሁዋላ፡-
ጥሩ ስሜት የማይሰማት ከሆነ፣
ለነገሮች ትኩረት ማጣትና ማሰብን ማቋረጥ፣
ልጅዋን በትክክል መንከባከብ ካቃታት፣
ለእራስዋ ተገቢውን ለማድረግና በየእለቱ ልትወጣው የሚገባትን ግዴታ መወጣት ሲያቅታት፣
ልጅዋን የመጉዳት ስሜት ሲፈጠርባት... ወዘተ
ድብርት (Postpartum Depression) ይዟት ሊሆን ስለሚችል በአስቸኩዋይ ወደሐኪም ቤት
መሔድ ይጠበቅባታል።

  በፊልም ዳይሬክተር ዮናስ ብርሃነ መዋ በየዓመቱ የሚካሄደው የጉማ ፊልም ሽልማት አራተኛው ዙር ሚያዚያ 23 ቀን 2009 ዓ.ም በብሄራዊ ቴአትር አዳራሽ ይካሄዳል፡፡ በዘንድሮው ሽልማት 73 ያህል ፊልሞች ተመዝግበው የነበረ ሲሆን 18ቱ ብቻ መስፈርቱን አሟልተው በዳኞች እንዲዳኙ መደረጉ ተገልጿል። ከ“በደሌ ስፔሻል” የህዝብ ምርጫ በስተቀር ሌሎቹ 17 ፊልሞች በ16 ምድቦች መወዳደራቸውን የሽልማቱ ዋና አዘጋጅ ዮናስ ብርሃነ መዋ ከትንት በስቲያ በብሄራዊ ቴአትር አዳራሽ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
   በዘንድሮው ሽልማት ላይ የተለመደው የቀይ ምንጣፍ ስነ ስርዓት ወደ ሰማያዊ ምንጣፍ መቀየሩን የገለፀው ዋና አዘጋጁ፤ አንድም ከውጭው ዓለም ተለይቶ የራሱን ቀለም እንዲይዝ ከህዝብ በቀረበው ጥያቄ መሰረት መቀየሩንና ላለፉት ሶስት ዓመታትም ሆነ ዘንድሮ በደሌ ቢራ፣ ለዚህ ፕሮግራም የክብር ስፖንሰር ሆኖ በመቀጠሉ ቀለሙን ከስፖንሰሩ ጋር ለማመሳሰል እንደሆነም በእለቱ ተገልጿል፡፡ በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ ሴቶች በተለይ የባህል አልባሳት ወንዶች ሙሉ ልብስ ጨርቅ ሱሪና መሰል የፕሮቶኮል ልብሶችን እንዲለብሱ የሚጠበቅ ሲሆን ጂንስ ሱሪ፣ ካኪ ሸሚዝና ሱሪ፣ ሸራ ጫማና መሰል ልብሶችን ለብሶ መታደም እንደማይቻል ተገልጿል፡፡

   ኢንሼቲቭ አፍሪካ በየዓመቱ የሚያዘጋጀውና ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ የሚካሄደው አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል፤ ሚያዚያ 20 ቀን 2009 ዓ.ም በጣሊያን የባህል ማዕከል ይከፈታል፡፡ እስከ ሚያዚያ 25 በሚቆየው በዚህ ፌስቲቫል ላይ በተለይ በስደት፣ በወጣቶች የስነ ተዋልዶ ጤና፣ በአካባቢያዊ ደህንነት፣ በአየር ንብረት ለውጥና በመሰል ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው የተሰሩ የአገር ውስጥና የውጭ ፊልሞች ለእይታ እንደሚቀርቡም ታውቋል፡፡
ከፊልሙም ባሻገር ከተለያዩ አለማት ተጋብዘው የሚመጡ እውቅ የፊልም ዳይሬክተሮች፣ አክተሮችና ፕሮዲዩሰሮች ለመገናኛ ብዙሀን፣ ለፊልም ሰሪዎች፣ ለፕሮዱዩሰሮችና ለተዋናዮች ሥልጠና ይሰጣሉ የተባለ ሲሆን አገራዊ አጀንዳዎች ተዘጋጅተው ትልልቅ የውይይት ጉባኤ እንደሚካሄድም ታውቋል፡፡ እነዚህ የተመረጡ ፊልሞች ከጣሊያን የባህል ማዕከል በተጨማሪ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤትም ለእይታ እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡
አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል፤ በየአመቱ ከ600 በላይ ፊልሞችን በማሰባሰብ የተመረጡ 60 ፊልሞችን ለእይታ ሲያበቃ መቆየቱን አስታውሶ፤ ባለፉት አመታት ከ400 በላይ ፊልሞችን ለእይታ ማብቃቱን ጠቁሟል፡፡

Page 1 of 330