Administrator

Administrator

Monday, 29 July 2019 00:00

የአድማስ ትውስታ

ከአዘጋጁ፡-

        ጋዜጣችን አዲስ አድማስ የተመሰረተችበትን 20ኛ ዓመት ከጥቂት ወራት በኋላ ታከብራለች:: የመጀመሪያው የአዲስ አድማስ ዕትም፣ ቅዳሜ
ታህሳስ 29 ቀን 1992 ዓ.ም ነበር ለአንባብያን የደረሰው፡፡ ወደ 20ኛው ዓመት በዓላችን በሚያዳርሱን ጥቂት ወራት “የአድማስ ትውስታ” በሚል በሰየምነው በዚህ አዲስ ዓምድ፤ ከቀድሞ ዕትሞች እየመረጥን ጊዜውንና ጋዜጣችንን እናስታውሳችኋለን፡፡

                    የዲሞክራሲ እጥረት ወይስ ጥሰት? (ለዜጐቻችን ህይወት ቅድምያ እንስጥ!)
                            አልአዛር ኬ

          በፖለቲካ ሆነ በኢኮኖሚ ጉዳዮች የተነሳ ብጥብጥ ተከስቶ የሰዎች ህይወት ሊጠፋ ስለብጥብጡ መንስኤና ስለ ሰዎቹ ህይወት መጥፋት ሳይሆን ህይወታቸው ስለጠፋው ሰዎች ቁጥር በፓርላማዋ ክርክር የምትገጥም እንደ ኢትዮጵያ ያለች ሀገር በአለም ለመኖርዋ እጠራጠራለሁ፡፡ ይህ አባዜአችን መቼ እንደሚለቀን አይታወቅም፡፡
ያለፈውን ብሔራዊ ምርጫ ተከትሎ በገጠመን የፖለቲካ ቀውስ በርካታ ዜጐች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ መንግስት የሞቱት ዜጐች ቁጥር በአስሮች የሚቆጠር ነው ሲል ተቃዋሚዎች ደግሞ የለም በመቶዎች የሚቆጠሩ ናቸው በሚል በፓርላማ ክርክር ተደርጐበት ነበር፡፡ በኋላ ላይ አጣሪ ኮሚሽን ተቋቁሞ የራሱን ማጣራት አድርጐ ሟቾቹ 193 ሲቪሎችና 6 ፖሊሶች ናቸው ብሎ ሪፖርቱን ሲያቀርብ መንግስት በፊት የገለፀው ቁጥር በአጣሪ ኮሚሽኑ ሪፖርት ባለመደገሙ ቅር ሲለው ተቃዋሚዎች ደግሞ እኛ ያልነው ቁጥር ልክ ቢሆንም ባይሆንም መንግስት የጠቀሰው ቁጥር ብቻ እንኳን ልክ አልሆነም በሚል የትክክለኝነት ስሜት ተሞልተው አይተናቸዋል፡፡ የሰው ህይወት ክብር በሌለበት፣ የዜጐች ደህንነት ሁለተኛ አጀንዳቸው በሆነበት ሀገር እንዲህ አይነቱ ክርክር በፓርላማ መካሄዱ ብዙም አያስገርምም፡፡
ነገር ግን በከፍተኛ የሀላፊነት ስሜት በፖለቲካ ጉዳይ የተነሳ ዜጐች የማይሞቱበትና አካላቸውን የማያጐድሉበት ስርአት እንዴት አድርገን እንገንባ በሚል አንድም አይነት ውይይት ለማድረግ አለመፈለግ ግን የሀገራችን ትልቁ እርግማን ነው፡፡
የሞቱብንን የቀብርን፣ እንዴትና በምን ሁኔታ እንደሞቱብንም የምናውቅ እኛ፤ የቆሰሉብንን ያስታመምንና በምንና እንዴት ሆነው እንደቆሰሉብንም የምናውቀው እኛ፤ የቆሰሉብንን ያስታመምንና በምንና እንዴት ሆነው እንደቆሰሉብንም የምናውቀው እኛው ሆነን፤ አንድ ኮሚቴ አጣራሁ ብሎ ብሎ ቢነግረን የምንመዝነው እቤታችን ጓዳ ካለው እውነተኛ የራሳችን ሪፖርት ጋር ነው፡፡
ባለፈው በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረገው የፓርላማ ውይይት ግርምቱ ሳይጠፋብን አሁን በቅርቡ በዚሁ ተመሳሳይ ጉዳይ ላይ በፓርላማ የተካሄደው ውይይት ሌላ አስገራሚ ነገሮች ነበሩት፡፡
በአጣሪ ኮሚሽኑ ሪፖርት ላይ የፓርላማው የህግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበው የውሳኔ ሀሳብ፣ በሁከቱ ወቅት የተከሰተው የሰብአዊ መብት አያያዝ እጥረት ላይ መንግስት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ፣ በቀጣይም ትምህርት ተወስዶበት ጥንቃቄ እንዲደረግ የሚያሳስብ ነው:: የደረገው ውይይት ግን ከላይ የተጠቀሰው ሃሳብ በተግባር እንደማይውል ያረጋገጠ፤ በፖለቲካ አያያዛችን ወደፊት በተአምርም ቢሆን መራመድ እንደማንችል ያሳየ ነበር፡፡
በውሳኔ ሀሳቡ ላይ የተደነገገው የዲሞክራሲ እጥረት፣ የዲሞክራሲ ጥሰት በሚለው ቃል ይተካልን በሚል በተቃዋሚዎች የቀረበው ሃሳብ ውሳኔው መንግስትን አጥፊ ነው ብሎ ስላልጠቀሰ የዲሞክራሲ ጥሰት ተፈጽሟል ቢባል በዘወርዋሬ መንግስትን ያመለክታል ከሚል ሃሳብ የመነጨ ይመስለኛል:: የዲሞክራሲ ጥሰት ሆነ እጥረት ተከስቷል ተብሎ በፈለገው አይነት አገላለጽ ቢፃፍ የሞቱትና የቆሰሉት ወገኖቻችን በእንዴት ያለ ሁኔታ እንደሞቱና እንደቆሰሉ እኛው ዋነኛ ባለቤቶቹ ጠንቅቀን ስለምናውቅ የቃላት አተካራው ጠብ የሚል ነገር የለውም፡፡
ነገር ግን ከኢህአዴግ ወገን የቀረበው ሙግት ከምንሠራው ስህተት መቸም ቢሆን ትምህርት ለመቅሰም ዝግጁነት እንደሌለን የሚያሳይ ነው:: አንድ የኢህአዴግ ተወካይ የተከበሩ የፓርላማ አባል፤ ነገሩን ያስረዱት፡፡ “እጥረት በባህሪው ጉድለት እንዳለ ያሳያል፤ የተሟላ ነገር የለም የሚል ነው፡፡ ጥሰት የሚለው ቃል ተመጣጣኝ አይደለም፤ ገደብ አልፏል በሚል ይቀመጥልኝ ተብሎ በሌላ መልኩ የቀረበ ስለሆነ እጥረት በሚለው ይቀመጥ እንላለን” በሚል ነው፡፡ እኒህ ተወካይ ያው የድርጅታቸው ነገር ሆኖባቸው የተናገሩት እንጂ የህዝቡን ስሜት ለመረዳት ሞክረው አሊያም በቀናነት ገምተውት ቢሆን ኖሮ ከዚህ የተሻለ ነገር ሊያቀርቡ ወይም ያቀረቡትን ከማቅረብ ይቆጠቡ ነበር ብዬ አስባለሁ:: መንግስት የዲሞክራሲ እጥረት አለብኝ ማለቱ እኔ የምፈልገውን ያህል ዲሞክራሲን አላሰፈንኩም እንጂ የቻልኩትን እየሰራሁ ነው፤ ለማለት እንደሆነ ይሁንለት እንበል፡፡ ነገር ግን 193 ዜጐች ህይወታቸውን ያጡት በምን ዓይነት ችግር እንደሆነ እኛ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ ዲሞክራሲ ያጥራቸዋል ሳይሆን በግልጽ ይጥሳሉ እየተባሉ በየጊዜው የሚወገዙት ሀገሮች በፖለቲካዊ ብጥብጥ 193 ዜጐቻቸው የማይሞቱባቸው እነሱ ከመላእክት ጋር እየሰሩ ይሆን?
በዲሞክራሲና በሰብአዊ መብት አያያዛቸው ለዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ደፍሮ የሚከራከርላቸው ሰው መቼም ብዙ እንደማይገኝ የታወቀ ነው፡፡ ታዲያ በመቶ የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎቻቸውን የማይገድሉት ስለ ሰማይ ቤቱ ህይወታቸው ስለሚያስቡ ይሆን? ግብፅ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኡጋንዳ ወዘተ…መሪዎቻቸው በስልጣናቸውን በተቃውሞ ቀልድ አያውቁም፡፡ ግን በመቶ የሚቆጠሩ ዜጐቻቸውን ሲፈጁ አይታዩም፡፡ ሞትና ፍጅት እኛ ሀገር ቀልድ የሆነበት ምክንያት ግን በእጅጉ ያስገርማል፡፡
መንግስት በጊዜው የተከሰተውን ችግር ለመፍታት በወሰደው እርምጀ የ193 ዜጐች እልቂት ተከስቷል፡፡ ይህ እርምጃ ገደብ ያለፈ እርምጃ ነው:: ተብሎ በመንግስት በኩል እንዲታመን መሞትና መቁሰል የነበረባቸው ዜጐች ስንት ሺ መሙላት ነበረበት፡፡ ነገሩ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ያ ሁኔታ መንግስት እንደተመኘውና እንዳደረገው ተመጣጣኝ ነው ተብሎ መወሰኑ ለኢህአዴግ የልቡን አድርሶለት ይሆናል፡፡ የህዝቡን ስሜትና ልብ ግን ከቶም አያሽርለትም፡፡
የእውነተኛው ሪፖርት ባለቤት የሆነውን ህዝብ ለቀባሪው አረዱት እንደተባለው ተመጣጣኝ ነው አይደለም፤ አጥሯል የለም ተጥሷል በሚል ለማሳመን እንዲያው ደከመ እንጂ ዋነኛው ትኩረቱ ሊሆን የሚገባው ከዚህ ስህተት ምን ተምሬአለሁ፤ ወደ ፊትስ እንዴት መራመድ አለብኝ የሚሉትን ጉዳዮች ነበር፡፡
ኢህአዴግ የዲሞክራሲ ጥሰት አልፈፀምኩም፤ የዲሞክራሲ እጥረት እንጂ በማለት በተወካዮቹ አማካሯነት መከራከሩ “ሞኝ በሞኝነት ሃሳቡ ለራሱ ይራቀቃል” የሚለውን የአይሁዶች አባባል ያስታውሳል፡፡
ጥሰት ፈጽመሀል አለመባል ከተጠያቂነት ነፃ ያደርገው ከመሰለው ላመነበት የዲሞክራሲ እጥረትና ዲሞክራሲ ላጠረበት ህዝብ የሚከሰው በምንድን ነው? ለዚህስ አልጠየቅም ሊል ይሆን? ለበርካታ አመታት ዲሞክራሲን ካላሰፈንን ወይም የዲሞክራሲ ግንባታችንን ካላሟላን እንደሀገር የመቀጠላችን ጉዳይ አጠያያቂ ነው፤ ዲሞክራሲ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳያችን ነው ብሎ ኢህአዴግ አስረግጦ ሲያስረዳን ኖሮአል፡፡ ታዲያ አሁን የዲሞክራሲ እጥረት ተከስቶብኛል ማለቱ በራሱ ማስጠንቀቂያ መሠረት የሀገሪቱን ህልውና ወደየት እየወሰደ ነው?
የኢህአዴግ አጋር ድርጅት አባል የሆኑ አንድ የተከበሩ የፓርላማ አባል፤ “መቻቻል፣ ዲሞክራሲን ማስፋትና ካለፈው ስህተት መማር ይጠቅማል”  ብለዋል፡፡
እኒህ የተከበሩ ሰው ስለ ኢህአዴግና ስለተቃዋሚ ፓርቲዎች ያላቸውን ግልጽ አቋም በደንብ ስለምናውቅ እንዲህ ያለ ሃሳብ መሰንዘራቸው አሪፍ ነገር ነው፡፡
በእርግጥም መቻቻልና ዲሞክራሲን ማስፋት፣ ካለፈ ስህተትም መማር ለሀገርና ለህዝብ የሚበጅ ነገር ነው፡፡
እነዚህን ቅዱስ ሀሳቦች በተግባር ለመተርጐም ደግሞ አጥፊ ጥፋቱን አምኖ ይቅርታ ቢጠይቅ፣ የበደለውን ቢክስ ከባላንጣው ጋር እርቅ ቢያደርግ ተገቢ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ቢያደርግ በእነዚህ አይነት አሰራሮች ዘመን ባጠገበችው ሀገራችን ይበልጥ ያተርፋል፡፡
ይህን ሃሳብ ኢህአዴግ በአባሉና በተወካዩ የተከበሩ የፓርላማ አባል በኩል የመለሰው “አገርን ከባለ ብጥብጥና አደጋ ለመታደግ ስለሆነ የተወሰነው እርምጃ ተመጣጣኝ ነው ብሎ ባስቀመጠበት ሁኔታ፤ አጥፍታችኋልና ይቅርታ ጠይቁ፤ ጐድታችሁአልና ካሳ ክፈሉ የሚል ነገር ማስቀመጥ ተገቢነት ያለው አይመስለኝም” በሚል ነው፡፡ እኒህ ሰው እንደ ኢህአዴግ አባልነታቸው ሳይሆን እንዲያው በሰውነታቸው ብቻ አስበው መልስ የሚሰጡ ቢሆን የ193 ሲቪል ዜጐችን መገደል ምን ይሉት ይሆን?
እንደ ኢህአዴግ የእርቅ፤ የይቅርታና የካሳን ጉዳይ ፈጽሞ ሊቀበል የማይችልባቸው ሁለት መሠረታዊ ባህሪዎች እንዳሉት ይሰማኛል፡፡ አንደኛው፡- እንዲህ ማድረግ ለጠላቶች መንበርከክና መሸነፍ ነው ብሎ ከህዝብ አንፃር ሳይሆን ከፓርቲ አንፃር ብቻ ከማየት ባህሪው ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ጠላቶች ብቻ እንጂ እኔ ስህተት ፈፃሚና አጥፊ አይደለሁም፤ ከሚለው አስተሳሰቡ ነው፡፡ ድሮ ንጉሱ እኔ ከዙፋኔ ከወረድኩ ኢትዮጵያ ያልቅላታል ይሉ ነበር እንደሚባለው፤ እኔ ካልመራሁዋት ይህቺ አገር የምጽአት ቀኗ ነገ ይሆናል ብሎ ከሚያስብ ድርጅት፤ እንዲህ ያለ አቋም መንፀባረቁ ብዙም አስገራሚ ነገር አይደም፡1 እንደ ሀገር መሪ ድርጅት ኢህአዴግ፤ ለኛም ለራሱም ሲል ከስህተት መማሩን ሊያሳየንና ከህዝብ ጋር እልህ መጋባቱን ማቆም ይገባዋል፡፡ አስራሁለተኛው ሰአት ሲመጣና ጊዜ ሲመሽ የሁሉም ማረፊያ ያው ህዝቡ ነው፡፡ ያኔ እንዲህ ያልኩት እንዲህ ያደረኩት ተገድጄ ነው፤ ተሳስቼ ነው ብዙም አያዋጣም፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ቢሆኑ የኢህአዴግ ስህተትና የኢህአዴግ ድክመት በምንም ነገር ቢሆን እነሱን የተሻሉና እንከን አልባ እንደማያደርጋቸው ጠንቅቀው ሊያውቁት ይገባል፡፡ ለሁሉም ችግሮች ኢህአዴግን ብቻ መርገም ኢህአዴግን ብቻ ማውገዝ ለህዝብ ጥቅም አያመጣም፡፡
ህዝብና ታሪክ ሁሉን እንደ የእጅ ስራው ብቻ ነው የሚመዝነው፡፡ የመንግስት ስልጣን አለመጨበጥ ከጥፋት ነፃ አያደርግም፡፡ በድጋፍ አብሮ ተሰልፎ ህይወቱን ለሰጠ ህዝብ፤ ካሳው ህብረት፣ አንድነትና የተሻለ ስራን እንጂ ለግል ስልጣን ያለ እረፍትና እፍረት መሿኮት ከቶም መሆን የለበትም፡፡
ለማጠቃለል በሀገራችን ፓርላማ፣ ዜጐች በፖለቲካ የተነሳ የማይሞቱበትና የማይቆስሉበት ስርአት እንዴት በህብረት እንገንባ በሚል ጉዳይ ላይ ውይይት ሲደረግ ማየት እናፍቃለሁ፡፡ ለትንሽ ለትልቁ ጉዳይ ይዋጣልን እያልን ጦርና ዘገር ሰባቂ ጀግኖች ሆነን ያተረፍነው ነገር ቢኖር የዜጐች ህልፈትን ብቻ ነው፡፡ አምላክ ይርዳን!!   

 የእውቁ ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ ይርጋ አበበ አለባቸው ‹‹ኢካቦድ፣ የተዛቡ አገራዊ ትርክቶችና ፍሬያቸው›› መጽሐፍ ከትላንት በስቲያ ሀሙስ ጀምሮ ገበያ ላይ ዋለ፡፡ መጽሐፉ በዋናነት ታላላቅ የፖለቲካ ወጎችን፣ ማህበራዊ ጉዳዮችን፣ የልጅነት ጊዜን፣ እንዲሁም ዋዛና ቁም ነገር የያዙ ነገር ግን አስተማሪ የሆኑ ትርክቶችን የያዘ ዘርፈ ብዙ ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡
አሁን በሕይወት በሌለችው ሰንደቅ ጋዜጣ፣ በአሀዱ ሬዲዮና በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች በተለይም በፖለቲካ ትንታኔ ጽሑፎቹና በስፖርት ዝንባሌው የሚታወቀው ጋዜጠኛ ይርጋ አበበ ‹‹የዘመኑ ተመስገን ገብሬ›› የሚያሰኘውን ከእድሜውና ከኖረው በላይ አንብቦና አንሰላስሎ የጻፈውን መጽሐፍ እነሆ በረከት ስለማለቱ አንጋፋው ጋዜጠኛ እና አርታኢ ጥበቡ በለጠ በመጽሀፉ ጀርባ ባስቀመጠው ማስታወሻ አስፍሯል፡፡ በ187 ገፅ የተቀነበበው መጽሐፉ በ67 ብር ከ83 ሳንቲም ለገበያ የቀረበ ሲሆን ጃፋር መጻህፍት መደብር በዋናነት እያከፋፈለው ይገኛል::

በመላው ዓለም አነጋጋሪ ለነበረው ‹‹ብላክ ፓንተር›› ፊልም ማስታወሻ ለሚሆነውና ዋካንዳ አድቨር ታይዚንግ አለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ ለሚሰራው ቪዲዮ ክሊፕ ሥራ ኢትዮጵያዊው ቶማስ ሀይሉ (ቶሚ ፕላሳ) ተመረጠ፡፡ የ27 ዓመቱ ወጣት  የሙዚቃ ሰው ከ40 በላይ  የሙዚቃ ስራዎችን የሰራ ሲሆን ወደ 48 የሚጠጉ የብሄር ብሄረሰቦችን ጭፈራ አሳምሮ እንደሚጫወት ታውቋል፡፡
ቶማስ ሀይሉ (ቶሚ ፕላስ)  ረቡዕ ረፋድ ላይ በካሌብ ሆቴል ከጋምቤላው ወጣት አቀንቃኝ ኤዲኬንዞና ከሰለሞኒክ ኢንተርቴይመንት ጋራ በጋራ በሰጠው መግለጫ፣ ይህን እድል በማግኘቱ የተሰማውን ደስታ ገልጾ በተሰማራበት የሙያ ዘርፍ አገሩን እንደሚያስጠራ በጋዜጣዊ መግለጫው አስታውቋል፡፡ የአፍሮ ቢት ስልተ ምት አቀንቃኙ ወጣት የኢትዮጵያን ሙዚቃ በተለይም ውዝዋዜ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ዳንስና ሙዚቃ ጋር አስማምቶ ለመስራትና አገሩን ለማስተዋወቅ በሚያደርገው ጥረት ይበልጥ ይታወቃል፡፡


        ከዕለታት አንድ ቀን አባትና ልጅ፣ ቁጭ ብለው ወጥመዳቸው አልገባ ብሎ ስላስቸገራቸው ጅብ ይመካከራሉ፡፡ አባት መላ ያሉትን ለልጃቸው ይነግሩታል፡፡ (አንዳንድ ተረቶች ተመላላሽ ታካሚ በመሆናቸው ብዙ ዘመን ተሻግረውም ድንገት ዳግሞ ይከሰታሉ፡፡ የሚከተለው ተረት ይሄ ዕድል ከገጠማቸው መካከል አንዱ መሆኑ ነው፡፡
አባት - “ቆይ ልጄ መላ መላውን ልንገርህ?”
ልጅ - “አባዬ እሺ መላው ምንድን ነው?”
አባት - “ልነግርህ አይደል አትቸኩላ!”
ልጅ - “እሺ ዘዴውን ብቻ ንገረኝ”
አባት - “እንካ ይሄን ጠመንጃ”
ልጅ - “ምን ላረግበት?”
አባት - “አትቸኩላ ልጄ!”
እጠመንጃው አፈሙዝ ላይ ሙዳ ሥጋ ታሥርና የገመዱን ጫፍ ቃታው ላይ ታስረዋለህ፡፡ ጅቡ ሙዳውን ሲጐትተው ቃታውን በራሱ ላይ ይስበዋል፡፡ አለቀለት ማለት ነው፡፡”
ልጅ - “አባዬ ከባድ ብልሃት ነው ያስተማርከኝ፡፡ አሁኑኑ ሄጄ ገመዱንና ሙዳ ሥጋውን አዘጋጀዋለሁ” ብሎ ልጅየው ይሄዳል፡፡ እንደተባለው ጠመንጃው አፈሙዝ ላይ ሙዳውን አስሮ ውጤቱን መጠበቁን ቀጠለ፡፡ ከጥቂት ስዓታት በኋላ ልጅየው ወደ አባቱ ሲሮጥ መጣና፤
አባት - “ልጄ ምን ተፈጥሮ ነው ይሄ ሁሉ ሩጫ?”
ልጅ - “አባዬ ጉድ ሆነናል?”
አባት - “እንዴት? “ለምን?”
ልጁም - “ጅቡ፣ ጠመንጃውን በአፈሙዙ በኩል ሳይሆን ሰደፉን ነክሶ ይዞት ሮጦ!”
አባት - “አዬ ልጄ ጉድ ሆነናላ! እንኳን ጠመንጃ ሰጥተኸው እንዲሁም አልቻልነው! ዕዳ ከሜዳ ነው የገጠመን!”
***
ከቶውንም እንደ አተት (አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት) የሚመላለስብንን የአገራችን ችግር፣ “የተማረ ይግደለኝ” የተባለለት ምሁር፤ ደግ ምላሽ ቢሰጥበት ደግ ነው!
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን” የመጨረሻውን ቃል ለጀግናው ተውለት ይበሉን እንጂ ጀግናው ማን እንደሆነ ገና ለይተን አላወቅንም፡፡ አለማወቃችንን ደግሞ እንደ በረከት ልንወስደው አንችልም፡፡ ራሳችንን ቅዱስ ለማስመሰል እየሞከርን ካልሆነ በስተቀር፡፡
የዱሮ መምህራችን ፖለቲከኛው ሌኒን (One Step forward two steps back) - አንድ ደረጃ ወደፊት ሁለት ደረጃ ወደ ኋላ ብሎናል፡፡ የገባን ገብቶናል፡፡ ያልገባን ገና ይገባናል፡፡
አሁን ኢትዮጵያ አገራችን ከእንደዚያ ያለ ማጥ ውስጥ የተዘፈቀችበት ሁኔታ ያለ ይመስላል፡፡ እየቆየ ግን የምትድንበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
ሐምሌት ….
“…በምናውቀው ስንሰቃይ
የማናውቀውንም ፈርተን
በህሊናችን ማቅማማት
ወኔያችንንም ተሰልበን
ከዕለት ወደዕለት ስንሳብ ካባቶች በወረስነው ጋድ
የአዘወተርነውን ፍርጃ
እያስታመምን መለማመድ
መርጠን መሆኑ አይካድም
ያልታየ አገር አይናፍቅም
ቢያሰኝም አይታወቅም
የመንቀሳቀሳችን አቅሙ
እያደር ከህሊናችን ይደመሰሳል ትርጉሙ”
ኢትዮጵያ ለማደግ የሚያስፈልጋትን ኮታ ትሻለች እንጂ መፈናፈኛ እስኪጠፋት ድረስ የተጫነችን አገር አይደለችም፡፡ መንገዷን ታውቅ ዘንድ መንገድ የምናውቅ ሰዎች ቀና ቀናውን እናሳያት፡፡ ተማርን የምንባል እናስተምራት፡፡ የልጆቿን አዕምሮ እናበልጽግላት፡፡ ለተስፋ መቁረጥ ዕድል አንስጥ፡፡ መግቢያ መውጪያው ያምርልን ዘንድ ከገብረክርስቶስ ደስታ ጋር፤
“ደሞም ማወቅ ማለት
ከውጪ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ የበራውን እንዲወጣ ማድረግ”
በተለይ ወጣቱ ውስጥ የበራ ብርሃን ካለ፣ በብርሃን ፍጥነት መንገድ እንስጠው፡፡ ብርታታችን የሚለካው በዚህ ነው፡፡ ሀገራችን መላ ትፈልጋለች፡፡ ብዙ መዘዘኛ ችግሮች አሉባት፡፡ እንዴት እንፍታለት ማለት ያባት ነው፡፡ ልጆቿን ማስተማር ምርጡ መላ ነው፡፡ ልጆቿ ስለሌሎች መጨነቃቸው አይቀሬ ነውና፡፡
ይለወጣል ቀኑ
ይሻራል ዘመኑ
እናንተ ራቁና ወደኛ ብቻ ኑ!!

Saturday, 27 July 2019 12:13

መልክቶቻችሁ

 “ክልል ካልሆንን ሞተን እንገኛለን!”

         ሰሞኑን በኤልቲቪ፣ የወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄን አስመልክቶ ቃለ ምልልስ የተደረገላቸውን አንድ የዩኒቨርሲቲ መምህርና የህግ ባለሙያ የሰጡትን ማብራሪያ በጥሞና አደመጥኩኝ፡፡ በነገራችን ላይ ከአንድ ዓመት ወዲህ በደቡብ ክልል፣ በዘመቻና በፉክክር በሚመስል መልኩ የክልልነት ጥያቄ ማቅረብ የጀመሩ ዞኖች ተወካይ ነን ባዮች (ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች) ለምን ጥድፊያ ውስጥ እንደገቡ ግራ ግብት ይላል፡፡ በቴሌቪዥን መስኮት ሲቀርቡ ለምን እንደሚቆጡና ማስጠንቀቂያ እንደሚያበዙም አላውቅም፡፡ አንድ ጥያቄ አለኝ::
 ለመሆኑ እኒህ ወገኖች “የክልልነት ጥያቄ” የሚያቀርቡት ለሕዝቡ ምን ሊፈይዱለት ይሆን? የኑሮ ደረጃውን ያሻሽሉለታል? የሥራ ዕድል ይፈጥሩለታል? ለሰራተኛው የደሞዝ ጭማሪ ያደርጉለታል? የተሻለ የጤና አገልግሎት ያቀርቡለታል? ወዘተ… ጥያቄው ብዙ ነው፡፡
እነዚህን መሰረታዊ ጥያቄዎች የማይመልሱ ከሆነ፤ ከዚህ ሁሉ ጥድፍያና ወከባ በስተጀርባ ሌላ አጀንዳ እንዳለ መጠርጠር ተገቢ ነው::  በተለይ ሀገር በነውጥ ማዕበል እየተናጠች፣ ግጭትና መፈናቀል በየቦታው እየፈነዳ ባለበት በዚህ ሰዓት “ዛሬውኑ ክልል ካልሆንን ሞተን እንገኛለን” ማለት የጤና አይደለም፡፡
ፖለቲከኞችና “የክልልነት ጥያቄ” አቀንቃኝ ልሂቃን (አክቲቪስቶች)፤ ከዚህ “አንገብጋቢ” የክልል አጀንዳ፤ የሚያገኙትን በቅጡ ብናውቅ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ምናልባት የበለጠ ሥልጣን?... ጥቅም?... ሀብት?...እንደው ምን ይሆን እንዲህ ዓይናቸውን አስጨፍኖ “አሁኑኑ ክልል!” የሚያስብላቸው?!
እንደ ማንኛውም የአገራችን ፖለቲከኛና ልሂቃን ‹‹የምንታገልለት ሕዝብ?” ማለት ቢያበዙብንም ቅሉ፤ የፈረደበት ምስኪን ሕዝብ ግን ክልል በሆነ ማግስት፣ ሌማቱ ሞልቶ እንደማያድር ጠንቅቀን እናውቃለን:: ሕዝቡ ክልል ከመሆን አንዳችም ጠብ የሚልለት ነገር እንደሌለ ይታወቃል፡፡ እነሱ ግን ሎተሪ የሚደርሰው እያስመስሉት ነው:: ባይሆን ሎተሪው የሚደርሰው ለእነሱ ነው - ለፖለቲከኞቹና አክቲቪስቶቹ፤ ለነገዎቹ የክልሉ ባለሥልጣናት!!
ሳላስበው ወደ ሌላ ርዕሰ ጉዳይ ገባሁ እንጂ የእኔ ጥያቄ፣ (ስጋቴም ነው) ዞኖቹ ወደ ክልልነት ባደጉ ማግስት፣ የየአካባቢው ተወላጅ ባልሆኑ ዜጐች  ላይ የሚደርሰውን አስከፊ የመፈናቀልና የሞት አደጋ ማነው የሚታደጋቸው የሚለው ነው፡፡
ወደ ኤልቲቪ ልመልሳችሁ፡፡ የወላይታን የክልልነት ጥያቄ የሚያስረዱት “ተወካይ ነን” ባዮች፤ ክልል በመሆን ሂደት፤ “የአካባቢው ተወላጅ ባልሆኑ ዜጎች ላይ ጥቃትና መፈናቀል እንደማይደርስ ምን ማስተማመኛ አለ?›› በሚል ከጋዜጠኛ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ ‹‹ማስተማመኛው ህገ መንግስቱ ነው›› ብለዋል:: ግን የምራቸውን ነው?! ህገ መንግስቱ መቼ በሲዳማ ለተፈናቀሉትና ጥቃት ለደረሰባቸው… ማስተማመኛ ሆነ? ከዚህ ቀደምስ… በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በግፍ ሲባረሩና ሲፈናቀሉ ሕገ መንግስቱ መቼ አዳናቸው? ህገ መንግስቱ ዜጎችን ከመፈናቀል ታድጎ ያውቃል እንዴ? እነዚህ የክልል ጥያቄ አቀንቃኞች “ህገመንግስቱ ይታደጋቸዋል” ሲሉ ከአንጀታቸው ነው ወይስ ከአንገታቸው? ለነገሩ እነሱ የፈለጉትን ያግኙ እንጂ አገርና ህዝብ በአንድ እግራቸው ቢቆሙ ደንታቸው አይመስለኝም:: ለዚህ ነው እየሆነ ያለው ሁሉ የሚሆነው፡፡ ለማንኛውም ግን አሁንም መንግስት ለዜጐቹ ጥላ ከለላ ሊሆናቸው ይገባል፡፡ ያለበለዚያ የምንፈራው ይደርሳል፡፡
ዳዊት - ከአዲስ አበባ

የእንግሊዝ የወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ ቦሪስ ጆንሰን በአብላጫ ድምጽ ማሸነፋቸውን ተከትሎ፣ ባለፈው ረቡዕ የቀድሞዋን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ በመተካት አዲሱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በይፋ ስልጣን ተረክበዋል፡፡
የመዲናዋ ለንደን ከንቲባ በመሆን ያገለገሉትንና እ.ኤ.አ በ2016 እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት አባልነቷ ትውጣ የሚል ሃሳብ በማቀንቀን በይፋ ዘመቻ ማድረግ የጀመሩትን ቦሪስ ጆንሰንን በተመለከተ፣ የተለያዩ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ካወጧቸው ዘገባዎች ጥቂቱን እነሆ ብለናል፡፡
የግል ህይወት
ከዲፕሎማት አባት እና ከአርቲስ እናት እ.ኤ.አ 1964 ሰኔ 19 ቀን ኒውዮርክ ሲቲ ውስጥ የተወለዱት ቦሪስ ጆንሰን፣ ብራስልስ ዋን በተባለ ትምህርት ቤት በኤተን ኮሌጅና በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እንደተከታተሉ የህይወት ታሪካቸው ያሳያል፡፡
ሁለት ጊዜ ትዳር መስርተው ያፈረሱት ጆንሰን በአሁኑ ጊዜም ኬሪ ሲሞንድስ ከተባለች ወዳጃቸው ጋር እንደሚኖሩ ተነግሯል፡፡
በእንግሊዝ ፓርላማ የወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ የሆኑት ቦሪስ ጆንሰን፣ እ.ኤ.አ ከ2008 እስከ 2016 ድረስ የእንግሊዝ ርዕሰ መዲና ለንደን ከንቲባ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፣ ከ2016 እስከ 18 ደግሞ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል፡፡
ደራሲና ጋዜጠኛው ጆንሰን
አዲሱ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፤ “ሰቨንቲ ቱ ቨርጂንስ” የተሰኘውን ተወዳጅ ረጅም ልቦለድ ጨምሮ አራት  መጽሐፍትን ለንባብ ያበቁ ምርጥ ደራሲ ስለመሆናቸው ዘ ጋርዲያን ይመሰክርላቸዋል፡፡
ቦሪስ ጆንሰን ታዋቂዎቹን ታይምና ዴይሊ ቴሌግራፍ መጽሔት ጨምሮ በተለያዩ ታዋቂ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ለረጅም አመታት በሪፖርተርነትና በአምደኝነት እንደሰሩ የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ በተለይም የአውሮፓ ህብረት አገራትን የሚተቹ ጽሁፎችን ለንባብ በማብቃት እንደሚታወቁ አስነብቧል፡፡ ጥሩ ጸሃፊ እንጂ የፕሬስ ህግና መመሪያዎችን የማያከብሩ ጋዜጠኛ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ጆንሰን፣ የተዛባ ጽሁፍ አውጥተዋል በሚል ከታይም መጽሔት መባረራቸውን ዘ ጋርዲያን ያስታውሳል፡፡
ጨዋታ አዋቂውና ፈጣን ተናጋሪው
ለማዳመጥ የሚከብድ ፍጥነት ያለውና በጩህት የታጀበ ንግግር መለያቸው እንደሆነ የሚነገርላቸው ቦሪስ ጆንሰን፣ በአንደበተ ርዕቱነታቸውና የተመረጡ ቃላትን በመጠቀም እንደሚታወቁ የዘገበው ቢቢሲ፣ ጮክ ብለው መናገራቸውን በልጅነታቸው ከነበረባቸው የመስማት ችግር ጋር የተያያዘ ነው ይላል፡፡
ቦሪስ ጆንሰን ከፈጣን ተናጋሪነታቸው ባልተናነሰ በጨዋታ አዋቂነታቸውና ቀልዶችን በመፍጠር እንደሚታወቁም ቢቢሲ ይገልጻል፡፡
ከ970 ሺህ ዶላር ወደ 187 ሺህ ዶላር?
ፎርብስ መጽሄት የቦሪስ ጀንሰንን ገቢ አስመልክቶ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ እንዳለው፣ ሰውዬው በፓርላማ አባልነታቸው በከንቲባነታቸውና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ዘመናቸው ያገኙት የነበረው ገቢ እንዲሁም በንግግር፣ በደራሲነትና በጸሐፊነት የሚከፈላቸው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡
ሰውዬው ከመስከረም ወር 2018 እስከ ሰኔ ወር 2019 በነበሩት ጊዚያት በድምሩ 970 ሺህ ዶላር ገቢ ያገኙ ሲሆን፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸው ያገኙት የነበረው 176 ሺህ ዶላር እንደነበርም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በህዳር ወር 2018 እስከ ሰኔ ወር 2019 በተለያዩ መድረኮች ላይ ንግግር በማድረግ ብቻ 560 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንደተከፈላቸው የሚነገርላቸው ጆንሰን፣ በ2018 ብቻ ከዴይሊ ቴሌግራፍ ጋዜጣ በደመወዝ መልክ 342 ሺህ ዶላር ያህል እንደተከፈለላቸውና  ለህትመት ካበቋቸው አራት መጽሐፍት ከ2017 እስከ 2019፣ 61.7 ሺህ ዶላር ያህል ገቢ እንዳገኙ ተዘግቦላቸዋል፡፡
ይህንን ሁሉ ገቢ ያገኙ የነበሩት ቦሪስ ጆንሰን በእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው የሚያገኙት አመታዊ ደመወዝ 186 ሺህ  ዶላር እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ አዲሱ ስልጣን ከገንዘብና ከገቢ አንጻር እንደማያዋጣቸው አውስቷል፡፡


የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር፤ እሳቸው በሌሉበት የአገሪቱ ብሔራዊ መዝሙር እንዳይዘመር የሚከለክል ህግ ማውጣታቸውን የአገሪቱን የማስታወቂያ ሚኒስትር ጠቅሶ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ የሕዝብ መዝሙር ከኤምባሲዎችና ከትምህርት ቤቶች በስተቀር በሌሎች ቦታዎች መዘመር የሚችለው ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር በስፍራው ከተገኙ ብቻ እንዲሆን ፕሬዚዳንቱ ባለፈው አርብ ባደረጉት የካቢኔ ስብሰባ ውሳኔ ማስተላለፋቸውን ማስታወቂያ ሚኒስትሩ ማይክል ማኩዌል በይፋ ማስታወቃቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የተለያዩ ባለስልጣናትና ተቋማት የህዝብ መዝሙሩን ዜማና ግጥም በቅጡ ሳይለማመዱ እንደነገሩ ሲዘምሩት እንደሚታዩ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ “ይህም የአገሪቱን ብሄራዊ ክብር የሚነካ ነው፣ ብሄራዊ መዝሙር ፕሬዚዳንቱ በተገኙበት ብቻ የሚዘመር እንጂ ማንም ተራ ዜጋ የሚያበላሸው አይደለም” ብለዋል፡፡
የሳልቫ ኬር መንግስት ፕሬዚዳንቱ በሌሉበት የህዝብ መዝሙር እንዳይዘመር ቢከለክልም፤ ድርጊቱን በፈጸሙ ላይ የሚወሰደውን እርምጃ በተመለከተ ግን ሚኒስትሩ ያሉት ነገር እንደሌለ ዘገባው ገልጧል፡፡

 እ.ኤ.አ በ2009 ለእይታ የበቃውና የምንጊዜም ባለከፍተኛ ገቢ ፊልም ሆኖ የዘለቀው የጄምስ ካሜሮን ፊልም አቫታር፣ ባለፈው እሁድ በአቬንጀርስ ኢንድጌም ክብሩን መነጠቁን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ካሜሩን በ1998 ለእይታ ያበቃው ታይታኒክ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በማግኘት ታሪክ መስራቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ በ2010 በሌላኛው ተወዳጅ ፊልሙ አቫታር 2 ቢሊዮን ዶላር በማግኘት የራሱን ክብረወሰን መስበሩንና ባለፈው እሁድ ግን በአቬንጀርስ ኢንድጌም ክብሩን መነጠቁን አመልክቷል፡፡
ባለፈው ሚያዝያ ለእይታ የበቃው አቬንጀርስ ኢንድጌም በድምሩ 2.79 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት፣ በአለማችን የፊልም ታሪክ ከፍተኛውን ገቢ ያገኘ ፊልም ሆኖ ከመንበሩ ላይ መቀመጡንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

ታዋቂው ፎርቹን መጽሄት የ2019 የአለማችን 500 ባለ ብዙ ገቢ ግዙፍ ኩባንያዎች ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን የአሜሪካው ዎልማርት 514.4 ቢሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ በማስመዝገብ በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
በ2018 የፈረንጆች አመት ግሩፕ 414.6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስመዘገበው የቻይናው ሲኖፔክ ሮያል የሁለተኛነትን ደረጃ ሲይዝ፣ ደች ሼል በ396.5 ቢሊዮን ዶላር የአለማችን የአመቱ ሶስተኛው ግዙፍ ኩባንያ ተብሎ መመዝገቡን ዘገባዎች አመልክተዋል::
ቻይና ናሽናል ፔትሮሊየም በ392.9 ቢሊዮን ዶላር፣ ስቴት ግሪድ በ387 ቢሊዮን ዶላር፣ ሳኡዲ አርማኮ በ335.9 ቢሊዮን ዶላር፣ ቢፒ በ303.7 ቢሊዮን ዶላር፣ ኤክሰን ሞቢል በ290.2 ቢሊዮን ዶላር፣ ቮልስዋገን በ278.3 ቢሊዮን ዶላር፣ ቶዮታ ሞተር በ272.6 ቢሊዮን ዶላር እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአመቱ የአለማችን ኩባንያዎች ናቸው፡፡
ከ34 የአለማችን አገራት የተውጣጡት የአመቱ 500 ግዙፍ ኩባንያዎች ባለፈው የፈረንጆች አመት (2018) በድምሩ 2.15 ትሪሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸውን የጠቆመው ፎርቹን መጽሔት፤ ኩባንያዎቹ በመላው አለም ለ69.3 ሚሊዮን ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
በዘንድሮው የፎርቹን ዝርዝር ውስጥ 13 አዳዲስ ኩባንያዎቿን በማካተት የምርጥ ኩባንያዎቿን ቁጥር 129 ያደረሰችው ቻይና፤ በዝርዝሩ ውስጥ ብዛት ያላቸውን ኩባንያዎች በማስመዝገብ፣ ከአሜሪካ በመቅደም የአንደኛነት ደረጃን መያዟ የተነገረ ሲሆን፣ አሜሪካ 121 ኩባንያዎቿን በዝርዝሩ ውስጥ በማካተት እንደምትከተል ተዘግቧል፡፡ በዝርዝሩ ውስጥ የ11ኛ ደረጃን የያዘው አፕል በሞባይል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከተሰማሩ ኩባንያዎች ዘንድሮም መሪነቱን የያዘ ሲሆን፣ በ15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሳምሰንግ ይከተለዋል፡፡


 የሱዳን ወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤትና የአገሪቱ ተቃዋሚ ሃይሎች ስልጣን ለመጋራት የሚያስችላቸውንና ለወራት የዘለቀውን ህዝባዊ ተቃውሞና ግጭት ያስቆማል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን  ስምምነት ባለፈው ማክሰኞ መፈራረማቸው ተዘግቧል፡፡
ሁለቱ ሃይሎች አንድ ሌሊት ሙሉ ሲወያዩና ሲከራከሩ ቆይተው በስተመጨረሻ የተፈራረሙት ስምምነት፣ የአገሪቱ ከፍተኛው የስልጣን እርከን የሆነውን ሉዐላዊ የጋራ ምክር ቤት አቋቁሞ፣ ለሶስት አመታት ያህል እየተፈራረቁ ለማስተዳደርና  በቀጣይም አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል እንደሆነ የዘገበው ቢቢሲ፤ የወታደራዊ ምክር ቤቱ ምክትል ሊቀ መንበር ሞሃመድ ሃምዳን ዶጋሊ ስምምነቱን “ታሪካዊ ክስተት” ሲሉ በአድናቆት መግለጻቸውን አመልክቷል፡፡
ተቀናቃኝ ሃይሎቹ ከህገ መንግስት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚያደርጉት ቀጣይ ስምምነት አርብ ዕለት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው ገልጧል፡፡
ሱዳንን ለ30 አመታት ያህል ያስተዳደሩት ኦማር አልበሽር ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ በህዝባዊ ተቃውሞ ከመንበራቸው መባረራቸውን ተከትሎ፣ ስልጣኑን የያዘው ወታደራዊ ምክር ቤት፣ ስልጣኑን በሲቪል ለሚመራ መንግስት ያስረክብ በሚል ሱዳናውያን ለወራት ተቃውሞ ሲያደርጉ እንደቆዩ ይታወሳል፡፡