Administrator

Administrator

 በህይወት ከሌሉ የአለማችን ዝነኞች ከፍተኛውን ገቢ በማግኘት ላለፉት አምስት አመታት በመሪነት የዘለቀው የፖፕ ሙዚቃ ንጉስ ማይክል ጃክሰን ዘንድሮም በ313 ሚሊዮን ፓውንድ አመታዊ ገቢ በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ ተዘግቧል፡፡
ማይክል ጃክሰን ከኤሚ ሚዩዚክ ፐብሊሺንግ በተባለው አሳታሚ ኩባንያ ውስጥ ካለው የአክስዮን ድርሻና በህይወት ሳለ የሰራቸውን ሙዚቃዎች ለማሳተም ከኩባንያዎች ጋር የተደረጉ ስምምነቶችን ጨምሮ በድምሩ 313 ሚሊዮን ፓውንድ ማግኘቱን የዘገበው ፎርብስ መጽሄት፤ ድምጻዊው ከዚህ አለም በሞት ከተለየበት እ.ኤ.አ 2009 በኋላ ባሉት አመታት በድምሩ 1.8 ቢሊዮን ፓውንድ ገቢ ማግኘቱን የጠቆመው ዘገባው፣ በህይወት ከሌሉ የአለማችን ዝነኞች በገቢ የሁለተኛነት ደረጃን የያዘው ሌላው ዘመን አይሽሬ ድምጻዊ ኤልቪስ ፕሪስሊ ሲሆን፣ ኤልቪስ ባለፉት 12 ወራት ጊዜ ውስጥ 31 ሚሊዮን ፓውንድ ገቢ ማግኘቱን አመልክቷል፡፡
በተወለደ በ42 አመቱ እ.ኤ.አ በ1977 ከዚህ አለም በሞት የተለየው ኤልቪስ ፕሪስሊ ባለፉት 12 ወራት የተጠቀሰውን ገቢ ያገኘው ከቀድሞ ሙዚቃዎቹ ሽያጭና ከሌሎች ገቢዎች እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ዝነኛው የጎልፍ ተጫዋች አርኖልድ ፓልመር በ27 ሚሊዮን ፓውንድ የሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፣ ታዋቂው ካርቱኒስት ቻርለስ ሹልዝ በ26 ሚሊዮን ፓውንድ አራተኛ፣ የሬጌው ሙዚቃ ንጉስ ቦብ ማርሌ ደግሞ በ18 ሚሊዮን ፓውንድ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
በፎርብስ መጽሄት የዘንድሮ የአለማችን ሟች ዝነኞች ገቢ ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት ሌሎች ዝነኞች መካከል እውቋ የፊልም ተዋናይ ማርሊን ሞንሮ የምትጠቀስ ሲሆን፣ በ11 ሚሊዮን ፓውንድ የ11ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡


 2.6 ቢሊዮን ወርሃዊ ተጠቃሚዎች፣ 33 ሺህ 606 ሰራተኞች አሉት


     ታዋቂው ማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ እስካለፈው መስከረም በነበሩት ያለፉት ሶስት ወራት ብቻ የ13.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱንና በየዕለቱ የሚጠቀሙ ደንበኞቹ ቁጥርም 1.49 ቢሊዮን መድረሱን አስታውቋል፡፡
የፌስቡክ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙክበርግ ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ባደረጉት መረጃ እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት ፌስቡክ፣ ዋትዛፕ፣ ኢንስታግራምና ሜሴንጀር የተሰኙትን የኩባንያው አገልግሎቶች የሚጠቀሙ ወርሃዊ ደንበኞች ቁጥር ከ2.6 ቢሊዮን በላይ ደርሷል፡፡
ፌስቡክ ባለፉት ሶስት ወራት ካገኘው ገቢ 92 በመቶ ያህል ድርሻ የያዘው ከሞባይል ስልኮች ማስታወቂያዎች ያገኘው ገቢ መሆኑን የጠቆሙት ዙክበርግ፣ ኩባንያው ከዚህ ማስታወቂያ 12.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱንና በፌስቡክ የተለያዩ ምርቶቻቸውንና አገልግሎቶቻቸውን የሚያስተዋውቁ ኩባንያዎች ቁጥር ከ6 ሚሊዮን በላይ መድረሱንም አስረድተዋል፡፡
በየዕለቱ በፌስቡክ፣ ዋትሳፕና ሜሴንጀር አማካይነት 100 ቢሊዮን ያህል የጽሁፍና የምስል መልዕክቶች እንደሚላኩ የተነገረ ሲሆን፣ ከ90 ሚሊዮን በላይ ኩባንያዎችም የፌስቡክ ገጾችን ከፍተው ራሳቸውን እያስተዋወቁና ስራዎቻቸውን እያቀላጠፉ እንደሚገኙ ዘገባው አስረድቷል፡፡
ባለፈው የካቲት ወር ላይ በተጀመረው የፌስቡክ የክፍት የስራ ቦታ ማመልከቻ አፕሊኬሽን አማካይነት በተለያዩ የስራ ቦታዎች ላይ ለመቀጠር የቻሉ ደንበኞች ቁጥርም ከአንድ ሚሊዮን በላይ መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፣ ፌስቡክ የሰራተኞቹን ቁጥር 33 ሺህ 606 ማድረሱንንም አክሎ ገልጧል፡፡

   በአገሪቱ ከ88 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በከፋ ድህነት ውስጥ ይገኛሉ

    ባለፉት አራት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ናይጀሪያውያን ወደ ከፋ ድህነት መግባታቸውንና በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ የአገሪቱ ዜጎች ቁጥር 88 ሚሊዮን መድረሱን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ተቀማጭነቱን በቪየና ያደረገው ወርልድ ፖቨርቲ ክሎክ የተሰኘ ተቋም ይፋ ባደረገው አለማቀፍ ሪፖርት እንዳለው፣ ከ1.9 ዶላር በታች ዕለታዊ ገቢ ባላቸው ወይም በከፋ ድህነት ውስጥ በሚገኙ ዜጎች ብዛት ናይጀሪያ ከአለማችን አገራት በቀዳሚነት ትገኛለች፡፡
በናይጀሪያ ድህነት ስር እየሰደደ እንደሚገኝ የጠቆመው ተቋሙ፣ መንግስት ችግሮችን ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት በቂ አለመሆኑንና አገሪቱ በ2030 ከድህነት ለመውጣት ያስቀመጠችውን ግብ ለማሳካት እንደማትችል የሚያመላክቱ ሁኔታዎች መኖራቸውንም አስረድቷል፡፡ የቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ያወጣውን ትንበያ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በመጪዎቹ 12 አመታት ጊዜ ውስጥ ከአለማችን እጅግ ድሃ ሰዎች መካከል ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑት በናይጀሪያ እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡
የአለም ባንክ በበኩሉ፤ በመላው አለም በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ከ1.6 ቢሊዮን በላይ መድረሱን ያስታወቀ ሲሆን፣ ከ29 በመቶ በላይ የሚሆኑትም ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገራት እንደሚኖሩ አስረድቷል፡፡


 ከአራት ወራት በፊት ከአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ ጋር ታሪካዊ የተባለውን ስብሰባ በማድረግ ከአለም ጋር የነበራቸውን ለአመታት የዘለቀ ኩርፊያ የደመሰሱት የሰሜን ኮርያው ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን፣ በቅርቡም አገራቸው የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱላት ለማግባባት በማሰብ ከ5 የአለማችን አገራት መሪዎች ጋር ተገናኝተው ለመምከር ማቀዳቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
ኪም ጁንግ ኡን ከደቡብ ኮርያው ፕሬዚዳንት ሙን ጃኢን እና ከቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂፒንግ ጋር በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገናኝተው እንደሚወያዩ መነገሩን የጠቆመው ዘገባው፣ ከጥቂት ወራት በኋላም ከጃፓኑን ፕሬዚዳንት  ሺንዙ አቤ ጋር ይገናኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡
ከአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ ጋር በመጪው ወር በድጋሚ ለመገናኘት ሳያስቡ አልቀሩም የተባሉት የወትሮው አመጸኛ ኪም ጁንግ ኡን፣ በዚያው ሰሞን ወደ ሩስያ አቅንተው ከፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ስብሰባ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና “ይምጡና እንማከር” ብለው ለሮማው ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የክብር ግብዣ መላካቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡

 በመላው አለም በሚገኙ የተለያዩ አገራት ባለፉት አስር አመታት በድምሩ ከ1 ሺህ በላይ ጋዜጠኞች እንደተገደሉና በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በየዕለቱ በአማካይ አንድ ጋዜጠኛ እንደተገደለ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል፡፡የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳለው፣ ጋዜጠኞቹ ዘገባዎችን በሚሰሩበትና ለህዝብ በሚያቀርቡበት ወቅት በስራ ገበታቸው ላይ እያሉ የተገደሉ ናቸው፡፡ባለፉት አስር አመታት በእነዚህ ጋዜጠኞች ላይ ግድያ ከፈጸሙት ሰዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ግድያውን በመፈጸማቸው በህግ ተጠያቂ እንዳልተደረጉና እንዳልተቀጡ ድርጅቱ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡በአለማችን የተለያዩ አገራት ግድያን ጨምሮ በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እያደገ መጥቷል ያለው ተቋሙ፣ መንግስታት በመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም የሚገፋፉ የጥላቻ ንግግሮችንና አባባሽ ድርጊቶችን እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ ብለነዋል፤ ማንም ስላልሰማን ደግመን እንለዋለን ይላል - አንድ የጥንት ታሪክ ፀሐፊ፡፡ የእኛም እንደዚያው ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ደገኛ ገበሬዎች አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ ሳር ቤት ነው ያላቸው፡፡ ደሳሳ ጎጆዎች ናቸው፡፡ በድንገት አንድ ቀን የአንደኛው ገበሬ ቤት ተለወጠ፡፡ ቆርቆሮ ቤት ሆነ፡፡ ጎረቤትየው ደነገጠና፤
“ወዳጄ፤ እንዴት ይሄ ቤትህ ሊለወጥ ቻለ? ምን ተዓምር ተገኘና ነው?”
ገበሬው፤
“አየህ በሬዎቼን ሸጥኳቸውና ታች ቆላ ወርጄ ብረታ ብረት ገዛሁ፡፡ ከዚያ ደጋ አምጥቼ ለቀጥቃጩ፣ ለባለእጁ፣ ማረሻ ለሚፈልገው ገበሬ ሸጥኩ፡፡ ብዙ ብር አገኘሁ፡፡ ቤቴን ለወጥኩ፡፡ አጥሬን ለወጥኩ፡፡ ራሴን ለወጥኩ!”
“በቃ፤ እኔም እንዳንተ አደርጋለሁ” አለና ሄዶ በሬዎቹን ሸጠ፡፡ ከዚያም ገበያ ገብቶ ማጭድ፣ አካፋ፣ ዶማ፣ ማረፊያ፣ ገሶ … ብቻ አለ የሚባል የብረት ግብዓት ገዝቶ፣ ተሸክሞ፣ ወደ ደጋ ዳገቱን ተያያዘው፡፡
ሆኖም ያን ሁሉ ብረት አቅሙ አልችል አለና ዳገቱ ወገብ ላይ ተዝለፍልፎ ወደቀ፡፡ የመንደሩ ሰው በዚያ ሲያልፍ አየውና፤
“አያ እገሌ ምን ሆነህ ነው?”
“ያ ጎረቤቴ ገበሬ ጉድ አርጎኝ ነው!”
“ምን አደረገህ?”
“ንግድ ጀምሬያለሁ ብሎ የንግዱን ጠባይ ነገረኝ፡፡ ባለኝ መሰረት ንግድ ውስጥ ገባሁ”
“ታዲያ እሱ ምን በደለህና ነው ጉድ አደረገኝ የምትለው?”
“ትርፉን ነግሮ መከራውን ሳይነግረኝ!”
***
አያሌ ትርፍ ያስገኛሉ የተባሉ ነገሮች መከራ እንዳላቸው መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ቀላል የሚመስሉ ግን ውስብስብ የሆኑ፣ ውስብስብ ሆነው የባሰ የሚወሳሰቡ፣ ሳንማርባቸው ያለፉ፣ ተምረንባቸው የተረሱ፣ ጨርሶ ያላጠናናቸው ብዙ ብዙ ቁምነገሮች አሉ፡፡
“ከበሮ በሰው እጅ ያምር
ሲይዙት ይደናገር!” የሚባለው ተረት፣ ለተሿሚዎቹ ሁሉ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው! በተለይ ሴት ተሿሚዎች መብዛታቸው አኩሪ የመሆኑን ያህል ኃላፊነታቸውን መወጣታቸው፣ ከሙስና የፀዱ መሆናቸው፣ የፆታ እኩልነትን ማበልፀጋቸው፣ ለበርካታ ሴቶች አርአያ መሆናቸው፣ ከወንዶች ይልቅ ዝርዝር ጉዳይ ላይ የማተኮር ክህሎታቸው (Meticulousness) እጅግ የላቁ ያደርጋቸዋል! ይሄ ቢሳካልን ላሜ ወለደች ነው! ይህን ዕድል እንደ ሌሎች ያመለጡን ዕድሎች እንዳይሆን መትጋት ያስፈልጋል፡፡ የእናቶች ፀጋ በእጃችን ነው፡፡ የህፃናት ፀጋ በእጃችን ነው፡፡ የትምህርት ፀጋ በእጃችን ነው! የሚያስጎመጅ ዕድል ባያመልጠን መልካም ነው! የዲሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የተስፋ፣ የራዕይ ጊዜ እየጀመረ ነውና እንጠቀምበት! ለብዙ ዓመታት የጮህንለት የሴቶች አጀንዳ መልካም ጉዞ ይጓዝ ዘንድ የወንዶችም የሴቶችም ጥያቄ አድርገን እንየው፡፡ አለበለዚያ “የማያስተኛ ነገር ነግረውን ተኝተው አደሩ” ይሆንብናል!!

ከ20 በላይ ፊልሞች ለዕይታ ይቀርባሉ

   በተለያዩ የአውሮፓ አገራት የተሰሩና ዓለም አቀፍ ሽልማት ያገኙ ከ20 በላይ ፊልሞች ለእይታ የሚቀርቡበት የአውሮፓ ፊልም ፌስቲቫል የፊታችን ሐሙስ በቫምዳስ መዝናኛ ይከፈታል፡፡ የአውሮፓ አገራት  አምባሳደሮችና የባህል ማዕከላት ዳይሬክተሮች ከትናንት በስቲያ በቫምዳስ የመዝናኛ ማዕከል በሰጡት መግለጫ፤ በፌስቲቫሉ ላይ የኢትዮጵያዊያን አጫጭር ፊልሞች ለእይታ እንደሚቀርቡና የአውሮፓና የኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች የልምድ ልውውጥ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
በዘንድሮ የፊልም ፌስቲቫል ላይ የቤልጂየም፣ የቼክ ሪፐብሊክ፣ የዴንማርክ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የሀንጋሪ፣ የአየርላንድ፣ የአዘርባጃንና የቱርክ ፊልሞች የሚታዩ ሲሆን ፊልሞቹ ዘጋቢ፣ ታሪካዊ፣ ኮሜዲና ድራማ ዘውግ ያላቸው እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ፊልሞቹ በየአገራቱ ቋንቋዎች የተሰሩና የእንግሊዝኛ ሰብታይትል ያላቸው ሲሆኑ ለእይታ የሚቀርቡትም በነፃ ነው ተብሏል፡፡
በዚህም መሰረት የፈረንሳዩ “LeBiro” የተሰኘው ፊልም በመክፈቻ ስነ ሥርዓቱ ላይ ሐሙስ ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ላይ የሚቀርብ ሲሆን ዓርብ ከቀኑ 8፡00 ላይ የኢትዮጵያ አጫጭር ፊልሞች፣ ከቀኑ 10፡30 ደግሞ የስፔይን፣የአውሮፓ ህብረትና የአፍሪካ ህብረት ፊልሞች ለእይታ ሲበቁ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ ከቀኑ 5፡00 ላይ የስውዲን የህፃናት ፕሮግራም፣ ከቀኑ 8፡00 የስሎቫኪያ፣ ከቀኑ 10፡00 የዩናይትድ ኪንግደም እና ከምሽቱ 12፡30 የኔዘርላንድስ ፊልም ለእይታ ይቀርባሉ፡፡ እሁድ ከቀኑ 8፡00 ደግሞ የፖርቹጋል፣ 10፡00 ላይ የኢጣሊያ፣ ምሽት 1፡00 ላይ የጀርመን ፊልሞች ይታያሉ ተብሏል፡፡
በቀጣዩ ሳምንት ሐሙስ ጥቅምት 29 ከቀኑ 10፡00 የቱርክ፣ ምሽት 1፡00 የአዘርባጃን ፊልሞች የሚታዩ ሲሆን ቅዳሜ ህዳር 1 ረፋድ 4፡00 ላይ የሀንጋሪ የህፃናት ፕሮግራም፣ ከቀኑ 8፡00 የቤልጂየም፣ 10፡00 ላይ  የፊንላንድ፣ ምሽት 12፡30 ደግሞ የዴንማርክ ፊልሞች ለእይታ እንደሚበቁ ታውቋል፡፡ እሁድ ህዳር 2 ቀን 2011 ዓ.ም የፌስቲቫሉ መዝጊያ ሲሆን ከቀኑ 8፡00 የአየርላንድ፣ 10፡00 የቼክ ሪፐብሊክ፣ ምሽት 1፡00 ደግሞ የፖላንድ ፊልሞች ታይተው፣ የፌስቲቫሉ መቋጫ እንደሚሆን ታውቋል፡፡  


አፕልና ሳምሰንግ 15 ሚሊዮን ዩሮ ተቀጥተዋል
 
ታዋቂው የኤሌክትሪክ መኪኖች አምራች ኩባንያ ቴስላ እስከ መስከረም በነበሩት ያለፉት 3 ወራት በድምሩ 311.5 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ ማግኘቱንና ባለፉት 15 አመታት ታሪኩ ይህን ያህል የሩብ አመት ትርፍ ሲያስመዘግብ ይህ ለሶስተኛ ጊዜው እንደሆነ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡
ኩባንያው ባለፉት ሶስት ወራት  ከበፊቱ በተሻለ ፍጥነት በርከት ያሉ የኤሌክትሪክ መኪኖችን አምርቶ ለደንበኞቹ ማስረከብ መቻሉ ገቢውንና ትርፉን እንዳሳደገለት የጠቆመው ዘገባው፣ የማምረት አቅሙን የበለጠ ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የጣሊያን የንግድ ውድድር ባለስልጣን መስሪያ ቤት፣ ወደ ግዛቴ ያስገቧቸውን የተለያዩ አይነት የሞባይል ምርቶቻቸውን ሆን ብለው ቶሎ እንዲደክሙ አድርገዋል በሚል በአፕል ላይ የ10 ሚሊዮን፣ በሳምሰንግ ላይ ደግሞ የ5 ሚሊዮን ዩሮ ቅጣት እንደጣለባቸው ተዘግቧል፡፡
ኩባንያዎቹ ለጣሊያን ገበያ ያቀረቧቸው የተለያዩ አይነት የሞባይል ስልኮች ቶሎ እንዲደክሙና አዝጋሚ እንዲሆኑ በማድረግ፣ ተጠቃሚዎች ሶፍትዌር አፕዴት እንዲያደርጉ ባልገተባ መንገድ ያስገድዳሉ፤ አፕዴቶቹም የስልኮቹን ፍጥነት ይቀንሳል በሚል ቅጣቱ እንደተጣለባቸው ተነግሯል፡፡
የስልኮችን አቅም የሚቀንስ ሶፍትዌር አፕዴት አላቀረብኩም ያለው ሳምሰንግ፤ የቀረበበትን ክስና ቅጣት በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቅ  ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፤ አፕልም ተመሳሳይ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁሟል፡፡

ዋረን በፌ በ1ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል

የአፍሪካው ቁጥር አንድ ባለጸጋ ናይጀሪያዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ፤ ከፍተኛ በጀት መድበው ትርጉም ያለው ስራን በሚያከናውኑ የአለማችን ምርጥ በጎ አድራጊዎች ዝርዝር ውስጥ የ6ኛ ደረጃን መያዛቸውን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
ከፍተኛ ገንዘብ ለበጎ አድራጎት ተግባራት በማዋል የሚታወቁ የአለማችን ግለሰቦችን ዝርዝር ይፋ ያደረገው ሪችቶፒያ የተባለ የእንግሊዝ ተቋም፣ በፋውንዴሽናቸው አማካይነት 1.25 ቢሊዮን ዶላር ለበጎ አድራጎት ተግባራት የመደቡት ዳንጎቴ 6ኛ ደረጃን መያዛቸውን አመልክቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ1981 ባቋቋሙት ፋውንዴሽን አማካይነት በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የመሰረተ ልማት ግንባታና የበጎ አድራጎት ስራ ሲያከናውኑ የቆዩት የ61 አመቱ ናይጀሪያዊ ቢሊየነር ዳንጎቴ፣ ከአጠቃላይ የተጣራ ሃብታቸው ከስምንት በመቶ በላይ የሚሆነውን ለበጎ አድራጎት ተግባር እንዳዋሉም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በተቋሙ የምርጥ በጎ አድራጊዎች ዝርዝር ውስጥ በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አሜሪካዊው ቢሊየነር ዋረን በፌ ሲሆኑ የማይክሮሶፍቱ መስራች ቢል ጌትስ በሁለተኛነት ይከተላሉ፡፡
እንግሊዛዊቷ ደራሲ ጄ ኬ ሮውሊንግስ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ አሜሪካዊቷ የቶክ ሾው አቅራቢ ኦፕራ ዊንፍሬይ አራተኛ፣ የቴስላ ኩባንያ ባለቤት ኤለን ሙስክ ደግሞ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ሪቻርድ ብራንሰን፣ ማርክ ዙክበርግ፣ ጄፍ ቤዞስና ማይክ ብሉምበርግ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአምስተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ ሌሎች በጎ አድራጊዎች ናቸው፡፡


በመላው አለም በሚገኙ የተለያዩ አገራት የኢንተርኔት ዋጋ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ሳቢያ አገልግሎቱን መጠቀም ያልቻሉ ሰዎች ቁጥር ከ2.3 ቢሊዮን በላይ መድረሱን አንድ አለማቀፍ የጥናት ሪፖርት አስታውቋል፡፡
አሊያንስ ፎር አፎርዴብል ኢንተርኔት የተባለው ተቋም በ61 የአለማችን አገራት ላይ የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው አመታዊ ሪፖርቱ እንዳለው፣ ጥናቱ ከተሰራባቸው አገራት መካከል ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከዜጎች የመክፈል አቅም በላይ የሆነ የኢንተርኔት ዋጋ ተመን ያላቸው ናቸው፡፡
በሁሉም አገራት የአንድ ጊጋ ባይት ኢንተርኔት ክፍያ ዋጋ ከአገራቱ አማካይ ወርሃዊ ገቢ ከ5 በመቶ በላይ እንደሚደርስ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት ክፍያ ውድነት በርካታ ዜጎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ከፍተኛ እንቅፋት መሆኑን ቀጥሏል፡፡ በአለማችን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር እድገት በአመቱ ቅናሽ ማሳየቱን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ2017 መጨረሻ ላይ የአለማችንን የኢንተርኔት አቅርቦት 50 በመቶ ለማድረስ ያስቀመጠውን ግብ ማሳካት እንዳልተቻለም አመልክቷል፡፡