Administrator

Administrator

    የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ 84 ሺህ 659 የሚገመቱ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህጻናት ምንም አይነት የትምህርት አገልግሎት እያገኙ እንዳልሆነ አስታውቋል፡፡ ዩኒሴፍ ትናንት የሰጠውን መግለጫ ጠቅሶ አናዶሉ ኤጀንሲ እንደዘገበው፣ በሁለቱ ክልሎች የተከሰቱ ግጭቶች 14 ሺህ ያህል ህጻናትን ከወላጆቻቸው ጋር እንዲለያዩ ምክንያት ሆነዋል ተብሎ ይገመታል፡፡
በሁለቱም ክልሎች 120 ሺህ የሚገመቱ ዕድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆናቸው ህጸናት እንዲሁም 20 ሺህ ነፍሰ ጡርና ጡት የሚያጠቡ እናቶች የአሰቸኳይ የንጥረምግብ አገልግሎቶች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ያለው ዘገባው፣ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱትን ህጻናት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት እንዲያገኙ ለማስቻል 2.9 ሚሊዮን ዶላር ያህል እንደሚያስፈልግ ዩኒሴፍ ማስታወቁን አመልክቷል፡፡

ደንበኞች ባሉበት ሆነው የአየር መንገዱን ሙሉ አገልግሎት ማግኘት ያስችላቸዋል

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞቹ ባሉበት ቦታ ሆነው የአየር መንገዱን የተለያዩ አገልግሎቶችን ማግኘት የሚችሉበትን የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ (አፕሊኬሽን) ተግባራዊ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ይህ የመረጃ መተግበሪያ (አፕሊኬሽን) ደንበኞች ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን በመጠቀም የበረራ ቲኬት መቁረጥ፣ ክፍያ መፈፀምና የበረራ ወንበር ቁጥር ባሉበት ቦታ ሆነው ለመምረጥ የሚያስችላቸው ነው ተብሏል፡፡
የገንዘብ ክፍያም በሞባይል ባንኪንግ አሊያም በኢንተርኔት መፈፀም ይቻላል ተብሏል። መተግበሪያው በጎግል ፕሌይ እና በአፕስቶር እንደሚገኝና ማንኛውም ሰው ዳውንሎድ አድርጎ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል አየር መንገዱ ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫው አስታውቋል፡፡
ደንበኞች ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ በእንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ፣ አረብኛና ሌሎች የውጭ ሃገር ቋንቋዎች አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ታውቋል፡፡ ይህ መተግበሪያ በአየር መንገዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች መሰራቱ የተገለፀ ሲሆን አገልግሎቱ ለደንበኞች ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም ገልፀዋል፡፡

     ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በባቡር መስመር የመገናኘት እቅድ እንዳላትና ከካርቱም ኢትዮጵያ ድንበር የሚደርስ የባቡር መስመር በቅርቡ መገንባት እንደምትጀምር የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከትናንት በስቲያ ከካርቱም ወደ ሌላኛዋ የሱዳን ከተማ ኤልገዚራ የተገነባውን የባቡር መስመር መርቀው ስራ ባስጀመሩበት ወቅት ደቡብ ሱዳን፣ ኢትዮጵያና ሱዳንን የሚያገናኝ ረጅም የባቡር መስመር ሃገራቸው እንደምትገነባ ተናግረዋል፡፡  
ወደ ኢትዮጵያ የሚገነባው የባቡር መስመር የራሷ ወደብ ለሌላት ኢትዮጵያ በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑንና ወደ ደቡብ ሱዳን የሚዘረጋው መስመርም በተለይ ከኬንያና ከኡጋንዳ ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ በምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰቦች መካከል መቀራረብና የንግድ ቅልጥፍናን ይፈጥራል ብለዋል- ፕሬዚዳንቱ፡፡
አሜሪካ በሱዳን ላይ ጥላው የነበረውን ማዕቀብ ካነሳች በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ መነቃቃት መጀመሩን የዘገበው ሱዳን ትሪቡን፤ አዳዲስ የባቡር መስመሮችን እየገነባች ከመሆኑ በተጨማሪ አሮጌዎቹንም እየጠገነች ስራ እያስጀመረች መሆኑን ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮ-ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ የባቡር መስመር ከታህሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም አንስቶ የመንገደኞች የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን በ4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው የባቡር መስመሩ፣ የመንገደኞችና የጭነት ትራንስፖርት ዋጋም ወጥቶለታል፡፡    
ለእቃ ማመላለሻ ባቡር ለአንድ ቶን በኪሎ ሜትር 1 ብር ከ75 ሳንቲም ሲሆን ለመንገደኞች ማጓጓዣ ከለቡ ተነስቶ ጅቡቲ ለመድረስ በወንበር ተቀምጠው ለሚሄዱ 503 ብር፣ በመኝታ ክፍሎች ተጠቅመው ለሚጓጓዙ እንደየ ደረጃው 671፣922 እና 1,006ብር ዋጋ ተተምኗል፡፡
ከለቡ ወደ ድሬደዋ ለመሄድ በወንበር 308 ብር እንዲሁም በአልጋ ለሚጓዙ እንደ አልጋው ደረጃ 410፣ 564 እና 616 ብር ተተምኗል፡፡ በልዩ መኝታ ክፍሎች ከለቡ ተነስተው ጅቡቲ ለሚጓዙ 1,258 ብር እና 1,341 ብር ዋጋ እንደወጣለት ታውቋል፡፡   

ዓለማችን ሊጠናቀቅ የቀናት ዕድሜ በቀረው የፈረንጆች ዓመት 2017፣ እጅግ በርካታ ክስተቶችን አስተናግዳለች፡፡ ባለፉት 12 ወራት ዓለማችን ያስተናገደቻቸውን ዋና ዋና ክስተቶች በተመለከተ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ከሰሞኑ ለንባብ ካበቋቸው አበይት መረጃዎች መካከል ጥቂቶቹን መርጠን እነሆ ብለናል!
የትራምፕ መምጣት
የፈረንጆች አመት 2017 አሃዱ ብሎ ሲጀምር፣ አለማችን ካስተናገደቻቸው ዋነኛ መነጋገሪያ ጉዳዮች መካከል የዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመት አንዱ ነበር፡፡ ለወራት በዘለቀው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የቅስቀሳ ዘመቻ ላይ “ሙስሊሞችን ከአገሬ አባርራለሁ” የሚለውን ጨምሮ በርካታ አወዛጋቢ ጉዳዮችን በአደባባይ ሲያስተጋቡ የከረሙት ትራምፕ፤ ዲሞክራቷን ተፎካካሪያቸው ሄላሪ ክሊንተንን አሸንፈው መንበረ ስልጣኑን ይረከባሉ ብሎ የጠበቃቸው ብዙ ሰው ባይኖርም፣ ድል ቀንቷቸው አለምን አስገርመዋል፡፡
በአመቱ የመጀመሪያ ወር ላይ በደማቅ በዓለ ሲመት፣ 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሆኑት ትራምፕ፤ አመቱን ሙሉ አለምን የሚያስገርሙና በአነጋጋሪነታቸው ጎልተው የወጡ እርምጃዎችን በመውሰድ ነበር ያሳለፉት፡፡
ሰብዓዊ ቀውሶች
በዓለማችን የከፋው የሰብዓዊ ቀውስ ሰለባ እንደሆነች አመቱን አገባድዳለች - በእርስ በእርስ ጦርነት የምትታመሰዋ የመን፡፡ ከ17 ሚሊዮን በላይ የመናውያን የሚልሱ የሚቀምሱት አጥተው አመቱን በርሃብ አልፈውታል፡፡ በአገሪቱ የተቀሰቀሰው የኮሎራ ወረርሽኝም 1 ሚሊዮን ያህል ዜጎችን ሲያጠቃ፣ ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለሞት ዳርጓል፡፡
የዓለም ባንክ ባወጣው አመታዊ ሪፖርት እንዳለው፤ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ በ45 የአለማችን አገራት ውስጥ የሚገኙ 83 ሚሊዮን ያህል ዜጎች የርሃብ አደጋ ተጠቂና የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ፈላጊ ነበሩ፡፡ ይህ ቁጥር ከሁለት አመታት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር፣ በ70 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡
የተፈጥሮ አደጋ
የፈረንጆች አመት 2017 ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከእስያ እስከ ደቡብ አሜሪካ፣ በተለያዩ የአለማችን አገራት በርካታ ቁጥር ያላቸው የተፈጥሮ አደጋዎች የተከሰቱበትና ከፍተኛ ጥፋት ያደረሱበት ነበር፡፡ 2017 የካሊፎርኒያና የፖርቹጋልን ጨምሮ በርካታ የሰደድ እሳቶች የተከሰቱበት ዓመት ነበር፡፡ ከአሜሪካዎቹ ሃሪኬኖች እስከ አየርላንድ አውሎንፋሶች ድረስ እጅግ ከፍተኛ ጥፋት አስከትለዋል፡፡
ሰሜን ኮርያ
ሰሜን ኮርያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዘንድሮ በሚሳኤል ሙከራና በኒውክሌር ማስፋፋት የተጠመደችበት ሆኖ ነበር ያለፈው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማዕቀብም ሆነ የአሜሪካና የሌሎች አገራት ዛቻና ማስፈራሪያ ያልበገራት ሰሜን ኮርያ፤ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ከ12 ጊዜያት በላይ የባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራዎችን አድርጋለች፡፡ ሰሜን ኮርያ ወሩ በገባ በሁለተኛው ሳምንት ወደ ጃፓን ባህር ባስወነጨፉት ሚሳኤል የተጀመረው የሚሳኤል ሙከራ፤ የአካባቢውን አገራት ብቻ ሳይሆን የተቀረውን አለምም ያስደነገጠና ስጋት ውስጥ ከትቶ ያለፈ ነበር፡፡
ሰሜን ኮርያና አሜሪካ፤ በቃላት ጦርነትና በፍጥጫ ነበር አመቱን ያገባደዱት፡፡ ትራምፕ እና ኪም ጁንግ ኡን አንዳቸው ሌላኛቸውን በቃላት ሲያዋርዱና ሲዘልፉ፣ ከአሁን አሁን ተታኮሱ በሚል አለምን ሲያስጨንቁ፣ አመቱን በቃላት ጦርነት አገባድደውታል፡፡
የሮሂንጋ ሙስሊሞች መከራ
የፈረንጆች 2017 በማይንማር ለሚኖሩ የሮሂንጋ ሙስሊሞች፣ ከመቼው ጊዜ የከፋ የመከራና የስቃይ ሆኖ ነበር ያለፈው፡፡ የማይንማር ወታደሮች በወራት ጊዜ ውስጥ ከ6 ሺህ 700 በላይ የሮሂንጋ ሙስሊሞችን መግደላቸው ተነግሯል፡፡ ቤታቸው በእሳት ሲጋይባቸው፣ ወገኖቻቸው አይናቸው እያየ ሲታረዱባቸው፣ ነፍሳቸውን ለማዳን በየጫካው የተበተኑና አገራቸውን ጥለው ወደ ጎረቤት ባንግላዴሽ የተሰደዱ የሮሂንጋ ሙስሊሞች ከ600 ሺህ በላይ እንደሚደርሱም የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡  የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ሆነ አለማቀፉ ማህበረሰብ የሚገባውን ያህል ትኩረት አልሰጠውም የተባለው የሮሂንጋ ሙስሊሞች ቀውስ፤ ለመጪው 2018 የፈረንጆች አመትም ባለበት ሁኔታ ይቀጥላል ተብሎ እየተነገረ ነው፡፡
የሽብር ጥቃቶች
ግንቦት 22 ቀን ምሽት ላይ…
በእንግሊዟ ማንችስተር የተዘጋጀውን የአርያና ግራንዴ የሙዚቃ ኮንሰርት ለመታደም በአዳራሽ ውስጥ የተገኙ የሙዚቃ አፍቃሪያን ራሳቸውን ያላሰቡት መከራ ውስጥ አገኙ፡፡ በአዳራሹ ውስጥ የተሰማው ድንገተኛ ፍንዳታ፣ ተደጋግሞ ቀጠለ፡፡ ሁሉም ነፍሱን ለማዳን በየአቅጣጫው ተራወጠ። 22 ያህል ሰዎችን ለሞት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎችም ለመቁሰል አደጋ ተዳረጉ፡፡
ልክ እንደ ማንችስተር ሁሉ፣ ከስቶክሆልም እስከ ባርሴሎና፣ ከበርሊን እስከ ፓሪስ በርካታ የአውሮፓ አገራት ከተሞች በሽብር ጥቃቶች እየተናወጡ ነበር አመቱን የገፉት፡፡ የሽብር ጥቃቱ አውሮፓ ላይ አያበቃም፡፡ አሜሪካን ጨምሮ በርካታ አገራት በአይሲስ እንዲሁም በተለያዩ ጽንፈኛ ቡድኖችና ወፈፌ ገዳዮች ሲሸበሩ ነው የከረሙት፡፡
የሙጋቤ መውረድ
አፍሪካ በአመቱ ካስተናገደቻቸው አነጋጋሪና ጉልህ ክስተቶች መካከል፣ ላለፉት 37 አመታት አገራቸውን የገዙት የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ስልጣን መልቀቅ አንዱ ነበር፡፡ ወታደሩ በሙጋቤ ላይ መፈንቅለ መንግስት አደረገ በሚል አስደንጋጭ ዜና የጀመረው የዚምባቡዌ ጉዳይ፤ አገሪቱን ወደ ከፋ የእርስ በእርስ ግጭት ይከታታል ተብሎ ሲገመት፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ፣ ሙጋቤ በሰላማዊ መንገድ ስልጣናቸውን ለተፎካካሪያቸው ምናንጋዋ አስረክበዋል፡፡
ዛሬም የባሪያ ፍንገላ
ሲኤንኤን አመቱ ከመጠናቀቁ በፊት ከወደ ሊቢያ ያሰማው ወሬም ሌላኛው አለምን ያስደነገጠ ጉዳይ ነበር፡፡ የባርነት ዘመን አበቃ ተብሎ ከታወጀ ከረጅም አመታት በኋላ፣ አፍሪካውያን በሊቢያ እንደ ሸቀጥ እየተሸጡና ለባርነት እየተፈነገሉ መሆኑን  የሚያትተው ይህ ዘገባ፤ ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡ የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ከሞት ጋር እየታገሉ አሰቃቂውን የውቅያኖስ ጉዞ ለመጋፈጥ አገራቸውን ጥለው ወደ አውሮፓ የስደት ጉዞ የጀመሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን፤ ሊቢያ ላይ በጨካኞች መዳፍ ላይ ወድቀው ለባርነት መሸጣቸው አለምን እያነጋገረ አመቱ ተገባድዷል፡፡
ኢየሩሳሌም
አመቱ ከመጠናቀቁ በፊት፣ አለምን ያስደነገጠ ነገር ከወደ ዋይት ሃውስ ተሰማ…
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ የኢየሩሳሌምን የእስራኤል መዲናነት እውቅና እንደሚሰጡ አስታወቁ፡፡ ይህን ተከትሎ እስራኤል በደስታ ስትፈነድቅ፣ ፍልስጤምና ፍልስጤማውያን ደግሞ በቁጣ ነድደው፣ አደባባይ በመውጣት፣ ትራምፕንና አሜሪካን አወገዙ፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ብቻ ሳይሆኑ በርካታ የአለማችን አገራት፣ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል ያለውን ለዘመናት የዘለቀ የይገባኛል ውዝግብ፣ ወደ ከፋ ምዕራፍ ያሸጋገረና ተገቢነት የሌለው ነው በማለት በይፋ የትራምፕን ውሳኔ አወገዙት፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም የትራምፕን ውሳኔ ውድቅ የሚያደርግ ውሳኔ ለማስተላለፍ አባል አገራቱ ድምጽ እንዲሰጡ አደረገ፡፡ 128 ያህል የአለማችን አገራት ሃሳቡን ደግፈው ድምጻቸውን በመስጠታቸውም፣ የትራምፕ ውሳኔ ውድቅ ተደረገ፡፡


  ስለ ጉዳዩ አስተያየት ከሰጡ ቻይናውያን፣ 90 በመቶው እርምጃውን ደግፈውታል

   የኢንተርኔት ነጻነትን በመጣስና ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ የሚታወቀው የቻይና መንግስት፤ ባለፉት 3 አመታት ብቻ ህግና መመሪያዎችን ጥሰዋል በሚል ከ13 ሺህ በላይ የተለያዩ ድረ-ገጾችን በመዝጋት ከአገልግሎት ውጭ ማድረጉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ቻይና በተለይ ደግሞ ፕሬዚዳንት ዢ ፒንግ ስልጣን ከያዙ በኋላ፣በነበሩት ያለፉት አምስት አመታት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በሚጥስ መልኩ በኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ላይ የምታደርገው ጥብቅ ቁጥጥርና ቅጣት በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል ያለው ዘገባው፤ የአገሪቱ መንግስት የሚሰነዘሩበትን ትችቶች ለማፈን፣ ብዙ ድረገጾችን እየዘጋ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡
አለማቀፍ ተቋማት የቻይናን ጥብቅ የኢንተርኔት ቁጥጥር በተደጋጋሚ ቢተቹትም፣ የአገሪቱ መንግስት ግን “ሁሉም አገራት የሚያደርጉትን ነው እያደረግሁ ያለሁት፤ በኢንተርኔት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር የማደርገው ብሄራዊ ደህንነቴን ለመጠበቅና ማህበራዊ መረጋጋትን ለመፍጠር በማሰብ ነው” ሲል ምላሽ መስጠቱ ተነግሯል፡፡
የመብት ተሟጋች ተቋማት፤ የቻይና መንግስት የዜጎቹን መብት እየጣሰ ነው ሲሉ ቢወነጅሉትም፣ የድረገጾቹን መዘጋት በተመለከተ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ከተጠየቁት ቻይናውያን መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአንጻሩ እርምጃውን እንደሚደግፉ መናገራቸውንም የሮይተርስ ዘገባ አስረድቷል፡፡
ቻይና 13 ሺህ ድረገጾችን በመዝጋቷ ሳቢያ 10 ሚሊዮን ያህል አካውንቶች ከአገልግሎት ውጭ ሆነዋል ያለው ዘገባው፤ “የአገሪቱ መንግስትም የተባለው ነገር እውነት መሆኑን አምኖ፣ ልቅ ወሲብና ብጥብጥ የሚያጭሩ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላትን አደገኛ ድርጊት ለማስቆም ስል ህገወጥ ድርጊቱን ሲፈጽሙ ያገኘኋቸውን ድረገጾች ዘግቻለሁ” ብሏል፡፡

ነዋሪነቷ በአሜሪካ ፔንሲልቫኒያ ግዛት የሆነው ሜሪ ሆሮማንስኪ በከፍተኛ ድንጋጤ ክው አለች። ያየቺውን ነገር ለማመን ቸግሯት በድንጋጤ ተንቀጠቀጠች፡፡ በህልሟ ይሁን በእውኗ እርግጠኛ መሆን አልቻለችም ነበር፡፡
ህልም እንዲሆን እየተመኘች፣ አስደንጋጩን ሰነድ በድጋሚ አየቺው - 284 ቢሊዮን ዶላር! እንደተመኘቺው ህልም አልሆነም፡፡ የግዛቲቷ የኤሌክትሪክ ሃይል መስሪያ ቤት፣”ባለፈው ህዳር ወር ለተጠቀምሺው የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት፣ 284 ቢሊዮን ዶላር ክፈይኝ” የሚል ሰነድ ነው የላከላት፡፡ በፍርሃት እየተንቀጠቀጠች ወደ መስሪያ ቤቱ ደወለች፡፡
“ምን ጉድ ነው የምታሰሙኝ?!...” ስትል ከዚህ የቁም ቅዠት እንዲገላግሏት ጓጉታ ጠየቀች፡፡
“እጅግ ይቅርታ እንጠይቃለን!... የቁጥር ስህተት ፈጽመናል፤መክፈል የሚጠበቅብሽ 284 ዶላር ብቻ ነው!” የሚል ከጭንቀት የሚገላግል፣ የምስራች የሆነ ምላሽ ሰጧት - የመስሪያ ቤቱ ተወካይ፡፡
እፎይ አለች! - ቢቢሲ ነው የዘገበው፡፡


    በቀዳማዊ ቴዎፍሎስ ፓትሪያርክ ህይወትና መንፈሳዊ አገልግሎት ዙሪያ በሚያጠነጥነው መፅሀፍ ላይ ዛሬ ከቀኑ 7፡30 ጀምሮ በኢትዮጵያ ሆቴል ዳሰሳና ጥናታዊ ፅሁፍ እንደሚቀርብ የፕሮግራሙ አዘጋጆች ገለፁ፡፡
 “የፓትሪያርክ ቴዎፍሎስ አሻራዎች” በሚል ርዕስ በሚካሄደው በዚህ ፕሮግራም ላይ አቡነ ማቴዎስ (ዶ/ር)፡- የፓትሪያርክ ቴዎፍሎስ አሻራ ከትምህርት አንፃር፣ ዶ/ር አግደው ገዴ፡- የፓትሪያርኩ አሻራ ከልማት አኳያ፣ ዶ/ር ምክረስላሴ ገ/አማኑኤል፡- ከውጭ ግንኙነታቸውና ከታሪክ አንፃር፣ መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል ከቤተክርስቲን አደረጃጀት ፅንሰ ሀሳብ አንፃርና ዶ/ር አሰፋ ዘሩ፡- በአጠቃላይ በመፅሀፉ ላይ ዳሰሳ እንደሚያቀርቡ የፕሮግራሙ አዘጋጆች ጠቁመዋል፡፡  በፕሮግራሙ ላይ ፓትሪያርኩ አቡነ ማቲያስንጨምሮ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ወ/ማሪያም፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ የወመዘክር ሀላፊዎችና የተለያዩ የሀይማኖት አባቶች እንደሚገኙም ታውቋል፡፡

 አብርሀም ግዛው ኢንተርቴይመንት ከጄቲቪ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር “ገናን ከልጆች ጋር” የተሰኘ ልዩ የበዓል መዝናኛ ፕሮግራም ያቀርባል፡፡ ፕሮግራሙ በዋናነት በበዓል ወቅት ትኩረት የሚነፈጋቸውን ልጆች ታሳቢ ያደረገ ሲሆን የፕሮግራሙ ቀረፃ ሳር ቤት በሚገኘው “ኤስ ኦ ኤስ” የህፃናት መንደር ነገ የሚቀረፅ ሲሆን እንደ ሌባና ፖሊስ፣ ቅልብልቦሽ፣ እምቡሼ ገላ፣ የገና ጫዋታ፣ ገበጣ፣ ሱዚና ሌሎች ጨዋታዎች የሚካሄድ ሲሆን በልጆች ጉዳይ ላይ ውይይት፣ የልምድ ልውውጥና ልዩ የቤተሰብ ተሞክሮዎች ለታዳሚው እንደሚቀርቡ አዘጋጁ አብርሀም ግዛው ገልጿል፡፡
ፕሮግራሙም የገና በዓል ዕለት ከረፋዱ ከ3፡00እስከ 4፡30 በጂቲቪ ኢትዮጵያ እንደሚተላለፍ ታውቋል፡፡

Tuesday, 02 January 2018 10:07

ያልታየ ዕድል!

 በመረረ ሀዘን ውስጥ እያለፈም ደስተኛ ነበር። በለቅሶ ሸለቆ መሀል፤ በሰቀቀን እንብርት ቆሞም መሣቅ ይችላል፡፡ በተለይ በትዳሩ ደስተኛ ነው። አንድ ልጁ ደመቀ ከመጣ ወዲህ ደሞ በጊዜ ቤቱ ገብቶ የልጁን ሁለት ጥርሶች ፈገግታ ሲያይ፣ ሁሉንም ነገር ይረሳዋል፡፡ ባለቤቱ በቀለችም መልካም ሰው ናት። አንዳንዴ ፊቱን ፀሀይ አክስሎት፣ አሻሮ መሥሎ ሲመጣ፣ ኮቱን ተቀብላ፤ ስማ፣ የሞቀ የእግር ውሃ ታቀርብለታለች፤ ያኔ ደስታው ሀዘኑን ይዳምጠዋል።
ከሠፈር ሲወጣም የሠፈሩን ደብር ተሣልሞ፣ “በቀኝ አውለኝ” ይላል፡፡ ዛሬ ግን በቀኝ አውለኝ ብሎ ወጥቶ ፣ በግራ ነው የዋለው፡፡ የቀጠረው ድርጅት ሥራ አስኪያጅ፣ ያልሆነ ነገር ተናግሮታል፡፡ በዚያ ላይ ጉርሻ የሚባል ነገር አልቀመሰም፤ እንዲያውም ጠዋት ሲወጣ፣ የልጁን ጡጦ ለመቀየርና ካናቴራ ነገር ሊገዛም አስቦ ነበር፡፡ አልተሳካም፡፡
ቀን አሥር ሰዐት ላይ ነበር ግምገማቸው። የሥራ ባልደረባው ታደለ፣ ከርሱ በፊት ሥራ አስኪያጁ ቢሮ ሲገባ ፈገግ ብሎ ነበር ያየው፡፡ ሲወጣም እንደዚያው ደስተኛ ነበር፡፡
እርሱ ሲገባ ግን የአለቃው ፊት ልክ አልነበረም። ከዚያም “ባለፈው ወር ምሥጉን ሰራተኛ አንተ ነበርክ፤ አሁን ግን ቁልቁል ወርደሃል፤ ስለዚህ የመጨረሻ ማሥጠንቀቂያ ነው፡፡… ሥራህን በደንብ ካልሠራህ የልጅ አባት ነኝ፤… የቤተሰብ ሃላፊ ነኝ---ማለት ተቀባይነት የለውም፡፡” አለው፤ሥራ አስኪያጁ፡፡
ጭንቅላቱ ሁለት ቦታ ተከካ፡፡
“ምንድነው ጥፋቴ?”
“ጥፋትህን እንደማታቅማ አትሁን!”
“እንዴት እያወቅኩ በእንጀራዬ እቀልዳለሁ!?”
አለቃው ጠረጴዛውን በእስክርቢቶ እየቀበቀበ፤ “…የተፈጠረልህ ዕድል አልገባህም፤ ምን ዐይነት ታላቅ ሥራ እንደሆነ  አላስተዋልክም…..”
አቀርቅሮ ዝም አለ፡፡ ሥራ ቢያገኝ፤ መቀየር ይፈልጋል፡፡ ግን ሥራ የለም፤ ሥራውን በግዱ ለምዶታል እንጂ እንደ ጥሩ ዕድል አያየውም፡፡
“ከትናንት ወዲያ ያስቀበርካቸው ሰው ምን እንደሆኑ ታውቃለህ?”
“ጭምጭታ ሠምቻለሁ፣ አሜሪካ ሀገር የኖሩ ፕሮፌሰር ናቸው አሉ…”
”እርሳቸውን የሚያህል፣ ሀገር የሆነ ሰው፣ ለማስቀበር ብቃት አለኝ ብለህ ታምናለህ?”
“በፍፁም!”
“የስንተኛ ክፍል ተማሪ ነህ?”
“አምስተኛ”
“አየኸው ልዩነታችሁን!”
አቀርቅሮ ለአፍታ በዝምታ ከቆየ በኋላ፤ “…ምንድነው ጥፋቴ ግን…?”
“ጥፋትህ…ጥፋትህ?”
በዓይኖቹም በጆሮዎቹም ጠበቀ- መልሱን፡፡
“አንደኛ…”
“አ?
“አስክሬን ተሸክመህ በፈገግታ መዋልህ፤ ያን ያህል የሀገር ዋርካ ወድቆ ጠላትህ የሞተ ይመስል…”
“እኔ ግን ፈገግ አላልኩም፣ እንዲያውም እህትየው በጣም ሲያለቅሱ ሆዴ ባብቶ እንባዬ ሲመጣ.. ሀሳቤን ወደ ትንሹ ልጄ ወሰድኩትና የጥርሶቹ ፈገግታ ሲታሰበኝ፣ ምናልባት ፈገግ ብዬ ይሆናል፡፡ ሌላ ምን ፈገግ የሚያሰኝ ነገር አለ? ያው ልጄ ነው። ለሥራ የሚያበረታኝም፣ የሚያነቃቃኝም እርሱ ነው፡፡ ከወለድኩ በኋላ… ህይወቴ ተለውጧል፡፡”
“ባትወልደው ይሻላል…”
“ለምን ጌታዬ…ፈጣሪ የሰጠኝን…”
“እርሱም እንዳንተ ሬሳ ተሸክሞ የሚሥቅ ጅል ነዋ የሚሆነው!”
ሀዘን ልቡን ሰበረው፡፡ ሥራውን ጥሎ ሊወጣ አስቦ ነበር፡፡ የቤት ኪራዩ፣ የልጁ ነገር፣ የሚስቱ ህይወት..ገታው፡፡
ስድብ ጠገበ፡፡ ዘለፋና ንቀት ፈሰሰበት፡፡
“የዛሬ ስድስት ወር የሞቱት ፕሮፌሰር ወንድም ግን ሸልመውኝ ነበር፡፡…” አለና፤ ከአፉ ያመለጠው ያህል  ደንግጦ ዝም አለ፡፡
“ዕድለኛ ነህ አልኩህ’ኮ!... ከፕሮፌሰሮች ጋር ትውላለህ”
“ኡይ ጋሽዬ --- ሰርግ ላይ እኮ አይደለም፣ ቀብር ላይ ነው፡፡ በለቅሶ ላይ ማንም ይገኛል፡፡ ሥልጣንና ዕውቀትም አይደለም፡፡ የኔ ቢጤውስ ይመጣ የለ!?”
“አይደለማ! አንተ’ኮ… የታላላቅ ሰዎችን አስክሬን ትሸከማለህ፤ የህይወት ታሪካቸው ሲነገር ታደምጣለህ፡፡ ላንተ ዩኒቨርሲቲ ነው ይሄ ዕድል!... እኔ አሜሪካ የኖርኩት፣ የሰው ሽንት ቤት እያጠብኩ ነው--”
“ሬሳ መሸከም ዕድል ነው ጋሼ?”
“የማንም ድሃ ሬሳ እንዳይመስልህ… የምትሸከመው..”
“…ቄሱ፤ ከሞተ አንበሳ በህይወት ያለ እንትን ይሻላል ነበር ያሉት--”
“በቃ ዝጋ!  ልታስተምረኝ ነው!”
ሀገር ቤት ሄዶ ሚስቱን በቀለችን ያገባበት ቀን ትዝ አለው፡፡ ሙሽራ ሆኖ ኮትና ሱሪ አድርጎ፣ ቬሎ ያጠለቀች ሚስቱን ዐይነ ርግብ ገልጦ ሲስማት፣ እልልታው አሰከረው፡፡ እልልታና ሣቅ ከረሳ ቆይቷል፡፡ ውሎው ለቅሶ ነው፤ ቀብር ነው፡፡ ድንግርግር አለው፡፡ ሙሾውን እንደ ዘፈን ለምዶታል፤ ብዙ ግጥሞችም ያውቃል፡፡ በተለይ ከባላገር የመጡ አልቃሾች፣የሚደረድሩት ቅኔ ያሥደንቀዋል፡፡
ኸረ ሚዜው ደሃ ነው፤ ሽቶው ውሃ ነው፡፡
ክንዱን በክንድዋ ቆልፎ ወደ መኪና ሲገባም ተዐምር ነበር የሆነበት፡፡ በልቡም ሥራ ሊቀይር አሥቦ ነበር፡፡ ሚስቱ እስካሁን ሥራውን አታውቅም፡፡ መርካቶ የሚሠራ ነው የሚመሥላት፡፡ አንዳንዴ በጎ ሰዎች አግኝተው፣ ጉርሻ የሰጡት ቀን፣ ሥጋ ይዞ ሲገባ፤ ብርቱካን ሲሸምት-- በለስ የቀናው ይመሥላታል፡፡
አንዴ በተለይ ሚኒስትር የነበሩ ሰው ቀብር ላይ አስከሬናቸውን ተሸክሞ ሄዶ፣ ሥርዐተ ቀብር ከተፈፀመ በኋላ ስለ ሰውየው ታሪክ ሲሰማ፣ እንባውን መቆጣጠር አቃተው፡፡ ጓደኞቹ ሁሉ የጎሪጥ እያዩ በትዝብት አላገጡበት፡፡ ኋላ እንደሚተርቡት አሰበ። ግን ምንም ማድረግ አልቻለም፡፡
በተለይ ሰውየው በየገጠሩ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት ያደረጉትን ጥረት፤ ከሥራ ጊዜያቸው በተጨማሪ በትርፍ ጊዜያቸው ሳይቀር፤ የገጠር ትምህርት ቤቶችን እየጎበኙ፣ ጎበዝ ተማሪዎች እንዲሸለሙ በማድረግ፣ የድሀ ልጆችንም በግላቸው እየረዱ፣ የህይወት ዘመናቸውን እንደፈፀሙ ሲሰማ አለቀሰ፡፡
“የዚህ ዐይነት ሰው ቢገጥመኝ፣ዛሬ እኔ እዚህ አልገኝም ነበር፡፡” ብሎ ነው - ለራሱ ያለቀሰው፡፡
መጨረሻ ላይ የሚኒስትሩ ወንድም ወደ ቤት ሊመለሱ ሲሉ፣ በእጅ ምልክት ጠሩትና፣ በጆሮው “አንተ ትልቅ ሰው ነህ፤ ልብህ እንዴት እንደተነካ አይቻለሁ፤ ወንድሜ እንዳንተ ላሉት ምስኪኖች ኖሮ የሞተ ወገን ወዳድ ነበር!” ብለው አምስት መቶ ብር በትንሽ ፖስታ ጠቅልለው በእጁ አሥያዙት፡፡ ደነገጠ፡፡ ድንጋጤው ለረጅም ሰዓታት አልለቀቀውም ነበር፡፡ የዛሬ ወር ገደማ---
እጁን የኋሊት አድርጎ በሀሳብ ጭልጥ እንዳለ፤ “ይህ የመጨረሻ ዕድልህ ነው!... አሁን መሄድ ትችላለህ!” አለው አለቃው፡፡ መረረው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ያ ሁለት ጥርሶቹን ብልጭ የሚያደርግ ልጁ ትዝ አለው፡፡ የህይወቱ ተስፋ፣ የመኖሩ ጉልበት እርሱ ነው፡፡
ባለቤቱ በተራዋ ፊቱ ድቅን አለችበት፡፡ እያሰላሰለ  አጎንብሶ ሲወጣ፤
“ምን አለህ?...ምን አለህ?” አሉት ጓደኞቹ፡፡
መልስ አልሰጠም፡፡ “በቃ፤ ከዛሬ ጀምሮ ሬሳ አልሸከምም!” ብሎ በቀጥታ ወደ ቤቱ አመራ፡፡
 ቤት ሲሄድ፤ “ምነው በዛብህ! ሥራ የለም እንዴ?”
በዝምታ ፊቱን ወደ ግድግዳ መልሶ ተኛ፡፡ ልጁም አልጋው ጥግ ላይ ተኝቷል፡፡
እንቅልፉ እምቢ ሲለው፣ ጉርሻ የተቀበለበትን ፖስታ ድንገት ከኪሱ አገኘው፡፡ ለካ ውስጡ ያላያት ብጣሽ ወረቀት ነበረች፡፡  
“እንዳንተ ላለው ሀገር ወዳድ ወጣት፣ ልቤና በሬ ክፍት ነው፡፡ ደስ ባለህና ሥራ በፈለግህ ጊዜ “አድማስ” የተባለው ባለ አራት ኮከብ ሆቴል ብቅ በል፡፡ ስልጠና ላዘጋጅልህ ፍቃደኛ ነኝ--”
እንደ እብድ ብድግ ብሎ ከቤቱ ወጣ፡፡ ለካስ ዕድል አለ!!

  አንዳንድ ተረት አድማጭ ሲያጣ ተደጋግሞ ይነገር ዘንድ ግድ ይሆናል፡፡ ያ ከዓመታት በፊት ያቀረብነው ተረት ስለ ጅቦቹና ስለ አህዮች ነው፡፡ ጅቦቹም፣ አህዮቹም ዛሬም አሉ፡፡ ስለዚህ ደግመን እንተርከዋለን፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ሶስት አህዮች በጠፍ ጨረቃ ሣር ሊግጡ ይወጣሉ-እንደ ሰው፡፡
አንድ ሣሩ የለመለመ መስክ ያገኙና መጋጥ ይጀምራሉ፡፡ ጥቂት እንደጋጡ ጅቦች ይመጡና ይከቧቸዋል፡፡ ጅቦቹ መደፈራቸው አናዷቸዋል፡፡ ስለዚህ ሊፈርዱባቸው ችሎት ተቀመጡ፡፡
1ኛ ጅብ ዳኛ፡- የመጀመሪያዋ አህያ እንድትቀርብ ያዛል፡፡
አህያ ገባች፡፡
የማህል ጅብ ዳኛ፡- “ወይዘሮ አህያ፤ በጠፍ ጨረቃ፣ በእኛ ግዛት፣ ሣር ልትግጪ ለመውጣት የቻልሺው ማንን ተማምነሽ ነው?”
1ኛ አህያ፡- “አምላክን ተማምኜ ነው፡፡ አምላኬ ምንም አደጋ እንዳይደርስብኝ ይጠብቀኛል፡፡ አደጋም ከደረሰብኝ በሆነ መንገድ ይበቀልልኛል፡፡ ለእሱ ምን ይሳነዋል?”
ጅቡ ዳኛ ወደ ጥግ እንድትቆም ያዟታል፡፡
“ሁለተኛዋ አህያ ግቢ” ይላሉ፡፡
ሁለተኛዋ አህያ ገብታ ትቆማለች፡፡
የመሀል ዳኛው ጅብ፡- “ወይዘሮ አህያ፤
በጠፍ ጨረቃ፣ በእኛ ግዛት፤ ሣር ልትግጪ ለመውጣት ያስቻለሽ ድፍረት ከየት መጣ? ማንን ተማምነሽ ነው?”
ሁለተኛዋ አህያ እንዲህ ስትል መለሰች፡-
“ጌታዬ፣ ባለቤቱን፣ እሱን ተማምኜ ነው፡፡ ማንም ጉዳት ቢያደርስብኝ ይበቀልልኛል፡፡ ንብረቱ ነኝና ንብረቱን በሚነካ ላይ እርምጃ መውሰዱ አይቀርም!”
ጅቡ መሀል ዳኛ፤ “ወደ ዳር ቁሚ” አላት፡፡
አህዩት ወደ ዳር ቆመች፡፡
“ሦስተኛዋ አህያ ግቢ” አሉ፤ የቀኝ ጅቡ ዳኛ፡፡
ገባች፡፡
“ወይዘሮ አህያ፤ በጠፍ ጨረቃ፣ በእኛ ግዛት ሣር ልትግጪ የወጣሽው ማንን ተማምነሽ ነው?”
ሦስተኛዋ አህያ መለሰች፡-
“እናንተ ጌቶችን፤ ደጋጎቹን ጅቦች ተማምኜ ነው፡፡ ሩህሩህ በመሆናችሁ እንደማትጨክኑብኝ ስለማውቅ ነው!”
ወደ ጎን እንድትቆም ታዘዘች፡፡ የተባለችውን አደረገች፡፡
ሦስቱ ዳኞች ጅቦች ተመካከሩ፡-
“ያችን አምላክን የተማመነችውን ብንበላት ዕውነትም ነገ ከነግ-ወዲያ አምላክ ይበቀለናል”
“ጌታዋን የተማመነችውን ብንበላት፣ ነገ ከነግ-ወዲያ፣ ጌታዋ ፍለጋ ከወጣና ካገኘን አይምረንም”
“እቺን በእኛ የተማመነችውን ብንበላት ማን ይጠይቀናል?”
“ዕውነት ነው የማንጠየቅባትን ብንበላ ነው ሰላም የምናገኘው!”
በሃሳቡ ተስማምተው ሁለቱን አሰናብተው ሶስተኛዋን ተቀራመቷት፡፡
* * *
ከማያስተማምን ሰለባ የሚያስተማምን ሰለባ ይሻላል-ለበይው! የሀገራችን ፖለቲካ ህይወት በዚህ ተረት የተመሰለውን ዓይነት ነው! ስንቱ ካድሬ ቀልጧል! ስንቱ ባለሥልጣን ተበልቷል! ስንቱ ጅል “ሆዱን ያየ ሆዱን ተወጋ” ሆኗል! ስንቱ ነብሰ ገዳይ “አስተማማኝ መሳሪያ ነኝ”፣ ማንም አይነካኝ” ሲል፤ በሠፈረው ቁና ተሰፍሯል? ስንቱ በሰው ግዛት ሲግጥ ተግጧል! የሚገርመው አሁንም ባለተራው ታማኝ ነኝ እያለ እጁን አጣጥፎ መቀመጡ ነው! ክቡ ቀለበት “በዲሞክራሲያዊ” መንገድ ሰው መዋጥ መሰልቀጡን ይቀጥላል፡፡ በመላከክ (Blame-Shifting) አንዳች ፍሬ የምናገኝ እየመሰለን፣ በመጠቆም እንኮራለን! በማስወጋት እንተማመናለን! ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፡-  “እንቅልፍ ነው እሚያስወስድህ” በሚለው ግጥሙ…
ትቻቸዋለሁ ይተውኝ
አልነካቸውም አይንኩኝ
ብለህ ተገልለህ ርቀህ
ዕውነት ይተውኛል ብለህ
እንዴት ተስፋ ታደርጋለህ?
የተወጋ በቅቶት ቢተኛ፣ የወጋ መች
እንቅልፍ አለው
የጅምሩን ካልጨረሰው….” የሚለን ባላንጣችን፤ መቼም እንደማይተኛልን ለማስገንዘብ ነው! ልብና ልቦና ይስጠን፡፡
ማርክ ትዌይን ስለ ተራ ተርታ ሰዎችና ስለ ደናቁርት የሚያስገነዝበንን ነገር አንርሳ፡-
“ካለህበት የላቀ ቦታ ጎትተው ያወርዱህና በእነሱ ሜዳ፣ ባገኙት ልምድ በመጠቀም ያሸንፉሃል!”
ዛሬም ዘዴው ያው ነው!
ፍርድ እንዳይዛባ ብለን ብዙ መመሪያ አውጥተናል፡፡ የመጣነውን መንገድ ርዝመት በክፋታችን ልክ እንዳንለካ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡
All men are equal but some men are more equal (ሁሉም ሰዎች እኩል ናቸው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን የበለጠ እኩል ናቸው እንደማለት ነው) ይለናል - ጆርጅ ኦርዌል በ “አኒማል ፋርም” ውስጥ። የእኛው ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ጥሩ አድርጎ ያብራራዋል፡-
“ሞትን ለሚሻ ሞትን ነው መንፈግ!
ህይወትን አለመቸር፡፡
ማህል ቤት ነው ጥቅም የሚሰጥ፡፡
ሰው ሆኖ ካሹት ጥቅም የማይሰጥ የለም!” ይለናል፡፡ ይህ እንግዲህ ነገ ለሚገደልና እባካችሁ መሞቴ ካልቀረ አሁኑኑ ለምን አትገድሉኝም? ለሚለው እሥረኛ የሰጡት ምላሽ ነው፡፡ ይሄ ሟች ዓርበኛ፤
“የሚያባርረኝ ጣሊያን እንቅፋት መትቶት በሞተ ነብስ-ገዳይ ተብዬ ታሠርኩኝ እንጂ፤ እኔስ ዓርበኛ አይደለሁም” የሚል ነው! ግፍ ይህ ወሰንህ፣ ይህ ዲካህ የሚባል አይደለም፡፡ ጊዜያችን ከደረሰ የተፃፈልንን ሞት ማግኘታችን አይቀሬ ነው፡፡ ሆኖም ወይ በመጣደፋችን፣ ወይ ሳንደራጅ ዘራፍ በማለታችን ለጥፋት እንዳረጋለን፡፡ እኛም ጠፍተን ጦሳችን ለሌላ ይተርፋል! “ጊዜዋ የደረሰ ቀበሮ አዳኝን ታስመሰግናለች” ማለት ይሄና ይሄ ብቻ ነው! ከዚህ ይሰውረን!!