Administrator

Administrator

   የትዊተር ጽሁፋቸው ከ3.2 ሚ. በላይ ላይኮችን አግኝቷል

      የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በቨርጂኒያ ግዛት በምትገኘው ቻርሎቴስቪል ከተማ የነጮች የበላይነት አራማጆች ከፈጠሩት የዘረኝነት ግጭትና ብጥብጥ ጋር በተያያዘ በትዊተር ድረገጽ ላይ ያስተላለፉት አጭር ጽሁፍ፣ 3.2 ሚሊዮን ላይኮችን በማግኘት፣ በትዊተር ድረገጽ ታሪክ ከፍተኛውን የተወዳጅነት ክብረወሰን ይዟል፡፡
የኦባማ የትዊተር ጽሁፍ 1.3 ሚሊዮን ጊዚያት ያህል በሌሎች የትዊተር ተጠቃሚዎች የተሰራጨ ሲሆን ይህም ጽሁፉን በትዊተር ተጠቃሚዎች በብዛት የተሰራጨ አምስተኛው ጽሁፍ አድርጎታል ተብሏል፡፡
ኦባማ ከአፓርታይዱ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ የግለ ህይወት መጽሃፍ የወሰዱትን፣ “ሰዎችን በቆዳ ቀለማቸው፣ በማንነታቸው ወይም በሃይማኖታቸው ሳቢያ እንዲጠላ ሆኖ የተወለደ ሰው የለም” የሚለውን አጭር ጽሁፍ፣ እየቅል ዝርያ ያላቸውን ህጻናት በመስኮት በኩል ሰላምታ ሲሰጡ ከሚያሳይ ፎቶግራፋቸው ጋር ቅዳሜ ዕለት በትዊተር የለቀቁት ሲሆን፣ ማክሰኞ ዕለት ጽሁፉ በከፍተኛ ሁኔታ በመሰራጨትና ተወዳጅነት በማግኘት የትዊተርን ክብረወሰን መያዙንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በትዊተር ተወዳጅነት ክብረወሰኑን ይዞ የነበረው ከወራት በፊት በማንችስተር የአርያና ግራንዴ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ ከተከሰተው የሽብር ጥቃት ማግስት ድምጻዊቷ ያስተላለፈቺውና 2.7 ሚሊዮን ጊዜ ላይክ የተደረገው የሃዘን መግለጫ መልዕክት እንደነበርም አስታውሷል፡፡
በትዊተር የማህበራዊ ድረገጽ ታሪክ በርካታ ቁጥር ባላቸው ተጠቃሚዎች ላይክ ከተደረጉ የመጀመሪያቹ ምርጥ 10 የትዊተር ጽሁፎች መካከል ስድስቱ የኦባማ መሆናቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ኦባማ በስማቸውና ፖተስ44 በሚል በከፈቷቸው ሁለት የትዊተር አካውንቶች እንደሚጠቀሙም ጠቁሟል፡፡

  ቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ እስካሁን በድምሩ 35 ቢ. ዶላር ለግሰዋል

      የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ የማይክሮሶፍት ኩባንያ መስራች ቢል ጌትስ፣ ባለፉት 20 አመታት ካደረጓቸው የበጎ አድራጎት ልገሳዎች እጅግ ከፍተኛው የተባለውን የ4.6 ቢሊዮን ዶላር ልገሳ ማድረጋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የ61 አመቱ ቢልጌትስ 4.6 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸውን 64 ሚሊዮን አክስዮኖችን ለበጎ አድራጎት መለገሳቸው በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ መደረጉን የጠቆመው ዘገባው፣ ይህ ገንዘብ ባለሃብቱ በአሁኑ ወቅት ካላቸው 89.9 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ሃብት 5 በመቶ ያህል እንደሚደርስም ገልጧል፡፡
ከማይክሮሶፍት ድርሻቸው በተደጋጋሚ ብዙ ገንዘብ ለበጎ አድራጎት በመለገስ የሚታወቁት ቢል ጌትስ፤ በአሁኑ ወቅት በማይክሮሶፍት ኩባንያ ውስጥ ከነበራቸው 24 በመቶ የአክስዮን ድርሻ የቀራቸው 1.3 በመቶ ብቻ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ይሄኛውን ልገሳ ከሰጡ በኋላም ከአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነርነት ዝቅ አለማለታቸውን አመልክቷል፡፡
ቢል ጌትስ እና ባለቤታቸው ሚሊንዳ ጌትስ እ.ኤ.አ ከ1994 አንስቶ ለበጎ አድራጎት ተግባራት የለገሱት አጠቃላይ ገንዘብ 35 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ያለው ዘገባው፣ ቢል ጌትስ ከማይክሮሶፍት ድርሻቸው በ1999 የፈረንጆች አመት 16 ቢሊዮን ዶላር፣ በ2000 አመት ደግሞ 5.1 ቢሊዮን ዶላር ለተመሳሳይ በጎ አላማ መለገሳቸውንም አስታውሷል፡፡
ቢልጌትስ በአለማችን በዘንድሮው አመት ከፍተኛው የበጎ አድራጎት ልገሳ ነው የተባለለትን ይሄኛውን የገንዘብ ልገሳ ያደረጉት ለየትኛው ፋውንዴሽን ወይም ተቋም እንደሆነ ግልጽ መረጃ አለመኖሩን ዘገባው አመልክቷል፡፡

Saturday, 19 August 2017 12:35

የሙያ ስነምግባር (ETHIS)

   የህክምና ባለሙያዎችን የሙያ ስነምግባር በሚመለከት ለዚህ እትም ማብራሪያቸውን እንዲሰጡን የጋበዝናቸው ዶ/ር ሙኒር ካሳ የጽንስና ማህጸን ህክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ዶ/ር ሙኒር እንደሚሉት ከሆነ አንድ ሐኪም ወደህክምና ሙያ ከመግባቱ በፊት በተወሰኑ ነገሮች ከእራሱ ጋር መስማማት ይጠበቅበታል፡፡ሐኪም ለማከም የአንድ ሰው ፈቃድ ይፈል ጋል፡፡  በአጠቃላይ ህብረተሰቡም ለእነዚህ ሐኪሞች እውቅና ሲኖራቸው የታመመን ሰው በአስፈላጊው ነገር ሁሉ ማለትም ከቀዶ ሕክምና ጀምሮ መድሀኒት ሰጥቶ እስከማከም ድረስ መፍቀዱን ያሳያል፡፡ ይህም ለምንድነው ተብሎ ሲጠየቅ ህብረተሰቡ እነዚያን ሐኪሞች ጥሩ ስራ ይሰራሉ ብሎ ስለሚያምናቸው ነው፡፡ ነገር ግን ያ እምነት እየተሸረሸረ ከመጣ ሰው ከዘመናዊ ሕክምና እየራቀ ወደባእድ አምልኮና ባህላዊ ሕክምና ይሄዳል፡፡ ለምሳሌ እንደእንግሊዝ ባሉ ሀገራት ህብረተቡ የጤና ተቋሞቻቸውን በጣም ስለሚወዱና ስለሚያምኑ ስለሚያከብሩም ጭምር ሐኪም በሚነግራቸው መመሪያ በሚገባ ምንም ሳያጉዋድሉ ይጠቀማሉ፡፡  ስለዚህ ያንን እምነት እንዲኖር ለማድረግ ሐኪሞች በማህራቸው ተሰብስበው አንድ ሐኪም በራሱና በሕመምተኞች መካከል ያለው ግንኙነት ምን መምሰል አለበት? በሐኪሞች መካከል ያለው ግንኙነት ምን መምሰል አለበት? ሐኪሙ በግሉስ ምን አይነት አቋም ይዞ መገኘት አለበት የሚለውን እና የመሳሰሉትን ነገሮች በጥንቃቄ ተመልክተው ህግ ያወጣሉ፡፡ ይህ ነው የሙያ ስነምግባር መመሪያ የሚባለው ብለዋል ዶ/ር ሙኒር ካሳ፡፡
የህክምናው የሙያ ስነምግባር ከወጣ በሁዋላ የሚመጣ አዲስ የህክምና ባለሙያ አሰቀድሞ በእነዚህ መሰረታዊ መርሆዎች ላይ መስማማት አለበት ፡፡ ሲስማማ ብቻ ነው ሐኪም የሚሆ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ የሚስማማ የህክምና ባለሙያ ወደሙያው ከመዝለቁ በፊት ከእርሱ በፊት በቀደሙ ባለሙያዎች የወጣውን እና የጸደቀውን ህግ በመስማማት በማመን ቃል ይገባል። በአሁኑ ጊዜ የአለም የህክምና ማህበር የጄኔቫ ስምምነት የሚባል ሐኪሞች ወደሙያው ከመግባታቸው በፊት የሚገቡዋቸው ቃለ መሀላዎች አሉ፡፡ ከእነርሱም ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
በጽኑ ሁኔታ ሕይወቴን በሙሉ የሰውን ዘር ለማገልገል ማመኔን ‘መስማማቴን ቃል እገባለሁ ይላል፡፡ ይህ ማለት ቀለም ‘ጾታ’ ዘር ‘ሀይማኖት ‘ድንበር ‘ሀብት የመሳሰሉትን ሰውን ከሰው የሚለዩት ነገሮች ሁሉ ሳይከልሉኝ በእኩል ለማገልገል ተስማምቻለሁ፡፡ ለዚህ ተግባር ሕይወቴን አሳልፌ እሰጣለሁ ብሎ ቃል ሲገባ ነው ወደሕክምና ስራው የሚገባው፡፡
ይህን የተማርኩትን ሙያ ሕሊናዬና ክብሬን በማይነካ ሁኔታ የሰውንም ክብር በማይነካ ሁኔታ ታካሚውን አገለግላለሁ ብሎ ቃል ሲገባ ነው ወደሙያው የሚቀላቀለው፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ ከባዱና ዋነኛው ደግሞ የህመምተኛዬን ጤና በማንኛውም ሁኔታ አስቀድማ ለሁ የሚለው ነው፡፡  ለምሳሌም ሐኪሙ ይህን ቃል ሲገባ በእሳቤው ውስጥ መግባት ያለበት በእኔ በእራሴ ሕይወትና ጤና ላይ እንኩዋን አንድ ነገር ቢፈጠር ቅድሚያ የምሰጠው የሕመም ተኛዬን ጤናና ሕይወት ማዳን ነው የሚለውን ቃል ሲገባ ነው አንድ ሐኪም ወደሙያው ሊቀላ ቀል የሚችለው፡፡ ስለዚህም አንድ ሰው ሐኪም ሲሆን ለማገልገል የሚመጣው እራሱን ሳይሆን ሌላውን ታካሚውን ወይንም ሕመምተኛውን ነው፡፡ ይህንን ቃሉን ሲያፈርስ ግን የሙያ ማህበሩ ተነጋ ግሮ ‘ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ‘የማይሻሻልና ህብረተሰቡን በትክክል የማያገለግል መሆኑ ሲረጋገጥ ለሙያው ብቁ አይደለም ብለው ሊያስወግዱት የስራ ፈቃዱንም ሊነጥቁት ይገባል፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን የሚፈጽም ማህበር በተደራጀ መልክ የለም፡፡ ወደፊት ግን የሙያ ማህ በራቱ ይጀምራሉ ብለን እንጠብቃለን። የሙያ ማህበራቱ ይህንን እርምጃ ቢወስዱ ሐኪሞቹ በህብረተሰቡ ዘንድ ተአማኒነትን እንደሚያተርፉ እሙን ነው ብለዋል ዶ/ር ሙኒር ካሳ፡፡
የሙያ ስነምግባር ደንብ በኢትዮጵያ ያለው አንድ ነው፡፡ እሱም የኢትዮጵያ ሐኪሞች ማህበር ያወጣው ነው። ነገር ግን የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች የሙያ ስነምግባር መመሪያ የላቸውም፡፡ ስለዚህም አሁን ከአሜሪካው የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ኮሌጅ እና ከአለምአቀፍ የስነተዋልዶ ጤና ስልጠና ማእከል በሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ ለመስራት ዝግጁ ነን ፡፡ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች የስነ ምግባር መመሪያ በሐኪሞች ማህበር በፊት ከተዘጋጀው በጣም የሚለይ ነው፡፡ የዚህም ምክንያቱ ጽሁፉ ሲጀምር ታሳቢ የሚያደርገው ሐኪሙ በስነምግባር ዙሪያ ምን አይነት ችግር አለበት? ከሚለው ስለሚነሳ ነው፡፡ ስነምግባር ማለት ለአንድ ሐኪም የትኛው ትክክል ነው ?የትኛው ነው መሰራት ያለበት? የሚለውን እና መሰል ነገሮችን የሚነግረው ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆን አንድ ምሳሌ አለ አሉ ዶ/ር ሙኒር፡፡
አንዲት ሴት ለመውለድ ወደሐኪም ቤት  ትመጣለች፡፡ ሴትየዋ በሐኪምዋ ስትታይ ደም ከሌላ ሰው ሊሰጣት ይገባል፡፡ እስዋ ግን በእምነትዋ ምክንያት ደም ከሌላ ሰው መውሰድ እንደማትፈልግ ለሐኪምዋ ትገልጻለች፡፡ ሐኪምዋ ግን ይህች ሴት ደም ካላ ገኘች መሞትዋ መሆኑን ስለሚያውቅ ይጨነቃል፡፡ ስለዚህ ከምትሞት ደም መውሰድ አለባት ብሎ ቢወስን እስዋ ደግሞ ደም ባለመውሰድ ብትሞት በእምነትዋ የምታው ቀውንና አገኛለሁ ብላ የምትጠብቀውን የዘላለም ሕይወት ሊነፍገኝ ነው ብላ ትቃወማለች፡፡ ምን ማድረግ ነው ያለበት? እንደዚህ ያሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሐኪሙ የሚመራበት የስነምግባር መመሪያ ሊኖረው ይገባል።
ከላይ የተጠቀሰውን አይነትና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ለመመለስ መሰረታዊ የማይጣሱ ደንቦች ምንድናቸው? የሚለውን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
በበሽተኛውና በሐኪሙ መሐከል ምን አይነት ግንኙነት መኖር አለበት የሚለው አንዱ ነው፡፡ ይህ ቃለ መሐላ የተፈጸመበትና የበሽተኛዬ ደህንነት ከሁሉ ነገር ይበልጣል የሚለውን የሚመለከት ነው፡፡
ሌላው …ስለራሱ በሽታና ስለደህንነቱ የሚወስነው ማነው? በሽተኛው ነው ወይንስ ሐኪሙ ነው? የሚ ለው ነው፡፡ ሐኪሙ መረጃ እና አማራጮችን መስጠት እንጂ መወሰን አይችልም፡፡ ስለዚህም የበሽተኛው መብት የማይደፈርና የማይገሰስ ነው፡፡
ቀጣዩ ፍትህ ነው፡፡ ፍትህ ማለት ሰውን ከሰው አላበላልጥም፡፡ ሐኪሙ ከበሽተኛ ጋር ባለኝ ግንኙነት ሁሉንም ሰው እኩል አክማለሁ ብሎ ማለት አለበት፡፡
የእራሱ የሃኪሙ ጸባይን በሚመለከትም ምግባሩ ምን ይመስላል? እንዴትስ ሊሰራ ይገባል? የሚለውን ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ሐኪም ምንጊዜም መዋሸት የለበትም፡፡
ሐኪም ታካሚውን መጥቀም አለበት፡፡ ሐኪም በሽተኛውን የሚጠቅም ነገር ባያደርግ እንኩዋን ጉዳት የሚያመጣ ነገር ግን አያደርግም፡፡
ሐኪሞች በየጊዜው እያነበቡ እራሳቸውን በእውቀት እየገነቡ በየጊዜው ከሚነደፈው የሳይንስ መርሐ ግብር ጋር እራሳቸውን ማዛመድ አለባቸው፡፡
ሌላው የጥቅም ግጭትን ማስወገድ ነው፡፡ አንድ ሐኪም ታካሚውን ወደሌላ ላቦራቶሪ ወይንም ክሊኒክ እንዲሄድ ሲመክር በግልጽ እዚያ ብትታከም ወይንም ምርመራህን ብታሰራ ጥሩ ቦታ ነው፡፡ በእርግጥ እኔ ኮሚሽን አገኝበታለሁ ወይንም አላገኝትም ብሎ መናገር መቻል አለበት፡፡ ይሁን እንጂ ሐኪም እንደዚህ ያለ የጥቅም ግጭት የሚፈጥር ነገር ውስጥ ከጅምሩም መግባት የለበትም ተብሎ ይታመናል፡፡
እንደማህጸንና ጽንስ ሐኪምነት ሴቶች በማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ጉዳት ይበልጥ መረዳትና መመስከር ስለሚቻል ሐኪም ብቻ መሆን ሳይሆን ስለሴቶቹ ችግር በአደባባይ ማስረዳት ወይ ንም መመስከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ችግሩን በውል ስለሚያውቁትና በተጨባጭ መረጃ በማስደገፍ ማስረዳት ሰለሚችሉ ተደማጭነታቸው ከፍተኛ ስለሚሆን ነው፡፡
ከላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች አብዛኛው የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች በአለም ዙሪያ የሚመሩበትና የሚከተሉት መሰረታዊ መርሆዎች ስለሆኑ በኢትዮያም እንዲዘጋጅ የታቀደው የጽንስና ማህጸን ህክምና የስነምግባር መመሪያ ከዚህ የዘለለ አይሆንም እንደ ዶ/ር ሙኒር ካሳ ማብራሪያ።
የሙያው ስነምግባር ቢቀረጽ በዋነኛነት አንድ የማህጸን ሐኪም ርህራሔ በተሞላበት መንፈስ ታካሚውን እንዲረዳ ያስችለዋል፡፡

ሩሲያውያን አንድ ተረት አላቸው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ንጉሥ በዋናው ከተማ ውስጥ እየተዘዋወረ ሳለ የጣት ቀለበቱ ይጠፋበታል፡፡ ወዲያው በጋዜጣ ላይ ማስታወቂያ ያወጣል፡፡ “የጣት ቀለበቴን አግኝቶ ላመጣልኝ ሰው ወሮታውን እከፍላለሁ” የሚል ነው ማስታወቂያው፡፡ አንድ ተራ ወታደር ዕድለኛ ሆነና ቀለበቱን አገኘ፡፡ “ምን ባደርግ ይሻላል” ሲል አሰበ፡፡ “ወደ ዋናው ጦር ክፍሌ ሄጄ ሪፖርት ባደርግ ጉዳዩ ወደ በላይ ይመራል፡፡ እያንዳንዱ የበላይ የራሱ የበላይ አለው፡፡ ስለዚህ ወደ በላይ ይመራዋል፡፡ ሃምሣ አለቃው ለመቶ አለቃው፤ መቶ አለቃው ለሻምበሉ፤ ሻምበሉ ለሻለቃው፣ ሻለቃው ለኮሎኔሉ፣ ኮሎኔሉ ለብርጋዲየር ጄኔራሉ እያለ ማለቂያ በሌለው የዕዝ ሰንሰለት ውስጥ ሲቀባበሉት መኖሩ ነው፡፡ ስለዚህ በቀጥታ ወደ ንጉሱ ሄጄ ቀለበቱን ባስረክባቸው ይሻላል” ብሎ ይወስናል፡፡
ወደ ቤተ - መንግሥቱ ይመጣል፡፡
የጥበቃ መኰንኑ፤ “እዚህ ምን ልታደርግ መጣህ?” ይለዋል፡፡
“የንጉሱን የጣት ቀለበት አግኝቼ ለማስረከብ ነው የመጣሁት” ይለዋል ተራ ወታደሩ፡፡
“በጣም ጥሩ ነው ወዳጄ፡፡ ለንጉሱ እነግርልሃለሁ፡፡ ነገር ግን በአንድ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ይኸውም ንጉሱ ቀለበቱን ስላገኘህላቸው ከሚሸልሙህ ነገር ግማሹን ለእኔ የምትሰጠኝ ከሆነ ነው፡፡ ተራ ወታደሩም በሆዱ፤
“ወቸ ጉድ! በዕድሜዬ ዛሬ አንድ መልካም ዕድል ቢገጥመኝ፤ እሷኑ የሚቀራመተኝ አዘዘብኝ፡፡ ግን ይሁን ግዴለም፡፡ ይካፈለኝ” ይልና ወደ ጥበቃ መኮንኑ ዞሮ፤ “ይሁን ከሽልማቱ ግማሹን ላካፍልህ እስማማለሁ፡፡ ነገር ግን በአንድ ቅድመ - ሁኔታ ነው” ይለዋል፡፡
“ምንድነው ቅድመ ሁኔታው?” ሲል ይጠይቃል የጥበቃ መኮንኑ፡፡
“ከማገኘው ሽልማት ግማሹን አንተ፤ ግማሹን እኔ እንደምወስድ የሚገልጽ ማስታወሻ ፃፍልኝ” ሲል ይጠይቃል፡፡
የጥበቃ መኮንኑ ማስታወሻውን ጽፎ ይሰጠዋል፡፡ ከዚያም ሄዶ ለንጉሱ ቀለበቱን ያገኘ ሰው መምጣቱን ይናገራል፡፡ ንጉሱም ቀለበታቸውን ስለማግኘቱ ያን ተራ ወታደር እጅግ አድርገው ያመሰግኑትና፤
“በጣም አመሰግናለሁ ጀግና ወታደር! ሁለት ሺህ ብር በሽልማት መልክ ሰጥቼሃለሁ” ይሉታል፡፡
“የለም ንጉሥ ሆይ፤ ለወታደር የሚገባው ሽልማት ሁለት ሺ ብር ሳይሆን ሁለት ሺ ጅራፍ ነው፡፡” ይላል፡፡
ንጉሡም፤ እየሳቁ፡-
“ምን ያለው ጅል ነው?” ብለው “እሺ ጅራፉ ይምጣ” አሉና አዘዙ፡፡
ተራ ወታደሩ ልብሱን ማወላለቅ ሲጀምር፣ በድንገት አንዲት ወረቀት ዱብ ትላለች፡፡
“የምን ወረቀት ነው እሱ?” ሲሉ ይጠይቃሉ ንጉሱ፡፡
“ንጉሥ ሆይ፤ ይህ ማስታወሻ የሽልማቴን ግማሹን የጥበቃ መኮንንዎ እንዲወስድ የተስማማንበትን ውል የሚጠቁም ነው”
ንጉሱ ሳቁና የጥበቃ መኮንኑን አስጠሩት፡፡ ከዚያም “እንግዲህ መቶው ጅራፍ ያንተ ነው ማለት ነው” አሉት፡፡
ቀጥሎም የጥበቃ መኮንኑን በጅራፍ ገራፊው ይገርፈው ጀመር፡፡ የመጨረሻው አሥር ጅራፍ እንደቀረ፣ ያ ተራ ወታደር ወደ ንጉሱ ጆሮ ጠጋ ብሎ፤ “ንጉሥ ሆይ፤ እኔ እንደሱ ስስታም ሰው አይደለሁም፤ የቀረውን ግማሹን ሽልማቴንም ሰጥቼዋለሁ!” ይላቸዋል፡፡
“እንዴት ያለህ ደግ ሰው ነህ ጃል” አሉና ንጉሡ፤ የጥበቃ መኮንኑ ሌላውን የጅራፍ ሽልማት እንዲወስድ አዘዙ፡፡ ያ የጥበቃ መኮንን በእምብርክኩ እስኪሄድ ድረስ ተለጠለጠ፡፡
ከዚያም ንጉሱ ተራ ወታደሩን ጠሩና፤ “በል ከዛሬ ጀምሮ ከሥራ መደብህ በክብር ተባረሃል፡፡ ለመቋቋሚያ ይሆንህ ዘንድ ሶስት ሺ ብር ተሸልመሃል?” አሉና አሰናበቱት፡፡
*   *   *
ከበላይ ወደ በላይ ሲመራ ከሚውል ጉዳይ ይሰውረን፡፡ በየደረጃው ሽልማትህን አካፍለኝ ከሚሉም ያውጣን! ለበቀል ብለን የመዘዝነው ጅራፍ፣ በራሳችን ላይ እንደሚዞር ማስተዋያ ልቦና አያሳጣን፡፡ ባሳበቅንበት ሊሳበቅብን፣ ባስቀጣነው ልንቀጣ፣ ባጨበጨብንበት ሊጨበጨብብን እንደሚችል፤ በጭራሽ አንዘንጋ፡፡
“አፈር ወስዶ ብለን፣ ያማረርነው አባይ
የሚያጨበጭብ ሰው፣ ይዞ ነጐደ ወይ?”
አለ አሉ ገጣሚ፤ ሆይ ሆይ ሲል ውሃ የወሰደውን ሰው አይቶ፡፡ እንሸለም ብለን ሌላውን መጉዳት፣ ውሎ አድሮ የከፋ ጉዳት ወደማስተናገድ ሊያመራ እንደሚችል ዐይናችንን ገልጠን እንይ፡፡ ተማርን የምንል፣ ሥልጣን ላይ ያለን፣ በሞቅ ሞቅ ሙስናችንን ለመሸፈን የምንፍጨረጨር፣ የባለቤቱ ልጅ ነን የምንል፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ፊታችን ያለው እየወደቀ፣ እያየን እኔን አይመለከትም እያልን የምንስቅ፣ “አቤቱ ወደ ፈተናም አታግባን” ብንል ይሻላል፡፡
አንድ አዛውንት፤ “በዚህ ዘመን ዘርዛራ ወንፊት፣ ቀጥሎ ጠቅጣቃ ወንፊት መኖሩን አዳሜ አያውቅም፤ ከዘርዛራው ወንፊት ያመለጠው፣ በጠቅጣቃው ወንፊት የተያዘውን እየሰደበና እያዋረደ ብዙ የሚቆይ ይመስለዋል” ሲሉ ስለ ስብሰባዎች ተናግረዋል፡ አንዱ ባንዱ ሲስቅ ጀምበር ጥልቅ አለ ነው ነገሩ፡፡
በሰው ገንዘብ፣ በሰው ንብረት ላይ መፍረድ ቀላል ነው፡፡ እርዳታ ላያደርጉ፣ ይሄ ይሁን ይሄ አይሁን ማለትም እጅግ ቀላል ነው፡፡ የማያግዝ “ቤቱን አስፍታችሁ ሥሩ” ይላል፤ እንደተባለው ነው፡፡
ሳናወያይና ሳናጠና መመሪያ አናውጣ፡፡ ሳናስብ አንናገር፡፡ ከተናገርን አንፈር፡፡ ካፈርኩ አይመልሰን ብለንም በግትርነት አንደንፋ፡፡ ላወቅነውና ላለምነው ጉዞ በልባምነት እንገስግስ፡፡
አለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራ የተባሉ ደራሲ “የጐጃም ትውልድ በሙሉ፤ ከአባይ እስከ አባይ” በተባለ መጽሐፋቸው፤ “የማኖ የላስታ ሰው ነው፡፡ ጀግና ፈረሰኛ ነበር፡፡ ሥነፀሐይን ሲያጭ “ምን ገንዘብ አለህ” ቢሉት፤ “ልብና ፈረስ አለኝ” አለ፤ አሉ፡፡ ዓላማ ያለው፣ ለሀገርና ለህዝብ አሳቢ የሆነ ሰው፤ ልብና ፈረስ ያስፈልገዋል፡፡ በቀላሉ ተስፋ መቁረጥ የለበትም፡፡ አርቆ አስተዋይ ሊሆን ይገባል፡፡ የዛሬን ብቻ ሳይሆን የነግ ተነግወዲያውን ሊያሰላ፣ ሊያሰላስል ያሻል፡፡ ዕድገትና ብልጽግና የዚህ መርህ የልጅ ልጆች ናቸው፡፡ “መልካም አስተዳደር ይኑር፡፡ ፍትሕ አይጓደል፤ የግለሰብም ሆነ የቡድን ወገናዊነት ይውደም፤ ሙስና ይወገድ፣ የዲሞክራሲ መብቶች ይከበሩ” እየተባለ ነጋ ጠባ የሚወተወተው፣ ለአንድ ሀገራችን ዕድገት እንጂ ጥቂቶች የሚያወለውሉባትና ብዙሃን በአጥንታቸው የሚሄዱባት አገር ትሆን ዘንድ አደለም፡፡ ያውም ለሀብታሞቹ እንኳ ባልተመቸው በአሁኑ ዓለም!!
ፕሮፌሰር ሳች የተባሉ ምሁር፤ “በዛሬ ጊዜ፤ ሀብታሞቹ የአናሳ ፍትሕና የተትረፈረፈ አለመረጋጋት ሰለባ ይሆናሉ (A Less Just and more unstable world) የሚሉትን አባባል በጥሞና ማውጣት ማውረድም ይኖርብናል፡፡ ፍርሃትንና የደህንነት ምቾት ማጣትን የምንቋቋምበት ሥርዓት መፍጠር ይኖርብናል፡፡ “የተገደበውን የፖለቲካ መንቀሳቀሻ ሥፍራ የሚተካ/የሚያካክስ መላወሻ ሜዳ መፈጠር አለበት” እንደሚለን ማለት ነው ፒተር ጊልስ፡፡ ዛሬ እንደ ዋዛ የዘጋነው በር ነገ ከናካቴው ተከርችሞ፤ ቆላፊውም ተቆላፊውም መንገድ እንዳያጡ ስጋቱን መግለፁ ነው፡፡
በጥቃቅን እርምጃዎቻችን ከባባድ ለውጥ ያመጣን አስመስለን ከማጋነን መቆጠብ ይኖርብናል፡፡ ችግሮቻችን ዝሆን አከል ናቸው፡፡ የዝሆንን ግዙፍ አካል እለካለሁ ብላ እንደተነሳችው ጉንዳን እንዳንሆን መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ሥር - ነቀልና ሥር የያዘ ለውጥ እያመጣን መሆኑን እያስረገጥን መጓዝ አለብን፡፡ በዚያው በትላንቱ ልባችንና አካሄዳችን እያለምን፤ ዛሬን አዲስ ነው ብለን ለማሳየት መሞከር፤ “ኖሮ በይው ልብሱን፣ ሰውዬውስ የቅድሙ ነው” እንደሚባለው የጉራጊኛ ተረት ይሆናል፡፡ Old wine in a new bottle እንደሚሉት መሆኑ ነው ፈረንጆቹ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2009 በጀት ዓመት ካደረጋቸው አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች 31.9 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱንና ከታክስ በፊት 14.6 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ፡፡
ባንኩ በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለፀው፤ በዓመቱ በተለያዩ ዘርፎች ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች ከወጪ ንግድ፣ ከሃዋላ፣ ከወጪ ምንዛሪ ግዥና ሌሎች አገልግሎቶች 4.5 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቱንም አስታውቋል፡፡ ባንኩ ከብድር ተመላሽ መሰብሰብ የቻለው 64.6 ቢሊዮን ብር ሲሆን 94.5 ቢሊዮን ብር ለልዩ ልዩ የሥራ መስኮች አዲስ ብድር መሰጠቱን ገልጿል፡፡
ህብረተሰቡ ስለቁጠባ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ በሽልማት ላይ የተመረኮዘ ቁጠባን የማበረታታት ሥራ መሠራቱም ተገልጿል፡፡ በእነዚህ ተግባራት አማካኝነትም 76.4 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉን መረጃው አመላክቷል፡፡ ይህ ክንውን የባንኩን ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ በ2008 ከነበረበት 288.4 ቢሊዮን ወደ 364.9 ቢሊዮን ብር ማድረስ አስችሏል ተብሏል፡፡
የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 485.7 ቢሊዮን ብር መድረሱንና የባንኩ ካፒታል ወደ 40 ቢሊዮን ብር ማደጉ ተገልጿል፡፡  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ወቅት 1222 ቅርንጫፎች መድረሱንና፣ ሂሳብ ያላቸው የባንኩ ጠቅላላ ደንበኞች ቁጥርም 15.9 ቢሊዮን መድረሱን መግለጫው አመልክቷል፡፡

ቀድሞ የተከሰሱበት የሽብር ወንጀል ቀርቶ፣ በወንጀለኛ ህጉ ይከላከሉ በሚል ፍ/ቤት ብይን የሰጠባቸው የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ “ከእስር ቢለቀቁ በድጋሚ አመፅ ሊያነሳሱ ይችላሉ” በሚል የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ ተደረገ፡፡  
በኦሮሚያ አካባቢዎች ከተቀሰቀሰ ህዝባዊ አመጽ ጋር ተያይዞ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው፣ በሽብር ድርጊት በመሳተፍ ወንጀል፣ ክስ የተመሰረተባቸው አቶ በቀለ ገርባ ጉዳይን የሚመለከተው ፍ/ቤት፤ ሐምሌ 7 ቀን 2009 ዓ.ም በሰጠው ብይን፣ በአቃቤ ህግ የቀረበባቸው የማስረጃ ዝርዝር፣ የሽብር ወንጀልን የሚያመላክቱ ባለመሆናቸው፣ “ግዙፍ ባልሆነ መሰናዳትና መገፋፋት” ወንጀል እንዲከላከሉ መወሰኑ ይታወሳል፡፡  
ይህን ተከትሎም እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠበት አንቀፅ ዋስትና የሚፈቀድበት በመሆኑ፣ ለፍ/ቤቱ የዋስትና ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ሁለት ምክንያቶችን በማቅረብ ዋስትናው እንዳይፈቀድ ተቃውሟል፡፡ “መጀመሪያውኑ ዋስትናውን የተከለከሉት በሽብር ወንጀል ጉዳይ ነው፤ አሁን የክሳቸው አንቀፅ ቢቀየርም የዋስትና ጥያቄ መነሳት የለበትም፤” ያለው አቃቤ ህግ፤ ተከሳሹ ከሀገር ውጭ ካሉ ሰዎች ጋር የሚገናኙ በመሆኑ ከአገር ቢወጡ አይመለሱም ሲል ተከራክሯል፡፡ በተጨማሪም ተከሳሹ  ከእስር ቢለቀቁ ህዝብን የማነሳሳት ተግባራቸውን ሊቀጥሉበት ይችላሉ በማለት የዋስትና ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግ ፍ/ቤቱን ጠይቋል፡፡  
የአቶ በቀለ ገርባ ጠበቆች በበኩላቸው፤ የተከሰሱበት አንቀጽ የዋስትና መብት የማይከለክል መሆኑን በመጥቀስ እንዲሁም አቶ በቀለ ገርባ ከዚህ ቀደም ከሀገር ወጥተው የተመለሱ በመሆናቸው ወጥተው ይቀራሉ የሚለው ግምት አይኖርም  በማለት የዋስትና ጥያቄ  ለፍ/ቤቱ ማቅረባቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡  
የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ፍ/ቤቱም፤”ተከሳሹ ከእስር ቢወጡ ህዝብን የማነሳሳት ተግባራቸውን ላለመቀጠላቸው ማረጋገጫ የለም” በሚል የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ ማድረጉን ጠበቃ አመሃ መኮንን፣ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ አቶ በቀለ ገርባ፣ከፊታችን ሰኞ ነሐሴ 8 ጀምሮ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን እንደሚያቀርቡ ታውቋል፡፡

በየመን የባህር ዳርቻ በህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች 120 ኢትዮጵያውንና ሶማሊያውያን ሆን ተብሎ ከጀልባ ላይ ወደ ባህር ተጥለው 50 የሚደርሡ ሰዎች መሞታቸው የአለም መገናኛ ብዙሃንን መነጋጋሪያ ሆኗል፡፡
አለማቀፉ የስደተኞች ድርጅትን (IOM) ጠቅሶ ዘገባውን ያሠራጨው ሲኤንኤን ረቡዕ እለት ወደ የመን እያመራች ባለች ጀልባ የተሣፈሩ 120 ኢትዮጵያዊያንና ሶማሊያውያን በአዘዋዋሪዎቹ ወደ ባህሩ ተጥለዋል ብሏል፡፡
በዚህም  50 ያህሉ መሞታቸው ሲረጋገጥ፣ 22ቱ የደረሱበት አለመታወቁን እንዲሁም 29ኙ በአይኦ ኤም የነፍስ አድን ሰራተኞች ህይወታቸው መትረፉ ተዘግቧል።
የስደተኞቹ አማካይ እድሜ 16 አመት መሆኑን የጠቆመው አይኦኤም፤ የታዳጊዎች ስደት መበራከት አሳሳቢ መሆኑን አስታውቋል፡፡  ከጥር 2009  ጀምሮ 55 ሺህ ያህል የምስራቅ አፍሪካ ዜጎች በየመን አቋርጠው ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሃገራት መግባታቸውን የሚጠቁመው የስደተኞች ድርጅቱ ሪፖርት፤ ከነዚህም ውስጥ 30 ሺህ ያህሉ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች፣ ሲሶ ያህሉም ሴቶች መሆናቸውን ያመለክታል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ፤ ከአዲስ አበባ ጅግጅጋ ባለው መስመር፣ በሃረር እና በባቢሌ ከተሞች አካፋይ ላይ በመሳሪያ የታገዘ ግጭት መኖሩን በመጠቆም፣ ዜጎቹ ወደ አካባቢዎቹ እንዳይንቀሳቀሱ ትናንት አስጠንቅቋል፡፡ ኤምባሲው ባወጣው መግለጫ፣ በአካባቢዎቹ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎም መንገዱ በፀጥታ ኃይሎች መዘጋቱንና የመከላከያ ሰራዊትም ወደ ስፍራው ማምራቱን አስታውቋል፡፡ የአሜሪካ ዜጎች በሥፍራው ከተገኙም እንቅስቃሴያቸው ጥንቃቄ የተሞላበት እንዲሆንና ግርግር ከበዛበት አካባቢ እንዲርቁም ኤምባሲው አሳስቧል፡፡
ባለፈው ዓመትና ዘንድሮ በከፊል፣ የአሜሪካ መንግስት በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተፈጠሩ አለመረጋጋቶችን ተከትሎ፣ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ የጉዞ ማስጠንቀቂያዎችን ለዜጎቹ ሲያስተላልፍ እንደነበር ይታወሳል፡፡

አባትና ልጅ ወደ አንድ ማህበር ስብሰባ ለማድረግ በፈረስ ሆነው ይሄዳሉ አሉ፡፡ መንገድ ላይ ሳሉ ክርክር ያነሳሉ፡-
አባት - ይሄ ፀሐይ እየጠነከረ ሲመጣ፣ የፈረሱ ጥላ በስተቀኝ በኩል ይሆናል
ልጅ - የለም በግራ ነው የሚሆነው
አባት - አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ዳገቱን ከወጣን በኋላ፣ እኛ ወደ ግራ ስለምንዞር ፀሐይ ጀርባውን ሳይሆን ጐኑን ነው የምትመታው፡፡ ግራ ጐኑን ስትመታው፣ ጥላው ወደ ቀኝ ይወድቃል፡፡
ልጅ - የለም የለም፡፡ ፀሐይ ወደ መሀል ሰማይ እየወጣች ስለምትሄድ፣ የፈረሱ ጥላም አቅጣጫውን ይቀይራል፡፡
አባት - እኛ ፈረሱ ላይ ስላለን ጥላው በደምብ አይታየንም
ልጅ - እንግዲያው ወርደን እንየዋ?
አባት - ልክ ነው፡፡ ብንወርድ በደምብ ይታየናል
ከፈረሱ ወርደው ፈረሱን ጉብታው ላይ አቆሙት፡፡ ፈረሱ መሳቅ ጀመረ፡፡
አባት - ይሄ ፈረስ ምን የሚያስቅ ነገር አግኝቶ ነው የሚስቀው?
ልጅ - ለምን አንጠይቀውም?
አባት - እሺ እንጠይቀው
ወደ ፈረሱ ተጠጉ፡፡
አባት - አንተ ፈረስ ምን የሚያስቅ ነገር አግኝተህ ነው የምትስቀው?
ፈረሱም እንዲህ ሲል መለሰ:-
“የምስቀው ስለገረማችሁኝ ነው”
አባት - ምናችን ነው ያስገረመህ?
ፈረስ - ከቤት ከወጣችሁ ጀምሮ ስለ እኔ ጥላ ስትጨቃጨቁ ሳዳምጥ ነበር። አሁን የእኔ ጥላ በቀኝ ወደቀ በግራ ፋይዳው ለእናንተ ምንድን ነው? ስንት ቁም ነገር ልትሰሩበት የምትችሉበትን ጊዜ በከንቱ ጭቅጭቅ ስታባክኑት ማየቴ ሲገርመኝ፤ ጭራሽ መሬት ወርዳችሁ ጥላዬን ለማየት ስትሞክሩ ተመለከትኩ፡፡ የሚያሳዝነኝ ለስብሰባ የሚጠብቃችሁ ማህበርተኛ ህዝብ ነው፡፡
አባትና ልጅ ፈረሱ ስለታዘባቸው በጣም ተናደዱ፡፡
አባት - አንተን በማያገባህ ገብተህ በእኛ ላይ በመሳቅህ መቀጣት አለብህ፡፡ እንዲያውም ካሁን ወዲያ እንዳትናገር አፍህ መለጐም አለበት፡፡
ፈረሱን አፉን ለጐሙት፡፡ ፈረሱ ግን በሆዱ መሳቁን ቀጠለ፡፡ እነሱም ስለጥላው አወዳደቅ ንትርካቸውን ቀጠሉ፡፡
*    *   *
በህዝብ ጊዜ፤ በሀገር ሰዓት የሚቀልዱ አያሌ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ እንዳላጠፉ በመቁጠር መልሰው ህዝቡን ይወቅሳሉ፡፡ ዞረው ሀገርን ያማርራሉ፡፡ በተናገሩት ሲያፍሩ ያዳመጣቸውን ጥፋተኛ ያደርጋሉ፡፡ ፀሐፌ-ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን፤
“የሚያባርረኝ ጠላት እንቅፋት መቶት በሞተ አርበኛ ተብዬ ታሰርኩ እንጂ እኔስ አርበኛ አልነበርኩም” እንዳለው መሆኑ ነው፡፡ ባጠፉት ጥፋት ሌሎችን መራገም፣ የዛሬ ህመማችን ብቻ አይደለም፡፡ የቆየ፤ የሰነበተ ደዌ ነው፡፡ በእንቶ ፈንቶውና በአርቲ-ቡርቲው ዘመን እያሳለፍን፣ ለሀገር እንደሰራን አድርገን ስንገበዝ ውዱ ጊዜ ይነቅዛል። ድምር ውጤቱ የኢኮኖሚው መንኮታኮት፣ የፖለቲካው መላ-ማጣት፣ የማህበራዊ ኑሮው መመሰቃቀል ይሆናል፡፡
የባህል መሸርሸር አደጋ፣ የትምህርት መውረድ አባዜ፣ የሃይማኖት ግጭት ሥጋት፣ የንግድ ሥርዓት ቅጥ-ማጣት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የፍትሕ መዛባት፣ ዐይን-ያወጣ የሙስና ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ቁጣ፣ የእከክልኝ - ልከክልህ ወገናዊነት ፖለቲካዊ ዘይቤ፣ የትውልድ ንቅዘት (degeneration)፣ የዘመቻ ሥራና መንገኝነት… ምኑ ቅጡ! ድምር ውጤታቸው ከቤተሰብ እስከ ህብረተሰብ የሚያናጋ ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንዶች ክስተቱን መግለፅን እንደ አሉታዊነት ያዩታል፡፡ እውነታው ግን ድክመታችንን አይተን መላ እንፍጠር የሚል ነው፡፡ “…ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” የሚል የማስጠንቀቂያ ደወልም አለው፡፡ “አትፍረድ ይፈረድብሃል” የሚል አንድምታም አያጣም! “መሄድ ቢሉሽ መሄድ ነወይ…” ብንልም ያስኬዳል፡፡
“አንተም እሳት ነበርክ እሳት አዘዘብህ
እንደገና ዳቦ እሳት ነደደብህ” የሚለውን ለማስተዋል ጭንቀላትን ይዞ መተከዝ አይጠይቅም!
መልካም የተሰራን ማመስገን ደግ ነው፡፡ የሚያስወቅሰው፣ አድሮም የሚያስጠይቀው እንከን - የሞላውን ነገር እንከን - የለሽ ነው ማለት ስንጀምር ነው! ፍፁም ነው ማለት ስንጀምር አዛዥ ናዛዥ እንሆናለን! ይሄኔ ግራ የገባው የራስ ወገን ሳይቀር፤
“ያ ንሥር እንደኔ ዓይነት ሆኖ፣ ምን አየር ላይ አወጣው?” ይለናል፤ እንደ ዶሮው!

• ሆስፒታሉ በአገልግሎት ጥራት መጓደል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል
• ቅዱስ ሲኖዶስ፤ ሆስፒታሉ እንደ አዲስ እንዲደራጅ ትእዛዝ ሰጥቷል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ብቸኛ ሆስፒታሏን በአግባቡ መቆጣጠርና ማስተዳደር ባለመቻሏ ለከፍተኛ ምዝበራ መጋለጡን በሆስፒታሉ ላይ የቀረበ ሪፖርት ያረጋገጠ ሲሆን፤ ቋሚ ሲኖዶስ፤ ምዝበራ ፈጽመዋል የተባሉ ሐኪሞችና የአስተዳደር ሠራተኞች ተባርረው፣ ሆስፒታሉ እንደ ዐዲስ እንዲደራጅ ወስኗል፡፡  
በቤተ ክርስቲያኗ ገንዘብ ከ23 ዓመት በፊት የተቋቋመው የምግባረ ሠናይ ጠቅላላ ሆስፒታል፤ በቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ትኩረት ተነፍጎት በመቆየቱ ለግለሰቦች ምዝበራና መጠቀሚያ ውሏል፤ ይላል - የምርመራ ሪፖርቱ፡፡
ቋሚ ሲኖዶሱ፣ ባለፈው ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም ባሳለፈው ውሳኔ፤ በሆስፒታሉ ውስጥ አላግባብ የሚፈጸም የደመወዝ ክፍያን ጨምሮ በሆስፒታሉ ላይ ከፍተኛ ብክነትና ምዝበራ እየተፈጸመ መሆኑን ከሪፖርቱ መረዳቱን በመግለጽ፣ ምዝበራ ፈጽመዋል ያላቸውን የሕክምና ባለሞያዎችና ሌሎች ሠራተኞች  የሥራ ውላቸው ተቋርጦ እንዲሰናበቱ ትእዛዝ ሰጥቷል። ሆስፒታሉም የቤተ ክርስቲያኒቱን ማኅበራዊ ተልእኮ ለማሳካትና ሥራንና ሠራተኛን ለማገናኘት በሚያስችል መልኩ ዳግም እንዲደራጅ ወስኗል፡፡  
ሆስፒታሉ፣ በቂ ካፒታልና በጀት ሳይኖረው፣ የጡረታ ጊዜያቸው ያለፈ የአስተዳደር ሓላፊዎች ለራሳቸው ከፍተኛ የደመወዝ ጭማሪ በማድረግ፣ የሕክምና ባለሞያዎችን ሲበድሉ መቆየታቸውም በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡ አሠራሩ የዘመድ አዝማድ በመሆኑም ተመሳሳይ የሞያ አገልግሎት በሚሰጡ ሐኪሞች መካከል ከፍተኛ የደመወዝ ልዩነት መኖሩን የሚጠቅሰው ሪፖርቱ፤ ሙሉ ጊዜያቸውን በሆስፒታሉ ተቀጥረው የሚሠሩ አንድ ሐኪም በወር 31 ሺሕ 943 ብር ሲከፈላቸው፣ በሳምንት ለተወሰኑ ቀናት ብቻ በትርፍ ጊዜያቸው የሚሠሩ ሌላ ሐኪም በአንጻሩ፣ 75 ሺሕ 169 ብር እንደሚከፈላቸው ይገልጻል፡፡
የሠራተኛ ቅጥርና ዕድገት ከሕግና መመሪያ ውጪ፣ ያለውድድርና ማስታወቂያ፣ በሥራ ሓላፊዎች የግል ይኹንታ ብቻ እንደሚፈጸም በሪፖርቱ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ለሠራተኞች ተገቢው ሞያዊ ክብር ሳይሰጥ መቆየቱና የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩ ተጠቁሟል። ለማጣራቱና ርምጃው መነሻ የሆነውን አቤቱታ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ያቀረቡት እማሆይ ምስጢረ ሥላሴ ከበደ፣ በነርስነት እያገለገሉ በትርፍ ጊዜያቸውና በግል ጥረታቸው ተምረው በጤና መኮንነት ተመርቀው የሞያ ፈቃድ ቢያገኙም፣ መድቦ ሊያሠራቸው አለመቻሉ በማሳያነት ቀርቧል፡፡ “የጤና መኮንነት የሞያ ሥራ ፈቃድ በሆስፒታሉ ውስጥ የሥራ መደብ ስለሌለው መድበን ልናሠራቸው አልቻልንም፤” በማለት ሥራ አስኪያጁ የሰጡት ምላሽም፣ ተገቢነትና ፍትሐዊነት የጎደለው ነው፤ ተብሏል፡፡ ሆስፒታሉን ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ የሚቆጣጠር ሥርዓት ባለመዘርጋቱ፣ የሥራ አመራር ቦርዱም ተገቢ ክትትል ባለማድረጉ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ብቸኛ ሆስፒታል የመዘጋት አደጋ ላይ እንደጣለውም ታውቋል፡፡
በአጠቃላይ የሆስፒታሉ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ በጡረተኞች እጅ ከመውደቁ የተነሳ ከተቋማዊ ዕድገት ይልቅ የግለሰቦች ጥቅም እንዲንሰራፋ ዕድል መክፈቱን የሚገልጸው ሪፖርቱ፤ ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎች ባለማሟላትና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉም  ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው ይጠቁማል፡፡ ማስጠንቀቂያውን ተከትሎ፣ ሆስፒታሉ ከተሰጠው ቀነ ገደብ በፊት ጉድለቱን ለማሟላት ያደረገው ጥረት እንደሌለና አፋጣኝ የእርምት ርምጃ መውሰድ ካልተቻለ፣ ቤተ ክርስቲያኗ ብቸኛ ሆስፒታሏን የማጣት አደጋ ተጋርጦባታል፤ ይላሉ - ምንጮች፡፡
አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት፣ ምንም እንኳን ርምጃው የዘገየ ቢሆንም፣ ቋሚ ሲኖዶሱ ሪፖርቱ በደረሰው በአጭር ጊዜ ውስጥ “ምዝበራ ፈጽመዋል፤ ለሆስፒታሉ ዕድገት ማነቆ ሆነዋል፤” በሚል የተጠቆሙትና የተጠረጠሩት ሥራ አስኪያጁ፣ የፋይናንስ መመሪያ ሓላፊው፣ የንብረትና የሰው ኃይል መምሪያ ሓላፊው እና የትርፍ ጊዜ ተቀጣሪ ጡረተኛ ሐኪሞች በሙሉ የሥራ ውላቸው ተቋርጦ፣ ሆስፒታሉ በሞያ ብቁ በሆኖ ባለሞያዎች በድጋሚ እንዲደራጅና እንዲመራ መወሰኑ ትልቅ ርምጃ ነው፡፡ አሁንም ግን ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓትና ማኔጅመንት ማበጀት የግድ መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ፡፡