Administrator

Administrator

 በቅርቡ በብሄራዊ ም/ቤት አባላት ተመርጠው ወደ ፓርቲው አመራር መምጣታቸው በገለፁት አቶ አዳነ ታደሰ የሚመራው የኢዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፤ ምርጫ ቦርድና መንግስት ኤዴፓን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ነው ሲሉ አማረሩ፡፡
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ፤ “ተመርጠን ወደ አመራር መጥተናል” ያሉበትን ጉዳይ አጣርቼ ውሳኔ እስከምሰጥ ድረስ በኢዴፓ አመራርነት የማውቀው ዶ/ር ጫኔ ከበደን ነው፤ ማለቱ ይታወሳል፡፡
የፓርቲው አዲሱ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ፤ በፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት የተመረጠበትን አግባብ የሚያስረዳ ቃለ ጉባኤ  ለቦርዱ ቢያቀርብም ተቀባይነት አለማግኘቱን በመጠቆም፤ “ምርጫ ቦርድና መንግስት ኢዴፓን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ነው” ብሏል፡፡
“አገሪቱ ከምትገኝበት የፖለቲካ ውጥረት አንፃር የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርአቱን ለማጠናከር መስራት ሲገባ ፓርቲን ለማዳከም እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠናል” ብለዋል- አመራሮቹ በሰጡት መግለጫ፡፡
የተቀናጀ በሚመስል መልኩ ምርጫ ቦርድና መንግስት በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ በመግባት ፓርቲያቸውን ለማፍረስ መንቀሳቀሳቸውን ማህበረሰቡና የሲቪክ ማህበራት በማጣራት ሃቁን ለህዝብ እንዲያቀርቡላቸውም ጠይቀዋል፡፡
በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረውን የአመራር ውዝግብ ለመፍታትም የፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት አባላት ለታህሳስ 15 ልዩ ስብሰባ መጠራታቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ስብሰባውን ጠርተዋል ተብለው ከተጠቀሱት መካከል የፓርቲው ስራ አስፈፃሚዎች መካከልም አቶ አዳነ ታደሰ፣ አቶ አስማማው ተሰማ፣ ወ/ሮ ሶፊያ ይልማ እና አቶ ልደቱ አያሌውን ጨምሮ 13 አመራሮች ይገኙበታል፡፡
በፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት ውሳኔ ከሥራ አስፈጻሚነት ተነስተዋል ከተባሉት አንዱ የሆኑት አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ፤ መግለጫውን አስመልክቶ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት “ግለሰቦቹ ይሄን መግለጫ በፓርቲው ስም የመስጠት መብት የላቸውም፣ ምርጫ ቦርድም አያውቃቸውም የህግ ተጠያቂነትንም ያስከትላል” ብለዋል፡፡

Saturday, 23 December 2017 09:07

አገርህ ያችው ናት!

አሴ!
ዛሬም አንረሳህም፣ እናስታውሳለን
አይሞትም ፈገግታህ
ብርሃን ይረጫል፣ተስፋችንን ያውቃል!
የዘራኸው አለ፣ ዘመን ቆጥሮ ዘልቋል፡፡
አሥራ ሶስት ዓመትክን ዛሬም ይዘክራል!
አሴ!
ያው እንደምታውቀው
ሥልጣንም ደክሞታል
የፀናው ሲጠና፣ የደከመው ወድቋል!
ወትሮም እንደዚያው ነው
አንደኛው ሲለሰን፣ ስንጥቅ ነው ሌላኛው
አገርህ ያችው ናት
ባንድ ምህዋር ላይ፣ ስትዞር የምታቃት!
እያደር ስትከር፣ ውል የሚጠፋባት
አሴ አላጣሃትም-
አገርህ ያችው ናት!
(ለአሰፋ ጐሣዬ 13ኛ ዓመት)
ነ.መ

Saturday, 23 December 2017 09:00

ርዕዩን ነጠቋት …!

ርዕዩን ነጠቋት …!

ኢትዮጵያን ሲያስባት፣ ከዘመናቷ ጠልቆ፣
ጭፍን ሐሳቧ ውስጥ፣ እንዳሸመቀች አውቆ፣
ነጯን ከጥቁር ተማጥቆ፣
ግራጫ ዶሴዋን ጠብቆ፣
የ’ኛን ዐስርት ዓመታት፣ በደቂቃ እድሜው
እየኖረው፣
ዓለም አቀፉን ዕውነታ፣ ሀገሩ በልማድ
ስትወቅረው …
ዘመኗን በ’ውቀት አሰፋ፡፡ የነቢይን
ገቢር ወርሶ፣
የኢዮብን ትዕግስት ጽናት፣ ከሰለሞን
ጥበብ ተውሶ፡፡
ርዕዩን ከአድማስ አሻግሮ፣ አምዶቿን
አለት ላይ ተክሎ፣
የልቡን ትጋት አክሎ፣
ሐሳቡን በጥበብ ሸጠ፤ ዕውቀትን
በአዲስ አብቅሎ፡፡
ዛሬ …
ርዕዩን ማነገት ታክቷት፣ እንደ ሰካራም ባልቴት
ሀገሩ ስትንገዳገድ፣
ነጻ ፈቃዷን ሳትኖረው፣ ድንቁርና ሠልጥኖባት
ስትዋጅ መጥፊያዋን መንገድ፣
ልዕልናዋም ረክሶ፣ እርቀ ሰላሙ ተሰውሮባት
ዘረ ሰቧም ተኳረፈ፤
ደም ፍላቷ ተንተክትኮ፣ አኬልዳማዋ ከሚታየው
እንኳንም እሱ ቀድሞ አረፈ፡፡

                                                                          ገዛኸኝ ፀ. ጸጋው

 በሙስሊም አገራት መካከል ትብብርን የመፍጠር ዓላማ ይዞ የተቋቋመው ኦርጋናይዜሽን ኦፍ ኢስላሚክ ኮፕሬሽን ባለፈው ረቡዕ በቱርክ መዲና ኢስታንቡል ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ላይ የተሳተፉ 57 የሙስሊም አገራት መንግስታት፣ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ለምስራቃዊ እየሩሳሌም፣ የፍልስጤም መዲናነት እውቅና እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ እየሩሳሌም የእስራኤል መዲና መሆኗን በተመለከተ ላስተላለፉት ውሳኔ የጋራ ምላሽ ለመስጠት ታስቦ በቱርኩ ፕሬዚዳንት ጣይብ ኤርዶጋን በተጠራው አስቸኳይ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት የአገራቱ መሪዎች ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ለእየሩሳሌም የእስራኤል መዲናነት የሰጡትን እውቅናም ውድቅ ማድረጋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
“የትራምፕ ውሳኔ ህጋዊነት የጎደለውና ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው” በሚል በጋራ ያወገዙት መንግስታቱ፤ አሜሪካ ይህንን ውሳኔዋን እንድትሽር የጠየቁ ሲሆን ይህንን ባለማድረጓ ለሚከተሉት ጥፋቶችና ቀውሶች ሁሉ ሃላፊነቱን ለመውሰድ እንድትዘጋጅም ማስጠንቀቃቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአገራቱ መሪዎች በጉባኤው ማብቂያ ላይ ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ አንዳንዶች እንደገመቱት በእስራኤልም ሆነ በአሜሪካ ላይ ምንም አይነት ማዕቀብ አለመጣላቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ይህም ሆኖ ግን የአገራቱ የጋራ አቋም የአሜሪካን ውሳኔና አቋም ያስቀይራል ተብሎ እንደማይጠበቅ ጠቁሟል፡፡
“የትራምፕ ውሳኔ ዓለማቀፍ ህጎችን የሚጥስ ትልቅ ወንጀል ነው፤ እየሩሳሌም የፍልስጤም መዲና ነበረች፤ አሁንም ናት፤ ወደፊትም ሆና ትቀጥላለች” ሲሉ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ጠንካራ አቋም የገለጹት የፍልስጤሙ ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ፤ “ለእየሩሳሌም የፍልስጤም መዲናነት እውቅና እስካልተሰጠ ድረስ በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ሰላምና መረጋጋት የሚባል ነገር አይታሰብም” ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡
የቱርኩ ፕሬዚዳንት ጣይብ ኤርዶጋን በበኩላቸው፤ ሃያላን አገራት እየሩሳሌም የፍልስጤም ዋና ከተማ ለመሆኗ እውቅና እንዲሰጡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን “አሜሪካ ይህንን ተገቢነት የሌለው ውሳኔ መሻር ይገባታል” ማለታቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

- የብሩንዲው መሪ ስልጣናቸውን ለማራዘም ዘመቻ ጀምረዋል
             - የኡጋንዳው አቻቸውም ስልጣን ላለመልቀቅ ህግ ሊያሻሽሉ ደፋ ቀና እያሉ ነው

    የስልጣን ዘመናቸውን ሊያጠናቅቁ 2 አመታት ብቻ የቀራቸው የብሩንዲው ፕሬዚደንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ ስልጣናቸውን ለማራዘም የሚያስችሏቸውን የህገ መንግስት ማሻሻያዎች በመደገፍ ድምጻቸውን እንዲሰጡ ደጋፊዎቻቸውን የማግባባት ዘመቻ ባለፈው ማክሰኞ መጀመራቸውንና ይህም አገሪቱን ወደ ከፋ ብጥብጥና ቀውስ ሊያስገባት ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱን መሪ የስልጣን ዘመን ገደብ የሚወስነውን የህገ- መንግስት አንቀጽ ለማሻሻል በቅርቡ ህዝበ ውሳኔ እንደሚካሄድ የጠቆመው ዘገባው፤ስልጣናቸውን በወቅቱ ካልለቀቁ በአገሪቱ የባሰ ግጭትና ብጥብጥ እንደሚከሰት ከተቀናቃኞቻቸው ማስጠንቀቂያ ቢደርሳቸውም፣ ንኩሩንዚዛ ግን ጊቴጋ በተባለው የአገሪቱ ግዛት የቅስቀሳ ዘመቻ መጀመራቸውን አመልክቷል፡፡
ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ለሁለት የስልጣን ዘመናት አገሪቱን የመሩት ፕሬዚዳንቱ፤ በ2015 ላይ ህገ መንግስቱን በማሻሻል ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን በይፋ ማስታወቃቸውን ተከትሎ፣ በአገሪቱ በተቀሰቀሰው የከፋ ግጭትና ብጥብጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
ንኩሩንዚዛን ለሁለት የስልጣን ዘመናት በመንበራቸው ላይ የሚያቆየውን የህገ መንግስት ማሻሻያ የማድረግ ሃሳቡን ያፈለቀው ፕሬዚዳንቱ መርጦ የሾመው የአገሪቱ ኮሚሽን እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ ራሳቸው የሚመሩት ካቢኔም ሃሳቡን እንዳጸደቀውና ህዝበ ውሳኔው እንዲካሄድ መፍቀዱን አመልክቷል፡፡ የአገሪቱ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፕሬዚዳንቱ የጀመሩትን የቅስቀሳ ዘመቻ ያወገዙ ሲሆን ፕሬዚዳንቱ እድሜ ልካቸውን በስልጣን ላይ የመቆየት ጽኑ ፍላጎታቸውን ለማሳካት እስከቻሉ ድረስ አገሪቱ ወደ እልቂትና የእርስ በእርስ ግጭት ብትገባ ግድ እንደሌላቸው ጠቁመዋል፡፡
ለ13 አመታት የዘለቀውን የብሩንዲ ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ግጭት ለማቆም በሚል እ.ኤ.አ በ2005 የአሩሻው ስምምነት መደረጉን ተከትሎ ስልጣን የያዙት ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ፣ በ2010 በተካሄደውና ተቃዋሚዎች ባልተሳተፉበት ምርጫ  አሸንፈው በገዢነት መቀጠላቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ በ2015 ላይም ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን እወዳደራለሁ ማለታቸውን ተከትሎ እንዲካሄድ የተወሰነው ህዝበ ውሳኔ  ማሻሻያውን የሚደግፍ ከሆነ፣ ሰውዬው በስልጣን ላይ የቆዩበት ጊዜ በድምሩ 14 አመታት እንደሚደርስ አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዮሪ ሙሴቬኒ፣ የአገሪቱን መሪ የዕድሜ ገደብ በማራዘምና አምስት አመት የነበረውን የፕሬዚዳንቱ አንድ የስልጣን ዘመን ወደ ሰባት አመት ከፍ በማድረግ ስልጣናቸውን ለማስቀጠል ባቀረቡት ረቂቅ ሃሳብ ላይ የአገሪቱ ፓርላማ በቅርቡ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ላለፉት ከ30 በላይ አመታት አገሪቱን የገዙት ሙሴቬኒ፤ በቀጣዩ ምርጫ 77 አመት እንደሚሆናቸውና ህጉ ግን ለመሪነት መወዳደር የሚችለው ዕድሜው ቢበዛ 75 አመት የሆነ ሰው እንደሆነ የሚደነግግ በመሆኑ፣ በምርጫው ለመወዳደርና ስልጣናቸውን ለማራዘም ሲሉ ህጉን የማሻሻል ሃሳብ ማቅረባቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የኡጋንዳ ፓርላማ የፕሬዚዳንቱ የዕድሜ ገደብ ይሻሻል በሚለው ሀሳብ ዙሪያ ለመምከር ከዚህ ቀደም በጠራቸው ስብሰባዎች ላይ ከፍተኛ አለመግባባትና ውዝግብ መፈጠሩን ያስታወሰው ቢቢሲ፣ የፓርላማው አባላት በወንበር እየተወራወሩ እስከመፈነካከት ደርሰው እንደነበርም አመልክቷል፡፡
ረቂቅ ሃሳቡ ለፓርላማ ውሳኔ ከቀረበ ቆየት ቢልም፣ በአፋጣኝ ድምጽ ሊሰጥበት ያልቻለው የአገሪቱ ህግ አውጪዎች ውሳኔውን የሚያጸድቅ የድጋፍ ድምጽ ለመስጠት ከሙሴቬኒ መንግስት ለእያንዳንዳቸው 83 ሺህ ዶላር በሙስና መልክ እንዲከፈላቸው በመጠየቃቸው ነው መባሉን ኦልአፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡

 ታዋቂው አፕል ኩባንያ ከዚህ ቀደም አምርቶ ለገበያ ካቀረባቸው የተለያዩ ሞዴል የማክ ኮምፒውተሮች ሁሉ ከፍተኛ አቅም የተላበሰውንና በርካታ ስራዎችን የመስራት ብቃት እንዳለው የተነገረለትን አዲሱን ምርቱን፣ አይማክ ፕሮን ከትናንት በስቲያ በይፋ አስመርቋል፡፡
የዓለማችን የወቅቱ የዴስክቶፕ ኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ከፍታ ማሳያ እንደሆነ የተነገረለትና ባለ27 ኢንች ስክሪን ያለው አይማክ ፕሮ፤ ምስሎችንና ቪዲዮዎችን በእጅግ ከፍተኛ ጥራት ኤዲት ከማድረግ ባለፈ በፍጥነቱና በሚያከናውናቸው ስራዎች ብዛት አቻ እንደማይገኝለት ተገልጧል፡፡
ከዘራፊዎች ለመከላከል የሚያስችል ራሱን የቻለ ሲስተም ያለውና ማራኪ ገጽታን የተላበሰው አይማክ ፕሮ፤ በምን ያህል  ዋጋ ለገበያ እንደሚቀርብ እስካሁን ድረስ ኩባንያው በይፋ ያስታወቀው ነገር ባይኖርም፣ አንዳንድ መረጃዎች ግን ከ5 ሺህ ዶላር በላይ እንደሚሆን ግምታቸውን መስጠታቸውን ሲኤንቢሲ ዘግቧል፡፡
አይፎን 8፣ አይፎን 8 ፕላስና አይፎን ኤክስ የተባሉትን አዳዲስ እጅግ ዘመናዊ ስማርት ፎን ምርቶቹን በመስከረም ወር ለዓለም ገበያ ያበቃውና በዓለማቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ሽያጭ እያስመዘገበ የሚገኘው አፕል ኩባንያ፤ በአዲሱ የኮምፒውተር ምርቱ ሽያጭ ስኬታማ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው አመልክቷል፡፡


 የመጀመሪያዎቹ 655 መኪኖች በሙሉ ከወዲሁ ተሸጠው አልቀዋል

    ማክላረን እና ቴስላ የተባሉት ታዋቂ የዓለማችን ኩባንያዎች ያመረቷቸው እጅግ ውድ የቤት መኪኖች ዋጋ፣ የአለምን ትኩረት ስበው መሰንበታቸውን  ዘ ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘግቧል፡፡
ማክላረን የተባለው ኩባንያ ከለንደን አቅራቢያ በሚገኘው ዋና መስሪያ ቤቱ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ይፋ ባደረገው መረጃ፣ ሴና የሚል ስያሜ ለሰጠው የስፖርት መኪናው 1 ሚሊዮን ዶላር የመሸጫ ዋጋ ማውጣቱን ያስታወቀ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ለገበያ ሊያቀርባቸው ያመረታቸውን 500 መኪኖቹን በሙሉ ከወዲሁ ሸጦ መጨረሱን አስታውቋል፡፡
789 የፈረስ ጉልበት አቅም ያለው ሴና፣እጅግ ፈጣንና ምቾት ያለው ልዩ መኪና እንደሆነ ያስታወቀው ኩባንያው፤ የመጀመሪያዎቹን መኪኖቹን በመጪው መጋቢት ወር ጄኔቫ ውስጥ በሚካሄደው አውደ ርዕይ ላይ በይፋ እንደሚያስመርቅ ገልጧል፡፡
ታዋቂው ኩባንያ ቴስላ በበኩሉ፤ በ2019 የፈረንጆች አመት በገበያ ላይ የሚያውለው የመጀመሪያው በኤሌክትሪክ የሚሰራ መኪና የመሸጫ ዋጋው 255 ሺህ ዶላር እንዲሆን መወሰኑን ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ዘ ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘግቧል፡፡ ራፒድኢ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይህ እጅግ ዘመናዊ የቤት መኪና፣ በአይነቱ የተለየ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ ኩባንያው ለመጀመሪያ ጊዜ አምርቶ ለገበያ የሚያቀርበውም 155 መኪኖችን ብቻ እንደሚሆን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸውን አመልክቷል፡፡ ኩባንያው ገና መኪናዎቹን በማምረት ሂደት ላይ ቢሆንም፣ ለገበያ ሊያቀርባቸው ያቀዳቸውንና እጅግ ውድ የሆኑትን 155 መኪኖቹን በሙሉ ገና ከወዲሁ ለደንበኞቹ ሸጦ መጨረሱን የጠቆመው ዘገባው፤ መኪናዎቹ አንድ ጊዜ ቻርጅ በተደረጉት የኤሌክትሪክ ሃይል እስከ 200 ማይል ርቀት መጓዝ እንደሚችሉም አስረድቷል፡፡ እስከ 1ሺህ የፈረስ ጉልበት የሚደርስ አቅም እንደሚኖረው የተነገረለትን ራፒድኢ በማምረት ላይ የሚገኘው ቴስላ፤ በቅርቡም ሞዴል 3ኤስ የተባሉ የኤሌክትሪክ መኪኖቹን ለመግዛት ከ450 ሺህ ደምበኞቹ የግዢ ጥያቄ እንደቀረበለት ያስታወሰው ዘገባው፤ ኩባንያው የመኪኖቹን ባትሪ በበቂ ሁኔታ ለማምረት ባለመቻሉ 260ዎቹን ብቻ ሊያመርት መቻሉን ጠቁሟል፡፡

ለ75ኛ ጊዜ ለሚከናወነው የ2018 “ጎልደን ግሎብ” ሽልማት በዕጩነት የቀረቡ ፊልሞች ዝርዝር ባለፈው ሰኞ ይፋ የተደረገ ሲሆን  ዘ ሼፕ ኦፍ ዎተር የተሰኘው ፊልም፣ ምርጥ ዳይሬክተርና ምርጥ ሴት ዋና ተዋናይትን ጨምሮ በሰባት ዘርፎች ለሽልማት በመታጨት ቀዳሚነቱን ይዟል፡፡
ስሪ ቢልቦርድስ እና ዘ ፖስት የተሰኙት ፊልሞችም እያንዳንዳቸው በስድስት ዘርፎች ለሽልማት የታጩ ፊልሞች እንደሆኑ የዘገበው ቢቢሲ፤ ሌዲ በርድ የተሰኘው ፊልም በበኩሉ፣ በአራት ዘርፎች በመታጨት ሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን አመልክቷል፡፡
በቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎች ዘርፍ፣ ለዘንድሮው የ”ጎልደን ግሎብ” ሽልማት ከታጩት መካከል፣ በስድስት የተለያዩ ዘርፎች የታጨው ቢግ ሊትል ላይስ በብዛት በመታጨት ቀዳሚነቱን ይዟል ተብሏል፡፡
የሆሊውድ የውጭ ፕሬስ ማህበር የሚያዘጋጀው አመታዊው የ”ጎልደን ግሎብ” ሽልማት አሰጣጥ ስነስርዓት በመጪው ጥር ወር መጀመሪያ ላይ በቢቨርሊ ሂልስ ካሊፎርኒያ በደማቅ ሁኔታ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡


    ኩራዝ ኢንተርናሽናል አሳታሚ ድርጅት ኦሮምኛ ቃላትን ወደ እንግሊዝኛና አማርኛ የሚተረጉም “ኦዳ” የተሰኘ መዝገበ ቃላት ዛሬ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ ስታዲየም ፊት ለፊት በሚገኘው የኦሮሞ ባህል ማዕከል ያስመርቃል፡፡
በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ኃላፊዎች፣ የመንግስት ባለስልጣናትና ደራሲያን ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡

 በሩሲያ የሳይንስና የባህል አዳራሽ (ፑሽኪን) በአይነቱ ልዩ የሆነ የሙዚቃ ኮንሰርት ዛሬ ከቀኑ 9፡30 ጀምሮ እንደሚካሄድ ማዕከሉ አስታወቀ፡፡ የሩሲያ ታዋቂ ሙዚቀኞች  ይሳተፉበታል በተባለው በዚህ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ ቫስሊ ፓደለስኒ የተባለው ፒያኖ ተጫዋችና ያና ጋይዱኬቪች የተባለችዋ ቫዮሊን ተጫዋች እንደሚሳተፉ የተገለፀ ሲሆን መግቢያው በነፃ  እንደሆነ ታውቋል፡፡
 በዕለቱ የሩሲያ የሻይ ስነ-ስርዓትና የኮክቴል ግብዣ መሰናዳቱን ገልፀው- ማዕከሉ ሁሉም ሰው በኮንሰርቱ ላይ ተገኝቶ ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፍም ጥሪ አቅርቧል፡፡